አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ
‹‹ኮከበ ክብር ጽዱል ፀሐዬ አግዓዚ ብሩህ አቡነ ጊዮርጊስ ጥዑመ ስመ ወሠናየ ግዕዝ መጋቤ ሃይማኖት ወመሠረተ ቤተ ክርስቲያን፤ አባታችን ጊዮርጊስ ዘጋስጫ የሚያበራ የክብር ኮከብ፣ የኢትዮጵያ ብሩህ ፀሐይ፣ ስሙ የሚጣፍጥ፣ ምግባሩ የቀና ነው።›› (ገድለ አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ)
መምህር ሰሎሞን ጥጋቡ
ሐምሌ ፮ ቀን ፳፻፲፬ ዓ.ም
የቅዱሳን ታሪክ የትውልድን አእምሮ የሚያንጽ እንዲሁም የእነርሱን ፈለግ እንድንከተል የሚያደረግ ነው፡፡ የቀደመውን ትውልድ በማውሳት፣ አሁን ያለውንና ወደፊት የሚመጣውን ትውልድ ደግሞ ከተያዘበት የኃጢአት አረንቋ ለማውጣትና ካለበት የሥጋ ሕማም ለመፈወስ እንዲሁም ሃይማኖትንና ጥበበ እግዚአብሔር ገንዘብ አድርጎ መንግሥተ ሰማያትን እንዲወርስ የደከሙት አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ ከቅዱሳኑ አባት አንዱ ናቸው።
አባ ጊዮርጊስ የተወለዱት ጥንተ ስሙ ብሔረ አምሃራ ነገሥታት መናገሻ ከነበረው ከአማራ ሳይንት አካበ በአሁኑ ደቡብ ወሎ ሀገረ ስብከት በቦረና አውራጃ በከለላ ወረዳ በወለቃ እናበበቶ ወንዝ መካከል በምትገኘዋ ልዩ ስሟ ሸግላ/ሰግላ/ደብረ ማኅው በ፲፫፻፶፯ ዓ.ም በአፄ ዳዊት ዘመነ መንግሥት ነው፡፡ አባታቸው ሕዝበ ጽዮን እናታቸው እምነ ጽዮን ይባላሉ፤ ቤተሰቦቻቸው ከካህናት ወገን እና ከነገሥታት ወገን ናቸው። እንደነ ኤልሳቤጥ እና እንደ ዘካርያስ በሕግ የጸኑ ደጋግ አባቶች ቢሆኑም ልጅ ስለ አልነበራቸው፤ ዘወትር ወደ ቤተ እግዚአብሔር በመመለስ በእመቤታችን በቅድስት ድንግል ማርያም ስዕል አድኅኖ ፊት እግዚአብሔር ልጅ እንዲሰጣቸው ይጸልዩ ነበር። ሁሉን ማድረግ የሚቻለው እግዚአብሔር ጸሎታቸዉን ካደረሱ በኋላ ‹‹አስመ አልቦ ነገር ዘይሳኖ ለእግዚአብሔር፤ ለእግዚአብሔር የሚሳነው ነገር የለምና›› ይህን ቅዱስ በቅዱስ ዑራኤል አብሣሪነት ተወልዷል፤ ቅዱሱ ጥቅምት ሦስት ቀን ፲፫፻፶፯ ዓም ተፀንሰው ሐምሌ ፯ ቀን ዕለተ ማክሰኞ ቅድስ አባታችን ተወለዱ። (ድርሳነ ዑራኤል)
አብርሃም ሥላሴን ባስተናገደበት ዕለት አባ ጊዮርጊስ ዕድሚያቸው ለትምህርት እስኪ በቃ ድረስ እናታቸው ጋር እግዚአብሔርን እንዲፈራና ትሕትናን ገንዘብ እንዲያደርግ እናቱ አስተማረችው። ከዚህ በመቀጠል አባታቸው በቤተ መንግሥት ከሚያገለግሉ ካህናት ወስደው ልጃቸውን በመልካም አስተዳደግ በቤተ ክርስቲያን ትምህርት በማስተመር አሳደጓቸው። ምንም እንኳን አባታቸው ወደ ተምህርት ቤት ቢወስዷቸውም ትምህርት ቶሎ ሊገባቸውም አልቻለም ነበር፤ ይህ የእርሳቸው ትምህርት አለመግባት የቅዱስ ያሬድን ታሪክ ያስመስላል፤ ቢሆንም ሁል ጌዜ የእመቤታችን ስዕል ፊት እየሆኑ ማኅፀናት ነበር። ከዕለታት አንድ ቀን እመቤታችን ተገልፃ ‹‹አይዞህ አታልቅስ፤ ትምህርት ተከልክሎብህ ሳይሆን የምትጠቀምበት ጊዜው እስኪ ደርስ ነው፤ አሁን ጊዜዉ ደርሷል›› አለችው፤ ‹‹እስከ ፯ ቀን በዚሁ እንዳለህ ጠብቀኝ›› ብለውም ተሠወረች። እርሳቸውም ተስፋውን ተቀብለው በሱባዔ እንዳሉ እንደተለመደው በስዕለ ማርያም ሥር ተደፍተው ሲያለቅሱ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም የመልአክት አለቃ ቅዱስ ዑራኤልን አስከትላ ጽዋ እሳት (ጽዋ ልቦና እንዳጠጠው ዕዝራ ሱቱኤልን) የሕይወት ጽዋ አጠጣችው። አባ ጊዮርጊስ የሕይወት ጽዋ ከተጎነጩ በኋላ የሰማይና የምድር ምሥጢር ተገለጸላቸው።
አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ የደረሱት መጽሐፍት ከሃምሳ በላይ ይሆናሉ፡፡ በስም የሚታወቁት ግን ሰዓታት ዘመዓልት ወዘሌሊት፣ ኖኅተ ብርሃን ከመጽሐፈ አርጋኖን ጋር አብሮ ታትሟል፣ ውዳሴ መስቀል፣ ቅዳሴ፣ ውዳሴ ሐዋርያት፣ አርጋኖነ ውዳሴ፣ ፍካሬ ሃይማኖት፣ መጽሐፈ ምሥጢር፣ ውዳሴ ስብሐት፣ እንዚራ ስብሐት፣ ሕይወተ ማርያም፣ ተአምኖ ቅዱሳን፣ መጽሐፈ ብርሃን እንዲሁም ጸሎት ዘቤት ናቸው፡፡ አባ ጊዮርጊስ እንደ ቅዱሳን ሐዋርያት ሀብተ መንፈስ ቅዱስ የተሞሉ አባት ናቸው፡፡
በዜማ ትምህርት በጣም ጠልቀው ያውቁ፣ የቅዱስ ያሬድን ዜማ በተለይም ድጓውን በዘመናት ከፋፍለው እና በየበዓላቱ አደራጅተው፣ ቅርጽ በማያስያዝ ለቅዱሳኑ ሁሉ በየባህሎታቸው የሚዜመውን አዘጋጅተው ለደቀ መዛሙራቶቻቸው በማስተማር እንዲስፋፋ አድርገዋል፡፡
አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ ድጓውን በደብር ነጎድጓድ ሐይቅ ለሰባት ፯ ‹በርእስ አድባራት ተድባበ ማርያም› አስተምረዋል፡፡ በዜማው በኩል አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ ከያሬድ በኋላ የተነሡ ዳግማዊ ያሬድ ሲባሉ በዘመኑ የነበሩትን መናፍቃንን በመከራከርና አስተምረው በመርታታቸው ‹ኢትዮጵያዊው ቄርሎስ› የሚል ስምም ተሰጥታቸዋል፡፡ አባ ጊዮርጊስ ስለ ሰማይ፣ ስለ መብረቅና ስለ ዝናም አፈጣጠርና ባሕርያት በሚገባ አስተምረዋል፡፡ ሆኖም ግን ድርሰቶቻቸውን የውጭ አንብባቢዎች ሲጠቀሙበት የሀገራችን ሰዎች ግን የታላቁን ቅዱስ ታሪክ እንኳን በቅጡ የማያውቅ ነው፡፡ እርሳቸው ግን የቤተ ክርስቲያን መብራት ናቸው፡፡ ምክንያቱም ዛሬ በቅዳሴው፣ በማኅሌቱ፣ በሰዓታቱ፣ በምሥጢሩና የምስጋና ድርሰቶች አሁንም ቤተ ክርስቲያን እየተጠቀመችባቸው ትገኛለች፡፡ ይህ ሕሙም ትውልድ መድኃኒት ያስፈልገዋለና መድኃኒቱን ለማግኘት ሌት ከቀን በመጾም፣ በመጸለይና መትጋት እንዳለበት በአጽንዖት አስተምረዋል፡፡አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ በአጼ ይስሐቅ ዘመነ መንግሥትም ‹‹ከፍተኛ የቤተ ክርስቲያን ተጠያቂ ሊቅ›› ተደርገው ተሹመው ነበር፡፡
አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ የትሕት፣ የርኅራኄና የምሥጢር ባለቤት አባት ናቸው፡፡ የርኅራኄ አባት ያልንበት ምክንያት እንዲህ ነው፤ በአንድ ወቅት ሳያመነኩሱ ገና ንጉሥ ዳዊት ልጃቸውን እንዲያገቡና በእርሳቸው ቦታ እንዲተከቱ በተደጋጋሚ ጥያቄ አቀረቡላቸው፡፡ እርሳቸውም የንጉሡን መልክእት በመስማትና ያሞክሮ ልብስ በመልበስ የመጣባቸውን ፈተና አልፈውታል፡፡ በዚህ ምክንያት ንጉሥ ዳዊት ስላልሰሟቸው ብዙ መከራና ሥቃይ አድርሰውባቸዋል፡፡ ግን እኚህ ንጉሥ መስቀሉን ሊያመጡ ሲሄዱ ጎዳና ላይ በቅሎ ረግጣቸው ሞቱ። አባ ጊዮርጊስም የንጉሡን ሞት በሰሙ ጊዜ ስቅስቅ ብለው አለቀሱ፡፡ ‹‹ምነው ያ ሲያንገላታህ፣ ብዙ መከራ ሲያደርስብህና በጨለማ ቤት ሲወረውርህ ደስ ሊል ይገባል እንጂ እንዴት ታለቅሳለህ?›› ብሎ ሰዎች ሲጠይቋቸው ‹‹እንደዚያም ቢሆን ንጉሡ እመቤታችንን ይወዱ ስለነበረ ነው ያዘንኩት›› ብለው መልሰውላቸዋል፡፡ በመጽሐፍ ‹‹የእግዚብሔር መንገድ ቅን ነው። ጻድቃን ይሄዱበታል፡፡ ሕግ ተላላፊዎች ግን ይወድቁበታል፤›› ተብሏል፡፡ (ሆሴ.፲፬፥፱)
አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ በተወለዱ በ፷ ዓመታቸው ኢትዮጵያ አበቅቴ አልቦ በሆነበት ጊዜ ጥንተ ዮን በወንጌላዊው ማቴዎች ዘመን ረቡዕ ቀን ይስሐቅ በነገሥ በዐሥራ አንድ ዓመት በ፲፬፻፰ ሐምሌ ፯ ቀን ዐርፈዋል፡፡
የጻድቁ በረከት በሁላችን ላይ ይደርብን፤ አሜን፡፡