የተሰጠህን አደራ ጠብቅ (፩ጢሞ. ፮:፳) (በእንተ ላ ሊበላ)

ብዙአየሁ ጀምበሬ
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ለሀገራችን ያበረከተችው አስተዋጽኦ በብዙ ዐውድ የሚገለጽ እና መጠነ ሰፊ ነው፡፡ ከእነዚህም መካከል በቋንቋ፤ በባሕል፤ በአለባበስ፤በሥነ ጽሑፍ፤ በኪነ ጥበብ፤ በኪነ ሕንፃ እና በቅርጻ ቅርጽ ዘርፍ የተደረጉት አስተዋጽዖዎች ተጠቃሽ ናቸው፡፡ ይህች ስንዱ የሆነች ቤተ ክርስቲያን ተፈጥሮአዊ የሆኑ የዕፀዋት ዝርያዎችን በአግባቡ በመጠበቅ እና በመንከባከብ የሀገር ሕልውናን በማስጠበቅ እና ተፈጥሮ ዑደቱ ሳይዛባ እንዲቀጥል በማድረግም እጅግ የጎላ አገልግሎቷን በማስመዝገብ ላይ ናት፡፡ ዝርያቸው ሊጠፉ የተቃረቡ የዕፀዋት ዓይነቶችን ጠብቃ ያቆየች የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ናት፡፡ በሥነ ጽሑፍ ዘርፍም ቢሆን ሀገራችን የራሷ ፊደል እንዲኖራት እና ለሥልጣኔ ጉልህ አስተዋጽዖ የሚያበረክቱ መጻሕፍት ባለቤት እንድትሆን ረድታለች፡፡

የንባብ ባሕልን ከሥር መሠረቱ በማጎልበት ለከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ምሳሌ ሊሆን የሚችል የአብነት ትምህርት ቤቶችን በማቋቋም አያሌ ምሁራን እንዲፈሩበት ጉልህ ሥራን ሠርታለች፡፡ በዜማውም ዘርፍ የዜማ ሥርዓትን ለዓለም በቀዳሚነት በማስተዋወቅ፣ ሰማያዊ ሥርዓት ያለውን ዜማ በሊቁ ቅዱስ ያሬድ አማካኝነት አበርክታለች፡፡ በኪነ ሕንፃ ዘርፍ ደግሞ በዓለማችን ታሪክ በየትኛውም ክፍላተ አህጉራት የማይገኙ እና ደግመው መሠራት ያልተቻሉ ልዩ ልዩ የኪነ ሕንፃ ጥበቦችን በውስጧ የያዘች፤ ያስተዋወቀች እና ጠብቃ ያቆየች ናት፡፡
ለምሳሌ ያህል የአክሱም ሐውልት፤ የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት እና የንጉሥ ፋሲለደስን ግንብ መጥቀስ በቂ ነው፡፡ ይህች ቤተ ክርስቲያን እነዚህን ቅርሶች ለሀገራችን እና ለመላው ዓለም ብታበረክትም ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ለእነዚህ ቅርሶች ተገቢው ጥበቃ እና እንክብካቤ ባለመደረጉ የተነሳ ለከፍተኛ ጉዳት እየተጋለጡ ይገኛሉ፡፡ እንዴት እንደተሠሩ መረዳት እንኳን ግራ እስኪገባን ድረስ አስተውለንና የአሠራር ጥበባቸውን አድንቀን ሳናበቃ በቂ ጥበቃ እና እንክብካቤ ሳይደረግላቸው በመቅረቱ አብዛኞቹ ቅርሶች ለአደጋ እንዲጋለጡ እና ሥጋት ውስጥ እንዲገቡ ሆነዋል፡፡ ይህ ደግሞ የታሪክ ተወቃሽ እንድንሆን ያደርገናል፡፡ ከእነዚህ በአሳሳቢ ሁኔታ ውስጥ ካሉት ቅርሶች መካከል በአሁኑ ሰዓት በከፋና እጅግ በአሳሳቢ በሆነ ሁኔታ ውስጥ የሚገኙት የላልይበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት ናቸው፡፡

የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት የተፈለፈሉት በ፲፪ኛው መቶ ክፍለ ዘመን በንጉሥ ላላሊበላ አማካኝነት ነው፡፡ ቅዱስ ላሊበላ ታኅሣሥ ፳፱ ቀን በ፲፪ ኛውመቶ ክፍለ ዘመን መግቢያ ከእናቱ ኪርወርና እና ከአባቱ ከዛን ሥዩም በላስታ ሮሐ ቤተ መንግሥት ዋሻ እልፍኝ ውስጥ ተወልዷል፡፡ በተወለደ ጊዜም በንብ ስለተከበበ እናቱ ማር ይበላል “ላል ይበላል” ብላ ስም መጠሪያ ይሆነው ዘንድ አውጥታለታለች፡፡ ማር ከፍተኛ ደረጃ ያለው ተወዳጅ ምግብ ስለሆነ መልካም፤ ስመ ጥር፤ ታላቅ ንጉሥ ይሆናል ስትል ላልይበላ ብላዋለች፡፡

በሌላ መልኩም “ላልይበላ ብሂል ንህብ አእመረ ጸጋሁ ብሂል፣ ላልይበላ ማለት ንብ ጸጋውን (ገዢውን) ዐወቀ” ማለት ነው፡፡ ቅዱስ ላልይበላ የብሉያትን እና የሐዲሳትን የትርጓሜ መጻሕፍት ጠንቅቆ የተማረ ነው፡፡ ውቅር አብያተ ክርስቲያናቱን ከአንድ ወጥ ዓለት በመፈልፈል ያነጸው ንጉሡ ከዐሥራ አንዱ የዛጉዌ ሥርወ መንግሥት ነገሥታት መካከል አንዱ ሲሆን በኢትዮጵያ ለ፵ ዓመታት ያህል ነግሦ እንደነበር የታሪክ መዛግብት ያስረዳሉ፡፡(ምንጭ፡ ገድለ ቅዱስ ላልይበላ ሰኔ 2003 ዓ.ም ገጽ13)፡፡የቅዱስ ላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት በቊጥር ዐሥራ አንድ ሲሆኑ፣እነርሱም፡- ቤተ-ማርያም፤ ቤተ-መድኃኔ ዓለም፤ቤተ-ደናግል፤ ቤተ-መስቀል፤ ቤተ-ደብረሲና፤ቤተ-ጎልጎታ፤ ቤተ-አማኑኤል፤ቤተ-አባሊባኖስ፤ቤተ-መርቆሬዎስ፤  ቤተ-ገብርኤል ወሩፋኤል፤ ቤተ-ጊዮርጊስ የተሰኙ ናቸው፡፡
ቤተ-ደብረሲና በመባል የሚጠራው ፍልፍል ቤተ ክርስቲያን ቤተ-ሚካኤል በመባልም ጭምር ይታወቃል፡፡ ከእነዚህ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት መካከልም በቅድሚያ የታነጸው ቤተ-ማርያም የተሰኘው ሲሆን በወርኃ ታኅሣሥ በ፳፱ኛው ቀን የጌታችን የአምላካችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል እና የቅዱስ ላሊበላ የልደት በዓል “ቤዛ ኲሉ” የሚዘመርበት ቤተ መቅደስ ነው፡፡ ከእነዚህ ፍልፍል አብያተ ክርስቲያናት መካከል በመጠን ከሁሉም የሚልቀው እና ግዙፍ የሆነው ቤተ-መድኃኔዓለም ሲሆን በዚሁ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ”አፍሮ አይገባ” በመባል የሚታወቀው የመስቀል ይገኛል፡፡
የላሊበላ አብያተ ክርስቲያናት ሲነሱ በሁላችን አእምሮ የሚታወስና ትዝ የሚለን ከላይ ሲታይ በመስቀል ቅርጽ የታነጸው እና ከሌሎች በተለየ የኪነ ሕንፃ ጥበብ የተወቀረው ቤተ-ጊዮርጊስ ነው፡፡ የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት ተሠርተው ለመጠናቀቅ ፳፫ ዓመታትን ፈጅተዋል፡፡ ውቅር አብያተ ክርስቲያናቱ በዓለም ላይ በሰው ልጆች ታሪክ ውስጥ ከተገለጡት አስደናቂ የኪነ ሕንፃ ጥበቦች መካከል ወደር እና አቻ የማይገኝላቸው ናቸው፡፡
የአብያተ ክርስቲያናቱ የኪነ ሕንፃ ንድፍ (Design) እና ሥነ ውበት (Aesthetics) በአስደናቂ ሁኔታ ተጣምሮ የተዋሐደበት ልዩ የመንፈሳዊ ምሕንድስና አሻራም የታየበት ነው፡፡እስካሁን ባለው የኪነ ሕንፃ እና የምሕንድስና ታሪክ ውስጥ እንደ ላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት ዓይነት የረቀቀ ጥበብ የታየበት ሥራ በየትኛውም የዓለም ክፍል ላይ እንዳልተሠራ መዛግብት ያስረዳሉ፡፡ ፡፡ የአሠራሩ መንገድ ከታች ከመሠረት ሳይሆን ከላይ ከጣራ መጀመሩ በዋነኛነት ልዩ ያደርገዋል፡፡ ከዓለት መፈልፈላቸው እና በሥራቸው የውኃ ማጠራቀሚያ ቋት መያዛቸውም በራሱ ለየት ያደርጋቸዋል፡፡ ንጉሥ ላሊበላ ይህንን አስደናቂ የኪነ ሕንፃ ሥራ ሲሠራ ከፈጣሪው ከልዑል እግዚአብሔር ባገኘው መንፈሳዊ ጥበብ እንደሆነ የታሪክ ድርሳናት ይገልጣሉ፡፡
እግዚአብሔር አምላክ ለመረጣቸው እና አካሄዳቸውን ከእርሱ ጋር ላደረጉ መልካም ሰዎች ጥበብን ያድላል፤ ለዚህም የባስልኤል እና የኤልያብን ታሪክ ከመጽሐፍ ቅዱስ ማስታወስ ያሻል፡፡ “ለመቅደስም ማገልገያ ሥራ ሁሉ ያደርጉ ዘንድ እንዲያውቁ እግዚአብሔር ጥበብንና ማስተዋልን የሰጣቸው ባስልኤልና ኤልያብ በልባቸው ጥበበኛዎችም ሆኑ፣ እግዚአብሔር እንዳዘዘው ነገር ሁሉ አደረጉ፡፡ ሙሴም ባስልኤልና ኤልያብን እግዚአብሔርም በልቡ ጥበብን ያደረገለትን በልብ ጥበበኛ ሰው ሁሉ ሥራውንም ለመሥራት ይቀርብ ዘንድ ልቡ ያስነሣውን ሁሉ ጠራቸው፡፡ (ዘጸ.፴፮፡፩-፩) እንዲል፡፡
የውቅር አብያተ ክርስቲያናቱ መሠረታዊ የጂኦሜትሪያዊ ልኬት(Geometric proportion) የንድፍ ሥርዓትን የጠበቁ ናቸው፡፡ በሥጋዊ ምርምር ሊደረስባቸው አይችልም፡፡ለዚህም ነው ልዩ የከበረና ዘመን የማይሽረው የኪነ ሕንፃ ቅርስ መሆን የቻለው፡፡ ለዚህም ነው የዓለም ዜጎች ያከበሩት እና በየጊዜው ለመጎብኘት ወደ ሀገራችን የሚመጡት፡፡ ስለ ላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት አስደናቂነት እና ዘመን የማይሽራቸው የታሪክ አካላት እንደሆኑ በተለያዩ የሀገር ውስጥ እና የውጭ ሀገር ምሁራን ዘንድ ጥናት ተደርጓል፤ በግልጽም ተመስክሯል፡፡ ከእነዚህም መካከል ጥቂቶቹን እናንሳ ከ፲፭፻፲፪ ዓ.ም እስከ ፲፭፻፲፰ ዓ.ም ድረስ ወደ ኢትዮጵያ በመምጣት አብያተ ክርስቲያናቱን የጎበኘው የፖርቹጋሉ ተወላጅ ፍራንሲስኮ አልቫሬዝ ስለ ላሊበላ ውቅር አቢያተ ክርስቲያናት ድንቅ ምስክርነት ሰጥቷል፡፡ ይህ ሰው የላሊበላን ውቅር አብያተ ክርስቲያናት የጎበኘ የመጀመሪያው አውሮፓዊ ዜጋ ሲሆን ጎብኝቶ ካጠናቀቀ በኋላም ስለ አብያተ ክርስቲያናቱ አስደናቂነት እጅግ ብዙ ጽፏል፡፡
በጽሑፉ ማጠናቀቂያ ላይም እንዲህ ብሏል “ስለ ላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት ሥራዎች ብዙ ብጽፍም የሚያምነኝ ሰው መኖሩ በጣም ያስጨንቀኛል፤ ያሳስበኛልም እስካሁን ያልኩትም እንኳ ቢሆን ውሸት ነው የሚሉኝ፡፡ ነገር ግን የጻፍኩት በሙሉ እውነት ለመሆኑ በኃያሉ እግዚአብሔር ስም እምላለሁ፡፡ እንዲያውም ከዚህ በላይ ማለት ይቻል ነበር፡፡ ሆኖም ስሜ በቀጣፊነት እንዳይነሳ እሰጋለሁ … ይህን የሚመስል በዓለም እንደማይገኝ እገልጻለሁ፡፡” በማለት ድንቅ ምስክርነቱን በዚያን ዘመን ገልጿል፡፡ (ምንጭ፡ገድለ ቅዱስ ላሊበላ ሰኔ 2003 ዓ.ም ገጽ 15)፡፡
ከዚህም በተጨማሪ አንድርዜይ በርትኒስኪ እና ዮዓና ማንቴል ኒየችኮ የተባሉት የታሪክ ጸሐፍት የኢትዮጵያ ታሪክ በሚለው መጽሐፋቸው ላይ “ንጉሡ በስሙ በሚጠራው በላሊበላ ከተማ እስከ ዛሬም ድረስ ዝናቸው ያልደበዘዘውን ከዓለት ተፈልፍለው የታነጹ አብያተ ክርስቲያናት መሥራቱ ታላቅ የታሪክ ባለውለታ አድርጎታል” በማለት ገልጸውታል፡፡ (ምንጭ፡-የኢትዮጵያ ታሪክ አንድርዜይ በርትኒስኪ እና ዮዓና ማንቴል ኒየችኮ ትርጉም አለማየሁ አበበ ገጽ 32፤2003 ዓ.ም እትም)፡፡
ዓለም የተደነቀባቸው እና በእጅጉ ያወደሳቸው የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት በ፲፱፸፻፱ ዓ.ም በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የትምህርት፤ የሳይንስ እና የባሕል ድርጅት (UNSCO) አማካኝነት በዓለም ቅርስነት ተመዝግበው ይገኛሉ፡፡ የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት ለቤተ ክርስቲያን ከሚሰጡት መንፈሳዊ አገልግሎት ባሻገር ለሀገራችን ኢትዮጵያም ባለውለታ ናቸው፡፡ ይህም ሲባል ከተለያዩ የዓለማችን ክፍሎች ቅርሶቹን ለመጎብኘት ከሚመጡ የውጭ ሀገራት ጎብኝዎች አማካኝነት በየዓመቱ ከፍተኛ ገቢ በቱሪዝም ዘርፍ ለመንግሥት እንዲገባ ማስቻሉ ነው፡፡ ከዚህም በላይ ደግሞ የሀገራችን አባቶች ዓለምን የሚያስደንቅ ረቂቅ የኪነ ሕንፃ አሻራ አስቀምጠውልን ማለፋቸው አስተዋይ ትውልዶች ከሆን የእነርሱን ፈለግ በመከተል በሥልጣኔ እድገት ከፍተኛ ማማ ላይ እንደምንቀመጥ አመላካች ነው፡፡

ለሀገር ውለታ የዋሉ እነዚህ ታሪካዊ ቅርሶች ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ግን ከፍተኛ የሆነ አደጋ ተጋርጦባቸው ይገኛል፡፡ ይኸውም በዕድሜ መግፋት እና ለቅርሶቹ ጥበቃ ተብለው በተሠሩት የብረት ጣሪያዎች(Shade structures) ምክንያት አብያተ ክርስቲያናቱ ላይ በግርግዳቸው በኩል የመሰንጠቅ አደጋ እየተስተዋለባቸው ይገኛል፡፡ ችግሩ በዚሁ ከቀጠለ እና አፋጣኝ እርምጃ መውሰድ ካልተቻለ ጉዳቱ አመዛኝ ሆኖ የቅርሶቹ ሕልውና ጥያቄ ውስጥ ሊገባ ይችላል፡፡ ለእኛ ለዚህ ትውልድ ሰዎች ደግሞ ከአባቶች በአደራ የተላለፉትን ዘመን የማይሽራቸውን ውድ ቅርሶች በአግባቡ ባለመጠበቅ የታሪክ ተወቃሽ ለመሆን እንበቃለን፡፡
ለመሆኑ ንጉሥ ላሊበላ ምን ይለን ይሆን? አባቶቻችንስ እንዴት ይታዘቡን ይሆን? እነዚያን የመሰሉ አይደለም ደግመን ለመሥራት ቀርቶ እንዴትስ እንኳን እንደተሠሩ ተመራምረን መድረስ ያልቻልንባቸውን ድንቅ የታሪክ አሻራዎች ሠርተው አስረክበውን እኛ እንዴት በኃላፊነት መጠበቅ እና በአግባቡ መንከባከብ ያቅተን? በሀገራችን የሚገኙ በኪነ ሕንፃውም በምሕንድስናውም ዘርፍ አንጋፋ ልምድ እና ዕውቀት ያላቸው የቤተ ክርስቲያን ብሎም የሀገሪቱ ምሁራንስ በዚህ ጉዳይ ለምን በአስቸኳይ መፍትሔ መስጠት አልቻሉም?
እንደ ሀገር የቤተ ክርስቲያን የሆኑትን ብቻ ሳይሆን በሀገሪቱ የሚገኙ ማንኛውም ሰው ሰራሽ እና ተፈጥሮአዊ ቅርሶች ላይ አደጋ ሲጋረጥ “የእከሌ ኃላፊነት ነው፣ እኔን አይመለከተኝም” በማለት ራስን ገለልተኛ ከማድረግ ይልቅ በመወያየት እና አግባብነት ያላቸውን ምክክሮች በማድረግ መፍትሔ ማምጣት ግድ ይለናል፡፡ ይህ ካልሆነ ግን “እነርሱም አልሠሩትም፤ እነርሱም አልጠበቁትም” ተብለን የታሪክ ተወቃሽ ሆነን እናልፋለን፡፡
የቤተ ክርስቲያን ሊቃውንት፤ የሀገሪቱ የባሕል እና ቱሪዝም ኃላፊዎች፤ የኪነ ሕንፃ እና ምሕንድስና ምሁራን፤ በየሥልጣን ተዋረዱ የሚገኙ የመንግሥት ባለድርሻ አካላት ብሎም እያንዳንዱ ምእመን ችግሩ ይመለከተኛል በማለት አስቸኳይ እና ቀጠሮ የማይሰጠው መፍትሔ ማምጣት አስፈላጊ ነው፡፡ ከዚህም በላይ እያንዳንዱ ምእመን ፈጣሪ ሀገራችንን፤ ሕዝቦቿን እና ቅርሶቻችንን እንዲጠብቅልን ዘወትር በጸሎት መጠየቅም ይጠበቅበታል፡፡
ለወደፊቱ ተመሳሳይ ችግር በቅርሶቻችን ላይ እንዳያጋጥም እና ቢያጋጥም እንኳን ተገቢውን መፍትሔ ለመስጠት ያስችለን ዘንድ በኪነ ሕንፃ እና በምሕንድስና ላይ የተሰማሩ የቤተ ክርስቲያን ልጆችን በማስተባበር ሥርዓትን እና ሥነ መዋቅርን የተከተለ የቤተ ክርስቲያን ቴክኒካዊ ክፍል መዘርጋት እና ከባለድርሻ አካላት ጋር አብሮ መስራት ያስፈልጋል፡፡ የሲቪል መሀንዲሶች(Civil and Structural Engineers )፣ የኪነ ሕንፃ እና የከተማ ልማት ባለሙያዎች(Architects Urban planners and Architectural Historians)፤ የኮንስትራክሽን ግንባታ ባለሙያዎች (Construction TechnologyManagement)፤ የመካኒካል መሐንዲሶች(Mechanical Engineers)፤ የአፈር እና የድንጋይ ምርምር ባለሞያዎች(Geologists and Geo Tech Engineers)፤የቅርስን እና አካባቢ ጥበቃ ባለሞያዎች(Culture and Heritage professionals)፤ የሥነ ሰብእ ተመራማሪዎች(Anthropologists)፤ የታሪክ ምሁራን (Historian) እና የቤተ ክርስቲያን አባቶችን ያሰባሰበ ቡድን በማቋቋም ችግሩ የተከሰተበትን ምክንያት በማጥናት እና በምን መልኩ ጥገና እና ዕድሳት ይደረግለት የሚለውን ታሳቢ በማድረግ መፍትሔ ሊሰጠው ይገባል፡፡

ይህ የሞያተኞች ቡድን ወደፊትም ተመሳሳይ ችግር በቤተ ክርስቲያን እና በሀገር ቅርሶች ላይ ሲጋረጥ መፍትሔ ለማምጣት የሚሠራ የቤተ ክርስቲያን የአስተዳድር ወይም የቴክኒክ አካል ተደርጎ ሊመሠረት ያስፈልጋል፡፡ እንዲህ ባለመሥራታችን ተመሳሳይ ችግሮች በተከሰቱ ቊጥር የመፍትሔ ያለህ እያልን መጮህ እና የቅርሶቹን የእንግልት እና የአደጋ ሥጋት ጊዜ ማስፋት እና እስከወዲያኛውም ድረስ ላናገኛቸው እና ላይተኩ ሆነው እንዲጠፉ እናደርጋለን፡፡ ከዚህ በፊት ከኢትዮጵያ በጣሊያን አማካኝነት ተወስዶ የነበረውን የአክሱም ሐውልት ለማስመለስ የተደረገውን ጥረት ለአብነት እንደ ጥሩ ተሞክሮ አድርጎ ማንሳት ያስፈልጋል፡፡ በጊዜው በሁሉም ባለድርሻ አካላት የተደረገውን ዓይነት ርብርብ አሁን ላይም በመድገም ቅርሶቻችንን መታደግ ያስፈልጋል፡፡
በሌሎች ሀገሮች የሚገኙ የሃይማኖት ተቋማት የቅርስ ጥበቃ እና እንክብካቤ የሚያደርጉ ከዲዛይን፤ ምሕንድስና እና ግንባታ ዘርፎች የተወጣጡ አባላትን ያካተቱ የቴክኒክ ክፍሎችን በማዋቀር የቅርስ ጥበቃ እና እድሳት (Conservation and Restoration) እንደ አስፈላጊነቱ ያደርጋሉ፡፡ የእኛም ሀገር የሃይማኖት ተቋማት ከነዚህ ሀገራት አብያተ ክርስቲያናት እና ሌሎች እምነት ተቋማት ተሞክሮ በመውሰድ በቅርሶቻችን ላይ የተጋረጠውን አደጋ መቀነስ ብሎም ማስቀረት ያስፈልጋል፡፡ አባቶቻችን የሠሩልንን እና ያስረከቡንን የታሪክ ቅርሶች በአግባቡ ተቀብለን እና ጠብቀን ለትውልድ ማስተላለፍ እና ቅብብሎሹ እንዲቀጥል ማድረጉ ከእያንዳንዳችን ይጠበቃል፡፡ በቤተ ክርስቲያን የአስተዳድር ሥነ መዋቅርም ቢሆን እንደዚህ ዓይነት ችግሮች ሲከሰቱ ከመንግሥት ባለድርሻ አካላት ጋር በመነጋገር መፍትሔ ማምጣት ጊዜ የሚሰጠው ጉዳይ መሆን የለበትም፡፡

               ወስብሐት ለእግዚአብሔር
ምንጭ፤ሐመር መጽሔት 26ኛ ዓመት ቁ7 ኀዳር2011 ዓ.ም

በትዳር ሕይወት የወላጆች ኃላፊነት

                                                                  ዲ/ን ተመስገን ዘገየ
መጽሐፍ ቅዱስ እግዚአብሔር አምላክ ሰውን በአርአያውና በአምሳሉ ፈጠረው ይለናል (ዘፍ፪-፳፮) አዳም ብቻውን ይሆን ዘንድ ያልፈቀደውና ብቻውን ቢሆን መልካም እንዳልሆነ የሚያውቅ አምላካችን የምትረዳውን ሔዋንን ከጎኑ አጥነት ፈጥሮለታል፡፡እግዚአብሔር ወንድና ሴት አድርጎ መፍጠሩ ለበረከት፤ለመባዛት በመሆኑ”ብዙ ተባዙ ምድርንም ሙሉአት” በማለት ሕገ በረከትን ሰጥቷአቸዋል፡፡ስለዚህ ጋብቻ በሰው ፍላጎት ብቻ የተገኘ አይደለም፡፡ስለ ጋብቻ በኦሪትም በወንጌልም ሕግ ተሰርቷል፡፡የአዳምና የሔዋን ጋብቻ የሕጋዊ ጋብቻ መሠረት ነው፡፡ጋብቻን ያከበሩ በሕጋዊ ጋብቻ የነበሩ ደጋግ ቅዱሳን በሕገ ልቡና እንደነበሩ ሁሉ በሕገ ኦሪትም ነበሩ፡፡ለምሳሌ የኢያቄምና የሐና ጋብቻ ቅዱስ ጋበቻ ነበር፡፡የተቀደሰ ጋብቻ በመሆኑ የቅድስት ድንግል ማርያም ወላጆች የአምላካችን የመድኀኒታችን አያቶች ለመሆን በቅተዋል፡፡
እንዲሁም የዘካርያስና የኤልሣቤጥ ጋብቻ የተባረከ ጋብቻ ነበር፡፡ ቡሩክና ሕጋዊ በመሆኑም መጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስን ማግኘት ችለዋል፡፡ጋብቻ የቅድስና ሕይወትን በሥርዓት የሚመሩበት የቤተሰብ መንግሥት በመሆኑ ክብሩና ልዕልናው ሊጠበቅ ይገባዋል፡፡ወላጆች ልጆችን መተካት አለባቸው ሲባል“መውለድ” ብቻ ማለት አለመሆኑን በሚገባ መረዳት ይገባል፡፡ቅዱስ ዳዊትም “ናሁ ጸጋሁ ለእግዚአብሔር ውሉድ ዕሤተ ፍሬሃ ለከርሥ፤ልጆች የእግዚአብሔር ስጦታ ናቸው (መዝ፻፳፮፥፫) ልጆች ማደግ ያለባቸው በእግዚአብሔር ትእዛዝና መንገድ ነው፡፡ክቡር የሆነው የሰው ልጅ ቀርቶ አራዊትም እንኳን ልጆቻቻውን በሥርዓት ያሳድጋሉ፡፡ ለምሳሌ፤አናብስትና አናብርት አዳኝ የዱር እንሰሳት ልጆቻቻውን እንዴት እያደኑ ማደግ እንዳለባቸው ያስተምራሉ፡፡
ጠቢቡ ሲራክ “የሰው አነዋወሩ በልጆቹ ይታወቃል”ይላል (ሲራ፲፩፥፳፰) በ፳፩ኛው ክፍለ ዘመን የወጣቱ ሥነ-ምግባር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየዘቀጠ መምጣቱ እውነት ነው፡፡ለዚህም ዋናው መሠረታዊ ችግር ሕዝቡ ከእግዚአብሔር ጋር ያለው ግንኙነት በተለያየ ምክንያት እየዛለ መምጣ ነው፡፡ወላጆች ልጆቻቸውን ማስተማር ያላባቸው ቀዳሚ ትምህርት“እግዚአብሔርን መፍራት“ነው፡፡(ምሳ፩፥፯) ልጆች ለሚጠይቁት ጥያቄ እንደ ዐቅማቸው ማስረዳት ይገባል፡፡ ሕፃናትን የሚያስተምሩ ሰዎች በፍቅርና በደስታ ማቅረብ ይኖርባቸዋል፡፡ልጆች ከጣፈጭ ምግብ ይልቅ የሚረኩት ከወላጆች በሚያገኙት ፍቅር ነው፡፡ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ “አባቶች ሆይ ልባቸው እንዳይዝል ልጆቻችሁን አታበሳጩ”ይላል (ቈላ፫፥፳፪) ልጆችን በፍቅር እንጂ በስድብ ፤በመደብደብ ፤በማበሳጨት፤በማስፈራራት ለማስተማር መሞከር እንደማይገባን ሐዋርያው አስተምሮናል፡፡
ሲራክ“የሰው አኗኗሩ በልጆቹ ይታወቃል (ሲራ፲፩፥፳፰) የላኪው ማንነት በተላከው እንደ ሚታወቅ የወላጆች ምንነት ማሳያ ልጆች ናቸው፡፡የኢትዮጵያ ሕዝብ ሥነ ምግባር የማይታይበት ልጅ ሲያጋጥማቸው”አሳዳጊ የበደለው” ይላሉ፡፡ስለዚህ ልጆችን በሥነ ምግባር ኮትኩቶ ማሳደግ ለነገ የማይባል ተግባር ነው፡፡አሁን አሁን በልጆቹ የሚደሰትና የሚጠቀም ወላጅ ሳይሆን በወለዷቸው ልጆች የሚያዝኑና የሚያለቅሱ ኢትዮጵያውያን ይበዛሉ፡፡ሲራክ “በሱ ጥፋት አንተ እንዳታፍር ልጅህን አስተምረው ያገለግልሃል”(ሲራ፴፥፲፫) ልጅን በሚገባ አስተምሮ ማሳደግ በጣም አስፈላጊ መሆኑን ቅዱሳት መጻሕፍት ያሰተምሩናል፡፡ የካህኑ የዔሊ ልጆች ፊንሐስና አፍኒን በታቦተ ጽዮን ድንኳን ሥር ያመነዝሩ ነበር ያሳፍራል፡፡ ዔሊ ልጆቹ ይህን የመሰለ ኃጢአት መፈጸማቸውን እያወቀ ባለመገሰጹ ቅጣት ተቀብሏል፡፡ልዑል እግዚአብሔር ዔሊን “ከእኔ ይልቅ ልጆችህን ለምን አከበርክ?(፩ኛሳሙ፪፥፳፱) በማለት ተቆጣው፡፡ሁለት ልጆቹንም ቀሰፋቸው፡፡ቅጣቱ በልጆቹና በእሱ ብቻ ተወስኖ አልቀረም፡፡ለሌላም ተረፈ አንጂ፡፡
ወላጆች ሆይ ልጆቻችንን እንዴት እናሳድጋቸው?
የነገው ትወልድ ሀገሩንና ቤተሰቡን የሚጠቅም በሥነ- ምግባር የታነጸ በሥራው የተመሰገነ ይሆን ዘንድ ዛሬ ያሉትን ልጆች በአግባቡ መያዝ ልዩ እንክብካቤ ማድረግ ይገባል፡፡ወላጆች ከማንም በላይ ሕፃናትን መልካሙንና ክፉንም በማሰተማር ቅርብ ናቸው፡፡እናትና አባት ከትምህርት ቤት ሲመለሱ ስለተማሩት ትምህርት መጠየቅ አለባቸው፡፡ልጆችም እንደሚጠየቁ ስለሚያውቁ ትኩረት ሰጥተው ይከታተላሉ፡፡ጥሩ ነገር በሠሩ ጊዜ ጥሩ ወጤት ባመጡ ጊዜ ሽልማት ማዘጋጀት ይገባል፡፡ወላጆች በቤት ውስጥ በቃል ሳይሆን በተግባር በክፉነት ሳይሆን በደግነት እያስተማሩ ሊያሳድጉ ይገባል፡እንዲህ ከሆነ የክፉ ምግባር ቦይ አይሆኑም፡፡አንድ ሰው በቅሎ ጠፋችበትና ወዲያ ወዲህ እየተንከራተተ ሲፈለግ በበቅሎ ሌብነት የሚጠረጠረው ሰው አብሮ ያፋልገው ጀመር፡፡ዘመድ መጥቶ “በቅሎህ ተገኘችልህ ወይ”ብሎ ቢጠይቀው አፈላላጊዬ የበቅሎዬ ሌባ ስለሆነ እንደምን አድርጌ በቅሎዬን ላገኛት እችላለሁ አለ ይባላል፡የልጆችን አእምሮዊ ዕድገት ለማሟላት ከሚደረጉ እንክብካቤዎች የሚከተሉት ይጠቀሳሉ
ተገጣጣሚ መጫዎቻዎችን በመጠቀም የቁጥር ስሌት እንዲያውቁ ማድረግ፤የቋንቋ ችሎታቸውን የሚያሳድጉ መንፈሳዊ ጹሑፎችን እንዲያነቡ ደጋግመው መንገርና ዕድሎችን ማመቻችት፡፡ወላጆች (ባልና ሚስቱ) በአንድነት ሁነው የቤተሰቡ መሪ በመሆናቸው ሊወስዱት የሚገባ ተግባር ይኖራል፡፡ልጆቻችንን በምግባር በማሳደግ የሚኖሩበትን ቤት የዕለት ከዕለት እንቅሰቃሴ እየተከታተሉ መሥመር በማስያዝ አገልጋዮች የሆኑ የቤት ሠራተኞችን ሳያማርሩ ሥራ ሳያበዙ በማሠራት መኖር ይጠበቅባቸዋል፡፡ወላጆች ይህንን ከባድ የቤተሰብ ኃላፊነት ሲወጡ በሚከተሉት ነጥቦች ቢመሩ መልካም ነው፡፡
፩.. በፍቅር፤ ልጆች ፍቅርን እንክብካቤን ከወላጆችና ከመምህራን ይፈልጋሉ፡፡የወላጆቹን ፍቅር እያገኘ ያደገ ልጅ መንፈሰ ጠንካራ፤ለሰው የሚያዝንና ታዛዥ ይሆናል፡፡አንዳንድ ወላጆች የቤተሰቡ ራስ መሆናቸውን በቊጣ በዱላ በመግለጽ ልጆቻቸውን በኃይል ብቻ ለመግዛት የሚሞክሩ አሉ ፡፡ይህ የተሳሳተ መንገድ ነውና ከስሕተት ጎዳና መመለስ ይኖርባቸዋል፡፡
፪..ትኩረት በመስጠት፣ ልጆች ከፍተኛ የሆነ ክትትልና ትኩረት ይፈልጋሉ፡፡የሚያከናውኑትን እያንዳንዱን ተግባራት እየተመለከተ በጎውን በጎ የሚላቸው ሲሳሳቱ የሚያርማቸው ይሻሉ፡፡ ልጆችን በንቃት መከታተል የወላጆችና የመምህራን ግዴታ ነው፡፡ወላጆች በዕረፍት ጊዜ ከልጆቻቸው ጋር መወያየት፣መመካከር፣የወደፊት ዕቅዳቸውን ምኞታቸውን በተመለከተ በግልጽነት መረዳት ይገባቸዋል፡፡
፫. በማስተማር፤ ንግሥት ዕሌኒ ቆስጠንጢኖስን በሥርዓት ኮትኩታ በማሳደጓ የሀገረ መሪ ለመሆን በቃ፡፡አሁንስ እኛ ልጆቻችንን እንዴት እያሳደግናቸው ነው? ሰው በሕፃንነቱ ተክል ማለት ነው፡፡ተክል የሚሆነውን ሁሉ ሊሆን ይችላል፡፡ቀጥ ብሎ ያድጋል ተወላግዶም ያድጋል የተወላገደውን ለማቃናት ብዙ ዋጋ ያስክፍላል፡፡ወላጆች በልጆቻቸው ዕድገት ትኩረት ሊሰጡት የሚገባ አንዱና ዋነኛው የልጆቻቸውን ተፈጥሮዊ ተሰጥኦ ማበልጸግ ነው፡፡ወላጆች ልጆችን የማሳደግ ክህሎት ለማዳበር ቅዱሳት መጻሕፍትን ማንበብ ይኖርብናል፡፡ከእኛ ቤት ሲገባ ግን መጸሕፍት ይኖር ይሆን? በተለያዩ የቤተሰብና የልጆች ነክ ጉደዮች በመሳተፍ ከተቻለ የሥነ ልቡና ባለሙያና የአብነት መምህራንን በማማከር የተሻለ ዕውቀት መጨመር ይቻላል፡፡
የልጆችን ተሰጥኦ ከልጅነታቸው ጀምሮ መረዳትና እውቅና መስጠት ለወላጆች ትልቅ ስኬትና አበረታች ነገር ነው፡፡ወላጆችና የአብነት መምህራን ልጆች ችሎታቸውን የሚያወጡበትን አማራጮችና ዕድሎችን ማመቻችት ይገባቸዋል፡፡በእኛ ሀገር ደረጃ ጥረህ ለፍተህ ብላ ኑር ነው እንጂ አማራጭ አንሰጥም ይህ ዘመንን አለመዋጀት ነውና መስተካከል ይኖርብናል፡፡የልጆችን እንቅስቃሴ በመከታተል የልጆችን ፍላጎት ማወቅ ይገባል፡፡ወላጆች ከትምህርት ስኬት ባሻገር የልጆቻቸውን ማኀበራዊ መንፈሳዊና ሥነ-ልቦናዊ ሕይወት መረዳት አለባቸው፡፡ወላጆችና መምሀራን ልጆችን ሲያናግሩ ሙሉ ትኩረት መስጠት አለባቸው፡፡
ልጆችን በልዩ ልዩ እንቅስቃሴዎች ማሳተፍ ይገባል
ወላጆች ልጆቻቸውን ሲያሳድጉ በትምህርታቸው ብቻ ስኬታማ ሆነው ትምህርታቸውን አጠናቀው እንዲመረቁ ብቻ ሳይሆን አጠቃላይ በመንፈሳዊ ሕይወታቸውም ስኬታማነት እንዲ ዘጋጁ የማደረግ ኃላፊነት አለባቸው፡፡ልጆችን ከትምህርት ቤት መልስ በተለያዩ ተግባራት እንዲሳተፉ ማድረግ የሚከተሉት ጠቀሜታዎች ይኖሩታል፡፡
ቴሌቪዥን በመመልከትና ጌም በመጫዎት የሚያሳልፉትን ጊዜ በመገደብ በሠርክ ጉባኤና በሰንበት ትምህርት ቤት ከመደበኛው ከትምህርት ውጭ የሆኑ ተግባራት ሲሳተፉ ወሳኝና ለወደፊት ሕይወታቸው ከፍተኛ ጠቀሜታ ያላቸው ማኀበራዊ ክህሎቶችን እንዲያዳብሩ ይረዳቸዋል፡፡ በውኃ ውስጥ መዋኘትም ለልጆች የሚመች የእንቅስቃሴ አይነት ነው፡፡በሳምንት ሁለት ጊዜ (ቅዳሜና እሑድ) ቢዋኙ አካላዊ ብቃታቸውን ያሻሽላል፡፡የመተንፈስ እንቅስቃሴ በማሻሻል ሂደት ለልጆች ጤንነት የአካል ብቃት የላቀ አስተዋጽኦ አለው፡፡ከትምህርት ቤት መልስም ሆነ በዕረፍት ቀናት የእግር ኳስ እንቅስቃሴ ማድረግ ወላጆች አብረው በመጫወት ካልተቻለም ልጆች ሲጫወቱ በመከታተል ,.በተግባር በማሳየት፣ልጆች ከሚሰሙት ይልቅ በሚያዩት ይሸነፋሉ፡፡ ከተነገራቸው ይልቅ የተመለከቱት በእነርሱ ኀሊና ትልቅ ቦታ አለው፡፡ ወላጆች ተግባራዊ የሆነ ሕይወትን ለልጆቻቸው ሊያስተምሩ ይገባል፡፡አሁን በየቤታችሁ ልጆች ምንድን ነው የሚያዩት አንዳንድ ወላጆች ልጆቻቸውን እንዳይጠጡ እየመከሩ እነርሱ ጠጥተው የሚገቡ አሉ፡፡አሁን የዚህ ሰውየ ልጅ ምን ይሆናል? ልቡ ባዶ ቅርጫት ራሱ ባዶ ቤት እየሆነ ነው፡፡ ፈቃደ ሥጋን ለፈቃደ ነፍስ በማስገዛት ልጆችን መልካም የሆኑ ነገሮችን ማስተማር አለብን አንድ ወቅት ሊቀ ጉባኤ አባ አበራ በቀለ “ራሱን ያሸነፈ የጎበዝ ጎበዝ ነው ሌለውን ያሸነፈ ተራ ጎበዝ ነው” ብለው ነበር፡፡ በዘመናችን ራስን ማሸነፍ ሰማዕትነት ነው፡፡
• ልጆች ማኅበራዊ ሚዲያዎችን በአግባቡ መጠቀም ይኖርባቸዋል
የመረጃ ልውውጥ ከማደረግ (በጎን መጥፎውንም) ማኅበራዊ ግንኙት ከማጠናከር (የጠፉ ጓደኞችን) ከማገናኘት አንጻር በአግባቡ ከተጠቀሙበት ትልቅ አስተዋጽዖ አለው፡፡የማኅበራዊ ሚዲያዎች ጉዳት ተመልሶ የማይገኝ ጊዜን ያባክናል፡፡አጠቃቀማችን በአግባቡ ካልሆነ ለትዳር ጠንቅ ነው ራሳቸውን አግዝፎ ለማሳየትና ማኅበራዊ ሚዲያዎችን ለዝሙት የሚጠቀሙ አሉ፡፡ በዘመናችን ችግሩን መናገር በራሱ ችግር ነው እንጂ ቴክኖሎጂው እየተራቀቀ ሲመጣ የትውልዱም ጥያቄ እንዲሁ እየተበራከተ ይመጣል፡፡የ፳፩ኛውን ክ/ዘመን ትውልድ ሥነ ልቡና በመረዳት ወላጆች እንደ እባብ ብልህ በመሆን ትውልዱ ያለበትን ሁኔታ ቀድመው ምን እየመጣ እንደሆነ መመልከት ይኖርባቸዋል፡፡
የመረጃ ቴክኖሎጂ ዓለምን ወደ አንድ መንድር እየተቀረ በመምጣቱ ሀገራችንም የዚሁ ቴክኖሎጂ ተጠቃሚ በመሆኑ አደጋ አለው፤በአግባቡ መጠቀምና መቆጣጠር አለመቻል መሠረታዊ ችግር ነው፡፡ልጆቻችን ውጤታማና ስኬታማ እንዲሆኑ ለማድረግ የመረጃ ቴክኖሎጂ አጠቃቀማቸውን መገደብና መቆጣጠር የወላጆች ኃላፊነት ነው፡፡ልጆች በቪዲዮ ጌም መጫወት ካለባቸው በወላጆች በጥንቃቄ የተመረጡ፣አዝናኝና የልጆችን የፈጠራ ችሎታ የሚያበለጽጉ ፣ለዕድሜአቸውና ለሥነ-ልቡናቸው የሚመጥኑ ቁጣና ጥቃት ያልበዛባቸው መሆን እንዳለባቸው ባላሙያዎች አበክረው ይመክራሉ፡፡የሚያስፈሩ ቪዲዎችና ጌሞችን የሚጫወቱ ልጆች የበለጠ ቍጣና ጥላቻ የሚያሳዩ ይሆናሉ፡፡ልጆች ያለ ገደብ ቴክኖሎጂ ከተጠቀሙ የአእምሮ ዕድገታቸው ይጎዳል፡፡የትምህርት አቀባባል ድክመት ያጋጥማቸዋል፡፡ላልተፈለገ የሰውነት ውፍረት ያጋልጣል፡፡ ለማሰታወስ ችግር ያጋጥማችዋል፡፡የቴክኖሎጂ ሱሰኛ ያደርጋል፣የእንቅልፍ እጦት ያጋጥማቸዋል፡፡
የልጆች ሥነ- ምግባርና መንፈሳዊ ሕይወት በምን ምክንያት ሊበላሽ ይችላል-?
በቂ ቁጥጥር ካለማድረግና ወላጅ ልጆቹን ሥነ-ምግባር ስለማያስተምር ታላላቆቻቸው እና ቤተሰቦቻቸው ሥነ-ምግባርን በማስተማር ረገድ ደከሞች በመሆናቸው፡፡ ሕፃናቱ አብረው የሚውሉት አብረው የሚማሩት ሰው ማንነት እንዲሁም የሚውሉበት አካባቢ መጥፎ መሆን ለእነርሱ የማይገቡ የማይመጥኑአቸውን ፊልሞችና ድርጊቶች ስለሚመለከቱ አንዳንድ ትምህርት ቤቶች ሥነ- ምግባርን አስመልክቶ የሚያስተላልፉት መልእክት አነሳ መሆን የሚያስፈልጋቸውን ነገሮች ባለማግኘት ምክንያት አግባብነት ወደ ሌላቸው ቦታዎች ሊሄዱ በመቻላቸው ምክንያት ነው፡፡ ልጆቻችን መከራ እንዲቋቋሙ አድርገን እናሰልጥናቸው ችግር ሲመጣ የሚቋቋሙ አናድርጋቸው፡፡ሕፃናት በማይጠቅሙ ዓለማዊ ፊልሞች ጨዋታዎች ድራማዎች፤ፍቅር ሰጥመው ካደጉ በኋ ክፉ ነገር ተው ብንል እንዴት ይቻላል? ልጆቻቸውን በሥርዓት ያስተማሩና ከቅጣት ያዳኑ ደጋግ አባቶች ነበሩ፡፡መጽሐፍ “ከእግዚእበሔር ሕግ እንዳይወጡ ሴት ልጆቻቸውንና ወንድ ልጆቻቸውንም፡አስተምረው ነበርና፤የሚቀርባቸው ክፉ ጠላት አልነበረም (፩መ.መቃቢያን፲፱፥፲፫)

 ወላጆች ለልጆቻቸው የእግዚአብሔርን ድንቅ ተኣምራት ፤የጻድቃንና የሰማዕታት ገድልና የሀገራቸውን ታሪክ በሚገባቸው መጠን እያስጠኑ የማሳደግ ኃላፊነት አለባቸው፡፡ከወላጅ ወደ ልጆች መተላለፍ የነበረበት የቃል ትምህርት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየደበዘዘ በመምጣቱ በትውልዱ ዘንድ ክፍተቱ እየበዛ መጥቷል፡፡በጥንቱ ባሕል መሠረት ልጆች ወላጆቻቸውን ቁመው ማብላት ነበረባቸው፡፡በእራት ጊዜ የእንጨት መብራት ይዞ ያበላ ነበር፡፡ይህም ቢሆን ልጅ ለወላጅ ያለውን አክብሮት ለመግለጽ የሚደረግ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጥንተ መሠረት ያለው ነው፡፡(ሉቃ፲፯፥፰፤፳፪፥፳፯)
ወላጆች ልጆቻቸውን በሥነ-ምግባር ኮትኩተው በሥነ ሥርዓት አስተምረው የማሳደግ ኃላፊነት እንዳለባቸወ ሁሉ ልጆችም ወላጆቻቸውን የመታዘዝ፤የማክበር ግዴታ አላባቸው፡፡ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ”ልጆች ሆይ ይህ ለጌታ ደስ የሚያሰኝ ነውና ለወላጆቻችሁ ታዘዙ”ይላል( ቈላ፫፥፳)ከሁሉ በፊት እናትና አባቱን የሚያከብር ልጅ ዕድሜው ይረዝማል(ዘጸ፳፥፲፪) ምክንያቱም ይመረቃልና፡፡ወላጆቹ የመረቁት ልጅ በእግዚአብሔር ዘንድም የተወደደ ነው፡፡ በመንፈሳዊና በምድራዊ ሀብት የበለጸገ ይሆናል፡፡”ምርቃት ትደርስህ ዘንድ ቢጠራህ አቤት ቢልክህ ወዴት ብለህ አባትህን አክብረው “(ሲራ፫፥፱) በታዛዥነታቸው፤በትሕትናቸው በወላጆቻቸው ከተመረቁት መካከል ያዕቆብንና ርብቃን ለአብነት ማንሳት ይበቃል (ኩፋ፳፥፷፭፤ዘፍ፳፬፥፷ ፤ኩፋ ፲፬፥፴፱)
ዲድስቅልያ አንቀጽ ፲፩፥፩ ”እናንትም አባቶች የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ይጠብቁ ዘንድ የክርስቶስን ጎዳና ይከተሉ ዘንድ ልጆቻችሁን አስተምሯቸው እጅ ሥራ አገልግሎት ይማሩ ዘንድ እዘዟቸው ሥራ ፈት ሁነው እንዳይቀመጡ”ይላል፡፡ብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ ካልዕ ሚያዝያ 23 ቀን 1982 ዓ.ም በሻሸመኔ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን ተገኝተው ሲያሰተምሩ ”ልጆቻችሁ ከመዝሙር ጋር ደግሞ ሃይማኖታቸውን ፤ሥነ ምግባራቸውን እንዲማሩ ያስፈልጋል፡፡ወደ ቤተ ክርስቲያን ስትመጡ ልጆቻችሁን ይዛችሁ ኑ ብቻችሁን ከመጣችሁ የምተሠሩትን አያውቁም፤ወደየት እንደ ሄዳችሁም አያውቁም፡፡ወራሾቻችሁም አይሆኑም ስለዚህ ቤተ ክርስቲያን ስትመጡ ልጆቻችሁን ይዛችሁ ኑ፤ሥዕሉን ይሳሙ፤ቅዳሴ ጠበሉን ይጠጡ ፡በእምነቱ አሻሹአቸው መስቀል እንዲሳለሙ አስተምሯቸው ዕጣኑንም ያሽትቱ የሚታጠነውን፤ሥጋወደሙን ይቀበሉ፤ቃጭሉን ይስሙ፤ደወሉ ሲደወል ይስሙ፤ቄሳቸው ማን እንደሆነ ቤተ ክርስቲያናቸው ማን እንደሆነች በውስጧም ምን ምን እንደሚሠራ ያጥኑ ፤ይማሩ፡፡ ወደ ሰንበቴም ስትሄዱ ይዛችኋቸው ግቡ ወደ ሰንበቴም ዳቦውን ተሸክመው ይምጡ እነርሱም ነገ ይህንን እንዲወርሱ የነገ ባለ አደራዎች መሆናቸውን እንዲያውቁ፡፡መመካት አይገባም የሚገባ ቢሆን እኛ ከዓለም ሁሉ የበለጠ መመካት ይገባን ነበር፡፡ምከንያቱም አባቶቻችንና እናቶቻችን ሥርዓታችንንና እምነታችንን ሁሉ ሰፍረው ቆጥረው ያስቀመጡልን ስለሆነ፤ይህ ትውልድ ይህንን ከቀበረ በኋላ ይህንን ካጠፋ በኋላ እንደገና ቤተ መዘክር እንዳይሄድ ነው ሃይማኖቱን ፍለጋ፤ታሪኩን ፍለጋ፤ስለዚህ እምነታችሁን፤ሥርዓታችሁንና መንፈሳዊ ውርሳችሁ እንድትጠብቁ አደራዬ የጠበቀ ነው”ብለው ነበር፡፡

ምንጭ፤ሐመር መጽሔት ፳፮ኛዓመት ቊ ፮ ጥቅምት ፳፻፲ወ፩ ዓ.ም

አንቲ ውእቱ ጽጌ መዓዛ ሠናይ (ውዳሴ ማርያም ዘእሑድ)

                                                                                መ/ር ዘለዓለም ሐዲስ
ከመስከረም ፳፮ እስከ ኅዳር ፭ ያለው ዘመን ወርኀ ጽጌ በመባል ይታወቃል፡፡ወርኀ ጽጌም የተባለበት ምክንያት ዕፀዋቱ አብበው ምድርን በአበባነታቸው አሸብርቀው የሚታዩበት ወር በመሆኑ ነው፡፡ጽጌ ማለት ጸገየ አበበ ካለው የግእዝ ሐረግ የተመዘዘ ሲሆን ጽጌ ትርጉሙ አበባ ማለት ነው ጌታችን በጽጌ መስለው የተናገሩ ነቢያት ናቸው ከዐበይት ነቢያት አንዱ የሆነው ኢሳይያስ ጌታን ከዕሤይ ሥር በትር ትወጣለች ከርሷም አበባ ይገኛል በማለት ጌታን በአበባው እመቤታችን በበትር መስሎ ተናግሯል፡ንጉሥ ሰሎሞንም በመኃልዩ“ጽጌ አስተርአየ በውስተ ምድርነ በምድራችን አበባ ታየ”በማለት ጌታን በአበባ እመቤታችን በምድር ይመስላታል(ኢሳ ፲፩፥፩)

የዘመነ ሐዲስ ሊቃውንትም የነቢያትን ምሳሌያዊ ምስጢር ከማብራራታቸው በተጨማሪ እመቤታችን በጽጌ በአበባ፣ልጇን ከአበባው በሚገኘው ፍሬና መዓዛ መስለው ተናግረዋል ከእነዚህ ሊቃውንት መካከል አንዱ የሆነው ቅዱስ ኤፍሬም “አንቲ ውእቱ ጽጌ መዐዛ ሠናይ እንተ ሠረጸት እምሥርወ ዕሤይ ከዕሤይ ሥር የተገኘች መዓዛዋ ያማረ ጽጌ አንቺ ነሽ በማለት እመቤታችን በአበባ (በጽጌ) ልጇን በመዓዛው መስሎ ተናግሯል ሌሎችም ሊቃውንት ተመሳሳይ ምሳሌ በመመሰል ምስጢረ ሥጋዌውን አብራርተዋል፡፡

ይህ ወራት በቀደሙት አባቶቻችን ዘንድ እስከ ፲፫ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ዘመነ ጽጌ እየተባለ እግዚአብሔር ምድርን በአበባ ማስዋቡ በቤተ ክርስቲያን ቢዘከርም እንደ አሁኑ ማኅሌተ ጽጌ ሰቆቃወ ድንግል እየተቆመ የእመቤታችን ስደት አይታሰብበትም ነበር፡፡ወቅቱ እግዚአብሔር ምድርን በአበባዎች የሚያስጌጥበት ስለሆነ ቅዱስ ያሬድ በዚህ ወቅት ምድር በአበባ የሚያስውቡትን የሽቱ ዕፀው ናርዶስ ቀንሞስ ሮማን የመሳሰሉትን እያነሣ ምድር በእነዚህ ሁሉ አበባዎች እንዳጌጠችና እንደተዋበች የተናገረውን የየየቀኑን መዝሙር እየዘመረች ቤተ ክርስቲያናችን እግዚአብሔርን ታመሰግንበት ነበር፡፡በኋላ ግን ከቅዱስ ያሬድ ቀጥለው የተነሱት ሊቃውንት ስለእመቤታችን መሰደድ ድርሰት የደረሱ ሊቃውንት የነቢያትን ምሳሌ መነሻ በማድረግ እመቤታችን አበባውን በሚያስገኙ ያማሩ ያማሩ የሽቱ ዕፀው፣ልጇን በጽጌ በአበባ እየመሰሉ ማኅሌተ ጽጌና ሰቆቃወ ድንግልን ከደረሱ ማኅሌቷንም መቆም ከጀመሩ በኋላ ወርኃ ጽጌ ተብሎ ከመታሰቡ በተጨማሪ የእመቤታችን የስደቷ መታሰቢያ ሁኖ መከበር ጀምሯል፡፡

በ፲፫ኛው መቶ ክፍለ ዘመን በአባ ዜና ማርቆስ አስተማሪነት ከአይሁዳዊነት ወደ ክርስቲያንነት የተመለሰው አባ ጽጌ ብርሃንና (ጽጌ ድንግል) አባ ገብረ ማርያም መምህር ዘደብረ ሐንታው ሁለቱ ማኅሌተ ጽጌንና ሰቆቃወ ድንግልን ደርሰው የእመቤታችን ስደት እያሰቡ ማኅሌት መቆም ከጀመሩበት ከ፲፫ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ጀምሮ እስከ አሁን ድረስ ማኅሌቱ ሳይቋረጥ ቀጥሏል፡፡ምእመናንንም የእመቤታችን ስደት ለማስታወስ በእመቤታችን ስም ማኅበር እየጠጡ ምንም ጾሙ የፈቃድ ቢሆንም ጾም እየጾሙ ዝክር እየዘከሩ ያከብሩታል ማኅበሩም የሚጠጣው በቤተ ክርስቲያን ወይም በተራራ ላይ ነው ከቤታቸው የማይጠጡበት ምክንያት እመቤታችን በረሃ ለበረሃ ስለተሰደደች ያንን ለማስታወስና እንደ እመቤታችን በመንገድ የደከመን እንግዳ ለመቀበል ነው፡፡
የማኅሌተ ጽጌ ደራሲ የሆነው አባ ጽጌ ብርሃን (ድንግል) ከመጠመቁ በፊት ዘካርያስ ተብሎ ይጠራ ነበር ለማመን ያበቃችውም ገባሪተ ኃይል የሆነች የእመቤታችን ሥዕል ናት ብዙ ተአምራትን ስታደርግ ስላየ ወደአባ ዜና ማርቆስ በመሔድ ተምሮ ለማመን በቅቷል ከአባ ዜና ማርቆስ ትምህርተ ሃይማኖትን ተምሮ በምንኵስና ሕይወት መኖር ከጀመረ በኋላም ያችን ለማመን ያበቃችውን ገባሪተ ኃይል ሥዕል ሳይሳለም አይውልም ነበር፡፡

ከሥዕሏ ፊትም ሲቆም የሚያቀርበው እጅ መንሻ (መባዕ) ስለሌው ይጨነቅ ነበር በኋላ ግን ይህ ዘመነ ጽጌ ሲደርስ በየቀኑ ሃምሳ ሃምሳ የጽጌረዳ አበባ እየፈለገ እንደ ዘውድ እየጎነጎነ ለዚያች ምስለ ፍቁር ወልዳ ሥዕል ያቀዳጃት ነበር በጋው ሲወጣ የጽጌረዳው አበባ ስለደረቀበት ከሥዕሏ ተንበርክኮ እመቤቴ በየቀኑ የማመጣልሽ የጽጌረዳ አበባ ደረቀ ስለአበባው ፈንታ መልአኩ ተፈሥሒ ተፈሥሒ እያለ ያመሰገነሽን ምስጋና በአበባው ቁጥር ልክ ሃምሳ ሃምሳ ጊዜ እንዳመሰግንሽ ፍቀጅልኝ በማለት ተማጸነ ከዚህ በኋላ በየቀኑ ተፈሥሒ ፍሥሕት የሚለውን የመልአኩን ምስጋና በየቀኑ ሲያቀርብላት ምስጋናው እንደጽጌረዳ አበባ እየሆነ ከአንደበቱ ሲወጣ እመቤታችን አበባውን እየተቀበለች ስትታቀፈው ሰዎች እያዩ ያደንቁ እንደነበር ገድለ ዜና ማርቆስ ያስረዳል፡፡
እሱም በድርሰቱ እንዲህ ሲል ገልጾታል“አባዕኩ ለኪ ስብሐተ ተአምር ዘይሤለስ በበሃምሳ ህየንተ ጽጌያት ሃምሳ ለስዕልኪ አክሊለ ርእሳ” ለስዕልሽ ዘውድ ይሆን ዘንድ ሃምሳ የጽጌ ረዳ አበባ አቀርብልሽ ስለነበረው ፈንታ ሦስት ጊዜ ሃምሳ(መቶሃምሳ) የሚሆን ምስጋናን አቀረብኩልሽ በማለት፡፡ስለዚህ ዘመነ ጽጌ ከዚያ ጊዜ ጀምሮ እግዚአብሔር ምድርን በአበባ ማስጌጡን ማሰባችን እንዳለ ሁኖ በተጨማሪ የእመቤታችን የስደቷን በዓል እናስብበታለን፡፡

                                           ስለምን ወደግብፅ ተሰደደ?   

ጌታችን ከመወለዱ በፊት ከጽንሰቱ እስከ ዳግም ምጽአቱ ድረስ ስለሚሠራው ሥራ አስቀድሞ በነቢያቱ እያደረ ትንቢት አናግሯል፡፡ መልአኩም ለዮሴፍ ብላቴናውን ሄሮድስ እንደሚገድለው ሲነግረው የሚሸሽበትን ቦታ ሳይቀር “ተንሥእ ንሣእ ሕፃነ ወእሞ ወሑር ውስተ ብሔረ ግብፅ” ተነስተህ እናቱንና ብላቴናውን ይዘህ ወደግብፅ ሽሽ በማለት ለስደቱ ግብፅን እንደመረጣት በትንቢቱ ተናግሯል(ማቴ፪፥፲፫) ከደቂቅ ነቢያት አንዱ ሆሤዕም ጌታችን ወደግብፅ እንደሚሰደድ “እምግብፅ ጸዋእክዎ ለወልድየ ልጄን ወደግብፅ ጠራሁት” ሲል ልዑለ ቃል ኢሳይያስ ደግሞ “ወይወርድ እግዚእነ ውስተ ምድረ ግብፅ እንዘ ይጼዐን ዲበ ደመና ቀሊል፤ጌታችን በፈጣን ደመና (በእመቤታችን ጀርባ) ተጭኖ ወደግብፅ ይወርዳል በማለት ተናግሯል (ሆሴ፲፩፥፩ ኢሳ ፲፱፥፩)ከሌሎች ሀገሮች ለስደቱ ግብፅ የተመረጠችበት ምክንያቱ ብዙ ቢሆንም ጥቂቶቹን እንመለከታለን፡፡
፩.ለፍቅሩ ስለሚሳሱለት፤ ጌታችን ወደግብፅ የተሰደደበት ምክንያት ግብፃውያን ኢትዮጵያውያንን ጨምሮ ጌታችን ከምንም በላይ ለፍቅሩ ይሳሱለት ስለነበረ ነው፡፡ይህንም ወደ ግብፅና ወደ ኢትዮጵያ በተሰደደ ጊዜ ግብፃውያንና ኢትዮጵያውያን እንዴት አክብረው እንደተቀበሉትና እንደሳሱለት በነገረ ማርያም የተጻፈው ታረክ ጥሩ ማስረጃ ነው ምንም ሰይጣን ያደረባቸው እነ ኮቴባን የመሰሉ አንዳንድ ክፉ ሰዎች ቢያጋጥሟቸውም ብዙዎቹ ደግሞ ለፍቅሩ በመሳሳት“ደም ግባቱ ከሰው ልጆች ሁሉ ያምራል”ተብሎ የተነገረለትን መልኩን በማየት ብቻ ለማመን የበቁ ደጋጎች ነበሩ እንኳን ቤት መስርተው በዓለም የሚኖሩት በበረሃ ውስጥ የሚኖሩ ሽፍታዎችም ለጌታችን ያሳዩት ርኅራኄና ፍቅር የተለየ ነበር፡፡ሕፃኑ ኢየሱስ ክርስቶስና እመቤታችን ዮሴፍና ሰሎሜ ኢየሩሳሌምን ለቀው ወደ ግብፅ ሲሰደዱ ግብፃዊው ጥጦስና አይሁዳዊ ዳክርስ ሁለት ወንበዴዎች በረሃ ውስጥ አግኝተዋቸው ነበር እስራኤላዊዉ ዳክርስ ልብሳቸውን ለመግፈፍ ሲፋጠን ግብፃዊዉ ጥጦስ ግን በልቡናው ርኅራኄ አድሮበት ለፍቅሩ በመሳሳት እነዚህ ሰዎች የቤተ መንግሥት ሰዎች ናቸው አሳዘኑኝ ወደ ዚህ ቦታ የመጡት ያለ ምክንያት አይሆንምና አንቀማቸው እንተውላቸው በማለት ለጌታ ያለውን ፍቅርና ርኅራኄ ገልጧል
ወደ ኢትዮጵያም በመጡበት ወራት ቤታቸውን እየለቀቁ ያስተናግዷቸው እንደ ነበር ድርሳነ ዑራኤል በሰፊው ይናገራል እመቤታችንም የኢትዮጵያ ሰዎች ባሳዩአት ፍቅር ስትደሰት ጌታችን የዐሥራት ሀገር ትሁንሽ ብሎ ሀገሪቱን ለእመቤታችን የሰጣት በወቅቱ የነበሩት ኢትዮጵያውያን ባሳዩት ደግነትና ርኅራኄ ነው፡፡ደጉ አባት አብርሃም እንግዳ በመቀበሉና ደግ በመሆኑ ሥላሴ ከቤቱ እንደ ገቡለት ሎጥም እንግዳ በመቀበል መላእክት ወደ ቤቱ ገብተው ሰዶምና ገሞራ ሲጠፉ ከጥፋት እንደታደጉት ጌታችን አባቶቻችን ባደረጉት ደግነት ኢትዮጵያ በእመቤታችን ምልጃ ሊጠብቃት ስለፈለገ የዐሥራት ሀገር አድርጎ ሰጣት ምን ጊዜም ሊምረው የወደደውን ሰው የእመቤታችን ፍቅር ያሳድርበታልና እመቤታችን እንድንወድ አድርጎ በአማላጅነቷ እንድንጠበቅ ፈቀደልን ጌታችን ወደ ግብፅና ወደ ኢትዮጵያ የተሰደደበት ምክንያት ለፍቅሩ ይሳሱለት ለነበሩት ኢትዮጵያና ግብፅ በፍቅር ለመገለጽ ሲሆን በተጨማሪም ገዳማተ ግብፅንና ገዳማተ ኢትዮጵያንም ለመባረክ ጭምር ነው፡፡በግብፅና በኢትዮጵያ ያሉ ታላላቅ ገዳማት የተባረኩት በስደቱ ወራት ነውና፡፡
ኪዳነ መልከ ጼዴቅን ለመፈጸም ነው፤መልከ ጼዴቅ ከዘመዶቹ ተለይቶ በምናኔ ሲኖር በሚያቀርበው መሥዋዕት በሚጸልየው ጸሎት በሥጋ ዘመዶቹ የሆኑትንና የማይዘመዱትን እንዲምርለት እግዚአብሔርን ይለምነው ነበር እንዲህ እያለ አቤቱ ለዲያብሎስ ከመገዛት ለአንተ ወደ መገዛት መልሰኸኛልና ከሀገሬም አውጥተህ አንተን ወደማመልክበት ቦታ አምጥተኸኛልና በደሌንም ይቅር ብለህልኛልና አመሰግንሃለሁ ነገር ግን እኔን ይቅር እንዳልከኝ ዘመዶቼንም ማርልኝ፡፡እግዚአብሔርም ልመናውን ተቀብሎ እንዲህ ሲል ድምፁን አሰምቶታል ልጄን ወደ ግብፅ በጠራሁት ጊዜ ዘመዶችህን እምርልሃለሁ ብሎ ቃለ ኪዳን ገብቶለት ነበር ዘመኑ ሲደርስ የተናገረውን የማያስቀር እግዚአብሔር የገባለትን ቃለ ኪዳን ለመፈጸም ወደግብፅ ተሰደደለት (ተረፈ ቄርሎስ ፳፭፥፩—፱) ኖኅ ከጥፋት ውኃ በኋላ መልአከ እግዚአብሔርን ከመካከላቸው እንደ ዳኛ አስቀምጦ ለሦስቱ ልጆቹ ለሴም ለካም ለያፌት ይህን ዓለም ቀኝ ቀኙን ለሴም መሀሉን ለያፌት ግራ ግራውን ለካም አውርሷቸዋል መልከ ጼዴቅ ትውልዱ ከካም ወገን ስለሆነ ምንም ዘመዶቼን ማርልኝ ብሎ የጸለየ ለሁሉም ዘመዶቹ ቢሆንም የአባቱ ወገኖች የካም ዘሮች ናቸውና ጌታ ወገኖቹን ሊምርለት ቃል ኪዳኑን ሊፈጽምለት ወደግብፅ ተሰዷል
.አጋንንትን ከግብፅና ከሰው ልቡና አስወጥቶ ለመስደድ ነው
ጌታ ገና ከመወለዱ በፊት ለልደቱ ሃያ አራት ቀን ሲቀረው መካነ ልደቱ ቤተ ልሔምን በመላእክት አስጠብቋት ነበር፡፡በዚህ ጊዜም አጋንንት በመላእክት ረቂቅ ጦር እየተወጉ ኢየሩሳሌምን ለቀው ሲወጡ የተሰደዱት ወደ ግብፅ ነበር አጋንንት በውስጣቸው አድርው ይመለኩባቸው የነበሩ ጣዖታትም ተሰባብረው ጠፍተዋል ይህንንም ጌታ ወደ ግብፅ በተሰደደ ጊዜ ራሳቸው አጋንንት በኢየሩሳሌም ማደሪያ እንዳሳጣኸን በዚህም ልታሳድደን መጣህን ብለው እንደ መሰከሩ በነገረ ማርያም ተጽፏል ጌታ ወደግብፅ የተሰደደበት ሦስተኛው ምክንያት እነዚህ አጋንንት ማደሪያ ካደረጓቸው የሰው ልቡናናና ከጣዖቱ አስወጥቶ በመስደድ አጋንንትን ለማሳደድ ነው፡፡ ይህንም ቴዎዶጦስ የተባለው ሊቅ ጌታ ተሰደደ ሲባል ብትሰማ ፍጡር ነው ብለህ አትጠራጠር ፈርቶ ሸሸም አትበል የጌታ መሰደድ ዲያብሎስን ከሰው ልቡና አስወጥቶ ለማሳደድ እንደሆነ እመን እንጅ ብሎ የተሰደደ ዲያብሎስን ለማሳደድ መሆኑን ገልጧል (ተረፈ ቄር፲፥፭)ይህ ሊቅ ጌታ የተሰደደው ዲያብሎስን ለማሳደድ ብቻ ሳይሆን ሰው መሆኑን ለሚጠራጠሩ፣ምትሐት ነው ለሚሉትም በትክክል ሰው መሆኑን ለማስረዳት እንደ ተሰደደ በዚሁ ምዕራፍና ቁጥር ይገልጻል ሰው ባይሆን ኑሮ አይሰደድም ነበር ፡፡
.አዳም ከዚህ ዓለም አፍአ በምትሆን ከገነት ተሰዶ ነበርና ለመካስ
ጌታችን በዕለተ ልደቱ የበለስ ቅጠል የለበሰ አህዮችና ላሞች እስኪያሟሙቁት ድረስ የተበረደ አዳም ከገነት ሲወጣ የበለስ ቅጠል ስለለበሰ ከልብሰ ብርሃን በመገፈፉ ስለተበረደ አዳም የተቀበለውን መከራ ተቀብሎ ለመካስ ነው፡፡ገና በሁለት ዓመቱ ከኢየሩሳሌም ወደግብፅ የተሰደደውም ከዚያው ሁኖ መዳን ተስኖት ሳይሆን አዳም ዕፀ በለስን በልቶ ከገነት እንደ ተሰደደ እሱም ከኢየሩሳሌም ወደ ምድረ ግብፅ ተሰዶ አዳም የተቀበለውን መከራ ተቀብሎ ለመካስ ነው፡፡አዳም ከገነት ወደ ማያውቀው ወደዚህ ዓለም ሲሰደድ ብዙ ፍዳና መከራ አግኝቶታል ፡ከአንዱ ቦታ ወደ አንዱ ቦታ በሚያደርገው እንቅስቃሴ እሾሁ ሲወጋው እንቅፋቱ ሲመታው ይህ ሁሉ የደረሰበት ከፈጣሪዉ ትእዛዝ በመውጣቱ መሆኑን ሲያስብ ዕንባው ከዓይኑ ያለማቋረጥ እንደምንጭ ውኃ ይፈስ ነበር፡፡
በገነት ሳለ የሚበላውና የሚጠጣው ከሰውነቱ ጋር ተዋሕዶ ይቀር ነበር እንጅ ወደ ኀሠርነት ስለማይለወጥ በልቶ ጠጥቶ መጨነቅ ሆድ ቁርጠት በልቶ መታመም በቁንጣን መሰቃየት አልነበረበትም ከገነት ከወጣ በኋላ ግን ይህ ሁሉ መከራ በርሱ ላይ መጥቶበታል ይህን ሁሉ መከራ ስለተቀበለ አዳም ወደዚህ ዓለም ሲሰደድ የተቀበለውን መከራ ተቀብሎ ሊክሰው ስለወደደ ወደ ግብፅ ተሰደደለት እንደተበረደ ተበረደለት በዕፀ በለስ ምክንያት ከገነት እንደወጣ በዕፅ ተሰቅሎ ያጣው ክብሩንና የክብር ቦታውን ገነትን መለሰለት
፭ ለሰማዕታት ስደትን ለመባረክ ፤ሰማዕትነት እሳትና ስለት ብቻ አይደለም ሀገርን ጥሎ መሰደድም ሰማዕትነት ነው፡፡ በመሆኑም ለሰማዕታት ስደትን ለመባረክ የማትችሉት መከራ ቢመጣባችሁ ተሰደዱ ለማለት ወደ ግብፅ ተሰደደ ስደት ከሰማዕትነት ገብቶ የተቆጠረበት ምክንያት መከራው በሰይፍ ተቆርጦ በስለት ተቀልቶ ከመሞት በላይ ስለሆነ ነው፡፡ከመከራ ሁሉ ከባዱ መከራም ደም ሳይፈስ በየጊዜው የሚፈጸመው የሰማዕትነት ተጋድሎ ነው በሰይፍ ተቀልቶ እሳት ውስጥ ገብቶ መሞት ቀላል ነው ባይባልም አስፈሪ ቢሆንም በስደት ልዩ ልዩ መከራ ከመቀበልና በየጊዜው ከመፈተን ግን የተሻለ ነው ሰይፍ የሚያስፈራው ለተወሰነ ደቂቃ ነው ስደት ግን በየጊዜው ከሰይፍ በላይ በሚያም መከራ መቆረጥና መሰቃየት ነው እመቤታችን በስደቷ ጊዜ ልጇ እንዳይሞትባት ከሰው ለመሰወር በበረሃው ስትሔድ ግሩማን አራዊት ያስደነግጧት ነበር ሰው ወዳለበት መንደር ስትሔድ ሰዎች ይጣሏታል፡፡
በዚያ ላይ ደግሞ ቀን ሐሩረ ፀሐዩ ሌሊት ቁረ ሌሊቱ እየተፈራረቀባት እሾሁ እየወጋት እንቅፋቱ እየመታት መውጫና መግቢያው በማይታወቅ በረሓ ውስጥ ገብቶ መሰቃየቱ የመንገዱ መጥፋት በዚያ አሰልችና አድካሚ ጉዞ ውስጥ የልጇ በውኃ ጥም መቃጠልና ማልቀስ ለእመቤታችን ሌላው ሰማዕትነት ነበር ይህን ሁሉ መከራ መቀበሏ ግን ሰማዕታትን በስደትና በልዩ ልዩ መከራ ሲሰቃዩ መከራውን እንዲችሉ ያደርጋቸዋል፡፡ለምን ይህ ሁሉ መከራ አገኘን ብሎ ተስፋ እንዳይቆርጡ ተስፋ ይሆናቸዋል ስለዚህ ለምን ይህ ሁሉ መከራ ደረሰብን ብለው ተስፋ እንዳይቆርጡ እመቤታችን ከተወደደ ልጇ ጋር ስደትን ባርካ ሰጠቻቸው እሷን መሠረት አብነት በማድረግም ብዙ ቅዱሳን ለሃይማኖታቸው ለቤተ ክርስቲያናቸው በስደትና በስለት መከራ ተቀበሉ ዋሻ ለዋሻ በረሓ ለበረሓ ተንከራተቱ ግን ተስፋ አልቆረጡም እመቤታችን መጽናኛ ሁናቸዋለችና ስለዚህ እመቤታችን በስለት ከሚፈጸመው መከራ ውጭ ያልተቀበለችው መከራ ስለሌለ እሞሙ ለሰማዕት የሰማዕታት እናታቸው እየተባለች ትመሰገናለች(ቅዳሴ ማርያም)
የቅዱሳንን ገድልና መከራ የሚናገረው ስንክሳር የቤተ ክርስቲያናችን መጽሐፍም ስደት እሳትና ስለት ብቻ አለመሆኑን እየተሰደዱ እየታሠሩ እየተገረፉ መከራ የሚቀበሉትን ቅዱሳን ሰማዕት ዘእንበለ ደም እያለ ይጠራቸዋል ሰማዕት ዘእንበለ ደም ማለትም ደማቸው ሳይፈስ ሰማዕትነትን የተቀበሉ ማለት ነው፡፡የእነዚህ ሰማዕታት ሰማዕትነት አንድ ጊዜ በማይገድል በየጊዜው በሚደርስ መከራ መሰቃየት ነውና፡፡
        በስደቷ ጊዜ ያገኛት መከራ
እመቤታችን ከተወደደ ልጇ ጋር በተሰደደችበት ጊዜ ልዩ ልዩ መከራ አግኝቷታል፡፡መከራውም ለእመቤታችን ኀዘን ጭንቅ ቢሆንም ለእኛ ግን ደስታና ድኅነት ነበር ምክንያቱም ከእመቤታችን በኋላ የነበሩ አባቶቻችንና የነርእሱ ልጆች የሆንነው እኛ ዛሬ ላይ ስደቷን መከራዋን እያሰብን የቻልን ሰውነታችን በጾም እያደከምን ያልቻልን ማኅሌት እየቆምን ለርሷና ለልጇ የምስጋና እጅ መንሻ እያቀረብን በስደቷ ወራት የደረሰባትን መከራ እያዘከርን እንድታማልደን እንማጸንበታለን በረከትም እናገኝበታለን፡፡ አባ ሕርያቆስ በቅዳሴ ማርያም ድርሰቱ ላይ “አዘክሪ ድንግል ንግደቶ ዘምስሌኪ እንዘ ትጐይዪ ምስሌሁ እሀገር ለሀገር በመዋዕለ ሄሮድስ ርጉም አዘክሪ ድንግል አንብዐ መሪረ ዘውኅዘ እምአዕይንትኪ ወወረደ ዲበ ገጸ ፍቁር ወልድኪ አዘክሪ ድንግል ረኀበ ወጽምዐ ምንዳቤ ወኀዘነ ወኵሎ ዐፀባ ዘበጽሐኪ ምስሌሁ፤ርጉም ሄሮድስ በነገሠበት ወራት ከአንቺ ጋር ከአንዱ ሀገር ወደ አንዱ ሀገር የተሰደደውን መሰደድ አሳስቢልን በአይኖችሽና በልጅሽ ፊት የወረደውን መሪር ዕንባ አሳስቢልን ረሀቡን ጥሙን ችግሩንና ኀዘኑን ያገኘሽንም ልዩ ልዩ መከራ አሳስቢልን (ቅዳሴ ማርያም)በማለት እመቤታችን ሔሮድስ በነገሠበት ወራት ከአንዱ ሀገር ወደሌላው ሀገር መሰደዷን፣ ከዓይኗ የፈሰሰውንና በልጇ ፊት የወረደውን ዕንባ አማላጅ አድርጋ እንድታሳስብልን ይናገራል ይህንም ቃል ቅዳሴ ማርያም በተቀደሰበት ቀን ቤተ ክርስቲያናችን ሁልጊዜ ካህናቱ ሥጋውን ደሙን አቀብለው ከተመለሱ በኋላ ትጸልየዋለች እኛን ኀጥአንንም ታማልድበታለች፡፡
እመቤታችን በተሰደደችበት ወራት ካጋጠማት ጭንቅ ጭንቅ መከራ ሁሉ የሚበልጠው በልጇ ላይ የሚመጣው መከራ ነበር ምክንያቱም ሀገር ጥላ የተሰደደችው ተወዳጁን ልጇን ከሞት ለማዳን ነውና፡፡ሄሮድስ አራት ወታደሮችን ከነሠራዊታቸው በሽልማት ሸልሞ እመቤታችን ከነልጇ ይዘው ከመጡ የበለጠ ሹመትና ሽልማት እንደሚጠብቃቸው አብስሮ ልኳቸው ነበር፡፡
የዮሴፍ ልጅ ዮሳ ይህንን ምስጢር ለአባቱ ለዮሴፍና ለእመቤታችን እንዲሁም ለሰሎሜ ለመንገር ከነበረው ኃይል ላይ የአንበሳ ኃይል ተጨምሮለት በፍጥነት ሲጓዝ እያለ የመልካም ነገር ጠላት የሆነው ሰይጣን መንገድ ላይ ጠብቆ ወዴት እንደሚሔድ ጠየቀው ዮሳም በየዋህነት የሚሮጥበትን ጉዳይ ሳይደብቅ ዘርዝሮ ነገረው ሰይጣንም የሄሮድስ ሠራዊት ቀድመው መሔዳቸውን በሔዱበት ፍጥነት ካገኟቸው እንደሚገድሏቸው ዮሳም በከንቱ እንዳይደክም ያዘነ በሚመስል ድምፅ እንዲመለስ ነገረው ዮሳ ግን ሐሳቡን ሳይቀበል ከሞቱም እቀብራቸዋለሁ በሕይወት ካሉም የሆነውንና የታሰበውን ነግሬ እንዲሸሹ አደርጋለሁ ብሎ መገስገስ ጀመረ ኃይል ከእግዚአብሔር ተጨምሮለታልና፡፡
ዮሳ እየሮጠ ሲሔድ መንገድ ላይ አገኛቸውና ገና ከመድረሱ እመቤታችን ያስደነገጠ ሕሊናዋን የረበሸ ምርር ብላም እንድታለቅስ የሚያደርግ አሰቃቂ ዜናን ነገራት እመቤታችንም የዮሳን ቃል ሰምታ ከአንዱ ሀገር ወደ ሌላኛው ሀገር የተሰደድኩት ከሞት ላላድንህ ነውን? ልጄ አንተን ሲገሉህ ከማይ እኔ አስቀድሜ ልሙት በማለት ስታለቅስ ሕፃኑ ኢየሱስ ክርስቶስ በእጁ ዕንባዎቿን በማበስ እንደማይሞት ከነገራት በኋላ ፊቱን ወደ ዮሳ መልሶ ዮሳ ዕሡይ ምጽአትከ (አመጣጥህ ዋጋ የሚያሰጥ መልካም) ነበር ነገር ግን እናቴን አስደንግጠሃታልና በዕለተ ምጽአት አስነሥቼ ዋጋህን እስከሰጥህ ድረስ ይህችን ደንጋይ ተተንተርሰህ ዕረፍ ብሎት ዐርፋል፡፡
እንግዲህ እመቤታችን በስደቷ ወራት ውኃ በመጠማት በመራብ እሾሁ እየወጋት እንቅፋቱ እየመታት ቀን የበረሓው ሐሩር እያቃጠላት ሌሊት ደግሞ ብርዱ እያሳቃያት ትጓዝ ስለነበር ያገኛትን መከራ በቃላት ገልጾ መጨረስ አይቻልም በተለይ ሰው ስታይ ልጇን የሚገድሉባት ስለሚመስላት በጣም ትጨነቅም ታለቅስም ነበር፡፡
አባ ሕርያቆስም በስደትሽ ወራት ያገኘሽን ልዩ ልዩ መከራ ከልጅሽ ዘንድ አሳስቢልን ያለው ያገኛትን መከራ አስባ እኛንም ከአስፈሪ ፈተና እንድታወጣን ነው አባቶችም እመቤታችን መከራዋን እያነሡ ካለቀሱና ከለመኗት ፈጥና እንደምትሰማ በሕይወታቸው ካገኙት ተሞክሮ ተነሥተው ይናገራሉ፡፡ስለዚህ እኛም በወርኀ ጽጌ ስደቷን ስናስብ የራሳችንንም የሀገራችንንም ችግር አብረን ልናስብ ይገባል፡፡በተለይ በሀገር የሚመጣ ችግር ለሁላችንም የሚተርፍ ስለሆነ እመቤታችን የዐሥራት ሀገሯን በአማላጅነቷ እንድትጠብቃት ሁላችንም የቻልነውን ያህል በወርኀ ጽጌ ተግተን ልንጸልይ ማኅሌት ልንቆም በጸሎት ልንበረታ ይገባል አምላካችን እግዚአብሔር የሀገራችን ጥፋት አያሳየን አሜን፡፡
ምንጭ፤ሐመር መጽሔት ፳፮ኛዓመት ቊ ፮ ጥቅምት ፳፻፲ወ፩ ዓ.ም

ኢየሱስ ስዱድ ተስፋሆሙ ለስዱዳን፤ ስደተኛው ኢየሱስ የስደተኞች  ተስፋቸው ነህ (ሰቆቃወ ድንግል)

                                                            በመጋቤ ሐዲስ በርሄ ተስፋ መስቀል

መጽሐፍም ታሪክም እንደሚነግረን በዓለም ብዙ ዓይነት ስደት አለ። ሁሉም ስደቶች ግን የአዳምንና የሔዋንን ስደት ተከትለው የመጡ ናቸው። ቀደምት ወላጆቻችን ሕገ እግዚአብሔርን ባፈረሱ ጊዜ ከገነት ተሰደው ምድረ ፋይድ ወርደዋል (ዘፍ. ፫፥፩፥፲፩)፡፡ ከዚህ በኋላ ከቦታ ወደ ቦታ መሰደድና መንከራተት የሰው ልጅ ዕጣ ፈንታ ሆኗል። በዘመነ ብሉይ የነበሩት ስደተኞችና በምርኮ የተያዙ ሁሉ ስደታቸውን በሚጠት የሚፈፅም፣ ኀዘናቸውን በደስታ የሚለውጥ አንድ መሢሕ እንደሚመጣ በተስፋ ይጠባበቁ  ነበር (መዝ. ፹፬፥፬፣ ሰቆቃወ ኤርምያስ. ፭፥፳፩)፡፡

ሊቁ አባ ሕርያቆስ “አንቲ ውእቱ ተስፋሁ ለአዳም አመ ይሰደድ እምገነት፤ አዳም አባታችን ከገነት በተሰደደ ጊዜ ተስፋው አንቺ  ነሽ” በማለት መናገሩ የአዳምና የሔዋን ሚጠት ማለት ወደ ቀደመው ክብር – ወደ ገነት መመለስ ድንግል ማርያም በወለደችው በክርስቶስ እንደሚሆንና ድንግል  ማርያምም ምክንያተ ድኅነት መሆኗን ለመግለጥ ነው።

በዘመነ ሐዲስም ቢሆን ጽድቅን ፍለጋ የሚሰደዱ እንዳሉ ሁሉ እንጀራን ፍለጋ ሀገር ጥለው ከወገን ርቀው የሚሰደዱ መከራና ግፍ የሚደርስባቸው ክርስቲያኖች አሉ። የእነዚህም ተስፋቸው  ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። ለዚህም ነው ስድተኞቹ በየሔዱበት ዓለም እየተሰባሰቡ የአምልኮ ሥርዓታቸውን የሚያካሔዱት። ይህን በመንፈስ ቅዱስ ምሪት የተገነዘቡት አባ ጽጌ ድንግል “ኢየሱስ ስዱድ ተስፋሆሙ ለስዱዳን ፥ ኢየሱስ  ግፉእ ተስፋሆሙ ለግፉአን”  በማለት  የተናገሩት።

ወደ ዋናው አሳባችን እንመለስና የባሕርይ አምላክ ኢየሱስ ክርስቶስ ከድንግል ማርያም በቤተ ልሔም በተወለደ ጊዜ ሰብአ ሰገል ኮከብ እየመራቸው ­“የተወለደው የአይሁድ ንጉሥ ወዴት ነው” እያሉ ወደ ኢየሩሳሌም መጡ (ማቴ. ፪፥፪)፡፡ ሰብአ ሰገል /የጥበብ ሰዎች ለምን ክርስቶስን የአይሁድ ንጉሥ ብለው ጠሩት? የሚል ይኖራል፦ ስም ላዕላዊ፣ ስም ማዕከላዊ፣ ስም ታሕታዊ የሚባል አለ። ስለዚህ

  • በስም ላዕላዊ – “አይቴ ሃሎ አምላክ /ፈጣሪ ዘተወልደ” ቢሏቸው ምን ሞኞች ናቸው ሰማይና ምድር የማይችሉትን እንዴት ተወለደ ይላሉ ባሏቸው ነበር።
  • በስም ታህታዊ – “አይቴ ሃሎ ሕፃን ዘተወልደ” ቢሏቸው ምን ሞኞች ናቸው በእስራኤል የተወለደው ስንት ሕፃን አለ ስንቱን እናውቃለን? ባሏቸው ነበርና፣
  • ስም ማእከላዊን ወስደው – “አይቴ ሃሎ ንጉሠ እስራኤል ዘተወልደ፤ የተወለደው የአይሁድ ንጉሥ ወዴት ነው?” – ቢሏቸው ሄሮድስ ምድራዊ ንጉሥ መስሎት ንጉሥማ ንጉሥን ሳይሽር ይነግሣልን ብሎ ደንግጧል (ማቴ. ፪፥፫)፡፡

ወንጌላዊው ማቴዎስ እንደ ጻፈልን ሰብአ ሰገል ጌታን ከእናቱ ከድንግል ማርያም ጋር ባገኙት ጊዜ ወድቀው ሰገዱለት ፥ እጅ መንሻውንም አቀረቡለት (ማቴ. ፪፥፪-፲፩) ዓይነቱም ወርቅ ፥ ዕጣን፣ ከርቤ  ነው። የቀረበው እጅ መንሻ እንዲህ መሆኑም ያጋጣሚ ጉዳይ ሳይሆን ምሥጢር አለው።

  • ወርቅ አመጡለት፦ ወርቅ ስንገብርላቸው የነበሩ ነገሥታት ቀድሞም ፍጡራን ኋላም ኃላፍያን ናቸው ፥ አንተ ግን ቀድሞም ያልተፈጠርክ ፥ በኋላም የማታልፍ ዘለዓለማዊ አምላክ ነህ ሲሉ ወርቅ አመጡለት። በተጨማሪም ወርቅ ጽሩይ እንደሆነ አንተም ጽሩየ ባሕርይ ነህ ለማለት ወርቅ አመጡለት።
  • ዕጣን አመጡለት ይህን ስናጥናቸው የነበሩት ጣዖታት ጥንቱም ፍጡራን ፥ ኋላም ኃላፍያን ናቸው ፥ አንተ ግን ቀድሞም ያልተፈጠርክ ኋላም የማታልፍ ነህ ሲሉ ዕጣን አመጡለት። በሌላ አገላለጽ ዕጣን ምዑዝ ነው አንተም ምዑዘ ባሕርይ ነህ ሲሉ ነው።
  • ከርቤ አመጡለት፦ ምንም ቀድሞ ያልተፈጠርክ በኋላም የማታልፍ ብትሆን ለሰው ስትል ፈቅደህ በተዋሐድከው ሥጋ የፈቃድ ሞትን መቀበል አለብህ ሲሉ ከርቤ አመጡለት።

በተጨማሪም ከርቤ የተሰበረውን እንዲጠግን ፥ የተለያየውን አንድ እንዲያደርግ አንተም ከማኅበረ መላእክት የተለየውን አዳምን ጽንዐ ነፍስን ሰጥተህ ወደ ቀደመ ቦታው ትመልሰዋለህ ሲሉ ከርቤ አመጡለት –  በማለት  ሊቃውንት ተርጉመዋል (ትርጓሜ ወንጌለ ማቴዎስ. ፪፥፲፩)፡፡ አዳምን ወደ ቦታው ለመመለስ ከተደረጉ የማዳን ሥራዎች መካከል የጌታ ስደት አንዱ ነው።

ኢትዮጵያዊው ሊቅ አባ ጊዮርጊስ መጽሐፈ ምሥጢር በተባለው ድርሰታቸው፦ “በዚያ በጽርሐ አርያም የሚደነቅ ከማይታይ አብ የመወለድ ምስጋና አለው ፥ በዚህም በቤተ ልሔም ከድንግል መወለድ ምስጋና አለው። በዚያ ከሰማያውያን ካህናት በወርቅ ማዕጠንት የዕጣኑን መዐዛ ይቀበላል ፥ በዚህም ወርቅንና ከርቤን ዕጣንንም ከሰብአ ሰገል ተቀበለ” በማለት ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል (ሉቃ. ፪÷፩-፲፯፣ ራእይ. ፰÷፰-፬፣ ማቴ. ፪÷፲፩፣ መጽሐፈ ምሥጢር ገጽ. ፷፰-፸)፡፡

የጥበብ ሰዎች የተወለደው የአይሁድ ንጉሥ ወዴት ነው? ባሉት ጊዜ ሄሮድስ በጉዳዩ ሰግቶ ሰብአ ሰገልን “ሒዱ ፥ ስለ ሕፃኑ በጥንቃቄ መርምሩ፤ ባገኛችሁትም ጊዜ እኔ ደግሞ መጥቼ  እንድሰግድለት ንገሩኝ” ብሏቸው እንደ ነበር እናስታውሳለን (ማቴ. ፪፥፰)፡፡ ምንም እንኳ ኢየሱስ  ክርስቶስ ነገሥታት የሚሰግዱለት የባሕርይ ንጉሥ መሆኑ እውነት ቢሆንም ነገር ግን ሄሮድስ  መጥቼ እንድሰግድለት ማለቱ በተንኮል ነበር። ስለዚህም የጥበብ ሰዎች ወደ ሄሮድስ እንዳይመለሱ  በሕልም ተረድተው በሌላ መንገድ ወደ ሀገራቸው ሔዱ (ማቴ. ፪፥፲፪)፡፡

ከዚያ በኋላ ነው መልአኩ ለዮሴፍ በሕልም ተገልጾ – “ሄሮድስ ሕፃኑን ሊገድለው ይፈልገዋልና ተነሣ ሕፃኑንና እናቱንም ይዘህ ወደ ግብፅ ሸሽ ፥ እስክነግርህም ድረስ በዚያ ተቀመጥ” በማለት የተናገረውና ጻድቁ ዮሴፍ ሕፃኑንና እናቱን ድንግል ማርያምን ይዞ በሌሊት ወደ ግብፅ የተሰደደው (ማቴ. ፪፥፲፫) ሄሮድስም ሰብአ ሰገል እንደ ተሳለቁበት ባወቀ ጊዜ የአይሁድ ንጉሥ ኢየሱስ ክርስቶስን ያገኘ መስሎት እጅግ ብዙ ሕፃናትን ፈጅቷል (ማቴ. ፪፥፲፮)፡፡ ጌታችን ግን ጊዜው ሳይደርስ ደሙን ሊያፈስ ፥ ሊሞትም አይገባምና ከሄሮድስ ፊት ያመልጥ ዘንድ ከእናቱ ጋር ተሰዷል።

ኢየሱስ ክርስቶስ ለምን ተሰደደ፤ ለምንስ ስደቱን ወደ ግብፅ አደረገው?

ክብር ምስጋና ይግባውና ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የተወለደበት ምክንያት እንዳለው ሁሉ የተሰደደበት እና ስደቱን ወደ ምድረ ግብፅ ያደረገበት ምክንያትም አለው። ይኸውም፡-

  • ትንቢተ ነቢያትን ለመፈጸም ነው፣

የዓለም መድኃኒት ኢየሱስ ክርስቶስ በዘመነ ሥጋዌው ያደረጋቸው ነገሮች በሙሉ አስቀድሞ በልብ የመከረውን ፥ ኋላም በነቢያት ያናገረውን ለመፈፀም እንጂ በአጋጣሚ የተከናወኑ አይደሉም። ወደ ግብፅ እንደሚሰደድም ትንቢት ተነግሮለት ነበር። “ከጌታ ዘንድ በነቢይ፦ ልጄን ከግብፅ ጠራሁት የተባለው እንዲፈጸም ወደ ግብፅ ሔደ ፥ ሄሮድስም እስኪሞት ድረስ በዚያ ኖረ” (ማቴ. ፪፥፲፬-፲፭) እንዲል፡፡ ነቢያት ትንቢታቸውን ሲናገሩ የጌታችንን መሰደድ ብቻ ሳይሆን ከማን ጋር ፥ ወዴት እንደሚሰደድ፣ በስደቱ ጊዜ ምን ምን እንደሚሠራ በግልፅ አስቀምጠውታል። የክርስትናን  አስተምህሮ እርግጠኛ የሚያደርገውም ይህ ነው።

ከነቢያቱ መካከል ነቢዩ ኢሳይያስ መንፈሰ እግዚአብሔር መርቶት ቅድስት ድንግል ማርያም የባሕርይ አምላክ ኢየሱስ ክርስቶስን ይዛ ወደ ምድረ ግብፅ እንደምትሰደድ “እነሆ እግዚአብሔር በፈጣን ደመና እየበረረ ወደ ግብፅ ይመጣል” (ኢሳ. ፲፱፥፩) በማለት ተናግሯል። ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ድንግል ማርያምን “አፍጣኒተ ረድኤት ማርያም በጊዜ ምንዳቤ ወአጸባ ለዓይን እምቀራንባ፤ በኀዘንና በችግር ጊዜ ሰውን ለመርዳት ከዓይን ጥቅሻ ይልቅ ድንግል ማርያም ፈጣን ናት” እያለች የምታመሰግነው ለዚህ ነው። ይህን የኢሳይያስን ትንቢት ሁለት ኢትዮጵያውያን ሊቃውንት እንደሚከተለው አመስጥረው ተርጉመውታል፡፡

  • ቅዱስ ያሬድ

መዓዛ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ያሬድ “… ኢሳይያስ ነቢይ ፥ ልዑለ ቃል እም ነቢያት ከልሐ ወይቤ እግዚአብሔር ጸባኦት ይወርድ ብሔረ ግብፅ፤ ከነቢያት ይልቅ ድምፁ ከፍ ያለው ነቢዩ ኢሳይያስ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር ወደ ግብፅ ምድር ይወርዳል ብሎ አሰምቶ ተናገረ። – ደመና ቀሊል ዘይቤ ኢሳይያስ ይእቲኬ ማርያም ድንግል እንተ ጾረቶ በከርሣ ለወልደ እግዚአብሔር፤ ኢሳይያስ ፈጣን ደመና ብሎ የተናገረላትም የእግዚአብሔር የባሕርይ ልጁን በማሕፀኗ የተሸከመችው ድንግል ማርያም ናት” (መዋሥዕት) በማለት አብራርቶታል፡፡

  • አባ ጊዮርጊስ ዘጋሥጫ

ዐምደ ሃይማኖት የተሰኘው ቅዱስ አባ ጊዮርጊስም “ሄሮድስ ኃሠሠ ዘኢይትረክብ ወእግዚእ ተግሕሠ ውስተ ምድረ ግብፅ ፥ ተጽዒኖ ዲበ ደመና ቀሊል ፥ በከመ ይቤ ኢሳይያስ – ናሁ እግዚአብሔር ይወርድ ውስተ ምድረ ግብፅ ተጽዒኖ ዲበ ደመና ቀሊል ፥ ደመናሰ ቀሊል አንቲ ክመ ኦ ቅድስት ድንግል፤ ሄሮድስ የማያገኘውን ፈለገ ጌታም በፈጣን ደመና ተጭኖ ወደ ግብፅ ምድር ሔደ ፥ ነቢዩ ኢሳይያስ እነሆ እግዚአብሔር በፈጣን ደመና ተጭኖ ወደ ግብፅ ምድር ይወርዳል ብሎ እንደ ተናገረ፥ ቅድስት ድንግል ሆይ ፈጣን ደመና መቼም መች ቢሆን አንቺ ነሸ። … እግዚአብሔር ተአንገደ ውስተ ምድረ ግብፅ ተሐዚሎ በዘባን፤ … እግዚአብሔር በጀርባሽ ታዝሎ በግብፅ ምድር እንግዳ ሆነ” (አርጋኖን ዘሰኑይ) እንዲል፡፡

የተከበራችሁ አንባብያን ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን እግዚአብሔርን የምታገለግልባቸው፥ ምእመናንን የምታስተምርባቸው ድርሳናት እንዳሏት እሙን ነው። እነዚህ ሁሉ መሠረታቸው መጽሐፍ ቅዱስ መሆኑንም ከሁለቱም ሊቃውንት ልናስተውል ይገባል። ከዚህ የተነሣ የማኅሌቱ፣ የቅዳሴውና የሰዓታቱ መሠረት መጽሐፍ ቅዱስ ነው ብለን መናገር እንችላለን። በሌላ አገላለጽ ድርሳናት ገድላት መደበኛ ሥራቸው ረቂቅ ምሥጢር የሆነውን መጽሐፍ ቅዱስ ማመሥጠር፥ ማብራራት ፥ መተርጎም መሆኑን ከሊቃውንቱ ድርሰት ተምረናል። ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን  ትምህርቷ ምሉእ ፥ እምነቷ ርቱዕ የሆነውም በዚህ ምክንያት ነው።

አምልኮ ጣዖትን ለማጥፋት ነው

ጌታችን ወደ ግብፅ የተሰደደበት ምክንያት አለው ያልነው እዚህ ላይ ይገለጻል። ይኸውም በዚያ ጊዜ ግብፃውያን ክሕደት ወይም አምልኮ ጣዖት ጸንቶባቸው ነበርና ይህን ክፉ አምልኮ ጣዖት ለማጥፋት፣ ለመደምሰስ ክርስቶስ ስደቱን ወደ ግብፅ አድርጎታል። ታላቁ ነቢይ ኢሳይያስ “እነሆ እግዚአብሔር በፈጣን ደመና እየበረረ ወደ ግብፅ ይመጣል።” ካለ በኋላ ዓላማውን ሲገልጽ  “የግብፅም ጣዖታት በፊቱ ይርዳሉ” ብሏል (ኢሳ. ፲፱÷፩)፡፡ ሊቁ ቅዱስ ያሬድም ጌታችን ወደ ግብፅ የተሰደደበትን ምክንያት ሲያስረዳ እንዲህ ብሏል፡- ይፈጽም ትንቢተ የሐድስ ብሊተ፤ ይክሥት  መንክራተ ፥ ዘሀሎ መልዕልተ፤ ለቢሶ ስብሐተ ፥ ብሔረ ግብጽ ቦአ ይሥዐር ጣዖተ፤ ወይንሥት ኵሎ ግልፍዋተ፤ ትንቢትን ይፈጽም ዘንድ፣ አሮጌውንም ያድስ ዘንድ፣ በላይ ያለውን ድንቅ ነገር  ይገልጥ ዘንድ፣ ምስጋናን ተጎናጽፎ ጣኦታትን ሊሽር፣ ምስሎችንም ሁሉ ሊያፈርስ ወደ ግብፅ ምድር ገባ /ድጓ ዘበአተ ግብፅ/ ሌላው ኢትዮጵያዊው ሊቅም ሰቆቃወ ድንግል በተሰኘው ድርሳኑ ድንግል ማርያምን ከታቦተ ጽዮን ጋር በማነጻጸር እንዲህ  ብሏል፡-

ታቦተ አምላክ እስራኤል ጽዮን ዘነገደት ምድረ ኢሎፍሊ፤ ወቀጥቀጠቶ ለዳጎን ነፍሳተ ብዙኅን ማህጎሊ፤ አመ ነገደት ቍስቋመ በኅይለ ወልደ ከሃሊ፤ ወድቁ አማልክተ ግብጽ መናብተ ሰይጣን ሐባሊ፤ ወተኅፍሩ ኵሎሙ ዘቦሙ አስጋሊ። ወደ ኢሎፍሊ ምድር ተማርካ የሄደች የእስራኤል አምላክ የቃል ኪዳኑ ታቦት ታቦተ ጽዮን፥ የብዙዎችን  ነፍሳት ያጠፋ ዳጎንን  ሰባበረችው። ድንግል ማርያምም ሁሉን ማድረግ በሚችል  ልጇ   ግብፅ ወደሚባል ሀገር በሔደች ጊዜ የሐተሰኛ ሰይጣን ዙፋኖች የሆኑ የግብፅ ጣዖታት ፈረሱ ፥ ጠንቋይ  አስጠንቋይ ያላቸው ሁሉ  ዐፈሩ (ሰቆቃወ ድንግል)፡፡

ከዚህ የምንረዳው የጌታችንና የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ስደት ተራ ስደት ሳይሆን ሰዎችን ከአምልኮ ጣዖት ወደ አምልኮቱ ማለትም ወደ አምልኮተ እግዚአብሔር ለማምጣት የተደረገ  መሆኑን መረዳት ተገቢ ነው። ስለዚህ  ጌታ  በስደቱ  ሰዎችን ከክህደት አድኗል ማለት ነው።

  • ስደትን ለሰማዕታት – ለቅዱሳን ሁሉ ባርኮ ለመስጠት

መልካም እረኛ በበጎቹ ፊት ይሔዳል። “የራሱንም ሁሉ ካወጣቸው በኋላ በፊታቸው ይሔዳል ፥ በጎቹም ድምፁን ያውቃሉና ይከተሉታል፤” (ዮሐ. ፲፥፬) እንዲል፡፡ መልካሙ እረኛ ክርስቶስ ሲሆን በጎች የተባሉትም ደጋጎቹ ምእመናን ናቸው። በፊታቸው ይሔዳል ሲል፡- ኢየሱስ ክርስቶስ መምህር፥ መሪ እንደ መሆኑ መጠን ምእመናንን ይመራቸዋል እንጂ በኋላ ሆኖ አይነዳቸውም። ይህ ማለት እኛ ክርስቲያኖች ልናደርጋቸው የሚገቡ ነገሮችን በሙሉ እርሱ አስቀድሞ በተግባር ፈጽሞ አሳይቶናል። ስለዚህ የክርስቲያኖች ትክክለኛው አርአያ አብነት ክርስቶስ ነው። መጠመቁን አብነት አድርገን ተጠምቀናል (ማቴ. ፫፥፲፮-፲፯)፣ መጾሙን አብነት አድርገን እንጾማለን (ማቴ. ፬፥፩-፲)፣ የምንጸልየው መምህራችን ኢየሱስ ክርስቶስ  በጌቴሴማኒ ስለ ጸለየ ነው (ማቴ. ፳፮-፵፩)፣ ጠላታችንን ይቅር ማለት ያለብን ክርስቶስን አብነት አድርገን ነው። (ቆላ. ፫፥፲፫)፤በፊት መሔድ ማለት ለመልካም  ነገር  ሁሉ  አብነት  አርአያ መሆን  ማለት ነው።

እንደዚሁ ሁሉ በመሰደዱ ምክንያት ስለ ጽድቅ ብለው ለሚሰደዱ ቅዱሳን፣ መናንያን ባሕታውያን ሁሉ አብነት ሆኗል። ጥምቀታችንን፣ ጾም ጸሎታችንን እንደ ባረከ ሁሉ፥ ስደቱንም ባረኮ ጀምሮ ሰጥቶናል። ለዚህም ነው “ስለ ጽድቅ የሚሰደዱ ብፁዓን ናቸው ፥ መንግሥተ ሰማያት የእነርሱ ናትና።” (ማቴ. ፭፥፲) በማለት የተናገረው፡፡

ጻድቃን ፥ ሰማዕታት በአጠቃላይ ቅዱሳን ሁሉ ክርስቶስን ተስፋ አድርገው ሀብትን ንብረትን ትተው ፥ ዓለምን ንቀው ተሰደዋል። ክርስቶስ በስደቱ ጊዜ ብዙ መከራዎችን እንደ ተቀበለ ቅዱሳንም  በዓላውያን ነገሥታት፣ ክፋት በጸናባቸው ሰዎች እጅግ ብዙ መከራን ተቀብለው ተሰደዋል። በዚህም ዋጋቸውን አግኝተዋል። ስለዚህ እራሱ ባርኮ ባይሰጠን ኖሮ ስደትን ማንም አይችለውም ነበር።

ከዚህ ሁሉ መረዳት የሚቻለው ክርስቶስ አብነት ያልሆነበት የጽድቅ፣ የበረከት ሥራ እንደሌለ ነው። ይህ ማለት ኢየሱስ ክርስቶስ ክርስቲያኖች ሊያደርጓቸው የሚገቡ መልካም ነገሮችን ሁሉ አስቀድሞ አድርጓቸዋል። በመሆኑም ክርስቲያኖች ሁሉ እረኛችንን ክርስቶስን አውቀን፣ ድምፁንም ለይተን በመረዳት በመልካም ነገር ሁሉ እረኛችንን ክርስቶስን እንመስል ዘንድ ይገባናል ማለት ነው።

  • ወደ ቀደመው ርስታችን ሊመልሰን ተሰዷል

ከላይ እንደ ተገለጠው የመጀመሪያው ስደተኛ አዳም ነው። በመቀጠልም ልጆቹ ሁሉ ስደተኞች ሆነዋል። ስለዚህ ዳግማይ አዳም ክርስቶስ የተሰደደው አዳምንና ልጆቹን ፍለጋ ነው (ሉቃ. ፲፭፥፩-፱)፡፡ ከዚህ በመነሣት ነው ሊቁ ቅዱስ ዮሐንስ አፈ ወርቅ “…ዘሐሰሶ ለበግዕ ግዱፍ ወሶበ ረከቦ ፆሮ ዲበ መትከፍቱ፤ የጠፋው በግ አዳምን የፈለገው ፥ ባገኘውም ጊዜ በትክሻው የተሸከመው እውነተኛ እረኛ” /ሃይማኖተ አበው ዘዮሐንስ አፈወርቅ/ በማለት የተናገረው። ከዚህ አኳያ የቀዳሚት ሔዋን ስደትም በዳግማዊት ሔዋን ድንግል ማርያም ስደት ተክሷል፡፡

መልአከ እግዚአብሔር ዮሴፍ ድንግል ማርያምን ይዞ እንዲሰደድ እንደ ነገረው ሁሉ ሦስት ዓመት ከስድስት ወራት ከሆናቸው በኋላ መልአኩ እንደገና “የሕፃኑን ነፍስ የፈልጉት ሞተዋልና ተነሣ ፥ ሕፃኑን እናቱንም ይዘህ ወደ እስራኤል ሀገር ሒድ” (ማቴ. ፪፥፳) በማለት ነግሮታል፡፡ ልብ በሉ ገዳዩ ሞተ ፥ ሊገደል የታሰበው ሕያው ሆነ። ዮሴፍም ሕፃኑን ክርስቶስን ከእናቱ ከድንግል ማርያም ጋር እንደ ተሰደደ ይዟቸው ወደ እስራኤል ተመልሶ ገባ (ማቴ. ፪፥፳፩) መንግሥተ ሰማያት የሚገቡት እነማን ናቸው ቢሉ ጌታን ከእናቱ ጋር የያዙት ናቸው።

ማጠቃለያ

የጌታችን ስደት ጠላታችን ዲያብሎስ ከሰዎች ልብ ወጥቶ እንዲሰደድ ያደረገ በመሆኑ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን በሚገባ ታከብረዋለች፡፡ ለዚህም ነው ሊቃውንቱ “ጕየተ ሕፃን አጕየዮ ለዲያብሎስ፤ የሕፃኑ ስደት ዲያብሎስን እንዲሸሽ አድርጎታል” በማለት የሚገልጡት።የተከበራችሁ የልዑል እግዚአብሔር ወዳጆች! ድንግል ማርያም ልጇን ወዳጇን ኢየሱስ ክርስቶስን ይዛ፣ ዮሴፍንና ሰሎሜን አስከትላ ከእስራኤል እስከ ግብፅ፥ ከዚያም እስከ ኢትዮጵያ በመሰደድ ለሦስት  ዓመት ከስድስት ወር እጅግ ብዙ መከራን ተቀብላለች (ራእ. ፲፪፥፩-፮፤ ፲፬-፲፰)፡፡

 አባ ጊዮርጊስ ዘጋሥጫ “እወ አማን እምውሉደ ሰብእ አልቦ ፥ ምንዳቤ ወግፍእ ዘከማኪ በውስተ ዓለም ዘረከቦ፤ ድንግል ሆይ! አዎን በእውነት ከሰው ልጆች መካከል በዚህ ዓለም እንደ አንቺ ችግርና መከራ የደረሰበት የለም” በማለት እንደመሰከሩት መከራዋም ልዩና እጅግ ብዙ ነው። በዚህም ድንግል ማርያም በነገረ ድኅነት ውስጥ የማይተካ ሚና ያላት መሆኑን መረዳት ይገባል። በተጨማሪም እናቶች ለልጆቻቸው ምን ያህል መሥዋዕትነት መክፈል እንዳለባቸው ያስተማረች የሕይወት  መምህር መሆኗን መገንዘብ ብልህነት ነው። የጌታ ስደት ስደታችንን፣ ሚጠቱ ሚጠታችንን የሚያመለክት ነው። በሌላ አገላለጥ የድንግል ማርያም ስደት የሔዋንን ስደት፣ ሚጠቷም እናታችን ሔዋን በዳግማዊት ሔዋን በድንግል ማርያም መመለሷን ያሳያል። የዮሴፍና የሰሎሜ ስደት የደቂቀ  አዳም ሁሉ ስደትን የሚያሳይ ሲሆን ሚጠታቸውም የአዳም ዘር ሁሉ በክርስቶስ የማዳን ሥራ ወደ ቀደመው ክብራችን፣ ወደ ገነት መመለሳችንን ያመለክታል። እንዲህም ስለሆነ ግብፅ የሲኦል ምሳሌ ፥ ኢየሩሳሌምም የገነት ምሳሌ ናት፡፡ በዚህ መሠረት ኢየሱስ ክርስቶስ ከእስራኤል ወደ ግብፅ ተሰዶ እንደገና ወደ እስራኤል መመለሱ፥ ከገነት የተሰደደው አዳም በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ስደትና አጠቃላይ የማዳን ሥራ ወደ ጥንተ ክብሩ መመለሱን የሚያጠይቅ ነው። እግዚአብሔር ከተሰደድንበት የጽድቅ ሥራ በንስሓ ይመልሰን፥ የድንግል እናቱን በረከትና ረድኤት ያድለን።

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

ምንጭ፤ስምዐ ጽድቅ ጋዜጣ ፳፮ኛዓመት ቁ፪/ቅጽ ፳፮ ቁጥር ፫፻፺፭ ከጥቅምት፩-፲፭ ቀን፳፻፲ወ፩ ዓ.ም

 

 

ሁለት አገልጋዮች በድንገተኛ የመኪና አደጋ ሕይወታቸው ዐለፈ

በካሣሁን ለምለሙ
የነቀምቴ ማእከል አገልጋይ የነበሩት ዲ/ን መልካሙ ረጋሳ እና ዲ/ን ሽፈራው ከበደ በገተማ ወረዳ ለአገልግሎት ሲፋጠኑ መስከረም ፳ቀን ፳፻፲፩ ዓ.ም በደረሰባቸው ድንገተኛ የመኪና አደጋ ሕይወታቸው ዐለፈ፡፡
ዘማሪ ዲ/ን መልካሙ ረጋሳ የነቀምቴ ማእከል ጸሐፊ የነበረ ሲሆን በ፲፱፻፹፮ ዓ.ም ከእናቱ ከወ/ሮ አሙሴ ተፈራ እና ከአባቱ አቶ ረጋሳ ተወለደ፡፡፡ ዘማሪ ዲ/ን መልካሙ ገና በልጅነቱ የብዙ ሙያዎች ባለቤት የነበረና የተለያዩ ጽሑፎችን፣ መንፈሳዊ ግጥሞችን እንዲሁም ዋሽትና ሌሎች መንፈሳዊ የዜማ መሣሪያዎችን ጭምር መጫወት የሚችል ነበረ፡፡ወንጌልን እየተዘዋወረ ከማስተማሩ በተጨማሪ በርካታ የመዝሙር ካሴቶችን አውጥቶ ለአገልግሎት አውሏል፡፡ ከልጅነቱ ጀምሮም ከቤተ ክርስቲያን ያልተለየና ዘወትር ቤተ ክርስቲያንን በዲቁናና በዝማሬ ሲያገለግል ቆይቷል፡፡
በ፳፻፭ ዓ.ም 12ኛ ክፍልን ካጠናቀቀ በኋላ መንፈሳዊ ሥዕላትን ይሥል ነበር፡፡ በአፋን ኦሮሞ የመዝሙር ካሴቶችን አበርክቷል፡፡ ዘማሪ ዲ/ን መልካሙ በትሕትና የሚታወቅና ያለ አባት ያሳደጉትን እናቱንና አያቱን በቻለው መጠን የሚረዳ ሲሆን በሰንበት ትምህርት ቤት ውስጥ ያሉ ሕፃናትን ዘወትር ነገረ ሃይማኖት የሚያስተምርና የዕድሜ እኩዮቹን የሚመክር በመሆኑ ለሁሉም ምሳሌ የሆነ ወጣት አገልጋይ ነበር፡፡
ዘማሪ ዲ/ን መልካሙ ለቅድስት ቤተ ክርስቲያን አገልግሎት ወደ ገተማ ደብረ ገነት ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን ከአገልጋይ ወንድሙ ከዲ/ን ሽፈራው ከበደ ጋር እየሔዱ ሳለ መስከረም ፳ ቀን ፳፻፲፩ ዓ.ም በደረሰባቸው ድንገተኛ የመኪና አደጋ ከጠዋቱ አንድ ሰዓት አካባቢ በተወለደ በ፳፬ ዓመቱ ሕይወቱ ዐልፏል፡፡

ዘማሪ ዲ/ን መልካሙ ረጋሳ

ለሰንበት ትምህርት ቤት ወጣቶችና ጽዋ ማኅበራት የተሐድሶ መናፍቃንን ጥፋት በተመለከተ ሥልጠና ለመስጠት እንዲሁም የገተማ ወረዳ ማእከል አባላትን ለመቃኘት እየሔዱ በነበረበት ወቅት አደጋው እንደደረሰባቸው የነቀምቴ ማእከል ያደረሰን መረጃ ያመለክታል፡፡
ሌላኛው ድንገተኛ የመኪና አደጋ ደረሰበት ዘማሪ ዲ/ን ሽፈራው ከበደ ኢትቻ ሲሆን ከአባቱ ከአቶ ከበደ ኢትቻ እና ከእናቱ ከወ/ሮ እየሩስ አለቃ በ፲፱፻፹፫ ዓ.ም በምሥራቅ ወለጋ ኪራሙ ወረዳ ሶምቦ ቀበሌ ገበሬ ማኅበር ተወለደ፡፡
ከ፩-፲ኛ ክፍል በኪረሙ አንደኛ እና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ትምህርቱን የተከታተለ ሲሆን ኤልፓ ኮሌጅ ጂማ ድስትሪክት የኮሌጅ ትምርቱን በጥሩ ውጤት አጠናቅቋል፡፡ በ፲፱፻፺፱ ዓ.ም በኪረሙ ቅድስት ሥላሴ ቤተ ክርስቲያን ዲቁናን ተቀብሎ ሲያገለግል ቆይቷል፡፡
በምዕራብ ወለጋ ባቦ ጋምቤላ ወረዳ፣ ህዳሴ ቴሌኮም ጋምቤላ፣ ነጆ ህዳሴ ተሌኮም እንዲሁም በነቀምቴ ከተማ ህዳሴ ቴሌኮም ውስጥ ከቤተ ክርስቲያን አገልግሎት በተጨማሪ ሀገሩን አገልግሏል፡፡
በኪረሙ ቅድስት ሥላሴ ሰንበት ትምህርት ቤት አባል እና ሥራ አስፈጻሚ የነበረ ሲሆን በማኅበረ ቅዱሳንም ከመደበኛ አባልነት ጀምሮ እስከ ሥራ አስፋጻሚነት አገልግሏል፡፡ በነጆ ወረዳ ማእከል ሒሳብና ንብረት ክፍል ሓላፊ እንዲሁም በነቀምቴ ማእከል ደግሞ የሰው ኃይል ልማት እና አስተዳደር በመሆን ሠርቷል፡፡
ዲ/ን ሽፈራው ከበደ የተሐድሶ መናፍቃን እንቅስቃሴ በተመለከተ ለምእመናንና ለአገልጋዮች በደብረ ገነት ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን ሥልጠና ይሰጥ እንደነበር ተገልጧል፡፡በሕይወቱ ትሑት፣ ታዛዥ እና በሕዝበ ክርስቲያኑ ዘንድ የሚወደድና በአገልግሎቱም አርአያ የሆነ ወጣት አገልጋይ ነበረ፡፡ ዲ/ን ሽፈራው ከበደ ባለ ትዳር እና የአንድ ወንድ ልጅ አባት ነበረ፡፡
ለአገልግሎት እየሔደ እያለ መስከረም ፳ ቀን ፳፻፲፩ ዓ.ም በደረሰበት ድንገተኛ የመኪና አደጋ በተወለደ በ፳፯ ዓመቱ ከዚህ ዓለም በሞት ተለይቷል፡፡ ዝግጅት ክፍሉም ለቤተሰቦቻቸውና ለመላው ሕዝበ ክርስቲያን መጽናናትን እየተመኘን እግዚአብሔር አምላክ የሟቾቹን ነፍስ በአፀደ ገነት እንዲያኖር እንጸልያለን፡፡

ዲ/ን ሽፈራው ከበደ

ምንጭ፤ስምዐ ጽድቅ ጋዜጣ ፳፮ኛዓመት ቁ፪/ቅጽ ፳፮ ቁጥር ፫፻፺፭ ከጥቅምት፩-፲፭ ቀን፳፻፲ወ፩ ዓ.ም

የኢትዮጵያውያን ይዞታ በሆነው በዴርሱልጣን ገዳም የቅዱስ ሚካኤል ቤተመቅደስ እድሳት ላይ የግብጽ ኮፕቲክ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን አባላት ያሳዩትን ሕገወጥ ተቃውሞ አስመልክቶ ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ የተሰጠ መግለጫ፤

በስመአብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱአምላክ አሜን!

ሁላችሁም እንደምታውቁት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን በኢየሩሳሌም ካሏት ጥንታውያንና ታሪካውያን ቅዱሳት መካናት ውስጥ አንዱና ዋናው በዴርሱልጣን የሚገኘው የመድኀኔዓለም፣ የአርባዕቱ እንስሳ እና የቅዱስ ሚካኤል ገዳማት ናቸው፡፡ከታሪክ እንደምንረዳው ኢትዮጵያውያንበምድረ እስራኤል የነበራቸው ርስት ከሦስት ሽህ ዓመት በላይ ያስቆጠረ ነው፡፡ በብሉይ ኪዳን የአሁኗ ኢትዮጵያ መልክዓ ምድራዊ መገኛዋን ከዓባይ ምንጭ ጋር በማያያዝ ያለምንም ማሳሳት ከአርባ ጊዜ በላይ የተመዘገበች፤ በታሪክ፣ በእምነትና በማኅበራዊ ትሥሥር ከእስራኤል ጋር የጸና ግንኙነት ያላት ሀገር ናት፡፡
ከንግሥተ ሳባ የኢየሩሳሌም ጉብኝት ጀምሮ ኢትዮጵያውያን ወደ ቅድስት ሀገር ያለማቋረጥ በየዓመቱ በዓለ ፋሲካን ለማክበር፣ ዓመታዊ አምልኮተ እግዚአብሔርን ለመፈጸም፣ በርስት የተሰጣቸውን ይዞታ ለማስከበርና በንግድ ሥራዎች ይጓዙ እንደነበር በታሪክም በቅዱሳት መጻሕፍትም የተረጋገጠ እውነት ነው፡፡
ለዚህም በሐዲስ ኪዳን ክርስትና ወደ ኢትዮጵያ ለመግባቱ ምክንያት የሆነውና በሐዋርያት ሥራ ምዕራፍ 8 ከቁጥር 26 እስከ 40 የተጻፈው የኢትዮጵያዊው ጃንደረባ ታሪክ አንዱ ማሳያ ነው፡፡
ኢትዮጵያውያን ወደ ኢየሩሳሌም በሚያደርጉት ጉዞ፣ መንፈሳዊና ማኅበራዊ ትሥሥርን ከማጠናከር ባሻገር በዴርሱልጣን እና በብዙ መካናት ቋሚ ይዞታን በማቋቋም በርካታ ገዳማትንና አድባራትን መሥርተዋል፣ መንበረ ጵጵስናም አቋቁመዋል፡፡ ይህም ድርጊት ኢትዮጵያ በኢየሩሳሌም የሕዝቦቿ ምልክትና መመኪያ እድትሆን አድርጓታል፡፡
ይሁን እንጅ ነባሩን ታሪካዊ እውነት ለመሻርና በማይገባ ሁኔታ ግብፃውያን በሌላቸው መብትና ሕጋዊ ባልሆነ የፈጠራ መረጃ ኢትዮጵያን ከኢየሩሳሌም የዴርሱልጣን ገዳም ባለቤትነቷን ለማሳጣት ብዙ ጥረቶች ሲደረጉ ቢቆዩም ኢትዮጵያውያን ሕይወታቸውን ሳይቀር መስዋዕት በማድረግ ሃይማኖታቸውንና ጥንታዊ ገዳማቸውን ጠብቀው እስከ አሁን ቆይተዋል፡፡
የኢትዮጵያውያን የኢየሩሳሌም ይዞታ ከቅዱሳት መጻሕፍት ማስረጃነት በተጨማሪ ኢየሩሳሌምን ይገዙ በነበሩ መሪዎች የግብርና የመንግሥት አዋጅ መዛግብት፣ ኢየሩሳሌም ድረስ ተጉዘው ታሪክ በጻፉ ምሁራን፣ በኢየሩሳሌም ተሳላሚዎች የግል ማስታወሻ እና በዓለም አቀፍ መዛግብት ሳይቀር የተመዘገበ ሐቅ ነው፡፡
ለምሳሌ ያህልም እንደነ አባ ጀሮም ያሉ የላቲን ታሪክ ጸሐፊዎች፣ እንደነ ከሊፋ ዑመርና ሳላሐዲን ባሉ ገዥዎች፣ በኢየሩሳሌም ተመሳሳይ ይዞታ ባላቸው በአርመንና በሶርያ ኦሬንታል ኦርቶዶክስ አብያተ ክርስቲያናት፣ በግሪክና በራሽያ የምሥራቅ ኦርቶዶክስ አብያተ ክርስቲያናት እንዲሁም በካቶሊክ ቤተክርስቲያን ልዩ ልዩ ገዳማት መዛግብት የተመሰከረ ነው፡፡
ይሁን እንጅ ግብፃውያን በሚፈጥሩት ግፍና ኢሰብዓዊ ድርጊት በይዞታችን ያለውን ገዳም ከጉዳት ለመጠበቅና ለማደስ አንኳ ሳንችል በመቅረታችን እየፈራረሰ ይገኛል፡፡
በመሆኑም ቤተክርስቲያኒቱ ስታሰማ በነበረው ተደጋጋሚ አቤቱታና የኢትዮጵያ መንግሥት ባቀረበው ሕጋዊ የመብት ጥያቄ መሠረት የእስራኤል መንግሥት ገዳሙን ለማደስ ቃል በመግባቱ እና በዚሁ መሠረት መንግሥት ቃሉን በመጠበቅ በቅርቡ ጉዳት ከደረሰበት ከቅዱስ ሚካኤል ቤተመቅደስ እድሳቱ በመጀመሩ የተሰማንን ከፍተኛ ደስታ በቅድስት ቤተክርስቲያን እና በመላው ኢትዮጵያውያን ስም በመግለጽ ልባዊ ምስጋናችንን እናቀርባለን፡፡
የተጀመረው እድሳት በዴርሱልጣን የሚገኙ እና እጅግ በአስከፊ ጉዳት ላይ ያሉ ሁሉንም የኢትዮጵያ ይዞታዎች በማዳረስ ገዳሙ ጥንታዊ ይዞታውን ጠብቆ ለትውልድ እንዲተላለፍ እንደሚደረግልን እናምናለን፡፡
አሁን እየተደረገ ያለውን ጥገና አስመልክቶ የኢትዮጵያ መንግሥትም ሆነ በመላው ዓለም የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ለእስራኤል መንግሥት ምስጋናችሁን እንድታቀርቡልን የግብጽ ቤተክርስቲያንን መሠረት የለሽ ክስና ሁከት በመቃወም ገዳማችሁን በመጠበቅ የበኩላችሁን እንድትወጡ፣ ወደ ፊትም ከግብጽ ያልተመለሱ ይዞታዎቻችንን ለማስመለስ ሁለንተናዊ እንቅስቃሴ እንድታደርጉ ጥሪ እናደርጋለን፡፡

በዚሁ አጋጣሚየ ግብጽ ኮፕቲክ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን አባላት በይዞታችን ላይ አግባብነት የሌለው ሥራን የማደናቀፍና በታሪክም ሆነ በማንኛውም የሰነድ ማስረጃ መሠረት የሌለው የባለቤትንት ጥያቄ በማንሣት እየፈጠሩት ያለውን አላስፈላጊ ሁከትና ብጥብጥ እንዲያቆሙ፣
ዴርሱልጣን የኢትዮጵያ ገዳም ምንጊዜም ቢሆን የኢትዮጵያ የነበረና ወደፊትም የኢትዮጵያ ሆኖ የሚቆይ ታሪካዊና ሃይማኖታዊ ቅርሳችን፣ የኢትዮጵያውያን በኢየሩሳሌም ቅድስት ሀገር በሁሉም ዘመን በቋሚነት ለመገኝታቸው ምስክር ስለሆነ ከዚህ የተሳሳተ ትንኮሳና ሁከት እንዲታቀቡ ጥሪያችንን እናስተላልፋለን፡፡
በመጨረሻም የተጀመረው የእድሳት ሥራ ተጠናክሮ በመቀጠል ሁሉንም የኢትዮጵያ የዴርሱልጣን ይዞታዎች በአግባቡ እንዲጠገኑልን፣
በኢትዮጵያ መንግሥትም ሆነ የሰው ልጅ ቅርስ ጥበቃ ለሚያሳስባቸው በጎ አድራጊዎች ሁሉ ጥሪያችንን እያስተላለፍን እድሳቱ ያለምንም እንቅፋትና ሁከት ከፍጻሜ እንዲደርስ ጸሎታችንና ምኞታችን መሆኑን እናስታውቃለን፡፡

እግዚአብሔር ኢትዮጵያንና ሕዝቦቿን ይባርክ
ወስብሐት ለእግዚብሔር አሜን!

አባ ማትያስ ቀዳማዊ
ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነጳጳሳት ዘኢትዮጵያ
ሊቀጳጳስ ዘአኵስም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት
ጥቅምት 21 ቀን 2011 ዓ.ም.
አዲስ አበባ፡ ኢትዮጵያ