‹‹ታጠቡ ንጹሐንም ሁኑ›› /ት.ኢሳ. ፩፡፲፮/

ዲያቆን ዘአማኑኤል አንተነህ

ቤተ ክርስቲያን የግል ንጽሕናንና የአካባቢ ንጽሕናንም መጠበቅ እንደሚገባ የጤና ሥርዓት ሳይዘረጋ በቀድሚነት አስተምራለች፡፡ ነቢየ እግዚአብሔር ኢሳይያስ ‹‹ታጠቡ ንጹሐንም ሁኑ፤ የሰውነታችሁን ክፋት ከዐይኖቼ ፊት አስወግዱ፤ ክፉ ማድረግንም ተው፤ መልካም መሥራትንም ተማሩ›› /ት.ኢሳ. ፩፡፲፮/ እንዲል የሥጋንም የነፍስንም ንጽሕና መጠበቅ ክርስቲያናዊ መመሪያ ነው፡፡

የግል ንጽሕናን መጠበቅ እንደሚገባ

ሰው ሥጋ ለባሽ በመሆኑ ከሥጋው የሚወጣውን ቆሻሻ በተገቢው መንገድ ማንጻት፣ ማጽዳት፣ ራሱንም ከርኩሰት መጠበቅ እንዳለበት ቤተ ክርስቲያን ታስተምራለች፡፡ ሰው ለዐይነ ምድሩ የተለየ ቦታ እና ቤት እንደሚያስፈልገው ሥርዓት የሠራች ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ናት፡፡

‹‹ሰውነቱን በውኃ ይታጠብ ፀሐይም በገባ ጊዜ ወደ ሰፈር ይመለስ ወደ ሜዳም ትወጣበት ዘንድ ከሰፈር ውጭ ቦታ ይኑርህ››/ ኦ.ዘዳግም ፳፫፡፲፩/ እንዳለ የግልን ንጽሕና መጠበቅ እንደሚገባ መጽሐፍ ቅዱስ ያስተምራል፡፡

የአካባቢን ንጽሕና መጠበቅ እንደሚገባ

የአካባቢን ንጽሕናን መጠበቅ ከጥንት የነበረ ሥርዓት ነው፤ እስራኤላውያን በእግዚአብሔር የታወጀውን ሕግ ለማዳመጥ በሲና ተራራ ከመሰብሰባቸው በፊት ሰውነታቸውን መታጠብና ልብሳቸውን ማጠብ እንደሚገባቸው ተነግሯቸዋል፤ ይህ ትምህርት በሞት መቀጮም የጸና ነበር፡፡ በእግዚአብሔር ፊት ርኩስ /ያልጸዳ/ አይፈቀድምና ‹‹አምላክህ እግዚአብሔር ሊያድንህ፣  ጠላቶችህንም በእጅህ አሳልፎ ሊሰጥህ፣ በሰፈርህ ውስጥ ይሄዳልና ስለዚህ ነውረኛ ነገር እንዳያይብህ ፊቱንም ከአንተ እንዳይመልስ ሠፈርህ የተቀደሰ ይሁን›› /ኦ.ዘዳግም.፳፫፡፲፬/ እንዲል የግልንም የአካባቢንም ንጽሕና መጠበቅ ሃይማኖታዊ ሥርዓትም ነው፡፡

ለሕሙማን የለይቶ ማቆያ ክፍል እንደሚያስፈልግ

በአሁኑ ዘመን የለይቶ ማቆያ ክፍል የምንለው ከጥንት ጀምሮ እስራኤላውያን ከእግዚአብሔር ታዘው እንደነበር እና ከሕገ ኦሪት ጀምሮ እንደ ነበር እንረዳለን፡፡ እግዚአብሔር ለእስራኤል በሰጠው ትምህርት ጤናቸውን እንዲጠብቁ፣ እንዲጠነቀቁ እና ንጹሕ እንዲሆኑ አስተምሯቸዋል፡፡ ንጹሕ እና ርኩሱንም ለይተው እንዲጠበቁም ታዘዋል፡፡ በተለይም ተላላፊ በሽታ በሚከሰትበት ጊዜ ንክኪ የሚያደርጉ ሁሉ ከሰፈር ለብቻ ተለይተው እንዲቀመጡ ታዟል ‹‹ደዌው ባለበት ዘመን ሁሉ ርኩስ ይሁን፤ እርሱ ርኩስ ነው፤ ለብቻው ይቀመጥ፤ መኖሪያውም ከከተማ በሜዳ ይሁን››/ ኦ.ዘሌ. ፲፫፡፵፮/

በሽታን ስለመከላከል

አሁን ባለው የሳይንስ ልህቀት በሽታን መከላከል የምንለው ከጥንትም በመጽሐፍ ቅዱስ የነበረ ሥርዓት ነው፤ ‹‹የተኛበት ምንጣፍ ሁሉ ርኩስ ነው፤ የሚቀመጥበትም ዕቃ ሁሉ ርኩስ ነው፤ ምንጣፉንም የነካ ሁሉ ልብሱን ይጠብ፤ በውኃም ይታጠብ እስከ ማታም ርኩስ ይሁን›› /ኦ.ዘሌ.፲፭፡፬/ እንዲል በሽታ ከመምጣቱ በፊት ንጽሕናን በመጠበቅ እና ቅድመ መከላከል ላይ መሥራት እንደሚገባ እንማራለን፡፡ ጠቢቡ ሰሎሞን ደግሞ ‹‹ላየኸው እህል ሁሉ አትሣሣ መጥኖ የሚበላ ሰው ጤነኛ ነው›› /መ.ሲራክ ፴፯፡፳፱ / በማለት ያስተምራል፡፡  ሁሉን በልክ ማድረግ ቅድመ መከላከል ነው፡፡ መልአኩም ለሶምሶን እናት ‹‹ነገር ግን ትጸንሻለሽ፤ ወንድ ልጅም ትወልጃለሽ፤ አሁንም ተጠንቀቂ፤ የወይን ጠጅም የሚያሰክርም ነገር አትጠጪ››/መ.መሳ.፲፫፥፫/ በማለት በሽታን ላለማምጣት ቅድመ ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚገባ ይገልጻል፡፡

ንጽሕናን መጠበቅ የአምልኮ መፈጸሚያ ሥርዓት ስለመሆኑ

በሕገ ኦሪት ካህናት በመገናኛው ድንኳን ውስጥ የሚያከናውኑትን አገልግሎት ከመጀመራቸው በፊት እጆቻቸውን እና እግሮቻቸውን መታጠብ ይጠበቅባቸዋል፤ ለመታጠቢያ የሚሆን ዕቃም ማዘጋጀት እንዳለባቸው ቅዱስ መጽሐፍ ያዛል፡፡

‹‹እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው የመታጠቢያ ሠን ከናስ  መቀመጫውንም ከናስ ሥራ በምስክሩ ድንኳንና በመሰዊያው መካከል ታኖረዋለህ፤ ውኃም ትጨምርበታለህ አሮን እና ልጆቹም እጆቻቸውን እና እግሮቻቸውን ይታጠቡበታል፤ ወደ ምስክሩ ድንኳን በገቡ ጊዜ እንዳይሞቱ እጆቻቸውን እና እግሮቻቸውን ይታጠቡ፤ ይህም ለእነርሱ ከእነርሱም በኋላ ለልጆቻቸው የዘላለም ሥርዓት ይሆንላቸዋል›› /ኦ.ዘፀ. ፴ ፥ ፲፯ /እንዳለ የዛሬዎቹ ካህናት እና ዲያቆናትም ወደ መቅደስ ከመግባታቸው በፊት የመታጠባቸው መነሻ ሥርዓት ይህ ነው፡፡ መጻሕፍት ውኃ እንኳን ባይኖር ሰው በምራቁ ቆሻሻውን ጠርጎ መዋል እንደሚገባ ይገልጻሉ፡፡

ስለዚህ በቤተ ክርስቲያናችን ሥርዓት ንጽሕናን መጠበቅ ጤንነትን ከመጠበቅ በላይ ወደ አምልኮ ሥርዓት ከመግባት በፊት የሚፈጸም የቅድመ አምልኮ መፈጸሚያ ሥርዓት ነው፡፡ ዲያቆናትም ሆኑ ካህናት ወደ መቅደስ የሚገቡት ታጥበው ነው፡፡ አይበለውና አንድ ካህን ወይም ዲያቆን ቢነስረው ሰሞነኛ ቀዳሽ ከሆነ ገብቶ መቀደስ አይችልም፡፡

ስለዚህ ንጽሕናን መጠበቅ ለሥጋ ብቻ ሳይሆን አምልኮንም ለመፈጸም የሚውል ቅድሚያ ሊደረግ የሚገባም ሥርዓት ነው፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስም በመዋዕለ ሥጋዌው የደቀ መዛሙርቱን እግር የማጠቡ ምሥጢር ብዙ ቢሆንም እማሬያዊ ትርጉሙ ግን ንጽሕናን መጠበቅ እንደሚገባ ያስተምራል፡፡

ሠለስቱ ምዕትም ንጽሕናን መጠበቅ እንደሚገባ አመስጥረው አስተምረዋል፤ ‹‹ወኢትትሐከይ ኀጺበ እግረ አኃው ሶበ መጽኡ ኀቤከ እስመ በእንተ ዛቲ ትእዛዝ ይትኃሠሥዎሙ ለእለ ያጸርዕዋ ለዛቲ ግብር ወለእመ ኮኑ ኤጲስ ቆጶሳት እስመ እግዚአብሔር ኀፀበ እግረ አርዳኢሁ ቅድመ ወአዘዞሙ ከማሁ ይግበሩ ፥ ወንድሞች ወደ አንተ በመጡ ጊዜ እግራቸውን ማጠብን ቸል አትበል  ይህችን ሥራ ቸል የሚሏትን ስለዚች ትእዛዝ ሥላሴ በፍዳ ይመረምሯችኋልና፡፡ ኤጲስ ቆጶሳትም ቢሆኑ እግዚአብሔር አስቀድሞ የደቀ መዛሙርቱን እግር አጥቦ እንዲሁ ያደርጉ ዘንድ አዝዟቸዋልና›› /ሃ.አበው ፳፥፳፱/ እንዲሁም በቤተ ክርስቲያናችን ሥርዓት ጌታችንን አብነት በማድረግ በሰሞነ ሕማማት በጸሎተ ሐሙስ በየአብያተ ክርስቲያናቱ ሕጽበተ እግር ይከናወናል፡፡ ከዚህም የተነሳ እንግዳ ሲመጣ እግር ማጠብ በቤተ ክርስቲያናችን የሚከናወን ሥርዓት ነው፡፡ ይህም ሥርዓት በሀገራችን ኢትዮጵያ ከሃይማኖት ሥርዓትነቱ አልፎ የተለመደ ባህል ሁኖ እየተተገበረ ይገኛል፡፡

እግዚአብሔር ሰውን ከውኃ መፍጠሩም ንጽሕና ለሰው ልጅ ሁሉ አስፈላጊ መሆኑን ያጠይቃል፡፡ ‹‹ጥሩ ውኃንም እረጭባችኋለሁ እናንተም ከርኩሰታችሁ ሁሉ ትነጻላችሁ›› /ት.ሕዝ. ፴፮ ፥ ፳፭ / በማለት ሕያው ቃሉ እንደሚገልጸው በውኃ ንጽሕናን መጠበቅ እንደሚገባ እንረዳበታለን፡፡

ወደ ቤተ ክርስቲያን ስንሄድ ንጽሕናን መጠበቅ እንደሚገባ

ያዕቆብም ወደ ቤቴል መሥዋዕት ሊያቀርብ በሚሄድበት ጊዜ ቤተሰቦቹ ንጹሐን እንዲሆኑ እና ልብሳቸውን እንዲለውጡ አዝዟቸው ነበር ‹‹ንጹሐንም ሁኑ፤ ልብሳችሁንም እጠቡ፤ ተነሱ እና ወደ ቤቴል እንውጣ›› /ኦ.ዘጸ. ፴፭ ፥ ፪ / በማለት ሰው ወደ ቤተ ክርስቲያን ሲሄድ ንጽሕናውን ጠብቆ መሄድ እንዳለበት የምንማርበት ሲሆን ሰው የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ በመሆኑ ሰውነቱንም ማርከስ እንደሌለበትም እንረዳለን፡፡

ፍትሐ ነገሥት ደግሞ ‹‹ወከመ ይኩን ለመልእክተ ቤተ መቅደስ ልብሰ ፀዓዳ ድልው፤ ለቤተ መቅደስ ማገልገያ ነጭ ልብስ ይሆን ዘንድ ይገባል / ፍትሐ ነገሥት አንቀጽ ፳፫ ቁጥር ፰፻፲፩ /

በተጨማሪም ሴት ልጅ የወር አበባ ካየች ወንድ ልጅ ሕልመ ሌሊት ካየ እስከ ተወሰነ ቀን ድረስ ወደ ቤተ ክርስቲያን መግባት አይፈቀድላቸውም /ኦ.ዜሌ. ፲፭ ፥ ፲፱ /

አሁን ባለንበት የ፳፻፲፪ ዓ.ም አጋማሽ ላይ ደግሞ ኮሮና የተሰኘ ዓለም አቀፍ ወረርሽኝ ተከስቷል፡፡ ይህን ለመከላከል ደግሞ ንጽሕናን መጠበቅ አንዱ መከላከያው እንደሆነ ተገልጿል፡፡

በቅዱስ መጽሐፍ እንደተገለጸው በሽታ አዳም እና ሔዋን በእግዚአብሔር ላይ አምፀው ሕግን ተላልፈው ከገነት ከወጡ በኋላ እንደመጣ ይነገራል፤ ቅዱስ ጳውሎስ ‹‹በአንድ ሰው በደል ምክንያት ኃጢአት ወደ ዓለም ገባ፤ እንደዚሁም ሁሉ ኃጢአትን ስለአደረጉ በሰው ሁሉ ላይ ሞት መጣ›› /ሮሜ. ፭ ፥ ፲፪ / እንዲል፡፡

አዳም እና ሔዋን ከማመፃቸው በፊት ግን በገነት ሳሉ ፍጹም ጤንነት ነበራቸው፤ እንኳን በሽታ ምንም ክፉ ነገር የማያውቁ ክፉም ነገር ደርሶባቸው የማያውቁ ነበሩ፤ ነገር ግን አዳም እና ሔዋን ከፈጣሪያቸው ጋር እንዲቆራረጡ የሚያደርጋቸውን ኃጢአት ፈጸሙ፤ እግዚአብሔርም ካስቀመጠላቸው ደረጃ ወይም መመሪያ ዝቅ አሉ ችግር ውስጥ ገቡ፡፡ ከዚህ ጊዜ በኋላ በሽታ እንደመጣ ይነገራል፤ በተለይም በየጊዜው በምንፈጽመው ኃጢአት ፈጣሪያችንን ስለምናስቀይም ቀድመው ያልነበሩ በሽታዎች በየጊዜው እየመጡ ነው፤ ቁጥራቸውም እየበዛ ይገኛል፤ አሁን የመጣው ኮሮናም የኃጢአት ውጤት ነው፡፡

ከበሽታ በዘለለ ደግሞ መቅሰፍት ከኃጢአት ብዛት የተነሳ እንደሚመጣ ቅዱሳት መጻሕፍት ይመሰክራሉ፤ እግዚአብሔር ቁጣውን ይልካል ተግሳጹን ያሳያል፡፡ ከእግዚአብሔር ስንወጣ ፣ ስመ እግዚአብሔርን መጥራት ስናቆም፣ እግዚአብሔርን ስናስቆጣ እግዚአብሔር በመዓት ይገስጸናል፡፡ ነቢዩ ሚክያስ ‹‹ባልሰሙም አሕዛብ ላይ በቁጣ እና በመዓት እበቀላለሁ››/ት.ሚክ. ፭ ፥ ፲፭ /፤ ነቢየ እግዚአብሔር ኢያሱም ‹‹እኛ እስከ ዛሬ ድረስ ከእርሱ ያልነጻንበት የፌጎር ኃጢአት ጥቂት ነውን? በእግዚአብሔር ማኅበር ላይ መቅሰፍት ወረደ››/መ. ኢያሱ. ፳፪፥፲፯/ በተጨማሪም ቅዱስ ዳዊት ‹‹አቤቱ በቁጣህ አትቅሰፈኝ በመዓትህም አትገስጸኝ››/መዝ. ፮፥፩/ በማለት ይገልጻል፡፡

ራስን መፈለግ እንደሚገባ

አሁን ላይ ይህ ዓለም አቀፍ ወረርሽኝ በዓለም ላይ ሲከሰት ብዙዎች ተሳስተው እግዚአብሔርንም አስቀይመው እንደነበር ይገልጻሉ፡፡ ስለዚህ እንደዚህ ዓይነት በሽታ ሲከሰት ራስን በመመርመር እግዚአብሔርን፤ በምን አስቀየምኩት? ምን ስሕተት ሠራሁ? ምን በደልኩ? ወደ ፊትስ የእግዚአብሔር ይቅርታ ለማግኘት ምን ማድረግ አለብኝ? በማለት ራስን በጽሙና መጠየቅ ይገባል፡፡ ለዚህ አብነት የሚሆነን በመጽሐፈ መነኮሳት ማር ይስሐቅ ላይ የተገለጸው ‹‹ዖፈ አሮድዮን›› ግብሩን ምሳሌ ማድረግ እንችላለን፡፡

በማር ይስሐቅ አንቀጽ ፳፰ ምዕራፍ ፫ እንደተገለጸው እልአሮድዮን የሚባል ወፍ አለ፤ ይህ ወፍ ድምፀ መልካም የሆነ እና ሰዎች በድምፁ ይሳቡለታል፡፡ እነርሱ ከሚያድሩበት ቦታ ተነስቶ ወደ በረሃ በሄደ ጊዜ እጅግ ደስ ይለዋል፡፡ የድምፁ ቃና መልካምነት በተመስጦ ራሱንም ምግብ እስከ መተው ያደርሰዋል፡፡ ለዚህ ወፍ የደስታ ምንጭ የሆነው ምሥጢር ከሰው መለየት ነው፡፡ ቀጥሎም የድምፁን ቃና መልካምነት በተመስጦ ማዳመጥ ነው፡፡ የዚህን ወፍ ድሞፁንና የዜማውን ስልት የሰማ ሁሉ መልቀሙን እስኪተው ድረስ፣ ሰውን ደግሞ መንገዱን እስኪዘነጋ ድረስ ፣ ምግቡንም እንዲተው ያደርገዋል፡፡

በዚህ ዓለም ላይ ብዙ ነገሮች ይሠራሉ፤ ነገር ግን ዓለም በፍጻሜው የሚያስደስት ነገር የለውም፡፡ የዓለምን ከንቱነት ከሰሞኑ ወረርሽኝ ተምረናል፤ ኃያላን ነን ያሉ ሁሉ ለሞት እጃቸውን ሰጥተዋልና፡፡

እልአሮድዮን ወፍ እንደዚህ ዓይነት ችግሮች ሲከሰቱ ግብሩ አብነት መሆን ይችላል፡፡ እንደዚህ ወፍ ራስን ሰውሮ መጸለይ አስፈላጊ ነው፡፡ በዓለም ስንኖር እግዚአብሔርን እናስቀይመዋለን፤ ከሰዶምና ከገሞራ በበለጠ ብዙ ወንጄሎች ተሰርተዋል፤ ለአእምሮ የሚከብዱ ብዙ በደሎች ተፈጽመዋል፤ እግዚአብሔር ግን የፍቅር አምላክ ነውና ይታገሰናል፡፡

በዓለም ውስጥ ብዙ ወንጀሎች ይሰራሉ፤ እንደዚህ ዓይነት ወንጀሎች ሲፈጸሙ ደግሞ ከሰው ተለይቶ ራስን ማዳመጥ አስፈላጊ ነው፤ ሰው እግዚአብሔርን ሲያስቀይም ተጸጽቶ ጥፋቱን ዐውቆ ራሱን መጠየቅ እና ወደ መልካም ነገሩ መመለስ አለበት፡፡

ሰው ኃጢአቱን እያሰበ ሲያለቅስ ዓለም ያስጥለዋል፤ ሰው ኃጢአቱን እያሰበ ሲጾም ጾሙ አይታወቀውም፤ ሰው በደሉን እያሰበ ሲሰግድ ስግደቱ አይታወቀውም፤ ሰው ተጸጽቶ ሲጸልይ ሁሉንም ነገር ረስቶ ወደ እግዚአብሔር ይመለሳል፤ ሁሉን ነገር ትተን ከዓለሙ ስንርቅ ደስ ይለናል፤ ከዓለሙ ሁካታና ከወረርሽኙ ስንጠበቅ ነፍሳችን ሐሤት ታደርጋለች፡፡ ስለሆነም በዚህ ጊዜ ኃጢአትን አስቦና ከዓለም በመለየት ተጸጽቶ ወደ እግዚአብሔር መመለስ ይገባል፡፡

በዚህ በመጽሐፈ መነኮሳት እንደተገለጸው የመነኩሴም ሕይወት እንደ ዖፈ እልአሮድዮን መሆን እንደሚገባው ይገልጻል፤ የመነኩሴም ሕይወት ከሰው ተለይቶ በበዓት ተከቶ የኖረ እንደሆነ ያን ጊዜ ሠማያዊ ደስታን ገንዘብ ያደርጋል፡፡ በተባሕትዎ ሆኖ ነፍሱ ከሥጋው የምትለይበትን ጊዜ ይጠብቃል፤ ይህም የነፍስ ሥራን ይመስላል፤ ከእእምሮ መንፈሳዊ የደረሰች ነፍስ ሁለንተናዋ ተማርካ ወደ እሷ ትሄዳለችና ሥጋዊ አነዋወሯን እስክትዘነጋው ድረስ ሥጋም መብልም መጠጥም እስኪተው ድረስ ከዚህ ዓለም አነዋወር እስኪወጣ ድረስ ተማርካ ትሄዳለች፡፡

‹‹ለመተቃቀፍ ጊዜ አለው ፥ ከመተቃቀፍ ለመራቅ ጊዜ አለው›› /መ.መክብብ ፫፥፭/  እንዲል ቅዱስ ቃሉ ለበሽታው አካላዊ መራራቅ አንዱ መከላከያ እንደሆነ በጤና ባለሙያ የተነገረ ሲሆን ጠቢቡ ሰሎሞን ለመተቃቀፍ ጊዜ አለው፤ ለመራራቅም ጊዜ አለው እንዳለ አሁን ለብቻ ሆነን ራሳችንን የምንወቅስበት ጊዜ ነው፡፡

‹‹አሁንም ምድርን ያነዋውጣት ዘንድ በተነሳ ጊዜ እግዚአብሔርን ከመፍራት እና ከግርማው ክብር የተነሳ ወደ ድንጋይ ዋሻ ግቡ፤ በመሬት ውስጥም ተሸሸጉ›› /ት.ኢሳ. ፪ ፥ ፲ / በማለት ነቢየ እግዚአብሔር ኢሳይያስ አስተምሯል፡፡ ፈጣሪ የሌለ እስኪመስል ድረስ ለኅሊና የሚከብዱ ኃጢአቶችን ሠርተናል፡፡ ስለዚህ የመጣው ቸነፈር እስኪያልፍ ድረስ የቻለ በገዳማት ሱባኤ ይዞ ካልቻለ በቤቱ በጸሎት ምሕረትን በመማጸን ከመዓቱ መራቅ ይገባል፡፡

‹‹ሕዝቤ ሆይ ሂድ ወደ ቤትህ ግባ፤ በርህን ከኋላህ ዝጋ፤ ቁጣው እስኪያልፍ ድረስ ለጥቂት ቀን ተሸሸግ››  ት.ኢሳ. ፳፮፥፳/ በማለት ቅዱስ ቃሉ እንደሚነግረን እንደዚህ ዓይነት ቁጣዎች ሲከሰቱ የተቻለው በዓት አጽንቶ፤ ያልተቻለው ደግሞ ከቤቱ ሆኖ ራሱን መጠየቅና መጸጸት እንዳለበት ቅዱስ ቃሉ ያስተምረናል፡፡ አዎ እግዚአብሔርን አስቀይሜዋለሁ ብሎ ራስን እየወቀስ አብዝቶ በመጾም፣ አብዝቶ በመጸለይና አብዝቶ በመስገድ መቅሰፍቱን መከላከል ይገባል፡፡

ይቆየን