የንባብ ባሕልን ለማሳደግ ውይይት ተካሄደ
ኅዳር 26 ቀን 2005 ዓ.ም.
በእንዳለ ደምስስ
የንባብ ባሕልን በማሳደግ በመረጃና በእውቀት የበለጸገ ማኅበረሰብ እንፍጠር በሚል ርዕስ የማኅበረ ቅዱሳን የጥናትና ምርምር ማእከል ያዘጋጀው የውይይት መድረክ ኅዳር 22 ቀን 2005 ዓ.ም. ከቀኑ 8፡00 ስዓት ላይ በማኅበሩ ሕንፃ ላይ ተካሄደ፡፡
ቀሲስ ዶ/ር ሰሙ ምትኩ የማኅበረ ቅዱሳን ሰብሳቢ በመርሐ ግብሩ ላይ ለተገኙት እንግዶች የእንኳን ደህና መጣችሁ መልእክት ያስተላለፉ ሲሆን የውይይት መድረኩ የተዘጋጀበትን ዋነኛ ምክንያት ሲገልጹም “በሀገራችን ብሎም በቤተ ክርስቲያናችን በጣም በአሳሳቢ ሁኔታ እየቀነሰ የመጣውን የንባብ ባሕል ለማሳደግ እንዲቻል የተዘጋጀ የውይይት መድረክ ነው፡፡ የማያነብ ትውልድ አዲስ ነገር መፍጠር አይችልም፤ አዲስ ነገርንም ለመቀበል ያስቸግረዋል፡፡ የንባብ ባሕላችን ምን ላይ እንደሚገኝ፤ ያጋጠሙ ችግሮችና ሊወሰዱ የሚገባቸው መፍትሔዎች ላይ ለመወያትና እንዲሁም ቤተ ክርስቲያን ትውልዱን በእውቀትና በመረጃ ከማነፅና ከመቅረፅ አንጻር ሊኖራት የሚገባት ሚና ምን መሆን እንዳለበት ለማመላከት ነው፡፡” ብለዋል፡፡
የውይይት መድረኩ በአቶ ወንድወሰን አዳነ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የኢትዮጵያ ቋንቋዎች ሥነ ጽሑፍ ትምህርት ክፍል መምህር የተመራ ሲሆን ዲያቆን ያረጋል አበጋዝ ለውይይት መድረኩ መነሻ የሚሆን ጥናታዊ ጽሑፋቸውን አቅርበዋል፡፡ ባቀረቡት ጽሑፍም “ሥነ ፍጥረት የሚነበብ መጽሐፍ ነው፡፡ መጽሐፍ እግዚአብሔር በመጀመሪያ ለፍጥረቱ የሰጠው ትልቁ ሥጦታ ነው፡፡” በማለት የጥናት ጽሑፋቸውን በመጀመር በመጽሐፍ ቅዱስ ስለ መጻሕፍት የተነገሩትን ጠቅሰዋል፡፡ ከእነዚህም መካከል” በእግዚአብሔር ቃል ሰማዮች ፀኑ፤ ሠራዊታቸውም ሁሉ በአፉ እስትንፋስ የባሕርን ውኃ እንደ ረዋት የሚሰበስብ ቀላዮችንም በመዝገቦች የሚያኖራቸው” መዝ.86፤6 “በእግዚአብሔር መጽሐፍ ፈልጉ አንብቡም አፌ አዟልና” (ኢሳይያስ 34፤16) በማለት ጠቅሰዋል፡፡ በተጨማሪም ከቅዱሳን አበው መካከል “ቅዱሳት መጻሕፍትን አለማወቅ የስህተት ሁሉ ምንጭ ነው” በማለት ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ከተናገረው በመነሣት የቅዱሳት መጻሕፍት ጠቀሜታን አብራርተዋል፡፡
መጻሕፍትን የማንበብ ፋይዳን አስመልክቶም ተጠቃሽ ናቸው ያሏቸውን ነጥቦች አንሥተዋል፡፡ ከእነዚህም መካከል፤ መጻሕፍት በዘመናት ሂደት የተከማቹ የሰው ልጆች የእውቀት መዛግብት የሚተላለፍባቸው መንገዶች መሆናቸው፤ መጻሕፍት ጓደኛ ስለመሆናቸው፤ መጻሕፍት የመንፈስ ምግቦች መሆናቸው፤ መጻሕፍት አንድን ርዕሰ ጉዳይ ወጥና ምሉዕ በሆነ ሁኔታ ለመዳሰስ ያስችላሉ፤ መጻሕፍት ተጠቃሽ /Quatable/ ናቸው፤ መጻሕፍት በተሳሳተ መንገድ መጥቀስም መጠቀስም ባያስቀሩም ስህተቶችን ይቀንሳሉ፤ መጻሕፍት ትውልድን ይሻገራሉ በማለት የመጻሕፍትን ፋይዳ በዝርዝር ዳስሰዋል፡፡
ዲያቆን ያረጋል አበጋዝ የንባብ ልምድ በኢትዮጵያ አስመልክቶ ባቀረቡት ትንተናም በዚህ ርዕሰ ጉዳይ ላይ ጥናቶች በጥልቀት ያለመሠራታቸውና አንድ ጥናት አቶ አለም እሸቱ የተባሉ ተመራማሪ ሙከራ ማድረጋቸውን ገልጸዋል፡፡ በጥናታቸውም መሠረት በ220 ሰዎች ላይ ለናሙና ያህል በቀረበ መጠይቅ ለምን መጻሕፍትን እንደማያነቡ በሰጡት ምላሽ “ላይኔ ስለምፈራ አላነብም፤ ሳነብ አይገባኝም፤ ምክንያቱን አላውቅም፤ የአውሮፓ እግር ኳስ እያለ እንዴት አነባለሁ፤ ትላልቅ መጻሕፍትን ሳይ ተስፋ ያስቆርጡኛል፤ ከቤተሰብ አልለመድኩም፤ ሴት ልጅ ቤት ውሰጥ ቁጭ ብላ ቤተሰብን ማገዝ እንጂ ለማንበብ አይፈቀድላትም ፤. . . የሚሉ ምላሾችን መስጠታቸው ንባብ በኢትዮጵያ ውስጥ አለማደጉን የሚያመላክቱ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡
በጥናታቸው ማጠቃለያም የንባብ ባሕልን ለማሳደግ መፍትሔ ይሆናሉ ያሏቸውንም ጠቁመዋል፡፡ የንባብ ፍላጎት እንዲኖር ማድረግ፤ ከሕፃንነት ጀምሮ የማንበብ ፍቅርና ልምድ እንዲኖር ማድረግ፤ የመጻሕፍት ስብስብና ክምችት መፍጠር እንደ መፍትሔ ካቀረቧቸው ውስጥ ይጠቀሳሉ፡፡
ጥናቱ ከቀረበ በኋላም በንባብ ባሕል ላይ ያተኮረ ውይይት የተካሄደ ሲሆን ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን፤ የዩኒቨርስቲ ምሁራንና ተማሪዎች እንዲሁም ተሳታፊዎች አስተያየቶቻቸውንና የመፍትሔ አሳቦቻቸውን አቅርበዋል፡፡ በአብዛኛው ከተጠቀሱት ውስጥም የንባብ ባሕላችንን ለማሳደግ በዋነኛነት ቤተሰብና ትምህርት ቤቶች ከፍተኛ ሓላፊነት እንዳለባቸው ፤ ልጆች ከሕፃንነት ጀምሮ ንባብን ባሕል አድርገው እንዲያድጉ ከፍተኛ ሥራ መሠራት እንደሚገባው አመላክተዋል፡፡
በመጨረሻም ማኅበረ ቅዱሳን አንባቢ ትውልድን ለመፍጥር በሚያደርገው አገልግሎት ውስጥ መጻሕፍትን የማሰባሰብ፤ ቤተ መጻሕፍቱን በዘመናዊ መልክ የማደራጀት ሥራ በመሥራት ላይ እንደሚገኝና በአሁኑ ወቅት ቤተ መጻሕፍቱ ከሁለት ሺህ የማይበልጡ መጻሕፍትን ብቻ አሰባስቦ አገልግሎት እየሰጠ መሆኑን፤ በዐራት ዓመታት ውስጥም የመጻሕፍቱን ቁጥር ሃምሳ ሺህ ለማድረስ መታቀዱን የጥናትና ምርምር ማእከሉ ዋና ዳይሬክተር ዲያቆን ዮሐንስ አድገ የገለጹ ሲሆን ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን፤ ምሁራንና ምእመናን አንባቢ ትውልድን ለመፍጠር በሚደረገው ጥረት ውስጥ እገዛ እንዲያደርጉ ጥሪያቸውን አቅርበዋል፡፡
በውይይቱ ላይ ጥሪ የተደረገላቸው ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን፤ የዩኒቨርሲቲ ምሁራንና ተመራማሪዎች፤ እንዲሁም ተማሪዎችና ምእመናን ተገኝተዋል፡፡