(በቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ)
ግንቦት 30/2003 ዓ.ም.
ዲ/ን ሽመልስ መርጊያ
መግቢያ
ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ የዮሐንስን ወንጌል በተረጎመበት በ21ኛው ድርሳኑ “ ጌታችን በእናታችን በቅድስት ድንግል ማርያም ጥያቄ በቃና ሰርግ ላይ ስለምን ውሃውን ወደ ወይን ጠጅነት እንደቀየረው ከአብራራ በኋላ ከዛሬ 1500 ዓመት በፊት በአሁኑ ጊዜ እንደ አዲስ ግኝት ተደርገው የሚታዩትን አብዝቶ በመመገብ የሚመጡትን የጤና ጉድለቶች ጽፎልን እናገኛለን ፡፡ ጽሑፉ ተተርጉሞ እንዲህ ቀርቦአል።
ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ውሃውን ወደ ወይን ጠጅነት ያኔ እንደቀየረ ዛሬም እኛን ድካማችንንና እንደ ወራጅ ውሃ በአንድ ቦታ ጸንቶ መቆየት የተሣነውን የሥጋ ፈቃዳችንን ከመቀየር አልተቆጠበም ፡፡ ዛሬም አዎን ዛሬም ልክ እንደ ወራጅ ውሃ ቀዝቃዛ ፣የፈጠነና ፣ ያልተረጋጋ ጠባይ ያላቸው ሰዎች አሉ ፡፡ እነዚህን ፈቃዶቻችንን ወደ ጌታችን እናምጣቸው ፤ እርሱ ወደ ወይንነት ይቀይራቸዋል፡፡ ከዚያም በኋላ ውኃ ሆነው ከእንግዲህ አይቀጥሉም ፡፡ ነገር ግን ለራሳቸውና ለሌሎች ደስታን የሚሰጡ አካላት ይሆናሉ ፡፡
ባልተረጋጋ ውሃ የተመሰሉት እነማን ናቸው ? ለዚህ ከንቱ ዓለም ሕሊናቸውን ያስገዙ ወገኖች ፣ የዚህን ዓለምን ቅምጥልነት ፣ አለቅነትንና ክብርን የሚሹ ናቸው፡፡ እነዚህ ፍቃዶቻችን እንደውኃ የሚፈሱ ፣ ፈጽሞ ያልተረጋጉ ፣ ለአመፃ የሚፋጠኑ ቁልቁል የሚምዘገዘጉ ውኆች ናቸው ፡፡
ዛሬ ሀብታም የነበረው ነገ ደሃ ይሆናል ፡፡ በአንድ ወቅት ዝናው ሲነገርለት፣ የተጌጠና የተንቆጠቆጠ ልብስ ለብሶ በሰረገላ ላይ የሚሄድና ብዙ አጃቢዎች የነበሩት ሰው ፣ ያለፈቃዱ ያን የተዋበ መኖሪያውን ተቀምቶ ወደ ወይኒ ተጥሎ ይገኛል ፡፡ ለሥጋው ደስታ የሚተጋው ሆዳሙ ደግሞ የሥጋ ፈቃዱን ከሞላ በኋላ ሆዱ ሳይጎድልበት ለአንድ ቀን መቆየት አይቻለውም ፡፡ ነገር ግን እነዚህ ምግቦች ከሆዱ ሲጠፉ ወደ ቀድሞው ምቾቱ ለመመለስ ሲል ከፊት ይልቅ አብዝቶ ይመገባል ፡፡ አመጋገቡም ሁሉን ጠራርጎ እንደሚበላ እንደጎርፍ ውሃ ነው ፡፡ በዝናብ ወቅት የሚነሣው ጎርፍ አስቀድሞ የነበረ ውሃ በከፈተለት ጎዳና ገብቶ ቦታውን ሁሉ ያጥለቀልቀዋል ፡፡ እንዲሁ በሆዳሙም ዘንድ እንዲህ ይሆናል ፡፡ አስቀድሞ የነበረው ሲጠፋ እርሱ በቀደደው ሌሎች የሥጋ ፍቃዶች በዝተው ይገባሉ ፡፡
ምድራዊው ነገር ይህን ይመስላል ፤ መቼም ቢሆን የተረጋጋ አይደለም ፡፡ መቼም ቢሆን አንዱ ሌላውን እየተካ የሚፈስ እና የሚቸኩል ነው ፡፡ ነገር ግን የቅምጥልነትን ኑሮ በተመለከተ ጣጣው በከንቱ መባከን ወይም መቻኮል ብቻ አይደለም ፡፡ ሌሎችም እኛን ከመከራ የሚጥሉን ችግሮችም አሉበት ፡፡ ቅምጥልነት ባመጣብን ጣጣ የሰውነት አቅማችን ይዳከማል ፣ እንዲሁም የነፍስ ጠባይዋም ይለወጣል ፡፡ ከባድ ጎርፍ ወንዙን በደለል ወዲያው እንደማይሞላው ፣ ቀስ በቀስ ግን እንዲሞላው ፣ እንዲሁ ቅምጥልነትና ዋልጌነት እንደ አልማዝ ብርቱ የሆነውን ጤንነታችንን ቀስ በቀስ ውጦ ያጠፋዋል ፡፡
ወደ ሐኪም ዘንድ ሄደህ ብትጠይቅ የበሽታዎች ሁሉ ምንጫቸው አብዝቶ ከመመገብ እንደሚመነጩ ይነግሩሃል ፡፡ ጠግቦ አለመብላትና ለሆድ የማይከብዱ ምግቦችን መመገብ ለጤንነት እናት ነው ፡፡ ስለዚህም የሕክምና ባለሙያዎች የጤንነት እናት ብለው ይጠሩታል ፡፡ እናም ጠግቦ አለመብላት የጤንነት እናት ከሆነ ፣ አብዝቶ መመገብ ደግሞ የበሽታዎች ሁሉ እናት እንደሆነ በዚህ ይታወቃል፡፡ አብዝቶ መመገብ ሰውነታችንን አዳክሞ በሕክምና ባለሙያ እንኳ ለማይድን በሽታ አጋልጦ ይሰጠናል ፡፡
አብዝቶ መመገብ ለሪህ ፣ ለአእምሮ ውስጥ የደም መፍሰስ ፣ ለዐይን የማየት ኃይል መቀነስ ፣ ለእጅ መዛል ፣ ለአካል ልምሾነት ፣ ለቆዳ መንጣት (ወደ ቢጫነት መቀየር ፤ በተለምዶ የጉበት በሽታ ለምንለው ምልክት ነው ተብሎ ይታመናል ) ስጉና ድንጉጥ መሆን ፣ ለኃይለኛ ትኩሳት እና ከጠቀስናቸው በላይ ለሆኑ ሌሎች ሕመሞች ያጋልጣል ፡፡ በዚህ የሚመጡትን የጤንነት ጠንቆች በዚች ሰዓት ውስጥ ዘርዝሮ ለመጨረስ ጊዜው አይበቃም ፡፡ እነዚህ ሁሉ ሕመሞች በተፈጥሮአችን ላይ የሚከሰቱት መጥኖ በመብላት ወይም በጾም አይደለም ፡፡ ነገር ግን ከሆዳምነታችንና ከአልጠግብ ባይነታችን የተነሣ የሚመጡብን ናቸው ፡፡ በእነዚህ ምክንያቶች የተነሣ በነፍሳችን ላይ የሚከሰቱብንን በሽታዎች ብንመለከት ዋዘኝነት ፣ ስንፍና ፣ ድንዛዜ ፣ የሥጋ ፍትወቶቻችን ማየል፣ እነዚህንና የመሳሰሉ ሕመሞች ነፍሳችንን ያጠቁዋታል ፡፡ ለእነዚህ ሁሉ ምንጫቸው ሳይመጥኑ አብዝቶ መመገብ ነው ፡፡ ከእንዲህ ዐይነት ቅጥ ያጣ አመጋገብ በኋላ የቅምጥሎች ነፍስ ክፉ አውሬዎች ሥጋዋን ተቀራምተው ከተመገቡዋት አህያ ያልተሻለች ትሆናለች ፡፡ ቅምጥሎችን ስለሚጠብቃቸው ሕመሞችና ስቃዮች ጨምሬ ልናገርን ? ከብዛታቸው የተነሣ ዘርዝሬ መጨረስ አይቻለኝም ፡፡
ነገር ግን በአንድ ማጠቃለያ አሳብ ሁሉንም ግልጽ አድርጌ ማስረዳት እፈልጋለሁ ፡፡ እንዲህ ከሚያደርጉ ከቅምጥሎች ማዕድ ማንም ደስ ብሎት አይመገብ ፡፡ አስቀድመን እንደተነጋገርነው ጾምና መጥኖ መመገብ የደስታና የጤንነት ምንጮች ሲሆኑ ያለቅጥ መመገብ ግን የበሽታና የደስታ ማጣት ሥር እና ምንጭ ናቸውና ፡፡
ሁሉ ነገር ከተሟላልን ፍላጎት የለንም ፡፡ ፍላጎት ከሌለ ደግሞ እንዴት ደስታን ልናገኛት እንችላለን ? ስለዚህም ድሆች ከባለጠጎች ይልቅ የተሻለ ማስተዋልና ጤና ያላቸው ብቻ አይደሉም ፣ ነገር ግን ታላቅ በሆነ ደስታ ውስጥ የሚኖሩ ጭምር ናቸው ፡፡ ይህንን ከተረዳን ከመጠጥና ከቅምጥልነት ሕይወት ፈጥነን እንሽሽ ፣ ከማዕዱ ብቻ አይደለም ፣ ከዚህ ሕይወት ከሚገኙት ፍሬዎች ሁሉ እንሽሽ ፡፡ እነርሱን በመንፈሳዊ ሕይወት በሚገኘው ደስታ ለውጠን በቅድስና እንመላለስ ፡፡ ነቢዩ “ በእግዚአብሔር ደስ ይበላችሁ እርሱ የልብህን መሻት ይሰጥሃል”(መዝ.36፥4) እንዳለው በጌታ ደስ ይበለን ፡፡ በዚህም ዓለም በሚመጣውም ዓለም በእርሱ በእግዚአብሔር መልካም ስጦታ ደስ ይለን ዘንድ የሰው ልጆችን በሚያፈቅረው በኩል ለእርሱ ለእግዚአብሔር አብ ለመንፈስ ቅዱስም ክብር ይሁን እስከዘለዓለሙ ፡፡ አሜን !!
በነገራችን ላይ የሕክምና ባለሙያዎች እንዲሁም የፍልስፍና ምሁራን(ተማሪዎች) በዚህ በቅዱስ ዮሐንስ ገለጻ ላይ ምን ይላሉ ? በmkwebsitetechnique@gmail.com ጻፉልን።