የ ‹ሀ፣ አ፣ ወ እና የ› በግሥ ርባታ የሚያመጡት ለውጥ
መምህር በትረማርያም አበባው
የካቲት ፲፬ ቀን ፳፻፲፬ ዓ.ም
ውድ አንባብያን! እንደምን ሰነበታችሁ? የእግዚአብሔር አምላካችን ስም የተመሰገነ ይሁን! ባለፈው የትምህርታችን ክፍለ ጊዜ ስምንቱን ስለ ዐበይት አናቅጽ እና ዐሥራው አስተምረናችሁ ነበር፡፡ በዚህ ሳምንት ደግሞ ለሰጠናችሁ መልመጃ ምላሽና የ ‹‹ሀ፣ አ፣ ወ እና የ›› የሚያመጡት የርባታ ለውጥ በግሥ ርባታ እንመለከታለን፤ በጥሞና ተከታተሉን!
የመልመጃ ጥያቄዎች
የሚከተሉትን ቃላት ከቀዳማይ እስከ ትእዛዝ አንቀጽ ዘርዝሩ!
፩) ኖመ-ተኛ (ቆመ)
፪) ጠበ-ብልሃተኛ ሆነ (ነደ)
፫) ሠምረ-ወደደ (ገብረ)
፬) ዘገበ-ሰበሰበ (ቀተለ)
፭) መነነ-ናቀ (ቀደሰ)
፮) ናፈቀ-ተጠራጠረ (ባረከ)
፯) ፄወወ-ማረከ (ዴገነ)
፰) ሞቅሐ-አሰረ (ጦመረ)
የጥያቄዎች መልሶች
፩) ኖመ፤ተኛ
ይነውም | ይተኛል |
ይኑም | ይተኛ ዘንድ |
ይኑም | ይተኛ |
፪) ጠበ፤ብልሃተኛ ሆነ
ይጠብብ | ብልሃተኛ ይሆናል |
ይጥብብ | ብልሃተኛ ይሆን ዘንድ |
ይጥብብ | ብልሃተኛ ይሁን |
፫) ሠምረ፤ወደደ
ይሠምር | ይወዳል |
ይሥመር | ይወድ ዘንድ |
ይሥመር | ይውደድ |
፬) ዘገበ፤ሰበሰበ
ይዘግብ | ይሰበስባል |
ይዝግብ | ይሰበስብ ዘንድ |
ይዝግብ | ይሰብስብ |
፭) መነነ፤ናቀ
ይሜንን | ይንቃል |
ይመንን | ይንቅ ዘንድ |
ይመንን | ይናቅ |
፮) ናፈቀ፤ተጠራጠረ
ይናፍቅ | ይጠራጠራል |
ይናፍቅ | ይጠራጠር ዘንድ |
ይናፍቅ | ይጠራጠር |
፯) ፄወወ፤ማረከ
ይፄውው | ይማርካል |
ይፄውው | ይማርክ ዘንድ |
ይፄውው | ይማርክ |
፰) ሞቅሐ፤አሠረ
ይሞቅሕ | ያሥራል |
ይሞቅሕ | ያሥር ዘንድ |
ይሞቅሕ | ይሠር |
የተወደዳችሁ አንባብያን! እነዚህን ምላሾች በትክክል ካገኛችሁ ትምህርቱ ገብቷችኋልና በርቱ! አሁን ደግሞ የዚህን ክፍለ ጊዜ ትምህርታችን እንደሚከተለው አቅርበነዋል፡፡ ተከታተሉን!
የ ‹ሀ፣ አ፣ ወ እና የ› በግሥ እርባታ የሚያመጡት የርባታ ለውጥ
‹ሀ› እና ‹አ› በቀተለ ቤት መጀመሪያ ላይ ሲመጡ በካልኣይ አንቀጽ ዐሥራውን ግእዝ ያደርጉታል። በዘንድና በትእዛዝ አንቀጽ ግን አይለወጥም።
ግእዝ | አማርኛ |
ሐለመ | አለመ |
የሐልም | ያልማል |
ይሕልም | ያልም ዘንድ |
ይሕልም | ያልም |
ግእዝ | አማርኛ |
አነመ | ሠራ |
የአንም | ይሠራል |
ይእንም | ይሠራ ዘንድ |
ይእንም | ይሥራ |
‹ሀ› እና ‹አ› በቀደሰ ቤት መጀመሪያ ላይ ሲመጡ በካልኣይ አንቀጽ ለውጥ አያመጡም። በዘንድና በትእዛዝ ግን ዐስራውን ግእዝ ያደርጉታል።
ግእዝ | አማርኛ |
ሐወጸ | ጎበኘ |
ይሔውጽ | ይጎበኛል |
የሐውጽ | ይጎበኝ ዘንድ |
የሐውጽ | ይጎብኝ |
ግእዝ | አማርኛ |
ዐመፀ | በደለ |
ይዔምፅ | ይበድላል |
የዐምፅ | ይበድል ዘንድ |
የዐምፅ | ይበድል |
‹ሀ› እና ‹አ› በገብረ ቤት መጀመሪያ ሲመጡ በካልኣይ አንቀጽ አሥራውን ግእዝ ያደርጉታል። በዘንድና በትእዛዝ አንቀጽ ግን ለውጥ አያመጡም።
ግእዝ | አማርኛ |
አምነ | አመነ |
የአምን | ያምናል |
ይእመን | ያምን ዘንድ |
ይእመን | ይመን |
ግእዝ | አማርኛ |
ኀልቀ | አለቀ |
የኀልቅ | ያልቃል |
ይኅለቅ | ያልቅ ዘንድ |
ይኅለቅ | ይለቅ |
ዐራት ፊደል ባለው የተንበለ ቤት ‹ሀ› እና ‹አ› መጀመሪያ ከመጡ በካልዓይ፣ በዘንድ እና በትእዛዝ አስራውን ግእዝ ያደርጉታል። አምስት ፊደል ባለው የተንበለ ቤት በካልዓይ፣ በዘንድ እና በትእዛዝ ዐስራውን ራብዕ ያደርጉታል።
ግእዝ | አማርኛ |
አንዘረ | መታ |
የአነዝር | ይመታል |
የአንዝር | ይመታ ዘንድ |
የአንዝር | ይምታ |
ግእዝ | አማርኛ |
ኀንገረ | እሽኮኮ አለ |
የኀነግር | እሽኮኮ ይላል |
የኀንግር | እሽኮኮ ይል ዘንድ |
የኀንግር | እሽኮኮ ይበል |
ግእዝ | አማርኛ |
አመድበለ | አከማቸ |
ያመደብል | ያከማቻል |
ያመድብል | ያከማች ዘንድ |
ያመድብል | ያከማች |
ግእዝ | አማርኛ |
አጽደልደለ | አበራ |
ያጽደለድል | ያበራል |
ያጽደልድል | ያበራ ዘንድ |
ያጽደልድል | ያብራ |
‹ሀ› እና ‹አ› በባረከ፣ በጦመረ፣ በክህለ፣ በሴሰየ ቤት መጀመሪያ ቢመጡ ለውጥ አያመጡም። ‹ሀ› እና ‹አ› በቀተለ ቤት መካከል ላይ ቢመጡ ካልኣይ አንቀጽን ፍጹም ሳድስ ያደርጉታል። በዘንድና በትእዛዝ ቅድመ መድረሻውን ግእዝ ያደርጉታል።
ግእዝ | አማርኛ |
መሐለ | ማለ |
ይምሕል | ይምላል |
ይምሐል | ይምል ዘንድ |
ይምሐል | ይማል |
ግእዝ | አማርኛ |
ሰአለ | ለመነ |
ይስእል | ይለምናል |
ይስአል | ይለምን ዘንድ |
ይስአል | ይለምን |
በቀደሰ ቤትና በገብረ ቤት ‹ሀ› እና ‹አ› በመካከል አይገኙም። በተንበለ፣ በባረከ፣ በጦመረ፣ በክህለ እና በሴሰየ ቤት መካከል ላይ ቢገኙም ለውጥ አያመጡም። ‹ሀ› እና ‹አ› በቀተለ ቤት በመድረሻ አይገኙም። ‹ሀ› እና ‹አ› ሦስት ፊደል ባለው የቀደሰ ቤት ለውጥ አያመጡም። አራትና ከዚያ በላይ ፊደል ባለው የቀደሰ ቤት ግን ቅድመ መድረሻውን ራብዕ ያደርጋሉ።
ግእዝ | አማርኛ |
ሰአለ | ለመነ |
ይስእል | ይለምናል |
ይስአል | ይለምን ዘንድ |
ይስአል | ይለምን |
ግእዝ | አማርኛ |
ተመክሐ | ተመካ |
ይትሜካሕ | ይመካል |
ይትመካሕ | ይመካ ዘንድ |
ይትመካሕ | ይመካ |
ግእዝ | አማርኛ |
ተፈሥሐ | ተደሰተ |
ይትፌሣሕ | ይደሰታል |
ይትፈሣሕ | ይደሰት ዘንድ |
ይትፈሣሕ | ይደሰት |
‹ሀ› እና ‹አ› በገብረ ቤት መድረሻ ላይ ሲገኙ በካልኣይ አንቀጽ ለውጥ አያመጡም። በትእዛዝና በዘንድ አንቀጽ ግን ቅድመ መድረሻውን ራብዕ ያደርጉታል።
ግእዝ | አማርኛ |
በጽሐ | ደረሰ |
ይበጽሕ | ይደርሳል |
ይብጻሕ | ይደርስ ዘንድ |
ይብጻሕ | ይድረስ |
ግእዝ | አማርኛ |
በልዐ | በላ |
ይበልዕ | ይበላል |
ይብላዕ | ይበላ ዘንድ |
ይብላዕ | ይብላ |
በተንበለ፣ በባረከ፣ በዴገነ፣ በጦመረና በክህለ ‹ሀ› እና ‹አ› በመድረሻ ቢመጡም ለውጥ አያመጡም። ‹ወ› በቀተለ፣ በገብረ እና በክህለ ቤት በካልኣይ አንቀጽ ለውጥ አያመጣም። በዘንድና በትእዛዝ አንቀጽ ግን ‹ወ› ይጎረዳል። ቅድመ መድረሻውንም ግእዝ ያደርገዋል።
ግእዝ | አማርኛ |
ወረደ | ወረደ |
ይወርድ | ይወርዳል |
ይረድ | ይወርድ ዘንድ |
ይረድ | ይውረድ |
ግእዝ | አማርኛ |
ወድቀ | ወደቀ |
ይወድቅ | ይወድቃል |
ይደቅ | ይወድቅ ዘንድ |
ይደቅ | ይውደቅ |
ግእዝ | አማርኛ |
ውኅዘ | ፈሰሰ |
ይውኅዝ | ይፈሳል |
የኀዝ | ይፈስ ዘንድ |
የኀዝ | ይፍሰስ |
‹ወ› በቀደሰ ቤትና በተንበለ ቤት መነሻ ቢመጣ ለውጥ አያመጣም። በጦመረ፣ በሴሰየ እና በባረከ ቤት ‹ወ› በመነሻ አይገኝም። ‹ወ› በመካከል ሲገኝ በስምንቱም አርእስት ለውጥ አያመጣም። ‹ወ› በገቢር ግሥ በቀተለ፣ በቀደሰ እና በተንበለ ቤት ሲገኝ ‹ወ› ይጎረድና ቅድመ መድረሻውን ካዕብ ያደርጋል።
ግእዝ | አማርኛ |
ነቀወ | ጮኽ |
ይነቁ | ይጮኻል |
ይንቁ | ይጮኽ ዘንድ |
ይንቁ | ይጩኽ |
ግእዝ | አማርኛ |
ለበወ | አስተዋለ |
ይሌቡ | ያስተውላል |
ይለቡ | ያስተውል ዘንድ |
ይለቡ | ያስተውል |
ግእዝ | አማርኛ |
ወርዘወ | ጎለመሰ |
ይወረዙ | ይጎለምሳል |
ይወርዙ | ይጎለምስ ዘንድ |
ይወርዙ | ይጎልምስ |
‹ወ› በተገብሮ ግሥ በቀተለ፣ በቀደሰ እና በተንበለ ቤት መድረሻ ሲመጣ ‹ወ› ይጎረድና ድኅረ መነሻውን ኃምስ አድርጎ ቅድመ መድረሻውን ሳብዕ ያደርጋል።
ግእዝ | አማርኛ |
ተፈነወ | ተላከ |
ይትፌኖ | ይላካል |
ይትፈኖ | ይላክ ዘንድ |
ይትፈኖ | ይላክ |
ግእዝ | አማርኛ |
ተደመረ | ተጨመረ |
ይዴመር | ይጨመራል |
ይደመር | ይጨመር ዘንድ |
ይደመር | ይጨመር |
ግእዝ | አማርኛ |
ተሠገወ | ሰው ሆነ |
ይሤጎ | ሰው ይሆናል |
ይሠጎ | ሰው ይሆን ዘንድ |
ይሠጎ | ሰው ይሁን |
‹ተ፣ ሰ፣ ዘ፣ ደ፣ ጠ፣ ፀ› ፊደላት ‹ተ› ን ተከትለው ከመጡ ‹ተ› ይጎረዳል። ተደመረ ብሎ ይትዴመር ሳይል ይዴመር ያለው ለዚያ ነው። በመድረሻ ሁለት ‹ወ› ደጊመ ቃል ከመጣ አይጎርድም ለውጥ አያመጣም።
ግእዝ | አማርኛ |
ከወወ | ተላከ |
ይከውው | ቅልጥፍጥፍ ይላል |
ይክውው | ቅልጥፍጥፍ ይል ዘንድ |
ይክውው | ቅልጥፍጥፍ ይበል |
‹የ› በስምንቱም አርእስት በመነሻና በመካከል ሲገኝ ምንም ለውጥ አያመጣም። ‹የ› በቀደሰ፣ በገብረ እና በባረከ ቤቶች መድረሻ ሲመጣ ‹የ› ን ጎርዶ ቅድመ መድረሻውን ሣልስ ያደርጋል።
ግእዝ | አማርኛ |
ጸለየ | ለመነ |
ይጼሊ | ይለምናል |
ይጸሊ | ይለምን ዘንድ |
ይጸሊ | ይለምን |
ግእዝ | አማርኛ |
ሰትየ | ጠጣ |
ይሰቲ | ይጠጣል |
ይስተይ | ይጠጣ ዘንድ |
ይስተይ | ይጠጣ |
ግእዝ | አማርኛ |
ሣቀየ | አሠቃየ |
ይሣቂ | ያሠቃያል |
ይሣቂ | ያሠቃይ ዘንድ |
ይሣቂ | ያሠቃይ |
በቀተለ ቤት ሲመጣ በካልዓይ ጎርዶ በዘንድና በትእዛዝ ሳይጎርድ ገብረን መስሎ ይረባል፡፡
ግእዝ | አማርኛ |
ገነየ | ተገዛ |
ይገኒ | ይገዛል |
ይግነይ | ይገዛ ዘንድ |
ይግነይ | ይግዛ |
‹የ› በመድረሻ ደጊመ ቃል በሆነ ጊዜ አይጎርድም። ምሳሌ፦
ግእዝ | አማርኛ |
ጻሕየየ | አረመ |
ይጻሐይይ | ያርማል |
ይጻሕይይ | ያርም ዘንድ |
ይጻሕይይ | ያርም |
በአምስቱ አዕማድ ከካልዓይ አንቀጽ እስከ ትእዛዝ አንቀጽ ያለው እንደሚከተለው ይረባል።
ግእዝ | አማርኛ |
ቀተለ | ገደለ |
ይቀትል | ይገድላል |
ይቅትል | ይገድል ዘንድ |
ይቅትል | ይግደል |
ግእዝ | አማርኛ |
አቅተለ | አስገደለ |
ያቀትል | ያስገድላል |
ይቅትል | ያስገድል ዘንድ |
ያቅትል | ያስገድል |
ግእዝ | አማርኛ |
ተቀትለ | ተገደለ |
ይትቀተል | ይገደላል |
ይትቀተል | ይገደል ዘንድ |
ይትቀተል | ይገደል |
ግእዝ | አማርኛ |
አስተቃተለ | አገዳደለ |
ያስተቃትል | ያገዳድላል |
ያስተቃትል | ያገዳድል ዘንድ |
ያስተቃትል | ያገዳድል |
ግእዝ | አማርኛ |
ተቃተለ | ተገዳደለ |
ይትቃተል | ይገዳደላል |
ይትቃተል | ይገዳደል ዘንድ |
ይትቃተል | ይገዳደል |
የመልመጃ ጥያቄዎች
የሚከተሉትን ግሦች ከካልዓይ እስከ ትእዛዝ አንቀጽ አርቡ!
፩) ፈረየ፤አፈራ
፪) ወለደ፤ወለደ
፫) ሰወረ፤ደበቀ
ረድኤተ እግዚአብሔር አይለየን።