ጾመ ነቢያት

በዲያቆን ኤፍሬም የኔሰው

ኅዳር ፲፬ ቀን ፳፻፲ ዓ.ም

እግዚአብሔር አምላካችን ዓለምን ለማዳን ሲል የሰውን ሥጋ መልበሱን፣ ከእናቱ ቅድስት ድንግል ማርያም ጋር ወደ ግብጽ ግብር መሰደዱን፣ በባሕረ ዮርዳኖስ መጠመቁን፣ በትምህርቱ ብርሃንነት ጨለማውን ዓለም ማብራቱን፣ ለሰው ልጆች ድኅነት ሲል ልዩ ልዩ ዓይነት መከራ መቀበሉን፣ መሰቀሉን፣ መሞቱን፣ ከሙታን ተለይቶ መነሣቱን፣ ማረጉንና ዳግም ለፍርድ የሚመጣ መኾኑን በአጠቃላይ የማዳን ሥራውን በየዘመናቱ የተነሡ ቅዱሳን ነቢያት በመንፈስ ቅዱስ ተቃኝተው አስቀደመው በትንቢት ተናግረዋል፡፡ ትንቢቱ ተፈጽሞ ለመመልከትም ‹‹አንሥእ ኃይለከ ፈኑ እዴከ፤ ኃይልህን አንሣ፤ እጅህን ላክ›› እያሉ በጾም በጸሎት ተወስነው አምላክ ሰው ኾኖ ዓለምን የሚያድንበትን ጊዜ በቀናት፣ በሳምንታት፣ በወራትና በዓመታት እያሰሉ ሲጠባበቁ ቆይተዋል፡፡ የእግዚአብሔርን ሰው መኾን ሲጠባበቁ የኖሩት የነቢያት ትንቢትና ጸሎትም በእግዚአብሔር ሰው መኾን ፍጻሜ አግኝቷል፡፡

ይህን ምሥጢር በማሰብ በየዓመቱ ከኅዳር ፲፭ ቀን ጀምሮ እስከ ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዓለ ልደት ዋይዜማ ድረስ እንድንጾም አባቶቻችን መምህራነ ቤተ ክርስቲያን ሥርዓት ሠርተውልናል፡፡ ይህ ጾም፣ ከሰባቱ አጽዋማት አንዱ ሲኾን፣ በስያሜም ‹‹ጾመ ነቢያት (የነቢያት ጾም)›› እየተባለ ይጠራል፡፡ ወቅቱ ለአዳም የተነገረው የድኅት ተስፋ የተፈጸመበት ስለ ኾነም ‹‹ጾመ አዳም (የአዳም ጾም)›› ይባላል፡፡ ስለ እግዚአብሔር ሰው መኾን በስፋት ትምህርተ ወንጌል የሚሰጥበት ወቅት በመኾኑም ‹‹ጾመ ስብከት (የስብከት ጾም)›› የሚል ስያሜ ተሰጥቶታል፡፡ የጾሙ መጨረሻ (መፍቻ) በዓለ ልደት በመኾኑ ደግሞ ‹‹ጾመ ልደት (የልደት ጾም)›› በመባል ይታወቃል፡፡ በተጨማሪም ‹‹ጾመ ሐዋርያት››  እየተባለ ይጠራል፡፡ ምክንያቱም ቅዱሳን ሐዋርያት ‹‹በዓለ ትንሣኤን ዐቢይ ጾምን ጾመን እናከብረዋለን፤ በዓለ ልደትንስ ምን አድርገን እናከብረዋለን?›› በማለት ነቢያት በጾሙበት ማለት ከልደተ ክርስቶስ በፊት ባለው ወቅት ጾመዋልና፡፡

በሌላ አጠራር ይኸው ጾመ ነቢያት ‹‹ጾመ ፊልጶስ (የፊልጶስ ጾም)›› በመባል ይታወቃል፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ፊልጶስ በአፍራቅያ እና አውራጃዋ ዅሉ እየተዘዋወረ በጌታችን አምላካችንና ድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስም ወንጌልን በማስተማር፣ ድንቅ ድንቅ ተአምራትን በማድረግ ብዙዎችን ወደ አሚነ እግዚአብሔር ሲመልስ ቆይቶ ትምህርቱን በማይቀበሉ የአፍራቅያ ሰዎች አማካይነት በሰማዕትነት ዐርፏል፡፡ ደቀ መዛሙርቱ ሥጋውን ሊቀብሩ ሲሉም ተሰወረባቸው፡፡ በዚህ ጊዜ በዓት ዘግተው፣ ሱባዔ ገብው፣ በጾም በጸሎት ተወስነው የሐዋርያውን ሥጋ ይመልስላቸው ዘንድ እግዚአብሔርን ቢለምኑት ልመናቸውን ተቀብሎ ሱባዔ በያዙ በ፫ኛው ቀን የቅዱስ ፊልጶስን ሥጋ (በድን) መልሶላቸው በክብር አሳርፈውታል፡፡ ደቀ መዛሙርቱ የሐዋርያውን ሥጋ ካገኙ በኋላ እስከ ጌታችን ልደት ድረስ ጾመዋል፡፡ ስለዚህም ጾመ ነቢያት፣ ‹‹ጾመ ፊልጶስ›› እየተባለ ይጠራል፡፡

ከዚሁ ዅሉ ጋርም ወልደ አምላክ ክርስቶስን በግብረ መንፈስ ቅዱስ እንደምትፀንሰው፣ መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምን ካበሠራት በኋላ ‹‹ሰማይና ምድር የማይወስኑትን አምላክ ፀንሼ ምን ሠርቼ እወልደዋለሁ?›› በማለት ጌታችንን ከመውለዷ አስቀድማ እመቤታችን ጾማዋለችና ይህ ጾም ‹‹ጾመ ማርያም›› በመባልም ይታወቃል፡፡ በአጠቃላይ በዚህ በጾመ ነቢያት፣ ነቢያትም ሐዋርያትም፣ ቀደምት አባቶቻችንም ጾመው በረከት አግኝተውበታል፡፡ እኛ ምእመናንም የነቢያት፣ የሐዋርያት፣ የጻድቃንና የሰማዕታት አምላክ ከእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም፣ ከቅዱሳን ነቢያትና ሐዋርያት በረከት እንዲያሳትፈን በዚህ በጾመ ነቢያት ወቅት በጾም በጸሎት ተወስነን እግዚአብሔርን ልንማጸነው ይገባናል፡፡ 

ወስብሐት ለእግዚአብሔር፡፡ 

ምንጭ፡ 

  • ፍትሐ ነገሥት ንባቡና ትርጓሜው፣ አንቀጽ ፲፭፡፡ 
  • ጾምና ምጽዋት (፳፻፩ ዓ.ም)፣ ዲያቆን ቃኘው ወልዴ፤ ገጽ ፵፯ – ፶፡

በአውሮፓ የሕፃናት እና ታዳጊዎች ሥርዓተ ትምህርት ተመረቀ

በእንግሊዝ ንዑስ ማእከል

ኅዳር ፲፫ ቀን ፳፻፲ ዓ.ም

በምረቃ ሥርዓቱ ላይ የተገኙ የሰሜን ምዕራብ አውሮፓ ሀገረ ስብከት ሠራተኞች እና ካህናት በከፊል

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሰ/ት/ቤ/ማ/መ/ ማኅበረ ቅዱሳን አውሮፓ ማእከል የተተኪ ትውልድ ሥልጠና ክፍል አስተባባሪነት የተዘጋጀ ከኢትዮጵያ ውጪ የሚኖሩ ሕፃናት እና ታዳጊዎችን ለማስተማር የሚያግዝ ሥርዓተ ትምህርት በእንግሊዝ አገር በለንደን ከተማ በደብረ ገነት ቅድስት ሥላሴ ቤተ ክርስቲያን ኅዳር ፫ ቀን ፳፻፲ ዓ.ም ተመረቀ፡፡

በምረቃ ሥርዓቱ ላይ የሰሜን ምዕራብ አውሮፓ ሀገረ ስብከት ሠራተኞች፣ ከየአብያተ ክርስቲያናት የመጡ ካህናት፣ የሰንበት ት/ቤት አባላት፣ የየአብያተ ክርስቲያናት ተወካዮች፣ የአካባቢው ምእመናንና በማኅበረ ቅዱሳን አውሮፓ ማእከል የእንግሊዝ ንዑስ ማእከል አባላት ተገኝተዋል፡፡

መርሐ ግብሩ በሊቀ አእላፍ ቆሞስ አባ አሮን ሳሙኤል በሰሜን ምዕራብ አውሮፓ ሀገረ ስብከት የሰ/ት/ቤ/ማደራጃ ክፍል ሓላፊ በጸሎት የተከፈተ ሲኾን፣ የሀገረ ስብከቱ ዋና ጸሐፊ ቀሲስ በለጠ የእንኳን ደኅና መጣችሁ መልእክት አስተላልፈው የሥርዓተ ትምህርቱን ምረቃና አጠቃላይ ዝግጅት አስተዋውቀዋል፡፡

ዶ/ር በላቸው ጨከነ በማኅበረ ቅዱሳን የአውሮፓ ማእከል ምክትል ሰብሳቢ እና የሥርዓተ ትምህርቱ ዝግጅት አስተባባሪም የሥርዓተ ትምህርቱ የዝግጅት ሒደት፣ ዓላማ፣ አስፈላጊነት፣ ይዘት እና ቀጣይ ሥራዎችን በተመለከተ ባቀረቡት ገለጻ በሥርዓተ ትምህርት ዝግጅቱ ከሠላሳ የሚበልጡ የቤተ ክርስቲያን ልጆች መሳተፋቸውን አመላክተዋል፡፡

ዶ/ር በላቸው እንዳብራሩት በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የሰሜን ምዕራብ አውሮፓ ሀገረ ስብከት ፈቃድ የተጀመረው የሕፃናትና ታዳጊዎች የሥርዓተ ትምህርት ዝግጅት ከሁለት ዓመታት በላይ የወሰደ ሲኾን፣ ዝግጅቱ ከመጀመሩ አስቀድሞም ከሦስት መቶ በላይ የሚኾኑ በእንግሊዝ አገር የሚኖሩ ምእመናን የተሳተፉበት የየአብያተ ክርስቲያናት ተሞክሮ፣ የልጆች የቋንቋ ክህሎት እና የቤተ ክርስቲያን ትምህርት ደረጃ፣ እንደዚሁም ወላጆች የተሳተፉበት በችግሮች እና የመፍትሔ አቅጠጫዎች ዙሪያ ያተኮረ የመነሻ ጥናት ተደርጓል፡፡

ጥናቱን መሠረት በማድረግም ለወደፊት የሚመለከታቸውን አካላት ዅሉ ለማሳተፍ የሚያስችል ጥናትና ምክረ ሐሳብ (ፕሮፖዛል) ለሰሜን ምዕራብ አውሮፓ ሀገረ ስብከት ቀርቦ የነበረ ሲኾን፣ የሀገረ ስብከቱ አስተዳደር ጉባኤም የቀረበውን ጥናትና ምክረ ሐሳብ ተቀብሎ በሀገረ ስብከቱ ሥር በሚገኙ አገሮች የወላጆች ኮሚቴ እንዲዋቀር ወስኗል፡፡ ለዚህም የሥራ መመሪያ ተዘጋጅቶ ለየአጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት መላኩ ተገልጿል፡፡

እንደ ዶ/ር በላቸው ጨከነ ገለጻ ወጥ የኾነ ሥርዓተ ትምህርት አለመኖር በአውሮፓ የሚኖሩ ታዳጊ ሕፃናትን ለማስተማር ከባድ ከሚያደርጉት ኹኔታዎች ዐቢይ ምክንያት ሲኾን፣ ይህን በመገንዘብ የሰሜን ምዕራብ አውሮፓ ሀገረ ስብከት ባወጣው የሥራ መመሪያ መሠረት በማኅበረ ቅዱሳን አውሮፓ ማእከል የተተኪ ትውልድ ሥልጠና ክፍል ባለሙያዎችን በመመደብ ሥራውን እንዲጀምር ተደርጓል፡፡

ከአምስት እስከ ዘጠኝ ዓመት የዕድሜ ክልል ውስጥ ለሚገኙ ሕፃናትና ታዳጊዎች ታስቦ የተዘጋጀው ሥርዓተ ትምህርቱ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት፣ ትምህርተ ሃይማኖት፣ ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን፣ የአማርኛ ቋንቋ እና የመዝሙር ጥናት የተሰኙ አምስት የትምህርት ዘርፎችን ያካተተ ሲኾን፣ የትምህርቶቹ አርእስትና ይዘቶችም በቤተ ክርስቲያን የሚከበሩ በዓላትንና ወቅቶችን መሠረት በማድረግ የተዘጋጁ ናቸው፡፡

የሥርዓተ ትምህርቱ ጥራዞች

በቀጣይነትም በአውሮፓ ማእከል አስተባባሪነት የሕፃናት እና ታዳጊዎች ክፍልን በመላው አውሮፓ በሚገኙ አብያተ ክርስቲያናት ለማቋቋምና ለማጠናከር፣ ለመምህራን ሥልጠና ለመስጠት፣ በየአገሩ የወላጆች ኮሚቴን ለማቋቋም እና ሥርዓተ ትምህርቱን በየአጥቢያው ለማዳረስ መታቀዱን ዶ/ር በላቸው ጨከነ አስረድተዋል፡፡

‹‹የእኛ ትወልድ፣ ነገ በመላው ዓለም ለምትኖረው ቤተ ክርስቲያን ድልድይ ነው፤›› ያሉት ዶ/ር በላቸው ጨከነ ለሥርዓተ ትምህርቱና ለሌሎችም ዕቅዶች ተግባራዊነት የሚመለከታቸው የቤተ ክርስቲያን አካላትና ምእመናን በትጋት ሊሠሩ እንደሚገባ በማሳሰብ መልእክታቸውን አጠቃለዋል፡፡

በምረቃ ሥርዓቱ ላይ የተገኙ ካህናትና ምእመናንም በዚህ ዝግጅት የተሳተፉ ወገኖችን ከማመስገን ጀምሮ ብዙ ጠቃሚ አስተያየት ሰጥተዋል፡፡ ለአብነትም ሊቀ አእላፍ ቆሞስ አባ አሮን ሳሙኤል በሰሜን ምዕራብ አውሮፓ ሀገረ ስብከት የሰ/ት/ቤ/ማደራጃ ክፍል ሓላፊ ዝግጅቱ አስፈላጊና ወቅታዊ መኾኑን ጠቅሰው በሕፃናት ላይ የሚሠራ ሥራ መሠረታዊ ለውጥ ለማምጣት የላቀ ጠቀሜታ እንዳለው ተናግረዋል፡፡

‹‹ይህ ሥራ ችግኝ ተከላ ነው›› ያሉት የለንደን ደብረ ገነት ቅድስት ሥላሴ ቤተ ክርስቲያን አስተዳዳሪ መልአከ ገነት ቀሲስ ከፍያለው አስቻለው በበኩላቸው ሕፃናትን የማስተማር አገልግሎት ለበርካታ ዓመታት በአእምሯቸው ሲመላለስ እንደ ቆየ አውስተው ‹‹ዝግጅቱ የልጆቻችንን ጥያቄ የሚመልስልን በመኾኑ ከአሁን በኋላ ዅላችንም በሓላፊነት ልንሠራበት ይገባል›› ሲሉ አሳስበዋል፡፡

‹‹በውጪ አገር ይህን ያህል ዓመት ስንኖር ዛሬ ገና ስለ ልጆቻችንን ማሰብ በመጀመራችን ደስ ብሎኛል›› በማለት ደስታቸውን የገለጹት ሊቀ ሊቃውንት ገብረ ሥላሴ ዓባይም በሰሜን ምዕራብ አውሮፓ ሀገረ ስብከት የስብከተ ወንጌል ክፍል ሓላፊ፣ ይህ ዝግጅት እንዲፈጸም ላደረገው ለእግዚአብሔር ምስጋና ካቀረቡ በኋላ ለሥራው ተግባራዊነትም ዅሉም ጠንክሮ መሥራት እንደሚገባው አስገንዝበዋል፡፡

በሊቨርፑል ከተማ የመካነ ቅዱሳን አቡነ ተክለ ሃይማኖት ቤተ ክርስቲያን አስተዳዳሪ ሊቀ ትጉሃን ቀሲስ ብርሃኑ ደሳለኝ ደግሞ ቤተ ክርስቲያናችን ያላትን ብዙ ሀብት በሚገባ እየተጠቀምንበት እንዳልኾነ አስታውሰው ዝግጅቱ ተጠናቆ ለምረቃ በመብቃቱም ‹‹ቤተ ክርስቲያናችን እንኳን ደስ ያላት! እናንተም እንኳን ደስ ያላችሁ!›› በማለት የተሰማቸውን ደስታ ገልጸዋል፡፡

መጋቤ ሐዲስ ክብረት የለንደን ደብረ ገነት ቅድስት ሥላሴ ቤተ ክርስቲያን አገልጋይም እንደዚሁ ይህ ዝግጅት ለሕፃናት መንፈሳዊ ሕይወት ከሚኖረው ጠቀሜታ ባሻገር ሕፃናት ከወላጆች ጋር እንዲግባቡ የሚያግዝ ሥራ መኾኑንም መስክረዋል፡፡ በተመሳሳይ መልኩ አንዳንድ ምእመናንም ለሥራው ውጤታማነት የሚጠቅሙ ገንቢ አስተያየቶችን ሰጥተዋል፡፡

በመጨረሻም የተዘጋጁት የመምህራን መምሪያ እና የሥርዓተ ትምህርት መድብሎች ከየአጥቢያው ለመጡ የሰበካ ጉባኤ ተወካዮች ከተሰጡ በኋላ በሰሜን ምዕራብ አውሮፓ ሀገረ ስብከት ዋና ጸሐፊ ቀሲስ በለጠ መርዕድ የማጠቃለያ መልእክትና ጸሎተ ቡራኬ የምረቃ ሥርዓቱ ተጠናቋል፡፡

‹‹በመንገድ ላይ እንዳላጠፋህ በፊትህ መልአክ እሰዳለሁ፤›› (ዘፀ. ፴፫፥፫)፡፡

በመምህር ኢዮብ ይመኑ 

ኅዳር ፲፪ ቀን ፳፻፲ ዓ.

በረኃብ ምክንያት ከከነዓን ወደ ግብጽ የተሰደዱት የያዕቆብ ቤተሰቦች፣ በአባታቸው በያዕቆብ ምርቃት በግብጽ ምድር ቍጥራቸውም እጅግ እየበዛ መጣ፡፡ መብዛታቸውም ከ፲፪፻፹ – ፲፬፻፵፭ ቅድመ ልደተ ክርስቶስ የተነሣውን፣ ዮሴፍን የማያውቀውን ንጉሥ አስፈራው (ዘፀ. ፩፥፰)፡፡ ንጉሡም ጠላት ይኾኑብናል ያም ባይኾን ጠላት ቢነሣብን አብረው ይወጉናል በሚል ፍርኃት፣ አገዛዙን አጸናባቸው፡፡ በከባድ ሥራ እየጠመደ በጭካኔ ጡብ እያስገነባ ፊቶም፣ ራምሴ፣ ዖን የተባሉ ታላላቅ ከተሞችን አሠራቸው፡፡ ኖራ እያስወቀጠ፣ ጭቃ እያስረገጠ በሥራ ደክመው ልጅ እንዳይወልዱ ጉልበታቸውን አደከማቸው፡፡ በጅራፍ እየገረፈ መከራ አጸናባቸው፡፡ ይህን ቢያደርግም ጉልበታቸው እየበረታ፣ ከእርሱ መከራ የአባቶቻቸው ምርቃትና ቃል ኪዳን እየረታ አሁንም በዙ፡፡ ንጉሡም ወንድ ሲወለድ በመግደል እስራኤልን ለመቆጣጠር ሞከረ፡፡ ነገር ግን የመከራው ብዛት የሕዝቡም ጩኸት የራሔልም ዕንባ የሕዝቡን መከራ ቅድመ እግዚአብሔር እንዲደርስ አደረገው፡፡

በግብጽ ምድር በመከራ የኖሩት እስራኤላውያን፣ በፈርዖንና በሠራዊቱ ላይ ከደረሱ ፱ መቅሠፍቶች፣ ፲ኛ ሞተ በኵር እና ፲፩ኛ ስጥመተ ባሕር በኋላ በእግዚአብሔር ፈቃድ፣ በቅዱስ ሚካኤል ተራዳኢነትና በሙሴ ጸሎት በተአምራት ከግብጽ ምድር ወጥተው ወደ ርስታቸው ከነዓን ገብተዋል፡፡ ‹‹በመንገድ ላይ እንዳላጠፋህ በፊትህ መልአክ እሰዳለሁ፤›› (ዘፀ. ፴፫፥፩-፫) ተብሎ እንደ ተጻፈው፤ ከመከራ የወጡትን እስራኤል በጉዟቸው ከሚገጥማቸው መሰናከል እየጠበቀ፣ በመንገድ ላይ እንዳይጠፉ እያማለደ፣ በምሕረት እየታደገ፣ ከጠላት ጋር ሲዋጉም አብሮ እየቀደመ፣ ከዲያብሎስ ተንኮል እየሰወረ እግዚአብሔር ወዳዘጋጀላቸው ሥፍራ ያስገባቸው የእግዚአብሔር መልአክ የቅዱስ ሚካኤል መታሰቢያ በዓል በየዓመቱ ኅዳር ፲፪ ቀን በቤተ ክርስቲያናችን ይከበራል፡፡

እግዚአብሔር የሰው ልጆችን ድካም የሚያውቅ አምላክ ነው፡፡ የሰው ልጅ ደግሞ የእግዚአብሔርን ውለታ የሚዘነጋ፣ የተደረገለትንም የሚረሳ፣ ፊቱ ባለ ነገር ላይ ብቻ የሚጨነቅ፣ ነገ በሚመጣው ብቻ የሚጠበብ እንጂ የትናንትና ታሪኩን አስቦ እግዚአብሔርን የሚያመሰግን ባለመኾኑ፣ የተደረገለትን ውለታ እንዳይረሳ ይልቁን እግዚአብሔርን እንዲያመሰግን እንደዚሁም ያለፉት ሥራዎቹ እንዳይረሱ መታሰቢያን ሰጥቶናል፡፡ የቅዱሳን በመታሰቢያ በዓላት እኛን እንድንድን ለመርዳትና ለማገዝ የተሠሩ ሥርዓቶች ናቸው፡፡ መጽሐፍ ‹‹መታሰቢያህም ለልጅ ልጅ ነው … ይህ ለሚመጣ ትውልድ ይጻፍ፡፡ የሚፈጠርም ሕዝብ ለእግዚአብሔር ዕልል ይላል›› (መዝ. ፻፩፥፲፪) እንዳለ የቅዱሳን በዓል መታሰቢያነቱ የእግዚአብሔርን ሥራ ለማድነቅ ለማመስገን ነው፡፡ ተጠቃሚዎቹ ደግሞ እኛ ምእመናን ነን፡፡ ከዚህም ባሻገር መጪውን ትውልድ ወደ እግዚአብሔር ማቅረቢያ፣ ለነገ መንፈሳዊ ሕይወት ማዘጋጃ፣ የበረከትም ማግኛ ይኾናል – መታሰቢያ፡፡

በመጽሐፍ ቅዱስ እንደ ተመዘገበው የዮርዳኖስን የሞላ ውኃ በእግዚአብሔር ተአምራት ተቋርጦ በደረቅ መሻገራቸው ለማሰብ ኢያሱ እስራኤላውያንን ‹‹በአምላካችሁ በእግዚአብሔር ታቦት ፊት ወደ ዮርዳኖስ መካከል እለፉ፡፡ ከእናንተም ሰው ዅሉ በእስራኤል ልጆች ነገድ ቍጥር በጫንቃው ላይ አንድ አንድ ድንጋይ ከዚያ ይሸከም፡፡ ይህም በመካከላችሁ ምልክት ይኾናል ልጆቻችሁም በሚመጣ ዘመን ‹የእነዚህ ድንጋዮች ነገር ምንድር ነው?› ብለው ሲጠይቁአችሁ እናንተበእግዚአብሔር ቃል ኪዳን ታቦት ፊት የዮርዳኖስ ውኃ ስለ ተቋረጠ ነው፤ እነዚህ ድንጋዮች ለእስራኤል ልጆች ለዘለዓለም መታሰቢያ ይኾናሉ› ትሏቸዋላችሁ፤›› ብሏቸዋል (ኢያሱ ፬፥፬-፯)፡፡ ይህም መታሰቢያ ዕለታት ወይም በዓላት ወይም ምልክቶች ጥቅም እንዳላቸው ያስረዳናል፡፡ በእነዚህ ዕለታት፣ ሰው እግዚአብሔርን አመስግኖ፣ ከቅዱሳኑ በረከት አግኝቶ፣ ራሱን በቅድስና ሥፍራ አውሎ፣ ቅድስናን ተምሮ ለቅድስና የሚያበቃውን በረከት ያገኛል፡፡  እግዚአብሔር አምላካችን ሥራ የሠራበት፣ በጽኑ ተአምራት ሕዝቡን የታደገበት መንገድ እንደ ቀላል በዝምታ የሚታለፍ ሳይኾን መታሰቢያ የሚደረግለት በዓል ነው፡፡ ‹‹ተዝካረ ገብረ ለስብሐቲሁ፤ ለተአምራቱ መታሰቢያአደረገ፤›› (መዝ. ፻፲፥፬) ተብሎ እንደ ተጻፈ፡፡

ስለዚህም ኅዳር ፲፪ ቀን እግዚአብሔር በታላላቅ ተአምራት ሕዝቡን ነጻ ያወጣበት ዕለት በመኾኑ የመታሰቢያ በዓል ኾኗል፡፡ እግዚአብሔር በባሕርዩ የእርሱ ለኾኑት ቅዱሳን ክብርና ሞገስ የሚሰጥ አምላክ ነው፡፡ ሰዎች የእርሱ የኾኑትን እንዲያከብሩለት የሚፈልግ አምላክም ነው፡፡ ለዚህም ነው ‹‹እነሆም መጥተው በእግሮችህ ፊት ይሰግዱ ዘንድ እኔም እንደወደድኹህ ያውቁ ዘንድ አደርጋቸዋለሁ፤›› በማለት የተናገረው (ራዕ. ፫፥፱)፡፡ ወዳጆቹን ማክበር እግዚአብሔርን ማክበር ነው፡፡ እነርሱን ማሰብም እርሱን ማሰብ ነውና ነው፡፡ ‹‹የእግዚአብሔርን ቃል የተናገሯችሁን ዋኖቻችሁን አስቡ፡፡ የኑሮአቸውንም ፍሬ እየተመለከታችሁ በእምነት ምሰሏቸው›› ተብሎ እንደ ተጽፏልና (ዕብ. ፲፫፥፯)፡፡

ቅዱሳኑን መመልከት እግዚአብሔርን መመልከት ነው፡፡ ስለዚህም ይህ የከበረ ዕለት፣ እስራኤል በመንገድ ላይ እንዳይጠፉ በቅዱስ ሚካኤል ተራዳኢነት፣ ጥበቃና መሪነት ወዳዘጋጀላቸው ሥፍራ መግባታቸውን የምናስብበት በዓል ነው፡፡ ቤቱ የእርሱ ቢኾንም መታሰቢያነቱን ለወዳጆቹ፣ ደስ ላሰኙት ቅዱሳኑ እግዚአብሔር ይሰጣል (ኢሳ. ፶፮፥፬)፡፡ ልዩ ከኾነው ስሙ ጋር ስማቸው አብሮ እንዲነሣ ያደርጋል፡፡ አድሮባቸው ሥራ ሠርቷልና እንዲሁ አይተዋቸውም፤ እንዲታሰቡለት ያደርጋል እንጂ፡፡ በቤቱም በፊቱም እነርሱ ሲታሰቡና ሲከብሩ ደስ ይሰኛል፡፡ ምንጩም ፈቃጁም እርሱ ራሱ ነውና፡፡ ‹‹እግዚአብሔርን ለሚፈሩ፣ ስሙንም ለሚያስቡ የመታሰቢያ መጽሐፍ በፊቱ ተጻፈ፤›› እንዳለ ነቢዩ (ሚል. ፫፥፲፮)፡፡ ቅዱሳኑ ስሙን በፍጹም አስበዋልና እግዚአብሔር ደግሞ ስማቸው በሌሎች (በእኛ) እንዲታሰብ ፈቅዷል፡፡ ከዚህ አኳያ ከእስራኤል ዘሥጋ ነጻ መውጣት ጋር ‹‹ስሜ በእርሱ ስለ ኾነ›› (ዘፀ. ፳፫፥፳) የተባለለት ቅዱስ ሚካኤል፣ በየዓመቱ ኅዳር ፲፪ ቀን መታሰቢያው ይከበራል፡፡

‹‹የእግዚአብሔር ሠራዊት አለቃ ኾኜ አሁን መጥቼአለሁ›› (ኢያሱ ፭፥፲፬) በማለት መልአኩ እንደ ተናገረው ኢያሱና እስራኤላውያንን የረዳቸው፣ ያጸናቸው እርሱ ቅዱስ ሚካኤል ነው፡፡ ዲያብሎስ በተንኮል የሙሴን መቃብር አሳይቶ ሕዝቡን በአምልኮ ጣዖት ሊጥል ሲያደባ በጣዖት ወድቀው እግዚአብሔርን በድለው እንዳይጠፉ ከፊታቸው ቀድሞ ከዲያብሎስ ስውር ሤራ የጠበቃቸው ቅዱስ ሚካኤል ነው፡፡ ‹‹የመላእክት አለቃ ሚካኤል ግን ከዲያብሎስ ጋር በተከራከረ ጊዜ ስለ ሙሴ ሥጋ ሲነጋገር ‹ጌታ ይገሥፅህ› አለው እንጂ የስድብን ፍርድ ሊናገረው አልደፈረም፤›› እንዲል (ይሁዳ፣ ቍ. ፱)፡፡ ዳግመኛም ቀኑን በደመና ዓምድ ከበረኃው ዋዕይ እየጋረደ፣ ሌሊቱን በብርሃን ዓምድ ጨለማውን እያስወገደ፣ ከመሰናክል እያዳነ ከመከራ እየጠበቀ እስራኤልን ነጻ አውጥቷቸዋልና ለቅዱስ ሚካኤል መታሰቢያ በዓል ተደርጎለታል (ዘፀ. ፳፫፥፳፤ መዝ. ፴፫፥፯)፡፡

በዘመነ ኦሪት የሶምሶንን አባት እና እናት ልጅ እንደሚወልዱ ባበሠራቸው ጊዜ ማኑሄ፣ ‹‹ነገርህ በደረሰ ጊዜ እንድናከብርህ ስምህ ማን ነው?›› (መሣ. ፲፫፥፲፯) በማለት የእግዚአብሔርን መልአክ መጠየቁ በምስጋና፣ በደስታ ቀናቸው ይህን ተአምራት ያሳያቸውን መልአክ ለማክበርና መታሰቢያ ለማድረግ ነበር፡፡ ይህም የቅዱሳንን በዓል የማበክበር ትውፊት ከጥንት ጊዜ ጀምሮ መኖሩን በሚገባ ያሳያል፡፡ የደስታ፣ የምስጋና ቃል የሚሰማበት ቀን ደግሞ ‹በዓል› ይባላል፡፡ መጽሐፍ ‹‹በዓል የሚያደርጉ ሰዎች የደስታ የምስጋና ቃል አሰሙ›› ይላልና (መዝ. ፵፩፥፭)፡፡ እግዚአብሔር በላያቸው ላይ አድሮ ሥራ የሠራባቸውን፣ ተአምራቱን የገለጸባቸውን ቅዱሳን መላእክት፣ ጻድቃንና ሰማዕታትን የመታሰቢያ በዓል እኛም በዚህ ዘመን በደስታና በምስጋና ማክበራንም ፍጹም አምላካዊና መንፈሳዊ መንገድ መኾኑን አምነን እንመሰክራለን፡፡ ‹‹ቀንን የሚያከብር ለጌታ ብሎ ያከብራል›› ተብሎ እንደ ተጻፈ (ሮሜ. ፲፬፥፮)፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር፡፡

አርዮስ እና መንፈቀ አርዮሳውያን በቤተ ክርስቲያን ላይ ያደረሱት ችግር – የመጨረሻ ክፍል

በቀሲስ ዶ/ር ምክረ ሥላሴ ገብረ አማኑኤል

ኅዳር ፲፪ ቀን ፳፻፲ ዓ.ም

፫. ከኒቅያ ጉባኤ በኋላ አርዮሳውያን እና መንፈቀ አርዮሳውያን

የኒቅያ ጉባኤ ከተፈጸመ ከሦስት ዓመት በኋላ ማለት በ፫፻፳፰ ዓ.ም የእስክንድርያው ሊቀ ጳጳስ እለእስክንድሮስ ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ፡፡ ሊቀ ጳጳስ እለእስክንድሮስ ከመሞታቸው አስቀድሞ በተናዘዙት ቃል መሠረት፣ በኒቅያው ጉባኤ የተዋሕዶ ጠበቃ የነበሩትና በኒቅያው ጉባኤ ትምህርተ ሃይማኖትን (ጸሎተ ሃይማኖትን) ያረቀቁት ታላቁ አትናቴዎስ በምትካቸው በጳጳሳት፣ በካህናትና በሕዝብ ሙሉ ድምፅ ተመርጠው የእስክንድርያ ፓትርያርክ ሆነው ተሾሙ፡፡ ፓትርያርክ አትናቴዎስ በኒቅያ ጉባኤ ጊዜ የአርዮስና የተከታዮቹን የክሕደት ትምህርት በመቃወም ባቀረቡት ክርክርና ለኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሃይማኖት መጠበቅ ባበረከቱት ተጋድሎ በምዕራብም ሆነ በምሥራቅ ባሉ አብያተ ክርስቲያናት ሁሉ ‹‹ታላቁ አትናቴዎስ›› እየተባሉ ይጠራሉ፡፡ አርዮሳውያን እና መንፈቀ አርዮሳውያን በኒቅያ ጉባኤ ከተወገዙ በኋላም በኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ላይ ዘመቻቸውን ከበፊቱ አብልጠው ስለ ቀጠሉ፣ ታላቁ አትናቴዎስ በጽሑፍና በቃል ትምህርት ለእነዚህ መናፍቃን ምላሽ መስጠታቸውን እስከ ዕለተ ሞታቸው ድረስ አላቋረጡም ነበር፡፡

የኒቅያ ጉባኤ እንደ ተፈጸመ አርዮስ እና የአርዮስ ተከታዮች ሁሉ በንጉሡ በቈስጠንጢኖስ ትእዛዝ ወደ ግዞት ተልከው ነበር፡፡ በዚህ ጊዜ አርዮሳውያን የንጉሡንና የፖለቲካ ባለ ሥልጣኖችን ለመወዳጀትና የእነርሱን ድጋፍ ለማግኘት ይሯሯጡ ጀመር፡፡ ስለዚህም ከሁለት ዓመት በኋላ ቆስጣንዲያ በተባለችው በንጉሡ እኅት እና የንጉሡ ወዳጅ በነበረው በኒቆምዲያው ኤጲስ ቆጶስ አውሳብዮስ አማካይነት ብዙዎቹ አርዮሳውያን ከግዞት እንዲመለሱ ታላቅ ሙከራ ተደረገ፡፡ በዚህም ምክንያት አርዮስና አያሌ አርዮሳውያን ከግዞት ተመለሱ፡፡ ከዚህ ጊዜ ጀምሮ ቤተ ክርስቲያንን ያወካት የነገሥታቱ በሃይማኖት ጉዳይ ጣልቃ መግባት ነበር፡፡ በጉባኤ ሲኖዶስ የተወገዘው አርዮስ ከውግዘት እንዲፈታና ወደ እስክንድርያ ተመልሶ በቤተ ክርስቲያን በየነበረው ሥልጣን አገልግሎቱን እንዲቀጥል ንጉሡ ለሊቀ ጳጳሱ ለአትናቴዎስ ትእዛዝ አስተላለፈላቸው፡፡ ንጉሡ ይህን ትእዛዝ ያስተላለፈው ‹‹አርዮስ ከክሕደቱ ተመልሷል›› ብለው ወዳጆቹ ያስወሩትን ወሬ በመስማትና ‹‹የአርዮስ የእምነት መግለጫ ነው›› ተብሎ የቀረበለትን ግልጽ ያልሆነ መረጃ በመመልከት ነበር፡፡ ነገር ግን ይህን መግለጫ አርዮስን ያወገዘው ሲኖዶስ መርምሮ ሲያጸድቀው ነበር – ከክሕደቱ መመለሱ የሚታወቀው፡፡

በ፫፻፳፱ ዓ.ም የአርዮስ ደጋፊ በነበረው በኒቆምዲያው ኤጲስቆጶስ አውሳብዮስ የተመራውና አርዮሳውያን በብዛት የነበሩበት ጉባኤ ተሰብስቦ ‹‹አርዮስ ከውግዘቱ ተፈቷል›› በማለት ወሰኑ፡፡ የውሳኔአቸውን ግልባጭ በማያያዝም አትናቴዎስ አርዮስን እንዲቀበለው ንጉሠ ነገሥቱ መልእክት አስተላለፈ፡፡ አትናቴዎስ ግን የንጉሡን ትእዛዝና የአርዮሳውያንን ጉባኤ ውሳኔ አልቀበልም አሉ፡፡ ያልተቀበሉበትንም ምክንያት በዝርዝር ለንጉሡ ጻፉ፡፡ አርዮሳውያንና መንፈቀ አርዮሳውያንም የአትናቴዎስን እምቢታ (የንጉሡን ትእዛዝ አለመቀበል) መነሻ በማድረግ አትናቴዎስን እና ሌሎች ኦርቶዶክሳውያን መሪዎችን ከንጉሠ ነገሥቱ ጋር ለማጣላት የተቻላቸውን ሁሉ ጥረት አደረጉ፡፡ አርዮስ ወደ እስክንድርያ ተመልሶ ወደ ቀድሞው የክህነት ሥልጣኑ እንዲመለስ ንጉሠ ነገሥቱ ቈስጠንጢኖስ ያዘዘውን ትእዛዝ አትናቴዎስ ባለመቀበላቸውና መንግሥት በአርዮስ ጉዳይ ጣልቃ መግባቱን በመቃወማቸው የተነሣም ንጉሠ ነገሥቱ እጅግ ተቈጥቶ ነበር፡፡

ፓትርያርክ አትናቴዎስ የአርዮስ መወገዝም ሆነ መፈታት የሚመለከተው ቤተ ክርስቲያንን እንጂ ቤተ መንግሥትን አለመሆኑን ገልጠው ከመጻፋቸውም በላይ፣ ‹‹በሲኖዶስ የተወገዘ በመንግሥት ሳይሆን በሲኖዶስ ነው መፈታት ያለበት›› እያሉ ይናገሩ ስለ ነበር ንጉሡ በዚህ እጅግ አልተደሰተም ነበር፡፡ ንጉሡ በአትናቴዎስ ላይ መቆጣቱን የሚያውቁ አርዮሳውያንም አትናቴዎስን በልዩ ልዩ የሐሰት ክሶች ይከሷቸው ጀመር፡፡ ከሐሰት ክሶቹም አንዱ ‹‹ከግብጽ ወደ ቊስጥንጥንያ ስንዴ እንዳይላክ አትናቴዎስ ከልክለዋል›› የሚል ሲሆን፣ ሌላው ደግሞ ‹‹በንጉሡ ላይ ለሸፈቱ ሽፍቶች አትናቴዎስ ስንቅና መሣሪያ ያቀብሉ ነበር›› የሚል ነበር፡፡ ሌሎችም ሞራልንና ወንጀልን የሚመለከቱ የሐሰት ክሶችም ቀርበውባቸዋል፡፡

ሆኖም ግን ንጉሠ ነገሥቱ ቈስጠንጢኖስ አትናቴዎስን ለመበቀል ጥሩ አጋጣሚ ስላገኘ በአትናቴዎስ ላይ የቀረቡት ክሶች በጉባኤ እንዲታዩ ትእዛዝ አስተላለፈ፡፡ ጉባኤውም በ፫፻፴፭ ዓ.ም በጢሮስ ከተማ ተካሔደ፡፡ አትናቴዎስም ማንንም ሳይፈሩ ወደ ጉባኤው ሔዱ፡፡ ጉባኤው እንደ ተጀመረም በአትናቴዎስ ላይ የቀረቡትን ክሶች መስማት ጀመረ፡፡ በዚህ ጉባኤ አብዛኞቹ አርዮሳውያን ስለነበሩ፣ አትናቴዎስ በተከሰሱባቸው ክሶች ሁሉ ነጻ ቢሆኑም በግፍ ወደ ግዞት ቦታ እንዲሔዱ ተፈርዶባቸው ትሬቭ (ፈረንሳይ ውስጥ የምትገኝ) ወደምትባል ቦታ ተጋዙ፡፡

፬. የአርዮስ ድንገተኛ ሞት

ፓትርያርክ አትናቴዎስን በግፍ ወደ ግዞት ቦታ እንዲሔዱ የፈረደባቸው የቂሣርያው ጉባኤ፣ ‹‹አርዮስ ተጸጽቶ ከክሕደቱ መመለሱን የሚያመለክት መጣጥፍ አቅርቧል›› በሚል ሰበብ አርዮስን ከግዝቱ ፈቶ ነጻ አወጣው፡፡ አትናቴዎስ ወደ ግዞት በመላካቸው አርዮሳውያን እና መንፈቀ አርዮሳውያን ምቹ ጊዜ አግኝተው ስለ ነበር አርዮስን ወደ ሀገሩ ወደ እስክንድርያ ለመመለስ ይሯሯጡ ጀመር፡፡ የአርዮስ ነጻ መውጣትም ንጉሡ በሚኖርበት በቊስጥንጥንያ በይፋ እንዲከበር በማሰብ አርዮስ በወዳጆቹና በደጋፊዎቹ ታጅቦ ወደ ቊስጥንጥንያ እንዲሔድ አደረጉ፡፡ በዚያም በሐዋርያት ቤተ ክርስቲያን ከቊስጥንጥንያው ሊቀ ጳጳስ ጋር እንዲቀድስና ወደ ክርስቲያን አንድነት መግባቱ በይፋ እንዲታወጅ ዝግጅት ተደርጎ ሳለ ሆዱን ሕመም ተሰምቶት ወደ መጸዳጃ ቤት ሔዶ በዚያው ቀረ፡፡ አርዮስ ስለ ዘገየባቸው ደጋፊዎቹ ሔደው ቢያዩት ሆድ ዕቃው ተዘርግፎ ሞቶ አገኙት፡፡ በዚህም ‹‹የእግዚአብሔር ቊጣና መቅሠፍት በአርዮስ ላይ ተገለጠ›› ተብሎ በብዙ ሰዎች ዘንድ ታመነ፡፡ ሆኖም በአርዮስ ሞት የተበሳጩ አንዳንድ የአርዮስ ደጋፊዎች የእግዚአብሔርን ፍርድ አይተው ከክሕደታቸው በመመለስ ፈንታ ‹‹አርዮስ የሞተው በመድኃኒት ተመርዞ ነው›› ብለው ማውራትና ማስወራት ጀመሩ፡፡

፭. አርዮሳውያን እና መንፈቀ አርዮሳውያን የኒቅያን ውሳኔ ለመቀልበስ ያደረጉት ዘመቻ

የእስክንድርያው ፓትርያርክ ታላቁ አትናቴዎስ የክርስቶስን አምላክነት የካደውን የአርዮስን ሞት የሰሙት ያለ ፍትሕ በግፍ በተጋዙበት ሀገር ሳሉ ነው፡፡ ታላቁ ቈስጠንጢኖስም ብዙ ጊዜ በሕይወት አልቆየም፡፡ ንጉሡ ታሞ ግንቦት ፳፩ ቀን ፫፻፴፯ ዓ.ም ከዚህ ዓለም በሞት ተለየ፡፡ ሦስቱ ልጆቹ ማለት ዳግማዊ ቈስጠንጢኖስ፣ ቆንስጣንዲያስ እና ቁንስጣ መንግሥቱን ለሦስት ተከፋፈሉት፡፡ ከሦስቱ ልጆቹ መካከል የምዕራቡን ክፍል ይገዙ የነበሩት ሁለቱ ማለት ኦርቶዶክሳውያኑ ዳግማዊ ቈስጠንጢኖስ እና ቁንስጣ ሲሆኑ፣ መናገሻ ከተማውን ቊስጥንጥንያ ላይ አድርጎ የምሥራቁን ክፍል ይገዛ የነበረው ደግሞ አርዮሳዊው ቆንስጣንዲያስ ነበር፡፡ ትልቁ ቈስጠንጢኖስ ከሞተ ከአንድ ዓመት በኋላ ኅዳር ፳፫ ቀን ፫፻፴፰ ዓ.ም አትናቴዎስ ተግዘውበት የነበረበትን ሀገር ይገዛ የነበረው ዳግማዊ ቈስጠንጢኖስ አትናቴዎስን ከተጋዙበት እንዲመለሱ አደረገ፡፡ አትናቴዎስ ከግዞት ወደ እስክንድርያ ሲመለሱም ሕዝቡ እጅግ ተደስቶ በዕልልታና በሆታ ተቀበላቸው፡፡ አቀባበሉም ለአንድ ተወዳጅ ንጉሠ ነገሥት የሚደረግ አቀባበል ዓይነት ነበር፡፡

ፓትርያርክ አቡነ አትናቴዎስ በአርዮሳውያንና በመንፈቀ አርዮሳውያን ነገሥታት ያለ ፍትሕ በግፍ ለአምስት ጊዜያት ያህል ሕይወታቸውን በግዞት ነው ያሳለፉት፡፡ በእስክንድርያ መንበረ ጵጵስና በፓትርያርክነት የቆዩት ለ፵፮ ዓመታት ቢሆንም፣ ፲፭ቱን ዓመታት ያሳለፉት በግዞትና በስደት ነበር፡፡ ፓትርያርክ አትናቴዎስ ከዕድሜያቸው አብዛኛውን ዘመን ያሳለፉት ከአርዮሳውያን ጋር በመታገልና በመዋጋት ነበር፡፡ አንድ ታሪክ ጸሓፊም ‹‹ሙሴ ለእስራኤል ሕዝብ ምድረ ርስትን ለማውረስ የጀመረውን ተግባር ከግቡ ሳያደርስ እንደ ተጠራ፣ አትናቴዎስም ከአርዮሳውያን ጋር ያደርጉ የነበረውን ትግል ሳይጨርሱ ነው ለሞት የተጠሩት፤›› በማለት የፓትርያርክ አትናቴዎስን ተጋድሎና የአገልግሎት ፍጻሜ ያስረዳሉ፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር፡፡

ማስገንዘቢያ

የተወደዳችሁ የማኅበረ ቅዱሳን ድረ ገጽ ተከታታዮች! ‹‹አርዮስ እና መንፈቀ አርዮሳውያን በጥንት ቤተ ክርስቲያን ላይ ያደረሱት ችግር›› በሚል ርእስ በቀሲስ ዶ/ር ምክረ ሥላሴ ገብረ አማኑኤል የተዘጋጀው ይህ ጥናታዊ ጽሑፍ፣ በግንቦት ወር ፳፻፰ ዓ.ም ለማኅበረ ቅዱሳን ጥናትና ምርምር ማእከል መቅረቡን፤ እንደዚሁም በኅዳር ወር ፳፻፱ ዓ.ም በታተመው ፳፬ኛ ዓመት ቍጥር ፯ ሐመር መጽሔት፣ ከገጽ ፰ – ፲፬ ለንባብ መብቃቱን ለማስገንዘብ እንወዳለን፡፡

አርዮስ እና መንፈቀ አርዮሳውያን በቤተ ክርስቲያን ላይ ያደረሱት ችግር – ክፍል ሦስት

በቀሲስ ዶ/ር ምክረ ሥላሴ ገብረ አማኑኤል

ኅዳር ፲፩ ቀን ፳፻፲ ዓ.ም

በስብሰባው ላይ አርዮሳውያን በኒቆምዲያው ኤጲስቆጶስ አውሳብዮስ አማካይነት የሃይማኖት መግለጫ (confession of faith) አቀረቡ፡፡ የተሰበሰቡት አባቶች አብዛኛዎቹ በጩኸትና በቁጣ ድምፅ የእምነት መግለጫውን ተቃወሙት፡፡ ጽሑፉንም በእሳት አቃጠሉት፡፡ ከዚህ በኋላ የቂሣርያው አውሳብዮስ በሀገረ ስብከቱ በጥምቀት ጊዜ የሚጠመቁ ሁሉ የሚያነቡት የሃይማኖት ጸሎት (መግለጫ) አቀረበ፡፡ ይህ መግለጫ ከኒቅያው የሃይማኖት ጸሎት ጋር ተመሳሳይነት ስለነበረው ለጊዜው ተቀባይነትን አግኝቶ የነበረ ቢሆንም ነገር ግን ‹‹ዋሕደ ባሕርይ ምስለ አብ›› ወይም ‹‹ዘዋሕድ ምስለ አብ በመለኮቱ›› (omoousios) የሚለውን አገላለጽ ባለማካተቱ ጠንከር ባሉ ኦርቶዶክሳውያን ዘንድ ተቀባይነት አላገኘም፡፡ በስብሰባው ወቅት አርዮስ ትክክለኛ የእምነት አቋሙን እንዲገልጽ ተጠይቆ ‹‹ሀሎ አመ ኢሀሎ ወልድወልድ ያልነበረበት ጊዜ ነበረ፡፡ አብ ወልድን ከምንም (እምኀበ አልቦ) ፈጠረውና የእግዚአብሔር ልጅ አደረገው፡፡ አብም ወልድን ከፈጠረው በኋላ ሥልጣንን ሰጥቶት ዓለሙን ሁሉ እንዲፈጥር አደረገው፤›› ብሎ ሲናገር አብዛኞቹ የጉባኤው አባላት በጌታችን ላይ የተናገረውን የጽርፈት (የስድብ) ቃል ላለመስማት ጆሯቸውን ሸፈኑ ይባላል፡፡

በክርክሩ ጊዜ ‹‹ወልደ አብ ኢየሱስ ክርስቶስ መድኃኒት ነው፤ አዳኛችን ነው፡፡ አዳኝ መሆኑን ካመንን የባሕርይ አምላክነቱን ማመን አለብን፡፡ የሚያድን እግዚአብሔር ብቻ መሆኑን ቅዱሳት መጻሕፍት ይመሰክራሉ፡፡ በቅዱሳት መጻሕፍት ምስክርነት የወልድ አምላክነት ከሰው ልጆች የመዳን ምሥጢር ጋር የተያያዘ ነው፡፡ ወልድ የባሕርይ አምላክ ካልሆነ ግን እኛም አልዳንም ማለት ነው፡፡ በእርሱ መዳናችንን ካመንን ግን ያዳነን እሱ አምላክ መሆኑን ማወቅና ማመን አለብን፡፡ ፍጡር ፍጡራንን ማዳን አይችልምና፤›› ብሎ አትናቴዎስ አርዮስን ሲጠይቀውና ሲከራከረው የሰሙት አብዛኞቹ የጉባኤው አባላት በደስታ ተዋጡ፡፡ አርዮስ ‹‹ወልድ በምድር ሕይወቱ ታላቅ ትሕትናንና ተጋድሎን በማሳየቱ በባሕርይ ሳይሆን በጸጋ የአምላክነትን ክብር ስላገኘ ስግደት ይገባዋል፤›› ይላል፡፡ አትናቴዎስም ‹‹ክርስቶስ ከባሕርይ አባቱ ከአብ ጋር አንድ ነው፡፡ ነገር ግን ወልድ ፍጡር ነውካልን ለእርሱ የአምልኮ ስግደት ማቅረብ አማልኮ ባዕድ ነዋ!›› ሲለው አርዮስ መልስ አላገኘም፡፡

ከአርዮሳውያን ጋር የከረረ ክርክር የተደረገው በሁለት ጉዳዮች ነበር፤ እነዚህም ፩ኛ አርዮስ ወልድን ‹‹ፍጡር ነው›› ለማለት ‹‹ሀሎ አመ ኢሀሎ ወልድወልድ ያልነበረበት ጊዜ ነበር›› ሲል ኦርቶዶክሳውያን ወልድን ዘለዓለማዊ ነው ለማለት ‹‹አልቦ አመ ኢሀሎ ወልድወልድ ያልኖረበት ጊዜ የለም›› ብለው የአርዮሳውያንን ክሕደት አጥላልተው አወገዙት፡፡ ፪ኛ አርዮስና ደጋፊዎቹ ‹‹ወልድ በባሕርዩ (በመለኮ) ከአብ ጋር አንድ አይደለም፤›› የሚሉትን ጉባኤው ካወገዘ በኋላ፣ ኦርቶዶክሳውያን ወልድን “Omo-ousios” (ዋሕደ ባሕርይ ምስለ አብ ወይም ዘዋሕድ ምስለ አብ በመለኮቱወልድ ከአብ ጋር በባሕርዩ በመለኮቱ አንድ ነው)›› አሉ፡፡ የአርዮስ ደጋፊዎች የነበሩትም የአርዮስን የክሕደት ትምህርት ያልተቀበሉ በማስመሰልና ኦርቶዶክሳውያን በመምሰል “Omoi-ousios” (የወልድ ባሕርይ ከአብ ባሕርይ ጋር ተመሳሳይ ነው) ብለው ሐሳብ አቀረቡ፡፡ የእነዚህንም ሐሳብ ጉባኤው ፈጽሞ አልተቀበለውም ነበር፡፡ እነዚህም መንፈቀ አርዮሳውያን (Semi-Arians) ተብለው ተወግዙ፡፡

“Omo-ousios” (ዋሕደ ባሕርይ ምስለ አብ በመለኮቱ ወይም ዘዋሕድ ምስለ አብ በመለኮቱ) የሚለውን ሐረግ አርዮሳውያንና መንፈቀ አርዮሳውያን አጥብቀው ተቃውመውት ነበር፡፡ ከዚህ በኋላ የኮርዶቫው ኤጲስቆጶስ ኦስዮስና የእስክንድርያው ሊቀ ዲያቆን አትናቴዎስ ባቀረቡት ሐሳብ መሠረት “Omo-ousios” (ዋሕደ ባሕርይ ምስለ አብ በመለኮቱ ወይም ዘዋሕድ ምስለ አብ በመለኮቱ ወይም ዘዕሩይ ምስለ አብ በመለኮቱ) የሚለው ሐረግ ተጨምሮበት፣ የወልደ አብ ኢየሱስ ክርስቶስን አምላክነት የሚያረጋግጥ ፯ አናቅጽ ያሉት ቃለ ሃይማኖት (ጸሎተ ሃይማኖት) ተዘጋጅቶ ቀረበና የጉባኤው አባቶች ሁሉ ፈረሙበት፡፡ ከጸሎተ ሃይማኖት ፯ አንቀጾች መካከል የመጀመሪያው አንቀጽ የሚከተለው ነው፤

‹‹ሁሉን በያዘ፣ ሰማይንና ምድርን፣ የሚታየውንና የማይታየውን በፈጠረ በአንድ አምላክ በእግዚአብሔር አብ እናምናለን፡፡ ዓለም ሳይፈጠር ከእርሱ በተወለደ፣ የአብ አንድ ልጁ በሚሆን በአንድ ጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ እናምናለን፡፡ ከብርሃን የተገኘ ብርሃን፣ ከእውነተኛ አምላክ የተገኘ አምላክ፣ የተወለደ እንጂ ያልተፈጠረ፣ በመለኮቱ ከአብ ጋር አንድ የሚሆን፣ ሁሉ በእርሱ የሆነ (የተፈጠረ) በሰማይም  በምድርም፡፡ ስለ እኛ ስለ ሰዎች እኛን ለማዳን ከሰማይ የወረደ፤ ሥጋ የሆነ፡፡ ሰው ሆኖም ስለ እኛ የታመመ፡፡ በሦስተኛውም ቀን ከሙታን ተለይቶ የተነሣ፡፡ ወደ ሰማይ የዐረገ፡፡ በሕያዋንና በሙታን ይፈርድ ዘንድ ዳግመኛ የሚመጣ፡፡ በመንፈስ ቅዱስም እናምናለን፡፡››

በመጨረሻም ከዚህ በላይ እንደተገለጠው ጉባኤው የወልድን አምላክነትና በባሕርይ (በመለኮት) ከአብ ጋር አንድ መሆኑን በውል አረጋግጦና ወስኖ አርዮስንና መንፈቀ አርዮሳውያንን አውግዞ ከማኅበረ ክርስቲያን ለይቷቸዋል፡፡ አርዮስና የተወገዙት አርዮሳውያን ሁሉ በንጉሠ ነገሥቱ እንዲጋዙ ተደርገዋል፡፡

፪. በኢትዮጵያ ጸሎተ ሃይማኖት በተለይ የ‹‹Omoousios tw patri›› ትርጕም

‹‹Omoousios tw patri›› የሚለው የግሪኩ ሐረግ በግእዝ የተተረጐመው ‹‹ዘዕሩይ ምስለ አብ በመለኮቱ›› ተብሎ ሲሆን፣ በአማርኛው ነጠላ ትርጕም ግን ‹‹በመለኮቱ ከአብ ጋር የሚተካከል›› ተብሎ ነው የተተረጐመው፡፡ የግሪኩ ቃል የሚገልጠው ‹‹በመለኮቱ ከአብ ጋር አንድ የሚሆን›› ማለትን ነው፡፡ ‹‹የሚተካከል›› የሚለው ቃል ግን የግሪኩንም ሆነ የግእዙን ሐረግ አይወክልም፡፡ እንዳውም ‹‹መተካከል›› የሚለው ቃል መመሳሰልን ወይም ምንታዌን (ሁለትዮሽን) ነው እንጂ አንድነትን አይገልጥም፡፡ ይህ ደግሞ የመንፈቀ አርዮሳውያንን ሐሳብ ስለሚመስል የኢትዮጵያ ሊቃውንት የአማርኛውን ትርጕም እንደገና ሊያስቡበት ይገባል፡፡ በእርግጥ ‹‹ዐረየ›› ማለት ‹‹ተካከለ ማለት ነው፡፡ አለቃ ኪዳነ ወልድ እንደሚሉት በሌላ መንገድ ግን ‹‹ዐረየ›› የሚለው ግስ ‹አንድ ሆነ የሚል ትርጕም አለው፡፡ ለምሳሌ ‹‹ወምስለ ብሉይ ኢይዔሪ›› የሚለው ኃይለ ቃል ‹‹ከአሮጌው ጋር አንድ አይሆንም›› ተብሎ ይተረጐማል፡፡ እንደዚሁም በመዝሙረ ዳዊት ‹‹እስመ ተማከሩ ኅቡረ ወዐረዩ›› የሚለው ኃይለ ቃል ‹‹አንድ ሆነው በአንድነት ተማክረዋልና›› የሚል ትርጕም አለው፡፡

ስለዚህ ‹‹ዘዕሩይ ምስለ አብ በመለኮቱ›› የሚለው ሐረግ ‹‹በመለኮቱ ከአብ ጋር አንድ የሚሆን›› ተብሎ መተርጐም አለበት፡፡ ‹‹በመለኮቱ ከአብ ጋር የሚተካከል›› ከተባለ ግን ይህ መንፈቀ አርዮሳዊ አነጋገር ይሆናል፡፡ ምክንያቱም መንፈቀ አርዮሳውያን ‹‹ወልድ ከአብ ጋር በመለኮት ይመሳሰላል እንጂ አንድ አይደለም›ነው የሚሉት፡፡ ሃይማኖተ አበውን የተረጐሙ አባቶችም ‹‹ዐረየ›› ወይም ‹‹ዕሩይ›› የሚለውን ቃል ‹አንድ የሆነ› ብለው ነው የተረጐሙት፡፡ ለምሳሌ ‹‹ወውእቱ ዕሩይ ምስሌሁ በመለኮት›› የሚለውን ሲተረጕሙ ‹‹እርሱም በመለኮት ከአብ ጋር አንድ ነው›› ብለውታል፡፡ እንደዚሁም ‹‹ነአምን በሥላሴ ዕሩይ በመለኮት›ሲተረጐም ‹‹በመለኮት አንድ በሚሆኑ በሥላሴ እናምናለን›› ተብሎ ነው፡፡ በተመሳሳይ መልኩ ‹‹ወበከመ ወልድ ዕሩይ ምስለ አብ በመለኮቱ›› የሚለው ኃይለ ቃል ትርጕም ‹‹ወልድ በባሕርዩ ከአብ ጋር አንድ እንደ ሆነ›› ማለት ነው፡፡ እንደዚሁም የቅዳሴው የአንድምታ ትርጕም ‹‹ዘዕሩይ ምስለ አብ በመለኮቱ›› የሚለውን ኃይለ ቃል የተረጐሙት ሊቅ ‹‹ከአብ ጋር በመለኮቱ አንድ የሚሆን›› በማለት ነው፡፡

እንግዲህ ‹‹ዘዕሩይ ምስለ አብ በመለኮቱ›› የሚለው ኃይለ ቃል ‹‹ከአብ ጋር በመለኮቱ አንድ የሚሆን›› ተብሎ ከተተረጐመ ምንም የእምነት ጕድለት ወይም ስሕተት አይኖረውም፡፡ ብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስም ይህን ኃይለ ቃል ‹‹ዘዕሩይየሚተካከል›› ተብሎ እንዳይተረጐም ብለው ‹‹ዘዋሕድ ምስለ አብ በመለኮቱ›› በማለት አርመዉታል፡፡ ትርጕሙ ጥሩ ነው፤ ነገር ግን ‹‹ዘዕሩይ›› የሚለው ቃል የወጣበት ‹‹ዐረየ›› የሚለው ግስ ከላይ እንደተገለጸው ‹‹አንድ ሆነ›› የሚል ትርጕም ስላለው ‹‹ዘዕሩይ›› የሚለው ግእዙ ባይለወጥ ጥሩ ይመስለኛል፡፡ መስተካከል ያለበት ግእዙ ሳይሆን የአማርኛው ትርጕም ነው፡፡ ብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስም በዋናው ጸሎተ ሃይማኖት ላይ ‹‹ዘዕሩይ›› የሚለውን ቃል ሳያርሙ እንዳለ አስቀምጠውታል፡፡

ይቆየን

አርዮስ እና መንፈቀ አርዮሳውያን በቤተ ክርስቲያን ላይ ያደረሱት ችግር – ክፍል ሁለት

በቀሲስ ዶ/ር ምክረ ሥላሴ ገብረ አማኑኤል

ኅዳር ፲ ቀን ፳፻፲ ዓ.ም

ተፍጻሜተ ሰማዕት ቅዱስ ጴጥሮስ በሰማዕትነት ከሞተ በኋላ በ፫፻፲፪ ዓ.ም አርኬላዎስ የእስክንድርያ ሊቀ ጳጳስ (ፓትርያርክ) ሆኖ በምትኩ ተሾመ፡፡ በዚህ ጊዜ አርዮስ ከክሕደቱ የተጸጸተ መስሎ ወደ ፓትርያርክ አርኬላዎስ ቀረበ፡፡ የአርዮስ ደጋፊዎችም ፓትርያርኩ ከውግዘቱ እንዲፈታው በአማላጅነት በመቅረባቸው፣ አዲሱ ፓትርያርክ የቀድሞውን ፓትርያርክ የተፍጻሜተ ሰማዕት ጴጥሮስን ትእዛዝና አደራ በመዘንጋት አርዮስን ከውግዘቱ ፈታው፡፡ ይባስ ብሎም የቅስና ማዕረግ ሰጥቶ ሾመው፡፡ ሆኖም አርኬላዎስ አንድ ዓመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ በሞት ተለየ፡፡ የሰማዕቱን የቅዱስ ጴጥሮስን ቃል ባለመጠበቁ የመቅሠፍት ሞት ነው የሞተው ይባላል፡፡

በአርኬላዎስም ምትክ ስመ ጥሩውና በዘመኑ ሁሉ ለቤተ ክርስቲያን እጅግ የተጋደለ አባት እለእስክንድሮስ (፫፻፲፪ – ፫፻፳፰ ዓ.ም) በካህናትና ምእመናን ተመርጦ ተሾመ፡፡ እለእስክንድሮስ ወዲያውኑ የአርዮስን የክሕደት ትምህርት በይፋ እየተቃወመ አርዮስን በጥብቅ አወገዘ፡፡ የአርዮስ ደጋፊዎች አርዮስን ከፓትርያርኩ ጋር ለማስማማት አጥብቀው ቢሞክሩም ፓትርያርክ እለእስክንድሮስ አልበገርም አለ፡፡ አርዮስ ተጸጽቶ፣ ስሕተቱን ለጌታ ለኢየሱስ ክርስቶስ ተናዝዞ ከተመለሰ ጌታ ምልክት ስለሚሰጠው ያንጊዜ እርሱ እንደሚቀበለው ነግሮ አሰናበታቸው፡፡ አርዮስ በበኩሉ በድፍረት የክሕደት ትምህርቱን ማሠራጨት ቀጠለ፡፡ ሕዝቡም ትምህርቱን በቀላሉ እንዲቀበለው የክሕደት ትምህርቱን በግጥምና በስድ ንባብ እያዘጋጀ ያሠራጭ ጀመር፡፡ ያም የግጥም መጣጥፍ ‹ታሊያ› ይባል ነበር፡፡ ትርጕሙም ማዕድ ማለት ነው፡፡ ሕዝብ ደግሞ ግጥም ማንበብ ስለሚወድና በግጥም መልክ ያነበበውን ስለማይዘነጋው የአርዮስን ትምህርት ለመቀበል ደርሶ ነበር፡፡

ሊቀ ጳጳሱ እለእስክንድሮስም ምእመናን ከአርዮስ የክሕደት ትምህርት እንዲጠበቁ እየዞረ በማስጠንቀቅ ያስተምር ጀመር፡፡ ፓትርያርኩም በ፫፻፲፰ ዓ.ም በእስክንድርያና በአካባቢዋ የሚገኙትን ጳጳሳትና ካህናት ሰብስቦ አርዮስንና ተከታዮቹን በጉባኤ አወገዛቸው፡፡ አርዮስ ግን ከስሕተቱ ባለመመለሱ ፓትርያርክ እለእስክንድሮስ በ፫፻፳፩ ዓ.ም አንድ መቶ የሚሆኑ የእስክንድርያንና የሊብያን ኤጲስቆጶሳት ሰብስቦ ጉባኤ በማድረግ የአርዮስን ክሕደት በዝርዝር አስረዳቸው፡፡ ሲኖዶሱም ጉዳዩን በሚገባ ከመረመረ በኋላ አርዮስን በአንድ ድምፅ አወገዘው፡፡ አርዮስም በበኩሉ እየዞረ ‹‹እለእስክንድሮስ ሰባልዮሳዊ ነውየሰባልዮስን የክሕደት ትምህርት ያስተምራል›› እያለ የሊቀ ጳጳሱን የእለእስክንድሮስን ስም ማጥፋት ጀመረ፡፡ በመሠረቱ ከሰባልዮስ ትምህርት ጋር የሚቀራረበው ‹‹ወልድ ፍጡር ነው›› (ሎቱ ስብሐት) የሚለው የአርዮስ ትምህርት ነው እንጂ ‹‹ወልድ የባሕርይ አምላክ ነውከአብም ጋር በባሕርይ አንድ ነው (ዘዋሕድ ምስለ አብ በመለኮቱ)›› የሚለው ትምህርት አይደለም፡፡

የአርዮስ ትምህርት በእስክንድርያና በመላዋ ግብጽ ብዙም ተቀባይነት ባለማግኘቱ ወደ መካከለኛው ምሥራቅ ወደ ሦርያና አንጾኪያ እየዞረ ቀድሞ ጓደኞቹ ለነበሩትና የእርሱን የክሕደት ትምህርት ለሚደግፉ ጳጳሳት ሁሉ ፓትርያርክ እለእስክንድሮስ ያለ አግባብ እንዳወገዘውና እንዳባረረው ከመንገሩም በላይ ‹‹እለእስክንድሮስ የሰባልዮስን ትምህርት ያስተምራል›› እያለ ስሙን ያጠፋ ጀመር፡፡ በዚያ የነበሩት የአርዮስ የትምህርት ቤት ጓደኞች ጳጳሳት ለምሳሌ የኒቆምዲያው ኤጲስቆጶስ አውሳብዮስና የቂሣርያው ኤጲስቆጶስ አውሳብዮስ የአርዮስን ሐሳብ ይደግፉ ስለነበር አርዮስ የክሕደት ትምህርቱን እየዞረ እንዲያስተምር ፈቀዱለት፡፡ ከዚህም በላይ ደፍረው ፓትርያርክ እለእስክንድሮስ አርዮስን እንዲቀበለው ጠየቁለት፡፡ ፓትርያርክ እለእስክንድሮስ ግን ይህንን ጥያቄ አልተቀበለውም ነበር፡፡ እንደውም እለእስክንድሮስ በበኩሉ የአርዮስን የክሕደት ትምህርት በመቃወምና በማውገዝ ብዙ ደብዳቤዎችን በመላዋ ግብጽና በመካከለኛው ምሥራቅ ለሚገኙ ሊቃነ ጳጳሳትና ኤጲስ ቆጶሳት ያስተላልፍ ጀመር፡፡

በአርዮስ ደጋፊ በኒቆምዲያ ኤጲስቆጶስ አውሳብዮስ አሳሳቢነትና ሰብሳቢነት በ፫፻፳፪ እና ፫፻፳፫ ዓ.ም በተከታታይ ሁለት ጉባኤያትን አድርገው የአርዮስ ትምህርት ትክክለኛ መሆኑን በማብራራትና ‹‹የአርዮስ ሃይማኖት ትክክል ስለሆነ መወገዝ አይገባውም›› በማለት የእለእስክንድሮስን ውግዘት በመሻር ለአርዮስ ፈረዱለት፡፡ አርዮስም ወደ እስክንድርያ ተመልሶ ያንኑ የክሕደት ትምህርቱን በስፋት ያስተምር ጀመር፡፡ በአርዮስ ክሕደት ምክንያት የተነሣው ውዝግብ በመላው የክርስትና አህጉር ሁሉ በተለይም በምሥራቁ የሮም ግዛት በመሠራጨቱ ቤተ ክርስቲያንና የሮም ግዛት በሙሉ እጅግ ታወኩ፡፡ ጳጳሳትና መምህራን እርስበርሳቸው ይነታረኩ ጀመር፡፡ በዚህም ሰላም ጠፍቶ በዚያው ወቅት የመላ የሮም ንጉሠ ነገሥት መንግ ሥት ብቸኛ ቄሣር የሆነውን ታላቁን ቈስጠንጢኖስ እጅግ አሳሰበው፡፡ ንጉሠ ነገሥት ቈስጠንጢኖስ በመላ ግዛቱ ሰላም እንዲሰፍን በመሻቱ ውዝግቡን በዲፕሎማሲያዊ መንገድ ለማብረድ መልእክተኞችን ደብዳቤ አስይዞ ወደየጳጳሳቱ ይልክ ጀመር፡፡ በደብዳቤውም የቃላት ጦርነት እንዲያቆሙና በሰላም እንዲኖሩ ይጠይቅ ነበር፡፡

ለዚህም መልእክት ጉዳይ ሽማግሌ የነበረውን በስፔን የኮርዶቫ ጳጳስ ኦስዮስን ወደ እስክንድርያ ደብዳቤ አስይዞ ላከው፡፡ ኦስዮስም በአንድ በኩል ከእለእስክንድሮስና ከግብጽ ኤጲስቆጶሳት ጋር፣ በሌላ በኩል ደግሞ ከአርዮስና ከእርሱ ደጋፊዎች ጋር ተወያይቶ በሁለቱ መካከል የነበረውን ልዩነት በሚገባ ከመረመረ በኋላ ወደ ንጉሠ ነገሥቱ ወደ ቈስጠንጢኖስ ተመልሶ ነገሩ ከባድ የሃይማኖት ጉዳይ ስለሆነ የመላው ሕዝበ ክርስቲያን ጳጳሳት የሚገኙበት ታላቅ ጉባኤ ተጠርቶ ውዝግቡ በጉባኤ ታይቶ ቢወሰን እንደሚሻል ለንጉሠ ነገሥቱ ምክር ሰጠ፡፡ ታላቁ ቈስጠንጢኖስም ምክሩን ተቀብሎ የመላው አብያተ ክርስቲያናት መሪዎች የሚሳተፉበት ዓለም አቀፋዊ ሲኖዶስ እንዲደረግ አዋጅ ነገረ፡፡ ጉባኤውም የቢታንያ አውራጃ ከተማ በሆነችው በኒቅያ እንዲሆን ተወሰነ፡፡ ለጉዞና ለኑሮ የሚያስፈልገው ወጪ ሁሉ ከመንግሥት ካዝና እንዲሆን ንጉሠ ነገሥቱ ትእዛዝ አስተላለፈ፡፡

ስለዚህም ቈስጠንጢኖስ በነገሠ በሃያ ዓመቱ በ፫፻፳፭ ዓ.ም በሮም ግዛት ውስጥ የነበሩት ሊቃነ ጳጳሳት፣ ኤጲስቆጶሳትና ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን እንዲሰበሰቡ ጥሪ አስተላለፈ፡፡ እያንዳንዱ ኤጲስቆጶስ ሁለት ቀሳውስትንና ሦስት ምእመናንን (ሊቃውንትን) ይዞ እንዲመጣ ንጉሡ በፈቀደው መሠረት ብዙ ቀሳውስትና ምእመናን (ሊቃውንት) በጉባኤው ላይ ተገኝተው ነበር፡፡ ለጉባኤው የተሰበሰቡት አባቶችም ፫፻፲፰ ያህሉ ነበር፡፡ በጉባኤው የተሰበሰቡትን አባቶች ቍጥር የቤተ ክርስቲያን ጸሐፊዎች ከፊሎቹ ከፍ፣ ሌሎቹ ደግሞ ዝቅ አድርገው ይጽፋሉ:: ለምሳሌ የቂሣርያው አውሳብዮስ ፪፻፶ ነበሩ ሲል፣ ቴዎዶሬት ደግሞ ፪፻፸ ነበሩ ይላል፡፡ እንደዚሁም ሶቅራጥስ ፫፻፤ ሶዞሜን ደግሞ ፫፻፳ ነበሩ ይላሉ፡፡

በጉባኤው የተሰበሰቡት አባቶች በሕይወታቸው ንጽሕናና ቅድስና መሰል የሌላቸው፣ በሃይማኖታቸውም የሐዋርያትን ፈለግ የተከተሉ ነበሩ፡፡ ከዚህም ሁሉ ጋር በገቢረ ተአምራት ከፍ ያለ ዝና ያላቸው ነበሩ፡፡ በስብሰባውም ላይ ሃያ አርዮሳውያን ኤጲስቆጶሶች፣ የተወሰኑ አርጌንሳውያንና የፍልስፍና ምሁራን ተጠርተው መጥተው ነበር፡፡ የጉባኤው የክብር ፕሬዝዳንት ንጉሠ ነገሥቱ ታላቁ ቈስጠንጢኖስ ሲሆን፣ ጉባኤውን በሊቀ መንበርነት እንዲመሩ የተመረጡት ሦስት ሊቃነ ጳጳሳት ነበሩ፡፡ እነዚህም፡- የእስክንድርያው ሊቀ ጳጳስ አቡነ እለእስክንድሮስ፣ የአንጾኪያው ሊቀ ጳጳስ ኤዎስጣቴዎስ እና የኮርዶቫው (የእስፔኑ) ጳጳስ ኦስዮስ ነበሩ፡፡ ከጉባኤው ተካፋዮች መካከል እጅግ የታወቁ ምሁራን ነበሩ፡፡

ከእነዚህም ጥቂቶቹ እጅግ የተማረ፣ ንግግር ዐዋቂና ለኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሃይማኖት ቀናተኛ የነበረው፣ የእስክንድርያ ቤተ ክርስቲያን ሊቀ ዲያቆን ሆኖ ለሊቀ ጳጳሱ ለእለእስክንድሮስ እንደ አፈ ጉባኤ የነበረው አትናቴዎስና ስመ ጥር የነበረው የቂሣርያው አውሳብዮስ ነበሩ፡፡ እንደዚሁም በዘመነ ስደት ጊዜ ለሃይማኖታቸው ብዙ ሥቃይ የተቀበሉ፣ ዓይናቸው የጠፋ፣ እጅ ወይም እግራቸው የተቆረጠ በቅድስናቸው የታወቁ አባቶችም ነበሩ፡፡ ከዚህም ሌላ በምንኵስና እና በብሕትውና ኑሯቸው እጅግ የታወቁ፣ የዛፍ ሥርና ቅጠል ብቻ በመብላት ይኖሩ የነበሩ፣ ተአምራትን በማድረግ በክርስቲያኖች ዘንድ እጅግ የተከበሩ አባቶች ነበሩ፡፡

ጉባኤው በአብዛኛው የተካሔደው በኒቅያ ከተማ በምትገኘው በእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ቤተ ክርስቲያን ሲሆን፣ አንዳንድ ጊዜ ደግሞ እዚያው ኒቅያ በሚገኘው በንጉሠ ነገሥቱ ቤተ መንግሥት አዳራሽ ይካሔድ እንደነበር ይነገራል፡፡ ጉባኤውም በሦስት ቡድን የተከፈለ ነበር፤ ይኸውም የመጀመሪያው የኦርቶዶክሳውያን፣ ሁለተኛው የአርዮሳውያን፣ ሦስተኛው ደግሞ የመንፈቀ አርዮሳውያን ቡድን ሲሆን፣ በመጀመሪያው ቡድን የነበሩት ኦርቶዶክሳውያን መሪዎችም የእስክንድርያው ሊቀ ጳጳስ እለእስክንድሮስ፣ ሊቀ ዲያቆኑ አትናቴዎስ፣ የአንጾኪያው ሊቀ ጳጳስ ኤዎስጣቴዎስ፣ የኮርዶቫው (የእስፔኑ) ኤጲስቆጶስ ኦስዮስ፣ የአንኪራው (ዕንቆራው) ኤጲስቆጶስ ማርሴሎስ ወዘተ. ነበሩ፡፡

ከእነዚህም ሁሉ በክርክሩ ወቅት ጠንካራና ከባድ ክርክር ይከራከር የነበረውና፣ ለተቃዋሚዎቹ አፍ የሚያስይዝ ምላሽ ይሰጥ የነበረው የእስክንድርያው ሊቀ ዲያቆን አትናቴዎስ ነበር፡፡ በሁለተኛው ቡድን የነበሩትም አርዮስና የንጉሡ ወዳጅ የነበረው የኒቆምዲያው ኤጲስቆጶስ አውሳብዮስ፣ የኒቅያው ኤጲስቆጶስ ቴኦግኒስ፣ የኬልቄዶን ኤጲስቆጰስ ማሪስና የኤፌሶን ኤጲስቆጶስ ሜኖፋንቱስ ነበሩ፡፡ አርዮስ ግን ተከሳሽ ስለነበረ በየጊዜው በጉባኤው እየተጠራ መልስ ይሰጥ ነበር እንጂ የሲኖዶሱ ተካፋይ አልነበረም፡፡ ሦስተኛው ቡድን የመንፈቀ አርዮሳውያን (የመሀል ሰፋሪዎች) ቡድን ሲሆን፣ የእነርሱ ወኪልም የታወቀው የቤተ ክርስቲያን ታሪክ ጸሐፊ የቂሣርያው ኤጲስቆጶስ አውሳብዮስ ነበር፡፡ ይህ ሰው መንፈቀ አርዮሳዊ ሆኖ ከቆየ በኋላ በመጨረሻ ወደ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሃይማኖት ተመልሷል፡፡

ይቆየን

አርዮስ እና መንፈቀ አርዮሳውያን በቤተ ክርስቲያን ላይ ያደረሱት ችግር – ክፍል አንድ

በቀሲስ ዶ/ር ምክረ ሥላሴ ገብረ አማኑኤል

ኅዳር ፱ ቀን ፳፻፲ ዓ.ም

በመጀመሪያው አራት መቶ ዓመታት ውስጥ ቤተ ክርስቲያን በብዙ አቅጣጫ የተለያዩ ችግሮች ደርሰውባት እጅግ ስትሠቃይ ቆይታለች፡፡ በቤተ ክርስቲያን ላይ የደረሱት ችግሮችም ከሁለት አቅጣጫዎች የመጡ ነበሩ፤ አንደኛው ከቤተ ክርስቲያን ውጭ ሲሆን ሁለተኛው ከዚያው ከቤተ ክርስቲያን ውስጥ የተነሡ ችግሮች ነበሩ፡፡ በመጀመሪያው አብዛኛውን ጊዜ ችግር የተነሣው ከአሕዛብ ነገሥታት ሲሆን፣

፩ኛ/ የሮም መንግሥት ገዢዎችና በክፍላተ ሀገሩ የነበሩት የእነርሱ ወኪሎች እነሱ ያመልኩአቸው የነበሩትን ጣዖታት ክርስቲያኖች ስለማይቀበሉና ጨርሰውም ስለሚያወግዙ፤

፪ኛ/ አሕዛብ ያደርጉት እንደነበረው ክርስቲያኖች ለሮም ነገሥታት የአምልኮ ክብር ስለማይሰጡ፣ በቤተ ክርስቲያን ላይና በክርስቲያኖች ላይ በየጊዜው ስደት ታውጆ ክርስቲያኖች ሲሠቃዩ ኖረዋል፡፡

፫ኛ/ የጣዖታት ካህናትና የጣዖታት ምስል ሠራተኞች በክርስትና ሃይማኖት መስፋፋት ምክንያት የጣዖት አምልኮ እጅግ ስለቀነሰና በአንዳንድ ቦታዎችም አምልኮ ጣዖት ጨርሶ ስለቀረ ኑሮአቸው በመቃወሱ፣ ከአሕዛብ ነገሥታት ጋር በመወገን በክርስቲያኖች ላይ ልዩ ልዩ ችግሮች ይፈጥሩ ነበር፡፡

በቤተ ክርስቲያን ላይ ከውስጥ የተነሡ ችግሮችም እጅግ የበዙና የከፉም ነበሩ፡፡ ከመጀመሪያ ጀምሮ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ብዙ መለያየትና መከፋፈል ስለታየ አንዲት ቤተ ክርስቲያን ለብዙ ክፍሎች ትከፋፈል ይሆናል ተብሎ ተፈርቶ ነበር፡፡ በግብረ ሐዋርያት ላይ እንደተጠቀሰው ከአይሁድ ወገን ወደ ክርስትና በገቡትና ከአሕዛብ ወገን ወደ ክርስትና በገቡት ክርስቲያኖች መካከል የታዩት ብዙ ልዩነ ቶች ነበሩ፡፡ ይህ ችግር በ፶፩ ዓ.ም በተደረገው በሐዋርያት ጉባኤ በተሰጠው ውሳኔ መፍትሔ አግኝቶ በመጠኑም ቢሆን ችግሩ ተወግዶ ነበር፡፡ በኋላ ደግሞ በሁለተኛውና በሦስተኛው መቶ ዓመት ላይ ተነሥተው የነበሩት ዶኬቲኮች፣ ግኖስቲኮችና የሰባልዮስና የጳውሎስ ሳምሳጢ ተከታዮች የነበሩ መናፍቃን ተነሥተው በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ብዙ የከፋ ብጥብጥ ተነሥቶ ነበር፡፡

ይህም ችግር በየክፍላተ ሀገሩ በተጠሩ ሲኖዶሶች (ጉባኤዎች) የቤተ በክርስቲያን አንድነት ተጠብቆ ቆይቷል፡፡ እንደዚሁም በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ስለምሥጢረ ሥላሴ ዶግማ (ትምህርት) በቤተ ክርስቲያን መምህራን መካከል ብዙ ልዩነቶች ተፈጥረው ነበር፡፡ የእነጳውሎስ ሳምሳጢና የእነሰባልዮስ የኑፋቄ ትምህርቶች በቤተ ክርስቲያን አህጉራዊ ጉባኤያት (ሲኖዶሶች) ተወግዘው በዚህ ምክንያት የተነሣው ውዝግብ ጥቂት ረገብ ብሎ ነበር፡፡ ነገር ግን ከግማሽ ምእት ዓመት በኋላ በአርዮስ የምሥጢረ ሥላሴ ትምህርት ምክንያት ማለት አርዮስ ‹‹ወልድ ፍጡር ነው›› (ሎቱ ስብሐት) ብሎ በመነሣቱ ቤተ ክርስቲያን ለብዙ ዓመታት ስትታወክና ስትበጠበጥ ቆይታለች፡፡

፩. የአርዮስ የክሕደት (የኑፋቄ) ትምህርት

አርዮስ ከሦስተኛው ምእት ዓመት አጋማሽ በኋላ በ፪፻፷ ዓ.ም አካባቢ በሰሜን አፍሪካ በሊብያ ነው የተወለደው፡፡ ስሙ እንደሚያመለክተው የትውልድ ዘሩ (የዘር ሐረጉ) የሚዘዘው ከግሪክ ሲሆን፣ የተገኘውም ከክርስቲያን ቤተሰብ ነበር፡፡ በትውልድ ሀገሩ መሠረታዊ ትምህርቱን ከአጠናቀቀ በኋላ እስክንድርያ በሚገኘው ከፍተኛ መንፈሳዊ ትምህርት ቤት ገብቶ ከፍተኛ ትምህርት ተምሯል፡፡ አርዮስ በእስክንድርያ ከፍተኛ ትምህርት ቤት ትምህርቱን ካጠናቀቀ በኋላ ወደመካከለኛው ምሥራቅ ሔዶ በአንጾኪያ ከፍተኛ መንፈሳዊ ትምህርት ቤት ገብቶ ከፍተኛ የትርጓሜ መጻሕፍት ትምህርትና የነገረ መለኮት ትምህርት ተምሯል፡፡ መምህሩም የታወቀው ሉቅያኖስ ነበር፡፡ ከእስክንድርያ ትምህርት ቤት ይልቅ የአንጾኪያ ትምህርት ቤት ለአርዮስ የክህደት ትምህርት ቅርበት እንደነበረው ብዙ ሊቃውንት ይናገራሉ፡፡

አርዮስ አብዛኛውን የኑፋቄ ትምህርቱን ያገኘው ከሉቅያኖስና ከአንጾኪያ ትምህርት ቤት ነው፡፡ በአንጾኪያ የሚፈልገውን ትምህርት ከጨረሰ በኋላ ወደ እስክንድርያ ተመልሶ ኑሮውን በዚያው አደረገ፡፡ አርዮስ እጅግ ብልህና ዐዋቂ ሰው በመሆኑ ብዙ ሰዎች ያደንቁት ነበር፡፡ አንደበተ ርቱዕም ስለነበረ ተናግሮ ሕዝብን በቀላሉ ማሳመን እንደሚችል ይነገርለታል፡፡ በዚያ በነበረው ዕውቀትና ታላቅ የንግግር ችሎታ የእስክንድርያ ፓትርያርክ የነበረው ተፍጻሜተ ሰማዕት ቅዱስ ጴጥሮስ ዲቁና ሾመው፡፡ የእስክንድርያ ከፍተኛ ትምህርት ቤት ከከፍተኛ መንፈሳዊ ትምህርት ሌላ የግሪክ ፍልስፍናን በተለይም የፕላቶንን ፍልስፍና ያስተምሩ ስለነበር፣ አርዮስም ፍልስፍናን በተለይም ሐዲስ ፕላቶኒዝም (Neo-Platonism) የተባለውን ፍልስፍና በሚገባ ተምሯል፡፡

በዚህም የእስክንድርያውን ከፍተኛ ትምህርት ቤት ታላቅ መምህር የነበረውን የአርጌንስን (Origen) የተዘበራረቀ የምሥጢረ ሥላሴን ትምህርት ተከትሎ መጓዝ ጀመረ፡፡ አርጌንስ በምሥጢረ ሥላሴ ትምህርቱ አብን ከወልድ፣ ወልድን ደግሞ ከመንፈስ ቅዱስ በማዕረግና በዕድሜ ያበላልጥ ነበር፡፡ አርጌኒስ አብን፣ ወልድንና መንፈስ ቅዱስን በማበላለጥ አብ ከወልድ እንደሚበልጥ፣ መንፈስ ቅዱስ ደግሞ ከወልድ እንደሚያንስ ያስተምር ነበር፡፡ ስለዚህ የአርዮስ የክህደት ትምህርቱ ዋናው መሠረት አርጌኒስ እንደሆነ አያጠራጥርም፡፡ ምንም እንኳን አርጌኒስ ስለቅድስት ሥላሴ ቢያስተምርም፣ አርዮስ አጥብቆ የተናገረውና የኑፋቄ ትምህርቱን ያስተማረው ስለአብ እና ስለወልድ ነበር፡፡ በአጠቃላይ የአርዮስ የክሕደት ትምህርት የሚከተለው ነው፤

፩. አብ ብቻ ዘለዓለማዊ (ዘአልቦ ጥንት ወኢተፍጻሜት) ነው፡፡ ወልድ ግን ዘለዓለማዊ አይደለም፡፡ ነገር ግን እርሱ ያልነበረበት ጊዜ ነበር ለማለት ‹‹ሀሎ አመ ኢሀሎ›› (እርሱ ያልነበረበት ጊዜ ነበር) እያለ ያስተምር ጀመር፡፡ ስለዚህ አብ አባት ተብሎ የተጠራውና እንደ አባት የታወቀው ከዘመናት በኋላ እንጂ ከዘመናት በፊት አብ ተብሎ አይጠራም አለ፡፡ ይህንን ያለው ‹‹ወልድ ፍጡር ነው›› (ሎቱ ስብሐት) ብሎ ያልነበረበት ጊዜ ነበረ ለማለት ነበር፡፡

፪. የአርዮስ ዋናው የክሕደት ትምህርቱ ‹‹ወልድ ፍጡር ነው›› (ሎቱ ስብሐት) ማለትም ‹‹ወልድ ከመፈጠሩ በፊት አልነበረም፤›› የሚል ነው፡፡ ‹‹አብወልድን ከምንም ፈጠረና የእግዚአብሔር ልጅ እንዲሆን አደረገውለወልድ ጥበብ፣ ቃል የሚባሉ የኃይላት ስሞች አሉት›› እያለ ያስተምር ነበር፡፡ ለክሕደቱ መሠረት የሆነውና ሁልጊዜ ይጠቅሰው የነበረውም፡- ‹‹ትቤ ጥበብ ፈጠረኒ መቅድመ ሉ ተግባሩጥበብ ከፍጥረቱ ሁሉ አስቀድሞ እኔን ፈጠረኝ አለች፤›› ተብሎ በመጽሐፈ ምሳሌ ፰፥፳፪ ላይ የተጠቀሰው ኃይለ ቃል ነበር፡፡ በአርዮስ አስተሳሰብ ጥበብ የተባለ ወልድ ነው፤ ስለዚህ እግዚአብሔር አብ መጀመሪያ ወልድን ፈጠረ፡፡  ከዚያ በኋላ ወልድ ዓለምንና በውስጡ ያሉትን ሁሉ ፈጠረ ብሎ ያምን ነበር፡፡ ያለ ወልድ ምንም የተፈጠረ ፍጥረት የለም ብሎ ያስተምርም ነበር፡፡

፫. ከዚህም ሌላ አርዮስ ወልድን ከአብ ሲያሳንስ ‹‹ወልድ በባሕርዩ ከአብ ጋር አንድ አይደለም›› ይል ነበር፡፡ በሌላ በኩል ግን ወልድን ከሌሎች ከፍጡራን እጅግ ያስበልጠዋል፡፡ ወልድም በጸጋ የአብ ልጅ እንደሆነ ይናገራል፡፡ እንደዚሁም ወልድ በምድር ሕይወቱ ታላቅ ትሕትናንና ተጋድሎን በማሳየቱ በባሕርይ ሳይሆን በጸጋ የአምላክነትን ክብር እንዳገኘ አርዮስ በአጽንዖት ይናገር ነበር፡፡

፬. በአርዮስ አመለካከት ወልድ በባሕርዩ ፍጹም ስላልሆነ የአብን መለኮታዊ ባሕርይ ለማየትም ለማወቅም አይችልም ይል ነበር፡፡

፭. አርዮስ ስለ መንፈስ ቅዱስ ሲናገር ‹‹ወልድ ለአብ የመጀመሪያ ፍጥረቱ እንደሆነ፣ መንፈስ ቅዱስ ደግሞ ለወልድ የመጀመሪያ ፍጥረቱ ነው›› ይል ነበር፡፡

ይህን የአርዮስን ክሕደት የሰማው የእስክንድርያ ቤተ ክርስቲያን ሊቀ ጳጳስ (ፓትርያርክ) ተፍጻሜተ ሰማዕት ቅዱስ ጴጥሮስ አርዮስን አስጠርቶ የሚያስተምረው ትምህርት ሁሉ የተሳሳተ መሆኑን ገልጾለት ከስሕተቱ ተመልሶና ተጸጽቶ ከቅዱሳን አበው ሲተላለፍ በመጣው በኦርቶዶክስ እምነት እንዲጸና መከረው፡፡ አርዮስ ግን ከአባቱ ከተፍጻሜተ ሰማዕት ጴጥሮስ የተሰጠውን ምክር ወደ ጎን በመተው የክሕደት ትምህርቱን በሰፊው ማስተማር ቀጠለ፡፡ ይህንን የተመለከተ ያ ደግ አባት አርዮስን አውግዞ ከዲቁና ማዕረጉ ሻረው፡፡ የግብጽ ቤተ ክርስቲያን ትውፊት እንደሚለው፣ ተፍጻሜተ ሰማዕት ቅዱስ ጴጥሮስ አርዮስን ያወገዘው ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በራእይ ተገልጦለት በሰጠው ትእዛዝ መሠረት ነው፡፡

በአንድ ሌሊት በራእይ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ በአንድ ወጣት አምሳል እንደ ፀሓይ የሚያበራ ረጅም ነጭ ልብስ (ቀሚስ) ለብሶ ለቅዱስ ጴጥሮስ ይታየዋል፡፡ ልብሱ ለሁለት የተቀደደ ሆኖ ቢያየው ጊዜ ቅዱስ ጴጥሮስ ደንግጦ ጌታን ‹‹መኑ ሰጠጣ ለልብስከልብስህን ማን ቀደደብህ?›› ብሎ ይጠይቀዋል፡፡ ጌታም ‹‹አርዮስ ልብሴን ቀደደብኝ›› ብሎ መለሰለት፡፡ ይኸውም በአባቶች ትርጕም ‹‹አርዮስ ከባሕርይ አባቴ ከአብ ለየኝ (አሳነሰኝ)›› ማለት ነው፡፡ ጌታም አርዮስን ከእንግዲህ ወዲያ ወደ ቤተ ክርስቲያን አንድነት እንዳይቀበለው አዝዞት ተሰወረ፡፡ ተፍጻሜተ ሰማዕት ጴጥሮስ ራእዩን ያየው በዲዮቅልጥያኖስ ስደት ጊዜ ተይዞ ለመገደል በእስር ቤት በነበረበት ወቅት ነበር፡፡ አርዮስም ቅዱስ ጴጥሮስ እንደሚገደል አውቆ ከውግዘቱ ሳይፈታው እንዳይሞት ከውግዘቱ እንዲፈታው አማላጆች ይልክበታል፡፡ ተፍጻሜተ ሰማዕት ቅዱስ ጴጥሮስ ግን አርዮስን ‹‹በሰማይና በምድር የተወገዘ ይሁን!›› በማለት ውግዘቱን አጸናበት፡፡ በዚያኑ ቀን ተማሪዎቹን አርኬላዎስን እና እለእስክንድሮስን አስጠርቶ ያየውን ራእይ በመግለጥ አርዮስን እንዳይቀበሉትና ከእርሱም ጋር ኅብረት እንዳይኖራቸው አዘዛቸው፡፡

ይቆየን

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን መገናኛ ብዙኃን አገልግሎት

በዲያቆን ኤፍሬም የኔሰው

ኅዳር ፩ ቀን ፳፻፲ ዓ.ም

የተወደዳችሁ የድረ ገጻችን ተከታታዮች! እንደሚታወቀው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የመገናኛ ብዙኃን አገልግሎት ድርጅት አቋቁማ መደበኛ የሃያ አራት ሰዓት የቴሌቭዥን መርሐ ግብር ከጀመረች ከሁለት ዓመታት በላይ ተቈጥረዋል፡፡ በዛሬው ዝግጅታችን፣ የቴሌቭዥን ሥርጭቱን አጀማመርና ጠቅላላ አገልግሎት በአጭሩ የሚያስቃኝ ጽሑፍ ይዘን ቀርበናል፡፡ መልካም ንባብ ይኹንላችሁ!

በቤተ ክርስቲያናችንና በአገራችን ታሪክ እንደሚታወቀው ያልተበረዘና ያልተከለሰ ኦርቶዶክሳዊ ዶግማና ሥርዓተ አምልኮ፣ የትርጓሜና የባሕረ ሐሳብ ትምህርት፣ በብራና የተጻፉ ቅዱሳት መጻሕፍት፣ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት፣ መሥዋዕተ ኦሪት ይቀርብባቸው የነበሩና እስከ አሁን ድረስ ተጠብቀው የቆዩ ጥንታውያን አድባራትና ገዳማት፣ የቅዱስ ያሬድ የዜማ ድርሰቶች፣ ሥርዓተ ማኅሌትና የመንፈሳውያን በዓላት አከባበር ሥርዓት፣ ወዘተ. የመሳሰሉ የሚዳሰሱና የማይዳሰሱ ቅርሶች በሙሉ ዓለምን የሚያስደምሙ የቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ሀብቶችና ልዩ ስጦታዎች ናቸው፡፡

ብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ ካልዕ በመጽሐፋቸው እንደ ጠቀሱት ሙሉ ትምህርት፣ ፍጹም ቋንቋ ከነፊደሉ፣ ሥነ ጥበብ፣ ሥነ ጽሑፍ፣ ኪነ ጥበብ፣ ታሪካዊና ጥንታዊ ቅርስ፣ እምነት፣ ነጻነት፣ አንድነት፣ የአገር ፍቅር የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ለኢትዮጵያ ሕዝብ ካበረከተቻቸው ብዙ ስጦታዎች መካከል የሚጠቀሱ ናቸው፡፡ እንደ ብፁዕነታቸው ማብራሪያ አሁንም ቢኾን ትውልዱ ጀግንነትን፤ አገር ወዳድነትን፤ ለሃይማኖት፣ ለታሪክና ለባህል ተቆርቋሪነትን ይዞ እንዲያድግ በማስተማርና በማበረታታት ረገድ ቤተ ክርስቲያን ድርሻ አላት (የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ታሪክ)፡፡

በረከታቸው ይደርብንና ካሁን በፊት በየጊዜው የተነሡ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን በቃል በማስተማርና መጻሕፍትን በማሳተም እነዚህን ሀብቶቿን ለመጠበቅና ለዓለም ለማስተዋወቅ ያደረጉት አስተዋጽዖ ከፍተኛ ነው፡፡ ከኅትመት ውጤቶች ባሻገርም መገናኛ ብዙኃንን በመጠቀም ቃለ እግዚአብሔር ለማስተማር ቀደምት የቤተ ክርስቲያን አባቶች ብዙ ደክመዋል፡፡ ለዚህም በአሁኑ ሰዓት አገልግሎት ባይሰጥም ቀደም ሲል የተጀመረው የሬድዮ መርሐ ግብር እንደዚሁም አሁንም አገልግሎት በመስጠት ላይ የሚገኙት መንፈሳዊ መጽሔቶች፣ ጋዜጦችና ድረ ገጾች ማስረጃዎች ናቸው፡፡ መገናኛ ብዙኃንን በተለይም የቴሌቭዥን ሥርጭትን በመጠቀም ረገድ እንደ ግብጽ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ያሉ አኃት አብያተ ክርስቲያናት ተሞክሮ በምሳሌነት የሚጠቀስ ነው፡፡

ብዙ ጊዜ እንደሚነገረው በሁለት ቋንቋዎች ብቻ የሚግባቡና በቍጥር ከዐሥር ሚሊዮን የማይበልጡ ምእመናን የሚገኙባት የግብጽ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ከዐሥር በላይ የቴሌቭዥን ጣቢያዎችን በመክፈት ትምህርተ ወንጌልን በመላው ዓለም በማዳረስ ላይ ትገኛለች፡፡ በምእመናን ብዛት ከኢትዮጵያ ብዙ እጥፍ የምታንሰዋ ግብጽ በዚህ መልኩ የመገናኛ ብዙኃን ተጠቃሚ ከኾነች ከሰማንያ በላይ ቋንቋዎችን የሚናገሩና ወደ አምሳ ሚሊዮን የሚደርሱ ምእመናን ባለቤት ለኾነችው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አንድ ብቻ ሳይኾን በርካታ የቴሌቭዥን ጣቢያዎች እንደሚያስፈልጓት አያጠያይቅም፡፡ ይህን እውነት ከግምት ውስጥ በማስገባት ቅዱስ ሲኖዶስ ባሳለፈው ውሳኔ ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ከዓመታት በፊት የሃያ አራት ሰዓት የቴሌቭዥን መርሐ ግብር ማሠራጨት ጀምራለች፡፡

በ፳፻፱ ዓ.ም በታተመው ዐዋጅ ነጋሪ መጽሔት እንደ ተገለጸው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የመገናኛ ብዙኃን አገልግሎት ድርጅት እንዲቋቋም ለማድረግ ጥናት እንዲካሔድ ለመጀመሪያ ጊዜ የተወሰነው በጥቅምት ወር ፳፻፮ ዓ.ም የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ነው፡፡ በዚያው ዓመት በግንቦት ወር በተካሔደው የቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤ፤ ሦስት ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት፣ በርካታ ባለሙያዎችና ሊቃውንት የተሳተፉበት ጥናት ለምልዓተ ጉባኤው ቀርቦ የድርጅቱ መተዳደሪያ ደንብ፣ የአርትዖትና የቴክኒክ መመሪያ ጸድቆ ሥራው እንዲጀመር ተወስኗል፡፡

ድርጅቱ፣ በቋሚ ሲኖዶስ በተሰየመው የቦርድ ሥራ አመራር ከአንድ ዓመት በላይ ተጨማሪ ጥናቶችን ሲያደርግ ቆይቶ በጥቅምት ወር ፳፻፰ ዓ.ም ለሥራው የሚያስፈልገው በጀት በቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ተወስኖለታል፡፡ ቦርዱ የተፈቀደውን በጀትና የተጠናውን ጥናት ወደ ተግባር ለመለወጥ ውድድር በማድረግ ለድርጅቱ ሥራ አስኪያጅ እንዲቀጠር አድርጓል፡፡ በቅዱስ ሲኖዶስ በጸደቀው የድርጅቱ መተዳደሪያ ደንብ መሠረት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የመገናኛ ብዙኃን አገልግሎት ድርጅት ዋና መሥሪያ ቤት በጠቅላይ ጽ/ቤቱ ግቢ ውስጥ ይገኛል፡፡

በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት አባታዊ መመሪያ ሰጭነት አስፈላጊ ቅድመ ኹኔታዎችን በሟሟላት፣ ተደጋጋሚ ውይይቶችንና ዓለም አቀፍ ዳሰሳዎችን በማድረግ ለሥርጭቱ ያመነበትን የሳተላይት ጣቢያ አወዳድሮ በመምረጥና የውል ስምምነት በማዘጋጀት በአፋጣኝ የሥርጭት አገልግሎቱን ጀምሯል፡፡ በኢየሩሳሌም ከሚገኙ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ገዳማት ጋር በተደረገ ስምምነት መሠረትም የቴሌቭዥን መርሐ ግብራቱ በአገር ውስጥ ተዘጋጅተው ኢየሩሳሌም በሚገኘው የሳተላይት ድርጅት አማካይነት ይሠራጫሉ፡፡ የቴሌቭዥን ጣቢያው የሥርጭት አድራሻም የሚከተለው ነው፤

Ethiopian Orthodox Tewahedo Church Television (EOTC TV)

Satellite: Eutelsat/Nilesat (ኢትዮጵያ)

Frequency …. 11353 (5) Vertical

Symbol rate …. 27500/FEC…5/6

Satellite: Galaxy 19 (G-19) (ሰሜን አሜሪካ)

Frequency …. 11960/Vertical

Symbol rate …. 22000/FEC…3/4

የድርጅቱ መዋቅርና አገልግሎት የተሟላ እንዲኾን በአስተዳደርና ፋይናንስ፣ በመርሐ ግብር ዝግጅት እና በቴክኒክ ዘርፍ ቦርዱ በሰየማቸው የቅጥርና የምዘና ኮሚቴ አባላት አስፈጻሚነት የሠራተኞች የቅጥር ሒደት ተከናውኗል፡፡ በቅጥር ሒደቱም ከመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽ/ቤት በወጣው ማስታወቂያ መሠረት ላመለከቱ ሠራተኞችና ለቤተ ክርስቲያን ሊቃውንት ቅድሚያ ተሰጥቷል፡፡ የሥርጭቱን አጠቃላይ ይዘትና ዓይነት በተመለከተም ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን፣ የቦርድ አባላትና የሚዲያ ባለሙያዎች የሚገኙበት የይዘትና የዓይነት ዝግጅት ኮሚቴ ተዋቅሯል፡፡ ይዘቱንና ዓይነቱን የሚያርምና የሚገመግም የኤዲቶሪያል ኮሚቴም ተቋቁሟል፡፡ የኤዲቶሪያል ኮሚቴው አባላትም በብፁዕ ጠቅላይ ሥራ አስኪጁ የተሰየሙና በቦርዱ የተመረጡ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን ናቸው፡፡ ድርጅቱ ካለበት ሠፊ ሥራና ከባድ ሓላፊነት አኳያ በቋሚነት የሚያስፈልጉት በርከት ያሉ ስቱዲዮዎች፣ የቅድመ ሥርጭትና ድኅረ ሥርጭት ተግባራት ማከናወኛነት የሚያገለግሉ በርካታ ክፍሎች፣ አብያተ መዛግብት፣ አስተዳደርና የባለሙዎች ቢሮዎች እንዲሟሉ ለማድረግ ድርጅቱ ከጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽ/ቤትና ከሚመለከታቸው የቤተ ክርስቲያኒቱ አባቶች መመሪያን በመቀበል በመሥራት ላይ ይገኛል፡፡

(ምንጭ፡- ዐዋጅ ነጋሪ መጽሔት፣ ፱ኛ ዓመት፣ ቍጥር ፲፪፤ ጥቅምት ፳፻፱ ዓ.ም፣ ገጽ 77-78)፡፡

ጽሑፋችንን ለማጠቃለል ያኽል፣ የሥልጣኔ ውጤቶች በተበራከቱበትና አብዛኞቹ ወጣቶች ዓለማዊ መልእክት በሚያስተላልፉ መገናኛ ብዙኃን ተጽዕኖ ውስጥ በወደቁበት በአሁኑ ዘመን ወጣቱን ትውልድ ወደ ጥፋት ከሚወስዱ መልእክቶች ለመታደግ ያመች ዘንድ ትምህርተ ወንጌልን ለማዳረስና ኦርቶዶክሳዊ ሕይወትን ለማስተማር፤ የቤተ ክርስቲያናችንን ሥርዓተ እምነት፣ ትውፊትና ልዩ ልዩ ሀብቷን ወይም የሚዳሰሱና የማይዳሰሱ ቅርሶቿን ለትውልድ ለማቆየት ብሎም ለዓለም ለማስተዋወቅ፤ እንደዚሁም በየጊዜው በቅዱስ ሲኖዶስ የሚወጡ መመሪያዎችንና መልእክቶችን በአፋጣኝ ወደ ሕዝበ ክርስቲያኑ ለማስተላለፍ መገናኛ ብዙኃንን፣ ከመገናኛ ብዙኃንም የቴሌቭዥን ሥርጭትን መጠቀም ከፍተኛ ጠቀሜታ አለው፡፡

በዚህ ዓላማ መሠረት የተጀመረው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የቴሌቭዥን ሥርጭትም በልዩ ልዩ ዓምዶቹ ትምህርተ ወንጌል በመስጠት፤ ቅዱሳት መካናትን፣ የሚዳሰሱና የማይዳሰሱ የቤተ ክርስቲያን ቅርሶችን በማስተዋወቅ፤ ጠቃሚ የኾኑ ማኅበራዊና ወቅታዊ ጉዳዮችን በማቅረብና መንፈሳዊ ዜናዎችን በመዘገብ አገልግሎቱን እንደ ቀጠለ ነው፡፡ የቴሌቭዥን ሥርጭቱን በተቀላጠፈ መልኩ ለማስቀጠልና ለምእመናን ለማዳረስ ይቻል ዘንድም መላው ሕዝበ ክርስቲያን ሐሳብ አስተያየት በመስጠትና በሌላም ልዩ ልዩ መንገድ በተቻለን አቅም ዂሉ የቤተ ክርስቲያናችንን የመገናኛ ብዙኃን አገልግሎት ድርጅት በመደገፍ የሚጠበቅብንን ክርስቲያናዊ ሓላፊነት እንወጣ ሲል የማኅበረ ቅዱሳን አማርኛ ድረ ገጽ ዝግጅት ክፍል መንፈሳዊ መልእክቱን ያስተላልፋል፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር፡፡

ዘመነ ጽጌ

በዶክተር ታደለ ገድሌ

ጥቅምት ፳፬ ቀን ፳፻፲ ዓ.ም

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሥርዓተ አምልኮ መሠረት ከመስከረም ፳፮ እስከ ኅዳር ፭ ቀን ያለው ወቅት ‹ዘመነ ጽጌ፤ ወርኀ ጽጌ› ተብሎ ይጠራል፡፡ በግእዝ ቋንቋ ‹ጸገየ› ማለት ‹አበበ፤ አፈራ፤ በውበት ተንቆጠቆጠ፤ በደም ግባት አጌጠ፤ የፍሬ ምልክት አሣየ› እንደ ማለት ነው፡፡ ከዚሁ ግስ ላይ ‹ጽጌያት› ብሎ ስም ማውጣት ሲቻል አበባማ፣ ውበታማ፣ አበባ የያዘና የተሸከመ ለማለት ደግሞ ‹ጽጉይ› ይላል፡፡ በተለይም ዘመነ ጽጌ (ወርኀ ጽጌ) የምትከበረው በሀገራችን ከወቅቶች ሁሉ በጣም በሚወደደው የመፀው ወቅት ነው፡፡ በዚህ ምድር በልምላሜና በውበት በምትንቆጠቆጥበት ወቅት በየሳምንቱ እሑድ ከመንፈቀ ሌሊት ጀምሮ ማኅሌተ ጽጌ የሚቆሙትና ሰዓታት የሚያደርሱት ካህናት እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምን በአበባ፣ በትርንጎ፣ በሮማን፣ በእንጆሪ … እየመሰሉ ለፈጣሪ መዝሙርና ምስጋና ያቀርባሉ፡፡

በዘመነ ጽጌ ‹‹ጊዜ ገሚድ በጽሐ ቃለ ማዕነቅ ተሰምዓ በምድርነ፤ ተመየጢ ተመየጢ ወንርዓይ ብኪ ሰላመ፤ እንዘ ተሐቅፊዮ ለሕፃንኪ፤ ክበበ ጌራ ወርቅ ጽሩይ በዕንቈ ባሕርይ ዘየኀቱ፤ አክሊለ ጽጌ ማርያም፤ ንዒ ርግብየ ወንዒ ሠናይትየ፤ እንተ ሐዋርያት ይሴብሑኪ መላእክት ይትለአኩኪ፤ ንዒ እምሊባኖስ ሥነ ሕይወት፤ ቡራኬሁ ለሴም፤ ተናግዶቱ ለአብርሃም መዓዛሁ ለይስሐቅ ወሰዋስዊሁ ለያዕቆብ ወናዛዚቱ ለዮሴፍ …›› ይህን የመሳሰሉ ኃይለ ቃላትን እያነሡ ሊቃውንቱና ምእመናኑ እግዚአብሔርንና እመቤታችንን ያመሰግናሉ፡፡

ይህም ማለት ‹‹… በአበባው ወቅት መሆን የሚገባው ነገር ሁሉ ደረሰ፡፡ የአዕዋፍ ውዳሴ ቃልም በምድራችን ተሰማ፡፡ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ሆይ! በአንቺ ሰላምን ማየት እንችል ዘንድ መመለስን ተመለሺ፡፡ ልጅሽን እንዳቀፍሽ፤ ክበቡ ያማረ ወርቅ እንደ ተጎናጸፍሽ የአበባ አክሊል ማርያም ርግቤ፣ ደጌ ሆይ! ነይ፡፡ ሐዋርያት የሚያመሰግኑሽ፤ መላእክት የሚላላኩሽ፤ የሕይወት መሠረት ከሊባኖስ ነይ፡፡ የሴም በረከቱ፤ የአብርሃም መስተንግዶው፤ የይስሐቅ ሽቶው፤ የያዕቆብ መሰላሉ፤ የዮሴፍ አጽናኙ …›› በሚሉና በሌሎችም የዜማ ስልቶች ካህናትና ዲያቆናት፤ ደባትር (ደብተሮች) በቅኔ ማኅሌት ውስጥ ጧፍ እያበሩና እየዘመሩ፤ ከበሮ እየመቱ፤ ጸናጽል እያንሹዋሹ፤ በመቋሚያ አየሩን እየቀዘፉና መሬቱን እየረገጡ፤ እየወረቡ ሌሊቱን ሙሉ ለእግዚአብሔር ምስጋና ያቀርባሉ፡፡

ሰዓታት የሚያደርሱ ካህናትም፡- ‹‹ትመስሊ ምሥራቀ፤ ወትወልዲ መብረቀ፤ ወታገምሪ ረቂቀ፡፡ ትመስሊ ፊደለ፤ ወትወልዲ ወንጌለ፤ ወታገምሪ ነበልባለ፡፡ ትመስሊ ጽጌ ረዳ፤ ወትወልዲ እንግዳ፤ ወታድኅኒ እሞተ ፍዳ … ሐረገ ወይን ሐረገ ወይን ዐፀደ ወይን አንቲ ማርያም›› ማለት፡- ‹‹በምሥራቀ ፀሐይ የምትመሰየሚው፤ እንደ መብረቅ ኃያል የሆነውን ጌታን የወለድሽ፤ ረቂቅ ምሥጢርን የምትችዪ፤ እንደ ፊደል ባለ ብዙ ዘር (ሆሄያት) የሆንሽ፤ ወንጌልን የወለድሽ፤ ነበልባለ እሳትን (ክርስቶስን) የተሸከምሽ፤ በጽጌ ረዳ አምሳል የምትመሰየሚው ቅድስት ማርያም ሆይ! የዓለሙን እንግዳ ፈጣሪን የወለድሽ፤ ከፍዳ ሞት የምታድኚ፤ የወይን ሐረግ የወይን ዐፀድ (ተክል) አንቺ ነሽ …›› እያሉ ያመሰግናሉ፡፡

‹‹እምግብጽ ጸዋዕክዎ ለወልድየ ለክብረ ቅዱሳን፤ ለቅዱሳን ክብር ልጄን ከግብጽ ጠራሁት›› በማለት ነቢዩ ሆሴዕ በምዕራፍ ፲፩ ቍጥር ፩ እና ፪ ላይ አስቀድሞ እንደ ተናገረው ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በልጅነቱ ወደ ምድረ ግብጽ (ምስር) የተሰደደው የነቢያት ትንቢት ይፈጽም ዘንድ ነው፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ሕፃናትን በመፍጀት ከሚታወቀው ከአረመኔው ንጉሥ ከሄሮድስ ለማምለጥ ነው፡፡ አምላካችን ክርስቶስ ያለጊዜው (ዕለተ ዓርብ) ደሙ አይፈስምና፡፡ ስለዚህም ‹‹ሕፃኑንና እናቱን ይዘህ ወደ ምድረ ግብጽ ሽሽ፤ ሄሮድስ ሕፃኑን ለመግደል ይፈልጋልና›› ብሎ መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል ለዮሴፍ በነገረው ቃል መሠረት ሕፃኑንና እናቱን ይዞ በሌሊት ወደ ግብጽ ምድር ተሰደደ፡፡ ይህንን ስደት አስመልክቶ ሰቆቃወ ድንግል የሚባለውን ቃለ እግዚአብሔር ካህናቱ በሚያሳዝን ዜማ ያደርሳሉ፤ ያቀርባሉ፡፡

ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በይሁዳ ግዛት በቤተልሔም በንጉሥ ሄሮድስ ዘመን በተወለደ ጊዜ በሄሮድስ ላይ ቅንዓት አድሮበት ነበር፡፡ ‹‹ከአንተ የሚበልጥና የሚልቅ ንጉሥ በቤተልሔም ይወለዳል›› የሚል ትንቢት ይሰማ ነበር፡፡ ‹‹ወአንቲነ ቤተ ልሔም ምድረ ኤፍራታ ኢትቴሐቲ እምነገሥተ ይሁዳ እስመ እምኔኪ ይወፅዕ ንጉሥ፤ አንቺ የኤፍራታ ምድር ቤተልሔም ሆይ! ብዙ ነገሥታት ከነገሡባት ከይሁዳ አታንሺም፤ የዓለም ንጉሥ የሚሆን ከአንቺ ይወጣልና›› የሚለው የነቢያት ትንቢት ሄሮድስን አስጨነቀው፡፡ በዚህ ላይ ደግሞ ሰብአ ሰገል (የጥበብ ሰዎች) ‹‹የተወለደው የአይሁድ ንጉሥ የት አለ? የምሥራቅ ኮከብ እየመራን መጥተናል፡፡ እንሰግድለት ዘንድ አመላክቱን›› ብለው ወደ ኢየሩሳሌም ብዙ መብዓ ይዘው መምጣታቸውን ሄሮድስ ሲሰማ ዓይኑ ፈጠጠ፤ ሰውነቱም ደነገጠ፡፡ ስለዚህም ጌታችንን ሊገድለው ወደደ፡፡

ለሥልጣን ስሱ የነበረው ሄሮድስ ‹‹ከእኔ በላይ ሌላ ምን ንጉሥ አለ?›› ብሎ ተቆጣና የካህናትን አለቆችና የሕዝቡን ጻፎች (ፈሪሳውያንን) አስጠርቶ በመሰብሰብ ‹‹ክርስቶስ የተወለደው የት ነው?›› ብሎ አፈጠጠባቸው፡፡ በኋላም አንደበቱን አለሰለሰና ‹‹እውነት ከሆነ እኔም እሰግድለት ዘንድ ፈልጉልኝ›› አለ ብልጡ ንጉሥ፡፡ ካህናቱም ከልቡ መስሏቸው ‹‹‹አንቺ ቤተልሔም የይሁዳ ምድር ከይሁዳ ገዢዎች ከቶ አታንሽም፤ ሕዝቤን እስራኤልን የሚጠብቅ መስፍን ከአንቺ ይወጣልና› ተብሎ በተጻፈው መሠረት ጌታችን የተወለደው በይሁዳ በቤተልሔም ነው፡፡ ሰብአ ሰገልም አምኃ (እጅ መንሻ) ለማቅረብ የሚሔዱት ወደዚያው ነው›› ብለው እቅጩን ነገሩት፡፡ ሄሮድስም መንገደኞቹን ሰብአ ሰገልን ጠራና ‹‹ወገኖቼ አደራችሁን ለተወለደው ልጅ መብዓ አድርሳችሁ በእኔ በኩል ተመለሱ፡፡ እኔ ደግሞ ሒጄ እሰግድለት ዘንድ ሁኔታውን ትነግሩኛላችሁ›› ብሎ አሰናበታቸው፡፡

እነርሱም ‹‹ኧረ ግድ የለም ንጉሥ ሆይ!›› ብለው የምሥራቁ ኮከብ እየመራቸው፤ ሕፃኑ ባለበት ቦታ ላይ ደርሰው፤ ወደ ቤትም ገብተው፤ ወድቀው ለሕፃኑ ሰገዱለት፡፡ ሳጥኖቻቸውንም ከፍተው እጅ መንሻ ወርቅና ዕጣን፣ ከርቤም አቀረቡለት፡፡ ሲመለሱ በሌላ መንገድ እንዲሔዱ መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል በሕልም ነግሯቸው ነበርና በሌላ መንገድ ወደ ሀገራቸው ተጓዙ፡፡ ሄሮድስ ይህን በመሰማ ጊዜም የበለጠ ቅንዓት አደረበትና ሕፃኑን ለመግደል ይበልጥ ተነሣሣ፡፡ በሐሳብ የተጨነቀው ንጉሥ ጉዳዩን ለመጠንቁል (ለጠንቋይ) አማከረ፡፡ ጠንቋይ መቼም እበላና እወደድ ባይ ነውና ‹‹‹እስከ ሁለትና ሦስት ዓመት ዕድሜ ለአላቸው ወንድ ሕፃናት ቀለብ ልሠፍርላቸው አስቤአለሁና ተሰብሰቡ› ብለው አዋጅ ያስነግሩ፡፡ ሕፃናቱን ሲሰበሰቡልዎም ያን ጊዜ ሁሉንም ይግደሏቸው፡፡ ከዚያ ውስጥ የእርስዎ የወደፊት ጠላት አብሮ ይሞታል›› ብሎ መከረው፡፡ በዚህ መሠረት በመቶ ሺሕ የሚቆጠሩ ሕፃናትን ሄሮድስ አስፈጅቷል፡፡ ‹‹ድምፅ በራማ ተሰማ፤ ለቅሶና ብዙ ዋይታ፡፡ ራሔል ስለ ልጆቿ አለቀሰች፡፡ መጽናናትም አልወደደችም፤ የሉምና›› የሚለው ትንቢትም ተፈጸመ፡፡

ከሦስት ዓመት ከመንፈቅ የግብጽ ስደት በኋላ ሊቃውንቱ፡- ‹‹ተመየጢ ማርያም ሀገረኪ ናዝሬተ፣ በላዕሌኪ አልቦ ዘያበጽሕ ሁከተ፣ ወኢትጎንድዪ በግብጽ ከመ ዘአልብኪ ቤተ፣ ዘየኀሥሦ ለወልድኪ ይእዜሰ ሞተ፣ በከመ ነገሮ መልአክ ለዮሴፍ ብሥራተ›› እያሉ ከስደት መመለሷን ያበሥራሉ፡፡ ትርጉሙም፡- ‹‹ማርያም ሆይ! ወደ ሀገርሽ ወደ ናዝሬት ተመለሺ፡፡ በአንቺ ላይ ሁከት የሚያመጣ ማንም የለም፡፡ ቤት እንደሌለሽ ሁሉ በግብጽ አትቆይ፡፡ ለዮሴፍ በሕልሙ መልአክ እንደ ነገረው የሕፃኑን ነፍስ የፈለገው (ጠላት ሄሮድስ) ሞቷልና›› ማለት ነው፡፡ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ምእመናን በዐርባው ቀን (በዘመነ ጽጌ) ወቅት የማርያምን የሽሽትና የመመለስ (የሚጠት) ታሪክ እያነሡ ውዳሴ የሚያቀርቡትና ማኅሌት የሚቆሙት በዚሁ ምክንያት ነው፡፡ በዚህ ወቅት ለእመቤታችን ክብር ሲባል የፈቃድ ጾም የሚጾሙ ምዕመናንና ምዕመናትም ብዙዎች ናቸው፡፡

መምህር ክፍሌ ወልደ ጻድቅ ‹የጽጌ ዚቅ› በሚለው፣ ዓመተ ምሕረት በሌለውና በእጅ ጽሑፍ ተዘጋጅቶ በታተመው መጽሐፋቸው ከገጽ 1 – 75 እንደ ገለጹት ከበዓለ ጽጌ ጋር የጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ፤ የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም፤ የቅዱን መላእክት፤ የቅዱሳም ጻድቃን እና የቅዱሳን ሰማዕታት በዓላት አብረው ይከበራሉ፡፡ ለአብነትም የሥላሴ፤ የአማኑኤል፤ የዐርባዕቱ እንስሳ፤ የሩፋኤል፤ የኪዳነ ምሕረት፤ የመጥምቀ መለኮት ዮሐንስ (ፅንሰቱ)፤ የእስጢፋኖስ፤ የወንጌላውያኑ ማቴዎስና የማርቆስ፤ የዘብዴዎስ ልጆች የያዕቆብና የዮሐንስ፤ የቶማስ ዘህንደኬ፤ የሐና፤ የአቡነ አረጋዊ፤ የቂርቆስ፤ የአባ ኤዎስጣቴዎስ፤ የአብርሃም፣ የይስሐቅና የያዕቆብ፤ የአብርሃ አጽብሐ ነገሥትና የሌሎችም ቅዱሳን በዓላት ተጠቃሾች ናቸው፡፡

በአጠቃላይ በዘመነ ጽጌ ዘወትር እሑድ፣ እሑድ በመላ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ አብያተ ክርስቲያናት ማኅሌት በመቆም ታላቅ በዓል ይደረጋል፡፡ የዐርባ ቀኑ ዘመነ ጽጌ (ወርኀ ጽጌ) መታሰቢያነቱ ለቅድስት ድንግል ማርያምና ለጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡ እመቤታችን ልጇን ይዛ ከሰሎሜና ከዮሴፍ ጋር ወደ ምድረ ግብጽ በተሰደዱ ጊዜ የደረሰባትን ጭንቅና ውኃ ጥም፤ ግፍና እንግልት ለማስታወስና ከግብጽ ወደ ሀገሯ ናዝሬት መመለስዋን (ሚጠቷን) ለመዘከር ሲባል በዘመነ ጽጌ የደመቀ አገልግሎት ይከናወናል፡፡ በዚህ ወቅት የሚቆመው የሰንበት ማኅሌቱ፣ መዝሙሩና ቅዳሴው እንደዚሁም የሚቀርበው የክብር ይእቲና የዕጣነ ሞገር ቅኔ ሁሉ በዘመነ ጽጌ ላይ የተመሠረተ ነው፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር፡፡