‹‹ለነገ አትጨነቁ፤ ነገ ለራስዋ ታስባለችና›› (ማቴ.፮፥፴፬)
ጭንቀት እንደ የማኅበረሰቡ አኗኗርና የኑሮ ፍልስፍና የሚሰጠው ትርጉም ከቦታ ቦታና ከሰው ሰው ይለያያል። የሕዝቦቻቸው መሠረታዊ ፍላጎቶች ባልተሟሉባቸው አንዳንድ ሀገራት ምጣኔ-ሀብታዊ አለመረጋጋት በብዛት የሚስተዋል የጭንቀት መንሥኤ ነው። በአንጻሩ ብዙዎቹ ዜጎቻቸው የቅንጦት ሕይወት በሚመሩባቸው ‹ሥልጡን› ሀገራት ደግሞ፥ ደስታ ይገኝባቸዋል ተብለው የሚጀምሩ የዝሙት፣ የሱስ፣ የዘፈን… የመሳሰሉት እኩይ ተግባራት ከጊዜያት በኋላ እግዚአብሔርን ፍለጋ በሚቃትተውና እውነተኛ ደስታ ምን ማለት እንደሆነ አንጠርጥሮ በሚያውቀው ውሳጣዊ ኅሊናቸው ዕረፍት የለሽ ሙግት የተነሣ ደስታ ሰጪነታቸው አብቅቶ መዳረሻቸው ጭንቀት ይሆናል። በጣም የሚያሳዝነው ደግሞ ለዚህ ኅሊናዊ ምሪት የሚሰጡት መልስ በአብዛኛው አሁንም ተቃራኒውን መሆኑ ነው። ‹‹ለምንድነው የምኖረው?›› ለሚለው ጥያቄያቸው መልሳቸው ‹‹ለምንም!›› የሚል ይሆንና የሕይወታቸውን ፍጻሜ ያበላሸዋል።…