“ወበእንተ ዝንቱ አስተርአየ ወልደ እግዚአብሔር ከመ ይሰዐር ግብሮ ለጋኔን”
ጥር 27 ቀን 2005 ዓ.ም.
በዲ/ን ኃይለ ኢየሱስ ቢያ
“የዲያብሎስን ሥራ ይሽር ዘንድ የእግዚአብሔር ልጅ ተገለጠ፡፡” 1ኛ ዮሐን.3፥8
ይህንን ኀይለ ቃል የተናገረው ቅዱስ ዮሐንስ ወንጌላዊ ነው፡፡ የተናገረበት ምክንያት፡-
የእግዚአብሔር አብ የባሕርይ ልጅ የጌታችን መድኀኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስን መገለጥ /ሰው ሆኖ የማዳን ሥራውን/ መፈጸሙን ለመግለጥ የተናገረው /የጻፈው ኀይለ ቃል ነው፡፡
-
መገለጥ ማለት ፡- ረቂቁ አምላክ በተአቅቦ ርቀቱን ሣይለቅ ውሱን ሥጋን ውሱኑም ሥጋ በተአቅቦ ውስንነቱን ሳይለቅ ረቂቅ መለኮትን የሆነበት በአጭር ቃል የቃል ግብር ለሥጋ የሥጋ ግብር ለቃል የሆነበት ረቂቅ ምስጢር ነው፡፡ በዚህም ምክንያት ቀዳማዊ ደኃራዊ የሆነው አምላክ ሞት የሚስማማው ሆነ፤ ዘመን የሚቆጠርለት ሥጋ ዘመን የማይቆጠርለት ሆነ፡፡ ሥጋ በማይመረመር ምስጢር የመለኮትን ገንዘብ ገንዘቡ ቢያደርግ “ፊተኛውና መጨረሻው ሕያውም እኔ ነኝ ሞቼም ነበርሁ ከዘላለም እስከ ዘላለም ድረስ ሕያው ነኝ” /ራእ.1፥17/ ማለት የቻለበት ምስጢር ነው፡፡ የረቀቀው ገዝፎ የገዘፈው ረቆ፣ ሰማያዊው ምድራዊ ምድራዊው ሰማያዊ ሆኖ መታየት ማለት ነው፣ ከዓለም ተሰውሮ የነበረው ምስጢር ግልጥ ሆኖ መታየት ማለት ነው ይህንንም ምሥጢር ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ በጢሞቴዎስ መልእክቱ “እግዚአብሔርን የመምሰል ምስጢር ያለጥርጥር ታላቅ ነው፤ በሥጋ የጠገለጠ፣ በመንፈስ የጸደቀ፣ ለመላእክት የታየ፣ በአሕዛብ የተሰበከ፣ በዓለም የታመነ፣ በክብር ያረገ /1ጢሞ 3፥16/ በማለት፡፡ ከልደት እስከ ዓቢይ ጾም መጀመሪያ ያለው ጊዜ ዘመነ አስተርእዮ /የመገለጥ ዘመን/ የመታየት ወቅት ይባላል