‹‹ያለ ደግ ልጆች ያላስቀረን እግዚአብሔር ይመስገን!›› ብፁዕ አቡነ ሉቃስ

ሐምሌ ፳ ቀን፣ ፳፻፰ ዓ.ም

በዲያቆን ኤፍሬም የኔሰው

abunu 1209

ይህ ‹‹ያለ ደግ ልጆች ያላስቀረን እግዚአብሔር ይመስገን!›› የሚለው ኃይለ ቃል ከብፁዕ አቡነ ሉቃስ ቃለ ምዕዳን የተወሰደ ሲኾን፣ ይኸውም ማኅበረ ቅዱሳን በጀት በመመደብና ምእመናንን በማስተባበር ለገዳማትና አብነት ትምህርት ቤቶች ያደረገውን ድጋፍና ያመጣውን ውጤት ለቤተ ክርስቲያን አባቶችና ለበጎ አድራጊ ምእመናን ለማሳወቅ ሐምሌ ፲፯ ቀን ፳፻፰ ዓ.ም በአዲስ አበባ ከተማ በግዮን ሆቴል በንግሥት ሳባ አዳራሽ ባዘጋጀው ልዩ መርሐ ግብር የተናገሩት ነው፡፡

 

በመርሐ ግብሩ ላይ ብፁዕ አቡነ ሉቃስ የሰቲት ሑመራ፣ የሰሜን ሱዳንና የግብጽ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፣ የትንሣኤ ዘጉባኤ ማሳተሚያ ድርጅት የበላይ ሓላፊ፤ የዐሥር ገዳማት አበ ምኔቶችና እመ ምኔቶች፤ የአብነት መምህራንና ደቀ መዛሙርት፤ የማኅበሩ ሥራ አስፈጻሚዎችና የልዩ ልዩ ክፍሎች አገልጋዮች፤ በጎ አድራጊ ምእመናንና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል፡፡

2S0A7158 - Copy

ብፁዕ አቡነ ሉቃስ በዕለቱ ቃለ ምዕዳን ሲሰጡ “ጸግወኒ እግዚኦ ውሉደ ቡሩካነ ወኄራነ እለ ይትኤዘዙ ለከ፤ አቤቱ ለአንተ የሚታዘዙ፣ የተባረኩ፣ ቸር የኾኑ ልጆችን ስጠኝ፤” የሚል ኃይለ ቃል ጠቅሰው “ያለ ልጆች ያላስቀረን፤ ታዛዥና ቤተ ክርስቲያንን የሚያገለግሉ ልጆችን የሰጠን እግዚአብሔር አምላክ የተመሰገነ ይኹን!” በማለት በየገዳማቱ በጾም በጸሎት ተወስነው፣ በሥራ ተጠምደው የሚኖሩ አባቶች መነኮሳትንና መነኮሳይያትን፤ ለገዳማትና ለአብነት ት/ቤቶች መስፋፋት ልዩ ልዩ ድጋፍ በማድረግ ላይ የሚገኙ ምእመናንንና ይህንን አገልግሎት የሚያስተባብረውን ማኅበረ ቅዱሳንን አመስግነዋል፡፡

 

መርሐ ግብሩ በብፁዕነታቸው ጸሎት ከተከፈተ በኋላ በማኅበረ ቅዱሳን የአዲስ አበባ ማእከል መዘምራንና በመምህር ወልደ ገብርኤል ይታይ ወቅታዊ ይዘት ያላቸው ያሬዳውያን ዝማሬያት ቀርበዋል፡፡

 

ዲያቆን ብርሃኑ አድማስም “ንገሩ” በሚል ኃይለ ቃል የቤተ ክርስቲያንን አስተምህሮና ታሪክ፤ የቅዱሳት መካናትን ጠቀሜታና አስተዋጽኦ፤ እንደዚሁም ያሉባቸውን ችግሮች ለሌሎች በማስረዳት ቤተ ክርስቲያናችንን ከልዩ ልዩ ችግር ነጻ ማድረግና የገዳማትንና የአብነት ትምህርት ቤቶችን ህልውና ማስጠበቅ እንደሚገባ የሚያስገነዝብ ትምህርተ ወንጌል ሰጥተዋል፡፡

 

በመርሐ ግብሩ በማኅበረ ቅዱሳን የቅዱሳት መካናት ልማትና ማኅበራዊ አገልግሎት ዋና ክፍል ‹ምርጥ ተሞክሮ› በሚል ርእስ ያሳተመው፤ ልዩ ልዩ ጉዳዮችን የሚዳስሰው የኤሌክትሮኒክስ ጋዜጣም በብፁዕ አቡነ ሉቃስ ቡራኬ ተመርቋል፡፡

Abun 229

ከዐሥሩ ገዳማት ከመጡ አበ ምኔቶችና እመ ምኔቶች መካከልም ከፊሎቹ ስለየገዳሞቻቸው ኹኔታና አገልግሎት እንደዚሁም ስለሚያከናውኗቸው ልማታዊ ሥራዎች የልምድ ተሞክሯቸውን አካፍለዋል፡፡

 

ማኅበሩ ምእመናንን በማስተባበር ካሠራቸው ተግባራት መካከልም በደብረ ሐይዳ አቡነ ቶማስ ገዳም የተገነባው የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክት በውሃ እጥረት ምክንያት የተበተኑ መነኮሳትና የአብነት ተማሪዎች  ወደ ገዳሙ እንዲመለሱና ቍጥራቸውም እንዲጨምር ማድረጉን  የገዳሙ አባቶች መስክረዋል፡፡

 

ለደብረ ገሪዛን ካስዋ ጕንዳጕንዶ ማርያም ገዳም ገቢ ማስገኛ ይኾን ዘንድ በአዲግራት ከተማ የተገነባው ሕንፃም ሌላው የማኅበረ ቅዱሳንና የበጎ አድራጊ ምእመናን ተሳትፎ ውጤት ሲኾን፣ ይህም በመቅኑን እጥረትና በልዩ ልዩ ችግር የቀዘቀዘው ገዳም ተመልሶ እንዲሰፋ ማስቻሉንና የአብነት ትምህርት ለመስጠት መልካም አጋጣሚ ማስገኘቱን የገዳሙ አበ ምኔት ተናግረዋል፡፡

 

የሚዛን ደብረ ከዋክብት አቡነ ተክለ ሃይማኖት የሴቶች ገዳም እመ ምኔትም ገዳሙ ከባንክ ፩.፰ (1.8) ሚሊዮን ብር ተበድሮ ባስገነባው ሕንፃ ከ፩ኛ – ፱ኛ (ከ1ኛ – 9ኛ) ክፍል ድረስ ዘመናዊ ትምህርት እያስተማረ እንደኾነና ሌሎችንም የልማት ሥራዎችን በማከናወን ላይ እንደሚገኝ፤ ማኅበረ ቅዱሳንም የሕንፃውን ዲዛይን ከመሥራት ጀምሮ ድጋፍ እንዳደረገላቸው ገልጸዋል፡፡ አያይዘውም በገንዘብ እጥረት ምክንያት ያልተጠናቀቁ ሕንፃዎች መኖራቸውንና ከተበደሩት ገንዘብም አብዛኛው አለመመለሱን አስታውሰው ለዚህም የምእመናን ድጋፍ እንዳይለያቸው ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል፡፡

 

የአቃቂ ደብረ ገነት አቡነ ሳሙኤል ገዳምም በማኅበሩ ድጋፍ የልብስ ስፌት መኪናና ጣቃ ጨርቅ፤ አንድ ተሽከርካሪ፣ እንደዚሁም ላሞችና የቤት ክዳን ቆርቆሮ ርዳታ ማግኘቱን፤ የገዳሙ መነኮሳይያትም በዘማናዊ ልብስ ስፌትና በእንስሳት ርባታ በሚያገኙት ገቢ ወላጅ የሌላቸውንና ረዳት ያጡ ልጆችን በመከባከብና በማስተማር ላይ እንደሚገኙ እመ ምኔቷ አስረድተዋል፡፡

 

በመርሐ ግብሩ ላይ በጎንደር አቡን ቤት ቅዱስ ገብርኤል የቅኔ ጉባኤ ቤት የቅኔ ደቀ መዝሙር የኾነው፤ ከዩኒቨርሲቲ በዲግሪ መርሐ ግብር ከተመረቀ በኋላ ማኅበሩ ባዘጋጀው የአባ ጊዮርጊስ ዘጋሥጫ ነጻ የትምህርት ዕድል በማግኘቱ ሥራውን ትቶ ወደ አብነት ትምህርት ቤት የገባው ዲያቆን እንዳልካቸው ንዋይና ከኢትዮጵያ የሁለት ዓመት ሕፃን እያለ ከወላጆቹ ጋር ወደ ካናዳ አገር የሔደው፤ የቅዱሳት መካናት ልማትና ማኅበራዊ አገልግሎት ዋና ክፍል ያዘጋጀውን የአብነት ትምህርት ቤት ሥርዓተ ትምህርት የሚያሳይ ዘጋቢ ፊልም በፌስ ቡክ ተመልክቶ በትምህርቱ በመማረኩ ወደ ዩኒቨርሲቲ መግባቱን ትቶ ወደ ኢትዮጵያ በመመለስ የአብነት ትምህርት መከታተል የጀመረው የቀድሞው ሔርሞን ተስፋዬ የአሁኑ ዘድንግል በመርሐ ግብሩ ላይ ተገኝተው ቅኔ አበርክተዋል፡፡

 

ባለዲግሪው የቅኔ ተማሪ ዲያቆን እንዳልካቸው ስሜቱን ሲገልጽም “ከአሁን በፊት አነጋጋሪ የነበረው የእኔ ወደ አብነት ትምህርት ቤት መግባት ዜና በወንድሜ በሔርሞን ታሪክ ተሸፍኗል፤ ለወደፊትም ወደ አብነት ትምህርት ቤት የሚገቡና የሁለታችንንም ታሪክ የሚያስረሱ ሌሎች ወንድሞቻችንም እንደሚበዙ ተስፋ አደርጋለሁ” ሲል አስተያየት ሰጥቷል፡፡

 

የአፍ መፍቻ ቋንቋው እንግሊዝኛ የኾነውና በጥረቱ የአማርኛም የግእዝም ቋንቋዎች ተናጋሪ መኾን የቻለው የቀድሞው ዘመናዊ ተማሪ የአሁኑ የቅኔ ደቀ መዝሙር ኢትዮ ካናዳዊው ዘድንግል ደግሞ ለአማርኛ አዲስ መኾኑን በሚመሰክሩ ቃላቱ “እግዚአብሔር ቢፈቅድልኝና ቢሳካልኝ ቅኔ ካስመሰከርሁ በኋላ አቋቋም ተምሬ በውጭው ዓለም በማኅሌት ለማገልገልና በካናዳና በአካባቢው የሚኖሩ ወጣቶችን የአብነት ትምህርት ለማስተማር ዐሳብ አለኝ” በማለት የወደፊት ርእዩን አስገንዝቧል፡፡

 

በመርሐ ግብሩ ማጠቃለያም የቅዱሳት መካናት ልማትና ማኅበራዊ አገልግሎት ምክትል የቦርድ ሰብሳቢ ወይዘሮ ዓለም ፀሐይ መሠረት ማኅበረ ቅዱሳን ገዳማትና አብነት ትምህርት ቤቶች ካለባቸው ችግር አኳያ ከፍተኛ ትኵረት ሰጥቶ ምእመናንን በማስተባበር በሚገኘው ድጋፍና በተፈጥሮ ሀብቶች በመታገዝ ቅዱሳት መካናቱ ራሳቸውን እንዲችሉ ለማድረግ ልዩ ልዩ አገልግሎት በመስጠት ላይ እንደሚገኝ ጠቅሰው “በቤተ ክርስቲያናችን ከሚገኙ ብዙ ሺሕ ገዳማትና የአብነት ትምህርት ቤቶች ቍጥር አንጻር ኹሉንም ተደራሽ ለማድረግ አልተቻለም፤ በአሁኑ ሰዓትም የዕለት ጕርስ እንኳን የማያገኙ አባቶችና እናቶች ያሉባቸው ገዳማትና የአብነት ትምህርት ቤቶች ይገኛሉ፡፡ ስለዚህም ለወደፊቱ ከማኅበሩና ከምእመናን ከዚህ የበለጠ አገልግሎት ይጠበቃል” ብለዋል፡፡

 

በመጨረሻም በአባታዊ ምክራቸውና በጸሎታቸው ከማኅበሩ ጎን የማይለዩትን ብፁዕ አቡነ ሉቃስንና ሌሎችንም የቤተ ክህነትና የየገዳማት አባቶችን፤ በጎ አድራጊ ምእመናንን፤ በየጊዜው ርዳታ የሚያደርገውን የአሜሪካ ማእከልን፤ እንደዚሁም ለመርሐ ግብሩ መሳካት ልዩ ልዩ አስተዋጽኦ ያበረከቱ የማኅበረ ቅዱሳን ልዩ ልዩ ማእከል አባላትን፤ በዕለቱ የተገኙ የዐሥሩን ገዳማት አበ ምኔቶችንና እመ ምኔቶችችን ወ/ሮ ዓለምፀሐይ መሠረት ማኅበሩን ወክለው ምስጋና ካቀረቡ በኋላ በብፁዕ አቡነ ሉቃስ ጸሎተ ቡራኬ የመርሐ ግብሩ ፍጻሜ ኾኗል፡፡

2S0A7234.MOV02

 

በተያያዘ ዜና ዋና ክፍሉ በደቡብ ምሥራቅ ትግራይ ሀገረ ስብከት ለሚገኙት ለደብረ ገነት ቀቀማ ቅድስት ማርያም እና ደብረ ዓሣ አባ ዮሐኒ ገዳማት የምግብ ድጋፍ ማድረጉን የመቀሌ ማእከል ለዝግጅት ክፍላችን አስታውቋል፡፡

 

በድጋፍ መርሐ ግብሩም የገዳማቱ መነኮሳት፣ የዋናው ማእከልና የመቀሌ ማእከል አባላት ተገኝተዋል፡፡

 

የመቀሌ ማእከል ዋና ጸሐፊ አቶ ሐጋዚ አብርሃ እንደ ገለጹት ሁለቱ ጥንታውያን ገዳማት ካለባቸው የምግብ ችግር አኳያ ቅድሚያ የተሰጣቸው ሲኾን፣ ለሁለቱ ገዳማትም በአጠቃላይ የሃያ ኩንታል ጤፍ እና ሥንዴ ድጋፍ ተደርጎላቸዋል፡፡

ገዳማት

ከዚህ በፊትም በዚሁ ሀገረ ስብከት በሕንጣሎ ውጅራት ወረዳ ለምትገኘው ቅድስት አርሴማ ገዳም ተመሳሳይ ድጋፍ መደረጉን አቶ ሐጋዚ ጨምረው ገልጸዋል፡፡

 

በአካባቢው በተከሠተው ድርቅ ምክንያት የገዳማቱ መነኮሳት በደረሰባቸው ረኃብ በዓለ ትንሣኤን ሳይቀር ጥሬ ቆርጥመው ማሳለፋቸውንና የዕለት ጕርስ ለማግኘት በመቸገራቸውም በዓታቸውን ለቀው ለመውጣት መገደዳቸውን የቀቀማ ቅድስት ማርያም ገዳም አበምኔት መምህር አባ ሠርፀ ድንግል እና የደብረ ዓሣ አባ ዮሐኒ ገዳም አበ ምኔት መምህር አባ ተክለ አብ አብርሀ ይናገራሉ፡፡

 

በዚህ ዓመት የተከበረውን የትንሣኤ በዓልን አስመልክቶ በኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን በተዘጋጀው መርሐ ግብርም ይህ የገዳሙ ኹኔታ መዘገቡን የመቀሌ ማእከል አስታውሷል፡፡

 

ለወደፊቱም “ገዳማት ለቤተ ክርስቲያን ህልውና መሠረት ናቸው፤ ጳጳሳቱ፣ መነኮሳቱ፣ ቀሳውስቱና ዲያቆናቱ ምንጫቸው ገዳማት ናቸው፡፡ ከኹሉም በላይ ገዳማት ከእግዚአብሔር ምሕረትን የሚለምኑ፣ ዘወትር በጾም በጸሎት የሚተጉ አባቶች መኖሪያዎች ናቸውና ኹሉም ሕዝበ ክርስቲያን ገዳማትን ቢደግፍ መልካም ነው” ሲሉ የገዳሙ አባቶችና እናቶች ጥሪያቸውን ያስተላልፋሉ፡፡

የአውሮፓ ማእከል ፲፮ኛ ጠቅላላ ጉባኤ ተካሔደ

 

ሐምሌ ፲፭ ቀን ፳፻፰ ዓ.ም

በአውሮፓ ማእከል

ገገገገገ

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በሰንበት ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ማኅበረ ቅዱሳን የአውሮፓ ማእከል ፲፮ኛ ጠቅላላ ጉባኤ ከሐምሌ ፩-፫ ቀን ፳፻፰ ዓ.ም በስዊድን አገር ስቶክሆልም ከተማ ተካሔደ።

 

በጠቅላላ ጉባኤው በተለያዩ የአውሮፓ አገሮች የሚኖሩ ከሰባ በላይ የማእከሉ አባላት፤ የዋናው ማእከልና የሰሜን አሜሪካ ማእከል ተወካዮች፤ እንደዚሁም ጥሪ የተደረገላቸው ካህናትና ምእመናን ተሳትፈዋል።

 

በስቶክሆልም መንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ቤተ ክርስቲያን አስተዳዳሪ በመልአከ ብርሃን አባ ገብረ ጊዮርጊስ ካሣዬና በአውሮፓ ማእከል ሰብሳቢ በቀሲስ ዶ/ር ያብባል ሙሉዓለም የእንኳን አደረሳችሁ መልእክት ተላልፏል።

 

“እስክመጣ ድረስ ያላችሁን ጠብቁ” /ራእ.፪፥፳፭/ በሚል ኃይለ ቃል በመምህር ፍቃዱ ሣህሌ ትምህርተ ወንጌል ተሰጥቷል።

 

የዋናው ማእከል መልእክትም በተወካዩ በአቶ ታምሩ ለጋ አማካይነት ለጉባኤው ቀርቧል።

 

በጉባኤው የመገናኛ ብዙኃን አጠቃቀምንና መንፈሳዊ ሕይወትን የሚዳስሱ ጥናቶች የቀረቡ ሲኾን፣ እንደዚህ ዓይነት ጥናቶች ለመንፈሳዊ ሕይወት መጠንከር ጠቃሚ በመኾናቸው ለወደፊቱም በተሻለና በተጠናከረ መልኩ እንዲቀርቡ የሚል አስተያየት በጉባኤው ተሳታፊዎች ተሰጥቷል፡፡

 

በተመሳሳይ መልኩ “ልጆችን በቤተ ክርስቲያን በተቀናጀ መልኩ ለማስተማር የእኛ ድርሻ” በሚል ርእስ አጭር የግንዛቤ ማስጨበጫ ጽሑፍ በተተኪ ትውልድ ሥልጠና አገልግሎት ክፍል ቀርቧል።

 

በተጨማሪም የሰሜን አሜሪካ ማእከል ተወካይ አቶ ትእዛዙ ካሣ “የውጭ አገር የማኅበረ ቅዱሳን አገልግሎት ተግዳሮቶችና ዕድሎች” በሚል ርእስ በውጭ አገር ያለውን የአገልግሎት ኹኔታና የማእከሉን ተሞክሮ የሚያስገነዝብ ጽሑፍ አቅርበዋል፡፡

 

የማእከሉ የ፳፻፰ ዓ.ም የሥራ አፈጻጸም ዘገባ ቀርቦ በጉባኤው ተሳታፊዎች ሰፊ ውይይት ተደርጎበታል፡፡

 

የቀጣይ ስድስት ዓመት ስልታዊ ዕቅድ አቅጣጫዎችም በዋናው ማእከል ተወካይ በአቶ ታምሩ ለጋና በአውሮፓ ማእከል ምክትል ሰብሳቢ በዶ/ር ታጠቅ ፈቃዱ አማካይነት ለጉባኤው ቀርበዋል፡፡

 

ለሚቀጥሉት ሁለት ዓመታት ማእከሉን በሥራ አስፈጻሚነት የሚመሩ አባላትም በአባቶች ጸሎት በዕጣ ተመርጠዋል፡፡ የኦዲት እና ኢንስፔክሽን ክፍል ሓላፊም በጉባኤው ተሰይሟል።

 

የ፳፻፱ ዓ.ም የማእከሉ እና ኦዲትና ኢንስፔክሽን ክፍል የአገልግሎት ዕቅድም ለጉባኤው ቀርቦ ውይይት ከተደረገበት በኋላ በምልዓተ ጉባኤው ጸድቋል፡፡

 

በመጨረሻም ለጉባኤው መሳካት አስተዋጽኦ ላደረጉ ለመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ቤተ ክርስቲያን ካህናት፣ ለስዊድን ንዑስ ማእከል አባላት፣ ለሰንበት ት/ቤት ወጣቶችና ለአካባቢው ምእመናን የማእከሉ ሰብሳቢ ቀሲስ ዶ/ር ያብባል ሙሉዓለምና የጉባኤው አዘጋጅ ኰሚቴ ሰብሳቢ አቶ ሳምሶን መለሰ ምስጋና ካቀረቡ በኋላ ጠቅላላ ጉባኤው በአባቶች ጸሎት ተጠናቋል።

ስብከተ ወንጌል የልማት መሠረት

ሐምሌ ፲፩ ቀን ፳፻፰ ዓ.ም

በዲያቆን ኤፍሬም የኔሰው

ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ “ሒዱና አሕዛብን ኹሉ በአብ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም እያጠመቃችኋቸው ያዘዝኋችሁንም ኹሉ እንዲጠብቁ እያስተማራችኋቸው ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው” ሲል በአምላካዊ ቃሉ ያዘዘውን መሠረት በማድረግና የቅዱሳን ሐዋርያትን ፈለግ በመከተል ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን በርካታ ሰባክያንን እያስተማረች በየቦታው ስታሰማራ ኖራለች፤ ወደፊትም ይህንን ተልእኮዋን ትቀጥላለች፡፡

ምክንያቱም ስብከተ ወንጌል ቃለ እግዚአብሔርን ለማስተማር ብቻ ሳይኾን የሰውን አእምሮ ለማልማት (መልካም አስተሳሰብን ለመገንባት) የሚያስችል ዋነኛው የቤተ ክርስቲያን መሣሪያ ነውና፡፡ ስለዚህም ነው ቤተ ክርስቲያናችን ከየመጻሕፍት ቤቱና ከመንፈሳውያን ኮሌጆች በየጊዜው መምህራንን እያስመረቀች ለስብከተ ወንጌል አገልግሎት የምታሰልፋቸው፡፡

የቤተ ክርስቲያንን ተልእኮ ለማስፈጸም የተቋቋመው ማኅበረ ቅዱሳንም በየግቢ ጉባኤያቱ ትምህርተ ሃይማኖትን ከሚያስተምራቸው ወንድሞችና እኅቶች በተጨማሪ ከአባቶችና ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመመካከር በልዩ ልዩ የአገራችን ክፍሎች የሚገኙ በርካታ ሰባክያንን በየቋንቋው እያሠለጠነና በአባቶች ቡራኬ እያስመረቀ ለስብከተ ወንጌል አገልግሎት እንዲሠማሩ በማድረግ ላይ ይገኛል፡፡

ማኅበሩ በዚህ ዓመትም ይህንን ተልእኮውን በመቀጠል አሠልጥኖ ያስመረቃቸው ሰባክያነ ወንጌል ከመኖራቸውም ባሻገር በአሁኑ ሰዓት እየሠለጠኑ የሚገኙ ወንድሞችም በርካታ ናቸው፡፡

ለዚህም በአዳማ ከተማ በአፋን ኦሮሞ ሠልጥነው የተመረቁ ሰባክያን፤ እንደዚሁም በአዲስ አበባና በሐሮ እየሠለጠኑ የሚገኙ ወንድሞች ማስረጃዎች ናቸው፡፡

በማኅበረ ቅዱሳን የአዳማ ማእከል ከበጎ አድራዎች በተገኘ ድጋፍ ከልዩ ልዩ ገጠራማ ሥፍራዎች የተውጣጡ ፳፰ ሰባክያንን በአፋን ኦሮሞ አሠልጥኖ ሐምሌ ፰ ቀን ፳፻፰ ዓ.ም አስመርቋል፡፡

Publication1

በምረቃ ሥርዓቱም የምሥራቅ ሸዋ ሀገረ ስብከት ሥራ አስኪያጅ መጋቤ ትፍሥሕት ሙሉጌታ ቸርነት፣ የሀገረ ስብከቱ ሠራተኞችና የየአድባራቱ አገልጋይ ካህናት፣ የአገር ሽማግሎች፣ በጎ አድራጊ ምእመናንና የማእከሉ ሥራ አስፈጻሚ አባላት ተገኝተዋል፡፡

በምረቃ መርሐ ግብሩ ትምህርተ ወንጌልና ዝማሬ የቀረበ ሲኾን፣ ምሩቃኑ በማእከሉ የተዘጋጀላቸውን የምስክር ወረቀት፣ የመጽሐፍ ቅዱስና የነጠላ ስጦታ ከአባቶች እጅ ተቀብለዋል፡፡ እንደዚሁም ምሩቃኑ ሥልጠናውን እንዲያገኙ ላደረጓቸው የማእከሉ ሥራ አስፈጻሚ አባላት ልዩ ልዩ ስጦታ አበርክተዋል፡፡

ለሠልጣኞቹ የማኅበሩ ሥራ አስፈጻሚዎችና የዝግጅት ክፍላችን አባላት በተገኙበት ሰኔ ፳፬ ቀን ፳፻፰ ዓ.ም ለሠልጣኞቹ የእንኳን ደኅና መጣችሁ አቀባበል የተደረገ ሲኾን፣ በዕለቱ የማኅበረ ቅዱሳን ዋና ጸሐፊ አቶ ተስፋዬ ቢኾነኝ፡- “ይህንን ሥልጠና ካጠናቀቃችሁ በኋላ ስብከተ ወንጌል መስጠት ብቻ ሳይኾን የአብነት ትምህርት በመማር ሥልጣነ ክህነት ተቀብላችሁ የሚያጠምቃቸውና ቀድሶ የሚያቈርባቸው ካህን ላላገኙ ወገኖቻችን ልትደርሱላቸው ይገባል በማለት መልእክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

የማኅበሩ ምክትል ዋና ጸሐፊ አቶ ሰይፈ ዓለማየሁ በበኩላቸው፡- “የስብከተ ወንጌል አገልግሎት በቃል ብቻ ሳይኾን በሕይወትም የሚሰበክ ተልእኮ መኾኑን ሳትዘነጉ በምትሔዱበት ስፍራ ኹሉ ለምታስተምሯቸው ምእመናንም ኾነ ለሌሎች ወጣቶች መልካም ምሳሌ ልትኾኑ ይገባል” ሲሉ ምክራቸውን ለግሰዋል፡፡

የአዳማ ማእከል ሰብሳቢ መ/ር ጌትነት ዐሥራት ደግሞ ሥልጠናው ሌሊትና ቀን ሲሰጥ መቆየቱን ጠቅሰው፣ ከትምህርተ ሃይማኖት በተጨማሪ የሥራ አመራር፣ የጊዜ አጠቃቀም፣ የስብከት ዘዴ፣ ወቅታዊ ኹኔታ፣ አገልግሎት፣ የሕይወት ተሞክሮና ተዛማጅ መርሐ ግብራት በሥልጠናው መካተታቸውን ገልጸዋል፡፡

ሰብሳቢው በመጨረሻም ለሥልጠናው መሳካት አስተዋጽኦ ላበረከቱ አባቶችና በጎ አድራጊ ምእመናን በማእከሉ ስም ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡

በተያያዘ ዜና በማኅበረ ቅዱሳን ትምህርትና ሐዋርያዊ አገልግሎት ዋና ክፍል የስብከተ ወንጌል ማስፋፊያ መርሐ ግብር ከ፳፫ ጠረፋማ አህጉረ ስብከት የተውጣጡ ሰባክያንን በማሠልጠን ላይ ይገኛል፡፡

የስብከተ ወንጌል ማስፋፊያ መርሐ ግብሩ አስተባባሪ አቶ ጌትነት ወርቁ ለዝግጅት ክፍላችን እንደ ገለጹት ከሰኔ ፳፮ ቀን እስከ ሐምሌ ፳፰ ቀን ፳፻፰ ዓ.ም ለአንድ ወር በሚቆየው በዚህ ሥልጠና የሚሳተፉ ሠልጣኞች ብዛት ፻፴ ሲኾን፣ ከእነዚህ መካከል ፵ዎቹ የዓቅም ማጎልበቻ፤ ፺ዎቹ ደግሞ የስብከተ ወንጌል ሥልጠና የሚወስዱ ወንድሞች ናቸው፡፡

ሥልጠናው የዓቅም ማጎልበቻ እና የስብከተ ወንጌል ሥልጠና በሚሉ አርእስት ለሁለት ተከፍሎ የሚሰጥ ሲኾን፣ የዓቅም ማጎልበቻው በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት በለቡ አቡነ ጎርጎርዮስ ትምህርት ቤት፤ የስብከተ ወንጌል ሥልጠናው ደግሞ በደቡብ ምዕራብ ሸዋ ሀገረ ስብከት በሶዶ ዳጪ ወረዳ ቤተ ክህነት በሐሮ ደብረ ጽጌ ቅዱስ በዓለ ወልድ ወቅዱስ ዑራኤል ገዳም የስብከተ ወንጌል አዳራሽ በመሰጠት ላይ ነው፡፡

የዓቅም ማጎልበቻ ሥልጠናው ከዚህ በፊት የስብከተ ወንጌል ሥልጠና ወስደው በየቋንቋቸው ሲሰብኩ ለነበሩ ወንድሞች እንደተዘጋጀና ዓላማውም ሠልጣኞቹ እንደ እነርሱ ያሉ ብዙ ሰባክያነ ወንጌልን እንዲያፈሩ፤ እንደዚሁም የተጠመቁ ወገኖችን በማጽናት በየቦታው የጽዋ ማኅበራትንና ሰንበት ት/ቤቶችን እንዲመሠርቱ፤ የተመሠረቱትንም እንዲያጠናክሩ ለማድረግ ለመጀመሪያ ጊዜ እንደ ተዘጋጀ፤ የስብከተ ወንጌል ሥልጠናው ደግሞ በልዩ ልዩ ቋንቋ የሚያስተምሩ ሰባክያነ ወንጌልን ለማፍራት የሚሠጥ ሥልጠና እንደ ኾነ አቶ ጌትነት አስታውቀዋል፡፡

ለሠልጣኞቹም የሶዶ ዳጪ ወረዳ ቤተ ክህነት ሊቀ ካህንና ሠራተኞች፣ የገዳሙ አበ ምኔትና ካህናት፣ የወረዳው አስተዳዳሪና ሠራተኞች፣ የማኅበረ ቅዱሳን ልዩ ልዩ ክፍሎች አገልጋዮችና በጎ አድራጊ ምእመናን በተገኙበት ሐምሌ ፪ ቀን ፳፻፰ ዓ.ም በሐሮ ደብረ ጽጌ ቅዱስ በዓለ ወልድ ወቅዱስ ዑራኤል ገዳም የእንኳን ደኅና መጣችሁ አቀባበል ተደርጎላቸዋል፡፡

በዕለቱ በቦታው ተገኝተን ቃለ መጠይቅ ያደርግንላቸው የወረዳው ቤተ ክህነት ሊቀ ካህን መልአከ ኃይል ቀሲስ ጀምበር ደበላ “ሥልጠናው በሐሮ ገዳም መሰጠቱ የአካባቢውን ምእመናን ከእኛስ ምን ይጠበቃል? እንዲሉና ወረዳ ቤተ ክህነቱም ለተሻለ አገልግሎት እንዲተጋ ያደርገዋል” ካሉ በኋላ ሥልጠናው እስኪጠናቀቅ ድረስ ዓቅማቸው በሚፈቅደው ኹሉ ለሠልጣኞቹ ድጋፍ እንደሚያደርጉ ቃል ገብተዋል፡፡

የገዳሙ አስተዳዳሪ ሊቀ ጉባኤ አባ ኤልያስ ወልደ ሥላሴ ደግሞ “ሠልጣኞቹ ከ፳፫ አህጉረ ስብከት የተውጣጡ የልዩ ልዩ ብሔረሰብ አባላት ናቸው፡፡ ስለዚህም ኢትዮጵያ ሐሮ ላይ ተሰብስባለች ማለት ይቻላል፡፡ እኛም በሠልጣኞቹ ፊት ስንገኝ በአበባ መካከል ላይ የቆምን ያህል ይሰማናል” ብለዋል፡፡ አያይዘውም “እግዚአብሔር ማኅበሩን ይጠብቅልን” ሲሉ ማኅበረ ቅዱሳንን መርቀዋል፡፡

የሶዶ ዳጪ ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ ባጫ ኮምቦሌ በበኩላቸው “እንደዚህ ዓይነት ሥልጠና በእኛ ቀበሌ መሰጠቱ ለወረዳው ብቻ ሳይኾን ለአገር ሰላምና ልማትም የጎላ አስተዋጽኦ ይኖረዋል፡፡ ምክንያቱም ሃይማኖት ሰላም ነው፤ ሃይማኖት ልማት ነው፡፡ ዛሬ የተካሔደው የችግኝ ተከላ መርሐ ግብርም አንዱ የልማት ማሳያ ነው” ሲሉ አስተያየት ሰጥተዋል፡፡

ከአቀባበሉ ሥርዓት ቀጥሎም በቢትወደድ ባሕሩ አብርሃም አስተባባሪነት ጥሪ በተደረገላቸው እንግዶችና በሠልጣኞቹ የችግኝ ተከላ መርሐ ግብር ተከናውኗል፡፡ የችግኝ ተከላው ዓላማም ቤተ ክርስቲያን ወንጌልን ብቻ ሳይኾን ልማትንም እንደምታስተምር ለማመልከት መኾኑን ቢትወደድ ባሕሩ ተናግረዋል፡፡

በመጨረሻም ለዚህ ሥልጠና ልዩ ልዩ አስተዋጽኦ ላበረከቱ አባቶች፤ ከአራት መቶ ሺሕ ብር በላይ በማውጣት የሥልጠናውን ሙሉ ወጪ ለሸፈኑት አንድ በጎ አድራጊ ወንድም፤ እንደዚሁም በአዳራሽ፣ በቁሳቁስ አቅርቦትና በመስተንግዶ በማገዝ ላይ ለሚገኙ ምእመናን የስብከተ ወንጌል ማስፋፊያው አስተባባሪ ማኅበሩን በመወከል ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡

የአሜሪካ ማእከል ልዩ ዐውደ ጥናት ሊያካሒድ ነው

ሐምሌ ፮ ቀን ፳፻፰ ዓ.ም

በአሜሪካ ማእከል

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የሰንበት ትምህርት ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ማኅበረ ቅዱሳን የአሜሪካ ማእከል *የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አስተዋጽኦ* በሚል ርእስ በፕሪንስተን ከሚገኘው /The Institute for Advanced Semitic Studies and Afroasiatic Studies/ በመባል ከሚታወቀው የሴሜቲክና የአፍሮ እስያ ከፍተኛ ምርምርና ጥናት ተቋም ጋር በመተባበር ሐምሌ ፳፬ ቀን ፳፻፰ ዓ.ም ልዩ ዐውደ ጥናት ያካሒዳል።

ዐውደ ጥናቱ በዋናነት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በተለያየ ዘርፍ ለኢትዮጵያና ለዓለም ያበረከተችውን አስተዋጽኦ በጥልቀት እንደሚዳስስና ቤተ ክርስቲያኗ ይህንን አስተዋጽኦና ሚናዋን በዘመናችን እንዴት ማስቀጠል እንዳለባት እንደሚመክር አዘጋጆቹ አስታውቀዋል።

ይህ ዐውደ ጥናት በታዋቂው የአሜሪካ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ መደረጉ የቅድስት ቤተ ክርስቲያናችንን አስተዋጽኦ ለዓለም ለማስተዋወቅ መልካም አጋጣሚ እንደሚፈጥርም ተጠቁሟል፡፡

በዐውደ ጥናቱ የፕሪንስተን ዩኒቨርሲቲ ፕሮፌሰር የኾኑት ኤፍሬም ይስሐቅ *የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን* በሚል ርእስ ያሳተሙት መጽሐፍ ለቤተ ክርስቲያን አገልግሎት ስለሚኖረው ፋይዳና በመጽሐፉ ጠቅላላ ይዘት ላይ ሰፊ ውይይት ይደረጋል፡፡

በአሜሪካ አህጉረ ስብከት ሊቃነ ጳጳሳት መልካም ፈቃድ በሚዘጋጀው በዚህ ልዩ ዐውደ ጥናት ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት፣ ካህናት፣ ምሁራን፣ የአሜሪካ ግዛቶችና የአካባቢው ምእመናን፣ እንደዚሁም የውጪ ሀገር ዜጎችና ተጋባዥ እንግዶች እንደሚሳተፉበት ከጥናቱ አዘጋጆች ለመረዳት ተችሏል።

ሊቀ ማእምራን ወመጋቤ ሐዲስ ወልደ ሰንበት ባይነሳኝ ዐረፉ

ሐምሌ ፩ ቀን ፳፻፰ ዓ.ም

በዲያቆን ቴዎድሮስ ኃይሉ

በሕይወት ዘመናቸው ኹሉ ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይሉ ቅድስት ቤተ ክርስቲያንን በቅንነትና በታማኝነት ሲያገለግሉ የነበሩት ታላቁ የቤተ ክርስቲያን ሊቅ፣ የትሕትናና የጸሎት አባት ሊቀ ማእምራን ወመጋቤ ሐዲስ ወልደ ሰንበት ባይነሳኝ ዐረፉ፡፡

0001

ከአቶ ባይነሳኝ ላቀውና ከወ/ሮ በፍታ ተሾመ ሐምሌ ፲፩ ቀን ፲፱፻፳፰ ዓ.ም በላስታ ደብረ ዘመዶ አካባቢ የተወለዱት፤ የአቋቋም፣ የቅኔ፣ የፍትሐ ነገሥትና የሐዲስ ኪዳን ትርጓሜ መምህሩ መጋቤ ሐዲስ ወልደ ሰንበት፣ ልዩ የትርጓሜ ጸጋ የተሰጣቸው፤ ፍቅረ ነዋይ የራቀላቸውና የሚያስተምሩትን ቃለ እግዚአብሔር በሕይወት የኖሩ አባት ነበሩ፡፡

መጋቤ ሐዲስ ወልደ ሰንበት ከ፲፱፻፷፭ ዓ.ም ጀምሮ በሰሜን ጎንደር ሀገረ ስብከት በመካነ ነገሥት ግምጃ ቤት ማርያም ቤተ ክርስቲያን ለአምስት ዓመታት ያህል በምክትል መምህርነት ያገለገሉ ሲኾን፣ የጉባኤው መምህር የኔታ ክፍሌ ካረፉበት ከ፲፱፻፸ ዓ.ም ጀምሮ እስከ ዕለተ ዕረፍታቸው ድረስም ጉባኤ ተክለው፣ ወንበር ዘርግተው በማስተማር በርካታ ሊቃውንትን አፍርተዋል፡፡

ከመካነ ነገሥት ግምጃ ቤተ ማርያም ቤተ ክርስቲያን ጉባኤ ቤት ደቀ መዛሙርት ያገኘነው መረጃ እንደሚያመለክተው፣ መጋቤ ሐዲስ ወልደ ሰንበት ባደረባቸው ሕመም ምክንያት በሕክምና ሲረዱ ቆይተው በተወለዱ በ፹ ዓመታቸው ሐምሌ ፩ ቀን ፳፻፰ ዓ.ም ከዚህ ዓለም በሞተ ሥጋ ተለይተዋል፡፡

ሥርዓተ ቀብራቸውም ሐምሌ ፪ ቀን ፳፻፰ ዓ.ም በሰሜን ጎንደር ሀገረ ስብከት በመካነ ነገሥት ግምጃ ቤት ማርያም ቤተ ክርስቲያን ይፈጸማል፡፡

የሊቁን የመጋቤ ሐዲስ ወልደ ሰንበትን አጠቃላይ አገልግሎትና ሙሉ የሕይወት ታሪክ ወደ ፊት በስፋት ይዘን እንቀርባለን፡፡

የካናዳ ማእከል ፲፪ኛ ጠቅላላ ጉባኤ ተካሔደ

ሐምሌ ፩ ቀን ፳፻፰ ዓ.ም

በካናዳ ማእከል

0002

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በሰንበት ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ማኅበረ ቅዱሳን የካናዳ ማእከል ፲፪ኛ ጠቅላላ ጉባኤ ከሰኔ ፳፭-፳፯ ቀን ፳፻፰ ዓ.ም በሀገረ ካናዳ አልበርታ ግዛት በካልጋሪ ከተማ ተካሔደ፡፡

በካናዳ ልዩ ልዩ ግዛቶች የሚገኙ የማኅበሩ አባላት የተሳተፉበት ጉባኤው በካልጋሪ ሐመረ ኖኅ ኪዳነ ምሕረት አገልጋይ ካህናትና ዲያቆናት በጸሎተ ወንጌል ከተከፈተ በኋላ፣ የካናዳ ሀገረ ስብከትና የማኅበሩ መልእክቶች ቀርበዋል፡፡

 

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የካናዳ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ማትያስ በመልእክታቸው የማኅበረ ቅዱሳን ካናዳ ማእከል አባላት በሀገረ ስብከተቻውና በካናዳ በሚገኙ ፲፱ አብያተ ክርስቲያናት የሚሰጡትን ሰፊ አገልግሎት ዘርዝረው፤ “በየአጥቢያችሁ ከሚገኙ ካህናትና ምእመናን ጋር በመተባበር ለቤተ ክርስቲያን ዕድገት፤ ለስብከተ ወንጌል መጠናከርና ለሰንበት ት/ቤት አገልግሎት መፋጠን ለሕፃናት ትምህርት ልዩ ትኩረት በመስጠት አገልግሎታችሁን የበለጠ እንድታጠናክሩ” ሲሉ አባላቱን አሳስበዋል፡፡

ጉባኤው ስለ ቤተ ክርስቲያን ወቅታዊ ኹኔታና የማኅበሩ እንቅስቃሴ፤ ስለ ቅዱሳት መካናትና አብነት ት/ቤቶች ነባራዊ ኹኔታና ስለሚያስፈልጋቸው ድጋፍ፤ የአባላትና የምእመናንን ተሳትፎ ስለ ማሳደግና በሌሎችም አጀንዳዎች ላይ ሰፊ ውይይት አድርጎ ጠቃሚ ውሳኔዎችን አስተላልፏል፡፡

በተጨማሪም የማእከሉ የ፳፻፰ ዓ.ም የአገልግሎት እንቅስቃሴ ሪፖርትና የ፳፻፱ ዓም የአገልግሎት ዕቅድ ቀርቦ ሰፊ ውይይት ተደርጎበታል፡፡ የ፳፻፱ ዓም የአገልግሎት ዕቅዱም በምልዓተ ጉባኤው ሙሉ ድምፅ ጸድቋል፡፡

በመጨረሻም አባላቱ በያሉበት ኾነው አገልግሎታቸውን ለማጠናከር ቃል ከገቡ፤ ፲፫ኛው የማእከሉ ጠቅላላ ጉባኤም ኦታዋ ላይ እንዲካሔድ ከተወሰነ በኋላ ጠቅላላ ጉባኤው በጸሎት ተፈጽሟል፡፡

የሕንፃ ቤተ ክርስቲያኑ ቃጠሎ መንሥኤ እየተጣራ ነው

ሐምሌ ቀን ፳፻፰ .

በዲያቆን ተመስገን ዘገየ

shema mareyam church

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በደቡብ ጎንደር ሀገረ ስብከት በስማዳ ወረዳ ቤተ ክህነት ሽሜ አዝማቾ ቀበሌ በምትገኘው በሽሜ ማርያም ሕንፃ ቤተ ክርስቲያን ላይ የደረሰው የእሳት ቃጠሎ መንሥኤ በወረዳው ፖሊስ ጽ/ቤት እየተጣራ እንደሚገኝ የወረዳ ቤተ ክህነቱ ሊቀ ካህን ቄስ ሞላ ጌጡ ተናገሩ፡፡

በቃጠሎው በሕንፃ ቤተ ክርስቲያኑ፣ በጥንታውያን የብራና መጻሕፍት፣ በመስቀሎች፣ በአልባሳትና በሌሎችም ንዋያተ ቅድሳት ላይ ከፍተኛ ጉዳት መድረሱን የወረዳ ቤተ ክህነቱ ሊቀ ካህን አስታውቀዋል፡፡

የቀበሌው ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሲሳይ በየነ እንደ ተናገሩት የአካባቢው ሕዝበ ክርስቲያን እሳቱን ለማጥፋት ከፍተኛ ጥረት ቢያደርግም የእሳት ቃጠሎው የደረሰው በሌሊት በመኾኑ አዳጋውን ለመቀነስ የተደረገው ጥረት ሳይሳካ ቀርቷል፡፡

ሰኔ ፯ ቀን ፳፻፰ ዓ.ም መንሥኤው ባልታወቀ ምክንያት በሽሜ ማርያም ሕንፃ ቤተ ክርስቲያን ላይ የእሳት ቃጠሎ አደጋ መድረሱ ይታወሳል፡፡ የቃጠሎው መንሥኤም በወረዳው ፖሊስ ጽ/ቤት እየተጣራ ይገኛል፡፡

*ከቃል በላይ ትኩረት ለቅዱስ ያሬድ*

ሰኔ ፳፰ ቀን ፳፻፰ ዓ.ም

በዲያቆን ኤፍሬም የኔሰው

እሑድ ሰኔ ፳፮ ቀን ፳፻፰ ዓ.ም በጠቅላይ ቤተ ክህነት አዳራሽ አንድ ልዩ መርሐ ግብር ተካሒዷል፡፡ መርሐ ግብሩን ያዘጋጀው የማኅበረ ቅዱሳን ትምህርትና ሐዋርያዊ አገልግሎት ዋና ክፍል ሲኾን፣ ዓላማውም የቤተ ክርስቲያናችን ብርሃን፣ የአገራችን ጌጥ የኾነውን ቅዱስ ያሬድንና ሥራዎቹን መዘከር ነው፡፡

በዕለቱ *ወሰማዕኩ ድምፀ ብዙኃን መላእክት በዐውዱ ለውእቱ መንበር፤ በዙፋኑም በእንስሶቹም በሽማግሌዎቹም ዙሪያ የብዙ መላእክትን ድምፅ ሰማሁ* /ራእ.፭፥፲፩/ በሚል ኃይለ ቃል ትምህርተ ወንጌል የሰጡት መጋቤ ሐዲስ ምሥጢረ ሥላሴ ማናየ *ቅዱስ ያሬድ ወንጌላዊው ዮሐንስ በራእይና በንባብ የነገረንን ሰማያዊ ማኅሌት በዜማ የተረጐመልን፤ ከጠፈር በላይ ያለውን ምሥጢር ለዓለም የገለጠ፤ ቤተ ክርስቲያንን ለምስጋና ያመቻቸ፤ የመላእክትን ዜማ ከሰው ጋር ያስተዋወቀ በአጠቃላይ በተፈጥሮው ሰው፣ በግብሩ መልአክ ነው* ብለው አስተምረዋል፡፡

*እንደ ቅዱስ ያሬድ ያሉ ቅዱሳን የእግዚአብሔር መመስገኛ ዐውዶች ናቸው* ያሉት መጋቤ ሐዲስ ቅዱስ ያሬድ ትምህርቱን፣ ዜማውን ያገኘው ከሰው ሳይኾን ከእግዚአብሔር መኾኑን ገልጸው *የእግዚአብሔር ጸጋ ያላደረበት ሰው ዜማውን መስማትም መሸከምም አይቻለውም* ሲሉ አስረግጠው ተናግረዋል፡፡ መጋቤ ሐዲስ በመጨረሻም *ከቃል በላይ ትኩረት ለቅዱስ ያሬድ* በማለት የዕለቱን ትምህርት አጠቃለዋል፡፡

በመርሐ ግብሩ የመጽሐፍ ቅዱስና የቅዱስ ያሬድ ሥራዎችን ዝምድና የሚያስገነዝብ ጥናታዊ ጽሑፍ ያቀረቡት መጋቤ ስብሐት ሲሳይ ወጋየሁ በጥናታቸው መጽሐፈ ድጓ ምሥጢሩ ሙሉ በሙሉ የተወሰደው ከመጽሐፍ ቅዱስ መኾኑን ምሳሌዎችን በመጠቀስ አስረድተዋል፡፡

በዕለቱ ቅዱስ ያሬድንና ሥራዎቹን የሚዘክሩ፤ እንደዚሁም ትውልዱ ከውጭው ዓለም ተጽዕኖ ነጻ ወጥቶ እንደ ቅዱስ ያሬድ ያሉ ሊቃውንትን ፈለግ መከተል እንደሚገባው የሚጠቁሙ ቅኔያት በታዕካ ነገሥት በዓታ ለማርያም ደቀ መዝሙር ተበርክተዋል፡፡

በተጨማሪም *ብፅዕት ከርሥ እንተ ጾረተከ ወብፁዓት አጥባዕት እለ ኀፀናከ አልቦ ዘየዐብዮ ወዘይሤንዮ ለላሕይከ ያሬድ ካህን* የሚል ቅዱስ ያሬድን የተሸከመችውን ማኅፀንና የጠባቸውን ጡቶች የሚያደንቅ፤ እንደዚሁም የካህኑ ያሬድን ላሕየ ዜማ (የዜማውን ማማር) የሚያሞግስ ዝማሬ በዋናው ማእከልና የአዲስ አበባ ማእከል ዘማርያን ቀርቧል፡፡

በተመሳሳይ መልኩ የውሉደ ያሬድ ሰንበት ትምህርት ቤት መዘምራን *አሠርገዋ ለኢትዮጵያ በስብሐት ወበሃሌ ሉያ ያሬድ ካህን ፀሐያ ለቤተ ክርስቲያን* በማለት ቅዱስ ያሬድ ኢትዮጵያን በምስጋና ማስጌጡን የሚያስረዳና የቤተ ክርስቲያን ፀሐይ መኾኑን የሚገልጽ ጣዕመ ዝማሬ አሰምተዋል፡፡

የማኅበረ ቅዱሳን መዝሙርና ኪነ ጥበብ አባላትም የቤተ ክርስቲያንን አስተምህሮ የጠበቀና የቅዱስ ያሬድን ዜማ መሠረት ያደረገ መዝሙር ማጥናትና መዘመር እንደሚገባ የሚያስገነዝብ ተውኔት አሳይተዋል፡፡

ቅዱስ ያሬድንና ሥራዎቹን ለመዘከር የተዘጋጀው ይህ መርሐ ግብር በጸሎት ተጀምሮ በጸሎት ተጠናቋል፡፡

የቤተ ክርስቲያን ትምህርት የመልካም ምግባር መሠረት!

ሰኔ ፳፯ ቀን ፳፻፰ ዓ.ም

በዲያቆን ኤፍሬም የኔሰው

የማኅበረ ቅዱሳን ጥናትና ምርምር ማእከል ሰኔ ፳፬ ቀን ፳፻፰ ዓ.ም በማኅበሩ ሕንፃ ሦስተኛ ፎቅ አዳራሽ የጥናት ጉባኤ አዘጋጅቶ ነበር፡፡

በዕለቱ *ሥነ ምግባርና ግብረ ገብነት* በሚል ርእስ በአቶ ዓለማየሁ ተክለ ማርያም (በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ትምህርትና ሥነ ባሕርይ ጥናት ኮሌጅ ተባባሪ ፕሮፌሰር) በቀረበው ጥናታዊ ጽሑፍ በአሁኑ ጊዜ በተለይ በከተማ አካባቢዎች በአብዛኞቹ ወጣቶች ዘንድ የሥነ ምግባር ጉድለት ማለትም ሰውን አለማክበር፣ ወላጆችንና መምህራንን መሳደብ፣ ከውጪው ዓለም የተወሰዱ ኢ-ግብረገባዊ የኾኑ ተግባራትን መፈጸም ወዘተ ዓይነት ጎጂ ባህሎች እየተለመዱ መምጣታቸው፤ ይህም የአገራችንን መልካም ገጽታ እያጠፋ እንደሚገኝ፤ ወጣቱ ትውልድ ቃለ እግዚአብሔርን ቢማርና ቅዱሳት መጻሕፍትን ቢመረምር የጠባይ ለውጥ እንደሚያመጣና የመልካም ምግባር ባለቤት መኾን እንደሚችል ተገልጿል፡፡

የአቶ ዓለማየሁ ጥናት ከዓለም ዐቀፋዊው ግብረ ገብነት አንጻር ስትቃኝ አገራችን ኢትዮጵያ የተሻለች ብትኾንም፣ ከጊዜ ወደጊዜ ግን የዜጎቿ መልካም ባህል ማለትም መተሳሰብ፣ መከባበር፣ መጠያየቅ፣ መቻቻል፣ የአገር ፍቅር፣ ወዘተ የመሳሰለው ጥሩ ልምድ እየቀነሰ መምጣቱን፤ እንደዚሁም አብዛኛው ወጣት በተለይ በከተማዎች ኢ-ገብረገባዊ ባልኾኑ እንደ ሱስ፣ ስካር፣ ዝሙት፣ ትዕቢት፣ ሥርዓት አልባ አለባበስ፣ ወዘተ የመሳሰሉ ተግባራት መያዙን በማስረጃ አቅርቦ ለዚህም ዋነኛው ምክንያት በትውልዱ አእምሮ ውሰጥ የሥነ ምግባር ትምህርት አለመሥረጹና በተጨማሪም ወጣቱ ትውልድ በዘመናዊ አስተሳሰብ መማረኩ፤ እንደዚሁም አስነዋሪ መረጃዎችንና ምስሎችን በሚያስተላልፉ ሚድያዎች ተፅዕኖ ሥር መውደቅ መኾኑን አትቷል፡፡

ጥናቱ ግብረ ገብነት፣ ፈሪሃ እግዚአብሔር፣ ዐሥርቱ ትእዛዛት፣ ከክፉ ምግባር መራቅ፣ ሰውን መውደድና ማክበር፣ የአገር ፍቅር፣ ወዘተ የሚያስረዱ የቤተ ክርስቲያን ትምህርቶች በዘመናዊው ሥርዓተ ትምህርት ተካተው ለተማሪዎች ይሰጡ በነበሩበት ዘመን የማኅበረሰቡ የመከባበር፣ የመፈቃቀርና የመተሳሰብ ባህሉ ከፍተኛ እንደነበረና ይህ ባህል እየቀነሰ መምጣቱን አውስቶ በአሁኑ ሥርዓተ ትምህርትም ምንም እንኳን ከአምስተኛ ክፍል ጀምሮ እስከ ዐሥራ ሁለተኛ ክፍል ድረስ የሥነ ዜጋና ሥነ ምግባር ትምህርት ተዘጋጅቶ መሰጠቱ ቢበረታታም በተማሪዎች ዘንድ የሚታየው መምህራንን አለማክበር፣ ፈተና ከሌሎች ተማሪዎች መስረቅ፣ ሥርዓት የሌለው አነጋገርና አለባበስ፣ ወዘተ የመሰሳሰለውን ኢ-ግብረገባዊ ድርጊት ለማስተካከልና ትውልዱን የመልካም ሥነ ምግባር ባለቤት ለማድረግ ግን ከዚህ የበለጠ መሥራት እንደሚገባ አሳስቧል፡፡

ወጣቱ ትውልድ ቃለ እግዚአብሔር ቢማር እንደሚለወጥ ሲመሰክሩ *ዛሬ የተማራችሁት መጽሐፍ ቅዱስ የነገ ሕይወታችሁ ስንቅ ነው* ያሉት የጥናቱ ባለቤት አቶ ዓለማየሁ በመጨረሻም *ምን እናድርግ?* በሚለው የጥናታቸው መደምደሚያ የሰው ልጅ ሦስት የጠባይ መገለጫዎች እንዳሉት፣ እነዚህም አንደኛ የሚያደርገውን የማያውቅ፤ ሁለተኛ የሚያደርገውን የሚያውቅና ሕግን የሚፈራ ነገር ግን ኢ-ግብረገባዊ፤ ሦስተኛ ግብረ ገባዊ ሰው መኾናቸውን ጠቅሰው ኹሉም ሰው *በእግዚአብሔር ፊት ኀጢአት አልሠራም* እንዳለው እንደ ዮሴፍ ሦስተኛውን ጠባይ ገንዘብ ካደረገ የሥነ ምግባር ለውጥ ማምጣት እንደሚቻል ገልጸው የቤተ ክርስቲያን ትምህርት መማር፤ ግብረ ገባዊ ሕይወትን ማጠናከር፤ ታማኝትን፣ እውነትንና ፍቅርን ማሥረጽ፤ አእምሮን ከክፉ አስተሳሰብ ማጽዳትና የመሳሰሉ ተግባራት ለመልካም ምግባር መሠረቶች መኾናቸውን ጠቁመዋል፡፡

ምሩቃኑ ስለ መልካም አስተዳደር እንዲያስተምሩ ፓትርያርኩ መመሪያ ሰጡ፡፡

ሰኔ ፳፯ ቀን ፳፻፰ ዓ.ም

በዲያቆን ኤፍሬም የኔሰው

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሦስቱም መንፈሳውያን ኮሌጆች የዘር ወቅት በኾነው በወርኃ ሰኔ ደቀ መዛሙርታቸውን አስመርቀዋል፡፡

ከእነዚህ ኮሌጆች አንዱ በኾነው በቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ በልዩ ልዩ ትምህርት ክፍሎችና መርሐ ግብራት ሲማሩ የቆዩ ደቀ መዛሙርት ሰኔ ፳፭ ቀን ፳፻፰ ዓ.ም የተመረቁ ሲኾን፣ የምረቃ ሥርዓቱም ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ፣ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት፣ የጠቅላይ ቤተ ክህነትና የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የየመምሪያ ሓላፊዎች፣ የክፍለ ከተሞች ወረዳ ቤተ ክህነት ሠራተኞች፣ የአድባራትና የገዳማት አስተዳዳሪዎች፣ የኮሌጁ ሥራ አመራር አባላትና የምሩቃን ቤተሰቦች በተገኙበት በጠቅላይ ቤተ ክህነት አዳራሽ ተከናውኗል፡፡

የኮሌጁ አካዳሚክ ምክትል ዲን መምህር ግርማ ባቱ እንዳስታወቁት የቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ በካህናት ማሠልጠኛነት ከተፈተበት ከ፲፱፻፴፮ ዓ.ም ጀምሮ በነገረ ሃይማኖት ትምህርት በርካታ መምህራንን እያፈራ የሚገኝ ሲኾን፣ ለወደፊቱም በሦስተኛ ዲግሪና በዶክሬት መርሐ ግብር ለማስተማር ዝግጅት በማድረግ ላይ ነው፡፡ በአሁኑ ሰዓት በአጠቃላይ ከ፲፰፻ (አንድ ሺሕ ስምንት መቶ) በላይ ደቀ መዛሙርትን እያስተማረ የሚገኘው ኮሌጁ በዘንድሮው የምረቃ ሥርዓቱ የግእዝ ቋንቋን ጨምሮ በልዩ ልዩ የትምህርት ክፍሎችና መርሐ ግብራት በድምሩ ፫፳፬ ዕጩ መምህራንን አስመርቋል፡፡

የምረቃ ሥርዓቱ በጸሎተ ወንጌል ከተከፈተ በኋላ በመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ሰ/ት/ቤት መዘምራን ያሬዳዊ ዝማሬ የቀረበ ሲኾን፣ ምሩቃኑም ልዩ ልዩ መልእክት ያዘሉ ቅኔያትን አበርክተዋል፡፡ በመቀጠልም ከፍተኛ ውጤት ያስመዘገቡ፤ እንደዚሁም ከኹሉም መርሐ ግብራትና ትምህርት ክፍሎች ተመዝነው ከ፩ኛ እስከ ፭ኛ ደረጃ ያገኙ ሴት ምሩቃን ከቅዱስ ፓትርያርኩና ከኮሌጁ የበላይ ሓላፊ ከብፁዕ አቡነ ጢሞቴዎስ እጅ የምስክር ወረቀትና ሽልማት ተቀብለዋል፡፡

ቅዱስ ፓትርያርኩ በዕለቱ *መከሩስ ብዙ ነው፤ ሠራተኞች ግን ጥቂቶች ናቸው፡፡ እንግዲህ የመከሩን ጌታ ወደ መከሩ ሠራተኞችን እንዲልክ ለምኑት፤* /ማቴ.፱፥፴፯-፴፰/ የሚለውን ኃይለ ቃል መነሻ በማድረግ ቃለ ምዕዳን በሰጡበት ወቅት *እኛ መክረን አስተምረን ዐሥራት በኵራት እንዲከፍሉ ባናደርጋቸውም ምእመናን ልጆቻችን ያላቸውን ከመስጠት ወደ ኋላ አይሉም፡፡ በመኾኑም በቤተ ክርስቲያናችን በተለይ በዐበይት ከተሞች የገንዘብ እጥረት የለም፤ ነገር ግን ገንዘብ አያያዛችን በደንብ ያልተደራጀ ስለኾነና ሙስና ስለበዛ በአግባቡ አገልግሎት ላይ እየዋለ አይደለም፡፡ ስለዚህም በምትሰማሩበት ቦታ ኹሉ ሙስና እንዲጠፋ፣ መልካም አስተዳደር እንዲሰፍን፣ ሐቀኞች እንድንኾን፣ የቤተ ክርስቲያናችን ንጽሕናና ቅድስና እንዲጠበቅ ልታስተምሩ ይገባል* በማለት ለምሩቃኑ አባታዊ መመሪያ ሰጥተዋል፡፡

*በሦስቱም ኮሌጆቻችን የምትመረቁ ልጆቻችን የቤተ ክርስቲያናችን ብርሃን ናችሁ!* በማለት ምሩቃኑን ያወደሱት ቅዱስነታቸው ስብከተ ወንጌል ትልቁ የቤተ ክርስቲያን ተግባር መኾኑን ገልጸው *እናንተ ብርሃን ኾናችሁ ጨለማውን ዓለም እንድታበሩ፤ ወደ ሌላ ሃይማኖት የገቡትን አስተምራችሁ እንድትመልሱ፤ እምነታችሁን አጥብቃችሁ ሌሎችንም እንድታጠነክሩ፤ በየቦታው በመናፍቃን የተዘረፉ ምእመናንም እንድታስመልሱና ከዘረፋ እንድትታደጉ፤ ሕይወቱንና ጤንነቱን ይጠብቅ ዘንድ፤ ከሱስ፣ ከአደንዛዥ ዕፅ፣ ከስካርና ከመሳሰሉት እኩያን ምግባራት ይርቅ ዘንድ ወጣቱን እንድታስተምሩ ቤተ ክርስቲያናችን አደራዋን ታስላልፋለች* ብለዋል፡፡

ምሩቃኑም ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የሠራውን፤ ሐዋርያት ያስተማሩትን ሕገ ወንጌል እንደዚሁም በሦስቱ የቤተ ክርስቲያን ጉባኤያት የተወሰኑ ቀኖናዎችን እንደሚጠብቁና እንደሚያስጠብቁ፤ የእመቤታችንን የቅድስት ድንግል ማርያምን፣ የመላእክትንና የቅዱሳንን አማላጅነት እንደሚያስተምሩ፤ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሥርዓቷን፣ ቀኖናዋን፣ እምነቷን፣ አስተምህሮዋንና ዶግማዋን እንደሚፈጽሙና እንደሚያስፈጽሙ፤ በተመደቡበት ቦታ ኹሉ በታማኝነት እንደሚያገለግሉ ቃል ገብተዋል፡፡

በመጨረሻም በቅዱስ ፓትርያርኩ ጸሎተ ቡራኬ የምረቃው ሥርዓት ተፈጽሟል፡፡

በተያያዘ ዜና በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የከሣቴ ብርሃን ፍሬምናጦስ መንፈሳዊ ኮሌጅ በልዩ ልዩ ትምህርት ክፍሎችና መርሐ ግብራት ያስተማራቸውን ደቀ መዛሙርት ሰኔ ፲፱ ቀን ፳፻፰ ዓ.ም ማስመረቁ ይታወሳል፡፡