ማኅበረ ቅዱሳን ከአዲሱ የሰንበት ትምህርት ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ሓላፊ ጋር ስለ ቀጣዩ የአገልግሎት ዘመን ተወያየ፡፡
ኅዳር 8/2004 ዓ.ም
በዲ/ን ኅሩይ ባየ

ኅዳር 8/2004 ዓ.ም
በዲ/ን ኅሩይ ባየ

በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ጠያቂነትና በግብጽ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን መልካም ፈቃድ ግብጻውያን ኦርቶዶክሳዊ የሕክምና ባለሙያዎች በኢትዮጵያ ነጻ አገልግሎት ሰጡ፡፡
የሕክምና ቡድኑ አባላት ከ27/2/2004 ዓ.ም – 1/3/2004 ዓ.ም ድረስ በአዲስ አበባ ውስጥ በሚገኙ ሆስፒታሎች በተለያዩ የሙያ ዘርፎች አገልግሎት እንደሰጡ ለማወቅ ተችሏል፡፡ ሃያ ሦስት አባላት ያሉት የሕክምና ቡድን አባላት መሪ የሆኑት ዶክተር ጆርጅ ታድሮስ እንደተናገሩት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን የአገልግሎት ጥሪ በቤተ ክርስቲያናቸው በኩል እንደደረሳቸው ሁሉም የተመረጡት ልዑካን ወደ ኢትዮጵያ ለመምጣት ሙሉ ፈቃደኛ ነበሩ፡፡
የሕክምና ቡድኑ አባላት መቀመጫቸው ሰሜን አሜሪካ፣ ካናዳ፣ እንግሊዝ ቢሆንም ቤተ ክርስቲያናቸው ለአገልግሎት በምትጠራቸው ወቅት ፈጣን ምላሽ ለመስጠት መምጣታቸውን አስረድተዋል፡፡በተለያዩ የዓለማዊ ሥራ ቦታ የተሰማሩ የኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያን ልጆች በሙያቸው ቤተ ክርስቲያንን ለማገዝ ሃይማኖት ሳይለዩ ለሕዝቦች ሁሉ ቀና ግልጋሎት ለመስጠት መትጋት እንደሚገባቸውም የቡድን መሪው ገልጸዋል፡፡
ቤተ ክርስቲያን የብዙኃን መጠጊያ ነች ያሉት የቡድን መሪው በኢትዮጵያ የግብጽ ኦርቶዶክሳዊ ሐኪሞች የሰጡት የሕክምና እርዳታ ወደፊት ከማኅበረ ቅዱሳንና ከመሰል የቤተ ክርስቲያን አካላትና ባለሙያዎች ጋር በመተባበር ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል፡፡የልዑካን ቡድኑ አባላት በኢትዮጵያ ቆይታቸው የሕዝቡን ክርስቲያናዊ ፍቅር በነጻነት ሃይማኖቱን የመከተል እድልና እንግዳ ተቀባይነቱ እንዳስደሰታቸው ተናግረዋል፡፡
ኅዳር 6/2004 ዓ.ም
በፈትለወርቅ ደስታ
በኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ በሰ/ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ማኅበረ ቅዱሳን “የሰለሞን ምቅናይ በተክሌ ዝማሜ በሚል ርእስ የተዘጋጀ ምስል ወድምጽ /ቪሲዲ/ ቅዳሜ ኅዳር 2/2004 ዓ.ም በጠቅላይ ቤተ ክህነት አዳራሽ ተመረቀ፡፡
በምረቃው ላይ ብፁዕ አቡነ ሰላማ የአክሱም ጽዮን ሊቀ ጳጳስ፣ ብፁዕ አቡነ እንድርያስ የደቡብ ጐንደር ሊቀ ጳጳስና ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያንና ተጋባዥ እንግዶች ተገኝተዋል፡፡
የማኅበሩ ሰብሳቢ ቀሲስ ዶ/ር ሙሉጌታ ስዩም በምረቃው ላይ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉ ሲሆን ቤተ ክርስቲያን የራሷ የሆነውን የዜማ፣ የአቋቋም ሥርዓት ጠብቃ በእንዲህ ዓይነት መልኩ ለምእመናን እንዲዳረስ ማኅበሩ የበኩሉን ድርሻ እንደሚወጣና ወደፊትም ከዚህ በተሻለ መልኩ እንደሚሠራ ገልፀዋል፡፡ ብፁዕ አቡነ እንድርያስም በዕለቱ “ምቅናይ” በሚል ርዕስ ሰፋ ያለ ትምህርት ሰጥተዋል፡፡ አያይዘውም ይህ የቤተ ክርስቲያን ቅርስና ሀብት ዜማ ዝም ብሎ የተገኘ ሳይሆን ሊቃውንቱ እድሜያቸውን ሙሉ ሲማሩት የኖሩት መሆኑንና ይህን የቤተ ክርስቲያን ሀብት ደግሞ በእንዲህ ዓይነት መልኩ ለትውልድ የማስረከብ ኃላፊነት የሁሉም የቅድስት ቤተ ክርስቲያን ልጆች ኃላፊነት መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በዕለቱ በየኔታ ተክሌ ሲራክ አማካይነት በተክሌ አቋቋምና ዝማሜ ታሪክ ላይ ጥናታዊ ጽሑፍ የቀረበ ሲሆን ይህ የተክሌ ዝማሜ በደብረ ታቦር ኢየሱስ ገዳም እስከ አሁን ድረስ የተክሌ አቋቋም ጉባኤ ምስክር ሆኖ እንደሚያገለግል ገልጸዋል፡፡
በመጨረሻም ብፁዕ አቡነ እንድርያስ ይህ ጅማሮ ጥሩ መሆኑን ገልፀው ይህ ዝማሜ የሊቃውንቱ ቢሆንም ለእይታ የበቃው በማኅበረ ቅዱሳን አማካይነት መሆኑና ማኅበሩም በዚህ ዙሪያ ከፍተኛ ኃላፊነትን ወስዶ የድርሻውን እየተወጣ እንደሆነ ገልጸው ነገር ግን ገና አልተነካም ወደፊት ብዙ ይጠበቃል ብለዋል፡፡
ቪሲዲው የተዘጋጀው በማኅበረ ቅዱሳን በሙያ አገልግሎት እና አቅም ማጎልበቻ ክፍል ዘርፍ ፕሮጀክት ተጠንቶና ሊቃውንቱ መክረውበት ነው፡፡
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በሰንበት ትምህርት ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ማኅበረ ቅዱሳን በኤሌክትሮኒክስ ሚዲያ ክፍል የተዘጋጁ 3 ሺህ የሚሆኑ የምስልና የድምጽ ሲዲዎች ኅዳር 8 ቀን 2004 ዓ.ም በማኅበሩ ጽ/ቤት እንደሚሠራጭ የምክረ ሐሳቡ አስተባባሪ ኢንጂነር ሙሉጌታ ጌትነት አስታወቁ፡፡
ኢንጅነር ሙሉጌታ እንደገለጡት የምስልና የድምጽ ሲዲዎችን ለማግኘትና ለማሠራጨት ምንም ዐይነት ትርፍ ታሳቢ ሳይደረግ የሲዲውን ዋጋ ብቻ በመሸፈን ማግኘት ይቻላል፡፡ በማያያዝም የሥርጭቱ ዋና ዓላማ ስብከተ ወንጌልን በተፋጠነ መንገድ ለምእመናን ማዳረስ ሲሆን በገበያ ላይ የሚገኙት የምስልና የድምጽ ሲዲዎች የምእመናንን ምጣኔ ሀብት የሚጎዱ በመሆናቸው በቀላሉ ቃለ እግዚአብሔር የሚስፋፋበትን መንገድ ለማመቻቸት፣ የተሐድሶ መናፍቃን ስሑት ትምህርቶች በሕዝበ ክርስቲያኑ ሰርገው ስለገቡ ትክክለኛ ኦርቶዶክሳዊ አስተምህሮ ያላቸውን የስብከት ሲዲዎች ምእመናን እንዲያገኙና ስለ ሃይማኖታቸው እንዲያውቁ ለመደገፍ፣ በከተማ የሚኖሩ ጥቂት ምእመናን የመካነ ድር አገልግሎት ተጠቃሚዎች ቢሆኑም አገልግሎቱ ውድና ዝቅተኛ ፍጥነት ስላለው የምስልና የድምጽ ዝግጅቶችን መመልከትና መስማት ስለማይችሉ ችግሩን አስወግዶ ተደራሽነትን ለማስፋፋት እንዲቻልና የቪሲዲ አገልግሎት ከገጠር እስከ ከተማ እየተስፋፋ በመምጣቱ ንጹህ የቤተ ክርስቲያን ትምህርቶችን ለሁሉም እንዲዳረስ ለማድረግ እንደሆነ አስተባባሪው አስገንዝበዋል፡፡
ስርጭቱ እስከ ሦስት ዙር የሚቀጥል ሲሆን በመጀመሪያው ዙር ለአዲስ አበባ ምእመናን ይከፋፈላል፡፡ በሁለተኛውና በሦስተኛው ዙር የሚከናወኑት ስርጭቶች ደግሞ ከአዲስ አበባ ውጭ ወደ ማእከላትና ግንኙነት ጣቢያዎች እንደሚላኩ ለማወቅ ተችሏል፡፡ ስርጭቱን በተመለከተ ራሱን የቻለ ኮሚቴ እንደተዋቀረም ተጠቁሟል፡፡
የምስልና የድምጽ ትምህርቶች የተዘጋጁት በማኅበረ ቅዱሳን የምስልና የድምጽ ክምችት ክፍል በተለያዩ ዘመናት የተቀረጹ የሊቃውንት ትምህርቶች፣ በኤሌክትሮኒክስ ሚዲያ ክፍል በተለያዩ መርሐ ግብሮች የተቀረጹና በአዲስ አበባ ራጉኤል ቤተ ክርስቲያን ሰ/ት/ቤት የተቀረጹ ትምህርቶች እንደሆኑ ተገልጧል፡፡ ዝግጅቱ ከትርፍ ነፃ በሆነ መልኩ ተዘጋጅቶ የሚሠራጭ በመሆኑ ምእመናን በቀላሉ እንዲጠቀሙበት ማኅበሩ ጥሪውን ያስተላልፋል ሲሉ አስተባባሪው አሳስበዋል፡፡
አዘጋጅ፡- በኢ/ኦ/ተ/ቤተ ክርስቲያን ሰ/ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ማኅበረ ቅዱሳን ሙያ አገልግሎትና አቅም ማጎልበቻ ዋና ክፍል
ቦታ፡-ጠቅላይ ቤተ ክህነት አዳራሽ
ሰዓት፡- ቅዳሜ ኅዳር 02/03/2004 ዓ.ም ከቀኑ 7፡30 ጀምሮ

{gallery count=1 width=350 height=300 counter=1 links=0 alignment=center animation=3000}smg30{/gallery}
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን 30ኛው መደበኛ መንፈሳዊ ጉባኤ ጥቅምት 7 ቀን 2004 ዓ.ም በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት የስብከተ ወንጌል አዳራሽ ከጠዋቱ 3 ሰዓት በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ጸሎተ ቡራኬ ተጀምሯል፡፡
የ48ቱ አህጉረ ስብከት ሊቃነ ጳጳሳት በከፊል የተገኙ ሲሆን ሁሉም የሀገር ውስጥ ሥራ አስኪያጆች ፣የመንበረ ፓትሪያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት የመምሪያ ሓላፊዎች ፣በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገር የሚገኙ የአድባራትና ገዳማት አስተዳዳሪዎች ፣ በኢትዮጵያ የስብከተ ወንጌልና ሐዋርያዊ ተልዕኮ መምሪያ ፣ የሕፃናትና ቤተሰብ ጉዳይ ድርጅት፣ የልማትና ክርስቲያናዊ ተራድኦ ኮሚሽን ሓላፊዎች የጉባኤው ተሳታፊዎች ናቸው።
ቅዱስነታቸው በጸሎተ ወንጌል ጉባኤውን ባርከው ከከፈቱ በኋላ በሰጡት ቃለ ምእዳን ሰው መግባባት የሚችለው እግዚአብሔር በሰጠው አእምሮ ሲጠቀምበትና በፈሪሃ እግዚአብሔር ሲኖር ነው። ፈሪሃ እግዚአብሔር ካለ ሰላም፣ ፍቅር፣ መግባባት፣ መዋደድና መከባበር ይኖራል ብለው በሰላማዊ መንገድ ሓላፊነትን መወጣት እንዲገባ አሳስበዋል፡፡
ቅዱስ ፓትርያርኩ አያይዘው በ2003 ዓ.ም በሞት የተለዩንን ብፁዕ አቡነ በርናባስን፣ ብፁዕ አቡነ ይስሐቅንና ብፁዕ አቡነ ሚካኤልን በጸሎት እናስባቸው ብለው ጸሎት አድርሰዋል፡፡
ሊቀትጉሃን ኃይለ ጊዮርጊስ ዳኜ፣ መጋቤ ሰናያት አሰፋ ስዩም፣ ሊቀ ስዩማን ራደ አስረስ፣ ንቡረ እድ ተስፋዬ ተወልደና መጋቤ ሐዲስ ይልማ ቸርነት የአቋም መግለጫ ረቂቅ እንዲያዘጋጁ ብፁዕ አቡነ ፊልጶስ ለጉባኤው አቅርበው ጉባኤው የተመረጡትን አርቃቂዎች በሙሉ ድምጽ አሳልፈዋል፡፡
ከረፋዱ 4 ሰዓት ጀምሮ ለ45 ደቂቃ ያህል የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽ/ቤት አጠቃላይ ሪፓርት በብፁዕ አቡነ ፊልጶስ የጠቅላይ ቤተ ክርህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ፣ የኢሉባቡርና ጋምቤላ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስና በንቡረ እድ ኤልያስ አብርሃ የጠቅላይ ቤተ ክህነት ምክትል ሥራ አስኪያጅ ቀርቧል፡፡ ከመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ሪፖርት ቀጥሎ የትግራይ ማዕከላዊ ዞን /አክሱም/ ሀገረ ስብከት ሪፖርት መቅረብ የነበረበት ቢሆንም የጋምቤላ ሀገረ ስብከት ሥራ አስኪያጅ ለሌላ ተልእኮ ወደ ሱዳን ሀገረ ስብከት መሔድ እንዲችሉ ፈቃድ ጠይቀው ቅድሚያ ሪፖርታቸውን አቅርበዋል፡፡
በጠዋቱ መርሃ ግብር የትግራይ ማዕከላዊ ዞን፣ የሲዳማ፣ የሰሜን ጎንደር፣ የምሥራቅ ሀረርጌ፣ ሀገረ ስብከት ሪፖርት ቀርቧል፡፡ ከሰዓት በኋላ በተያዘው መርሃ ግብር ከቀኑ 8 ሰዓት እስከ 11፡30 ድረስ የጅማ ዞን ሀገረ ስብከት፣ በትግራይ ክልል ሀገረ ስብከት የመቀሌ፣ የኢሊባቡር፣ የድሬዳዋ፣ የጋሞጎፋ፣ የሰሜን ወሎ፣ የባሌ፣ የደቡብ ጎንደርና የምሥራቅ ወለጋ አህጉረ ስብከት ሪፖርት ቀርቧል፡፡
ረቡዕ ጥቅምት 8 ቀን 2004 ዓ.ም ከጠዋቱ 3 እስከ 6፡30 በነበረው መርሐ ግብር የአርሲ፣ የትግራይ ምሥራቅ /አዲግራት/፣ የምዕራብ ጎጀም፣ የከፋ ቦንጋ፣ የሰሜን ሸዋ፣ የአሶሳና የደቡብ ወሎ ሀገረ ስብከት ሪፖርት ቀርቦ እንዳበቃ የቆሜ አቋቋም ሊቃውንት ወረብ አቅርበዋል፡፡
በሊቃውንቱ የቀረበው ወረብ እንደተጠናቀቀ የምሥራቅ ሸዋ ሀገረ ስብከት ፣ የምሥራቅ ጎጃም፣ የምዕራብ ሐረርጌና የትግራይ ደቡባዊ ዞን /ማይጨው/ አህጉረ ስብከት ሪፖርት በንባብ ተሰምቷል፡፡
ከሰዓት በኋላ በተያዘው መርሃ ግብር የደቡብ ኦሞ፣ የሰሜን ምዕራብ ሸዋ የሰላሌ ሀገረ ስብከት የሐዲያና ስልጤ፣ የዋግ ሕምራ፣ የምዕራብ ሸዋ፣ የአፋር፣ የአዊ ዞን፣ የሶማሊያ፣ የምዕራብ ወለጋ፣ የትግራይ ሰሜናዊ ምዕራብ ዞን ሽሬ ሀገረ ስብከትና የትግራይ ሰሜናዊ ምዕራብ ዞን ሽሬ ሀገረ ስብከትና የጉራጌ ሀገረ ስብከት ሪፖርት ከቀረበ በኋላ ውይይት ተካሒዷል፡፡
30 ዓመት ያስቆጠረው የሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ ካሳለፈው ረዥም ጉዞ ጋር ሲነጻጸር የሚጠበቅበትን ውጤት እያስመዘገበ እንዳልሆነ በመንበረ ፖትርያርክ ጠቅላይ ጽ/ቤት የቀረበው ሪፓርት ያስረዳል፡፡
አጠቃላይ ጉባኤው እስከ ጥቅምት 11 ቀን 2004 ዓ.ም የሚቀጥል ሲሆን ለቤተ ክርስቲያን የሚጠቅሙ ውይይቶችና የውሳኔ ሐሳቦች እንደሚቀርቡበት ይጠበቃል፡፡
የኢትዮጵያን ዕሥራ ምዕት ምክንያት በማድረግ በቤተ ክርስቲያኒቱ ሊቃውንት “የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስትያን ታሪክ ከልደተ ክርስቶስ እስከ 2000 ዓ.ም” በሚል ርእስ የተዘጋጀው መድበል ይህንኑ ሐሳብ ሲያጠናክር፤ “ቅዱስ አባ ሰላማ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ መንበረ ጵጵስናውን አክሱም ላይ አድርጎ በሀገራችን የወንጌልን ብርሃን በሰፊው ስለገለጠ ከሣቴ ብርሃን ተባለ” ይልና “በዚሁ በአራተኛው መቶ ክፍለ ዘመን የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን በዓለም አቀፍ ደረጃ የታወቀች ብሔራዊት ቤተ ክርስቲያን ለመሆን መብቃቷን ታሪክ ያስረዳል” ይላል፡፡
ለስም አጠራሩ ክብር ይግባውና ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደዚህ ዓለም በመጣበት ወቅት ቅድስት ቤተ ክርስቲያንን መሥርቶአል፡፡ ቅዱሳን ሐዋርያቱን “እኔን ማን ትሉኛላችሁ?” ብሎ በጠየቃቸው ጊዜ “አንተ ክርስቶስ የሕያው እግዚአብሔር ልጅ ነህ” ብሎ ቅዱስ ጴጥሮስ መልሶ ነበር፡፡ ከዚህም በኋላ “አንተ ዓለት ነህ በዚህችም ዓለት ላይ ቤተ ክርስቲያኔን እሠራታለሁ፤ የሲኦልም ደጆች ሊያናውጿት አይችሉም፡፡” በማለት ቤተ ክርስቲያንን በሐዋርያት መሠረት ላይ መሠረተ/ማቴ.16÷16-18/፡፡
ይህ ሐዋርያ በመልእክታቱ ምእመናንን ሲገሥጽና ሲመክር ሲያስተምር የኖረ ሲሆን በሁለተኛይቱ መልእክቱ ላይ ግን ለዚህ ጽሑፍ መነሻ የሆነ ኃይለ ቃልን ጽፏል፡፡ “ስለዚህ እነዚህን ነገሮች ምንም ብታውቁ በእናንተም ዘንድ ባለ እውነት ብትጸኑ ስለ እነዚህ ዘወትር እንዳሳስባችሁ ቸል አልልም፡፡ ሁል ጊዜም በዚህ ማደሪያ ሳለሁ በማሳሰቤ ላነቃችሁ የሚገባኝ ይመስለኛል፤ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንዳመለከተኝ ከዚህ ማደሪያዬ መለየቴ ፈጥኖ እንዲሆን አውቃለሁና፡፡ ከመውጣቴም በኋላ እነዚህን ነገሮች እንድታስቡ በየጊዜው ትችሉ ዘንድ እተጋለሁ” /2ኛጴጥ. 1÷13-15/
ብታውቁም፤ ብተጸኑም ማሳሰቤን ቸል አልልም!
ቅዱስ ጴጥሮስ በመልእክታቱ ስለ ክርስቶስ የባሕርይ አምላክነትና ስለ ሰው ልጅ ብሎ ስለተቀበለው መከራ፣ ክርስቲያኖች ሊኖራቸው ስለሚገባ መንፈሳዊ አኗኗር፣ አለባበስ፣ ስለ ጋብቻና ቤተሰባዊ ጉዳዮች፣ በምእመናን ላይ ስለሚመጡ መከራዎችና የዲያብሎስ ውጊያዎች፣ ድል ሲያደርጉም ስለሚያገኙት ጸጋና ዋጋ፣ ስለሚደርሱበት መዓርግ በአጠቃላይ በቀላሉ ተዘርዝሮ የማያልቅ ሰፊ ትምህርትን በመልእክቱ አስተምሯል፡፡ ይሁንና ሐዋርያው አውቀውታል፣ ጸንተዋል ብሎ ማሳሰቡን አላቆመም፡፡ ሰው ከመንገድ የሚስተው በእውቀት ጉድለት ብቻ አይደለም፡፡ እያወቁ መሳት፣ ጸናሁ ሲሉም መጥፋት አለ፡፡ ስለዚህም “አሳስባችሁ ዘንድ ቸል አልልም፡፡” አለ፡፡ ቅዱስ ጴጥሮስ መንጋውን ጠብቅና አሰማራ የተባውን አደራ የማይረሳ፣ በጥበቃ ተሰላችቶ ቸል የማይል፣ ትናንት የበሉት የጠጡት ይበቃቸዋል የማይል በመሆኑ ያውቁታል ብሎ ከመናገር ሳይቆጠብ “ዘወትር እንዳሳስባችሁ ቸል አልልም፡፡” አለ፡፡
በዚህ ማደሪያ ሳለሁ!
ሥጋ የነፍስ ማደሪያ ናት፤ አዳሪዋ ነፍስ ከማደሪያዋ ሥጋ ስተለይ ሰው ያን ጊዜ ሞተ ይባላል፡፡ “ከነፍስ የተለየ ሥጋ የሞተ ነው” እንዲል /ያዕ.2÷26/ ጻድቁ ኢዮብም “ይህ ቁርበቴም ከጠፋ በኋላ÷ በዚያን ጊዜ ከሥጋዬ ተለይቼ እግዚአብሔርን እንዳይ አውቃለሁ፡፡” ኢዮ.19÷26/ ያለው ሥጋ ጊዜያዊ ማደሪያ መሆኑን ሲያስረዳና ራሱን ከነፍስ አንጻር አድርጎ በሞት ሥጋውን ጥሎ እንደሚሄድ ሲናገር ነበር፡፡
ቅዱስ ጴጥሮስ “በዚህ ማደሪያዬ ሳለሁ በማሳሰቤ ላነቃችሁ ይገባኛል፡፡” ሲል በሥጋዬ ሳለሁ፣ ነፍሴ ሳትወሰድ ማለቱ ነበር፡፡ ቅዱስ ጴጥሮስን ቀሪ ዕድሜውን በችኮላ የሚጠቀመው ለሌላ ሥጋዊ ተርታ ጉዳዮች ሳይሆን ምእመናን ያስተማረውን ትምህርት እንዳይገድፍና አንዳይጠፉበት በማሳሰብ ማንቃት ነው፡፡
ጌታዬ እንዳመለከተኝ መለየቴ ፈጥኖ እንዲሆን አውቃለሁ!
“በእግዚአብሔር ፊት የቅዱሳኑ ሞት የከበረ” ስለሆነ ሞት ለቅዱሳን ድንገተኛና ያልተጠበቀ አይሆንባቸውም፡፡ እርግጥ ነው ሰው ሁሉ ሟች እንደ ሆኑና የሞትን አይቀሬነት በመጥቀስ ሁሉም ሰው እንደሚሞት ያውቃል ሊባል ይችላል፡፡ ቅዱሳን ግን የሚሞቱ መሆናቸውን የሚያውቁት ሞት አይቀርም ብለው ሳይሆን የሚሞቱበትን ጊዜና ሁኔታ ለመረጣቸው ለባሪያዎቹ የሚያደርገውን የማይሠውር እግዚአብሔር ገልጣላቸው ነው፡፡ የሚከተሉት የሊቀ ነቢያት ሙሴንና የቅዱስ ጳውሎስን ንግግሮች እንመልከት፡-
“እኔ ግን በዚህች ምድር እሞታለሁ ዮርዳኖስንም አልሻገርም” /ዘዳ.4÷22/
“በመሥዋዕት እንደሚደረግ የእኔ ሕይወት ይሠዋልና የምሄድበትም ጊዜ ደርሷል” /2ኛጢሞ.4÷6/
እነዚህ ታላላቅ ቅዱሳን የሚሞቱ መሆናቸቸውን ብቻ ሳይሆን የሚሞቱበትን ቦታ ጊዜ አስቀድመው መናገራቸው ከእግዚአብሔር ስለተነገራቸው ነው፡፡ የቅዱሳን አባቶቻችንን እና የቅዱሳት እናቶቻችንን ገድላት ስንመረምር ቅዱሳን ዕለተ እረፍታቸው ቀድሞ በእግዚአብሔር እንደሚነገራቸው እንረዳለን፡፡
ቅዱስ ጴጥሮስም ሰው እንደመሆኑ “መሬት ነህና ወደ መሬት ትመለሳለህ” ብሎ ጌታ ለሁሉ ካመለከተው ጥሪ በተጨማሪ ከቅዱሳን አንዱ እንደመሆኑ ከመሞቱ በፊት እንደሚሞት ያውቅ ነበር፡፡ ጌታችን ከዕርገቱ በፊትና ከዕርገቱ በኋላ ሁለት ጊዜ ተገልጦ ስለሞቱ ነግሮታል፡፡
ከዕርገቱ በፊት ከላይ የጠቀስነውን የእረኝነት አደራ ከሰጠው በኋላ “እውነት እውነት እልሃለሁ አንተ ጎልማሳ ሳለህ ወገብህን በገዛ ራስህ ታጥቀህ ወደምትወደው ትሄድ ነበር፤ ነገር ግን በሸመገልህ ጊዜ እጆችህን ትዘረጋለህ ሌላውም ያስታጥቅሃል ወደማትወደውም ይወስድሃል፡፡” ብሎታል፡፡ ወንጌልን ጽፎ በብዙ ቦታዎች የጻፈውን ሲተረጉምና ሲያትት የምናገኘው ቅዱስ ዮሐንስ ወንጌላዊ ትርጓሜን ሳንሻ ንባቡ ላይ “በምን ዓይነት ሞት እግዚአብሔርን ያከብር ዘንድ እንዳለው ሲያመለክት ይህን አለ፡፡” ብሎ የጌታን ንግግር ትርጓሜ አስከትሎ ጽፎልናል፡፡
በእርግጥም ቅዱስ ጴጥሮስ በሸመገለ ጊዜ እጆቹን በተዘቀዘቀ መስቀል ላይ ዘርግቶ ቁልቁል መሰቀል ትንቢተ ክርስቶስን ፈጽሟል፡፡
ጌታችን ከዐረገ በኋላ ደግሞ ቅዱስ ጴጥሮስ በሮም ሲያስተምር “ልበ ንጹሖች ብጹዓን ናቸው፡፡” ብሎ ባስተማረው ትምህርት ሚስቶቻችንን አሸፈተብን ያሉ ሰዎች ተነሡበት፡፡ በዚህን ወቅት ሴቶቹ ተማክረው ቅዱስ ጴጥሮስ እንዲሸሽ ነገሩት ከከተማይቱ ወጥቶ ሊሄድ ሲል ጌታችን ተገልጦ ታየው “ጌታ ሆይ ወዴት ትሄደለህ” ቢለው “ዳግም በሮም ልሰቀል” በማለት ነገረው፡፡ ቅዱስ ጴጥሮስ በዚህ ልቡ ተነክቶ ወደ ሮም ተመለሰና የሰማዕትነትን አክሊል ተቀዳጀ፡፡ “ጌታችን እንዳመለከተኝ” ያለው ይህን ነበር፡፡
ከመውጣቴም በኋላ አንድታስቡ በየጊዜው ትችሉ ዘንድ እተጋለሁ!
ከላይ የተመለከትናቸው ሃሳቦች ቅዱስ ጴጥሮስ ጊዜ ሞቱ እንደቀረበ አውቆ መናገሩን እና ምእመናን የተማሩትን በማሳሰብ ሲያነቃቸው እንደነበር የሚያስረዱ ናቸው፡፡ እስካሁን የተመለከትናቸው የሚያወሱት ይህ ሐዋርያት በሕይወት ሳለ ስለሚያደርጋቸው ነገር ነበር፡፡ በመጨረሻው ዐረፍተ ነገር ግን “ከመውጣቴ በኋላ የሚል ሐረግ እናገኛለን፡፡ “ከመውጣቴ በኋላ” ሲል ምን ማለቱ ነው?
ቀደም ባሉት ዐረፍተ ነገሮች እንደሚሞትና ይህንንም ጌታችን እንዳመለከተው ተናግሮ ነበር፡፡ ስለዚህ መውጣቴ ያለው ሞቱን እንደ ሆነ እሙን ነው፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስ ሞት መውጣት ተብሎ ሲነገር የቅዱስ ጴጥሮስ የመጀመሪያ አይደለም፡፡ በታቦር ተራራ ከሙሴና ኤልያስ ጋር ስለመነጋገሩ በተጻፈበት ስፍራ “በክብርም ታይተው በኢየሩሳሌም ሊፈጽም ስላለው ስለ መውጣቱ ይናገሩ ነበር” ይላል፡፡ በኢየሩሳሌም የተፈጸመው መውጣቱ ደግሞ ሞቱ ነው፡፡ /ሉቃ.9÷31/ ስለዚህ ቅዱስ ጴጥሮስ ባስተማርኳችሁ እንድትጸኑ “ከሞትኩም በኋላ እተጋለሁ!” እያለ ነው፡፡ “ከሞትኩ በኋላ” የሚለውን እናቆየውና “እተጋለሁ!” የሚለውን ቃል በጥቂቱ እናብራራው፡፡
ትጋት ምንድርን ነው? ትጋት አንድ ነገር ያለማቋረጥ፣ ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይሉ፣ ያለመታከት ማድረግ ነው፡፡ ጠቢቡ ሰሎሞን “ታካች ሰው ምንም አደን አያድንም፤ የሰው የከበረ ሀብቱ ትጋት ነው” በማለት ትጋት የታካችነት ተቃራኒ መሆኑንና ጥቅሙን ተናግሯል /ምሳ.12÷27/፡፡ ጌታችን በምሴተ ሐሙስ ቅዱሳን ሐዋርያቱን “ከእኔ ጋር አንዲት ሰዓት እንኳን ልትተጉ አልቻላችሁምን? ወደ ፈተና እንዳትገቡ ትጉና ጸልዩ” ብሎ ገሥጿቸው ነበር /ማቴ.26÷30/፡፡ ጸጋ መንፈስ ቅዱስን ከተቀበሉ በኋላ ግን ሐዋርያት ትጉሐን ነበሩ፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ እንደ መሰከረላቸው “ወደዚህም ወደ ተሰፋ ቃል አሥራ ሁለቱ ወገኖቻችን ሌሊትና ቀን በትጋት እያመለኩ ይደርሱ ዘንድ አለኝታ አላቸው” /ሐዋ.26÷7/ በዚህ ሁሉ ትጋት አለመታከት፣ አንድን ነገር ሌሊትና ቀን ማድረግ መሆኑን ተረዳን፡፡
ቅዱስ ጴጥሮስ “ከመውጣቴም በኋላ እነዚህን ነገሮች እንድታስቡ በየጊዜው ትችሉ ዘንድ እተጋለሁ” ሲል የሚተጋው በምንድርን ነው? እየዞረ በማስተማር ይሆን? ይህማ ቢሆን ከመሄዴ በፊት ላሳስባችሁ ባላለን ነበር፡፡ ደግሞም ማስተማሩን በሚገባ ፈጽሞ በሰማዕትነት አርፏል፡፡ ታዲያ ከሞተ ወዲያ የሚተጋው ምን በማድረግ ነው? የትስ ነው የሚተጋው? መቼስ በመቃብር ያለሥጋው ሊተጋ አይችልም፡፡ “የሞቱትስ ተነሥተው ያመሰግኑሃልን? በመቃብርስ ውስጥ ቸርነትህን ይናገራሉን?” ብሏል ቅዱስ ዳዊት /መዝ.87÷15/ ራሱ ቅዱስ ጴጥሮስም “ከማደሪያዬ እለያለሁ፡፡ ብሎ ከሞተ ወዲያ እኔ የሚላት ነፍሱን እንደሆነ አስረድቶናል፡፡ ታዲያ በነፍሱ በሰማይ ምን እያደረገ ይሆን የሚተጋው? መቼስ በሰማይ እርሻ ቁፋሮ፣ ጽሕፈት፣ ድጒሰት የለም፡፡ ሐዋርያው በምን ይሆን የሚተጋው? በጸሎት ነዋ!
ስለዚህ ቅዱስ ጴጥሮስ “እንደተማራችሁት መኖርን እንዳትዘነጉ በየጊዜው /አንድ ጊዜ ብናስብ አንድ ጊዜ መዘንጋት አለና/ ትችሉ ዘንድ ከሞትኩም በኋላ ያለማቋረጥ ያለመሰልቸት ስለ እናንተ በመጸለይ እተጋለሁ! ማስተማርና መልእክትን ጽፎ መተው ብቻ ሳይሆን በተማራችሁት መገኘት እንድትችሉ በአጸደ ነፍስም ብሆን እለምናለሁ፣ እማልዳለሁ! እያለ ነው፡፡
በቅዱስ ጴጥሮስ ዓለትነት የተመሠረተችው ቅድስት ቤተ ክርስቲያን በአደባባይ ስለእርሷ የተጻፋላት፣ በደሙ የዋጃት አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ ራሷ ነው፡፡ እርሱ በሁሉ የሞላ ሲሆን “ሁሉን በሁሉ ለሚሞላ ለእርሱ ሙላቱ የሆነች” አካሉ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ናት /ኤፌ.1÷22/፡፡ ቤተ ክርስቲያን የክርስቶስ አካሉ ስትሆን ክርስቶስ ደግሞ የቤተ ክርስቲያን ራሷ ነው፡፡ እኛ ደግሞ የሰውነት አካል ክፍሎች ነን፡፡ “እንግዲህ እናንተ የክርስቶስ አካሉ ናችሁ፤ እያንዳንዳችሁ የአካሉ ክፍሎች ናችሁ፡፡” ተብለናል /1ኛቆሮ.12÷27/፡፡ በቤተ ክርስቲያን ሕይወትን የሚሰጡ ጥምቀትን፣ ንስሐን፣ ቊርባንን የመሳሰሉ ምስጢራትን በመፈጸም ራሳችን ከሆነው ከመድኃኔዓለም ጋር አንድ እንሆናለን፡፡
ክርስቲያኖች ሲሞቱ ከዚህ ኅብረት ይነጠላሉ ማለት አይደለም፡፡ ራሷ ክርስቶስ በሰማይም በምድርም ስላለ ቤተ ክርስቲያንም በምድርም በሰማይም አለች፡፡ ስለዚህ አንድ ክርስቲያን ነፍሱ ከሥጋው ስትለይ ወደ ሰማያዊቱ አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን ይሄዳል፡፡ የሰማይዋ ቤተ ክርስቲያን ደግሞ ድል በነሱ ቅዱሳን የተሞላች ፍጹም መንፈሳዊ የሆነ ሥርዓት ያለባት፣ ሥጋዊ ደማዊ አሳብ የማይሰለጥንባት ናት፡፡ ከእኛ ተለይተው ወደዚያ ኅብረት የተደመሩ ወገኖቻችን በላይ ያሉ የክርስቶስ አካላት ናቸው፡፡ ከእኛ በምድር ካለነው የክርስቶስ አካላት ጋር አንድነታቸው አይቋረጥም፡፡ የክርስቶስ አካል አይከፈልማ! ስለዚህ በሰማይ ካሉት ድል የነሡ ቅዱሳን ጋር እኛ ደካሞቹ በጸሎት እንገናኛለን፡፡
“ዐይን እጅን አልፈልግሽም ልትላት አትችልም፤ ደካሞች የሚመስሉህ የአካል ክፍሎች ይልቁንም የሚያስፈልጉህ ናቸው፡፡ ተብሎ እንደተነገረ እኛ ኃጢአተኞቹ የቤተ ክርስቲያን የአካል ክፍሎች ብንሆንም ቅዱሳኑ ስለ እኛ ይጸልያሉ /1ቆሮ.12÷21/፡፡ ምክንያቱም ደካማ ብንሆንም ለቅዱሳን እናስፈልጋቸዋለን፡፡ ቅዱሳን ኃጥአንን ካልወደዱ ቅድስናቸውን ያጣሉ፡፡ እኛን ካልወደዱ “እኔ ክርስቶስን እንደመሰልሁ እናንተም እኔን ምሰሉ” “አሁን እኔ ሕያው ሆኜ አልኖርም፤ ክርስቶስ ግን በእኔ ይኖራል፡፡” ብለው ለመናገር እንደምን ይችላሉ? /ገላ.2÷20/
እኛ በሥጋ ድሆች የሆኑ ነዳያንን በመመጽወት እንደምንከብር ቅዱሳንም በነፍስ ድሆች የሆንን እኛን በአማላጅነት ጸሎታቸው እየመጸወቱ ይከብራሉ፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ “ለድሀ ግን የሚራራ ምስጉን ነው፡፡” ይላልና በምግባር ድሆች ለሆንን ለእኛ መራራት የቅዱሳን ግብር ነው፡፡ “ጻድቅ ሰው ለእንስሳው ነፍስ ይራራል” ተብሎ እንደተነገረላቸው ቅዱሳን ክቡር ሆነን ሳለን ለማናውቅ እንደሚጠፉ እንስሶች ለመሰልን ለእኛ ለኃጢአተኞች ይራራሉ፤ ይማልዱማል /ምሳ.12÷10፣ 14÷21/፡፡
ቅዱሳን በሕይወተ ሥጋ እያሉ መከራን ታግሠው ስለ ሌሎች በደል ይለምናሉ፡፡ ሳይበድሉ ራሳቸውን በኃጢአትኛው ቦታ አርገው፣ ከደካሞች ጋር እንደ ደካማ ሆነው ይማልዳሉ፡፡ ታዲያ ነፍሳቸው ከሥጋቸው ተለይታ “ሲሄዱና ከክርስቶስ ጋር ሲኖሩ” /ፊል.1÷23/ ምንኛ ይለምኑ ይሆን?
በምድር ያለችው ቤተ ክርስቲያን በሕይወተ ሥጋ ለሌሉና ወደ ሰማዩ ኅብረት ለሄዱ ምእመናን ጸሎተ ፍትሐትን፣ መታሰቢያን በማድረግ፤ ለዚያ የሚያበቃ ቅድስና ያላቸውን ደግሞ በዓላቸውን በማክበር ታስባቸዋለች /2ጢሞ.1÷17-18/፡፡ በሰማይ ያሉት ቅዱሳን ደግሞ ቅዱስ ጴጥሮስ እንዳለው ስለ እኛ ይተጋሉ፡፡ የቤተ ክርስቲያንን መከራና የምእመናንን ስቃይም በዝምታ አይመለከቱም፡፡ በዙፋኑ ፊት ቆመው “ቅዱስና እውነተኛ ጌታ ሆይ እስከ መቼ ድረስ አትፈርድም? ስለ ደማችንስ በምድር በሚኖሩት ላይ እስከ መቼ አትበቀልም?” እያሉ ያማልዳሉ፡፡ /ራእ.6÷10/ የቅዱስ ጴጥሮስ በረከቱ አይለየን! አሜን፡፡
/ምንጭ፡ ሐመር ሐምሌ 2002 ዓ.ም./
ሚያዚያ 25፣ 2003ዓ.ም
ፕሮቴስታንቶችና ፕሮቴስታንታዊ መንገድ የሚከተሉ አንዳንዶች የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ወንጌልን አልሰበከችም የሚል ክርክር ይዘው ይቀርባሉ፡፡ ዝግጅት ክፍላችን ጥያቄያቸውን ለመመለስ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያንና ምእመናንን በምላሹ እንዲሳተፉበት ጋብዘናል፡፡ ለዚህ እትም የያዝነውን እነሆ!
“ቤተክርስቲያናችን ዘመናትን የተሻገረችበት ኃይሏ ወንጌል ነው”
ቤተክርስቲያን ወንጌልን ስትሰብክ ሁለት ሺሕ ዓመታት አልፏታል። ይህንንም ሊቃውንቱ ምእመናንም ያስረዱትና የተረዱት ነው። ወንጌል ካልተሰበከ ክርስቲያኖች እንዴት ለአሁን ዘመን ደረሱ? ወንጌል መሠረት፣ በጎ እርሾ ሳይሆነው፣ ወንጌል ብርታት ሳይሆነው ይህን ሁሉ ዘመናት አቆራርጦ፣ ድልድዩን አልፎ እንዴት እዚህ ደረሰ? ወንጌል ቤተ ክርስቲያናችን ዘመናትን የተሻገረችበት ኃይሏ ነው፡፡
በቤተክርስቲያን ሊቃውንቱ የሚያነቧቸው፣ የሚተረጉሟቸው፣ ምእምናን የሚሰሟቸው፣ የሚታነጹባቸው ድርሳናት፣ ተአምራት ወንጌል ናቸው። እነዚህ መጻሕፍት ወንጌልን የሚፈቱ፣ የሚተረጉሙ፣ የሚያመሰጥሩ ናቸው። ከዚህ ውጭ የሆኑ መጻሕፍት በቤተክርስቲያን አይነበብም፣ አይተረጎምም፣ አይሰማም። ቤተክርስቲያን ወንጌልን የምትሰብከው በቃል፣ በመጽሐፍ ብቻ ሳይሆን በድርጊትም ነው። ጥምቀት ወንጌል ነው። ቤተክርስቲያንም ጥምቀት የዘወትር ሥራዋ ነው። ወንጌል ስለ ጥምቀት ነው የሚነግረን። የክርስቶስ ቅዱስ ሥጋውን ክቡር ደሙም በየዕለቱ ይቀርባል፤ ይህ ወንጌል ነው። ወንድሞቻችን፣ እኅቶቻችን የተቀደሰውን ጋብቻቸውን በተቀደሰው ቦታ፣ በተቀደሰው ጸሎት በምስጢረ ተክሊል ይፈጽማሉ። ይህም ወንጌል ነው። እናቶቻችን፣ አባቶቻችን፣ ወንድሞቻችን፣ እኅቶቻችን ከዚህ ዓለም ሲሸኙ በሥርዐተ ፍትሐት፤ ብሉያትና ሐዲሳት እየተነበቡ፣ ያሬዳዊ ዜማ እየተዜመ ነው። ይህ ወንጌል ነው። አላዛርን ከመቃብር ተነሥ እንዳለው፤ የታሰረበትን ፍቱት እንደተባለ እንደተ ፈታ ሁሉ፤ ካህናትም ከኃጢአት እስራት እየፈቱ ሕዝባቸውን መሸኘት፤ “አቤቱ እግዚኦ ይቅር በለው ሲያውቅ፣ ሳያውቅ በሠራው ኃጢአት ይቅር በለው” እያሉ መሸኘት ወንጌል ነው።
ቤተክርስቲያን ራሷም፣ እግሯም፣ መሠረቷም፣ ጉልላቷም ወንጌል ነው። ይህን በቅንነት፣ በበጎ ነገር፣ በምስጢር፣ በትርጓሜ ለሚያዩት ነው። በጥላቻ ካዩት ነጩም ጥቁር ነው፤ ብርሃኑ ጨለማ ነው፤ በጥላቻ ማየትና በፍቅር ማየት፤ በሐሰት መናገርና በእውነት መናገር መካከል ሰፊ ልዩነት አለ። የቤተክርስቲያን ጥንተ ጠላቶች ለቤተክርስቲያን በጎ ይመሰክራሉ ብለን ከጠበቅን የተሳሳትን ይመስለኛል። መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ጸሐፍት ፈሪሳውያንን “እግዚአብሔር ከእናንተ ምስክርነትን አይፈልግም” ነው ያላቸው። ጸሐፍት ፈሪሳውያን ስለ ክርስቶስ በጎ ስለማይመሰክሩ ስለማይናገሩ ነው። ምክንያቱም በጭፍን፣ በቅናት፣ ስለጠሉት ነው። ቤተክርስቲያንም ከጠላቶቿ የእውነት ምስክርነትን አትጠብቅም፤ በበጎ ለሚያዩአት ግን ምስክርነቱ በእጅ የሚጨበጥ (የሚዳሰስ) በዐይነ የሚታይ ነው።ቤተክርስቲያን ወንጌል ያልሰበከችበት ዘመንም፣ ጊዜም የለም። ወንጌል አልተሰበከም ለሚሉ ሰዎች ትናንት አለነበሩም፣ ዛሬም የሉም። ለነገሩስ የት ሆነው ያዩታል? ቢኖሩም አይገባቸውም፤ ውስጣቸውም በብዙ ችግር የተተበተበ፤ በቅራኔ የተሞላ ነው። በቅራኔ የተሞላ ደግሞ ከውጭ የሚነገረውን በጎ ነገር ለመቀበል ዝግጁ አይደለም።
“ቤተክርስቲያን ክርስቶስን የምትሰብከው በቃል ብቻ ሳይሆን በድርጊትም ነው”
ሰው በተሰጠው የፈቃድ ነጻነት መሠረት የፈለገውን የመናገር መብት አለው። ፍሬ ነገሩ እውነቱ የቱ ነው? ሐሰቱስ? የሚ ለው ነው። ዲያብሎስ ስለ ቅዱስ ሚካኤል የብርሃን መላክነት አይመስክርም፤ ሊመሰክርም አይችልም። «ሚካኤል ደካማ ነው» እያለ የፈለገውን መናገር ይችላል። የዲያብሎስን ምስክርነትም ሚካኤል አይፈልገውም፣ አይቀበለውምም። ዲያበሎስ የፈለገውን ቢናገር ሚካኤልን አይከፋውም፤ ከጠላቱ ቡራኬ ስለማይጠብቅ። እንደዚሁ ሁሉ የእኛም ቤተክርስቲያን የሌሎችን ቤተእምነቶች ምስክርነትም ሆነ ክስ አታደንቀውም፤ አትደነግጥበትምም የእኛ ቤተክርስቲያን ጨርቅ ሰጥታ ጉቦ ሰጥታ እንዳልተስፋፋች ሁሉም ያውቁታል፤ ታዲያ ወንጌልና ክርስቶስን ሳትሰብክ ቤተክርስቲያን ሆና ሁለት ሺሕ ዓመታትን እንዴት ተሻገረች? አሸናፊ ስለሆነች በእውነቷ ብቻ ቆማ የምትኖር ናት። ጉቦ አይከፈልባትም፣ ማባበያም አትጠይቅም።
ቤተክርስቲያን ክርስቶስን የምትሰብከው በቃል ብቻ ልብን አሻክሮ ምላስን አለዝቦ በማነብነብ አይደለም፤ በድርጊት በማሳየትም እንጂ። በአንድ ታላቅ ዓመታዊ ክብረ በዓል በአንድ ቤተክርስቲያን በአንድ ቀን ብቻ የምናደርገው ስብሐተ እግዚአብሔር፤ ስብከቱ፣ ቅዳሴው፣ ማኅሌቱ፣ ዋዜማው በተግባርም ታቦት ይዘን ቆመን ያስተላለፍነው ትምህርት በጠቅላላው መናፈቃኑ ለአንድ ዓመት ከጮኹበት፣ ብዙ ነገር ካወጡበት «አገልግሎት» እጅግ ብልጫ አለው። የዚህ አጠቃላይ አገልግሎታችን ዋነኛ ማእከልም ወንጌልና የጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነገረ ድኅነት ነው፡፡ ንዋያተ ቅድሳቶቻችን በሙሉ ስብከቶች ናቸው። በቅዳሴ ላይ ቄሱ፣ ዲያቆኑ መስቀል ይዞ የሚዞረው ምን ለማሳየት ነው? ቀሳውስት ዕጣን እያጠኑ “ስብሐት ወክብር ለሥሉስ ቅዱስ” እያሉ ሲያመሰግኑ ምስጢረ ሥላሴ እና ምስጢረ ሥጋዌን መስበከ፣ ማስተማራቸው ነው። ልብሰ ተክህኖዎቹ ከታቦተ ሕጉ ጀምሮ ንዋያተ ቅድሳቱ ሁሉ መስቀል የሚደረግበት ለጌጥ አይደለም። ይህ ስብከት አይደለም እንዴ? መቅደስ ውስጥ ስንቀድስ በአራቱ ማእዘን የምንቆመው ጽርሃ አርያምን እያሳየን ነው። እነርሱ የማያስተውሉትን ሰባቱ ሰማያትን አምጥተን መቅደሱ ላይ ቁጭ አድርገን የምናሳያቸው ለስብከት ነው። ኪሩቤል እንዴት አድርገው ጌታን እንደተሸከሙት ታቦቱን መንበሩ ላይ አስቀምጠን ስንቀደስ እናሳያለን። በተጨባጭ እያሳየን እያሰተማርን ነው።
ደስ ሊለን ይገባል፤ ለሁለት ሺሕ ዘመን ወንጌል ሳይነበብባት በተለያየም መንገድ ሳይሰበክባት የማትውል የማታድር እንደ ሀገር ኢትዮጵያ እንደ ቤተክርስቲያንም የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን ነች። ቢያንስ በቅዳሴ ላይ ሰባኪ ያልቆመባቸው፣ ወንጌል ያልተሰማባቸው፣ ሃይማኖት አበው የማይነበብባቸው ገዳማትና አብያተክርስቲያናት የሉም። ስለዚህ ስብከት መንዘፍዘፍና ዓላማ የሌለው ጩኸት አይደለም። በእርጋታ፣ በማስተዋል፣ በጥንቃቄ የሚፈጸም በብዙ ዓይነት መንገድ የሚከናወን፤ ያልነበሩትን የምናመጣበት የነበሩትን የምናጸናበት አገልግሎት መሆኑን ሁሉም ይረዳ።
በዲ/ን እሸቱ
ሚያዝያ 26፣2003ዓ.ም
ሰው ማነው? ብሎ ለጠየቀ “ሰው ንግግሩን ይመስላል” እንዳትለኝ ንግግሩ እምነቱን የሚያመለክት ዕውቀት አይሆነውምና ነው፡፡ ለሰው ባሕርያዊ ተፈጥሮና ዕውቀት ምስክሩ ውስጣዊ የአዕምሮ አቋምና የሕሊና ሕግ ነው ብለንም አንደመድምም፡፡ ሰው እንዲያውቅ የተመደበለት የሕግ ተፈጥሮ ዕውቀት መጀመሪያ ክፍል መልካምን ማወቅ፡፡ ሁለተኛ ክፋትን ንቆ መልካምን ገንዘብ ማድረግ፡፡ ሦስተኛ መልካምን በግብር መግለጽ ናቸው፡፡ የቤተ ክርስቱያን ሊቃውንት ይሁዳን ሲገልጹ “በአፍ አምኖ በልቡ የካደ” ይሉታል፡፡ ባህላችን “አፈ ቅቤ፤ ሆደ ጩቤ” እንዲል፡፡
የክርስቲያናዊ ሥነ ምግባር መሠረት ያለ ትምህረት በተፈጥሮ የሚሰጥ ሲሆን ይህም ሕገ ልቦና፤ ሕገ ህሊና፤ ሕገ ተፈጥሮ ወይንም ሕገ ጠብዓያዊ በመባል ይታወቃል፡፡ ሕገ ኦሪትና ሕገ ወንጌል፤ ሕገ ሕሊናን ይተረጉማሉ፡፡ ለአብነት ብንጠቅስ አዳምና ሔዋን ቅዱስ ዳዊትና ይሁዳን፤ ከመጸጸት ክፉዎችን ከማዘን የምታደርሳቸው የሕሊና ኮሽታ ነች፡፡ በኑሮ ሂደት ሀዘን፣ ጸጸት ርትዕ በምናደርግበት ጊዜ ልዩ መንፈሳዊ ጥበብ አልያም ዕውቀት በመታደል ሳይሆን ሰው በመሆናችን በሕሊና ውስጥ የተቀረጸ በህሊና ሚዛን የሚሰጥ ፍርድ በመኖሩ ነው፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ሕገ ሕሊና በጽሑፍ ከተሰጡን ሕግጋት /ሕገ ኦሪት፣ ሕገ ወንጌል፣ ማሕበራዊ ሕግ/ በላይ ሰማያዊና ምስጢርን ለመጠበቅ ሲያገለግል እናገኘዋለን፡፡ የቤተ ክርስቲያን የሀገር የግል ምስጢር ይጠበቅ ዘንድ መንፈሳዊ ሕግና ማህበረሰባዊ ሕግ ይደነግጋል፡፡ የአምላክ እናት ድንግል ማርያም ያለ ምድራዊ ሕግ አስገዳጅነት በሕገ ልቦና ዳኝነት ለሰማያዊ ምስጢር የታመነች ነበረች “እናቱ ማርያም በልቧ ትጠብቀው ነበር” እንዲል፡፡ /ሉቃ.2÷19/፡፡
“ሰው ራሱ መጽሐፍ ነው” የሚለው የአነጋገር ስልት የሚያስተላልፈው ሰው ይነበባል፤ ይጠናል፤ ይተነተናል ይጸድቃል፤ ይሻራል ለማለት ነው፡፡ እነዚህን ተግባራት ለሌሎችም ሆነ ለራሳችን ለድርጊታችን ብያኔ ፍርድ ለመስጠት ረቂቅ የሕሊና ልጓም እንደ መሠረት ሆኖ ያገለግላል፡፡ ሰው በውስጡ የሚያረጋግጣት እውነት በክበበ አዕምሮ በሚጨበጥ ሕገ ባሕርይ ከመገለፅ እምቢ አትልም፡፡ እግዚአብሔርን ደስ ለማሰኘት እምነት በቅድሚያ እንዲገኝ ግድ ቢሆንም በተግባር ወይንም በድርጊት ካልተዋሃደ ክርስቲያናዊ ሕይወታችን ፍሬ ቢስ፤ ረብ የሌለው ከንቱ ድካም ይሆናል፡፡ ለመሆኑ እምነታችን ከድርጊታችን ለምን ተዛነፈ? በጽናት የምናምነውን እምነት አጥቦ የመውሰድ ብቃት ያለው ሃይል ይኖር ይሆን? በዕለት ተዕለት ማኅበራዊ መስተጋብር የምንወስናቸው መጠነ ሰፊ ጥቃቅን ውሳኔዎች ውህደ ሃይማኖት ምግባር የታሹ ወይስ የስሜት ውጤቶች ናቸው? እርግጥ ነው ስሜት አልባ ሰብአዊ ፍጡር ሊሆን አይችልም፡፡ ነገር ግን ነፍስን ደስ የሚያሰኝ ሰማያዊ እውነት ከስሜት በላይ ነው፡፡ በገሃዱ ዓለም በብዙዎቻችን ሕይወት የሚታየው ውሳኔዎቻችን በድካም ባካበትነው ዕውቀት፤ መንፈሳዊ አስተምህሮ፤ ዓለማዊ ጥበብ፤ የቅዱሳን ሕይወት ሳይሆን ለስሜት ያጋደለ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ ለሁለት ጌታ መገዛት አይቻልም የሚለውን ኃይለ ቃል ከጌታችን ከመድኃኒታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ የተማረው ይሁዳ ለ30 ብር ሸጦታል ለምን ትለኝ እንደሆን ሰው ክፉን ነገር እስኪሰራ ሰው ልበ ሙሉ ይሆናልና ነው፡፡ ሁለተኛው የህሊና ዓይን ከነፍስ ባይለይም በኃጢአት ምክንያት ይጨልማል ይደክማልና ነው፡፡ በአጭር አገላለጽ ድርጊታችንን የሚቆጣጠረው በዕለቱ ስሜታችንን ያቀጣጠለው ኃይል እንጂ በጥረት ያካበትነው ትምህርት ወይም ዕውቀት ሆኖ አይታይም፡፡ ሰው ሆይ ለምን ይሆን…
