የጂንካ ማእከል የመጀመሪያውን የሐዊረ ሕይወት ጉዞ ወደ ስብከት ኬላ አደረገ
ጂንካ ማእከል
በጂንካ ማእከል በማኅበረ ቅዱሳን ጂንካ ማእከል የመጀመሪያውን የሐዊረ ሕይወት ጉዞውን በደቡብ ኦሞ ሀገረ ስብከት፣ በበና ጸማይ ወረዳ፣ ጫሊ ቅድስት ሥላሴ ስብከት ኬላ ታኅሣሥ 17 ቀን 2008 ዓ.ም በደማቅ ሁኔታ ተካሄደ፡፡በጉዞው ላይ የደቡብ ኦሞ ሀ/ስብከት የመምሪያ ሓላፊዎች፣ የጂንካ ከተማ ገዳም፣ አስተዳደርና የአቢያተ ክርስቲያናት አስተዳዳሪዎች እንዲሁም ከአዲስ አበባ የመጡ ተጋባዥ እንግዶች፣ ሰባኬ ወንጌልና ዘማሪያን በአጠቃላይ 1000 ምእመናን ተሳትፈዋል፡፡
ጉዞው ቤተ ክርስቲያን ባልታነፀበት የስብከት ኬላ እና ሁልጊዜም “አጥምቁን እና ቤተ ክርስቲያን ሥሩልን” ወደሚሉት አርብቶ አደር ወገኖቻችን ጋር መደረጉ ከሌሎች ማእከላት ልዩ ያደርገዋል ተብሏል፡፡
ጉዞው ታኅሣሥ 17 ቀን 2008 ዓ.ም ጠዋት 12፡30 ላይ በቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን ምእመናን በተገኙበት በአንቀጸ ብፁዓን አቡነ ተክለ ሃይማኖት ገዳም አበምኔት ቆሞስ መ/ር አባ ኤፍሬም ፈቃዴ በጸሎት የተከፈተ ሲሆን በአስተባባሪዎች አማካኝነት ሁሉም ምእመናን ወደተዘጋጀላቸው መኪና ከገቡ በኋላ ጉዞው ተጀመረ፡፡ በጉዞው ላይ በአስተባባሪዎች አማካኝነት በክርስትና ሕይወት ዙሪያ ውይይት እየተደረገ መዝሙር እየተዘመረ እና ከተጓዦች ጥያቄ እየተሰበሰበ የጉዞው ቦታ ላይ ተደርሷል፡፡ በቦታውም ያሉ አርብቶ አደር ምእመናን “ሁሌም አጥምቁን ቤተ ክርስቲያን ሥሩልን” የሚሉን በርካታ ምእመናን በቋንቋቸው በዝማሬ ተጓዦችን ተቀብለዋል፡፡
የጧዋቱ መርሐ ግብር በካህናት ጸሎተ ወንጌል የተከፈተ ሲሆን ትምህርትም በመምህራን ወንጌል ተሰጥቷል ፡፡ከሰዓት በኋላ ከጂንካ አጥቢያ በተገኙ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን በቆሞስ መ/ር አባ ኤፍሬም ፈቃዴ የአንቀጸ ብፁዓን አቡነ ተክለ ሃይማኖት ገዳም አበምኔት ከሕዝብ የተነሳውን ጥያቄዎችን፣ ሊቀ ብርሃናት ኤልያስ ዘውዴ በቤተ ክርስቲያን የምእመናን ድርሻ ምንድነው? መሪጌታ ዘመልአክ የበዓታ ለማርያም ቤተ ክርስቲያን አስተዳዳሪ የልጆች አስተዳደግ ምን መምሰል አለበት? በሚል ርእስ ለምእመናን በቂ መልስ የሰጡ ሲሆን፣ በጉባኤው ላይ የተገኙት ቀሲስ ዶ/ር ሙሉጌታ ስዩም ደግሞ ስለ ቅዱስ ጋብቻ እና የንስሐ ሕይወት ዙሪያ ከአባታዊ ምክር ና ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ÃÃÃÃÂ ስለ ጫሊ ስብከት ኬላ አመሠራረትና አሁን ስላለው የአገልግሎት እንቅስቃሴ እና ስለ ቀጣዩ ዕቅዳቸው በጥያቄና መልስ የተብራራ ሲሆን፤ ስብከት ኬላውም ጳጉሜ 3 በ1999 ዓ/ም በአቡነ ዕንባቆም እንደተባረከ ተገልጧል፡፡
በመጨረሻም የጂንካ ማዕከል ሰብሳቢ አቶ ዘላለም ጌታቸው አጠቃላይ መልእክት፣ ማሳሰቢያና ለስብከት ኬላው ገቢ በማሰባሰብ እና በጉዞው አስተዋጽኦ ላደረጉ አካላት ምስጋና በማቅረብ በጂንካ ደብረ ቀራኒዮ መድኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያን አስተዳዳሪ አማካኝነት በጸሎት ተዘግቶ የመርሐ ግብሩ ፍጻሜ ሆኗል፡፡ ከተጓዦች መካከል እንግዶች በሰጡት አስተያየት ጉዞው ቢደገምና ሌሎችም እንዲህ ዓይነቱን ዝግጅት ቢካፈሉ ጠቀሜታው የጎላ ነው ብለዋል፡፡ ማኅበሩም የአገልግሎት ማኅበር መሆኑን ተገንዝበናል ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡