002 olonkomi

የሐዊረ ሕይወት መርሐ ግብር ቅድመ ዝግጅት በኦሎንኮሚ ደብረ ብስራት ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን

â€Â¢ መርሐ ግብሩ በማኅበሩ ድረ ገጽ ከጠዋቱ 3:00 ሰዓት ጀምሮ በቀጥታ ይተላለፋል፡፡

መጋቢት 11 ቀን 2007 ዓ.ም.

በእንዳለ ደምስስ

002 olonkomiማኅበረ ቅዱሳን መጋቢት 13 ቀን 2007 ዓ.ም. በምዕራብ ሸዋ ሀገረ ስብከት በደንዲ ወረዳ ቤተ ክህነት ኦሎንኮሚ ደብረ ብስራት ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን የሚካሔደው የሐዊረ ሕይወት መርሐ ግብር ቅድመ ዝግጅት በመጠናቀቅ ላይ ነው፡፡

አዘጋጅ ኮሚቴው ከቤተ ክርስቲያኑ ሰበካ ጉባኤና ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅንጅት በመሥራት መርሐ ግብሩን የተሳካ ለማድረግ በእንቅስቃሴ ላይ ይገኛል፡፡ ኮሚቴው ወደ ስፍራው በመጓዝም ክንውኑን ገምግሟል፡፡

 

የድንኳን ተከላው እየተፋጠነ ሲሆን፤ ጊዜያዊ የመጸዳጃ ቤቶች ዝግጅት ሙሉ ለሙሉ መጠናቀቁን አረጋግጧል፡፡ የተግባር ቤት፤ የመኪና ማቆሚያ፤ የምግብ መስተንግዶ ስፍራዎች ተለይተዋል፡፡ በምእመናን አቀባበል ሁኔታም ዝግጅቶችን በማድረግ ላይ ይገኛል፡፡

የማኅበሩ ኤሌክትሮኒክስ ሚዲያ ክፍል በማኅበሩ ድረ ገጽ ላይ የቀጥታ ሥርጭት ለማድረግ ባለሙያዎችን ስፍራው ድረስ በመላክ ማስተላለፍ እንደሚችል ሙከራ አድረጎ ተመልሷል፡፡ በዚህም መሠረት በእለቱ ከጠዋቱ 3:00 ሰዓት ጀምሮ መርሐ ግብሩን በቀጥታ ያስተላልፋል፡፡

001 olonkomiየኦሎንኮሚ ደብረ ብስራት ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን በ1907 ዓ.ም. የተተከለ ሲሆን፤ 100ኛ ዓመቱን ጥር 16 እና 17 ቀን 2007 ዓ.ም. በድምቀት አክብሯል፡፡ ታቦቱም በ1906 ዓ.ም. ከወሎ ክፍለ ሀገር ወረኢሉ እንደመጣ፤ አሁን ባለበት ቦታ ላይ ከመተከሉ በፊት በኤጄርሳ ለፎ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን ለአንድ ኣመት በደባልነት ቆይቷል፡፡ ቤተ ክርስቲያኑ የተተከለው በከፍታ ቦታ ላይ በመሆኑ ቀድሞ የአካባቢው ልጆች በየዓመቱ የደብረ ታቦርን በዓል ያከብሩበት ነበር፡፡ ቦታውም “የልጆች ተራራ” እየተባለ ሲጠራ ቆይቷል፡፡

በአሰቦት ገዳም ደን ተቀስቅሶ የነበረው እሳት ሙሉ ለሙሉ ጠፍቷል

መጋቢት 11 ቀን 2007 ዓ.ም.

በእንዳለ ደምስስ

በአሰቦት ገዳም ደን ላይ ተቀስቅሶ የነበረው እሳት ሙሉ ሙሉ መጥፋቱን ከገዳሙ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

ማኅበረ መነኮሳቱ፤ የፌደራል ፖሊስ አባላት እና ምእመናን ባደረጉት ከፍተኛ ጥረት በአሁኑ ስዓት ሙሉ ለሙሉ ለማጥፋት በመቻሉ በገዳሙ ውስጥ ማኅበረ መነኮሳቱ የተለመደውን አገልግሎታቸውን ቀጥለዋል፡፡ 

beg madleb 02

የመምህር አካለ ወልድ የሐዲስ ኪዳን የመጻሕፍት ትርጓሜ ት/ቤት የበግ ማድለብ ፕሮጀክት ተግባራዊ ሊደረግ ነው

መጋቢት 9 ቀን 2007 ዓ.ም

ከደሴ ማእከል

beg madleb 02የደቡብ ወሎ ሀገረ ስብከት ከ20 በላይ የወረዳ ቤተ ክህነት ሲኖሩት፤ እነዚህም ብዛት ያላቸው ጥንታውያን ገዳማትና አድባራትን እንዲሁም የአብነት ት/ቤቶችን አቅፎ የያዘ ነው፡፡ ሀገረ ስብከቱ ካሉት ጥንታውያን የአብነት ት/ቤቶች የቦሩ ሥላሴ የመምህር አካለ ወልድ የሐዲስ ኪዳን የመጻሕፍት ትርጓሜ ት/ቤት አንዱ ነው፡፡

ት/ቤቱ በደቡብ ወሎ ሀገረ ስብከት በደሴ ወረዳ ቤተ ክህነት ቦሩ በሚባል ቀበሌ በቦሩ ደብረ ብርሃን ቅድስት ሥላሴ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ የሚገኝ ሲሆን፤ ከደሴ የ10 ኪ.ሜ መንገድ ነው፡፡ ይህ ትምህርት ቤት በ18ኛው መቶ ክፍለ ዘመን መጨረሻ የቀለም ቀንድ ተብለው በሚጠሩት በዐራት ዓይናው በመ/ር አካለ ወልድ የተቋቋመ ለሀገርና ለቤተ ክርስቲያን የጠቀሙ ሊቃውንትን ሲያፈራ የነበረ ነው፡፡

በአሁኑ ወቅት 16 የሚደርሱ የሐዲሳት ትርጓሜ መጻሕፍት ተማሪዎችን ተቀብሎ በሀገረ ስብከቱ፣ በማኅበረ ቅዱሳን ዋናው ማእከል እና በጎ አድራጊ ምእመናን ድጋፍ እየተደረገላቸው እያስተማረ ይገኛል፡፡ ት/ቤቱ በአቅም ማነስና ተያያዥ ችግሮች ምክንያት ለብዙ ዓመታት ተዘግቶ የነበረ ሲሆን፤ ለቤተ ክርስቲያን አገልግሎት ቀናኢ በሆኑት በብፁዕ አቡነ አትናቴዎስ የደቡብ ወሎ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ከፍተኛ ጥረት ካለፉት 9 ዓመታት ወዲህ እንደገና ተከፍቶ ለቤተ ክርስቲያን አገልግሎት መፋጠን የሚያግዙ ተተኪ አገልጋዮችን እያፈራ ይገኛል፡፡

beg madlebት/ቤቱ ቀድሞ ለብዙ ዓመታት እንዲዘጋ ያደረገውና አሁንም አገልግሎቱን እየተፈታተነው ያለውን መሠረታዊ የኢኮኖሚ ችግር ቀርፎ የተማሪዎችን ቁጥር እና የጉባኤያቱን ዓይነት በመጨመር ለቤተ ክርስቲያን ተተኪ አገልጋዮችን በማፍራት ሐዋርያዊ አገልግሎትን ለማጠናከር ይቻል ዘንድ በማኅበረ ቅዱሳን የደሴ ማእከል የቅዱሳት መካናት ማኅበራዊ አገልግሎትና ልማት ክፍል ከበጎ አድራጊዎች በተገኘ ድጋፍ የበግ ማድለብ ፕሮጀክት ቀርጾ ከደቡብ ወሎ ሀገረ ስብከት ጋር የፕሮጀክት ማስፈጸሚያ የውል ሰነድ መጋቢት 3 ቀን 2007 ዓ.ም ተፈራርሟል፡፡

በእለቱ የሀገረ ስብከቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ መምህር ቆሞስ አባ ገብረ ሥላሴ በላይ እና የሀገረ ስብከቱ ሰራተኞች የተገኙ ሲሆን፤ ገንቢና ስጋት ሊሆኑ የሚችሉ ሀሳቦች ተነስተው ውይይት ከተደረገባቸው በኋላ ከሀገረ ስብከት፣ ከማኅበረ ቅዱሳን ደሴ ማእከል፣ ከት/ቤቱ፣ ከደብሩ ሰበካ ጉባኤና ከምእመናን የተውጣጡ ስድስት አባላት ያሉት ኮሚቴ ተቋቋሟል፡፡

በአሁኑ ወቅት የመገልገያ ቁሳቁሶች ተገዝተው የበጎች ማድለቢያና ማቆያ ቤት መሠራቱን የደሴ ማእከል ጸሐፊ ዲ/ን ሰለሞን ወልዴ በውይይቱ ወቅት ገልጸዋል፡፡

እንደ ጸሐፊው ገለጻ የፕሮጀክቱ ሙሉ ሥራ በሁለት ዙር የሚጠናቀቅ ሲሆን የመጀመሪያውን ዙር ቀሪ ሥራዎች በአጭር ቀናት ውስጥ በማጠናቀቅ የበግ ማድለቡ ሥራ እንዲጀመር ርብርብ እየተደረገ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡የፕሮጀክቱን የመጀመሪያ ዙር ሥራ አጠናቆ አገልግሎት ለማስጀመርም ብር 135,993 /አንድ መቶ ሰላሳ አምስት ሺህ ዘጠኝ መቶ ዘጠና ሶስት/ ብር እንደሚያስፈልግ ለማወቅ ተችሏል፡፡

abune gm 003

በዝቋላ ገዳም የተቀሰቀሰው እሳት ለማዳፈን ጥረት እየተደረገ ነው

የካቲት 26 ቀን 2007 ዓ.ም.

በእንዳለ ደምስስ

abune gm 003ከማክሰኞ የካቲት 24 ቀን 2007 ዓ.ም. ጀምሮ በዝቋላ ደብረ ከዋክብት አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ገዳም የተቀሰቀሰው እሳት በትናንትናው እለት ተባብሶ የነበረ ቢሆንም ወደ ሌላ ቦታ ሳይዛመት ከሸለቆው ውስጥ ለማዳፈን ጥረት የተደረገ መሆኑን የገዳሙ አበምኔት አባ ገብረ ማርያም ዛሬ ጠዋት በስልክ ገልጸዋል፡፡

በሸለቆው ውስጥ የተዛመተው እሳት ማኅበረ መነኮሳቱ፤ ምእመናንና የፖሊስ ኃይል ባደረጉት ርብርብ ከሸለቆው ሳይወጣ ለማቆም ተችሏል፡፡ ነገር ግን ከተዳፈነው እሳት ከፍተኛ ጭስ እየወጣ በመሆኑ እሳቱ እንዳይቀጣጠል ጥረት በማደረግ ላይ እንደሚገኙም አበምኔቱ ገልጸዋል፡፡

በገዳሙ ደን ላይ ለተከሰተው እሳት ቃጠሎ መንስኤ ከሰል በማክሰል ላይ በነበረ አንድ ግለሰብ እንደሆነ ከገዳሙ ያገኘነው መረጃ አመልክቷል፡፡

ግለሰቡ በድብቅ ከሰል በማክሰል ላይ ሳለ እሳቱ ከቁጥጥሩ ውጪ በመሆኑ ሲገለገልበት የነበረውን አካፋና ሹራብ ጥሎ እንደተሰወረ ለማረጋገጥ ተችሏል፡፡

የካቲት 25 ቀን 2007 ዓ.ም. የእሳቱን መንስኤ ለመጣራት በወንበር ቀበሌ ጽ/ቤት ከወረዳና ከዞን ከመጡ የፖሊስ ባለሥልጣናት ጋር በተደረገ ውይይት የግለሰቡ ማንነት ታውቋል ሲሉ በስብሰባው የተሳተፉ መነኮሳት ገልጸዋል፡፡ ፖሊስ ግለሰቡን ለመያዝ ክትትል እያደረገ ሲሆን፤ እሳቱ ዳግም እንዳይነሳም ጥረት እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል፤፤

 

ምኩራብ(የዐቢይ ጾም ሦስተኛ ሳምንት)

የካቲት 20 ቀን 2007 ዓ.ም.

የዕለተ ሰንበት መዝሙር (ከጾመ ድጓ)

ቦአ ኢየሱስ ምኩራበ አይሁድ ወመሐረ ቃለ ሃይማኖት ወይቤሎሙ ምጽዋተ አበድር እመሥዋዕት አነ ውእቱ እግዚኣ ለሰንበት ወአቡሃ ለምሕረት እግዚኣ ውእቱ ለሰንበት ወልደ እጓለ እመሕያው ኢትግበሩ ቤተ አቡየ ቤተ ምስያጥ ቤትየሰ ቤተ ጸሎት ይሰመይ ቦአ ምኩራቦሙ ወገሠፆሙ ያርምሙ አንከሩ ምህሮቶ ሞገስ ቃሉ ወጣዕመ ነገሩ ወሣዕሣዓ አፉሁ፡፡

 

ትርጉም:- ጌታችን ኢየሱስ ወደ አይሁድ ምኩራብ ገባ፤ የሃይማኖት ቃልን አስተማረ፤ ከመሥዋዕት ይልቅ ምሕረትን እወዳለሁ፤የሰንበት ጌታዋ የምሕረት አባቷም እኔ ነኝ፤ የሰው ልጅም የሰንበት ጌታዋ ነው ፡፡ያባቴን ቤት የንግድ ቦታ አታድርጉት፤ቤቴስ የጸሎት ቤት ይባላል (እያለ የሃይማኖትን ቃል አስተማራቸው፡)፡ ወደ ምኩራባቸውም ገብቶ ዝም ይሉ ዘንድ ገሠፃቸው፤ እነርሱም ትምህርቱን፣ የቃሉን ግርማ፣ የአነጋገሩን ጣዕምና፣ የአንደበቱን ቅልጥፍና አደነቁ።

 

ምንባባት

መልዕክታት

(ቆላ. 2÷16-ፍጻ.)፡- እንግዲህ በመብልም ቢሆን÷ በመጠጥም ቢሆን÷ በልዩ ልዩ በዓላትም ቢሆን÷ በመባቻም ቢሆን÷ በሰንበትም ቢሆን የሚነቅፋችሁ እንዳይኖር ተጠንቀቁ፡፡ ይህ ሁሉ ይመጣ ዘንድ ላለው ጥላ ነውና። አካሉ ግን የክርስቶስ ነው፡፡ በመታለልና ራስን ዝቅ በማድረግ ለመላእክት አምልኮ ትታዘዙ ዘንድ ወድዶ÷ በአላየውም በከንቱ የሥጋው ምክር እየተመካ የሚያሰንፋችሁ አይኑር፡፡ ሥጋ ሁሉ ጸንቶ በሚኖርበት÷ በሥርና በጅማትም በሚስማማበት÷ በእግዚአብሔርም በሚያድግበትና በሚጸናበት በሚሞላበትም በራስ አይጸናም፡፡

 

ከዚህ ዓለም ኑሮ ከክርሰቶስ ጋር ከሞታችሁ እንደገና በዓለም እንደሚኖሩ ሰዎች እንዴት ትሠራላችሁ? እንዴትስ ይህን አትዳስስ÷ ይህን አትንካ÷ ይህንም አትቅመስ ይሉአችኋል? ይህ ሁሉ እንደ ሰው ትእዛዝና ትምህርት ለጥፋት ነውና፡፡ ይህም ስለ ልብ ትሕትናና እግዚአብሔርንም ስለ መፍራት÷ ለሥጋም ስለ አለማዘን ጥበብን ይመስላል፤ ነገር ግን ከሥጋ በላይ ነው እንጂ ምንም ክብር የለውም፡፡

(ያዕ. 2÷14-ፍጻ.)፡- ወንድሞቻችን ሆይ÷ እምነት አለኝ፤ ምግባር ግን የለኝም የሚል ሰው ቢኖር÷ ምን ይጠቅመዋል? በውኑ እምነቱ ልታድነው ትችላለችን? ከወንድሞቻችን÷ ወይም ከእኅቶቻችን÷ የታረዙ ወይም የዕለት ምግብ ያጡ ቢኖሩ÷ ከእናንተም አንዱ÷ “በሰላም ሂዱ÷ እሳት ሙቁ÷ ትጠግባላችሁም” ቢላቸው÷ ለችግራቸውም የሚሹትን ባይሰጣቸው ምን ይጠቅማቸዋል? እንዲሁም ሥራ የሌለው እምነት ቢኖር በራሱ የሞተ ነው፡፡

 

ነገር ግን አንድ ሰው÷ “አንተ እምነት አለህ÷ እኔም መልካም ሥራ አለኝ፤ እስቲ ሃይማኖትህን ከሥራህ ለይተህ አሳየኝ፤ እኔም እምነቴን በሥራዬ አሳይሃለሁ” ይላል፡፡ አንተም እግዚአብሔር አንድ እንደ ሆነ ታምናለህ፤ መልካምም ታደርጋለህ፤ እንዲህስ አጋንንትም ያምናሉ፤ ይንቀጠቀጣሉም፡፡ አንተ ሰነፍ ሰው÷ እምነት ያለ ምግባር የሞተች እንደ ሆነች ልታውቅ ትወዳለህን? አባታችን አብርሃም ልጁን ይስሐቅን ወደ መሠዊያው ባቀረበው ጊዜ÷ በሥራው የጸደቀ አይደለምን? እምነት ለሥራ ትረዳው እንደ ነበር÷ በሥራውም እምነቱ እንደ መላችና ፍጽምት እንደ ሆነችም ታያለህን?

 

መጽሐፍ÷ “አብርሃም በእግዚአብሔር አመነ፤ ጽድቅ ሆኖም ተቈጠረለት” የሚለው ተፈጸመ፤ የእግዚአብሔርም ወዳጅ ተባለ፡፡ ሰው በሥራ እንደሚጸድቅ በእምነት ብቻም እንዳይደለ ታያለህን? እንዲሁ ዘማይቱ ረአብ ደግሞ ጒበኞችን ተቀብላ÷ በሌላ መንገድ ባወጣቻቸው ጊዜ በሥራ አልጸደቀችምን? ከነፍስ የተለየ ሥጋ የሞተ እንደ ሆነ÷ እንዲሁ ደግሞ ከሥራ የተለየ እምነት የሞተ ነው፡፡

 

ግብረ ሐዋርያት

(የሐዋ.10÷1-8)፡- በቂሳርያም ቆርኔሌዎስ የሚባል አንድ ሰው ነበር፤ ኢጣሊቄ ለሚሉት ጭፍራም የመቶ አለቃ ነበር፡፡ እርሱም ጻድቅና ከነቤተሰቡ እግዚአብሔርን የሚፈራ ነበር፤ ለሕዝቡም ብዙ ምጽዋት ይሰጥ ነበር፤ ዘወትርም ወደ እግዚአብሔር ይጸልይ ነበር፡፡ የእግዚአብሔር መልአክም በራእይ ከቀኑ በዘጠኝ ሰዓት በግልጥ ታየው፤ ወደ እርሱም ገብቶ÷ “ቆርኔሌዎስ ሆይ÷” አለው፡፡ ወደ እርሱም ተመልክቶ ፈራና÷ “አቤቱ÷ ምንድን ነው?” አለ፤ መልአኩም እንዲህ አለው÷ “ጸሎትህም ምጽዋትህም መልካም መታሰቢያ ሆኖ ወደ እግዚአብሔር ዐርጎአል፡፡ አሁንም ጴጥሮስ የሚባለውን ስምዖንን ይጠሩልህ ዘንድ ወደ ኢዮጴ ከተማ ሰዎችን ላክ፡፡ እርሱም ቤቱ በባሕር አጠገብ ባለው በቊርበት ፋቂው በስምዖን ቤት እንግድነት ተቀምጦአል፡፡ልታደርገው የሚገባህን እርሱ ይነግርሃል፡፡” ያነጋገረውም መልአክ ከሄደ በኋላ ከሎሌዎቹ ሁለት÷ ከማይለዩት ጭፍሮቹም አንድ ደግ ወታደር ጠራ፡፡

 

ምስባክ

መዝ.68፡9፡- እስመ ቅንዐተ ቤትከ በልዐኒ፤ ትዕይርቶሙ ለእለይትዔየሩከ ወድቀ ላዕሌየ፤ ወቀጻዕክዋ በጾም ለነፍስየ፡፡

ትርጉም፦ የቤትህ ቅንዓት በልታኛለችና የሚሰድቡህም ስድብ በላዬ ወድቆአልና ነፍሴን በጾም አስመረርኋት፡፡

 

ወንጌል

(ዮሐ. 2÷12-ፍጻ.)፡- ከዚህም በኋላ እርሱና እናቱ÷ ወንድሞቹና ደቀ መዛሙርቱም ወደ ቅፍርናሆም ወረዱ፤ በዚያም ብዙ ያይደለ ጥቂት ቀን ተቀመጡ፡፡ የአይሁድም የፋሲካቸው በዓል ቀርቦ ነበር፤ ጌታችን ኢየሱስም ወደ ኢየሩሳሌም ወጣ፡፡ በቤተ መቅደስም በሬዎችንና በጎችን÷ ርግቦችንም የሚሸጡትን÷ገንዘብ ለዋጮችንም ተቀምጠው አገኘ፡፡ የገመድም ጅራፍ አበጀ፤ በጎችንና በሬዎችን÷ ሁሉንም ከቤተ መቅደስ አስወጣ፤ የለዋጮችንም ገንዘብ በተነ፤ ገበታዎቻቸውንም ገለበጠ፡፡ ርግብ ሻጮችንም÷ “ይህን ከዚህ አውጡ፤ የአባቴን ቤት የንግድ ቤት አታድርጉ” አላቸው፡፡ ደቀ መዛሙርቱም÷ “የቤትህ ቅናት በላኝ” የሚል ቃል ተጽፎ እንዳለ ዐሰቡ፡፡

 

አይሁድም መልሰው÷ “ይህን የምታደርግ ምን ምልክት ታሳያለህ?” አሉት፡፡ ጌታችን ኢየሱስም÷ “ይህን ቤተ መቅደስ አፍርሱት፤ በሦስተኛውም ቀን አነሣዋለሁ” ብሎ መለሰላቸው፡፡ አይሁድም÷ “ይህ ቤተ መቅደስ በአርባ ስድስት ዓመት ተሠራ፤ አንተስ በሦስት ቀኖች ውስጥ ታነሣዋለህን?” አሉት፡፡ እርሱ ግን ይህን የተናገረው ቤተ መቅደስ ስለ ተባለ ሰውነቱ ነበር፡፡ ከሙታን በተነሣ ጊዜም ደቀ መዛሙርቱ ስለዚህ እንደ ነገራቸው ዐሰቡ፤ በመጻሕፍት ቃልና ጌታችን ኢየሱስ በነገራቸውም ነገር አመኑ፡፡

 

ጌታችን ኢየሱስም በፋሲካ በዓል በኢየሩሳለም ሳለ ብዙ ሰዎች ያደረገውን ተአምራት ባዩ ጊዜ በስሙ አመኑ፡፡ እርሱ ጌታችን ኢየሱስ ግን አያምናቸውም ነበር፤ ሁሉን እያንዳንዱን ያውቀዋልና፡፡ የሰውንም ግብሩን ሊነግሩት አይሻም፤ እርሱ በሰው ያለውን ያውቅ ነበርና፡፡

 

abune gm 003

በዝቋላ ገዳም የኢሬቻ በዓል እንደሚከበር በሚዲያ የተሰራጨው ዜና ማረሚያ እንዲሰጥበት ቅዱስ ፓትርያርኩ አሳሰቡ

የካቲት 14 ቀን 2007 ዓ.ም.

abune gm 003በዝቋላ ደብረ ከዋክብት አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ገዳም ላይ በመጋቢት ወር መጨረሻ የኢሬቻ በዓል እንደሚከበር መስከረም 15 ቀን 2007 ዓ.ም. በኢትዮጵያ ብሮድ ካስቲንግ ኮርፖሬሽን በኦሮምኛና በአማርኛ ቋንቋ መተላለፉ ተገቢ እንዳልሆነና ችግር ሊፈጥር የሚችል መሆኑን በመግለጽ የተላለፈው መረጃ እርማት እንዲደረግበት ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት ለኦሮምያ ክልላዊ መንግሥት ርዕሰ መስተዳድር ለክቡር አቶ ሙክታር ከድር በጻፉት ደብዳቤ ጠየቁ፡፡

abune gebre menfes kidus 004“የሃይማኖቶች እኩልነት በታወጀበት የኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ሕግ መንግሥት አንዱ ቤተ እምነት የሌላውን እምነት መንቀፍም ሆነ መንካት እንደሌለበት ተደንግጓል” ያሉት ቅዱስነታቸው፤ በሚዲያ ሽፋን የተሰጠው ጉዳይ ሕገ መንግሥቱን የሚተላለፍ፤ የገዳሙን መናንያን መነኮሳትና በአካባቢው የሚኖሩ ሕዝበ ክርስቲያኖችን የሚያስቆጣ በመሆኑ የክልሉ መንግሥት ለተዘገበው ጉዳይ እርማት እንዲሰጥበት ለኦሮምያ ክልላዊ መንግሥት ርዕሰ መስተዳደር ለክቡር አቶ ሙክታር ከድር በጻፉት ደብዳቤ አሳስበዋል፡፡

ዝርዝሩን ከሚመለከታቸው አካላት እንደደረሰን የምናቀርብ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

 

hawassa 1a

የሀዋሳ ቅዱስ ገብርኤል ገዳም ባለ 4 ፎቅ ሁለገብ ህንጻ እና የመጀመሪያ ደረጃ ት/ቤት አስመረቀ

 

የካቲት 09ቀን 2007ዓ.ም.

ዲ/ን ያለው ታምራት

hawassa 1aበሲዳማ፣ጌዲኦ.አማሮና ቡርጂ ሀገረ ሰብከት በሐዋሳ ወረዳ ቤተ ክህነት የሀዋሳ ቅዱስ ገብርኤል ገዳም አዲስ ያሰገነባውን ባለ 4 ፎቅ ሁለ ገብ ህንጻ እና ት/ቤት ብፁዕ አቡነ ገብርኤል ፣የክልሉ ከፍተኛ ባለ ሥልጣናት እና ምዕመናን በተገኙበት የካቲት 7 ቀን 2007 ዓ.ም በድምቀት አስመረቀ፡፡

 

ብፁዕ አቡነ ገብርኤል የምርቃ መርሐግብሩን በጸሎት ባርከው ከከፈቱ በኋላ ባስተላለፉት መልዕክት “ዛሬ በምንመርቃቸው የልማት ሥራዎች ለቤተ ክርስቲያን እና ለመንግስት ከፍተኛ ገቢ የሚያስገኙ ከመሆናቸው በተጨማሪ ከፍተኛ የሥራ ዕድል ይፈጥራሉ” ብለዋል፡፡ ብፁዕነታቸው አክለውም “ት/ቤቱ በሃይማኖት ሳይለይ የልዩ ልዩ ቤተ እምነት ተከታዮች ልጆች ተቀብሎ በሥነ ምግባር ታንጸው እንዲያድጉ በማድረግ ለሀገር የሚጠቅም ትውልድ አያፈራ ይገኛል” ብለዋል፡፡hawassa2b

 

የዕለቱ የክብር እንግዳ የደቡብ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድርና የንድግና ኢንደስትሪ ቢሮ ኃላፊ አቶ መለሰ አለሙ እንደገለጹት “የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ሰላምና ልማትን ከመገንባት አንጻር እያበረከተችው ያለችው አስተዋጽኦ ከፍተኛ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ የተገነባው ሁለ ገብ ህንጻ ለሀዋሳ ከተማ ተጨማሪ ውበት ሆኗል” ብለዋል፡፡

 

hawassa3a

የገዳሙ የልማት ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ተከስተ ብርሃን ሀጎስ በሪፖርታቸው እንደገለጹት “ይህ ከስድስት ዓመት በፊት ግንቦት 2001 ዓ.ም የመሰረት ድንጋይ ተጥሎ ዛሬ ለምረቃ የበቃው ሁለገብ ህንጻ 30 ሚሊዮን ብር ወጪ የሚገመት ሲሆን ከገዳሙ ካዝና ወጪ የተደረገው 8 ሚሊየን ብር ብቻ ነው፡፡ ቀረው ወጪ ግን በኮሚቴው አባላትና እና በከተማው በሚገኙ ባለ ሀብት የቤተ ክርስቲያን ልጆች የተሸፈነ እንደ ሆነ” ገልጸዋል፡፡ የኮሚቴው ሰብሳቢ ህንጻው የተሰራበትን ዓላማ ሲገልጹ “ይህን ህንጻ በማከራየት የሚገኘው ገቢ ለገጠር አብያተ ክርስቲያናት መርጃ እንዲሆን ታስቦ የተገነባ ነው” ብለዋል፡፡

 

በመጨረሻ በገዳሙ የተሠሩት የልማት ሥራዎች ሁለ ገብ ባለ 4 ፎቅ ህንጻ እና የመጀመሪያ ደረጃ ት/ቤት በተጋዛዥ እንግዶችና ምዕመናን ተጎብኝተዋል፡፡ ከጉብኝቱ በኋላ ያናገርናቸው ምዕመናን እንደገለጹልን የገጠር አብያተ ክርስቲያናን ከመዘጋት አደጋ ለመታደግ በከተማ የሚገኙ አድባራት እንደዚህ አይነት የልማት ሥራ መስራት አለባቸው ብለዋል፡፡

 

የማቴዎስ ወንጌል

የካቲት 2 ቀን 2007 ዓ.ም.

ምዕራፍ ዐሥራ አራት

በዚህ ምዕራፍ፡-
1. ስለ መጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ አሟሟት
2. ጌታችን አምስት ሺሕ ሰዎችን ስለመመገቡ
3. ጌታችን በባሕር ላይ ስለመራመዱ እንመለከታለን

1.የመጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ አሟሟት
እሥራኤል በአራት ክፍል ተከፍላ በምትዳደርበት ዘመን የአራተኛው ክፍል ገዥ ሆኖ እስከ 39 ዓ.ም. በገሊላ የገዛው ሄሮድስ አንቲጳስ ይባል ነበር፡፡ ይህ ሰው የወንድሙን የሄሮድስ ፊልጶስን ሚስት ሄሮድያዳን በማግባቱ፣ መጥምቀ መለኮት ዮሐንስ ሳይፈራና ሳያፍር ገሰጸው፡፡ ዘሌ.18፡16 በዚህም ምክንያት ዮሐንስን አሲዞ አሳሰረው፡፡ እንዳይገድለው ግን ሕዝቡን ፈራ፡፡

ሄሮድስ የልደቱ በዓል ባከበረበት ቀን የሄሮድያዳ ልጅ በዘፈኗ አስደሰተችው፡፡ ከደስታውም የተነሣ የምትለምነውን ሁሉ እንዲሰጣት ቃል ገባላት፡፡ እርስዋም በእናትዋ ተመክራ የመጥምቁን ዮሐንስን ራስ በዚህ በወጭት አድርገህ ስጠኝ አለችው፡፡ ለጊዜው በያዝንም ነገር ግን ስለ መሐላው አንድም በዙሪያው የተሰበሰቡ ሰዎች “ቃሉ ግልብጥብጥ ነው፤” ይሉኛል ብሎ ፈርቶ የጠየቀችውን ፈጸመላት፡፡ በወጭት መሆኑም ለጊዜው እስራኤል ደም ስለማጸየፉ ሲሆን፤ ለፍጻሜው ግን የከበረች የቅዱስ ዮሐንስ ራስ በዚህች በርኲሰት እጅ እንዳይያዝ እግዚአብሔር በጥበብ ያደረገው ነው፡፡

ሄሮድስን ኢየሱስ ክርስቶስ ስለ ጠባዩ ቀበሮ ብሎታል፡፡ ሉቃ.23፡6-12 ቀበሮ የተንኮለኛና የደካማ ሰው ምሳሌ ነው፡፡ መኃ.2፡15፣ ነህ.4፡3፡፡ ጲላጦስ ኢየሱስ ክርስቶስን ይዞ በላከበት ጊዜም በንቀት ዘብቶበታል፡፡ ሉቃ.23፡6-12፡፡

2.አምስት ሺህ ሰዎችን እንደ መገበ
ጌታችን የቅዱስ ዮሐንስን ሞት ሰምቶ ወደ በረሃ ፈቀቅ አለ፡፡ ሕዝቡም ሰምቶ ተከተለው፡፡ በመሸም ጊዜ ደቀመዛሙርቱ ሕዝቡን እንዲያሰናብት ጠየቁት፡፡ ይህም ለዚያ ሁሉ ሕዝብ የሚሆን ምግብ ስለሌለ የሚበሉትን እንዲገዙ ነበር፡፡ እርሱ ግን ለጊዜው የተገኘውን አምስት የገብስ እንጀራና ሁለት ዓሣ ባርኮ ሁሉንም እስኪጠግቡ ድረስ መገባቸው፡፡ ተርፎም አሥራ ሁለት መሶብ ተነሣ፡፡ የተመገቡትም ሕዝብ ሴቶችና ሕፃናት ሳይቆጠሩ አምስት ሺህ ወንዶች ነበሩ፡፡ ሴቶቹ ያልተቆጠሩበት ምክንያት በአደባባይ ሲበሉ በሃፍረት ዳር ዳር ስለሚሉ ነው፤ ሕፃናት ደግሞ ከሚበሉት የሚፈረፍሩት ስለሚበዛ ነው፡፡

ጌታችን ያን ሁሉ ሕዝብ በመንደር አጠገብ መመገብ ሲችል ርቆ ወደ ምድረ በዳ የወጣበት ምክንያት ነበረው፡፡ ይህም፡-

 

1ኛ “ጥንት አባቶቻችሁን ከመንደር አውጥቼ /ከግብፅ አውጥቼ/ አርባ ዘመን ሙሉ መና የመገብኋቸው እኔ ነኝ፡፡ አሁንም በሥልጣኔ፣ በተአምራቴ መገብኋችሁ፡፡” ሲላቸው ነው፡፡

 

2ኛ. ተአምራቱን ከመንደር አጠገብ አድርጐት ቢሆን ኖሮ “ፈጣን ፈጣን ደቀመዛሙርቱን በጐን ወደ መንደር እየላከ ያስመጣው ነው፤” ብለው በተጠራጠሩ ነበር፡፡ ስለሆነም ለጥርጥር ምክንያት እንዳይኖራቸው አድርጎ ተአምራቱን ገልጦላቸዋል፡፡ ከዚህም ሌላ በበረሃ ያውም በምሽት ሕዝቡን በውኃ አጠገብ በሣር ላይ አስቀምጧቸው መመገቡ “በፍጻሜው ዘመን በምቹ ሥፍራ በመንግሥተ ሰማያት መንፈሳዊ ምግብ እመግባችኋለሁ፡፡ በውኃ /በጥምቀት/ በሚገኝ ክብርም አከብራችኋለሁ፡፡” ሲላቸው ነው፡፡

 

በዚህ ታሪክ ውስጥ አምስቱ እንጀራ የአምስቱ አዕማደ ምሥጢር ምሳሌ ነው፡፡ እነኚህም፡- 

1ኛ. ምሥጢረ ሥላሴ
2ኛ. ምሥጢረ ሥጋዌ
3ኛ. ምሥጢረ ጥምቀት
4ኛ. ምሥጢረ ቁርባን
5ኛ. ምሥጢረ ትንሣኤ ሙታን ናቸው፡፡

ሁለቱ ዓሣ ደግሞ የፍቅረ እግዚአብሔርና የፍቅረ ቢጽ ምሳሌዎች ናቸው፡፡ ፍቅረ እግዚአብሔር ማለት እግዚአብሔር አምላክን በፍጹም ነፍስና በፍጹም ሐሳብ መውደድ ነው፡፡ ፍቅረ ቢጽ ደግሞ ባልንጀራን እንደራስ አድርጐ መውደድ ነው ዘዳ.6፡5፣ ማቴ.22፡37 በተጨማሪም እንጀራውና ዓሣው የሥጋውና የደሙ ምሳሌ ነው፡፡

3.በባሕር ላይ እንደተራመደ
ጌታችን በተአምራት ሕዝቡን መግቦ ካሰናበተ በኋላ ይጸልይ ዘንድ ብቻውን ወደ ተራራ ወጣ፡፡ እንዲህም ማድረጉ “ተአምራት ተደረገልን ብላችሁ ጸሎታችሁን አትተዉ” ለማለት ለአብነት ነው፡፡ ከሌሊቱም በአራተኛው ክፍል ዘባነ ባሕርን /የባሕርን ጀርባ/ እየተረገጠ በማዕበል ስትጨነቅ ወደ ነበረችው ወደ ደቀመዛሙርቱ ታንኳ መጣ፡፡ ደቀመዛሙርቱ ግን ምትሃት መስሏቸው ፈርተው ጮኹ ወዲያውም “አይዟችሁ እኔ ነኝ አትፍሩ፤” አላቸው፡፡

 

ስምዖን ጴጥሮስም “አንተ ከሆንክስ እዘዘኝና ወደ አንተ ልምጣ፤” አለው፡፡ ጌታም “ባሕሩን እየተረገጥክ ና” ብሎ አዘዘው፡፡ ስምዖን ጴጥሮስ ግን መጓዝ ከጀመረ በኋላ ነፋሱን አይቶ ፈራ፡፡ ሊሰጥምም በጀመረ ጊዜ “ጌታ ሆይ አድነኝ” ብሎ ጮኸ፤ ጌታም እጁን ዘርግቶ ያዘውና “አንተ እምነት የጎደለህ ለምን ተጠራጠርህ” አለው፡፡ “ከርሱ ጋር ሳለሁ ጥፋት አያገኘኝም ፣ አትልም ነበር” ሲለው ነው፡፡ በመርከብ ያሉትም “በእውነት የእግዚአብሔር ልጅ ነው፤” ብለው ሰገዱለት፤ ተሻግሮም በጌንሴሬጥ ብዙ ሕሙማንን ፈወሰ፡፡ ሕሙማኑም የተፈወሱት የልብሱን ጫፍ በእምነት በመዳሰሳቸው ነበር፡፡

በዚህ ታሪክ ከሌሊቱ በአራተኛው ክፍል መባሉ እሥራኤላውያንን ሰዓተ ሌሊቱን በአራት ክፍል ስለሚከፍሉት ነው፡፡ ይህም፡-
1ኛ. ከምሽቱ እስከ ሦስት ሰዓት
2ኛ ከሦስት ሰዓት እስከ ስድስት ሰዓት
3ኛ. ከስድስት ሰዓት እስከ ዘጠኝ ሰዓት
4ኛ. ከዘጠኝ ሰዓት እስከ ንጋት ነው፡፡ /በዚህ ክፍል ሌሉቱ እያለፈ ነው፣ እየነጋ ነው ይባላል፡፡/ ይህ ሰዓት ማዕበል ፈጽሞ የማይነሣበት ሰዓት ነው፡፡ ነገር ግን ተአምራቱን ለመግለጽ የፈለገ አምላክ ኢየሱስ ክርስቶስ ያለ ሰዓቱ ማዕበል እንዲነሣ አድርጓል፡፡ እንዲህ ባይሆን ኖሮ “ድሮም ማዕበል ይነሣል፣ ደግሞም ጸጥ ይላል፤ ምን አዲስ ነገር አለ” ባሉ ነበር፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ በአራተኛው ሰዓተ ሌሊት ወደ ባሕር መምጣቱ በአራተኛው ክፍለ ዘመን ወደ ዓለም የመምጣቱ ምሳሌ ነው፡፡

በአራት የተከፈሉት ዘመናትም፡-
1ኛ. ዘመነ አበው
2ኛ. ዘመነ መሣፍንት
3ኛ. ዘመነ ነገሥት
4ኛ. ዘመነ ካህናት ናቸው፡፡

የነፋሱ ኃይልም የጽኑ መከራ ምሳሌ ነው፡፡ ከዚህም ሌላ ባሕር የዓለም ምሳሌ ስትሆን ታንኳይቱ ደግሞ የቤተ ክርስቲያን ምሳሌ ናት፡፡ በመሆኑም ቤተ ክርስቲያን በየጊዜው የሚነሣባትን የመከራ ማዕበል ፀጥ የሚያደርግላት አምላክ አላት፡፡ ለዚህም ሳይታክቱ “እግዚኦ፣ እግዚኦ፣ እግዚኦ ማለት ያስፈልጋል፡፡

ምንጭ፡- ስምዐ ጽድቅ ጋዜጣ 5ኛ ዓመት ቁጥር 3 ታኅሣሥ 1990 ዓ.ም.

 

ሱባዔና ሥርዓቱ

መጋቢት 17 ቀን 2008 ዓ.ም

መ/ር ሳሙኤል ተስፋዬ

ሱባዔ ምንድን ነው?

ሱባዔ በሰዋስው ትርጉሙ ሰባት ማለት ነው፡፡ ሱባዔ በመንፈሳዊ አተረጓጎም አንድ ሰው ከዚህ ቀን እስከዚህ ቀን በጸሎት ከፈጣሪዬ እገናኛለሁ ብሎ የሚያቅደው መንፈሳዊ ዕቅድ ነው፡፡ ሰባት ቁጥር በእስራኤላውያን ዘንድ በሥራም በቃልም የሚገለጥ ፍጹም ቁጥር ነው፡፡ ለምሳሌ፡- ፈጣሬ ዓለማት እግዚአብሔር በሰባተኛው ቀን ሥነ ፍጥረትን ከመፍጠር ማረፉ፣ ለጸሎት የሚተጉ ምእመናን በቀን ለሰባት ጊዜ ማመስገናቸው የሰባት ቁጥርን ፍጹምነት ያመለክታል፡፡ ዘፍ.2፥2፤ መዝ.118፥64፡፡ ከዚህ አንጻር አንድ ሰው ለሰባት ቀናት ቢጾም አንድ ሱባዔ ጾመ ይባላል፡፡ ለዐሥራ አራት ቀን ቢጾም ሁለት ሱባዔ ጾመ እያለ እየጨመረ ይሄዳል፡፡

መቼ ተጀመረ?

ሱባዔ የተጀመረው ከውድቀት በኋላ በመጀመሪያው ሰው በአዳም ነው፡፡ ቅዱሳን መላእክት አዳምን ጸሎት መጸለይን እንዳስተማሩት የመጽሐፍ ቅዱስ ሊቃውንት ይናገራሉ፡፡ መላእክት ለአዳም ጊዜያትን አስተምረውት ነበር፡፡ ቅዳሴ ማርያም ትርጓሜ፡፡ አዳም ጥፋቱን አምኖ ከባሕር ውስጥ ሱባዔ በመግባቱና በመጸለዩ እግዚአብሔር በማይታበል ቃሉ ከአምስት ቀን ተኩል በኋላ ከልጅ ልጅህ ተወልጄ አድንኀለሁ ሲል ቃል ኪዳን ገብቶለታል /መጽሐፈ ቀሌምጦስ አንቀጽ አራት/፡፡

ሱባዔ ለምን?

የሰው ልጅ ኃጢአት በሚስማማው የሥጋ ሰውነቱ ዘወትር ፈጣሪውን ይበድላል፡፡ በፈጸመው በደል ኅሊናው ይወቅሰዋል፡፡ ይጸጸታል፡፡ በመጀመሪያ ደፍሮ በሠራው ኃጢአት በኋላ ይደነግጣል፡፡ ይህ በማንኛውም ሰብአዊ ፍጥረት ኅሊና ውስጥ የሚፈራረቅ ክስተት ነው፡፡ በዚህ ጊዜ የፈጣሪውን ይቅርታ ለማግኘት ያስባል፤ ይተክዛል፡፡ በውስጡ ሰውነቴ በእግዚአብሔር ሕግ ደስ ይለኛል. ነገር ግን በብልቶቼ ባለ በኃጢአት ሕግ የሚማርከኝ ሌላ ሕግ አያለሁ፡፡ እኔ ምንኛ ጐስቋላ ሰው ነኝ ለዚህ ሞት ከተሰጠ ሰውነት ማን ያድነኛል? እንዳለ ቅዱስ ጳውሎስ፡፡ ሮሜ.7.22-25፡፡

ሰው በደፋርነቱ የኃያሉን አምላክ ትእዛዝ ተላልፎ ትካዜ ሽክም ሲያስጨንቀው ሸክሙን የሚያቃልልበትና የሚያስወግድበት መንፈሳዊ ጥበብ ከቸሩ ፈጣሪ ተሰጥቶታል፡፡ ይኸውም በጥቂት ድካመ ሥጋ ያልተወሰነ ጸጋ እግዚአብሔር የሚያገኝበት ሥርዓት ሱባዔ ነው፡፡ ከጥንት እስከ ዛሬ አንድ ሰው በትካዜ ሽክም መንፈሱ ሲታወክ የነፍስና የሥጋ ጸጥታውን ለመመለስና ለማስከበር መጾምና መጸለይ ግድ ይሆንበታል፡፡ በዚህ ጊዜ አመክሮ /ሱባዔ/ ይገባል፡፡

እግዚአብሔርን ለመማፀን

ሰው ሱባዔ ከሚገባባቸው መሠረታዊ ጉዳዮች አንዱ እግዚአብሔርን ለመማፀን ነው፡፡ ማንኛውም ሰው ሱባዔ ሲገባ በቁርጥ ወደ ፈጣሪው የሚያቀርበው ተማኅፅኖ ሊኖረው ይገባል፡፡ ምንም የምንጠይቀው /የምንማፀነው/ ነገር ሳይኖር ሱባዔ ብንገባ የምናገኘው መልስ አይኖርም፡፡ ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታና ዝግጅት ሱባዔ የሚገቡ ሰዎች ከሱባዔ በኋላ ምን እንደ ተመለሰላቸው የሚያውቁት ነገር ስለማይኖር ሱባዔ በመግባታቸው የሚያገኙት ነገር የለም፡፡ 

ስለዚህ ሱባዔ ከመግባታችን በፊት፡- ሱባዔ የምገባው ለምንድን ነው? በማለት ራሳችንን መጠየቅ ይኖርብናል፡፡ ለምሳሌ አንድ ክርስቲያን በግል ሕይወቱ ዙሪያ ስለ ሀገር ሰላም፣ ስለ ጓደኛው ጤና ወዘተ ጉዳዮች ላይ ፈጣሪውን ይማፀናል፡፡ በዚህ ጊዜ በግል ሕይወቱም ሆነ በሀገር ጉዳይ ለገባው ሱባዔ ወዲያውኑ መልስ ሊያገኝ ይችላል፤ እንዲሁም መልሱ ሊዘገይ ይችላል፡፡ በዚህ ጊዜ ከተሐራሚው ትዕግሥት /መታገሥ/ ይጠበቅበታል፤ ለምን ላቀረብኩት ጥያቄ ቶሎ መልስ አልተሰጠኝ? በማለት ማማረርና እግዚአብሔርን መፈታተን ተገቢ አይደለም፡፡ እግዚአብሔር ሥራውን የሚሠራበትና ለሚማፀነውም መልስ የሚሰጥበት የራሱ ጊዜ አለው፡፡ ለምሳሌ በጓደኛው ውድቀት ምክንያት ሱባዔ ገብቶ በአንድ ሳምንት ውስጥ መልስ ያገኘ የአንድ ገዳም አገልጋይ ታሪክ መመልከት ተገቢ ነው፡፡

«አኃው ለተልእኮ በወጡበት አንዱን ድቀት አግኝቶት አድሯል፡፡ በነጋው ወንድሜ እኔ ድቀት አግኝቶኛልና እንግዲህ ወዲህ ተመልሼ ከዚያ ገዳም አልሔድም፤  አለው፡፡ እኔም እንጂ አግኝቶኛል፤ ይልቁንስ ሔደን ኃጢአታችንን ለመምህረ ንስሐችን ነግረን፤ ቀኖናችንን ተቀብለን እንደ ቀደመው ኾነን እንኖራለን ብሎ አጽናንቶ ይዞት ሔደ፡፡ ሔደው ለመምህረ ንስሐቸው ነግረው ቀኖናቸውን ተቀብለው 1 /አንድ/ ሱባዔ፣ ቀኖና እንዳደረሱ ሰረይኩ ለከ በእንተ ዘኢገብረ እኁከል፤ ኃጢአት ስላላደረገው ወንድምህ ይቅር ብዬሃለሁ የሚል ድምፅ አሰምቶታል፡፡ /ዜና አበው/፡፡

ከላይ ታሪካቸው የሰፈረው የገዳም አገልጋዮች ለአገልግሎት በተላኩበት አገር አንዱ ድቀት አግኝቶት በዝሙት ሲወድቅ ጓደኛው እንደ እርሱ ድቀት እንዳገኘው አድርጐ ጓደኛውን በማጽናናት ወደ ገዳም በመመለስ አንድነት ኾነው ሱባዔ ይገባሉ፡፡ አንድ ሱባዔ /ሰባት ቀን/ እንደ ጨረሱ ከእግዚአብሔር ዘንድ ኃጢአት ሳይሠራ ለአንተ ብሎ ሱባዔ ስለገባው ወንድምህ ስል ይቅር ብዬሃለሁ የሚል ፈጣን መልስ አግኝቷል፡፡ ስለዚህ ሱባዔ በግል ሕይወትም ሆነ በጓደኛችን ሕይወት ዙሪያ ስንገባ ፈጣን ወይም የዘገየ መልስ ሊሰጠን ስለሚችል በትዕግሥት መጠባበቅ ይኖርብናል፡፡

የቅዱሳንን በረከት ለመሳተፍ

ቅዱሳን አባቶችና ቅዱሳት እናቶች የተጋደሉትን ተጋድሎ በማዘከር ቃል ኪዳን በተሰጣቸው ገዳማትና አድባራት የሚገባ ሱባዔ የቅዱሳኑን በረከት ተካፋይ ያደርጋል፡፡ ቅዱሳን በሚጋደሉበት ቦታ ከወንዶችና ከሴቶች ልጆች ይልቅ የሚበልጥ ስም እሰጣቸዋለሁ፤ የማይጠፋ የዘላለም ስም እሰጣቸዋለሁ /ኢሳ.56.6/ በማለት እግዚአብሔር ቃል ኪዳን ስለ ገባላቸው ሱባዔ በመግባት በረከታቸውን መሳተፍ ይቻላል፡፡ በጾመ ነቢያት የነቢያትን በረከት ለመሳተፍ፣ በጾመ ሐዋርያት የሐዋርያትን በረከት ለመሳተፍ፣ በጾመ ፍልሰታ የእመቤታችንን በረከት ለመሳተፍ ሱባዔ መግባት የነበረና ወደ ፊትም የሚኖር የቤተ ክርስቲያን ሥርዓት ነው፡፡ ዛሬ ይህን ሥርዓት በመከተል የተለያዩ ቅዱሳንን በረከት ለመቀበል /ለመሳተፍ/ የቅዱሳን አፅም ካረፈበት ገዳም በጾም፣ በጸሎት፣ በጉልበትም ገዳማትን በማገልገል የቅዱሳንን በረከት ደጅ የሚጠኑ ምእመናንና መናንያን በየገዳማቱ እጅግ በርካታ ናቸው፡፡

ይኸውም በመጽሐፈ ነገሥት ካልዕ በምዕራፍ 2.9 እንደ ተመለከተው ነቢዩ ኤልሳዕ መምህሩን ኤልያስን በማገልገል የኤልያስ በረከት በእጥፉ በኤልሳዕ ላይ አድሮበታል፡፡ ይህን አብነት በማድረግ በየገዳማቱ በትሕርምት የሚኖር መናንያንን ያገለገሉበትን ገዳም አባት በረከት በእጥፍ እየተቀበሉ ለሌሎችም የሚያቀብሉ አባቶች በየገዳማቱ አሉ፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ ሆኖ በስመ ገዳማዊ የምእመናንን ገንዘብ የሚዘርፉና የእውነተኛ መነኮሳትንና መናንያንን የተቀደሰ ሕይወት የሚያጐድፉ መኖራቸውን መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡

የተሰወረ ምሥጢር እንዲገለጥልን

በዘመነ ብሉይ እግዚአብሔር ለአንዳንድ ነገሥታት ራእይ በማሳየት ምሥጢርን ይሰውርባቸው ነበር፡፡ ለምሳሌ የግብፁን ፈርዖን፣ የባቢሎኑን ናቡከደነፆርንና ብልጣሶርን መጥቀስ ይቻላል፡፡ ዘፍ.41.14-36፡፡ ዳን.4.9፤ ዳን.5.4፡፡ እነዚህ ነገሥታት በግል ሕይወታቸውም ሆነ በመላው ሽክም ወደ ፊት ሊፈጸም የሚችል ራእይ ቢያዩም ቅሉ ራእዩን በትክክል ተረድተው እንዲህ ይሆናል የማለት ብቃት አልነበራቸውም፡፡ ስለዚህ በዘመናቸው ይኖር የነበሩትን ነቢያት ሱባዔ ገብተው የሕልማቸውን ትርጉም እንዲነግሩአቸው ይማፀኑ ነበር፡፡ ነቢያትም ሱባዔ በመግባት ነገሥታቱ ያዩትን የምሥጢረ ሥጋዌ ነገርና የመንግሥታቸውን አወዳዳቅ ገልጸው ይናገሩ ነበር፡፡ ዳን.5.28፡፡

እንዲሁም ቅዱሳን በየራሳቸው ያዩት ራእይ ምሥጢር ሲከደንባቸው የራእዩ ምሥጢርና ትርጉም እንዲገለጥላቸው ሱባዔ ይገባሉ፡፡ እግዚአብሔርም በንጽሕና ሆነው የገቡትን ሱባዔ ተመልክቶ ምሥጢር ይገልጥላቸዋል፡፡ ለምሳሌ ነቢዩ ዕዝራ የመጻሕፍትን ምሥጢር እንዲገልጥለት ሱባዔ ቢገባ የጠፉትን የብሉይ ኪዳን መጻሕፍት ዳግም መልሶ ለመጻፍ ችሏል፡፡ መዝ.8.1፡፡

በዘመነ ሐዲስ በሰፊው የሚወሳው ቅዱሳን ሐዋርያት ከነሐሴ 1-14 የገቡት ሱባዔ ነው፡፡ ይህ ሱባዔ ተሰውሮ የነበረውን የቅድስት ድንግል ማርያምን ትንሣኤ ተረድተው በረከቷን ለመሳተፍ አብቅቷቸዋል፡፡

እመቤታችን ያረፈችው ጥር 21 ቀን 50 ዓመተ ምሕረት ነው፡፡ ሐዋርያት ሊቀብሯት ወደ ጌቴ ሰማኔ ይዘዋት ሲሄዱ አይሁድ በታተኗቸው፡፡ በዚህ ጊዜ ቅዱሳን መላእክት የእመቤታችንን ሥጋዋን ወስደው በገነት ከዕፀ ሕይወት ሥር አኑረውታል፡፡/ተኣምረ ማርያም፤ ስንክሳር ነሐሴ 16 ቀን/፡፡ በዚህ ጊዜ እነርሱ ተደናግጠው ስለተበታተኑ የእመቤታችን የዕረፍቷ ያስጨንቃቸው ነበር፡፡
ቅዱስ ዮሐንስ በተመስጦ እየሄደ ሥጋዋን ያጥን ነበር፡፡ ለሐዋርያት ይህን ይነግራቸዋል፡፡ ለዮሐንስ ተገልጣ ለእኛ ሳትገለጥ ብለው በነሐሴ ሱባዔ ገቡ፡፡ ሁለተኛው ሱባዔ ሲፈጸም በ14ኛው ቀን መልአክ ሥጋዋን አምጥቶ ሰጥቶአቸዋል፤ ቀብረዋታል፡፡ በሦስተኛው ቀን ነሐሴ 16 ቀን ተነሥታ ዐርጋለች፡፡ /ተኣምረ ማርያም፤ ስንክሳር ነሐሴ 16 ቀን/፡፡

እንግዲህ ለቅዱሳን ሐዋርያት የእመቤታችን የዕረፍትና የዕርገት ምሥጢር የተገለጠላቸው በሱባዔ ነው፡፡ ይህን መሠረት በማድረግ ሐዋርያዊት ቤተ ክርስቲያን የእመቤታችንን የዕርገቷን በረከት ለማግኘት ትጾማለች፡፡ በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ይህን የሱባዔ ወቅት ሕፃናትም ሳይቀሩ ይሳተፉታል፡፡

ሱባዔ ነቢያት

እግዚአብሔር ለአዳም የገባውን ቃል ኪዳን መሠረት በማድረግ ቀደምት ነቢያት በተነሡበት ዘመን ቅደም ተከተል ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ሰው መሆንና ዳግም መምጣት ትንቢት ተናግረዋል፡፡ ሱባዔም ቆጥረዋል፡፡ ኢሳ.7.14፡፡ መዝ.49.3፡፡ ዘካ.13.6፤ ዘካ.14.1፡፡ የአንዱ ነቢይ ትንቢታዊ ንግግርና ሱባኤ በአነጋገርና በአቆጣጠር ከሌላኛው ነቢይ ጋር ይለያያል፡፡ ምክንያቱም እግዚአብሔር ትንቢቱን ሲያናግር ምሳሌውን ሲያስመስል ጐዳናው ለየቅል በመሆኑ ነው፡፡ ከጥንት ጀምሮ እግዚአብሔር በብዙ ዓይነትና በብዙ ጐዳና ለአባቶቻችን በነቢያት ተናገረ፡፡ እንዲል፡፡ ዕብ.1.1፡፡ የአቆጣጠር ስልታ ቸውና የሱባዔ መንገዳቸው ቢለያይም ዓላማና ግባቸው ግን አንድ ነው፡፡

ሱባዔ አዳም

አዳም ትንቢት በመናገርና ሱባዔ በመቁጠር የመጀመሪያውን ሥፍራ ይይዛል፡፡ ምክንያቱም በገነት ሰባት ዓመት ከአንድ ወር ከዐሥራ ሰባት ቀን በተድላና በደስታ ከኖረ በኋላ ሕግ በማፍረሱና የፈጣሪውን ቃል በመጣሱ ያለምንም ትካዜና ጉስቁልና ከሚኖርበት ዔደን ገነት ተባርሯል፡፡ ዘፍ.3.24፡፡ እርሱም ፈጣሪው እንዲታረቀው፣ በዐይነ ምሕረት እንዲጐበኘው፣ ቅዝቃዜው ሰውነት ከሚቆራርጥ ባሕር ውስጥ በመቆም ለሠላሳ አምስት ቀን /አምስት ሱባዔ/ ሱባዔ ገብቷል፡፡ በባሕርዩ የሰውን ልጅ እንግልት የማይወድ ቸሩ ፈጣሪ የአዳምን ፈጽሞ መጸጸት ተመልክቶ በኀሙስ ዕለት ወበመንፈቃ ለዕለት እትወለድ እምወለተ ወለትከ ወእድኅክ ውስተ መርህብከ ወእቤዝወከ በመስቀልየ ወበሞትየኸ በአምስት ቀን ከልጅ ልጅህ ተወልጄ አድንሃለሁ ብሎ ተስፋውን ሰጠው፡፡ አዳም የተሰጠውን ተስፋ ይዞ በዓለመ ሥጋ ለዘጠኝ መቶ ሠላሳ አመት ከኖረ በኋላ መከራና ችግር ከበዛበት ዓለም በሞት ተለይቷል፡ 

በወንጀል ተከሶ በወኅኒ የተፈረደበት ሰው ከእስር የሚፈታበትን ዕለት በማውጣት በማውረድ ወራቱንና ዓመታቱን እንደሚቆጥር፣ አዳምም በሞት ቢለይም በሲኦል የነፍስ ቅጣት ካለበት ሥፍራ ይኖር ስለነበር የተሰጠውን ተስፋ በማሰብ ሱባዔውን እየቆጠረ የተናገረውን የማያስቀር የማያደርገውን የማይናገር ጌታየ እነሆ አድንኀለሁ ብሎ የገባልኝ ዘመን ተፈጸመ፤ ሰዓቱ አሁን ነው፤ እያለ ሲያወጣ ሲያወርድ ቸር አምላክ ሰው ኾኖ ሥጋ ለብሶ በአካለ ነፍስ ወደ ሲኦል ወርዶ፡- ተንሥኡ ለጸሎት ለጸሎት ተነሡ፤ ሰላም ለኩልክሙ፤ ሰላም ለእናንተ ይሁን በማለት አዳምን ከነልጅ ልጆቹ ነጻ አውጥቶታል፡፡ አዳምን በመከተል ልጆቹም አበው ቅዱሳን ነቢያት ሱባዔ በመግባት የተስፋን ዘመን በመቁጠር በመልካም ግብር ተከትለውታል፡፡ በዚህም መሠረት በርካታ ነቢያት በተለያየ ስልት ሱባዔ ቆጥረዋል፤ እኛም ሱባዔ ከቆጠሩ ነቢያት የተወሰኑትን በዚህ ጽሑፍ እንደሚከተለው እናቀርባለን፡፡

ሱባዔ ሔኖክ

ጻድቁ ሔኖክ፣ የያሬድ ልጅ ሲሆን፣ በትውልድ ከአዳም ሰባተኛ ነው፡፡ እርሱም በሕይወቱ እግዚአብሔርን ደስ ለማሰኘት ቤት ንብረቱን በመተው በሱባዔና በትሕርምት እግዚአብሔርን አገልግሏል፡፡ ፍጹም አካሔዱን ከእግዚአብሔር ጋር ያደረገ ሰው በመሆኑ በብሉይ ኪዳንም ሆነ በሐዲስ ኪዳን መልካም ግብር ተመስክ ሮለታል፡፡ ሔኖክም አካሄዱን ከእግዚአብሔር ጋር አደረገ፡፡ ዘፍ.5.22፡፡ ይህም በመሆኑ እግዚአብሔር የሱባዔውን ዋጋ ቅዱስ መንፈሱን በረድኤት ስለ አሳደረበት ትንቢት ተናግሯል፤ ሱባዔ ቆጥሯል፡፡ በሰማይ ተሰውሮ ሳለ ስለ ቅዱሳን መላእክት፣ ስለ መሲሕ ኢየሱስ ክርስቶስ፣ ስለ ፀሐይና ጨረቃ አመላለስ /ዑደት/ የሚተርክ በስሙ የተሰየመውን መጽሐፍ ጽፏል፡፡ ዘፍ.5 21-24፡፡ ይሁዳ ቁ.14፡፡ ሔኖክ 1.9፡፡

ሱባዔ ሔኖክ የሚባለው ነቢዩ ሔኖክ በመስፈርት የቆጠረው ሱባዔ ነው፡፡ መስፈርቱ /ማባዣ ቁጥር/ 35 ሲሆን 35’19 ሲበዛ በውጤቱ 685 ዓመት ይሆናል፡፡ 685’12 ስናባዛው 7980 ይሆናል፡፡ ይኸውም ሐሳብ የሚያስረዳው ስለክርስቶስ ምጽአት ነው፡፡

ዓለም ከተፈጠረ ጀምሮ አሁን የደረስንበት ዘመን 7497 ይሆናል፡፡ ይህን ለማረጋገጥ በ5500 ዓመት ላይ 1997 ዓመትን መደመር ነው፡፡ በዚህን ጊዜ ከላይ ያስቀመጥነውን 7497 ዓመት ይሰጠናል፡፡ በነቢዩ ሔኖክ አቆጣጠር መሠረት ምጽአተ ክርስቶስ በ7980 ይሆናል፡፡ ከላይ ሔኖክ የቀመረውን ቁጥር ይዘን ከ7980 ዓመት ላይ አሁን ያለንበትን ዘመን /1997/ ስንቀንስ 483 ዓመት እናገኛለን፡፡ ስለዚህ በሔኖክ ሱባዔ መሠረት ምጽአተ ክርስቶስ ሊሆን 483 ዓመት ይቀራል፡፡ 

ሱባዔ ዳዊት

ነቢዩ ዳዊት ከእስራኤል ነገሥታት ሁሉ ታላቅና ተወዳጅ ንጉሥ ነበር፡፡ ዘመነ መንግሥቱ 1011-971 ከክርስቶስ ልደት በፊት እንደ ነበር ይታመናል፡፡ ነቢዩ ዳዊት ልበ አምላክ እንደ መሆኑ ትንቢት ተናግሯል፡፡ ሱባዔ ቆጥሯል፡፡ ይኽውም ቀመረ ዳዊት በመባል ይታወቃል፡፡ እስመ ዐሠርቱ ምእት ዓመት በቅድሜከ፤ ከመ ዕለት እንተ ትማልም ኃለፈት፤ ሺ ዓመት በፊትህ እንዳለፈች እንደ ትላንት ቀን፡፡ /መዝ.89.4/ የሚለውን መምህራን ሲቆጥሩት 1140 ዓመት ይሆናል፡፡ ይኸውም በጌታ ዘንድ 1140 ዓመት እንደ አንድ ቀን እንደሆነ ነቢዩ ዳዊት ተናግሯል፡፡ ይህም ለዳዊት ሱባዔ መቁጠሪያ /መሥፈሪያ/ ሆኖ አገልግሏል፤ 1140*7= 7980 ዓመት ይሆናል፡፡ ይህም ዓለም ከተፈጠረ ጀምሮ በ7980 ዓመት ክርስቶስ ዳግም እንደ ሚመጣ የሚያመለክት ነው፡፡ 

ሱባዔ ዳንኤል

ነቢዩ ዳንኤል ምድቡ ከዐበይት ነቢያት ነው፡፡ እስራኤል ወደ ባቢሎን ሲማረኩ ተማርኮ ወደ ባቢሎን ወርዷል፡፡ እርሱም ስለ ክርስቶስ መምጣት ትንቢት ተናግሯል፤ ሱባዔም ቆጥሯል፡፡ ሰብአ ሰንበታተ አድሞሙ ለሕዝብከ፤ ሰባ ሰንበት ወገኖችህን ቅጠራቸው፡፡ ይኸውም ክርስቶስ ከ490 ዓመት በኋላ ሰው መሆኑን የሚያመለክት ትንቢት ነው፡፡ እንዲሁም እስከ ክርስቶስ ንጉሥ ትትሐነፅ መቅደስ ወእምዝ ትትመዘበር፤ እስከ ንጉሥ ክርስቶስ ድረስ መቅደስ ትታነፃለች በኋላም ትፈርሳለች ሲል ተናግሯል፡፡ 

የአቆጣጠር ስልቱም በዓመት ሲሆን ይኸውም ሰባቱን ዓመት አንድ እያሉ መቁጠር ነው፡፡ ይኽውም ሱባዔ ሰንበት ይባላል፡፡ ዳንኤል ሱባዔ ከቆጠረበትና ትንቢት ከተናገረበት ጀምሮ ክርስቶስ እስከ ሚወለድ 490 ይሆናል፡፡ መስፈርቱ /ማባዣው/ ሰባት ስለሆነ 7*70 ስናባዛው 490 እናገኛለን፡፡ ይኸውም ነቢዩ ሱባዔ ከቆጠረና ትንቢት ከተናገረ ከ490 ዓመት በኋላ የክርስቶስን መወለድ ያመለክታል፡፡

በአጠቃላይ ከላይ የተመለከትናቸው ቅዱሳን ነቢያት አካሄዳቸውን ከእግዚአብሔር ጋር በማድረግ ሱባዔ ገብተው በትሕርምት በመኖራቸው ድንቅ የሆነውን የክርስቶስን ልደትና ዳግም ምጽአት ለመተንበይ ችለዋል፡፡ ሱባዔ መግባት የራቀን ለማቅረብ የረቀቀን ለማጉላት ብቃትን ከእግዚአብሔር ዘንድ የሚያስገኝ መንፈሳዊ ጥበብ መሆኑን መገንዘብ ተገቢ ነው፡፡

የሱባዔ ዓይነቶች

የግል ሱባዔ/ዝግ ሱባዔ/

የግል ሱባዔ አንድ ሰው ብቻውን ሆኖ በቤትና በአመቺ ቦታ የሚይዘው ማንም ሰው ሳያየው በግሉ የጸሎት በኣቱን ዘግቶ በሰቂለ ኅሊና ሆኖ ፈጣሪው ብቻ እንዲያየው እንዲሰማው በኅቡዕ የሚፈጽመው ሱባዔ ነው፡፡ ማቴ.6፡5-13፡፡ በዚህ ዓይነት መልክ አንድ ሰው ሱባዔ ሲገባ ዘጋ ይባላል፡፡ ዝግ ሱባዔ የያዘ ሰው የሚያስፈልገውን ነገር ይዞ ወደ በኣቱ ከተከተተ በኋላ ሱባዔው እስኪፈጸም ድረስ ከሰው አይገናኝም፡፡ መዝ. 101-6-7፡፡

የማኅበር ሱባዔ

የማኅበር ሱባዔ የሚባለው ካህናት፣ ምእመናን ወንዶችና ሴቶች፣ ሽማግሌዎችና ወጣቶች በአንድ ሆነው በቤተ ክርስቲያንና አመቺ በሆኑ ቦታዎች ሁሉ ተሰብስበው የሚገቡት ሱባዔ ነው፡፡ በብሉይ ኪዳን የነበሩ ምእመናን ወደ እግዚአብሔር በመሄድ ይጸልዩ ነበር፡፡ 1ኛ ሳሙ.1፡9፤ መዝ.121፡1፤ ሉቃ.18፡10-14፡፡

በሐዲስ ኪዳንም የሐዋርያት ተከታዮች የኾኑ መነኮሳት፣ ካህናትና ምእመናን በገዳማት፣ በአድባራት፣ የሰንበት ት/ቤት ተማሪዎች፣ የጽዋ ማኅበርተኞች ስለ ማኅበራቸው ጥንካሬና ከማኅበርተኞቹ መካከል አንዱ ችግር ሲገጥመው የማኅበር ሱባኤ ይያዛል፡፡.

የዐዋጅ ሱባዔ

የዐዋጅ ሱባዔ በአገር ላይ ድንገተኛ አደጋ፣ አባር ቸነፈርና ጦርነት ሲነደ እንዲሁም ለማኅበረ ምእመናን አስጊ የሆነ መቅሰፍት ሲከሰት፣ እግዚአብሔር መሽቱን በምሕረት ቁጣውን በትዕግሥት እንዲመልስ የሚያዝ የሱባዔ ዓይነት ነው፡፡ ለዚህ ዓይነቱ ሱባዔ የነነዌ ሰዎችና በፋርስ በስደት ይኖር የነበረ እስራኤላውያን ተጠቃሾች ናቸው፡፡ የነነዌ ሰዎች የዮናስን ስብከት ሰምተው ከሊቅ እስከ ደቂቅ ለሦስት ቀን ከመብል ከመጠጥ ተከልክለው በመጾም በመጸለይ እግዚአብሔር መዓቱን በምሕረት ቁጣውን በትዕግሥት እንዲመልስ አድርገዋል፡፡ ሌላው በፋርስ በስደት ይኖር የነበረ አይሁድ በአስቴር ትእዛዝ የያዙት ሱባዔ ተጠቃሽ ነው፡፡ በዚያን ዘመን አርጤክስስ አይሁድ በያሉበት እንዲገደሉ በማዘዙ ከዚህ የጅምላ ጭፍጨፋ ለመዳን አይሁድ በዐዋጅ ሱባዔ ገብተዋል፡፡ አስቴር ገብታ ንጉሡን ስታናግረው ሌላው ሕዝብ በውጭ ዐዋጅ ዐውጀው ሱባዔ ገብተው ፈጣሪያቸውን ተማፅነዋል፡፡ አስቴር 4፡16 – 28፡፡

በአገራችንም ይህን የመሰለ የዐዋጅ ሱባዔ በዐፄ ምኒልክ ዘመነ መንግሥት ተደርጓል፡፡ ፋሽስት ጣልያን አገራችንን በመውረር ኢትዮጵያን ቅኝ ተገዥ ለማድረግ ድንበሯን አልፎ በመጣበት ወቅት ንጉሠ ነገሥት ምኒልክ፡-ጉልበት ያለህ በጉልበትህ ጉልበት የሌለህ በጸሎትህ ርዳኝ በማለት የዐዋጅ ሱባዔ መያዛቸው ይነገራል፡፡ በዚህም መሠረት በየገዳማቱ ምሕላ ተይዟል፤ ንጉሡም ታቦተ ጊዮርጊስን ይዘው ዓለምን እጅግ ያስደነቀ ጥቁሮችን ለነጻነታቸው እንዲነሣሱ የሚያስችል ፋና ወጊ የሆነ ድል አግኝተው አገራችንን ለቅኝ ግዛት ያሰበውን ፋሽስት ጣልያንን ማሸነፋቸው በከፍተኛ ስሜት የምናስታውሰው ነው፡፡

ቅድመ ዝግጅት

ሱባዔ መግባት የሚፈልግ ምእመን ቅድመ ዝግጅት ማድረግ ይኖርበታል፡፡ ያለምንም ዝግጅት ሱባዔ መግባት ለፈተና ያጋልጣል፡፡ ስለዚህ ቅድመ ሱባዔ /ሱባዔ ከመግባት አስቀድሞ/፣ ጊዜ ሱባዔ/ በሱባዔ ጊዜና ድኅረ ሱባዔ /ከሱባዔ በኋላ/ ዝግጅት አስፈላጊ ነው፡፡

ቅድመ ሱባዔ /ሱባዔ ከመግባት አስቀድሞ/

በመጀመሪያ ሱባዔ የምንገባበትን ምክንያት ለይቶ ማወቅ ያስፈልጋል፡፡ አንድ ሰው ሱባዔ የሚገባበትን ዓላማ ለይቶ ካስቀመጠ ከሱባዔ በኋላ የሚጠበቀውን ነገር ማግኘት አለማግኘቱን ይረዳል፡፡ ይህ ሳይሆን ሱባኤ ቢገባ ከሱባኤው በኋላ የጠየቀው ነገር ስለሌለ ትርጉም ያጣል፡፡ ስለዚህ ሱባዔ ከመግባታችን በፊት ለምን ሱባኤ ለመግባት እንዳሰብን ለይተን ማወቅ ይኖርብናል፡፡

ሱባዔ ለመግባት የወሰንበትን ምክንያት ከለየን በኋላ ምክንያታችንን ይዘን የንስሐ አባታችንን ማማከር ያስፈልጋል፡፡ ምክንያቱም በምክረ ካህን መጓዝ መጀመር ክርስቲያናዊ ግዴታ ነው፡፡ ከዚህ ባሻገር በአባትነታቸውና በሕይወት ልምዳቸው ምን ማድረግ እንደሚገባን ምክር ለማግኘት እገዛ ያደርግልናል፡፡ ቅድመ ሱባኤ ከንስሐ አባት ጋር መመካከር ተገቢ ይሆናል፡፡ ለምሳሌ አንድ ሰው በሱባዔ ወቅት የተለያዩ ፈተናዎች ቢያጋጥሙት የተሰጠውን ምክር በመጠቀም ፈተናውን ለመቋቋም ይችላል፡፡ እንዲሁም የንስሐ አባቱ በሱባዔ ወቅት በጸሎት እንዲያስቡት መማከር የራሱ የሆነ ድርሻ አለው፡፡

ሱባዔ ለመግባት ስናስብ ለምን ያህል ቀናት መቆየት እንዳለብን መወሰን ያስፈልጋል፡፡ ሱባዔ ከዚህ እስከዚህ እቆያለሁ ብለን ዕቅድ የምንይዝበት ነው፡፡ እንደ አቅማችንና እንደ ችሎታችን ከዚህ ቀን እስከዚህ ብለን በመወሰን ሱባዔ መግባት ተገቢ ይሆናል፡፡ ለምሳሌ፡- ምንም ዓይነት ልምድ ሳይኖረው አንድ ሰው በዋሻ እዘጋለሁ ቢል ከጥቅሙ ጉዳቱ ሊያመዝን ይችላል፡፡ ምክንያቱም በሱባዔ ወቅት ፈተና ስለሚበዛ የሚመጣበትን ፈተና መቋቋም ባለመቻል ሱባዔው ሊቋረጥ ይችላል፡፡ ስለዚህ ቅድመ ሱባዔ ዐቅምንና ችሎታን አገናዝቦ መወሰን ተገቢ ነው፡፡

ሌላው ቅድመ ሱባዔ ለሱባዔ ተስማሚ የሆነ ወቅትና ቦታ መምረጥ ተገቢ ነው፡፡ በቤተ ክርስቲያን በአብዛኛው ሱባዔ የሚገባው አጽዋማትን ተከትሎ ነው፡፡ ስለዚህ ሱባዔ የምንገባበት ወቅት የጾም ወቅት መሆን አለመሆኑን መለየት ያስፈልጋል፡፡ በአጽዋማት ወቅት የሚያዝ ሱባዔ ለተሐራሚ ጠቀሜታው እጅግ የጐላ ነው፡፡ ምክንያቱም በአጽዋማት ወቅት ብዙ አባቶች ሱባዔ ስለሚይዙ ከአባቶች ጸሎት ጋር ልመናችንና ጸሎታችን ሊያርግ ይችላል፡፡ ስለዚህ ወቅትን ለይቶ ማወቅ ያስፈልጋል፡፡

እዚህ ላይ ከወርኃ አጽዋማት ውጭ ሱባዔ አይያዝም የሚል አቋም ለመያዝ አይደለም፡፡ አንድ ሰው ፈተና ከአጋጠመው በማንኛውም ጊዜ ሱባዔ ሊገባ እንደሚችል እዚህ ላይ ለመጠቆም እንወዳለን፡፡ ከዚህም ባሻገር ሱባዔ የምንይዝበትን ቦታ መምረጥ አለብን፡፡ ለሱባዔ የምንመርጣቸው ቦታዎች ለፈተና የሚያጋልጡ መሆናቸውን ማረጋገጥ ያስፈልጋል፡፡ ይኸውም ሱባዔ ከተገባ በኋላ ኅሊናችን እንዳይበተን እገዛ ያደርግ ልናል፡፡ ጫጫታና ግርግር የሚበዛበት ቦታ በሰቂለ ኅሊና ለመጸለይ አያመችም፡፡ ስለዚህ ሱባዔ የምንይዝባቸው ቦታዎች ከከተማ ራቅ ያሉ ገዳማትና አድባራት ተመራጭ ናቸው፡፡

ጊዜ ሱባዔ /በሱባዔ ጊዜ/

በጸሎት ሰዓት ዓምድና ግድግዳ ሳይደገፉ መቋሚያ ሳይዙ በሁለት እግር ቀጥ ብሎ በመቆም መጸለይ ይኖርብናል፡፡ እንዲሁም ፊትን ወደ ምሥራቅ መልሶ መቆም ወዲያና ወዲህ ወደ ግራ ወደ ቀኝ አለመዟዟር በሰፊሐ እድ በሰቂለ ኅሊና ኾኖ መጸለይ ይገባል፡፡ መዝ.5፡3፤ መዝ.133፡2፤ ዮሐ.11፡41፡፡

በሱባዔ ወቅት በቅደም ተከተል መጸለይ አለብን፡፡ መጀመሪያ በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አአትብ ገጽየ ወኩለንታየ በትእምርተ መስቀልኸ በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አንዱ አምላክ መላ ሰውነቴን በትእምርተ መስቀል አማትባለሁ እያለ ሰጊድን ከሚያነሣው ሲደርስ መስገድ መስቀልን ከሚያነሣ ላይ ስንደርስ ማማተብ ይገባል፡፡

በማስከተል አቡነ ዘበሰማያት፣ መዝሙረ ዳዊት፣ ውዳሴ ማርያምና ሌሎች በመዝገበ ጸሎት የተካተቱትን መጸለይ፤ ቀጥሎ አቡነ ዘበሰማያት፣ ጸሎተ እግዝእትነ ማርያምን፣ ጸሎተ ሃይማኖትን ከጸለይን በኋላ አቡነ ዘበሰማያት መድገም፤ ከዚያ 41 ጊዜ ኪርያላይሶን ይባላል፡፡ ሌላው በሱባዔ ጊዜ ከተሐራሚ የሚጠበቀው ነገር ኃጢአቱን እያሰበ ማዘን ማልቀስ ነው፡፡ ሲያለቅስም ለእያንዳንዱ በደል እንባ ማፍሰስ ያስፈልጋል፡፡

በመጨረሻም ሱባዔ የገባ ሰው ሱባዔውን ሳይጨርስ ወይም ሱባዔውን አቋርጦ ከማንም ሰው ጋር ፈጽሞ መገናኘት የለበትም፡፡

ድኅረ ሱባዔ /ከሱባዔ በኋላ/

ለቀረበ ተማኅፅኖ እግዚአብሔር የሚያደርግልንን ነገር መጠበቅ ይኖርብናል፡፡ እግዚአብሔር ላቀረብንለት ምልጃና ጸሎት እንደ ልባችን መሻት እንደ እርሱ ቸርነት እርሱ በወደደ ጊዜ ያደርግልናል፡፡ ሱባዔ የገባ ሰው ሁሉ ራእይ ላያይ ይችላል፡፡ ምክንያቱም የእግዚአብሔር መልስ አሰጣጥ ለማንም ግልጽ አይደለም፡፡ ከሱባዔ በኋላ መጀመሪያ የምናገኘው የኅሊና ሰላምን ነው፡፡ ይህ ትልቅ የአምላክ ስጦታ ነው፡፡ ከዚህ ባሻገር ሱባዔ ገብተን ያሰብነውን ካላገኘን ዳግመኛ ተዘጋጅተን እስከ መጨረሻው ሰዓት መማፀን መጽናት ይኖርብናል፡፡

የ፳፻፯(2007)ዓ/ም ዐብይ ጾምና በዓላቱ

 ጥር 29 ቀን 2007 ዓ.ም.

የ2007 ዓ.ም. ዘመን አቆጣጠር በዓላትና አጽዋማትን በአዲሱ ዓመት መባቻ ማቅረባችን ይታወሳል፡፡ አሁን ያለንበት ወቅት የነነዌ ጾም አልፈን ዐብይ ጾምን የምንቀበልበት ወቅት በመሆኑ መረጃውን ለማስታወስ ይህንን ዝግጅት ያቀረብን ሲሆን የምትፈልጉትን ቀን ለማወቅ ከማኅበሩ ድረ ገጽ ላይ ያለውን የዘመን መቁጠሪያ በመቀያየር መጠቀም ትችላላችሁ፡፡

 

የበዓላትና የአጽዋማት ኢየዐርግና ኢይወረድ

1. ጾመ ነነዌ ከጥር 17 ቀን በታች ከየካቲት 21 ቀን በላይ አይውልም
2. ዐቢይ ጾም ከየካቲት 1 ቀን በታች ከመጋቢት 5 ቀን በላይ አይውልም
3. ደብረ ዘይት ከየካቲት 28 ቀን በታች ከሚያዝያ 2 ቀን በላይ አይውልም፡፡
4. በዓለ ሆሣዕና ከመጋቢት 19 ቀን በታች ከሚያዝያ 23 ቀን በላይ አይውልም፡፡
5. በዓለ ስቅለት ከመጋቢት 24 ቀን በታች ከሚያዝያ 28 ቀን በላይ አይውልም፡፡
6. በዓለ ትንሣኤ ከመጋቢት 26 ቀን በታች ከሚያዝያ 3ዐ ቀን በላይ አይውልም፡፡
7. ርክበ ካህናት ከሚያዝያ 20 ቀን በታች ከግንቦት 24 ቀን በላይ አይውልም፡፡
8. በዓለ ዕርገት ከግንቦት 5 ቀን በታች ከሰኔ 19 ቀን በላይ አይውልም፡፡
9. ጾመ ሐዋርያት ከግንቦት 16 ቀን በታች ከሰኔ 20 ቀን በላይ አይውልም፡፡
10. ጾመ ድኅነት ከግንቦት 18 ቀን በታች ከሰኔ 22 ቀን በላይ አይውልም፡፡

 

ሁለት ዓይነት የተውሳክ አቆጣጠር አለ

 

1. የዕለት ተውሳክ በቅዳሜ ይጀምራል፡፡
የቅዳሜ ተውሳክ 8፤ የእሑድ ተውሳክ 7፤ የሰኞ ተውሳክ 6፤ የማክሰኞ ተውሳክ 5፤ የረቡዕ ተውሳክ 4፤ የሐሙስ ተውሳክ 3፤ የዓርብ ተውሳክ 2

 

2. የአጽዋማትና የበዓላት ተውሳክ
የነነዌ ተውሳክ 0፤ የዐቢይ ጾም ተውሳክ 14፤ የደብረ ዘይት ተውሳክ 1፤ የሆሣዕና ተውሳክ 2፤ የስቅለት ተውሳክ 7፤ የትንሣኤ ተውሳክ 9፤ የርክበ ካህናት ተውሳክ 3፤ የዕርገት ተውሳክ 18፤ የጰራቅሊጦስ 28፤ የጾመ ሐዋርየት ተውሳክ 29፤ የጾመ ድኅነት ተውሳክ 1

 

በዓላትና አጽዋማት የሚውሉበት ቀን
– ጾመ ነነዌ
– ዐብይ ጾም
– ጾመ ሐዋርያት – ሰኞ

– ደብረ ዘይት
– ሆሣዕና
– ትንሣኤ
– ጰራቅሊጦስ – እሑድ

– ስቅለት -ዓርብ

– ርክበ ካህናት
– ጾመ ድኅነት -ረቡዕ

– ዕርገት -ሐሙስ ቀን ይሆናል፡፡

 

የ፳፻፯(2007)ዓ/ም 

ጾመ ነነዌ
  ጥር ፳፭ 
ዓብይ ጾም
   የካቲት ፱
ደብረ ዘይት
    መጋቢት ፮
ሆሳዕና
   መጋቢት ፳፯
ስቅለት
   ሚያዚያ ፪
ትንሣኤ
    ሚያዚያ ፬
ርክበ ካህናት
    ሚያዚያ ፳፰ 
ዕርገት
    ግንቦት ፲፫ 
ጰራቅሊጦስ
    ግንቦት ፳፫
ጾመ ሐዋርያት
   ግንቦት ፳፬ |