‹‹ጠፈር ይሁን፤ ውኃም ከውኃ ይለይ›› (ዘፍ.፩፥፮)
እግዚአብሔር በዕለተ ሰኑይ በቀዳሚት ሰዓት ሌሊት ‹‹ጠፈር ይሁን፤ ውኃም ከውኃ ይለይ›› ብሎ ቢያዘው ከዚህ እስከ ብሩህ ሰማይ ሞልቶ የነበረውን ውኃ ከአራት ከፍሎ አንድን እጅ በመካከል ከምሥራቅ እስከ ምዕራብ ከሰሜን እስከ ደቡብ ዘረጋው፡፡ (ዘፍ.፩፥፮) እንደ ቤተ መንግሥት አዳራሽ ወደ ላይ ጠበብ አድርጎ እንደ ብረት አጸናው፤ ይህ የምናየው ሰማይ ነው፤ ጠፈር ይባላል፡፡ ጠፈር ማለትም ሥዕለ ማይ (የውኃ ሥዕል) ማለት ነው፡፡ እግዚአብሔር ጠፈርን መፍጠሩ ስለምንድነው? ቢሉ ረቡዕ የሚፈጥረውን ፀሐይን ሊያቀዘቅዝ ሰውም ይህን እያየ ሰማያዊ ርስት እንዳለው እንዲያውቅ ነው፡፡ እጅግም ነጭ ከሆነ ዓይን እየበዘበዘ እያንጸባረቀ ለሰው የደዌ ምክንያት ይሆን ነበርና፡፡ በድስት ያለ ውኃ በሚታጠብ ጊዜ የእሳት ማቃጠል ሲበዛበት እንደሚሰበር ጠፈርም የፀሐይ ማቃጠል ሲበዛበት እንደ ሸክላው በፈረሰ ነበርና እንዲያጸናው ሐኖስን በላይ አደረገለት፡፡ (መጸሐፈ ሥነ ፍጥረት ገጽ ፳-፳፫