ሰባቱ ምስጢራተ ቤተ ክርስቲያን

በሊቀ ጉባኤ አባ አበራ በቀለ
 
ለሥጋ ሕይወታችን ልደት ፣ እድገትና ሌሎችም ነገሮች እንዳሉት መንፈሳዊ ሕይወታችንም እንደዚሁ ይኸንኑ የሚመስሉ ሁኔታዎች አሉት፡፡ በዚህ መሠረት አንድ ሰው መንፈሳዊ ልደትን የሚያገኘው በእምነትና በምሥጢረ ጥምቀት እንደሆነ እንረዳለን፡፡ ከዚህም ቀጥሎ ምሥጢረ ሜሮንና ምሥጢረ ቁርባን በተከታታይ ይፈጸማሉ፡፡ እነርሱም መንፈሳዊ ልደታችንንና እድገታችንን ከፍጹምና ያደርሱታል፡፡የአገልግሎትና የአንድነት ጸጋ የምናገኝባቸው ደግሞ ምሥጢረ ክህነትና ምሥጢረ ተክሊል ናቸው፡፡

ምስጢራተ ቤተ ክርስቲያን መግቢያ

በሊቀ ጉባኤ አባ አበራ በቀለ
 
እግዚአብሔር የመረጣቸውን ሁሉ በሀብት ስቦ በረድኤት አቅርቦ ወደ ራሱ ይጠራቸዋል ፤ ያቀርባቸዋል፡፡ የተጠሩት ደግሞ በንዑሰ ክርስቲያንነት ደረጃ ቃለ እግዚአብሔርን እየሰሙ ከቆዩ በኋላ አዲስ ሕይወትን እንዲቀዳጁና ጸጋ መንፈስ ቅዱስን እንዲያገኙ የሚያበቃቸው ሌላ መንገድና ሥርዓት አስፈላጊ ስለሆነ ጌታ ራሱ አዘጋጅቶላቸዋል ፤ ሁላችንንም በዚህ መንገድ እንድንሄድ አዞናል፡፡ መንገድ የተባለውም ቃሉን ሰምቶ መፈጸምና ያዘዘንን የቤተ ክርስቲያን ምሥጢራት ሁሉ መፈጸም ነው፡፡