ክፉን በጋራ እናርቅ
መጋቤ ምሥጢር ስንታየሁ አባተ
ኢትዮጵያ ሥነ ፈለክንና ሥነ ከዋክብትን፤ በአንድ አምላክ የማምለክን ፅንሰ ሐሳብ ያበረከተች ሀገር ናት:: በእነዚህ ሁሉ ዘመናት እጅግ ሰፊና ጥልቅ የእምነት የባህል የፍልስፍና አስተምህሮዎችን ከትውልድ ወደ ትውልድ ስታስተላልፍ ቆይታለች:: ይህ ማለት ደግሞ ዜጎቿ ከጥንት ጀምሮ የራሳቸው የሆነ ጠንካራ የሥነ ጾታ የትዳር የቤተሰብ አስተምህሮ አላቸው:: አንድ ወንድ በአንዲት ሴት፤ አንዲት ሴት በአንድ ወንድ ጸንተው የሚኖሬባት ሀገር ናት፡፡ ተፈጥሯቸው ከሰው እጅግ ባነሱና አእምሮ በሌላቸው በእንስሳት ዘንድ እንኳን የማይታሰብ የተመሳሳይ ጾታ ርኩስነትን የሚጸየፉ መሆናቸውም የዜጎቻችን የማይለወጥ እምነት ነው:: ይህን እምነት በሕዝቡ ልቡና በማሥረፅ ደግሞ ግንባር ቀደም መሪዎቹ የሃይማኖት መሪዎች ናቸው:: እነዚህ መሪዎች የሚያስተምሩባቸው የተቀደሱና የእግዚአብሔር በረከት መቀበያ መካናት ገዳማት አድባራት አሏቸው:: እነዚህን ሕዝቡ ከራሱ በላይ የሚሳሳላቸውን፤ ከአምላክ በረከት የሚያገኙባቸውን፤ በጫማው እንኳን የማይረግጣቸውን፤ አቧራውን በእምነት ዘግኖ በመቀባትና በውኃ በጥብጦ በመጠጣት ፈውስ የሚያገኝባቸውን የተቀደሱ ቦታዎች ከመጥፎና ከረከሰ ሥራቸው የተነሣ የሚጸየፋቸው «ሰዎች» በጉብኝት ስም የከበረውን ሲያረክሱበት ማየት የሚችል ተፈጥሯዊ ሰብእና ሊኖረው አይችልም::
በእግዚአብሔር አርአያና ምሳሌ ከተፈጠሩ በኋላ እግዚአብሔር በማይከበርበት፤ ከክፉ ምኞታቸው የተነሣ ለርኩስ መንፈስ የተሰጡትን ግብረ ሰዶማውያንን ቀርቶ ሌላውን መፍራት አባቶቻችን አላስተማሩንም:: እኛ የፈራነው ግርማ አልባ አካላቸውን ሳይሆን ከእግዚአብሔር መንፈስ በተራቆተ ሕይወታቸው የሌላ በሆነ መንፈሳቸው ተመልተዋልና ምድራችንን እንዳያጎሰቁሉ ነው:: ከዚህም በተጨማሪ «የራሳችንን አስተሳሰብ በማንም ላይ ለመጫን አይደለም» የሚለው የቶቶ የግብረ ሰዶማውያን አስጎብኚ ድርጅት ባለቤት የዳን ዌር አባባል አሳማኝ አይደለም:: «የየትኛውም ሃይማኖት ተከታይ የሆነ ሰው የሚያስፈራው ነገር ያለ አይመስለኝም:: የማንንም ሃይማኖት ልንጋፋም ሆነ የራሳችንን አስተሳሰብ በሰዎች ላይ ለመጫን አይደለም ወደ ኢትዮጵያ የምንሄደው:: እንዲያውም ባህሉን ለማየትና ለመረዳት እንዲሁም ለማድነቅ ነው የምንፈልገው» የሚል መግለጫ ሰጥተዋል::
ነገር ግን ተቃራኒ አስተሳሰብን ወደ ሌላው ለማሥረፅ እኮ የግድ ማስተማር፤ መወያየት ወይም መከራከር አያስፈልግም::ማንኛውም ትምህርትና ልምድ የሚቀሰመው በማትና በመስማት ነው:: ስለሆነም ይህንን መጥፎ ተግባር ይዘው ወደ ሀገራችን እንዳይመጡ በእግዚአብሔር ስም እናሳስባለን::
ዳን ዌር በንግግራቸው «ባህሉን ለማየትና ለማድነቅ» ወደ ኢትዮጵያ ለመሄድ መወሰናቸውን ገልጸዋል:: የኢትዮጵያ ባህል የኢትዮጵያውያን የእምነት ተቋማት አስተምህሮ ውጤቶች ናቸው:: ባህሎቻችን የተቀረፁትና መልክ የያዙት በሃይማኖታዊ አስተምህሮዎቻችን ነው:: በዚያ ላይ እንጎበኛቸዋለን ብለው ያቀዷቸው ቦታዎች የእምነት ማእከላት እንጂ የባህል መገለጫዎች አይደሉም:: ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል፤ ቅዱስ ላሊበላ ገዳም፤ አክሱም ጽዮን ማርያም፤ ጎንደር ዐርባ አራቱ ታቦታት ወይስ የጣና ሐይቅ ገዳማት፤ የትኞቹ ናቸው የባህል መዳረሻዎች?
ኢትዮጵያ መመኪያዋ ጉልበቷና ተስፋዋ እግዚአብሔር ብቻ መሆኑን፤ ሀገራችን ያለፉትን እጅግ መራራና ዘግናኝ ጦርነቶችን የምዕራባውያንን ጣልቃ ገብነት ተቋቁማ ያሳለፈችው እግዚአብሔር ክንድ፤ ተስፋና መመኪያ ሆኗት እንጂ በምዕራባውያኑ ርዳታ አይደለም:: መሪዎቻችን በሁሉ ታናሽ ስትሆኑ በታላቋ ኢትዮጵያ ላይ በክቡር ዜጎቿም ላይ መሪ አድርጎ ያስቀመጣችሁን እግዚአብሔርን አስቡት:: የሃይማኖት አባቶችም በዚህ ጉዳይ ግንባር ቀደም መሪ ሆናችሁ እነዚህ ግለሰቦች ወደ ሀገራችን እንዳይገቡ ማሳሰብ አለባችሁ::
ኢትዮጵያውያን በታሪካችን ሌላውን ወረን አናውቅም:: በትዕቢት ሀገራችንን፤ እምነታችንን፤ ባህላችንንና ትውልዳችንን ሊወር የመጣውን ደግሞ እጅ ነሥተን መመለስ እንችልበታለን:: በመሆኑም ጊዜው ደርሶ አላስፈላጊ ነገር ውስጥ ሁላችንም ከመግባታችን በፊት ከቀበሌ ጀምሮ እስከ ማእከላዊው መንግሥት በሥልጣን ላይ ያላችሁ ኃላፊዎች በየእምነታችን ከአጥቢያ ጀምሮ እስከ ሲኖዶስ ያለን የእምነት አባቶች ክፉውን በጋራ ለማራቅ እንመካከር:: በየአድባራቱና በየገዳማቱ ያለን ሁላችንም ኢትዮጵያ ተስፋዋና ኃይሏ እግዚአብሔር ስለሆነ ራሳችንን በንስሓ አንጽተን እንጸልይ::