ሰባቱ ምሥጢራተ ቤተ ክርስቲያን
ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! እንዴት አላችሁልን? ጾመ ፍልሰታን እንዴት አሳለፋችሁ? ከሕፃን እስከ አዋቂ በአንድነት የሚጾሙት ጾመ ፍልሰታ እንግዴት አበቃ! ሁላችሁም እንደ ዓቅማችሁ በመጾም ስታስቀድሱ እንደ ነበር እናምናለን፡፡ አባቶቻችን ቅዱሳን ሐዋርያት ትንሣኤዋን እና ዕርገቷን እንዲመለከቱ ሱባኤ በገቡ ጊዜ እንደባረከቻቸው እኛንም ዛሬ ትባርከናለች፡፡
ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! ዓመቱ እየተገባደደ ነው፤ በአዲስ ዓመት በሚጀመረው ትምህርት በርትታችሁ ለመማር ዝግጅት እያደረጋችሁ ነው? ታዲያ በክረምቱ ሰ/ት/ቤት በመሄድ እንማር፤ እንዘምር እንደነበር፣ ትምህርት ሲከፈትም በዕረፍት ቀናችሁ ቤተ ክርስቲያን መሄድን፣ መንፈሳዊ ትምህርትን መማርን መቀጠል አለባችሁ፤ ባለፈው ትምህርታችን ከሰባቱ ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን የልጅነት ጸጋን አዲስ ሕይወትን የሚያሰጡ ምሥጢራት የሚባሉትን ምሥጢረ ጥምቀት፣ምሥጢረ ሜሮን፣ ምሥጢረ ቁርባን ተመልክተናል፤ ዛሬ ደግሞ የነፍስና የሥጋ ቁስልን (ሕመም) የሚፈውሱ ስለሆኑት ምሥጢረ ንስሐ እና ምሥጢረ ቀንዲል እንማራለን፤ መልካም!