ጾመ ሰብአ ነነዌ
በርእሰ ደብር ብርሃኑ አካል
ጥር ፳፮ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም
ጾመ ነነዌ ከሰባቱ የአዋጅ አጽዋማት አንዷ ስትኾን የምትጾመውም ለሦስት ቀናት ነው፡፡ ይህቺ ጾም የምትጀመርበት ዕለትም ልክ እንደ ዐቢይ ጾም ሰኞን አይለቅም፡፡ ጾሟ የምትጀመርበት ቀን ሲወርድ ወይም ወደ ኋላ ሲመጣ እስከ ጥር ፲፯ ቀን ድረስ ነው፡፡ ቀኑ ሲወጣ ወይም ወደ ፊት ሲገፋ ደግሞ እስከ የካቲት ፳፩ ቀን ይረዝማል፡፡ ጾመ ነነዌ በእነዚህ ፴፭ ቀናት ውስጥ ስትመላለስ (ከፍ እና ዝቅ ስትል) ትኖራለች፤ ከተጠቀሱት ዕለታት አትወርድም፤ አትወጣም፡፡ በዚህ ዓመትም (፳፻፱ ዓ.ም) ጥር ፳፱ ቀን ትጀመራለች፡፡
‹‹ጾመ ሰብአ ነነዌ፤ የነነዌ ሰዎች ጾም›› የሚለው የጽሑፋችን ርእስ እንደሚያስረዳው ይህቺን የሦስት ቀን ጾም የጾሟት በነነዌ ይኖሩ የነበሩ ሰዎች ናቸው፡፡ ከተማዋም (ነነዌ) በጤግሮስ ወንዝ ዳርቻ የምትገኝ ስትኾን መሥራቿም ናምሩድ ነው /ዘፍ.፲፥፲፩-፲፪/፡፡ ጥንታዊቷ የነነዌ ከተማ ለአሦር መነሻ የኾነች፤ እጅግ ሰፊና ያማረች፤ የቅጥሯ ርዝመትም ፲፪ ኪሎ ሜትር የሚሸፈን ነበር፡፡ በከተማዋ ንጉሡ ሰናክሬም ብዙ ሕንጻዎችን ገንብቶባት ነበር /ዮናስ ፬፥፲፩/፡፡ በዚያ ዘመን የነበሩ የነነዌ ሰዎች ኀጢአታቸው በዝቶ እግዚአብሔር ሊያጠፋቸው ሲል ቸርነትና ምሕረቱ የማያልቅበት እግዚአብሔር መክሮ፣ ዘክሮ እንዲመልሳቸውና ንስሐ እንዲገቡ ነቢዩ ዮናስን ወደ ነነዌ ሕዝብ ላከው /ሉቃ.፲፩፥፴/፡፡
ዮናስ የስሙ ትርጕም ‹ርግብ› ማለት ነው፡፡ በዳግማዊ ኢዮርብዓም ዘመነ መንግሥት የነበረ ነቢይ ነው፡፡ ይህ ነቢይ መኖሪያው በገሊላ በጋትሔፌር ድንበር ከተማ ነበረ፡፡ አባቱም አማቴ ይባላል፡፡ ኢዮርብዓም ሶርያውያንን አባሮ የእስራኤልን ድንበር እንዲመልስ ነቢዩ ዮናስ ትንቢትን ተናግሯል /፪ኛነገ.፲፬፥፳፭፤ ዮናስ ፩፥፩/፡፡ ነቢዩ ኤልያስ ያስነሣው የሰራጵታዋ መበለት ሕፃን ነቢዩ ዮናስ እንደ ኾነ የቤተ ክርስቲያን ታሪክ ያስረዳል /፩ኛነገ.፲፯፥፲፱/፡፡ መድኀኒታችን ክርስቶስም የዮናስን ከዓሣ ኾድ መውጣት የራሱ ትንሣኤ ምሳሌ አድርጎ ነግሮናል /ማቴ.፲፪፥፲፱-፵፪፤ ሉቃ.፲፩፥፴-፴፪/፡፡
እግዚአብሔር ‹‹ሔደህ በነነዌ ላይ ስበክ›› ባለው ጊዜ ነቢዩ ዮናስ ‹‹አንተ መሐሪ ነህ፤ ልትጠፉ ነው ብዬ ተናግሬ ብትምራቸው ሐሰተኛ ነቢይ እባላለሁ›› ብሎ ላለመታዘዝ እስራኤልን ለቆ በመርከብ ወደ ተርሴስ ሸሸ፡፡ እግዚአብሔርም ታላቅ ነፋስን አስነሥቶ መርከቧ በማዕበል እንድትመታ አደረገ፡፡ ከዮናስ ጋር በመርከቧ ተሳፍረው የነበሩ ነጋድያንም ያላቸውን ሀብት ወደ ባሕሩ መጣል ሲጀምሩ ነቢዩ ዮናስ ጥፋቱን ተገንዝቦ ‹‹ማዕበሉ በእኔ ምክንያት የመጣ ስለ ኾነ ንብረታችሁን ሳይኾን እኔን ወደ ባሕር ጣሉኝ›› ብሎ ተማጸናቸው፡፡ እነርሱም ‹‹ስለዚህ ሰው ነፍስ እንዳንጠፋ፣ ንጹሕም ደም በእኛ ላይ እንዳይደረግብን አይኾንም›› አሉ፡፡
ወደ ባሕሩ ለመጣል ዕጣ በተጣጣሉ ጊዜም ዕጣው በዮናስ ላይ ስለ ወጣ ነጋድያኑ ዮናስን ወደ ባሕሩ ጣሉት፡፡ ወዲያውኑ ከእግዚአብሔር ዘንድ የታዘዘ ታላቅ ዓሣ አንበሪ ዮናስን በአፉ ተቀብሎ ሦስት ቀንና ሦስት ሌሊት አሳድሮ ወደ ነነዌ አደረሰው፡፡ እግዚአብሔር የቅል ተክልን ምሳሌ በማድረግ ቅጠሉ በመድረቁ ዮናስ ባዘነ ጊዜ ‹‹አንተ ላልደከምክበት እና በአንድ ቀን በቅሎ ላደገ ቅል ስታዝን እነሆ በታላቂቱ ነነዌ ከተማ ያሉ ከአንድ መቶ ሃያ ሺሕ በላይ ሕዝብና እንስሳቱ የእጄ ፍጥረቶች ስለ ኾኑ ያሳዝኑኛል›› በማለት ነቢዩ ዮናስም ውሸታም ላለመባል መኮብለሉ ስሕተት መኾኑን አስረድቶታል፡፡
ዮናስም ነነዌ መሬት ላይ መድረሱን ባወቀ ጊዜ ከእግዚአብሔር መሸሽ አለመቻሉን ተረዳ፤ የነነዌ ሰዎችንም ‹‹ንስሐ ግቡ›› እያለ መስበክ ጀመረ፡፡ የነነዌ ሰዎችም ንስሐ በገቡ ጊዜ እግዚአብሔር ይቅር ብሎ ከጥፋት አድኗቸዋል፡፡ ሐሰት እንዳይባልም እሳቱ እንደ ደመና ኾኖ ከላይ ታይቶአል፡፡ የታላላቁ ዛፍ ቅጠል እስኪጠወልግ ድረስ አድርቆ ለሕዝቡ አሳይቷቸዋል፡፡ ንስሐቸው በከንቱ እንዳልቀረ አስረድቷቸዋል /ትንቢተ ዮናስን በሙሉ ይመልከቱ/፡፡ ታኅሣሥ ፭ ቀን የሚነበበው የመጽሐፈ ስንክሳር ክፍል ‹‹ወበልዐ አሐደ ኀምለ›› በማለት ንስሐ ያልገቡ አንድ አገር ያህል ሰዎች በእሳቱ እንደ ጠፉ ይነግረናል፡፡
ጾመ ነነዌ የሦስት ቀን ሱባኤ ናት፤ በሦስት ቀናት ጾምና ጸሎት ንስሐ የገቡ የነነዌ ሰዎች ከጥፋት እንደ ዳኑ ዅሉ፣ በብሉይ ኪዳን አስቴር ሦስት ቀን ጾማ፣ ጸልያ በእስራኤል ላይ የመጣውን መቅሠፍት እንዲመለስ አድርጋለች /አስ.፬፥፲፭-፲፮/፡፡ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምም ከበዓል ስትመለስ ሕፃኑ ልጇ ኢየሱስ ክርስቶስ መንገድ ላይ ጠፍቶአት ከሦስት ቀን ፍለጋ በኋላ በቤተ መቅደስ አግኝታዋለች /ሉቃ.፪፥፵፮/፡፡ ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስም ለሄሮድስ በሰጠው ምላሽ መልስ ሦስት ቀን የሱባኤ ፍጻሜ መኾኑን ገልጿል /ሉቃ.፲፫፥፴፪/፡፡
ጾመ ነነዌ የእግዚአብሔርን ቸርነትና መሐሪነት የምናስታውስበት ጾም ነው፡፡ ይኸውም እኛ ፍጡራኑ በበደልን ጊዜ ፈጽሞ ከማጥፋት ይልቅ ምክንያት ፈልጎ እንድንድን ያደርገናል፡፡ ዮናስ ለስብከት ፈቃደኛ ባይኾን እንኳን እግዚአብሔር በተለየ ጥበቡ እንዲሔድ አድርጎታል፡፡ በእርግጥ እግዚአብሔር ሌላ የሚልከው ነቢይ አጥቶም አይደለም፤ እርሱንም ጭምር ሊያስተምረው ስለ ፈለገ እንጂ፡፡ የነነዌ ሰዎች የተነሳሕያን ምሳሌ ናቸው፡፡ ይህም ማለት ሰው ጥፋቱን አምኖ ንስሐ ከገባ እግዚአብሔር ይቅር ማለቱን አይተውም፡፡ ለዚህም ነው ዮናስን ‹‹አንተ ላልደከምክበት እና በአንድ ቀን በቅሎ ላደገ ቅል ስታዝን እነሆ በታላቂቱ ነነዌ ከተማ ያሉ ከአንድ መቶ ሃያ ሺሕ በላይ ሕዝብና እንስሳቱ የእጄ ፍጥረቶች ስለ ኾኑ ያሳዝኑኛል›› ያለው፡፡
ቀደምት የቤተ ክርስቲያን አባቶቻችን ይህን እና ሌሎች አጽዋማትን እንድንጾም የወሰኑልን ያለ ምክንያት አይደለም፡፡ ሕጉ የተዘጋጀልን እንደ ነነዌ ሰዎች እኛም ጾመን፣ ጸልየን ከኀጢአታችን እንነጻ ዘንድ ነው፡፡ ዛሬ ዓለማችን በኀጢአት ማዕበል እየተናወጠች ባለችበት ወቅት እኛም እንደ ነነዌ ሰዎች ከበደላችን ብንመለስ እና ንስሐ ብንገባ ቸሩ ፈጣሪያችን እግዚአብሔር ይቅርታና ምሕረት የባሕርይ ገንዘቡ ስለ ኾነ ‹‹ወደ እኔ ተመለሱ፤ እኔም ይቅር እላችኋለሁ፤›› ይለናል፡፡
ስለኾነም በነቢዩ ዮናስ ላይ የተደረጉ ተአምራትንና ካለመታዘዝ የሚመጣ ቅጣት ቀላል አለመኾኑን በማስተዋል፣ ለነነዌ ሰዎች የወረደውን ምሕረት በመገንዘብ ለእግዚአብሔርም ኾነ ለሃይማኖት አባቶች እና ለወላጆቻችን መታዘዝ ይገባናል፡፡ ስንጾምም እግዚአብሔር አምላካችን መዓቱን በምሕረት፣ ቍጣውን በትዕግሥት መልሶ በኀጢአት ለጠፋው ዓለም ይቅርታውን ይልካል፡፡ በመጾማችን ራሳችን ከመዓትና ከመቅሠፍት ከመዳናችን ባሻገር በእኛ በደል ምክንያት አገራችን፣ ዕፀዋቱና እንስሳቱም ሳይቀር ከድርቅና ከቸነፈር ይተርፋሉና፡፡
ወስብሐት ለእግዚአብሔር፡፡