ጳጕሜን ፩ ቀን ፳፻፰ ዓ.ም
በዝግጅት ክፍሉ
የተወደዳችሁ ምእመናን! ማኅበረ ቅዱሳን ከነሐሴ ፳፯-፳፱ ቀን ፳፻፰ ዓ.ም ድረስ ፲፪ኛ ጠቅላላ ጉባኤውን በጠቅላይ ቤተ ክህነት ስብከተ ወንጌል አዳራሽና በማኅበሩ ሕንጻ ፫ኛ ፎቅ ለሦስት ቀናት አካሒዷል፡፡ ከዓርብ ምሽት እስከ እሑድ ሌሊት ድረስ የነበረውን የጉባኤውን አጠቃላይ ይዘት በአጭሩ እናስቃኛችሁ!
ከነሐሴ ፳፮ ቀን ፳፻፰ ዓ.ም ጀምሮ የማኅበሩ መደበኛ አገልጋዮች ለአገልግሎት የሚጠቀሙባቸውን ልዩ ልዩ ንብረቶቻቸውን በተዘጋጀላቸው ጊዜያዊ ቦታ በማስቀመጥ ቢሮዎቻቸውን ለእንግዶች ማረፊያ ለቀዋል፡፡ ከዚያች ሰዓት በኋላ የመግቢያ መለያ ከተሰጣቸው አባላት በስተቀር ማንኛውም አባል ወደ ሕንጻው እንዲገባ አይፈቀድለትም፡፡ በዚህ ጉባኤ ለመሳተፍ ከአሜሪካ፣ ከአውሮፓ፣ ከዐረብ አገሮችና ከአፍሪካ አህጉር፤ ከአገር ውስጥ ደግሞ ከአራቱም የኢትዮጵያ አቅጣጫዎች የመጡ በርካታ ወንድሞችና እኅቶች በአዲስ አበባ ከተማ ከመንበረ ፓትርያርክ ቅድስተ ቅዱሳን ማርያም ገዳም በስተምዕራብ አቅጣጫ በተገነባው የማኅበረ ቅዱሳን ሕንጻ ተሰባስበዋል፡፡
በዕለተ ዓርብ ነሐሴ ፳፯ ቀን ፳፻፰ ዓ.ም ለጉባኤው ተሳታፊዎችና ጥሪ ለተደረገላቸው እንግዶች አቀባበል ከተደረገላቸው በኋላ ምሽት ፲፪ ሰዓት ላይ ጠቅላላ ጉባኤው በማኅበር ጸሎት ተጀምሮ በጸሎት እስከ ተጠናቀቀበት ነሐሴ ፳፱ ቀን ፳፻፰ ዓ.ም ድረስ የነበሩ መርሐ ግብራት የቀኖቹ በጠቅላይ ቤተ ክህነት ስብከተ ወንጌል አዳራሽ፤ የማታዎቹ ደግሞ በማኅበሩ ሕንጻ ተከናውነዋል፡፡ ለተሳታፊዎቹ አቀባበል በተደረገበት ዕለትም ፈቃደ ሥጋን ለፈቃደ ነፍስ ማስገዛት እንደሚገባ የሚያስገነዝብ ትምህርተ ወንጌል በመምህር ቸርነት አበበ ተሰጥቷል፡፡
በዚህ ጠቅላላ ጉባኤ የጠቅላይ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ ብፁዕ አቡነ ዲዮስቆሮስን ጨምሮ ብፁዕ አቡነ ሉቃስ፣ ብፁዕ አቡነ ሰላማ፣ ብፁዕ አቡነ ገብርኤልና ብፁዕ አቡነ እንጦንስ ተገኝተው ቃለ ምዕዳንና ጸሎተ ቡራኬ ሰጥተዋል፡፡ ኹሉም የማኅበረ ቅዱሳን አባላት በእግዚአብሔር ጥበብ ለአገልግሎት የተጠሩ መኾናቸውን ተረድተው፣ የተሰጣቸውን ልዩ ልዩ ጸጋ ተጠቅመው፣ በፈተና ጸንተው ቅድስት ቤተ ክርስቲያንን በትዕግሥትና በትጋት ማገልገል እንደሚገባቸው የሚያተጋ መልእክት ያለው ትምህርተ ወንጌል ‹‹በወንዝ ዳር ጣለችው›› በሚል ኃይለ ቃል በዲያቆን ዶ/ር ያረጋል አበጋዝ ተሰጥቷል፡፡
በተጨማሪም የተሳታፊዎችን ግንዛቤ የሚያዳብሩ ጥናቶችም ቀርበዋል፡፡ ከእነዚህ መካከልም ኦርቶክሳዊነትን የሚፈታተኑ ዓለም ዓቀፍ ችግሮች በምእመናን ላይ የሚያደርሷቸውን ተጽዕኖዎችና መፍትሔዎቻውን በስፋት የዳሰሰ ጥናት ‹‹በፈታኝ ነባራዊ ኹኔታዎች እየኖሩ ኦርቶዶክሳዊ ተቋማዊ አገልግሎትን መፈጸም እንዴት ይቻላል?›› በሚል ርእስ በዲያቆን ብርሃኑ አድማስ፤ ከቤተ ክርስቲያን አባቶች፣ ከማኅበራትና በጎ አድራጊ ምእመናን ጋር በመስማማት እንዴት ማገልገል እንደሚቻል የሚያስገነዝብ ‹‹የባለ ድርሻና አጋር አካላት ውጤታማነትና ስኬታማነት›› በሚል ርእስ በማኅበሩ ዋና ጸሐፊ በአቶ ተሰፋዬ ቢኾነኝ የቀረቡት ጥናቶች ይጠቀሳሉ፡፡
በጠቅላላ ጉባኤው ማኅበሩን የሚመሩ ሥራ አመራሮች ተመርጠዋል፡፡ ማኅበሩ በ፳፻፯ እና በ፳፻፰ ዓ.ም በሁለት ዓመታት ውስጥ ያከናወናቸው ዘርፈ ብዙ ተግባራት፤ የማኅበሩ አጠቃላይ የገቢ መጠንና ለአገልግሎት ማስፈጸሚያ ያወጣው ገንዘብ፤ ማኅበሩ አገልግሎቱን ለመፈጸም በሚያደርገው እንቅስቃሴ ያጋጠሙት ልዩ ልዩ ችግሮችና የተወሰዱ መፍትሔዎች በዝርዝር ለጉባኤው ቀርበዋል፡፡ እንደዚሁም የሁለት ዓመቱ አጠቃላይ የሒሳብ ሪፖርት በተመሰከረላቸውና ሕጋዊ ዕውቅና በተሰጣቸው የውጪ ኦዲተሮች ሪፖርት ተደርጓል፡፡ ሪፖርቱም የማኅበሩን ጥንቃቄ የተሞላበትና አርአያነት ያለው ዘመናዊ የሒሳብ አጠቃቀም ዘዴ የሚያመላክት መኾኑ በኦዲተሮቹ ተገልጿል፡፡
ከጉባኤው አዳዲስ ክሥተቶች ውስጥ በጠቅላላ ጉባኤው ማጠቃለያ ነሐሴ ፳፱ ቀን ፳፻፰ ዓ.ም በዕለተ እሑድ ምሽት የብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳትና የሰባክያነ ወንጌል ምክርና የአደራ ቃል ያለበት የ፳ ደቂቃ ዘጋቢ ፊልም የጉባኤውን ተሳታፊዎች አስለቅሷል፡፡ በተለይ ብፁዕ አቡነ ቀውስጦስ ቤተ ክርስቲያን ችግር ውስጥ መኾኗንና ለአገር የዋለችው ውለታ ተረስቶ ምንም እንዳልሠራች መቈጠሯን ሲያስረዱ፤ እንደዚሁም ‹‹ምንም ብትበሳጩ ቤተ ክርስቲያንን በጠላትነት እንዳታዩአት በእግዚአብሔር አደራ እላችኋለሁ›› እያሉ ለወጣቶች መልእክት ሲያስተላልፉ አረጋዊው ጳጳስ ያሰሙት የነበረው የለቅሶ ድምፅና እርጅና ባደከመው ፊታቸው የሚፈሰው ዕንባቸው፤ እንደዚሁም በፊልሙ ላይ የብፁዕነታቸውን ቃለ ምዕዳን የሚቀበሉ ምእመናን ሰቆቃ የጠቅላላ ጉባኤውን መንፈስ ሙሉ በሙሉ ወደ ኀዘን ለውጦታል፡፡
ፊልሙ ከተጠናቀቀ በኋላ ሳይቀር የመርሐ ግብር መሪው ዕንባውን መቈጣጠር ሲያዳግተው ተስተውሏል፡፡ ‹‹ማርያም ኀዘነ ልቡና ታቀልል፤ ማርያም የልብን ኀዘን ታቀላለች›› የሚለው ዝማሬ ከተዘመረ በኋላ ነበር በመጠኑም ቢኾን የጉባኤው የኀዘን መንፈስ ወደ ውይይት ሊመለስ የቻለው፡፡ ዘጋቢ ፊልሙ የጉባኤውን ተሳታፊዎች ከማስለቀሱ ባለፈ ኹሉም የራሱን ድርሻ ዐውቆ ቤተ ክርስቲያንን በትጋት ለማገልገል እንዲነሣሣ ጭምር ማድረጉን አስተያየት ከሰጡ አባቶች፣ ወንድሞችና እኅቶች ስሜት ለመረዳት ተችሏል፡፡
ጉባኤው ከኀዘኑ ሲረጋጋም በልዩ ልዩ የአገልግሎት ዘርፍ ባስመዘገቡት ውጤት በአርአያነት የተመረጡ ከአገር ውስጥ ደብረ ማርቆስ፣ ጎንደር፣ ደሴና ጅንካ፤ ከውጪ አገር ደግሞ አሜሪካ በድምሩ ፭ ማእከላት በተወካዮቻቸው አማካይነት የልምድ ተሞክሯቸውን አቅርበዋል፡፡ ከተሞክሮው መካከልም የአሜሪካ ማእከል የአካባቢውን ምእመናን በማስተባበር ሕፃናት የአብነት ትምህርት እንዲማሩ ማድረጉና ሕፃናቱ ከንባብ ጀምሮ እስከ መጽሐፍ ቤት ድረስ ያለውን የአብነት ሥርዓተ ትምህርት ሲያቀርቡ የሚያስቃኘው ዘጋቢ ፊልም የማእከሉን ጥረት ከማስደነቁ ባሻገር ኢትዮጵያውያን ወላጆች ‹‹እኛስ ምን ሠራን?›› እንዲሉ አድርጓቸዋል፡፡ በተመሳሳይ መልኩ ዋናው ማእከል በሁለት ዓመታት የአገልግሎት ጊዜው ያጋጠሙትን ችግሮች ያለፈበት መንገድና የወሰዳቸውን የመፈትሔ ርምጃዎች የሚያመለክት የልምድ ተሞክሮም በማኅበሩ ሰብሳቢ ለጉባኤው ቀርቧል፡፡
ተሳታፊዎች የቡድን ውይይት ሲያደርጉ
በመቀጠል የጠቅላላ ጉባኤው ዐቢይ ኰሚቴ ሰብሳቢ አቶ ዳንኤል ገብረ መድኅን በማጠቃለያ ሪፖርታቸው የጉባኤው ተሳታፊዎች ላሳዩት ታዛዥነት፣ ትሕትናና ቅንነት፤ እንደዚሁም በውይይትና አስተያየት በመስጠት ላደረጉት የነቃ ተሳትፎ፤ በተጨማሪም ድርጅቶችን ጨምሮ ድጋፍ ሰጪ ክፍሎችና በጎ አድራጊ ምእመናን በዐሳብ፣ በጉልበት፣ በገንዘብ፣ በቁሳቁስ አቅርቦት፣ በጽዳት ሥራ፣ የሕክምና አገልግሎት በመስጠትና በመስተንግዶ ላበረከቱት ልዩ ልዩ አስተዋጽዖ አቶ ዳንኤል በኰሚቴው ስም መንፈሳዊ ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡
የጠቅላላ ጉባኤው ዐቢይ ኰሚቴ አባላት
በመጨረሻም የማኅበሩ ሰብሳቢ የማጠቃለያ ንግግር ሲያደርጉ በመጀመሪያ ጉባኤው በሰላም ተጀምሮ በሰላም እንዲፈጸም ያደረገውን ልዑል እግዚአብሔርን አመስግነው ለ፲፫ኛው ጉባኤ በሰላም እንዲያደርሳቸው መልካም ምኞታቸውን ከገለጹ በኋላ በጠቅላላ ጉባኤው ለተገኙ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት፣ ለተጋባዥ እንግዶችና ከመላው ዓለም ለመጡ የጉባኤው ተሳታፊዎች፤ እንደዚሁም አዳራሹን ለፈቀደው ለጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት፣ ጠቅላላ ጉባኤው በአግባቡ እንዲከናወን ላደረገው ለዐቢይ ኰሚቴውና ለጉባኤው መሳካት ልዩ ልዩ ድጋፍ ላደረጉ አካላት ኹሉ በማኅበሩ ስም መንፈሳዊ ምስጋናቸውን ካቀረቡ በኋላ ከምሽቱ 7፡30 በአባቶች ጸሎት ፲፪ኛው ጠቅላላ ጉባኤ ተፈጸሟል፡፡ ተሳታፊዎችም በከበሮና በጭብጨባ ‹‹ንሴብሖ ለእግዚአብሔር ስቡሐ ዘተሰብሐ›› እያሉ ጉባኤውን እግዚአብሔርን በዝማሬ አመስግነዋል፡፡
በአጠቃላይ ለሦስት ቀናት የተካሔደው የማኅበረ ቅዱሳን ፲፪ኛው ጠቅላላ ጉባኤ የእግዚአብሔር ጥበቃ ያልተለየው ጉባኤ ነበር፤ ማለትም ማኅበሩ የጉባኤውን ተሳታፊዎች የሚጠብቅ ኃይል አላሰማራም፡፡ ነገር ግን በእግዚአብሔር ቸርነት፣ በቅዱሳን መላእክት ተራዳኢነት ያለምንም መሰናክል በሰላም ሊጠናቀቅ ችሏል፡፡ ይህ ጉባኤ ከዚህ በፊት ከተካሔዱት ጉባኤያቱ በተለየ መልኩ ብፁዓን አበው የተገኙበት፤ በርካታ የጠቅላይ ቤተ ክህነት መምሪያ ሓላፊዎችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች የተሳተፉበት፤ ብዙ ቁም ነገሮች የተዳሰሱበትና አባላቱ የተደሰቱበት ልዩ ጉባኤ ነበር፡፡ ጠቅላላ ጉባኤው ውበት እንደኖረው ካደረጉት ነጥቦች መካከል እርስበርስ መደማመጥ፣ የተሳታፊዎቹ የነቃ ተሳትፎና ትሕትና፣ የአንድነት መንፈስና የምልዓተ ጉባኤው ጥንቃቄ የተሞላበት ውሳኔ ዋነኞቹ ሲኾኑ ለጉባኤው አስደሳች ክሥተት ከኾኑት መርሐ ግብራት ደግሞ በዘመናዊው ትምህርታቸው ከፍተኛ ውጤት አስመዝግበው የተሸለሙ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎች ሜዳልያዎቻቸውን ለማኅበሩ ማስረከባቸው አንደኛው ነው፡፡
ወስብሐት ለእግዚአብሔር፡፡