ትጋት
ሰኔ ፩፤፳፻፲፭ ዓመተ ምሕረት
የክርስቲያናዊ ምግባራችን ጽናት ከሚገለጽባቸው ዋነኞቹ ተግባራት መካከል ትጋት አንዱ ነው፡፡ ጸሎትን፣ ጾምንና ስግደትን በማብዛት የሚገለጸው ትጋታችን ክርስትናችንን የምናጠነክርበት ምግባራችን ነው፡፡ ዘወትር ሥርዓተ ጸሎትና ጾምን ጠብቀን መኖራችን በመንፈሳዊ ሕይወታችን ጠንክረንና ማንኛውንም ፈተና አልፈን እንድናንጓዝ ይረዳናልና ትጋታችንን ማጠንከር የምንችለው ዕለት ከዕለት ስንጸልይ፣ በሥርዓት ስንጾምና አብዝተን ስንሰግድ ነው፡፡
በዓለም ስንኖር መከራችን ሊበዛ ይችላል፤ ቢሆንም ግን መከራው የሚቆምበት ጊዜ አለና ያን ተስፋ በማድረግ የምንተጋው እግዚአብሔር አምላካችንን በማሰብ ነው፡፡ ለሥጋችን እንደምንተጋው ሁሉ ለነፍሳችንም አብዝተን መትጋት እንደሚገባ ለማስረዳት ቅዱስ ጴጥሮስ “ከፊት ይልቅ ትጉ” የሚል መልእክት ለሕዝበ ክርስቲያን አስተላለፈልን፡፡ (፪ኛጴጥ.፳፩፥፲)
ሐዋርያው በመትጋት ላይ ላሉት ሰዎች ይህን ቃል ሲያስተላልፍ ልክ እንደ ገበሬ ነው፡፡ አንድ ገበሬ እርሻ እያረሰ ሳለ በሬዎቹ የበለጠ እንዲተጉ ለማድረግ የሚያሳያቸው ጅራፉን ነው፤ ጅራፉን ባሳያቸው ሰዓት የበለጠ ጉልበት አውጥተው ያርሳሉ፤ ገበሬውም አይገርፋቸውም፡፡ ሆኖም ግን መንገዱን ማሳየት ስላለበት ያሳያቸዋል፤ ሐዋርያው ጳውሎስም ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመዋዕለ ስብከቱ ወንጌልን በማስተማር የክርስትናን ሕይወት ትጋት አሳይቷቸዋል፡፡ የጌታችን ቅዱስ ቃል ዕውቀት በመሆኑ ልንማርና ልናውቅ እንደሚገባ በዚህ አስተምሮናል፡፡
ማንኛውም ነገር ፍሬ ያፈራልና በፈቃደኝነት የምንማረው ዕውቀት ለማግኘት ነው፤ ትምህርተ ሃይማኖት፣ የቤተ ክርስቲያን ትምህርት፣ ነገረ ድኅነትና ስለ ቅዱሳን ገድልም ጭምር እንማራለን፡፡ እነዚህ የቤተ ክርስቲያን ምሰሶዎች ናቸው፤ አምስቱ አዕማደ ምሥጢራትን ማለትም ምሥጢረ ሥላሴ፣ ምሥጢረ ሥጋዌ፣ ምሥጢረ ጥምቀት፣ ምሥጢረ ቁርባን እና ምሥጢረ ትንሣኤ ሙታንን ልናውቃቸው የምንችለው ስንማር ነው፡፡ ዕውቀት ደግሞ ከመማር የምናገኘው ነው፤ ስለዚህም መማር ያስፈልገናል፡፡ ስንማር እያንዳንዱ ዕውቀት ይጨመርልናል፤ ተግባራችንን ሁሉ በዕውቀት ታግዘን የምንተገብረው ከሆነ አንሳሳትም፡፡
አስቀድሞ በቅዱሳን ነቢያት ላይ አድሮ አምላካችን እግዚአብሔር በተለያየ መንገድ አስተምሮናል፤ ይህ የቅዱስ ጴጥሮስ ቃል ደግሞ የዓለም ፍጻሜ ጊዜው መቼ እንደሆነ ባለማወቃችን እንድንጠነቀቅ እንዲሁም እንድንተጋ እና እንድንጸልይ የሚያሳስብ ነው፡፡
የምጽአት ቀን ከመምጣቱ በፊትም መትጋት እንደሚያስፈልገን ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ ባስተማረን መሠረት ልንተጋ ይገባል፡፡ ምክንያቱም የነፍሳችን ስንቅ የምንሰንቀው በተሰጠን የተወሰነ የምድራዊ ሕይወት ስለሆነ በወጣትነታችን ዘመን ላይ ባለን ጉልበት፣ ዕውቀትና መንፈሳዊ ሀብት በመትጋት እስከ ዘመን ፍጻሜ ልንኖር ይገባል፡፡ ትጋታችን ጥንካሬ፣ ብርታትና ጽናት ይሆነናልና፡፡
በጸሎትና በስግደት የታገዘ ጾም ደግሞ በክርስትና ሕይወት እንድንኖር ከማድረጉም በላይ ለበለጠ ቅድስና ያበቃናል፡፡ ትጋታችንም ከመጠራታችን ጋር የተያያዘ ሆኖ እንድንጸና የሚያመለክት ነውና፡፡ ሆኖም በተለያየ መንገድ ተጠርተናል፤ በመንፈሳዊነታችንም የተለያየ ሱታፌ አለን፡፡ አንዳንዶቻችን ለማስተማር፣ ሌሎቻችን ለዘማሪነት፣ ወይም ለምንኩስናና ለገዳም ሕይወት የተጠራን እንኖራለን፡፡ መክሊታችን የምናውቅ፣ የምንነግድበትና የምናተርፍበት ጥቂት ብንሆንም ሁላችን ግን በአንድም በሌላ ተጠርተናል፡፡ ሁላችንም የተጠራነው ግን በክርስቶስ ክርስቲያን ተብለን ለምንድንበትና ለምንጸድቅበት የክርስቲያናዊ ሕይወት በመሆኑ በጽድቅ ጎዳና ተጉዞ መንግሥተ ሰማያትን ለመውረስ ከምንም በላይ መትጋት ያስፈልጋልና፡፡
ቅዱስ ጴጥሮስ “ትጋትን ሁሉ እያሳያችሁ በእምነታችሁ በጎነት ጨምሩ” ያለን ለዚህ ነው፡፡ (፪ኛጴጥ.፩፥፭) እምነት ያለ በጎ ሥራ ከንቱ ነውና፡፡ ቅዱስ ያዕቆብም እምነት አለን ብለው በተስፋ ይኖሩ ለነበሩት ለዕብራውያን ሰዎች በእምነታቸው ብቻ እንደማይድኑና በጎ ሥራን መሥራት እንደሚያስፈልጋቸው ነግሯቸዋል፤ በእምነት በጎነት መጨመር ያስፈልጋል፡፡
በበጎነት መትጋት ማለት በየዕለት ኑሯችን ውስጥ ለራሳችን የምናደርገውን ማንኛውም መልካም ነገር ሁሉ ለሰዎች ሳናቋርጥ ማድረግ ነው፡፡ ዘወትር የዕለት ጉርሻችን ስናሟላ ለተራቡት ማብላትን፣ ለሰውነታችን አልባሳት ስንለብስ ለተራቆቱት ማልበስን፣ መጠለያችንንና መኖሪያችንን ስናዘጋጅ በጎዳና ላሉት ስደተኞች ማረፊያ ማሰብ ተገቢ ነው፡፡ እነዚህ ክርስቲያናዊ ተግባራችን ፈጣሪን ደስ የሚያሰኙ በመሆናቸው በትጋታትን ጊዜ አምላካችን ይጨመርልናል፡፡ ጸሎታችን የሰመረ እንዲሆን፣ ጾማችን ተቀባይነት እንዲኖረው እንዲሁም በስግደት እንድንተጋ ብርታትና ጽናት ይሆነናል፡፡
ስለዚህም በማንኛውም ጊዜ በየትኛውም ዓይነት ሁኔታ ውስጥ ብንሆን፣ መከራና ችግራችን ይብዛም ይነሥም፣ ሕይወታችን ሰላም ይሁን ወይም ሁካታ ይብዛበት፣ ደስተኛም እንሁን ኀዘንተኛ በክርስቲያናዊነታችን ሳናማርር በትጋት ልንኖር ይገባል፡፡ በተለይም በአሁኑ ጊዜ ሃይማኖታችን፣ ቤተ ክርስቲያናችን እና ሀገራችን ላይ ጠላት ሸምቆ ሊያጠፋን እያሳደደን በመሆኑ ይህን ሴራና ክፋት ለመመከት በርትተን በጾም፣ በጸሎትና በስግደት ልንተጋ እንደሚገባ የሐዋርያው ቃል ያስተምረናል፡፡
ዓለማችን በተለያዩ የማኅበረሰባዊ፣ የኢኮኖሚያዊና የፖለቲካዊ ችግሮች ተውጣ፣ ሕዝቦቿም በመከራና ሥቃይ ተከበውና መፍትሔ አጥተው በጭንቅ ባሉበት በዚህ ዘመን ማድረግ የምንችለው ቀደሚ ተግባር ወደ አምላካችን እግዚአብሔር መጮህ ስለሆነ እርሱም እንዲሰማንና መልስ እንዲሰጠን አብዝተን መጸለይ ይጠበቅብናል፡፡ ጸሎታችን ደግሞ በስግደት የታገዘ መሆን እንዳለበት ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን ያዘናል፡፡ ዘወትር ከመጸለይና ከመስገድም ባሻገር የአጽዋማት ወቅቶችን ሳናጓድል በመጠበቅ ልንጾም ይገባል፡፡
አምላካችን እግዚአብሔር በጸሎት፣ በጾምና በስግደት እንድንተጋ ይርዳን፤ አሜን!