የከተራ በዓል በጃን ሜዳ
ጥር 10 ቀን 2007 ዓ.ም.
በእንዳለ ደምስስ
የ2007 ዓ.ም. የከተራ በዓል ቅዱስ ፓትርያርኩ፤ ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት፤ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን፤ በኢትዮጵያ የግብጽ አምባሳደር፤ የተለያዩ ሀገራት ዲፕሎማቶች፤ የየአድባራትና ገዳማት ሓላፊዎችና አገልጋዮች፤ የማኅበረ ቅዱሳን መዘምራን፤ የሰንበት ትምህርት ቤት መዘምራን፤ ምእመናንና ክብረ በዓሉን ለመከታተል ከውጭ ሀገር የመጡ ጎብኚዎች በተገኙበት በጃን ሜዳ በድምቀት ተከበረ፡፡
ከ11 አድባራትና ገዳማት በክብር የወጡት 13 ታቦታት ከየአጥቢያቸው በሊቃውንቱና በሰንበት ትምህርት ቤት መዘምራን ዝማሬ፤ በምእመናን እልልታና ሽብሸባ ታጅበው ከ6 ኪሎ ወደ ጃን ሜዳ በሚወስደው መስቀለኛ መንገድ ላይ ተገናኝተው በሊቃውንቱ ዝማሬ ቆይታ አድርገዋል፡፡
ከፊት የየአጥቢያ ሰንበት ትምህርት ቤቶችና የማኅበረ ቅዱሳን መዘምራንን በማስቀደም ታቦታቱ በቅዱስ ፓትርያርኩ፤ በብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት፤ እንዲሁም ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን ታጅበው ጃን ሜዳ ደርሰዋል፡፡
የእለቱ ተረኛ የቀበና መካነ ሕይወት አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ቤተ ክርስቲያን ሊቃውንትና የሰንበት ትምህርት ቤቱ መዘምራን በዓሉን የተመለከተ ያሬዳዊ ወረብ በየተራ በማቅረብ ቀጥሏል፡፡
በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት መልካም ፈቃድ ብፁዕ አቡነ ማርቆስ የምሥራቅ ጎጃም ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ “እነሆ በውኃ መጠመቁን ማን ይከለክለኛል?” የሐዋ. 8፤26 በሚል እለቱን በማስመልከት ኢትዮጵያዊው ጃንደረባ ለፊልጶስ የጠየቀውን ጥያቄ መነሻ በማድረግ ትምህርት ወንጌል ሰጥተዋል፡፡
ቅዱስነታቸው በሰጡት ቃለ ምእዳን “አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዮሐንስ ተጠምቆ የበደል እዳችንን ደምስሶልን ወደ ጥንተ ልጅነታችን የተመለስንበት በመሆኑ ታላቅ በዓል ነው፤ በረከትም የምናገኝበት ነው” ብለዋል፡፡
በመጨረሻም ታቦታቱ ወደተዘጋጀላቸው ድንኳን በማምራት በትምህርተ ወንጌል፤ በሊቃውንቱ እንዲሁም በማኅበረ ቅዱሳንና በሰንበት ትምህርት ቤቶች መዘምራን ያሬዳዊ ዝማሬ እየቀረበ በዓሉ ቀጥሏል፡፡