ከጠረፋማ አካባቢዎችና ከግቢ ጉባኤያት ለተውጣጡ ተተኪ መምህራን ሥልጠና እየተሰጠ ነው
ሐምሌ 17 ቀን 2006 ዓ.ም.
እንዳለ ደምስስ
- 850 የግቢ ጉባኤያት ተማሪዎች ድቁና ተቀብለዋል፡፡
በማኅበረ ቅዱሳን የትምህርትና ሐዋርያዊ አገልግሎት ዋና ክፍል አስተባባሪነት ከጠረፋማ ኣካባቢዎችና ከግቢ ጉባኤያት ለተውጣጡ ተተኪ መምህራን በአቡነ ጎርጎርዮስ የትምህርትና ሥልጠና ማእከል፤ እንዲሁም በስድስት ማእከላት ሥልጠና እየተሰጠ ይገኛል፡፡
አርባ ዘጠኝ ከተለያዩ ጠረፋማ አካባቢዎች የመጡ ተተኪ መምህራን ከሠኔ 30 ቀን 2006 ዓ.ም. ጀምሮ አዲስ አበባ በሚገኘው አቡነ ጎርጎርዮስ ትምህርትና ሥልጠና ማእከል ሥልጠናቸውን እየተከታተሉ ሲሆን፤ እስከ ሐምሌ 30 ቀን 2006 ዓ.ም. ይቆያሉ፡፡ በአንድ ወር ቆይታቸውም ትምህርተ ሃይማኖት፤ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት፤ አምስቱ አዕማደ ምሥጢራት፤ ሐዋርዊ ተልእኮ፤ የቤተ ክርስቲያን ታሪክ፤ ነገረ ቅዱሳን፤ ምሥጢራተ ቤተ ክርስቲያን፤ ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያንና ኦርቶዶክሳዊ መዝሙር በተሰኙ ርዕሶች ዙሪያ ሥልጠና እየወሰዱ ይገኛሉ፡፡
ከአርባ ዘጠኙ ሠልጣኞች መካከል ሁለቱ ቀሳውስት ሲሆኑ፤ ዐሥራ ሦስቱ ዲያቆናት ናቸው፡፡ ከጋምቤላ ክልል የመጣው ዲያቆን ቶንግ በሥልጠናው ገንቢ ዕውቀት ማግኘቱንና ከተለያዩ አካባቢዎች ከመጡት ሠልጣኞች ጋር ባለው ቆይታ ከፍተኛ የልምድ ልውውጥ ማድረጉን ገልጧል፡፡
ለሥልጠናው መሳካት የደብረ ኃይል ቅዱስ ራጉኤል ቤተ ክርስቲያን አንቀጸ ብርሃን ሰንበት ትምህርት ቤት የጎልማሶች ክፍል የስልሣ ሺህ (60,000) ብር ድጋፍ አድርጓል፡፡
በተመሣሣይ ሁኔታ ከግቢ ጉባኤያት ለተውጣጡ 361 ተተኪ መምህራን በስድስት ማእከላት በአሰላ (በኦሮምኛ ቋንቋ)፤ እንዲሁም በዝዋይ፤ በጅማ፤ በባሕር ዳር፤ በደቡብ ማስተባበሪያ (ሐዋሳ)፤ በማይጨው እና ከኬንያ ማእከል አንድ ሰልጣኝ ሥልጠናውን እየተከታተሉ ይገኛሉ፡፡
በተያያዘ ዜና ማኅበረ ቅዱሳን ኢትዮጵያ ውስጥ በሚገኙ ከ340 በላይ ዩኒቨርስቲዎችና ኮሌጆች ውስጥ ለሚገኙ ተማሪዎች የቤተ ክርስቲያን ትምህርት የሚሰጥ ሲሆን፤ በ2006 ዓ.ም. በግቢ ጉባኤያት የሚሰጠውን ትምህርት ካጠናቀቁ 40,000 ተማሪዎች ውስጥ 850ዎቹ ከብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት የድቁና ማዕረግ ተቀብለዋል፡፡