በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚማሩ አባላት መንፈሳዋ ጉዞ አካሄዱ

ሚያዚያ 21 ቀን 2005 ዓ.ም.

በዳዊት ደስ

የማኅበረ ቅዱሳን የአዲስ አበባ ማእከል “መራሔ ፍኖት” በሚል መሪ ቃል በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት እየተማሩ ላሉ የቤተ ክርስቲያን ልጆች መንፈሳዊ ጉዞ ወደ ሱሉልታ ደብረ ምሕረት ቅድስት ሥላሴ ቤተ ክርስቲያን ሚያዚያ 20 ቀን 2005 ዓ.ም. አካሄደ፡፡

የጉዞውን ዓላማ አስመልክቶ አስተባባሪ የሆነው ሸዋለም ተክሉ ከዚህ ቀደም በግቢ ሲማሩ የነበሩ ተሞክሮአቸውን የሚያካፍሉበት፣ ተማሪዎች መንፈሳዊም ሆነ በሚማሩት ትምህርታቸው ያለባቸውን ጥያቄ የሚመለስበትና የክርስትና ሃይማኖት ተከታይ ሆነው ወደ ግቢ የማይመጡትን ተማሪዎችን በግቢ እየመጡ እንዲማሩ ለማድረግ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

አያይዘውም ይህ የግቢ ጉባኤ አንድነት መርሐ ግብር ለአራተኛ ጊዜ የተካሄደ ሲሆን ከጉዞው የሚጠበቀው ውጤት በመንፈሳዊ ሕይወታቸው የዛሉ የመንፈስ ብርታት የሚያገኙበት፣ የግቢያት የአባላት ቁጥር ወደተሻለ እድገት እንዲመጣ ለማድረግ ነው ሲሉ አስተባባሪው ተናገረዋል፡፡

በዕለቱ በግቢ ጉባኤ ተማሪዎችና በዘማርያም መዝሙር ቀርቢል፣ ትምህርተ ወንጌል የተሰጠ ሲሆን ግቢያቱ በተለያየ ርዕሰ ጉዳይ የተጠየቁ ጥያቄች ምላሽ ተሰጥተውባቸዋል፡፡ በመርሐ ግብሩ ሲሳተፉ ያገኘናቸው ወጣት ዮዲት ተገኔ የሮያል ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ ተማሪ ስትሆን በዚህ ጉዞ ለመጀመሪያ ጊዜዬ ነው የተጓዝኩት፡፡ ጉዞው ትልቅ ነገር አስተምሮኛል፡፡ የሌሎችን ግቢ ጉባኤ ተማሪዎች ጋር አስተዋውቆኛል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ላይ እየተሠራ ያለውን ተግባር እንዳይ አድርጎኛል በማለት ገልጻለች፡፡

ሌላው የ5 ኪሎ ግቢ ጉባኤ ተማሪ የሆነው ናትናኤል ስዮም በጉዞው በመሳተፌ በውስጤ ይመላለስ የነበሩብኝ ጥያቄዎች ተመልሰውልኛል፡፡ እንደዚህ አይነት መርሐ ግብሮች ወጣቱን የሚያንፁ ስለሆነ ማኅበሩ አጠናክሮ ሊሠራበት የሚገባ ተግባር ነው፡፡ ሲል አስተያየቱን ሰጥቷል፡፡ በጉዞው ላይ ከ60 በላይ ከሚሆኑ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎች የመጡ ከሁለት ሺህ በላይ ተጓዦች ተሳትፈዋል፡፡

ቅዱስ ፓትርያርኩ ከማኅበረ ቅዱሳን ቴሌቪዥን ጋር ልዩ ቃለ መጠይቅ አደረጉ

ሚያዚያ 17 ቀን 2005 ዓ.ም.


 abune matyas 17

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት ከማኅበረ ቅዱሳን ቴሌቪዥን ጋር በዓለ ትንሣኤን ምክንያት በማድረግ ልዩ ቃለ መጠይቅ አደረጉ፡፡ በዚህ አንድ ሰዓት የፈጀ ቃለ መጠይቅ ላይ ቅዱስነታቸው ስለ ልጅነት ጊዜያቸው ፣ በትምህርት ቤት ሳሉ ስለነበሯቸው ገጠመኞች ፣ ስለ ምንኩስና ሕይወት፣ በቤተ ክርስቲያኒቱ ስላሉ ልዩ ልዩ አስተዳደራዊና ችግሮች እና በተሠጣቸው ሓላፊነት ምን ሊሠሩ እንዳሰቡ ፣ ስለ ቅድስት ሀገር የርስት ጉዳይ ከግብፅ ቤተ ክርስቲያን ጋር ለመሥራት ስለታሰበው መፍትሔ እና ስለ ዕርቀ ሰላሙ ጉዳይ ሰፋ ያለ ማብራሪያ የሠጡ ሲሆን ሙሉ ቃለ መጠይቁ በማኅበሩ የቴሌቪዥን መርሐ ግብር ከበዓለ ትንሣኤ ጀምሮ እንደሚቀርብ የማኅበሩ ሬድዮና ቴሌቪዥን ክፍል አስተባባሪ ዲያቆን ሄኖክ ኃይሌ ገልጸዋል፡፡

የማኅበረ ቅዱሳን በኢቢኤስ ቴሌቪዥን መርሐ ግብር ከተጀመረበት የካቲት ፲፮ ፳፻፭ ጀምሮ እስከ በዓለ ትንሣኤ ድረስ ዐሥር ልዩ ልዩ መርሐ ግብራትን ያስተላለፈ ሲሆን የተጀመረበትን ሰዓት በማስተካከልም መርሐ ግብሩ ዘወትር እሑድ ከ5፡30 – 6፡00 ሰዓት ድረስ ሆኗል፡፡ የተላለፉ ዝግጅቶችም በኢንተርኔት http:// eotc.tv ላይ በማንኛውም ሰዓት መከታተል ይቻላል፡፡ ዝግጅቶቹን በመመልከት በስልክና በኢንተርኔት አድራሻዎቻችን ገንቢ አስተያየቶቻችሁን የሠጣችሁን ምዕመናንን እያመሰገንን ለበለጠ ሥራ ረድኤተ እግዚአብሔር እንዳይለየን ጸልዩልን ሲሉ የክፍሉ አስተባባሪ ገልጸዋል፡፡  

sera 2 1

ሠራተኛ ጉባኤያት በቤተ ክርስቲያን ትልቅ ድርሻ እንደሚጠበቅባቸው ተገለጸ

ሚያዚያ 15 ቀን 2005 ዓ.ም.

በዳዊት ደስታ

sera 2 1የማኅበረ ቅዱሳን የአዲስ አበባ ማእከል ትምህርትና ሐዋርያዊ አገልግሎት ክፍል የሠራተኛ ጉባኤ የአንድነት መርሐ ግብር ሚያዚያ 13 ቀን 2005 ዓ.ም. በጠቅላይ ቤተ ክህነት የስብከተ ወንጌል አዳራሽ በተካሄደው መርሐ ግብር ሠራተኛ ጉባኤያት በቤተ ክርስቲያን ትልቅ ድርሻ እንደሚጠበቅባቸው ተገለጸ፡፡

የመርሐ ግብሩን ዓላማ አስመልክቶ የትምህርትና ሐዋርያዊ አገልግሎት ክፍል ሓላፊ የሆኑት ኀይለ ማርያም መድኅን “በአዲስ አበባ ማእከል ሥር ሆነው የሚማሩ 22 የሚደርሱ የሠራተኛ ጉባኤያት ለቤተ ክርስቲያን እውቀታቸውን፣ ገንዘባቸውን፣ ጊዜያቸውን ሊያበረክቱ የሚያስችላቸውን ነገር ማስጨበጥና በተደራጀ ሁኔታ ቤተ ክርስቲያንን በአቅም ማገልገል የሚችሉበትን ሁኔታ ለመፍጠር ነው” በማለት ገልጸዋል፡፡

አያይዘውም እንደዚህ ዓይነት መርሐ ግብር ሲዘጋጅ የመጀመሪያ ጊዜ በመሆኑ ወደፊት የተለያዩ የሠራተኛ ጉባኤያትን በአንድነት ለማጠናከር በቤተ ክርስቲያን ከዚህ ቀደም ከሚሠሩት የተሻለ ሥራ እንዲሠሩ ለማድረግ የታሰበ ነው በማለት ሓላፊው ተናግረዋል፡፡

በዕለቱ በዲ/ን ያረጋል አበጋዝ “የቤተ ክርስቲያን ተልዕኮና ዓላማ እና የልጆቿ ድርሻ” በሚል ጥናታዊ ጽሑፍ፣ ትምህርተ ወንጌልና መዝሙር ቀርቧል፡፡ በቀረበው ጥናታዊ ጽሑፍsera 2 2 አስተያየትና ጥያቄዎች ቀርበው ከጥናት አቅራቢው ምላሽ ተሰጥቶባቸዋል፡፡

በመርሐ ግብሩ ላይ ሲሳተፉ ያገኘናቸው አቶ ተስፋዬ አሻግሬ “በዛሬዋ ቀን በመገኘቴ ትልቅ ደስታ ተሰምቶኛል፡፡ ምክንያቱም በርካታ መሥሪያ ቤቶች ጉባኤ ያካሂዳሉ፡፡ ከመማር ባለፈ ምንም ድርሻ እንዳለን እንኳ አናውቅም ነበር፡፡ ዛሬ ግን ቤተ ክርስቲያናችን ከኛ ከልጆቿ ብዙ ነገር እንደምትጠብቅና መሥራት እንደምንችል አውቄበታለው” በማለት ገልጸዋል፡፡

በዕለቱ በተደረገው መርሐ ግብር ከአምስት መቶ በላይ የሆኑ በተለያየ መሥሪያ ቤት የሚሠሩ የሠራተኛ ጉባኤ ተሳታፊዎች ተገኝተዋል፡፡

health

ለአብነት ተማሪዎች በጤና አጠባበቅ ላይ ያተኮረ ሥልጠና ተሰጠ

ሚያዚያ 14 ቀን 2005 ዓ.ም.

በእንዳለ ደምስስ

healthበማኅበረ ቅዱሳን የቅዱሳት መካናት ልማትና ማኅበራዊ አገልግሎት ዋና ክፍል ከጎንደር ማእከል ጋር በመተባበር በጎንደር ውስጥ ከሚገኙ አብነት ትምህርት ቤቶች ለተውጣጡ ተማሪዎች በግልና በአካባቢ ንጽህና አጠባበቅ ላይ ያተኮረና አንድ ቀን የወሰደ ስልጠና በደብረ ኀይል ወደብረ ጥበብ በዓት ለማርያም ቤተ ክርስቲያን አዳራሽ  ሚያዚያ 12 ቀን 2005 ዓ.ም. ተሰጠ፡፡

“ጤና ሀብት ነው” በሚል መሪ ቃል የተሰጠውን ሥልጠና በማስመልከት በማኅበረ ቅዱሳን የቅዱሳት መካናት ልማትና ማኅበራዊ አገልግሎት ዋና ክፍል የአብነት ትምህርት ቤቶች ክትትል ክፍል ምክትል ኃላፊና የፕሮጀክቱ አስተባባሪ ሊቀ ዲያቆን መሐሪ መዘምር የሥልጠናውን ዓላማ አስመልክቶ በሰጡት ማብራሪያ “በአብነት ትምህርት ቤቶች ውስጥ ከፍተኛ የሆነ የጤና ችግሮች ይታያሉ፡፡ ይህንንም መነሻ በማድረግ 25 ሺህ ተማሪዎችን ተጠቃሚ የሚያደርግ ፕሮጀክት በመቅረጽ የጤና አጠባበቅ ትምህርት ለአብነት ትምህርት ተማሪዎች ለመስጠት አቅደን ወደ ትግበራ በመሸጋገር ላይ እንገኛለን፡፡ ጎንደር ከተማ ውስጥ እስከ 2000 ተማሪዎች ይገኛሉ ተብሎ ስለሚገመት ለሁሉም ሥልጠና ለመስጠት ስለሚያዳግት ከየአብነት ትምህርት ቤቱ ለተውጣጡ 200 ተማሪዎች ሥልጠናውን እየሰጠን እንገኛለን፡፡ ተማሪዎቹም በአብነት ትምህርት ቤቶቻቸው ውስጥ ለሚገኙ ጓደኞቻቸው የአቻ ለአቻ ሥልጠና እንዲሰጡ እናደርጋለን፡፡” ብለዋል፡፡

በጎንደር ማኅበረ ቅዱሳን ማእከል የአብነት ትምህርት ቤቶቹን የጤና አጠባበቅ ሁኔታ የሚከታተልና የሚቆጣጠር ኮሚቴ እንደሚዋቀር የተገለጸ ሲሆን የግልና የአካባቢ ንጽህና ለመጠበቅ የሚረዱ ቁሳቁሶች እደላና አጠቃሙን ለማሳየት በየአብነት ትምህርት ቤቶቹ የሙከራ ሥራ እንደሚሠራ ሊቀ ዲያቆን መሐሪ መዘምር ገልጸዋል፡፡

ከመንበረ ፀሐይ ቁስቋም ማርያም ገዳም የቅኔ ጉባኤ ቤት ተማሪ የሆኑት መሪ ጌታ ዮሴፍ ታረቀኝ ስለ ሥልጠናው ጠቀሜታ ሲገልጹ “አብሮ ስላደገብን ቀሸሽ ብለን ስለምንታይ ለተለያዩ በሽታዎች ስንጋለጥ ኖረናል፡፡ ንጽሕናችንን መጠበቅ የሚጠቅመው ራሳችንን ስለሆነ ማኅበረ ቅዱሳን እየሰጠን ያለውን ስልጠና ወስጄ ለተማሪዎች በቅኔ ነገራ ወቅትም ሆነ አመቺ በሆነ ስዓት ለማስተማር ተዘጋጅቻለሁ” ብለዋል፡፡

ስልጠናው የግልና የአካባቢ ንጽሕና አጠባበቅ፤ የውኃ አያያዝና አጠቃቀም፤ የምግብ አያዝና አጠቃቀም፤ የበሽታ መንስኤዎች፤ የበሽታ መተላለፊያ መንገዶች፤ ተላላፊ በሽታዎችን መከላከል፤ ወባ፤ የግርሻ በሽታ፤ . . . የሚሉ ርዕሶችን ያካተተ ሲሆን ለሃያ አምስት ሺህ ተማሪዎች በአራት ዓመታት ውስጥ ተጠቃሚ ለማድረግ እስከ አንድ ሚሊዮን ብር እንደሚፈጅ ተገልጧል፡፡  

ኒቆዲሞስ

ሚያዚያ 12 ቀን 2005 ዓ.ም.

በመ/ር ሳሙኤል ተስፋዬ

እግዚአብሔር “ጾምን ቀድሱ ጉባኤውንም ዐውጁ ሽማግሌዎችንና በምድር የሚኖሩትን ሁሉ ወደ አምላካችሁ ወደ እግዚአብሔር ሰብስቡ ወደ እግዚአብሔርም ጩኹ በጽዮን መለከት ንፉ ጾምንም ቀድሱ” በማለት ዐውጀን መጾም ያለብንን ጾም እንድንፆም በነብዩ ኢዩኤል ነግሮናል፡፡ ኢዩ.1፥14፣ 2፥15

እግዚአብሔር ሙሴን በእሥራኤል ልጆች ዘንድ ከሰውም ከእንስሳም ማኅፀንን የሚከፍት በኲርን ሁሉ ለእኔ ቀድስልኝ በማለቱ /ዘጸ.13፥12 ከሰው፣ ከዕለታትት ተለይተው የተቀደሱ ነበሩ፡፡ አጽዋማትም በዐዋጅ ተለይተው ይጾማሉ፡፡ ከእነዚህ ውስጥም፡- የዐብይ ጾም ይገኛል፡፡

ዐብይ ጾም ዐብይነቱ ነብያት፣ ሐዋርያት፣ ቅዱሳን የጾሙት ጾም ሳይሆን የጠፋውን የሰውን ልጅ ለመፈለግ፣ የሞተውን አዳምን ለማስነሣት አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሰው ሆኖ ወደዚህ ዓለም የመጣው ወልደ አብ ወልደ ማርያም በመብል የተጀመረውን የሞት መንገድ ለማጥፋት በጾም ስለጀመረው ነው፡፡

አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመዋዕለ ሥጋዌው ያደረጋቸውን የድኅነት ጉዞና ድንቅ ድንቅ ተአምራት ዋጋ የተከፈለባቸው በመሆናቸው አባቶቻችን በሠሩልን ሥርዓት መሰረት በዐብይ ጾም ወራት ዘወረደ ብለን ጀምረን ትንሣኤ ብለን አስከምናከብርበት ድረስ ያሉትን ሰንበታት ለሰው ልጆች የተከፈለልንን ዋጋ እያሰብን እንማረዋለን፣ አንዘምራለን፣ እንጸልያለን፡፡ ከነዚህ ሰንበታት በ7ኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ደግሞ ኒቆዲሞስ ተብሎ ተሰይሞ ይከበራል፡፡

ከፈሪሳውያን ወገን የአይሁድ አለቃ በነበረው በኒቆዲሞስ የተሰየመ ሰንበት ነው፡፡ የአይሁድ አለቆች አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስን “ምልክት አሳየን” እያሉ ይፈታተኑት ነበር፡፡ ስለሞቱና ትንሣኤው በምሳሌ ቢነግራቸው አልገባቸውም፡፡ ሲያስተምር ብዙዎች ያምኑ ነበር፡፡ ለአይሁድ አለቆች ግን ጭንቅ ነበር፤ የታመሙ ሲፈወሱ ሕጋችን ተሻረ ይሉ ነበር፡፡ በዚህ ሁሉ ተአምራትና ትምህርት የአይሁድ አለቆች ክርስቶስን ለመክሰስ በሚፈልጉበት ወቅት ከአይሁድ አለቆች አንዱ ኒቆዲሞስ በቀን እንዳያደርገው አይሁድን ፈርቶ አንድም ጊዜ አላደርሰው ብሎ እንደ አይሁድ አለቆች ኢየሱስን መቃወሙን ትቶ በሌሊት ወደ ኢየሱስ ክርስቶስ ዘንድ ሄደ፡፡

አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ በነፍስ የታመሙትን በቃሉ በሥጋ የታመሙትን በተአምራቱ ሲፈውስ፤ ኒቆዲሞስ ሰምቶና ተመልክቶ “መምህር ነኝ” ብሎ በመምህርነቱ ሳይኮራ አለቅነቱን መመኪያ ሳያደርግ፡፡ በልቦናው የተሳለውን እውነትን የመፈለግ ስሜት አንግቦ ጌታው መምህሩ ዘንድ በሌሊት ገሠገሠ ዮሐ.3÷1

ደርሶም ምስክርነቱን እንዲህ ሲል መስጠት ጀመረ “መምህር ልታስተምር ከእግዚአብሔር ዘንድ እንደመጣህ እናውቃለን፡፡ እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር ከሆነ በቀር አንተ የምታደርገውን ተአምራት ሊያደርግ የሚችል የለምና” ዮሐ.9÷24፣ የሐዋ.ሥራ 10÷38 በማለት መመስከር ሲጀምር ጎዶሎን የሚሞላ፡፡ አላዋቂነት በአዋቂነት የሚለውጥ፡፡ ከምድራዊ እውቀት ወደ ሰማያዊ ምስጢር የሚያሸጋግር አምላክ፡፡ “ዳግመኛ ያልተወለደ የእግዚአብሔርን መንግሥት ለማየት አይችልም” ዮሐ.3÷6 1ጴጥ.1÷23 በማለት የአይሁድ መምህር ለሆነው ኒቆዲሞስ ቢያስተምረው ስለዳግመኛ መወለድ ከመጽሐፍ ቢያገኘውም ምስጢሩ አልተገለጠለትምና “ሰው ከሸመገለ በኋላ ዳግመኛ መወለድ እንደምን ይቻላል? ዳግመኛ ይወለድ ዘንድ ወደ እናቱ ማኅፀን ተመልሶ መግባት ይችላልን?” በማለት ጥያቄ አቅርቧል፡፡

“እውነት እውነት እልሃለሁ ዳግመኛ ከውኃና ከመንፈስ ቅዱስ ያልተወለደ ወደ እግዝአበሔር መንግሥት ሊገባ አይችልም፡፡ ኤፌ.5÷26 ከሥጋ የተወለደ ሥጋ ነው፡፡ ከመንፈስም የተወለደ መንፈስ ነውና፡፡ በማለት አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ ቢያስረዳው ምስጢሩ ከአቅሙ በላይ የሆነበት ኒቆዲሞስ እንደምን ይቻላል? በማለት ጠይቋል፡፡ አበ ብዙኀን አብርሃም ከአምላኩ ሞገስን አግኝቶ፤  የሰዶምና ገሞራ ጥፋት እንዳይደርስ እያማለደ ከእግዚአብሔር ጋር ሲነጋገር እንደ ነበረ፤ ኒቆዲሞስም አላዋቂነቱን አምኖ ያልገባውን ምስጢር አምላኩን የመጠየቅ ዕድል በማግኘቱ ሲጠይቅ፣ ኢየሱስ ክርስቶስም “አንተ የእስራኤል መምህራቸው ነህ ግን ይህን ነገር አታውቅምን? በምድር ያለውን ስንነግራቸው ካላመናችሁ በሰማይ ያለውን ብንነግራችሁ እንደምን ታምናላችሁ? ከሰማይ ከወረደው ከሰው ልጅ በቀር ወደ ሰማይ የወጣ የለም ….፡፡ሙሴ ምድረ በዳ እባቡን እንደ ሰቀለ የሰው ልጅ እንዲሁ ይሰቀላል፡፡ ያመኑበት ሁሉ ለዘለዓለም ሕያው ሆኖ እንዲኖር እንጂ እንዲጠፉ አይደለም…..” ዮሐ.3÷14፡፡ እያለ ለድኅነተ ዓለም እንደ መጣ ሰው በመብል፣ አምላኩን ከድቶ ልጅነቱን ትቶ ከእግዚአብሔር ቢለይም የሰው ልጅ ያጣውን ልጅነት ለመመለስ ስመ ግብርና ሀብተ ወልድን ለመስጠት መምጣቱን አስረዳው፡፡ “ሐወጽከኒ ሌሊተ ወፈተንኮ ለልብየ፡፡ አመከርከኒ ወኢተረከ በዓመፃ በላዕሌየ፡፡ ከመ ኢይንብብ አፉየ ግብረ እጓለ እመሕያው፡፡ ልቤን ፈተንከው በሌሊትም ጎበኘኸኝ ፈተንከኝም ምንም አላገኘህብኝም፡፡ የሰውን ሥራ አፌ እንዳይናገር ፈቃዴ ነው” መዝ.16÷3 እንዳለ ቅዱስ ዳዊት ምስጢረ ሥጋዌን የድኅነት ምስጢር ገልጾለታል፡፡

በሌሊት ከአምላኩ ተምሮ ምስጢሩ የተገለጸለት ኒቆዲሞስ ፍርሃት ርቆለት ቀድሞ በአደባባይ ሄዶ መማርን የፈራ ምስጢሩ ሲገለጽለት አይሁድ በሰቀሉት ዕለት ሳይፈራ ከአርማትያሱ ዮሴፍ ጋር ቅዱስ ሥጋውን ገንዞ ለመቅበር በቃ “ወአልቦ ፍርሃት ውስተ ተፋቅሮትነ፡፡ ፍጹም ፍቅር ፍርሃትን አውጥቶ ይጥላል ማቴ.27÷58፣ 1ዮሐ.4÷18 እንዲል፡፡

ያመነ የተጠመቀ ይድናል፡፡ ያላመነ ያልተጠመቀ ይፈረድበታል ማር.16÷16፡፡ ባለው አማናዊ ቃል ኪዳን መሠረት አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስን እንደ አምላክነቱ አምነን  ለመንግሥቱ ዜጋ እንድንሆን ለኒቆዲሞስ ምስጢሩን ጥበቡን የገለጸ አምላክ ለኛም ይግለጽልን፡፡

gedamat 11

የኔታ ይቆዩን የገዳማት ዐውደ ርእይ በፓሪስ ከተማ

ሚያዚያ 11 ቀን 2005 ዓ.ም.

በዲ/ን ደረጄ ግርማ

 

gedamat 11የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ማኅበረ ቅዱሳን አውሮፓ ማእከል የፈረንሳይ ግንኙነት ጣቢያ ገዳማትና አብነት ትምህርት ቤቶችን የሚያስተዋውቅ ዐውደ ርእይ ማዘጋጀቱን ገለጠ።

 

ዐውደ ርእዩም የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያንን ታሪክና ለሀገር ያበረከተችውን አስተዋጽኦ፣ በተለይም ጥንታዊ ገዳማት ትናንትና ዛሬ እንዲሁም የአብነት ትምህርት ቤቶችን ነባራዊ ሁኔታ የሚዳስስ፤ እየተደረጉ ያሉ ድጋፎችን የሚጠቁም እንዲሁም ከሕዝበ ክርስቲያኑ የሚጠበቀውን ድርሻ የሚያመላክት ዐውደ ርእይ ይቀርባል።

ከዚህም በተጨማሪ የአባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ ስኮላርሸፕ፤ የላይ ቤት ትርጓሜ ፕሮጀክት እንዲሁም የቅዱስ ያሬድ 1500 ዓመት መታሰቢያ የሚያመላክቱ ጹሑፎች ቀርበው ውይይት ይደረግባቸዋል፡፡ ዐውደ ርእዩም ሚያዚያ ፲፰ ቀን ፳፻፭ ዓም ለፓሪስ እና አካባቢ ምእመናን እንደሚቀርብ ተገልጿል። ከፓሪስ ደብረ ም/ቅ/ማርያም ሰበካ ጉባኤ ጋር በመተባበር ሚያዚያ ፲፱ ቀን ፳፻፭ ዓም ልዩ የስብከተ ወንጌል መርሐ ግብር የተዘጋጀ ሲሆን በዕለቱም በገዳማት እና አብነት ትምህርት ቤቶች ወቅታዊ ሁኔታ ላይ ውይይት እንደሚካሄድ ከዝግጅቱ አስተባባሪ ኮሚቴ የደረሰን መረጃ አመልክቷል። ለዚህ ዝግጅት አስፈላጊውን ድጋፍ ለማድረግ የማኅበረ ቅዱሳን ቅዱሳት መካናትና ማኅበራዊ አገልግሎት ዋና ክፍል አንድ ልዑክ እንዲሚልክ ለማወቅ ተችሏል።

 
በአውሮፓ የምትገኙ ሁላችሁም በዝግጅቱ እንድትታደሙ የተጋበዛችሁ ሲሆን በርቀት ያላችሁ ለመርሐ ግብሩ ስኬት በጸሎት እንድታግዟቸው አስተባባሪ ኮሚቴው ጥሪውን አስተላልፏል።

seletena 2 2

ከየማእከላቱ ለተውጣጡ ተጠሪዎች የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥልጠና ተሰጠ

ሚያዚያ 9 ቀን 2005 ዓ.ም.

በዳዊት ደስታ

seletena 2 2በማኅበረ ቅዱሳን የቅዱሳት መካናት ልማት እና ማኅበራዊ አገልግሎት ዋና ክፍል ከየማዕከላቱ ለተውጣጡ 38 የክፍል ተጠሪዎች ከሚያዝያ 4 ቀን 2005 ዓ.ም. በዋናው ማእከል የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥልጠና ተካሄደ፡፡

የሥልጠናውን ዓላማ አስመልክቶ የቅዱሳት መካናት ልማት እና ማኅበራዊ አገልግሎት ዋና ክፍል ዳይሬክተር ዲ/ን አእምሮ ይሄይስ “የማኅበሩን ስልታዊ ዕቅድ ተጠሪዎቹ ግንዛቤ ኖሮአቸው በቀጣይ በየማእከላቱ የሚሠሩትን ሥራ በተግባር ላይ እንዲያውሉ ለማስቻል  ነው” ብለዋል፡፡

አያይዘውም ሥልጠናው በዚህ ዓመት ለመጀመሪያ ጊዜ የተካሄደ ሲሆን፣ በቀጣይም  በገዳማት ላይ የሚሠራውን የልማት ሥራ በጋለ ሆኖ ከታሰበበት ለማድረስ ያግዛል ሲሉ ሓላፊው ገልጸዋል፡፡

ከሥልጠናው ተሳታፊዎች መካከል የደሴ ማእከል የቅዱስት መካናት ልማት እና ማኅበራዊ አገልግሎት ክፍል ተጠሪ ወ/ት ስንታየው እሸቱ በሥልጠናው የተለያዩ ግንዛቤዎችን አግኝቻለሁ፡፡ በተለይ የአብነት ትምህርት ቤት ላይ የምንሠራቸውን ሥራ እንዴት ማጠናከርና ገቢ ማሰባሰብ እንዳለብን፣ ፕሮጀክት እንደምንቀርጽና እንደምንተገብር ተንዝቤያለሁ፡፡

ሌላው ከአሰበ ተፈሪ ማእከል የመጣው አቶ ብርሃኑ እንዳለ በሀገራችን በሚገኙአብያተ ክርስቲያናት የአገልጋይ እጥረት ይስተዋላል፡፡ ከዚህ አንጻር የአብነት ትምህርት ቤቶች ተተኪ አገልጋይ የሚፈራባቸው በመሆኑ ብዙ ሊሠራ እንደሚገባ የሚያመለክትና ችግሮችን ለመቅረፍ የሚያስችል ነው ብለዋል፡፡

ለሦስት ቀን በተካሄደው መርሐ ግብር ሉላዊነት እና የቤተ ክርስቲያን የማእከላት ድርሻ ምን መምሰል አለበት፣ የአባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ ስኮላር ሺፕ ፕሮግራም አፈጻጸም ማእከላት ድርሻቸው ምን መሆን አለበት፣ ቤተ ክርስቲያን ለልማት ያላት ምቹነትና ተግዳሮቶች፣ የሀብት ምንነት የፕሮጀክት ሠነድ ዝግጅት፣ የንግድ ዕቅድ ዝግጅት (ለገዳማት፣ አብያተ ክርስቲያናት፣ አብነት ት/ቤት ተማሪዎች) በሚሉ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ያተኮረ ሥልጠናና ውይይት ተደርጓል፡፡

በመርሐ ግብሩም ላይ የማኅበሩ ዋና ጸሐፊን ጨምሮ ከሁሉም ማእከላት የተውጣጡ 38 የቅዱሳት መካናት ልማት እና ማኅበራዊ አገልግሎት ዋና ክፍል ተጠሪዎች ተሳትፈዋል፡፡

“መኑ ውእቱ ገብር ኄር” “ታማኝ አገልጋይ ማነው”? ማቴ.24፥45

ሚያዚያ 4 ቀን 2005 ዓ.ም.

በመ/ር ምስጢረ ሥላሴ ማናየ

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ስያሜ የዐቢይ ጾም ስድስተኛው እሑድ ወይም ሳምንት ገብር ኄር ይባላል፡፡ ሰያሜውን የሰጠውም ኢትዮጵያዊ ሊቅ ቅዱስ ያሬድ ነው፡፡ ጾመ ድጓ በተባለው ከአምስቱ መጻሕፍቶቹ አንዱ በሆነው ጾመ ድጓ መጽሐፍ ሳምንቱን የዐቢይ ጾም ሳምንታት ስያሜዎች ከነሥርዓተ ማኅሌቱ አዘጋጅቷል፡፡ ስለዚህ በስድስተኛው የዐቢይ ጾም ሳምንት ከዋዜማው ቅዳሜ ጀምሮ በቤተ ክርስቲያን፡- የሚዘመረው ዝማሬ፣ የሚሰበከው ስብከት፣ የሚሰጠው ትምህርት ገብርኄርን የሚያወሳ ነው ማለት ስለ ታማኝ አገልጋይ ነው፡፡ በማቴ.25፥14-25 የተገለጸውና በዕለቱ የሚነበበው ወንጌልም የሚነግረን ይህን ነው፡፡

“አንድ ባዕለ ጸጋ ሰው ባሪያዎችን ጠርቶ ለአንዱ አምስት መክሊት ሰጠው፣ ሁለት መክሊት የሰጠውም አለ፣ አንድ መክሊትም የሰጠው አለ፡፡ ከዚህ በኋላ ወደሩቅ አገር ሄደ፡፡ አምስት መክሊት የተቀበለውም ወጥቶ ወርዶ ሌላ አምስት አትርፎ አስር አደረገ፡፡ ሁለት የተቀበለውም አትርፎ አራት አደረገ፡፡ አንድ የተቀበለው ግን ሄዶ መሬቱን ቆፍሮ በሻሽ ጠቅልሎ የጌታውን መክሊት ቀበራት፡፡

ከብዙ ጊዜ በኋላ ጌታቸው መጥቶ ተቆጣጠራቸው፡፡ አምስት መክሊት የተቀበለው ቀርቦ ጌታዬ አምስት መክሊት ሰጥተኸኝ ነበር እነሆ አምስት አተረፍኩ አለው፡፡ “ገብርኄር ወምዕመን ዘበሁድ ምዕምነ ኮንከ ዲበ ብዙህ እሰይመከ ባዕ ውስተ ፍስሐሁ ለእግዚእከ” “አንተ ታማኝ ባሪያ በጥቂቱ ታምነሃል በብዙ እሾምሃለሁ ወደ ጌታህ ደስታ ግባ” አለው፡፡ ሁለት የተቀበለውም ቀርቦ ጌታዬ ሁለት መክሊት ሰጥተኸኝ ነበር እነሆ ወጥቼ ወርጄ ሌላ ሁለት አትርፌ አራት አድርጌአለሁ፡፡ “አንተ ታማኝ በጎ አገልጋይ በጥቂቱ ታምነሃል በብዙ እሾምሃለሁ ወደ ጌታህ ደስታ ግባ” አለው፡፡

አንድ መክሊት የተቀበለው ግን ቀርቦ “ጌታዬ አንተ ክፉና ጨካኝ ካልዘራህበት የምታጭድ ካልበተንህበት የምትሰበስብ እንደሆንክ ስለአወቅሁ መሬቱን ቆፍሬ ቀበርኋት እነኋት መክሊትህ” አለው፡፡ “አንተ ሰነፍ ባሪያ መክሊቴን በጊዜ ልትሰጠኝ በተገባህ ነበር እኔም ወጥቶ ወርዶ ለሚያተርፍ በሰጠሁት ነበር”፡፡

ንዑ የዚህን ሀኬተኛ መክሊት ውሰዱና አስር መክሊት ላለው ስጡት፡፡ ላለው ይሰጡታል ይጨመርለታል ለሌለው ግን ያለውን ይቀሙታል፡፡ ንዑ ይህን ሰነፍና ሃኬተኛ ባሪያ እጅ እግሩን አሥራችሁ ጽኑዕ ጨለማ ወደአለበት ውሰዱት ጩኸትና ጥርስ ማፋጨት ወዳለበት ጨምሩት” አለ ማቴ.25፥14-25፡፡

ባዕለ ጸጋ የተባለው ጌታ ነው፡፡ መክሊት የተባለው ልዩ ልዩ የአገልግሎት ጸጋ ነው፡፡ ያተረፉት በሚገባ በታማኝነት ያገለገሉ ቅዱሳን ሰዎች ናቸው መክሊቱን የቀበረው ደግሞ በታማኝነት በተሰጠው ጸጋ ማገልገል ሲገባው ያላገለገለ ነው፡፡ ጌታቸው ሊቆጣጠራቸው መጣ ማለት በዕለተ ምጽአት ለሁሉም በአገለገለው አገልግሎት ዋጋ ለመስጠት እንደሚመጣ ያሳየናል፡፡

ያገለገሉትን ወደ ጌታህ ደስታ ግባ አላቸው ማለት ታማኝ አገልጋዮች መንግሥተ ሰማያትን ይወርሳሉና፡፡ ሰነፎች ደግሞ ጥርስ ማፋጨት ስቃይ ጽኑዕ ጨለማ ባለበት ሲዖል መግባታቸውን የሚያሳይ ነው፡፡

ከላይ ያነሳነው የቅዱስ ወንጌል ቃል፡- “ታማኝ አገልጋይ ማነው”? ይህ እያንዳንዱ በአርዓያ እግዚአብሔር የተፈጠረ የሰው ልጅ ጥያቄ ነው የዚህን አምላካዊ ጥያቄ መልስ መስጠት ከሰው ልጆች ይጠበቃል፡፡

1.    ታማኝ አገልጋይ ማነው? ሙሴ ነው፡፡
ሙሴ ታማኝ አገልጋይ ነበር ታማኝ አገልጋይ መሆኑን ቅዱሳት መጻሕፍት ይመሠክራሉ፡፡ “በመካከላችሁ ነቢይ ቢኖር እኔ እግዚአብሔር በራእይ እገለጥለታለሁ ወይም በህልም አናግረዋለሁ ባሪያዬ ሙሴ ግን እንዲህ አይደለም እርሱ በቤቴ ሁሉ የታመነ ነው” ዘኁ.12፥6፡፡ ይህ የፍጡር ምስክርነት ሳይሆን በፈጣሪው የተሰጠ ምስክርነት ነው፡፡ በዕውኑ በዘመናችን እንኳን ፈጣሪ ፍጡራን ታማኝነቱን የሚመሰክሩለት አጋልጋይ ይኖር ይሆን? እንጃ የሙሴን ታማኝ አገልጋይነት በረሃ፣ ስደት፣ መከራ፣ የፈርዖን ግርማ እና ቁጣ ያልበገረው አርባ ዓመት ስለ ወንድሞቹ በመሰደድ አርባ ዓመት ደግሞ የተሰደደላቸው ወንድሞቹን በመምራት ባሕር በመክፈል፣ ጠላት በመግደል፣ መና በማውረድ ደመና በመጋረድ ውኃ ከዓለት አፍልቆ በማጠጣት መከራውን ከወገኖቹ ጋር በመቀበል የቀኑ ሀሩር የሌሊቱን ቁር/ ብርድ/ ታግሶ በታማኝነት አገልግሏል፡፡ ታማኝነቱ እስከሞት ነበር፡፡

“ሙሴም ወደ እግዚብሔር ተመልሶ ወዮ እኒህ ሕዝብ ታላቅ ኀጢአት ሠርተዋል፡፡ ለራሳቸውም የወርቅ አማልክት አድርገዋል፡፡ አሁን ይህን ኀጢአታቸውን ይቅር በላቸው ያለዚያ ግን ከጻፍከው መጽሐፍ እባክህ ደምስሰኝ ከባለሟልነትህ አውጣኝ /ዘጸ.32፥31፡፡ አያችሁ ታማኝ አገልጋይ እኔ ልሙት ሌሎች ይዳኑ የሚል ነው አሁን የምናየው ግን ፈጽሞ ከዚህ የተለየ ነው፡፡ ሰዎች ይሙቱ እኔ ልኑር ሰዎች ጦም ይደሩ እኔ ልብላ ሰዎች ይራቆቱ እኔ ልልበስ ሰዎች ይዘኑ እኔ ልደሰት ነው፡፡ ይህ ታማኝ አገልጋይ ያለመሆን መገለጫ ነው፡፡ ታማኝ አገልጋይ ለሚያገለግላቸው ሰዎች ጥቅም ቅድሚያ የሚሰጥ እንጂ የራሱን ጥቅም የሚያስቀድም አይደለም፡፡ ዛሬ በዓለማችን የምንመለከተው ግን “ጩኸት ለአሞራ መብል ለጅግራ” የሚባለውን መሰል ነው፡፡ በታማኝ አገልጋዮች ድካም የሚሸለሙ ታማኝ አገልጋዮች በሠሩት ሪፖርት የሚያቀርቡ፣ የሚወደሱ ከጥቅሙ እንጂ ከድካሙ መክፈል የማይሹ እንቅፋት የሚመታው እግርን ነው፡፡ አክሊል የሚቀዳጀው ግን ራስ ነው፡፡ ታማኝ አገልጋይ ማለት እንደራስ አክሊል ዘውድ የሚጸፋ ብቻ ሳይሆን እንደ እግር እንቅፋቱን፣ እሾሁን፣ መከራውን ውጣ ውረዱን ድካሙን የሚቀበል ነው፡፡ በጥቅም ጊዜ ለራሱ በአካፋ የሚዝቅ ሌሎች በጭልፋ የሚቆነጥር አይደለም፡፡ ሙሴ ባሕር የከፈለው መና ያወረደው ደመና የጋረደው ውኃ ያፈለቀው ለራሱ አልነበረም ለሚመራቸው ሕዝብ ነበር እንጂ፡፡ ታማኝ አገልጋይ ያሰኘውም ይኸው ነው፡፡ በዚህ ከብሮበታል ተመስግኖበታልም፡፡

2.    ታማኝ አገልጋይ ማነው? ዳዊት ነው፡፡
ዳዊት ዘመነ መሳፍንት አልፎ ዘመነ ነገሥት ሲተካ እስራኤልን በንጉሥነት እንዲያገለግል እግዚአብሔር ከበግ ጥበቃ መርጦ በተሰጠው ሥልጣን ያልተመነ የሳዖልን በትረ መንግሥት በሳሙኤል እጅ ተቀብቶ ተቀብሏል፡፡

በተሰጠው ሥልጣን በታማኝነት ሕዝበ እስራኤልን መርቷል፡፡ ታማኝነቱንም እግዚአብሔር ለሙሴ እንደ መሰከረለት ለእርሱም መስክሮለታል፡፡
“እግዚአብሔር እንደልቡ የሆነ ሰው መርጧልና” የዘይቱን ቀንድ ሞልተህ በልጆቹ መካከል ለእኔ ንጉሥ አዘጋጅቻለሁና ወደ እሴይ ወደ ቤተልሔም እልክሃለሁ” 1ሳሙ.13፥13፣ 16፥2፡፡

“ወረከብክዎ ለዳዊት ገብርየ ወቀባዕክዎ ቅብዐ ቅዱስ” እንዲል መዝ.88፥20፡፡ “ባሪያዬ ዳዊትን አገኘሁት የተቀደሰ ዘይትንም ቀባሁት” ይህን አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ ሰዓታት በተባለው ድርሰቱ፡- “ረከብክዎ ለዳዊት ገብርየ ብዕሴ ምዕመነ ዘከመልብየ” አገልጋዬ ዳዊትን እንደ ልቤ የታመነ ሰውን ሆኖ አገኘሁት ሲል ተርጉሞታል፡፡ የተገኘው በታማኝነት ነበር ከነገሠ በኋላም ታማኝ ነበር አሁን በዚህ ዓለም የምንኖር እኛ ግን በድኅነት ታማኝ እንሆንና ሀብት ሹመት ሥልጣን ሲመጣ ታማኝነትን እናጣለን፤ እንዲያውም ታማኝነትን እንንቀዋለን፡፡ መስረቅ ጀግንነት ይመስለናል፡፡ መዋሸት ሥልጣኔ ይሆንልናል፡፡ ዳዊት ሳይሾም በጎቹን በመጠበቅ ታማኝ ነበር፡፡ በጎቹን የሚነጥቅ ተኩላ አንበሳ ቢመጣ በኋላው ተከትሎ ነብሩን በጡጫ አንበሳውን በእርግጫ ብሎ በጎቹን ያስጥለው ነበር፡፡

“እኔ ባሪያህ የአባቴን በጎች ስጠብቅ አንበሳ ወይም ድብ ይመጣ ነበር ከመንጋውም ጠቦት ይወሰድ ነበር በኋላውም እከተለውና እመታው ነበር ከአፉም አስጥለው ነበር በተነሳብኝም ጊዜ ጉረሮውን አንቄ እመታውና እገድለው ነበር፡፡ ይህም ፍልስጥኤማዊ ከነዚያ እንደ አንዱ ይሆናል እንግዲህ እገድለው ዘንድ ከእስራኤል ተግዳሮትን አስወግድ ዘንድ ዛሬ አልሄድምን? የሕያው አምላክ ጭፍሮችን ይገዳደር ዘንድ ይህ ቆላፍ ምንድን ነው? ከአንበሳና ከድብ ያስጣለኝ እግዚአብሔር ከዚህ ያልተገረዘ ፍልስጥኤማዊ እጅ ያስጥለኛል” አለ 1ሳሙ.17፥34፡፡

ዛሬስ ቢሆን በእስራኤል ዘነፍስ በምዕመናን ላይ የሚገዳደሩ ብዙ ፍልስኤማውያን ተሰልፈዋል እነዚህን ድል የሚነሣ በጎቹን ምዕመናን ከተኩላ ከአንበሳና፣ ከድብ አፍ የሚታደግ ታማኝ አገልጋይ ማነው ከምእመናን ተግዳሮት የሚያርቅ ፈጣሪዬ ከመከራ ያድነኛል ብሎ የሚታመን የኢአማንያን ብዛት የማያስፈራው ማን ነው? ከትንሽነቱ እስከ ታላቅነቱ የታመነ አገልጋይ ማነው? ለተሾመበት ሓላፊነት ታማኝ ማነው? አሁንም ዓለማችን ከሥጋውያን ባለ ሥልጣናትም ሆነ ከመንፈሳዊያን መሪዎች የምትሻው ታማኝ ሰው ነው በሙስና ያልተዘፈቀ ጉቦ አይኑን ያላጨለመበት ለመንጋው አርአያና ምሳሌ የሚሆን ሰው ታማኝ አገልጋይ ማለት ያ ነው፡፡ በመኀላ የተቀበለውን የአገልግሎት ሓላፊነት የማይዘነጋ ጳጳስ፣ ቄስ፣ ዲያቆን፣ ሰባኪ፣ መምህር፣ ሐኪም፣ ዳኛ፣ ነጋዴ፣ ተማሪ፣ ወታደር፣ የቤት ሠራተኛ፣ የቢሮ ሠራተኛ ታማኝ መሆን አለበት፡፡

መንጋው በክህደት ሲጠፋ ዝም ብሎ የሚያይ ጳጳስ፣ ቄስ፣ ዲያቆን፣ መምህር፣ ሰባኪ፣ ታማኝ አይደለም ታማሚው እየተሰቃየ የሚዝናና ቆይ ሻይ ልጠጣና የሚል ሐኪም ታማኝ አይደለም፡፡ ፍርድ የሚያጎድል ድሆችን የሚበድል ለደሃ አደጎች የማይፈርድ ዳኛ ታማኝ አገልጋይ አይደለም፡፡

ቅቤ በሙዝ እና በድንች ቀላቅሎ በርበሬ በገል ጨምሮ ሌሎችን አጭበርብሮ የሚሸጥ ነጋዴ ታማኝ አገልጋይ አይደለም፡፡ እየነገደ ያለው በሰው ሕይወት መሆኑን መዘንጋት የለበትም፡፡ እንደእየ አቅሙ በተሰጠው የአገልግሎት ዘርፍ ታማኝ መሆን አለበት፡፡

3.    ታማኝ አገልጋይ ማን ነው? ዮሴፍ ነው፡፡
ዮሴፍ ለወንድሞቹ ምግባቸውን ተሸክሞ የእርሱ ስንቅ ቢያልቅ የወንድሞቹን ስንቅ ያልበላ በትንሽ የታመነ ሰው ነበር፡፡ ወንድሞቹ ሸጠውት በቤተ ጴጥፋራ በሚያገለግልበት ጊዜም ታማኝ ነበር፡፡ ታማኝነቱ በጲጥፋራ ቤት ጌታ አድርጎታል፡፡

“ዮሴፍ ተሸጠ አገልጋይም ሆነ እግሮቹ በእግር ብረት ስለሰሉ ሰውነቱም ከብረት አመለጠች ቃሉ ሳይደርስ የእግዚአብሔር ቃል ፈተነው ንጉሥ ላከ ፈታውም የሕዝብ አለቃ አድርጎ ሾመው የቤቱም ጌታ አደረገው በገንዘቡ ሁሉ ላይ ገዢ አደረገው፡፡ አለቆቹን እንደ እርሱ ይገስጽ ዘንድ ሽማግሌዎችን እንደ እርሱ ጥበበኞች ያደርጋቸው ዘንድ” መዝ.104፥17፡ በዚህ ሁኔታ የነበረው ዮሴፍ የጌታው ሚስት ሲወጣ ባቱን ሲገባ ደረቱን እያየች ዐይኗን ጣለችበት በዝሙት አይን ተመለከተችው፡፡

“የጌታውም ሚስት በዮሴፍ ላይ ዐይኗን ጣለችበት ከእኔም ጋር ተኛ አለችው እርሱም እምቢ አለ፡፡ ለጌታው ሚስቱ እንዲህ አላት እነሆ ጌታዬ በቤቱ ያለውን ሁሉ ለእኔ በእጄ አስረክቦኛል፡፡ በቤቱ ያለውን ምንም የሚያውቀው የለም በዚህ ቤት ከአኔ የሚበልጥ ሰው የለም፡፡ ሚስት ስለሆንሽ ከአንቺ በቀር ያልሰጠኝ ነገር የለም እንዴት ይህን ትልቅ ክፉ ነገር አደርጋለሁ? እንዴትስ በእግዚአብሔር ፊት ኀጢአትን እሠራለሁ ይህን ነገር በየዕለቱ ለዮሴፍ ትነግረው ነበር” ዘፍ.39፥7፡፡

በዮሴፍ ታማኝነት የጌታው ቤት ተባርኳል፡፡ ሀብቱ በዝቷል፡፡ በታማኝነቱ በቤቱ ያለውን ሁሉ ተረክቦ ነበር የቀረበለት ፈተና ግን ከባድ ነበር፤ ይህን በታማኝነቱ ማለፍ ችሏል፡፡ ዛሬ በእየአንዳንዱ ጓዳ እንደ እሳት የሚያቃጥሉ አገልጋዮች ናቸው ያሉት ልጅ በፈላ ውኃ የሚቀቅሉ ናቸው የሚበዙት እንኳን በሁሉ ገንዘብ ለመሾም አይደለም፡፡ በጥቃቅን ዕቃዎች እንኳን የሚታመን ጠፍቷል፡፡ ዮሴፍ ግን በታማኝ አገልጋይነቱ በመጣበት መከራ ቢታሰር እንኳ ያለ ሹመት አላደረም የእስረኞች አለቃ ነበር፡፡ ከእስር ቤት ሲወጣም ግብፅን በሙሉ መርቷታል፡፡ በግብፃውያን በሙሉ ተሾሟል በጥቂቱ ታምኗልና፡፡ “በጥቂቱ የታመነ በብዙ ይሾማል” እንዲል ማቴ.25፥24፡፡

ጌታውም መልካም አንተ የታመንህ በጎ አገልጋይ በጥቂት የታመንህ ስለሆንህ በብዙ እሾምሀለሁ” ከነዚህ ሦስት ታማኝ አገልጋዮች ሕይወት ሁሉም የሰው ልጅ ታማኝ አገልጋይነት የሚያሰጠውን ክብርና ጸጋ ተመልክቶ በታማኝነት ማገልገል ይገባዋል፡፡ ታማኝ መሆን መጀመሪያ የሚጠቅመው ለራስ ነው ከዚያ በኋላ ለሀገር ለወገን ለቤተ ክርስቲያን ላመኑት ላላመኑት ሁሉ ይጠቅማል፡፡ በመጨረሻም የጽድቅ አክሊልን ያቀዳጃል መንግሥተ ሰማያትን ያወርሳል፡፡ በሰውም በእግዚአብሔርም ፊት ያስከብራል፡፡

ጻድቃን ሠማዕታት ቅዱሳን በታማኝ አገልግሎታቸው ፈጣሪያቸውን ደስ አሰኝተው ከብረዋል፡፡ በሓላፊው ገንዘብ ያልታመኑት ይሁዳ፣ ሐናንያ፣ ሰጲራ፣ የደረሰባቸውን ጉዳት አይተናል፡፡ በአካን ወልደ ከርሚንም ተመሳሳይ ቅጣት ደርሶበታል ሐዋ.5፥1፣ 1፥25፡፡

ለዚህ ነበር ቅዱስ ዳዊት “አቤቱ አድነኝ ደግ ሰው አልቋልና ከሰው ልጆችም መተማመን ጎድሏልና” መዝ.11፥1፡፡ ስለዚህ ሁሉም በአለበት ያአገልግሎት መስክ ታማኝ አገልጋይ ሆኖ “አንተ በጎ ታማኝ አገልጋይ በጥቂቱ ታምነሃል በብዙ እሾምሀለሁ” የሚለውን የጌታውን የምስጋና ቃል መስማት ይገባዋል፡፡ መልካም አገልግሎት አገልግለን መንግሥቱን እንድንወርስ “ገብርኄር” እንድንባል አምላካችን ይርዳን፡፡

ሐዊረ ሕይወት በሆለታ ደብረ ኤዶም ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን

ሚያዚያ 1 ቀን 2005 ዓ.ም.

በእንዳለ ደምስስ

ሪፖርታዥ

መጋቢት 22 ቀን 2005 ዓ.ም. ሌሊት

ማኅበረ ቅዱሳን ወደ ሆለታ ደብረ ኤዶም ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን የተዘጋጀው የሐዊረ ሕይወት /የሕይወት ጉዞ/ መርሐ ግብር ላይ ለመሳተፍ ምእመናን ከሌሊቱ 12፤00 ጀምሮ አምስት ኪሎ በሚገኘው በመንበረ ፓትርያርክ ቅድስተ ቅዱሳን ማርያም ገዳም እና በማኅበረ ቅዱሳን ጽሕፈት ቤት ዙሪያ በመሰባሰብ ወደ ተዘጋጁት መኪናዎች ለመግባት ይጠባበቃሉ፡፡ እያንዳንዳቸው 61 ሰው የመጫን አቅም ያላቸው 85 አንደኛ ደረጃ አውቶቡሶች ከናዝሬት የልጃገረዶች ትምህርት ቤት እስከ ማኅበረ ቅዱሳን ጽሕፈት ቤት ፤ እንዲሁም ከትንሳኤ ዘጉባኤ ማተሚያ ቤት እሰከ መንበረ ፓትረያርክ ቅድስተ ቅዱሳን ማርያም ገዳም ሰልፋቸውን ይዘው፤ በሮቻቸውን ከፍተው ምእመናንን በመጫን ላይ ተጠምደዋል፡፡ ትራፊክ ፖሊሶች አካባቢው በመኪናና ሰው እንዳይጨናነቅ ያስተባብራሉ፡፡

ምእመናን በሐዊረ ሕይወት መርሐ ግብር አስተባባሪዎች አማካይነት የጉዞ ቲኬታቸውን እያሳዩ ለጉዞው የተዘጋጀውን ባጅ እየተቀበሉ ወደ ተዘጋጀላቸው አውቶቡሶች ይገባሉ፡፡ ለምእመናን የተዘጋጀው ባጅ ሁለት መልእክቶችን ያዘለ ሲሆን በጽህፈት ቤት ግንባታ አብይ ኮሚቴ የተዘጋጀው ሰረገላ አስክንድር /በማኅበሩ ሕንፃ ላይ አሳንሰር ለመግጠም እንዲቻል  ምእመናን ድጋፍ እንዲያደርጉ ባለ 15፤ 150 እና ባለ 600 ብር ቲኬት በሽያጭ ላይ ስለመሆኑ የሚልገጽ ባጅ/ ፤ እንዲሁም በማኅበረ ቅዱሳን የቅዱሳት መካናት ልማትና ማኅበራዊ አገልግሎት ዋና ክፍል አስተባባሪነት የተዘጋጀ ከመጋቢት 25 እስከ ሚያዚያ 11 ቀን 2005 ዓ.ም. የሚቆይ ለአብነት ትምህርት ቤቶች የጽዳት እቃዎች ማሰባሰቢ ሳምንት በሚል ለኣብነት ትምህርት ተማሪዎች የሚሆኑ የተለያዩ ለጽዳትና ለምግብ ማብሰያና መጠጫ፤ ለአካባቢና ለግል ንጽህና መጠበቂያ የሚሆኑ ቁሳቁስ ምእመናን እንዲለግሱ የሚያሳስብ ባጅ ነው፡፡

ከለሊቱ 12፡30 ሰዓት ጀምሮ መኪናዎቹ ጉዟቸውን ጀምረዋል፡፡ ከአዲስ አበባ ውጪ የሚገኙ ማእከላት ተጓዦቻቸውን ይዘው ወደ ሆለታ በመሔድ ላይ ናቸው፡፡
መርሐ ግብሩን በኢንተርኔት በቀጥታ ሥርጭት ለማስተላለፍ በዝግጅት ላይ የሚገኙት የIT ባለሙያዎችና ጋዜጠኞች የተዘጋጀላቸው መኪና በምእመናን በመያዙ ምክንያት ለስርጭቱ የሚያገለግሉትን የኤሌክትሮኒክስ መሳሪያዎችን ሌሎች መገልገያ እቃዎች በፒክ አፕ መኪና ላይ ጭነው እነሱም ከእቃዎቹ ጋር /ፍጹም፤ ቴዲ፤ ኤይተነው፤ ብዙአየሁ፤ ሄኖክ/ ተጭነዋል፡፡ እኔና በሥርጭቱ ወቅት ጽሁፎችን በመጻፍ እገዛ የምታደርግልን ጸሐፊያችን የምስራች ገቢና ቦታ ተይዞልናል፡፡ የ30 ኪሎ ሜትሩን መንገድ የመኪናውን ፍጥነትና የንፈሱን ግርፋት ተቋቁመው ወደ ሆለታ በሰልፍ የሚተሙት አውቶቡሶችን በማለፍ፤ አልፎ አልፎም ወርደን በካሜራችን የአውቶቡሶቹን በረድፍ መትመም እየቀረጽን ሆለታ ደብረ ኤዶም ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲቲያን ደረስን፡፡

በሰፊ ይዞታ ላይ ያረፈው የሆለታ ደብረ ኤዶም ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን በማኅበረ ቅዱሳን የሙያ አገልግሎት ክፍል ባለሙያዎች ዲዛይኑ ተዘጋጅቶ በነፃ የተሰጠ ሲሆን ግንባታው በመፋጠን ላይ ነው፡፡ ከአዲሱ ሕንፃ በስተ ምስራቅ አቅጣጫ በ1968 ዓ.ም. የተተከለው አነስተኛ ሕንፃ ቤተ ክርስቲያን አገልግሎት በመስጠት ላይ ይገኛል፡፡ የደብሩ አስተዳደር ጽ/ቤት፤ የሰበካ ጉባኤ ጽ/ቤት፤ የሰንበት ትምህርት ቤት አነስተኛ አዳራሽ፤ ለአጸደ ሕጻናት መማሪያነት የተሰሩ አራት ክፍሎች . . . በቤተ ክርሰቲያኑ ዙሪያ ይገኛሉ፡፡  
ቀድመውን የደረሱት አውቶቡሶች ምእመናንን አውርደው በተዘጋጀላቸው ስፍራ ላይ ተደርድረዋል፡፡ ምእመናን ከአውቶቡሶቹ እየወረዱ ቤተ ክርስቲያን እየተሳለሙ በአስተናጋጆች አማካይነት ወደ ተዘጋጀው የዳቦ መክፈልት እየተቀበሉ ወደ ተዘጋጀው ደንኳን በማምራት ቦታቸውን ይይዛሉ፡፡

ጠዋት
ከጠዋቱ 3፡00 ሰዓት ብፁዕ አቡነ ሉቃስ የሰቲት ሑመራ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ለመርሐ ግብሩ ልዩ ትኩረት በመስጠት ቡራኬያቸውን ለመስጠት በሆለታ በደብረ ኤዶም ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን ተገኝተዋል፡፡ የደብሩ የአቋቋም የአብነት መምህራንና ተማሪዎች የአቋቋም ትምህርት ሂደት ለማሳየት መምህራቸውን ከብበው፤ በዝማሬ ትምህርታቸውን ይወጣሉ፡፡ መምህሩ ቀለምና ዜማ እንዳይሰበር ይቆጣጠራሉ፡፡ ቀለም የሚስተውን ወይም ዜማ የሚሰብር ካጋጠማቸው አስተካክል በሚል በዓይናቸው ገረፍ ያደርጉታል፡፡

ከጠዋቱ 3፡30 ሰዓት ሲሆን በብፁዕ አቡነ ሉቃስ የሰቲት ዑመራ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ መሪነትና ቡራኬ መርሐ ግብሩ በጸሎተ ወንጌል ተከፈተ፡፡

የጸሎት መርሐ ግብሩ እንደተጠናቀቀ ከቀደምት ቤተ ክርስቲያንን ለማገልገል ከተመሠረቱት ማኅበራት መካከል የማኅበረ ሰላም የመዝሙር ክፍል አባላት ያሬዳዊ ዝማሬ አቅርበዋል፡፡ 

በሰዋሰው ብርሃን መንፈሳዊ ኮሌጅ የቅኔ መምህር የነበሩና በቤተ ክርስቲያን አገልግሎት በተለያዩ ሓላፊነቶች በመመደብ እያገለገሉ የሚገኙ በመንፈሳዊ ትምህርት የበለጸጉና በዘመናችን ከሚገኙ ሊቃውንት መካከል አንዱ የሆኑት ንቡረ ዕድ ከፍለ ዮሐንስ በተጋባዥ እንግድነት የተገኙ ሲሆን “መንግስተ ሰማያት ሰው ወስዶ በእርሻው የዘራትን የሰናፍጭ ቅንጣት ትመስላለች” /ማቴ.13፡31/ በሚል ርዕስ ሰፋ ያለ የወንጌል ትምህርት ሰጥተዋል፡፡

 
“የእግዚአብሔር መንግሥት የተባለች ቃለ ወንጌል ምሥጢረ ሥጋዌን ሲያመለክት ነው፡፡ሰናፍጭ በመዘራቷ ነው የበቀለችው ትለመልማለችም፤ ብዙም ፍሬ ታፈራለች፡፡ ለእናትነት ከዚህ ዓለም በመረጣት በድንግል ማርያም ትመሰላች፡፡ ከሥጋዋ ሥጋ፣ ከነፍሷ ነፍስ ነስቶ በየጥቂት አድጎና ምስጢረ ጥምቀትን ፈጽሞ እኛን የጠበቀን ያሳደገን መድኀኒታችን ኢየሱሰ ክርስቶስን አስገኝታለችና፡፡ የተበተነውን ሕይወታችንን ሊሰበሰበው ስለፈቀደ ነው፤ ወደ እኛ የቀረበው፡፡ ይህንን ማኅበር የመሠረቱት ጥቂቶች ናቸው፡፡ በሰናፍጭ ቅንጣቱ እንደ ተማርነው በማኅበሩ ጥላ ሥር ብዙዎች በእግዚአብሔር መግቦት ተሰባስበዋል፡፡ እግዚአብሔር እያሠራው ነው፡፡ ይህ ማኅበር ቤተ ክስቲያናችንን፣ አባቶቻችንን እንዲሁም ምእመናንን እንዲያገለግል የእግዚአብሔር ፈቃድ እያሰራው ነው፡፡ ምእመናንም መጠቀም የኛ ፋንታ ነው፡፡ ማኅበሩን ብንጠቀምበት፣ ብንተባበረው መልካም ነው፡፡ ከልጆቻችን ፍቅርን፣ ትሕትናን፣ ራስን ዝቅ ማድረግን፣ በጥሻው ውስጥ የወደቁት አባቶችን መጠየቅ ፤ ማጽናናትን እንማራለን፡፡ በጥምቀት ያገኘነውን ልጅነት አክብረን መኖር አለብን፡፡ ክርስቲያናዊ ሥነ ምግባር የሁል ጊዜ ሥራችንን ሊሆን ይገባል፡፡ በጾም፣ በጸሎት የአጋንንት ክንድ መቁረጥ አለብን ቅዱስ ጳውሎስ ሰይፍን እንድናነሳ የሚነገረን ወንጌልን እንድንጫማ፣ ሥነ ምግባርን ታጥቀን መኖር እንዳለብን ሲያስተምረን ነው፡፡ ዛሬ አስለቃሾች ብንሆን ነገ አልቃሾች እንዳንሆን ልንጠነቀቅ ይገናል፡፡ ወዮባዮች እንዳንሆን በክርስቲየናዊ ሥነ ምግባር ሌሎችን መርዳት ይገባናል፡፡ መዳን ዝም ብሎ ፈረስ ጭኖ፣ መኪና ነድቶ የሚመጣ አይደለም በጎ ሥራ በመሥራት ግን ይገኛል፡፡ ያሰባሰበን እምነታችን ነው፡፡ ለነገ ቀጠሮ መያዝ አያስፈልግም፡፡ ለመዳን የሚፈልግ ሁሉ ይድናል፡፡ እኛም ድነናል፡፡ ልትድን ትወዳለህን የሚለውን አምላካዊ ቃል ሁል ጊዜ የምንጠየቀው ጥያቄ ነው፡፡ አዎ መዳን እንፈልጋለን ብለን የመጣን ነን፤ መዳን ስለምትፈልጉ ትጾማላችሁ፣ ንስሐ ትገባላችሁ፤ ሥጋወ ደሙ ወደሚሰጥበት ቤተክርስቲያን ትገሰግሳላችሁ፡፡ ይህ ሁሉ የሚሆነው መዳን ስለምትፈልጉ ነው፡፡” በማለት ሰፊ ትምህርት ሰጥተዋል፡፡

 

በመቀጠልም በዲ/ን ዘማሪ ቴዎድሮስ ዮሴፍ ዝማሬ የቀረበ ሲሆን በመልአከ ገነት አባ ወ/ጊዮርጊስ አበጀ የደብረ ኤዶም ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን አስተዳዳሪ የደብሩን ታሪክ በአጭሩ አቅርበዋል፡፡

 

በሆለታ ደብረ ኤዶም ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን የተደረገው የሐዊረ ሕይወት መርሐ ግብር እስከ ምሳ ሰዓት የተካሔደውን ከላይ ያስቃኘናችሁ ሲመስል በመርሐ ግብሩ ላይ በአጠቃላይ 5700 ምዕመናን የአጥቢያው ምእመናንን ሳይጨምር መሳተፋቸውን ከአስተባባሪ ኮሚቴው የደረሰን መረጃ ያመለክታል፡፡ የምሳ መርሐ ግብሩም
በተሳካ ሁኔታ ተካሒዷል፡፡

ከሰዓት በኋላ
ከሰዓት በኋላ በተያዘው መርሐ ግብር መሠረት የማኅበረ ቅዱሳን የመዝሙር ክፍል አባላት ያሬዳዊ ዝማሬ በማቅረብ የተጀመረ ሲሆን ከጠዋት ጀምሮ በመርሐ ግብሩ ላይ በመገኘት ምእመናንን በመባረክ የቆዩት ብፁዕ አባታችን አቡነ ሉቃስ የሰቲት ሑመራ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ከስዓት በኋላ ለሌላ አገልግሎት ወደ አዲስ አበባ ስለሚመለሱ ቃለ ምእዳንና ቡራኬ ሰጥተዋል፡፡   

 
ብፅዕነታቸው በሰጡት ቃለ ምዕዳን “የእግዚአብሔር ልጆች  የእግዚአብሔር ሥራ ይሠራሉ፡፡ መመሰባሰባችን ከሁሉም በላይ ፈቃዱ የእግዚአብሔር ነው፡፡ የክርስትና ጉዞ ተምሮ መቅረት ተገንብቶ መፍረስ አይደለም፡፡ የክርስቶስ ልጆች የምንሆነው የክርስቶስን ሥራ ስንሠራ ነው፡፡ መሠረቱ ደግሞ ፍቅር ነው፡፡ የክርስትና ሃይማኖት እውነት እንጂ  ሐቁን አለባብሶ አቆንጅቶ ማስቀመጥ አይደለም፡፡ የክርስቶስ ሥራዎች በእኛ ሕይወት ውስጥ ሊታይ ይገባል፡፡ ይህ የእግዚአብሔር ጉባኤ ነው፡፡ እግዚአብሔር ባይመራው በፀሐይ እየተመቱ አፈር ላይ ተቀምጦ መማር አይቻልም” ብለዋል፡፡ ብፁዕነታቸውም ቡራኬ ሰጥተው ወደ አዲስ አበባ የተመለሱ ሲሆን ጉባኤው ግን ቀጥሏል፡፡
ከስዓት በኋላ ከተያዙት መርሐ ግብራት መካከል ዲ/ን ብርሃኑ አድማስ “በኢየሩሳሌም የሚኖሩ” መ.ኢያሱ.15፥63  በሚል ርዕስ የዕለቱን የወንጌል ትምህርት ሰፋ አድርገው ሰጥተዋል፡፡  

ዲያቆን ብርሃኑ አድማስ በሰጡት የወንጌል ትምህርት “የከነዓንን ምድር የወረሱት የኤፍሬም ልጆች ናቸው፡፡ በጌዝርም የተቀመጡትን ከነዓናዊያንንም አላሳደዷቸውም እሰከ ዛሬም ድረስ ከነዓናዊያን በኤፍሬም ልጆች መካከል ተቀምጠዋል፡፡ ከነዓን ርጉም ፍሬ ቢስ ማለት ነው የተቀደሰውን የሚረግጥ፣ በጎውን እያየ የማይጠቀም፤ እንቁውን የሚረግጥ…. ኤፍሬም ማለት ደግሞ ፍሬያማ ማለት ነው፡፡ ኢያቡሳውያንም ከአፍሬማውያን ጋር አብረው ኖረዋል፡፡  ዛሬም ኢያቡሳውያን  በቤተ ክርስቲያን ውስጥ በተለያዩ ምክንያቶች አብረውን ይኖራሉ፤ ማጥፋት ባንችልም በግብራቸው ግን ልንተባበር አይገባም፡፡ ኑፋቄውን ማሳደድ መናፍቁን ማዳን፤ የዝሙትን መንፈስ መገሰጽ ዘማዊውን ማንጻት፤ የንፍገት መንፈስን ማሳደድ ንፉጉን ቸር፤ ለጋስ ማድረግ ይገባል፡፡ ይህ ነው መልካም ጦርነት የምንለው፡፡ አንዳንድ ጊዜ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ መልካም ያልሆኑ ነገሮችን ስንመለከት፤ አንዳንድ መናፍቃንን ስንመለከት፤ በቤተክርስቲያን ውስጥ በምግባር እጅግ የራቁና ባልተገባ ሕይወት ውስጥ ቤተ ክርስቲያንን ለማሽከርከር የሚጥሩ ሰዎችን ስናይ እግዚአብሔር ለምን ዝም ይላል እንላለን፡፡

“በየቤቱ እንደ ጸሎት መጽሐፍ የራሱን ኑፋቄ ይዞ የሚዞር አለ፡፡ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ሆኖ መጥፎ ሥራ የሚሰራውን ተመልክቶ ቤተ ክርስቲያን ትክክል አደለችም ማለት፣ በጎውን ደግሞ አይቶ ቤተ ክርስቲያን መጥፎ የለባትም ማለት አይቻልም፡፡ በኢየሩሳሌም ሁለቱም አይነት ሰዎች አሉና፡፡ ዛሬ በገዳማት ውስጥ ሆነው የሚያጭበረብሩ ሰውን  እንዲህ ታገኛላህ እያሉ የሚያታልሉእንዳሉ ሁሉ ሲያዩአቸው ምናምንቴ መስለው ስለ ሕዝብና ስለ ሀገር የሚጸልዩም አሉ” ብለዋል፡፡  

ከዲያቆን ብርሃኑ አድማስ የወንጌል ትምህርት በኋላ ዘማሪ ዲ/ን ዳዊት ፋንታዬ ያሬዳዊ ዝማሬ በመቅረብ የእለቱ መርሐ ግብር ቀጥሏል፡፡

ምእናን እንዲመለሱላቸው የሚፈልጓቸውን ጥያቄዎች በስልክ፤ በኢሜይል፤ እንዲሁም በአካል በመገኘት ለሐዊረ ሕይወት አስተባባሪ ኮሚቴው ያደረሱትን ምላሽ እንዲሰጥባቸው ማድረግ የመርሐ ግብሩ አንዱ አካል ስለነበር ዲያቆን ያረጋል አበጋዝ በእያንዳንዱ ጥያቄ  ላይ ሰፋ ያለ ትንታኔ በማቅረብ ምላሽ ተሰጥቶባቸዋል፡፡ ከተነሱት ጥያቄዎች መካከልም “በቤተ ክርስቲያን ውስጥ አርአያ የማደርገው ሰው አጣሁ፡፡ ተስፋ በመቁረጥ ላይ ነኝ፡፡ ምን ትመክሩኛላችሁ?” ለሚለው ዲያቆን ያረጋል ሲመልሱም “ሃይማኖት ከእግዚአብሔር ጋር የሚኖረን ግንኙነት ነው፡፡ ከሰዎች ጋር በተለያየ ምክንያቶች ልንገናኝ እንችላለን፡፡ ከእግዚአብሔር ፍቅር ተነሳ ነው ሰውን የምንወደው እንጂ ስለ ሰዎች ፍቅር ብለን አይደለም እግዚአብሔርን የምንወደው፡፡ መነሻው እግዚአብሔር ነው፡፡ ወደ ቤተ ክርስቲያን ስንመጣ ፤  ክርስትናን ስናውቅ መጀመሪያ ሰዎችን አይደለም ማወቅ ያለብን፡፡ ሰዎች ወደ እግዚአብሔር ሊመሩን ይችላሉ፡፡ እነዚህ መንገዶች ናቸው፡፡ መድረሻው ግን አሁንም እግዚአብሔር ነው፡፡ ስለዚህ መጀመሪያ መተዋወቅ ያለብን ከእግዚአብሔር ጋር ነው፡፡ እኛ ግን ወደ ቤተ ክርስቲያን እንመጣና ከእግዚአብሔር ጋር ሳይሆን ከሰዎች ጋር እንተዋወቃለን፡፡ እግዚአብሔርን ትተን ከሰዎች ጋር እንጣበቃለን፡፡ እነዚያ ሰዎች ሲጠፉ እኛም አብረን እንጠፋለን፡፡ ቤተ ክርስቲያንን በአንዳንድ ወዲህ ወዲያ በሚሉ ሰዎች መለካት የለብንም፡፡ ማሰብ ያለብን የጸኑትን ነው፡፡ ስለዚህ አርአያ የምናደርጋቸው ሰዎች ከእግዚአብሔር እንደማይበልጡ መረዳት አለብን፡፡ ከሰዎች ይልቅ እግዚአብሔርን ማየት ስንጀምር ተስፋ መቁረጥ ከኛ ይርቃል፡፡ አርአያ የምናደርጋቸው ሰዎች ከቤተ ክርስቲያን ቢወጡ እንኳን እኛ ተስፋ ያደረግነው እግዚአብሔር እንዳለን ስለምንረዳ እንጸናለን፡፡” በማለት ምላሻቸውን ሰጥተዋል፡፡

ነብዩ ኤልያስ ከብሔረ ሕያዋን ወደ ምድር ወርዷል፡፡ እኛንም ልኮናል የሚሉ ወገኖች ተነሥተዋልና አስተምህሯቸው ምንድነው? ብታብራሩልን በማለት ለተጠየቀው ጥያቄም ዲያቆን ያረጋል በሰጡት ምላሽ “ሰንበት ቀዳሚት ናት፤ እሁድን ማክበር ስህተት ነው፡፡ ኤልያስ ሰንበትን ወደ ቅዳሜ ይመልሳል፤ እስካሁን እውነተኛው የመልከ ጼዲቅ መሥዋእት ስላልተሰዋ አሁን ኤልያስ እውነተኛውን የመልከ ጼዲቅ መስዋእት ይዞ መጥቷል፤ የጌታችን የመድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዓለ ልደት ታህሣሥ 29 ሳይሆን መስከረም 1 ቀን ነው መከበር ያለበት፤ የዳዊት ኮከብ ተብሎ የሚጠራው ባለ ስድስት ጫፉ ኮከብን ይዛችሁ ጸንታችሁ ቁሙ፤ በቅርቡ በባሕር ዳር ውስጥ ሰውር ጉባኤ ተካሒዷል፡፡ ከኒቂያ፤ ከኤፌሶንና ከቁስትንትኒያ ጉባኤያት በላይ ተካሒዷል፡፡ በዚህ ጉባኤም ከገነትና ከብሔረ ሕያዋን ቅዱሳን መጥተው ተገኝተዋል፤ ካህናትን የገሰጸችና ከነመጻሕፍቶቻቸው ቤተ መቅደሳቸውን ያጠፋች ዮዲት ቅድስት ናት ይላሉ” በማለት ስለ ኤልያስ ወረዷል እያሉ በማስተማር ላይ ስለሚገኙት ሰዎች አስተምህሯቸውን ገልጸዋል፡፡

በመጨረሻም ቀሲስ ዶክተር ሰሙ ምትኩ የማኅበረ ቅዱሳን ሰብሳቢ የማኅበረ ቅዱሳን አመሠራረት፤ እያከናወናቸው ስለሚገኙ የአገልግሎት ዘርፎች በአጭሩ በመዳሰስ ለምእመናን ግንዛቤ ያስጨበጡ ሲሆን መርሐ ግብሩንም በማጠናቀቅ በጸሎት ተዘግቶ ምእመናን ወደ መኪናዎቻቸው አምርተው በሰላም ጉዞው እንደተጀመረ በሰላም ተጠናቋል፡፡