ፈረሰኛው ቅዱስ ጊዮርጊስ

እንደምን ሰነበታችሁ ልጆች? ደህና ናችው? እግዚያብሔር ይመስገን እንዳላችሁ ተስፋ እናደርጋለን፡፡ ልጆች! ትምህርት እንዴት ነው? ከዓለማዊው ትምህርታችሁ ጎን ለጎን እናንተን ያስተምራል እንዲሁም በምግባር ያንጻል ብለን ያሰበነውን ታሪክ ይዘንላችሁ ቀርበናል፡፡ ልጆች በዚህ ዕትማችን ይዘንላችሁ የቀርብነው የሰማዕቱ ቅዱስ ጊዮርጊስን ታሪክ ነው፡፡ ከታሪኩ ብዙ እንደምትማሩ ተስፋ እናደርጋለን፤ በጽሞና እንድታነቡም ተጋብዛችኋል፤ መልካም ንባብ ይሁንላችው፡፡

በመንፈሳዊ ሕይወታችን መለወጥ ለምን ተሳነን?

እግዚአብሔር ከእኛ የመልካም ሥነ ምግባርና የሃይማኖት ፅናትን ይፈልጋል፡፡ በሃይማኖት የሚኖር ሰው አስተማሪ ሕይወት ያለው ሰው መሆን አለበት፡፡ ሃይማኖቱንም በሥራና በምግባር መግለጽ አለበት፡፡ ለዚህ ነው ጌታችን “እናንተ የምድር ጨው ናችሁ፤ ጨው አልጫ ቢሆን  በምን ይጣፍጣል? ወደ ውጭ ተጥሎ በሰው ከመረገጥ በቀር ወደ ፊት ለምንም አይጠቅምም። እናንተ የዓለም ብርሃን ናችሁ። በተራራ ላይ ያለች ከተማ ልትሠወር አይቻላትም። መብራትንም አብርተው ከዕንቅብ በታች አይደለም እንጂ በመቅረዙ ላይ ያኖሩታል፤ በቤት ላሉት ሁሉም ያበራል። መልካሙን ሥራችሁን አይተው በሰማያት ያለውን አባታችሁን እንዲያከብሩ ብርሃናችሁ እንዲሁ በሰው ፊት ይብራ፤” መብራት የተባለው ሃይማኖትና ምግባራችን ነው፡፡ (ማቴ.፭፥፲፫-፲፮)

‹‹በንስሓ ተመለሱና በሕይወት ኑሩ›› (ሕዝ.፲፰፥፴፪)

ዓለም ኃጢአተኝቱን ላለማመን ይህንን የመጣብንን መቅሠፍት (ኮሮና ቫይረስ) ‹‹እንዲህ የምትባል ሀገር ናት ያመረተችው፤ ከእንትና ቤተ ሙከራ አፈትልኮ የወጣ ቫይረስ ነው፤›› በማለት የተለያዩ የሽፍጥ ምክንያቶችን ትደረድራለች፡፡ ይሁን እንጂ ማንም ምንም ቢል እውነታው ግን ‹‹የኃጢአት ደመወዝ ሞት ነው›› ተብሎ እንደተጻፈ የሰው ልጅ የኃጢአት ደመወዙን ከእግዚአብሔር እጅ እየተቀበለ ነው፡፡ (ሮሜ.፮፥፳፫)

“ዐርገ ሰማያተ በዐምደ ደመና፤ በደመና ወደሰማይ ዐረገ” (ቅዱስ ያሬድ)

ዲያቆን ዐቢይ ሙሉቀን

ኢትዮጵያዊው ሊቅ ቅዱስ ያሬድ ይህን ቃል እንደተናገረው ዝማሬ በሚባለው የመጽሐፍ ክፍል   እናገኘዋለን። ሊቁ የጌታችንን የማዳን ጉዞ ከፅንሰቱ ጀምሮ እስከ ዕርገቱ ብሎም እስከ ዳግም ምጽአቱ ከብሉያት እና ከሐዲሳት እያጣቀሰ አምልቶና አስፍቶ ያስረዳበትን ቃል ስለዕርገቱ በተናገረው የምስጋና ክፍል ውስጥ እናገኘዋለን፤ ሙሉ ንባቡም እንዲህም ነው።

“ዐርገ ሰማያተ በዐምደ ደመና፤ ለድንግል ዘፈትሐ ማኅፀና፤ ለደቂቀ እስራኤል ዘአውረደ መና፤ ውእቱኬ ዘአድኃና ለሶስና እምእደ ረበናት፤ ዐርገ ሰማያተ በዐምደ ደመና፤ በደመና ወደ ሰማይ ዐረገ፤ የድንግልን ማኅፀን የፈታ፣ ለእስራኤል ልጆች መናን ያወረደ፤ ሶስናን ከረበናት እጅ ያዳነ በደመና ወደ ሰማይ ዐረገ፡፡” በዚህ ኃይለ ቃል ዐረገ የተባለው ማን ነው? በደመና ዐረገ የተባለውስ ምን ማለት ነው? የድንግልን ማኅፀን የፈታው፣ ለእስራኤል መናን ያወረደው፣ ሶስናን ከረበናት እጅ ያዳነው ማን ነው? የሚለውን እንመለከታለን።

ዐረገ የተባለው ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡ የእርሱ ወደሰማይ ማረግ የሌለበት ቦታ ኑሮ ካለበት ቦታ ወደሌለበት ቦታ ሄደ ማለት አይደለም፡፡ ነገር ግን የማዳን ሥራውን ፈጽሞ ወደባሕርይ አባቱ መመለሱን፤ የማዳን ሥራውን መፈጸሙን፤ በሥጋ በክብር ማረጉን ለመግለጽ ነው፡፡ (ዝማሬ ዘዕርገት)

ጌታችን ኢየሱስ በደመና ዐረገ መባሉ ሊቃውንት እንደሚነግሩን ደመና ክብሩና ልዕልናው በመሆኑ ነው። “ዘበእንተ ዕበይከ ትትሜሰል በደመና፤ ስለ ልዕልናህ በደመናት ትመሰላለህ” እያሉ ሊቃውንቱ ያመሰግኑታል። በሐዋርያት ሥራም “ወነሥአቶ ደመና ወዐርገ ሰማየ እንዘ እሙንቱ ይኔጽሩ ኀቤሁ፤ ደመናም ተቀበለችው፤ እነርሱም ወደእርሱ እያዩ ወደሰማይ ዐረገ” ተብሎ ተጽፏል። ነቢየ እግዚአብሔር ቅዱስ ዳዊትም “ዐርገ እግዚአብሔር በይባቤ ወእግዚእነ በቃለ ቀርን፤ እግዚአብሔር በዕልልታ ጌታችንም በመለከት ድምፅ ዐረገ” በማለት እንደነገረን በክብር በይባቤ መላእክት ማረጉን ያስረዳል። (ሐዋ.፩፥፱፤ መዝ.፵፮፥፭)

በሌላ መልኩ በደመና ዐረገ የተባለው ደመና እመቤታችን ድንግል ማርያም ናት፤ ከእርሷ  በነሣው ሥጋ ዐረገ ማለት ነው። ነቢየ እግዚአብሔር ኢሳይያስ “እነሆ እግዚአብሔር በፈጣን ደመና ተቀምጦ ወደግብፅ ይመጣል” ብሎ አስቀድሞ በትንቢቱ የተናገረላት ደመና እመቤታችን በመሆኗ ነው። ሊቁ ቅዱስ ያሬድም “ደመናሰ ዘይቤ ይእቲኬ ማርያም እንተ ጾረቶ ዲበ ዘባና፤ ደመናስ የሚላት አምላክን በጀርባዋ የተሸከመችው ማርያም ናት” በማለት ያስረዳል። ስለዚህ “በደመና ዓምድ ዐረገ” ሲል ከድንግል ማርያም በተዋሐደው ሥጋ ወደሰማይ ዐረገ ማለት ነው።  ከላይም እንደገለጽነው ዐረገ መባሉ በሥጋ እንጂ በመለኮቱማ ምሉዕ በኵለሄ፣ በሁሉም ቦታ፣ በሁሉም ጊዜ ምሉዕ ነው። (ኢሳ.፲፱፥፩)

ይህ በክብር በይባቤ መላእክት፣ ከማርያም በተዋሐደው ሥጋ በደመና ዐረገ የተባለው ማን ነው? ለሚለው ጥያቄ ሊቁ ቅዱስ ያሬድ ከብሉይ ከሐዲስ እየጠቀሰ እንዲህ ያስረዳናል።

ሀ. የድንግልን ማኅፀን የፈታው ነው። “ለድንግል ዘፈትሐ ማኅፀና፤ የድንግልን ማኅፀን የፈታው ነው።” እናታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በመላእክትም በሰውም አንደበት የተመሰከረላት፣ ጥንት ነቢያት ትንቢት የተናገሩላት፣ በኋላም ሊቀ መላእክት ቅዱስ ገብርኤል፣ የመጥምቀ መለኮት የቅዱስ ዮሐንስ እናት ቅድስት ኤልሳቤጥ የመሰከሩላት ዘለዓለማዊት ድንግል ናት። ከዚህች ድንግል ማኅፀኗን ዙፋን አድርጎ በኅቱም ድንግልና ተፀንሶ በኅቱም ድንግልና የተወለደው ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። ነቢዩ ኢሳይያስ “እነሆ ድንግል ትፀንሳለች፤ ወንድ ልጅንም ትወልዳለች፤ ስሙንም አማኑኤል ብላ ትጠራዋለች” በማለት እንደተናገረው ከድንግል ማርያም የተወለደው አማኑኤል ተብሎ በነቢዩ ትንቢት የተነገረለት እግዚአብሔር ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። (ኢሳ. ፯፥፲፬)

ለ. ለእስራኤል መናን ያወረደው ነው። ይህ በኅቱም ድንግልና ተፀንሶ በኅቱም ድንግልና የተወለደው ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለእስራኤል መና እያወረደ አርባ ዓመት ሙሉ በበረሃ እስራኤልን የመራው ነው። ነቢዩ ዳዊት “በልዑ ወጸግቡ ጥቀ ወኢያህጥዖሙ እምዘ ፈቀዱ፤ በሉ፤ እጅግም ጠገቡ፤ ለምኞታቸውም አላሳጣቸውም” ተብሎ የተናገረለት አምላክ ወልደ አምላክ በተዋሐደው ሥጋ ወረደ፤ ተሰደደ፤ ጾመ፤ ተራበ፤ ተሰቀለ፤ ሞተ፤ ተነሣ፣ ዐረገ እየተባለ ይነገርለታል። በቦታ የማይወሰን አምላክ ቦታ ተወሰነለትና ወረደ፤ ዐረገ እየተባለም ተነገረለት። ስለዚህ ይህ በክብር ዐረገ የተባለው ማን ነው? የሚል ሰው ካለ ጥንት እስራኤልን በበረሃ መና እያወረደ ሲመግብ የኖረው ዛሬም ለዘወትርም መግቦቱ ለዐይን ጥቅሻ ያህል እንኳን የማያቋርጠው እግዚአብሔር ወልድ ነው። (መዝ.፸፯፥፳፱)

ሐ. “ውእቱኬ ዘአድኃና ለሶስና እምእደ ረበናት፤ ሶስናን ረበናት እጅ ያዳናት ነው።” በትንቢተ ዳንኤል ተጽፎ እንደምናገኘው ይህቺ ሶስና መልከ መልካም ባለትዳር ለትዳሯም ታማኝ ነበረች። ነገር ግን የአይሁድ መምህራን ከመልከ መልካምነቷ የተነሣ በዝሙት ተነደፉና ለፈቃደ ሥጋቸው ጠየቋት፤ እርሷ ደግሞ ከእነርሱ ኃላፊነትና ሥልጣን ይልቅ ለእግዚአብሔር መገዛት መረጠችና ምኞታቸውን ለመፈጸም ፈቃደኛ አልሆነችም። በዚህ ጊዜ እነርሱ አጥፍተው ደግሞ ወነጀሏትና “ከወንድ ጋር አግኝተናታል” ብለው በአይሀድ ሸንጎ አቆሟት፤ እርሷም ወደ እግዚአብሔር ጸለየች። የለመኑትን የማይነሣው የነገሩትን የማይረሳው አምላካችን እግዚአብሔር መላኩን ልኮ ከረበናቱ እጅ አዳናት።

ሊቁ ቅዱስ ያሬድም ብሉዩን ከሐዲስ አስማምቶ እየጠቀሰ በደመና ወደሰማይ ያረገው፣ ጥንት ጀምሮ ጥበቃው ያልተለየን፣ በዚህም ሶስናን ከረበናት እጅ ያዳነ አምላክ ወልደ አምልክ እንደሆነ ያስረዳናል። ሶስና በእግዚአብሔር በመታመኗ ምንም እንኳን መምህር በመሆናቸው ተሰሚነትን የሚያገኙ ቢመስላቸውም፣ እንዳሰቡትም በአይሁድ የፍርድ ሸንጎ ቢያቀርቧትም እርሷ ግን እውነተኛ ዳኛ እግዚአብሔር እንዳለ በማመን ዐይኗን ወደእግዚአብሔር አቀናች። ነቢየ እግዚአብሔር ዳዊት “ቅሩብ እግዚአብሔርም ለየዋሐነ ልብ፤ እግዚአብሔር በልባቸው የዋሐን ለሆኑ ቅርብ ነው” ብሎ እንደነገረ፤ በቅዱስ ወንጌልም ልበ ንጹሐን ብፁዓን ናቸው፤ እግዚአብሔርን ያዩታልና” ተብሎ እንደተጻፈው በንጹሕ ልብ እግዚአብሔርን ስለለመነች ከመጣባት መከራ አዳናት። (መዝ.፴፫፥፲፰)

እኛም የሶስናን ልቡና ልብ ልናደርግ ይገባል፤ ካልሆነ ግን ከንቱ ጩኸት አይጠቅምም፤ እንደፈሪሳዊው በትምክህት መናገር ሳይሆን እንደ ቀራጩ በትሕትና ማንባት ከዐይን ጥቅሻ የፈጠነ ምላሽ ያሰጣል።

ምን አልባትም ሰዎች በማወቅም ይሁን ባለማወቅ ሊበድሉን ይችሉ ይሆናል። ግን እኛ እንደፈሪሳዊው ያለ ሳይሆን እንደ ቀራጩ በትሕትና የተሞላ ጩኸት እንጩኽ። እንደአይሁድ መምህራን ራስ አጥፍቶ ጥፋትን ወደሰው በሚሰነዝሩት አግባብ ሳይሆን እንደሶስና  “በእግዚአብሔር  ፊት ከምበድል ኃጢአት ሳልሠራ በእጃቸው መውደቅ ይሻለኛል” ማለት  ይኖርብናል። “ከዐንጀት ካለቀሱ እንባ አይገድም” እንደሚባለው ከልባችን ካለቀስን እና ከልባችን ከተመለስን የምንችለውን ማድረግ እንችላለን። ከልብ ካለቀስን ደግሞ እግዚአብሔር አምላካችን ዛሬም ሕያው በመሆኑ አብሮን አለና ጸሎታችንን ይሰማናል።

ዛሬ ሀገራችንም ሆነ ቤተክርስቲያናችን እጅግ ከባድ ፈተና ላይ ወድቃለች። ጥንት ክርስቶስ በመከራ የመሠረታት፣ ዛሬም መስቀሉን ተሽክማ ትገኛለች፤ በዚህም መከራዋ በዝቷል፡፡ እኛም ችግራችን በመብዛቱ በአንድ በኩል በሽታው ሲያሰቃየን በሌላ በኩል ደግሞ እርስ በእርሳችን መስማማት አቅቶናል። ጸሎታችንም “ሳል ይዞ ስርቆት፣ ቂም ይዞ ጸሎት” እንደሚባለው ሁኖብናል። ከዚህ ሁሉ መከራ ለእስራኤል መና ያወረደው፣ በድንግልና ተፀንሶ በድንግልና የተወለደው፣ ሶስናን ከረበናት እጅ የታደገው እግዚአብሔር አምላካችን እንዲሰውረን፣ መአቱን በትዕግሥት ቁጣውን በምሕረት እንዲመልስልን፣ የእግዚአብሔር አምላካዊ ቸርነት፣ የድንግል ማርያም አማላጅነት፣ የቅዱሳን ሁሉ ተራዳኢነት አይለየን፤ አሜን።

‹‹እምነትም ተስፋ ስለምናደርገው ነገር የሚያስረግጥ፥ የማናየውንም ነገር የሚያስረዳ ነው›› (ዕብ. ፲፩፥፩)

ማንኛውም የሕይወት ውጣ ውረድ ቢያጋጥመን በእምነት ከጸናን የማናልፈው ነገር የለም፡፡ የማንዘለው የችግር እና የመከራ ግንብ፣ የማንሻገረው ባሕር እና መሰናክል አይኖርም፡፡ ነቢየ እግዚአብሔር ቅዱስ ዳዊት በእምነት ከእግዚአብሔር ጋር ከኖርን የሚያስፈራን አንዳች ነገር አለመኖሩን ሲያስረዳ ‹‹በሞት ጥላ መካከል እንኳን ብሔድ፤ አንተ ከእኔ ጋር ነህና ክፉን አልፈራም፤ በትርህና ምርኩዝህ እነርሱ ያጽናኑኛል›› ብሏል፡፡ (መዝ. ፳፪፥፬)

‹‹ድኀነት››

የሰው ልጅ በኃጢአት ምክንያት ያጣውን የተፈጥሮ ጸጋ ክብር በአዲስ ተፈጥሮ እንደገና ለመታደል መብቃቱን ለመግለጽ የሚነገር ልዑል ቃል ‹‹ድኀነት›› ነው፡፡ ድኀነት የሚለው ቃል አዳም በክርስቶስ የታደለውን የሕይወተ ሥጋና ሕይወት ነፍስ፣ በረከተ ሥጋና በረከተ ነፍስ ጸጋ ወይም በሌላ አነጋገር የሞተ ሥጋና የሞተ ነፍስ ድቀት የደረሰበት አዳም በክርስቶስ ኢየሱስ ያገኘው ትንሣኤውና ሕይወት የሚገለጽበት ሕያው ቃል ነው፡፡

‹‹የሱራፌል አምሳላቸው ቅዱስ ያሬድ››

እግዚአብሔር አምላክን ‹‹ቅዱስ ቅዱስ ቅዱስ›› እያሉ በመንበሩ ፊት ቆመው እንደሚያመሰግኑ ሁሉ ኢትዮጵያዊ ማኅሌታይ ቅዱስ ያሬድ ‹‹ቅዱስ ቅዱስ ቅዱስ›› እያለ በመላእክት ቋንቋ ፈጣሪውን በማመስገኑ እና ዜማውን ከእነርሱ በመማሩ በመጽሐፈ ስንክሳር ‹‹አምሳሊሆሙ ለሱራፌል፤ የሱራፌል አምሳላቸው›› ተብሏል፡፡

“ደኅንነት ከእግዚአብሔር ዘንድ ነው” (ትንቢተ ዮናስ ፪፥፲)

እግዚአብሔር ከበሽታ ይፈውሳል፤ ከችግርና መከራም ይሰውራል፡፡ በየጸበል ቦታው ተጠምቀው ከኤች አይ ቪ፣ ከካንሰር እና ከሌሎች በሽታዎች የተፈወሱ ሰዎች እንዳሉ ዓይናችን እንዲሁም የሕክምና ማስረጃዎች ምስክሮች ናቸው፡፡ እግዚአብሔር ኃያል አምላክ፤ ሥራውም ድንቅ ነው፤ ተአምራትንም ያደርጋል፡፡ ነገር ግን ድኅነተ ሥጋንም ሆነ ድኅነተ ነፍስን ከእርሱ ለማግኘት እምነት ያስፈልጋል፡፡

“በመከራዬ ሳለሁ ወደ አምላኬ ወደ እግዚአብሔር ጮኽሁ” (ትንቢተ ዮናስ ፪፥፫)

በመጀመሪያ ራሳችን “በደለኛው እኔ ነኝ፤ ኃጢአተኛ ነኝ፤” ብለን አምነን መጸጸት አለብን፤ ጸጸትም ወደ ንስሓ ይመራናል፡፡ እግዚአብሔር ልብንና ኩላሊትን የሚመረምር አምላክ ነውና ውስጣችንን ከክፋት ሳናነጻ በሐሰተኛ አንደበት በንጸልይና ምሕረትን ብንለመን ልመናችንን አይቀበለንም፤ ሁሌም እርሱን በመፍራት መኖር እንዳለብን ቃሉ ይገልጻል፤ “ነገር ግን ቀኑን ሙሉ እግዚአብሔርን በመፍራት ኑር” (መጽሐፈ ምሳሌ ፳፫፥፲፯) እንደተባለው እግዚአብሔርን አምላክን በንጹሕ ልቡና ልንማጸን ይገባል፡፡