የማቴዎስ ወንጌል
ግንቦት 22 ቀን 2006 ዓ.ም.
ይህ ወንጌል በምዕራፎች ብዛት የመጀመሪያው ወንጌል በመሆን 28 ምዕራፎች ዐቅፏል፡፡ በቁጥሮች ብዛት ደግሞ ሁለተኛ ወንጌል ሆኖ 1068 ቁጥሮችን አካቷል፡፡ የተጻፈው ከማርቀስ ወንጌል ቀጥሎ በ58 ዓ.ም. አካባቢ ነው፡፡ የጌታን ትምህርት በሰፊው በማቅረብ ቀዳሚውን ሥፍራ ይዟል፡፡ ከ1068 ቁጥሮች መካከል 644ቱ የጌታ ትምህርቶች ናቸው፡፡ ይኸም ከወንጌሉ 60% ማለት ነው፡፡ በዚህ አቀራረቡ ከዮሐንስ ወንጌል ጋር ሲዛመድ ከሉቃስና ከማርቆስ ወንጌል ይለያል፡፡
ወንጌሉን የጻፈው ለአይሁድ በመሆኑ ከ150 በላይ የብሉይ ኪዳን ጥቅሶችን አቅርቢል፡፡ በዚህም የተነሣ ብሉይ ኪዳንን አብዝቶ በመጥቀስ ከሌሎቹ ወንጌሎች ይበልጣል፡፡ ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ቀድሞ በነቢያት የተነገረለት መሲሕ መሆኑን ለማስረገጥ ሲል አንድን ታሪክ ከጻፈ በኋላ “በዚህም…. ተብሎ የተነገረው /በነቢይ የተጻፈው/ ተፈጸመ” ብሎ ይመሰክራል፡፡
ሐዋርያው ቅዱስ ማቴዎስ ትውፊትን በብዛት የተጠቀመ ሐዋርያ ነው፡፡ ማቴዎስ ወንጌሉን ስለ ጻፈበት ቋንቋ ሦስት ዓይነት አሳብ ቀርቧል፡፡
-
በዕብራይስጥ፡- የቤተ ክርስቲያናችንን ሊቃውንት ጨምሮ ብዙ ምሁራን የተስማሙት ቅዱስ ማቴዎስ ወንጌሉን በዕብራይስ ቋንቋ ጻፈው በሚለው አሳብ ነው፡፡ ነገር ግን አስካሁን ድረስ የዕብራይስጡ ዋና ቅጅ (original copy) አልተገኘም፡፡
-
በአራማይክ፡- ፖፒያስ የተባለው አባት በ2ኛው መቶ ክፍለ ዘመን እንደገለጠው ሐዋርያው ቅዱስ ማቴዎስ አስቀድሞ የጌታችንን ትምህርቶችን በአራማይክ ቋንቋ ሎጂያ (logia) በተባለው መጽሐፍ ሰብስቦት ነበር፡፡ በኋላም ወንጌሉን ሲጽፍ የጌታን ትምህርቶች የገለበጠው ከዚህ መጽሐፉ ነው፡፡ አራማይክ ከዕብራይስጥ ዘዬዎች (dialects) አንዱ ሲሆን በመጀመሪያው መቶ ክፍለ ዘመን አካባቢ የመካከለኛው ምሥራቅ /በተለይም በፍልስጥኤም ምድር/ ዋና ቋንቋ (lingual franca) ነበረ፡፡ ጌታም ወንጌሉን የሰበከው በአራማይክ ቋንቋ በመሆኑ ማቴዎስ የወንጌሉን መነሻ ረቂቅ በዚህ ቋንቋ ጽፎታል፡፡ በወንጌሉ ግን እጅግ በጣም ጥቂት ቃላትን /ለምሳሌ ኤሎሄ ኤሎሄ ላማ ሰበቅታኒ፡፡ ማቴ.27፥46/ ብቻ ከመጠቀሙ በቀር የአራማይክ ቃላት ተተርጉመው ቀርበዋል እንጂ አጻጻፉ አራማይክን አልተከተለም፡፡
-
በግሪክ፡- አብዛኞቹ ጥንታውያን ቅጂዎች የሚገኙት በግሪክ ቋንቋ በመሆኑ በግሪክ ቋንቋ ተጻፈ የሚል አሳብ አለ፡፡ ጥንታውያን አበው (apologists) የማቴዎስን ወንጌል ሲጠቅሱ የተጠቀሙትም የግሪኩን ነው፡፡ በቤተ ክርስቲያናችን ትውፊት መሠረት ግን የማቴዎስን ወንጌል ወደ ግሪክ /ፅርዕ/ የተረጎመው ዮሐንስ ወንጌላዊ ነው፡፡
የማቴዎስ ወንጌል ከማርቆስ ወንጌል በኋላ በሁለተኛነት ተጽፎ እያለ የመጀመሪያውን ተርታ ያገኘበት ዋናው ምክንያት አቀራረቡ ለብሉይ ኪዳንና ለሐዲስ ኪዳን ድልድይ ስለሆነና የብሉይ ትንቢትና ምሳሌ በሐዲስ ኪዳን መፈጸሙን ስለሚያሳይ ነው፡፡ ወንጌሉን የጻፈው በምድረ ይሁዳ ተቀምጦ እንደሆነ ይነገራል፡፡
ምዕራፍ አንድ
ይህ ምዕራፍ ቅዱስ ማቴዎስ የጌታችንን የልደት ሐረግ የዘረዘረበት ነው፡፡ ዓላማውም ያላመኑት አይሁድ የጌታችንን መሢሕነት አምነው የተቀበሉትን ጌታ ወልደ ዳዊት ወልደ አብርሃም መሆኑን ሰፍራችሁ ቆጥራችሁ አስረክቡን ስላሉአቸው ለእነርሱ ግልጽ ለማድረግ ነው፡፡ አይሁድ በትንቢት መሢህ ከዳዊትና ከአብርሃም ዘር እንደሚወለድ ያውቁ ነበርና፡፡
የዳዊት ልጅ የአብርሃም ልጅ ብሎ አብርሃምንና ዳዊትን ብቻ ማንሳቱ ከነገሥታት ዳዊት፣ ከአበው አብርሃም ብቻ ይወልዱታል ማለት ሳይሆን እነዚህ ሁለቱ ምክንያት ስላላቸ ነው፡፡
ለአብርሃምና ለዳዊት ብዙ ትንቢት ተነግሮላቸው ስለነበርና እንዲሁም ተስፋ ለተስፋ ሲያነጻጽር ነው “የምድር ወገኖች በዘርህ ይባረካሉ” ተብሎ ለአብርሃም ተስፋ ተሰጥቶታል፡፡ ለዳዊት ደግሞ “ከሆድህ ፍሬ በዙፋንህ ላይ አስቀምጣለሁ” መዝ.131፥11፡፡
አንድም ዳዊት ሥርወ መንግሥት ነው፡፡ አብርሃምም ሥርወ ሃይማኖት ነውና፡፡ እንዲሁም ከአይሁድ ወገን በክርስቶስ ያመኑትን ገና ያላመኑት የአብርሃም የዳዊት ዘር መሆኑን አስረዱን ስላሉአቸው ወንጌላዊውም ይህን ለማስረዳት የአብርሃምንና የዳዊትን ስም ለይቶ ጠራ፡፡
“አብርሃም ይስሐቅን ወለደ”
የአብርሃም ልጆች ብዙዎች ሆነው ሳለ ይስሐቅን ብቻ ለይቶ ለምን አነሣ?
ወንጌላዊው የተነሣበት ዋና ዓላማ የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ልደት ከነማን እንደሆነ ለማስረዳት ነው፡፡ የጌታ መወለድ ደግሞ ከይስሐቅ እንጂ ከአጋር ከተወለደው አስማኤል ወይም ከኬጡራ ከተወለዱት አይደለምና፡፡
“ይስሐቅም ያዕቆብን ወለደ” ያዕቆብና ኤሳው በአንድ ቀን ከአንድ እናት ተወልደው ሳለ ኤሳውን ለይቶ ለምን ተወው? ቢባል
ነቢይ የሆነ እንደሆነ ልደተ አበውን ጠንቅቆ ይቆጥራልና መላውን ዘር ያነሣል፡፡ ወንጌላዊ ግን የሚሻ የጌታን ልደት ነው፡፡ የጌታም መወለድ ከያዕቆብ ነው እንጂ ከኤሳው አይደለምና፡፡ ትንቢት የተነገረለት ምሳለ የተመሰለለት ለያዕቆብ ነው፡፡
-
ትንቢት፡- “ከያዕቆብ ኮከብ ይወጣል ከእስራኤል ኃጢአትን ያስወግዳል” ዘኁ.25፥17፡፡
-
ምሳሌ፡- ያዕቆብ ከወንድሙ ከኤሳው ተጣልቶ ወደ አጎቱ ወደ ላባ ሲሄድ ከምንጭ አጠገብ ደረሰ፡፡ ውኃው ድንጊያ ተገጥሞ በጎቹ ከምንጩ ዙሪያ ከበው ቆመው ኖሎት /እረኞች/ ተሰብስበው አገኘ፡፡ /ድንጊያውን አንስታችሁ በጎቹን አታጠጧቸውም? ብሎ እረኞቹን ቢጠይቃቸው፡፡ መላው ኖሎት ካልተሰበሰቡ ከፍቶ ማጠጣት አይሆንልንም አሉት፡፡ ውኃው ኩሬ ነው ጠላት ጥቂት ራሱን ሆኖ መጥቶ መርዝ እንዳይበጠብጥበት ለሃምሳ ለስድሳ የሚከፈት ድንጊያ ገጥመው ይሄዳሉ፡፡ ያዕቆብም ራሔል ስትመጣ ባየ ጊዜ ብቻውን ለስድሳ የሚነሳውን ድንጊያ አንሥቶ ውኃ ተጠምተው በጉድጓዱ ዙሪያ ተመስገው ለነበሩት በጎች አጠጥቷቸዋል፡፡ ዘፍ.2፥1-12፡፡ ይህም መሳሌ ነው፡፡
-
ያዕቆብ የጌታችንና የመድኀኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ፣
-
ደንጊያው የመርገመ ሥጋ የመርገመ ነፍስ፣
-
ውኃው የሕይወት የድኅነት፣ የጥምቀት፣
-
በጎች የምዕመናን፣
-
እረኞች የነቢያት የብሉይ ኪዳን ካህናት፣
-
ራሔል የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም ምሳሌ ናቸው፡፡ በሰው ልጅ ሕይወት ላይ ተጭኖ ይኖር የነበረውን መርገም አንሥቶ ለዘላለም ሕይወትን የሰጠ ከድንግል ማርያም በሥጋ የተወለደው ጌታ ነውና፡፡
-
“ያዕቆብም ይሁዳንና ወንድሞቹን ወለደ”
-
የይስሐቅን ልደት በተናገረ ጊዜ ሌሎች የአብርሃም ልጆችን አላነሣም፡፡ የያዕቆብንም ልደት ሲናገር መንትያውን ኤሳውን አላነሣም አሁን ግን “ይሁዳንና ወንድሞቹን” በማለት ወንድሞቹን ጭምር ለምን አነሣ? ቢሉ
-
ጌታችን የተወለደው ከአሥራ ሁለቱ ነገደ እስራኤል መሆኑን ለማስገንዘብ፡፡ የሁሉም አባታቸው ያዕቆብ ነውና፡፡
-
ይሁዳን ብቻ አንሥቶ ቢተው ሌሎቹ አባቶቻችንን ከቁጥር ለያቸው ነቢያት ቢሆኑ ባልለዩ ነበር እንዳይሉት መልእክቱ ለሁሉም ነገድ ነው የሚጻፈው፡፡
-
እንዲሁም ለምሳሌ እንዲመቸው ብሎ ነው ከአሥራ ሁለቱ ነገደ እስራኤል ያልተወለደ ምድረ ርስትን አይወርስም፡፡ የአሥራ ሁለቱ ሐዋርያትንም ትምህርት ያልተቀበለ ሁሉ መንግሥተ እግዚአብሔርን አይወርስምና፡፡
-
“ይሁዳም ከትዕማር ፋሬስንና ዛራን ወለደ”
የይስሐቅን ልደት በተናገረ ጊዜ እናቱ ሣራን፣ የያዕቆብን ልደት በተናገረ ጊዜም ርብቃን የይሁዳንና የወንድሞቹን ልደት በተናገረ ጊዜ እነ ልያን እነ ራሔልን አላነሣም አሁን ደርሶ የትዕማርን ስም ለምን አነሣ?
ትዕማር የተነሣችበት ለየት ያለ ምክንያት ስላላት ነው፡፡ ይሁዳ የሴዋን ሴት ልጅ አግብቶ ኤርን፣ አውናንን፣ ሴሎምን ይወልዳል፡፡ ለበኽር ልጁ ለኤር ከአሕዛብ ወገን የምትሆን ትዕማር የምትባል ብላቴና አምጥቶ አጋባው፡፡ ኤርም በእግዚአብሔር ፊት ክፉ ነበርና እግዚአብሔርም ቀሠፈው፡፡ ይሁዳም ከበኲር ልጁ ሞት በኋላ ሁለተኛ ልጁ አውናንን “ወደ ወንድምህ ሚስት ግባ አግባትም ለወንድምህም ዘርን አቁምለት አለው፡፡ አውናንም ዘሩ ለእርሱ እንዳይሆን ዐወቀ ወደ ወንድሙ ሚስት በገባ ጊዜ ለወንድሙ ዘር እንዳይሰጥ ዘሩን በምድር ያፈስሰው ነበር፡፡ ይህም ሥራው በእግዚአብሔር ዘንድ ክፉ ነበር እርሱንም ደግሞ ቀሰፈው፡፡
ይሁዳም ምራቱን ትዕማርን “ልጄ ሴሎም እስኪያድግ ድረስ በአባትሽ ቤት መበለት ሆነሽ ተቀመጪ አላት እርሱ ደግሞ እንደ ወንድሞቹ እንዳይሞት ፈርቶ፡፡ ትዕማርም ሄዳ በአባትዋ ቤት ተቀመጠች፡፡
ከብዙ ጊዜ በኋላ የይሁዳ ሚስት ሞተች ይሁዳም ተጽናና የበጎቹን ጠጉር ወደሚሸልቱት ሰዎችም ወደ ተምና ወጣ፡፡ ሴሎም እንደ አደገ ይሁዳም ያላት ነገር እንዳልተፈጸመላት ባየች ጊዜ እንዳታለለኝ ላታልለው ብላ ልብሰ ዘማ ለብሳ ጃንጥላ አስጥላ ድንኳን አስተክላ ከተመሳቀለ መንገድ ቆየችው፡፡ ምራቱ እንደ ሆነች አላወቀም ነበርና ወደ እርሷ ሊገባ ወደደ፡፡ እርስዋም፡- ወደ እኔ ብትገባ ምን ትሰጠኛለህ አለችው የፍየል ጠቦት ከመንጋዬ እሰድድልሻለሁ አላት እርስዋም እስክትሰድድልኝ ድረስ መያዣ ትሰጠኛለህ አለችው እርሱም ምን መያዣ ልስጥሽ አላት፡፡ እርስዋም ቀለበትህን፣ አምባርህን በእጅህ ያለውን በትር አለች፡፡ እርሱም ሰጣትና ከእርስዋ ደረሰ እርስዋም ፀነሰችለት፡፡
ይሁዳም መያዣውን ከሴቱቱ ይቀበል ዘንድ በወዳጁ በዓዶሎማዊው እጅ ፍየሉን ጠቦት ላከላት እርስዋንም አላገኛትም፡፡ እርሱም የአገሩን ሰዎች በኤናይም በመንገድ ዳር ተቀምጣ የነበረች ጋለሞታ ወዴት ናት? ብሎ ጠየቃቸው፡፡ እነርሱም፡- በዚህ ጋለሞታ አልነበረችም አሉት፡፡
ከሦስት ወር በኋላ ለይሁዳ ምራትህ ትዕማር ሴሰነች በዚህም የተነሣ ፀነሰች ብለው ነገሩት ይሁዳም፡- አውጡአትና በእሳት ትቃጠል አለ፡፡ እርስዋም ባወጡአት ጊዜ ወደ አማትዋ እንዲህ ብላ ላከች፡- ለዚህ ለባለ ገንዘብ ነው የፀነስሁት ተመልከት ይህ ቀለበት፣ ይህ ባርኔጣ /መጠምጠሚያ/ ይህ በትር የማን ነው? ይሁዳም ዐወቀ፡- ከእኔ ይልቅ እርስዋ እውነተኛ ሆነች ልጄን ሴሎምን አልሰጠኋትምና አለ፡፡ ዘፍ.38፥1-30፡፡
የፀነሰችውም መንታ መሆኑን ዐውቃ ነበርና በምትወልድበት ጊዜ አዋላጂቱን አስቀድሞ የተወለደውን በኲሩን እንድናውቀው ቀይ ሐር እሠሪበት አለቻት፡፡ አስቀድሞ ዛራ እጁን ሰደደ አዋላጂቱም ቀይ ፈትል ወስዳ በእጁ አሰረች፡፡ ፋሬስ እሱን ወደ ኋላ ስቦ ተወለደ ፋሬስ ማለት ጣሽ ማለት ነው፡፡ እንዲሁም ያየነው ቀርቶ ያላየነው ወጣ ማለት ነው፡፡ ዛራ /ዘሐራ/ መልከ መልካም ማለት ነው፡፡ ይህ ሁሉ ምሳሌ ነው፡፡
- ምንጭ፡- ስምዐ ጽድቅ ጋዜጣ 3ኛ ዓመት ቁጥር 1 ታኅሥሥ 1988 ዓ.ም.
ይቀጥላል