በሰሜን ሸዋ ሰላሌ ሀገረስብከት በኤጀሬ ወረዳ የቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን ተቃጠለ

 

በሕይወት  ሳልለው

በትናትናው ዕለት በሰሜን ሸዋ በሰላሌ ሀገረስብከት በኤጀሬ ወረዳ የቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን መቃጠሉን የወረዳው ፖሊስ አስታወቀ፡፡ ማንነታቸው ያልታወቁ ግለሰቦች የቤተ ክርስቲያኑን ጣሪያና መጋረጃ በማቃጠል ግድግዳውን ሙሉ ለሙሉ አፍርሰዋል፡፡ቁጥራቸው ባልተረጋገጠ ግለሰቦች ላይ ከባድ ጉዳት ሲያደርሱ የቅዱስ ዮሐንስ ቤተ ክርስቲያንንም እንደዘረፉ ፖሊስ አያይዞ አስታውቋል፡፡

በተጨማሪም እንደተገለጸው፤ በቃጠሎው ሳቢያ በወቅቱ ረብሻ ተነስቶ ነበር፡፡ ሌሎች ሶስት ቤተ ክርስቲያናት ላይም ተመሳሳይ ጥፋት ሊፈጽሙ የነበሩ ግለሰቦችን የአካባቢው ሰዎች ባደረገለት ትብብር ፖሊስ በቁጥጥር ስር ለማዋል ችሏል፡፡

እኛም በቀጣይ ዝርዝር መረጃ ሲደርሰን እንገልጻለን፡፡

«ጌታችን ኢየሱስ መፃጒዕን ፈወሰው» (ዮሐ.፭፥፮-፱)

በሕይወት  ሳልለው

«መፃጒዕ» ለ፴፰ ዓመት የአልጋ ቁራኛ የነበረና ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዕለተ ሰንበት የፈወሰው ሰው ነው፡፡ ጌታችንም ያን ሰው በአልጋ ተኝቶ ባየው ጊዜ መዳን እንደሚፈልግ አውቆ ጠየቀው፤ «ልትድን ትወዳለህን?»  መፃጒዕም «አዎን ጌታዬ ሆይ፤ነገር ግን ውኃው በተናወጠ ጊዜ ወደ መጠመቂያው የሚያወርደኝ ሰው የለኝም፤እኔ በምመጣበት ጊዜ ሌላው ቀድሞኝ ይወርዳል፤ አለው»፤ ጌታም «ተነሥና አልጋህን ተሸክመህ ሂድ» ባለው ጊዜ፤ ወዲያውኑም ድኖ አልጋውን ተሸክሞ ሄደ፤ያች ቀንም ሰንበት ነበረች፤ዮሐ.፭፥፮-፱

በኢየሩሳሌም የነበሩ አይሁድ ግን ጌታችን ያደረገለትን ተአምር ባለማመን፤ በሰንበት ቀን አልጋ ተሸክሞ መሄድ ዕለቱን ማርከስ እንደሆነ መፃጒዕን ለማሳመን ሞከሩ፤ ዕለተ ሰንበት ከዐሥርቱ ትእዛዛት አራተኛው «የሰንበትን ቀን ቅዱስ አድርገህ መጠበቅ እንዳለብህ አትርሳ፤»ይላልና ዘፀአት ፳፥፰-፲፡፡

እርሱ ግን ለ፴፰ ዓመት ከአልጋ ላይ መነሳት እንኳን ባልቻለበት ሁኔታ ያ ያዳነው ሰው አልጋውን ተሸክሞ እንዲሄድ ባዘዘው ጊዜ ያለ ምንም ጥርጣሬ፤ በእምነት ተፈውሶና ተነሥቶ መሸከም እንደቻለ ነገራቸው፡፡ እነርሱም በመጓጓት ያዳነውን ሰው ማንነት ቢጠይቁትም ሊነግራቸው አልቻለም ፤ጌታችን ከእነርሱ ተሰውሮባቸው ነበርና፡፡

በዚህች የተቀደሰች ሰንበት ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሌሎች ድውያንን እየፈወሰ፤ ጎባጣዎችን እያቀና ፣ ዕውራንን እያበራ፣ አንካሶችን እያዳነ፤ ለምፃሞችንም በመለኮታዊ ኃይሉ እያነጻ፤ልምሾዎችን እያዳነና አጋንንትን እያወጣ የዋለበት ዕለትም ነበር።

ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን አምስት ገበያ ሕዝብ ይከተለው እንደ ነበር በቅዱሳት መጻሕፍት በስፋት ተገልጾም እናገኛለን፡፡ «አምስት ሺህ ሰዎች ያህሉ ነበርና ለደቀ መዛሙርቱ በየክፍሉ አምሳ አምሳውን አስቀምጡአቸው አላቸው፤» (ሉቃ.፱፤፲፬) እንዲል፡፡ ሕዝቡም ጌታችንን  የተከተሉበት የተለያየ ዓላማና ምክንያት ነበራቸው፡፡ በትምህርቱ ተማርከው፣ ተአምራቱን ሰምተው፣ ከተያዙበት የአጋንንት ቁራኝነት ለመፈወስ፣ ረሀባቸውንና ጥማቸውን ለማስታገስ፣ መልኩን ለማየት፣ ጎዶሏቸውን ይሞላላቸው ዘንድ ይከተሉት ነበር፤እንደ መሻታቸውም ተፈጽሞላቸዋል፡፡

በዕለተ ሰንበትም ቤተ ክርስቲያን መሄድ ተገቢ ስለሆነ መፃጒዕ ከበሽታው በመዳኑና መራመድ በመቻሉ ወደዚያው አቀና፡፡ ጌታችንንም በቤተ መቅደስ ውስጥ ሲያስተምር አገኘው፤ ጌታም እንዲህ አለው «እነሆ ድነሃል፤ግን ከዚህ የባሰ እንዳያገኝህ ተጠንቀቅ»፤ዮሐ.፭፥፲፬፡፡ እርሱም የተባለውን በፀጋ ሰምቶ አይሁድ ካሉበት ስፍራ ሔደ፤ ባገኛቸውም ጊዜ ያዳነው ሰው ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መሆኑን ነገራቸው፡፡

አይሁድ ግን ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን በምቀኝነት ሊገድሉት ይፈልጉ ነበር፡፡ አንዱ ክሳቸው ሰንበትን ይሽራል የሚልም ስለነበር መፃጒዕ “በሰንበት የፈወሰኝ እሱ ነው” በማለት ቢመስክርም ለ፴፰ ዓመት ከተያዘበት ሥቃይ የገላገለውን አምላኩን በመካድ በጥፊ እስከ መምታት ደረሰ፡፡

ጻድቁ ኢዮብ «መንገዴን ፈጽሞ ዐወቀ፣ እንደ ወርቅም ፈተነኝ፣ እንደ ትእዛዙ እወጣለሁ፣ መንገዱንም ጠብቄያለሁ፣ ፈቀቅም አላልሁም» በማለት በመከራው ዘመን ለአምላኩ የነበረውን ፍጹም እምነት መሰክሯል፤ ኢዮ.፳፫፣፲፩፡፡

አምላካችን ያደረገለትን ድኅነትና ተአምር ምስክር መሆኑ ተገቢ ቢሆንም፤መፃጒዕ ግን ምላሹን በክሕደት ገለጸ፡፡ ጌታችን በዮሐንስ ወንጌል ፭፥፴፪ ላይ «ነገር ግን ለእኔ የሚመሰክር ሌላ ነው፤ ስለ እኔ የሚመሰክረው ምስክርነቱ እውነት እንደሆነ አውቃለሁ»፤ብሏል፡፡

ምርጥ ዕቃ የተሰኘው ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስንም ከክሕደት፣ አምላኩንም ከማሳደድ መልሶ የወንጌል ገበሬ ስላደረገው «የጽደቅ አክሊል ተዘጋጅቶልኛል» እንዲል (፪ኛ ጢሞ.፬፤፰)፤ እስከ ሞት ድረስ ታመነ፤ አንገቱንም ለሰይፍ አሳልፎ እስከ መስጠት አደረሰው፡፡ መፃጒዕ ግን ለክሕደት ራሱን አሳልፎ ሰጠ፣ ክሕደቱንም በጥፊ በመማታት ገለጸ፡፡

ቤተ ክርስቲያናችን ሁሉንም በሥርዓት የምታከናውን ስንዱ እመቤት ናትና በዐቢይ ጾም ከሚገኙት ሰንበታት ውስጥ ዐራተኛውን ሳምንት መፃጒዕ ብላ ሰይማዋለች፡፡ አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ብንወድቅ እንደሚያነሣን፣ ብንታመም እንደሚፈውሰን ለማስተማር እንዲሁም ደግሞ ከመፃጒዕ ሕይወት እንማር ዘንድ መታሰቢያውን አደረገች፡፡

«ዳግመኛ እንዳትበድል ተጠንቀቅ» ዮሐ.፭፤፲፬፤ እንዳለ ከኃጢአት ወደ ጽድቅ፣ ከሞት ወደ ሕይወት፣ እንሸጋገር ዘንድ፣ የአምላካችንን ቃል መፈጸም እንደሚገባን፣ እሰከ ሞትም መታመን እንዳለብን ያስተምረናል፡፡ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ቅፍርናሆም በገባ ጊዜ አንድ የመቶ አለቃ ወደ እርሱ መጥቶ «አቤቱ ልጄ ሽባ ሆኖ እጅግ እየተጨነቀ በቤት ተኝቷል፤» ብሎ ለመነው፤ ጌታችንም «እኔ መጥቼ እፈውሰዋለሁ» አለው፡፡ የመቶ አለቃውም «አቤቱ አንተ ከቤቴ ጣራ በታች ልትገባ አይገባኝም፡፡ ነገር ግን በቃልህ እዘዝ ልጄም ይድናል» አለ፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስም መቶ አለቃውን እጅግ አደነቀ፤ «እውነት እላችኋለሁ፣ በእስራኤል ሁሉ እንዲህ ያለ እምነት አላገኘሁም» ብሎ መሰከረለት፤ በመቶ አለቃውም እምነት ተደነቀ፡፡ «እንደ እምነትህ ይሁን» አለው፤ ከዚያም ሰዓት ጀምሮ ልጁ ዳነ፤ ማቴ.፰፤፭-፲፫፡፡

ይህ በእምነት ጽናት የተገለጸ ሕይወት ነው፡፡ መፃጒዕ ግን ያዳነውን አምላኩን በዓይኑ አይቶ፣ በእጁ ዳስሶ፣ ለ፴፰ ዓመታት የተኛበትንና የተሸከመውን አልጋ እንደገና እሱ ተሸክሞት እንዲሄድ ዕድሉን የሰጠውን አምላኩን ካደ፡፡ በእምነት የጸኑ፣ እንደ ቃሉም የተጓዙ፣ እስከ ሞትም የታመኑት ሲድኑ «ኑ የአባቴ ቡሩካን» ሲባሉ፤ በክህደት ያጠናቀቁትን ደግሞ «አላውቃችሁም» ተብለው ጥርስ ማፋጨት፣ እሳቱ ማያንቀላፋበት ጥልቅ እንዲወረወሩ ሁሉ፤ መፃጒዕ ዕድሉን አበላሸ፡፡ ጽድቅ በፊቱ ቀርቦለት መርገምን መረጠ፣ ከዘለዓለማዊ ሕይወት ይልቅ ዘለዓለማዊ ሞትን ምርጫው አደረገ፡፡

ምርጫችን የቱ ይሆን? በዐቢይ ጾም ወቅት ቤተ ክርስቲያናችን ሰንበታቱን ስያሜ ሰጥታ ስናከብር እንማርባቸው ዘንድ ነው፡፡ ጽድቅን በመሻት ሕይወታችን ከእግዚአብሔር ጋር እንድናደርግ፣ መንገዱንም እንከተል ዘንድ ነው፤ «ሕግህ ለእግሬ መብራት፣ ለመንገዴም ብርሃን ነው»፤ መዝ.፻፲፰፤፻፭ ላይ ተብሎ እንደተጻፈው፡፡

የክርስትና ሕይወት ፈተና የተሞላባት ናትና፤ በኑራችን ውስጥ የሚገጥመንን መሳናክልና ውጣ ውረድ ለመቋቋም ሁሌም በእምነትና በሃይማኖት መኖር ብቸኛ መፈትሔ ነው፡፡ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስም በዚህ ሳምንት ተአምራትን ከማድረጉ በላይ ለሕይወታችን ስንቅ የሚሆነን የወንጌል ቃል አስተምሮበታል፡፡ «ቃሉም የላችሁም፤በእናንተ ዘንድም አይኖርም፤እርሱ የላከውን አላመናችሁምና፤ መጻሕፍትን መርምሩ፤ በእነርሱም የዘላለም ሕይወትን የምታገኙ ይመስላችኋልና፤እነርሱም የእኔ ምስክር ናቸው»፤ ብሏል፤የሐ.፭፥፴፰፥፴፱፡፡

“እግዚአብሔርን የሚፈልግ ልብ ደስ ይበለው” እንደተባለው አምላካችን የጎደለንን እንዲሞላልን በጾም፣ በጸሎት፣ በፍጹም ትሕትና እና እምነት ልንተጋ ያስፈልጋል፤ መዝ.፻፭፣፫፤ ፩ኛ ዜና.፲፮፤፲፡፡ «ዳግመኛ እንዳትበድል ተጠንቀቅ»፤ እንደተባለውም መፃጒዕ የአምላካችንን ቃል ዘንግተን፣ የተደረገልንን መልካም ነገር ሁሉ በክፉ እንዳንለውጥ መጠንቀቅ ከእኛ ኦርቶዶክሳውያን ይጠበቃል፡፡ የአምላካችንን ቃል በሕይወታችን ዘመን ሁሉ በመፈጸም፣ እስከ መጨረሻው እንድንጸና አምላካችን ይርዳን፤ አሜን!

ምኲራብ

                                                                                                                ገብረእግዚአብሔር ኪደ

ምኲራብ ማለት ቤተ ጸሎት ማለት ሲሆን ናቡከደነፆር ቤተ መቅደስን አፍርሶ አይሁድን ወደ ባቢሎን ማርኮ ከወሰዳቸው በኋላ ሕገ ኦሪትን ለመማርና ለጸሎት በየቦታው የሰሩት ቤት ነው፡፡ በኢየሩሳሌም ብቻ ይገኝ በነበረው ቤተ መቅደስ ማንም እስራኤላዊ በዓመት ሦስት ጊዜ አምልኮውን መፈጸም ግዴታው የነበረ ሲሆን፥ በምኵራብ ግን በየዕለቱ እየተገናኙ ቅዱሳት መጻሕፍትን ያነቡ፤ ይተረጕሙና ይሰሙም ነበር (ሕዝ.፲፩፥፲፮፣ ሐዋ.፲፭፥፳፩)፡፡

ኢትዮጵያዊው ሊቅ ቅዱስ ያሬድ ፥ በልብ መታሰቡ፣ በቃል መነገሩ፣ በቅዱሳት መጻሕፍትም መዘከሩ ከፍ ከፍ ይበልና፤ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በምኵራበ አይሁድ እየተገኘ እንዳስተማረ፣ ድውያንን እንደ ፈወሰ፣ በዚያ ይነግዱ የነበሩትንም ማስወጣቱን አስመልክቶ በዐቢይ ጾም ከሚገኙት ሳምንታት መካከል ሦስተኛውን እሁድ ምኵራብ ብሎታል፡፡ “ኢየሱስ ወደ አይሁድ ምኵራብ ገባ፤ የሃይማኖትም ቃል አስተማረ፡፡ ከመሥዋዕት ይልቅ ምጽዋትን እወዳለሁ፡፡ የሰንበት ጌታዋ የምሕረት አባትዋ እኔ ነኝ አላቸው፡፡ የአባቴን ቤት የሸቀጥ ቦታ አታድርጉት፡፡ ቤቴ የጸሎት ቤት ተብሎ ይጠራል፡፡ ወደ ምኵራብ ገብቶ ተቈጣቸው፡፡ ዝም እንዲሉም ገሠጻቸው፡፡ እነርሱም ትምህርቱን፣ የቃሉን ግርማ፣ የአነጋገሩንም ጣዕም የንግግሩንም ርቱዕነት አደነቁ” በማለትም ይዘምራል – በጾመ ድጓው ! ከዚህም መረዳት እንደምንችለውም፡-

አንደኛ ቅዱስ ያሬድ ምኲራብን “የአይሁድ ምኵራብ” ብሎ እንደ ጠራው እንመለከታለን፡፡ በዕለቱ በሚነበበው ወንጌል ላይም፥ ወንጌላዊ ቅዱስ ዮሐንስ ቀርቦ የነበረውን ፋሲካ “የእግዚአብሔር ፋሲካ” (ዘጸ.፲፪፡፥፲፩) ማለትን ትቶ “የአይሁድ ፋሲካ” ብሎ እንደ ጠራው እናያለን (ዮሐ.፪፥፲፪)፡፡ ሊቁ ራሱ ቀጥሎ እንደ ነገረን፥ አይሁድ ከፈቃደ እግዚአብሔር ፈቀቅ ብለው እንደ ነበረ፥ ጌታችን ግን የሰው ሥርዓትንና ወግን ሳይኾን “የሃይማኖትን ቃል” ወይም ወንጌልን እንዳስተማራቸው እንገነዘባለን፡፡

ምንም እንኳን ከላይ እንደ ተናገርነው አይሁድ በዚያ በምኵራብ በየዕለቱ ቅዱሳት መጻሕፍትን ያነበቡ የነበሩ ቢኾኑም፥ በገጸ ንባባቸው ብቻ ድኅነት የሚገኝ ይመስላቸው ስለ ነበረ ጌታችን “የሃይማኖትን ቃል” አስተማራቸው (ዮሐ.፭፡፥፴፱)፡፡ ዳሩ ግን ምን ያደርጋል፤ አብዛኞቹ ይህን አልተቀበሉትም፡፡ ይህን የተመለከተው አፈ ጳዝዮን ዮሐንስ አፈወርቅ በልደት ድርሳኑ ላይ እንዲህ አለ፡- “በአይሁድ ዘንድ ድንግል እንድትፀንስ ተነገረ፤ በእኛ ዘንድ ግን እውነት ኾነ፡፡ ትንቢት ለምኵራብ ሃይማኖት ለቤተ ክርስቲያን ነውና፡፡ ያቺ ትንቢትን ገንዘብ አደረገች፤ ይህችም ሃይማኖትን ገንዘብ አደረገች፡፡ ምኵራብ ምሳሌን ሰጠች፤ ቤተ ክርስቲያን አመነችበት፡፡ ምኵራብ ትንቢት አስገኘች፤ ቤተ ክርስቲያን ተቀበለችው፡፡ ምኵራብ ትንቢቱን በምሳሌ አስተማረች፤ ቤተ ክርስቲያን በሃይማኖት ጸናችበት፥ ረብሕ ጥቅም አደረገችው፡፡ ከዚያም የወይን ሐረግ (መስቀል) ተተከለ፤ በእኛ ዘንድ ግን የጽድቅ ፍሬ ተገኘ፡፡ ያቺ ወይንን በዐውድማ ረገጠች፤ አሕዛብ የምሥጢሩን ገፈታ ጠጡ፡፡ ያቺ የስንዴ ቅንጣትን ዘራች፤ አሕዛብ በሃይማኖት ሰበሰቡት፡፡ አሕዛብ ጽጌረዳን በቸርነቱ ሰበሰቡ (ሃይማኖትን ገንዘብ አደረጉ)፤ እሾኹ ግን በአይሁድ ዘንድ ቀረ፡፡ ይኸውም ክሕደት ኑፋቄ ነው፡፡ ትንሽ ወፍ ሰነፎች ተቀምጠው  ሳሉ  ጥላውን  ጥሎባቸው  ይኼዳል፡፡  አይሁድም በብራና የተጻፈውን መጽሐፍ ተረጎሙ፤ አሕዛብ ግን ምሥጢሩን ተረዱ” እያለ እንዳመሠጠረው (ሃይማኖተ አበው ዘዮሐ.አፈ.፣ ፷፮፥፳፩-፳፬)፡፡

ሁለተኛ ቅዱስ ያሬድ “እግዚአብሔር ከመሥዋዕት ይልቅ ምጽዋትን” እንደሚወድ ነግሮናል፡፡ ይኸውም አብዛኛው አይሁድ ጌታችን እንደ ተናገረ ከአፍ ብቻ ሃይማኖታውያን የነበሩ በውስጣቸው ግን እንዳልነበሩ የሚያመለክት ነው (ማቴ.፳፫፡፳፯)፡፡ እግዚአብሔር ግን የሚፈልገው የልብ መታደስን፣ የሕይወት መዓዛ መለወጥን፥ በአጭሩ እግዚአብሔር መምሰልን ነው፡፡ ስለዚህ ጌታችን “የምሕረት አባትዋ እኔ ነኝ” እያለ ይህን ያስተምራቸው ዘንድ ወደ “አይሁድ ምኵራብ” እንደ ገባ እንመለከታለን፡፡ ምሕረት በሦስት መልኩ የምትፈጸም ስትሆን እነርሱም ምሕረት ሥጋዊ፣ ምሕረት መንፈሳዊና ምሕረት ነፍሳዊ ይባላሉ፡፡ ምሕረት ሥጋዊ የሚባለው ቀዶ ማልበስ ቈርሶ ማጉረስ ነው፡፡ ምሕረት መንፈሳዊም መክሮ አስተምሮ ክፉን ምግባር አስትቶ በጎ ምግባር ማሠራት ነው፡፡ ምሕረት ነፍሳዊ ደግሞ ክፉን ሃይማኖት አስትቶ በጎ ሃይማኖት ማስያዝ ነው፡፡ ስለዚህ እግዚአብሔር አምላካችን ከየትኛውም ዓይነት መሥዋዕት ይልቅ ደስ ብሎ የሚቀበለው ይህን እንደ ሆነ ከዚህ እንማራለን፡፡

ሦስተኛ፥ ቤተ መቅደሱ ቤተ ምሥያጥ ሆኖ እንደ ነበረ ሊቁ ቅዱስ ያሬድ ነግሮናል፡፡ ቤተ መቅደሱ ከተመሠረተበት ዓላማ ርቆ፣ የገበያና የንግድ ቦታ ሆኖ፣ “ተዉ” ብሎ የሚቈጣ ሰው ጠፍቶ፣ “ርግብ ሻጮች” በዝተው እንደ ነበረ በዕለቱ ከሚነበበው ወንጌልም እንመለከታለን (ዮሐ.፪፥፡፲፬)፡፡ ስለዚህ ጌታችን ይህን ያደርጉ የነበሩትን ሲገለባብጥባቸው፥ አንደኛ- ዓላማቸውን ስለ መሳታቸው ሲነግራቸው፣ ሁለተኛ- መሥዋዕተ ኦሪትን ሲያሳልፍ፣ ሦስተኛ- ዛሬም ጭምር ቅዱስ ሥጋውና ክቡር ደሙ በሚፈተትበት ሥፍራ ይህን የሚያደርጉትን “ከቶ አላውቃችሁም” እንደሚላቸው የሚያስገነዝብ ነው፡፡ ዳግመኛም “ርግብ ሻጮች” የተባሉት በተጠመቁ ጊዜም ሆነ ከዚያ በኋላ የተቀበሉትን መንፈሳዊ ሀብት ለምድራዊ ሥራ ለኃጢአት ንግድ የሚጠቀሙበትን “ከእኔ ወግዱ” እያለ በፍርድ ቃሉ ጅራፍ ወደ ውጭ ጨለማ እንደሚያወጣቸው የሚያስተምር ነው፡፡

ቅዱስ ያሬድ ሌላው የነገረንና በአራተኛ ደረጃ ልናየው የምንችለው፥ ክብር ይግባውና ጌታችን ሲያስተምራቸው ሁሉም እንደ ተደነቁ እንመለከታለን፡፡ ይኸውም እንደ ነቢያት “እግዚአብሔር እንዲህ አለ”፣ “ሙሴ እንዳዘዘ”፣ “ሳሙኤል እንደ ተናገረ” በማለት ሳይሆን እንደ ባለ ሥልጣን እንደ ሠራዔ ሕግ “እኔ ግን እላችኋለሁ” እያለ ያስተምራቸው ስለ ነበረ ነው፡፡ ይህም የባሕርይ አምላክነቱን የሚገልፅ ነው፡፡

እግዚአብሔርን የምትወዱት፥ ይልቁንም እግዚአብሔር አብልጦ የሚወድዳችሁ ሆይ ! እንግዲያውስ እኛም እንፍራ፡፡ ከፈቃደ እግዚአብሔር ፈቀቅ ብለን መቅደስ ሰውነታችን የእግዚአብሔር ሳይሆን “የአይሁድ ምኵራብ” እንዳይባል እንፍራ፡፡ ደገኛ ዘር ይኸውም የወንጌል ዘር ተዘርቶብን ሳለ የክፋት ፍሬ ተገኝቶብን ያን ጊዜ እንዳናፍር አሁን እንፍራ፡፡ ምሕረት ሥጋዊን፣ ምሕረት መንፈሳዊንና ምሕረት ነፍሳዊን በቃል ያይደለ፤ እንደ ዓቅማችን በተግባር እንፈጽም፡፡ በእውነት ያለ ሐሰት ብርሃናችን በሰዎች ሁሉ ፊት በርቶ በእኛ ምክንያት እግዚአብሔር የሚከብረው፥ እግዚአብሔርም እኛን የሚያከብረን ያን ጊዜ ነውና፡፡ ቤተ መቅደሱንና ቤተ መቅደስ ሰውነታችን ቤተ ምሥያጠ ኃጢአት አድርገነው እንደ ኾነ ወይም እንዳልኾነ ቆም ብለን እንይ፡፡ ርግብ ሻጮች ሆነን እንዳንገኝና ሥርየት የሌለው ኃጢአት እንዳያገኘን እንፍራ፡፡ ይህን ያደረግን እንደ ሆነም ጌታችን ዳግም በመጣ ጊዜ “ኑ እናንተ የአባቴ ብሩካን” ከሚላቸው ጋር አንድ እንሆናለን፡፡ዛሬም ዘወትርም እስከ ዘለዓለሙ ድረስ ክብርና ጌትነት የባሕርይ ገንዘቡ የሚሆን ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በለጋስነቱና ሰውን በመውደዱ ይህን ለማግኘት የበቃን ያድርገን፥ አሜን !

የኀዘን መግለጫ

“ብንኖረም ብንሞትም ለእግዚአብሔር ነን”፤ሮሜ ፲፬፥፰

እሁድ መጋቢት ፩ ቀን ፳፻፲፩ ዓ.ም. ከጠዋቱ ፪፡፵፰ ደቂቃ ከአዲስ አበባ ቦሌ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ ተነስቶ ወደ ኬንያ ናይሮቢ በመጓዝ ላይ የነበረው ET ፫፻፪ የመንገዶኞች አውሮፕላን ከ፮ ደቂቃ በረራ በኋላ ከአዲስ አበባ በቅርብ ርቀት ከምትገኘው ደብረዘይት ወድቆ መከስከሱ ይታወቃል፡፡በመሆኑም ፻፵፱ መንገደኞች ፰ የበረራ አስተናጋጆችን ጨምሮ በድምሩ ፻፶፯ ሰዎች በሙሉ የአደጋው ሰለባ ሆነዋል፡፡ ከእነዚህ ውስጥ ፲፯ ያህሉ ኢትዮጵያውያን ሲሆኑ ሌሎቹ ደግሞ የ፴፫ ሀገራት ዜጎች መሆናቸው ታውቋል፡፡ በዚህ ድንገተኛ ክስተት ለተጎዱ መላው ወገኖቻችን፤ ኢትዮጵያውያንንና ቤተሰቦቻቸውን ጨምሮ እግዚአብሔር አምላክ ነፍሳቸውን በአጸደ ገነት ዕቅፍ ያሳርፍልን ፤ ለቤተሰቦቻቸውም መጽናናትን ይሰጥልን ዘንድ እንጸልያለን፡፡

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በሰንበት ትምህርት ቤቶች ማደራጃ መምሪያ  ማኅበረ ቅዱሳን

‹‹እንደሚንሿሿ ጸናጽል ሆኛለሁ›› (፩ኛቆሮ.፲፫፥፩)

                                                                                                 ዲያቆን ዮሴፍ በቀለ 

ጸናጽል ድምፁ መልካም የሆነ የምስጋና መሳርያ በመሆኑ ከቀደሙት ሌዋውያን አሁን እስካሉት የሐዲስ ኪዳን ቤተ መቅደስ መዘምራን ፣ ከቀደመው የሙሴ ድንኳን ዛሬ ቤተ ክርስቲያን ድረስ በእግዚአብሔር ፊት ይዘነው የምንቆመው መሳርያ ነው፡፡ ምስጋናችንም ሆነ መዝሙራችን ያለከበሮና ጸናጽል ምን ውበት ሊኖረው ይችላል ብለን እንጀምራለን? አንጀምረውም፡፡ የሊቃውንቱ መዳፍ ያለ ጸናጽል አይንቀሳቀስም፣ ቅኔ ማኅሌቱም ያለ ከበሮ አይደምቅም ፤ እንደ ጾመ ኢየሱስ ያለ ቀን ካልገጠመው በስተቀር ቅኔ ማኅሌት ከነዚህ  ነገሮች አይለይም፤ ይገርማል! ዳሩ ግን አንድም ቀን ቢሆን በዚህ ሁሉ የአገልግሎት ዘመናቸው ወደ ቤተ መቅደስ ገብተው ለሥጋውና ለደሙ ክብር በሚደረገው አገልግሎት ተሳትፈው አይተናቸው አናውቅም፤ ጥንትም ሆነ ዛሬ አገልግሎታቸው ከውጭ ብቻ ነው፡፡

ቅዱስ ጳውሎስ የባዶ ሕይወት ተምሳሌት አድርጎ ተጠቅሞበታል፤ “የሰውን ሁሉ ልሳን ባውቅ፣ በመላእክትም ቋንቋ ብናገር ፍቅር ግን ከሌለኝ እንደሚጮኽ ነሐስ፤ እንደሚንሿሿም ጸናጽል ነኝ” (፩ቆሮ ፲፫÷፩) ይላል፡፡ ይህን ስመለከት ከልጅነቴ ጀምሮ በቤተ መቅደሱ ያደገች ነፍሴን አሰብኩና እስራኤል ሲማረኩ “ጽዮንን ባሰብናት ጊዜ አለቀስን” ብለው እንደተናገሩ እኔም ለተማረከችውና ባዶዋን ለቀረችው ጽዮን ሰውነቴ አለቀስኩላት፤ ከኔ በቀር ጽዮን ሰውነቴ ባለተስፋ ምድር መሆኗን ማን ያውቅላታል? የተገባላትንስ ቃል ኪዳን ከኔ በቀር ማን ያውቅላታል?

ስለዚህ ደጋግሜ በባቢሎን ወንዞች አጠገብ ሆኜ ምርር ብየ አለቀስኩላት፤ ደግሜ ደጋግሜም እንዲህ አልኳት፤ እንደሚጮኽ ነሐስ፣ እንደ ሚንሿሿም  ጸናጽል ነሽ አልኳት፡፡ እስኪ አስቡት! ያለኔ ማኅሌቱ አይጀመር፣ ዝማሬው አይደምቅ ፣ የሊቃውንቱ ጉሮሮ አይከፈት፣ ሽብሻቧቸው አያምርበት ፣ እጃቸው ያለኔ አይንቀሳቀስ፣ ቅኔው አይጸፋ፡፡ እስኪ ንገሩኝ! ምኑ ነው ያለኔ የሚያምረው፤ በየትኛው አገልግሎት ነው እኔ የማልገባው፤ የትኛውስ ሊቅ ነው ያለኔ በእግዚአብሔር ምስጋና ላይ የተገኘው ፤ ጥንትም ሆነ ዛሬ እኔ ለዚች ቤተ መቅደስ አገልግሎት አስፈልጋለሁ ፡፡

ያለበለዚያማ ማኅሌቱ ምን ውበት ሊኖረው፤ ማንስ ነው እኔ በሌለሁበት ያለ እንቅልፍ የሚያገለግለው፤ ከከበሮው ተስማምቶ በሚወጣው መልካሙ ድምፄ ብዙዎቹ ይመሰጣሉ፣ የድምፄን ውበት በውስጠኛው ጆሯቸው እየሰሙ እንዲህ አሳምሮ የፈጠረኝን “ድምፁ መልካም በሆነ ጸናጽል አመስግኑ” እያሉ ያመሰግናሉ፡፡ የድምፄን መልካምነት ብቻ እየተመለከቱ ወይ መታደል ብለው ያደንቃሉ፤ እኔ እስከማዜም ድረስ በጉጉት ይጠባባቃሉ ፤ሰው ሲዳር፤  ሲሞትም ሆነ ሲሾም ያለኔ ምኑ ያምራል፤ አምጡት፣ አምጡት ይባላል፡፡

ይህን ሁሉ ክብሬን አየሁና በሰዎች መካከል በኩራት ተቀምጨ ሳለሁ ከዕለታት አንድ ቀን የሥጋየን መጋረጃ ግልጥ አደረግሁና ነፍሴን ተመለከትኋት፤ ትጮኻለች! አዳመጥኳት፤ ላደርገው የሚገባኝን እንኳን ያለደረግሁ፤ የማልጠቅም ባሪያ ነኝ፡፡ እንደሚጮኽ ነሐስ፣ እንደሚንሿሿም ጸናጽል ሆኛለሁ እያለች ታንጎራጉራለች፡፡

የሚጎሰመው ነጋሪት፣ የሚመታው ከበሮ፣ የሚንሿሿው ጸናጽል ለራሳቸው ምን ተጠቅመዋል? ከነሱ በኋላ እየተነሣ ስንት ትውልድ ነው የእግዚአብሔርን መንግሥት የወረሰ፣ ከተስፋው  የደረሰ፤ ሌላው በነሱ ተጠቅሞ አድማሳትን በቅድስናው ሲያካልል፣ መላእክትን ሲያክል፤ እነሱ ግን አሁንም ምድራውያን ናቸው፡፡ በዚህኛው ትውልድም አልተለወጡም፤ ጌታ እስኪመጣ ከዚህ ዓይነት ሕይወት የሚወጡም አይመስሉም፤

እኔም እንደነሱ ነኝ! ቃሉን እሰብካለሁ፣ ዝማሬውን እዘምራለሁ፣መወድሱን እቀኛለሁ፣ሰዓታቱን አቆማለሁ፤ ኪዳኑን አደርሳለሁ፤ መጽሐፍ ቅዱስን ከዳር እስከዳር አንብቤአለሁ፡፡ ዳሩ ግን መች እኖርበታለሁ ፤ ሰዎቹ ከአፌ የሚወጣውን ቃሉን እየሰሙ የሕይወቴ ነጸብራቅ እየመሰላቸው ይገረማሉ፤ እንደኔ ለመሆን ይቀናሉ፤ እኔ ግን ሳላስበው እንደሚጮኽ ነሐስ፣ እንደሚንሿሿም ጸናጽል ሆኛለሁ፡፡  እጮኻለሁ እንጅ  ለምን እንደምጮኽ እንኳን አላውቅም፤ በምጮኸው ጩኸት ከቶ አልለወጥም፤ ከኔ በኋላ እየተነሱ ብዙዎቹ ከምሥራቅና ከምዕራብ እየመጡ ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ገብተዋል ፤ ከኔ በኋላ ቃሉን የሰሙት በቃሉ ተለውጠው ንስሓ ገብተዋል፡፡ እኔ ግን ዛሬም ሳያውቅ እንደሚጮሕ ነሐስ፣ ሳይወድ እንደሚንሿሿውም ጸናጽል ሆኛለሁ፡፡

የምጮኸው ገብቶኝ ቢሆንኮ ከኔ የሚቀድም ማንም አልነበረም፡፡ ነገር ግን ይህ እንዳይሆን ሕይወት የሌለኝ ቆርቆሮ ነኝ፤ ድምፄ መልካም ነው፣ ትጋቴ ግሩም ነው፡፡ ከምስጋናው ጋር መስማማቴ፣ በሁሉም እጅ መግባቴ መልካም ነበር፤ ሆኖም ፍቅር የለኝምና ምን ይሆናል፡፡  ሥጋየን ለሰማይ አዕዋፍ ብሰጥ ፣ያለኝንም ለድሆች ባካፍል ፣ የድሆች አባት ብባል ፣አጥንቴም እስኪታይ ብጾም ብጸልይ ፍቅር ግን ከሌለኝ ያው እንደሚጮኸው ነሐስ እንደሚንሿሿውም ጸናጽል መሆኔ አይደለ? ሥጋውን ደሙን ካልተቀበልኩ የኔ መጮኽ ምን ሊጠቅም ! ለካ ለሥጋውና ለደሙ የሚያስፈልገው በበጎ ዝምታ ዝም ያላለው እንደኔ የሚንሿሿው ጸናጽል አይደለም ብላ ነፍሴ ስታለቅስ እኔንም አስለቀሰችኝ ፡፡

ኦ!አምላኬ ጸናጽልነቴን ለውጥልኝ፣ነሐስነቴን አርቅልኝ!

  ‹‹እኔ ቅዱስ ነኝና ቅዱሳን ሁኑ›› (ዘሌ.፲፱፥፪)

 

መምህር ኃይለሚካኤል ብርሀኑ

የዐቢይ ጾም ሁለተኛው ሳምንት (ሰንበት) ቅድስት ይባላል፡፡ ስያሜው የቅዱስ ያሬድ ሲሆን የመዝሙሩ ርዕስ የጾመ ድጓው መክፈያ ሆኖ የሚጠራበት ስም ነው፡፡ ከቅድስት ሰኞ ጀምሮ ጾመ ኢየሱስ ይባላል፡፡ በዚህ ሳምንትም ስለ እግዚአብሔር ቅድስና የሚያነሱ መዝሙራት ይቀርባሉ፤ እኛም እግዚአብሔርን መቀደስ (ማመስገን) እንዳለብን የሚገልጹ ምንባባት ይነበባሉ፣ትምህርት ይሰጣል፡፡

እግዚአብሔር ቅዱስ ነው፤ ቅድስናውም ከማንም ያላገኘው የባሕርይ ገንዘቡ ነው፡፡ ይህም ማለት እግዚአብሔር በባሕርዩ ቅዱስ ነው፡፡ ቅዱሳን መላእክት፣ቅዱሳን ጻድቃን፣ቅዱሳን ሐዋርያት፣ ቅዱሳን ሰማዕታት፣ ቅዱሳን አበው፤ ቅዱሳት አንስት፤ ቅዱሳን ሊቃውንት፣ቅዱሳን ጳጳሳት፣ ቅዱሳን መነኮሳት፣ ቅድስናን ያገኙት በባሕርዩ ቅዱስ ከሆነው ከአምላካችን ከቅዱስ እግዚአብሔር ነው፡፡

ቅዱስ የሚለውን ቃል ስንመለከት ምስጉን፣ክቡር፣ንጹሕ፣ የተለየ የሚል ትርጉም ይሰጣል፡፡ እግዚአብሔር ቅዱስ ነው ስንልም ቅዱስ ቅዱስ ቅዱስ ተብሎ የሚመሰገን፤ የቅድስና ምንጭ በቅድስናው የተቀደሰ፤ ቅዱሳንን የሚቀድስ ቅዱሰ ቅዱሳን ነው፤ኢሳ (፮፥፩)፡፡

ፍጡራንስ ቅዱስ ተብለው መጠራታቸው እንዴት ነው? ብለን ብንጠይቅ  እግዚአብሔር ከፍጥረቱ ሁሉ የተለየ ቅዱስ ስለሆነ ወደ እርሱ የተጠሩና የመጡ ለእርሱ ክብር የተለዩ ቅዱሳን ይባላሉ፡፡ ይህም ማለት  ቅድስናን በጸጋ አግኝተው እንዲያጌጡበት የተጠሩት ሰውና መላእክት ሲሆኑ ለእግዚአብሔር አገልግሎት የዋሉ የመቅደሱ ዕቃዎች አልባሳቶች በአጠቃላይ ንዋያተ ቅዱሳቱ ቅዱስ ተብለው ይጠራሉ፡፡ እኛም እግዚአብሔር በክርስቶስ ኢየሱስ ወደ መንግሥቱ ሲጠራንና ልጅነትን ሲሰጠን ለእግዚአብሔር ተለይተን የመንፈስ ቅዱስ ማደሪያዎች እንሆናለንና፤ቅዱሳን ተብለን እንጠራለን፡፡

 እግዚአብሔር ‹‹እኔ ቅዱስ ነኝና ቅዱሳን ሁኑ›› ብሎ እንደተናገረው ንጽሕናን ቅድስናን በጸጋ እግዚአብሔር ገንዘብ ያደረጉ ሰዎች ቅዱሳን ይባላሉ፡፡ እንዲሁም ሰውና መላእክት የሚገናኙባት፣ድኅነተ ሥጋ ድኅነተ ነፍስን የምታስገኝ ቤተ ክርስቲያን ቅድስት ናት ስንል ለእግዚአብሔር አምልኮ የተለየች ክብርትና ንጽሕት ናት ማለት ነው፡፡ ክርስቶስ ለራሱ ትሆን ዘንድ የለያት ነፍሱን ስለ እርስዋ አሳልፎ እስከ መስጠት የወደዳት ፣ በደሙ የዋጃትና በቃሉ ያነጻት የክርስቶስ አካሉ ቤተ ክርስቲያን ንጽሕት ናትና ክርስቶስ ክቡር እንደሆነ ክብርት፣ ንጹሐ ባሕርይ እንደሆነ ንጽሕት፣ ያለ ነውርና ያለ ነቀፋ የኖረች የክርስቶስ ሙሽራ ናት  ማለታችን ነው፡፡

ፍጡራን የቅድስናቸው ምንጭ ቅዱስ እግዚአብሔር ነው፤ ከላይ እንዳየነው እርሱ የቅዱሳን ቅዱስ ነውና፡፡ በሙሴ መጽሐፍ እንደ ተጠቀሰው እስራኤልን እግዚአብሔር ከግብጻውያን እጅ እንዳዳናቸውና ግብጻውያንም እንደሞቱ በባሕር ዳር አዩ፡፡ ቅዱስ እግዚአብሔር በግብጻውያን ላይ ያደረጋትን  ታላቂቱን እጅ አዩ፡፡ ሕዝቡም እግዚአብሔርን ፈሩ፤ በእግዚአብሔርም አመኑ፤ ባሪያውንም ሙሴን አከበሩ፡፡ በአንድነትም በዝማሬ እግዚአብሔርን አመሰገኑ፤ በዝማሬያቸውም የእግዚአብሔርን ቅድስና እንዲህ ሲሉ ገለጹ ‹‹አቤቱ በአማልክት መካከል አንተን የሚመስል ማን ነው? በቅዱሳንም ዘንድ እንደ አንተ የከበረ ማን ነው? በምስጋና የተደነቅህ ነህ፤ ድንቅንም የምታደርግ ነህ፤ ቀኝህን ዘረጋህ ምድርም ዋጠቻቸው›› (ዘፀ ፲፭፥፲፩) በማለት መስክረዋል፡፡

አምላከ አማልክት፤ እግዚአ አጋዕዝት ጌታ በቅድስና የከበረ ነው፡፡ ምስጋናውም ቅዱስ እንደሆነ ያየውና የሰማው ኢሳይያስ ስሙን ቅዱስ ብሎ ጠርቶታል፡፡ ‹‹እንግዲህ እተካከለው ዘንድ በማን መሰላችሁኝ?›› (ኢሳ ፵፥፳፭) ይላል ቅዱሱ እግዚአብሔር፡፡

  ቅዱስ ዮሐንስም በራእዩ እንደተናገው ‹‹አንተ ብቻ ቅዱስ ነህ›› ብለው መላእክት በሰማይ በባሪያው በሙሴ መዝሙር እንደሚያመሰግኑት ጽፎልናል፡፡ ‹‹ሁሉን የምትገዛ ጌታ አምላክ ሆይ! ሥራህ ታላቅና ድንቅ ነው፤ የአሕዛብ ንጉሥ ሆይ መንገድህ ጻድቅና እውነት ነው፤ ጌታ ሆይ አንተን የማይፈራና ስምህን የማያከብር ማን ነው? አንተ ብቻ ቅዱስ ነህና፡፡  በአሕዛብ ሁሉ ላይ ሥልጣን ያለህ አንተ ነህ፤ አቤቱ ፍጥረትህ ሁሉ በፊትህ ይሰግዳሉ፤ ፍርድህ ተገልጦአልና››፤ (ራእ.፲፭፥፫) ይላል፡፡

በአፈ መላእክት ቅዱስ ተብሎ የሚጠራውና የሚቀደሰው በልሳነ ሰብእም ይትቀደስ ስምከ (ስምህ ይቀደስ) እየተባለ የሚጠራ ስሙ ቅዱስ ነው፡፡ ነቢዩ ኢሳይያስ ቅዱሳን መላእክት ቅዱስ ስሙን እየጠሩ እንደሚያመሰግኑት ሲመሰክር “አንዱም ለአንዱ ቅዱስ ቅዱስ ቅዱስ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር ምድር ሁሉ ከክብሩ ተሞልታለች እያለ ይጮኽ ነበር” ሲል ገልጾታል(ኢሳ.፮፥፫)፡፡

ቅዱሱን የወለደች እመ አምላክ ድንግል ማርያምም “ወቅዱስ ስሙ፤ስሙ ቅዱስ ነው ብላ መስክራለች” (ሉቃ.፩፥፶)፡፡ ቅዱስ እግዚአብሔር ስለ ራሱ ቅድስና ሲናገርም “እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ ቅዱስ ነኝና እናንተም ቅዱሳን ሁኑ” (ዘሌ.፲፱፥፪) ብሏል፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስም በመልእክቱ የእግዚአብሔር ፈቃድ በእርሱ ቅድስና እንድንቀደስ እንደሆነ ሲገልጽ “የጠራችሁ ቅዱስ እንደሆነ እንዲሁ እናንተም በአካሄዳችሁ ሁሉ ቅዱሳን ሁኑ” ይላል (፩፥፲፭)፡፡

የጠራን እግዚአብሔር ቅዱስ እንደሆነ በቅድስና መኖር ያስፈልጋል፡፡ ከእግዚአብሔር የተወለድንበት ምሥጢረ ጥምቀት የቅድስናችን መጀመሪያ ስለ ሆነ የመንፈስ ቅዱስ ቤት ለመሆን ተሠራን፡፡ ነገር ግን ከቅድስና የሚያጎድሉንን ክፉ ተግባራት ስንፈጽም እንበድላለንና በጸጋ ያገኘነውን ሀብተ መንፈስ ቅዱስ እናጣለን፡፡ ስለዚህ እንዳንበድልና ቅድስናን እንዳናጣ ተግተን በእውነት እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ መኖር ያስፈልጋል፡፡

ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለምን ጾመ?

ዲያቆን ዮሴፍ በቀለ  

በገዳም ቆሮንቶስ ፵ ቀንና ለሊት የጾመው

ሀ/ ሕግን ሊፈጽም

የሕግ ሁሉ ባለቤት የሆነው አምላካችን እግዚአብሔር ጾምን ለአዳም የሰጠው ጥንታዊው ሕግ ከእግዚአብሔር ዘንድ ሰማያዊ ዋጋ የሚያገኝበት ጸንቶ እንዲቆም የሚያስችለውና ከክፉ የሚጠብቀው መንፈሳዊ መከላከያው መድኃኒት ሆኖ የተሰጠው ፤  ኦሪትም የተሰራችው በጾም ነበር፡፡ አባታችን ሙሴ ኦሪት ዘዳግም  ፱፥፱ ላይ “ሁለቱን የድንጋይ ጽላት እግዚአብሔር ከእናንተ ጋር የተማማለባቸውን የቃልኪዳን ጽላት እቀበል ዘንድ ወደ ተራራ በወጣሁ ጊዜ በተራራውም አርባ ቀንና አርባ ለሊት ተቀምጬ ነበር፤ እንጀራ አልበላሁም፤ ውሃም አልጠጣሁም”፤ አለ፡፡ በዚህም ሙሴ የኦሪትን ሕግ ተቀበለ፤ እናም ሕግን ለመቀበል በቅድሚያ መጾም ያስፈልጋል ፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ ሕግን ሲፈጽም በቅድሚያ የወንጌል መጀመሪያ ያደረገው ጾምን ነው፤ የማቴዎስ ወንጌል ፬፥፩-፲፩ ላይ “እኔ ሕግ ልሽር ሳይሆን ልፈጽም ወደ ምድር ወርጃለሁ”፤ አለ፡፡

ለ/ዕዳችንን ሊከፍል (ካሳ ሊሆነን)፤

እግዚአብሔር ለአባታችን አዳም “ይህንን ዕፀ በለስ አትብላ፤ የበላህ እንደሆነ ትሞታለህ”፤ ብሎት የነበረውን ትእዛዝ ተላልፎ በራሱ ፍቃዱ ተጠቅሞ የተከለከለችዋን ፍሬ በላ፤ ሕግንም ጣሰ፡፡ ስለዚህ አዳም በመብላት ያመጣውን ሞት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከተጠመቀ በኋላ  ለ፵ ቀን ለ፵ ለሊት ባለመብላት ባለመጠጣት ዕዳችንን ከፈለ፡፡ ደሙን አፍሶ፤ ሥጋውን ቆርሶ፤ በቀራንዮ አደባባይ ተሰቅሎ አዳምን ከሞት ወደ ሕይወት፤ ከሲኦል ወደ ገነት መለሰው፡፡

ሐ/ለአርያነት፤ የመንፈሳዊና የበጎ ምግባር ሁሉ መነሻው ጾም ነው፡፡  የዕለተ ዐርብ የማዳኑን ሥራ በጾም ጀመረ፤ የወንጌል ሥራ መጀመሪያም አደረጋት፡፡ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዚህ ዓለም በዮርዳኖስ ከተጠመቀ በኋላ  ሥራውን በጾም እንደ ጀመረ ሐዋርያትም ስለተረዱ እርሱን በመምሰል ሥራቸውን በጾም ጀመሩት፡፡ አባቶቻችን ጾምን የትምህርት መጀመሪያ አደረጓት፤ በዚህም ለዘለዓለም ከእግዚአብሔር ጋር በመንግሥቱ እንዲኖሩ በር ስለከፈተላቸው ለአርአያነት ነው ብለን ተቀበልነው፡፡ ሆኖም ሳይጾም ጹሙ አላለንም፤ በምድር እስካለንና እርሱ አርአያ እስከሆነን ድረስ  ከመዓትና ከዘላለም እሳት ለመዳን በጾምና ጸሎት ልንኖር ያስፈልጋል፡፡፡

መ/ሊያስተምረን፤ የተፈቀደውን እየፈጸምን፤ የተከለከልነውን በመተው ሕግ እያከበርን በትምህርተ ወንጌል ድኅነትን እንድናገኝና የነፍሳችን ቁስል እንዲፈወስ ለክርስቶስ ሕይወታችንን መስጠት አለብን፡፡ እንዲሁም ለመጾም ድፍረት ያላት ነፍስ ቀጣይነት ባለው መንፈሳዊ ልምምድ ራስን መግዛት ለሥጋ ፈቃድ የሚያስፈልገውን ምግብና መጠጥ በመተው የሥጋ ፈቃድን ድል በመንሣት ለነፍስ ፈቃድ ማስገዛት ይቻላል ፡፡ ይህቺ ነፍስ ክርስቶስ ያስተማራትን ከተገበረች የሚመጣባትን ከባድ ነገር ሁሉ እስራቱንና ግርፋትን መቋቋም ይቻላታል፡፡ ስለዚህ መጾም በኃጢአታችን እንድንጸጸትና ወደ አግዚአብሔር እንድንመለስ (እንድንቀርብ )ብቻ ሳይሆን ለዘለዓለም ከእግዚአብሔር ጋር ለመኖር ያለንን ፍቅር ለመግለጽ እንድንችል ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አስተምሮናል፡፡

ሠ/ ዲያብሎስን ድል ለመንሣት፤ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በማቴዎስ ወንጌል ፬፥፩-፲፩ ላይ መዋዕለ ጾሙ ሲፈጸም ሰይጣን በሦስት ነገር ማለትም በስስት፣ በትዕቢትና በፍቅረ ንዋይ ተፈታተነው፡፡ በስስት ቢፈትነው በትዕግስት፣ በትዕቢት ቢቀርበው በትሕትና፤ በፍቅረ ንዋይ ሊያታልለው ቢሞክር በጸሊአ ንዋይ ድል ነሣው፡፡ ዛሬ እነዚህን ማሳቻ መንገዶች ለይተን ጠላታችንን ድል መንሣት እንችላለን፤ ክርስቶስ ሳጥናኤልን ስለ እኛም ተዋጋው፤ በገሃነም ጣለው፡፡ በዮሐዋንስ ወንጌል ፲፮፥፴፫ ላይ “ስለዚህ እኔ ዓለምን ድል ነስቼዋለኹና ድል ንሱ” ያለበት ምክንያትም ጾም ደዌ ነፍስን ትፈውሳለችና፡፡ የሥጋ ምኞትን አጥፍታ የነፍስን ረኃብ ታስታግሳለችና፤ ከዲያብሎስ ቁራኝነት በማላቀቅ ከክርስቶስ ጋር አንድ ታደርጋለች፡፡

እኛ ለምን እንጾማለን?

ጌታችን አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመጾም ለነፍሳችን ካሳ እንደሆነን ሁሉ እየጾምን፤ ጠላታችን ሳጥናኤልን ድል ነሥተን አባቶቻችን የወረሱትን ርስት እንድንወርስ እንጾማለን፡፡ ጾም በመንፈሳዊ ሕይወት የመበልጸጊያና የሰውነት መሻትን ለእግዚአብሔር መሥዋዕት አድርጎ የማቅረቢያ መንገድ ነው፡፡ በዚህም ጾም የወንጌልና የበጎ ሥራ ሁሉ መጀመሪያና የትሩፋት ጌጥ እንደሆነ ሁሉ፤ መጀመሪያና መጨረሻ የሌለው፤ አልፋና ኦሜጋ ልዑል እግዚአብሔር ለአዳም የሰጠው የመጀመሪያ ትእዛዙ ነው፡፡ ዘፍጥረት ፪፡፲፯ ላይ “ነገር ግን መልካሙንና ክፉን ከሚያስታውቀው ዛፍ አትብላ፤ ከእርሱ በበላህ ቀን ሞትን ትሞታለህና”፤ ብሎ ያዘዘው ትእዛዝ ይህ ነውና፡፡

ጾም ስንል፤ ፩ኛ እግዚአብሔርን የምንፈራበትና ከእግዚአብሔር ምሕረት የምንለምንበት መንገድ ነው፡፡

ዕዝራ ፰፡፳፫ ላይ “ስለዚህም ነገር ጾምን ወደ እግዚአብሔር ለመንን፤ እርሱም ተለመነን”፤ በማለት ጾም እግዚአብሔርን መለመኛ እና ጸሎታችንን እንዲሰማን የምናደርግበት መሣሪያችን መሆኑን በተግባር እንዳገኙ እንረዳበታለን፡፡

፪ኛ ኀዘናችንን እና ችግራችንን ለእግዚአብሔር የምንነግርበትና  የምናቀርብበት መንገድ ነው፡፡

ነቢዩ ኢዩኤልም ሕዝበ እስራኤልን ሐዘን በገጠማቸው ጊዜ፤ በመከራም ሳሉ ትንቢተ ኢዩኤል ፩፥፲፬ ላይ የነገራቸው ቃል “ጾምን ቀድሱ፤ ጉባኤውንም አውጁ፤ ሽማግሌዎችንና በምድር የሚኖሩትን ሁሉ ወደ አምላካችሁ ወደ እግዚአብሔር ቤት ሰብስቡ፤ ወደ እግዚአብሔር ጩኹ”፤ በማለት ወደ እግዚአብሔር መጸለይ እንደሚገባ ነግሮናል፡፡ ትንቢተ ኢዩኤል ፪፡፲፪ ላይም “እግዚአብሔር በፍጹም ልባችሁ በጾምም፣በለቅሶና በዋይታ ወደ እኔ ተመለሱ፤ በጽዮን መለከትን ንፉ፤ ጾምንም ቀድሱ፤ ጉባኤውንም አውጁ”፤ በማለት ነግሮናል፡፡ ስለዚህ ለእግዚአብሔር በመብላት፣ በመጠጣትና በሥጋ ፍላጎት ሆነን የፍላጎታችን፣ የሰላማችንንና የአንድነታችን መሻት መጠየቅ የለብንም፡፡ መጀመሪያ እራሱ ክርስቶስ ማድረግ ያለብንን የተግባር ሥራ እንድንሰራ የነገረን ከችግራችንና ከሐዘናችን ለመላቀቅ በምድር ለምንኖር ሁሉ መጾም እንዳለብን እራሱ ባለቤቱ እግዚአብሔር በነቢያት አድሮ ነግሮናል፡፡

፫ኛ ስብራታችን የምንጠግንበትንና መልካም የሆነ ትውልድ የሚታነጽበት መሣሪያ ነው፤

ትንቢተ ኢሳያስ ፶፰፡፲፪ ላይ “ከድሮ ዘመን የፈረሱት ስፍራዎችህ ይሠራሉ፤ መሠረትህም ለልጅ ልጅ ዘመን ይሆናል፤ አንተም ሰባራውን ጠጋኝ የመኖሪያ መንገድንም አዳሽ ትባላለህ”፡፡ እንዲሁም በቁጥር ፭ ላይ “እኔ ይህንን ጾም የመረጥሁ አይደለሁም”፤ እንደዚችም ባለች ቀን ሰው ራሱን ማሳዘን እንደሌለበትና በዚህም ጾም ራሱን ቢያስገዛ በዚያን ጊዜ በእግዚአብሔር ይታመናል፤ በምድርም በረከት ላይ ይኖረዋል፤ እግዚአብሔርም በያዕቆብም ርስት ይመግበዋል፤ እርሱ እግዚአብሔር ተናግሯልና”፡፡

፬ኛ የአምልኮ መንገድ ነው፤

የሐዋርያት ሥራ ፲፫፡፩-፪ ላይ እንደተገለጸው መንፈስ ቅዱስ ለሥራ የጠራቸውን በርናባስንና ሳውልን ያሰናበቷቸውም በጾምና በጸሎት ነበር፡፡ በዚያም ጊዜም ከጾሙ፤ ከጸለዩ፤ እጃቸውንም ከጫኑ በኃላ አሰናበቷቸው፡፡ አንድ ሰው የአምልኮ መንገድ ሲጀምር መጾም መጸለይ እንዳለበት እራሱ ኢየሱስ ክርስቶስ እንዳስተማረን፤ ጾም የአምልኮ መንገድ ስለሆነች ነው፡፡ ሐዋርያትንም የጠፋውን ትውልድ ለመፈለግ ሐዋርያዊ ጉዞ ከማድረጋቸው በፊት ጾመዋል፡፡

፭ኛ አጋንትን የምናወጣበት እና ርኩሳን መናፍስትን የምንዋጋበት መሣሪያችን ነው፤ማር ፱፡፳፱  ጌታችን ደቀመዛሙርቱ ማውጣት አቅቷቸው የነበረውን ጋኔን እርሱ ካወጣው በኋላ ወደ እርሱ ቀርበው “እኛ ልናወጣው ያልቻልን ስለምን ነው?” ብለው በጠየቁት ጊዜ ስለ እምነታቸው ማነስ መሆኑን ነገራቸው:: “ይህ ወገን በጸሎትና በጾም ካልሆነ በምንም ሊወጣ አይችልም’ ነው ያላቸው፡፡ ስለሆነም ያለ ጾምና ጸሎት አጋንንት ማውጣት አይቻልም፡፡ ጾምን እየነቀፉና እያጥላሉ እንዲሁም በተግባር ሳይጾሙ አጋንንት እናወጣለን ማለት፤ የአጋንንት መዘባበቻና መጫወቻ እንደሆነ መረዳት ያስፈልጋል፡፡

ቤተ ክርስቲያንን ከጠላት ስውር ደባ ለመጠበቅ ጾምና ጸሎት ያስፈልጋል!

           

በሕይወት ሳልለው

ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የመሠረታት ቅድስት ቤተ ክርስቲያን የድህነታችን መገኛና መገለጫ ናት፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ “ለእግዚአብሔር የሚገባ ቅንዓት እቀናላችኋለሁና፤ ወደ እርሱ አቀርባችሁ ዘንድ ለአንዱ ንጹሕ ድንግል ሙሽራ ለክርስቶስ አጫቻችኋለሁና” (፪ቆሮ ፲፩፥፪) ሲል በቆሮንቶስ መልእክቱ ገልጿል፡፡

ቤተ ክርስቲያናችን በጠላት ስትታደን እንደኖረች ታሪክ ያስረዳናል፡፡ ልጆቿም እንደሷ ብዙ መከራን እንዳዩ፤ ያለበደላቸው መከራን እንደታገሱና ለእምነታቸው ብዙ መሥዋዕትነት እንደከፈሉም አንብበን ተረድተናል፡፡ ለምሳሌ “ዘመነ ሰማዕታት ብዙ መከራን ያሳለፈችበት ዘመን ነበር፡፡ ሁልጊዜ ቤተ ክርስቲያንን ስናይ ዕለተ ዐርብን እናስባለን፡፡ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በደሙ የመሠረታት፤ካህናት፤ ቀሳውስትና አገልጋዮች የሥራ ድርሻቸውን የሚያካሂዱባት የተቀደሰች ስፍራ ቤተ ክርስቲያን ናት” በማለት መጋቤ ሐዲስ ቀሲስ መንግሥቱ ማርያም፤ በአዲስ አበባ ሀገር ስብከት የቦሌ ቡልቡላ መድኃኔዓለም ቤተ ክርቲስያን የስብከተ ወንጌል ሐላፊ አስረድተዋል፡፡

የኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ህልውናዋ ሊጠበቅ ይገባል፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በየክፍለ ሀገራቱ አብያተ ክርስቲያናት እየተቃጠሉ መሆኑ በይፋ እየተነገረ ነው፡፡ ከጅማው ክስተት በኋላ ቤተ ክርስቲያናችን ላይ በተደጋጋሚ ችግር ደርሷል፡፡ ለዚህ የሀገር ጉዳይ መፍትሔ ለማግኘት የሃይማኖት አባቶች፤ አገልጋዮችና የሁላችንም ኃላፊነት ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያንን ያቃጠሉ ሰዎች ሲያልፉ በዘመነ ሰማዕታት ውስጥ ያለፈች ቤተ ክርስቲያን ግን ዛሬም ነገም ምእመኖቿን አስተምራ፤ሥጋ ወደሙን እያቀበለች ትኖራለች፡፡

“የምእመናን ድርሻ ደግሞ ቤተ ክርስቲያንን መጠበቅ ነው፡፡ የቤተ ክርስቲያን መከራ እንዲቆም ጾምና ጸሎት ያስፈልጋል፤ያለበለዚያ ግን እሳትን ሰማዕትነት ነው ብለን አናስበውም፤መከራ ነው እንጂ፡፡  ሰማዕታት የሃይማኖት ፍሬ እንዳያመልጣቸውና አክሊልም እንዳያልፈን በማለት ይሯሯጡ ነበር፡፡ በመጀመሪያ፤ እንኳን መንፈሳዊ ሥራ ሥጋዊ  ሥራም ያለ የእግዚአብሔር ፍቃድ አይሳካም” ሲሉም መጋቤ ሐዲስ ቀሲስ መንግሥቱ ማርያም ጨምረው አብራርተዋል፡፡

ይህ የጠላት ሴራና ክፋት በተለያየ መንገድ ምእመናንንና ቤተ ክርስቲያንን ለማጥፋት የሚደረግ በመሆኑ ከሥር መሠረት ልንመረምረው ይገባል፡፡ “የአማኞችን መብት ጠብቀው የአምልኮት ሥርዓታቸውን በሀገራቸው በነፃነት እንዲፈጽሙ የሃይማኖት መሪዎች ጥብቅና ሊቆሙላቸው ይገባል፡፡ ሲሰደዱ፤ ሲገደሉና ለተለያየ ጥቃት ሰለባ ሲሆኑ ዝም ብለን ማየት የለብንም፡፡ ይህ የአገልጋዮች ምግባር እየቀዘቀዘ በመሄዱ፤ ቤተ ክርስቲያን ለዚህ አይነት ተፅዕኖ ተዳርጋለች፡፡ አንዳንድ ሰዎች በኃይል ወይም በነውጥ የሚያደርጉት አግባብ የሌለው ተግባር ሊወገዝ ይገባል” ሲሉ የቅዱስ ጳውሎስ የሐዲስ ኪዳን መምህር መጋቤ ሐዲስ አእምሮ ደምሴ ገልጸዋል፡፡

የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን እንድትደክም፤ ምእመናን ላይ ጥርጣሬ እንዲፈጠር እንዲሁም የትክክለኛዋ ሃይማኖት ተከታይና ክርስቲያናዊ ምግባር እንዳይኖር በስውር ተመሳስለውና በስመ ሰባኪ የጠላትን ምኞት ለማሳካት ደፋ ቀና የሚሉ ተኵላዎችም በዝተዋል፡፡ “የበግ ለምድ ለብሰው ወደ እናንተ ከሚመጡ ከሐሰተኞች ነቢያት ተጠንቀቁ፤ በውስጣቸው ግን ነጣቂ ተኩላዎች ናቸው”፤(ማቴ ፯፥፲፭) ሲል ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አስቀድሞ ነግሮናል፡፡

ከኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሃይማኖት የራቁ ሰዎች ከቤተ ክርስቲያን ቀኖና፤ ሥርዓትና ትውፊት ውጪ በመሆን ከራሳቸውም አልፎ ሌሎችን ያስታሉ፡፡ ጠላታችን ዲያብሎስ ከጥንት ጀምሮ ምእመናንን ተስፋ ማስቆረጥ፤ ከእምነታቸውና ሃይማኖታቸው ማስወጣት ተግባሩ ነውና  ልንጸና ይገባል፡፡ ይህም የሚሆነው አምነን፤ተጠምቀን በበጎ ምግባር ታንጸን በሕገ እግዚአብሔር መኖር ስንችል ነው፡፡ በመጽሐፍ እንደተጻፋው እነዚህ ጸንተው ይኖራሉ የሚላቸው ሦስት ነገሮች እምነት፤ተስፋና ፍቅር  ናቸው፤ (፩ቆሮ ፲፫፥፲፫)፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ በቆሮንቶስ መልእክቱ እንደገለጸው “ደስ የሚላችሁን እንድታደርጉ እንረዳችኋለን እንጂ እንድታምኑ ግድ የምንላችሁ አይደለም”፤ (፪ቆሮ ፩፥፳፬) ፡፡

እንዲህ እምነት በጠፋበት፤ የመናፍቅ ቅሰጣ በበዛበት፤ ዓለም በኃጢአት ማዕበል በምትናወጥበት ወቅት ከሐሰተኞች ትንቢት መጠንቀቅ ይኖርብናል፡፡ ጌታችንም እንደተናገረው “የሚያስታችሁ እንዳይኖር ተጠንቀቁ፤ ብዙዎች እኔ ክርስቶስ ነኝ እያሉ በስሜ ይመጣሉና፤ብዙዎችንም ያስታሉ፤ጦርነትን፥ የጦርነትንም ወሬ ትሰሙ ዘንድ አላችሁ፤ ይህ ሊሆን ግድ ነውና ተጠንቀቁ፤ አትደንግጡ፤ ነገር ግን ፍጻሜው ገና ነው”፤(ማቴ ፳፬፥፬-፮)፡፡

ከጠላት ስውር ደባ ለማምለጥ የእግዚአብሔር ቸርነት ከእኛ ጋር ሊሆን  ያስፈልጋል፡፡ ከሃይማኖት አባቶች ጋር ያለንን ኅብረት ማጠንክር ስንችልም ፈጣሪያችን ያድነናል፡፡ እያንዳንዳችን ቤተ ክርስቲያን መሔድ፤ ክርስቲያናዊ ምግባርን ማዘውተር፤ ዘወትር መጸለይ፤ ንስሓ መግባትና መጾምም  ይጠበቅብናል፡፡

 

 

 

 

ዘወረደ እምላዕሉ አይሁድ ሰቀሉ፤ ከላይ(ከሰማይ) የወረደውን አይሁድ ሰቀሉት፤(ቅ/ያሬድ)

 

 

ዲያቆን አቢይ ሙሉቀን

በቦታ የማይወሰነው አምላክ ሥጋን በመዋሕዱ ወረደ፤ ተወለደ፤ ተሰደደ፤ ተራበ፤ ተጠማ፣ ተሰቀለ እየተባለ ይነገርለታል፡፡ የእኛን ሥጋ ተዋሕዶ ወደዚህ ዓለም መጥቶ በአጭር ቁመት በጠባብ ደረት በመወሰን ተወለደ፤ ሦስት ዓመት ከሦስት ወር ወንጌልን ዞሮ አስተማረ፤ በመስቀል ላይ መከራን ተቀበለ፤ ሞተ፤ተቀበረ፤ተነሣ፤ ዐረገ፡፡ ዘለዓለማዊ አምላክ በመሆኑም በሁለም ስፍራ ይኖራል፡፡ ሊቁ ቅዱስ ያሬድ በዐቢይ ጾም እግዚአብሔር ሊመሰገንበት የሚገባውን ምስጋና በጀመረበት ክፍሉ “ሃሌ ሃሌ ሉያ ዘወረደ እምላዕሉ አይሁድ ሰቀሉ ወሚመ ኢያእመሩ እግዚአ ኵሉ ዘያሐዩ በቃሉ፤ ቅድመ ዓለም የነበረ፣ ዛሬም ያለ፣ ዓለምን አሳልፎ የሚኖር፤ ከላይ (ከሰማይ) የወረደውን አይሁድ ሰቀሉት፤” ብሏል፡፡ ነገር ግን  አላወቁም፤ በቃሉ የሚያድን የሁሉ ጌታ ነውና” በማለት ጾመ ድጓ በሚባለው ድርሰት ይገልጸዋል፡፡

በዚህ ክፍለ ንባብ ሊቁ ቅድመ ዓለም የነበረ፣ ዛሬም ያለ፣ ወደፊትም ዓለምን አሳልፎ የሚኖር እንደ ሆነ፣ እንዲሁ ስለ ልዕልናው በሰማያት የምትኖር ይባላልና ከሰማይ የወረደውን አይሁድ ሰቀሉት አለ፡፡ እርሱ ራሱ ለደቀ መዛሙርቱ የጸሎት ሥርዓት ሲያስተምራቸው “አባታችን ሆይ በሰማያት የምትኖር…” ብላችሁ ጸልዩ ብሎ የእርሱ አባትነት ሰማያዊ እንጂ ምድራዊ እንዳልሆነና ከምድራዊ አባት የተለየ እንደሆነ በማስረዳት “በሰማያት የምትኖር በሉኝ” አለ፡፡ ሊቁም ይህን መሠረት አድርጎ “ከሰማይ የወረደውን አይሁድ ሰቀሉት” አለን፡፡

ከሰማይ የወረደው ቅድመ ዓለም አብ ያለ እናት በማይመረመር ጥበቡ የወለደው ድኅረ ዓለም ድንግል ማርያም ያለ አባት በማይመረመር ጥበብ የወለደችው ኢየሱስ ክርስቶስ ወልደ አብ ወልደ ማርያም ነው፡፡ ሥጋዊ ልደት የሆነ እንደሆነ ከአባት ዘር ከእናት ደም ተከፍሎ ይወለዳል፡፡ የኢየሱስ ክርስቶስ ልደት ግን ከአብ ያለእናት፤ ከእናት ያለአባት ሲሆን  እንዲህ ነው ተብሎ አይመረመርም፡፡ በማይመረመር ልዩ ጥበብ ስለተወለደ ስለልዕልናው በሰማይ የምትኖር ይባላል፡፡ ዘበእንተ ዕበይከ ትትሜሰል በደመናት፤ ስለልዕልናህ በደመናት ትመሰላለህ እንዲል፤ ስለዚህ ከላይ ከሰማይ የወረደውን ማለት በልዕልና ያለውን የሚኖረውን አምላክ አይሁድ ሰቀሉት፡፡

የአይሁድን ግብዝነት የጌታን ሁሉን ቻይነትም ሲያስረዳን፤  “ምንም አላወቁም፤ የሰቀሉት በቃሉ የሚያድነውን የሁሉን ጌታ ነው” ይለናል፡፡ በማቴዎስም ወንጌል ፱፥፲፰ ታሪኩ ተመዝግቦ እንደምናገኘው የመቶ አለቃው ልጁ በታመመበት ጊዜ “እባክህ አድንልኝ” በማለት ተማጸነው፤ “እኔ መጥቼ አድንልኃለሁ” ብሎትም ነበር፡፡ የመቶ አለቃውም በበኩሉ ፍጹም እምነትን የተሞላ ስለነበር “ሁሉ ይቻልሃል፤ በቃልህ ብቻ ተናገር ልጄ ይድናል” ብሎ ስለሁሉን ቻይነቱ  በምሳሌ ተናገረ፡፡ ጌታም የመቶ አለቃውን እምነት አድንቆ እንደወደድክ ይደረግልህ አለው፤ ልጁም ተፈወሰ፡፡ ይህንም የሚያውቀው ሊቁ ቅዱስ ያሬድ “እግዚአ ኵሉ ዘየሐዩ በቃሉ የሚያድን የሁሉ ጌታ” በማለት ገልጾታል፡፡

እንግዲህ ቤተ ክርስቲያን ጌታ ከሰማየ ሰማያት መውረዱን፣ ከድንግል ማርያም መወለዱን፣ መሰደዱን፣ መጠመቁን፣ በገዳመ ቆሮንቶስ መጾሙን በአጠቃላይ የነገረ ድኅነት ጉዞ ብላ ትገልጸዋለች፡፡ ገዳመ ቆሮንቶስ ገብቶ ፵ መዓልት  ፵ ሌሊት ጾመ፡፡ የዐቢይ ጾም ሳምንት መግቢያ የሆነውን የመጀመሪያውን ሳምንት “ዘወረደ፤ ከሰማይ የወረደው አምላክ” በማለት ታስበዋለች፡፡

በዚህም ሳምንት ከሰማየ ሰማያት መውረዱን፣ ከድንግል ማርያም መወለዱን፣ ለዓለም ቤዛ ሲል መከራ መቀበሉን የምናስብበት ሳምንት ነው፡፡ ይህ ሳምንት ጾመ ሕርቃል በመባልም ይታወቃል፡፡ ጾመ ሕርቃል የተባለበትም ምክንያት ጌታችን የጾመው ፵ መዓልት ፵ ሌሊት ሲሆን እኛ ግን ፶፭  ቀናት እንጾማለን ፡፡  ይህም የሆነበት ምክንያት ጌታ ከጾመው ፵ ቀን በተጨማሪ ቅዳሜና እሁድ ለብቻው ተቆጥሮ አንድ ሳምንት፡፡ በመጨረሻ ያለው አንድ ሳምንት ሰሙነ ሕማማት በመሆኑ በመጀመሪያ ያለው አንድ ሳምንት ደግሞ ጾመ ሕርቃል ይባላል፡፡ ሐዋርያት፡- ጌታ ፵  መዓልት ፵  ሌሊት ከዘረጋ ሳያጥፍ ከቆመ ሳይቀመጥ ነው የጾመው፤ እኛ ደግሞ እሑድና ቅዳሜ አንጾምም በማለት በመጀመሪያ ያለውን አንድ ሳምንት ጨምረው ጹመውታል፡፡

ሌላው በፍትሕ መንፈሳዊ አንቀጽ ፲፭ እንደምናገኘው በ፯ኛው መቶ ክፍለ ዘመን በኢየሩሳሌም ፎቃ፣ በሮም ደግሞ ሕርቃል የሚባሉ ነገሥታት ነበሩ፡፡ ይህ የኢየሩሳሌሙ ንጉሥ ፎቃ ጨካኝና ለክርስቲያኖች የማይራራ ሆነ፡፡ በዚህ ጊዜ ሕዝቡ፤ ለሮሙ ንጉሥ “እባክህ ከእንዲህ ካለው ጨካኝ ንጉሥ አድነን፤ እኛ ላንተ እንገዛለን” በማለት ይልኩበታል፡፡ እርሱም ለጊዜው ቸል ብሏቸው ቆይቶ ነበር፡፡ከዕለታት አንድ ቀን “ግዙራን ይነሥእዋ ለመንግሥትከ፤ ክርስቲያኖች መንግሥትህን ይወርሷታል” የሚል ራእይ አይቶ፤ ይህ የኢየሩሳሌሙ ንጉሥ ነው በማለት እንደገና የላካችሁብኝን ነገር አልረሳሁትም፡፡ ነገር ግን ሐዋርያት ነፍስ ያጠፋ ዕድሜ ዘመኑን ይጹም ብለዋልና፤ ያን ብፈራ ነው እንጂ አላቸው፡፡ እነሱም የአንድ ሰው ዕድሜ ፸ ፹ ነው፤ እኛ ተከፋፍለን እንጾምልሃለን ብለውት ጠላታቸውን አጥፍቶላቸዋል፡፡ እነሱም ተከፋፍለው አንድ ሳምንት ጹመውታል፡፡

ስለዚህም በንጉሡ በሕርቃል ምክንያት ስለተጾመ ጾመ ሕርቃል ይባላል፡፡ ታሪክ ያላወቁት አንድ ጊዜ ብቻ ጾሙ፡፡ ታሪክ ያወቁት ደግሞ ቀድሞም ሐዋርያት ጹመውታል በማለት መጾም ቀጥለዋል፡፡ ቤተ ክርስቲያንም ይህን መሠረት አድርጋ ከጌታ ጾም መግቢያ ላይ እንዲጾም ሥርዓት ሠርታለች፤ በመሆኑም ምእመናን ከጾሙ በረከት ያገኙ ዘንድ እንዲጾሙ ታስተምራለች፡፡ በዘመኑ ክርስቲያኖች ከጨካኙ ግዛት የዳኑበት ነው፡፡ ዛሬም ምእመናን ከጨካኙ ዲያብሎስ ፈተና፣ መከራና የጭካኔ አገዛዝ ነጻ የሚወጡበት ነውና ሊጾሙት ይገባል፡፡

በአጠቃላይ ይህ ጾም የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስን ከሰማየ ሰማያት መውረድ፤ ከቅድስት ድንግል ማርያም መወለድና ወደዚህ ዓለም መምጣት የሚታሰብበት ስለሆነ “ዘወረደ” ተብሎ ተሰይሟል፡፡ ሊቁ ቅዱስ ያሬድ “እስመ ጾም ትፌውስ ቁስለ ነፍስ ወታጸምም ኵሎ ዘሥጋ ፍትወታተ፤ጾም የነፍስን ቁስል ታድናለች፤ የሥጋን ፍላጎትንም ታስታግሳለች፡፡” ጾመን፤ ጸልየን፤ የሚታገለንን የሥጋ ፍላጎት ለማስታገሥ፣ ነፍሳችንን ለማዳን፣  ከእግዚአብሔር ጋር ለመገናኘት፣ የኃጢአት ስርየት ለማግኘት ይህን ጾም በመጾም በረከተ ሥጋ በረከተ ነፍስን እናገኝ ዘንድ እግዚአብሔር ይፍቀድልን፤ አሜን፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር