በጸሎተ ሐሙስ የተፈጸሙ ተግባራት 

በሊቀ ማእምራን ብርሃነ መስቀል አጠና

የሊቃውንት ጉባኤ አባል

መጋቢት ፳፮ ቀን ፳፻፲ ዓ.ም

በዕለተ ሐሙስ ከተፈጸሙ ዐበይት ተግባራት አንዱ መድኃኒታችን ክርስቶስ ‹‹ይህ ሥጋዬ ነው፤ ይህ ደሜ ነው፤›› ብሎ አማናዊ ሥጋውንና ደሙን መስጠቱ ነው (ማቴ. ፳፮፥፳፮-፳፰)፡፡ እንደዚሁም ይህ ዕለት ሰፊ ጸሎት የተደረገበት የጸሎት ቀን ነው፡፡ ጌታችን ሐሙስ ዕለት ወዙ እንደ ውኃና እንደ ደም ወርዶ መሬቱን ጭቃ እስኪያደርገው ድረስ መላልሶ ስለ ጸለየ ዕለቱ ‹ጸሎተ ሐሙስ› ተብሎ ተጠርቷል፡፡ ጌታችን የጸለየበትን ቦታም ወንጌላውያኑ በተለያየ ስያሜ ጠርተውታል፤ ማቴዎስና ማርቆስ – ዐፀደ ወይንጌቴሴማኒ ሉቃስ – ደብረ ዘይት ዮሐንስ – ‹ማዕዶተ ቄድሮስፈለገ አርዝዐፀደ ሐምል በማለት ሰይመውታል (ማቴ.፳፮፥፴፮፤ ማር.፲፬፥፴፪፤ ሉቃ. ፳፩፥፴፯፤ ፳፪፥፴፱፤ ዮሐ. ፲፰፥፩)፡፡

በተጨማሪም ይህ ዕለት (ሐሙስ) ያለ እርሱ ፈቃድ ሊይዙት እንደማይችሉ ለማስረዳት ጌታችን በመለኮታዊ ኃይሉ እንደ ቅጠል እንዲረግፉ ካደረጋቸው በኋላ በይቅርታው ብዛት መልሶ በማስነሣት በፈቃዱ ራሱን ለአይሁድ አሳልፎ የሰጠበት ዕለት ነው (ዮሐ. ፲፰፥፭-፰)፡፡ በዕለተ ሐሙስ ከተከናወኑ ዐበይት ተግባራት መካከል ሠራዔ ሕግ፣ ፈጻሜ ሕግ የኾነው ጌታችን አምላካችንና መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሕገ ኦሪትን እየፈጸመ አድጓልና በኦሪት ሥርዓት የሚፈጸመውን የመጨረሻውን በግዐ ፋሲካ (የፋሲካ በግ) ከደቀ መዛሙርቱ ጋር መመገቡ አንደኛው ነው፡፡ ይሁዳ እንደሚያስይዘው ለሐዋርያት በምልክት ማስረዳቱ ሁለተኛው ሲኾን (ዮሐ. ፲፫፥፳፩)፤ እንደ አገልጋይ ራሱን ዝቅ አድርጎ የደቀ መዛሙርቱን እግር ማጠቡ ደግሞ ሦስተኛው ነው፡፡

ጌታችን የደቀ መዛሙርቱን እግር የማጠቡ ምሥጢር

ጌታችን አምላካችንና መድኃኒታን ኢየሱስ ክርስቶስ የደቀ መዛሙርቱን እግር ካጠበ በኋላ ‹‹እናንተ መምህራችን፣ ጌታችን ትሉኛላችሁ፤ መልካም ትላላችሁ፡፡ እኔ ጌታችሁ መምህራችሁ ስኾን ዝቅ ብዬ እግራችሁን ካጠብኋችሁ እናንተም ዝቅ ብላችሁ የወንድሞቻችሁን እግር ልታጥቡ ይገባችኋል፡፡ ምሳሌ ኾኛችኋለሁና፤›› በማለት የትሕትና ሥርዓት ሠርቶ እነርሱም በሥራ እንዲገልጡት አዝዞአቸዋል (ዮሐ. ፲፫፥፲፭)፡፡ በግእዝ የተጻፈ አንድ ትርጓሜ ወንጌል ‹‹እዘርእ ፍቅረ ወትሕትና ውስተ አልባቢክሙ፤ ፍቅርንና ትሕትናን በልባችሁ እዘራለሁ፤›› እንዳላቸው ይናገራል፡፡

ሠለስቱ ምእትም በአንቀጸ መነኮሳት ‹‹ወኢትትሐከይ ኀፂበ እግረ አኃው ሶበ መጽኡ ኀቤከ እስመ በእንተ ዛቲ ትእዛዝ ይትኀሠሥዎሙ ለእለ ያጸርዕዋ ለዛቲ ግብር ወለእመ ኮኑ ኤጲስ ቆጶሳተ እስመ እግዚአብሔር ኀፀበ እግረ አርዳኢሁ ቅድመ ወአዘዞሙ ከማሁ ይግበሩ፤ ወንድሞች ወደ አንተ በመጡ ጊዜ እግራቸውን ማጠብን ቸል አትበል፡፡ ይህችን ሥራ ቸል የሚሏትን ስለዚህች ትእዛዝ ሥላሴ በፍዳ ይመረምሯቸዋልና፡፡ ኤጲስቆጶሳትም ቢኾኑ እግዚአብሔር አስቀድሞ የደቀ መዛሙርቱን እግር አጥቦ እንዲሁ ያደርጉ ዘንድ አዝዟቸዋልና፤›› (ሃይማኖተ አበው ፳፥፳፱፤ ፩ኛ ጢሞ. ፭፥፱-፲)፡፡

የጌታችንን ትሕትና በተናገረበት ክፍል፣ ሊቁ ያዕቆብ ዘሥሩግ ‹‹የማይታዩ ረቂቃን መላእክቱ አደነቁ፤ ከልዑል ዙፋኑ ወርዶ ለደቀ መዛሙርቱ ሲያገለግል ባዩት ጊዜ አገልጋዮቹ መላእክት ደነገጡ፡፡ ትሕትና ወዳለበት ፍቅር የአሕዛብ እግረ ልቡናን ያቀና ዘንድ ግሩም እሳት በትሕትና መገለጡን ባዩ ጊዜ ብርሃናት ደነገጡ፤›› ይላል (ሃይማኖተ አበው ፹፰፥፰)፡፡ ፊልክስዩስም ‹‹ወኅፅበተ ፋሲካ ትትሜሰል በምሥጢረ ትሕትና ፍጽምት፤ የፋሲካ ኅፅበት ፍጹም በኾነ የትሕትና ሥራ ትመሰላለች›› ብሏል (መጽሐፈ መነኮሳት)፡፡

አባ ጊዮርጊስ ዘጋሥጫ በመጽሐፈ ምሥጢር ‹‹… ጌታችን ወደ ስምዖን ጴጥሮስ በደረሰ ጊዜ ጴጥሮስምአቤቱ እግሬን የምታጥበኝ አንተ ነህን? አለው፡፡ እርሱም መልሶእኔ እግርህን ከላጠብሁህ አንተም ከእኔ ጋር ዕድል ፈንታ የለህምአለው፡፡ ይህም ማለትእኔ በአገልጋይ ምሳሌ እግርህን ካላጠብሁ አንተም ከበታችህ ላሉ ራስህን ዝቅ ማድረግ አትችልም፡፡ ራስህን ዝቅ ካላደረግህም የእነርሱ አለቃ መኾን አትችልም፡፡ በሰማያት ባለው መንግሥቴስ ከእኔ ጋር እንዴት አንድ ለመኾን ትችላለህ?››› በማለት ራሱ ትሑት ኾኖ ጴጥሮስን ትሑት ይኾን ዘንድ አጥብቆ እንደ መከረው ይናገራል፡፡

በቅዱሳት መጻሕፍት መነሻነት ዘወትር በግልጥ ሲከናወን የኖረውን፤ አሁንም ባለ ማቋረጥ እየተከናወነ የሚገኘውን፤ ለወደፊትም የሚከናወነውን ቅዱስ የኾነውን የኦርቶዶከሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ትውፊታዊ ሥርዓት ወደ ጐድን በመተው ግምታዊ ልማድን እየተከተለ ‹‹የሐዋርያት ጥምቀት በኅፅበተ እግር ነው፤ እኛ የዳነው በኅፅበተ እግር ነው፤›› የሚሉ ሰዎች አሉ፡፡ ቤተ ክርስቲያናችን ስታጠምቅም፣ ቅብዐ ቅዱስ ስትቀባም ከራስ ጀምራ ነው፡፡ በመጨረሻም በራስ ላይ እፍ ብላ መንፈስ ቅዱስን በማሳደር ነው እንጂ እግርን በማጠብ አጥምቃ አታውቅም፡፡

ይኸውም ከሐዋርያት የተገኘ፤ ከሐዋርያት ሲያያዝ የመጣ ትውፊታዊና ቅዱስ ሥርዓት ነው እንጂ አሁን የተፈጠረ አዲስ ባህል አይደለም፡፡ ስለዚህም የጸሎተ ሐሙስ ኅፅበተ እግር ጥምቀት ሳይኾን ፍጹም ትሕትናን ሠርቶ ለማሠራት ጌታችን የፈጸመው ተግባር ነው፡፡ ይህንም ያለ ጥርጥር ልንቀበለውና ልንተገብረው ይገባል፡፡ ከዚህ ሌላ የሐዋርያት ጥምቀት አንዳንዶቹ ‹‹ተከተሉኝ›› ሲላቸው ነው፤ አንዳንዶቹ ደግሞ በበዓለ ኀምሳ መንፈስ ቅዱስ በወረደላቸው ጊዜ ነው ይላሉ፡፡ ይህ ዅሉ አባባል ግን መጽሐፍ ቅዱሳዊ አይደለም፡፡ በቅዱሳት መጻሕፍት ማስረጃነት ያልተደገፈ ግምታዊ አሳብ ነው እንጂ፡፡

በዕለተ ሐሙስ በተከናወነው ኅፅበተ እግር ሐዋርያት እንደ ተጠመቁ የሚናገሩ ብዙዎች ናቸው፡፡ ነገር ግን ይህ ኅፅበት መድኃኒታችን ክርስቶስ ወሰንና አቻ የሌለው ፍጹም ትሕትናውን የገለጠበት ምሥጢር እንጂ ጥምቀት እንዳልኾነ ብዙ መጻሕፍት ይስማማሉ፡፡ ከዚህ በላይ የተዘረዘሩ መጻሕፍት በሙሉ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የደቀ መዛሙርቱን እግር ማጠቡ ፍጹም ትሕትናውን ለመግለጥ እንደ ኾነ በማያሻማ ኹኔታ አረጋግጠዋል፡፡

ሐዋርያት በዚህ ጊዜ (በኅፅበተ እግር) ተጠመቁ የሚል ግን ማኅበረ ሐዋርያት ከባስልዮስ መጽሐፍ አገኘን ብለው ከጠቀሷት አንዲቷ ጥቅስ በስተቀር ሌላ አልተገኘም፡፡ ከዚህ ላይ ልናስተውለው የሚገባ ቁም ነገር ቅዱስ ጳውሎስ ‹‹ጌታ አንድ ነው፤ ሃይማኖት አንዲት ናት፤ ጥምቀትም አንዲት ናት፤›› (ኤፌ. ፬፥፭) ባለው መሠረት ሠለስቱ ምእት በጉባኤ ኒቅያ በተናገሩት የሃይማኖት ጸሎት ‹‹ኀጢአት በሚሰረይባት በአንዲት ጥምቀት እናምናለን›› (ሃይማኖተ አበው ፲፯፥፲፪) ከማለታቸውም ባሻገር ጥምቀት እንዳይደገም፣ እንዳይከለስ በፍትሕ መንፈሳዊ ከልክለዋል፡፡

ኅፅበተ እግር በቤተ ክርስቲያን

በየዓመቱ የሕማማት ሐሙስ በየአብያተ ክርስቲያናቱ፣ ዘወትር በየቀኑ በየገዳማቱና ትምህርት ቤቶች ለሚስተናገዱ እንግዶች ዅሉ ኅፅበተ እግር ይከናወናል፡፡ ኅፅበት ጥምቀት ነው ከተባለ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስም ሠለስቱ ምእትም ኅፅበተ እግሩ ባለማቋረጥ ዅልጊዜ ሲተገበር (ሲከናወን) ሰዎች ዅሉ በየጊዜው ይጠመቃሉ ማለት ነው፡፡ ይህም ሐዋርያትና ሠለስቱ ምእት ጥምቀት አንድ ጊዜ ብቻ እንዲፈጸም ከወሰኑ በአንድ ምላስ ሁለት ምላስ ያሰኛል፡፡ በአንዲት ቤተ ክርስቲያን የሚጣረሱ ተቃራኒ ሥርዓቶችን ማራመድ አይቻልምና፡፡ ከዚሁ ዅሉ ጋር ደግሞ የእግር መታጠብ ጥምቀት ከኾነ ጌታችን እግራቸውን አጥቦ ‹‹እንዲህ አድርጉ›› ብሎ አዞናልና አዲስ ተጠማቂዎችን አብሶም ሕፃናትን መላ አካላቸውን እያጠመቅን ለምን በቅዝቃዜ እናሰቃያቸዋለን? እግራቸውን ብቻ አጥበን ‹‹ተጠምቃችኋል›› እያልን አናሰናብታቸውም? እስኪ በማስተዋል እንመርምረው፡፡

መድኀኔ ዓለም ክርስቶስ በመዋዕለ ስብከቱ ያከናወናቸው አምላካውያት ተአምራት እንዳይገለጡ ‹‹ይህን ለማንም እንዳትናገሩ፤›› እያለ አጥብቆ ይከለክል ነበር (ማቴ. ፰፥፬፤ ፱፥፴፤ ፲፮፥፳፤ ፲፯፥፲፱)፡፡ ይኸውም ገደቡ ካሣ እስከሚፈጸም እስከ ትንሣኤ ድረስ ኾኖ ከዚያ በኋላ ግን ተአምራቱ መነገር እንዳለበት ‹‹ወልደ እጓለ እመ ሕያው ክርስቶስ ከሙታን እስኪነሣ›› ብሎ ግልጽ አድርጎታል (ማቴ. ፲፯፥፲፱)፡፡ ይህንም ‹‹መከራን ከፊት አስቀምጦ፣ ደስታን፣ ክብርን መናገር ስለሚገባ ነው›› ብለው ሊቃውንቱ አትተውታል፡፡

በዚህ አንጻር ጌታችን እስከ መስቀል ሞት ድረስ ከፊቱ ከባድ መከራ ተደግሶለት እያለ ‹‹በኅፅበተ እግር ሐዋርያትን አጠመቀ፤ ልጅነትን ሰጠ›› ማለት አያስሔድም፡፡ ምክንያቱም አንድ መንግሥት ሕገ መንግሥቱን የሚያውጀው፤ ሹመት፣ ሽልማትን መስጠት የሚጀምረው ጠላቱን ድል አድርጎ መንግሥቱን ካደላደለ በኋላ ነው፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስም ዓለሙን ያዳነውና ልጅነትን የሰጠው ዲያብሎስን በመስቀል ድል ከነሣው በኋላ ነው እንጂ በኅፅበተ እግር አይደለም፡፡

ከኅፅበተ እግር በኋላ ሊይዙት ወደ እርሱ የመጡትን የካህናት አለቆችን፣ የቤተ መቅደስ ሹሞችንና ሽማግሌዎችን ጌታችን እንዲህ ብሏቸዋል፤ ‹‹ሌባን እንደምትይዙ በሰይፍና በጎመድ ልትይዙኝ መጣችሁን? ዘወትር ከእናንተ ጋር በቤተ መቅደስስኖር እጃችሁን እንኳ አልዘረጋችሁብኝም፤ ነገር ግን ጊዜያችሁ ይህ ነው፡፡ የጨለማው አበጋዝም ሥልጣኑ ይህ ነው፤›› (ሉቃ. ፳፪፥፶፪-፶፫)፡፡ ጌታችን የደቀ መዛሙርቱን እግር ካጠበበት እና በአትክልት ቦታ ከጸለየበት ከሐሙስ ማታ እስከ ዓርብ እኩለ ቀን ድረስ ለመግለጽ እጅግ የሚከብድና የሚያሰቅቅ ሥቃይና መከራን በፈቃዱ ተቀብሏል፡፡

ከዚህ አሰቃቂ መከራና ሞት በፊት ቅዱሳን ሐዋርያት ተጠመቁ፤ ልጅነትን አገኙ ማለት ከጋብቻ በፊት ልጅ መውለድ እንደ ማለት ከመኾኑም በላይ የዓለም ቤዛ የኾነውን የጌታችንን ሞት ከንቱ ዋጋ አልባ ማድረግ ነው፡፡ እንዴት ቢባል በክርስቶስ ክርስቲያን የተባለ በሙሉ ከሐዋርያት በተገኘ ልጅነት ነው፤ ቅዱሳን ሐዋርያት ከጌታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ ሞት በፊት በተከናወነ ኅፅበተ እግር ተጠመቁ ከተባለ ሞቱ ምንም ሥራ አልሠራም ማለት ነውና፡፡ ወገኔ ሆይ! ከዚህ በላይ እንደ ተገለጠው የዳንኸውና ልጅነትን ያገኘኸው በክርስቶስ ሞትና ደም እንጂ በእግር መታጠብ እንዳልኾነ ልታስተውል ይገባል፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር፡፡

ከማግሥተ ሆሣዕና እስከ ዕለተ ረቡዕ

መጋቢት ፳፭ ቀን ፳፻፲ ዓ.ም

ከሰሙነ ሕማማት ዕለታት ውስጥ ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በሦስቱ ዕለታት (በሰኞ፣ ማክሰኞ እና ረቡዕ) ያከናወናቸው ተግባራት የሚከተሉት ናቸው፤

ሰኞ

ጌታችን አምላካችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በሆሣዕና ማግሥት (ሰኞ ዕለት) ከቢታንያ ወደ ኢየሩሳሌም ሲገባ ሁለት ተግባራትን አከናውኗል፤ አንደኛ ከቅጠል በስተቀር ፍሬ ያልተገኘባትን ዕፀ በለስ ረግሟል፡፡ ሁለተኛ ወደ ቤተ መቅደስ ገብቶ የሚሸጡትንና የሚለውጡትን አስወጥቷል (ማቴ. ፳፩፥፲፪-፲፯፤ ማር. ፲፩፥፲፯፤ ሉቃ. ፲፱፥፵፭-፵፮)፡፡ በቅዱስ ማቴዎስ አገላለጥ ‹‹በማግሥቱ ተራበ›› የሚል ኃይለ ቃል እንመለከታለን፡፡ ነቢዩ ኢሳይያስ ‹‹እግዚአብሔር ለዘለዓለም አይራብም፤ አይጠማም፤ አይደክምም፤›› በማለት ተናግሯል (ኢሳ. ፵፮፥፳፭)፡፡ በቅዱስ ወንጌል በመጀመሪያ ቃል እንደ ነበረ፤ ያ ቃል ቀዳማዊ እንደ ኾነ፤ ቃልም በእግዚአብሔር ዘንድ እንደ ነበረ፤ ያም ቃል እግዚአብሔር እንደ ኾነ ተጽፏል (ዮሐ. ፩፥፩-፪)፡፡ ጌታችንም በመዋዕለ ትምህርቱ ‹‹የእኔስ መብል የላከኝን የአባቴን ፈቃድ አደርግ ዘንድ፤ ሥራውንም እንፈጽም ዘንድ ነው፤›› በማለት አስተምሯል (ዮሐ. ፬፥፴፬)፡፡ ታዲያ ጌታችን ለምን ተራበ?

ሰማያውያን መላእክት እንዳይራቡ አድርጎ የፈጠረ፤ እስራኤልን ገበሬ በማያርስበት፣ ዘር በሌለበት፣ ዝናብ በማይጥልበት ምድረ በዳ የመገበ፤ በአምስት አንጀራና በሁለት ዓሣ ከአምስት ሺሕ የሚበልጡ ሰዎችን የመገበ ጌታ ‹‹ተራበ›› ተብሎ ሲነገር እጅግ ይደንቃል፡፡ በእርግጥ ኢየሱስ ክርስቶስ ፍጹም አምላክ ፍጹም ሰው በመኾኑ አልተራበም አንልም፡፡ የጌታችን ረኃብ የድህነት (የማጣት) አይደለም፡፡ የክርስቶስ ረኃቡ የበለስ ፍሬ ሳይኾን የሃይማኖትና የመልካም ሥነ ምግባርን ፍሬ የሻ መኾኑን ለማጠየቅ ‹‹ተራበ›› ተባለ፡፡ ‹‹በለስ ብሂል ቤተ እስራኤል እሙንቱ፤ በለስ የተባሉ እስራኤላውያን ናቸው›› እንዲል፡፡ ጌታችን የፈለገውን ባለማግኘቱ ጉባኤ አይሁድን ረግሟል፡፡ በአይሁድ ጉባኤ የነገሠውን ኃጢአት፤ በበለስ አንጻር መርገሙን ታላቁ ሊቅ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ‹‹በአንጻረ በለስ ረገማት ለኃጢአት፤ በበለስ አንጻር ኃጢአትን ረገማት›› በማለት ያስዳል፡፡

እስራኤልም በአንድ ወገን የተጠበቀባቸውን ፍሬ ባለ ማፍራታቸው ተረግመዋል፡፡ ሊቁ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ እስራኤል ከፍቅር ይልቅ ርግማን እንዳገኛቸው፤ አሕዛብ ደግሞ የቃሉን ትምህርት ሰምተው የእጁን ተአምራት አይተው እንዳመኑበትና የእግዚአብሔር የጸጋ ልጁ ለመኾን እንደ በቁ ሲመሰክር እንዲህ ይላል፤ ‹‹አሕዛብ አስተጋብኡ ጽጌሬዳ በኂሩቱ ወሶኩሰ ተርፈ ኀበ አይሁድ ዘውእቱ ሕፀተ ሃይማኖት፤ አሕዛብ በእግዚአብሔር ቸርነትአበባ ሰበሰቡ፤ በአይሁድ ዘንድ ግን እሾኹ ተረፈ፡፡ ይኸውም የሃይማኖት ጉድለት ነው፤›› ብሎ ተርጕሞታል፡፡ እሾኽ የእርግማን፤ አበባ የእግዚአብሔር ጸጋ ልጅነት ምሳሌ ነው፡፡

የእግዚአብሔር ቤተሰቦች! ዛሬ ጌታችን ወደ መቅደስ ሕይወታችን ቢመጣ ምን ያገኝ ይኾን? ፍሬ ወይስ ቅጠል? የእግዚአብሔር ቃል ‹‹ለንስሐ የሚገባ ፍሬአድርጉ፤›› ይለናልና፡፡ ስለዚህ እግዚአብሔር ከእኛ የሚፈልገውን የመንፈስ ቅዱስ ፍሬ ማፍራት ይጠበቅብናል (ማቴ. ፫፥፰፤ ገላ. ፭፥፳፪)፡፡ ጌታችን በዳግም ልደት ሲመጣ ከሰው ልጅ ሃይማኖት መገኘቱ አጠራጣሪ እንደ ኾነ ተናግሯል፡፡ ‹‹የሰው ልጅ ወደዚህ ዓለም ሲመጣ ሃይማኖት ያገኝ ይኾንን?›› ሕይወታችንን በአምላካዊ ሥልጣኑ የቃኘ አምላክ ለፍርድ በመጣ ጊዜ የእምነት ፍሬ አፍርተን እንዲያገኘንና ዘላለማዊ መንግሥቱን እንዲያወርሰን የጽድቅ ሥራ ለመሥራት እንትጋ፡፡

ማክሰኞ

በማቴዎስ ወንጌል ፳፩፥፳፰፤ ፳፭፥፵፮፤ በማርቆስ ፲፪፥፲፪፤ ፲፫፥፴፯፤ በሉቃስ ፳፥፱፤ ፳፩፥፴፰ የሚገኙ የመጽሐፍ ቅዱስ ኃይ ቃላት ማክሰኞ ዕለት የሚነገሩ ትምህርቶችን ይዘዋል፡፡ በዚህ ዕለት ጌታችን በቤተ መቅደስ ረጅም ትምህርት ስላስተማረ ዕለቱ ‹‹የትምህርት ቀን›› ይባላል፡፡ ክርስቲያን የኾነ ዅሉ ከሥጋዊ ነገር ርቆ በዚህ ሰሞን የሃይማኖት ትምህርት ሲማር፣ ሲጠይቅ መሰንበቱ መጽሐፋዊ ሥርዓት ነው፡፡ በዚህ ዕለት ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስለ ሥልጣኑ ተጠይቋል፡፡ ጠያቂዎቹ የካህናት አለቆችና የሕዝብ አለቆች ሲኾኑ፣ ጥያቄውም፡- ‹‹በማን ሥልጣን እነዚህን ታደርጋለህ? ይህንስ ሥልጣን የሰጠህ ማነው?›› የሚል ነበር፡፡

ይህ ጥያቄ ጌታችን ሰኞ ዕለት ሁለት ነገሮችን ማከናወኑን ተከትሎ የተነሣ ጥያቄ ነው፡፡ ይኸውም ጌታችን ሲያደርጋቸው የነበሩ ተአምራትና ድንቅ ድንቅ ሥራዎች የካህናት አለቆችን ስላስቀኗቸው ጌታችንን ከሮማ መንግሥት ባለ ሥልጣናት ጋር ለማጋጨት የቀየሱት ስልት ነው፡፡ ጌታችን በቤተ መቅደስ የነበሩትን ነጋዴዎችን አባሯል፤ መደባቸውን ገለባብጧል፡፡ ነጋዴን ማባረርና መደብን ማስለቀቅ መንግሥታዊ ሥራ ነው፡፡ ጌታችን ‹‹በራሴ ሥልጣን›› ቢላቸው ‹‹ፀረ መንግሥት አቋም አለው›› በማለት ከሮማ መንግሥት ዘንድ ለማሳጣት ነበር ዕቅዳቸው፡፡

ጌታችን ግን የፈሪሳውያንን ጠማማ አሳብ ስለሚያውቅ ‹‹የዮሐንስ ጥምቀት ከየት ነው? ከሰማይ ነው ወይስ ከምድር?›› ሲል ሌላ ጥያቄ ጠይቋቸዋል፡፡ ጌታችን ፈሪሳውያን ላቀረቡለት ጥያቄ ቀጥተኛ ምላሽ አልሰጠም፡፡ ምክንያቱም ጥያቄው ለከሳሾቹ ዓላማ መሳካት አመቺ ኹኔታን ስለሚፈጥር ጥያቄውን በጥያቄ መልሶላቸዋል፡፡ እነርሱም ‹‹ከሰማይ ነው›› ቢሉት ‹‹ለምን አላመናችሁበትም?›› እንዳይላቸው፤ ‹‹ከሰው ነው›› ቢሉት ደግሞ ሕዝቡ ዮሐንስን እንደ አባት ይፈሩት፣ እንደ መምህር ያከብሩት ነበርና ሕዝቡ እንዳይጣሏቸው ስለ ፈሩ ‹‹ከወዴት እንደ ኾነ አናውቅም›› ብለው መለሱለት፡፡ እርሱም ‹‹እኔም በማን ሥልጣን እነዚህን እንደማደርግ አልነግራችሁም›› አላቸው፡፡

አይሁድ ይህን ጥያቄ መጠየቃቸው እርሱ የሚያደርጋቸውን ተግባራት ዅሉ በራሱ ሥልጣን እንዲያደርግ አጥተውት አልነበረም፤ ልቡናቸው በክፋትና በጥርጥር ስለ ተሞላ ነበር እንጂ፡፡ ዛሬም ቢኾን መልካም ሥራን በሠራን ጊዜ ከልዩ ልዩ ወገኖች የሚመጡ ፈተናዎች ለመልካም ሥራችን እንቅፋት ሊኾኑ እንደሚችሉ መገንዘብ አለብን፡፡ ብዙ ወገኖች ‹‹ለቅን አሳባችን ለምን ሰዎች ክፉ ነገር ይመልሱልናል?›› በማለት ሲጠይቁ ይሰማል፡፡ ለቅን አሳባችን ከዓለም ዘንድ ተቃራኒ ነገር እንደሚጠብቀን ለመረዳት ‹‹ዓለም የሚወደው የገዛ ወገኑን ነው›› የሚለውን የጌታችንን ትምህርት ልብ ይሏል፡፡ በዘመናችን አሳልፈው ሊሰጡን የሚፈልጉ ሰዎች ፈታኝ ጥያቄ እንደሚያቀርቡልንም ከወዲሁ ልንገነዘብ ይገባል፡፡

ረቡዕ

በቅዱስ ማቴዎስና በቅዱስ ማርቆስ ወንጌላት እንደ ተገለጸው በዕለተ ረቡዕ የሚከተሉት ሦስት ተግባራት ተፈጽመዋል፤

  • አንደኛ የካህናት አለቆች፣ የሕዝብ ሽማግሌዎችና ጸሐፍት ፈሪሳውያን በጌታችን ላይ ተማክረዋል፤
  • ሁለተኛ ጌታችን በስምዖን ዘለምጽ ቤት ሳለ አንዲት የተጸጸተች ሴት ሽቱ ቀብታዋለች፡፡
  • ሦስተኛ ከዳተኛው ይሁዳ ጌታችንን አሳልፎ ለመስጠት ከጸሐፍት ፈሪሳውያንና ከካህናት አለቆች ዘንድ ሠላሳ ብር ለመቀበል ተስማምቷል፡፡

የካህናት አለቆችና የሕዝብ ሹማምት በጌታችን ላይ ይሙት በቃ ለመወሰን የሰበሰቡት ሸንጐ ‹‹ሲኒሃ ድርየም›› ይባላል፡፡ በዚህ ሸንጐ ላይ በአብዛኛው የተሰየሙት ሰዱቃውያን ሲኾኑ ሌሎቹ ደግሞ ጸሐፍት ፈሪሳውያን ነበሩ፡፡ ሸንጐው በአጠቃላይ ሰባ ሁለት አባላት የነበሩት ሲኾን የሚመራውም በሊቀ ካህናቱ በቀያፋ ነበር፡፡ በዕለቱ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን እንዴት እንደሚገድሉት አይሁድ በዚህ ሸንጎ መክረዋል፡፡ ከዳተኛው ይሁዳም ጸሐፍት ፈሪሳውያንና የካህናት አለቆች በጌታን ላይ የነበራቸውን ጥላቻ ያውቅ ስለ ነበር ‹‹ምን ልትሰጡኝ ትወዳላችሁ? እኔም አሳልፌ እሰጣችኋለሁ፤›› በማለት ጌታችን አሳልፎ ሊሰጣቸው እንደሚችል ተስማምቷል፡፡

ጌታችን ያስተምር በነበረበት ወቅት የአስቆሮቱ ይሁዳ ከምእመናን ለሚገባው ገንዘብ ሰብሳቢ (ዐቃቤ ንዋይ) ነበር፡፡ ከሚሰበሰበው ሙዳየ ምጽዋት ለግል ጥቅሙ እየቀረጠ የማስቀረት የእጅ አመል ነበረበት፡፡ ይሁዳ ፍቅረ ንዋይ እንደሚያጠቃው ድብቅ አመሉ ጎልቶ የወጣው ጌታችን በለምጻሙ በስምዖን ቤት ሳለ አንዲት ሴት ዋጋው ውድ የኾነ ሽቱ በቀባችው ጊዜ ነው፡፡ በዚያች ዕለት ይሁዳ የተቃውሞ ድምፅ ካሰሙት አንዱ ነበር፡፡ ‹‹ይህ ሽቱ ተሽጦ ለድሆች ቢሰጥ መልካም ነበር፤›› በማለት ያቀረበው አሳብ ‹‹አዛኝ ቅቤ አንጓች›› እንደሚባለው ነበር፡፡ ይሁዳ፣ ሽቱ ሲሸጥ የሚያገኘው ጥቅም ነበረ፤ ሽቶው በጌታችን እግር ሥር ከፈሰሰ ለእርሱ የሚተርፈው የለም፡፡ ተቆርቋሪ መስሎ ያቀረበው አሳብ ተቀባይነት በማጣቱም በቀጥታ ከካህናት አለቆች ዘንድ ሔዶ ጌታንን በሠላሳ ብር ለመሸጥ ተዋዋለ (ማቴ. ፳፮፥፫-፲፮፤ ማር. ፲፬፥፩-፲፩፤ ሉቃ. ፳፪፥፩፮)፡፡

የአስቆሮቱ ይሁዳ እንደ ሌሎች ሐዋርያት ከጌታችን ተምሯል፡፡ በረከተ ኅብስቱን ተመግቧል፡፡ ልዩ ልዩ ተአምራት በጌታችን እጅ ሲደረጉ ዅሉ ተመልክቷል፡፡ ጌታችንም ከሌሎች ሐዋርያት ሳይለየው እግሩን አጥቦታል፡፡ ከዳተኛው ይሁዳ ግን ለሐዋርያነት የጠራውን፣ ተንበርክኮ እግሩን ያጠበውን ጌታ ለሞት አሳልፎ ሰጥቷል፡፡ ‹‹የሰው ልጅስ ስለ እርሱ እንደ ተጻፈ ይሔዳል፤ ነገር ግን የሰው ልጅ አልፎ ለሚሰጥበት ለዚያ ሰው ወዮለት!›› ተብሎ እንደ ተጻፈ (ማቴ. ፳፮፥፳፬)፡፡ ሌሎች ሐዋርያት ከጌታችን ዘንድ ፍቅሩን ገንዘብ ሲያደርጉ ይሁዳ ግን እርግማንን ነው ያተረፈው፡፡ ‹‹ገንዘብ የኃጢአት ሥር ነው፤›› ተብሎ አንደ ተነገረ የኃጢአት ሥር የተባለው ገንዘብ የክርስቲያኖችን ሕይወት ያዳክማልና ምእመናን እንደ ይሁዳ በገንዘብ ፍቅር እንዳንወድቅ መጠንቀቅ ያስፈልጋል፡፡ ሰው ‹‹ይህን ዓለም ቢያተርፍ ነፍሱን ከጐዳ ምን ይጠቅመዋል?›› ተብሎ የተነገረውን ቃል ልብ ማለት ጠቃሚ ነው፡፡

ክርስቲያን ነን በማለት የክርስትናውን ስም በመያዝ እምነታቸውን፣ የቆሙበትን ዓላማ በመገንዘብ የሚለውጡ ሰዎች ዛሬም እንደ ይሁዳ ጌታችንን እየሸጡት እንደ ኾነ ሊገነዘቡት ይገባል፡፡ ለድሆች መመጽወት ክርስቲያናዊ ግዴታ ነው፡፡ ዳሩ ግን በድሆች ስም የሰውን ገንዘብ ለግል ጥቅም ማዋል እጅግ የከፋ ኃጢአት ነው፡፡ እንደዚህ ዓይነት ሰዎች ለገንዘብ ብለው ድሆችን ለረኃብ ለችግር ባልንጀራቸውን ለመከራ እና ለሞት አሳልፈው ሲሰጡ ምንም አይጸጽታቸውም፡፡ እውነተኛ ክርስቲያኖች ግን ሕይወታችንን ለገንዘብ ፍቅር ሳይኾን ለእምነታችንና ለባልንጀራችን አሳልፈን መስጠት ይኖርብናል፡፡ በፍቅረ ንዋይ ተጠምደን ሰዎችን አሳልፎ በመስጠት ለአይሁዳዊ ሸንጐ ምቹ ኾነን መገኘት እንደሌለብን መገንዘብ አለብን፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር፡፡

ምንጭ፡- ስምዐ ተዋሕዶ – የሰሙነ ሕማማት ልዩ ዕትም፣ ማኅበረ ቅዱሳን፤ ከሚያዝያ ፩ – ፲፭ ቀን ፳፻፬ ዓ.ም፣ ገጽ ፬ – ፮፡፡

 ሰሙነ ሕማማት (ከዕለተ ሰኑይ እስከ ቀዳሚት ሰንበት)

በመምህር ቸርነት አበበ

መጋቢት ፳፬ ቀን ፳፻፲ ዓ.ም

መግቢያ

ከአባታችን አዳም በደል ወይም ስሕተት በኋላ በሕማማት፣ በደዌያት፣ በመቅሠፍታት፣ ወዘተ በብዙ መከራ የሰው ልጅ ሊኖርባቸው ግድ የኾነባቸው ዘመናት ጥቂቶች አልነበሩም፡፡ የሰው ልጅ ቢያጠፋ፣ ቢበድል፣ ከሕገ እግዚአብሔር ቢወጣ እንኳን የዋህ፣ ታጋሽ፣ ቸር፣ አዛኝ የኾነው አምላክ የጠፋውን ሊፈልግ፣ የተራበውን ሊያጠግብ የታረዘውን ሊያለብስ፣ ፍቅር ላጣው ፍጹም ፍቅር ሊለግስ፣ ሰላም ለሌለው ፍጹም ሰላም ሊሰጥ፣ ተስፋ ለሌለው ተስፋ ሊያጐናጽፍ ከሰማይ ወረደ፤ ከቅድስት ድንግል ማርያም ተወለደ፤ በገዳመ ቆሮንቶስ ዐርባ ቀንና ሌሊት ጾመ፡፡ በጾሙም የኀጢአት ሥሮች ወይም ራሶች የተባሉትን ስስትን፣ ትዕቢትንና ፍቅረ ንዋይን ድል አደረገልን፡፡ እኛ እርሱ የጾመውን ጾም እንድናከብር እንድንጾም ምሳሌ ኾነን፡፡ ዲያብሎስን ድል አድርጐ ድል እንድንነሣው ኃይልና ምሳሌ ኾነን፡፡

ሰሙነ ሕማማት ምንድን ነው?

‹ሰሙን› – ‹‹ሰመነ ስምንት (ሳምንት) አደረገ›› ማለት ነው፡፡ ይኸውም ከዕለተ ሆሣዕና ሠርክ እስከ ትንሣኤ ሌሊት ያለውን ጊዜ ወይም ቀናት የሚያመለክት ነው፡፡ ‹ሕማም (ሕማማት)› – ‹ሐመ ታመመ› ከሚለው የግእዝ ግስ የተገኘ ሲኾን ይህም የሰውን ዘር ዂሉ ከዲያብሎስ ባርነት ነጻ ለማውጣት ጌታችን አምላካችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በፈቃዱ የተቀበላቸውን ጸዋትወ መከራዎች የሚያሳስብ ነው፡፡ ዕለታቱ የዓመተ ኵነኔ ወይም የዓመተ ፍዳ ምሳሌዎች ናቸው፡፡ ክርስቲያኖች የክርስቶስን ውለታ እያሰቡ እጅግ የሚያዝኑበት፣ የሚያለቅሱበት፣ የሚሰግዱበት ቤት ንብረታቸውን ትተው ከሌላው ቀናትና ጊዜያት በተለየ መልኩ ቤተ ክርስቲያናቸውን የሚማጸኑበት፤ ጧት ማታ ደጅ የሚጠኑበት፤ ኀጢአታቸውን በቤተ ክርስቲያን አደባባይ ለካህኑ የሚናዘዙበት በዓመት አንድ ጊዜ ብቻ የሚገኝ ሳምንት ነው፡፡

በዚህ ሳምንት ብዙ አዝማደ መባልዕት አይበሉም፤ ይልቁን በመራብ በመጠማት በመውጣት በመውረድ በመስገድ በመጸለይ በመጾም በየሰዓቱ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስን ጸዋትወ መከራዎች በማሰብ አብዝቶ ይሰገዳል፡፡ መከራውን፣ ሕማሙን፣ ድካሙን የሚያስታውሱ ከቅዱሳት መጻሕፍት ኢሳይያስ፣ ኤርምያስ መዝሙረ ዳዊት፣ ግብረ ሕማማት ወዘተ በየሰዓቱ ይነበባል፡፡ መስቀል መሳለም የለም፡፡ ካህናትም ‹‹እግዚአብሔር ይፍታህ›› አይሉም፡፡ ሥርዓተ ፍትሐት አይፈጸምም፡፡ ይኸውም ይህ ሳምንት ከሞት ወደ ሕይወት የተሸጋገርንበት ከጨለማ ወደ ብርሃን የተጓዝንበት የመሸጋገሪያ ወቅት ምሳሌ በመኾኑ ነው፡፡ በዕለተ ምጽአት መላእክት የመለከት ድምፅ በማሰማት የዳግም ምጽአትን ዕለት ለማሳሰብ ምእመናን ጥሪውን ሰምተው ለዚህም አስቀድመው ተዘጋጅተው የበዓሉ ታዳሚዎች መኾናቸውን በማጠየቅ በዚህ ሳምንት ዲያቆኑ ቃጭል እየመታ በየሰዓቱ ምእመናኑን ያሳስባል፡፡

በሰሙነ ሕማማት የሚገኙ ዕለታትና ስያሜዎቻቸው

ዕለተ ሰኑይ (ሰኞ)

ይህ ዕለት አንጾሖተ ቤተ መቅደስ (የቤተ መቅደስ መንጻት) እና መርገመ በለስ የተፈጸመበት ዕለት ነው (ማቴ. ፳፩፥፲፰-፳፪፤ ማር. ፲፩፥፲፩፤ ሉቃ. ፲፫፥፮-፱)፡፡ ወንጌላዊው ቅዱስ ሉቃስ «ወመሰለ ሎሙ ወይቤሎሙ አሐዱ ብእሲ በለሰ ቦቱ ውስተ ዐፀደ ወይኑ ወየሐውር ይንሣእ ፍሬሃ ወኢይረክብ …፤ ይህንም ምሳሌ አለ፤ ለአንድ ሰው በወይኑ አትክልት የተተከለች በለስ ነበረችው፡፡ ፍሬም ሊፈልግባት ወጥቶ ምንም አላገኘም …›› በማለት እንደ ጠቀሰው በበለስ ስለ ተመሰለ የሰው ልጅ ሕይወት በማሰብ እንዲመለስ ንስሐ እንዲገባ በሕይወትም እንዲኖር እግዚአብሔር ኢየሱስ ክርስቶስ ማሳሰቡን ያጠይቃል፡፡ ንስሐ አልገባም አልመለስም ያለም በለሷ እንደ ጠወለገችና እንደ ተቈረጠች ዂሉ ፍሬ ባለማፍራታቸው እንደሚቈረጡ እንደዚሁም ወደ እሳት እንደሚጣሉ መጽሐፍ ቅዱስ በግልጽ ያስረዳል፡፡ በለስ የተባለች ቤተ እስራኤል ፍሬ የተባለ ደግሞ ሃይማኖትና ምግባር ነው፡፡ ዂላችን ቤተ እስራኤላውያን ፍሬ ሃይማኖት ወምግባር አስተባብረን ይዘን መገኘት ይገባናል፡፡ ፍሬ አልባ እንዳንኾን ጌታ ሲመጣም እንዳናፍር የመጽሐፉን ቃል ልንጠብቅና ልንፈጽም ይገባናል፡፡ በዚህ የሕማማት የመጀመሪያ ቀን ዕለተ ሰኑይ የምናስበው የምንዘክረው የሰው ልጅ ሕይወት በከንቱ በቸልተኝነት እንዳይደክም፣ እንዳይጠወለግ፣ እንዳይደርቅ፣ ወደ እሳትም እንዳይጣል ማድረግ ይገባናል፡፡

ዕለተ ሠሉስ (ማክሰኞ)

ይህ ዕለት ጌታችን ሰኞ በተናገረውና ባደረገው ተአምር ላይ አይሁድ ጥያቄ ያቀረቡበት እርሱም መልስ በመስጠት ያስተማረበት ቀን ነው፡፡ በዚህም ምክንያት ‹‹የጥያቄ እና የትምህርት ቀን›› በመባል ይታወቃል፡፡ ጥያቄውም ጌታ ባደረገው አንጽሖተ ቤተ መቅደስ ምክንያት ለጸሐፍትና ፈሪሳውያን ይኸውም ትምህርት ማስተማር፣ ተአምራት ማድረግ፣ ገበያ መፍታትን ‹‹በማን ሥልጣን ታደርጋለህ? ይህንስ ሥልጣን ማን ሰጠህ?›› የሚል ነበር (ማቴ. ፳፩፥፳፫-፳፯)፡፡ ቅዱስ ማቴዎስ እንደ ተናገረው ጌታችንም ‹‹እውነት እላችኋለሁ፤ ቀራጮችና ጋለሞቶች ወደ እግዚአብሔር መንግሥት በመግባት ይቀድሙአችኋል›› በማለት አይሁድ በሚከተሉት ልማድ መንግሥተ ሰማያትን መውረስ እንደማይችሉ አስተምሯል (ማቴ. ፳፩፥፳፰)፡፡

ዕለተ ረቡዕ

ይህ ዕለት ደግሞ የአይሁድ ሊቃነ ካህናትና ጸሐፍት ጌታን እንዴት መያዝ እንደሚችሉ ምክር የጀመሩበት ቀን ነው፡፡ በዚህም ምክንያት ዕለቱ ‹‹የምክር ቀን›› በመባል ይጠራል፡፡

ዕለተ ሐሙስ

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዚህ ዕለት ፍጹም ሰው ፍጹም አምላክ መኾኑን ለመግለጥ እና ለአርአያነት ጸሐፍት ፈሪሳውያን የአይሁድ ካህናት መጥተው እስኪይዙት ድረስ ሲጸልይ በማደሩ ምክንያት ጸሎተ ሐሙስ በመባል ይታወቃል፡፡ ትሕትና ፍቅር መታዘዝ እንዲሁም የአገልግሎትን ትርጉም ለማስረዳትና ለማስገንዘብ የደቀ መዛሙርቱን እግር በማጠቡ ሕጽበተ ሐሙስ በመባልም እንደሚጠራ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን ይናገራሉ፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ዮሐንስም ‹‹እግራቸውንም አጥቦ ልብሱንም አንሥቶ ዳግመኛ ተቀመጠ፡፡ እንዲህም አላቸው፤ ያደረግሁላችሁን ታስተውሉታላችሁን? … እንግዲህ እኔ ጌታና መምህር ስኾን እግራችሁን ካጠብሁ እናንተ ደግሞ እርስ በእርሳችሁ ትተጣጠቡ ዘንድ ይገባችኋል›› ሲል ተናግሯል (ዮሐ. ፲፫፥፲፪-፳)፡፡

‹‹ይህ ስለ እናንተ በመስቀል ላይ የሚቈረሰው ሥጋዬ ነው እንካችሁ ብሉ፤ ይህ ስለ እናንተ የሚፈስ ደሜ ነው ከእርሱ ጠጡ›› በማለት ምሥጢረ ቍርባንን የመሠረተበት ወይም ራሱ ምስጢረ ቍርባንን የጀመረበት ቀን በመኾኑ ‹‹የምሥጢር ቀን›› ተብሎ ይጠራል፡፡ ይኸውም የሰው ልጆች ሥጋውንና ደሙን ተቀብለን ከእርሱ ጋር አንድነትና ኅብረት እንዲኖረን ጥንተ ጠላት ዲለብሎስንም ፍጹም ድል ነሥተን ሰማያዊት ርስት መንግሥተ ሰማያትን እንድንወርስ ለማስቻል ነው (ማቴ. ፳፮፥፳፮-፳፱)፡፡ አይሁድ ጌታችንን ለመያዝ በእነርሱ ጥበብና ፍላጐት ቀስ ብለው መጥተው የያዙበት ቀን ስለ ኾነ በዚህ ዕለት በለሆሳስ (ብዙ የድምፅ ጩኸት ሳይሰማ) የቅዳሴ ሥርዓት ይፈጸማል፡፡ ስለ ኾነም መላው ሕዝበ ክርስቲያን በዚህ የኅፅበት፣ የምሥጢር፣ የጸሎት ቀን በተባለው በዚህ ዕለት በንስሓ ታጥበው ሥጋ ወደሙ እንዲቀበሉ ቤተ ክርስቲያን በአጽንዖት ታስተምራለች፡፡

ዕለተ ዐርብ

ሐዋርያው ቅዱስ ጳዉሎስ ‹‹አውቀውስ ቢኾን የክብርን ጌታ ባልሰቀሉት›› (፩ኛ ቆሮ. ፩፥፲፰)፡፡ እንዳለ ይህ ዕለት የአይሁድ ካህናት ያለ በደል ያለ ጥፋት ንጹሕና ጻድቅ የኾነውን ጌታ የሰቀሉበት ዕለት ነው፡፡ ዕለቱም ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የዓለም ዂሉ መድኀኒት ለአዳምና ለልጆቹ ሲል በመልዕልተ መስቀል በቀራንዮ አደባባይ ተሰቅሎ መዋሉን የምናስብበት ታላቅ ቀን ነው (ማቴ. ፳፯፥፴፭-፸፭)፡፡ የሰው ልጆች በዘር ኀጢአት (ቁራኝነት) ይኖሩበት የነበረው የጨለማ ሕይወት ያከተመበት ፍጹም ድኅነት ያገኙባት ታላቅ ዕለት ናት፡፡ ክርስቲያኖች ዂልጊዜም ዕለተ ዓርብ ሲመጣ ሕማሙን ስቅለቱን ሞቱን የምናስብበት ጊዜ ነው፡፡ በሮማውያን ሕግና ሥርዓት መስቀል የወንጀለኞች መቅጫ ምልክት የሕይወት መቅጫ ዓርማ ኾኖ ሳለ ለእኛ የዲያብሎስ ድል መንሻ ስላደረገው በስቅለቱና በሞቱም ሕይወትን አገኘን፡፡ በዚህም ምክንያት ‹‹መልካሙ ዓርብ›› በመባል እንደሚታወቅ የቤተ ክርስቲያን አባቶች ያትታሉ፡፡

ዕለተ ቀዳሚት ሥዑር

ዕለተ ቀዳሚት እግዚአብሔር የሚታዩትንና የማይታዩትን፣ በእግር የሚሔዱትን እና በክንፍ የሚበሩትን በባሕር የሚዋኙትን እንስሳትን በመጨረሻም ሰውን በአርአያውና በአምሳሉ ፈጥሮ ያረፈባት ዕለት ናት፡፡ ይህች የመጀመሪያው ቅዳሜ ለእግዚአብሔር የዕረፍት ዕለት ናት፡፡ እግዚአብሔርን ሥነ ፍጥረት ፈጥሮ ስላረፈባት ‹‹ሰንበት ዐባይ›› (ታላቋ ሰንበት) ትባላለች፡፡ ታላቋን ሰንበት እስራኤላውያን እንዲያከብሯት ታዟል (ዘፍ. ፩፥፫)፡፡ ዕለተ ቀዳሚት በዘመነ ሐዲስም የተለየ የደኅነት ሥራ ተከናውኖባታል፡፡ ጥንት ሥነ ፈጥረትን በመፍጠር ዕረፍት እንደ ተደረገባት ዂሉ የፍጥረት ቁንጮ የኾነውን አዳምን ለማዳን ሕማምና ሞት የተቀበለው ቸሩ አምላክ በመቃብር አርፎባታል (ማቴ. ፳፯፥፷፩)፡፡

በዚህች ዕለት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በከርሰ መቃብር ዐርፎ የዋለባት ዕለት በመሆኗ ‹‹ቀዳሚት ሥዑር›› ትሰኛለች፡፡ ‹‹ቀዳሚት ሥዑር›› የተባለችበት ምክንያትም በዓመት አንድ ቀን ስለ ምትጾም ነው፡፡ ይኸውም ቅድስት ድንግል ማርያም እና ወዳጆቹ ቅዱሳን ሐዋርያት ጌታችን ተላልፎ ከተሰጠበት ዕለት አንሥተው ብርሃነ ትንሣኤዉን እስኪያዩ ድረስ እኽል ውኃ በአፋቸው አልዞረም፡፡ ይመኩበትና ተስፋ ያደርጉት የነበረ አምላካቸው በመቃብር ስላረፈ ዕለቷን ሞቱን በማሰብ ትንሣኤውን በመናፈቅ በጾም አክብረዋታል፡፡ ከቅዱሳን ሐዋርያት በቅብብሎሽ በመጣው ትውፊት መሠረት ቅዱሳን ሐዋርያት በማዘን፣ በመጾምና በመጸለይ ዕለቷን እንዳከበሯት የተዋሕዶ ልጆችም የተቻላቸው ከዓርብ ጀምረው ያከፍላሉ (ይጾማሉ)፤ ለሁለት ቀን እኽል ውኃ ሳይቀምሱ ያድራሉ፡፡ ያልተቻላቸው ደግሞ ዓርብ ማታ በልተው ቅዳሜን በመጾም በዓለ ትንሣኤን ያከብራሉ፡፡

በዚህ ዕለት ከሰኞ ከሆሣዕና ማግሥት ጀምረው እስከ ዓርብ ድረስ በስግደት እና በጾም ያሳለፉ ምእመናን በዕለተ ቀዳሚት በቅፅረ ቤተ ክርስቲያን ይሰበሰባሉ፡፡ የጠዋቱ ጸሎት ሲፈጸም ካህናቱ ‹‹ገብረ ሰላመ በመስቀሉ፤ በመስቀሉ ሰላምን መሠረተ›› እያሉ በቤተ ክርስቲያን ለተሰበሰቡት ምእመናን ቄጠማ ያድላሉ፡፡ ይኸውም የምሥራች ምልክት ነው፡፡ ምሥጢሩም በኖኅ ዘመን ከተፈጸመው ታሪክ ጋር የተያያዘ ነው፡፡ ቅዱስ መጽሐፍ እንደሚነግረን በጻድቁ ኖኅ ዘመን የነበሩ ሕዝቦች ከሕገ እግዚአብሔር ውጪ ኾነው እጅግ የሚያሳዝን ኀጢአት በሠሩ ጊዜ በንፍር ውኃ ተጥለቅልቀዋል፡፡ በወቅቱ ጻድቁ ኖኅ ወደ መርከብ ይዞአቸው ከገባው እንስሳት መካከል የውኃውን መጕደል ለመረዳት ርግብን በመርከብ መስኮት አሾልኮ ይለቃታል፤ እርሷም ቄጠማ በአፍዋ ይዛ ትመልሳለች (ዘፍ. ፱፥፩-፳፱)፡፡

ኖኅም በዚህ ቄጠማ የውኃውን መድረቅ ተረድቶ ተደስቷል፡፡ ቄጠማ፣ ለጥፋት ውኃ መድረቅ የምሥራች መንገሪያ እንደ ኾነ አሁንም በክርስቶስ ሞት ሞተ ነፍስ ከሰው ልጆች ተወገደ ስትል ቤተ ክርስቲያን ለልጆቿ ቄጠማ ታድላለች፡፡ ምእመናንም የምሥራች ተምሳሌት የኾነዉን ቄጠማ በግንባራቸው ያስሩታል፡፡ የክርስቶስ ተከታዮች ዂሉ ከጨለማ ወደ ብርሃን፣ ከሚያቃጥለው ዋዕየ ሲኦል (የሲኦል ቃጠሎ) ወደ ልምላሜ ገነት ጥንተ ማኅደራቸው መመለሳቸውን በዚህ አኳኋን እየገለጡ በዓለ ትንሣኤን በቅድስት ቤተ ክርስቲያን ያከብራሉ፡፡ ከበዓሉ ረድኤት፣ በረከት ያሳትፈን፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

ስግደትና ሰላምታ በሰሙነ ሕማማት

በሊቀ ማእምራን ብርሃነ መስቀል አጠና 

የሊቃውንት ጉባኤ አባል

መጋቢት ፳፬ ቀን ፳፻፲ ዓ.ም

ሰሙነ ሕማማት ሰሙነ ስቅለትም ይባላል፡፡ ይኸውም ከሆሣዕና ማግስት (ከሰኞ) ጀምሮ እስከ ዓርብ ስቅለት ያለው ክፍለ ጊዜ ሲኾን ይህም ከጌታችን አምላካችንና መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ዐበይት በዓላት መካከል አንዱ ነው፡፡ ‹‹እርሱ ግን በእውነት ደዌያችንን ተቀበለ፤ ሕማማችንንም ተሸከመ፡፡ ስለ እኛም ታመመ፡፡ እኛም እንደ ታመመ፣ እንደ ተገረፈ ቈጠርነው፡፡ እርሱ ግን ስለ ኃጢአታችን ቈሰለ፤ ስለ በደላችንም ታመመ፡፡ የሰላማችንም ተግሣፅ በእርሱ ላይ ነበረ፡፡ በእርሱም ቊስል እኛ ተፈወስን፤›› በማለት ነቢዩ ኢሳይያስ እንደ ገለጸው (ኢሳ. ፶፫፥፬-፭)፣ ሰሙነ ሕማማት የክብርና የሥልጣን ዅሉ ባለቤት፣ ዅሉን ቻይ፣ ኃያል የኾነው አምላክ እኛን ከመውደዱ የተነሣ የእኛን ዕዳ ለመክፈል በመስቀል እስከ መሞት ድረስ እጅግ ከባድና አሰቃቂ የኾነ መከራ በፈቃዱ የተቀበለበት ሰሙን ከመኾኑም ባሻገር እኛ ፍጹም ድኅነትን ያገኘንበት ጊዜ ነው፡፡

ስግደት የአምልኮ ስግደት እና የአክብሮት ስግደት ተብሎ በሁለት ይከፈላል፡፡ እኛ ኢያሱ ለመልአኩ እንደ ሰገደ ዮሐንስ፤ ወንጌላዊም እንደዚሁ ለመልአኩ መላልሶ እንደ ሰገደ እግዚአብሔር አምላክ ላከበራቸው ቅዱሳን መስገድ ያከበራቸው እግዚአብሔርን ማክበር መኾኑን አውቀን የአክብሮት ስግደት ስንሰግድላቸው ያልገባቸው ሰዎች ከኢያሱና ከዮሐንስ በላይ ለእግዚአብሔር አምልኮት ተቈርቋሪ በመምሰል ይዘብቱብናል፤ ባይገባቸው ነው፡፡ አንዳንድ ሰዎችም እንደዚሁ ‹‹በሰሙነ ሕማማት ሌሎች በዓላት ተደርበው ሲውሉ ስግደት አይገባም፤›› እያሉ ሕዝቡን በየጊዜው ያደናግራሉ፡፡ በፍትሐ ነገሥት አንቀጽ ፲፭ ‹‹በጌታችን በዓል፣ በእመቤታችን በዓል ሥጋ ወደሙ ከተቀበሉ በኋላ ሰጊድ አይገባም፤›› ይልና በጌታ በዓል አድንኖ፤ በእመቤታችን በዓል አስተብርኮ በቅዱሳን በዓል ሰጊድ ይላል፡፡ ነገር ግን ይህ ሐተታ ለየትኛው ስግደት እንደ ተነገረ መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡

አንደኛ የሕማማት ዝርዝር ኹኔታ የተጻፈው በአንቀጸ ጾም ነው፤ ይህ ሐተታ ግን የሚገኘው በአንቀጸ ጸሎት ነው፡፡ ከሕማማት ጋር ፈጽሞ ግንኙነት የለውም፡፡ ሁለተኛ ፍትሕ መንፈሳዊ በአንቀጽ ፲፭ ሐተታውን ሲጀምር ‹‹ወዘይጼሊ ቅድመ ይስግድ ወበዘይበጽሕ ዝክረ ሰጊድ ለእግዚአብሔር ልዑል በጊዜ ጸሎት›› በማለት የሚጸልይ ሰው አስቀድሞ (በመጀመሪያ) አንድ ጊዜ ወይም ሦስት ጊዜ ሰጊድን ከሚያነሣ አንቀጽ ላይ ሲደርስ፣ ለአብነትም ‹‹ንሰግድ ለከ ዘለከ ይሰግድ ኵሉ ብርክ፤ ንስግድ ሎቱ ወንሰብሖ ምስለ አብ ወወልድ፤ ንሰግድ ለከ ክርስቶስ፤ እሰግድ ለአብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐተ ስግደተ፤ እሰግድ ለእግዝእትነ ማርያም ድንግል ወላዲተ አምላክ፤ እሰግድ ለመስቀለ እግዚእነ ኢየሱስ ክርስቶስ›› የመሳሰለ ንባብ ሲያጋጥም መስገድ እንደሚገባ ያዛል፡፡

ስለዚህ በግል ጸሎት ጊዜና በንስሓ ወቅት ስለሚሰገደው ስግደት ወይም አንድ ባሕታዊ ፆር እንዳይነሣብኝ ብሎ፤ ምእመናን ክብር ለማግኘት ብለው ስለሚሰግዱት ስግደት የተወሰነውን ሥርዓት ከሕማማት በዓል አከባበር ጋር ያለ ስፍራው ማምጣት ስሕተት ነው፡፡ ምክንያቱም ሰሙነ ሕማማት ዓርብ ስቅለትን ጨምሮ ከጌታችን ዐበይት በዓላት አንዱ ነው፡፡ በዓሉ ደግሞ የሚከበረው በማኅሌት፣ በቅዳሴ ሳይኾን ባለቤቱ በመሠረተው በኀዘን፣ በጸሎት፣ በልቅሶ፣ በስግደት ነውና፡፡ ስለኾነም ማንኛውም በዓል የዓመትም ይኹን የወር በዓል ከሕማማት ጋር ቢገጥም እንኳ አልፎ ከፋሲካ በኋላ ይከበራል እንጂ በሕማማት ውስጥ አይከበርም፡፡ ስግደትም አይከለከልም፡፡ ታዲያ በዓሉ ቦታውን ለቆ ሒዶ እያለ የሕማማትን ስግደት እንዴት ያስቀራል?

መጽሐፉ በጌታችን በዓል ‹አድንኖ›፤ በእመቤታችን በዓል ‹አስተብርኮ› ብሎ በቅዱሳን በዓል ‹ስግደት› ነው የሚለው፡፡ እንኳን በሰሙነ ሕማማት የቅዱሳን በዓላት በሚውሉባቸው ሌሎች ዕለታትም ስግድት መስገድ አይከለከልም፡፡ እነዚያ በግምት የሚነጉዱ ሰዎች ግን ‹‹የቅዱሳን በዓል በሕማማት ሲውል አይሰገድም፤›› እያሉ ችግር ሲፈጥሩና ‹‹እገሌ በበዓል ጊዜ ይሰግዳል ይላል፡፡ መናፍቅ ነው፤›› እያሉ የእውነተኞችን መምህራን ስም ሲያጠፉ ይስተዋላሉ፡፡ ስለዚህ የሚመለከተው አካል ተዉ ሲላቸው ካልተመለሱ ጥብቅ ትምህርት ሊሰጣቸው ይገባል፡፡

በመሠረቱ ሰላምታ በቁሙ ፍጹም ጤና፣ ዕረፍት፣ ፍቅር፣ አንድነት፣ ደኅንነት፣ ተድላ፣ ደስታ፣ ሰላምታ፣ ቡራኬ፣ የምርቃት ቃል፣ ሰው ሲገናኝ ወይም ሲለያይ የሚናገረው የሚፈጽመው ተግባር ነው (መጽሐፈ ሰዋስው ዘኪዳነ ወልድ)፡፡ ስለኾነም ሰላም በየትኛውም ቦታ፣ በማንኛውም ጊዜ ለዅሉ የሚበጅ፤ ከዅሉም በላይ እጅግ ጠቃሚ ተግባር ነው፡፡ ጎጂና በጣም ክፉ ወይም አደገኛ ኾኖ የተገኘው የጥፋት ልጅ የተባለው የይሁዳ ሰላምታ ነው፡፡ ‹‹ይህንንም ሲነግራቸው ሕዝቡ ደረሱ፤ ከዐሥራ ሁለቱ ደቀ መዛሙርት አንዱ ይሁዳ ይመራቸው ነበር፡፡ ወደ ጌታችን ኢየሱስም ቀርቦ ሳመው፤ የሰጣቸው ምልክት ይህ ነበር፡፡የምስመው እርሱ ነውና አጽንታችሁ ያዙት፤አላቸው፡፡ ጌታችን ኢየሱስምይሁዳ! የሰውን ልጅ በመሳም ታስይዘዋለህን? ልታስገድለው አይደለምን?› አለው›› (ሉቃ. ፳፪፥፵፯-፵፰፤ ማቴ. ፳፮፥፵፯-፶፮፤ ማር. ፲፬፥፫-፶፤ ዮሐ. ፲፰፥፫-፲፪)፡፡

ጌታችን በዚህ ኹኔታ ከተያዘ በኋላ ነው እስከ ሞት ድረስ ያን ዅሉ መከራ የተቀበለው፡፡ ስለኾነም ከሰሙነ ሕማማት እስከ በዓለ ትንሣኤ (ክርስቶስ ተንሥአ እሙታን) እስከሚባል ድረስ መስቀል ወይም መጽሐፍ መሳለም እንዳይገባ ‹‹ወኢይትአምኁ በበይናቲሆሙ ዘእንበለ በዕለተ ፋሲካ ወኢየአምኁ መስቀለ ወወንጌለ፤ ያለ ፋሲካ ቀን እርስ በእርሳቸው አይሳሳሙ፤ መስቀልንና ወንጌልንም አይሳለሙ፤›› ተብሎ ተደንግጓል (ፍት.መን. ገጽ ፪፻፳፯)፡፡ ጸዋትወ ዜማም ‹‹ይሁዳ ኢየሱስ ክርስቶስን ስለ ሳመው ወይም በመሳም ስላስያዘው እርስ በርሳቸው አይሳሳሙ፤ ወንጌልንና መስቀልንም አይሳለሙ፡፡ የሞቱትንም ሰዎች አይፍቱ፤›› ይላል (ገጽ. ፺፬-፺፯)፡፡

በግብረ ሕማማት ገጽ ፵፯ እና ፭፻፺፭ ‹‹ወኢይትአምኁ በበይናቲሆሙ ወኢይአምኁ ወንጌለ ወመስቀለ በእንተ ዘአምኆ ይሁዳ ወኢይዝክሩ ሰሞሙ ለእለ ኖሙ ቅዱሳን አበው ወኢይበሉ ሐዳፌ ነፍስ›› ይላል፡፡ ይህ ትእዛዝ በእነዚህ ዅሉ መጻሕፍት እየተደጋገመ መጠቀሱ ለአጽንዖተ ነገር ነው፡፡ በሰሙነ ሕማማት እርስበርስ መሳሳም ከይሁዳ ሰላምታ ጋር የተያያዘ ስለ ኾነና የይሁዳ ተባባሪ ስለሚያሰኝ እስከ ትንሣኤ ድረስ መሳሳምም ኾነ ወንጌልንና መስቀልን መሳለም ተከልክሏል፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር፡፡