“ዐርገ ሰማያተ በዐምደ ደመና፤ በደመና ወደሰማይ ዐረገ” (ቅዱስ ያሬድ)

ዲያቆን ዐቢይ ሙሉቀን

ኢትዮጵያዊው ሊቅ ቅዱስ ያሬድ ይህን ቃል እንደተናገረው ዝማሬ በሚባለው የመጽሐፍ ክፍል   እናገኘዋለን። ሊቁ የጌታችንን የማዳን ጉዞ ከፅንሰቱ ጀምሮ እስከ ዕርገቱ ብሎም እስከ ዳግም ምጽአቱ ከብሉያት እና ከሐዲሳት እያጣቀሰ አምልቶና አስፍቶ ያስረዳበትን ቃል ስለዕርገቱ በተናገረው የምስጋና ክፍል ውስጥ እናገኘዋለን፤ ሙሉ ንባቡም እንዲህም ነው።

“ዐርገ ሰማያተ በዐምደ ደመና፤ ለድንግል ዘፈትሐ ማኅፀና፤ ለደቂቀ እስራኤል ዘአውረደ መና፤ ውእቱኬ ዘአድኃና ለሶስና እምእደ ረበናት፤ ዐርገ ሰማያተ በዐምደ ደመና፤ በደመና ወደ ሰማይ ዐረገ፤ የድንግልን ማኅፀን የፈታ፣ ለእስራኤል ልጆች መናን ያወረደ፤ ሶስናን ከረበናት እጅ ያዳነ በደመና ወደ ሰማይ ዐረገ፡፡” በዚህ ኃይለ ቃል ዐረገ የተባለው ማን ነው? በደመና ዐረገ የተባለውስ ምን ማለት ነው? የድንግልን ማኅፀን የፈታው፣ ለእስራኤል መናን ያወረደው፣ ሶስናን ከረበናት እጅ ያዳነው ማን ነው? የሚለውን እንመለከታለን።

ዐረገ የተባለው ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡ የእርሱ ወደሰማይ ማረግ የሌለበት ቦታ ኑሮ ካለበት ቦታ ወደሌለበት ቦታ ሄደ ማለት አይደለም፡፡ ነገር ግን የማዳን ሥራውን ፈጽሞ ወደባሕርይ አባቱ መመለሱን፤ የማዳን ሥራውን መፈጸሙን፤ በሥጋ በክብር ማረጉን ለመግለጽ ነው፡፡ (ዝማሬ ዘዕርገት)

ጌታችን ኢየሱስ በደመና ዐረገ መባሉ ሊቃውንት እንደሚነግሩን ደመና ክብሩና ልዕልናው በመሆኑ ነው። “ዘበእንተ ዕበይከ ትትሜሰል በደመና፤ ስለ ልዕልናህ በደመናት ትመሰላለህ” እያሉ ሊቃውንቱ ያመሰግኑታል። በሐዋርያት ሥራም “ወነሥአቶ ደመና ወዐርገ ሰማየ እንዘ እሙንቱ ይኔጽሩ ኀቤሁ፤ ደመናም ተቀበለችው፤ እነርሱም ወደእርሱ እያዩ ወደሰማይ ዐረገ” ተብሎ ተጽፏል። ነቢየ እግዚአብሔር ቅዱስ ዳዊትም “ዐርገ እግዚአብሔር በይባቤ ወእግዚእነ በቃለ ቀርን፤ እግዚአብሔር በዕልልታ ጌታችንም በመለከት ድምፅ ዐረገ” በማለት እንደነገረን በክብር በይባቤ መላእክት ማረጉን ያስረዳል። (ሐዋ.፩፥፱፤ መዝ.፵፮፥፭)

በሌላ መልኩ በደመና ዐረገ የተባለው ደመና እመቤታችን ድንግል ማርያም ናት፤ ከእርሷ  በነሣው ሥጋ ዐረገ ማለት ነው። ነቢየ እግዚአብሔር ኢሳይያስ “እነሆ እግዚአብሔር በፈጣን ደመና ተቀምጦ ወደግብፅ ይመጣል” ብሎ አስቀድሞ በትንቢቱ የተናገረላት ደመና እመቤታችን በመሆኗ ነው። ሊቁ ቅዱስ ያሬድም “ደመናሰ ዘይቤ ይእቲኬ ማርያም እንተ ጾረቶ ዲበ ዘባና፤ ደመናስ የሚላት አምላክን በጀርባዋ የተሸከመችው ማርያም ናት” በማለት ያስረዳል። ስለዚህ “በደመና ዓምድ ዐረገ” ሲል ከድንግል ማርያም በተዋሐደው ሥጋ ወደሰማይ ዐረገ ማለት ነው።  ከላይም እንደገለጽነው ዐረገ መባሉ በሥጋ እንጂ በመለኮቱማ ምሉዕ በኵለሄ፣ በሁሉም ቦታ፣ በሁሉም ጊዜ ምሉዕ ነው። (ኢሳ.፲፱፥፩)

ይህ በክብር በይባቤ መላእክት፣ ከማርያም በተዋሐደው ሥጋ በደመና ዐረገ የተባለው ማን ነው? ለሚለው ጥያቄ ሊቁ ቅዱስ ያሬድ ከብሉይ ከሐዲስ እየጠቀሰ እንዲህ ያስረዳናል።

ሀ. የድንግልን ማኅፀን የፈታው ነው። “ለድንግል ዘፈትሐ ማኅፀና፤ የድንግልን ማኅፀን የፈታው ነው።” እናታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በመላእክትም በሰውም አንደበት የተመሰከረላት፣ ጥንት ነቢያት ትንቢት የተናገሩላት፣ በኋላም ሊቀ መላእክት ቅዱስ ገብርኤል፣ የመጥምቀ መለኮት የቅዱስ ዮሐንስ እናት ቅድስት ኤልሳቤጥ የመሰከሩላት ዘለዓለማዊት ድንግል ናት። ከዚህች ድንግል ማኅፀኗን ዙፋን አድርጎ በኅቱም ድንግልና ተፀንሶ በኅቱም ድንግልና የተወለደው ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። ነቢዩ ኢሳይያስ “እነሆ ድንግል ትፀንሳለች፤ ወንድ ልጅንም ትወልዳለች፤ ስሙንም አማኑኤል ብላ ትጠራዋለች” በማለት እንደተናገረው ከድንግል ማርያም የተወለደው አማኑኤል ተብሎ በነቢዩ ትንቢት የተነገረለት እግዚአብሔር ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። (ኢሳ. ፯፥፲፬)

ለ. ለእስራኤል መናን ያወረደው ነው። ይህ በኅቱም ድንግልና ተፀንሶ በኅቱም ድንግልና የተወለደው ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለእስራኤል መና እያወረደ አርባ ዓመት ሙሉ በበረሃ እስራኤልን የመራው ነው። ነቢዩ ዳዊት “በልዑ ወጸግቡ ጥቀ ወኢያህጥዖሙ እምዘ ፈቀዱ፤ በሉ፤ እጅግም ጠገቡ፤ ለምኞታቸውም አላሳጣቸውም” ተብሎ የተናገረለት አምላክ ወልደ አምላክ በተዋሐደው ሥጋ ወረደ፤ ተሰደደ፤ ጾመ፤ ተራበ፤ ተሰቀለ፤ ሞተ፤ ተነሣ፣ ዐረገ እየተባለ ይነገርለታል። በቦታ የማይወሰን አምላክ ቦታ ተወሰነለትና ወረደ፤ ዐረገ እየተባለም ተነገረለት። ስለዚህ ይህ በክብር ዐረገ የተባለው ማን ነው? የሚል ሰው ካለ ጥንት እስራኤልን በበረሃ መና እያወረደ ሲመግብ የኖረው ዛሬም ለዘወትርም መግቦቱ ለዐይን ጥቅሻ ያህል እንኳን የማያቋርጠው እግዚአብሔር ወልድ ነው። (መዝ.፸፯፥፳፱)

ሐ. “ውእቱኬ ዘአድኃና ለሶስና እምእደ ረበናት፤ ሶስናን ረበናት እጅ ያዳናት ነው።” በትንቢተ ዳንኤል ተጽፎ እንደምናገኘው ይህቺ ሶስና መልከ መልካም ባለትዳር ለትዳሯም ታማኝ ነበረች። ነገር ግን የአይሁድ መምህራን ከመልከ መልካምነቷ የተነሣ በዝሙት ተነደፉና ለፈቃደ ሥጋቸው ጠየቋት፤ እርሷ ደግሞ ከእነርሱ ኃላፊነትና ሥልጣን ይልቅ ለእግዚአብሔር መገዛት መረጠችና ምኞታቸውን ለመፈጸም ፈቃደኛ አልሆነችም። በዚህ ጊዜ እነርሱ አጥፍተው ደግሞ ወነጀሏትና “ከወንድ ጋር አግኝተናታል” ብለው በአይሀድ ሸንጎ አቆሟት፤ እርሷም ወደ እግዚአብሔር ጸለየች። የለመኑትን የማይነሣው የነገሩትን የማይረሳው አምላካችን እግዚአብሔር መላኩን ልኮ ከረበናቱ እጅ አዳናት።

ሊቁ ቅዱስ ያሬድም ብሉዩን ከሐዲስ አስማምቶ እየጠቀሰ በደመና ወደሰማይ ያረገው፣ ጥንት ጀምሮ ጥበቃው ያልተለየን፣ በዚህም ሶስናን ከረበናት እጅ ያዳነ አምላክ ወልደ አምልክ እንደሆነ ያስረዳናል። ሶስና በእግዚአብሔር በመታመኗ ምንም እንኳን መምህር በመሆናቸው ተሰሚነትን የሚያገኙ ቢመስላቸውም፣ እንዳሰቡትም በአይሁድ የፍርድ ሸንጎ ቢያቀርቧትም እርሷ ግን እውነተኛ ዳኛ እግዚአብሔር እንዳለ በማመን ዐይኗን ወደእግዚአብሔር አቀናች። ነቢየ እግዚአብሔር ዳዊት “ቅሩብ እግዚአብሔርም ለየዋሐነ ልብ፤ እግዚአብሔር በልባቸው የዋሐን ለሆኑ ቅርብ ነው” ብሎ እንደነገረ፤ በቅዱስ ወንጌልም ልበ ንጹሐን ብፁዓን ናቸው፤ እግዚአብሔርን ያዩታልና” ተብሎ እንደተጻፈው በንጹሕ ልብ እግዚአብሔርን ስለለመነች ከመጣባት መከራ አዳናት። (መዝ.፴፫፥፲፰)

እኛም የሶስናን ልቡና ልብ ልናደርግ ይገባል፤ ካልሆነ ግን ከንቱ ጩኸት አይጠቅምም፤ እንደፈሪሳዊው በትምክህት መናገር ሳይሆን እንደ ቀራጩ በትሕትና ማንባት ከዐይን ጥቅሻ የፈጠነ ምላሽ ያሰጣል።

ምን አልባትም ሰዎች በማወቅም ይሁን ባለማወቅ ሊበድሉን ይችሉ ይሆናል። ግን እኛ እንደፈሪሳዊው ያለ ሳይሆን እንደ ቀራጩ በትሕትና የተሞላ ጩኸት እንጩኽ። እንደአይሁድ መምህራን ራስ አጥፍቶ ጥፋትን ወደሰው በሚሰነዝሩት አግባብ ሳይሆን እንደሶስና  “በእግዚአብሔር  ፊት ከምበድል ኃጢአት ሳልሠራ በእጃቸው መውደቅ ይሻለኛል” ማለት  ይኖርብናል። “ከዐንጀት ካለቀሱ እንባ አይገድም” እንደሚባለው ከልባችን ካለቀስን እና ከልባችን ከተመለስን የምንችለውን ማድረግ እንችላለን። ከልብ ካለቀስን ደግሞ እግዚአብሔር አምላካችን ዛሬም ሕያው በመሆኑ አብሮን አለና ጸሎታችንን ይሰማናል።

ዛሬ ሀገራችንም ሆነ ቤተክርስቲያናችን እጅግ ከባድ ፈተና ላይ ወድቃለች። ጥንት ክርስቶስ በመከራ የመሠረታት፣ ዛሬም መስቀሉን ተሽክማ ትገኛለች፤ በዚህም መከራዋ በዝቷል፡፡ እኛም ችግራችን በመብዛቱ በአንድ በኩል በሽታው ሲያሰቃየን በሌላ በኩል ደግሞ እርስ በእርሳችን መስማማት አቅቶናል። ጸሎታችንም “ሳል ይዞ ስርቆት፣ ቂም ይዞ ጸሎት” እንደሚባለው ሁኖብናል። ከዚህ ሁሉ መከራ ለእስራኤል መና ያወረደው፣ በድንግልና ተፀንሶ በድንግልና የተወለደው፣ ሶስናን ከረበናት እጅ የታደገው እግዚአብሔር አምላካችን እንዲሰውረን፣ መአቱን በትዕግሥት ቁጣውን በምሕረት እንዲመልስልን፣ የእግዚአብሔር አምላካዊ ቸርነት፣ የድንግል ማርያም አማላጅነት፣ የቅዱሳን ሁሉ ተራዳኢነት አይለየን፤ አሜን።

“ኦሪትና ነቢያት በእነዚህ በሁለቱ ትእዛዛት ጸኑ” (ማቴ.፳፪፥፵)

መድኅነ ዓለም ኢየሱስ ክርስቶስ በተናገረው በዚህ ኀይለ ቃል ፍቅር የሁሉም ነገር ማሰሪያና መደምደሚያ መሆኑን እንማራለን፡፡ ሰው የሕግ ሁሉ ማሰሪያ የሆነውን እርሱም ፍቅርን ገንዘብ ሊያደርግ እንደሚገባ ያስረዳበት አማናዊ ትምህርት በመሆኑም ሁሉም ሊያውቀውና ሊረዳው እንዲሁም በተግባር ሊፈጽመው የሚገባ ነው፡፡

“በመካከላችንም ሆኖ በመስቀሉ አስታረቀን፤ በልዩ ትንሣኤውም ሰውን ዳግመኛም ወደ ገነት መለሰው” (ቅዱስ ኤፍሬም)

አፈ በረከት ቅዱስ ኤፍሬም እመቤታችንን ለማመስገን አጅግ አብዝቶ ይለምን የነበረ፤ በእመቤታችን ጥሪም “አመስግነኝ” የተባለ ታላቅ ሰው ነበር፡፡ በድርሰቱ ምሥጢረ ሥላሴን፣ ምሥጢረ ሥጋዌን፣ ምሥጢረ ጥምቀትን፣ ምሥጢረ ቊርባንን፣ ምሥጢረ ትንሣኤ ሙታንን፣ በአጠቃላይ ሃይማኖትን ከምግባር፣ ነገረ ድኅነትን ከነገረ ቅዱሳን ጋር አስማምቶ የደረሰና ያስተማረ ታላቅ አባት ነው፡፡ በአባቶች የተመሰለውን ምሳሌና በነቢያት የተነገረውን ትንቢት አመሥጥሮና አራቅቆ የተረጎመ ሊቅም ነው፡፡ በመሆኑ ነገረ ድኅነትን በተናገረበት ምስጋናው “በመካከላችን ሆኖ በመስቀሉ አስታረቀን፤በልዩ ትንሣኤውም ሰውን ዳግመኛ ወደ ገነት መለሰው” የሚለውን ኃይለ ቃል እናገኛለን፡፡

ከዕለተ ትንሣኤ እስከ ዳግም ትንሣኤ

ከዕለተ ትንሣኤ እስከ ዳግም ትንሣኤ ባሉት ዕለታት በቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን የሚፈጸመው መንፈሳዊና ሐዋርያዊ አገልግሎት ልክ እንደ መጀመሪያው የትንሣኤ ሥርዓት ኾኖ ይከናወናል፡፡ ከትንሣኤ እሑድ ጀምሮ እስከ ሳምንቱ እሑድ ድረስ የሚገኙት ዕለታትም ‹ሰሙነ ፋሲካ› ወይም ‹ትንሣኤ› እየተባሉ ይጠራሉ፤ የየራሳቸው ምሥጢራዊ ስያሜም አላቸው፡፡

ዓርብ ስቅለት (የድኅነት ቀን)

ዓርብ ስቅለት የዕዳ ደብዳቤያችን በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ለመጨረሻ ጊዜ የተደመሰሰበት፤ ከአጋንንት አገዛዝ ነጻ የወጣንበት ዕለት ስለኾነ ‹የድኅነት ቀን› ይባላል፡፡

ሆሳዕና

ሆሼዕናህ ከሚል ከዕብራይስጥ ቃል የተገኘው ሆሳዕና ትርጓሜው እባክህ አሁን አድን ማለት ነው፡፡ ይህ ቃል በዘመነ ብሉይ በቀደምት ነቢያት ዘንድ የተለመደ ቃል ነው፡፡ አቤቱ እባክህ አሁን አድን፣ አቤቱ እባክህ አሁን አቅና፣ በእግዚአብሔር ስም የሚመጣ ቡሩክ ነው፡፡ (መዝ.፻፲፯፥፳፭-፳፮) የሆሳዕና በዓል ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በአህያ ጀርባ ተቀምጦ ወደ ኢየሩሳሌም ሲገባ የሚቀድሙትና የሚከተሉት ሕዝብ በተለይም አእሩግና ሕፃናት ሆሳዕና ለዳዊት ልጅ፣ በጌታ ስም የሚመጣ የተባረከ ነው፣ ሆሳዕና በአርያም በማለት ጌታችንን በክብር መቀበላቸው የሚታወስበት በዓል ነው፡፡ በዓሉም ሆሳዕና የሚለውን ስያሜ ያገኘው በዕለቱ ከተዘመረው መዝሙር ነው፡፡

ኒቆዲሞስ

በመዘነ ሥጋዌ የጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ወደ ምደር መምጣትና መሲሕ መባል ያልተቀበሉት በርካታ እስራኤላዊያን እርሱን እስከመስቀል እንደደረሱ ወንጌል አስተምሮናል፡፡ ሆኖም በፍጹም እምነት እስከ መጨረሻው ከተከተሉት ፈሪሳውያን አንዱ ኒቆዲሞስ ለታላቅ ክብር የበቃ ሰው ነው፡፡ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ይህን ታላቅ ሰው ለመዘከር የዐቢይን ጾም ሰባተኛ እሑድ በስሙ ሰይማ ታከብረዋለች፤ ተከታዮቿ ምእመናንም የእርሱን አሠረ ፍኖት እንዲከተሉ ትመክራለች፤ ታስተምራለችም፡፡

‹‹መኑ ውእቱ ገብር ኄር፤ ታማኝ አገልጋይ ማነው?›› (ማቴ.፳፬፥፵፭)

‹‹ገብር ኄር ወምእመን ዘበሁድ ምእምነ ኮንከ ዲበ ብዙህ እሰይመከ ባዕ ውስተ ፍስሐሁ ለእግዚእከ፤ አንተ ታማኝ ባሪያ በጥቂቱ ታምነሃል፤ በብዙ እሾምሃለሁ፤ ወደ ጌታህ ደስታ ግባ››

‹‹ስለማስመሰል ርኅራኄው ሰይጣንን ተጠንቀቀው›› ብፁዕ አቡነ ሺኖዳ ሣልሳዊ

የሰይጣን የማስመሰል ርኅራኄው የቱን ያህል አሳሳች እንደሆነ እንኳን አንረዳውም፡፡ ካሳተን በኋላም ያሳተን እርሱ መሆኑን መረዳት እየተሳነን ለውድቀታችን ሰዎችን፣ ዕድልን፣ ሁኔታዎችን እና ጊዜን ሰበብ እንድናደርግ ያደርገናል፡፡ ለዚህ ማሳያ የሚሆነው በተለይ በየጠበሉ ‹‹እከሊት ናት መድኃኒት ያደረገችብሽ፤ እከሌ ነው መድኃኒት ያደረገብህ›› እያለ ራሱን ሲያጋልጥ የምንሰማው የሰዎች ታሪክ እማኝ ነው፡፡ ‹‹ሐሰተኛ ነውና፤ የሐሰት አባትም ነው›› እንደተባለው፡፡ (ዮሐ. ፰፥፵፬) በዚህ ሐሰተኛነቱም አንዳንዶችን የአጋንንቱን ምስክርነት አምነው እንዲካሰሱ ባስ ሲል ወደከፋ ነገር እንዲደርሱ ያደርጋቸዋል፡፡

«አቤቱ፥ አምናላሁ፤ ነገር ግን አለማመኔን ርዳው» (ማር.፱፥፳፬)

«እምነትስ፣ ተስፋ ስለምናደርገው ነገር የምታረጋግጥ፥ የማናየውንም ነገር የምታስረዳ ናት» (ዕብ. ፲፩፥፩) እንደተባለው ሰው ተስፋን ከአምነት ያገኛል፡፡ አዳም ቢበድልም እንኳን ቸሩ አምላክ እግዚአብሔር በኋላ ዘመን ከልጅ ልጁ ተወልዶ እንደሚያድነው ቃል በጋባለት ጊዜ ተስፋ አግኝቷል፡፡ የመዳኑን ነገር በእምነቱ ተስፋ ሆነለት፡፡ እምነት ለእግዚአብሔር ያለንን ፍቅር የምንገልጥበት፣ እርሱን ደስ የምናሰኝበት የሕይወት መሠረት ነው፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ይህን ሲያስረዳ «ያለ እምነትም እግዚአብሔርን ደስ ማሰኘት አይቻልም» ብሏል፡፡ (ዕብ.፲፩፥፮)