እግዚአብሔር በደብረ ታቦር
በዲያቆን ኤፍሬም የኔሰው
ነሐሴ ፲፬ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም
‹እግዚአብሔር› የሚለው ቃል ሦስቱም አካላት (አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስ) በጋራ የሚጠሩበት መለኮታዊ ስያሜ ነው፡፡ ‹‹አንሰ ሶበ እቤ እግዚአብሔር እብል በእንተ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ ከመ በአሐዱ ስም ሥሉሰ ያምልኩ፤ እኔ ‹እግዚአብሔር› በአልኹ ጊዜ ስለ አብም፣ ስለ ወልድም፣ ስለ መንፈስ ቅዱስም እናገራለሁ፡፡ (ምእመናን) በአንዱ ስም (በእግዚአብሔር) ሦስቱ አካላትን ያመልኩ ዘንድ›› እንዳለ ቅዱስ ጎርጎርዮስ ነባቤ መለኮት (ሃይማኖተ አበው)፡፡
ቅዱሳት መጻሕፍት እንደሚነግሩን እግዚአብሔር አምላካችን በብሉይም ኾነ በሐዲስ ኪዳን በአንድነቱም በሦስትነቱም በግብር (በሥራ)፣ በራእይ፣ በገቢረ ተአምራትና በልዩ ልዩ መንገድ ለፍጡራኑ ተገልጧል፡፡ በብሉይ ኪዳን በቅዱሳን ነቢያትና በመሳፍንት፣ በነገሥታት፣ በካህናትና በነቢያት ላይ በማደር፤ በጻድቃኑ ላይ ቸርነቱን፣ በክፉ አድራጊዎች ላይ ደግሞ መቅሠፍቱን በመላክ በልዩ ልዩ ምልክትና በተአምራት ይገለጥ ነበር፡፡ በሐዲስ ኪዳን ደግሞ ለአዳምና ለልጆቹ በገባው ቃል መሠረት የሰውን ሥጋ ለብሶ፣ በአጭር ቁመት በጠባብ ደረት ተወስኖ በአካለ ሥጋ ተገልጦ በገቢረ ተአምራቱ፣ በትንሣኤውና በዕርገቱ አምላክነቱን አሳይቷል፡፡ የብሉይ ኪዳኑ መገለጥ በምልክት፣ በራእይ፣ በድምፅና በመሳሰሉት መንገዶች የተደረገ መገለጥ ነበር፤ የሐዲስ ኪዳኑ ግን አምላካችንን በዓይነ ሥጋ ያየንበት መገለጥ ስለ ኾነ ከዅሉም የተለየ ጥልቅ ምሥጢር አለው፡፡ ‹‹መቼም ቢኾን እግዚአብሔርን ያየው አንድ ስንኳ የለም፤ በአባቱ እቅፍ ያለ አንድ ልጁ እርሱ ተረከው›› (ዮሐ. ፩፥፲፰) በማለት ወንጌላዊው ዮሐንስ እንደ ገለጸው፡፡
እግዚአብሔር በሐዲስ ኪዳን ያደረዉን መገለጥ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን ከምሥጢረ ሥላሴ ጋር በሚያያዙ ሦስት ዐበይት መንገዶች ይገልጹታል፡፡ ይኸውም በእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም፣ በዮርዳኖስና በደብረ ታቦር ላይ እንደ ኾነ ያስረዳሉ፡፡ ‹‹በላዕሌኪ ወበዮርዳኖስ ወበታቦር ሥልሰ ጊዜያተ ዘአልቦ ተውሳከ ወአልቦ ሕጸተ ለውሉደ ሰብእ ያርኢ ዘሥላሴሁ ገጻተ ጽጌኪ ድንግል ተአምሪሁ ከሠተ ወበፀዳሉ አብርሀ ጽልመተ›› እንዳለ ደራሲ (ማኅሌተ ጽጌ)፡፡ ትርጕሙም እግዚአብሔር አምላክ ጭማሬም ጉድለትም የሌለበት ሦስትነቱን ለሰው ልጅ ያሳይ ዘንድ በእመቤታችን፣ በዮርዳኖስ እና በታቦር ሦስት ጊዜ ተአምራቱንና ምሥጢረ መለኮቱን መግለጡን፤ በብርሃነ መለኮቱም ጨለማውን ዓለም ብርሃን ማድረጉን ያስረዳል፡፡ ይህም ጌታችን በእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ማኅፀን ተወስኖ ሲወለድ፤ እንደዚሁም በዮርዳኖስ ወንዝ በተጠመቀበት ዕለት እግዚአብሔር አብ ‹‹የምወደው ልጄ እርሱ ነው፤ እርሱን ስሙት›› ብሎ ሲመሰክር፣ መንፈስ ቅዱስም በርግብ አምሳል ወርዶ በራሱ ላይ ሲያርፍ፤ በተመሳሳይ መልኩ በደብረ ታቦር ብርሃነ መለኮቱን ሲገልጥ መለኮታዊ አንድነቱና አካላዊ ሦስትነቱ መታወቁን ያመለክታል፡፡ በዛሬው ዝግጅታችን የምናቀርበው ትምህርትም እግዚአብሔር በደብረ ታቦር የመገለጡን ምሥጢር የተመለከተ ነው፡፡ መልካም ንባብ!
በቅዱስ ወንጌል እንደ ተጻፈው ጌታችን አምላካችንና መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ተስእሎተ ቂሣርያ በዋለ በስድስተኛው ቀን ማለትም ሐዋርያት ሰዎች ክርስቶስን ማን እንደሚሉት በተናገሩ፤ ቅዱስ ጴጥሮስም ክርስቶስ የባሕርይ አምላክ መኾኑን በመሰከረ በሳምንቱ (ነሐሴ ፲፫) ምሥጢረ መለኮቱን ይገልጥላቸው ዘንድ ጌታችን ሦስቱን ደቀ መዛሙርት መርጦ ወደ ረጅም ተራራ ይዟቸው ወጥቷል (ማቴ. ፲፯፥፩)፡፡ ይህ ተራራ ታቦር መኾኑንም ሐዋርያት በሲኖዶሳቸው ጠቅሰውታል፡፡ ሊቀ ነቢያት ሙሴ ከመቃብር ወጥቶ፤ ነቢዩ ኤልያስም ከብሔረ ሕያዋን መጥቶ በተገኙበት ጌታችን በተወለደ በ፴፪ ዓመት ከ፯ ወር ከ፲፭ ቀኑ፣ በዘመነ ማቴዎስ፣ ነሐሴ ፲፫ ቀን በዕለተ እሑድ በዚህ ተራራ ምሥጢረ መለኮቱን ገልጧል፡፡ (መጽሐፈ ታሪክ ወግስ፣ በመ/ር አፈወርቅ ተክሌ፣ አዲስ አበባ፣ ፳፻፭ ዓ.ም፤ ገጽ ፫፻፲፬–፫፻፲፯ እና ፬፻፩)፡፡
የጌታችን ብርሃነ መለኮቱ ሲገለጥም ፊቱ እንደ ፀሐይ አበራ፤ ልብሱም ነጭ ኾነ፡፡ ቅዱስ ጴጥሮስ ‹‹በዚህ መኖር ለእኛ መልካም ነው፡፡ አንዱን ለአንተ፣ አንዱን፣ ለሙሴ አንዱን ለኤልያስ ሦስት ዳስ እንሥራ›› እያለ ተማጸነ፡፡ እንዲህ ማለቱም ጌታችን በተአምራቱ ሲራቡ እያበላቸው፣ ሲጠሙ እያጠጣቸው፣ ሲታመሙ እየፈወሳቸው፣ ቢሞቱ እያነሣቸው፤ ሙሴም እንደ ቀድሞው ደመና እየጋረደ፣ መና እያወረደ፣ ባሕር እየከፈለ፣ ጠላትን እየገደለ፤ ኤልያስ ደግሞ ሰማይን እየለጎመ፣ እሳት እያዘነመ፣ ዝናም እያቆመ አብረው በደብረ ታቦር እንዲኖሩ የነበረዉን መሻት ያመላክታል፡፡ የራሱን የሐዋርያትን ሳያነሣ የነቢያትን ስም መጥቀሱም በአንድ በኩል ትሕትናውንና ጌታችን አብሮ ያኖረኛል ብሎ ተስፋ ማድረጉን፤ በሌላ በኩል ደግሞ የክርስቶስን አምላክነት በሚገባ አለመረዳቱን ያመላክታል፡፡ ጌታችንን በተራራ ላይ በሰው ሠራሽ ቤት ይኖር ዘንድ ጠይቆታልና (ትርጓሜ ወንጌለ ማቴዎስ)፡፡
አምላከ ሰማይ ወምድር ክርስቶስ በሰው እጅ በተሠራ ቤት እንደማይኖር ይታወቅ ዘንድም ሰማያዊ ብሩህ ደመና ጋረደቻቸው፡፡ ‹‹በእርሱ ደስ የሚለኝ የምወደው ልጄ ይህ ነው፤ እርሱን ስሙት›› የሚል ቃል ከእግዚአብሔር አብ ዘንድ መጣ፡፡ ‹‹እርሱን ስሙት›› ማለቱም ጌታችን ዓለምን ለማዳን እንደሚሞት ሲናገር ቅዱስ ጴጥሮ ‹‹አይኹንብህ›› ብሎት ነበርና ‹‹እሞታለሁ›› ቢላችሁ ‹‹አትሞትም›› አትበሉት ሲል ነው፡፡ ሙሴና ኤልያስም ከጌታችን ጋር ሲነጋገሩ ተሰሙ፤ ስለ ክርስቶስ የተናገሩት ትንቢትም በደብረ ታቦር ተረጋገጠ፡፡ የፊቱን ግርማ ለማየትና የመለኮትን ድምፅ ለመስማት አልተቻላቸውምና ሙሴ ወደ መቃብሩ፣ ኤልያስም ወደ መጣበት ተመለሱ፡፡ ቅዱሳን ሐዋርያትም የመለኮትን ፊት አይተው መቆም አልተቻላቸውምና ደንግጠው ወደቁ፡፡ ጌታችንም አጽናንቶ ኃይሉን ብርታቱን ካሳደረባቸው በኋላም እርሱ ከንቱ ውዳሴን የማይሻ አምላክ ነውና ዅሉም በጊዜው እስኪለጥ ድረስ ማለትም ቅዱሳን ሐዋርያት መንፈስ ቅዱስን ተቀብለው የክርስቶስ አምላክነቱን፣ ሞቱን፣ ትንሣኤውን፣ ዕርገቱንና ዳግም ምጽአቱን ለዓለም እስኪሰብኩ ድረስ ያዩትም ምሥጢር ለማንም እንዳይነግሩ አዝዟቸዋል (ማቴ. ፲፯፥፩-፱፤ ማር.፱፥፪-፱)፡፡
በብሉይ ኪዳን ሊቀ ነቢያት ሙሴ ከእግዚአብሔር ጋር ሲነጋገር ቆይቶ ወደ ሕዝቡ ሲሔድ ፊቱ ያንጸባርቅ እንደ ነበርና የእስራኤላውያን ዓይን እንዳይጎዳ ሙሴ ፊቱን ይሸፍን እንደ ነበር ተጽፏል (ዘፀ. ፴፬፥፴፭)፡፡ ሙሴ የእግዚአብሔርን ድምፅ በመስማቱ ብቻ ፊቱ ያንጸባርቅ ከነበረ እግዚአብሔርን ፊት ለፊት በዓይን ተመልክቶ ብርሃኑን መቋቋምማ ምን ያህል ከባድ ይኾን?
እግዚአብሔር አምላክ በደብረ ታቦር ያደረገው መገለጥ በዘመነ ኦሪት ለሙሴ የሰጠውን ተስፋ ያስታውሰናል፡፡ ነቢዩ ሙሴ በዘመኑ ‹‹… አምላክነትህን (ባሕርይህን) ግለጽልኝ›› ሲል እግዚአብሔርን ተማጽኖት ነበር፡፡ እግዚአብሔርም ‹‹በባሕርዬ ፊቴን አይቶ የሚድን የለምና ፊቴን ማየት አይቻልህም … እኔ በምገለጽልህ ቦታ ዋሻ አለና በብርሃን ሠረገላ ኾኜ እስካልፍ ድረስ በዋሻው ውስጥ ቁመህ ታየኛለህ፡፡ በባሕርዬ አይተህ ደንግጠህ እንዳትሞት በብርሃን ሠረገላ ኾኜ እስካልፍ ድረስ ቀዳዳ ባለው ዋሻ እሠውርሃለሁ፡፡ በብርሃን ሠረገላ ኾኜ ካለፍኹ በኋላ እጄን አንሥቼልህ ከወደ ኋላዬ ታየኛለህ እንጂ በባሕርዬ ግን ፊቴን ማየት አይቻልህም›› በማለት ለሙሴ ምላሽ ሰጥቶት ነበር፡፡ ይህም በፊት በፊት የሚጓዝ ሰው ኋላው (ጀርባው) እንጂ ፊቱ እንደማይታይ ጌታም በምልክት እንጂ በአምላክነቱ ለፍጡራኑ አለመገለጡን ያስረዳል፡፡ ምሥጢሩም አምስት ሺሕ ከአምስት መቶ ዓመት ሲፈጸም አምላክ ሰው ኾኖ ሥጋ ለብሶ በደብረ ታቦር በባሕርዩ እስኪገለጥለት ድረስ ሙሴ በመቃብር ተወስኖ እንደሚቆይ ያጠይቃል (ትርጓሜ ኦሪት ዘፀአት፣ ፴፫፥፲፫-፳፫)፡፡
እግዚአብሔር ‹‹ጀርባዬን ታያለህ›› ብሎ ለሙሴ በገባው ቃል መሠረት እነሆ በደብረ ታቦር በግርማ መለኮት፣ በክበበ ትስብእት (በለበሰው ሥጋ) ታየ፡፡ ነቢዩ ሙሴ ብርሃነ መለኮቱን በተመለከተ ጊዜም ‹‹ፊቴን ማየት አይቻልህም›› ያለው ቃሉ ይፈጸም ዘንድ የክርስቶስን ፊት ማየት አልተቻለውምና ወደ መቃብሩ ገባ፡፡ ኤልያስም ብርሃነ መለኮቱን አይቶ መቆም ስለ ተሳነው ወደ ብሔረ ሕያዋን ተመለሰ፡፡ የክርስቶስን መሞት በሥጋዊ ስሜት ተረድቶ ‹‹አይኹንብህ›› ያለው ቅዱስ ጴጥሮስ፤ መለኮታዊ ሥልጣንን የተመኙት ቅዱሳን ያዕቆብና ዮሐንስም አብሯቸው እየኖረ የማያውቁት ክርስቶስ የባሕርይ አምላክ መኾኑን በተረዱ ጊዜ ደንግጠው ወደቁ፡፡ እግዚአብሔር በደብረ ታቦር አንድነቱን፣ ሦስትነቱን ገለጠ፤ ከግርማ መለኮቱ የተነሣም ዓለም ተናወጠ፡፡
ጌታችን በዮርዳኖስ ሲጠመቅ የተገለጠው ምሥጢረ ሥላሴና የኢየሱስ ክርስቶስ አምላክነት በደብረ ታቦር በገሃድ ተረጋግጧል፡፡ የቤተ ክርስቲያን ምሳሌ የኾነው ደብረ ታቦር ምሥጢረ ሥላሴ ተገልጦበታል፤ የክርስቶስ አምላክነት ተመስክሮበታል፡፡ በደብረ ታቦር ብርሃነ መለኮቱ እንደ ተገለጠና የእግዚአብሔር አብ ምስክርነት እንደ ተሰማ ዅሉ ዛሬም በቅድስት ቤተ ክርስቲያን ምሥጢረ ሥላሴ ሲነገር፣ የመለኮት ሥጋና ደም ሲታደል ይኖራል፡፡ በደብረ ታቦር ነቢያትም፣ ሐዋርያትም እንደ ተገኙ ዅሉ በቤተ ክርስቲያን ብሉይና ሐዲስ ኪዳን ይሰበካል፡፡ ሥርዓተ ቅዳሴ የሚፈጽሙ ልዑካን አምስት መኾናቸውም በደብረ ታቦር የተገኙትን ሙሴን፣ ኤልያስን፣ ጴጥሮስን፣ ያዕቆብንና ዮሐንስን ያስታውሱናል፡፡ ዘወትር በቤተ መቅደሱ የሚፈተተው ኅብስትና የሚቀዳው ወይን ደግሞ በደብረ ታቦር የተገለጠው የጌታችን አምላካችንና መድኀኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ቅዱስ ሥጋው፣ ክቡር ደሙ ነው፡፡
አንድም ደብረ ታቦር የመንግሥተ ሰማያት ምሳሌ ነው፤ በደብረ ታቦር ነቢያትም ሐዋርያትም እንደ ተገኙ መንግሥተ ሰማያትንም ዅሉም ምእመናን በአንድነት ይወርሱታልና፡፡ ከመዓስባን ሙሴ፣ ከደናግል ኤልያስ መገኘታቸውም ደናግልም መዓስባንም በአንድነት ወደ መንግሥተ ሰማያትን እንደሚገቡ ያጠይቃል፡፡ አንድም ደብረ ታቦር የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ምሳሌ ነው፡፡ እግዚአብሔር አምላክነቱንም ሰዉነቱንም በደብረ ታቦር እንደ ገለጠ ከእመቤታችን ከነፍስና ከሥጋዋ ጋር ተዋሕዶ ሰዉም አምላካም መኾኑን አሳይቷል፡፡ አምላክ ሰው፤ ሰውም አምላክ መኾኑ በድንግል ማርያም ማኅፀን ተገለጧል፡፡ በደብረ ታቦር ነቢያትም ሐዋርያትም እንደ ተገኙ እመቤታችንም የነቢያት ትንቢት ተፈጽሞባታል፤ የሐዋርያት ስብከት ጸንቶባታል፡፡ እርሷ አምላክን ለመሸከም ተመርጣለችና እመቤታችን በደብረ ታቦር ትመሰላለች፡፡ እንደዚሁም ደብረ ታቦር የአብያተ ጉባኤ (የአብነት ትምህርት ቤቶች) ምሳሌ ነው፡፡ በደብረ ታቦር የእግዚአብሔር ሦስትነት፣ አንድነት እንደ ታወቀ፤ ብርሃነ መለኮቱም እንደ ተገለጠ፤ ነቢያትና ሐዋርያትም እንደ ተገኙ ዅሉ በየአብነት ትምህርት ቤቶችም ምሥጢረ ሥላሴ፣ ነገረ መለኮት፣ ክብረ ቅዱሳን፣ ትንቢተ ነቢያትና ቃለ ወንጌል ዘወትር ይነገራል፣ ይሰበካል፤ ይተረጐማል፡፡
በአጠቃላይ ከጌታችን አምላካችንና መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ዐበይት በዓላት መካከል አንደኛው የኾነው በዓለ ደብረ ታቦር እግዚአብሔር ምሥጢረ መለኮቱን የገለጠበት በዓል በመኾኑ በቤተ ክርስቲያናችን በየዓመቱ ነሐሴ ፲፫ ቀን በድምቀት ይከበራል፡፡ የአብነት ት/ቤት ደቀ መዛሙርትና ምእመናንም ብርሃነ መለኮቱን በደብረ ታቦር የገለጠ አምላክ ብርሃነ ምሥጢሩን በየልቡናቸው እንዲገልጥላቸው ለመማጸን ጸበል ጸሪቅ አዘጋጅተው ይዘክሩታል፡፡ ከዘመናት በፊት የተመኘውን የአምላኩን ፊት ከሙታን ተነሥቶ ለማየት የታደለው ሊቀ ነቢያት ሙሴ የተወለደውም በዚህች ዕለት ነው፡፡
እንዲህ እኛም በክርስቲያናዊ ምግባር ጐልምሰን፣ በትሩፋት ሥራ ከፍ ከፍ ብለን ከተገኘን በደብረ ታቦር እንደ ተደረገው ዅሉ በተቀደሰችው የእግዚአብሔር ተራራ በቤተ ክርስቲያን የሚፈጸሙ ምሥጢራትን ለመሳተፍ፣ የክርስቶስ ማደርያ በኾነችው በቅድስት ድንግል ማርያም እና ባለቤቱ ባከበራቸው በሌሎችም ቅዱሳን አማላጅነት ለመጠቀም፣ በየጉባኤ ቤቱ የሚቀርበዉን ጥበብ ለመቅሰም፣ በሚመጣው ዓለምም ሰማያዊ መንግሥቱን ለመውረስ እንበቃለን፡፡ አምላካችን በግርማ መለኮቱ ተገልጦ ለፍርድ በመጣ ጊዜ በቀኙ ያቆመን ዘንድም በክርስትና ሃይማኖት መጽናት፣ ትሕትናን ገንዘብ ማድረግ፣ በጥቅሉ በበጎ ምግባር መበርታት ይጠበቅብናል፡፡ ምሥጢረ መለኮቱን በደብረ ታቦር የገለጠ ጌታ ለእኛም መንፈሳዊውን አእምሮ፣ ማስተዋልና ጥበቡን ይግለጥልን፡፡
ወስብሐት ለእግዚአብሔር፡፡