ሐምሌ ፳፰ ቀን ፳፻፰ ዓ.ም
ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት ጾመ ማርያምን በማስመልከት ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት፤ የጠቅላይ ቤተ ክህነት፣ የማኅበረ ቅዱሳን፣ የመንግሥትና የግል መገናኛ ብዙኃን ጋዜጠኞች በተገኙበት ሐምሌ ፳፰ ቀን ፳፻፰ ዓ.ም በመላው ዓለም ለሚገኙ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ምእመናን ቃለ ምዕዳን ሰጥተዋል፡፡ የቅዱስ ፓትርያርኩን ሙሉ ቃለ ምዕዳንም እንደሚከተለው አቅርበነዋል፤
በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን
በሀገር ውስጥም ሆነ በተለያዩ ክፍለ ዓለማት የምትገኙ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ምእመናን ወምእመናት፣ እንኳን ለሁለት ሺሕ ስምንት መቶ ዓመተ ምሕረት የቅድስት ድንግል ማርያም ጾመ ፍልሰታ በሰላም አደረሳችሁ !!
‹‹ቃለ እግዚአብሔር ንጹሕ ወያሐዩ ለዓለም፤ የእግዚአብሔር ቃል ንጹሕ ነው፤ ለዘላለሙም ያድናል›› (መዝ.18፡9)፡፡
ነቢየ እግዚአብሔር ዳዊት ስለቃለ እግዚአብሔር አስመልክቶ በዘመረው መዝሙር ሲናገር ‹‹የእግዚብሔር ቃል ንጹሕ ነው›› ይላል፤ በእርግጥም የእግዚአብሔር ቃል የተለያዩ ፍጡራን ከሚናገሩዋቸው ቃልት ልዩ፤ ንጹሕ፤ ቅዱስና ክቡር ነው፡፡
የፍጡራን ቃል ከሐሰት፤ ከወላዋይነት፤ ካላዋቂነት፤ ከጥርጣሬ፤ ከአስመሳይነት፤ ከአታላይነትና ከዓቅም ውሱንነት ጋር ተቀላቅሎ ስለሚነገር ንጹሕ ነው ብሎ መናገር አይቻልም፤ የእግዚአብሔር ቃል ግን ከዚህ ሁሉ የተለየ በመሆኑ ፍጹም ንጹሕ ነው፤ እውነትም ነው፤ የእግዚአብሔር ቃል ንጹሕ ብቻ ሳይሆን ኃያልም ነውና በተናገረው መሠረት ከሚፈጸም በቀር ፍጹም የማይቀለበስ ነው፡፡
‹‹የእግዚአብሔር ቃል ከሚወድቅ፤ ሰማይና ምድር ቢያልፍ ይቀላል›› የሚለው የጌታችን የአምላካችንና የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ኃይለ ትምህርት፣ የእግዚአብሔር ቃል ከሁሉም በላይ የሆነ ክብር፣ ኃይልና ጽናት ያለው መሆኑን ያስገነዝበናል፡፡ በመሆኑም ንጹሕና እውነት የሆነውን የእግዚአብሔር ቃል በማጣመም፤ ወይም በመሸራረፍ፤ ወይም በመቀናነስ ወይም ለራስ ፍላጎት በሚያመች ሁኔታ እያዛቡ መናገርና ማስተማር በእግዚአብሔር መንግሥት ከሁሉ ይልቅ ታናሽ የሚያደርግ መሆኑ በቅዱስ ወንጌል ተጽፎአል፤ (ማቴ.5፡19)፡፡
የእግዚአብሔር ቃል እውነተኛና ንጹሕ የመሆኑን ያህል ሕያውና ዘለዓለማዊ ነው፤ በሁለት ወገን ስለት ካለው ሰይፍም ይልቅ የሚቆርጥና የሚለይ ኃይል አለው፤ (ዕብ.4$12)፡፡ ይህም ማለት የእግዚአብሔርን ቃል እንዳለ ተቀብለው የሚጠብቁትንና የሚታዘዙለትን ለዘለዓለሙ ሕያዋን የማድረጉን ያህል፣ የሚሸራርፉትንና የሚያጣምሙትን ደግሞ የመቅጣት ሥልጣን ያለው መሆኑን ያሳየናል፡፡ በመሆኑም የሰው ልጅ ድኅነት፤ ቃሉን በመጠበቅና ባለመጠበቅ ሚዛን ላይ ተቀምጦ እንዳለ መገንዘብ አለብን፡፡
የተወደዳችሁ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻችን ምእመናንና ምእመናት !!
ንጹሕና ሕያው የሆነው፣ ሰዎችንም ለዘለዓለሙ በሕይወት እንዲኖሩ የሚያደርገው የእግዚአብሔር ቃል፣ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምን በተመለከተ የተናገረው እውነት አለ፤ በቀጣዮቹ ሁለት ሱባኤያት የቅድስት ድንግል ማርያምን ነገረ ፍልሰት ምክንያት በማድረግ የምንፈጽመው አምልኮተ እግዚአብሔር፤ የእግዚአብሔር ቃል ስለ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም የተናገረውን በማስታወስና ለቃሉ ተገዥ በመሆን ነው፤ የእግዚአብሔር ቃል ስለ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ብዙ ተናግሮአል፤ ከተናገራቸውም መካከል፡-
- ጸጋን የተሞላሽ ሆይ ደስ ይበልሽ፤
- እግዚአብሔር ካንቺ ጋር ነው፤
- ከሴቶች መካከል የተባረክሽ ነሽ፤
- በእግዚአብሔር ፊት ጸጋን አግኝተሻል፤
- መንፈስ ቅዱስ በአንቺ ላይ ይመጣል፤ የልዑልም ኃይል ይፀልልሻል፣
- የጌታዬ እናት ወደኔ ትመጣ ዘንድ እኔ ማነኝ?
- ብፅዕት ነሽ፤ ትውልድ ሁሉ ብፅዕት ይሉኛል፣
- እነሆ ልጅሽ እነኋት እናትህ፤ የሚሉ ይገኙባቸዋል፡፡
ስለሆነም እግዚአብሔር ስለ ቅድስት ድንግል ማርያም የተናገረውን ቃል ጠቅለል አድርገን ስንመለከት በዋናነት የሚያሳየው ቅድስት ድንግል ማርያምን የጌታ እናት መሆኗን አምነው በመቀበል ‹‹ትውልድ ሁሉ ብፅዕት ነሽ›› እያሉ እንዲያከብሯት በእግዚአብሔር መታዘዙ ነው፤ ምክንያቱም የድንግል ማርያም ክብር፣ ከእግዚአብሔር ክብር ጋር የተያያዘ ባህርይ አለውና ነው፤ ቅድስት ድንግል ማርያም ምልእተ ጸጋ፤ ሙኃዘ ፍሥሐ፣ ምልእተ በረከት፤ የእግዚአብሔር ባለሟል፤ የመንፈስ ቅዱስ ማደሪያ፤ ከእግዚአብሔር ጋር ያለች፤ ብፅዕት፤ ባትሆን ኖሮ ጌታን ለመውለድ የሚያስችል ንጽሕናና ቅድስና አይኖራትም ነበር፤ እግዚአብሔር ንጹሐ ባህርይ እንደ መሆኑ መጠን በንጹሐንና በቅዱሳን አድሮ ይኖራልና፡፡
ቅድስት ድንግል ማርያም ጸጋን፤ በረከትን፤ ባለሟልነትን፤ የመንፈስ ቅዱስ ማደሪያ መሆንን፤ በድንግልና መፅነስን በእግዚአብሔር ኃይል መከለልን ገንዘብ አድርጋ መገኘቷ፤ ከእርስዋ የተወለደው ማን እንደሆነ በትክክል እንድናውቅ ያስችለናል፡፡
ቅድስት ድንግል ማርያምን ወላዲተ አምላክ ሳንል፤ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን አምላክ ወሰብእ ወሰብእ ብለን ማመንና መዳን አንችልም፤ ቅድስት ድንግል ማርያምን ምልእተ ጸጋ፣ ምልእተ በረከት፤ ሙኃዝ ፍሥሐ፤ ብፅዕት፤ ንጹሕት፤ ቅድስት ስንል ነው ከእርስዋ የተወለደውን ጌታ የባህርይ አምላክ ነው ማለት የምንችለው፣ ምክንያቱም የቅድስት ድንግል ማርያም ልዩ ጸጋና ቅድስና ለጌታችንና ለመድኃኒታችን ለኢየሱስ ክርስቶስ ማንነት አስረጅ በመሆኑ ‹‹ትውልድ ሁሉ ብፅዕት ነሽ›› እያልን እመቤታችንን እንድናከብር የእግዚአብሔር ቃል አዞናልና፤ (ሉቃ 1፡45-48)፡፡
ጌታችንና አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ በእርሱና በቅድስት ድንግል ማርያም ያለው ግንኙነት የእናትነትና የልጅነት እነደሆነ ሁሉ በምእመናንና በድንግል ማርያም መካከል ያለው ግንኙነትም በእናትነትና በልጅነት ደረጃ እንዲሆን አዞአል፤ (ዮሐ 19፡26-27)፡፡
በሁሉም ዘንድ እንደሚታወቀው አንድን ልጅ አቅፋ፣ አዝላ፣ አጥብታ፣ መግባ፣ ንጽሕናውን ጠብቃ በእንክብካቤ የምታሳድግ እናት ታስፈልገዋለች፤ እናትም የሚያከብራትና የሚያስከብራት ልጅ ያስፈልጋታል፡፡ እንደዚሁም ሁሉ ጌታችን እመቤታችንን የምእመናን እናት እንድትሆን ሲያደርግ፣ በሥጋዊም ሆነ በመንፈሳዊ ሕይወታችን ተጎሳቁለን እንዳንጎዳ በጸሎቷ፣ በልመናዋ፣ በአማላጅነቷ እያገዘችና እየደገፈች ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ልታደርሰን ብሎ እንደሆነ ልብ ብሎ ማስተዋሉ ተገቢ ነው ፡፡
ምእመናንም የእመቤታችን ልጆች እንድንሆን ማድረጉ በዚህ ዓለም ስንኖር እርስዋን አክብረንና በስሟ እየተማፀን የበረከቷና የጸጋዋ ተካፋይ እንድንሆን ብሎ እንደሆነ በውል መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ዮሐንስ ‹‹እነኋት እናትህ›› ከተባለበት ሰዓት ጀምሮ እመቤታችንን ወስዶ በቤቱ አኑሯታል፤ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ እመቤታችን በእያንዳንዱ አማኝ ልጇ ቤት በመንፈስ እየገባች ትኖራለች፡፡
በዚህ የጌታችን ቃል፣ የሐዋርያት ትምህርትና ትውፊት መሠረት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ምእመናን ቤት፣ የእመቤታችን ቤት ሆኖ ይገኛል፤ ምክንያቱም በቤቱ የድንግል ማርያምን ሥዕል አስገብቶ እምዬ እናቴ፣ ብፅዕት ነሽ እያለ የማይጸልይና የማይማጸን የለምና፡፡ በዚህም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ምእመን የሆነ ሁሉ የእግዚአብሔርን ቃል ሳይሸራርፍ፣ ሳይቀናንስና ሳያጣምም እንዳለ ተቀብሎ እየፈጸመ ይገኛል፤ ቃሉን በምልአት በመጠበቁና በመፈጸሙም እንደ ቃሉ ተስፋ ለዘለዓለም ሕያው ሆኖ ይኖራል፡፡
የተወደዳችሁ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻችን ምእመናንና ምእመናት!
እግዚአብሔር በቅድስት ድንግል ማርያም በኩል የሰጠን ትልቁ ስጦታ ፍጹም ፍቅር ነው፤ ይኸውም በእናትና በልጅ መካከል ያለውን ፍቅር ነው፤ ያ ፍቅር ነው እስካሁን እመቤታችንና እኛን አስተሳስሮ የሚገኘው፤ ከዚህ ፍቅር ሊለዩን የሚሞክሩትን ሁሉ በእግዚአብሔር ቃል፣ በኦርቶዶክሳዊና በኢትዮጵያዊ መንፈስ ልንቋቋማቸው ይገባል፡፡ ቅድስት ድንግል ማርያምን ብፅዕት ነሽ እያለ የሚያመሰግን ሁሉ፣ እንደ ኤልሳቤጥ በመንፈስ ቅዱስ የተሞላና የእግዚአብሔርን ቃል በምልአት የያዘ መሆኑን እርግጠኛ ይሁን፡፡
በእኛና በቅድስት ድንግል ማርያም ያለው ፍቅር ዓቢይና ጥልቅ እንደመሆኑ መጠን፣ ስመ ማርያምን ጠርቶ ቁራሽ እንጀራ የሚለምን ሁሉ፣ ስለእርስዋ ፍቅር ብለን ለድሆች ስንዘክር፣ የነበረው ሃይማኖታዊ ተግባራችን ዛሬም ሳይቀዘቅዝ ሊቀጥል ይገባል፡፡
በዚህ በጾመ ማርያም ወቅት የተራቡትን በማጉረስ የታረዙትን በማልበስ፣ የታመሙትን በመጠየቅ፣ የታሠሩትን እግዚአብሔር ያስፈታችሁ በማለት፣ በማኅበረ ሰቡ መካከል መቻቻልን፣ መተማመንን፣ ወንድማማችነትን፣ ስምምነትን፣ ፍቅርንና ሰላምን በማስፈን ሱባኤውን ልንፈጽም ይገባል፤ ከዚህም ጋር በአሁኑ ጊዜ በስፋት እያጋጠመ ያለውን የትራፊክ አደጋ መቀነስ ይቻል ዘንድ፣ ምእመናን ሁሉ ወደ ቤተ ክርስቲያን ሲመላለሱም ሆነ በሌላ ቦታ እንቅስቃሴ ሲያደርጉ ጥንቃቄ ባልተለየው ሁኔታ እንዲሆን፣ ሹፌሮችም ሲያሽከረክሩ ኃላፊነት፣ ጥንቃቄና ማስተዋል ባልተለየው ሁኔታ እንዲሠሩ መንፈሳዊ መልእክታችንን እናስተላልፋለን፤ በየቤተ ክርስቲያኑ የሚገኙ መምህራንና ሰባክያንም የጉዳዩን አሳሳቢነት በማስገንዘብ ሕዝቡ ከትራፊክ አደጋ ጥንቃቄ ያደርግ ዘንድ በዚሁ ሱባኤ ሰፊ ትምህርትና ምክር እንዲሰጡ አደራ ጭምር መልእክታችንን በእግዚአብሔር ስም እናስተላልፋለን፡፡
እግዚብሔር ኢትዮጵያን ይባርክ ይቀድስ፤
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
አሜን፡፡
አባ ማትያስ ቀዳማዊ
ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ
ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት