የቀለሙ ልጅ
በመዝሙርና ሥነ ጥበባት ክፍል
ግንቦት ፫ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም
ከጸሐፊው ማስታወሻ…
ቅዱሳን መላእክትና የሰው ልጆች የልዑል እግዚአብሔርን ስም አመስግነው ክብሩን ለመውረስ ተፈጠሩ፡፡ የሥጦታ ሁሉ ባለቤት የሆነው እግዚአብሔር አምላክ በጣዕመ ዜማ ፍጡራን ያመሰግኑት ዘንድ ተወዳጅ ሥጦታን ሰጣቸው፡፡ ጻድቁ ኢዮብ እንዳስተዋለው፤ በፍጡራን ዜማ ሲመሰገን እግዚአብሔር አምላክ ደስ ተሰኝቶ ‹‹ከዋክብት በተፈጠሩ ጊዜ መላእክቴ ሁሉ በታላቅ ድምጽ አመሰገኑኝ›› አለ፡፡ (ኢዮ. ፴፰፥፯)
የአዳም ዘጠነኛ ትውልድ ኢዮቤልም፤ እግዚአብሔር አምላክ በልዩ ልዩ የዜማ መሳሪያ ይመሰገን ዘንድ በገና እና መሰንቆን ለልጆቹ አስተማረ፡፡ መላእክት ከጥንተ ፍጥረታቸው ጀምሮ በየነገዳቸው በሰማያት፤ የሰው ልጆችም በተሰጣቸው ጸጋ በምድር በዜማ እግዚአብሔርን አመሰገኑት፡፡ (‹‹መላእክት›› በዲያቆን አቤል ካሣሁን)
ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በቤተ ልሔም ግርግም ከእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በተወለደ ጊዜ መላእክት እና የሰው ልጆች በዝማሬ ተባበሩ፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ እና ሲላስ በወህኒ ቤት ታስረው ሥቃይ ጸንቶባቸው ሳሉ በመንፈቀ ሌሊት ተነሥተው አምላካቸውን በመዝሙር ባመሰገኑ ጊዜ ሰንሰለቱ ከእግሮቻቸው ላይ ወደቀ፤ ከመከራም ዳኑ፡፡ (ሐዋ. ፲፮፥፳፬- ፴፬)
እግዚአብሔር አምላክ ለእኛ ለልጆቹ ያላደረግልን ነገር ምን አለ? አንድያ ልጁን ቤዛ አድርጎ እስኪሰጥ ድረስ ዓለሙን እንዲሁ ወደደው፡፡ ለዚህ ሁሉ ፍቅር … ለዚህ ሁሉ ውለታ.. ለእግዚአብሔር ምን እንከፍለዋለን? መልሳችን ምንም ነው!… ከአንድ ነገር በቀር… እርሱም የከንፈራችን ፍሬ ‹ምስጋና› ነው፡፡
ይህንን ምስጋና ሀገረ እግዚአብሔር ኢትዮጵያ እጆቿን ወደ እግዚአብሔር ዘርግታ እንደ ምግብ በልታው እንደ ውኃ ጠጥታው ልቧ እንዲረካ፤ የፍጥረት ባለቤት የሥጦታ ጌታ፤ በረቀቀ ዜማ በኢትዮጵያውን ልጆቹ ሊመሰገን ወዶ ማሕሌታዊው ቅዱስ ያሬድን አስነሣ፡፡
መናኙ ሊቁ ቅዱስ ያሬድ ሰማያዊውን ውዳሴ በተሰጠው ጸጋ… የዜማውን ድምፅ በሦስት ዓይነት ግእዝ፣ ዕዝልና አራራይ ብሎ ሰይሞ አርእስተ ዜማውን በሃያ ሁለቱ ሥነ ፍጥረት አሰናድቶ … ድጓ፣ ጾመ ድጓ፣ ምዕራፍ፣ ዝማሬ፣ መዋሥዕት የተሰኙ የዜማ መጻሕፍትን እና የዐሥራ ዐራቱን ቅዳሴያት ዜማቸውን ደርሶ፣ በስምንት የዜማ ምልክቶች የዜማ አጠቃቀሙን ለይቶ፣ የብሉይ እና የሐዲስ መጻሕፍትን በዜማ አመሥጥሮ ለዓለም ሁሉ አበረከተ፡፡
ይህን ልዩ ጣዕም ያለውን ተወዳጅ ዜማ የኢትጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ልጆች ከሞቀ ቤታቸው ወጥተው ረኃብ እና እርዛት፣ በሽታ እና ብቸኝነት ሳይበግራቸው ሙሉ ጊዜአቸውን ሰጥተው ለብዙ ዓመታት በጉባኤ ቤት ከመምህራን እግር ሥር ቁጭ ብለው ተማሩት፡፡ ሊቃውንት አባቶቻችን ሰማያዊውን ዜማ ሳይሰለቹት እና ሳይጠግቡት ዕረፍተ ሞት እስኪገታቸው ድረስ መላ ዘመናቸውን እግዚአብሔርን አመሰገኑበት፤ አመስግነውም ከበሩበት፡፡… ዛሬስ? ይህንን ጥያቄ ዓለማዊ ሕይወት ለሚኖር ለአንድ ሰው አቀረብኩለት፡- እርሱም መለሰልኝ፡-
ዓለማዊው ሰው፡- ዛሬማ በዚህ ሃያ አንደኛው መቶ ክፍለ ዘመን
የትናንቱን ተረት ለልጅ አቆይተን
‹‹አንድ ያሬድ የሚሉት ቅዱስ ሰው ነበረ
ከምድር ተነጥቆ ሰማይ ቤት አደረ
ከሰማይ መላእክት ጥዑም ዜማን ሰምቶ
ደግሞም ከዎፎች ተረድቶ
ከበሮ፣ ጸናጽል፣ መቋሚያ አዘጋጅቶ
ሃሌ ሉያ ብሎ የሰማይን ሥርዓት በምድር ሠራልን
እኛም ተሳካልን በአቋራጭ ከበርን
መላእክት ሁነናል አክናፍ ተሠራልን
ለነገሥታት ጌታ ውዳሴ አቀረብን››
እያልን የተረክነው ውሸት ይበቃናል
የምድር ግራቪቲ እንዴት ይለቀናል?
እንኳን በዚያ ትውልድ ቴክኖሎጂን ሳያውቅ
ከምድር ተነሥቶ ደመናውን አልፎ ሰማይ ሊሰነጥቅ
ዛሬም በእኛ ትውልድ ጨረቃን ለመሰንጠቅ
…የግድ ያስፈልጋል መንኮራኩር ማምጠቅ
ደግሞስ!… ከመቼ ጀምሮ ወፎች ተናገሩ
የመላእክትን መድረስን ጀመሩ!
እነዚህ ተረቶች ከሐዲሱ ኪዳን ወንጌል ጋር ተጣብቀው
ዘመን ተሻገሩ እውነተኞች መስለው
ለእያንዳንዱ ድርጊት… መረጃ ያስፈልጋል!
ከተረት አባቶች ማን ያብራራልኛል?
- አንድ የአብነት ተማሪም ይህን ሰምቶ፡- አባቴ ሲጠራ ሲነሣ ሰማሁኝ
የአብራኩ ክፋይ የቀለሙ ልጅ ነኝ
አባቴን አታንሳው እኔ እበቃለሁኝ
አባትህ ተረት ነው ብለህ ለጠየከኝ
ስማኝ ወዳጄ ሆይ!…
አባቴ እውነት ነው በእምነት የከበረ
እምነቱን በሥራ ገልጦ ያስተማረ
ተመልከት ድጓውን!… አባቴን አየኸው?
አንብበው… ተርጉመው… አልሞተም ሕያው ነው
ጨበጥከው?… ዳሰስከው?… ተረት ነው?….
መቼ ተረዳኸው!…
አንብበህ ተርጉመህ ካላመሠጠርከው፡፡
ለካስ ጎዶሎ ነህ ዕውቀትህ ጥቂት ነው
እንዴት ይገባሃል ካላስተረጎምከው
ብትረዳው ኑሮ እውነቱ ቢገባህ
ብራና የፋቁ፣ ብዕር የቀረጹ እጆቹን ታያለህ
ሊቁ ቅዱስ ያሬድ… ከንቱ ከሆነችው ዓለም ተለይቶ
‹‹መብል ለሆድ፣ ሆድም ለመብል›› መሆኑን ተረድቶ
በቅዱስ ጳውሎስን አብነት በርትቶ
ለወገቡ ጠፍር ታጠቀ ቀበቶ
አባቱ ጳውሎስ ከሦስተኛ ሰማይ እንደተነጠቀ
ቃልም እንደሰማ ከሰው የረቀቀ
የኔ አባት ያሬድም ከሦስተኛ ሰማይ በመንፈስ ተነጥቆ
የረቀቀውን ቃል ከመላእክት ሰምቶ
ከወፎች ተማረ ተረዳ ጠንቅቆ፡፡
በወፎቹ ዜማ እጅግ ተገርመሃል
ግን ወፎች ዝም ቢሉ የቢታንያ ድንጋይ… …ለአምላክ ይዘምራል፡፡
ደግሞም ካስፈለገ ሰይፍ የመዘዘውን የተቆጣ መልአክ…
…አሕያው እያየ በለዓም ካላየው
የእግዚአብሔርን ክብር የሰው ቃል አውጥቶ ይገልጣል አህያው፡፡
አስተዋልክ ወዳጄ የአህያውን ያክል መረዳት ካቃተህ
እንኳን የያሬድን ሰማያዊ ዜማ ልትረዳ ሰምተህ
በምድር ያለውን የእግዚአብሔርን ጥበብ…
…በሥነ ፍጥረቱ አትረዳም አይተህ፡፡
- ዓለማዊው ሰው፡- ዓይኖቼ እንደናቁህ… ንቄም እንደተውኩህ
አይደለም ዕውቀትህ… ግሩም ነው ጽናትህ
ተረት ተረት… ያልኩት እውነት ነው አያትህ
ዛሬም እየኖረ ይታያል በአንተ ውስጥ የቀለም አባትህ
ግና! ጥያቄ አለኝ?
ደግሞም የደነቀኝ
ኧኽ…ኧኽ… ይገርማል ኮፊያህ የቆሎ ተማሪው
የለበስከው ካባ የበግ አጎዛ ነው
የልብስህ አደፋ አፈር ነው የሚመስለው
ለካስ እንዲህ ክስት!… ጥቁርቁር!… ያልከው
ቆሎ እየቆረጠምክ ጾምህን ያደርከው
የያሬድን ዜማ ድጓ ለማጥናት ነው?
ከሆነ ይገርማል?
የከፈልከው ዋጋ በጣም ያሳዝናል፡፡
- የአብነት ተማሪው፡- ሰው በሰውነቱ እጅግ ያስደንቃል
የእግዚአብሔርን ጥበብ እየመረመረ ዕፁብ ዕፁብ ይላል
ያልታደለው ደግሞ በለበስኩት ካባ ሲደነቅ ይውላል
ይሁን ተናግርሀል አፈር ነው የምመስለው
ጥንትም የአዳም ሥጋ መገኛው መሬት ነው
ይህን የአፈር ክምር
ለእግዚአብሔር ክብር…
…በፊቱ ብትጥለው
ፊቱ አይዳሰስም ረቂቅ እሳት ነው
አፈሩን ይጠቁራል እሳቱ ሲበላው
የጠቆረው አፈር በእሳቱ ሲነጥር የጠራ ወርቅ ነው፡፡
ተመልከት ወዳጄ!…
መዝሙረኛው ዳዊት ንሴብሖ እያለ
በእግዚአብሔር ፊት ንግሥናውን ጣለ
በሰገነቱ ላይ ከፍ ብላ ቁማ ሜልኮል ተሳለቀች
ተሳልቃም አልቀረች ማሕፀኗን ዘጋች
ንጉሡ ዳዊት ግን ዝቅ ብሎ ወርዶ
ለእግዚአብሔር ክብር ራሱን አዋርዶ
የእግዚአብሔር ልጁ… የዳዊት ልጅ ሆነ፡፡
የዳዊት ልጅ ኃያል… የዳዊት ልጅ ንጉሥ
በመስቀል ላይ ዋለ ሰውን ለመቀደስ
ስለ ቸርነቱ… ስለ ፍጹም ፍቅሩ
ቅዱሳን አባቶች!…
ከዓለም ተለይተው በመስቀል ከበሩ
ፍቅር መከራ ነው መስቀል ያሸክማል
መከራ ድልድይ ነው ነፃነት ያወጣል
ነፃነት ወንጌል ናት
ወንጌልም ድኅነት ናት
አባቶች በጽናት የተጋደሉባት
የለበስኳት ካባ… ከአባቴ ያገኘኋት… ገጸ በረከት ናት
ጀግኖች አባቶቼ እየተመገቡ የመላእክትን መና
በዱር በበረሃ በዋሻ ወደቁ
የሜልኮል ልጆች ግን… ግብራቸው ነውና…
…በያሬድ ምስጋና ዛሬም ተሳለቁ፡፡
- ዓለማዊ ሰው፡- አልሰማህም እንዴ?
ሰማያዊ ዜማ ከተማ መነነ
አዝማሪው ዘፋኙ የድጓውን ዜማ እያቀነቀነ
የሙዚቃው ኖታ ምንጩ ያሬድ ሆነ
ክፉ ዛፍ አብቦ ካፈራው ፍሬዎች
አንዷ ሙዚቃ ናት ለዓለም የተመቸች
አይገርምም ተማሪው!
ይህች የኃጢአት ፍሬ ከያሬድ ተገኘች
ደግሞ በሌላ መልክ የአምላክ ምስጋና ነች፡፡
- የአብነት ተማሪው፡- ዳንኪራን ቀድሰው ዘፋኝን ሊያከብሩ
ከወይን ፍሬ እሾህ መልቀም ጀመሩ
ሙዚቃ ዕዝል ነው… ግእዝ ነው! እያሉ
ጽድቅ እና ኃጢአትን እየቀላቀሉ
የሃይማኖት ድንበር ቅጥር አፈረሱ
ክርስቲያኖች ንቁ!… በሃይማኖት ቁኑ…
…የተቀደሰውን ለውሾች አትስጡ
ዕንቍዎቻችሁን አጥብቃችሁ አጽኑ…
…በእሪያ ፊት ወድቀው… እንዳይረገጡ፡፡
ልብ አድርግ ወዳጄ!…
የፍጥረት ባለቤት በመልኩ በአምሳሉ አዳምን ሲፈጥረው
በሕይወት እንዲኖር እስትፋስን ሰጠው
ስቡሕ… ቅዱስ.. ብሎ እንዲያመሰግነው፡፡
አዳም ተነሣስቶ ቅጠል በልቶ ሙቶ ምስጋና ቢጠፋው
የእግዚአብሔር ልጅ ሙቶ ዳግም ሊያስተምረው
ምስጋናውን መርጦ ከሕፃናቱ አፍ ለራሱ አዘጋጀው
የተማሩ ልጆች ‹‹ሆሣዕና ለዳዊት ልጅ›› በአርያም እያሉ ዘንባባ ቆረጡ
ያልተማሩት!… ጸሐፍት ካህናት… በልጆች ተቆጡ
ብፁዕ ቅዱስ ያሬድ… ምስጋና የባሕርዩ ከሆነ…
…ልዑል ኃያል ጌታ…ምስጋናን ተማረ
…ሃሌ ሉያ ብሎ አርያም ዘመረ
የአርያም ዝማሬ በምድር ተዘራ
ሠላሳ እና ስልሳ መቶ ፍሬ አፈራ
- በዚያች በፍርድ ቀን በመከር ሊለዩ
እሾህ አሜከላው ስንዴውን ላይመስሉ
የያሬድን ዜማ እየቆነጸሉ
እንደ!… ጸሐፍት… ካህናት… እውነትን ሊገሉ
የያሬድን ዜማ ሙዚቃ ነው አሉ!
አትድከም ወዳጄ!…
የቄሣር… ለቄሣር የእግዚአብሔር… ለእግዚአብሔር የተለዩ ናቸው
መረዳት ከፈለክ ጠለቅ ብለህ ገብተህ መርምረህ እያቸው
- ዓለማዊ ሰው፡- በእውነት ተማሪው!…
እምነት ማንነትህ በእጅግ ያስደንቃል
አንተ ያወከውን መርምሮ ለማወቅ ልቡናየ ጓጉቷል
ባዶነቴ ጎልቶ… ጥፋት ተሰምቶኛል
በተሰጠህ ጸጋ መንፈሴ ተማርኳል
ምራኝ ወደ ድጓው ከአባቶችህ ሀገር
የመላክት ዜማ ከሚቀጸልበት ሰማያዊ መንደር
አልብሰኝ ካባህን የአባቶችህ መንፈስ በእኔ ላይ እንዲያድር
የቄሣርን ትቼ እንድሆን የእግዚአብሔር፡፡
- የአብነት ተማሪው፡- ልበሰው ካባየን ከእምነት አትራቆት
ገና ታገኛለህ ለእግሮችህ ጫማ ለጣትህ ቀለበት
ፍሪዳውም ታርዶ ሕይወት ይሰጥሃል ተርበህ እንዳትሞት
የጠፋው ሲመለስ ደጅ ደጁን እያየ ይጠብቃል አባት
እንሂድ እንፍጠን ገብተን እንድናድር ዛሬ ከአባትህ ቤት፡፡
ቸር እንሰንብት!