የቅዱስ ዮሐንስ መጥምቅ ልደት

በዲያቆን ኤፍሬም የኔሰው

 ሰኔ ቀን ፳፻፱ .

ዮሐንስ ማለት ‹‹እግዚአብሔር ጸጋ ነው›› ማለት ነው፡፡ ቅዱስ ወንጌልም መጥምቀ መለኮት ዮሐንስን ፍሥሐ ወሐሴት (ተድላና ደስታ) ይለዋል፤ ወላጆቹ በእርሱ መወለድ ተደስተዋልና (ሉቃ. ፩፥፲፬)፡፡ ቅዱስ ዮሐንስ ሰኔ ፴ ቀን የተወለደበት፤ መስከረም ፩ ቀን ቃል ኪዳን የተቀበለበት፤ መስከረም ፪ ቀን በሰማዕትነት ያረፈበት፤ ጥር ፲፩ ቀን ጌታችንን ያጠመቀበት፤ የካቲት ፴ ቀን ራሱ የተገኘችበት፤ ሚያዝያ ፲፭ ቀን ራሱ ያረፈችበት (ነፍሱ የወጣችበት)፤ ሰኔ ፪ ቀን ደግሞ ፍልሰተ ዐፅሙ (ዐፅሙ የፈለሰበት) በዓል በቤተ ክርስቲያናችን በየዓመቱ ይከበራል፡፡ በዛሬው ዝግጅታችንም የልደቱን ታሪክ በአጭሩ እናስታውሳችኋለን፤

በቅዱስ ሉቃስ ወንጌል ምዕራፍ አንድ፣ ከቍጥር አንድ ጀምሮ እንደ ተገለጸው ካህኑ ዘካርያስ እና ሚስቱ ቅድስት ኤልሳቤጥ የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ዅሉ በመፈጸም ያለ ነቀፋ የሚኖሩ ጻድቃን ነበሩ፡፡ ኤልሳቤጥም መካን ነበረችና ልጅ አልነበራቸውም፡፡ ልጅ ይሰጣቸው ዘንድም እግዚአብሔርን ዘወትር ይማጸኑት ነበር፡፡ ካህኑ ዘካርያስ ወደ ቤተ መቅደስ ገብቶ ዕጣን በማሳረግ ላይ ሳለም የእግዚአብሔር መልአክ በዕጣኑ መሠዊያ ቀኝ ቆሞ ጸሎቱ እንደ ተሰማና ሚስቱ ቅድስት ኤልሳቤጥ እንደምትወልድ፤ ስሙንም ዮሐንስ እንደሚለው፤ በመወለዱም ብዙዎች እንደሚደሰቱ፤ ልጁም በእግዚአብሔር ፊት ታላቅ እንደሚኾን፤ የወይን ጠጅ እና የሚያሰክር መጠጥ እንደማይጠጣ፤ እንደዚሁም ከእናቱ ማኅፀን ጀምሮ መንፈስ ቅዱስ እንደሚሞላበት ነገረው፡፡

ካህኑ ዘካርያስም መልአኩን ‹‹እኔ ሽማግሌ ነኝ፤ ሚስቴም አርጅታለችና ይህን በምን አውቃለሁ?›› አለው፡፡ መልአኩም ‹‹እኔ በእግዚአብሔር ፊት የምቆመው ገብርኤል ነኝ፤ እንድናገርህም ይህችንም የምሥራች እንድሰብክልህ ተልኬ ነበር፡፡ እነሆም በጊዜው የሚፈጸመውን ቃሌን ስላላመንህ ይህ ነገር እስከሚኾን ቀን ድረስ ዲዳ ትኾናለህ፤ መናገርም አትችልም›› አለው፡፡ ከውጪ ቆመው ጸሎት ሲያደርጉ የነበሩት ሕዝብም ዘካርያስን ከቤተ መቅደስ እስኪወጣ ይጠብቁት ነበር፤ በመዘግየቱም ይደነቁ ነበር፡፡ ከቤተ መቅደስ በወጣም ጊዜ ሊያናግራቸው ባለመቻሉ ይጠቅሳቸው ነበር፡፡ በኹኔታውም በቤተ መቅደስ ራእይ እንዳየ አስተዋሉ፡፡ እርሱም ድዳ ኾኖ ኖረ፡፡ የማገልገሉም ወራት ሲፈጸምም ወደ ቤቱ ሔደ፤ ከሁለት ቀን በኋላም አረጋዊቷ ቅድስት ኤልሳቤጥ ፀነሰች፡፡ ቅድስት ኤልሳቤጥም በመካንነቷ ከሰዎች የሚደርስባት ሽሙጥ ተወግዷላታልና ‹‹እግዚአብሔር በዚህ ወራት ከሰው ስድቤን ያርቅ ዘንድ እንዲህ አደረገልኝ›› ስትል ለአምስት ወራት ተሸሸገች፡፡

የመውለጃዋ ቀን ሲደርስም ዘመነ ብሉይ ሊፈጸም፣ እግዚአብሔር ሰው ሊኾን (በሥጋ ሊገለጥ) ስድስት ወራት ሲቀረው፣ ሰኔ ፴ ቀን ንዑድ፣ ክቡር የኾነው መጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ ተወለደ፡፡ ዘመዶቹ ስሙን በአባቱ መጠርያ ዘካርያስ› ሊሉት ቢወዱም እናቱ ግን ‹‹ዮሐንስ ይባል› አለች፡፡ የመልአኩን የብሥራት ቃል ባለመቀበሉ አንደበቱ ተይዞ የነበረው ካህኑ ዘካርያም ስሙ ዮሐንስ ይባል ብሎ ሲጽፍ አፉ ተከፈተ፤ አንደበቱም ተፈታ፡፡ በመንፈስ ቅዱስ ተቃኝቶም ‹‹አንተ ሕፃን ሆይ! የልዑል ነቢይ ትባላለህ፤ መንገዱን ልትጠርግ በጌታ ፊት ትሔዳለህና፡፡ የኀጢአታቸው ስርየት የኾነውን የመዳን ዕውቀት ለሕዝቡ ትሰጣለህ፡፡ ይህም ከላይ የመጣ ብርሃን በጐበኘበት በአምላካችን ምሕረትና ርኅራኄ ምክንያት ነው፡፡ ብርሃኑም በጨለማና በሞት ጥላ ተቀምጠው ላሉት ያበራል፤ እግሮቻችንንም በሰላም መንገድ ያቀናል፤›› በማለት የቅዱስ ዮሐንስን ነቢይነት እና አጥማቂነት፣ እንደዚሁም የክርስቶስን የማዳን ትምህርት አብሣሪነት የሚመለከት ትንቢት አስቀድሞ ተናገሯል (ሉቃ. ፩፥፶፯-፸፱)፡፡

በአጠቃላይ መጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ ከአዲስ ኪዳን አበው አንዱ የኾነ፣ ንጹሓን ነቢያት፣ ቅዱስ ገብርኤልና አባቱ ዘካርያስ ትንቢት የተናገሩለት፤ ከሕፃንነቱ ጀምሮ ቅኑት እንደ ገበሬ፣ ጽሙድ እንደ በሬ ኾኖ እግዚአብሔርን ያገለገለ፤ በፍጹም ልቡ ዓለምን የናቀ፤ ከተድላዋና ከደስታዋም የተለየ፤ አምላክን ለማጥመቅ የታደለ ሐዋርያ፣ መምህር፣ ሰማዕት፣ ባሕታዊ፣ ነቢይ፣ ጻድቅ ነው፡፡ ሊቁም ከመላእክት፣ ከነቢያት፣ ከካህናት፣ ከሐዋርያት መካከል እንደርሱ መለኮትን ለማጥመቅ የተመረጠ አለመኖሩን በመጥቀስ ‹‹… ዮሐንስ ከማከ ሶበ ፈተዉ ወጽሕቁ፤ እሳተ ነዳዴ ኢተክህሎሙ ያጥምቁ፤ ራጉኤል በትጋሁ ወኢዮብ በጽድቁ፤ዮሐንስ ሆይ! ራጉኤል በትጋቱ፣ ኢዮብም በጽድቁ ቢመኙም ኾነ ቢጨነቁ እንደ አንተ የሚነድ እሳትን (መለኮትን) ሊያጠምቁ አልተቻላቸውም›› ሲል ታላቅነቱን መስክሮለታል (መልክአ ዮሐንስ መጥምቅ፣ ለአዕይንቲከ)፡፡

የቅዱስ ዮሐንስ በረከቱ ይደርብን፤ ጸሎቱ ይጠብቀን፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር፡፡

ምንጭ፦

  • መጽሐፈ ስንክሳር፣ ሰኔ ፴ ቀን፤
  • የሉቃስ ወንጌል አንድምታ ትርጓሜ፣ ሉቃ. ፩፥፩-፹፤
  • ገድለ ዮሐንስ መጥምቅ፡፡

ዘመነ ክረምት – ክፍል አንድ

በዲያቆን ኤፍሬም የኔሰው

ሰኔ ፳፱ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም

በቤተ ክርስቲያናችን አስተምህሮ ወቅቶች በአራት ይከፈላሉ፡፡ በቅዱስ ያሬድ የዜማ መጻሕፍት፣ እንደዚሁም በመጽሐፈ ግጻዌ እንደ ተገለጸው እነዚህም፡- ዘመነ መጸው (መከር)፣ ዘመነ ሐጋይ (በጋ)፣ ዘመነ ጸደይ (በልግ) እና ዘመነ ክረምት ይባላሉ፡፡ ከአራቱ ወቅቶች መካከል ከሰኔ ፳፭ እስከ መስከረም ፳፭ ቀን ድረስ ያለው ጊዜ (አሁን የምንገኝበት ወቅት) ዘመነ ክረምት ተብሎ ይጠራል፡፡

እንደ ማስገንዘብያ፡- ክረምቱ የሚጀምረው ሰኔ ፳፮ ቀን ቢኾንም ከዋይዜማው ጀምሮ የሚነገረው ቃለ እግዚአብሔር ዘመነ ክረምትን የሚመለከት ስለ ኾነ ከሰኔ ፳፭ ቀን ጀምረን መቍጠር እንችላለን፡፡ መምህራነ ቤተ ክርስቲያን እንዳስረዱን ከዋይዜማው ወይም ከመነሻው ጀምረን ቀኑን መጥቀሳችን የአስተምህሮ ለውጥ አያመጣም፡፡ ይህ አቈጣጠር ለሌሎች ወቅቶች እና ለዘመነ ክረምት ክፍሎችም ተመሳሳይ መኾኑን ከወዲሁ ለማስገንዘብ እንወዳለን፡፡

የተወደዳችሁ የማኅበረ ቅዱሳን ድረ ገጽ ተከታታዮች! በዚህ ዝግጅት ዘመነ ክረምትን የሚመለከት ተከታታይ ትምህርት ይዘን ቀርበናል፡፡ መልካም የንባብ ጊዜ!

‹ክረምት› ከረመ፣ ከረመ ካለው የግእዝ ቃል የተገኘ ሲኾን፣ ትርጕሙም የዝናም፣ የአዝርዕት፣ የአረም ጊዜ፤ እንደዚሁም ዕፅዋት፣ አዝርዕትና አትክልት በቅለው፣ ለምልመው የሚያድጉበት፣ ምድር በአረንጓዴ ዕፀዋትና በልምላሜ የምታሸበርቅበት ወቅት ማለት ነው፡፡ ይኸው ዘመነ ክረምት በሰባት ንዑሳን ክፍሎች ይመደባል፤ የክፍፍሉ መሠረት ሊቁ ቅዱስ ያሬድ ሲኾን፣ ክፍሎቹም የሚከተሉት ናቸው፤

፩ኛ ከሰኔ ፳፮ እስከ ሐምሌ ፲፰ ቀን ያለው ጊዜ በአተ ክረምት ወይም ዘርዕ፣ ደመና፤

፪ኛ ከሐምሌ ፲፱ እስከ ነሐሴ ፱ ቀን ያለው ጊዜ መብረቅ፣ ነጎድጓድ፣ ባሕር፣ አፍላግ፣ ጠል፤

፫ኛ ከነሐሴ ፲ – ፳፯ ቀን ዕጕለ ቋዓት፣ ደሰያት፣ ዓይነ ኲሉ፤

፬ኛ ከነሐሴ ፳፰ እስከ ጳጉሜን ፭ (፮) ቀን ጎህ፣ ነግህ፣ ጽባህ፣ ብርሃን፣ መዓልት፤

፭ኛ ከመስከረም ፩ – ፯ ቀን ዮሐንስ፤

፮ኛ ከመስከረም ፰ – ፲፬ ቀን ፍሬ፤

፯ኛ ከመስከረም ፲፭ – ፳፭ ቀን ፀአተ ክረምት (የክረምት መውጫ) ወይም ዘመነ መስቀል፡፡

እያንዳንዱን ክፍለ ክረምትም በመጠኑ እንደሚከተለው ለመዳሰስ እንሞክራለን፤

፩. በአተ ክረምት (ዘርዕ፣ ደመና)

ከሰኔ ፳፮ እስከ ሐምሌ ፲፰ ቀን ድረስ ያለው የመጀመሪያው የክረምት ክፍለ ጊዜ በአተ ክረምት ወይም ዘርዕ፣ ደመና ይባላል፡፡ በዚህ ወቅት ስለ ክረምት መግባት፣ ስለ ዘርዕ፣ ስለ ደመና እና ስለ ዝናም የሚያዘክሩ መዝሙራትና ምንባባት ይዘመራሉ፤ ይነበባሉ፡፡ ይህ ወቅት ደመና ሰማዩን የሚሸፍንበት፤ የዝናም መጠን የሚያይልበትና መሬት በዝናም ረክታ ዘር የምታበቅልበት ጊዜ ነው፡፡

በአተ ክረምት (የክረምት መግብያ)

በዘመነ ክረምት መጀመርያ (መግብያ) ሳምንት በቤተ ክርስቲያናችን የሚቀርበው የቅዱስ ያሬድ መዝሙር የሚከተለው ነው፤

‹‹ደምፀ እገሪሁ ለዝናም ሶበ ይዘንም ዝናም ይጸግቡ ርኁባን ደምፀ እገሪሁ ለዝናም ሶበ ይዘንም ዝናም ይትፌሥሑ ነዳያን ደምፀ እገሪሁ ለዝናም ወሠርዐ ሰንበተ ለሰብእ ዕረፍተ ደምፀ እገሪሁ ለዝናም ደምፀ እገሪሁ ለዝናም››

የመዝሙሩ ቀጥተኛ ትርጕም፡-

‹‹የዝናም ኮቴው ተሰማ፡፡ ዝናም በሚዘንም ጊዜ የተራቡ ይጠግባሉ፡፡ የዝናም ኮቴው ተሰማ፡፡ ዝናም በሚዘንም ጊዜ ድሆች ይደሰታሉ፡፡ የዝናም ኮቴው ተሰማ፡፡ አምላካችን ለሰው ልጅ ዕረፍት ሰንበትን ፈጠረ፡፡ የዝናም ኮቴው ተሰማ፡፡ የዝናም ኮቴው ተሰማ፡፡››

ይህ መዝሙር ከሰኔ ፳፮ ጀምሮ ያለው ወቅት ክረምቱ የሚገባበት እና ዝናም በብዛት የሚጥልበት ጊዜ መኾኑን የሚያበሥር ሲኾን፣ በተጨማሪም ዝናም በሚዘንብበት ጊዜ የሚበቅለውን እኽልና የምንጮችን መብዛት ተስፋ በማድረግ የተራቡ እንደሚጠግቡ፤ የተጠሙም እንደሚረኩ የሚያትት ምሥጢር ይዟል፡፡ እንደዚሁም ጊዜ ለበጋ፣ ጊዜ ለክረምት የሚሰጥ አምላክ ለሰው ልጅ ማረፊያ ትኾን ዘንድ ዕለተ ሰንበትን መፍጠሩንም ያስረዳል፡፡ በዚህ ሳምንት በዕለተ ሰንበት በቅዳሴ ጊዜ የሚነበቡ ምንባባትም የሚከተሉት የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች ናቸው፤

፩ኛ ቆሮንቶስ ፲፭፥፴፫ – ፶፩

ፍሬ ዐሳቡ፡- አዝርዕት በስብሰው እንደሚበቅሉ ዅሉ የሰው ልጅም ከሞተ በኋላ ከሞት እንደሚነሣ፤ ሲነሣም እግዚአብሔር እንደ ሥራው መጠን ዋጋውን እንደሚከፍለው፤ እንደዚሁም የሰው ልጅ ሞቱንና የሚያገኘውን ሰማያዊ ዋጋ በማሰብ ከኀጢአት መለየት እንደሚገባው ያስረዳል፡፡

ያዕቆብ ፭፥፲፮ እስከ ፍጻሜው

ፍሬ ዐሳቡ፡- ነቢዩ ኤልያስ በጸሎት ዝናም እንዳይዘንምና እንደገና እንዲጥል ማድረጉን በመተረክ እኛም እምነቱ ካለን በጸሎት ኹሉን ማድረግ እንደሚቻለን ይናገራል፡፡

ግብረ ሐዋርያት ፳፯፥፲፩ – ፳፩

ፍሬ ዐሳቡ፡- ቅዱስ ጳውሎስና ተከታዮቹ መርከባቸው በማዕበል ክፉኛ መናወጧንና በእግዚአብሔር ኃይል መዳናቸውን፤ በባሕሩ ውስጥም በጨለማ ለብዙ ጊዜ መቆየታቸውን በማውሳት ይህ ወቅት (ዘመነ ክረምት) የውኃና የነፋስ ኃይል የሚያልበት ጊዜ መኾኑን ያስተምራል፡፡

ምስባክ፡- መዝሙር ፻፵፮፥፰

ኃይለ ቃሉ፡- ‹‹ዘይገለብቦ ለሰማይ በደመና ወያስተዴሉ ክረምተ ለምድር ዘያበቍል ሣዕረ ውስተ አድባር፡፡››

የመዝሙሩ ቀጥተኛ ትርጕም፡- ‹‹ሰማዩን በደመና የሚሸፍን፣ ለምድርም ዝናምን የሚያዘጋጅ፣ ሣርን በተራሮች ላይ የሚያበቅል እርሱ ነው፡፡››

የመዝሙሩ ፍሬ ዐሳብ፡- እግዚአብሔር ሰማዩን በደመና የሚሸፍን፤ ዝናምንም (ክረምትን) ለምድር (ለሰው ልጅ) የሚያዘጋጅ፤ እንደዚሁም በተራሮች ላይ ሣርን (ዕፀዋትን) የሚያበቅል አምላክ መኾኑን ያስገነዝባል፡፡

ወንጌል፡- ሉቃስ ፰፥፩-፳፪

ፍሬ ዐሳቡ፡- ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ቃለ እግዚአብሔርን በዘርዕ፣ የምእመናንን ልቡና (የመረዳት ዓቅም) ደግሞ በመንገድ፣ በዓለት፣ በእሾኽና በመልካም መሬት በመመሰል ቃሉን ሰምተው በሚለወጡትና በሚጠፉት መካከል ስላለው ልዩነት ማስተማሩን ያስረዳል፡፡

ቅዳሴው፡- ቅዳሴ ኤጲፋንዮስ ሲኾን ይህ ቅዳሴ ስለ ዝናም፣ ደመና፣ መብረቅ፣ ባሕርና መሰል ፍጥረታት ዑደት፤ እንደዚሁም እግዚአብሔር ዓለማትን በጥበቡ ፈጥሮ የሚገዛና የሚመግብ አምላክ መኾኑን ስለሚያብራራ በዘመነ ክረምት ይቀደሳል፡፡

ጠቅለል አድርገን ስንገልጸው በዘመነ ክረምት መጀመርያ ሳምንት ከአዝርዕት፣ ከዝናም፣ ከልምላሜ፣ ከውኃ ሙላትና ከባሕር ሞገድ ጋር ተያያዥነት ያላቸው ትምህርቶች ከሰው ልጅ ሕይወትና ከምግባሩ እንደዚሁም በምድር ከሚያጋጥሙት ፈተናዎች ጋር እየተነጻጸሩ ይቀርባሉ፡፡ የወቅቱን ትምህርት ከሕይወታችን ጋር አያይዘን ስንመለከተውም ዘመነ ክረምት የክርስትና ምሳሌ ነው፡፡ ገበሬ በክረምት ብርዱንና ዝናሙን ሳይሰቀቅ ለሥራ ይሰማራል፤ በበጋው የእጁን ፍሬ ያገኝ ዘንድ የክረምቱን መከራ ይታገሣል፡፡ ይህም ምእመናን በሰማያዊው ዓለም የምናገኘውን ተድላና ደስታ በማሰብ በምድር ቆይታችን የሚደርስብንን ልዩ ልዩ መከራ በትዕግሥት ማሳለፍ እንደሚገባን ያስገነዝባል፡፡

ይቆየን

ለተተኪ መምህራን ሥልጠና መስጠቱን የአሜሪካ ማእከል አስታወቀ

ሠልጣኞቹ ከአሠልጣኝ መምህራን እና ከኦሀዮ ደ/ሰ/ቅ/ገብርኤል ቤ/ክ የመስተንግዶ ኮሚቴ አባላት ጋር

ሰኔ ፳፯ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሰንበት ት/ቤቶች ማደራጃ መምርያ ማኅበረ ቅዱሳን የአሜሪካ ማእከል በኒውዮርክ ሀገረ ስብከት በኮሎምበስ ኦሀዮ ደብረ ሰላም ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን ከሰኔ ፲፮ – ፲፰ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም ለሦስት ቀናት የቆየ የተተኪ መምህራን ሥልጠና መስጠቱን አስታወቀ፡፡

እንደ ማእከሉ ማብራርያ በማእከሉ የትምህርት፣ ሐዋርያዊ ተልእኮ እና የምክር አገልግሎት ዋና ክፍል አዘጋጅነት በተሰጠው በዚህ ሥልጠና በቍጥር ከዐሥር ከሚበልጡ ስቴቶች ከየንዑሳን ማእከላቱ የተወከሉ የቤተ ክርስቲያን አገልጋይ ቀሳውስት፣ ዲያቆናት እና የሰንበት ት/ቤት ወጣቶች የተሳትፉ ሲኾን፣ የሥልጠናው ዓላማም ሠልጣኞቹ በስብከተ ወንጌል ሊያገለግሉ የሚችሉበትን ዕውቀትና ክህሎት እንዲያዳብሩ ለማገዝ ነው፡፡

ትምህርተ ሃይማኖት (ዶግማ)፣ መንፈሳዊ አስተዳደር፣ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት፣ የቤተ ክርስቲያን ታሪክ፣ ምሥጢራተ ቤተ ክርስቲያን፣ ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን፣ የስብከት ዘዴ እና ክብረ ቅዱሳን በሥልጠናው የተካተቱ የትምህርት ክፍሎች ሲኾኑ፣ መልአከ ጽዮን ቀሲስ በላቸው ወርቁ፣ መልአከ ሰላም ቀሲስ ያሬድ ገብረ መድኅን፣ ቀሲስ ኅብረት የሺጥላ፣ መምህር ሙሉጌታ ኃይለ ማርያም እና መምህር ብርሃኑ አድማስ ሥልጠና በመስጠት የተሳተፉ መምህራን ናቸው፡፡

ለሦስት ቀናት በተሰጠው በዚህ ሥልጠና በወቅታዊ የቤተ ክርስቲያን ጉዳዮች ላይ ሰፊ ውይይት የተደረገ ሲኾን፣ በውይይቱ በቂ ግንዛቤ እንዳገኙ ከሠልጣኞቹ ለመረዳት መቻሉንም ማእከሉ በዘገባው አትቷል።

በሥልጠናው የመፈጸሚያ ዕለት እሑድ ከቅዳሴ በኋላ በተደረገው የምረቃ መርሐ ግብር በመምህር ብርሃኑ አድማስ ትምህርተ ወንጌል የተሰጠ ሲኾን፣ ሠልጣኞቹም ያሬዳዊ ዝማሬ አቅርበዋል፡፡ በማእከሉ የተዘጋጀው የምስክር ወረቀትም በመልአከ ጽዮን ቀሲስ በላቸው ወርቁ አማካይነት ለሠልጣኞች ተበርክቷል፡፡

በመርሐ ግብሩ ማጠቃለያ የደብረ ሰላም ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን አስተዳዳሪ ቀሲስ ያሬድ ገብረ መድኅን ሥልጠናው በደብራቸው በመሰጠቱ እርሳቸውም ኾኑ ምእመናኑ እጅግ መደሰታቸውን ከገለጹ በኋላ ለወደፊት ሥልጠናው በየጊዜው ሲዘጋጅ ደብራቸው በመስተንግዶ ተባባሪ እንደሚኾን ቃል ገብተዋል።

መልአከ ጽዮን ቀሲስ በላቸው ወርቁ በበኩላቸው ሥልጠናው ተግባራዊ በመኾኑ የተሰማቸው ደስታ ወሰን እንደ ሌለው ገልጸው ሠልጣኞቹ በተሰጣቸው አደራ ቤተ ክርስቲያንን በትጋት እንዲያገለግሉ መክረዋል።

አያይዘውም ለሥልጠናው መሳካት አስተዋጽዖ ያደረጉ የማእከሉ ሥራ አስፈጻሚ አባላትን፣ ሥልጠናውን በትጋት ያስተባበሩ የትምህርት ክፍል ሓላፊዎችን፣ እንደዚሁም የምግብና መኝታ ሙሉ ወጭውን በመቻል በመስተንግዶው ድጋፍ ያበረከቱ ቀሲስ ያሬድ ገብረ መድኅንን፣ በአጠቃላይ የኦሀዮ ደ/ሰ/ቅ/ገብርኤል ሰበካ ጉባኤ አመራር አባላትን እና ሕዝበ ክርስቲያኑን መልአከ ጽዮን ቀሲስ በላቸው ወርቁ ከልብ አመስግነዋል።

የአሜሪካ ማእከል ሰብሳቢ አቶ ማስተዋል ጌጡ በዕለቱ ባስተላለፉት መልእክት ሠልጣኞቹ በሥልጠናው የቀሰሙትን ትምህርት አስፋፍተውና አሳድገው የቅድስት ቤተ ክርስቲያንን ሐዋርያዊ ተልእኮ በማፋጠን የድርሻቸውን እንዲወጡ አሳስበዋል።

በመጨረሻም የተተኪ መምህራን ሥልጠናው ለወደፊትም በየዓመቱ እንደሚሰጥ ያስታወቁት ሰብሳቢው፣ ከአሁን በፊት የሥልጠና ዕድሉን ያላገኙ ቀሳውስት፣ ዲያቆናት እና የሰንበት ት/ቤት ወጣቶች ሥልጠናውን እንዲወስዱ ለማድረግ ማኅበረ ቅዱሳን ቅድመ ኹኔታዎችን በማመቻቸት ላይ እንደሚገኝ አስገንዝበዋል፡፡

‹‹እናንተ የቤተ ክርስቲያን ባለ አደራዎች ናችሁ›› – ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ

በዲያቆን ኤፍሬም የኔሰው

ሰኔ ፳፮ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት የቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ ደቀ መዛሙርቱን ባስመረቀበት ዕለት ተገኝተው በሰጡት ቃለ ምዕዳን ‹‹እናንተ የቤተ ክርስቲያን ባለ አደራዎች ናችሁ›› በማለት ተመራቂዎቹ ወንጌልን ከዳር እስከ ዳር የማዳረስ አደራ እንዳለባቸው አስገንዝበዋል፡፡

‹‹እናንተ ከመልካም ዛፍ የተገኛችሁ መልካም ፍሬዎች እንደ መኾናችሁ ይህን ፍሬያችሁን እንድታካፍሉ ቤተ ክርስቲያን አደራ ትላችኋለች›› ያሉት ቅዱስነታቸው ‹‹መብራታችሁ በሰዉ ዅሉ ፊት ይብራ›› የሚለውን የወንጌል ቃል መነሻ አድርገው በከተማ ብቻ ሳይወሰኑ በየገጠሩ በመዘዋወር በአታላዮች የሚወሰዱ ወገኖችን እንዲጠብቁ እና እንዲያስተምሩ ተመራቂዎቹን አሳስበዋል፡፡

ቅዱስ ፓትርያርኩ፣ በየገጠሩ አንድ ሰባኬ ወንጌል ጠፍቶ በየከተሞች በተለይም በአዲስ አበባ በአንድ አጥቢያ ከሁለት በላይ መምህራን መመደባቸውን ተችተዋል፡፡

ሴቶች በመንፈሳዊ ኮሌጁ ተምረው በመመረቃቸውና ከፊሎቹም ከፍተኛ ውጤት በማስመዝገባቸው መደሰታቸውን የገለጹት ቅዱስነታቸው፣ ይህን ፈለግ ተከትለው በየኮሌጆቹ የሚሰጠውን ትምህርተ ሃይማኖት እንዲከታተሉና ራሳቸውን በቃለ እግዚአብሔር እንዲያጎለብቱ እናቶችና እኅቶችን መክረዋል፡፡

በመጨረሻም ተመራቂዎቹ በሚሠማሩበት ቦታ ዅሉ በስብከተ ወንጌል ተግተው በማገልገል፤ የቤተ ክርስቲያን አባቶች ደግሞ የሰባክያነ ወንጌልን አገልግሎት በመቈጣጠር፤ ምእመናኑም ከትክክለኞች መምህራን ትክክለኛውን ቃለ ወንጌል በመማር መንፈሳዊ ሓላፊነታቸውን እንዲወጡ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ አባታዊ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ ደቀ መዛሙርቱን ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያኩ፣ ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት፣ ሰባክያነ ወንጌል፣ አባቶች ካህናት፣ ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች እና የተመራቂ ቤተሰቦች በተገኙበት ሰኔ ፳፬ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም በጠቅላይ ቤተ ክህነት ስብከተ ወንጌል አዳራሽ በቅዱስ ፓትርያርኩ ቡራኬ አስመርቋል፡፡

ኮሌጁ ደቀ መዛሙርቱን ያስመረቀው በቀን፣ በማታ በተመላላሽ እና በርቀት መርሐ ግብር፤ በልዩ ልዩ የትምህርት ክፍል፤ በማስተርስ፣ በዲግሪ እና በዲፕሎማ ማዕረግ ነው፡፡ በዕለቱ ተመራቂዎቹ ባለ አምስት አንቀጽ የአገልግሎት ቃል ኪዳናቸውን በተወካያቸው አማካይነት አቅርበዋል፡፡ ሴቶች እኅቶቻችንም በልዩ ልዩ ማዕረግ የተመረቁ ሲኾን ከእነርሱ መካከል ጥቂቶቹ ከፍተኛ ውጤት በማስመዝገብ መሸለማቸው ቅዱስ ፓትርያርኩን ጨምሮ ብዙዎችን አስገርሟል፡፡

የቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ ከተመሠረተበት ጊዜ አንሥቶ እስከ አሁን ድረስ ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳትን ጨምሮ በርካታ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያንን ሲያፈራ የኖረና በማፍራት ላይ የሚገኝ አንጋፋ የትምህርት ማእከል ነው፡፡

የቤተ ክርስቲያን ባለ አደራዎች ሰባክያነ ወንጌል መፍለቂያ የኾነው ኮሌጁ ከኦርቶዶክሳዊው አስተምህሮ ያፈነገጠ የኑፋቄ ትምህርት ሲያዛምቱ የተገኙ ሰርጎ ገብ ተማሪዎችን ከአሁን በፊት አውግዞ እንደ ለየ፤ ለወደፊትም ኦርቶዶክሳዊው አስተምህሮ ሳይፋለስ ለትውልድ ይተላለፍ ዘንድ ሥርዓቱን የጠበቀ ትምህርት የመስጠት ተልእኮዉን አጠናክሮ እንደሚቀጥል በኮሌጁ የቦርድ ሥራ አመራር ሪፖርት ተገልጿል፡፡