በአታ ለእግዝእትነ ውስተ ቤተ መቅደስ

ከደጋጎቹ ቅዱሳን አባቷና እናቷ ኢያቄምና ሐና የተወለደችው እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ወደ ቤተ መቅደስ የገባችበት ቀን የከበረ ነው፡፡ በበጎ ምክር በእግዚአብሐርም ፈቃድ ይህ ሆነ፤ በዚያን ጊዜ ኢያቄምና ሐና “….ሆዷ ዘመድ ሳይወድ አፏ እህል ሳይለምድ ወስደን እንስጥ” ብለው በመማከር መባዕም ጨምረው ወደ ቤተ መቅደስ ሄዱ፡፡   

ተዝካረ ልደቱ ለኤልያስ ነቢይ

ኀዳር ፴፤፳፻፲፰ ዓመተ ምሕረት

ቅዱሳት መጻሕፍት ነቢዩ ኤልያስ የተወለደው በታኅሣሥ ፩ ቀን ከነገደ ሌዊ እንደሆነ ይገልጻሉ፤ የአባቱ ስም ኢያስንዩ የእናቱ ስም ቶና ይባላሉ፡፡ በተቀደሰች የልደት ቀኑም አባቱ ብርሃን የለበሱ አራት ሰዎች ሲሰግዱለትና ሕፃናት በሚጠቀልሉበት ጨርቅ ፈንታ በእሳት ሲጠቅልሉት  ተመልክቷል፡፡ (መጽሐፈ ስንክሳር ዘኅዳር ፩፣ መዝገበ ታሪክ ገጽ ፹፬)

ኢትዮጵያ ሊቅ አባ ጊዮርጊስ ዘጋሥጫ በተአምኆ ቅዱሳን መጽሐፉ ስለዚሁ ነቢይ እንዲህ ሲል ተናግሯል፤ “ቴስቢያዊ (የቴስቢያ ሰው)፤ ኮሬባዊ (ወደ ኮሬብ ተራራ የወጣ)፣ ታቦራዊ (በታቦር ተራራ የተገኘ)፣ ዝናብ እንዳይዘንብ ሰማይን የለጐመ ለሆነ፣ የጸሎቱ ቃልም በአዶናይ ዦሮ ውስጥ ለተሰማ፣ ውኃውን እስኪበላ ደርሶ እሳትን ከሰማይ ያወረደ ለሆነ፣ በእሳት ሠረገላ ተጭኖ ወደ ተድላ ደስታ ቦታ ለገባ ለነቢዩ ለኤልያስ ሰላምታ ይገባል።”

ሊቁ አርከ ሥሉስም በአርኬ መጽሐፉ ላይ ደግሞ እንዲህ ብሏል፤ “ምድራዊ የሆነ የዓለም ሕይወትን አራግፈህ ለማረፍ ወደ ሰማያት ያረግህ ለሆንክ ለአንተ ለኤልያስ ሰላም እላለሁ፡፡ አክአብን ለተናቀ ሥራው እየዘለፍከው ጣዖታትን የቀጠቀጥክ ማምለኪያዎቹን ያፈረስክ በምስጋናህ ምንኛ ተመሰገንህ።”

ቅዱሱ መጽሐፍ የዚህን ፈፍ  ነቢይ ስም “ኤልያስ” ፻ (መቶ) ጊዜ ጠቅሶታል፡፡ ድንቃ ድንቅ ተአምራቱንም መዝቦት እናገኛለን፤ ከእነዚህም መካከል አክአብና ኤልዛቤል ጣዖት በማምለከታቸው ኤልያስ ሦስት ዓመት ከ ስድስት ወር ዝናብን በጸሎቱ አቁሟል፡፡ (፩ኛ ነገ. ፲፯)፤ የሰራጵታዋን መበለት የሞተ ልጇን አስነሥቷል፡፡ (፩ኛ ነገ.፲፯፥፲፱)

ለአምላካችን እግዚአብሔር ያቀረበውን መሥዋዕት እሳት ከሰማይ ወርዶ የበላለት ነቢይ እንደሆነም መጽሐፍ ቅዱስ ምስክር ነው፤ (፩ኛ ነገ ፲፰) ከሦስት ዓመት ከስድስት ወር በኋላ ቀርሜሎስ ወጥቶ በመጸለይ ዝናብ እንዲዘንብ አድርጓል፤ (፩ኛ ነገ. ፲፰) አካዝያስ የላካቸውን ፶ (ኀምሳ) አለቃዎች እሳት ከሰማይ አውርዶ አቃጥሏል፤ (፪ኛ ነገ. ፩) በመጐናጸፊያው የዮርዳኖስን ወንዝ ከፍሏል፤ (፪ኛ ነገ.፪፥፲፬) በእሳት ሠረገላ በዐውሎ ነፋስ ወደ ሰማይ ወጥቷል፤ (፪ኛ ነገ.፪፥፲፩)፣ በደብረ ታቦር ጌታ ምሥጢረ መንግሥቱን ሲገልጽ ከሙሴ ጋር ዐብሮ ተገኝቷል፤ (ማቴ.፲፯፥፬) ዳግመኛ በመምጣት በሐሳዌ መሲሕ ጊዜ ሰማዕትነትን ይቀበላል፡፡ (ማቴ.፲፯፥፲፩)

የነቢዩ ኤልያስ በረከት ይደርብን!

 

ሥዕለ አድኅኖ

 ክፍል ሦስት

ዲያቆን ተስፋዬ ቻይ 

ኀዳር ፴፤፳፻፲፰ ዓመተ ምሕረት

ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! እንዴት አላችሁ? እንኳን ለጾመ ነቢያት (የገና ጾም) አደረሳችሁ! ይህ ጾም የሚጾመው አባቶቻችንን ነቢያት እግዚአብሔር በሰጠን ተስፋ በገባልን ቃል ኪዳን መሠረት ከሰማያት ወርዶ እንዲያድነን “አቤቱ ውረድ፤ ተወለድ፤ አድነን” እያሉ የጾሙት ጾም ነው፤ እኛ ደግሞ ከሰማያት ወርዶ፣ ከእመቤታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም ተወልዶ አድኖናል እያልን ውለታውን እያስታወስን እንጾመዋለን፡፡ ከሰባቱ የዐዋጅ አጽዋማት አንዱ ስለሆነ እኛም እንደ አቅማችን ልንጾመው ይገባል! መልካም!

ትምህርታችሁንም በርትታችሁ ተማሩ! የመንፈቀ ዓመቱ ፈተናም እየተቃረበ ነው፤ በደንብ በማጥናት ጥሩ ውጤት ማስመዝገብ አለባችሁ! በሰንበት ቤተ ክርስቲያን በመሄድ መማርን፣ማገልገልንም እንዳትረሱ።

ባለፈው ትምህርታችን ስለ ሥዕለ አድኅኖ በተማርነው ትምህርት ሥዕለ አድኅኖ እንዴት መሣል እንዳለበት በመጠኑ ተምረናል፡፡ ዛሬ ደግሞ ሥዕለ አድኅኖ ሲሣል የምንጠቀማቸው ቀለማት (ከለር) ምን ዓይነት መሆን እንዳበቸውና ምክንያቱን የተወሰኑትን ለአብነት እንመለከታለን፡፡

ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! ለቅዱሳት ሥዕላት የምንጠቀማቸውን የቀለማት ውክልና ከማየታችን በፊት ቀለም ምንድን ነው የሚለውን እንመልከት፤ ቀለም የሚለውን ሊቁ አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ የቃላትን ፍቺ (ምሥጢር) በተረጎሙበት መጽሐፋቸው ቀለም በቁሙ “ኅብር፣ ፈሳሽ፣ ዓይነት፣ መጣፊያ፣ ማቅለሚያ” ብለው አብራርተውታል፡፡ (ኪዳነ ወልድ መዝገበ ቃላት ገጽ ፯፻፺፫/793)

ቀለማት በቅድስት ቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ ሥዕለ አድኅኖ ሲሣሉ የሚያስተላልፉት መልእክትም አላቸው፤ የፈጣሬ ዓለማት የቅድስት ሥላሴ፣ የእመቤታችን ቅድስት ደንግል ማርያምን፣ ሥዕል ሲሣል የሚቀባው ቀለም ዓይነት የራሱ የሆነ ትርጒምና የሚያስተላልፈው ነገር አለው፤ የቅዱሳን መላእክትን፣ የቅዱሳን አበውን፣ የቅዱሳት እናቶችን ሥዕልም በሚሳልበት ጊዜ የተጋድሏቸውን ጽናት፣ የክብራቸውን ዓይነት፣ የመጠሪያ ስያሜአቸውን ለመለያነትም ያገለግላል፡፡

ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! የቅዱሳን ሥዕለ አድኅኖ ሲሣል በሥዕሉ ባለቤት በራሱ           ዙሪያ በክብ ቅርጽ ጸዳለ ብርሃን (አክሊለ ብርሃን) ተደርጎ ይሣላል፤ በዚህም ለመግለጽ የተፈለገው ቅዱሳን በቤተ ክርስቲያን የቅድስና ማዕረግ እንደተሰጣቸው ለመግለጽ ነው፡፡

 ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! ክቡ ቅርጽ በቅድስት ሥላሴና በጌታችን በመድኃኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ሥዕለ አድኅኖ ላይ የሚደረገው ጸዳለ ብርሃን የእግዚአብሔር ቅድስና የባሕርይው መሆኑን ለመግለጽ ነው፡፡ ለቅዱሳን ሲደረግ ደግሞ አምላካችን የባሕርይ ቅድስናውን መልካም በመሥራታቸው በጸጋ (በስጦታ) ለቅዱሳን ቅድስናን እንደሰጣቸው ለመግለጽ የቅዱሳት ሥዕለ አድኅኖ ሲሣል በራሳቸው ዙሪያ በብርሃን ክብ ቅርጽ ይደረግላቸዋል፡፡

 ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! በቤተ ክርስቲያናችን ቀኖና መሠረት አብዛኛውን ጊዜ የምንጠቀማቸው ቀለማት ነጭ፣ ሰማያዊ፣  ቢጫ፣ አረንጓዴና ቀይ ሲሆኑ ቀለማቱ ራሱን የቻለ ምሥጢር ወይም ትርጒም አላቸው፡፡

 ነጭ፡- የድል አድራጊነት፣ የንጽሕና እና የፍጹምነት ምሳሌ ነው፡፡ ቅዱሳን ዓለምንና ምኞቱን ድል ያደረጉ ልበ ንጹሐን በመሆናቸው ነጭ ልብስ ለብሰው ይሣላሉ፡፡ እንዲሁም ደግሞ መለኮታዊ ክብርንም ያሳያል፡፡ ለምሳሌ በደብረ ታቦርና በትንሣኤ ሥዕሎች ላይ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነጭ ልብስ ለብሶ ይሣላል፡፡ (ኦርቶዶክሳዊ ቅዱሳት ሥዕላት ገጽ ፸፬)

ሰማያዊ፡- ሥዕለ አድኅኖ ሲሣሉ ሰማያዊ ቀለምን መቀባቱ በመልካም ሥራው ሰማያዊውን ሀብት (መንግሥተ ሰማያትን) ገንዘብ ለማድረግ (ለመውረስ) አባቶቻችን ቅዱሳን በፈቃደ ነፍስ ለመመራት መልካም ሥራን ለመሥራታቸው፣ ኃጢአትን መጥላታቸውን ለሰዎች መልካምን ማድረጋቸውን ለማመልከት እንዲሁም በመንፈስ ፍሬዎች በተባሉ በትዕግሥት፣ በትሕትና፣በፍቅር፣ በደስታ፣ በእምነት፣ በቸርነት (ገላ. ፭፥፳፪) ፈቃደ ሥጋን (ክፉ ምኞቶችን ሁሉ ድል ማድረጋቸውን ለማመልከት ለሥዕለ አድኅኖ ሲሣሉ ይህንን ቀለም እንጠቀመዋለን፡፡ሌላው ደግሞ ከቁጣ፣ ከቂም፣ ከበቀል ርቀው በትሕትናን ለመኖራቸው ምሳሌ ነው፡፡

 ቢጫ፡- ይህ ቀለም እውነተኛነትንና ብርሃንነትን ይገልጻል፡፡ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በትምህርቱ ‹‹እናንተ የዓለም ብርሃን ናችሁ …›› (ማቴ.፭፥፲፬) በማለት እንዳስተማረው በመልካም ሥራቸው ለሌላው ብርሃን የሆኑትን ቤተ ክርስቲያን የቅድስና ማዕረግ ላይ የደረሱትን ቅዱሳን እውነተኞችና የዓለም ብርሃን ናችሁ ስትል በራሳቸው የብርሃን አክሊል በቢጫ አድርጋ ትሥላለች፡፡

አረንጓዴ፡- ከልምላሜና ከጸዳል ጋር ስለሚያያዝ መንፈሳዊ ትርጒሙ መታደስን አዲስ ሕይወት፣ ደኅንነትና ተስፋን ያሳያል፡፡ በዚህ መሠረት በትንሣኤ በአዲስ ሕይወት እንደምንኖር ያመለክትልናል፤ አረንጓዴነትና ሕይወት ተወራራሽ ይሆናሉ፡፡

 ቀይ፡- ሥዕለ አድኅኖ  ሲሣሉ በቀይ ቀለም መሳላቸው ሰማዕትነትን ያሳያል፤ ቅዱስ ጳውሎስ ለዕብራውያን ምእመናን በላከወ መልእክቱ ‹‹…በድንጋይ ተወግረው ሞቱ፣ ተፈተኑ በመጋዝ ተሰነጠቁ፣ በሰይፍ ተገድለው ሞቱ ሁሉን እያጡ መከራን እየተቀበሉ እየተጨነቁ የበግና የፍየል ሌጦ ለብሰው ዞሩ ዓለም አልተገባቸውምና በምድረ በዳና በተራራ በዋሻና በምድር ጉድጓድ ተቅበዘበዙ …›› (ዕብ.፲፩፥፴፮) በማለት እንደገለጸው ስለ ሃይማኖታቸው መከራ የተቀበሉትን ሰማዕት የሆኑትን ቅዱሳን አባቶቻችንና እናቶቻችን ሥዕለ አድኅኗቸው በቀይ ቀለም ይሣላል፤ ቅዱሳን ነፍሳቸውን ለመከራና ለሞት አሳልፈው ስለ ክርስቶስና ስለ ቤተ ክርስቲያን ብለው መስጠታቸውን ለማመልከት ይህንን ቀለም እንጠቀመዋለን፤ እንዲሁም ቀይ ቀለም የነጻ አውጪዎችም ምልክት ተደርጎ ይወሰዳል፡፡

ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! ለዛሬ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሐዶ ሥዕለ አድኅኖ ሲሣል ምንን ዓይነት ቀለማት እንደምንጠቀም በመጠኑ ለአብነት ተመልክተናል፤ በቀጣይ በሥዕለ አድኅኖ የተደረጉ ተአምራት እንማራለን፤

ሁል ጊዜም እንደምንነግራችሁ በዘመናዊ ትምህርታችሁ በርትታችሁ ተማሩ ለወላጅ መታዘዝን፣ ለሰዎች መልካም ማድረግን እንዳትረሱ፤ በሰንበት ወደ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን በመሄድ መንፈሳዊ ትምህርትንም ተማሩ፡፡ ቸር ይግጠመን!

ስብሐት ለእግዚአብሔር

ወለወላዲቱ ድንግል

ወለመስቀሉ ክቡር አሜን!!!

 

 

ትሩፋን

ኀዳር ፳፮፤፳፻፲፰ ዓመተ ምሕረት

 ቅዱሱ መጽሐፍ ትሩፋን ከጦርነት፣ ከስደት፣ ከምርኮ የተረፉትን ሰዎች እንደሚያመልክት ይነግረናል፡፡ “ትሩፍ” ጥሬ ቃሉ “የቀረ፣ የተረፈ፣ ቀሪ፣ ትርፍ” የሚል ትርጓሜ አለው፡፡ (መጽሐፈ ሰዋስው ወግስ ወመዝገበ ቃላት ሐዲስ፣ ገጽ ፱፻፫) ናቡከደነፆር እስራኤልን ወደ ባቢሎን ማርኮ ከወሰዳቸው ከሰባ ዘመን በኋላ በባቢሎን የቀሩት ከተማረኩት ሽማግሎች ትሩፋን ይባላሉ። በንጉሡ ዘመነ መንግሥት ከኢየሩሳሌም ተማርከው ሰባ ዘመን በፋርስ በባቢሎን የሚኖሩ የእስራኤል ሕዝብ ትሩፋነ ባቢሎን እንደሆኑም መጽሐፍ ያስረዳናል። (ዕዝራ ፪፥፩)

በተለያዩ ዘመናት በአንድም በሌላ ምክንያት በሰዎች፣ በጎሳ፣ በማኅበረሰብ ዘንድ እንዲሁም በሀገራት መካከል በሚከሰት ጦርነት እልቂት አልያም የግፍ ግድያና ጭፍጨፋ የተነሣ የብዙዎች ሕይወት ይጠፋል፤ ታሪክ ለዚህ ቀደምት ምስክር እንደሆነ የምናውቀው እውነት ነው፡፡ የጦርነት ወሬ ደግሞ ለእኛ አዲስ የሆነ ነገር አይደለም፡፡ እራሱ ጌታ በወንጌል ሲናገር  ‹‹ጦርንም የጦርንም ወሬ ትሰሙ ዘንድ አላችሁ፤ ይህ ሊሆን ግድ ነውና ተጠበቁ፤ አትደንግጡ፤ ዳሩ ግን መጨረሻው ገና ነው። ሕዝብ በሕዝብ ላይ መንግሥትም በመንግሥት ላይ ይነሣልና፥ ራብም ቸነፈርም የምድርም መናወጥ በልዩ ልዩ ስፍራ ይሆናል›› እንዳለው ምድር ላይ እነዚህ ሁሉ መከራዎች እየተከሰቱ እንደሆነ ለማንም የተደበቀ አይደለም፡፡ (ማቴ.፳፬፥፮-፯)

ታዲያ የጦርነት አስከፊ ገጽታው እንጂ መልካም ጎኑ ምን አልባት እርሱ ባወቅና በፈቀደ ጠላትን ከሀገር የማስወጣቱ ተግባር ነው፡፡ በዚህም አብዛኛዎቻችን ጦርነትን በውዴታ ሳይሆን በግዴታ የምንቀበለው ነው፡፡ ከሁሉም አስከፊው ደግሞ ቤተሰቦቻቸውን፣ ዘመድ አዝማዳቸውንና ወዳጆቻቸውን የሚያጡ ትሩፋን የሚገጥማቸው ሥቃይና ጉዳት ነው፡፡ በአንድ በኩል ከአሰቃቂ ግድያ አልያም ከሞት መትረፍ ቢያስደስትም በሌላ በኩል ግን የሚወዱትን ማጣት እጅግ አስከፊ ነው፡፡ ከምንም በላይ ግን የሞት ሞት የሆነው የነፍስ ሞት አሰቃቂ ነው፡፡

ሰዎች ሞትን እንፈራለን፤ የሥጋ ሞት አስጨናቂ እንደሆነ ማንም የማይክደው ሐቅ ነው፡፡ ነገር ግን ሊቁ ቅዱስ ያሬድ ‹‹ኢትፍርህዎ ለሞት፤ ፍርህዋ ለኃጢአት፤ ሞትን አትፍሩ፤ ኃጢአትን እንጂ›› ይለናል፡፡ ሊያስጨንቀን የሚገባው በኃጢአት ምክንያት የሚመጣብንን የነፍሳችን ሞት እንጂ የሥጋ ሞት ሊሆን እንደማይገባ በዚህ ቃል እንረዳለን፡፡ ‹‹አፈር ነህና ወደ አፈር ትመለሳለህ›› በሚለው አምላካዊ ቃል ሥጋዊ ሞት አይቀሬ በመሆኑም ምንም ለማንቀይረው  ነገር መጨነቁ ጥቅም የለውም፡፡ (ዘፍ.፫፥፲፱) 

የነፍስ እንጂ የሥጋ ጦርነት ትሩፋን ባንሆን እጅጉን ይመረጣል፡፡ ቃሉን ተረድተው፣ በሕጉ ኖረው ትእዛዙን የጠበቁ ጻድቃን ሁሉ በነፍሳቸው አትርፈው ከዚህ ዓለም ድካምና ዕረፍት በክብር እንደተለዩ ቅዱሳት መጻሕፍት ምስክር ናቸው፡፡ (ገድለ ቅዱሳን) አብነት መሆናቸውን ደግሞ በክርስቶስ ክርስቲያን የተባልን የእግዚአብሔር ቤተሰቦች ሁላችን ማወቅ አለብን፡፡   እውነት ስለሆነው አንድ ጌታና አንዲት እውነተኛ ሃይማኖት ሲሉ መከራን በመቀበል በቀናው መንገድ ተጉዘው መልካም ፍሬን ያፈሩ ቅዱሳን፣ ጻድቃን፣ ሰማዕታት የነፍስ አትራፊዎች/ትሩፋን/ ናቸው፡፡

የልባችን መሻት የሁላችንም ምኞት መሆን ያለበት ይህ ነገር ሆኖ ሳለ፣ በመንፈስ ውጊያ ለማሸነፍ የሚያስችለንን ስንቃችንን ደግሞ ማከማቸት አስፈላጊ በሆነበት ሰዓት፣ እኛ ግን እየተጨነቅን ያለነው በጊዜያዊ ችግርና ወቅታዊ የእርስ በርስ ጦርነት ላለመሞት ነው፡፡ የሥጋዊ ሞትን ፈርተን በምንዘናጋበት ጊዜ ግን ነፍሳችንን እንደ አንበሳ ነጥቀው ሊጥሏት ይችላሉና ይህንን እንፍራ!

ነፍስ ዘለዓለማዊ ስትሆን ሥጋ ግን ጊዜያዊ ነው፤ አላፊ ጠፊ የሆኑ ምድራዊ ነገሮችን ለሟሟላት በሚል በምድር ለመኖር ስንሻ ከሁለት ያጣም የመሆን ሁኔታ ሊኖር ስለሚችል መጠንቀቅ ይገባል፡፡ ስለ ሥጋዊ ሞት ስናስብ መንፈሳዊ ዝለት ያጋጥመናል፤ በዚህም ጊዜ ነፍሳችን ትጎዳለች፤ ታድፋለች፤ ትመነምናለች፡፡

ሰው ጦርነትን ፈርቶ ሊሸሽ ይችላል፤ መሰደደም ሆነ መደበቅም አይከፋም፤ ግን ግልጽ የሆነውን አስከፊ ሁኔታና እየተካሄደ ያለውን ጦርነትም ይሁን እልቂት ማስቆም ካልተቻለ ሃይማኖታችን በሚፈቅድልን ተገቢ መንገድ ድምጻችንን ማሰማቱና መልእክት ማስተላለፍ እንጂ የጠላት ወገን ከሆኑ አካላት ጋር ግብ ግብ መፍጠር አልያም ጦርነት ውስጥ መግባት አላስፈላጊ ነው፡፡ ጠላት ፊት ለፊት መጥቶ ሊገለን ቢፈልግ እንኳን “ማኅተባችንን አንበጥስም” ብለን አንገታችንን ለሰይፍ ሰውነታችንን ለሞት አሳልፈን መስጠት ሰማዕትነት ነው፤ የክብር ሞትም ያሰጠናል፡፡

በእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በተለይም በዕረፍት በዓሏ በየወሩ ፳፩ ቀን የሚነበበው መልክአ ማርያም ‹‹ኃጥአን ከታላቅ የደስታ አደባባይ በተሰደዱ ጊዜ ምርኮ እሆንሽ ዘንድ ከእነርሱ ለይተሽ አስቀሪኝ›› ይለናል፡፡ (መልክአ ማርያም) ይህ ድንቅ ጸሎት የሚያመለክተን ከጦርነት ምርኮኝነት ለማምለጥ ማቀድ ሳይሆን ከኃጥአን ጎራ ላለመቆጠር መሻት እንዳለብን እንዲያውም የፍቅር ምርኮ መሆን እንደሚገባ ነው፡፡

ንጽሕት ቅድስት ከምትሆን የአምላክ እናት የተለመነው ይህ መማጸኛ ለሁላችን እንደሚሆን  እናምናለን፡፡ የነፍሳችንን ጥፋት የማይፈልገው አምላካችን አንዲያ ልጁን አሳልፎ ሰጥቶ ያዳነን ክብርት በሆነች እናቱ ድንግል ማርያም ነውና ታማልደን፣ ትለምንልን እና ትራዳን ዘንድ መማጸን የተገባን ነን፡፡ ከጠላት ሰይጣን የመንፈስ ውጊያ እንድታተርፈን፣ ምርኮዎቿ  እንድታደርገንን እንለምናት፡፡

ስብሐት ለእግዚአብሔር

ወለወላዲቱ ድንግል

ወለመስቀሉ ክቡር አሜን!!!

 

አጠንተ መንበሩ!

ኀዳር ፳፫፤፳፻፲፰ ዓመተ ምሕረት

አልፋና ኦሜጋ የሆነው አምላካችን ቅድመ ዓለም አስቀድሞ ሲለሠስ ሲቀደስ እንደኖረ ሁሉ ድኅረ ዓለም በፍጥረታቱ ሁሉ ሲመሰገን፣ ሲቀደስና ሲከበር ይኖራል፡፡ ስሙን ለመቀደስ ክብሩን ለመውረስ የፈጠራቸው መላእክትና ሰውም ይህን ግብር የሚሠሩ ቀደምት ፍጥረታት ናቸው፡፡ (መጽሐፈ አክሲማሮስ ዘእሑድ)

የአምላካችን እግዚአብሔር ምስጋና በሰማይና በምድር ነው፤ በዓለመ መላእክት ዘወትር “ቅዱስ ቅዱስ ቅዱስ” እያሉ ከሚያመሰግኑት መላእክት ሁሉ በላይ “አጠንተ መንበሩ” ተብለው የሚጠሩት “ካህናተ ሰማይ” ናቸው፡፡ በምድር ባለች ማኅደረ መለኮት የአምላክ ማደሪያ ቤተ ክርስቲያን ምድራዊ ካህናት በታቦቱ ፊት ማእጠንት እያጠኑ እንደሚያመሰግኑ ሁሉ፣ ቅዱሳን ሱራፌል ሃያ አራቱ ካህናትም የቅድስት ሥላሴን መንበር እያጠኑ ሳያቋርጡ ያመሰግናሉ፡፡

ነቢዩ ኢሳይያስም ስለ እነርሱ ሲናገር እንዲህ ብሏል፤ ‹‹ንጉሥ ዖዝያን በሞተበት ዓመት እግዚአብሔርን በረዥምና ከፍ ባለ ዙፋን ላይ ተቀምጦ አየሁት፤ የልብሱም ዘርፍ መቅደሱን ሞልቶት ነበር። ሱራፌልም ከርሱ በላይ ቆመው ነበር፥ ለእያንዳንዱም ስድስት ክንፍ ነበረው፤ በሁለት ክንፍ ፊቱን ይሸፍን ነበር፥ በሁለቱም ክንፍ እግሮቹን ይሸፍን ነበር፥ በሁለቱም ክንፍ ይበር ነበር። አንዱም ለአንዱ፦ ‘ቅዱስ፥ ቅዱስ፥ ቅዱስ፥ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር፣ ምድር ሁሉ ከክብሩ ተሞልታለች’ እያለ ይጮኽ ነበር።›› (ኢሳ.፮፥፩-፭) ቅዱስ ዮሐንስ ደግሞ ‹‹በዙፋኑ ዙሪያም ሃያ አራት ዙፋኖች ነበሩ፥ በዙፋኖቹም ላይ ነጭ ልብስ ለብሰው በራሳቸውም የወርቅ አክሊል ደፍተው ሃያ አራት ሽማግሌዎች ተቀምጠው ነበር›› ብሏል፡፡ (ራእይ ፬፥፬)

እነዚህ ቅዱሳን መላእክት ሱራፌል ሥጋ የሌላቸው ረቂቅ የእውነት ካህናት ናቸው፡፡ ከሰማያዊ ሠራዊት ሁሉ ከፍ ከፍም ይላሉ፡፡ የሰው ልጆችን ጸሎት፣ ምጽዋትንና ጽድቅን በልዑል እግዚአብሔር ፊት ያቀርባሉ፡፡ የሚጸለየውን ጸሎትና የሚሠዋውን መሥዋዕት በማዕጠንታቸው እያሳርጉ ሕያዋን ሆነው ይኖራሉ፤ አይሞቱም፤ አይለወጡም፡፡

በከበረች ኅዳር ፳፬ (ሃያ አራት) ቀን የስማቸው ትርጓሜ ሱራፌል “አጠንተ መንበሩ ለልዑል፣ ኤልሻዳይ” የሆነ ካህናተ ሰማይ የበዓላቸው መታሰቢያ ነው፤ አባታችን ጻድቁ አቡነ ተክለ ሃይማኖትም ከሃያ አራቱ ካህናተ ሰማይ ጋር የሥሉስ ቅዱስን መንበር ያጠኑበት ዕለት  ነው፡፡

የቅዱሳን መላአክት ሱራፌል፣ የቅዱሱ አባታችን ተክለ ሃይማኖት ጸሎት፣ አማላጅነትና ተረዳኢነት አይለየን፤ ከበዓሉ በረከት ይደርብን!

ጽዮን ማርያም

ኀዳር ፲፱፤፳፻፲፰ ዓመተ ምሕረት

 ጽዮን “”ጸወን” ከሚለው የግእዝ ቃል የተገኘ ሲሆን “አምባ፣ መጠጊያ” ማለት ነው፡፡ እመ ብዙኀን የሆነችውን የአምላክ እናት ቅድስት ድንግል ማርያምን የሚገለጽ መሆኑን  “ማኅደረ አምላክ” በሚለው ትርጒም እንረዳለን፡፡ ጽዮን የሚለው ስያሜ በቁሙ ለታቦት፣ ለጽላት ሲያገለግል በትንቢታዊ ምሥጢሩ ግን ለድንግል ማርያም፣ ለቤተ ክርስቲያንና ለዘለዓለማዊት ርስተ መንግሥተ ሰማያት ያገለግላል::

ታቦተ ጽዮን “ጽላተ ኪዳን፣ ታቦተ ሕጉ” እየተባለችም ትጠራለች:: “ጽሌ” ማለት “ሰሌዳ” ማለት ሲሆን “ጽላት” ደግሞ በብዙ ቁጥር ነው:: “ኪዳን” ደግሞ በፈጣሪና በሰው ልጆች መካከል ያለ “ውል፣ ስምምነት” ነው፡፡ ታቦተ ጽዮን ዐሥርቱ ቃላት የተጻፈባት በመሆኗ የእግዚአብሔር ሕግጋትን የያዘ ናት፡፡ በዚህም በሕጉ እንድመራ ትእዛዙን እንድፈጽም ያሳስበናል፡፡

አልፋና ኦሜጋ፣ ኤልሻዳይ የሆነው አምላካችን እግዚአብሔር አስቀድሞ ለእስራኤል ሕዝብ ቅድስት የምትሆን ማደሪያውን ታቦተ ጽዮንን በነቢዩ ሙሴ አካማኝነት የሰጣቸው ክብር፣ ሞገስ፣ አምባ እንድትሆናቸው ነው፡፡ (ዘጸ. ፴፩፥፲፰)  ለ፭፻ (አምስት መቶ) ዓመት ከእነርሱ ሳትለይ ከአምላክ ጋር መገናኛ፣ በጦርነት ጊዜም ማሸነፊያ ኃይላቸው ሆናም ኖራለች፡፡

ሀገረ እግዚአብሔር የሆነችው ኢትዮጵያም ለከበረች ታቦተ ጽዮን መቀመጫ ለመሆን ታድላለች፡፡ በቀዳማዊው እብነ መለክ፣ እብነ ሐኪም/በቀዳማዊ ምኒልክ ዘመነ መንግሥት አማካኝነት ወደ ሀገራችን የመጣችው ታቦቷ እስከ አሁን ድረስ በአክሱም ጽዮን ቤተ ክርስቲያን እንደምትገኝ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን ይናገራሉ፡፡ (መጽሐፈ ክብረ ነገሥት) የጌታችን ድንቅ ቸርነት የተደረገልን እኛ የድንግል ማርያም የዐሥራት ልጆች የአምላክን ሥራ ልናደንቅና ልናመሰግን ይገባል፡፡

ሀገራችን የገባበትን እንዲሁም አክሱም ጽዮን ቤተ ክርስቲያን የተቀመጠበት ኅዳር ፳፩ ቀንንም ታላቅ በዓልን እናደርጋለን፡፡

የአምላካችን እግዚአብሔር ቸርነት፣ የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ጸሎት፣ አማላጅነትና ተራዳኢነት አይለየን፤ ከበዓሉ በረከት ያሳትፈን፤ አሜን!

 

የተቀማ ማንነት

ኀዳር ፲፯፤፳፻፲፰ ዓመተ ምሕረት

የማንነት ጥያቄ በሁላችንም አእምሮ ውስጥ የሚታሰብ ነው፤ ምላሽ አግኝተን የተሻለ መረዳት ያለን ስንቶቻችን እንደሆንን ማወቅ አዳጋች ቢሆንም በዘመናት ሂደት በሰዎች ታሪክ ውስጥ ካካበትነው ዕውቀት አልያም ደግሞ ባሳለፍነው ተሞክሮ የተወሰነ መረዳት ሊኖረን እንደሚችል መገመት አያዳግትም፡፡ በተለይም የአምላክን ቅዱስ ቃል ተምረን የምናውቅበት የቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ በመጠኑ እንኳን ካለን የመፈጠራችን ምክንያት ወይም የመኖራችን ትርጒም ይገባናል፡፡

ዓለምን ከእነጓዟ የፈጠረ ኤልሻዳይ የሆነው አምላካችን እግዚአብሔር በአርአያውና በአምሳሉ ሰዎችን ከሌሎች ፍጥረታት ለይቶ ሲፈጥረን  ስሙን እንድንቀድስና ክብሩን እንድንወርስ እንደሆነ ቅዱሱ መጽሐፍ አስቀድሞ ይነግረናል፡፡ (ዘፍ.፩፥፳፮) በዕፀ በለስ ምክንያት የሰው ዘር ያጣውን ልጅነት ሊመልስለት አንዱ እግዚአብሔር ወልድ ባሕርይውን ዝቅ አድርጎ፣ ከሰማየ ሰማያት ወርዶ፣ ከንጽሕት ድንግል ተወልዶ፣ መከራን ተቀብሎ፣ በመስቀል ተሰቅሎ የሞተልን፣ ሥጋውን ቆርሶ ደሙን አፍሶ ብሉ ጠጡ ያለን ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነፍሳትን ከሲኦል አውጥቶ የድኅነትን መንገድ የመሠረተልን መከራ መስቀሉን ተቀብለን በክርስቶስ ክርስቲያን እንድንሆን ነው፡፡

ቅዱስ ቃሉን አስተምሮ፣ በፈቃዱና በቸርነቱ የሰጠን እውነተኛዋ ሕይወት ክርስትና የማንነታችን መገለጫ መሆኗን ግን ተረድተን ይሆን? ‹‹እኔ መንገድና እውነት ሕይወትም ነኝ›› ያለን ጌታ እርሱ ክርስቶስ ተብሎ ክርስቲያን እንድንባል እንዳደረግን፣ በእውነተኛውም መንገድ መጓዝ እንዳለብን የተረዳን ስንቶቻችን እንሆን? (ዮሐ.፲፬፥፮)

የምድራዊ ሕይወት ባመጣብን ጣጣ፣ በድመክመታችን ሳቢያና በኃጢአታችን ብዛት ለጥፋት ተዳርገን፣ ቀና በሚመስለው ጎዳና አሳችና ጠማማ መንገድ እየተጓዝን ያለን፣ ማንነታችንን የተቀማን ሰዎች ጥቂት አይደለንምና ቆም ብለን ልናስብ ይገባል፡፡ አስቀድሞ ጥንተ ጠላታችን ዲያብሎስ ከፈጣሪያችን አጣልቶ ለ፶፻፭፻ (አምስት ሺህ አምስት መቶ) ዘመን ፍዳ አጽንቶ በኃጢአት ባርነት ገዝቶ እንዳሠቃየን ሁሉ ዛሬም አሳሳች በሆነችው ዓለም ጠፍተን እንድንቀር በተለያየ መንገድ ያጠምደናል፡፡ በጥቅም፣ በሀብት፣ በዝና የተደለሉት ወንድሞቻችን ዛሬ የት ናቸው? የዓለም ብልጭልጭ እያዋዛች ስባ፣ ጎትታ ጥላቸው፣ በርኩስ መንፈስ ተይዘው፣ በስካር ለዝሙት የተዳረጉ የዳንኪራ ቤት ደንበኞች የሆኑ ከእኛ የወጡ ኦርቶዶክሳውያንም ናቸው፡፡

“በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ” እንዲሉ በኃጢአታችን ሳቢያ የአምላክ ቁጣ በላያችን በበረታበት በዚህ ጊዜ ምድራዊ ሕይወትን እንኳን ለመኖር አዳጋችና አሳሳቢ ደረጃ በደረሰበት ወቅት፣ ዛሬ እንሙት መቼ በማናውቅበት በአሁኑ ሰዓት ተስፋ አጥተን፣ ማንነታችን ተቀምተናልና እናስተውል! እንመለስ! የተቀማ ማንነታችን እናስመልስ!

ክርስትና ሕይወት ነው፤ እርሱ ክርስቶስ በሞቱ ሞትን አጥፍቶ እውነተኛ ሕይወትን ሰጥቶናልና፡፡ ተስፋ ነው፤ የመሠረታት አምላክ ነውና፡፡ ብርታትና ጽናት ነው፤ መከራ መስቀሉ ኃይልን ያደርጋልና፡፡ ‹‹መስቀል ኃይልነ›› እንዲል፡፡ (የዘወትር ጸሎት) ሥቃይና መከራ ችለን ፈተናችንን ማለፍ የሚቻለን፣ ዓለም የምታመጣብንን ሥቃይ መቋቋም፣ እስከ መጨረሻውም ልንጸና የምንችለው ክርስቶስ በተቀበለልን ጽኑ ሥቃይ በመስቀሉ ቤዛነት አምነን እርሱን ስንከተል እንጂ “ጦር መዛዥ ስለመጣ እኛም መሣሪያ ይዘን ጦርነት እንግጠም” ማለት ለማንም አይበጅም፤ ማንነታችንም አይደለም፡፡ ይህ ፍራቻ የፈጠረው የተሳሳተ አስተሳሰብና አካሄድ በመሆኑ “ጠላት ሲመጣ ዝም ብለን መሞት ሞኝነት ነው፤ ተዋግተን ማሸነፍ አምላክ የፈቀደው ነው” ብለን ለባሰ ጥፋት እንዳንዳረግ እንጠንቀቅ!

ይልቁንም ጠላትን ለማሸነፍ የሚያስችለንን ጥንተ ጠላት ዲያብሎስ የወሰድብንን የተቀማ ማንነታችንን “ክርስቲያናዊነታችንን” እናስመልስ፤ በእንደዚህ ዓይነት ወቅት ጦርነት ሲኖር ፍራቻ እንዲፈጠርብን ያደረገብን ያጣነው ማንነታችን ነው፤ ለሃይማኖት መሞት ክብር እንጂ ውርደት አይደለምና፡፡ የሰማዕትነትን ክብር ከታደሉ ቅዱሳን ጋር እንድቆጠር የሚያደርገን ክርስትናችንን ማጣት እጅጉን ያሳስባልና በጊዜ መመለስ ያስፈልጋል፡፡

ከምንም በላይ የንስሓ ልብ ይኑረን! ርኅራኄ አጥተን ለወገኖቻችን ምሕረትን ማድረግ ያልቻልን አካላት በሙሉ ትክክል የሆንን ሊመስለን ይችላል፡፡ ሆኖም ግን ነገሩ የተገላቢጦሽ ነው፡፡ በመልክም፣ በገጽም፣ በባሕርይም የሚመስለንን ፍጡር በአሰቃቂ ሁኔታ መጨፍጨፍ ወይም ለማጥፋት መፈለግ ማንንም አይጠቅምምና፡፡ የራስን ወንድም ወይም ወገን መግደል ምኑ ላይ ይሆን ጥቅሙ? ይህ ክርስቲያን ከሆንን ሰዎች አይጠበቅምና ልብ እናድርግ! ማንነታችን ስለተቀማን ደግሞ እንዘን!

በቁጭትና በመንፈሳዊ ቅንዓት ተነሣሥተንም እውነተኛ ማንነታችን እንፈልግ፤ እናስመልስ፤ ክርስቲያን የሆነ ሁሉ ለወገኑ ለጠላቱም ጭምር የሚጸልይ እንጂ ስለ ጎዳኝ ልጉዳው፣ ስለ መታኝ ልምታው፣ ስለ ተጠቀመብኝ ልጠቀምበት፣ ስለ ረገመኝ ልርገመው፣ ቤተሰቤን ስለ ገደለብኝ ልግደልበት አይልም፡፡ የሚያሣቃዩንንና በዳዮቻችንን መታገሥ፣ የሚረግሙንን መመረቅ፣ ለሚያሳዱዱን መጸለይ ለፍቅር የሞተልን፣ በቀራንዮ እንደ በግ እየተጎተተ፣ ጥፊንና ሕማማን እንዲሁም ግርፋትን ችሎ፣ እንዲያውም ለጠላቶቹ “አባት ሆይ፥ የሚያደርጉትን አያውቁምና ይቅር በላቸው” ብሎ የለመንንና የተሠዋልን ጌታ አስተምሮናል፡፡

በክፋት፣ በምቀኝነት፣ በክፉ ቅንዓት ምድር ላይ መርዝ ረጭቶ የበረዘን ጠላት ማንነታችን ቀምቶ ከፈጣሪ እንዳጣለን በማስተዋል የደኅነታችን መገኛ ወደ ሆነው፣ ክርስቶስ ተብሎ ክርስቲያን እንድባል ያደለን፣ የእውነተኛ ማንነታችን መገለጫ የሆነውን ክርስትናችን ወደ ሰጠን አምላካችን እንመለስ፡፡ ኃይላችን እርሱ ነውና፤ ማሸነፊያችን እርሱ ነውና፤ ተስፋችን እርሱ ነውና፤ ዘለዓለማዊ ሕይወትና ተድላ ደስታን የሚሰጠን እርሱ ነውና የተቀማ ማንነታችን እናስመልስ!

 

ስብሐት ለእግዚአብሔር

ወለወላዲቱ ድንግል

ወለመስቀሉ ክቡር አሜን!!!

 

 

ነቢያት ለምን ጾሙ?

ኅዳር ፲፭፤፳፻፲፰ ዓመተ ምሕረት

የአዳም ዘር በሙሉ በኃጢአት ባርነት ተይዞ፣ ለ፶፻፭፻ ዓመታት በፍዳ አረንቋ ውስጥ ሲኖር ተስፋ ሲያደርግ የነበረው የእግዚአብሔር አብ ልጅ እግዚአብሔር ወልድ ለአዳም የገባለትን የመዳን ቃል ኪዳን ነው፡፡ ይህም ይፈጸም ዘንድ ነቢያት አስቀድሞ ትንቢት ተናግረዋል፡፡

ከእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ስለ መወለዱ ፥ ወደ ግብፅ ስለ መሰደዱ ፥ በባሕረ ዮርዳኖስ ስለ መጠመቁ ፥ ብርሃን በሆነው ትምህርተ ወንጌል ጨለማውን ዓለም ስለ ማብራቱ ፥ ለሰው ልጆች ድኅነት ጸዋትወ መከራ ስለ መቀበሉና ስለ መሰቀሉ ፥ ስለ ትንሣኤው ፥ ስለ ዕርገቱና ስለ ዳግም ምጽአቱ ትንቢት ተናግረው አላቆሙም፡፡

ነቢዩ ዳዊት “እጅህን ከአርያም ላክ አድነኝም” በማለት ሲማጸን (መዝ.፻፵፫፥፯) ነቢዩ ኢሳይያስ ደግሞ “እነሆ፥ ድንግል ትፀንሳለች፥ ወንድ ልጅም ትወልዳለች፥ ስሙንም አማኑኤል ብላ ትጠራዋለች” በማለት ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከድንግል ማርያም እንደሚወለድ አስቀድሞ ተናግሯል፡፡ (ኢሳ.፯፥፲፬) በዚህም የተስፋ ቃል “ኃይልህን አንሳ፤ እጅህንም ላክ” በማለት ነቢያት እየተማጸኑ ጾመዋል፡፡

የነቢያት ጾም (የገና ጾም) ከኅዳር ፲፭ ጀምሮ ለ ፵፫ ቀናት የሚጾም ሲሆን ፋሲካው (ፍቺው) በልደት በዓል ነው፤ ይህም ጾም በዘመነ ብሉይና በዘመነ ሐዲስ ቅዱሳንና ምእመናን ጾመውታል፡፡ እኛም አምላካችን ቸርነቱን እንዲያበዛልን፣ ከፈተና እንዲያወጣን፣ ወቅታዊውን ሀገራዊ ችግር ይፈታልን ዘንድ፣ ከመከራ ሥጋ ከመከራ ነፍስ እንዲሠውረን ጾሙን እንጹም!

የጌታችን ቸርነት፣ የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም እና የቅዱሳን ነቢያት ጸሎት፣ አማላጅነትና ተረዳኢነት አይለየን፤ አሜን!

 

“ይትሌዓል መንበሩ!” ቅዱስ ያሬድ

ኀዳር ፲፩፤፳፻፲፰ ዓመተ ምሕረት

አሸናፊና ኃያል፣ ሁሉን ቻይ የሆነ የእግዚአብሔርን ገናንነትና እርሱን የሚመስል አምላክ እንደሌለ የሚያመለክት የስሙ ትርጓሜ “መኑ ከመ አምላክ፤ እንደ አምላክ እግዚአብሔር ያለ ማን ነው?” የሆነ፣ የመላእክት ሁሉ አለቃ ሊቀ መላእክት ቅዱስ ሚካኤል በኅዳር ፲፪ የተሸሞበት ቀን “እግዚኡ ረሰዮ ለውእቱ ሚካኤል እምኵሎሙ መላእክት ይትሌዓል መንበሩ፤ ጌታው ሚካኤልን ከመላእክት ሁሉ መንበሩን ከፍ ከፍ አደረገው” እየተባለ ይከበራል፡፡

የእግዚአብሔር ሠራዊት ሁሉ አለቃ የሆነው መልእኩ ሚካኤል መላእክትን ሁሉ የሚያዝ ነው፡፡ መላእክት ደግሞ አለቃቸውን ያከብራሉ፤ ይታዘዛሉ፤ ከትእዛዙም አይወጡም፡፡ ሳጥናኤል በትዕቢቱ ከክብሩ ተዋርዶ ወደ ምድር ሲጣል አምላክ ቅዱስ ሚካኤልን በእርሱ ፈንታ በዐሥሩ ከተማ በመቶውም ነገደ መላእክት ላይ ሾሞታል፡፡ የእግዚአብሔር ሕዝብ በሆኑት ላይ ጭምርም ሾመው፡፡ … ዐይኑን አንሥቶ ተመለከተ፤ እነሆም የተመዘዘ ሰይፍ የያዘ ሰው በፊቱ ቆመ፤ ኢያሱም ወደ እርሱ ቀርቦ፤ “ከእኛ ወገን ወይስ ከጠላቶቻችን ወገን ነህ? አለው፡፡ እርሱም “እኔ የእግዚአብሔር ሠራዊት አለቃ ሆኜ አሁንም ወደ አንተ መጥቼአለሁ”  እንዲል፡፡ (ኢያ.፭፥፲፫)

ሠራዊተ መላእክት የሚያከብሩትንና የሚታዘዙለትን የመላእክት አለቃ ቅዱስ ሚካኤልን እኛም እንደ ነቢዩ ኢያሱ እናከብረዋለን፤ እንታዘዘዋለን፡፡ መላእክትን ማክበርና መታዘዝ እንደሚገባ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፡፡ “በመንገድህ ይጠብቅህ ዘንድ ወዳዘጋጀሁትም ሥፍራ ያገባህ ዘንድ እነሆ እኔ መልአክህን በፊትህ እሰዳለሁ፤ በፊቱ ተጠንቀቁ፤ ቃሉንም አድምጡ፤ ስሜም በእርሱ ስለሆነ ኃጢአት ብትሠሩ ይቅር አይልምና አታስመርሩት፤ አንተ ግን ቃሉን ብትሰማ፣ ያልሁህንም ሁሉ ብታደርግ፣ ጠላቶችህን እጣላቸዋለሁ፣ የሚያስጨንቁህንም አስጨንቃቸዋለሁ፣ መልአኬ በፊትህ ይሄዳልና…፡፡” (ዘጸ.፳፫፥፳-፳፪)

በበዓሉ መታሰቢያ በኅዳር ፲፪ ቀን የክብር ባለቤት በሆነ በእግዚአብሔር ፈቃድ ክንፎቹን ወደ ሲኦል ያወርዳል፤ ኃጥአንንም ወደ አዲሲቱ ምድር ያወጣቸዋል፤ ይኸውም የመላእክት አለቃ የሚካኤል ሠራዊት ይሆናሉ፡፡ ይቅርታ የተደረገላቸውና ምሕረት አግኝተው በአንድ ጊዜ በክንፉ ያወጣቸው ስፍር ቁጥር የላቸውም፡፡ ቅዱስ ሚካኤል በየዓመቱ በኅዳር ፲፪ ቀን እንዲህ እያደረገ እልፍ ነፍሳትን ያወጣል፡፡ የቤተ ክርስቲያን ወገኖች የሆኑትን ሁሉ እንደ ሥራቸው ወደ ሰማያዊት ኢየሩሳሌም ይወስዳቸዋል፡፡ ከዚህም በኋላ ወደ አብ መጋረጃ ውስጥ ይገባል፤ በዚህች ዕለት ምድራዊትና ሰማያዊት ስለሆነች ምሕረቱም ከመንበሩ በታች ይሰግዳል፡፡ ስለውኃ ምንጮች፣ ስለ ወይን ቦታዎች፣ ስለ ምድር ፍሬዎች በምድርም ላይ ስለሚኖሩ ስለ ሰው ልጆች ነፍስ ሁሉ፣ ስለ እንስሳትም፣ ስለ ሰማይ ወፎችም፣ ስለ ባሕር ዓሣዎችም፣ በምድር ላይና በባሕር ውስጥ ስለሚንቀሳቀሱ ሁሉ የምሕረት ባለቤት ከሆነ ከአብ ዙፋን በታች ሁልጊዜ በማመስገን ይሰግዳል፤ ልመናውንም እስኪሰማውና የምሕረትንም ቃል እስኪያስተላልፍለት ድረስ ከእግረ መንበሩ ሥር አይነሣም፡፡

ለዚህ ዓለም ምሕረትን የሚለምኑ ቅዱሳን መላእክትም በየዓመቱ ኅዳር ፲፪ ቀን በእግዚአብሔር የዙፋኑ ዐውደ ምሕረት ዙሪያ ተሰብስበው ስለ ሰውና ስለ እንስሳትም ሁሉ ምሕረትን የሚለምን ቅዱስ ሚካኤል ከአብ መጋረጃ ውስጥ በወጣ ጊዜ ቸርና መሐሪ አብ ለቅዱስ ሚካኤል የሰጠው ልብሱን እነዚያ መላእክት ይመለከታሉ፤ ይቅርታን የማግኘት ምልክታቸው ነውና፡፡ ስለዚህ እነዚህ ቅዱሳን መላእክት በምድር ላይ ምሕረት እንደተደረገ ሰውንም እንስሳትንም ይቅር እንዳለ በዚህ ዓለምም የሚሆነውን ሁሉ አይተው ቅዱስ ሚካኤል በለበሰው ልብስ አምሳል ያውቁታል፡፡

መጽሐፈ ስንክሳር እንደሚለው ይህ እጅግ የከበረ ገናና መልአክ ቅዱስ ሚካኤል “ከቅዱሳን ሰማዕታት ጋራ በመሆን ገድላቸውን እስኪፈጽሙ ድረስ የሚያጽናናቸውና የዘወትር ጠባቂአቸው ሆኖ የሚራዳቸው እርሱ ነው፡፡” የብዙዎቹንም ቅዱሳን ገድል ስንመለከት የዘወትር ጠባቂያቸው ቅዱስ ሚካኤል ነው፡

መልአክ ቅዱስ ሚካኤል ያደረገውም ተአምር ይህ ነው፡- የእግዚአብሔር ወዳጅ የሆነ ስሙ ዱራታዎስ የሚባል አንድ ሰው ነበረ፡፡ የሚስቱም ስም ቴዎብስታ ነው፡፡ እነርሱም ሁልጊዜ ያለማቋረጥ የዚህን የከበረ መልአክ የቅዱስ ሚካኤልን የበዓሉን መታሰቢያ ያደርጉ ነበር፡፡ ከዚህም በኋላ በሀገር ውስጥ ችግር በሆነ ጊዜ ገንዘባቸው አለቀ፡፡ ለቅዱስ ሚካኤልም ለበዓሉ መታሰቢያ የሚያደርጉትን እስኪያጡ ድረስ ቸገራቸው፡፡ ዱራታዎስም ሸጦ ለመልአኩ በዓል መታሰቢያ ያደርገው ዘንድ የእርሱንና የሚስቱን ልብስ ይዞ ወጥቶ ሄደ፡፡

የመላእክት አለቃ ቅዱስ ሚካኤልም በታላቅ መኰንን አምሳል ለዱራታዎስ ተገልጦ ወደ ባለጸጎች ሄዶ በእርሱ ዋስትና በአንድ ዲናር አንድ በግ እንዲወስድ፣ ሁለተኛም ወደ ባለ ስንዴ ዘንድ ሄዶ በእርሱ ዋስትና ስንዴን እንዲወስድ ዳግመኛም ወደ ዓሣ አጥማጅ ዘንድ ሄዶ አንድ ዓሣ እንዲወስድ ነገር ግን ወደ ቤቱ ሳይርስ የዓሣውን ሆድ እንዳይቀድ አዘዘው፡፡ ዱራታዎስም እንደታዘዘው አደረገ፡፡ ቤቱም በተመለሰ ጊዜ ቤቱ ሁሉ በበረከት ተመልቶ አገኘው፡፡ እርሱም እጅግ ተደስቶ የዚህን የክበር መልአክ የመታሰቢያውን በዓል አደረገ፡፡ ጦም አዳሪዎችንና ድኆችን ጠርቶ አጠገባቸው፡፡

ከዚህም በኋላ ለዱራታዎስና ለሚስቱ ቅዱስ ሚካኤል ሁለተኛ ተገለጠላቸው፡፡ ዱራታዎስንም የዓሣውን ሆድ እንድሰነጥቅ አዘው፡፡ በሰነጠቀውም ጊዜ ፫፻ (ሦስት መቶ) የወርቅ ዲናር በዓሣው ሆድ ውስጥ ተገኘ፡፡ ቅዱስ ሚካኤል ዱራታዎስንና ሚስቱን ቴዎብስታን እንዲህ አላቸው፤ “ከዚህ ዲናር ወስዳችሁ ለባለ በጉ፣ ለባለ ዓሣውና ለባለ ስንዴው ዕዳችሁን ክፈሉ፡፡ የቀረውም ለፍላጎታችሁ ይሁናችሁ፤ እግዚአብሔር አስቧችኋልና በጎ ሥራችሁን፣ መሥዋዕታችሁንና ምጽዋታችሁን አስቦ በዚህ ዓለም አሳመረላችሁ፤ በኋለኛውም መንግሥተ ሰማያትን አጀጋጀላችሁ” አላቸው፡፡

እነርሱም ይህን ነገር ሲሰሙ ደነገጡ፡፡ የከበረ ገናናው መልአክም “ከመከራችሁ ሁሉ ያዳንኳችሁ የመላእክት አለቃ እኔ ሚካኤል ነኝ፤ መሥዋዕታችሁንና ምጽዋታችሁን ወደ እግዚአብሔር ፊት ያሳረግሁ እኔ ነኝ፡፡ አሁንም በዚህ ዓለም ከበጎ ነገር እንድታጡ አላደርጋችሁም” አላቸው፡፡ ይህንንም ከነገራቸው በኋላ ወደ ሰማያት ወጣ፡፡ እነርሱም በፍርሃትና በክብር ሰገዱለት፡፡

የመላእክት ሁሉ አለቃ የቅዱስ ሚካኤል ጥበቃው፣ ጸሎቱ፣ አማላጅነቱና ተራዳኢነቱ አይለየን፤ ከበዓሉ ረድኤት በረከት ይክፈለን፤ አሜን!

(ምንጭ፡ድርሳነ ቅዱስ ሚካኤል፣ መጽሐፈ ስንክሳር ዘወርኃ ኅዳር)

 

አርባእቱ እንስሳ

ኀዳር ፰፤፳፻፲፰ ዓመተ ምሕረት

ዓለምን በመላ ከእነ ጓዟ ድንቅ አድርጎ የፈጠረ የሁሉን ቻይ የአምላክን ክብር መግለጽ ማን ይቻለዋል? ለእርሱ ክብር የሚመጥንስ ዙፋን ከየት ይገኛል? መንበረ ሥላሴን መሸከምስ ምንኛ ድንቅ ነው? እኒህ ቅዱሳን ኪሩቤልና ሱራፌል ግን ለእዚያ ክብር በቅተዋልና በዓላቸውን እናደርግ ዘንድ ይገባል፡፡

ቅዱስ ኤጲፋንዮስ በመጽሐፈ አክሲማሮስ ላይ እንደገለጸው “ኪሩቤል ከወገባቸው በታች አንድ ከወገባቸው በላይ አራት አድርጎ ሲፈጥራቸው ዐይናቸው ብዙ ነው፤ አለቃቸውም ኪሩብ ሲሆን የሰው መልክና የአንበሳ መልክ ያለው ነው፡፡”
ሱራፌል ደግሞ “የንስር መልክና የእንስሳ መልክ ያለው ነው፤ አለቃቸውም ሱራፊ ሲባል ሲፈጥራቸውም ስድስት ስድስት ክንፍ አድርጎ ፈጥሯቸዋል፡፡ አለቃቸው የንስር መልክና የእንስሳ መልክ ያለው ነው፡፡”

ቅዱስ ዮሐንስ በራእዩ “ፊተኛውም እንስሳ አንበሳን ይመስላል፥ ሁለተኛውም እንስሳ ጥጃን ይመስላል፥ ሦስተኛውም እንስሳ እንደ ሰው ፊት ነበረው፥ አራተኛውም እንስሳ የሚበረውን ንስር ይመስላል። አራቱም እንስሶች እያንዳንዳቸው ስድስት ክንፎች አሉአቸው፥ በዙሪያቸውና በውስጣቸውም ዓይኖች ሞልተውባቸዋል፤ ቅዱስ፥ ቅዱስ፥ ቅዱስ፥ የነበረውና ያለ የሚመጣውም ሁሉንም የሚገዛ ጌታ አምላክ እያሉ ቀንና ሌሊት አያርፉም” ይላቸዋል። (ራእይ ፬፥፯-፱)
ነቢዩ ኢሳይያስ ሲገልጻቸው “ንጉሡ ዖዝያን በሞተበት ዓመት እግዚአብሔርን በረዥምና ከፍ ባለ ዙፋን ላይ ተቀምጦ አየሁት፤ የልብሱም ዘርፍ መቅደሱን መልቶት ነበር፤ ሱራፌልም ከርሱ በላይ ቆመው ነበር፤ ለእያንዳንዱም ስድስት ክንፍ ነበረው፤ በሁለት ክንፍ ፊቱን ይሸፍን ነበር፤ በሁለቱም ክንፍ እግሮቹን ይሸፍን ነበር፤ በሁለቱም ክንፍ ይበር ነበር፤ አንዱም ለአንዱ ቅዱስ፣ ቅዱስ፣ ቅዱስ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር ምድር ሁሉ ከክብሩ ተመልታለች እያለ ይጮኽ ነበር” ይላል፤ (ኢሳ.፮፥፩-፫) ይህ መሸፈናቸው ያድናቸዋል ቢሉ? ትእምርተ ፍርሀት ነው፤ ዛሬ በዚህ ዓለም ሴቶችን ሕፃናትን እንመታችኋለን ባሏቸው ጊዜ እጃቸውን መጋረዳቸው የሚያድናቸው ሆኖ ሳይሆን ትእምርተ ፍርሀት እንደሆነ ሁሉ፡፡

አንድም በሁለት ክንፋቸው ፊታቸውን መሸፈናቸው ፊትህን ማየት አይቻለንም ሲሉ፣ በሁለት ክንፋቸው እግራቸውን መሸፈናቸው ከፊትህ መቆም አይቻለንም ሲሉ፣ ሁለት ክንፋቸውን ወዲያና ወዲህ ያደርጋሉ አለ፤ ትእምርተ ተልእኮ ነው፡፡

አንድም በሁለት ክንፋቸው ፊታቸውን መሸፈናቸው ባሕርይህን መመርመር አይቻለንም ሲሉ፣ በሁለት ክንፋቸው እግራቸውን መሸፈናቸው ባሕርይህን መረማመድ መተላለፍ አይቻለንም ሲሉ ሁለት ክንፋቸውን ወዲያ ወዲህ ያደርጋሉ፤ ከእእምሮ ወደ አእምሮ የመፋለሳቸው ምልክት ነው፡፡

አንድም ሁለት ክንፋቸውን ወደ ላይ አድርገው ይታያሉ አለ፤ ወደላይ ቢወጡ ቢወጡ አትገኝም ሲሉ፣ ሁለት ክንፋቸውን ወደታች አድርገው ይታያሉ፤ ወደታች ቢወርዱ ቢወርዱ አትገኝም ሲሉ፣ ክንፋቸውን ወዲያና ወዲህ ያደርጋሉ፤ ወዲያና ወዲህ ቢሉ አትገኝም ሲሉ፤ አንድም ወደላይ መዘርጋት በሰማይ ምሉእ ነህ ሲሉ፣ ወደታች መዘርጋቸው በምድርም ምሉእ ነህ ሲሉ፤ ወዲያና ወዲህ መዘርጋታቸው በሁሉ ምሉእ ነህ ማለታቸው ነው፤ አንድም ወደላይ መዘርጋት ትእምርተ ተመስጦ ወደታች መዘርጋት ትእምርተ ትሕትና፣ ወዲያና ወዲህ ረብቦ መታየት ትእምርተ ተልእኮ ነው፡፡

ሁለት ክንፋቸውን ወደላይ ሁለት ክንፋቸውን ወደታች ሁለት ክንፋቸውን ወዲያና ወዲህ አድርገው ትእምርተ መስቀል መሥራታቸው በብሉይ ኪዳን ከሆነ እንዲህ ባለ መስቀል ተሰቅለህ ዓለምን ታድነዋለህ ሲሉ፣ በዘመነ ሐዲስ የሆነ እንደሆነ እንዲህ ባለ ትእምርተ መስቀል ተሰቅለህ ዓለምን አድነኸዋል ሲሉ ነው፡፡ የእነዚህ አርባእቱ እንስሳ መላእክት ፊታቸው በርካታ ምሥጢራትን ሲያመለክቱ ገጸ ሰብእ በማቴዎስ፣ ገጸ አንበሳ በማርቆስ፣ ገጸ ላህም በሉቃስ፣ ገጸ ንስር በዮሐንስ ተመስሏል።

ዳግመኛም የሰው ፊት ያለው መልአክ ለሰው ልጆች ይማልዳል። የአንበሳ ፊት ያለው መልአክ ለዱር አራዊት ይለምናል። የላም ፊት ያለው መልአክ ለእንስሳት ይጸልያል። የንስር ፊት ያለው መልአክ ለሰማይ አዕዋፋት ሁሉ ይለምናል በማለት ሊቃውንት ያመሰጥራሉ።
በሌላ ምሥጢር የሰው ገጽ ያለው የጌታን ሰው የመሆንን ነገር፣ የላም መልክ ያለው በቀራንዮ ላይ ደሙን ማፍሰሱ፣ የአንበሳው መልክ ያለው የጌታችንን ትንሣኤ፣ የንስር መልክ ያለው የጌታን ዕርገት እንደሚያመለክቱ ቀደምት መተርጒማን ይተነትኑታል።

ዳግመኛም ቅዱስ ዮሐንስ ይህንኑ በራእይ ያየውን ሲመሰክር እንዲህ ይላል፡- “በዙፋኑም ፊት ብርሌ የሚመስል የብርጭቆ ባሕር ነበረ፤ በዙፋኑም መካከል፣ በዙፋኑ ዙሪያም አራት እንስሶች አሉ፤ ….. እነዚህ እንስሶችም በዙፋን ላይ ለተቀመጠው ከዘለዓለም እስከ ዘለዓለም በሕይወት ለሚኖረው ለእርሱ ክብርና ውዳሴን ምስጋናንም ይሰጣሉ” በማለት ገልጿቸዋል፡፡ (ራእ.፬.፮-፱፣ ስንክሳር ዘኅዳር ገጽ ፪፻፸፯)

ከቅዱሳት መጻሕፍት መካከል አንዱ የሆነው መጽሐፈ ስንክሳር ደግሞ ኅዳር ስምንት ቀን “ሥጋ የሌላቸው የአርባዕቱ እንስሳ በዓላቸው ነው፡፡ እነርሱም የእግዚአብሔርን መንበር የሚሸከሙ ሠረገላዎቹ ናቸው” በማለት ይገልጻል፡፡

የቅዱሳኑ ኪሩቤልና የሱራፌል ጸሎት፣ አማላጅነትና ተራዳኢነት አይለየን፤ በረከታቸው ይደርብን፤ አሜን!