መስጠትና መቀበል (ሐዋ፳፥፴፭)

 

                                                                                                                                                                በዲ/ን ተመስገን ዘገየ

መስጠትና መቀበል በሁለትና ከዚያ በላይ በሆኑ አካላት መካከል ይፈጸማል፡፡ይህም ያለው ለሌለው መስጠት የሌለው ካለው መቀበልና እርስ በእርስ መመጋገብ ነው፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስ ተመዝገቦ እንደምናገኘው ‹‹ከሚቀበል ይልቅ የሚሰጥ ብፁዕ ነው››(ሐዋ.፳፥፴፭) ይላል፡፡   በዚህ ኃይለ ቃል ላይ የሚሰጥ አለ ደገሞ የሚቀበል አለ፡፡ በዚህ ግንኙነት ውስጥ የሚሰጠው ከሚቀበለው ይልቅ ዋጋው ታላቅ ነው፡፡ ስለዚህ በክርስቲያናዊ ሕይወት መስጠት ብፅዕና የሚያስገኝ ስለሆነ ባለን ነገር ሁሉ መስጠትን ልንሻ  ያስፈልጋል፡፡ እግዚአብሔር ለእያንድንዳችን የተለያየ ጸጋ ሰጥቶናል፡፡ ከእኛ የሚጠበቀው ባለን ጸጋ መጠን ማገልገል ነው፡፡

ለዚህም ነው ሐዋርው ቅዱስ ጳውሎስ በመልእክቱ፡- ‹‹እግዚአብሔር በሰጠን ጸጋ መጠን ልዩ ልዩ ስጦታ አለን ትንቢት የሚናገር እንደ እምነቱ መጠን ይናገር የሚያገለግልም በማገልገሉ ይትጋ የሚያስተምርም በማስተማሩ ይትጋ የሚመክርም በመምከሩ ይትጋ የሚሰጥም በልግስና ይስጥ የሚገዛም በትጋት ይግዛ የሚመጸውትም በደስታ ይመጽውት››(ሮሜ.፲፪፥፮)እንዲል፡፡ ከመልእክቱ እንደተረዳነው መስጠት ብዙ አይነት ነው፡፡ ከነሱም ውስጥ ለምሳሌ ያህል የተወሰኑትን እንደሚከተለው ለማየት እንሞክራለን፡፡

1.ፍቅርን መስጠት

ክርስቲያናዊ ፍቅር ከልብ የተተከለ የመውደድ ኃይል አለው፡፡የክርስቲያኖች የመጀመሪያው ፍቅር የቤተሰብ ፍቅር ነው፡፡ፍቅር የሚጀምረው ከቤተሰብ ነውና፡፡”ነገር ግን በእርሱ ስለሆኑት ይልቁንም ስለቤተሰቦቹ የማያስብ ማንም ቢሆን ሃይማኖቱን የካደ ከማያምን ሰው ይልቅ የከፋ ነው(1ኛጴጥ5÷8) ፍቅር የምግባራት ሁሉ ራስ ነው፡፡ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ የመንፈስ ፍሬ በማለት ከዘረዘራቸው መካከል የመጀመሪያው ፍቅር ነው (ገላ፭÷፳፪) በዘመናችን ግን ይህ የመንፈስ ፍሬ ከሰው ልጆች ልቡና ጠፍቷል፡፡ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ደቀ -መዛሙርቱ  በደብረ ዘይት ስለ ዓለም ፍጻሜ በጠየቁት ጊዜ ምልክቱን ሲነግራቸው ከሰው ልጅ ዘንድ ፍቅር እንደሚቀዘቅዝ አሳስቧቸዋል፡፡ ”ከዐመፃ ብዛት የተነሣ የብዙ ሰዎች ፍቅር ትቀዘቅዛለች” በማለት (ማቴ24÷12) የፍቅር ሸማ ከሰው ልጆች  ልቡና ውስጥ ተገፍፎ ወድቋል፡፡

“ዳሩ ግን የነገር ሁሉ መጨረሻው ቀርቧል እንግዲህ እንደ ባለአእምሮ አስቡ ትጸልዩም ዘንድ በመጠን ኑሩ ፍቅር የኀጢአትን ብዛት ይሸፍናልና ከሁሉ በፊት እርስ በእርሳችሁ ተዋደዱ ”ይላል (፩ኛጴጥ፬÷፯) ወጥ ማጣፈጫው ጨውና ቅመም እንደሆነ ሁሉ የሰው ማጣፈጫውም ሃይማኖትና ፍቅር ነው፡፡የፍቅር ምንጩ ክርስቶስ  ነው፡፡ አምስት ሺህ አምስት  መቶ ዘመን ለተራቡ ሥጋውን አብልቶ ደሙን አጠጥቶናልና“ወአጽገቦሙ እምበረከቱ ለርኁባን፤ የተራቡትንም በቸርነቱ አጠገባቸው(ሉቃስ1፥53) ዘለዓለማዊ ሕያው አምላክ እግዚአብሔር በቃላት ከመነገርና  በልቡና  ከመታሰብ በላይ የሆነውን ጥልቅ ፍቅሩን የገለጠው  በመስቀል ነው፡፡በአዳም በደል ምክንያት“እኛ ሁላችን እንደ በጎች ተቅበዝብዘን ጠፋን እያንዳንዳችንም በየመንገዳችን ነጎድን”(ኢሳ፶፫÷፮)፡፡

ነገር ግን የሰው ልጆች በኃጢአታችን ምክንያት ከእግዚአብሔር ተለይተን እንዳንቀር አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ  በደል ሳይኖርበት የእኛን በደል ተሸክሞ  እኛን ለማዳን በመስቀል ላይ በመሞት ፍቅሩን ገልጾልናል፡፡ ሊቁ  አባ ሕርያቆስም ይህንኑ ሲመሰክር “ፍቅር ሰሐቦ ለወልድ ኃያል እመንበሩ ወአብጽሖ እስከ ለሞት፤ፍቅር ኃያል ወልድን ከዙፋኑ አወረደው እስከ ሞትም አደረሰው” ብሏል (ቅዳሴ ማርያም)፡፡

እግዚአብሔር አብ ለሰው ልጅ ያለውን ፍቅር በልጁ በኩል ገልጦልናል፡፡ እርሱም ቅድመ ዓለም የነበረ የባሕርይ ልጁ ኢየሱስ ክርስቶሰ ነው፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ፍጹም ፍቅሩን ካሳየን በኋላ ‹‹እኔ እንደወደድኋችሁ እርስ በርሳችሁ ትዋደዱ ዘንድ ትእዛዜ ይህች ናት››(ዮሐ.፲፭፥፲፪) በማለት እርሱ እንዲሁ እንደወደደን እኛም እንዲሁ እንዋደድ ዘንድ አዞናል፡፡ ለዚህም ነው ሐዋርያው ቅዱስ ዮሐንስ ” ማንም እግዚአብሔርን እወዳለሁ እያለ ወንድሙን የማይወድ ያላየውን እግዚአብሔርን እንዴት ሊወድ ይችላል? (፩ኛዮሐ ፬÷፰-፲፪) በማለት ያስተማረን፡፤ ስለዚህ ነገ ነፍሳችን  ልብሰ ጸጋዋን  ተገፋ  ከክርስቶስ ፊት እራቁቷን እንዳትቆም ዛሬ በዚህ ዓለም ሳለን የፍቅር ሸማኔ ሁነን ልብሰ ጸጋ ልንሠራላት ይገባል፡፡ድሩን ሃይማኖት ማጉን ፍቅር አድርገን የክብር ልብስ የሠራንላት እንደሆነ ሞገስ ታገኛለች፡፡

ሰው ለፍቅር ዘወትር የጋለ ብረት ምጣድ ሁኖ ከተገኘ ዕድሉ የቀዘቀዘና የፈዘዘ አይሆንበትም”ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስም “በሰዎችና በመላእክት ልሳን ብናገር ፍቅር ግን ከሌለኝ እንደሚጮኽ ናስ ወይም እንደሚንሸዋሽዋ ጸናጽል ሆኜኛለሁ….”(፩ኛቆሮ፲፫÷፩-፰) ቅዱስ ጳውሎስ እምነትን፣ተስፋንና ፍቅርን ከዘረዘረ በኋላ የሚበልጠው ፍቅር ነው ይላል፡፡ ክርስቲያኖች የሚኖረን ፍቅር እንደ ፀሐይ እንጂ እንደ ጨረቃ መሆን የለበትም፡፡ፀሐይ ሁል ጊዜ  ሙሉ ነች የእኛ  ፍቅር  ወጥ መሆን አለበት እንጂ ጥቅም ስለምናገኝ ብቻ ሰዎችን የምናፈቅር ከሆነ ጨረቃ ሁነናል ማለት ነው፡፡”በቃልና በኑሮ በፍቅርም፣በእምነትም በንጽሕናም ለሚያምኑቱ ምሳሌ ሁን “(፩ኛጢሞ፬÷፲፩-፲፪)ክርስትና የምንተርከው ታሪክ ሳይሆን በፍቅር የምንኖረው ሕይወት ነው፡፡ፍቅር ለሌሎች በመስጠት ክፉ የሚያስቡትን በፍቅር ማሸነፍ ይገባል፡፡

           2.ምጽዋትን መስጠት

ምጽዋት ሥርወ ቃሉ የግእዝ ቋንቋ ነው፡፡ትርጓሜውም  ስጦታ፣ችሮታ፣ልግስና  ማለት ነው፡፡ ሰዎች  በሰዎች ላይ የሚያዩትን  ችግር  በማገናዘብ የተቸገሩትን መርዳት  ከፍጹም ፈቃድና ርኅራኄ የሚያደርጉት ስጦታ ምጽዋት ይባላል፡፡ በፍትሐ ነገሥት ፍትሕ መንፈሳዊ አንቀጽ ፲፮ ቊ125-127 እንደተገለጠው ምጽዋት ምሕረት ነው፡፡እግዚአብሔር ከሰጪዎች ጋር የሚሰጥ  ከተቀባዮች ጋር ሁኖ የሚቀበል  በመስጠትና በመቀበል  በሰዎች መካከል  መተሳሰብና መረዳዳት  እንዲኖር ሀብትን ለሀብታሞች የሚሰጠው ከእነርሱ የሚያንሱትን እንዲያስተናግዱበት ነው፡፡ብላቴን ጌታ ኅሩይ ወልደ ሥላሴ ምጽዋትን የተረጎሙት እንዲህ በማለት ነው “ምጽዋት ማለት የዕለት ምግብና የዓመት ልብስ  ለቸገራቸው ሰዎች ገንዘብ መስጠት ነው ደግሞም ምክር ለቸገራቸው መምከር፣ትምህርት ለቸገራቸው ማስተማር ምጽዋት ነው(ጎሐ ጽባሕ ገጽ ፳፬)፡፡

ምጽዋትን ለተቸገረ ሰው የሚሰጥ ሰው ለእግዚአብሔር መስጠቱ ነው፡፡ ጠቢቡ ሰሎሞንም” ለደሀ ቸርነትን የሚያደርግ ለእግዚአብሔር ያበድራል በጎነቱንም መልሶ ይከፍለዋል፡”ይላል(ምሳ፲፱÷፲፯)ምጽዋት ብልሆች ሰዎች  በእግዚአብሔር ዘንድ የሚያስቀምጡት አደራ ነው፡፡ ደካሞችን በጉልበት፣ያልተማሩትን በዕውቀት የሙያ ርዳታ የሚስፈልጋቸውን በሙያ መርዳት ምጽዋት ነው፡፡ምጽዋት መስጠት አስፈላጊ እንደሆነ ምጽዋት ሰጪዎችም በእግዚአብሔር ዘንድ የሚጠብቃቸው ከፍተኛ ዋጋ እንዳላቸው በብሉይና  በሐዲስ ኪዳናት በሰፊው ተገልጦ ይገኛል፡፡”ድሆች ከምድር ላይ አይታጡምና በሀገር ውስጥ ላለ ደኃ ለተቸገረውም ወንድምህ እጅህን ትከፍታለህ ብዬ አዝዝሃለሁ”(ዘዳ፲፭÷፲፩)

“ወንድምህ ቢደኸይ እጁ ቢደክም አጽናው  እንደ እንግዳ እንደመጻተኛ  ካንተ ጋር ይኑር”(ዘሌ፳፭÷፴፭) ልዑል እግዚአብሔርም ከመሥዋዕት ይልቅ ምጽዋትን አብልጦ እንደሚወድ  በነቢያቱ አንደበት ተናግሯል፡፡“……እኔ የመረጠሁት ጾም …እንጀራህን ለተራበ ትቆርስ ዘንድ ስደተኞች ደሆችን ወደ ቤትህ ታገባ ዘንድ የተራቆተውን ብታይ ታስበው ዘንድ አይደለምን?(ኢሳ፶፯÷፯) መጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ በትምህርቱ ተማርከው ለመጠመቅ የመጡትን ሰዎች እንዲህ በማለት የምጽዋትን አስፈላጊነት አስተምሯቸዋል፡፡ ”ሁለት ልብስ ያለው  ሰው  ለሌላው ያካፍል ምግብም ያለው እንዲሁ ያድርግ “ይላል (ሉቃ፫÷፲፩)፡፡

ክርስቲያኖች የሚመጸውቱት ከተረፋቸው ሳይሆን ካላቸው ነው (ሉቃ፳፩÷፩-፬)ለዚህም ምክንያቱ ደግሞ አስቀድመን እንዳየነው ምጽዋት ትልቅ የክርስትና ቁልፍ በመሆኗ ነው፡፡ብዙዎቻችን የኃጢአት ሥር በተባለው በገንዘብ መውደድ ልባችን ስለታሰረ ምጽዋት የሚመስለን ከተትረፈረፈው ኪሳችን አንድ ብር ለነዳይ መስጠት ነው፡፡ምጽዋት ብድሩ ከልዑል እግዚአብሔር ይገኛል በሚል እምነት ለተቸገሩ ሰዎች የሚሰጥ ልግስና እንደመሆኑ አቀራረቡ ከግብዝነትና ከከንቱ ውዳሴ የጠራ መሆን እንዳለበት ጌታችን አስተምሯል፡፡ የድሆችን ጩኸት ሰምቶ  በችግራቸው  በመድረስ ምላሽ የሚሰጥ  እሱ በተቸገረ ጊዜ  በጎ ምላሽ ከእግዚአብሔር ዘንድ ያገኛል፡፡ምጽዋት የክፉ ጊዜ ዋስትና ነው፡፡

ቅዱስ ዳዊት ”ብፁዕ ዘይሌቡ ላዕለ ነዳይ ወምስኪን እምዕለት እኪት ያድኅኖ እግዚአብሔር፣እግዚአብሔር የዐቅቦ ወያሐይዎ ወያበፅዖ ዲበ ምድር፤ለችግረኛና ለምስኪን የሚያስብ ምስጉን ነው እሱንም እግዚአብሔር ከክፉ ቀን ያድነዋል”(መዝ፵÷፩-፪) ጠቢቡ ሰሎሞንም “ፈኑ ኅብስተከ ውስተ ገጸ ማይ እስመ በብዙኅ መዋዕል ትረክቦ፤እንጀራህን በውኃ ፊት ላይ ጣለው ከብዙ ዘመን (ቀን) በኋላ ታገኘዋለህና”(መክ ፲፩÷፩) እንዴት ሰው ዐይኑ እያየ እንጀራውን በውኃ ላይ ጥሎ ከብዙ ቀን በኋላ ያገኘዋል ልንል እንችላለን እንጀራህን በውኃ ላይ ጣለው ማለት ምጽዋትህን  ለተቸገሩት ለድሆች ስጥ  ማለት ነው፡፡ ከብዙ ቀን በኋላ ታገኘዋለህ ማለት የምጽዋቱን ዋጋ በገነት በመንግሥተ ሰማያት ታገኘዋለህ ማለት ነው፡፡በውኃ ውስጥ የጣሉት እንዳይታይ ሰውረህ ሳትታይ ምጽዋት ስጥ ውኃ የበላው እንዳይገኝ ከዚያ ተመጽዋች ዋጋ አገኛለሁ ሳትል  ምግብህን በከርሠ ርኁባን  መጠጥህን  በጕርዔ ጽሙኣን አኑር ማለት ነው (ዘዳ15÷7)

ምጽዋት የሚመጸውቱ ሰዎች የሚጠቀሙትን ያህል የማይመጸውቱ ሰዎች ይጎዳሉ፡፡ብዙ በረከትንም ያጣሉ፡፡

በመጨረሻ የፍርድ ጊዜም ወቀሳ ተግሣጽ ፍዳ ይጠብቃቸዋል፡፡ ሰው ከሚረገምባቸው የጥፋት ሥራዎች አንዱ ለድሆች አለማዘንና አለመራራት ነው፡፡እስመ ኢተዘከረ ይግበር ምጽዋተ ሰደደ ብእሴ ነዳየ ወምስኪነ፤ምጽዋትን ያደርግ ዘንድ አላሰበም ችግረኛና ምስኪን አሳዷልና“ይላል (መዝ፻፰÷፲፭)ምጽዋት በመስጠት ሰው ፈጣሪውን በሥራ ይመስለዋል፡፡ለሰው ማዘን መራራት ገንዘብ መስጠት ከአምላክ ባሕርይ የሚገኝ ነውና”ወበምጽዋት ይትሜሰሎ ሰብእ ለፈጣሪሁ እስመ ውሂበ ምፅዋት ወተሣህሎ እምነ ጠባይዕ አምላካዊ “እንዳሉ (፫፻.) ፡፡

ምጽዋት መስጠት ለአምላክ ማበደር ነው፡፡ከአምላክ ጋር የሚነግዷት ንግድ ናት፡፡“ወምጽዋትሰ ልቃሕ አምላካዊት ወይእቲ ካዕበ ተናግዶ አምላካዊት ማእምንት ርብሕት“እንዲሉ  ፫፻.ዳግመኛም ቍርባን ናት በከርሠ ነዳያን የምትቀርብ ናት ”ወይእቲ ካዕበ  ቍርባን  ውክፍት  በኀበ መቅደስ  ነባቢት “እንዳሉ( ፫፻.) ራሱን  መርዳት የሚችል ሰው የሰውን ገንዘብ አይቀበል ወጥቶ ወርዶ  ራሱን ይርዳ፡

ቅዱሳን ሐዋርያትም ገንዘብ እያለው ምጽዋት የሚቀበል ወዮለት ብለዋል፡፡ምጽዋት ከክፉ ታድናለች፤ኃጢአትን ታስተሠርያለች፡፡ውኃ እሳትን እንዲያጠፋ ምጽዋትም ኃጢአትን ታጠፋለች” ለእሳት ዘትነድድ ያጠፍኣ ማይ ወከማሁ ምጽዋትኒ ታኀድግ ኃጢአተ “እንዳለ ሲራክ ፫÷፳፰፡፡ ሊቁ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ደግሞ “ወእመ ትብሎ አንሰ ወሀብኩከ  ብዙኀ  ጊዜ እብለከ ኢትበልዕኑ አንተ በኵሉ ጊዜ፣ብዙ ጊዜ ሰጠሁት  ይበቃሃል አትበል አንተ ጠዋት ማታ ትበላ የለምን ?እንደራስህ አታየውምን ?”ይላል፡፡

ምጽዋት የሚሰጠው ለሰዎች መልካም ነገር በማድረግ ከእግዚአብሔር መልካም ነገር ለማግኘት ነው፡፡”ስጡ ይሰጣችኋል“ተብሏልና (ማቴ.፲፥፰፣2ኛቆሮ.፱፥፯—፲፪) በምጽዋት የተጠቀሙ ብዙዎች ናቸው፡፡ምናሴ ጠላቶቹ ከመከሩበት መቅሠፍት የዳነው ምጽዋትን በመመጽወቱ ነበር

የጌታን ትእዛዝ፣ፈቃድና ትምህርት መሠረት አድርገው ያስተማሩ ቅዱሳን ሐዋርያትም “ካለው የሚሰጥ ብፁዕ ነው ”በሚል ኃይለ ቃል የምጽዋትን ነገር ትኩረት ሰጥተውታል (የሐዋ.ሥራ ፳÷፴፮) ዕዝ ፱÷፭)ምጽዋትንበፍቅር መመጽወት ይገባል፡፡አበው “ከፍትፍቱ ፊቱ“እንዲሉ፡፡ቅዱስ ያዕቆብ “በጎ ለማድረግ ዐውቆ ለማይሠራው  ኃጢአት ነው“(ያዕ፬÷፲፯) ይህን በጎ ምግባር ሠርተን እንዲንጠቀም የእጃችንን እስራት አምላካችን ይፍታ በእርግጥ የእግዚአብሔር ስጦታውን በቃላት ተናግረን አንጨርሰውም (፪ኛቆሮ፱÷፲፭)

  1. ለሚጠይቁን ተገቢ የሆነ ምላሽ መስጠት

ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ “በእናንተ ስላለ ተስፋ ምክንያት ለሚጠይቋችሁ ሁሉ መልስ ለመስጠት የተዘጋጃችሁ ሁኑ ነገር ግን በቅንነትና በፍርሀት ይሁን”ይላል( ፩ጴጥ፫÷፲፭ )

ሰሎሞንም“ ልጄ ሆይ ጠቢብ ሁን ልቤንም ደስ አሰኘው ለሚሰድቡኝ መልስ መስጠት ይቻለኝ ዘንድ”ይላል( ምሳ፳፯÷፲፩) “በውኑ ለቃል ብዛት መልስ መስጠት አይገባምን?ወይስ ተናጋሪ ሰው እንደ ጻድቅ ይቈጠራልን?ትምክህትህስ ሰዎችን ዝም ያሰኛቸዋልን?…(ኢዮ፲፩÷፪)

ዘመናችን ከየትኛውም ጌዜ  በተለየ  በእምነት ስም የተቋቋሙ ድርጅቶች ከቀን  ወደ ቀን  የበዙበትና  እንደ አሸን የሚፈሉበት መሆኑን በዐይናችን እያየን በጀሯችን እየሰማን  ነው፡ በአፍሪካ ቀንድ የምትገኘውን የሦስት ሺህ ዓመታት የሃይማኖት ባላ ታሪክ ሀገራችንን ኢትዮጵያንም በየዘመኑ ከመፈታተን ያረፉበት ጊዜ የለም፡፡ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን ግን ጥያቄዎችን በትሕትና በመቀበል ለመናፍቃኑ ተገቢውን ምላሽ ሲሰጡ በመቆየታቸው እናት ቤተ ክርስቲያን ከሥር መሠረቷን ከላይ ጉልላቷን ለማፍረስ የመጡት ሳይሳካላቸው እነርሱ ፈራርሰው ቀርተዋል፡፡ይህን የመናፍቃን ክዶ የማስካድና ተጠራጥሮ የማጠራጠር የኑፋቄ ዘመቻ ለመግታት የክርስቶስን የባሕርይ አምላክነት በጉባኤ  በማስተማር መናፍቃን ለቃቅመው ላመጡት ጥያቄ ኦርቶዶክሳውያን አባቶቸች በየዘመናቱ ተገቢውን ምላሽ  በመስጠት አሳፍረው መልሰዋቸዋል፡፡ በእምነት ስም በየጓዳው የሚቋቋሙ የመናፍቃን ድርጅቶች ዓላማ የኢትዮጵያውያንን የሃይማኖት መሠረት  በማናጋት ሕዝቡ የራሴ የሚለውን እምነቱንና ሥርዓቱን መንፈሳዊ የሆኑ ነገሮችን እንዲያጣ  ማድረግ ነው፡፡ስለዚህ ምእመናን ነቅተውና ተግተው ሊጠብቁ ይገባቸዋል፡፡

በመሆኑም እነዚህንና መሰል በጎ ምግባራትን ማድረግ ከአንድ ክርስቲያን የሚጠበቅ ሃይማኖታዊ ግዴታ መሆኑን መገንዘብ ያሻል፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በወንጌል ‹‹በከንቱ የተቀበላችሁትን በከንቱ ስጡ››(ማቴ.፲፥፰) ብሎ እንዳስተማረን በተሰጠን ጸጋ ያለ መሰሰት ማገልገልና በልግስና መሥጠት ያስፈልጋል፡፡ ይህንን ብናደርግ ዋጋችን ታላቅ ነው፡፡

ምንጭ፤ ሐመር መጽሔት 26ኛ ዓመት ቁጥር 3 ሐምሌ 2010ዓ.ም

 

 

በአሜሪካ የዲሲ ንዑስ ማእከል አቡነ ጎርጎርዮስ ትምህርት ቤት ተማሪዎችን አስመረቀ

ከአሜሪካ ማእከል
በማኅበረ ቅዱሳን በአሜሪካ የዲሲ ንዑስ ማእከል አቡነ ጎርጎርዮስ ትምህርት ቤት ነሐሴ ፲፪ ቀን ፳፻፲ ዓ.ም ለሰባት ወራት ያስተማራቸውን 64 ተማሪዎችን የተማሪ ወላጆችና የማኅበሩ አመራር አባላት በተገኙበት በሜሪላንድ ግዛት አስመረቀ፡፡
በምረቃው መርሐ ግብር ላይ የትምህርት ቤቱ አስተባባሪ ዲ/ን ሙሉጌታ ኃይለ ማርያም የማኅበሩን መልእክትና የአቡነ ጎርጎርዮስ ትምህርት ቤትን የ፳፻፲ ዓ.ም ሪፖርት አቅርበዋል፡፡
ዲ/ን ሙሉጌታ ኃይለ ማርያም “ከማኅበረ ቅዱሳን ዓላማዎች ልጆች የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን ትምህርት፣ ሥርዓትና ትውፊት በመማር፣ ለአባቶቹ ተተኪ እንደሆን ማድረግ በመሆኑ ላለፉት ፳፯ ዓመታት ወደ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት በገቡ ወጣቶች ላይ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ ሲሠራ ቆይቷል፤አሁንም እየሠራ ይገኛል” ብለዋል፡፡
አያይዘውም “ሥራው ብዙ ውጤት ያስገኘ ቢሆንም በሀገር ውስጥም ሆነ በውጭ ሀገር ከሚገኘው ወጣት የተተኪ ትውልድ ቊጥር አንጻር ሲታይ እጅግ በጣም አነስተኛ በመሆኑ አጥቢያ አብያተ ክርስቲያናትና ሰንበት ትምህርት ቤቶች ከሕፃናት በመጀመር ሲያስተምር ቆይቷል፡፡ ከመዋዕለ ሕፃናት ጀምሮ ማስተማር አስፈላጊ መሆኑን በመገንዘብ ከ፲፱፻፺፩ ዓ.ም ጀምሮ ሕፃናትና ወጣቶችን ተቀብሎ በማስተማር ላይ ይገኛል፡፡ በርካታ አብያተ ክርስቲያናትም ትምህርት ቤት በመክፈት በማኅበሩ የሥርዓተ ትምህርትና የሙያ እገዛ እየተደረገላቸው በማስተማር ላይ ይገኛሉ” በማለት የማኅበሩን አገልግሎት ገልጠዋል፡፡

“በዲሲ ንዑስ ማእከልም ከ፳፻፲ ዓ.ም በመጀመር አሁን ያለንበት ደረጃ ደርሰናል፡፡ 64 ተማሪዎችን ተቀብለን በሳምንት አንድ ቀን ቅዳሜ ለሰባት ወራት በማስተማር ቆይተናል” ብለዋል፡፡ በቋንቋ ክፍል ስድስት በቃል ትምህርት አንድ፣ ሦስት ረዳት፣ እንዲሁም በመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት አንድና አንድ ተጨማሪ በአጠቃላይ 11 መምህራን ተሳታፊ እንደነበሩ ገልጠዋል፡፡
በምረቃው የተማሪ ወላጆች ማእከሉ ተማሪ የመቀበል አቅሙን ማሳደግ እንዳለበትና ያለውን ልምድ ለአጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት ማካፈል የሚችልበትን መንገድ እንዲያመቻች ጠቁመዋል፡፡

አባቶቻችን ለዕርቅ አርአያ በመሆናቸው ዘመኑን ዋጅተዋል

 

ማስታረቅና ማስማማት ከሰላም መሪ የሚገኝ አርአያነት ያለው ተግባር ነው ይቅር ማለትም እንደዚሁ፡፡ በዓለም ላይ ተቈጥረው የማያልቁ ጦርነቶች ቢካሔዱም ለጊዜው የተሸነፈ የመሰለው ጊዜ እስከሚያገኝ አድፍጦ እንዲቆይ ማድረግ ቻለ እንጂ አማናዊ ሰላም ማምጣት አልቻለም፡፡ አንዱ ሌላውን ሲወር፣ አንዱ ሌላውን ሲያስገብር ኖሯል፡፡ አባቶቻችን ዘመኑን ሲዋጁ የኖሩት ዕርቅ በማድረግ የተለያዩትን በማስማማት ነው፡፡

የጦርነት ውጤቱ ቂምና በቀል ሲሆን የዕርቅ ውጤቱ ሰላም ነው፡፡ ቂምና በቀል የሚያመጣው ዕርቅና ሰላም መፍጠር ብቻ መሆኑን መንፈሳውያንም ሥጋውያንም መጻሕፍት ያስተምራሉ፡፡ በዚህ ምድር የሚያስተዳድሩ መንግሥታት ሳይቀር ከጥል ምንም ጥቅም እንደማያገኙ እየተረዱት መጥተዋል፡፡ የሃይማኖት ሰዎች ደግሞ ሰላም መፍጠር ከአምላካቸው የተቀበሉት በመሆኑ በተግባር ሲፈጽሙት ኖረዋል፡፡ ክርስቲያኖች ከአምላካቸው የተቀበሉት ይቅር ማለትን በተለያዩት መካከል አንድነት፣ በተጣሉት መካከል ሰላም መፍጠርን አባቶቻችን ዕርቅ መፈጸማቸው ለቤተ ክርስቲያን ያለውን በቊዔት በቃላት ገልጦ መጨረስ አይቻልም፡፡ ዓለምን መዋጀት የቻሉትና ንግግራቸው ተቀባይነት ሲያገኝ የኖረው ሰላማውያን፣ ይቅር ባዮች፣ የትሕትና ሰዎች በመሆናቸው ነው፡፡

አምላካችን እግዚአብሔር በድለነው ሳለ ይቅር ያለን እኛም የበደሉንን ይቅር ብለን አርአያውን ለመከተል እንድንችል ነው፡፡ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የፈጸመውን ለሌሎች ማስተማር እና በተግባር መግለጥ ከአባቶች የሚጠበቅ በመሆኑ አሁን የተፈጸመውም መልካም ነው፡፡ የምንናገረው ፍሬ የሚያፈራው ስለ ሰላም፣ ስለ አንድነት፣ ስለ ፍቅር፣ ስለ ትሕትና፣ ስለ ይቅር ባይነት የምናስተምረውን በተግባር መግለጥ ስንችል ነው፡፡ የያዝነው እውነት፣ የተናገርነው ትክክል ሊሆን ይችላል፡፡ ስለ ባልንጀራ ድካም ብሎ መተው፣ ዝቅ ብሎ በትሕትና ለሰላም መገኘት አርአያ መሆን ከሃይማኖት ሰው የሚጠበቅ ተግባር ነው፡፡ ይህን የምንለው ሃይማኖታችን የተመሠረተው በፍቅርና በትሕትና በመሆኑ አሁን የተፈጸመው ዕርቅም የወንጌሉ ቃል በተግባር መፈጸሙን ያሳያል ብለን ስለምናምን ነው፡፡ ሁለቱም ወገኖች ግማሽ መንገድ በመሔድ የሚጠበቅባቸውን መፈጸማቸው ወደ ፊት የሚከሠት ነገርም በትሕትና ይሸነፋል፡፡ በዚህ ደግሞ ቤተ ክርስቲያናችን ትጠቀማለች፡፡

ዘመኑ የሚጠይቀው ከአምላካችን የተቀበልነውንና ቀደምት አባቶቻችን ያስተማሩንን በተግባር በመግለጥ ሰላማዊነታችንንና የሰላም ምንጭ የሆነ ሃይማኖት ያለን መሆናችንን ለማስመስከር ሰላማችን ዘላቂነት እንዲኖረው የሚያደርግ ሥራ መሥራት ነው፡፡ ሌሎችን ይቅር ለማለት ትሕትና ያስፈልጋልና፡፡ ይቅር በማለታችን ሀገር ሰላም ታገኛለች፡፡ ይህም በተግባር መታየት ጀምሯል፡፡ በዚህ ተግባራችንም በሰውም በእግዚአብሔርም ዘንድ እንከበራለን፤ ታሪክም በመልካም ሲያነሣን ይኖራል፡፡ እንኳን ቤተ ክርስቲያን ዓለም የምታስታውሰው መልካም የሠሩትን ነውና፡፡

የእምነት አባቶች ድሀ ተበደለ ፍርድ ተጓለ ብለው በድፍረት መናገርና የተሳሳተውን መገሠጽ የሚችሉት የበደላቸውን ይቅር ሲሉ፣ እግዚአብሔርን የበደለውን ከእግዚአብሔር ሲያስታርቁ ነው፡፡ ይህን ሲያደርጉ እምነት ያለውም የሌለውም የሚናገሩትን ይሰማል፤ አድርግ ያሉትን ያደርጋል፡፡ ይህም ባይሆን ምክንያት እናሳጣዋለን፡፡ ከእምነት የወጣሁት እንዲህ ስለሆነ ነው እንዳይል ያደርጋል፡፡ ሰሞኑን አሜሪካና ኢትዮጵያ የሚገኙ አባቶች ዕርቅ በመፈጸማቸውም ከርትዕት ሃይማኖት ወጥተው የነበሩ ይመለሳሉ፡፡ በእምነትም ይጠናሉ፡፡

ከሁለት አሥርት ዓመታት በፊት በተፈጠረ ታሪካዊ ክሥተት በአባቶች መካከል አለመግባባት ተፈጥሮ ነበር፡፡ አለመግባባቱ የሃይማኖት ልዩነት ባለመሆኑም አባቶቻችን ተወያይተው ለመስማማት በቅተዋል፡፡ ሰማይ ተቀደደ ቢለው ሽማግሌ ይሰፋዋል አለ እየተባለ የሚጠቀሰው የአበው ንግግር መፍትሔ የሌለው ችግር፣ ዕርቅ የማይፈታው ልዩነት አለመኖሩን ያሳያል፡፡ የተጣሉ ሲታረቁ፣ የታሠሩት ሲፈቱ፣ የተለያዩ አንድ ሲሆኑ እየተመለከትን ነው፡፡ ይህ ደግሞ ለሀገርም ለቤተ ክርስቲያንም ታላቅ ተስፋ የሚፈነጥቅ ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያንም በተደጋጋሚ ልዑክ እየላከች ዕርቁ ተግባራዊ እንዲሆን ስታደርግ ቆይታ ጊዜው ሲደርስ ዛሬ እውን ሆኖ አየን፡፡

የቤተ ክርስቲያን ተልእኮዋ ሰላምን ማብሠር፣ ለተጨነቁት መፍትሔ መስጠት፣ የተለያዩትን አንድ ማድረግ ነው፡፡ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የዓለም ብርሃን ሆኖ ተከታቹን የዓለም ብርሃን ያስባላቸው ሰላማውያን፣ ይቅር ባዮች፣ ለሌላው ሲሉ ራሳቸውን ሳይቀር አሳልፈው የሚሰጡ በመሆናቸው ነው፡፡ ታላቁ ቴዎዶስዮስ አሠርቶት የነበረውን ሐውልት ሕዝበ ክርስቲያኑ በብስጭት ባፈረሰው ጊዜ ንጉሡን በምክርም በተግሣጽም ይቅር እንዲል ያደረገው ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ነው፡፡ ይህም ንጉሡም የሚመራውን ሕዝብ ጨፍጭፎ በታሪክ እንዳይወቀስ፣ ቅዱሱም በደል ሲፈጸም ፈርቶ ዝም አለ ተብሎ እንዳይተች አድርጎታል፡፡

ቂርቆስና ኢየሉጣ ከእሳት በወጡበት በብሥራተ መልአክ በቅዱስ ገብርኤል የመታሰቢያ ዕለት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን አባቶች አንድ ሆነዋል፡፡ በዚህም የምእመናን ተስፋ ለምልሟል፡፡ የጥል ግድግዳ ፈርሷል፡፡ ይህ ታላቅ መንፈሳዊ ተግባር የተፈጸመበት ዕለት ለቤተ ክርስቲያናችን ታላቅ የደስታ ዕለት ነው፡፡ ይህ ዕለት ሰይጣን ቤተ ክርስቲያንን ለመዋጋት ጥይቱን የጨረሰበት፣ ዝናሩን አራግፎ ባዶ እጁን የቀረበት ነው፡፡ ዕለቱ የሰይጣን ጥርሱ የረገፈበትና የቤተ ክርስቲያን ብርሃን ለዓለም የተገለጠበት በመሆኑ የቤተ ክርስቲያን የደስታ ቀን ነው፡፡

ለዚህ ዕለት ደርሶ የተገኘውን ዕርቅ አይቶ የማይደሰት ቢኖር ዲያብሎስ ብቻ ነው፡፡ ዕርቁ እውን እንዲሆን መለያየት እንዲወገድ፤ የተፈጠረው ክፍተት መፍትሔ እንዲያገኝ ያደረገ እግዚአብሔር ይመስገን፡፡ ዕርቁ እውን እንዲሆን በቅን ልቡና የተቀበላችሁ ሁለቱም ቅዱሳን ፓትርያርኮቻችን የፈረሰውን አንድነት በዘመነ ፕትርክናችሁ ለመጠገን፤ የተለያየውን አንድ ለማድረግ፤ የሻከረውን ለማለስለስ ያበቃችሁ እግዚአብሔር ይመስገን፡፡ አባቶቻችንን ለዕርቅ ያበቋቸውን ምክንያቶች እንደሚከለው እናቀርባለን፡፡

  1. ለቤተ ክርስቲያን አንድነት ቅድሚያ መስጠታቸው፡- የሃይማኖት አባት በእግዚአብሔርና በምእመናን መካከል የሚገኝ ድልድይ ነው፡፡ አባቶች የእግዚአብሔርን ምሕረት ወደ ሕዝበ ክርስቲያን የሚያደርሱ፣ የሕዝቡን ጸሎትና ይቅርታ ጠያቂነት ወደ እግዚአብሔር የሚያደርሱ ናቸው፡፡ በደል ሲፈጸምም ምህላ ይዘው፣ መሥዋዕት አቅርበው ለአባቶቻችን ስለገባህላቸው ቃል ኪዳን ብለህ ይቅር በለን በማለት ለምነው ይቅርታ ያሰጣሉ፡፡ ይህ ተግባርም ያላመኑትን ስቦ በማምጣት የድኅነት ተካፋይ፣ እንዲሆኑ ከሥላሴ ልጅነትን እንዲያገኙ ሲያደርግ ኖሯር፡፡ አሁን የተፈጠረው ሰላምም የራሱ የሆነ አስተዋጽኦ ይኖረዋል፡፡ ሐዋርያዊ አገልግሎትን ለማጠናከርም ያግዛል፡፡

የሃይማኖት አባት ተቀዳሚ ተልእኮ የእግዚአብሔርን ቤተ ክርስቲያን መጠበቅ ነው፡፡ በክርስቶስ ደም የተዋጀች ቤተ ክርስቲያን ለዓለም ብርሃን ስትሆን ኖራለች፡፡ የቤተ ክርስቲያን የአባቶችን ተልእኮ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ “በገዛ ደሙ የዋጃትን የእግዚአብሔርን ቤተ ክርስቲያን ትጠበቁ ዘንድ መንፈስ ቅዱስ እናንተን ጳጳሳት አድርጎ ለሾመባት ለመንጋው ሁሉና ለራሳችሁ ተጠንቀቁ፡፡ ከእኔ በኋላ ለመንጋይቱ የማይራሩ ነጣቂዎች ተኲላዎች እንደሚመጡ እኔ አውቃለሁ” (ሐዋ. ፳፥፳፰-፳፱) በማለት ገልጦታል፡፡ ከዚህም ቅድስት ቤተ ክርስቲያን የተዋጀችውና የተመሠረተችው እስከ ሞት ድረስ በወደዳት በክርስቶስ መሆኑን እንረዳለን፡፡ ይህች ቤተ ክርስቲያን ተጠብቃ የኖረችውና ወደፊትም እስከ ምጽአት የምትኖረው በግብር አምላካቸውን በሚመስሉ፣ አሠረፍኖቱን በተከተሉ አባቶች መሆኑን ሐዋርያው ነግሮናል፡፡ አባቶች ቤተ ክርስቲያንን ለመጠበቅ፣ ምእመናንን ለመከባከብ ሓላፊነት የሰጣቸው እግዚአብሔር መሆኑንም ያስገነዝባል፡፡

አባቶች ሌላውን እንዲጠብቁ ሓላፊነት ሲሰጣቸው ራሳቸውን በመጠበቅ፣ ለሌላው እንቅፋት ላለመሆን በመጠንቀቅ፣ ምእመናንን ነጣቂ እንዳይወስዳቸው ንቁ ሆነው እንዲጠብቁ በማሳሰብ ነው፡፡ ዕርቅ ለማድረግ የተሰለፉ አባቶችም ይህንን ሁሉ በማሰብ የፈጸሙት፣ ሓላፊነተቻውን ለመወጣትና ከተጠያቂነት ነፃ ለመሆን ያከናወኑት መልካም ተግባር ነው፡፡ ለቤተ ክርስቲያን አንድነትና ለምእመናን ሕይወት መጨነቅ ይህ ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያን የተመሠረተችው ለምእመናን ነውና፡፡ የካህናትንና የአባቶችን ግንኙነት ነቢዩ “ከመንገዱ ይመለስ ዘንድ ኃጢአተኛውን ብታስጠነቅቀው እርሱም ከመንገዱ ባይመለስ በኃጢአቱ ይሞታል አንተ ግን ነፍህን ታድናለህ” (ሕዝ. ፴፫፥፱) በማለት ገልጦታል፡፡ አባቶቻችን ለቤተ ክርስቲያን አንድነት ቅድሚያ በመስጠታቸው ስምምነት ላይ ደርሰዋል፡፡ ቅዱሳን ፓትርያኮች በዘመናቸው ሰላም መፈጸሙ እግዚአብሔር ምን ያህል እንደሚወዳቸው ማስገንዘቢያ ነው፡፡

  1. ቀኖና ቤተ ክርስቲያን ዘመኑ የሚጠይቀውን መፍትሔ መስጠታቸው፡- ቅድስት ቤት ክርስቲያን የምትመራው በቀኖና ነው፡፡ የቀኖና ቤተ ክርስቲያን መጠበቅ የምእመናን መጠበቅ፣ የዶግማ መጠበቅ ነው፡፡ ለቅድስት ቤተ ክርስቲያን የሚጠቅመው የተጣሰውን ቀኖና እንዴት መፍተሔ እናብጅለት የሚለው በመሆኑ ከሁለቱም ወገን ለዕርቅ የተመረጡ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት መፍትሔ ሰጥተዋል፡፡ ወደፊት በአንድ ላይ እየተወያዩ ለሌሎች ችግሮችም መፍትሔ እንደሚሰጡ ማመን ይገባል፡፡ የአንጾኪያ፣ የቊስጥንጥንያ፣ የግብፅ አብያተ ክርስቲያናት ችግር በገጠማቸው ጊዜ መፍትሔ እንደሰጡት ቤተ ክርስቲያናችንም ለተፈጠረው ችግር መፍትሔ ሰጥታለች፡፡ እንኳን እግዚአብሔርን የያዙ አባቶቻችን እምነት የሌላቸውም በሕገ ተፈጥሮ ተመራምረውና እግዚአብሔር የሰጣቸውን ዕውቀት ተጠቅመው ሰውን ከሰው ያስታርቃሉ፡፡ ሽማግሌዎች ሰውን ከሰው ካስታረቁ፣ በመገዳደል የሚፈላለጉትን ደም ካደረቁ የሃይማኖት አባቶች ከዚያ በላይ መሥራት ይኖርባቸዋል፡፡ ከተፈጠረው ችግር የበለጠ ቤተ ክርስቲያንን የጎዳትና ምእመናንን ያለያያቸው ለችግሩ ያለን አመለካከት ነበር፡፡ ይህ አሁን ተወግዷል፡፡

ለዕርቀ ሰላሙ የተወከሉ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት ወደፊት መከናወን ስላለበት ጉዳይ እንዲህ ብለዋል፡- “ከቀኖና ቤተ ክርስቲያን ጥሰት የተነሣ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ፈተና ላይ ወድቃለች። ይህም ይታወቅ ዘንድ ሁለተኛው ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ቴዎፍሎስ ተላልፈው ለሞት ከተሰጡበት ጊዜ ጀምሮ እስከ አሁን ድረስ የቀኖና ቤተ ክርስቲያን ጥሰት እንደ ተፈጸመ በልኡካኑ ታምኖበታል። ስለሆነም ለአለፉት ዘመናት የቅድስት ቤተ ክርስቲያንን መብትና ክብር በመጠበቅና በማስጠበቅ በውጭም ሆነ በውስጥ በአገር ቤት የሚገኘው ቅዱስ ሲኖዶስ ሓላፊነቱን መወጣት ባለመቻሉና ከጊዜው ጋራ አብሮ ባለመሔዱ፣ ስለተፈጸመው ጥፋትና ለዘመናት በቤተ ክርስቲያኒቱ መለያየት የተነሣ በጥልቅ ኃዘን ልባችው የተሰበረውን የቅድስት ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን ልጆች ያለፉትንም ሆነ ዛሬ ላይ ያሉትን በጋራ ይቅርታ እንዲጠይቅ የልኡካኑ ጉባኤ በአንድ ድምፅ ተስማምቶ ወስኖአል።

ስለሆነም ከሁለቱም ሲኖዶስ መዋሐድ በኋላ ያለፈው የቀኖና ጥሰት ስሕተት ለወደፊቱ እንዳይደገም የቅድስት ቤተ ክርስቲያንም ሉዓላዊነት ተጠብቆና ጸንቶ እንዲኖር ለማድረግ ሕገ ቤተ ክርስቲያንንና ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያንን መሠረት ያደረገ ደንብ በቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ እንዲዘጋጅ የልኡካኑ ጉባኤ በአንድ ድምፅ ተስማምቶ ወስኖአል።”

  1. ለምእመናን ሕይወት መጨነቃቸው፡- ለምእመን ሕይወት መጨነቅ የአባቶች ተግባር ነው፡፡ እነ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ፣ ባስልዮስ ዘቂሳርያ፣ አትናቴዎስ ዘእስክንድርያ የሚጠቀሱት ለምእመናን መንፈሳዊ ሕይወት ብቻ ሳይሆን ለኑሮዋቸውም የሚጨቁ ስለነበሩ ቤተ ክርስቲያን በመልካም ታነሣቸዋለች፡፡ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ የደሀ ጠበቃ የተባለው ንግሥት አውዶክሶያ የድሀይቱን ርስት በቀማቻት ጊዜ እንድትመልስላት ደጋግሞ መክሯታል፡፡ ንግሥቲቱ አልመልስም ባለች ጊዜ ከቤተ ክርስቲያን አንድነት፣ ከምእመናን ኅብረት አውግዞ ለይቷታል፡፡ በዚህም የድሀ ጠበቃ ተብሏል፤ ለምእመናን ሕይወት የሚነጨቅ መሆኑንም በተግባር ገልጧል፡፡ ለምእመናን ሕይወትም ለአባቶች ታዛዥነትንም አጣምሮ መያዝ መንፈሳዊ ሕይወታችን እንዲለመልም ትሩፋታችን ፍሬ እንዲያፈራ ያደርጋል፡፡

የአባት ተግባር ለመንጋው መንፈሳዊ ሕይወት መጠንከር ነቅቶ ማገልገል በመንጋው ሕይወት መዛል ላለመጠየቅ ሓላፊነትን መወጣት ነው፡፡ አባቶች ሹመት ሲመጣባቸው በገድል ላይ ገድል፣ በትሩፋት ላይ ትሩፋት የሚጨምሩት ለሌላው እንቅፋት ላለመሆንና እነሱ በፈጸሙት ጥቂት ስሕተት ምእመናን ተሰነካክለው ከሃይማኖት እንዳይወጡ በማሳብ ነው፡፡ ሹመትን የሚሸሹትም በሌሎች ውድቀት ተጠያቂ ላለመሆን ነው፡፡ እግዚአብሔር ካላስገደዳቸውና ምእመናን ካላለቀሱባቸው ሹመቱን በጅ ብለው አይቀበሉም፡፡ ይህንን የሚያደርጉት ሹመቱ ኃላፊ የእነሱ ዓላማ ግን ዘለዓለማዊ በመሆኑ ነው፡፡ መንፈስ ቅዱስ መርጧቸው ምእመናንን ለመጠበቅ በተሾሙበት ተጠያቂ ላለመሆን ምክንያት መፍጠር ዘለዓለማዊውን በጊዜያዊው መለወጥ መሆኑን ስለተረዱት ነው፡፡ አባቶች ለምእመናን ሕይወት የሚጨነቁ ከሆነም ምእመናንም አብረው ይሰደዳሉ፡፡ ወደ እግዚአብሔር አልቅሰው ለመንበራቸው እንዲበቁ ያደርጋሉ፡፡

የዕርቁ ተግባራዊ መሆን ሌትም ቀንም በጸሎት እግዚአብሔርን ሲለምኑ ለኖሩ ወደፊትም ለሚለምኑ ገዳማውያንም ተስፋ የሚሰጥ ለጸሎታቸው እግዚአብሔር መፍትሔ መስጠቱን ማረጋገጫ ነው፡፡ ገዳማውያን አባቶች እግዚአብሔር ለሀገራችንም ለቤተ ክርስቲያናችንም ምሕረት እንዲያወርድ ይለምናሉ፡፡ በአባቶች መካከል ተፈጥሮ የነበረው ልዩነት መፍትሔ እንዲያገኝ ኢትዮጵያም አሜሪካም ለሚገኙ አባቶች የጻፉት ደብዳቤ እንዲህ ይላል፡፡

“እስከ ዛሬ ችግሩ ባለመፈታቱ የቤተ ክርስቲያናችን ጉዳይ ስላሳሰበንና ለትውልዱም መለያየትን አውርሰን እኛም እናንተም የታሪክ ተወቃሽ ከመሆንና በእግዚአብሔር ዘንድም ዋጋ የሚያሳጣ ሥራ ይዘን መቅረብ ስለሌለብን ይህ ጉዳይ በበረሃ በወደቁና በዝጉሐን ገዳማውያን አባቶች ተመክሮበት፣ ታምኖበትና ተጸልዮበት የተላከ መልእክት ስለሆነ እስከ አሁን የተደረጉ ጥረቶች ተጠናክረው የምንመኘው አንድነት አማናዊ ሆኖ ለማየት እንችል ዘንድ በዚህ መንገድ ላይ የሚያጋጥሙ ማናቸውንም መሰናክሎች ሁሉ አልፋችሁና አሸንፋችሁ የምንናፍቀውን የቅድስት ቤተ ክርስቲያንን አንድነት ታሳዩን ዘንድ የሊቀ ሐዋርያት ቅዱስ ጴጥሮስን ሥልጣን በሰጣችሁና ዓለሙን በደሙ በዋጃት በጌታችን በመድኃኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ስም፣ በእናቱ በቅድስት ድንግል ማርያም ስም እንዲሁም ገዳማትን በመሠረቷቸው በታላላቆቹ አባቶቻችን በአቡነ አረጋዊ፣ በአቡነ ኢየሱስ ሞዓ፣ በአቡነ ተክለ ሃይማኖት፣ በአቡነ ዜና ማርቆስ፣ በአቡነ ሳሙኤል፣ በአቡነ ያሳይ፣ በአቡነ ዐምደ ሥላሴ፣ በአቡነ ዘዮሐንስ፣ በአቡነ ኂሩተ አምላክ፣ በአቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ እንዲሁም ስማቸውን ባልጠራናቸው በሌሎችም ኦርቶዶክሳውያን አባቶቻችን ስም ተማጽኗችንን እናቀርባለን” በማለት ተማጽነው ነበር፡፡ ከእንግዲህ ሰላም እንዲፈጠር ላደረገው እግዚአብሔር ምስጋና ያቀርባሉ፡፡

  1. ዘመኑን መዋጀታቸው፡- እስከ አሁን የሚለያዩን እንጂ አንድ የሚያደርጉን፣ የሚጣሉን እንጂ የሚያስታርቁን ምክንያቶች ጥቂት ነበሩ፡፡ አሁን ሁኔታዎች በመለወጣቸው አባቶቻችንም ዘመኑን ለቤተ ክርስቲያን አንድነት ተጠቅመውታል፡፡ ይህንንም ጊዜ መጠቀምና ጽኑ መሠረት ገንብቶ ማለፍ ለነገ የማይባል ተግባር መሆኑን ተረድተዋል፡፡ እግዚአብሔር ባወቀ ቤተ ክርስቲያን ፈተና ላይ ወድቃ ቆይታ ነበር፡፡ ፈተናውን እንደ መልካም አጋጣሚ ከተመለከትነውና ለወደፊቱ ጽኑ መሠረት ካስቀመጥን ተዳክሞ የነበረው ሐዋርያዊ አገልግሎት እንዲጠናከር፣ ወደፊት ለሚመጣውም ትውልድ ማስተማሪያ ሊሆን የሚችል ሥራ መሥራት ያስችላል፡፡ ዘመኑን ተጠቅመን ሥራ ከሠራንበት እንደምንመሰገን ሐዋርያው “እንዲህ እንደ ዐዋቂዎች እንጂ እንደ አላዋቂዎች ሳይሆን እንዴት እንደምትመላለሱ በጥንቃቄ ዕወቁ፡፡

ቀኖቹ ክፉዎች ናቸውና ዘመኑን ዋጁት፡፡ ስለዚህም ሰነፎች አትሁኑ የእግዚአብሔርን ፈቃድ አስተውሉ እንጂ” (ኤፌ. ፭፥፲፭-፲፯) በማለት ምክሮናል፡፡ የሃይማኖት ሰው ትላንት የተከናወነውን፣ ዛሬ በመተግበር ላይ ያለውን፣ ነገ ሊፈጸም የሚገባውን መረዳት ይቻለዋል፡፡ ለዚህ ነው ከስንት ሺሕ ዘመን በፊት የተነገረው ልክ ዛሬ የተፈጸመ ያህል ችግራችንን ሲፈታ ሕይወታችንን ሲያንጽ የሚገኘው፡፡ አባቶቻችንም በዚህ ሁሉ ነገር በፍጥነት በሚለዋወጥበት ዘመን ትውልዱ እንዲረጋጋ፣ ከቤተ ክርስቲያን የራቀው እንዲቀርብ የሚያደርግ ሥራ መሥራት ችለዋል፡፡ የተጀመረው ፍጻሜ እንዲያገኝ እግዚአብሔር ይርዳን እንላለን፡፡

  1. በታሪክ ከመወቀስ ራሳቸውን ነፃ በማውጣታቸው፡- በየዘመናቱ የተፈጸሙትን እያነሣን ተዋንያን የነበሩትን የምንተቸውም የምናመሰግነውም ለጥፋቱም ለልማቱም ተጠያቂ ስለነበሩ ነው፡፡ አባቶች መልካም እየሠሩ ቢወቀሱ ክብር ይሆናቸዋል፡፡ ለጥፋት ተባባሪ ከሆኑ ግን የሠሩት ተገለጠ እንጂ ሐሜት ደረሰባቸው፣ ተወቀሱ አያሰኝም፡፡ ለጊዜያዊ ጥቅም፣ ነገ ለሚያልፍ ሹመት ታሪክም እግዚአብሔርም እንዲወቅሳቸው ራሳቸውን ያደከሙ በታሪክ ተከሥተው አልፈዋል፡፡ በዘመኑ የተፈጠረውን አጋጣሚ ተጠቅመው ዕርቅ ለመፈጸም ሀገር ውስጥ ያሉ አባቶች ያስተላለፉት መግለጫ መልካም ነው፡፡ ውጭ ያሉትም ለዕርቅ የተወከሉትን አባቶች የተቀበሉበት መንገድ ከእስከ አሁኑ የተለየና ምእመናንን ያስደሰተ ነው፡፡ ይህም አባቶቻችን ዘመኑን እየቀደሙት መሆኑን የሚያሳይ በመሆኑ የተጀመረው ከዳር እንዲደርስና የልዩነት አጥር እንዲፈርስ አድርጓል፡፡ በትሕትና ከቀረብንና እግዚአብሔርን ካስቀደምን የማይፈታ ችግር አለመኖሩንም አሳይቷል፡፡

አባቶቻችን እንኳን የእምነት ልዩነት ለሌላቸው በእምነት የሚለዩትንም በፍቅር ስበው የቤተ ክርስቲያን አካል ሲያደርጉ ኖረዋል፡፡ ይህ የአባቶች ተግባር እስከ ምጽአት የሚቀጥል ነው፡፡ አንድን መነናዊ ወደ ክርስትና ስለመለሰው አንድ አባት የተጻፈውን በተግባር መፈጸም ዜና አበው የተሰኘው መጽሐፍ “በግብፅ ውሰጥ በበረሃ የሚኖር አንድ ቅዱስ ሰው ነበር፡፡ ከእርሱ ርቆ ደግሞ መነናዊ የሆነ (የማኒ እምነት ተከታይ) እነሱ ካህን የሚሉት አንድ ሰው ነበር፡፡ በአንድ ወቅት ይህ ሰው ከመሰሎቹ አንዱን ሊጠይቅ ሲሔድ ኦርቶዶክሳዊው ቅዱስ ከሚኖርበት ቦታ ላይ ሲደርስ መሸበት፡፡ ሆኖም መነናዊ መሆኑ እንደሚታወቅ ስላወቀ ወደዚህ ኦርቶዶክሳዊ አባት ብሔድ አይቀበለኝም በማለት በጣም ተጨነቀ፡፡ ሆኖም ምንም አማራጭ ስላልነበረው ሔደና አንኳኳ፡፡ አረጋዊውም አባት በሩን ከፈተለት፡፡ እርሱም ማንነቱን አወቀው፡፡ ደስ ብሎት በፍቅር ተቀበለው፡፡ ምግብ ከሰጠው በኋላ አስተኛው፡፡

መነናዊውም ሰው ሌሊት ይህን ሁኔታ ሲያሰላስል አደረና ስለ እኔ ምንም ያልጠረጠረው እንዴት ዓይነት ሰው ቢሆን ነው? በእውነት ይህ ሰው የእግዚአብሔር ሰው ነው አለ፡፡ ሲነጋም ከእግሩ ላይ ወድቆ ከአሁን በኋላ እኔ ኦርቶዶክሳዊ ነኝ አለው፡፡ ከእርሱም ጋር ኖረ” በማለት ያስነብበናል፡፡ ይህ አባት ላለማስገባት የሚያግዘውን በመጥቀስ መከልከል ይችል ነበር፡፡ ብርሃን መሆንን መረጠና መነናዊውን ወደ በዓቱ አስገባው፡፡ መነናዊውም በብርሃኑ ተማርኮ ከብርሃኑ ጋር ኖረ፡፡ በዘመናችን መፈጸም የሚያስፈልገውም እንዲህ ዓይነት የብርሃን ሥራ ነው፡፡ ዘመኑን መዋጀት፣ የተማሩትን በሕይወት መግለጥ ማለትም ይህ ነው፡፡ በዚህ ወቅት አባቶቻችን ያደርጉትም መልካም ነው፡፡ የምእመናን ተስፋ እንደለመለመ ማሳያ ነው፡፡

  1. መለያየት ለመናፍቃን በር እንደሚከፍት በመረዳታቸው፡- መለያየት የሚጠቅመው ለሰይጣን ብቻ አይደለም፡፡ የግብር ልጆቹ፣ የዓላማ አስፈጻሚዎቹ ለሆኑትም ጭምር እንጂ፡፡ ያልተባለውን የተባለ እያስመሰሉ፣ ያልተነገረውን ተነገረ እያሉ የአባቶችን ልብ ሊያሻክሩ፣ ልዩነቱን ሊያሰፉ ይችሉ የነበሩ መናፍቃን ከእንግዲህ ዐርፈው ይቀመጣሉ፡፡ አባቶቻችን በመስማማታቸው የሰይጣንም የመናፍቃንም ቅስም ተሰብሯል፡፡ ለአባቶች ያሰቡ፣ ለቤተ ክርስቲያን የተቆረቆሩ እየመሰሉ ምዕራባውያን የጫኗቸውን በቤተ ክርስቲያን ላይ ለማራገፍ ሲሞክሩ ነበር፡፡ ልዩነቱም ለጥፋት ተልእኳቸው ሲያግዛቸው ነበር፡፡ ምእመናን በማይጠቅም ጉዳይ ጊዜያቸውን እንዲያባክኑ፣ አባቶች በአንድ ላይ ሆነው ቤተ ክርስቲያንን የሚጠቅም ተግባር እንዳይፈጽሙ ዕንቅፋት ሲፈጥሩ ቢቆዩም አሁን እንቅፋቷ ተወግዷል፡፡ ለወደፊቱም አባቶቻችን እየተመካከሩ ምእመናን በእምነት እንዲጸኑ፣ ያላመኑት እንዲያምኑ ሐዋርያዊ አገልግሎቱን ከእስከ አሁኑ የበለጠ ያጠናክሩታል ብለን እናመንለን፡፡

ዕርቁ በመፈጸሙ ምክንያት አጥተዋል፡፡ አባቶች በፍቅር ተገናኝተው አብረው ጸሎት በማድረጋቸው ለልዩነት ምክንያት የሆነው ሰይጣን አፍሯል፡፡ የሰይጣን ዓይን የሚጠፋው ክንፉ የሚሰበረው አባ ጊዮርጊስ እንዳለው በጸሎትና በፍቅር ነው፡፡ ጸሎት መራጃ ነውና የጠላትን ወገብ ይሰብረዋል፡፡ ጸሎትም ጦር ነውና ዓይኑን ይወጋዋል፡፡ የአባቶች አንድ መሆን ለቤተ ክርስቲያንና ለምእመናን ደስታ ሲሆን ለጠላት ግን ኀዘን ነው፡፡ በየዋህነት ከቤተ ክርስቲያን የወጡትን ለመመለስ የሚያስችል ሥራ ለመሥራት ከእንግዲህ መንገዱ ምቹ ይሆናል፡፡ አሜሪካም ኢትዮጵያም የሚገኙ አባቶች ይህን ሁሉ አስበው ለዕርቁ ተግባራዊ መሆን የበኩላቸውን ተወጥተዋል፡፡ የወደፊቱ አገልግሎት እንዲቃና ምእመናን በጸሎት፣ ሊቃውንት በምከር ሊያግዙ ይገባል እንላለን፡፡ የተጀመረው ለፍጻሜ እንዲደርስ የእግዚአብሔር ቸርነት፣ የእመቤታችን አማላጅነት፣ የቅዱሳን ሁሉ ረድኤት አይለየን፡፡

ምንጭ-ስምዐ ጽድቅ ጋዜጣ ከነሐሴ 1-15ቀን 2010ዓ.ም        

“ሰላምን ሻት ተከተላትም”(መዝ.፴፫፥፲፬)

በመ/ር ኃይለ ሚካኤል ብርሃኑ
ሰላም ማለት ጸጥታ፣ ዕረፍት፣ እርጋታ፣ እርካታ ማለት ሲሆን የእርስ በእርስ ስምምነት በአንድነት አብሮ መኖር መቻልና የዕረፍት ስሜት እንደሆነ የመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት ያስረዳል፡፡ነቢየ እግዚአብሔር ቅዱስ ዳዊት “ሰላምን ሻት ተከተላትም” ብሎ ከመናገሩ አስቀድሞ የመጽሐፉን ክፍል ወደ ኋላ መለስ ብለን የተነሳንበትን ኃይለ ቃል ሙሉ አሳቡን ለመረዳት ስንመለከተው እንዲህ የሚል ቃል እናገኛለን፡፡ “ልጆቼ ኑ ስሙኝ እግዚአብሔርን መፍራት አስተምራችሁ ዘንድ፤ ሕይወትን የሚፈቅድ ሰው ማን ነው? በጎ ዘመንንም ለማየት የሚወድድ ማን ነው? አንደበትህን ከክፉ ከልክል ከንፈሮችህም ሸንገላን እንዳይናገሩ ከክፉ ሽሽ መልካንም አድርግ ሰላምን ሻት ተከተላትም” ይላል፡፡
ልበ አምላክ ቅዱስ ዳዊት ሰላምን የምንሻበትን ምክንያት በዚሁ በተመለከትነው ኃይለ ቃል ላይ ገልጦታል፡፡ እንደ አባትነቱ እግዚአብሔር ልጆቹ ለምንሆን ለእኛ ሊያስተምረን የፈቀደለትንና እርሱ በሕይወቱ ገንዘብ አድርጎት በእግዚአብሔር እንደ ልቤ ተብሎ የተመረጠበትን ጥበብ ለእኛም ሲያካፍለን “እግዚአብሔርን መፍራት አስተምራችኋለሁአለ፡፡ምክንያቱም እግዚአብሔርን መፍራት ከሁሉ ይልቅ ቀዳሚ ነውና፡፡ ለዚህም ነው አባትና ልጅ ተባብረው(ተቀባብለው) የጥበብ መጀመሪያ እግዚአብሔርን መፍራት እንደሆነ የነገሩን(መዝ. 111፥10፣ምሳ.1፥7፣9፥10)፡፡
ከሁሉ አስቀድሞ በሕይወታችን እግዚአብሔርን መፍራት ትርጉም ላለው ሕይወት አስፈላጊ ነው፡፡ ሰላምን የምንሻበት መንገድ እሱ ነውና፡፡ ቅዱስ ዳዊት እግዚአብሔርን መፍራት ሕይወትን የሚያስገኝና በጎ ዘመንን ለማየት የምንችልበት የጥበብ (የዕውቀት) ሁሉ መሠረት ነው፡፡ ይህንንም ከገለጸ በኋላ “ሕይወትን የሚፈቅድ ሰው ማን ነው? በጎ ዘመንንም ለማየት የሚወድድ ማን ነው? ብሏል፡፡ ከላይ እንዳየነው ሕይወትን ለማግኘት የሚሻ በጎ ዘመንንም ለማየት የሚፈልግ ጥበብን (ማስተዋልን) ገንዘብ ያደረገ ሰው ነው፡፡ በመሆኑም ሕይወትን ለማግኘትና በጎ ዘመንን ለማየት የሚሻ ሰው ምን ማድረግ እንዳለበት ስንመለከትም ቅዱስ ዳዊት እንደነገረን ቀጥለን በዝርዝር እንመለከታቸዋለን፡፡
      ፩ኛ አንደበትን ከክፉ መከልከል
የሰው ልጅ በልቡ ያሰበውን በአንደበቱ ይናገራል፡፡ በልብ የታሰበውን መልካምም ይሁን ክፉ የሚያውቀው እግዚአብሔር ብቻ ሲሆን ነገር ግን የታሰበው ነገር በውጫዊ ሰውነት ላይ በሚታዩ ምልክቶች (ገጽን በማየት) መታወቅ የሚችልበት አጋጣሚ ከተፈጠረ ወይም በአንደበት ቢነገርና በሥራ ቢተገበር ሰዎች ይረዱት ይሆናል፡፡
ይሁንና አንደበትን ከክፉ ካልከለከሉት ሰዎችን የሚጎዳና የማይሽር ጠባሳ ጥሎ የማለፍ በዚያም ሰበብ ተናጋሪውን ሳይቀር ሁለተኛውን አካል በቁጣ በመጋበዝ ለሞት የማብቃት ዕድል አለው፡፡ ለዚህም ነው ቅዱስ ያዕቆብ በመልእክቱ “ምላስ እሳት ናት እነሆ ትንሽ ምላስ በሰውነታችን ውስጥ ዐመፅ የተመላበት ዓለም ናት ሥጋችንን ትበላዋለች ውስጣዊ ሰውነታችንንም ትጠብሰዋለች ከገሃነምም ይልቅ ታቃጥላለች” ይላል፡፡
ስለዚህ ሕይወትን የሚፈቅድና በጎ ዘመንን ለማየት የሚፈልግ ሰው አንደበቱን ከክፉ ነገር መከልከልና መጠበቅ ያስፈልጋል፡፡ ተናግሮ ሰውን ላለማስቀየምና ላለማስከፋት መጠንቀቅ አለበት፡፡ ሌላውንም ሰው ወደ ጥፋት ላለመምራት ማስተዋል ተገቢ ነው፡፡ አንደበት ኃያል ነውና ጦር ከፈታው ወሬ የፈታው ይበልጣል የሚል አባባል እንዳለ እናስታውሳለን፡፡
አንደበትን ከክፉ ካልከለከልነው ስድብንና ሐሜትን እናበዛለን፡፡ ይህ ደግሞ ከሕይወት ጎዳና የሚያወጣ ክፉ ተግባር ነው፡፡ በጓደኛ መካከል፣ በባልና ሚስት መካከል፣ በአንድ ሀገርና በሌላው ሀገር መካከል፣በጎሳና በጎሳ መካከል ፣ በጎረቤትና በጎረቤት መካከል ሐሜትና መነቃቀፍ፣ ስድብና ጥላቻ ካለ በጎ ዘመንን ማየት አይቻልም፡፡ ነገር ግን ሕይወትንም ሆነ በጎ ዘመንን ለማየት አንደበትን ከክፉ መከልከልና በጎ ነገርን ማውራት አስፈላጊ ነው፡፡
                                                           ፪ኛ. ከክፉ መሸሽ
ከክፉ መሸሽ ማለት ክፉን ከማድረግ መቆጠብና ክፉ ከሚያደርጉት ጋር በክፋታቸው አለመተባበር ነው፡፡ የእግዚአብሔር ሰው ሁል ጊዜም ቢሆን ከክፉዎች ጋር ኅብረት የለውም አባታችን ያዕቆብ ልጆቹን በሚመርቅበት ጊዜ ክፉ ሥራ ከሠሩ ከልጆቹ የክፋት ሥራ ጋር እንደማይተባበርና ከክፋት ጋር ኅብረት እንደሌለው ገልጧል፡፡ “ስምዖንና ሌዊ ወንድማማቾች ናቸው፡፡ በጭቅጭቃቸውና በጦራቸው ዐመጽን ፈጸሟት በምክራቸው ሰውነቴ አትገናኛቸው አሳቤም በአመጻቸው አትተባበርም በቊጣቸው ሰውን ገድለዋልና በገዛ ፈቃዳቸውም የሀገርን ሥር ቆርጠዋልና ቁጣቸው ርጉም ይሁን ጽኑ ነገርና ኩርፋታቸውም ብርቱ ነበርና በያዕቆብ እከፋፍላቸዋለሁ በእስራኤልም እበታትናቸዋለሁ” (ዘፍ.49፥5)
ያዕቆብ ምንም እንኳ በሥጋ የወለዳቸው ልጆቹ ቢሆንም በፈጸሙት ክፉ ሥራ ግን እንደማይተባበር ከክፉ ሥራቸው የራቀና ከክፋት የተለየ መልካም አሳብ እንዳለው ገልጧል፡፡ ዛሬም ቢሆን የሰው ልጆች ክፋትና በደል እየበዛ ባለበት ሰዓት የእግዚአብሔር ልጆች ከክፋት፣ ከተንኮል፣ ከውሸት፣ ከሌብነት፣ ከቅሚያ፣ ከዝርፊያ፣ ከጭካኔ፣ ከሴሰኝነት፣ ከዘማዊነት፣ ከዘረኝነት በአጠቃላይ ለራስም ለሀገርም ከማይበጁ እኩይ ምግባራትና ከሚፈጽሟቸው ሰዎች ጋር መተባበር የለብንም፡፡ ቅዱስ ዳዊት እንደነገረን ሕይወትን ለማግኘት የምንሻና በጎ ዘመን ለማየት የምንፈልግ ሁሉ ከክፉዎች ጉባኤ መለየትና አለመተባበር ያስፈልጋል፡፡
                                                     ፫ኛ. መልካም ማድረግ
ሕይወትን ለማግኘትና በጎንም ዘመን ለማየት የሚሻ ሰው ሁሉ መልካምን ሁሉ ሊያደርግ ያስፈልገዋል፡፡ ከክፉ መሸሻችንና ከከፉዎች ጋር አለመተባበራችን መልካም ሥራ ለመሥራት መሆን አለበት እንጂ ከሥራ ርቀን እንዲሁ እንድንኖር አይደለም፡፡ያለ በጎ ሥራ መኖር ስንፍና ነውና፡፡
እግዚአብሔር የሰውን ውድቀቱንና መጥፋቱን የማይሻ አምላክ ስለ ሆነ በማወቅም ይሁን ባለማወቅ በክፉ ሥራ ተጠምዶ የነበረ ሁሉ ሊመለስና በሕይወት ሊኖር ይገባዋል፡፡ በቀደመው ስሕተቱ ወንድሙን ያሳዘነ፣ሰው የገደለ፣አካል ያጎደለ፣ ግፍን የፈጸመ፣የድሃውን ገንዘብ በተለያየ ሰበብ የዘረፈ፣ጉቦ የተቀበለ፣በነዚህና መሰል እኩይ ሥራዎች ሀገሩን የጎዳ፣ እግዚአብሔርን የበደለ ሁሉ ከልብ በመጸጸት በልቅሶና በዋይታ ወደ እገዚአብሔር መመለስ ያስፈልገዋል፡፡ ለዚህም አምላካችን ልዑል እግዚአብሔር በነቢዩ ሕዝቅኤል ላይ አድሮ ኃጢአተኛው ከኃጢአቱ ተመልሶ በሕይወት መኖር እንዳለበት አስገንዝቦናል፡፡
“እኔ ሕያው ነኝና ኃጢአተኛው ከመንገዱ ተመልሶ በሕይወት ይኖር ዘንድ እንጂ ኃጢአተኛው (በደለኛው) ይሞት ዘንድ አልፈቅድም ይላል ጌታ እግዚአብሔር፡፡የእስራኤል ቤት ሆይ ተመለሱ ከከፉ መንገዳችሁ ተመለሱ ስለምንስ ትሞታላችሁ? (ሕዝ.33፥11) እንዲል፡፡
እግዚአብሔር በነቢዩ ላይ አድሮ እንደ ነገረን በደለኛ ሰው በበደሉ ቀጥሎ መጥፋት የለበትም፡፡መመለስና በሕይወት መኖር ያስፈልገዋል እንጂ፡፡ እሱም እንደ በደሉ ዓይነት የቅርታ ጠይቆ፣ ንስሓ ገብቶ፣ የበደለውን ክሶ፣ የሰረቀውን መልሶ፣ የሰበረውን ጠግኖ፣ ያጎደለውን መልቶ በፍጹም መጸጸት ሊመለስና መልካም በመሥራት ሌት ተቀን ከሚተጉት ጋራ በመልካም ሥራ ሊተባበር ያስፈልገዋል፡፡
ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ እንዳስተማረን “ስለዚህ ሐሰትን ተውአት ሁላችሁም ከመንገዳችሁ ጋር እውነትን ተነጋገሩ እኛ አንድ አካል ነንና አትቆጡ አትበድሉም ፀሐይ ሳይጠልቅም ቊጣችሁን አብርዱ ለሰይጣንም መንገድን አትስጡት የሚሰርቅም እንግዲህ አይስረቅ ነገር ግን ድሃውን ይረዳ ዘንድ በእጆቹ መልካም እየሠራ ይድከም” (ኤፌ. 4፥25) ይላል፡፡
                                                                           ሰላምን መሻት 
ሰላም ለሁሉ ነገር አስፈላጊና ሁሉን ለማድረግ የምንችልበት የመልካም ነገር ሁሉ በር ነው፡፡ ሰላምን መፈለግ ሕይወትን ለማግኘትና በጎ ዘመንንም ለማየት ያስችላል፡፡ በአይነቱ ሰላምን በሁለት መልኩ እናየዋለን፡፡ እሱም የውስጥ ሰላምና የውጭ ሰላም ወይም ውስጣዊ ሰላምና ውጫዊ ሰላም ብለን እንመድበዋለን፡፡
የሰው ልጅ ለመኖር ውስጣዊ ሰላምም ሆነ ውጫዊ ሰላም ያስፈልጉታል፡፡ ውስጣዊ ሰላም የምንለው አንድ ሰው ከፍርሐት፣ ከጭንቀት፣ ከመረበሽ፣ ከሥጋትና ወዘተ ነጻ ሆኖ መኖር ሲችል ውስጣዊ ሰላም አለው ይባላል፡፡ ይህም የውስጥን ሰላም ከሚያደፈርሱ፣ አእምሮን ከሚረብሹ፣ ልብን ከሚያቆስሉ፣ የጸጸት እሮሮን ከሚያስከትሉ ነገሮች ስንርቅና ለአእምሮ የሚመች ሥራ ስንሠራ ውስጣችን ሰላም ይሆናል፡፡ውጫዊ ሰላም የምንለው ደግሞ፡- ከቤተሰብ፣ ከጓደኛ፣ ከጎረቤት፣ ከሀገራት ጋር ተስማምተንና ተግባብተን ተቻችለንና ተረዳድተን በፍቅር ተሳስረን መኖር ነው፡፡ በመሆኑም ሰላም ከጥል፣ ከመለያየት፣ ከመጠላላት፣ ከመገፋፋት፣ ከመነቃቀፍ ተቆጥበን የጠብንና የጦርነትን ወሬ ባለመስማትና በስምምነት ተግባብቶ በመኖር የሚገለጥ ነው፡፡ ስለዚህ ሰላም ለሁሉ እንደሚያስፈልገው ካወቅን የሰላም መገኛ ማን እንደሆነና ሰላም ከየት እንደሚገኝ ማወቅ ደግሞ አስፈላጊ ነው፡፡

                                                                         የሰላም መገኛ
ሰላም የሚገኘው የሰላም ባለቤት ከሆነው ከልዑል እግዚአብሔር ነው፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ እንደገለጠው እውነተኛ ሰላም ከእግዚአብሔር ይገኛል፡፡ እርሱ የሰላም አምላክ ነውና (ሮሜ. 15፥33)፡፡ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የሰላም አለቃ ተብሏል፡፡ “ሕፃን ተወዶልናልና ወንድ ልጅም ተሰጥቶናልና አለቅነትም በጫንቃው ላይ ይሆናል ስሙም ድንቅ መካር፣ ኃያል አምላክ፣ የዘለዓለም አባት፣ የሰላም አለቃ ተብሎ ይጠራል” (ኢሳ. 9፥6) እንዲል፡፡
ዓለም ለአምስት ሺሕ አምስት መቶ ዘመን ያህል ሰላሙን አጥቶ በመቅበዝበዝ ይኖር የነበረ ሲሆን በጌታችን በመድኃኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ሰው መሆን፣ መሞትና መነሣት እውነተኛውን ሰላም አግኝቷል፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በእርሱ ሞት ምክንያት ፍርሐት ጸንቶባቸው ለነበሩት ደቀ መዛሙርት “ሰላምን እተውላችኋለሁ ሰላሜንም እሰጣችኋለሁ እኔ የምሰጣችሁ ዓለም እንደሚሰጠው አይደለም ልባችሁ አይደንግጥ አትፍሩም (ዮሐ.14፥27) በማለት ፍርሐትን፣ ስጋትን፣ ጭንቀትን፣ ሁከትን፣ መረበሽን የሚያርቀውን (የሚያስወግደውን) እውነተኛውን ሰላም አደለን፡፡
ነቢየ እግዚአብሔር ቅዱስ ዳዊት እንዳለው ሕይወትን ለማግኘትና በጎ ዘመንን ለማየት የምንሻ ሁሉ ሰላምን መሻት ያስፈልጋል፡፡ ደግሞም ሰላምን መሻት ብቻ ሳይሆን መከተል ተገቢ ነው፡፡ ምክንያቱም መሻት ብቻውን ዋጋ ሊኖረው ስለማይችል፡፡ መሻታችን ወደ ማግኘት የሚደርሰው የምንሻውን ነገር ለማግኘት ወደ መገኛው መጓዝና መቅረብ ሲቻል ነው፡፡ ለዚህም ነው ሰላምን ሻት ካለ በኋላ ተከታላትም በማለት በሰላም መንገድ መጓዝ፣ የሰላም ወሬ ማውራት፣ ለሰላም የሚስማማ ሥራ መሥራት የራሳችን ሰላም መጠበቅና የሌላውንም ሰላም አለማደፍረስ ማለት እንደሆነ የነገረን፡፡በሀገራችን ኢትዮጵያ በአሁኑ ሰዓት እየተሰማ ያለው የሰላም ዜና፣እየዘነበ ያለው ሰላም ፣እየተጠረገ ያለው የሰላም መንገድ ለዚሁ ማሳያ ነው፡፡ በአንድም ይሁን በሌላ ምክንያት ተራርቀው የነበሩ ሁለት አካላት የሚያለያያቸውን የጥላቻ ድንበር አፍርሰው የሚያገናኛቸውን የፍቅር ድልድይ መመሥረት አንዱ የሰላም መንገድ የሰላም መገለጫ ነው፡፡
ወደ ቤተ ክርስቲያን አባቶችም ስንመጣ ቀደም ሲል በነበሩት ዓመታት ተለያይቶ የነበረው ቅዱስ ሲኖዶስ ልዩነቱን እንደ ውበት ቆጥሮ ወደ መቀራረብና ወደ አንድነት ጉባኤ ለመምጣት የዘረጋው የሰላም መድረክ አንዱ የሰላም መገለጫ ነው፡፡ስለዚህ እንደ ግል ከራስ ጋር ተስማምቶ፣እንደ ሀገር በሀገር ውስጥ ካሉት ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ጋር ተግባብቶ መኖር የሚያስችሉትን የፍቅር መረቦች መዘርጋት የሰላም መንገድ፣ ሰላምን መሻትና መከተል ነው፡፡
የእግዚአብሔር ሰላም ለሁላችን ይሁንልን፡፡ አሜን
ምንጭ፤ሐመር መጽሔት 26ኛ ዓመት ቁጥር 3 ሐምሌ 2010ዓ.ም

  የ፳፻፲፩ ዓ.ም የአጽዋማት ባሕረ ሐሳባዊ ቀመር

በዲ/ን ታደለ ሲሳይ

በዘመናት ሁሉ የነበረው ያለውና የሚኖረው፣ ሁሉን የፈጠረ በሁሉም ያለ እግዚአብሔር ብቻ ነው፡፡ ለእርሱ በዚህን ጊዜ መኖር ጀመረ፣ በዚህን ጊዜ መኖር ያቆማል የማይባልለት የህልውናው መጀመሪያም ሆነ መጨረሻ የሌለው ዘለዓለማዊ ነው፡ “ተራሮች ሳይወለዱ ምድርም ዓለምም ሳይሠሩ ከዘላለም እስከ ዘለዓለም ድረስ አንተ ነህ”፡፡ “ኢየሱስም እውነት እውነት እላችኋለሁ አብርሃም ሳይወለድ እኔ አለሁ አላቸው፡፡”፣ ብሏል፡፡ በተጨማሪም፣ “ኢየሱስ ክርስቶስ ትናንትናና ዛሬ እስከ ዘለዓለም የሚኖር እርሱ ነውና” እንዲል /መዝ.89÷2፣ዮሐ. 8÷56-69 ዕብ.13÷8/፡፡

የሰው ልጅ ሐሳቡ፣ ንግግሩና ተግባሩ የሚከናወነው በጊዜ ነው፡፡ የጊዜያትና የዘመናት ቁጥርም ከሰው ልጅ ሕይወት ጋር የተቆራኘ ነው፡፡ የጊዜያትና የዘመናት ቁጥርም ከሰው ልጅ ሕይወት ጋር የተቆራኘ ነው፡፡ ዘመን ማለት በኅሊና ሲመረመር የጊዜና የዕድሜን መጠንና ልክ የሚወስን መሆኑን መጽሐፈአቡሻኸር ያስረዳል፡፡  ይህ ዘመን የሚባለው የጊዜ ዕድሜ በስያሜው አጠራር መሠረት ኃላፊ፣ የአሁንና የትንቢት/የወደፊት/  ጊዜ ተብሎ በሦስት ክፍላተ ጊዜ ይመደባል፡፡ «ወፉካሬሁሰ ለዘመን በውስተ ልብ አርአያ ወሰን ውእቱ ለጊዜ ዕድሜ ወዝንቱሰ ጊዜ ዕድሜ ዘስሙ ዘመን ይትከፈል እመንገለ ስሙ ኅበ ሠለስቱ ክፍል ኀበ ዘኅለፈ ዘመነ ወኀበ ዘይመጽእ ወኀበ ዘሀሎሂ እንዲል[1]፡፡

ከጥንተ ፍጥረት እስከ ዳግም ምጽአት ድረስ ያለው ዘመን ሁሉ በእነዚህ ሦስት ጊዜያት ሲሠፈርና ሲቆጠር ይኖራል፡፡ ያለፈውንና የሚመጣውን ዘመን ቆጥሮና ሠፍሮ መረዳትና ማስረዳት  እንደሚገባ ሲገልጽ ደግሞ፣  “ተሰአሉ  ዘቀደሙ መዋዕለ ዘኮነ እምቅድሜክሙ እምአመ ፈጠሮሙ እግዚአብሔር ለእጓለ እመሕያው ዲበ ምድር እም አጽናፈ ሰማይ እስከ አጽናፈ ሰማይ ለእመ ኮነ ዝንቱ ነገር፤ እግዚአብሔር  ሰውን በምድር ላይ ከፈጠረው ጀምሮ ከሰማይ ዳር እስከ ዳርቻዋ ድረስ ከቶ እንዲህ ያለ ታላቅ ነገር ወይም እንደ እርሱ ያለ ተሰምቶ እንደሆነ ከአንተ በፊት የነበረውን የቀድሞው ዘመን ጠይቅ”  ተብሎ ተጽፏል /ዘዳ.4÷32 ፡፡

ልበ አምላክ ዳዊትም ያለፈውን ዘመን በማስታወስ “የድሮውን ዘመን አሰብሁ፤ የዘለዓለሙን ዓመታት አሰብሁ፤ አጠነጠንሁም” በማለት ተናግሯል /መዝ.76÷51/፡፡

ዳግመኛም ይህ ዓመታትን ቆጥሮ ዘመኑን ያወቀው ልበ አምላክ ዳዊት ሲጸልይ፣ “ንግረኒ ውኅዶን ለመዋዕልየ፤ የዘመኔን አነስተኛነት ንገረኝ” ብሏል/መዝ.101÷23፡፡ ክቡር ዳዊት የዘመኑን ቁጥር ሲያሰላ እየቀነሰ እንደሚሔድ ገብቶታል፡፡ ይህ ግን ከኃጢአቱ የተነሣ አይደለም፡፡ ይልቁንም ስለ እርሱ የተጻፈው ምሥክርነት “ዳዊትም በራሱ ዘመን የእግዚአብሔርን አሳብ ከገሰገሰ በኋላ አንቀላፋ”  ይላል/ሐዋ.13÷37/፡፡ ይህ ደግሞ ዘመንን ታረዝማለች፡፡ እንዲል /ምሳ.10÷27/

በመሆኑም ኦርቶዶክሳውያን አባቶቻችንን ሥርዓት ጠብቀን፣ ሕገ እግዚአብሔርን አክብረን፣ እግዚአብሔር ሠፍሮ የሰጠንን ዘመን እርሱ በገለጸልን አቆጣጠር እየተጠቀምን በየዓመቱ አጽዋማትን እንጾማለን፣ በዓላትን እናከብራለን፡፡ በመሆኑም እንደእስካሁኑ ሁሉ ዛሬም የ2011 ዓ.ም አጽዋማትንና በዓላትን እንደሚከተለው እናወጣለን፡፡

                                                                  መባጃ ሐመር
ለአጽዋማትና በዓላት ማውጫ ወሳኝ የሆነው ነጥብ መባጃ ሐመር ነው፡፡ መባጃ ሐመር መባጊያ ሐመር እየተባለም ይጠራል፡፡ መባጊያ ሐመር ሲሆን የበጋ መመላለሻ የሚል ትርጉም ይሰጣል፡፡ በሌላ በኩል መባጃ በራሱ ማቆያ፣ ማክረሚያ ተብሎ ይተረጎማል፡፡

ሐመር መርከብ፣ መጓጓዣ የሚለውን ትርጉም ያስገኛል፡፡ መባጃ ሐመር የመጥቅዕና የዕለታት ተውሳክ ድምር ሆኖ አጽዋማትና በዓላት የሚውሉበትን ቀን ያመለክታል፡፡ በሐመር የተመሰለውም አጽዋማትና በዓላት ወደ ላይና ወደታች የሚመላለሱበት ሥርዓት /መርከብ/ ስለሆነ ነው፡፡

በአጠቃላይ መባጃ ሐመር ማለት የአጽዋማትንና የበዓላትን መዋያ ወይም መግቢያ ቀን ለማወቅ የሚያገለግል ልዩ ቁጥር ማለት ነው፡፡ [2]

ከሰባቱ አጽዋማት መካከል አራቱ በመባጃ ሐመር መሠረት በየዓመቱ እየተቀያየሩ ወይም ቀመር እየተሠራላቸው የሚወጡ ሲሆን፣ ሦስቱ ግን ያለ መባጃ ሐመር በየዓመቱ በተመሳሳይ ወቅት ይባጃሉ፡፡

በመባጃ ሐመር የሚባጁት አራት አጽዋማት ዐቢይ ጾም፣ ጾመ ድኅነት፣ ጾመ ነነዌና ጾመ ሐዋርያት ሲሆኑ፣ ያለ ማባጃ ሐመር በየዓመቱ ቋሚ ጊዜ ይዘው የሚብቱት ሦስቱ አጽዋማት ደግሞ ጾመ ነቢያት፣ ጾመ ገሃድና ጾመ ማርያም /ፍልሰታ/ ናቸው፡፡

ከላይ በተመለከትነው መሠረት መባጃ ሐመር የአጽዋማትና የበዓላት ማስገኛ ልዩ ቁጥር ነው ካልን ቁጥሩ እንዴት እንደሚገኝ ማወቅ ያስፈልገናል፡፡ መባጃ ሐመርን ለማግኘት መጥቅዕንና በዓለ መጥቅዕ የዋለበትን ዕለት ተውሳክ እንደምራለን፡፡ ይቆየን

ተውሳክ
ተውሳክ ማለት ለአንድ ጾም ወይም ለአንድ ዕለት የተሰጠ ልዩ ቁጥር (ኮድ) ማለት ነው፡፡ በዚህ ቁጥር መሠረትም አጽዋማትንና በዓላትን ማውጣት ይቻላል፡፡

ተውሳክ ማለት ጭማሪ፣ ተጨማሪ ማለት ሲሆን ለበዓላትና ለአጽዋማት ማውጫ ያገለግላል፡፡[3] እንዲል፡፡

መጥቅዕ ማለት ነጋሪት ወይም ደወል ማለት ነው፡፡ ነጋሪት ሲመታ፣ ደወል ሲደወል ሕዝብ ይሰበሰባል፤ መልእክትም ይተላለፋል፡፡ በዓላትና አጽዋማትም በመጥቅዕ ይሰበሰባሉ፤ መዋያቸውንም በዚህ ማወቅ ይቻላል፡፡ በዚህም መሠረት መጥቅዕ ከዕለታት ተውሳክ ጋር ተደምሮ መባጃ ሐመርን ያስገኛል፡፡

      መባጃ ሐመር = መጥቅዕ + በዓለ መጥቅዕ የዋለበት ዕለት ተውሳክ

መጥቅዕ= ያለፈው ዓመት መጥቅዕ + ጥንተ መጥቅዕ (ጥንተ መጥቅዕ በየዓመቱ የማይቀያየር ቁጥር ሲሆን ይኸውም 19 ነው፡፡)

መጥቅዕን በዚህ መንገድ ማግኘት ከቻልን፣ በዓለ መጥቅዕ እንዴት እንደሚገኝ አሁን እንመለከታለን፡፡

‹‹መጥቅዕ ሲበዛ ከመስከረም ንዛ፤ መጥቅዕ ሲያንስ ጥቅምትን ዳስ››

ይህ ታላቅ መልእክት ያለው የአባቶቻችን አባባል ሲሆን ለበዓለ መጥቅዕ ማውጫ የሚያገለግል ንግግራዊ ፎርሙላ ወይም ቀመር ነው፡፡ መጥቅዕ ሲበዛ ከመስከረም ንዛ ማለት በዓለ መጥቅዕን በጥቅምት አውል ማለት ሲሆን፣ መጥቅዕ ሲያንስ ጥቅምትን ዳስ ማለቱ መጥቅዕ ባነሰ ጊዜ በዓለ መጥቅዕን በጥቅምት አውለው ማለት ነው፡፡

መጥቅዕ በዛ የሚባለው ከዐሥራ አራት በላይ ሲሆን ነው፤ አነሰ የሚባለው ደግሞ ከዐሥራ አራት በታች ሲሆን ነው፡፡ በዚህም መሠረት መጥቅዕ ከዐሥራ አራት በላይ ከሆነ በዓለ መጥቅዕ በመስከረም ይውላል፤ መጥቅዕ ከዐሥራ አራት በታች ከሆነ ደግሞ በዓለ መጥቅዕ በጥቅምት ይውላል፡፡ ይህ ሁል ጊዜም ቢሆን የሚያገለግል ሕግ ነው፡፡ ለዚህም ነው አበው ‹‹መጥቅዕ ሲበዛ ከመስከረምንዛ፤ መጥቅዕ ሲያንስ ጥቅምትን ዳስ›› ያሉት፡፡

ለምሳሌ የ2011ን መባጃ ሐመር እንፈልግ፡፡

መባጃ ሐመርን ከመፈለጋችን በፊት ግን መጥቅዕን ማወቅ የግድ ነው፡፡ መጥቅዕን ለማወቅ ደግሞ የወንበርን ዓመታዊ ስሌት ማግኘት ያስፈልጋል፡፡ በመሆኑም፤

ወንበር = ቅልክ+ድልክ – 1

19

=5500+2011 -1

19

=395 ቀሪ 6-1

ወንበር =5

የ2011 ወንበር 5 ነው ማለት ነው፡፡

ከዚህ በመነሣት መጥቅዕን ለማግኘት፤

መጥቅዕ= ወንበር (ጥንተ መጥቅዕ)

= 5(19)

30

= 3 ቀሪ 5

መጥቅዕ = 5

መባጃ ሐመር = መጥቅዕ + በዓለ መጥቅዕ የዋለበት ዕለት ተውሳክ

መጥቅዕ = 5

በዓለ መጥቅዕን ለማግኘት፤ መጥቅዕ ከዐሥራ አራት በታች ስለሆነ ጥቅምት ላይ በዓለ መጥቅዕ ይውላል፡፡ ስለዚህ ጥቅምት 5 ሰኞ በዓለ መጥቅዕ ሲሆን፤ ይህ በዓለ መጥቅዕ የዋለበት ዕለት ሰኞ ተውሳኩ 6 ነው ማለት ነው፡፡

ስለዚህ፤

መባጃ ሐመር = መጥቅዕ + በዓለ መጥቅዕ የዋበት ዕለት ተውሳክ

መጥቅዕ = 5

በዓለ መጥቅዕ የዋለበት ዕለት = ሰኞ

የሰኞ ተውሳክ = 6

መባጃ ሐመር = 5 + 6 = 11

ስለዚህ የ2011 ዓ.ም መባጃ ሐመር 11 ስለሆነ በዚህ መሠረት የ2011ን በዓላትና አጽዋማት ማውጣት ይቻላል፡፡

የመባጃ ሐመር ዋነኛ አገልግሎት ከአጽዋማት ተውሳክ ጋር እየተደመረ በዓላትንና አጽዋማትን ማስገኘት ነው፡፡ ስለዚህ የአጽዋማትንና የበዓላትን ተውሳክ ማወቅ ይጠበቅብናል፡፡በመሆኑም መባጃ  ሐመሩንና የበዓላትና የአጽዋማትን ተውሳክ በመጠቀም የ2011ን የበዓላትና የአጽዋማትን መግቢያ እናገኛለን፡፡

ጾመ ነነዌ
ጾመ ነነዌ የራሱ የሆነ ተውሳክ የለውም፡፡ የሚወጣውም ያለ ተውሳክ በመባጃ ሐመር ብቻ ነው፡፡

ሀ. በዓለ መጥቅዕ በመስከረም በሚውልበት ጊዜ ጾመ ነነዌ በጥር ይውላል፡፡

ለ. በዓለ መጥቅዕ በጥቅምት በሚሆንበት ጊዜ ጾመ ነነዌ በየካቲት ይውላል፡፡

ሐ. መጥቅዕ ከ፲፬(14) በላይ ሆኖ ከዕለት ተውሳክ ጋር ስንደምረው ከ፴(30) ከበለጠ ጾመ ነነዌ በየካቲት ይውላል፡፡

ከላይ የተዘረዘሩት አራት ነጥቦች መቼም ቢሆን የማይለወጡ ቋሚ ሕጎች ናቸው፡፡ በመሆኑም እነዚህን አራቱን በቃል አጥንቶ መያዝ ያስፈልጋል፡፡

ምሳሌ፡- ከላይ የተመለከትነውን የ2011 ዓ.ምን ጾመ ነነዌ እናውጣ፡፡

መጥቅዕ 5 ሲሆን በዓለ መጥቅዕ ጥቅምት ሰኞ ነው፡፡ መባጃ ሐመሩ ደግሞ 11 ነው፡፡ ከላይ በ‹‹ለ››እንደተመለከትነው በዓለ መጥቅዕ በጥቅምት በሚሆንበት ጊዜ ጾመ ነነዌ በየካቲት ይውላል ብለናል፡፡ በተጨማሪም ጾመ ነነዌ ተውሳክ ስለሌላት በመባጃ ሐመርብቻ ነው የምትወጣ ብለናል፡፡ ስለዚህ መባጃ ሐመሩ 11 ስለሆነ የካቲት 11 ቀን ጾመ ነነዌ ትገባለች ማለት ነው፡፡

ዐቢይ ጾም
የዐቢይ ጾምን ተውሳክ ለማግኘት ከጾመ ነነዌ ማግስት ጀምሮ እስከ ዐቢይ ጾም ያሉትን ቀናት መቁጠር ነው፡፡ እኒህም ቀናት ፲፬(14) ናቸው፡፡ በመሆኑም የዐቢይ ጾም ተውሳክ ፲፬(14) ነው ማለት ነው፡፡

ለምሳሌ በ2011 ዓ.ም ዐቢይ ጾም የገባው፤

የዐቢይ ጾም መግቢያ = የ2011 ዓ.ም መባጃ ሐመር + የዐቢይ ጾም ተውሳክ

መባጃ ሐመር = 11

የዐቢይ ጾም ተውሳክ = ፲፬(14)

የዐቢይ ጾም መግቢያ = 11 + 14 = 25

የካቲት 25 የዐቢይ ጾም መግቢያ ነው ማለት ነው፡፡

ደብረ ዘይት
ከጾመ ነነዌ ማግስት እስከ ዐቢይ ጾም ያሉትን ቀናት ቆጥረን የዐቢይ ጾም ተውሳክ ፲፬(14) ነው ብለናል፡፡ የደብረ ዘይትን ተውሳክ ለማግኘትም በተመሳሳይ መልኩ ከጾመ ነነዌ ማግስት እስከ ደብረ ዘይት ያሉትን ቀናት ስንቆጥር ፵፩(41) ቀናትን እናገኛለን፡፡ ለ፴(30) ሲካፈል ቀሪ (፲፩)11ን እናገኛለን፡፡ ስለዚህ የደብረ ዘይት ተውሳክ ፲፩(11) ነው ማለት ነው፡፡

ደብረ ዘይት = የ2011 ዓ.ም መባጃ ሐመር + የደብረ ዘይት ተውሳክ

= 11 + 11

= 22

ከየካቲት ቀጥሎ ያለው ወር መጋቢት ስለሆነ መጋቢት 22 ደብረዘይት ነው ማለት ነው፡፡

ሆሣዕና
ከጾመ ነነዌ ማግስት እስከ ሆሣዕና ያሉት ቀናት ፷፪(62) ናቸው፡፡ እንደተለመደው ለ፴(30) ስናካፍለው ፪(2) ቀሪ እናገኛለን፡፡ በመሆኑም የሆሣዕና ተውሳክ (፪)2 ነው ማለት ነው፡፡

በ2011 ዓ.ም፤

ሆሣዕና መግቢያ = የ2011 ዓ.ም መባጃ ሐመር + የሆሣዕና ተውሳክ

= 11 + 2

= 13

ሚያዝያ 13 በዓለ ሆሣዕና ነበር ማለት ነው፡፡

ስቅለት
ከጾመ ነነዌ ማግስት እስከ ስቅለት ያሉት ቀናት ሥልሳ ሰባት ናቸው፡፡ ለሠላሳ ስናካፍለው ቀሪ ፯(7)ን እናገኛለን፡፡ በመሆኑም የስቅለት ተውሳክ ፯/7/ ነው ማለት ነው፡፡

በ2011 ዓ.ም፤

ስቅለት = የ2011 ዓ.ም መባጃ ሐመር + የስቅለት ተውሳክ

= 11 + 7

= 18

ሚያዝያ 18 ስቅለት ነው ማለት ነው፡፡

ትንሣኤ
ከጾመ ነነዌ ማግስት እስከ ትንሣኤ ያሉት ቀናት ሥልሳ ዘጠኝ ናቸው፡፡ ለሠላሳ ስናካፍለው ቀሪ ፱(9) እናገኛለን፡፡ በመሆኑም የትንሣኤ ተውሳክ ፱ (9) ነው ማለት ነው፡፡

በ2011 ዓ.ም፤

ትንሣኤ = የ2011 ዓ.ም መባጃ ሐመር + የትንሣኤ ተውሳክ

= 11 + 9

= 20

ሚያዝያ 20 ትንሣኤ ነው ማለት ነው፡፡

ርክበ ካህናት
ከጾመ ነነዌ ማግስት እስከ ርክበ ካህናት ያሉት ቀናት ፺፫(93) ናቸው፡፡ ለሠላሳ ስናካፍለውቀሪ ፫(3)ን እናገኛለን፡፡ በመሆኑም የርክበ ካህናት ተውሳክ ፫(3) ነው ማለት ነው፡፡

በ2011 ዓ.ም፤

ርክበ ካህናት = የ2011 መባጃ ሐመር + የርክበ ካህናት ተውሳክ

= 11 + 3

= 14

ግንቦት 14 ርክበ ካህናት ነው ማለት ነው፡፡

ዕርገት
ከጾመ ነነዌ ማግስት እስከ በዓለ ዕርገት ያሉት ቀናት ፻፰(108) ናቸው፡፡ ፻፰(108)ን ለ፴(30) ስናካ ፍለው ፫(3) ጊዜ ደርሶ ፲፰(18) ይቀራል፡፡ በመሆኑም የዕርገት ተውሳክ ፲፰(18) ነው ማለት ነው፡፡

በ2011 ዓ.ም፤

ዕርገት = የ2011 ዓ.ም መባጃ ሐመር + የስቅለት ተውሳክ

= 11 + 18

= 29

ግንቦት 29 ዕርገት ነው ማለት ነው፡፡

ጰራቅሊጦስ
ከጾመ ነነዌ ማግስት እስከ ጰራቅሊጦስ ያሉት ቀናት ፻፲፰(118)ናቸው፡፡ ፻፲፰(118)ን ለ፴(30) ስናካፍለው ፫(3) ቀሪ ፳፰(28) ይሆናል፡፡

፳፰(28) የጰራቅሊጦስ ተውሳክ ይሆናል፡፡

በ2011 ዓ.ም፤

ጰራቅሊጦስ = የ2011 ዓ.ም መባጃ ሐመር + የጰራቅሊጦስ ተውሳክ

= 11 + 28

= 39

ለ፴(30) ሲካፈል 9 ቀሪ ይሆናል፡፡ ጰራቅሊጦስ ሰኔ 9 ነው ማለት ነው፡፡

ጾመ ሐዋርያት
ከጾመ ነነዌ ማግስት እስከ ጾመ ሐዋርያት ያሉት ቀናት ፻፲፱(119) ናቸው፡፡ ፻፲፱ (119)ን ለ፴(30) ስናካፍለው ፫(3) ጊዜ ደርሶ ፳፱ (29) ይቀራል፡፡

፳፱(29) የጾመ ሐዋርያት ተውሳክ ነው ማለት ነው፡፡

በ2011 ዓ.ም፤

ጾመ ሐዋርያት = የ2011 ዓ.ም መባጃ ሐመር + የጾመ ሐዋርያት ተውሳክ

= 11 + 29

= 40

40 ለ30 ሲካፈል 1 ቀሪ 10 ይሆናል፡፡

ስለዚህ ሰኔ 10 የጾመ ሐዋርያት መግቢያ ነው ማለት ነው፡፡

ጾመ ድኅነት
ከጾመ ነነዌ ማግስት እስከ ጾመ ድኅነት ያሉት ቀናት ፻፳፩(121) ናቸው፡፡ ፻፳፩(121) ለ፴(30) ሲካፈል ፬(4) ጊዜ ደርሶ ፩(1) ይቀራል፡፡ የጾመ ድኅነት ተውሳክ ፩(1) ነው ማለት ነው፡፡

በ2011 ዓ.ም፤

ጾመ ድኅነት = የ2011 ዓ.ም መባጃ ሐመር + የጾመ ድኀነት ተውሳክ

= 11 + 1

= 12

ሰኔ 12 የጾመ ድኅነት መግቢያ ዕለት ነው ማለት ነው፡፡

በአጠቃላይ የአጽዋማቱ ተውሳክ እንደሚከተለው ነው፡፡

አጽዋማት       ተውሳክ           የመዋያ ዕለት

ጾመ ነነዌ        = አልቦ (0)         የካቲት 11

ዐቢይ ጾም        = ፲፬(14)           የካቲት 26

ደብረ ዘይት       = ፲፩(11)          መጋቢት 22

ሆሣዕና          = ፪(2)             ሚያዝያ 13

ስቅለት           = ፯(7)             ሚያዝያ 18

ትንሣኤ          = ፱(9)             ሚያዝያ 20

ርክበ ካህናት      = ፫(3)             ግንቦት 14

ዕርገት           = ፲፰(18)          ግንቦት 29

ጰራቅሊጦስ       = ፳፰(28)          ሰኔ 9

ጾመ ሐዋርያት    = ፳፱(29)          ሰኔ 10

ጾመ ድኅነት       = ፩(1)            ሰኔ 12

ኢየዐርግና ኢይወርድ
እነዚህ አጽዋማት ምንም እንኳን በየዓመቱ የየራሳቸው ቀመራዊ ማውጫ ቢኖራቸውም ገደብ ግን አላቸው፡፡ ገደባቸውም በግእዝ ኢይወርድና ኢየዐርግ ሲባል፣ ኢይወርድ የታችኛው እርከን፣ ኢየዐርግ ደግሞ የላይኛው እርከን ነው፡፡ በአማርኛው ገደብ ልንለው እንችላለን፡፡ በዚህም መሠረት የአጽዋማት ገደብ የሚከተለውን ይመስላል፡፡

አጽዋማትና በዓላት          ኢይወርድ    ኢየዐርግ

ጾመ ነነዌ             ጥር 17             የካቲት 21

ዐቢይ ጾም           የካቲት 1             መጋቢት 5

ደብረ ዘይት          የካቲት 28            ሚያዝያ 2

ሆሣዕና             መጋቢት 19           ሚያዝያ 23

ስቅለት          መጋቢት 24           ሚያዝያ 28

ትንሣኤ            መጋቢት 26           ሚያዝያ 30

ርክበ ካህናት        ሚያዝያ 20             ግንቦት 24

ዕርገት             ግንቦት 5                ሠኔ 9

ጰራቅሊጦስ         ግንቦት 15               ሠኔ 19

ጾመ ሐዋርያት      ግንቦት 16               ሠኔ 20

ጾመ ድኅነት        ግንቦት 18               ሠኔ 22

ቋሚ የመግቢያ ጊዜ ያላቸው አጽዋማት
                               ጾመ ነቢያት
ጾመ ነቢያት በአራቱም ዘመናት ምን ጊዜም ኅዳር ዐሥራ አምስት እንዲጾም ተወስኗል፡፡

                                   ጾመ ገሀ  ድ
ጾመ ገሀድ የትክ ጾም ነው፡፡ ይህ ጾም ዓርብንና ሮብን የሚያሽር በዓል በዓርብና በሮብ ሲውል በትኩ በዋዜማው የሚጾም ጾም ነው፡፡ ለምሳሌ ጥምቀት ዓርብ ቢውል ሐሙስ ጾመ ገሀድ ይሆናል፡፡ ነገር ግን አበው ለጾም ማድላት አለብን በማለት ጾመ ገሀድ ምንጊዜም ጥምቀት በጾም ቀን ዋለም አልዋለም በዋዜማው እንዲጾም ወስነዋል፡፡

                                   ጾመ ፍልሰታ 
ሐዋርያት የእመቤታችንን ትንሣኤ ለማየት ይበቁ ዘንድ ሱባኤ ገብተው የጾሙት ጾም ሲሆን ምንጊዜም ነሐሴ አንድ ቀን ገብቶ ከሁለት ሱባኤ በኋላ የእመቤታችን ዕርገት ይፈጸማል፡፡

[1]  አቡሻኸር አንቀጽ 1 ገጽ 17 (የብራና ጽሑፍ)

[2] ዲ/ን ታደለ ሲሳይ ባሕረ ሐሳብ በቀላል አቀራረብ ገጽ 71

[3]  ዝኒ ከማሁ ገጽ 66

በኢትዮጵያ ሱማሌ ክልል በተከሰተው ችግር ከማኅበረ ቅዱሳን የተሰጠ መግለጫ!

 

                                                               እንግዲያስ ሰላም የሚቆምበትን እርስ በርሳችንም የምንታነጽበትን እንከተል /ሮሜ  1419/

         በሀገራችን በኢትዮጵያ የሚካሔደውን የመንግሥት የአሠራር ለውጥ ተከትሎ ላለፉት ጥቂት ወራት በተለያዩ አካባቢዎች ግጭቶች መከሰታቸው የሚታወቅ ነው፡፡ በግጭቶችም ከሀብት ውድመት እስከ ክቡሩ የሰው ሕይወት ኅልፈት ድረስ መከሰቱ እና በዚህም መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ማዘኑና ለመፍትሔውም በሚችለው ሁሉ መረባረቡ የሚታወቅ ነው፡፡ ባለፉት ሁለት ቀናት በሶማሌ ክልል የተከሰተው ግን በተለይ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያንን በተለየ ሁኔታ አደጋ ውስጥ መክተቱ ደግሞ የበለጠ አሳዝኖናል፡፡ ይልቁንም ደግሞ ግጭቱ ሆነ ተብሎ ሃይማኖትን መሠረት ያደረገ ሰፊ ጥፋት ለመቀስቀስ የታሰበ መምሰሉ በእጅጉ አሳስቦናል፡፡ ሆኖም ክርስቲያኖችም ሆኑ የሌላ እምነት ተከታዮች ነገሩን በጥንቃቄና ኃላፊነት በሚሰማው ሁኔታ እንደሚይዙት እምነታችን ታላቅ ነው፡፡

የኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አገልጋዮች እና አማኞች ላይ ልዩ ትኩረት አድረገው ግድያ መፈጸማቸው፣ አብያተ ክርስቲያንን ማቃጠላቸው እና የአማኞቹን ሀብት ንብረት መዝረፋቸውና ማቃጠላቸውም ቢሆን ለሟቹቹ የሰማዕትነትን ክብር ከማቀዳጀቱና ለቤተ ክርስቲያንም ጸጋና ኃይል ከማጎናጸፍ ያለፈ ዘላቂ ጉዳት ሊያስከትል አይችልም፡፡ ምክንያቱም ክርስቲያኖች “በእኔ ሳላችሁ ሰላም እንዲሆንላችሁ ይህን ተናግሬአችኋለሁ። በዓለም ሳላችሁ መከራ አለባችሁ፤ ነገር ግን አይዞአችሁ፤ እኔ ዓለምን አሸንፌዋለሁ” /ዮሐ 16፥33 / በሚለው የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ቃል አምነውና ታምነው የሚኖሩ የሰላም ሰዎች ናቸውና፡፡ ሰማዕትነቱም ቢሆን ለሟቾቹ ብቻ ሳይሆን መከራውን፣ ስቃዩንና ጭንቀቱ ሁሉ ለደረሰባቸው ሁሉ ነውና ሥርየተ ኃጢአትንና ጸጋ እግዚአብሔርን ያበዛላቸዋል እንጂ ቤተ ክርስቲያንን ሊያጠፋት አይችልም፡፡ እንዲያውም በዘመነ ሰማዕታት እንደሆነው በሌላ አካባቢ ያሉ ክርስቲያኖችን ሁሉ ለሰማዕትነት የሚያበቃ በዚያ ጉዳት የደረሰባቸውንም በመርዳት፤ አብያተ ክርስቲያኑንም የበለጠ አድርጎ በመሥራት የሰማዕትነቱ ተካፋይ የመሆን እድል ይሰጣቸዋል፡፡ በፍትሐ ነገሥታችን አንቀጸ ሰማዕታት ላይ እንደተገለጸውም በዚያ የተጎደቱን ለመርዳት የሚረባረቡ ሁሉ ቁጥራቸው ከሰማዕታት ስለሆነ በመንፈሳዊ ዐይን ለሚያዩት ሁሉ ጥቅም እንጂ ጉዳቱ እምብዛም ነው፡፡

ለክርስቲያኖች እንዲህ ያለ መንፈሳዊ ጠቀሜታ ቢኖረውም የሰው ሕይወት ክቡር ከመሆኑ የተነሣ ደግሞ በማናቸውም የሰው ልጆች ላይ ያለአግባብ የሚደርሰው ጥፋት በእጅጉ ያሳዝነናል፤ ያሳስበናልም፡፡ ስለዚህም ከመንግሥት ጀምሮ ኃላፊነት ያለባቸው አካላት ሁሉ ይህን የመሰለ ችግር እየሰፋና እየተበራከተ እንዳይሔድ ቅድመ ጥፋት የጥንቃቄና የሰዎችን ሁሉ የደኅንነት ዋስትና የሚያረጋግጡ እርምጃዎችን መውሰድ ይኖርባቸዋል፡፡ በዚህ ዐይነት ድርጊት የተሳተፉ አካላትንም ለሕግ በማቅረብ ለሰዎች ዋስተናን ለአጥፊዎችም ትምህርትን መስጠት ይኖርባቸዋል፡፡

ጥፋት አድራሾቹ “የሰላምንም መንገድ አያውቁም። በዓይኖቻቸው ፊት እግዚአብሔርን መፍራት የለም” /ሮሜ 3፥17-18 / ተብሎ በቅዱሱ ሐዋርያ የተነገረላቸው መሆናቸውን ለመረዳት አይቸግርም፡፡ ስለዚህም እነዚህ አካላት የየትኛውንም ሃይማኖት የማይወክሉና የራሳቸውን ሰላም አጥተው የሌሎቻችንም ለመውሰድ የተነሡ መሆናቸውን ተረድቶ የእነርሱ ጠባይን ላለመውሰድና ለበቀልና ለመሳሰሉት ተጨማሪ አደጋ አምጭ ነገሮች ተጋላጭ እንዳሆን መጠበቅም ክርስቲያናዊ ብቻ ሳይሆን የመልካም ዜግነት ግዴታችን መሆኑንም ለማስታወስ እንወድዳለን፡፡  በዚህ አጋጣሚ ጥፋቱ ከደረሰው በላይ እንዳይሆን ስትከላከሉና የመልካም ዜግነት ግዴታችሁን ስትወጡ ለነበራችሁ ክቡር የሱማሌ ክልል ህዝብ ከፍ ያለ አክብሮታችንን እናቀርብላችሀለን፡፡ አሁንም በየመጠለያውና በየቦታው ያሉ የጉዳት ሰለባዎችን በመደገፍና ከወደቁበት በማንሳት አርአያነታችሁን እንድምታሳዩንእናምናለን፡፡

በሶማሌ ክልልና በሌሎችም ሆናችሁ ይህ አደጋ የደረሰባችሁ ክርስቲያኖችም ነቢዩ ኢሳይያስ “በአንተ ታምናለችና በአንተ ለምትደገፍ ነፍስ ፈጽመህ በሰላም ትጠብቃታለህ” /ኢሳ 26 ፤ 3/ ሲል በተናገረው ቃለ መጽሐፍ ተማምናችሁ ብትጸኑ ለሰማዕትነት ክብር ከታጩት በቀር እግዚአብሔር እንደሚጠብቃችሁ የታመነ አምላክ ነውና አትረበሹ፡፡ ከዐለም የሆነው ሁሉ ስለመጥፋቱም አትጨነቁ፡፡ “ስለዚህ እላችኋለሁ፥ ስለ ነፍሳችሁ በምትበሉትና በምትጠጡት፥ ወይም ስለ ሰውነታችሁ በምትለብሱት አትጨነቁ፤ ነፍስ ከመብል ሰውነትም ከልብስ አይበልጥምን?” /ማቴ 6 ፤ 25/ ሲል ያስተማረንን ጌታችንን አስታውሳችሁ እንድትጸኑ በፍጹም ፍቅርና ትሕትና ልናሳታውሳችሁ እንወድዳለን፡፡ እንደታዘዝነውም ለሚያሳድዷችሁና መከራውን ላመጡብን ሁሉ ከልብና ከእውነት እንጸልይላቸው፤ ጌታችንን አብነት አድረገንም በአንድነት አቤቱ  የሚያደርጉትን አያውቁምና ይቅር በላቸው ብለን በየዕለቱ እንጸልይላቸው፡፡ በየትም ዐለም ያለን ክርስቲያኖች ሁላችንም ከመቼዉም ጊዜ በላይ ስለቤተ ክርስቲያናችን፣ ስለሀገራችንና በስደትና በመከራ ላይ ስላሉት ሁሉ እግዚአብሔር በሃይማኖታቸው መጽናትን፤ በፍቅርም ይቅርታ ማድረግን በልቡናቸው ይጨምር ዘንድ በጥፋት ጎዳናም ያሉት ልቡና አግኝተው ይመለሱ ዘንድ ጊዜ ወስደን ሥራዬ ብለን ልንጸልይ ይገባናል፡፡ ከዚህም በሻገር ከሰማዕትነት ክብር እንካፈልና እኛንም ልንሸከመው ከማንችለው ፈተና እግዚአብሔር ይጠብቀን ዘንድ የተፈናቀሉትን ለማቋቋም፣ የተቸገሩትን ለመርዳት፣ የፈረሱ አብያተ ክርስቲያንን ለማሳነጽና የሰማዕታቱን ቤተ ሰቦች በዘላቂ ለመርዳት መነሣሣትና ኃላፊነታችንን በአግባቡ በፍጥነት ልንወጣ ይገባናል፡፡

ጉዳት በማድረስ ከምክር እስከ ገቢር የተሳተፋችሁትም በማወቅም ባለማወቅም ከፈጸማችሁት ጥፋት ትመለሱና የእግዚአብሔርንም ይቅርታ ተገኙ ዘንድ “ከክፉ ሽሽ መልካምንም አድርግ ሰላምን እሻ ተከተላትም” /መዝ 34፥14/  በሚለው ቃለ መጽሐፍ እንለምናችኋለን፡፡ የማትመለሱ ከሆነ ግን እርሱ የቁጣ ፊቱን ወደ እናንተ ባዞረ ጊዜም ሊያድናችሁ የሚችል ኃይል የለም፡፡ በነቢዩ ዳዊት “እግዚአብሔርን የምትረሱ እናንተ፥ ይህን አስተውሉ አለዚያ ግን ይነጥቃል የሚያድንም የለም” /መዝ 50 ፤ 22/ ተብሎ ተጽፏልና፡፡ ስለዚህም ይህን አምላካዊ ማስጠንቀቂያ አስባችሁ እንድትመለሱና ሀገራችን የሰላምና የፍቅር ሀገር እንድናደርጋት በእውነት እንማጸናችኋለን። ሁላችንም ልንጠቀም የምንችለው በሰላም፣ በፍቅርና በመተሳሰብ ብቻ ነውና በታላቁ ሐዋርያ በቅዱስ ጳውሎስ ቃል “እንግዲያስ ሰላም የሚቆምበትን እርስ በርሳችንም የምንታነጽበትን እንከተል በማለት ጥሪያችንን እናቀርብላችኋለን /ሮሜ  14፥19/።

እግዚአብሔር አምላካችን ሀገራችንን ሕዝቦቿን ሁሉ በጽኑ ሰላም ይጠብቅልን፤ አሜን፡፡

 ማኅበረ ቅዱሳን

 

 

 

 

 

 

ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል በተፈጠረው ችግር የተሰጠ መግለጫ

Betekihenet megelecha

ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል በተፈጠረው ችግር የተሰጠ መግለጫ

Betekihenet megelecha