የመስቀል ኃይልና ቅርጾች በሚል ርዕስ የነገረ ቤተክርስቲያን የጥናት ጉባኤ ሊካሔድ ነው

ጥናታዊ ጽሑፉ የፊታችን ቅዳሜ ታህሳስ 16 ቀን 2008 ዓ.ም አዲስ አበባ አምስት ኪሎ ቅድስተ ማርያም አካባቢ በሚገኘው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የሰንበት ት/ቤቶች ማደራጃና መምሪያ ማኅበረ ቅዱሳን ሕንጻ 3ኛ ፎቅ ላይ በሚገኘው አዳራሽ ይካሔዳል፡፡

“የመስቀሉ ኃይልና ቅርጾች በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን” በሚል ርዕስ የተዘጋጀው የነገረ ቤተ ክርስቲያን የጥናት ጉባኤ ላይም ቁጥራቸው ከ350-400 የሚደርሱ ተሳታፊዎች ይገኙበታል ተብሎ ሲጠበቅ፤ በጉባኤው ላይም ከብፁዓን አባቶች፣ ከቤተ ክህነት የመመሪያ ሓላፊዎች፣ ከዩኒቨርሲቲ ምሑራን እና ከሌሎች ማኅበራት የተወጣጡ በርካታ ባለድርሻ አካላት ይገኛሉ ተብሎ ይታሰባል፡፡

በጉባኤው ላይ በሚቀርበው ጥናታዊ ጽሑፍም የመስቀል ኃይልና ቅርጾችን በተመለከተ ግንዛቤ ከመፍጠርም በተጨማሪ አጠቃላይ ስለ መስቀል ገናናነት በማስረዳት ትውልዱ ለመስቀሉ የሚገባውን ክብር እንዲሰጥ ያደርጋል፡፡በማኅበረ ቅዱሳን ጥናትና ምርምር ማዕከል ያገኘነው መረጃ እንደሚጠቁመው በዕለቱ የሚቀርበው ጥናታዊ ጽሑፍ ርዕስን አስመልክቶ ውይይት የሚደረግ ሲሆን በጉባኤው ላይ ሁሉም ምዕመናን መሳተፍ የሚችሉ መሆኑ ታውቋል፡፡

ጉባኤው ከቀኑ 8፡00 ሰዓት እስከ 11፡30 ይቆያል ተብሎ ይጠበቃል፡፡