ዘመነ ዕርገት – ካለፈው የቀጠለ

በዲያቆን ኤፍሬም የኔሰው

ግንቦት ቀን ፳፻፱ .

በቅዳሴ ጊዜ የሚነበቡ ምንባባትም በዕለተ ዕርገት (ሐሙስ) ከተነበቡት ጋር ተቀራራቢነት ያላቸው የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች ናቸው፡፡ ለማስታወስ ያህልም ከጳውሎስ መልእክት ሮሜ ፲፥፩ እስከ ፍጻሜው፤ ከሌሎች መልእክታት ፩ኛ ጴጥሮስ ፫፥፲፭ እስከ ፍጻሜው ድረስ ይነበባሉ፡፡ የሐዋርያት ሥራ፣ ምስባኩና ቅዳሴው ከሐሙስ ዕለቱ (ከዕርገት) ጋር አንድ ዓይነት ሲኾን ወንጌሉም ሐሙስ ጠዋት (በነግህ) የተነበበው ሉቃስ ፳፥፵፭ እስከ ፍጻሜው ድረስ ያለው ኃይለ ቃል ነው፡፡

በዘመነ ዕርገት ከሚቀርቡ ዝማሬያት መካከል ‹‹ዐርገ ሰማያተ በዐምደ ደመና›› የሚለው አንደኛው ሲኾን፣ ይህም ከእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ከሥጋዋ ሥጋ፣ ከነፍሷ ነፍስ የነሣ (የተዋሐደ)፤ ለእስራኤላውያን በሲና በረኀ መና ያወረደ፤ ሶስናን ከረበናት እጅ ያዳነ፤ ሰንበትን ለሰው ልጆች ዕረፍት የሠራ፤ የክርስትና ሃይማኖትን ያቀና (የመሠረተ)፤ ከሰማይ የወረደው የሕይወት እንጀራ፤ በባሕርዩ ምስጋና የሚገባው ጌታችን አምላካችንና መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በደመና ተጭኖ ወደ ሰማይ ማረጉን የሚያስረዳ ሰፊ ምሥጢር አለው፡፡

ሊቁ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ዐርባ ስድስተኛውን የመዝሙረ ዳዊት ክፍል በተረጐመበት አንቀጹ ‹‹‹ድል መንሳት ባለበት የነጋሪት ድምፅ እግዚአብሔር ዐረገ› አለ እንጂመላእክት አሳረጉት› አላለም፡፡ በፊቱ መንገድ የሚመራው አልፈለገም፡፡ በዚያው ጎዳና እርሱ ዐረገ እንጂ፤›› በማለት ጌታችን አምላካችንና መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በአምላካዊ ሥልጣኑ ወደ ሰማይ ማረጉን ተናግሯል፡፡ በተመሳሳይ ምሥጢር የጌታችንን ዕርገት ከነቢዩ ኤልያስ ዕርገት ጋር በማነጻጸር ነቢዩ ኤልያስ በመላእክት ርዳታ ወደ ሰማይ መወሰዱን፤ መድኀኒታችን ክርስቶስ ግን የመላእክት ፈጣሪ ነውና በእነርሱ ርዳታ ሳይኾን በገዛ ሥልጣኑ ማረጉን ሊቁ ያስረዳል (፪ኛነገ.፪፥፩-፲፫፤ ሐዋ.፩፥፱-፲፪)፡፡

ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ በተጨማሪም ‹‹ሕማም የሚስማማው ግዙፍ ሥጋን ተዋሕዶ ሳለ ከስቅለቱ አስቀድሞ በባሕር ላይ ከሔደ፣ ዛሬ ነፋስን ከፍሎ ሲያርግ ቢታይ ማንም ማን አይጠራጠር፡፡ ሥጋው አልተለወጠምና፤››  ሲል ጌታችን ከሞቱና ከትንሣኤው አስቀድሞ በውኀ ላይ እንደ ተራመደ ዅሉ፣ ከሙታን ተለይቶ ከተነሣ በኋላም በለበሰው ሥጋ በክብር በምስጋና ወደ ሰማይ ማረጉን አስረድቷል (ሃይማኖተ አበው ዘዮሐንስ አፈወርቅ፤ ክፍል ፲፫፣ ምዕ.፷፯፥፲፪-፲፭)፡፡

መጽሐፈ ስንክሳርም በዓለ ዕርገት የክብር ባለቤት ጌታችንና መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከእኛ በነሣው ሥጋ ከአባቱና ከመንፈስ ቅዱስ ጋራ ወዳለው የአንድነት አኗኗሩ ወደ ሰማይ ያረገበት ዕለት መኾኑን ጠቅሶ፣ ‹‹ያን ጊዜ በኪሩቤል ላይ ተቀምጦ ወጣ፤ በነፋሳትም ክንፎች ላይ ኾኖ ወጣ፤›› (መዝ.፲፯፥፲) የሚለው የዳዊት ትንቢት በዚህች ቀን መፈጸሙን ያትታል፡፡ በተጨማሪም ‹‹ሌሊት በራእይ አየሁ፤ እነሆም እንደ ሰው ልጅ የሚመስል በሰማይ ደመና መጣ፡፡ በዘመናትም ወደ ሸመገለው ደረሰ፡፡ ወደ ፊቱም አቀረቡት፡፡ ወገኖችና አሕዛብ፣ በልዩ ልዩ ቋንቋም የሚናገሩ ኹሉ ይገዙለት ዘንድ ግዛትና ክብር፣ መንግሥትም ተሰጠው፡፡ ግዛቱም የማያልፍ የዘለዓለም ግዛት፤ መንግሥቱም የማይጠፋ ነው፤›› የሚለው የነቢዩ ዳንኤል ትንቢት በጌታችን ዕርገት መፈጸሙን ይናገራል (ዳን.፯፥፲፫-፲፬፤ መጽሐፈ ስንክሳር፣ ግንቦት ፰ ቀን)፡፡

ከላይ እንደ ተመለከትነው በዘመነ ዕርገት በማኅሌት፣ በቅዳሴ፣ በመሥዋዕት ጊዜ በቤተ ክርስቲያን የሚሰጡ ትምህርታት፣ የሚቀርቡ መዝሙራትና የሚነበቡ መጻሕፍት የእግዚአብሔርን ሰው መኾን፣ ተአምራቱን፣ ሕማሙን፣ ሞቱን፣ ነፍሳትን ከሲኦል ማውጣቱን፣ ትንሣኤውን፣ ለሐዋርያትና ለቅዱሳት አንስት መግለጡን፣ በተለይ ደግሞ ዕርገቱን፣ ዳግም ምጽአቱንና ምእመናን በእርሱ አምነው የሚያገኙትን ድኅነት፣ ጸጋና በረከት፣ እንደዚሁም የመንግሥተ ሰማያትን ምሥጢር የሚያስረዳ ይዘት አላቸው፡፡

ከዚሁ ዅሉ ጋርም ምርኮን (የነፍሳትን ወደ ገነት መማረክ) የሚያትቱ ትምህርቶች የሚሰጡትም በዚህ በዘመነ ዕርገት ወቅት ሲኾን፣ ይኸውም በሰይጣን ባርነት ተይዘው ይኖሩ የነበሩ ነፍሳት በኢየሱስ ክርስቶስ አምላካዊ ሥልጣን ነጻ መውጣታቸውን ያመለክታል፡፡ ‹‹ምርኮን ማረከህ፤ ወደ ሰማይም ወጣህ፡፡ ስጦታህንም ለሰዎች ሰጠህ፡፡ ያድሩ ዘንድ ይክዱ ነበርና፤›› እንዳለ ቅዱስ ዳዊት (መዝ.፷፯፥፲፰)፡፡ ይህም ጌታችን ነፍሳትን ከሲኦል ወደ ገነት እንደ መለሰ እና ለምእመናን የሥላሴ ልጅነትን እንደ ሰጠ የሚያስረዳ ሲኾን፣ ‹‹ያድሩ ዘንድ ይክዱ ነበር›› ሲልም በክህደት ይኖሩ የነበሩ ዅሉ ጌታችን በሰጠው ልጅነት ተጠርተው፣ አምነውና በሃይማኖት ጸንተው መኖራቸውን ያጠይቃል፡፡

በአጠቃላይ ዘመነ ዕርገት ወደ ላይ የመውጣት፣ የማረግ፣ ከፍ ከፍ የማለትና የማደግ ወቅት ነው፡፡ ይኸውም በአካል ማረግን (ከፍ ከፍ ማለትን) ወይም ወደ ሰማይ መውጣትን ብቻ ሳይኾን፣ በአስተሳሰብና በምግባር መለወጥን፣ በአእምሮ መጐልመስንም ያመለክታል፡፡ ከዅሉም በላይ መድኀኒታችን ክርስቶስ ወደ ሰማይ እንደ ዐረገ እና ዳግም ለፍርድ ተመልሶ እንደሚመጣ በስፋት የሚነገርበት ወቅት ነው – ዘመነ ዕርገት፡፡ ‹‹እናንተ የገሊላ ሰዎች ሆይ! ወደ ሰማይ እየአያችሁ ስለ ምን ቆማችኋል? ይህ ከእናንተ ወደ ሰማይ ያረገው ኢየሱስ፣ ወደ ሰማይ ሲሔድ እንዳያችሁት እንዲሁ ዳግመኛ ይመጣል፤›› ተብሎ እንደ ተጻፈ (ሐዋ.፩፥፲፩)፡፡ እኛም ሞት የማያሸንፈው አምላክ የኢየሱስ ክርስቶስ ልጆች እንደ መኾናችን በሞት ከመወሰዳችን በፊት (በምድር ሳለን) ለሰማያዊው መንግሥት የሚያበቃ መልካም ሥራ መሥራት ይጠበቅብናል፡፡ እናም ሕሊናችን በጽድቅ ሥራ እንዲያርግ (ከፍ ከፍ እንዲል) ዘወትር በሃይማኖታችን እንጽና፤ በክርስቲያናዊ ምግባር እንበርታ፤ በትሩፋት ሥራ እንትጋ፡፡

በሞቱ ሕይወታችንን ለመለሰልን፤ በትንሣኤው ትንሣኤያችንን፣ በዕርገቱ ክብራችንን ለገለጠልን፤ ዜና ብሥራቱን፣ ፅንሰቱን፣ ልደቱን፣ ዕድገቱን፣ ስደቱን፣ ተአምራቱን፣ ሕማሙን፣ ሞቱንና ትንሣኤውን በሰማንበት ዕዝነ ልቡናችን፣ ባየንበት ዓይነ ሕሊናችን ዕርገቱንም እንድንሰማና እንድናይ ዕድሜ ለንስሐ ሰጥቶ እስከ ዛሬ ድረስ እንደ ለጠበቀን ልዑል እግዚአብሔር ክብር ምስጋና ይደረሰው፡፡ ዳግም ለፍርድ በሚመጣበት ጊዜም ‹‹እናንተ ቡሩካን ወደ እኔ ›› የሚለውን የሕይወት ቃል እንዲያሰማን ቅዱስ ፈቃዱ ይኹንልን፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር፡፡

ምንጮች፡

  • መጽሐፍ ቅዱስ፣ የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፤ አዲስ አበባ፣ ፳፻ .ም፡፡
  • መዝሙረ ዳዊት ንባቡና ትርጓሜው፣ ተስፋ ገብረ ሥላሴ፤ አዲስ አበባ፣ ፲፱፻፹፪ .ም፡፡
  • ማኅቶተ ዘመን፣ / በሙሉ አስፋው፣ ገጽ ፻፺፩፻፺፬፤ አዲስ አበባ፣ ፳፻፩ .ም፡፡
  • ዝማሬ ወመዋሥዕት፣ ትንሣኤ ማሳተሚያ ድርጅት፤ አዲስ አበባ፣ ፲፱፻፹፱ .ም፡፡

ዘመነ ዕርገት 

በዲያቆን ኤፍሬም የኔሰው

ግንቦት ቀን ፳፻፱ .

‹ዕርገት› በግእዝ ቋንቋ ማረግ፣ ከታች ወደ ላይ መውጣት ማለት ሲኾን የጌታችን ትንሣኤ በተከበረ በዐርባኛው ቀን የሚውለው ዐቢይ በዓልም ‹ዕርገት› ይባላል (ኪዳነ ወልድ ክፍሌ፣ ገጽ ፯፻፷)፡፡ በዓለ ዕርገት ጌታችን አምላካችንና መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከሙታን ከተነሣ በኋላ ለዐርባ ቀናት በግልጽም በስውርም ለቅዱሳን ሐዋርያትና ለቅዱሳት አንስት መጽሐፈ ኪዳንን፣ ትርጓሜ መጻሕፍትን፣ ምሥጢራትን፣ ሕግጋትንና ቀኖናተ ቤተ ክርስቲያንን ሲያስተምር ቆይቶ ወደ ቀደመ ዙፋኑ ወደ ሰማይ በክብር በምስጋና ማረጉን በደስታ የምንዘክርበት ዐቢይ በዓል ነው፡፡ በዓለ ዕርገት በቤተ ክርስቲያናችን በየዓመቱ በድምቀት ይከበራል፡፡ በዓሉ የሚውልበት ዕለት ሐሙስን ባይለቅም ቀኑ ግን የአጽዋማትና በዓላት ማውጫ ቀመርን ተከትሎ ከፍ እና ዝቅ ይላል፡፡

በዚህ መሠረት የዘንድሮው በዓለ ዕርገት ግንቦት ፲፯ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም ይውላል ማለት ነው፡፡ ከጌታችን የዕርገት በዓል ጀምሮ (ከበዓለ ትንሣኤ ዐርባኛው ቀን) እስከ በዓለ ጰራቅሊጦስ ዋዜማ (ዐርባ ዘጠነኛው ቀን) ድረስ ያለው ወቅትም ‹ዘመነ ዕርገት› ተብሎ ይጠራል፡፡ በዘመነ ዕርገት ውስጥ በሚገኘው እሑድ (ሰንበት) ሌሊት ሊቃውንቱ የሚያደርሱት መዝሙርም ‹‹በሰንበት ዐርገ ሐመረ›› የሚል ሲኾን ይኸውም ጌታችን በሰንበት ወደ ታንኳ በመውጣት ባሕርንና ነፋሳትን እንደ ገሠፀ፤ ሐዋርያቱንም ‹‹ጥርጥር ወደ ልቡናችሁ አይግባ፤ አትጠራጠሩ›› እያለ በሃይማኖት ስለ መጽናት እንዳስተማራቸው፤ እንደዚሁም ወንጌልን ይሰብኩ፣ ያስተምሩ ዘንድ በመላው ዓለም እንደሚልካቸው፤ በሰማያዊ መንግሥቱ ይኖሩ ዘንድም ዳግመኛ መጥቶ እንደሚወስዳቸው የሚያስገነዝብ መልእክት አለው (ሉቃ.፰፥፳፪-፳፬፤ ዮሐ.፲፬፥፪፤ ፳፥፳፩)፡፡

በበዓለ ዕርገት ሊቃውንቱ ሌሊት በማኅሌት፣ በዝማሬ እግዚአብሔርን ሲያመሰግኑ ያድራሉ፡፡ ሥርዓተ ማኅሌቱ እንዳበቃ የሚሰበከው የነግህ ምስባክም፡- ‹‹ዘምሩ ለእግዚአብሔር ዘዐርገ ውስተ ሰማይ ሰማይ ዘመንገለ ጽባሕ ናሁ ይሁብ ቃሎ ቃለ ኃይል›› የሚለው የዳዊት መዝሙር ሲኾን፣ ቀጥተኛ ትርጕሙ፡- ‹‹በምሥራቅ በኩል ወደ ሰማየ ሰማያት ለወጣ (ላረገ) ለእግዚአብሔር ዘምሩ፤ የኀይል የኾነውን ቃሉን እነሆ ይሰጣል፤›› ማለት ነው (መዝ.፷፯፥፴፫)፡፡ ምሥጢራዊ ትርጕሙ ደግሞ ‹‹ነፍሳትን ይዞ ከሲኦል ወደ ገነት ለወጣ፤ አንድም በደብረ ዘይት በኩል ላረገ ለእግዚአብሔር ምስጋና አቅርቡ›› የሚል መልእክት አለው፡፡ እንደዚሁም ጌታችን በዐረገ በዐሥረኛው ቀን ‹የኀይል ቃል› የተባለ መንፈስ ቅዱስን ለሐዋርያት እንደ ላከላቸው፤ በተጨማሪም ጌታችን በሕያዋን እና በሙታን (በጻድቃን እና በኃጥአን) ላይ ለመፍረድ ዳግም እንደሚመጣ፤ እኛም ይህንን የጌታችንን የማዳን ሥራ እያደነቅን ለእርሱ ምስጋና፣ ዝማሬ ማቅረብ እንደሚገባን ያስረዳናል – ምስባኩ፡፡

በነግህ (ከቅዳሴ በፊት የሚነበበው) ወንጌል ደግሞ ሉቃስ ፳፬፥፵፭ እስከ መጨረሻው ድረስ ያለው ኃይለ ቃል ነው፡፡ ቃሉም ጌታችን አምላካችንና መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከሰማየ ሰማያት እንደሚወርድ፣ የሰውን ልጅ ለማዳን ሲል መከራ እንደሚቀበል፣ እንደሚሞት፣ ከሙታን ተለይቶ እንደሚነሣ፣ ወደ ሰማይ እንደሚያርግና ዳግም እንደሚመጣ በነቢያት የተነገረው ትንቢት መፈጸሙን፤ ለዚህም ቅዱሳን ሐዋርያት ምስክሮች መኾናቸውን ማለትም በመላው ዓለም እየዞሩ ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ የማዳን ሥራ እንዲሰብኩና በሰማዕትነት እንዲያልፉ፤ እንደዚሁም ሰማያዊ ሀብትንና ዕውቀትን እስኪያገኙ ድረስ በኢየሩሳሌም እንዲቆዩ መታዘዛቸውን ያስረዳል፡፡ ይህ ምሥጢር ለጊዜው የሐዋርያትን ተልእኮ የሚመለከት ይኹን እንጂ ለፍጻሜው ግን ዅላችንም ቅዱሳት መጻሕፍት የተናገሩትን ቃል አብነት አድርገን የእግዚአብሔርን ሰው መኾንና የማዳኑን ሥራ አምነን፣ ሌሎችንም በማሳመን በሃይማኖታችን ጸንተን መኖር እንደሚገባን፤ እግዚአብሔር አምላካችን ኃይሉን፣ ጸጋውን፣ ረድኤቱን እንዲያሳድርብንም ከቅድስት ቤተ ክርስቲያን መለየት እንደሌለብን የሚያስገነዝብ መልእክት አለው፡፡

በቅዳሴ ጊዜ የሚነበቡ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎችም ከቅዱስ ጳውሎስ መልእክት ዕብራውያን ፩፥፩ እስከ ፍጻሜው ድረስ፤ ከሌሎች መልእክታት ደግሞ ፩ኛ ጴጥሮስ ፫፥፲፰ እስከ ፍጻሜው፤ የሐዋርያት ሥራ ፩፥፩-፲፪ ሲኾኑ፣ ምስባኩም ‹‹ዐርገ እግዚአብሔር በይባቤ ወእግዚእነ በቃለ ቀርን ዘምሩ ለአምላክነ ዘምሩ›› የሚለው ነው፡፡ ትርጕሙም ‹‹በዕልልታና በመለከት ድምፅ ላረገ ለአምላካችን፣ ለጌታችንና ለመድኀኒታችን ለኢየሱስ ክርስቶስ ምስጋና አቅርቡ›› ማለት ነው (መዝ.፵፮፥፭-፮)፡፡ ወንጌሉ ደግሞ፣ ማርቆስ ፲፮፥፲፬ እስከ ፍጻሜ ድረስ ሲኾን ቃሉም በነግህ ከተነበበው የወንጌል ክፍል ቃል ተመሳሳይነት አለው፡፡ ቅዳሴውም ቅዳሴ ዲዮስቆሮስ ሲኾን ይህ ቅዳሴ ከሦስቱ አካላት አንዱ የኾነውን የእግዚአብሔር ወልድን (የኢየሱስ ክርስቶስን) ዘለዓለማዊነት የሚያስረዳ፤ ሥጋዌዉን፣ ሕማሙን፣ ሞቱን፣ ትንሣኤዉን፣ ዕርገቱንና ዳግም ምጽአቱንም የሚናገር በመኾኑ በዘመነ ትንሣኤ፣ በዘመነ ዕርገትና በበዓለ ኀምሳ ሰሙን ይቀደሳል፡፡

ቅዱስ ዲዮስቆሮስ በቅዳሴዉ መጀመሪያ ላይ ሀልዎተ እግዚአብሔርንና ምሥጢረ ሥላሴን መሠረት በማድረግ ለእግዚአብሔር ምስጋና ካቀረበ በኋላ፣ ቍጥር ፴፩ ላይ ‹‹… ወበ፵ ዕለት አመ የዐርግ ሰማየ አዘዞሙ እንዘ ይብል ጽንሑ ተስፋሁ ለአብ፤ከሙታን ተለይቶ በተነሣ በዐርባኛው ቀን በብርሃን፣ በሥልጣን፣ በይባቤ ወደ ሰማይ በሚያርግበት ጊዜ ‹አብ የሚሰድላችሁ መንፈስ ቅዱስን እስክትቀበሉ ድረስ ከዚህ ቆዩ ብሎ አዘዛቸው›፤›› በማለት ቅዱስ ወንጌልን መሠረት ባደረገ ኃይለ ቃል ጌታችን ወደ ሰማይ ስለ ማረጉና ለሐዋርያት አምላካዊ ትእዛዝ ስለ መስጠቱ ይናገራል (ሉቃ.፳፬፥፵፱)፡፡

ይቆየን

ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ የተሰጠ መግለጫ

ግንቦት ፲፬ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ አሐዱ አምላክ አሜን፡፡

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ መደበኛ ስብሰባ፣ በዓመት ሁለት ጊዜያት እንዲኾን በፍትሕ መንፈሳዊ በተደነገገው መሠረት የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ የዘንድሮውን መደበኛ የረክበ ካህናት ስብሰባ ከበዓሉ ዋዜማ ከግንቦት ፩ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም ጀምሮ ለ፲፬ ቀናት ያህል ሲወያይ ሰንብቷል፡፡

በምልዓተ ጉባኤው የተደረገውን የመክፈቻ ንግግር በተመለከተ፡-

  • በቤተ ክርስቲያኒቱ የሥራ ዘርፍ ዙሪያ እየተሠሩ ያሉትን ማኅበራውያን ተግባራት የዳሰሰ፤
  • በአገራችን አንዳንድ አካባቢ በዝናም እጥረት ምክንያት ድርቅ ባስከተለው ችግር ለተጎዱ ወገኖች ሊደረግ የሚገባውን ሰብአዊ አገልግሎት ያገናዘበ፤
  • በአገራችንና በቤተ ክርስቲያናችን ዅለንተናዊ ዕድገት የሚበጀውን በማመቻቸት በዅሉም አቅጣጫ ያለው ኅብረተሰብ የሥራ ተነሳሽነቱን በበለጠ አጐልብቶ እንዲንቀሳቀስ የሚያስችል መልእክት መኾኑን ምልዓተ ጉባኤው ተመልክቶ ለተላለፈው አጠቃላይ መመሪያ ትኵረት ሰጥቶ በቀረበው አጀንዳ ከተወያየ በኋላ በርከት ያሉ ውሳኔዎችን አሳልፏል፡፡ ከውሳኔዎቹም መካከል ዋና ዋናዎቹ የሚከተሉት ናቸው፤

፩. ከፍ ብሎ እንደ ተገለጸው ዅሉ በአሁኑ ጊዜ በአገራችን በአንዳንድ አካባቢ በተከሠተው ድርቅ ለረኃብ የተጋለጡ ወገኖቻችንን ለመታደግ መንግሥት እያደረገ ያለውን ከፍተኛ ጥረት በመገንዘብ፣ ቤተ ክርስቲያናችንም የልማትና ክርስቲያናዊ ተራድኦ ኮሚሽን ሓላፊነቱን ወስዶ ከርዳታ ሰጪዎች ጋር በመነጋገርና በማስተባበር የሚገኘውን ርዳታ ድርቁ የተከሠተባቸው የክልል መሪዎች በሚሰጡት አቅጣጫ እንዲፈጸም ቅዱስ ሲኖዶስ ወስኗል፡፡

፪. ከቤተ ክርስቲያናችን እምነትና ሥርዓት ውጭ በመደራጀት የኑፋቄ ትምህርት ሲያካሒድ የበረው ‹አሰግድ ሣህሉ› የተባለ ግለሰብ ለበርካታ ዓመታት የኑፋቄ ትምህርት ሲያሠራጭ መኖሩ በመረጃ የተደረሰበትና የተረጋገጠበት በመኾኑ ከአሁን በኋላ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ስም እንዳያስተምር፣ ምእመናንም እንዳይከተሉት ምልዓተ ጉባኤው ከግንቦት ፫ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም ጀምሮ ቃለ ውግዘት አስተላልፏል፡፡ ከቤተ ክርስቲያኒቱ ዕውቅና ውጭ ምንም ዓይነት ፈቃድ ሳያገኙ በተመሳሳይ ኹኔታ አዳራሽ ተከራይተው በቤተ ክርስቲያናችን ስም ‹‹ወንጌል እናስተምራለን፤ ዝማሬ እናሰማለን›› የሚሉ ሕገ ወጦች ከእንዲህ ዓይነት ድርጊታቸው እንዲታረሙ፤ ምእመናንንም በተለይ ወጣቱ ትውልድ እንዲህ ዓይነት ሕገ ወጦችን ከመከተልና ሃይማኖታችሁን ከሚበርዙ ኃይሎች እንድትጠበቁ ቅዱስ ሲኖዶስ አበክሮ ያሳስባል፡፡

፫. የቤተ ክርስቱያኒቱ መገናኛ ብዙኃን ጉዳይን በተመለከተ የሚዲያ ድርጅቱ በሰው ኃይል እንዲጠናከር፤ የሚያስተላልፋቸው መልእክቶችም ጥራት እንዲኖራቸው ማድረግ በሚቻልበት ኹኔታ ላይ የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ተነጋግሮ፣ ለ፳፻፲ በጀት ዓመት ብር 12,000,000.00 (ዐሥራ ሁለት ሚሊዮን ብር) ተፈቅዶለት በበጀት ተጠናክሮ ሥራውን እንዲቀጥል ተስማምቷል፡፡

፬. በኢየሩሳሌም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ስለ ዴር ሡልጣን ገዳም ችግር ጉዳይ ጉባኤው በስፋት ከተነጋገረ በኋላ ችግሩን አስመልክቶ መፍትሔ ማግኘት እንዲቻል ለኢፊድሪ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ በኢትዮጵያ ለእስራኤል ኢምባሲ እና በእስራኤል ለኢትዮጵያ ኢምባሲ ደብዳቤ እንዲጻፍላቸው ተወስኗል፡፡

፭. ሚያዝያ ፲ ቀን በሚነበበው መጽሐፈ ስንክሳርና በፍትሕ መንፈሳዊ መጽሐፍ ላይ ‹‹ኢትዮጵያውያን ከራሳቸው ሊቃውንት ጳጳሳትን አይሹሙ›› የሚለው በ፯ተኛው መቶ ዓመት ግብጻውያን አባቶች በሥርዋጽ ያስገቡት ሕገ ወጥ ጽሑፍ ስለ ኾነ ምልዓተ ጉባኤው ተነጋግሮ ጽሑፉ የአገራችንና የቤተ ክርስቲያንን ክብር የሚነካ ኾኖ በመገኘቱ ከአሁን በኋላ ጽሑፉ እንዳይነበብ፤ ከመጻሕፍቱም ውስጥ እንዲወጣ፤ ወደፊትም በሚታተሙ መጻሕፍት እንዳይገባ ተወስኗል፡፡

፮. ሥርዓተ ምንኵስና እና ሥልጣነ ክህነት አሰጣጥን አስመልክቶ ቀደም ባሉት ዓመታት የተወሰኑ ውሳኔዎች በአብዛኛው አፈጻጸም ላይ ችግሮች እንዳሉ ስለሚታይ ወደፊት የሚወሰነው ተጠብቆ እንዲሠራበት ጉባኤው ተስማምቷል፡፡

፯. ሕጋዊ ፈቃድ የሌላቸው ሰባክያንና አጥማቂዎች በቤተ ክርስቲያኒቱ ውስጥ አገልግሎት እንዳይሰጡ የተወሰነ ቢኾንም ውሳኔው መከበር ስላልቻለ፤ ችግሮችም በስፋት የሚታዩ ስለ ኾነ አሁንም በውሳኔው መሠረት የቁጥጥሩ ሥራ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ተስማምቷል፡፡

፰. በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ስም በአዲስ አበባም ኾነ በየአህጉረ ስብከቱ በማኅበር ተደራጅተው ገዳማትን በማስጐብኘትም ኾነ በቤተ ክርስቲያኒቱ ስም በልዩ ልዩ አቅጣጫ የሚንቀሳቀሱ ማኅበራትን መቆጣጠር የሚቻልበት የማኅበራት ማደራጃ ደንብ እንዲወጣ ቅዱስ ሲኖዶስ ወስኗል፡፡

፱. የቤተ ክርስቲያኒቱ ዅለንተናዊው ችግር በባለሙያ ተጠንቶ እንዲቀርብ ቀደም ሲል በተወሰነው መሠረት ጥናቱ ተጠናቆ ከቀረበ በኋላ ጉባኤው ተመልክቶ የሕግ ባለሙያዎችና የቤተ ክርስቲያን ሊቃውንት ባሉበት ተመርምሮና ተስተካክሎ ለጥቅምቱ ፳፻፲ ዓ.ም የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ እንዲቀርብ ተወስኗል፡፡

፲. የስብከተ ወንጌል መስፋፋት፤ የሰንበት ት/ቤትና የመንፈሳውያን ኮሌጆች መጠናከር፤ የአብነት ት/ቤቶች መደራጀትና በበጀት እንዲደገፉ ማድረግ የቤተ ክርስቲያኒቱ ዓይነተኛ ተግባር መኾኑን ምልዓተ ጉባኤው ተነጋግሮ፣ በስብከተ ወንጌል ትምህርት አሰጣጥና በመንፈሳውያን ኮሌጆች ደቀ መዛሙርት አያያዝ ጥብቅ ክትትል እንዲደረግ ጉባኤው ወስኗል፡፡

፲፩. የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የራሷ የኾነውን ሀብትና ቅርስ በባለቤትነት መጠበቅና ማስጠበቅ እንዲቻል ተዘጋጅቶ የቀረበውን ጥናት ቅዱስ ሲኖዶስ ካዳመጠና ከተወያየበት በኋላ የመጨረሻ ውሳኔ ለመስጠት በቅድሚያ በቋሚ ሲኖዶስ ታይቶ እንዲቀርብ ወስኗል፡፡

፲፪. ብፁዓን አበው በሌሉባቸው አህጉረ ስብከት የሚመደቡ ዕጩዎች ቆሞሳት ምርጫን በተመለከተ ከአገር ውስጥና ከአገር ውጪ የሚገኙ ቆሞሳትን በማወዳደር ፲፮ ቆሞሳት ለኤጲስ ቆጶስነት ተመርጠዋል፤ በዓለ ሢመታቸውም ሐምሌ ፱ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም እንዲፈጸም ተወስኗል፡፡

፲፫. ኤጲስ ቆጶሳት የሌሉባቸውን የውጭ አህጉረ ስብከት በተመለከተም በጥቅምቱ ፳፻፲ ዓ.ም በቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ እየታየና እየተጠና ብፁዓን አበው እንዲመደቡባቸው ለማድረግ ቅዱስ ሲኖዶስ ተስማምቷል፡፡

፲፬. በኦሮምያ ክልል በሰባት ዞኖች በሚገኙ ዩኒቨርስቲዎች የሚማሩ ተማሪዎች ‹‹መንፈሳዊውን ትምህርት በቋንቋችን እንዳንማር ማኅበረ ቅዱሳን በደል አድርሶብናል›› በሚል ባቀረቡት አቤቱታ ዩንቨርሲቲዎቹ ያሉበት አህጉረ ስብከት ጉዳዩን ግራና ቀኝ አጣርተውና ተመልክተው መፍትሔ እንዲሰጡና ውጤቱ ለቅዱስ ሲኖዶስ እንዲቀርብ ተወስኗል፡፡

ቅዱስ ሲኖዶስ ከዚህ በላይ በተገለጹት የውሳኔ ነጥቦችና በሌሎችም ዐበይት ጉዳዮች ላይ ለ፲፬ ቀናት ሲወያይ ሰንብቶ ስብሰባውን በጸሎት አጠናቋል፡፡

እግዚአብሔር አምላክ ኢትዮጵያንና

ሕዝቦቿን ይባርክ፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር፤

አሜን፡፡

አባ ማትያስ ቀዳማዊ

ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ

ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት

ግንቦት ፲፬ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም

ፍልሰተ ዐፅሙ ለአቡነ ተክለ ሃይማኖት

በዝግጅት ክፍሉ

ግንቦት ፲፩ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም

ቅዱሳን ጻድቃን በሕይወተ ሥጋ ሳሉም ኾነ ካረፉ በኋላ (በዐጸደ ሥጋም ኾነ በዐጸደ ነፍስ) በጸሎታቸው ለሚታመኑ፣ በቃል ኪዳናቸው ለሚማጸኑ ምእመናን በመጸለይና ወደ እግዚአብሔር በማማለድ ድኅነተ ሥጋ፣ ድኅነተ ነፍስን የሚያስገኙልን የችግር ጊዜ አማላጆቻችንና አስታራቂዎቻችን ናቸው፡፡ ቅዱሳን በጸሎታቸውና በትምህርታቸው ከከበቡን የነፍስ ጠላቶች፤ ከርኲሳን መናፍስትና ከጨለማው ልጆች፤ ከክፉ ሰዎች ሽንገላና ተንኰል ለመሰወርና ለመጠበቅ ከእግዚአብሔር የተቀበሉት ሥልጣን ምን ጊዜም ሲሠራ ይኖራል፡፡ በጻድቃን መኖር አገር ከጥፋት ትድናለች፡፡

የጻድቃንን ስም ጠርቶ እግዚአብሔርን በመለመን በረከትና ረድኤት ይገኛል፡፡ ስለ ጻድቃን ብሎ እግዚአብሔርም ምሕረቱን ያድላል፡፡ እነርሱን ማሰብና ማክበር፣ ሥራቸውንም መዘከር ክርስቲያናዊ ሕይወታችንን ያጐለምሳል፡፡ ለድኅነተ ሥጋ፣ ለድኅነተ ነፍስ ይረባል፤ ይጠቅማል፡፡ ስለዚህም ነው ቅዱስ ወንጌል ቅዱሳን ጻድቃንን እንድናስባቸው፣ በስማቸውም ለድሆችና ለጦም አዳሮች እንድንመጸውት፣ መታሰቢያቸውን እንድናደርግ የሚመክረን፤ የሚያስተምረን (ማቴ.፲፥፵፩-፵፪)፡፡ ከእነዚህ ቅዱሳን መካከልም ኢትዮጵያዊው ጻድቅ አቡነ ተክለ ሃይማኖት አንደኛው ናቸው፡፡

በየዓመቱ ግንቦት ፲፪ ቀን ቅዱስ ሚካኤል ሊቀ መላእክት፣ ኢትዮጵያዊው ንጉሥ እስክንድር፣ ሊቁ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ፣ ቅዱስ መስቀል፣ ቅዱስ እስጢፋኖስ፣ ቅዱስ ሚናስ፣ የመላልዔል ልጅ ያሬድ እና ጻድቁ አቡነ ተክለ ሃይማኖት በቤተ ክርስቲያናችን ይታሰባሉ፡፡ በዛሬው ዝግጅታችን የጻድቁ አባታችንን የፍልሰተ ዐፅም ታሪክ የስማቸውን ትርጕም በማስቀደም እንደሚከተለው በአጭሩ አቅርበነዋል፤

‹ተክል› ማለት ፍሬያማ ዕንጨት፣ ዛፍ፣ ቅመም፣ ቅጠላ ቅጠል፣ የሚበላ፣ የሚሸተት፣ ገነታዊ ዕፅ፣ እንዲሁም ሕግ ሥርዓት ማለት ነው (ኪዳነ ወልድ ክፍሌ፤ ማቴ.፲፭፥፲፫)፡፡ ‹ሃይማኖት› ማለት ደግሞ በሀልዎተ እግዚአብሔር፣ በእግዚአብሔር አምላክነት፣ በሥላሴ አንድነትና ሦስትነት፣ በቅዱሳን ተራዳኢነት ማመን፤ አምኖም መመስከር ማለት ነው፡፡ ‹ተክለ ሃይማኖት› የሚለው ሐረግም የሃይማኖት ተክል፣ ይኸውም የጽድቅ ፍሬን ያፈራና ከኃጢአት ሐሩር ማምለጫ ዛፍ፤ ምእመናንን በቃለ ወንጌል ያጣፈጠ ቅመም፤ መዓዛ ሕይወቱ የሚማርክ፣ ቢመገቡት ረኃበ ነፍስን የሚያስወግድ ቅጠል፤ የጻድቃን መጠለያ ዕፅ የሚል አለው፡፡ መጽሐፈ ገድላቸውም ‹‹ተክለ ሃይማኖት ማለት የአብ፣ የወልድ፣ የመንፈስ ቅዱስ ተክል ማለት ነው›› በማለት የስማቸውን ትርጕም ያትታል፡፡ ጻድቁ አባታችን ተክለ ሃይማኖት በአሚነ ሥላሴ ጸንተው ሌሎችንም እንዲጸኑና እንዲያምኑ አድርገዋልና፡፡

‹‹… ስምዑ ወለብዉ ፍቁራንየ መጽሐፈ ዜናሁ ለክቡር ወቅዱስ ወለብፁዕ ፍቁረ እግዚአብሔር ዘይትነበብ በዕለተ ፍልሰተ ሥጋሁ አመ ፲ወ፪ ለግንቦት ውእቱ ድሙር ምስለ በዓለ ትንሣኤሁ ለእግዚእነ ኢየሱስ ክርስቶስ ወበዓለ ሚካኤል ሊቀ መላእክት ፍቁሩ ለተክለ ሃይማኖት፤ ወዳጆቼ ሆይ፣ የከበረ፣ የተቀደሰ፣ የተደነቀ፣ የእግዚአብሔር ወዳጅ የሚኾን የአባታችን የተክለ ሃይማኖትን ክብሩን፣ ገናንቱን የሚናገረውን፤ ዐፅሙ በፈለሰበት ግንቦት ፲፪ ቀን የሚነበበውን መጽሐፍ አስተውላችሁ ስሙ፡፡ ይኸውም ከጌታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ የትንሣኤ በዓል እና ከተክለ ሃይማኖት ወዳጅ ከሊቀ መላእክት ቅዱስ ሚካኤል በዓል ጋር የተባበረ ነው …፤›› (ገድለ ተክለ ሃይማኖት ምዕ.፷፪፥፭-፰)፡፡

አቡነ ተክለ ሃይማኖት በ፲፫ኛው መቶ ክፍለ ዘመን መጀመሪያ አካባቢ በአገራችን ኢትዮጵያ ምድር በሰሜን ሸዋ ሀገረ ስብከት ኢቲሳ (ደብረ ጽላልሽ) ከአባታቸው ካህኑ ጸጋ ዘአብ እና ከእናታቸው እግዚእ ኀረያ አብራክ የተገኙ ቅዱስ አባት ናቸው፡፡ አባታችን ሕይወታቸዉን ሙሉ ለእግዚአብሔር በመስጠት፣ እንደ በሬ ተጠምደው፣ እንደ ገበሬ ታጥቀው ይህንን ዓለም ንቀው፣ በጾም በጸሎት ተወስነው፣ በብሕትውና ከመኖራቸው ባሻገር እንደ ቅዱሳን ሐዋርያት ወንጌልን በመላው ኢትዮጵያ እየተዘዋወሩ የሰበኩ፣ በጌታችን በመድኃኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ድውያነ ሥጋን በተአምራት፣ ድውያነ ነፍስን በትምህርት የፈወሱ ሐዋርያ ናቸው፡፡ ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችንም ይህንን ውለታቸውን በማሰብና ከእግዚአብሔር ዘንድ የተሰጣቸውን ቅድስና መሠረት አድርጋ በስማቸው ጽላት ቀርፃ ስታከብራቸው ትኖራለች፡፡

አቡነ ተክለ ሃይማኖት በዚህ ዓለም የኖሩበት ዕድሜ ዘጠና ዘጠኝ ዓመት ከዐሥር ወር ከዐሥር ቀን ነው፡፡ በእናት አባታቸው ቤት ፳፪ ዓመት፤ በከተታ ፫ ዓመት፤ በዊፋት ፱ ወር፤ በዳሞት ፲፪ ዓመት፤ በአማራ ፲ ዓመት፤ በሐይቅ ፲ ዓመት፤ በደብረ ዳሞ ፲፪ ዓመት፤ በትግራይ ገዳማት በመዘዋወርና ወደ ኢየሩሳሌም በመመላለስ ፩ ዓመት፤ ዳዳ በሚባል አገር ፩ ወር፤ በአሰቦ ገዳም ፳፱ ዓመት ከ፲ ቀን መቆየታቸውን መጽሐፈ ገድላቸው ይናገራል (ገ.ተ.ሃ ፶፱፥፲፬-፲፭)፡፡

ጻድቁ አባታችን ምድራዊ ሕይወታቸውን በተጋድሎና በሐዋርያዊ አገልግሎት ከፈጸሙ በኋላ ከዚህ ዓለም ውጣ ውረድ የሚያልፉበት ቀን በተቃረበ ጊዜ ጌታችን አምላካችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከእናቱ ከቅድስት ድንግል ማርያም፣ ከቅዱሳን መላእክት፣ ከቅዱሳን ነቢያትና ከቅዱሳን ሐዋርያት ጋር ወደ እርሳቸው በመምጣት የሚያርፉበት ዕለት መድረሱን ነግሯቸው፣ የተጋድሏቸውን ጽናት አድንቆላቸው በስማቸው መታሰቢያ ለሚያደርጉ፣ ለነዳያን ለሚመጸዉቱ ቤተ ክርስቲያን ለሚያሠሩ የምሕረት ቃል ኪዳን ሰጥቷቸው በክብር በምስጋና ወደ ሰማይ ዐረገ፡፡

አቡነ ተክለ ሃይማኖትም የዕረፍት ጊዜያቸው መቃረቡን ባወቁ ጊዜም የመንፈስ ልጆቻቸውን ጠርተው ጌታችን የነገራቸውን ዅሉ አስረድተው አባታዊ ምክርና ተግሣፅ ከሰጧቸው በኋላ ነሐሴ ፳፬ ቀን ከዚህ ዓለም ድካም ዐረፉ፡፡ የመንፈስ ልጆቻቸውም ለአንድ ቅዱስ አባትና ካህን በሚገባ ሥርዓት በማኅሌት፣ በዝማሬና በምስጋና ቀበሯቸው፡፡ ጌታችንም ከእመቤታችንና ከቅዱሳን መላእክት ጋር ተገልጾ ታያቸው፤ ነፍሳቸውንም ‹‹የጠራሽ፣ ንጽሕት ነፍስ ሆይ! ወደ እኔ ነዪ›› ብሎ በክብር ተቀበላት፡፡

ወደ ፍልሰተ ዐፅማቸው ታሪክ ስንመለስ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ከዚህ ዓለም ውጣ ውረድ ከተለዩ በ፶፯ኛው ዓመት የካቲት ፲፱ ቀን ለመንፈስ ልጃቸው ለአባ ሕዝቅያስ ብርሃን ለብሰው በሕልም ተገለጡላቸውና ‹‹ወዳጄ ሕዝቅያስ ሆይሰላም ለአንተ ይኹን! ጌታዬበኋለኛው ዘመን ከዚህ ሥፍራ ልጆችህ ሥጋህን ያፈልሳሉያለኝ ዘመን ደርሷልና ሳትዘገይ ልጆቼን ዅሉ ቅጠራቸውና እስከምፈልስበት ቀን ድረስ ግንቦት ፲፪ ቀን ይሰብሰቡ፡፡ እናንተም በምስጋና በጸሎት መንፈሳዊ በዓልን አድርጉ፡፡አባቴ ተክለ ሃይማኖትየሚለኝ ዅሉ በዚህች በፍልሰተ ዐፅሜ ቀን ይምጣ፤ መንፈሳዊ በዓልንም ያድርግ፡፡ እኔና ቅዱስ ሚካኤል ከወዳጄ አባ ፊልጶስ ጋር ስለ እኔ ፍቅር የተሰበሰበውን ሕዝብ ልንባርክ እንመጣለን፤›› ከአሏቸው በኋላ ተሠወሯቸው፡፡

አባ ሕዝቅያስም እንደ ታዘዙት ‹‹የአባታችሁን ዐፅም ከዋሻው ወደ ታላቁ ቤተ ክርስቲያን ታፈልሱ ዘንድ ኑ፤ ተሰብሰቡ›› ብለው የአባታችን ወዳጆች ባሉባቸው አገሮች ዅሉ መልእክት ላኩ፡፡ ምእመናንም ጥሪውን ተቀብለው በዓሉን ለማክበር ከአራቱም አቅጣጫ ተሰበሰቡ፡፡ ዐሥራ ሁለቱ መምህራንም መጡ፤ እነዚህም፡- የወረብ አገሩ አባ አኖሬዎስ፣ የፈጠጋሩ አባ ማትያስ፣ የእርናቱ አባ ዮሴፍ፣ የሞረቱ አባ አኖሬዎስ፣ የመርሐ ቤቴው አባ መርቆሬዎስ፣ የጽላልሹ አባ ታዴዎስ፣ የወገጉ አባ ሳሙኤል፣ የወንጁ አባ ገብረ ክርስቶስ፣ የድንቢው አባ መድኃኒነ እግዚእ፣ የዳሞቱ አባ አድኃኒ፣ የክልአቱ አባ ኢዮስያስ እና የመሐግሉ አባ ቀውስጦስ ናቸው፡፡

እነዚህ መምህራን ከአባ ሕዝቅያስ ጋር በመኾን የአቡነ ተክለ ሃይማኖትን ዐፅም ከዐረፈበት ዋሻ ባወጡት ጊዜ ዐፅማቸው ዕለት የተገነዘ በድን ይመስል ነበር፤ መዓዛውም ሽቱ፣ ሽቱ ይሸት ነበር፡፡ በአባታችን ዐፅም ቀኝና ግራም መስቀል ተተክሎ ነበር፡፡ በዐፅማቸውም ብዙ ድንቅ ተአምራት ተደርገዋል፡፡ ይህንን የአባታችንን ዐፅም አባ ሕዝቅያስና ዐሥራ ሁለቱ መምህራን በሣጥን አክብረው ወደ ቤተ ክርስቲያኑ ወስደው በመንበሩ ፊት ሦስት ጊዜ አዞሩት፡፡

በዚህች ዕለት አስቀድመው የካቲት ፲፱ ቀን ለአባ ሕዝቅያስ በሕልም እንደ ነገሯቸው ብፁዕ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ከቅዱስ ሚካኤልና ከአባ ፊልጶስ ጋር ወደ ቤተ ክርስቲያኑ መጥተው ዐፅማቸው እስኪያረፍ ድረስ ከመንበሩ ተቀምጠው ቆይተው ዐፅማቸው ካረፈ በኋላ የተሰበሰበውን ሕዝብ ባርከው በክብር ወደ ሰማይ ዐረጉ፡፡ መምህራኑና ምእመናኑም በዓሉን በታላቅ ደስታ አክብረው በሰላም ወደየቤታቸው ተመለሱ፡፡ በዘመኑ የአቡነ ተክለ ሃይማኖት ፍልሰተ ዐፅም በዋለበት ዕለት ርክበ ካህናትም አብሮ መከበሩ በዓሉን ልዩ ድምቀት ሰጥቶት እንደ ነበር በመጽሐፈ ገድላቸው ተገልጿል፡፡ ከዚያን ዘመን ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ በታላቁ ገዳም በደብረ ሊባኖስ ቅዱሳን ፓትርያሪኮች፣ ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳትና በርካታ ምእመናን እየተሰበሰቡ በዓሉን በድምቀት ያከብራሉ (ገ.ተ.ሃ ፷፭፥፩-፳፬)፡፡

የብፁዕ አባታችን ዐፅም በፈለሰበት ዕለት ዐሥራ ሁለቱ መምህራን እና በርካታ ምእመናንን እንደ ተሰበሰቡ ዅሉ እኛንም እግዚአብሔር አምላካችን በኢየሩሳሌም ሰማያዊት ይሰብስበን፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር፡፡

ምንጭ፡

  • መጽሐፈ ስንክሳር፣ ግንቦት ፲፪ ቀን፡፡
  • ገድለ ተክለ ሃይማኖት፣ ፲፱፻፹፱ .ም፤ አዲስ አበባ፡፡

ዝክረ ቅዱስ ያሬድ ኢትዮጵያዊ

ቅዱስ ያሬድ

በዲያቆን ኤፍሬም የኔሰው

ግንቦት  ቀን ፳፻፱ .

በየዓመቱ ግንቦት ፲፩ ቀን ከሚታወሱ ቅዱሳን መካከል የእመቤታችን እናት ቅድስት ሐና፣ ቅድስት ታውክልያ፣ ቅዱስ በፍኑትዩስ፣ አባ አሴር፣ ቅዱስ ያሬድ፣ ብፅዕት አርሴማ፣ ቅድስት ኤፎምያ፣ ቅድስት አናሲማ፣ ቅድስት ሶፍያ፣ አባ በኪሞስ፣ አባ አብላዲስ፣ አባ ዮልዮስ እና ስማቸውን ያልጠቀስናቸው ሌሎች በርካታ ቅዱሳንም ተጠቃሾች ናቸው፡፡ በዛሬው ዝግጅታችን ‹የቤተ ክርስቲያን እንዚራ›፣ ‹የኢትዮጵያ ብርሃን› እየተባለ የሚጠራውን የቤተ ክርስቲያናችን ድምቀት፣ የአገራችን ኩራት የኾነውን የጥዑመ ልሳኑ ማኅሌታይ ቅዱስ ያሬድን ታሪክ በአጭሩ ልናስታውሳችሁ ወደድን፤

ቅዱስ ያሬድ ሚያዝያ ፭ ቀን በ፭፻፭ ዓ.ም በአገራችን በኢትዮጵያ በአክሱም ከተማ ከአባቱ ከአብዩድ (ይስሐቅ) እና ከእናቱ ታውክልያ (ክርስቲና) ተወለደ፡፡ ዕድሜው ለትምህርት ሲደርስ ከአጎቱ ከአባ ጌዴዎን ዘንድ ትምህርት ሊማር ቢሔድም ለበርካታ ዓመታት ትምህርት ሊገባው አልቻለም ነበር፡፡ በዚህም የተነሣ መምህሩ ይገርፉት፣ ይገሥፁት ነበር፡፡ እርሱም ከትምህርቱ ክብደት ባለፈ የመምህሩ ተግሣፅ ሲበረታበት ጊዜ ከአባ ጌዴዎን ቤት ወጥቶ በመሸሽ ላይ ሳለ ደክሞት ከአንድ ዛፍ ሥር ተቀመጠ፡፡

ከዛፉ ሥር ተጠልሎ ሳለ አንድ ትል ፍሬውን ለመመገብ ወደ ዛፉ ሊወጣ ሲል መውጣት ስለ ተሳነው በተደጋጋሚ ሲወድቅ ቆይቶ ከብዙ ሙከራ በኋላ ከዛፉ ላይ ሲወጣ፤ ፍሬውንም ሲመገብ ይመለከታል፡፡ ቅዱስ ያሬድ የትሉን ትጋት ከአየ በኋላ እርሱም በተደጋጋሚ ሙከራ ቢያደርግ የከበደው ምሥጢር እንደሚገለጽለት በማመን ወደ መምህሩ ተመልሶ ይቅርታ በመጠየቅ ትምህርቱን እንደ ገና መቀጠል ጀመረ፡፡ እግዚአብሔርን በጸሎት እየተማጸነ ትምህርቱን ሲከታተል ከቆየ በኋላ በአጭር ጊዜ ውስጥ ልቡናው ብሩህ ኾኖለት የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት ትርጓሜን አጠናቆ መዓርገ ዲቁና ተቀበለ፡፡

እግዚአብሔርም የክብር መታሰቢያ ሊያቆምለት ወዷልና ከኤዶም ገነት ሦስት አዕዋፍን ልኮ በሰው አንደበት እንዲያናግሩት አደረጋቸው፡፡ እነርሱም ካናገሩት በኋላ ወደ ኢየሩሳሌም ሰማያዊት አወጡትና በዚያም የሃያ አራቱን ካህናተ ሰማይ (ሱራፌል) ማኅሌት ተማረ፡፡ ወደ ምድርም ተመልሶ በአክሱም ጽዮን በሦስት ሰዓት ገብቶ በታላቅ ቃል፡- ‹‹ሃሌ ሉያ ለአብ ሃሌ ሉያ ለወልድ ሃሌ ሉያ ለመንፈስ ቅዱስ ቀዳሚሃ ለጽዮን ሰማየ ሣረረ ወበዳግም አርአዮ ለሙሴ ዘከመ ይገብር ግብራ ለደብተራ፤ ለአብ ምስጋና ይገባል፤ ለወልድ ምስጋና ይገባል፤ ለመንፈስ ቅዱስ ምስጋና ይገባል፡፡ የጽዮን ደገኛዋ ሰማይን ፈጠረ፡፡ ዳግመኛም እንዴት መሥራት እንዳለበት የድንኳንን አሠራር ለሙሴ አሳየው፤ አስተማረው፤›› እያለ በዜማ እግዚአብሔርን አመሰገነ፡፡ የቅዱስ ያሬድን ድምፅ የሰሙ ዅሉ ጳጳሳቱና ነገሥታቱ ሳይቀሩ ካህናቱም ምእመናኑም ወደ እርሱ ተሰብስበው ሲሰሙት ዋሉ፡፡ ይህንንም ምስጋና ‹አርያም› ብሎ ሰየመው፤ ይኸውም በዜማ ትምህርት ቤት ከቃል ትምህርቶች አንደኛው ኾኖ በቤተ ክርስቲያን በመሰጠት ላይ ይገኛል፡፡

መጽሐፈ ስንክሳር ቅዱስ ያሬድን፡- አምሳሊሆሙ ለሱራፌል፤ የሱራፌል አምሳላቸው› ይለዋል፡፡ ከመላእክት ወገን የኾኑት ሱራፌል እግዚአብሔርን ‹‹ቅዱስ ቅዱስ ቅዱስ›› እያሉ በመንበሩ ፊት ቆመው እንደሚያመሰግኑ ዅሉ ቅዱስ ያሬድም ‹‹ቅዱስ ቅዱስ ቅዱስ›› እያለ በመላእክት ቋንቋ እግዚአብሔርን አመስገኗልና፤ ደግሞም የተማረው ከእነርሱ ነውና የሱራፌል አምሳላቸው› ተባለ፡፡ እርሱም፡- ‹‹ሃሌ ሉያ ዋይ ዜማ ዘሰማዕኩ በሰማይ እመላእክት ግናይ እንዘ ይብሉ ቅዱስ ቅዱስ ቅዱስ እግዚአብሔር መልዐ ሰማያተ ወምድረ ቅድሳተ ስብሓቲከ፤ ምስጋና ለእግዚአብሔር ይኹን! ቅዱስ ቅዱስ ቅዱስ እግዚአብሔር፤ የምስጋናህ ስፋት ሰማይና ምድርን መላ፤›› እያሉ ሲያመሰግኑ ከመላእክት የሰማሁት ምስጋና ምንኛ ድንቅ ነው? በማለት ዜማውን የተማረው ከመላእክት መኾኑን በድርሰቱ መስክሯል (ኢሳ.፮፥፫)፡፡

ከዚያ በኋላ በመንፈስ ቅዱስ ተቃኝቶ ከዓመት እስከ ዓመት ድረስ በየክፍለ ዘመኑ በክረምትና በበጋ፣ በመጸውና በጸደይ፣ በአጽዋማትና በሰንበታት፣ እንዲሁም በመላእክት፣ በጻድቃን፣ በሰማዕታት፣ በደናግል በዓላት የሚደረስ ቃለ እግዚአብሔር በሦስት ዜማዎች ማለትም በግእዝ፣ በዕዝልና በአራራይ ደረሰ፡፡ የሰው ንግግር፣ የአዕዋፍ፣ የእንስሳትና የአራዊት ጩኸት ዅሉ ከእነዚህ ከሦስቱ ዜማዎች እንደማይወጡ መጽሐፈ ስንክሳር ይናገራል፡፡ በዘመኑ የነበረው ንጉሥ ገብረ መስቀል በሊቁ ዜማ ረቂቅነት እና የድምፅ ማማር ከመመሰጡ የተነሣ የቅዱስ ያሬድን እግር በጦር መውጋቱም በመጽሐፈ ስንክሳር እንዲህ ተመዝግቧል፤

በአንዲት ዕለት ቅዱስ ያሬድ ከብሉይና ከሐዲስ፣ እንደዚሁም ከሊቃውንትና ከመነኮሳት የተውጣጣውን መንፈሳዊ ድርሰቱን ከንጉሡ ፊት ቆሞ ሲዘምር ንጉሡ በድምፁ በመማረኩ የተነሣ ልቡናው በተመስጦ ተሠውሮበት (የሚያደርገዉን ባለማወቁ) የቅዱስ ያሬድን እግር በጦር ወጋው፡፡ ከቅዱስ ያሬድ እግር ደምና ውኃ ቢፈስስም ነገር ግን ማኅሌቱን እስኪፈጽም ድረስ ሕመሙ አልተሰማውም ነበር፡፡ ንጉሡም ያደረገዉን ዅሉ ባወቀ ጊዜ ደነገጠ፤ ጦሩንም ከእግሩ ነቅሎ ‹‹ስለ ፈሰሰው ደምህ ዋጋ የምትፈልገዉን ዅሉ ለምነኝ›› እያለ ተማጸነው፡፡ ቅዱስ ያሬድም ‹‹ላትከለክለኝ ማልልኝ›› ብሎ ቃል ካስገባው በኋላ ወደ ገዳም ሔዶ ይመነኵስ ዘንድ እንዲፈቅድለትና እንዲያሰናብተው ለመነው፡፡ ንጉሡም ከመኳንንቱ ጋር እጅግ አዘነ፤ ተከዘ፡፡ ከእርሱ እንዲለይ ባይፈልግም ነገር ግን መሐላዉን ማፍረስ ስለ ከበደው አሰናበተው፡፡

ከዚያም ቅዱስ ያሬድ በአክሱም ጽዮን ቤተ መቅደስ በታቦተ ጽዮን ፊት ቆሞ፡ ‹‹ቅድስት ወብፅዕት ስብሕት ወቡርክት ክብርት ወልዕልት አንቀጸ ብርሃን መዐርገ ሕይወት …፤ፈጽሞ የከበርሽና የተመሰገንሽ፣ ከፍ ከፍም ያልሽ፣ የብርሃን መውጫ የሕይወት ማዕረግ የኾንሽ …›› እያለ አንቀጸ ብርሃን የተሰኘውን የእመቤታችንን ምስጋና እስከ መጨረሻው ድረስ ደረሰ፡፡ ይህንን ጸሎት ሲያደርስም አንድ ክንድ ያህል ከመሬት ከፍ ብሎ ይታይ ነበር፡፡ ከዚህ በኋላ ወደ ሰሜን አገር ሔዶ (ሰሜን ተራሮች አካባቢ) በጾም በጸሎት ተወስኖ ሥጋውን እጅግ እያደከመ ኖሮ ገድሉን በዚያው ፈጸመ፡፡ እግዚአብሔርም ስሙን ለሚጠራ፣ መታሰቢያውን ለሚያደርግ ቃል ኪዳን ሰጠው፤ ከዚያም በሰላም ዐረፈ፡፡

(ምንጭ፡መጽሐፈ ስንክሳር፣ ግንቦት ፲፩ ቀን)፡፡

የቤተ ክርስቲያን ሊቃውንት በገድለ ቅዱስ ያሬድ ላይ እና በመጽሐፈ ስንክሳር እንደ መዘገቡልን ግንቦት ፲፩ ቀን ቅዱስ ያሬድ ከዚህ ዓለም ውጣ ውረድ ያረፈበት ቀን ነው፤ እዚህ ላይ ግን አከራካሪ ጉዳይ አለ፤ ይኸውም አንደኛው ቅዱስ ያሬድ ሞቶ ተቀብሯል የሚል ሲኾን፣ ሌላኛው ደግሞ ቅዱስ ያሬድ እስከነነፍሱ ተሠወረ እንጂ አልሞተም የሚል ነው፡፡ በእርግጥ ቃሉን በትኩረት ለተመለከው ሰው ዐረፈ ማለት ሞትን ብቻ ሳይኾን እንደነሄኖክ ከዚህ ዓለም ጣጣ እና እንግልት ተለይቶ በሕይወት እያሉ (ሳይሞቱ) ተሠውሮ መኖርንም ያመለክታል፡፡ የቤተ ክርስቲያን መምህራን እንደሚያስተምሩን እነእገሌ ቀበሩት የሚል ቃል ስለማይገኝ ቅዱስ ያሬድ ተሠወረ እንጂ ሞተ ተብሎ አይነገርለትም፡፡ ለዚህም ማስረጃ እርሱ በተሠወረበት ተራራ አካባቢ እና በስሙ በተመሠረተው በደብረ ሐዊ ቅዱስ ያሬድ ገዳም እስከ አሁን ድረስ የከበሮ (የማኅሌት) ድምፅ ይሰማል፤ የዕጣን መዓዛም ይሸታል፡፡ ይህም ቅዱሱ ከሰው ዓይን ተሠውሮ እግዚአብሔርን እያመሰገነ እንደሚገኝ አመላካች ነው፡፡

በመጨረሻም የቅዱስ ያሬድ ድርሰቶች ለቤተ ክርስቲያን ብቻ ሳይኾን ለአገርም ድንቅና ወደር የሌላቸው ሀብቶች መኾናውን ዅላችንም ልብ ልንለው ይገባል፡፡ በመኾኑም የዜማ ድርሰቶቹ (ድጓ፣ ጾመ ድጓ፣ ምዕራፍ፣ ዝማሬ፣ መዋሥዕት) እንደ ሌሎቹ ቅርሶች ዅሉ በዩኔስኮ እንዲመዘገቡ የሚመለከታቸው አካላት ከፍተኛ ርብርብ በያደርጉ መልካም ነው፡፡ በቅዱስ ያሬድ ዜማ የሚደምቁት በዓለ ጥምቀት እና በዓለ መስቀል በዩኔስኮ ሲመዘገቡ ዜማውን ከበዓላቱ ለይቶ ማስቀረት አይገባምና፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር፡፡

የ፳፻፱ ዓ.ም ርክበ ካህናትን አስመልክቶ ከቅዱስ ፓትርያርኩ የተበረከተ ቃለ ምዕዳን  

ግንቦት ፪ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን

‹‹ወይእዜኒ ዕቀቡ ርእሰክሙ ወኵሎ መራዕየ ዘሀሎ ኀቤክሙ፤ አሁንም ራሳችሁንና በእናንተ ሥር ያለውን መንጋ ዅሉ ጠብቁ፤›› (ሐዋ. ፳፥፳፰)፡፡

ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት

መዋዕለ ጾሙን በሰላም አስፈጽሞና ከበዓለ ትንሣኤው አድርሶ፣ እንደዚሁም ዅላችንን ከየሀገረ ስብከታችን አሰባስቦ በዚህ ዓመታዊና ቀኖናዊ የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ስብሰባ በአንድነት ስለሰበሰበን እግዚአብሔር አምላካችን ስሙ የተመሰገነ ይኹን፤ እናንተም እንኳን በደኅና መጣችሁ!

ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት

ከላይ የተጠቀሰው ኃይለ ቃል የመንጋው እረኞች የኾን ዅሉ በቃለ እግዚአብሔር ጐልብተን፣ በመንፈስ ቅዱስ ኃይል ተቃኝተን ራሳችንንና ምእመናንን እንዴት መጠበቅ እንዳለብን የሚያመለክት የእግዚአብሔር ታላቅ የጥሪ ቃል ነው፡፡ ቅዱሳን ሐዋርያትና ቀደምት ቅዱሳን አበው የሥልጣነ ክህነትና የመንበረ ሐዋርያት ወራሽ የኾነው የቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤ በዓመት ሁለት ጊዜ በቋሚነትና በመደበኛነት እንደዚሁም ለቤተ ክርስቲያን ጉዳይ አስፈላጊ ኾኖ በተገኘ ጊዜ ዅሉ እየተሰበሰበ የቤተ ክርስቲያንን ጉዳይ እንዲገመግም፣ እንዲያጠና እና መፍትሔ እንዲሰጥ መደንጋጋቸው ያለ ምክንያት አልነበረም፡፡

የጉባኤው መሠረታዊ ዓላማ ጌታችን አምላካችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አስቀድሞ እንደ ተናገረው ከመጀመርያ አንሥቶ ልዩ ልዩ ፈተና ተለይቶአት የማያውቅ ቤተ ክርስቲያን በመከራው ጽናት ተሰቃ ወይም ተስፋ ቈርጣ ዓላማዋን እንዳትስት እስከ ሕይወት መሥዋዕትነት ሊዘልቅ የሚችል ጥብቅ ክትትልና ጥበቃ ለማድረግ እንዲቻል ነው፡፡

ይህም በመኾኑ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን በቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤ አማካይነት ነገራተ ቤተ ክርስቲያንን በጥልቀትና በአስተዋይነት እየተረጐመች፣ እንደዚሁም መንፈስ ቅዱስን መሪ በማድረግና አስፈላጊው መሥዋዕትነትን በመክፈል ከውጭና ከውስጥ የሚሰነዘሩባትን ጥቃቶችን እየተቋቋመች እነሆ በአሸናፊነት ከዘመናችን ደርሳለች፡፡ ይህም ሊኾን የቻለው በመንፈስ ቅዱስ ኃይል የተቃኙ ቅዱሳን አበው በፈጸሙት ተጋደሎና ወደር የለሽ መሥዋዕትነት እንደ ኾነ አይዘነጋም፡፡

የመንፈሳዊ ጥበቃና ክትትል ተግባር በቤተ ክርስቲያናችን ሥርዓተ ቀኖና መሠረት በቤተሰብ ደረጃ በነፍስ ወከፍ ጠባቂ ካህን ወይም የነፍስ አባት እንዲኖር የተደረገበት ዐቢይ ምክንያትም የጥበቃውንና የክትትሉን ተግባር አስተማማኝና ዘላቂ ለማድረግ ነው፡፡ የተግባሩ መነሻም የጌታችን ትምህርትና ትእዛዝ ነው፡፡

እኛ የቤተ ክርስቲያን መሪዎችና አገልጋዮች ሕፃኑንም ወጣቱንም፣ ጐልማሳውንና ሽማግሌውንም አንድ አድርገን እንድንጠብቅና እንድናሰማራ ጌታችን በባሕረ ጥብርያዶስ ‹‹ግልገሎቼን ጠብቅ፤ ጠቦቶቼን ጠብቅ፤ በጎቼን ጠብቅ፤›› በማለት ለቅዱስ ጴጥሮስ በሰጠው ትእዛዝ መሠረት አዞናል (ዮሐ. ፳፩፥፲፭-፲፯)፡፡ እኛም ትእዛዙንና ሓላፊነቱንም ወደንና ፈቅደን ተቀብለናል፡፡

ከበዓለ ትንሣኤ በኋላ በሃያ አምስተኛው ቀን የሚካሔደውና ረክበ ካህናት ተብሎ የሚታወቀው፣ በዛሬው ዕለት የምንጀምረው የቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤም መሠረቱ ይህ የባሕረ ጥብርያዶስ የጥበቃ ትእዛዝና ትምህርት እንደ ኾነ ይታወቃል፡፡ የቤተ ክርስቲያን ዐቢይ እና ዋና ተልእኮም ዐቂበ ምእመናን እንደ ኾነ በቅዱስ ወንጌል በተደጋጋሚ ተጽፏል፡፡ በመኾኑም ቅዱሳን ሐዋርያትም ኾኑ ቅዱሳን አበው ዋነኛ ተግባራቸው ምእመናንን ማስተማር፣ ማሳመን፣ ማጥመቅ፣ ምሥጢራተ ቤተ ክርስቲያንን ማደል፣ ከዚያም ምእመናንን በዕለተ ተዕለት ኑሮአቸው መጠበቅና ክትትል ማድረግ ነበር፡፡

ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት

ሐዋርያዊት፣ ህልወተ ኵሉ ወይም በዅሉም ያለች፣ አንዲትና ቅድስት የኾነችው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በረጅሙ የሁለት ሺሕ ዘመናት ጉዞዋ አንድነቷ ሳይናጋ፣ ሐዋርያዊ ተልእኮዋ ሳይቋረጥ ለዘመናት የዘለቀችው ካህናት በነፍስ አባትነት እያንዳንዱን ቤተሰብ በመጠበቃቸው፣ በማስተማራቸውና በመከታተላቸው ነው፡፡ ዛሬም ቢኾን እየተስፋፋ ለመጣው የምእመናን ቅሰጣ ዋና መከላከያው የነፍስ አባትን ተልእኮ ማእከል ያደረገ በቤተሰብ ውስጥ የነፍስ ወከፍ ጠበቃ ሲጠናከር ብቻ እንደ ኾነ ግንዛቤ ሊወሰድበት ይገባል፡፡

ይህንን የግብረ ኖሎት ሥራ በተፈለገው መጠን ግቡን እንዲመታ በየሀገረ ስብከቱ የካህናት ማሠልጠኛ በማቋቋም፣ ዘመኑን ያገናዘበና በቀላሉ ወደ ተግባር የሚያሸጋግር የሥልጠና መርሐ ግብር በመንደፍ ካህናቱን ከዳር እስከ ዳር በማነቃነቅ፣ አስተማማኝ ጥበቃ ማረጋገጥ ይኖርብናል፤ ይህንን ተግባር ለማፋጠን የሊቃነ ጳጳሳት ፈቃደኝነትና ተነሳሽነት ከፍተኛውን ድርሻ ይወስዳል፡፡

ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት በከፊል

እንደ እውነቱ ከኾነ ዛሬም ለሃይማኖቱ ተቆርቋሪ የኾነ፣ ለእምነቱ አድርግ የተባለውን የሚያደርግ ሕዝብ እግዚአብሔር አልነሣንም፤ በእኛ በኩል ግን የሚቀር ብዙ ሥራ እንዳለ አይካድም፡፡ ከዚህ አንጻር እተየፈታተነን ያለውን የቅን አገልግሎትና የመልካም አስተዳደር ክፍተት በፍጥነት አስተካክለን ወደ ሕዝቡ የጥበቃ ተግባር መሠማራት ወቅቱ የሚጠይቀው ተግባር መኾኑን ማስተዋል አለብን፡፡

አሁን ባለው የጥበቃና የክትትል ክፍተት ቍጥር በርከት ያለ ወጣት እየኮበለለ እንደ ኾነ ማወቅ አለብን፤ አለሁ የሚለው ወጣትም ቢኾን ኦርቶዶክሳዊ መርሕና ቀኖናን በቅጡ ባለማወቁ ሲደናገርና የተቃራኒ አካላት ባህልና ሥርዓትን ሲደበላልቅ ይታያል፡፡ ይህ ዅሉ ሊኾን የቻለው ጌታችን እንዳስተማረንና እንዳዘዘን ከግልገልነት ዕድሜ ጀምረን ወጣቱን ባለመጠበቃችንና ባለመከታተላችን እንደ ኾነ ሊሠመርበት ይገባል፡፡

ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት የቅዱስ ስኖዶስ አባላት

በቅዱስ ሲኖዶስ አመራር ሰጪነትና የበላይ ተቆጣጣሪነት የሚመራው የግብረ ኖሎት ጥበቃ የምእመናንን ዅለንተናዊ ሕይወት የሚያካልል ሊኾን ይገባል፡፡ ምእመናን ለሃይማኖታቸው የሚታመኑ፤ ለአገራቸው ዕድገትና ልማት የሚቆረቆሩ፤ በአንድነት፣ በስምምነትና በፍቅር የመኖር ጥቅምን የሚገነዘቡ፤ በማንነታቸውና በባህላቸው፣ በታሪካቸውና በእምነታቸው የሚኮሩ በአጠቃላይ የተስተካከለ መንፈሳዊና ሥነ ልቡናዊ ሰብእናን የተላበሱ እንዲኾኑ በርትተን የማስተማር፣ የመጠበቅና የመከታተል ሃይማኖታዊና ሀገራዊ ሓላፊነት አለብን፤ ይህም በታቀደ፣ በተደራጀ፣ በተጠናከረና ተከታታይነት ባለው የአፈጻጸም ሥልት ሊከናወን ይገባል፡፡

በመጨረሻም

በዚህ ዓመታዊና ቀኖናዊ የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ የቀረቡትን አጀንዳዎች ቅዱስ ሲኖዶስ በጥልቀት በማስተዋልና ለቤተ ክርስቲያናችን በሚበጅ መልኩ በማጤን፣ እንደዚሁም ለቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ህልውና መጠበቅ የሚያስችሉ ውሳኔዎችን በማሳለፍ ሐዋርያዊ ግዳጁን እንዲወጣ እያሳሰብን የሁለት ሺህ ዘጠኝ ዓመተ ምሕረት የረክበ ካህናት ቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ በዛሬው ዕለት መጀመሩን እናበሥራለን፡፡

እግዚአብሔር አምላካችን የተባረከና የተቀደሰ ጉባኤ ያድርግልን!

 ወስብሐት ለእግዚአብሔር፤ አሜን፡፡

አባ ማትያስ ቀዳማዊ

ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ

ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት፤

ግንቦት ፪ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም፤

አዲስ አበባ፣ ኢትዮጵያ፡፡

ርክበ ካህናት

በዲያቆን ኤፍሬም የኔሰው

ግንቦት ፪ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም

‹ርክብ› ወይም ‹ረክብ› የሚለው ቃል ‹ተራከበ፤ ተገናኘ› ከሚለው የግእዝ ግስ የወጣ ሲኾን፣ ትርጕሙም ማግኛ፣ መገኛ፣ መገናኛ ማለት ነው (ኪዳነ ወልድ ክፍሌ ገጽ ፰፻፴፩)፡፡ ‹ክህነት› የሚለው ስያሜም ከጵጵስና ጀምሮ እስከ ዲቁና ድረስ ያሉትን የቤተ ክርስቲያን መዓርጋት የሚያጠቃልል ቃል ሲኾን ካህን (ነጠላ ቍጥር)፣ ካህናት (ብዙ ቍጥር) በአንድ በኩል ቀሳውስትን የሚወክል ኾኖ በሌላ በኩል ደግሞ የጳጳሳት፣ የኤጲስ ቆጶሳት፣ የቀሳውስት፣ የዲያቆናት የጋራ መጠሪያ ነው፡፡ ‹ርክበ ካህናት› የሚለው ሐረግም የካህናት መገኛ፣ መገናኛ፣ ጉባኤ (መሰባሰቢያ)፣ መወያያ፣ ወዘተ የሚል ትርጕም አለው፡፡ በአጭሩ ‹ርክበ ካህናት› ማለት – የአባቶች ካህናት ማለትም የብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት (የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት) ጉባኤ ማለት ነው፡፡

በቅዱስ ዮሐንስ ወንጌል እንደ ተገለጸው ጌታችን አምላካችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከሞት ከተነሣ በኋላ ለሦስተኛ ጊዜ ተገልጦ ከዐሥራ አንዱ ቅዱሳን ሐዋርያት ጋር ምሳ በልቷል፡፡ ከምሳ በኋላም ጌታችን ቅዱስ ጴጥሮስን ሦስት ጊዜ ጠርቶ ‹‹ትወደኛለህን?›› እያለ ከጠየቀው በኋላ እንደሚወደው ምላሽ መስጠቱን ተከትሎ በቅደም ተከተል ‹‹በጎቼን ጠብቅ፤ ጠቦቶቼን አሰማራ፤ ግልገሎቼን ጠብቅ፤›› በማለት የአለቅነት ሥልጣን ሰጥቶታል፡፡ ይህ ምሥጢር ለጊዜው ጌታችን ሐዋርያትን፣ ሰብዐ አርድእትንና ሠላሳ ስድስቱን ቅዱሳት አንስት በአጠቃላይ መቶ ሃያውን ቤተሰብእ እንዲጠብቅና እንዲከባከብ ቅዱስ ጴጥሮስን ማስጠንቀቁን፤ ለፍጻሜው ግን የቤተ ክርስቲያን አባቶች (ጳጳሳት) መምህራንንና መላው ሕዝበ ክርስቲያንን እንዲጠብቁና እንዲያስተዳድሩ በእግዚአብሔር መሾማቸውን የሚያስረዳ ምሥጢር አለው (ዮሐ.፳፩፥፩-፲፯)፡፡

ይህን የጌታችንን ትእዛዝና የሐዋርያትን ሥልጣነ ክህነት መሠረት በማድረግ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ በዓመት ሁለት ጊዜ ጉባኤ ያደርጋል፤ የመጀመሪያው ጉባኤ ጥቅምት ፲፪ ቀን (የቅዱስ ማቴዎስ በዓል) ሲኾን፣ ሁለተኛው ደግሞ ርክበ ካህናት ነው፡፡ በዓሉ (ርክበ ካህናት) ወሩና የሚውልበት ቀን የበዓላትንና የአጽዋማትን ቀመር ተከትሎ ከፍና ዝቅ ቢልም በየዓመቱ የትንሣኤ በዓል በተከበረ በ፳፭ኛው ቀን በዕለተ ረቡዕ ይውላል፡፡ የአጽዋማትና የበዓላት ቀመር ከመዘጋጀቱ በፊት ማለትም በቅዱስ ድሜጥሮስ አማካኝነት ዐቢይ ጾም ሰኞ፣ ስቅለት ዓርብ፣ ትንሣኤ እሑድ፣ ርክበ ካህናት ረቡዕ፣ ዕርገት ሐሙስ፣ ጰራቅሊጦስ እሑድ እንዲኾን ከመደረጉ በፊት ርክበ ካህናት ግንቦት ፳፩ ቀን ይውል ነበር (መጽሐፈ ግጻዌ፣ ግንቦት ፳፩ ቀን)፡፡

ከዚህ በኋላ በዓለ ትንሣኤ በዋለ በ፳፭ኛው ቀን፣ በበዓለ ኃምሳ እኩሌታ በዕለተ ረቡዕ ርክበ ካህናት እንዲዘከር የቤተ ክርስቲያን አባቶች ወስነዋል፡፡ በያዝነው ዓመት በ፳፻፱ ዓ.ም የትንሣኤ በዓል ከተከበረበት ዕለት (ሚያዝያ ፰ ቀን) ጀምሮ ብንቈጥር ፳፭ኛው ቀን ግንቦት ፪ ቀን ነው፡፡ በመኾኑም የዘንድሮው ርክበ ካህናት ግንቦት ፪ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም ይውላል ማለት ነው፡፡ ይህ በዓል (ርክበ ካህናት) ከቅዱሳን ሐዋርያት ጀምሮ ቅድስት ቤተ ክርስቲያንን ሲመሩ የቆዩ አባቶቻችን በጋራ በመሰባሰብ ለቅድስት ቤተ ክርስቲያን የተቀላጠፈ አገልግሎት እንደዚሁም ለምእመናን አንድነትና መንፈሳዊ ዕድገት የሚበጁ መንፈሳውያን መመሪያዎችን የሚያስተላልፉበት ዕለት ነው፡፡ በዚህ ዕለት ቅዱስ ሲኖዶስ በሚያደርገው ጉባኤ የሚተላለፉ መመሪያዎችና የሚጸድቁ ውሳኔዎች ለቤተ ክርስቲያን ዕድገት፣ ለምእመናን አንድነት፣ ለአገር ሰላምና ደኅንነት የሚጠቅሙ ይኾኑ ዘንድ ዅላችንም በጾም በጸሎት እግዚአብሔርን መጠየቅ ይኖርብናል፡፡

አምላካችን ቤተ ክርስቲያናችንንና አባቶቻችንን ይጠብቅልን፤ እኛንም ለአባቶች የሚታዘዝ ልቡና፣ ሓላፊነታችንን የምንወጣበትን ጥበብና ማስተዋልን ያድለን፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር፡፡