ከዕለተ ትንሣኤ እስከ ዳግም ትንሣኤ
ሊቀ ትጉሃን ኃይለ ጊዮርጊስ ዳኘ
ከዕለተ ትንሣኤ እስከ ዳግም ትንሣኤ ባሉት ዕለታት በቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን የሚፈጸመው መንፈሳዊና ሐዋርያዊ አገልግሎት ልክ እንደ መጀመሪያው የትንሣኤ ሥርዓት ኾኖ ይከናወናል፡፡ ከትንሣኤ እሑድ ጀምሮ እስከ ሳምንቱ እሑድ ድረስ የሚገኙት ዕለታትም ‹ሰሙነ ፋሲካ› ወይም ‹ትንሣኤ› እየተባሉ ይጠራሉ፤ የየራሳቸው ምሥጢራዊ ስያሜም አላቸው፡፡ ስያሜአቸውንም በአጭሩ እንደሚከተለው እንመለከታለን፤
ሰኞ
የትንሣኤው ማግሥት ዕለተ ሰኞ ‹ፀአተ ሲኦል› ወይም ‹ማዕዶት› ትባላለች፡፡ ይህቺውም ጌታችን በትንሣኤው ነፍሳትን ከሲኦል አውጥቶ ወደ ገነት አሻግሮ ለማስገባቱ መታሰቢያ ናት (ዮሐ. ፲፱፥፲፰፤ ሮሜ. ፭፥፲-፲፯)፡፡
ማክሰኞ
ይህቺ ዕለት፣ ለሐዋርያው ቶማስ መታሰቢያ ትኾን ዘንድ ‹ቶማስ› ተብላ ትጠራለች፡፡ የትንሣኤው ዕለት እሑድ ማታ ጌታችን በዝግ ቤት ገብቶ ለሐዋርያት ሲገለጽ ቶማስ ከእነርሱ ጋር አልነበረም፡፡ በመጣ ጊዜ ሌሎቹ ሐዋርያት ትንሣኤውን ቢነግሩት ‹‹ሳላይ አላምንም›› ብሎ ነበር፡፡ በሳምንቱ እርሱ በተገኘበት ጌታችን በድጋሜ ለሐዋርያት ተገለጸ፡፡ ስለዚህም ይህቺ ዕለት በሐዋርያው ቶማስ ስም ተሰይማለች (ዮሐ. ፳፥፳፬-፴)፡፡
ረቡዕ
ጌታችን ከሞተና ከተቀበረ ከአራት ቀናት በኋላ ከመቃብር ጠርቶ ላስነሣው ለአልዓዛር መታሰቢያ ናት፡፡ በክርስቶስ ሥልጣን የአልዓዛርን ከሞት መነሣት አይተው ብዙ ሕዝብ በጌታችን ስለ አመኑ ዕለቲቱ (ረቡዕ) ‹አልዓዛር› ተብላ ትታሰባለች (ዮሐ. ፲፩፥፴፰-፵፮)፡፡
ኀሙስ
ይህቺ ዕለት ‹‹ከአምስት ቀን ተኩል በኋላ (አምስት ሺሕ ከአምስት መቶ ዓመት ሲፈጸም) ከልጅ ልጅህ ተወልጄ አድንሃለሁ፤›› ተብሎ ቃል የተገባለት የአዳም ተስፋው ተፈጽሞ ከነልጅ ልጆቹ ወደ ቀደመ ክብሩ ለመግባቱ መታሰቢያ ኾና ‹የአዳም ኀሙስ› ወይም ‹አዳም› ተብላ ትከበራለች (ሉቃ. ፳፬፥፳፭-፵፱)፡፡
ዐርብ
የትንሣኤ እሑድ ስድስተኛዋ ዐርብ ደግሞ በክርስቶስ ደም ለተመሠረተችው ቅድስት ቤተ ክርስቲያን መታሰቢያ ትኾን ዘንድ ‹ቤተ ክርስቲያን› ተብላ ትጠራለች (ማቴ. ፳፮፥፳፮-፳፱፤ ሐዋ. ፳፥፳፰)፡፡
ቀዳሚት ሰንበት
በሰሙነ ፋሲካው ያለችው ቀዳሚት ሕዝቡ ከአንዳንዱ በቀር ገበያ እንኳን ስለማይገበያይባት ‹የቁራ ገበያ፣ የገበያ ጥፊያ› ተብላ ትጠራለች፡፡ በቤተ ክርስቲያን ደግሞ ጌታችን በዘመነ ሥጋዌው በገንዘባቸውና ጕልበታቸው ላገለገሉት፤ በስቅለቱ ጊዜ እስከ ቀራንዮ ድረስ ለተከተሉት፤ በትንሣኤው ዕለት በሌሊት ወደ መቃብሩ ሽቱና አበባ ይዘው ለገሰገሱት፤ በትንሣኤውም ጌታችንን ከዅሉ ቀድሞ ለማየት ለበቁት ሴቶች መታሰቢያ ትኾን ዘንድ ‹ቅዱሳት አንስት› ተብላ ትጠራለች (ማቴ. ፳፭፥፩-፲፩፤ ሉቃ. ፳፫፥፳፯-፴፫፤ ፳፬፥፩-፲)፡፡
እሑድ ሰንበት
በዋናው ትንሣኤ ሳምንት የምትመጣዋ ዕለተ እሑድ ‹ዳግም ትንሣኤ› ተብላ ትዘከራለች፡፡ ከላይ እንደ ተጠቀሰው ጌታችን በትንሣኤው ዕለት ማታ በዝግ በር ገብቶ፣ በቅዱሳን ሐዋርያት መካከል ተገኝቶ ‹‹ሰላም ለዅላችሁ ይኹን!›› በማለት ትንሣኤውን ሲገልጽላቸው ሐዋርያው ቶማስ አልተገኘም ነበር፡፡ በኋላ ከሔደበት ሲመጣ ጌታችን እንደ ተነሣ እና እንደ ተገለጸላቸው ሐዋርያት በደስታ ሲነግሩት ‹‹በኋላ እናንተ ‹አየን› ብላችሁ ልትመሰክሩ፤ ልታስተምሩ፤ እኔ ግን ‹ሰምቼአለሁ› ብዬ ልመሰክር፤ ላስተምር? አይኾንም፤እኔም ካላየሁ አላምንም›› አለ፡፡
ስለዚህም የሰውን ዅሉ፤ ይልቁንም የመረጣቸው የወዳጆቹን የልብ ዐሳብ የሚያውቀው፣ ቸርነቱ ወሰን የሌለው የባሕርይ አምላክ መድኃኔ ዓለም ክርስቶስ ልክ እንደ መጀመሪያው ትንሣኤ ዕለት አበው ሐዋርያት በተዘጋ ቤት በአንድነት ተሰባስበው እንዳሉ በሩን ሳይከፍት ገብቶ ‹‹ሰላም ለዅላችሁ ይኹን!›› በማለት በመካከላቸው ቆመ፡፡ ቶማስንም ‹‹ያመንህ እንጂ ተጠራጣሪ አትኹን፤ እነሆ የተቸነከሩ እጆቼንና እግሮቼን፣ የተወጋ ጐኔንም ናና እይ፤›› ብሎ አሳየው፡፡
እርሱም ምልክቱን በማየቱ፣ በመዳሰሱ ትንሣኤውንና አምላክነቱን እንደ ፍላጎቱ በመረዳቱ ‹‹ጌታዬ፣ አምላኬ ብሎ መስክሮ›› የክርስቶስን ትንሣኤ አመነ፡፡ የሳምንቷ ዕለተ ሰንበት፣ የትንሣኤው ምሥጢር ለሁለተኛ ጊዜ ለሐዋርያት የተገለጠበት ዕለት በመኾኑ የትንሣኤው ሳምንት እሑድ ‹ዳግም ትንሣኤ› ተብሎ ይጠራል፤ ይከበራል (ዮሐ. ፳፥፳፬-፴)፡፡
ብርሃነ ትንሣኤውን የገለጸልን አምላካችን ለብርሃነ ዕርገቱም በሰላም ያድርሰን!
ወስብሐት ለእግዚአብሔር