ርደተ መንፈስ ቅዱስ
መጋቤ ብሉይ ዮሴፍ ደሳለኝ
ሰኔ ፲፩ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም
ርደተ መንፈስ ቅዱስ ወይንም የመንፈስ ቅዱስ መውረድ በብሉይ ኪዳን በትንቢት የተነገርና በሐዲስ ኪዳን የተፈጸመ ነው፡፡ ነቢዩ ኢዮኤል ስለ መንፈስ ቅዱስ ወደዚህ ዓለም መውረድ፣ በመንፈስ ቅዱስ ጸጋና ሀብትነት ዓለም እንደሚታነጽና ሃይማኖት እንደሚጸና እንዲህ ሲል ተናግሯል፤ ‹‹ከዚህም በኋላ እንዲህ ይሆናል፤ መንፈሴን በሥጋ ለባሽ ሁሉ ካይ አፈሳለሁ፡፡›› (ኢዩ. ፪፥፳፰)
ብዙ ዘመን የተባለውም ሰዎች በኃጢአት አረንቋ የኖሩበትን እንዲሁም እግዚአብሔር ወልድ ለሰዎች ድኅነት ወደዚህ ዓለም ከመምጣቱ በፊት የነበሩትን ፭፼፭፻ (አምስት ሺህ አምስት መቶ) ዘመናት ነው፡፡ አምላካችንም መንፈሱን በሰዎች እንደሚያፈስ የተናገረበት ምክንያት በመጽሐፍ ቅዱስ በቅዱሳን ሐዋርያት ላይ ‹‹መንፈስ ቅዱስ መላባቸው›› ተብሎ እንደተገለጸው የመንፈስ ቅዱስ መፍሰስ በቅዱሳኑ እንደሚያሳድርባቸው ሲያመለክት ነው፡፡ እነርሱም ትንቢትን እንደሚናገሩ፣ እንደሚያስተምሩ፣ አስተዋይና ዐዋቂ እንደሚሆኑ በነቢዩ ኢዩኤል ላይ አድሮ በተናገረው መሠረት ለሰዎች ሁሉ መንፈስ ቅዱስ በወረደበት ዕለት ተሰጥቷል፡፡ (ሐዋ. ፪፥፬)
በብሉይ ኪዳን የተነገረው ትንቢትም በሐዲስ ኪዳን ተፈጽሞ በአባቶቻችን ላይ እንዲሁም በሰዎች በሙሉ መንፈስ ቅዱስ እንደተሰጠ እንመለከታለን፡፡ ለምሳሌ በዮሐንስ ወንጌል ምዕራፍ ፲፬፥፲፪-፲፯ ያለውን ኃይለ ቃል ስንመለከት እግዚአብሔር አምላክ ወደ ሰማይ እንደሚያርግ፣ ከዚያም በኋላ መንፈስ ቅዱስን እንደሚልክልን ይገልጻል፤‹‹አብ ለዘለዓለም ከእናንተ ጋር ይኖር ዘንድ ሌላ አጽናኝ ይልክላችኋል፡፡ እርሱም ዓለም ስለማያየውና ስለማያውቀው ሊቀበለው የማይችለው የእውነት ነው፡፡›› ጌታችን ኢየሱስም ዓለም እንደማያየው የተናገረው መንፈስ ቅዱስ የሰዎች ልዩ ኃይልና ሀብት መሆኑን ሲገልጽ ነው፡፡ (ዮሐ. ፲፬፥፲፭-፲፯)
በሉቃስ ወንጌል እንደተጻፈው ደግሞ ጌታችን ኢየሱስ ድኅነተ ዓለምን ፈጽሞ ከሙታን ተለይቶ ከተነሣ በ፵ኛው ቀን ወደ ሰማየ ሰማያት በሚያርግበት ጊዜ ደቀ መዛሙርቱን ይዞ ወደ ቢታንያ ከወጣ በኋላ በተስፋ እንዲጠብቁና ከሰማይ የሚወርደውን መንፈስ ቅዱስ እስከሚጎናጸፉ ድረስ የእግዚአብሔርን ትእዛዛ እንዲመጠበቅ እንዲህ ሲል አዘዛቸው፤ ‹‹እነሆ፥ እኔ የአባቴን ተስፋ ለእናንተ እልካለሁ፤ እናንተ ግን ከአርያም ኃይልን እስክትለብሱ ድረስ በኢየሩሳሌም ከተማ ተቀመጡ፡፡›› ከዚህም መመሪያ በመነሣት አባቶቻችን የአምላካቸውን ትእዛዝ አክባሪዎችና ጠባቂዎች በመሆናቸው ወደ ኢየሩሳሌም ተመልሰው በቤተ መቅደስ እግዚአብሔርን እያመሰገኑ ቆዩ፡፡ (ሉቃ. ፳፬፥፵፱)
ከዚህም በኋላ ዓለምን ዞረው በመንፈስ ቅዱስ ኃይል በሁሉም ቋንቋ ተናገሩ፤ አስተማሩም፡፡ ‹‹ኀምሳው ቀንም በተፈጸመ ጊዜ ሁሉም በአንድነት በአንድ ቦታ ተሰብስበው ነበር፡፡ ድንገትም እንደ ዐውሎ ነፋስ ድምፅ ያለ ከሰማይ ድምፅ መጣ፤ የነበሩትንም ቤት ሞላው፡፡ እንደ እሳት የተከፋፈሉ የእሳት ላንቃዎችም ታዩአቸው፤ በሁሉም ላይ ተቀመጡባቸው፡፡ ሁሉም መንፈስ ቅዱስን ተሞሉ፤ ይናገሩ ዘንድ መንፈስ ቅዱስ እንደ አደላቸው መጠንም እየራሳቸው በሀገር ሁሉ ቋንቋ ይናገሩ ጀመር›› እንዲል፤ (ሐዋ. ፪፥፩-፬)
መንፈስ ቅዱስም በብሉይ ኪዳን ለተለያዩ አበው አባቶች ምሥጢራትን እንደገለጠና ትንቢትን እንዳናገረ ሁሉ በሐዲስ ኪዳን ደግሞ ሐዋርያት አባቶቻችን በአንድ ዝግ ቤት በነበሩበት ጊዜ በማጽናት ነገሥታትን ሳይፈሩ በአደባባይም እንዲሰብኩ አድርጓቸዋል፡፡ ሰማያዊ ኃይልን ለብሰዋልና ጥበብም ተገለጠላቸው፤ የተለያየ ቋንቋም መናገር የጀመሩት በዚህን ጊዜ ነበር፡፡ መንፈስ ቅዱስ ከሳቲ ነውና ምሥጢርን ስለገለጠላቸው በ፸፪ ቋንቋዎችን በአንድ ጊዜ መናገር ችለዋል፡፡ ከዚህም ባሻገር አባቶቻችን በ፸፪ቱ ቋንቋዎች አልተገቱም፡፡ ‹‹በእሳት አምሳል መንፈስ ቅዱስ ወርዶ ተዋሐዳቸው፤ ከዚያም በኋላ በዓለም ሁሉ ቋንቋ ተናገሩ›› ተብሎ ተነግሯልና፤ ይህም ማለት ዓለም አቀፋዊ ቋንቋዎች ተናገሩ እንጂ በእነዚያ ቋንቋዎች ብቻ አልተገቱም፡፡ (ሐዋ. ፪፥፩-፬)
ሐዋርያት ፸፪ ቋንቋ መቻላቸው ሕዝቡ የ፸፪ቱ ዓይነት ቋንቋ ተናጋሪ ስለነበረ ነው፡፡ ስለዚህም በአደባባይ ወጥተው በሚያናገሩትና በሚገባቸው ቋንቋ ማስተማር ችለዋል፡፡ ቅዱስ ጴጥሮስ ሲያስተምር ፫፼ (ሦስት ሺህ) ሰዎች በአንድ ጊዜ አሳምኖ ያጠምቅ የነበረውም ለዚህ ነው፡፡ ይህም መንፈስ ቅዱስ ከሣቴ በመሆኑ አይገደቤነቱን የሚያስረዳ ነው፤ መንፈስ ቅዱስ አንድ ስለሆነ አይከፋፈልም፡፡ ነገር ግን የእግዚአብሔር ረቂቅ ሰማያዊ ኃይል ስለሆነ ገናናነቱን ይገልጽ ዘንድ አንድ የሆነው መንፈስ ቅዱስ በሐዋርያት ሁሉ ላይ አደረባቸው፡፡
ነቢዩ ኢዩኤል የተናገረው ትንቢት የተፈጸመው ‹‹መንፈሴን በሥጋ ለባሽ ሁሉ ላይ አፈሳለሁ›› ብሎ በተናገረው መሠረት ነበርና ዛሬም ቤተ ክርስቲያናችን ቃሉን ታስተምራለች፤ ዕለቱን ትዘክራለች፡፡ (ኢዩ. ፪፥፳፰)
ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያንም ስለ ወረደው መንፈስ ቅዱስ አምስት መሠረታዊ ትርጓሜ እንዳሉት ያስተምራሉ፡፡ እነርሱም፤
፩ኛ መንፈስ ቅዱስ ናዛዚ ነው፤ ትርጓሜውም አረጋጊ ወይንም የሚያረጋጋ ማለት ነው፡፡ መንፈስ ቅዱስ ያልተረጋጉትን ያረጋጋልና፤ ወንጌል ሲሰበክ የእግዚአብሔር ቃል በመሆኑ ሰዎችን ወይንም ምእመናን የሚያረጋጋ ኃይል ነው፡፡
፪ኛ መንፈስ ቅዱስ መጽንዒ ወይም የሚያጸና ነው፤ በተለያዩ ዘመናት የተነሡ ነቢያት፣ ቅዱሳን አባቶችና ሐዋርያት እንዲሁም ጻድቃን ሰማዕታትም ሰይፉና ስለቱን የታገሡት፣ መከራና ሥቃዩን የቻሉትና መስቀሉን የተሸከሙት አጽናኒው መንፈስ ቅዱስ በውስጣቸው ስላደረባቸው ነው፡፡
ለምሳሌ ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መከራና ሥቃይ ሲቀበልልን ጴጥሮስ ግን የጌታችን ደቀ መዝሙር እንደሆነ ባጋለጡበት ጊዜ እርሱ እንደማያውቀው በመገዘት ሦስት ጊዜ ክዷል፤ የዚህም ምክንያት እርሱ በዚያን ወቅት የመሰቀልን ነገር ወይንም ቅጣት ሲመለከት በመጀመሪያ ፈርቶ ስለነበር አልጸናም፤ ነገር ግን መንፈስ ቅዱስን ከተጎናጸፈ በኋላ የፈራውን መስቀል በሮም ዳግም ሲመለከትና ሊሰቅሉትም ሲይዙት ላለመሰቀል አልፈረም፤ መንፈስ ቅዱስ አድሮበታልና፡፡ ስለዚህም ጌታችን ኢየሱስ እንደተሰቀለው ወደ ላይ ሳይሆን ቊልቊል ዘቅዝቀው እንዲሰቅሉት ነግሯቸው ሰቅለውታል፤ ምክንያቱም ጌታችን ወደ ላይ የተሰቀለው ሰዎችን ለማዳን በመሆኑ ጴጥሮስ ደግሞ እራሱን ማዳን የማይችል ደካማ ፍጡር እንደሆነ ያምን ነበር፡፡ (መጽሐፈ ስንክሳር ዘወርኀ ሐምሌ፣ ፭ ቀን)
፫ኛ መንፈስ ቅዱስ መንጽሒ ወይም የሚያነፃ ነው፤ የሰዎችን ኃጢአት የሚያስወግድ፣ ከእድፋችን የሚያነጻ፣ ሰውነትን ለእግዚአብሔር ማደሪያ የሚያዘጋጅ ነው፡፡
፬ኛ መንፈስ ቅዱስ ከሳቲ ወይም ምሥጢር የሚገልጽ ነው፡፡ በብሉይ ኪዳን ነቢዩ ሙሴና ዕዝራን ስንመለከት እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ በየዘመናቱና በየደረጃው ምሥጢራትን እየገለጸላቸው መጻሕፍትን ጽፈዋል፡፡
ሊቃውንትም መናፍቃንን አውግዘው እየለዩ በመንፈስ ቅዱስ ኃይል ምሥጢር እየተገለጸላቸው ለሚጠይቋቸው ጥያቄ መልስ እየሰጡ ጠላትን አሳፍረው፣ የሃይማኖትን ሥርዓት ደንግገው ለእኛ ለጆቻቸው አስተላልፈዋል፡፡ ይህም በሥጋዊ ፍላጎት ተነሣስተው ያደረጉት ሳይሆን በመንፈስ ቅዱስ ኃይል ያደረጉት መሆኑ ነው፤ በመንፈስ ቅዱስ ምሥጢር ገላጭነት ምሥጢርን ከምሥጢር እያራቀቊ ያላመኑትን እያሳመኑ ሕግና ሥርዓቱን አስቀምጠውልናል፡፡
፭ኛ መንፈስ ቅዱስ መስተፍስሒ ወይም የሚያስደስት ነው፤ ያዘኑ ሰዎችን ከኀዘን ያወጣል፤ ኀዘናቸውንም ወደ ደስታ ይቀይራል፤ ሐዋርያት በተዘጋ ቤት ተቀምጠው ያዝኑ ነበር፤ ጌታችን ወደ ሰማይ ባረገ ሰዓት ግን አጽናንቷቸዋል፡፡ ‹‹እስከ ዓለም ፍጻሜ በዘመኑ ሁሉ ከእናንተ ጋር እኖራለሁ›› እንዲል፤ ምክንያቱም የማይለይ የመንፈስ ቅዱስን ኃይል ሰጥቷቸዋልና ለዘለዓለም ከእነርሱ ጋር ይኖራል፡፡ (ማቴ. ፳፰፥፳)
በአባቶቻችን ሐዋርያት ላይ ያደረ መንፈስ ቅዱስ በሁላችን ላይ አድሮ ትልቅ ሥራን ይሠራልና በመንፈስ ቅዱስ ኃይል ዛሬም ጸንተን፣ የእግዚአብሔርን ትእዛዝ እየተገበርን አምላካችንን የሚያስደስት ሥራ ሠርተን የማያልፈው መንግሥቱን እንድንወርስ የአምላካችን ቅዱስ ፈቃድ ይሁንልን፡፡
ወስብሐት ለእግዚአብሔር