‹‹እግዚአብሔር መልካም ነው፤ በመከራ ቀን መሸሸጊያ ነው›› (ናሆም ፩፥፯)

እግዚአብሔር አምላክ የሰዎችን ደኅነትን የሚሻ መልካም አባት በመሆኑ ልጆቹን ከመከራ ይሸሽጋል፡፡ በዘመነ ኦሪት እስራኤላውያን በግብፅ በባርነት ሲኖሩ ከመከራ ሠውሯቸዋል፤ ነፃ ሊያወጣቸውም ፈቅዶ ነቢዩ ሙሴን እንዲህ አለው፤ ‹‹እኔ እግዚአብሔር ነኝ፤ ከግብፃውያንም ተገዥነት አወጣችኋለሁ፥ ከባርነታችውም አድናችኋለሁ፤ በተዘረጋ ክንድ፤ በታላቅ ፍርድም እታደጋችኋለሁ፥ ለእኔም ሕዝብ እንድትሆኑ እቀበላችኋለሁ፥ አምላክም እሆናችኋለሁ፤ እኔም ከግብፃውያን ባርነት ያወጣኋችሁ እግዚአብሔር አምላካችሁ እንደሆንሁ ታውቃላችሁ፡፡›› (ዘፀ. ፮፥፮-፯)

‹‹እግዚአብሔርም የፈጠረው ሁሉ እጅግ ያማረ እንደሆነ ተመለከተ›› (ዘፍ.፩፥፴፩)

በባሕርዩ ክቡር የሆነው እግዚአብሔር የፈጠረው ሁሉ ክቡር ነው። ይሁን እንጂ አበው በብሂላቸው ‹‹ከጣትም ጣት ይበልጣል›› እንዲሉ እጅግ የከበሩ ፍጥረታትም አሉ። ከእነዚህ እጅግ የከበሩ ፍጥረታት ከሚባሉት መካከል በቀዳሚነት የሚገኘው የሰው ልጅ ነው። ስለዚህ የሥነ ፍጥረትን ታሪክ የጻፈልን ሊቀ ነቢያት ሙሴ ሁሉንም ፍጥረታት ከፈጠረ በኋላ ‹‹መልካም እንደሆነ አየ›› እያለን ይመጣና ሰው ላይ ሲደርስ ግን ‹‹እጅግ መልካም እንደሆነ አየ›› በማለት ይደመድማል። ሊቁ ቅዱስ ያሬድም ‹‹ሰንበት ተዐቢ እምኵሉ ዕለት ወሰብእ ይከብር እምኵሉ ፍጥረት፤ ከዕለታት ሰንበት ትበልጣለች፤ ከፍጥረታትም ሁሉ ሰው ይበልጣል›› በማለት እንደነገረን የሰውን ልጅ እጅግ ክቡር ፍጥረት መሆኑን ያስረዳናል። የሰው ልጅ ክቡርነት በተመለከተ መጻሕፍት አምልተውና አስፍተው ይናገራሉ። (ዘፍ.፩፥፴፩)

ቅዱስ ወንጌል

ወንጌል፡- ወንጌል የሚለው ቃል ‹‹ሄዋንጌሊዎን›› ከሚለው የግሪክ ቃል የመጣ እንደሆነና በግእዝ ቋንቋም ብሥራት፣ ምሥራች፣ አዲስ ዜና፣ መልካም ወሬ፣ ደስ የሚያሰኝ፣ ስብከት ማለት እንደሆነ አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ ይገልጻሉ፡፡ (በመጽሐፈ ሰዋስው ወግስ ወመዝገብ ቃላት ሐዲስ ገጽ ፫፻፺፬)

ጥምቀት

በዘመነ ሥጋዌ በናዝሬት ከተማ፤ ዮርዳኖስ ወንዝ የእስራኤል ሕዝብ በመጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ እጅ ለመጠመቅ ተራ ይዘው በሚጠብቁበት ጊዜ እርሱ እንዲህ እያለ ይሰብክ ነበር፤ ‹‹እናንተ የእፉኝት ልጆች፥ ከሚመጣው መቅሠፍት ታመልጡ ዘንድ ማን ነገራችሁ? እንግዲህ ለንስሓ የሚያበቃችሁን ሥራ ሥሩ፤ አብርሃም አባታችን አለን በማለት የምታመልጡ አይምሰላችሁ፤ እግዚአብሔር ከእነዚህ ድንጋዮች የአብርሃም ልጆችን ማንሣት እንደሚችል እነግራችኋለሁ፡፡ እነሆ፥ ምሳር በዛፎች ላይ ተቃጥቶአል፤ መልካም ፍሬ የማያፈራውን ዛፍ ሁሉ ይቈርጡታል፤ ወደ እሳትም ይጥሉታል፡፡›› (ሉቃ.፫፥፯-፱)

ሕዝቡም ምን ቢያደርጉ እንደሚሻል በተራ በተራ ይጠይቁት ጀመር፤ እርሱም ለእያንዳንዱ ሲመልስ፤ ሁለት ልብስ ያለው አንዱን ለሌለው እንዲሰጥ፣ ለተራበ እንዲያበላ፣ ቀራጮችን ደግሞ ከታዘዙት አትርፈው አንዳይውስዱ እንዲሁም ጭፍሮችን በማንም ላይ ግፍ እንዳይፈጽሙ እየመከረ አጠመቃቸው፡፡ እነርሱም በልባቸው እጅግ እያደነቁ ከጌታችን ኢየሱስ ጋር መሰሉት፡፡ ቅዱስ ዮሐንስ ግን እንዲህ አላቸው ‹‹እኔ በውኃ አጠምቃችኋለሁ፤ ግን የሚበልጠኝ የጫማውን ማሰሪያ እንኳን ልፈታለት የማይገባኝ ይመጣል፤ እርሱ በመንፈስ ቅዱስ፣ በእሳትም ያጠምቃችኋል፡፡›› (ሉቃ.፫፥፲፮-፲፯)

ሕዝቡ ሁሉም ከተጠመቁ በኋላ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ዮርዳኖስ ወንዝ ውስጥ ገብቶ ሊጠመቅ ወደ እርሱ ሲጠጋ ቅዱስ ዮሐንስ ግን ‹‹እኔ በአንተ ልጠመቅ እሻለሁ፤ አንተ ወደ እኔ ትመጣለህን?›› በማለት ከለከለው፡፡ ጌታችን ኢየሱስም መልሶ አሁንስ ተው፤ እንዲህ ጽድቅን ሁሉ ልንፈጽም ይገባናልና›› አለው፡፡ እርሱም ተወው፤ ጌታችን ኢየሱስም ከተጠመቀ በኋላ ወዲያውኑ ከውኃ ወጣ፤ በዚይች ቅጽበትም ሰማይም ተከፈተ፤ መንፈስ ቅዱስም በርግብ አምሳል ወርዶ በራሱ ላይ ሲቀመጥ አየ፡፡ እነሆም በእርሱ ደስ የሚለኝ የምወድደው ልጄ ይህ ነው የሚል ድምጽ ከሰማይ መጣ፡፡›› (ማቴ.፫፥፲፫-፲፯)

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የባሕርይ ልጁ መሆኑን እግዚአብሔር አብ ልጄ ብሎ መሰከረ፤ እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ በርግብ አምሳል ወረደ፤ ወልደ እግዚአብሔር ሰው ሆኖ ተጠምቆ በፅንፈ ዮርዳኖስ ታየ፡፡
እግዚአብሔር አምላክም ለአዳም የገባለነትን ቃል ለመፈጸም አንድ ልጁን ልኮ ከኃጢአት ባርነት አወጣው፡፡ ስለዚህም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደዚህ ዓለም የመጣው አዳምን እና ሔዋንን ከባርነት ነፃ ለማውጣትና ድኅነት ሊሆናቸው ነውና በጥምቀቱ ጊዜ በዮርዳኖስ ወንዝ በሰይጣን ተቀብሮ የነበረውን የዕዳ ደብዳቤያቸውን ቀደደላቸው። ይህንንም ቅዱስ ጳውሎስ እንዲህ በማለት ተናግሮታል። ‹‹እናንተም በበደላችሁና ሥጋችሁን ባለመገረዝ ሙታን በሆናችሁ ጊዜ፥ ከእርሱ ጋር ሕይወትን ሰጣችሁ። በደላችሁን ሁሉ ይቅር አላችሁ። በእኛ ላይ የነበረውን የሚቃወመንንም በትእዛዛት የተጻፈውን የዕዳ ጽሕፈት ደመሰሰ፤…።›› (ቆላ.፪፥፲፫-፲፬)

ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለነፍሳችን ድኅነት ይሆነን ዘንድ ተጠምቆ አርአያ ሆኖናል፡፡ በጥምቀቱም ጥምቀትን ባርኮልናል፤ በኦሪት ጥምቀት ሥጋን እንጂ ነፍስን አይፈውስምና እርሱ በተጠመቀው ጥምቀታችን ተባረከልን፡፡
እኛም ስንጠመቅ በአዳም በደል ተወስዳ የነበረች ልጅነታችን ተመልሶ፣ የዕዳ ደብዳቤያችንም እንዲደመሰስልን አስረዳን፡፡ እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስም ቀደማዊና ደኃራዊ እንደሌለው እንደተመሰከረ እኛም ስንጠመቅ ከሥላሴ መወለዳችን ይረጋገጥልና፡፡ (ዮሐ. ፫፥፭፣ የሐዋ. ፪፥፴፰፣ ቆላ. ፪፥፲፩-፲፬)

ጥምቀት ለክርስቲያኖች ሁለተኛ ልደታቸው ነው፡፡ ከሥጋ የተወለደ ሁሉ ወደ ፈቃደ ሥጋው ስለሚያደላ መንፈሳዊ ልደት ያስፈልገዋል፡፡ ‹‹ሰው ዳግመኛ ካልተወለደ በቀር ወደ የእግዚአብሔር መንግሥት ሊገባ አይችልም፡፡›› (ዮሐ. ፫፥፫-፭)
በዘመነ ብሉይ ይፈጸም የነበረው ጥምቀት የንስሓ ጥምቀት ነበር፡፡ በሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ ‹‹ንስሓ ግቡ ኃጢአታችሁ ይሠረይ ዘንድ እያንዳንዳችሁ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ተጠመቁ›› ብሏቸው እንደተናገረው ጥምቀት ኃጢአትን ያስተርይልናል፡፡ (ሐዋ. ፪፥፴፯-፴፰)
በሐዲስ ኪዳን የሚፈጸመው ግን የልጅነት ጥምቀት ነው፤ ይህን ተከትሎ ወንድ ልጅ በዐርባ ሴት ልጅ በሰማንያ ቀን ይጠመቃሉ፡፡ የዚህም ምክንያት አዳም በተፈጠረ በ፵ ቀኑ፣ ሔዋንም በተፈጠረች በ፹ ቀኗ ወደ ርስታቸው ገነት እንደገቡ ሕፃናትም በ፵ እና በ፹ ቀናቸው ተጠምቀው የሰማያዊት ኢየሩሳሌም አምሳል ወደሆነችው ወደ ቤተ ክርስቲያን ይገባሉ፡፡
በተጨማሪም ቅዱስ ጳውሎስ ‹‹ነገር ግን በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ እኛ ሁላችን በሞቱ እንደተጠመቅን ሁላችሁ ይህን ዕወቁ፤ እኛ ሁላችን ከሞቱ ጋር አንድ እንሆን ዘንድ እንደ ተጠመቅን አታውቁምን? እንግዲህ ክርስቶስ በአብ ክብር ከሙታን እንደተነሣ እንዲሁ እኛ በአዲስ ሕይወት እንድንመላለስ ከሞቱ ጋር አንድ እንሆን ዘንድ በጥምቀት ከእርሱ ጋር ተቀበርን›› በማለት በጥምቀት ክርስቶስን እንደምንመስለው ተናግሯል፡፡ ‹‹ከሞቱ ጋር አንድ እንሆን ዘንድ በጥምቀት ከእርሱ ጋር ተቀበርን›› የሚለውን በገቢር ለመግለጽ እንዲሁም ‹‹በጥምቀት ደግሞ ከሙታን ባስነሣው በእግዚአብሔር ሥራ በማመናችሁ ከእርሱ ጋር ተነሳችሁ›› ያለውን እንዲሁ በድርጊት ለማሳየት ነው፡፡ (ሮሜ ፮፥፫-፬፣ቆላ. ፪፥፲፪)

‹‹ያመነ የተጠመቀ ይድናል፤ ያላመነ ያልተጠመቀ ይፈረድበታል›› እንደተባለው ከገሃነመ እሳት ፍርድ እንድናለን። ሰው ክርስቲያን ይባል ዘንድ ሀብተ መንፈስ ቅዱስ ማግኘት አለበት፡፡ ይህም በልጅነት የሚያገኘው በረከት በተቀደሰ ውኃ በመጠመቁ ነው፡፡ ካልሆነ ግን የእርኩስ መፈንስ ማደሪያ ወይንም መናፈቅ ይሆናል ማለት ነው፡፡ (ማር. ፲፮ ፥ ፲፮)
በእምነት ለተጠመቀ ሰው ግን ጥምቀት ፈውሰ ሥጋን እንዲሁም ፈውሰ ነፍስን ይሰጣል፤ ምክንያቱም እምነት ኃይልን ታደርጋለችና ጥምቀት ድኅነት መሆኑን አምነን ከተጠመቅን ኃጢአታችን ይሠረይልናል፤ ይህም ጌታችን ጥምቀትን ባርኮ ስለሰጠን በምሥጢረ ጥምቀት የምንረዳው ነው፡፡

ጌታችን ኢየሱስ የጥምቀትን ሥርዓት ከመሰረተልን በኋላ ደቀ መዛሙርቱን በአብ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም የሰውን ዘር እንዲያጠምቁ አዟቸዋል፡፡ የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ተከታዮች በሙሉም በምሥጢረ ጥምቀት እንደምንረዳው ሥርዓቱን ጠብቀን እንጠመቃለን፤ ይህም ሥርዓት ከዋዜማው ከተራ ጀምሮ የሚፈጸም ነው፡፡ (ማቴ. ፳፰፥፲፱-፳)
የጥምቀት በዓል በእነዚህ ሁለት ቀናት ውስጥ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስን በዓለ ጥምቀት እና ተግባር የሚያመለክቱ ብዙ መንፈሳዊ ሥነ ሥርዓቶች ይከናወናሉ፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የጠፋውን ፍጥረቱን ፍለጋ ወደ ዓለም እንዴት እንደወረደ የሚገልጹ ያሬዳዊ ዝማሬዎች እና መዝሙሮች በከተራ ይዘመራሉ፡፡

ሁሉም የቃል ኪዳኖች (ታቦቶች) በእያንዳንዱ አብያተ ክርስቲያናት ውስጥ በአቅራቢያው ውኃ ወዳለበት ወደ ጅረት ገንዳ ይሄዳሉ፡፡ የዚህም ምሥጢር ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከኢየሩሳሌም ወደ ዮርዳኖስ ወንዝ እንዴት እንደሄደ የሚያሳይ ነው፤ አንድ ሌሊት ማሳለፉ ጌታችን በትህትና የእርሱን ተራ መጠበቁን የሚያሳይ ነው፡፡ በቅዱስ ዮሐንስ እጅ ከተጠመቁት ሕዝቦች መካከል ተጠምቋልና፡፡ ይልቁንም ተራውን በመጠበቅ የትህትናን ተግባር አሳይቶናል፡፡ ታቦታቱም ከሕፃናት፣ ከወላጆች፣ ከወጣቶች፣ ከአረጋዊያን፣ ከሰንበት ትምህርት ቤቶች ተማሪዎች፣ ከቤተ ክርስቲያን ሊቃውንት እና ከሌሎችም ምእመናን ጋር በሁሉም ክርስቲያኖች ይታጀባሉ፡፡

ሌሊቱን በውዳሴ በማኅሌት ካሳለፉ በኋላ ውኃው በፓትርያኩ፣ በሊቀ ጳጳሳት እና በካህናት ከመባረኩ በፊት ማለዳ ቅዳሴ ይጀምራል፤ ምእመናንም የቅዳሴ አካል ለመሆን ቀደም ብለው ይገኛሉ፡፡ ሃይማኖት አባቶችም ውኃውን በአብ፣ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም ከባረኩት በኋላ ወደ ተሰበሰቡት ክርስቲያኖች በብዛት ውኃውን ለመርጨት ዝግጅት ያደርጋሉ፡፡

በዚያን ጊዜ ክርስቲያኖች በሺዎች ከሚቆጠሩ ዓመታት በፊት በዓይነ ኅሊናቸው ወደኋላ በመመለስ የጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ጥምቀት በማሰብ ከተረጩ በኋላ በደስታ ታቦታቱን በኅብረት ወደየቤተ ክርስቲያን በማጀብ ይጓዛሉ፤ ካህናቱም የያሬድን ዝመሬ በመዘመር በዓሉን ያከብራሉ፡፡

ሕፃናት፣ ወጣቶች እንዲሁም አረጋዊያን በሙሉ በዝማሬው ይሳተፋሉ። የቅዱሱ ታቦትም በደኅና ወደ መንበሩ ሲመለስ ሕዝቡ በመንፈሳዊ ደስታ ወደ ቤታቸው ይሄዳሉ፡፡ ኢትዮጵያውያን በዚህ አስደናቂ እና መንፈሳዊ ክርስቲያናዊ ምግባር አማካኝነት የእግዚአብሔርን ልጅ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ማወደሱን የቀጠልን ሲሆን ለመጪው ትውልድም ይህንኑ እንድናስተላልፍ በእምነት እና ሃይማኖት ልንጸና ይገባል፡፡

እግዚአብሔር አምላክ በጥምቀቱ ፈውሰ ሥጋንና ፈውሰ ነፍስን ያድለን ዘንድ ፍቃዱ ይሁንልን፤ አሜን!

‹‹በቸልተኝነት እና በግዴለሽነት ፈጣሪን አትርሱ!›› ሊቀ ጉባኤ አባ አበራ በቀለ

ቸልተኝነትና ግዴለሽነት በዚህ ትውልድ ከመንጸባረቁም ባሻገር ሰዎች ፈጣሪን ረስተውና ሃይማታቸውን ትተው እንዲኖሩ አድርጓቸዋል፡፡ በተለያዩ አጋጣሚዎችም የእግዚአብሔርን ቃል ሲሰሙም ሆነ ምንባባትን ሲያነቡ በግዴለሽነትና ቸል ብሎ በማለፍ ሌሎች ነገሮች ላይ ትኩረት ይሰጣሉ፡፡ ምድራዊ ሕይወታቸው ላይ ብቻ በማተኮር ለጥቅም በመገዛትና ጊዜያዊ ደስታን ለማግኘት ሲሉም መንፈሳዊነትን ንቀው ዓለማዊ ሕይወት እየኖሩ ይገኛሉ፡፡

‹‹በራስህ አስተያየት ጠቢብ አትሁን›› (ምሳ. ፫፥፯)

በቅርብ ጊዜ ከተነሡት ፍልስፍናዎች አንዱና እጅግም የተስፋፋው የኢ-አማንያን አመለካከት ማለትም ‹‹ሃይማኖት የጦርነት ምንጭ ነው፤ ስለዚህ አያስፈልግም›› በሚል ክርስትናን እና ተዋሕዶ ሃይማኖትን በመንቀፍ ለቤተ ክርስቲያን መቃጠልና ለበርካታ ምእመናን ሞት መንሥኤም ሆኗል፡፡ ይህ የምዕራባውያን አስተሳሰብ የቤተ ክርስቲያንን ሕልውና መጋፋትና የተዋሕዶ ሃይማኖት አረንቋ ከሆነ ሰነባብቷል፡፡ ስለሆነም ከምን ጊዜውም የበለጠ ክርስቲያኖች በሃይማኖት እና በእምነት ሊጸኑ እንደሚገባ እንረዳለን፡፡

‹‹እግዚአብሔር ብርሃን ነው፤ ጨለማም በእርሱ ዘንድ ጥቂትስ እንኳ የለም›› (፩ዮሐ. ፩፥፭)

ፀሐይ በቀን፣ ጨረቃም በጨለማ ለምድር ብርሃን እንደሆኑ ሁሉ አምላካችን እግዚአብሔር በአማኞቹ ልብ ያበራል፤ ቅዱስ ዮሐንስ በመልእክቱ ‹‹እግዚአብሔር ብርሃን ነው፤ ጨለማም በእርሱ ዘንድ ጥቂትስ እንኳ የለም›› ሲል እንደተናረው በእርሱ ዘንድ ጨለማ የለም፤ ሁሌም ብርሃን ነው፡፡ ‹‹ከእንግዲህም ወዲህ ሌሊት አይኖርም፤ የመብራት ብርሃን፥ ወይም የፀሐይ ብርሃን አያስፈልጋቸውም፤ እግዚአብሔር ያበራላቸዋልና፤ ለዘለዓለምም እስከ ዘለዓለም ይነግሣሉ›› እንደተባለው ያ ብርሃን ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ  ነው፡፡ (ራእ. ፳፪፥፭)

‹‹በበለስ ዛፍ ሥር አየሁህ›› (ዮሐ.፩፥፶፩)

እግዚአብሔር ሁላችንንም ከበለስ በታች ያውቀናል፡፡ እግዚአብሔር ዝም የሚለው ስለማያውቀን አይደለም፡፡ ናትናኤልን እያወቀው ተንኮል የሌለበት የእስራኤል ሰው እንደሆነ ተናገረ፡፡ ጌታችን ኢየሱስ በገሊላ ባሕር እንዳስተማረው ትምህርት ሊሰሙ፣ ሊማሩ፣ ሊለወጡ ባለመቻላቸውም ‹‹ኮራዚ ወዮልሽ! ቤተ ሳይዳ ወዮልሽ! በእናንተ የተደረገው ተአምራት በጢሮስና በሲዶና ተደርጎ ቢሆን ቀድሞ ማቅ ለብሰው አመድም ነስንሰው በተቀመጡ ንስሓም በገቡ ነበር፡፡ ነገር ግን ጢሮስና ሲዶና ከእናንተ ይልቅ በፍርድ ቀን ይቅርታን ያገኛሉ፡፡ አንቺም ቅፍርናሆም እስከ ሰማይ ድረስ ከፍ ከፍ ብትዪ እስከ ሲኦል ትወርጃለሽ›› ብሎ ጌታችን ተናገሯል፡፡ (ሉቃ.፲፥፲፫-፲፭)

‹‹እንደተማራችሁት በሃይማኖት ጽኑ›› (ቆላ. ፪፥፯)

ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ልጆቿ ሃይማኖታቸውን እንዲያጸኑ ታስተምራለችና ስለሃይማኖታችን ልንኖር ይገባል፤ ሃይማኖት የእግዚአብሔርን ህልውና ማወቅ ለእርሱ መታመን ነውና ምእመናን ሁሉ በሃይማኖት መጽናት አለብን፡፡ ይህም በሕይወታችን የሚመጣብንን መከራ እና ፈተና ሁሉ በትዕግሥት እንድናልፍ ይረዳናል። ቅዱስ ጳውሎስ አስቀድሞ ለቆላስይስ ምእመናን ማስተማሩን በማስታወስ እኛ ክርስቲያኖች በቅድሚያ የተማርነውን ትምህርት አጽንተን በሃይማኖት እንድንቆይ ነግሮናልና።

‹‹የዮና ልጅ ስምዖን ሆይ ትወደኛለህን?›› (ዮሐ. ፳፩፥፲፭)

የዮና ልጅ ስምዖን በቤተ ሳይዳ ዓሣ አጥማጅ የነበረ ሰው ነው፡፡ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በተጠመቀበት ዕለት ማግሥት ከዐሥራ ሁለቱ ሐዋርያት አንዱ አድርጎ መረጠው፤ ስሙም ጴጥሮስ ተባለ፡፡ ወንጌልን ይሰብክ እና ምእመናንም ይፈውስ ዘንድ ሥልጣንና ኃይልን የተሰጠው ቅዱስም ሆነ፡፡ የአስቆርቱ ይሁዳ ጌታን ለአይሁድ አሳልፎ እስኪሰጠው ድረስም ከእርሱ ጋር ኖሯል፡፡ ፍጹም ሃይማኖት፣ ለጌታውም ቅንዓት እና ፍቅርም ነበረው፡፡ (ስንክሳር ሐምሌ ፭)