ዕውቀት ሥጋዊ ወመንፈሳዊ
ዕውቀት ‹ዖቀ› ከሚለው የግዕዝ ግሥ የተገኘ ነው፤ ትርጓሜውም ‹ዐወቀ› ወይም አንድን ነገር በአግባቡ መረዳትንና መገንዘብን እንዲሁም አንድን ነገር ለመፈጸምና ለማከናወን የሚያስችለንን ችሎታ የሚገልጽ ነው፡፡ በሌላ መልኩ ዕውቀት አንድን ችግር ለማስወገድ የሚያስችል አቅም ወይም ችሎታ መሆኑ ይታመናል፡፡ በግሪኩ ግኖስ የሚል ትርጉም ያለው ሲሆን ዕውቀትን የሁሉም ነገር መፍቻ ቁልፍ አድርጎ የመመልከት ዝንባሌም ያለው ሲሆን ሰው በዕውቀቱ የዘለዓለም ሕይወትን ድኅነትን እንደሚያገኝ በግኖስቲኮች ዘንድ ይታመናል፡፡ በአንጻሩ ዕውቀት የላቸውም ተብለው የሚታሰቡ ሰዎች አላዋቂዎች ወይም አግኖስ ተብለው የሚጠሩ ሲሆን እነዚህ አካት ያልበራላቸው በጨለማ ውስጥ ያሉ እንደሆነ በግሪክና በሮማ ሥልጣኔ ዘመን ይታመን እንደነበር እንገነዘባለን፡፡