የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በዝርወት ክፍል ሁለት

ሐምሌ 3 ቀን 2005 ዓ.ም

በዲ/ን ዶ/ር መርሻ አለኸኝ

ባለፈው ዕትማችን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ በዝርወት /ከኢትዮጵያ ውጪ/ ያደረገችውን ረዥም ሐዋርያዊ ጉዞ የሚዳስስ ጽሑፍ ማውጣታችን ይታወሳል፡፡ ቀጣዩን ደግሞ እንደሚከተለው አቅርበነዋል፡፡

2. አፍሪካ
የኢ.ኦ.ተ.ቤ. የጥቁሩን ሕዝብ መወከል የሚያስችላት ታሪካዊ አጋጣሚ ቢኖራትም ከዓለም ቀድማ በተመሠረተችበት አህጉር ለሚገኘው ሕዝቧ የሰጠችው አገልግሎት ሰፊ የሚባል አይደለም፡፡ እሷ አገልግሎት ባለመስጠቷ ጥቁሩ ሕዝብ ባሕሉና ልማዱ በፈጠረው ሀገረ ሰብአዊ እምነት ተይዞ ከአሚነ እግዚአብሔር ርቆ ለረጅም ዘመናት እንዲቆይ ሆኗል፡፡ አፍሪካውያን ከብዙ ሺሕ ዓመታት በኋላ ከኢትዮጵያ በእጅጉ ዘግይተው ወንጌልን የተቀበሉ አውሮ¬ውያን ያስተማሯቸውን ተቀብለዋል፡፡ ይልቁንም ቤተ ክርስቲያናችን ወደ ሕዝቡ መሔዷ ቀርቶ ራሱ ሕዝቡ እሷን ፈልጎ እንዲመጣ ኾኗል፡፡ በእርግጥ ቤተ ክርስቲያናችን ቀደም ባሉት ጊዜያት እስከ ሱዳንና ሱማልያ ተስፋ ፍታ እስልምና እስከሚቀማት ድረስ በርካታ አፍሪካውያንን በሃይማኖት ይዛ እንደቆየች የሚያስረዱ የታሪክ መዛግብት አሉ፡፡ ቤተ ክርስቲያኗ በአፍሪካ ያላት የሳሳ ታሪክ በአጭሩ እንደሚከተለው ቀርቧል፡፡

2.1 ኬንያ
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ከ1967/68 ዓ.ም ጀምሮ በናይሮቢ አገልግሎት መስጠት ጀምራለች፡፡ በ1978 ዓ.ም የተመሠረተው የደብረ መድኃኒት መድኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያንም ለምእመናን አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም በስደተኞች ካምፕ የመድኃኔዓለምና ለኬንያዎች የቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን በስደተኞተ ካምፕ አካባቢ እንዳለ ይነገራል፡፡

 
2.2 ሱዳን
በካርቱም ከተማ ቤተ ክርስቲያን ተቋቁማ ከ1932 ዓ.ም ጀምሮ አገል ግሎት በመስጠት ላይ ትገኛለች፡፡

2.3 ደቡብ አፍሪካ
ይህች ሀገር ከኢትዮጵያውያኑ በተጨማሪ ለኢትዮጵያና ብሔራዊት ቤተ ክርስቲያኗ ልዩ ፍቅር ያላቸውና የኢ.ኦ.ተ.ቤ. ተከታዮች ነን ብለው የሚያምኑ ሰዎች በብዛት የሚኖሩባት ናት፡፡ እነዚህ ሰዎች ይህንን እምነታቸውን በተግባር ለመተርጎም እ.ኤ.አ. ከ1872 ዓ.ም ጀምሮ እንቅስቃሴ አድርገው እ.ኤ.አ. በ1892 ዓ.ም. የተወሰኑ ምእመናን ከነበሩበት የሜቶዲስት ቤተ ክርስቲያን ተለይተው በመውጣት “የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን” ብለው አቋቋሙ፡፡ ኢትዮጵያ በአድዋ ጦርነት በጣልያኖች ላይ የተቀዳጀችው የድል ዜና እንቅስቃሴያቸውን የበለጠ እንዲጎለብትና ማኅበራቸው እንዲጠናከር አድርጓል፡፡ ቤተ ክርስቲያኗ በነበሩባት ውስጣዊ ችገሮች የተነሣ የፈለጉትን ያህል ልታጠናክራቸው ባትችልም አልፎ አልፎ በሚያገኙት ዕርዳታና የአይዞአችሁ መልእክት ቤተ ክርስቲያናችን በአካባቢው ላለው ሕዝብ አገልግሎት ስትሰጥ እንድትቆይ አድርጓታል፡፡ በ1993 ዓ.ም ደግሞ በስደት ወደ አካባቢ የሔዱ ኢትዮጵያውያን ምእመናን ከደቡብ አፍሪካውያኑ የእምነት ወንድሞቻቸው ጋር በመተባበር የመድኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያንን አቋቁመዋል፡፡

3. አውሮፖ
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሐዋርያዊ እግሯ አውሮፖን የረገጠው /በጊዜው በኢጣልያ ፍሎሬንስ በተደረገው ዓለም ዐቀፍ የአብያተ ክርስቲያናት ጉባኤ ከኢየሩሳሌም የኢትዮጵያ ገዳማት ተመርጠው በተላኩ ልኡካን አማካይነት /ከ15ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ጀምሮ  እንደኾነ ታሪክ እማኝነቱን ቢሰጥም በይፋ በተደራጀ መልኩ ተቋቁማ አገልግሎት መስጠት የጀመረችው በ20ኛው መቶ ክፍለ ዘመን አጋማሽ ጀምሮ ነው፡፡ በዚህ ረገድ በቀዳሚነት የሚጠቀሰው ኢትዮጵያ በፋሺስት ጣልያን በተወረረችበት ጊዜ ንጉሠ ነገሥት ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ወደ ሎንዶን ካደረጉት ስደት ጋር ለአጭር ጊዜም ቢሆን በተሰጠው አገልግሎት ጀምሮ በ1964 ዓ.ም በትውልደ ጃማይካውያን የቤተ ክርስቲያኗ ልጆች አማካይነት ተቋማዊ መልክ ይዞ እንዲቀጥል የተደረገው ነው፡፡ በአሁኑ ጊዜ በታላቋ ብሪታንያ አምስት ያህል አብያተ ክርስቲያናትና ከሦስት በላይ የጽዋ ማኅበራት ይገኛሉ፡፡

ከእንግሊዝ ቀጥሎ ቤተ ክርስቲያና ችን የደረሰችበት ሀገር ጀርመን ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያናችን በአካባቢው እንቅስቃሴ የጀመረችው በወቅቱ ለትምህርት ወደዚህ ሀገር መጥተው በነበሩት መልአከ ሰላም ዶ/ር መርዐዊ ተበጀና ዶ/ር በዕደ ማርያም አማካይነት ሲኾን በአሁኑ ወቅት ሰባት ያህል አጥቢያ አብያተ ክርስቲያናትና ከሦስት የማያንሱ የጽዋ ማኅበራት ይገኛሉ፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ከ15 ያላነሱ አብያተ ክርስቲያናት ማለትም በግሪክ /አንድ/፣ በጣልያን /ሦስት/፣ በስዊዘርላንድ /ሦስት/ በስዊድን /ሁለት/፣ በኖርዌይ /ሁለት/፣ በቤልጅየም /አንድ/፣ በኦስትርያ /አንድ/፣ በፈረንሳይ /አንድ/ አብያተ ክርስቲያናት የሚገኙ ሲሆን ወደ ቤተ ክርስቲያን ደረጃ ለማደግ ክትትል እየተደረገላቸው ያሉ ጽዋ ማኅበራት በተለያዩ የአውሮ¬ፖ ሀገራት አሉ፡፡

4. አውስትራሊያ
በዚህ አህጉር የቤተ ክርስቲያናችን እንቅስቃሴ ጥንታዊ የሚባል አይደለም፡፡ በአሁኑ ወቅት ከሦስት ያላነሱ አብያተ ክርስቲያናት የሚገኙ ሲሆን እንደዚሁ በጽዋ ማኅበርነት የተደራጁ የምእመናን ኅብረቶች አሉ፡፡

5. ሰሜን አሜሪካ
የቤተ ክርስቲያናችን የሰሜን አሜሪካ እንቅስቃሴ የተጀመረው ከ1944 ዓ.ም ጀምሮ ሲኾን ቤተ ክርስቲያን በኦፊሴል የተመሠረተችው ግን በ1951 ዓ.ም በአቡነ ቴዎፍሎስ ተባርኮ ኒውዮርክ ላይ በተቋቋመው የቅድስት ሥላሴ ቤተ ክርስቲያን አማካይነት ነበር፡፡ ይህ ቤተ ክርስቲያን የተቋቋመው በወቅቱ የኢትዮጵያን የጥቁር ሕዝብ አርአያነት አምነው ያስተጋቡ ለነበሩ አፍሪካ አሜሪካውያን ሲሆን ቤተ ክርስቲያኑ ቅዳሴ ቤቱ ተከብሮ በተቋቋመበት ዕለት 275 አፍሪካ አሜሪካውያን በመጠመቅ የቤተ ክርስቲያን አካል እንደሆኑ መዛግብት ያስረዳሉ፡፡ በዚህ ዓይነት በርቀት ለናፈቃት ጥቁሩ ሕዝብ ፓ-ስፊክን አቋርጣ የተቋቋመችለት ቤተ ክርስቲያን እየዋለ እያደረ በልዩ ልዩ ምክንያት ሀገሩን ትቶ ወደ አህጉሩ የሚሰደደው ሕዝብ ቁጥር እየበዛ ሲሔድ እሷም እየተስፋፋች ዛሬ ካለችበት ደረጃ ደርሳለች፡፡ በአሁኑ ወቅት በአህጉሩ ከ90 በላይ አብያተ ክርስቲያናት ይገኛሉ፡፡ 

 
6. ካናዳ
በካናዳ የቤተ ክርስቲያን አገልግሎት የተጀመረው በቶሮንቶ ከተማ በአንድ ምእመን ድጋፍ በተገዛ ሕንፃ ውስጥ በ1964 ዓ.ም ሲሆን በአሁኑ ወቅት በመላ አህጉሩ ከሃያ አምስት በላይ አብያተ ክርስቲያናት አሉ፡፡

7. ካሪብያን ሀገሮች
በዚህ ትሪንዳድ ቶቤጎን ጉያናንና ጃማይካን በሚያጠቃልለው አካባቢ ቤተ ክርስቲያን አገልግሎት የጀመረችው በ1964 ዓ.ም. በአባ ገብረ ኢየሱስ /በኋላ አቡነ አትናቴዎስና አቶ አበራ ጀንበሬ አማካይነት ሲኾን በአሁኑ ወቅት ከአምስት በላይ አብያተ ክርስቲያናት ይገኛሉ፡፡

8. ትሪንዳድና ቶቤጎ
ቤተ ክርስቲያን በቅኝ ገዥዎቹ በደረሰበት ተፅዕኖ በማንነት ፍለጋ ይናውዝ ለነበረው ለዚህ አካባቢ ጥቁር ሕዝብ አገልግሎት መስጠት የጀመረችው ከ1944 ዓ.ም ጀምሮ ሲሆን ከዚያ ጊዜ ጀምሮ በተደረጉ ሐዋርያዊ እንቅስቃሴዎች በብዙ ሺሕ የሚቆጠሩ ነፍሳት በጥምቀት ከማኅፀነ ዮርዳኖስ ከአብራከ መንፈስ ቅዱስ ተወልደው በቤተ ክርስቲያን ዕቅፍ ውስጥ ገብተዋል፡፡ እየገቡም ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት በዚህ አካባቢ ከአምስት ያላነሱ አብያተ ክርስቲያናት ይገኛሉ፡፡  

9. ጃማይካ
በዚህ አካባቢ ይኖሩ የነበሩ ሕዝቦች ጣልያን ኢትዮጵያን በወረረችበት ጊዜ የነጻነታቸው ተስፋ ምድራዊ ርስት አድርገው ይቆጥሯት ለነበረችው ኢትዮጵያ አጋርነታቸውን ለማሳየት “ራስ ተፈሪያን” የሚል ቡድን መሥርተው ነበር፡፡ ንጉሡ በ1958 ዓ.ም በጃማይካ ይፋ ጉብኝት ካደረጉ በኋላ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ እምነት ተከታይ የመሆን ፍላጎት እያየለ በመምጣቱ የመጀመሪያዪቱ ቤተ ክርስቲያን በኪንግስተን ጃማይካ ተቋቋመች፡፡ ከዚያም በኋላ ግንቦት 6 ቀን 1962 ዓ.ም. ለመጀመሪያ ጊዜ ጃማይካ ሲገቡ ብሔራዊ አቀባበል በተደረገላቸው ብፁዕ አቡነ ይስሐቅ አማካይነት ቤተ ክርስቲያን ከፍተኛ ሐዋርያዊ አገልግሎት ሰጥታ ዛሬ ካለችበት ደረጃ ደርሳለች፡፡

II. አስተዳደራዊ መዋቅር
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ከላይ በቀረበው መልኩ ዓለም ዐቀፋዊ አገልግሎት ስትሰጥ እንደየዘመኑ ሁኔታ የራሷን አስተዳደራዊ መዋቅር እየዘረጋች ሲሆን ዛሬ ባለችበት ደረጃ የዝርወት እንቅስቃሴዋን በመምራት ላይ ያለችው 12 ያህል አህጉረ ስብከትን በማቋቋም ነው፡፡ እነዚህም የመላ አፍሪካ ሀገረ ስብከት፣ የአውስትራሊያ ሀገረ ስብከት፣ የመካከለኛው ምሥራቅ ሀገረ ስብከት፣ የሰሜን ምዕራብ አውሮፓ ሀገረ ስብከት፣ የደቡብ ምሥራቅ አውሮፓ ሀገረ ስብከት፣ የኢየሩሳሌም ሀገረ ስብከት፣ የዲሲና አካባቢው ሀገረ ስብከት፣ የኒውዮርክና አካባቢው ሀገረ ስብከት፣ የካሪብያን ሀገራት ሀገረ ስብከትና የካናዳ ሀገረ ስብከት ናቸው፡፡

 
እዚህ ላይ ሳይጠቀስ ማለፍ የሌለበት ቤተ ክርስቲያናችን በልዩ ልዩ የዓለም አብያተ ክርስቲያናት መካከል ማኅበራዊ መረዳዳትንና ቅርርብን ዓላማው አድርጎ በ1948 ዓ.ም በአምስተርዳም የተመሠረተው የዓለም አብያተ ክርስቲያናት ኅብረት /World Council of Cherches/ ሲመሠረት በመሳተፍ ከመሠረቱ ሀገራት አንዷ መሆኗ ነው፡፡ በተጨማሪም በአፍሪካ ደረጃ በ1963 ዓ.ም ናይሮቢ ኬንያ ላይ የተቋቋመው የአፍሪካ አብያተ ክርስቲያናት ጉባኤ መሥራች አባል ናት፡፡ ከያዝነው ርእስ አንጻር የቤተ ክርስቲያኗ የእነዚህ ጉባኤያት አባል መሆን ብዙም የጠቀማት አይመስልም፡፡ ወይም ጉባኤያቱን በአግባቡ መጠቀም አልቻለችም፡፡ 

    
III.  ችግሮች
ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ዓላማዋ ሰማያዊ እንደመሆኑ በተለያዩ ጊዜያት የዓላማዋ ተፃራሪ በሆነው ዲያብሎስ ስትፈተን ኖራለች አሁንም በመፈተን ላይ ትገኛለች፡፡ በዚህ አካባቢ ያለችዋ ቤተ ክርስቲያናችንም ከምሥረ ታዋ ጀምሮ ልዩ ልዩ ችግሮች አጋጥመዋታል፡፡ ዛሬም እነዚሁ ችግሮች ሰማያዊ አገልግሎቷን በስፋት በክርስቶስ የባሕርይ አምላክነት አምነው በጉያዋ ለተሰበሰቡ ስዱዳን ልጆቿ እንዳትሰጥ ያደርጓታል፡፡

በአካባቢው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ያሉባትን ችግሮች ውስጣዊ እና ውጫዊ ብለን ከፍለን ማየት እንችላለን፡፡ ውስጣዊ ስንል በየደረጃው ካሉ አንዳንድ የቤተ ክርስቲያኗ አካላት፣ ካህናት፣ ምእመናን፣ ሰበካ ጉባኤያት፣ ሰንበት ትምህርት ቤቶች ወ.ዘ.ተ.፣ የሚመጡ ችግሮችን ሲሆን ውጫዊ ስንል ደግሞ ከቤተ ክርስቲያኗ ውጭ ካሉ አካባቢያዊ ነባራዊ ሁናቴዎች የሚመጡትን ችግሮች ነው፡፡

የግእዝ ቁጥሮች አጻጻፍ

ሐምሌ 17 ቀን 2005 ዓ.ም.

በመ/ት ኑኀሚን ዋቅጅራ

የግእዝ ቋንቁ ጥንታዊያን ከተሰኙ ቋንቋዎች መካከል አንዱ ሲሆን ኢትዮጵያውያን ሊቃውንት በቀን አቆጣጠርና በሥነ ጽሑፎቻቸው ሲጠቀሙበት ከትውልድ ወደ ትውልድ ሲተላለፍ ቆይቷል፡፡ ዛሬም የግእዝ ቁጥሮች በኢትዮጵያውያን ዘንድ ሰፊ ሥፍራ አላቸው፡፡

በዚህ ዓምዳችን የግእዝ ቁጥሮችን አጻጻፍና የንባብ ስያሜአቸውን ማቅረባችንን እንቀጥላለን፡፡
የግእዝ ቋንቋ እንደ ማንኛውም ቋንቋ እራሱን የቻለ የቁጥር አጻጻፍ ስልቶች አሉት፡- እነዚህ ቁጥሮች እኛ በተለምዶ አጠራር የአማርኛ ቁጥሮች ብለን እንጠራቸዋለን፡፡ ይሁን እንጂ ትክክለኛውን አካሄድ ስንመለከት በአጠቃላይ የአማርኛ ብቻ ሳይሆኑ ልክ እንደ አማርኛ ፊደሎች ሁሉ ቁጥሮቹም መነሻቸው ግእዝ መሆኑን እንረዳለን፡፡

የግእዙም ሆነ አሁን እኛ የምንጠቀምበት ቁጥር ማለትም ከዐ/ዜሮ/ ጀምረን የምንጽፈው የአማርኛ ቁጥር ሳይሆን ስያሜው ከየት እንደመጣ ትክክለኛ መረጃዎች ባይኖሩም 0፣ 1፣ 2፣ 3….. እየተባሉ የሚዘረዘሩት ቁጥሮች የዐረብኛ ቁጥሮች ተብለው እንደሚጠሩ በተለያዩ መጻሕፍት ተጽፈው እናገኛለን፡፡

በኢትዮጵያ የቀን አቆጣጠር /የቀን መቁጠሪያ/ ላይ የምናገኛቸውን በየወቅቱ የሚከበሩተን ሃይማኖታዊ በዓላትንና ብሔራዊ በዓላትን ለማክበር የምጠቀመው የቀን አቆጣጠር የግእዝ ቁጥር /ኢትዮጵያዊ/ ቁጥር እንደሆኑ በግልጹ ልንረዳውና ተገቢውን ስያሜ አውቀን በስሙ ልንጠራው ይገባናል፡፡

የግእዝ ቁጥሮችን በዝርዝር ጽፈን መጨረስ ባንችልም ከብዙ በጥቂቱ በመሠረታዊነት የምንጠቀምባቸውን ቁጥሮች ከዚህ በመቀጠል እንመለከታለን፡፡

 

የግእዝ ቁጥሮች በአኀዝ

የግእዝ ቁጥሮች በፊደል

የዐረብኛ ቁጥር

አልቦ

0

አሐዱ

1

ክልኤቱ

2

ሠለስቱ

3

አርባዕቱ

4

ሐምስቱ

5

ስድስቱ

6

ስብዓቱ

7

ስመንቱ

8

ተሰዓቱ

9

አሠርቱ

10

፲፩

አሠርቱ ወአሐዱ

11

፲፪

አሠርቱ ወክልኤቱ

12

፲፫

አሠርቱ ወሠለስቱ

13

፲፬

አሠርቱ ወአርባዕቱ

14

፲፭

አሠርቱ ወሐምስቱ

15

፲፮

አሠርቱ ወስድስቱ

16

፲፯

አሠርቱ ወሰብዓቱ

17

፲፰

አሠርቱ ወስመንቱ

18

፲፱

አሠርቱ ወተሰዓቱ

19

እስራ

20

፳፩

እስራ ወአሐዱ

21

፳፪

እስራ ወክልኤቱ

22

፳፫

እስራ ወሠለስቱ

23

፳፬

እስራ ወአርባዕቱ

24

፳፭

እስራ ወሐምስቱ

25

፳፮

እስራ ወስድስቱ

26

፳፯

እስራ ወሰብዓቱ

27

፳፰

እስራ ወሰመንቱ

28

፳፱

እስራ ወተሰዓቱ

29

ሠላሳ

30

፴፩

ሠላሳ ወአሐዱ

31

፴፪

ሠላሳ ወክልኤቱ

32

፴፫

ሠላሳ ወሠለስቱ

33

፴፬

ሠላሳ ወአርባዕቱ

34

፴፭

ሠላሳ ወሐምስቱ

35

፴፮

ሠላሳ ወስድስቱ

36

፴፯

ሠላሳ ወሰብዓቱ

37

፴፰

ሠላሳ ወሰመንቱ

38

፴፱

ሠላሳ ወተሰዓቱ

39

አርብዓ

40

ሃምሳ

50

ስድሳ

60

ሰብዓ

70

ሰማንያ

80

ተሰዓ

90

ምዕት

100

፻፩

ምዕት ወአሐዱ

101

፻፪

ምዕት ወክልኤቱ

102

፻፫

ምዕት ወሠለስቱ

103

፻፬

ምዕት ወአርባዕቱ

104

፻፭

መዕት ወሐምስቱ

105

፻፮

ምዕት ወስድስቱ

106

፻፯

ምዕት ወሰብዓቱ

107

፻፰

ምዕት ወስመንቱ

108

፻፱

ምዕት ወተሰዓቱ

109

፻፲

ምዕት ወአሠርቱ

110

፻፲ወ፩

ምዕት አሠርቱ ወአሐዱ

111

፻፲ወ፪

ምዕት አሠርቱ ወክልኤቱ

112

፻፲ወ፫

ምዕት አሠርቱ ወሠለስቱ

113

፻፲ወ፬

ምዕት አሠርቱ ወአርባዕቱ

114

፻፲ወ፭

ምዕት አሠርቱ ወሐምስቱ

115

፻፲ወ፮

ምዕት አሠርቱ ወስድስቱ

116

፻፲ወ፯

ምዕት አሠርቱ ወሰብዓቱ

117

፻፲ወ፰

ምዕት አሠርቱ ወስመንቱ

118

፻፲ወ፱

ምዕት አሠርቱ ወተሰዓቱ

119

፻፳

ምዕት ወእስራ

120

፻፴

ምዕት ወሠላሳ

130

፻፵

ምዕት ወአርብዓ

140

፻፶

ምዕት ወሃምሳ

150

፻፷

ምዕት ወስድሳ

160

፻፸

ምዕት ወሰብዓ

170

፻፹

ምዕት ወሰማንያ

180

፻፺

ምዕት ወተሰዓ

190

፪፻

ክልኤቱ ምዕት

200

፪፻ወ፩

ክልኤቱ ምዕት ወአሐዱ

201

፪፻ወ፪

ክልኤቱ ምዕት ወክልኤቱ

202

፪፻ወ፫

ክልኤቱ ምዕት ወሠለስቱ

203

፪፻ወ፬

ክልኤቱ ምዕት ወአርባዕቱ

204

፪፻ወ፭

ክልኤቱ ምዕት ወሐምስቱ

205

፪፻ወ፮

ክልኤቱ ምዕት ወስድስቱ

206

፪፻ወ፯

ክልኤቱ ምዕት ወሰብዓቱ

207

፪፻ወ፰

ክለኤቱ ምዕት ወስመንቱ

208

፪፻ወ፱

ክልኤቱ ምዕት ወተሰዓቱ

209

፪፻ወ፲

ክልኤቱ ምዕት ወአሠርቱ

210

፪፻፲ወ፩

ክልኤቱ ምዕት አሠርቱ ወአሐዱ

211

፪፻፲ወ፪

ክልኤቱ ምዕት አሠርቱ ወክልኤቱ

212

፪፻፲ወ፫

ክልኤቱ ምዕት አሠርቱ ወሠልስቱ

213

፪፻፲ወ፬

ክልኤቱ ምዕት አሠርቱ ወአርባቱ

214

፪፻፲ወ፭

ክልኤቱ ምዕት አሠርቱ ወሐምስቱ

215

፪፻፲ወ፮

ክልኤቱ ምዕት አሠርቱ ወስድስቱ

216

፪፻፲ወ፯

ክልኤቱ ምዕት አሠርቱ ወሰብዓቱ

217

፪፻፲ወ፰

ክልኤቱ ምዕት አሠርቱ ወሰመንቱ

218

፪፻፲ወ፱

ክልኤቱ ምዕት አሠርቱ ወተሰዓቱ

219

፪፻፳

ክልኤቱ ምዕት ወእስራ

220

፪፻፴

ክልኤቱ ምሪዕት ወሠላሳ

230

፪፻፵

ክልኤቱ ምዕት ወአርብዓ

240

፪፻፶

ክልኤቱ ምዕት ወሃምሳ

250

፪፻፷

ክልኤቱ ምዕት ወስድሳ

260

፪፻፸

ክልኤቱ ምዕት ወሰብዓ

270

፪፻፹

ክልኤቱ ምዕት ወሰማንያ

280

፪፻፺

ክልኤቱ ምዕት ወተሰዓ

290

፫፻

ሠለስቱ ምዕት

300

፬፻

አርባዕቱ ምዕት

400

፭፻

ሐምስቱ ምዕት

500

፮፻

ስድስቱ ምዕት

600

፯፻

ስብዓቱ ምዕት

700

፰፻

ስመንቱ ምዕት

800

፱፻

ተሰዓቱ ምዕት

900

፲፻

አሠርቱ ምዕት

1000

፳፻

እስራ ምዕት

2000

፴፻

ሠላሳ ምዕት

3000

፵፻

አርብዓ ምዕት

4000

፶፻

ሃምሳ ምዕት

5000

፷፻

ሳድስ ምዕት

6000

፸፻

ሰብዓ ምዕት

7000

፹፻

ሰማንያ ምዕት

8000

፺፻

ተሰዓ ምዕት

9000

፻፻

እልፍ

10,000

፪፻፻

ክልኤቱ እልፍ

20,000

፫፻፻

ሠለስቱ እልፍ

30,000

፬፻፻

አርባዕቱ እልፍ

40,000

፭፻፻

ሐምስቱ እልፍ

50,000

፮፻፻

ስድስቱ እልፍ

60,000

፯፻፻

ሰብዓቱ እልፍ

70,000

፰፻፻

ስመንቱ እልፍ

80,000

፱፻፻

ተሰዓቱ እልፍ

90,000

፲፻፻

አሠርቱ እልፍ

100,000

፳፻፻

እስራ እልፍ

200,000

፴፻፻

ሠላሳ እልፍ

300,000

፵፻፻

አርብዓ እልፍ

400,000

፶፻፻

ሃምሳ እልፍ

500,000

፷፻፻

ስድሳ እልፍ

600,000

፸፻፻

ሰብዓ እልፍ

700,000

፹፻፻

ሰማንያ እልፍ

800,000

፺፻፻

ተሰዓ እልፍ

900,000

፻፻፻

አእላፋት

1,000,000

፲፻፻፻

ትእልፊት

10,000,000

፻፻፻፻

ትልፊታት

100,000,000

፲፻፻፻፻

ምእልፊት

1,000,000,000

 

begena 16

አቡነ ጎርጎርዮስ የሥልጠና ማእከል የበገና ተማሪዎችን አስመረቀ

ሐምሌ 17 ቀን 2005 ዓ.ም.

በታመነ ተክለ ዮሐንስ

begena 16የማኅበረ ቅዱሳን የልማት ተቋማት የአቡነ ጎርጎርዮስ የትምህርትና ሥልጠና ማእከል በዜማ መሣሪያ ያሠለጠናቸውን ተማሪዎች እሑድ ሐምሌ 6 ቀን 2005 ዓ.ም አስመረቀ፡፡ ማእከሉ በመደበኛ የትምህርት መርሐ ግብሩ የአስኳላ ትምህርትን የሚሰጥ ሲሆን፤ በማታ እና በእሑድ ቅዳሜ የሥልጠና መርሐ ግብሩ ደግሞ የአብነትና የዜማ መሣሪያዎችን ሥልጠና ያካሄዳል፡፡ በያዝነው ዓመት በማታው መርሐ ግብር ለተከታታይ ዘጠኝ ወራት ሲሰጥ በነበረው የዜማ መሣሪያዎች ሥልጠና 208 ተማሪዎችን ያስመረቀ ሲሆን፤ ከነዚህ ውስጥ ከ170 በላይ የሆኑት በበገና እንዲሁም ቀሪዎቹ 30 ደግሞ በመሰንቆ የሠለጠኑ ናቸው፡፡

በተቋሙ የትምህርትና ሥልጠና ማእከል ሥራ አስኪያጅ የሆኑት አቶ አብዮት እሸቱ እንደገለጹት “በትምህርት መርሐ ግብሩ የሚሰጡት የአብነት ትምህርቶች (ግዕዝና የቅዳሴ ተሰጥኦ) እንዲሁም የዜማ መሣሪያዎች (በገና፣ መሰንቆ፣ ዋሽንትና ከበሮ) ሥልጠና፤ በዋነኝነት ዓላማ አድርገው የያዙት የሠልጣኞቹን የመንፈሳዊ ሕይወት ተመስጦ ለማሳደግ ሲሆን፤ በተያያዥነትም ወደቀጣዩ ትውልድ የሚደረገውን  የመንፈሳዊ ቅርስ የቅብብል መንገድ ለማጠናከር ነው” ብለዋል፡፡ ሠልጣኞቹ ከምረቃ በኋላ በ2003 ዓ.ም በተመሠረተው የበገና ቤተሰብ ማኅበር በመታቀፍ ጥምቀትን በመሰሉ ታላላቅ መንፈሳዊና የሕዝብ ክብረ በዓላት ላይና በሌሎች ወሳኝ መድረኮች ላይ የበገና አገልግሎትን ይሰጣሉ፡፡ ይሁን እንጂ ካለው የአቅም እጥረት እና የጥያቄ ብዛት አንጻር ተመጣጣኝ የሆነ አገልግሎት ለምእመናኑም ሆነ ለቤተ ክርስቲያን ማበርከት እንዳልተቻለ አሳውቀዋል፡፡

ሥራ አስኪያጁ “የትምህርትና የሥልጠና ዘርፉን በመምህራን ከማጎልበት አንጻር የመምህራን የትምህርት ማስረጃ የተሟላ ካለመሆን የተነሣ የበገና መምህራን እጥረት የሚታይ ሲሆን፤ እንደመፍትሄ እየተወሰደ ያለ እርምጃ ቢኖር ከምሩቃን መካከል የላቀ ብቃት ያሳዩትን በመምረጥና ልዩ ሥልጠና በመስጠት ተተኪ መምህራንን የማፍራት ሥራ ነው” ብለዋል፡፡ ነገር ግን በሌሎች የዜማ ትምህርት ዘርፎች መሰል ችግሮች እንደማይታዩ ገልጸው፤ ይልቁንም ከቅዱስ ያሬድ የዜማ ትምህርት ቤት በሚወጡ መምህራን በመታገዝ ደረጃውን የጠበቀ ትምህርት እንደሚሰጥ አሳውቀዋል፡፡ ማእከሉ ከያዘው የተደራሽነት  ዓላማ አንጻር ሥልጠናውን ለማንኛውም አካል በግልጽ የሚሰጥ ሲሆን፤ እስካሁን ባለው መረጃ መሠረት አሥር ያህል የውጭ ዜጎች በበገና ላይ ያተኮረ ሥልጠና ወስደዋል፡፡

የሥልጠና ማእከሉ በቀጣይ የተደራጀ መዋቅር በመቅረጽ ከሕገ ቤተ ክርስቲያን ሥርዓትና አስተምህሮ አንጻር የተፈቀዱትን የዜማ መሣሪያዎች ሥልጠና፤ የአብነት ትምህርትን በተጠናከረ መልኩ ለመቀጠልና ከተቋሙ የሚመረቁ ተማሪዎች ሕጋዊ የሆነ እውቅና እንዲያገኙ እንዲሁም ማእከሉን ወደ TVT ደረጃ ለማሳደግ ከትምህርት ሚኒስቴር እውቅናን ለመጠየቅ ተቋሙ በዝግጅት ላይ እንደሚገኝ ዋና ሥራ አስኪያጁ ገልጸዋል፡፡

በመጨረሻም ሓላፊው  ባስተላለፉት መልእክት  ሁሉም ኢትዮጵያዊ ሃይማኖትና ብሔር ሳይለይ የሀገር ቅርስ የሆነውን የበገና ትምህርት ቢማር በመጪው ትውልድ ከሚመጣ ወቀሳ መዳን እንደሚቻል ገልጸዋል፡፡

medaliya 1

ከፍተኛ ውጤት ለማስመዝገቤ ምስጢሩ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ መኖሬ ነው

ሐምሌ 5 ቀን 2005 ዓ.ም.

በእንዳለ ደምስስ

ሰሞኑን ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎች በመመረቅ ላይ ይገኛሉ፡፡ ከተመራቂ ተማሪዎች መካከል ከፍተኛ ውጤት በማስመዝገብ ሁለት የወርቅ ሜዳልያዎች የተሸለመችውንmedaliya 1 አንዲት እኅት ለዛሬ እንግዳችን አድርገናታል፡፡ አንዱን የወርቅ ሜዳልያዋንም “በግቢ ጉባኤ ውስጥ በመሳተፍ በመንፈሳዊ ሕይወቴ እንድበረታና ዓላማዬን እንዳሳካ እገዛ አድርጎልኛል” ለምትለው ማኅበረ ቅዱሳን በሥጦታ አበርክታለች፡፡ የዩኒቨርስቲ ቆይታዋን፤ በግቢ ጉባኤ ውስጥ ስለነበራት ተሳትፎ እና በሌሎችም ጉዳዮች ላይ አነጋግረናታል፡፡ መልካም ቆይታ፡፡

ጥያቄ፡- ራስሽን ብታስተዋውቂን?

ፋንታነሽ ፡- ፋንታነሽ ንብረት እባላለሁ፡፡ የመጣሁት ከሚዛን ቴፒ ዩኒቨርስቲ ሚዛን ግቢ ጉባኤ ነው፡፡ የተመረቅሁት አዲስ የትምህርት ዘርፍ በሆነው በኮፕሬቲቭ አካውንቲንግ /Cooprative Accounting/ በመጀመሪያ ዲግሪ ነው፡፡

ጥያቄ፡-  ከቤተሰብ ርቀሽ ወደ ዩኒቨርስቲ መግባቱ አልከበደሽም?

 
ፋንታነሽ፡-  ወደ ዩኒቨርስቲው ስገባ ከለመድኩትና ካደግሁበት አካባቢ የተለየ ስለነበር ከብዶኛል፡፡ የገጠሙኝ ችግሮችም ነበሩ፡፡ ሴት መሆኔ፤ ለዩኒቨርስቲው አዲስ ከመሆን ጋር ተዳምሮ ብቸኝነት፤ እንዲሁም የትምህርት ቁሳቁስ ያለመሟላት ችግሮች ነበሩ፡፡ ቀስ በቀስ ለመድኩት፡፡ በእግዚአብሔር ኃይል ችግሮቹን ሁሉ መቋቋም ቻልኩ፡፡

 
ጥያቄ፡- በግቢ ጉባኤ ላይ የነበረሽ ተሳትፎ ምን ይመስል ነበር?

ፋንታነሽ፡- ወደ ዩኒቨርስቲው ስገባ በግቢ ጉባኤ ውስጥ ይሳተፉ የነበሩ የማውቃቸውን ልጆችን አገኘሁ፡፡ በግቢ ጉባኤያት  አማካይነት ከእሑድ እስከ ሰኞ የሚካሔዱትን መርሐ ግብሮች መረጃ ወሰድኩኝ፡፡ ሰዓቴን አብቃቅቼ በዚሁ መሠረት መከታተል ጀመርኩኝ፡፡ ከቤተሰቦቼ ጋር እያለሁ በሰንበት ትምህርት ቤት ውስጥ እሳተፍ ስለነበር ብዙም አልተቸገርኩም፡፡ ከሁለት ወራት በኋላ በአስተባባሪነትና በመዝሙር ክፍል ውስጥ በአባልነት ማገልገል ጀመርኩ፡፡ ዩኒቨርስቲ ከገባሁ በኋላ የቤተሰብ ተጽእኖ ውጪ ስለሆንኩ ራሴን በአግባቡ የመምራት ሓላፊነት ስላለብኝ ከፍተኛ ጥንቃቄ አደርግ ነበር፡፡በግቢ ጉባኤ አገልግሎትም ጥሩ ተሳታፊ ነበርኩ ማለት እችላለሁ፡፡

ጥያቄ፡- የትምህርት አቀባበልሽ እንዴት ነበር?

 
ፋንታነሽ፡-  ብዙ ማንበብ አልወድም፡፡ ትልቁ አቅሜ የነበረው በክፍል ውስጥ የነበረኝ ትምህርት የመቀበል ችሎታ ነው፡፡ በምንም ምክንያት የትምህርት ክፍለ ጊዜዬን አልቀጣም፡፡ በአግባቡም እከታተላለሁ፡፡ ከትምህርት ውጪ የማሳልፈው ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ነው፡፡ ማታ ማታ በጣም ለአጭር ሰዓት የቤት ሥራዎቼን መሥራት፤ በክፍል ውስጥ ስማር ግር ያለኝ ነገር ካለ በድጋሚ መከለስ ላይ አተኩራለሁ፡፡ እንደ ሌላው ተማሪ ለረጅም ሰዓት መሸምደድ አልወድም፡፡

የመጀመሪያ ዓመት ላይ ግን ትንሽ ያነበብኩ ይመስለኛል፡፡ ግቢውን ለመላመድ፤ የአስተማሪዎቹን የትምህርት አሰጣጥና የፈተና አወጣጥ ግንዛቤ ስላልነበረኝ ይህንን ለመቋቋም በመጠኑም ቢሆን አነበብኩ፡፡ ቀሪዎቹን ዓመታት ግን ለንባብ ብዙም አልተጨነቅሁም፡፡ ተማሪ ከተማሪ በትምህርት አቀባበል ረገድ እንለያያለን፡፡ አንዳንዱ ለረጅም ሰዓት የማንበብ ልምድ ይኖረዋል፡፡ እኔ ግን ከእግዚአብሔር የተሰጠኝ ስጦታ ነው፡፡ ክፍል ውስጥ በአስተማሪዎቼ የሚሰጠውን ገለጻ በደንብ የመያዝ ብቃቱ አለኝ፡፡ ሙሉ ለሙሉ እንዳልረሳው መጠነኛ ክለሳ ብቻ ነው የማደርገው፡፡

ጥያቄ፡- ከተማሪዎች ጋር ለመላመድ አልተቸገርሽም?

ፋንታነሽ፡- የክፍለ ሀገር ልጅ ነኝ፡፡ የመጣሁት ከዳንግላ ነው፡፡ ዶርም/ማደሪያ/ የተመደብኩት ከአዲስ አበባ ልጆች ጋር ነበር፡፡ ቀስ በቀስ ለመቅረብ ጥረት አድረጌ ነበር፡፡ ዓለማዊ ፕሮግራሞች በግቢው ውስጥም ሆነ ውጪ ሲዘጋጁ አብሬያቸው እንድሔድ ይገፋፉኛል፡፡ “ሕይወት ማለት እኮ ይህ ነው” ይሉኛል፡፡ እኔ ግን በትምህርቴም ሆነ በመንፈሳዊ ሕይወቴ ስኬታማ መሆን ዋነኛው ዓላማዬ ስለነበር አሳባቸውን አልተቀበልኳቸውም፡፡ የራሴን አካሔድ በመምረጥ በእነሱ ተጽእኖ ሥር ላለመውደቅ ጥረት አደረግሁ፡፡ ቅርበቴ ሁሉ ከመንፈሳዊ እኅቶችና ወንድሞች ጋር እንዲሆን ወሰንኩ፡፡ የወሰድኩት አቋም ትክክል እንደነበር ዛሬ ላይ ሆኜ ሳስበው ያስደስተኛል፡፡ ትክክል ነበርኩ፡፡

ጥያቄ፡- እስቲ ስለ ውጤትሽ አጫውቺን?

ፋንታነሽ፡- በመጀመሪያ ዓመት ያመጣሁት ውጤት 3.98 ነበር፡፡ አንድ “B” ብቻ ነው ጣልቃ የገባው እንጂ ሁሉንም “A” ነው ያመጣሁት፡፡ በተከታታይ ዓመታት አራት ነጥብ ነው ያስመዘገብኩት፡፡ ነገር ግን በመጨረሻ ዓመት ላይ ፈተና እየወሰድን እናቴ በመታመሟ ምክንያት ከቤተሰብ እንድመጣ መልእክት ስለደረሰኝ ለዩኒቨርስቲው አስፈቅጄ ሄድኩኝ፡፡ ስመለስ ምንም ሳላጠና ተፈትኜ “B” አመጣሁ፡፡ በዚህም መሠረት ስመረቅ አጠቃላይ ውጤቴ /GPA/ 3.96 ሆነ፡፡

ጥያቄ፡- በአንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት የደረጃ ተማሪ ነበርሽ?

ፋንታነሽ፡- በጭራሽ!! በአንደኛም ሆነ በሁለተኛ ደረጃ ትምህርቴ የደረጃ ተማሪ አልነበርኩም፡፡ በመካከለኛ ደረጃ ላይ እገኝ ነበር፡፡ ዩኒቨርስቲ ስገባ ውስጤን በደንብ ያሳመንኩት ይመስለኛል፡፡ ዓላማዬ ስኬታማ እሆን ዘንድ ነበር ተሳካልኝ፡፡

ጥያቄ፡- በዩኒቨርስቲው ቆይታሽ ከቤተሰብ ቁጥጥር ውጪ መሆንሽ ያሳደረብሽ ተጽእኖ አልነበረም?

ፋንታነሽ፡- ከቤተሰብ ጋር ስንኖር እያንዳንዱን እንቅስቃሴያችን፤ የት ገባሽ፤ የት ወጣሽ ስለምንባል ቁጥጥሩ ይበዛል፡፡ ቁጥጥራቸው ለመልካም እንደሆነና ጥሩ ደረጃ ላይ እንድንደርስ ከማሰብ የሚመነጭ ነው፡፡ ዩኒቨርስቲ እንደምገባ ካወቅሁበት ቀን ጀምሮ ራሴን ሳዘጋጅ ነበር፡፡ ከገባሁም በኋላ በዙሪያዬ ያሉትን ፈተናዎች ለመቋቋም ጥረት አድርጌያለሁ፡፡ የቤተሰቦቼ ቁጥጥር ጠቅሞኛል እንጂ አልጎዳኝም፡፡ ተጽእኖም አልፈጠረብኝም፡፡

ጥያቄ፡- በቤተ ክርስቲያን አገልግሎት ውስጥ በመኖርሽ ተጠቅሜያለሁ ትያለሽ?

ፋንታነሽ፡- ቤተ ክርስቲያን ለኔ መሠረቴ ናት፡፡ እምባዬን ጠርጋልኛለች፡፡ በዩኒቨርስቲው ውስጥ የማማክረው፤ የሚደግፈኝ በሌለበት ሲጨንቀኝ፤ ዙሪያው ገደል ሲሆንብኝ ቤተ ክርስቲያን ሄጄ አለቅሳለሁ፡፡ ለእመቤቴ ጭንቀቴን ሁሉ እነግራታለሁ፡፡ መንገዴንም ቀና ታደርግልኛለች፡፡ እረጋጋለሁ፡፡ በዚህ ሁኔታ እግዚአብሔር ባይደግፈኝ ኖሮ እዚህ ደረጃ መድረስ አልችልም ነበር፡፡ በመንፈሳዊም ሆነ በስጋዊ ሕይወቴ ተጠቅሜያለሁ ማለት ይቻላል፡፡

ጥያቄ፡- በግቢ ውስጥ ትልቁ የተማሪዎች ችግር ምንድነው?

ፋንታነሽ፡- ብዙ ችግሮች አሉ፡፡ በተለይም ራስን ካለማዘጋጀት የሚመነጩ ችግሮች በቀላሉ የሚታለፉ አይደሉም፡፡ ተማሪዎች በእምነት ከማይመስላቸው ሰው ጋር ይገጥማሉ፡፡ በተለይም እህቶች ከወንዶች ጋር በሚኖራቸው ቅርበት የማንኛውም እምነት ተከታይ ይሁን እንዳልባረር ያስጠናኛል፤ ይደግፈኛል፤ ያለብኝን የፋይናንስ ችግር ያቃልልልኛል በማለት ይቀራረባሉ፡፡ ወዳልተፈለገ አቅጣጫም ያመራሉ፡፡ ሂደቱ ያስፈራል፡፡ አደርግልሻለሁ – አድርጊልኝ ወደመባባል ይደርሳሉ፡፡

ሌላው በዩኒቨርስቲ ውስጥ ጎልቶ የሚታየው ሃሜት ነው፡፡ በግቢ ጉባኤያት ውስጥ ጭምር የሚከሰት ነው፡፡ አንመካከርም፡፡ በነበርኩበት ግቢ ጉባኤ ውስጥ ትልቅ ክፍተት ነው ከምላቸው ነገሮች አንዱ ይህ ጉዳይ ነው፡፡ አንዱ አንዱን መገሰጽ ያለመቻል ችግር፡፡

ጥያቄ፡- በግቢ ጉባኤ ውስጥ የሚሰጠው ትምህርት ምን ያህል ረድቶሻል?

ፋንታነሽ፡- በግቢ ጉባኤ ውስጥ የሚሰጠው ትምህርት ጥሩ ነው፡፡ ሁሉንም ኮርሶች መጨረስ ባንቸልም ስለ እምነታችን ጥሩ ግንዛቤ የሚያስጨብጥ ነው፡፡ የማላውቀውን እንዳውቅ አድርጎኛል፡፡ በተለይም መንፈሳዊ ሕይወቴ ላይ ከፍተኛ ለውጥ እንዳመጣ ረድቶኛል፡፡ በራስ ጥረት ደግሞ ማበልጸግ፤ ማጠንከር ያስፈልጋል፡፡

ጥያቄ፡- ከወንድሞችና እህቶች ጋር የነበራችሁ ቅርበትና መደጋገፍ እንዴት ይገለጻል?

ፋንታነሽ፡- የመደጋገፍ፤ የመተባበር እንቅስቃሴዎች አሉ፡፡ አንዳችን ከተኛን ሌሎቻችን የመቀስቀስ፤ የመደጋገፍ፤ አብሮ ቤተ ክርስቲያን የመሄድ ልምዱ የዳበረ ነው፡፡
ጥያቄ፡- ከንስሀ አባቶቻችሁ ጋር ያላችሁ ቅርበት ብትገልጪልን?

ፋንታነሽ፡- ዩኒቨርስቲው በቅርቡ ከመከፈቱ አንጻር ከንስሀ አባቶቻችን ጋር የመገናኘትና የመመካከር ጥረቶች እየተደረጉ ነው፡፡ ከዚያ በፊት ግን አብረውን የነበሩ ብዙ ወንድሞችንና እህቶችን አጥተናል፡፡

ጥያቄ፡- ከፍተኛ ውጤት በማምጣትሽ ምንድነው የተሸለምሽው?

medaliyaፋንታነሽ፡- ሁለት የወርቅ ሜዳልያዎችን ነው የተሸለምኩት፡፡ አንዱ ከዩኒቨርስቲው አጠቃላይ ተመራቂዎች መካከል ከፍተኛ ነጥብ በማምጣቴ የተሸለምኩት ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ከተመራቂ ሴት ተማሪዎች ከፍተኛ ነጥብ በማምጣቴ ነው፡፡

ጥያቄ፡- ከፍተኛ ውጤት ለማስመዝገብ የበቃሽበት ዋነኛ ምሥጢር ምንድነው?

ፋንታነሽ፡- የኔ ከፍተኛ ውጤት ማስመዝገብ ትልቁ ምስጢር በቤተ ክርስቲያን ውስጥ መኖሬ ነው፡፡ ይህ ደግሞ ለሌሎች ምሳሌ መሆን የሚችል ነው፡፡ በዩኒቨርስቲው የሚሰጠውን ትምህርት ከመንፈሳዊ ትምህርት ጋር አጣጥሞ መጓዝ እንደሚቻል የኔ ውጤት ምስክር ነው፡፡ ሌሎችንም የሚያስተምር ነው፡፡

ጥያቄ፡- ሜዳልያሽን ለማኅበረ ቅዱሳን ለመስጠት እንዴት ወሰንሽ?

ፋንታነሽ፡- ማኅበሩ የሚያከናውናቸው ተግባራት ለቤተ ክርስቲያን የሚጠቅሙ በመሆኑ፤ በተለይም በግቢ ጉባኤያት ተማሪዎች እምነታቸውን እንዲያውቁ የሚያደርጋቸው ጥረቶች በጣም ያስደስተኛል፡፡ እኔም የዚህ ጥረት ውጤት በመሆኔ፤ ሌሎችም የኔን አርአያ እንዲከተሉ ለማድረግ ነው፡፡

ጥያቄ፡- ወደፊት ካንቺ ምን እንጠብቅ?

ፋንታነሽ፡- እድሉ ቢያጋጥመኝ አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በየአመቱ የሚሰጠውን የነጻ ትምህርት እድል / /Scholarship/  ተጠቃሚ መሆን እፈልጋለሁ፡፡ በጣም እያሰብኩበት ነው፡፡ በተጨማሪም ቤተ ክርስቲያንንና አገሬን ማገልገል እፈልጋለሁ፡፡ በቤተ ክርስቲያን አገልግሎት ውስጥ በመሳተፍ አቅሜ የሚፈቅደውን አስተዋጽኦ አደርጋለሁ፡፡ በተለይም ማኅበረ ቅዱሳን የሚያከናውናቸውን ሥራዎች ማገዝ እንዳለብኝ አምናለሁ፡፡

ጥያቄ፡- ለተማሪዎች የምታስተላልፊው መልእክት ካለሽ?

ዩኒቨርስቲ ስንገባ ማንም አያየኝም የሚል ድምዳሜ ላይ ስለምንደርስ ራሳችንን ወደፈለግነው አቅጣጫ የመምራት ነገር ይታያል፡፡ ከጓደኛ ምርጫ ጀምሮ ችግሮች ይታዩብናል፡፡ የመጣንበትን ዓላማ በመዘንጋት ደካማ ውጤት በማስመዝገብ እስከ መባረር እንደርሳለን፡፡ ከማይመስሉን ጋር በመግጠም ዳግም ልንንሳ በማንችልበት ሁኔታ አልባሌ ቦታዎች ላይ እንወድቃለን፡፡

በመጀመሪያ ደረጃ የወደፊት ህይወታችንን ለማሳካት ብለን ከቤተሰቦቻችን መለየታችንን ማሰብ ይገባናል፡፡ ዓላማችን መማር ነው፡፡ ጠንክረን በመማር የወደፊት ህይወታችንን አቅጣጫ ማስያዝ ይጠበቅብናል፡፡ የወደፊት ህይወታችን የተመሰረተው ዛሬ በምናስመዘግበው ውጤት ነው፡፡ የመጨረሻ ግባችን ምን መሆን እንዳለበት ከመጀመሪያው ውስጣችንን አሳምነን መነሳት ያስፈልጋል፡፡ ነፃነት የሚባለውን ነገር ከፈለግን ከተመረቅን በኋላ የራሳችንን ሕይወት የምንመራበት አንዱ መንገድ ስለሆነ ያኔ እንደርስበታለን፡፡ ነፃነትን እንደፈለጉ ከመሆን ጋር ማዛመድም የለብንም፡፡ ዓላማ ሊኖረን ግድ ነው፡፡

እግዚአብሔር ይስጥልኝ፡፡

እኔም እግዚአብሔር ይስጥልኝ!!

     
 
 

ብዙ ከተሰጠው ከእርሱ ብዙ ይፈለግበታል

ሐምሌ 4 ቀን 2005 ዓ.ም.

የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ቤተ ክርስቲያናችን ካሏት አህጉረ ስብከት ሁሉ ለየት የሚልበት ባሕርያት አሉት፡፡ ሀገረ ስብከቱ የሀገሪቱ ዋና ከተማ እንደመሆኑ በተለያዩ ምክንያቶች ከሁሉም አህጉረ ስብከት የሚመጡ ክርስቲያኖች አገልግሎት የሚያገኙባቸው ገዳማትና አድባራት ያሉበት ሀገረ ስብከት ነው፡፡ በተለያዩ ቋንቋዎች የሚናገሩ የተለያዩ ባህሎች ያሏቸው የቤተ ክርስቲያን ቤተሰቦች ተገናኝተው በአንድነት መንፈስ አገልግሎት የሚያገኙበትና የሚቀበሉበት ሀገረ ስብከትም ነው፡፡

ሀገረ ስብከቱ በርካታ የቤተ ክርስቲያናችን መምህራን ሊቃውንት የሚገኙበትም ሀገረ ስብከት ነው፡፡ በመንፈሳዊው ትምህርት ብቻ ሳይሆን በዓለሙ የሚሰጠውን ማኅበራዊና የተፈጥሮ ሳይንስ፣ የሙያና የቀለም ትምህርቶች የተማሩ አንቱ የተባሉ የቤተ ክርስቲያኒቱ ልጆችም የሚገኙበት ሀገረ ስብከት ነው፡፡ ከሁሉም በላይ ደግሞ ቤተ ክርስቲያንን በታላቅ ፍቅር የሚጠብቃት፣ አገልግሎቷን ዕለት ዕለት የሚሻ ቸርና የዋህ ሕዝበ ክርስቲያን ያለበት ነው፡፡ በዚህም ምክንያት ቤተ ክርስቲያን የምትተዳደርበትን ብዙ የገንዘብ የቁሳቁስና የሰው ኃይል ሀብት ይዞ የሚገኝ ነው፡፡ ከዚህም የተነሣ አርአያነት ያለው አግልግሎትን ሊሰጥም እንደሚችል የሚታሰብ ነው፡፡

እነዚህ ከላይ የተጠቀሱት ሀገረ ስብከቱን ልዩ የሚያደርጉ ባሕርያቱ፤ ሀገረ ስብከቱ ያሉትን ብዙ ሀብቶች የሚያሳይ ነው፡፡ ብዙ ካለው ደግሞ ብዙ ይፈለግበታል የሚለው መጽሐፋዊ ቃል ከሀገረ ስብከቱ የምንሻውን ነገር በተሰጠው ልክ እንድንጠብቅ ያስገድዳል፡፡ ከሁሉም በላይ ደግሞ በነገር ሁሉ ለሌሎች አህጉረ ስብከት የሚኖረውን አርአያነት፡፡

ሀገረ ስብከቱ ብዙ ገንዘብ የሚያንቀሳቅስ እንደመሆኑ ለቤተ ክርስቲያኒቱ ሌሎች አህጉረ ስብከት ምሳሌ የሚሆን የገንዘብ አስተዳደርና አጠቃቀም ሥርዓት ሊኖረው ይገባል፡፡ ብዙ የገንዘብ አስተዳደር ሊቃውንት የሆኑ በርካታ የቤተ ክርስቲያን ልጆች ባለሙያዎች ያሉበት ሀገረ ስብከት በመሆኑ ቀጥሮ በማሠራትም ይሁን የነጻ አገልግሎት ሥርዓት በመዘርጋት አሠራሩን ዘመናዊ፣ ግልጽነት ያለው፣ ተጠያቂነት ያለበት፣ ለሙስና በር የማይከፍት ማድረግ ይቻለዋል፡፡ በአጠቃቀም ረገድም በግልጽነት በተሠራ ዕቅድና የዕቅድ አፈጻጸም ሥርዓት፣ አጠቃላይ አገልግሎቱን ባገናዘበ ሁኔታ፣ አሳማኝ በሆነ መንገድ ሊተገበር ይገባዋል፡፡ የንብረት አስተዳደሩም በተመሳሳይ መቃኘት ይገባዋል፡፡

ሀገረ ስብከቱ ያሉት ቅርሶች አያያዝና ጥበቃ ጉዳይም እንዲሁ መሻሻል ያለበትና በተሻለ አያያዙም ለሌሎች በቅርስ ሀብታቸው ለበለጸጉ አህጉረ ስብከት ምሳሌ ሊሆን ያስፈልጋል፡፡ ያለውን ለአገልግሎት የሚያስፈልግ የሰው ኃይልም ወጥ በሆነ ሥርዓት መምራት አለበት፡፡ አድባራትና ገዳማት ከልክ በታች ወይም ከልክ በላይ መያዝ አለመያዛቸውን፣ ለአገልግሎቱ የሚያስፈልገውን ሙያ ይዘው መገኘት አለመገኘታቸውን፣ ተገቢ እና ወጥነት ባለው የቅጥርና የዝውውር ሥርዓት እየተመራ መሆኑን፣ ከዚያ ጋር ተያይዘው የሚመጡ ሙስናና የአድልዎ አሠራሮች መኖር አለመኖራቸውን መመርመርና ማረጋገጥ ሀገረስብከቱ ወደፊት በአሠራር የለውጥ ሂደቱ ውስጥ ሊመረምራቸው የሚገቡ ነጥቦች ናቸው፡፡ በሀሜት ደረጃ የሚነሡትን የጎጠኝነት፣ የጎሰኝነት እና የቤተሰባዊ አሠራሮች መኖር አለመኖራቸውን መመርመር እንዳይከሠቱም የሚያደርግ ግልጽነት ያለው አሠራር ተግባራዊ ማድረግ ይገባል፡፡

ሀገረ ስብከቱ አርአያ ሊሆን የሚገባው በውስጥ አስተዳደራዊ ሥርዓቱ ብቻ አይደለም በስብከተ ወንጌልና በሌሎችም መንፈሳዊ አገልግሎቶችም ጭምር መሆን አለበት፡፡ በርካታ ሰባክያነ ወንጌልን ማሠልጠን፣ ማፍራት ጊዜው የሚጠይቀውን የትምህርትና ሥልጠና ዘዴዎች ተግባራዊ ለማድረግ መንቀሳቀስ አለበት፡፡ በቂና ብቁ አገልጋይ ካህናትን ማፍራት አለበት፤ ወይም ያሉትን በዚያ ደረጃ ማድረስ ይገባዋል፡፡ በዚህም ላይ ተመሥርቶ ለሃይማኖት ቤተሰቦች ለእንግዶችና መጻተኞች ተፈላጊውን የምስጢራት አገልግሎት ሊሰጥ፣ አርኪ የስብከተ ወንጌል ዐውድማ ሊሆን ይገባል፡፡ ሌሎች አህጉረ ስብከቶችንም ተንቀሳቅሰው የሚያስተምሩ የሚመክሩ ሊቃውንትን ማፍራት አለበት፡፡ ዘመናዊ የሆኑ የመገናኛ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም ስብከተ ወንጌልን ማስፋፋት ይጠበቅበታል፡፡ በቂ የሚዲያ አውታሮች ያስፈልጉታል፡፡ በርካታ የብቃት ማእከሎችን ሊገነባ ይፈለግበታል፡፡

ከላይ ከተጠቀሱ መንፈሳዊ አገልግሎቶች በተጓዳኝ የልማትና ማኅበራዊ አገልግሎቶችን በማስፋፋት ለሕዝበ ክርስቲያኑም ብቻ ሳይሆን ለሀገሪቱ ዘርፈ ብዙ አስተዋጽኦ ሲያደርግ መታየት አለበት፡፡ ቢያንስ ትምህርት ቤቶችንና የሕክምና ማእከላትን ከዚህ በፊት የነበሩ መልካም ጅምሮችን መነሻ አድርጎ በዓይነት፣ በቁጥርና በጥራት ማሳደግና ማስፋፋት ከዚህ ሀገረ ስብከት በእጅጉ ይጠበቃል፡፡  

ይህ ሁሉ እንዲሆን ግን ሀገረ ስብከቱ የሚሰጣቸውን አገልግሎቶችና የአሠራር ሥርዓቱን በመላና ግምት ሳይሆን በጥናት አስደግፎ በምክክርና አሳማኝ በሆኑ አካሔዶች እንዲመራ ይጠበቅበታል፡፡ ማኅበረ ካህናቱ እርስ በእርስ የሚኖራቸው ግንኙነት ከምእመናን ጋር የሚኖራቸው ትስስር በየጊዜው ሊያድግ ሊሻሻል ይገባል፡፡ ምእመናን በሰበካ ጉባኤያት ያላቸው ተሳትፎ እንዲያድግና ቤተክርስቲያናቸውን በቅርበት የሚያገለግሉበት በቤተክርስቲያናቸው አሠራር ውስጥ አስተያየት እንዲሰጡ እንዲወስኑም ሆነው ሊታቀፉ ይገባል፡፡ በሀገረ ስብከቱ የሚገኙ ገዳማትና አድባራት ከሚታሙበት የሙስናና አድሏዊ አሠራር መጽዳት አለባቸው፡፡ አገልጋይ ካህናቱ በትምህርተ ወንጌልና በተለያዩ ዘርፈ ብዙ ሙያዎች ሊታነጹ ይገባል፡፡ ሕግ የጸናበት ሥርዓት የሚከበርበት ሀገረስብከት መሆን አለበት፡፡

ሀገረ ስብከቱ የማሻሻያ እርምጃ ለመውሰድ አሁን የጀመራቸው ጥረቶች የሚበረታቱ ናቸው፡፡ ከላይ እንደጠቀስነው በጥናትና በጥንቃቄ ለመፈጸም ጥረት የሚደረግ ከሆነ ውጤት እንደሚኖረው ይታመናል፡፡ ለዚህም የሚመለከታቸው ሁሉ ማለትም የሀገረ ስብከቱ ሠራተኞች የአድባራትና ገዳማት አስተዳዳሪዎች፣ ማኅበረ ካህናቱ፣ የሰንበት ትምህርት ቤት አባላትና ምእመናን፤ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ቤተሰብ የሆኑ ሁሉ አገልግሎት ማግኛ የሆነው የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት በሚፈለገው አርኪ የአገልግሎት ደረጃ ላይ እንዲደርስ የየድርሻቸውን ሊወጡ ይገባል፡፡ የማኅበረ ቅዱሳን አባላትም ሀገረስብከቱ የሚሻውን አስፈላጊ ድጋፍ ሁሉ ለማድረግ ያላቸውን ዝግጁነት ለመግለጽ ይወዳሉ፡፡

 ወስብሐት ለእግዚአብሔር 

 

  • ምንጭ፡- ሐመር መጽሔት 21ኛ ዓመት ቁጥር 2 ሰኔ 2005 ዓ.ም.

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በዝርወት

ሐምሌ 3 ቀን 2005 ዓ.ም

በዲ/ን ዶ/ር መርሻ አለኸኝ

የዚህ ጽሑፍ ዓላማ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በዝርወት /ከኢትዮጵያ ውጭ/ ያደረገችውን ረጅም ሐዋርያዊ ጉዞ በአጭሩ በመዳሰስ፤ ጉዞዋ ዛሬ የደረሰበትን ምዕራፍ መቃኘት ነው፡፡ የዛሬው ከታየ ዘንድ ግን ጽሑፉ በመጠኑም ቢሆን ጥናታዊ መልክ ይኖረው ዘንድ ዛሬ ቤተ ክርስቲያኗ በውጭው ዓለም ለምትሰጠው አገልግሎት እንቅፋት ናቸው ተብለው ሊጠቀሱ ከሚችሉ ችግሮች ዋና ዋና የሚባሉትን በማቅረብ የይሁንታ አሳብ ይሰነዝራል፡፡

ኢትዮጵያ እንደ ሀገር እምነትን በተመለከተ የግንኙነት መስመሯን ወደ ውጭ መዘርጋት የጀመረችው ቅድመ ክርስትና ከ1000 ዓ.ዓ. ገደማ ጀምሮ ነው፡፡ በቃልም በመጣፍም የቆየን የሀገራችን ወፍራም የእምነት ታሪክ እንደሚነግረን ንግሥተ ሳባ በሕገ ልቡና እግዚአብሔርን ሲያመልክ የነበረ ሕዝቧን በመወከል ወደ ኢየሩሳሌም ተጉዛ ከንጉሡ ከሰሎሞን ጋር በመወያየት እግዚአብሔር ለእሱና ለሕዝቡ የገለጠውን ሕገ ኦሪት ይዛ ወደ አገሯ ተመልሳለች፡፡ ሕዝቧንም በዚሁ የኦሪት ሕግና እምነት እንዲመራ አድርጋለች፡፡ እሷ የጀመረችው ግንኙነትም በኋላ የመንፈሳዊ ጥበብ ፍለጋ ጉዞዋ ሌላ ውጤት በሆነው ልጇ ቀዳማዊ ምንልክና እሱ ባመጣቸው ሌዋውያን ካህናት አማካይነት ተጠናክሮ ቀጥሏል፡፡

ከክርስትና በፊት የነበረውን ድዮስጶራዊ እንቅስቃሴና ግንኙነት በዚሁ እንተወውና የክርስቶስ መወለድና ታላቅ የማዳን ሥራ ለዓለም ከታወጀበት ወዲህ ያለውን ታሪክ እንመልከት፡፡ መግቢያ ይሆነን ዘንድ የዝርወት እንቅስቃሴዋን የምናይላት የኢ.ኦ.ተ.ቤ. እንዴት እንደ ተመሠረተች በሌላ አገላለጥ ክርስትና ወደ ሀገራችን እንዴትና መቼ እንደገባ በአጭሩ እንመልከት፡፡ እኛ ኢትዮጵያውያን ከክርስትና ጋር የተዋወቅንበትን ጊዜ አስመልክቶ ከላይ እንደተጠቀሰው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በአበው ያስቆጠረው ሱባኤ ሞልቶ፣ በነቢያት ያስነገረው ትንቢት እውነት ሆኖ በቤተልሔም በተወለደ ጊዜ ይህንን ታላቅ ዜና በጥበብ ተረድተው፣ በኮከብ እየተመሩ ቤተልሔም ደርሰው በመስገድ ለንጉሠ ሰማይ ወምድርነቱ ወርቅ፣ ለክህነቱ ዕጣን፣ አዳምን ለማዳን በመስቀል ላይ ስለሚቀበለው ሕማምና ሞት ከርቤ እጅ መንሻ አቅርበው ወደ ሀገራቸው ከሔዱት ነገሥታት አንዱ ኢትዮጵያዊ ነው የሚል ታሪክ አለ፡፡

በክርስቶስ የባሕርይ አምላክነት አምኖ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስስም ተጠምቆ ክርስትናን በመያዝ ወደ ሀገራችን የገባው የኢትዮጵያ ንግሥት ሕንደኬ በጅሮንድ /የገንዘብ ሹም/ የነበረው ኢትዮጵያዊው ጃንደረባ ነው፡፡ እንደኦሪቱ ሥርዐት ማንኛውም የብሉይ ኪዳንን እምነት የተቀበለ ወንድ የሆነ ሁሉ በዓመት የሚያከብራቸው በዓላት ነበሩ፡፡ እነዚህም በዓላት በዓለ ናዕት /የቂጣ በዓል/፣ በዓለ ሰዊት /የእሸት በዓል/፣ በዓለ መጸለት /የዳስ በዓል/ ይባሉ ነበር፡፡ በዚህም መሠረት በርካታ ኢትዮጵያውያን የእምነታቸው ሥርዐት በሚያዝዘው መሠረት ከበዓለ ፋሲካ ሰባት ሱባኤ በኋላ የሚከበረውን በዓለ ሰዊትን ወደ ኢየሩሳሌም መንፈሳዊ ጉዞ በማድረግ ያከብሩ ነበር፡፡ /ሶፎ. 3፥10/፡፡ ቅዱስ መጽሐፍ መዝግቦት በምናገኘው ታሪክ መሠረት ሐዋርያት በጌታ ልደት የተበሰረችውን ወንጌል ያለፍርሐትና ያለመሰቀቅ ዓለምን ዞረው ያስተምሩ ዘንድ አጽናኝ የሆነውን መንፈስ ቅዱስን የላከላቸው በ34 ዓ.ም በዓለ ሰዊት በተከበረበት ዕለት ነበር፡፡ /ሐዋ. 3፥10/ በዚህም መሠረት ሐዋርያት መንፈስ ቅዱስን ተቀብለው በየሀገሩ ቋንቋ ሲናገሩና እግዚአብሔርን ሲያመሰግኑ በመደነቅ ከሰሙት ምእመናን መካከል ኢትዮጵያውያንም ይገኙበት እንደነበረ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ በዓለ ሐምሳን አስመልክቶ በሰጠው ስብከቱ መስክሯል፡፡ /ድርሳን ዘቅዱስ ዮሐንስ አፈ ወርቅ ዘበዓለ ሃምሳ/፡፡

በዚሁ በዓል ተሳትፎ የቅዱሳት መጻሕፍትን ምሥጢር እየመረመረ ወደ ሀገሩ በመመለስ ላይ የነበረው ኢትዮጵያዊው ጃንደረባ ከወንጌላዊው ፊል ጶስ ጋር ተገናኘ፡፡ ፊልጶስም ያነበው የነበ ረውን የትንቢት መጽሐፍ ለክርስቶስ እንደተነገረ አምልቶ አስፍቶ ተረጎመ ለት፡፡ ጃንደረባውም በትምህርቱ አመነ፡፡ ተጠመቀ፡፡ በዚህ ዓይነት ክርስትናን ይዞ ወደ ኢትዮጵያ ገባ፡፡ እሱም በተራው ይኸንኑ የክርስቶስን የባሕርይ አምላክነት ዜና ለሕዝቡ አሰማ፡፡ /ሐዋ. 8፥26-40/ አውሳብዮስ ዘቂሳርያ የቤተ ክርስቲያን ታሪክ 2ኛ መጽሐፍ ቀ. 1/፡፡ በዚህ ዓይነት እንደ ሕገ ኦሪቱ ሁሉ በቤተ መንግሥቱ በኩል አድርጎ ወደ ኢትዮጵያ የገባው ክርስትና በዐራተ ኛው መ.ክ.ዘ. ተቋማዊ መልክ ይዞ በሀገር ውስጥና በውጭው ዓለም ኢትዮ ጵያዊ ጉዞውን ጀምሯል፡፡

ከላይ ከቀረበው ታሪክ የምንረ ዳው ሀገራችን ኢትዮጵያ አስቀድሞ ከሕገ ኦሪት ኋላም ከሕገ ወንጌል ጋር የተዋወቀችው በዘረጋችው የውጭ ግንኙነት አማካይነት እንደሆነ ነው፡፡

I. የአገልግሎት ጉዞ ከትላንት እስከ ዛሬ
ቤተ ክርስቲያኗ እንደ መንፈሳዊ ተቋም ከተመሠረተችበት ጊዜ ጀምሮ እስከ አሁን ድረስ በዝርወት ያደረገችውን እንቅስቃሴ እንደሚከተለው በወፍ በረር በክፍል በክፍል እናየዋለን፡፡

1. በመካከለኛው ምሥራቅ   
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በውጭው ዓለም ካላት ሐዋርያዊ ጉዞ ታሪክ ሰፋ ያለውንና ቀዳሚውን ምዕራፍ የሚወስደው በመካከለኛው ምሥራቅ የጻፈችውና ያጻፈችው ነው፡፡ ይህም ሊሆን የቻለው ኢትዮጵያ ከአካባቢው ሀገራት ጋራ ካላት መልክአ ምድራዊ መቀራረብ እንዲሁም የባሕልና የእምነት መዛመድ የተነሣ ነው ማለት ይቻላል፡፡ ቤተ ክርስቲያኗ በዚህ አካባቢ ያደረገችው እንቅስቃሴና አስቀምጣ ያለፈችው የታሪክ አሻራ በወግ አልተጠናም፡፡ የሆነው ሆኖ የሚታወቀውን እንቅስቃሴዋን በሀገራቱ በመከፋፈል ለማየት እንሞክር፡፡

1.1 በኢየሩሳሌም
ኢትዮጵያ እምነትን በሚመለከት ከኢየሩሳሌም ጋር ያላት ግንኙነት ከንግሥተ ሳባ ዘመነ መንግሥት ጀምሮ እንደሚሔድ ተመልክተናል፡፡ ከዚያ ጊዜ ጀምሮ ሀገራችን ከእስራኤል ጋር ባላት ቅርርብ መሠረት በተለያዩ ጊዜ ያት ልዩ ልዩ ገዳማትን በማቋቋም ስታገለግልና ስትገለገል ቆይታለች፡፡ በአሁኑ ጊዜ ቤተ ክርስቲያኗ በኢየሩሳሌም የራሷ ሀገረ ስብከት ያላት ሲሆን በሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ የበላይ ጠባቂነት የሚተዳደሩ ሰባት ቅዱሳት መካናት አሏት፡፡

1.2 በግብፅ
ቤተ ክርስቲያኗ ከምሥረታዋ ጀምሮ ከአምስቱ አኃት አብያተ ክርስቲያናት አንዷ ከሆነችው የግብፅ ቤተ ክርስቲያን ጋር የጠበቀ ግንኙነት ነበራት፡፡ ለ1600 ዓመታት ያህል ግብፃውያን ሊቃነ ጳጳሳት ወደ ሀገራችን በመምጣት ቤተ ክርስቲያኗን መርተዋል፡፡ የዚያኑ ያህል የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ምእመናንና አባቶችም ወደ ግብፅ እየሔዱ ሐዋርያዊ አገልግሎት ሰጥተዋል፡፡ ከሐዋርያዊ አገልግሎቷ መካከል ለግብፃውያኑ ስለእምነት ነፍስን አሳልፎ መስጠት /ሰማዕትነት/ ተጠቃሽ ነው፡፡ አባ ሙሴ ጸሊም ወደ ግብፅ በመሔድ ልዩ ልዩ ተጋድሎ ሲፈጽም ቆይቶ መነኮሳትን ለማጥፋትና ገዳማቸውን ለማቃጠል አረማዊ ሠራዊት በመጣ ጊዜ ከግብፃውያኑ ቀድሞ ሰማዕትነት ተቀብሏል፡፡ ይህ አባት ሰማዕትነትን እንዲቀበሉ ያጸናቸው ታላቅ ኢትዮጵያዊ ሐዋርያ እንደሆነ ቅዱሳት መጻሕፍት ምስክርነታቸውን ይሰጣሉ፡፡ የዚህ ሐዋርያ ተግባር ተሰዐቱ ቅዱሳንን ወደ ኢትዮጵያ እንደሳበ በስፋት ተመዝግቦ የሚገኝ ታሪክ ነው፡፡

በ11ኛው መ.ክ.ዘ. በአስቄጥስ በረሃ በሚገኘው ዮሐንስ ሐፂር ገዳም ውስጥ የኢትዮጵያውያን መነኮሳት እንደነበሩ፤ በ1330 በ1330 አቡነ ብንያም 2ኛ የተባሉት የግብፅ ፓትርያርክ የዮሐንስ ሐፂርን ገዳም በጎበኙ ጊዜ ኢትዮጵያውያንና ግብፃውያን መነኮሳት በዝማሬ እንደ ተቀበሏቸው፣ ጻድቁ አቡነ ተክለ ሃይማኖት በገዳመ አስቄጥስ ጉብኝታቸው ወቅት በገዳመ ዮሐንስ ሐፂር ቆይታ ማድረጋቸው፣ የኢትዮጵያዊው ጻድቅ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ሥዕል በ1517 ዓ.ም በአቡነ መቃርዮስ ገዳም ለጎብኝዎች ማረፊያ በተሠራው ቤተ ክርስቲያን ግድግዳ ላይ ተሰቅሎ መገኘቱ፤ እንዲሁም በግብፅ ውስጥ ዴር አል ሱርያን ተብሎ በሚታወቀው በሶርያውያን ገዳም ኢትዮጵያውያን መነኮሳት ይኖሩ እንደ ነበርና አንድ ትልቅ ቤተ መጻሕፍት እንዳቋቋሙ መዛግብት ያስረዳሉ፡፡ በደቡብ ግብፅ በሚገኘው የቁስቋም ገዳም ከ14ኛው እስከ 17ኛው መ.ክ.ዘ. ድረስ ኢትዮጵያውያን የራሳቸው ገዳም ነበራቸው፡፡ በዚህ ዘመን የተጋድሎን ሕይወት ለግብፃውያኑ ካስተማሩት ኢትዮጵያ ውያን አበው መካከል አቡነ አብደል ጣሉት አል ሐበሽና አቡነ አብደል መሢሕ /ገብረ ክርስቶስ/ በመባል የሚታወቁት ሁለት አበው ተጠቃሽ ናቸው፡፡

በአሁኑ ወቅት ከ1985 ዓ.ም ጀምሮ ብዙ ኢትዮጵያውያን ወደ ግብፅ በስደት በመግባታቸው በግብፅ የአባስያ ሰንበት ት/ቤት አቋቁመው አገልግሎት በመስጠት ላይ ይገኛል፡፡

1.3 በሀገረ ናግራን
በዛሬዋ የመን ደቡብ ዓረቢያ ይገኝ የነበረ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ሀገረ ስብከት ሲሆን በዚህ ቦታ ቤተ ክርስቲያን ለ300 ዓመታት አገልግላለች፡፡ በዚህ አካባቢ ጻድቁ ዐፄ ካሌብ በአይሁድና አረማውያን እንግልት የደረሰባቸውን ክርስቲያኖች በማዳን ታላቅ ተጋድሎ ከመሥራታቸውም ባሻገር አብያተ ክርስቲያናትን አሳንፀው ቤተ ክርስቲያኗ የተገፉትን በመጠበቅ የተበተኑትን በመሰብሰብ በኩል ሰፊ አገልግሎት እንድትሰጥ አድርገው ተመልሰዋል፡፡  

1.4 በሶርያ
በዚህ አካባቢ ቤተ ክርስቲያናችን የሰጠችው ሰፊ አገልግሎት በወግ ስላልተጠና ሰፊ ሐተታ ማቅረብ ባይቻልም ዛሬም ድረስ ሙሴ አል ሐበሻ በመባል የሚታወቀው ገዳምና የዐፄ ገብረ መስቀል ልጅ አባ ሙሴ እንደ መሠረተው የሚነገረው ገዳም መገኘቱ ቤተ ክርስቲያናችን በአካባቢው ያላትን ታሪካዊነትና ጥንታዊነት ይመሰክራል፡፡  

1.5 አርመን
ኢትዮጵያዊው ጻድቅ አቡነ ኤዎስ ጣቴዎስ፣ አባ ባኪሞስ፣ አባ መርቆ ሬዎስና አባ ገብረ ኢየሱስ የተባሉ ደቀ መዛሙርታቸውን አስከትለው ግብፅ ወርደው የግብፁን ፓትርያርክ አቡነ ብንያምን አነጋግረው ወደ ኢየሩሳሌም ከሔዱ በኋላ በአርመን በተለይም ዛሬ ቱርኮች በያዟት ሲሲሊያ በተባለች ቦታ ለ14 ዓመታት ሐዋርያዊ አገልግሎት ሰጥተዋል፡፡   

1.6.  በአሁኑ ጊዜ በመካከለኛው ምሥራቅ
ቤተ ክርስቲያናችን ጥንት ቀይ ባሕርን ተሻግራ በመካከለኛው ምሥራቅ የሰጠችውን አገልግሎት በዚህ ዓይነት ካየን ዘንድ በአሁኑ ወቅት በየመን፣ በሰንዓ፣ በዓረብ ኢምሬቶች፣ በሊባኖስ አብያተ ክርስቲያናት መንፈሳዊ አገልግሎት ለመስጠት ተቋቁመዋል፡፡ በዓረብ ኢምሬቶች ውስጥ በሻርጂያ፣ ዱባይ፣ አቡዳቢ እና አል ዓይን ከተሞች አገልግሎት የሚሰጥ ሲሆን ሕንፃ ቤተ ክርስቲያን ለመሥራት እንቅስቃሴው ተጀምሯል፡፡  

 

  • ምንጭ፡- ስምዐ ጽድቅ ጋዜጣ 20ኛ ዓመት ቁጥር 19 ከሰኔ 1-15 ቀን 2005 ዓ.ም.

ሰዋሰወ ግእዝ ክፍል አራት

ሐምሌ 3 ቀን 2005 ዓ.ም.

በመ/ት ኑኀሚን ዋቅጅራ

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን

 

  •  ፊደል ብሂል – ርዕሰ መጻሕፍት -የመጻሕፍት (የጽሑፍ) መጀመሪያ
  • ፊደል ብሂል – ነቅዓ ጥበብ – የጥበብ ምንጭ /የእውቀት መፍለቂያ/
  • ፊደል ብሂል – መጽሔተ አእምሮ – የአእምሮ መስታወት
  • ፊደል ብሂል – ጸያሔ ፍኖት – መንገድ ጠራጊ /በር ከፋች/
  • ፊደል ብሂል – መራሔ እውራን ውእቱ – ፊደል ሰዎችን ካለአዋቂነት /ከድንቁርና እውርነት አውጠቶ ወደ ብርሃን የሚመራ ነው፡፡   

ባለፈው ሳምንት አምዳችን ስለ ግእዝ ፊደላትና ስለ ዝርዋን የግእዝ ፊደላት የአዘራዘር ሥልትና የፊደላት ትርጉም ተመልክተናል፡፡ በዛሬው አምዳችን ደግሞ ስለ አማርኛ ፊደላትና የአማርኛ ዝርዋን ፊደላትን እንመለከታለን፡፡

የአማርኛ ፊደላት የምንላቸው በቁጥር ፯/ሰባት/ ናቸው፡፡ የአማርኛ ፊደላት ከጊዜ በኋላ በዋንኞቹ የግእዝ ፊደላት ላይ የተወሰነ ቅጥያ በማድረግ የተመሠረቱ ፊደላት ናቸው፡፡ የአማርኛ ፊደላት የአዘራዘር ሥልት እንደ መነሻዎቹ የግእዝ ፊደላት ሲሆን በግእዝ በካዕብ በሣልስ በራብዕ በኀምስ፣ በሳድስና በሳብዕ የአዘራዘር ሥልት ይዘረዘራሉ፡፡ የአማርኛ ፊደላት የአማርኛ ፊደል የተባሉበት ዋናው ምክንያት በግእዝ ቋንቋ በሚዘረዘሩ ግሦችና የፊደላት ትርጉም አለመጠቀሳቸውና አብዛኛውን ጊዜ በግእዝ ቋንቋ በሚጻፉ ጽሑፎችና ሥነ ጽሑፍ ላይ አለመጠቀሳቸውም ነው፡፡ ለአማርኛ ፊደላት መነሻ የሆኑትን የግእዝ ፊደላትና የአማርኛ ፊደላትን ከነአዘራዘራቸው በቅደም ተከተል ከዚህ በመቀጠል እንመለከታለን፡፡

ከዚህ የምንረዳው በፊደል ገበታ ላይ የአማርኛ ፊደላት ተብለው ከሚጠሩት ፊደላት መካከል እነዚህ ፯/ሰባት/ ፊደላት ብቻ ሌሎቹ የግእዝ ፊደላት መሆናቸው ነው፡፡

መነሻ የግእዝ ፊደላት

ግእዝ

ካዕብ

ሣልስ

ራብዕ

ኀምስ

ሳድስ

ሳብዕ

       ሰ

 

 

 

 

 

 

        ተ

 

 

 

 

 

 

        ነ

 

 

 

 

 

 

       ከ

 

 

 

 

 

 

        ዘ

 

 

 

 

 

 

        ደ

 

 

 

 

 

 

        ጠ

 

 

 

 

 

 

 

ከዚህ በመቀጠል ደግሞ የአማርኛ ፊደል ዲያሎችን /ዝርዋን የአማርኛ/ ፊደላትን እንመለከታለን፡፡

ዝርዋን የአማርኛ ፊደላት
ዝርዋን ማለት ብትን ሕግንና ቅደም ተከተልን ያልጠበቀ ማለት ነው፡፡ ዝርዋን የአማርኛ ፊደላት የምንላቸው በግእዝና በአማርኛ ፊደላት ላይ በተለየ መልኩ በራብዑ /በአራተኛው/ ፊደል ዝርዝር ላይ በስተመጨረሻ ወይም ከላይ ቅጥያ በማድረግ የተፈጠረ ፊደልና በአንድ ነጠላ ዝርዝር ብቻ የሚገለጽ በአማርኛ ጽሑፍ ላይ ብቻ የሚገኝ የፊደል ዝርዝር ነው፡፡ ዝርዋን የአማርኛ ፊደላት አብዛኛውን ጊዜ የሚያገለግሉት በአንስታይ /በሴት/ ጾታ ማለትም በሩቅ ድርጊት አመልካች በነጠላ የሴት ጾተ የሚገለጸውን ቃል የእራስነትዋን ለመግለጽ የምንጠቀምበትን ቃል ሁለት ተከታታይ ሳድስና ራብዕ ፊደላትን በመዋጥ በአንድ ፊደል በዝርው የአማርኛ ፊደል በመተካት የፊደላትን ቁጥር በመቀነስ ያገለግላል፡፡

ዝርዋን የአማርኛ ፊደላት የሚባሉት
           ሏ፣ ሟ፣ ሿ፣ ሯ፣ ቧ፣ ቷ፣ ዟ፣ ዧ፣……. ናቸው፡፡

ምሳሌ፡- ልብዋ …. ልቧ፣ ቤተሰብዋ…..ቤተሰቧ
           እርስዋ… እርሷ፣ እጅዋ….. እጇ ወዘተ…….

ለዛሬ ያለንን አምድ በዚህ እናበቃለን በቀጣይ ሳምንት የግእዝ አኀዝ ቁጥሮችን የአጻጻፍና የአነባበብ ሥልት እንመለከታለን እስከዚያው ቸር ይግጠመን፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

gebi 01

የአዲስ አበባ ማእከል የግቢ ጉባዔያት ተማሪዎችን አስመረቀ

ሐምሌ 1 ቀን 2005 ዓ.ም.

በእንዳለ ደምስስ

በማኅበረ ቅዱሳን የአዲስ አበባ ማእከል የግቢ ጉባዔያት ማስተባበሪያ ክፍል፤ የቅዱስ ማርቆስ አካባቢ ማስተባበሪያ፤ የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የግቢ ጉባኤያት ተማሪዎችን በቅድስትgebi 01 ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ አዳራሽ ሰኔ 30 ቀን 2005 በድምቀት አስመረቀ፡፡ ተማሪዎቹ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ /ከስድስት ኪሎ፤ ከአምስት ኪሎ ቴክኖሎጂ ፋኩልቲ፤ ከአራት ኪሎ የተፈጥሮ ሳይንስና ከቅዱስ ጳውሎስ/ በተለያዩ የትምህርት ዘርፎች በድኅረ ምረቃና በመጀመሪያ ዲግሪ የተመረቁ ሲሆኑ በግቢ ቆይታቸው መንፈሳዊ ትምህርታቸውን ሲከታተሉ የነበሩ አንድ ሺህ የሚደርሱ ተማሪዎች ናቸው፡፡ 

ብፁዕ አቡነ ፊልጶስ የኢሉባቦርና ጋምቤላ አኅጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ በመርሐ ግብሩ ላይ በመገኘት ባስተላለፉት ቃለ ምእዳንና ቡራኬ “ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሐዋርያትን ካስተማራቸውgebi 02 በኋላ በሚሔዱበት ሁሉ አልተለያቸውም፡፡ እሱን መርህ አድርገው በዓለም ሁሉ ተበትነው ወንጌልን አስተማሩ፡፡ እናንተም የእምነትን መሣሪያ ይዛችኋል፤ በሥራችሁ ሁሉ እግዚአብሔር ይከተላችኋል፡፡ እናንተ ቀናዎች ከሆናችሁ ከሚመጣባችሁ ክፉ ነገር ይጠብቀችኋል፡፡ በቀኝ እጃችሁ እምነታችሁን፤ በግራ እጃችሁ ከዩኒቨርስቲ የቀሰማችሁትን እውቀት ይዛችሁ ተሰማሩ፡፡ ቤተ ክርስቲያንንም አገልግሉ” በማለት የአደራ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

የማኅበረ ቅዱሳን ሰብሳቢ ቀሲስ ዶክተር ሰሙ ምትኩ በበኩላቸው ለተመራቂ ተማሪዎች የእንኳን ደስ ያላችሁ መልእክት ያሰተላለፉ ሲሆን  “መማር ለማወቅ ነው፤ ማወቅ ለመሥራት፤ መሥራት ደግሞ ለውጤት ነው፡፡ በዚህ ሂደት የሰው ልጅ ባሕርይው እንደተጠበቀ ሆኖ ብዙ ለውጦችን ያሳያል፡፡ እነዚህን ለውጦች በአግባቡ ተጠቅሞ ወደ ውጤት ለመድረስ በተለይም በመንፈሳዊው ትምህርት ከቅድስት ቤተ ክርስቲያን የመጽሐፍ ቅዱስን ቃል ከተማሩ ወገኖች ብዙ ይጠበቃል፡፡ በቤተ ክርስቲያናችን በተማሩ ሰዎች ሊሠሩ የሚገባቸው በርካታ ተግባራት አሉ፡፡ እነዚህን ተግባራት ከአጥቢያ ጀምረን እስከ ላይ ድረስ ቀረብ ብለን በማየት፤ እንደየአቅማችንና እንደ ሥራው ሁኔታ ሠርተን ውጤት ልናመጣ ይገባል፡፡ ይህንንም መሠረት በማድረግ በምትሠማሩበት የሥራ ቦታ በግቢ ውስጥ በጥቂቱ የጀመራችሁትን መንፈሳዊ ጉዞ አብዝታችሁ እንድትቀጥሉ መንፈሳዊ ጥሪያችንን እናቀርባለን ” ብለዋል፡፡gebi 03

“ህያዋን ድንጋዮች” በሚል ርዕስ በዲያቆን ብርሃኑ አድማስ የወንጌል ትምህርት የተሰጠ ሲሆን የአዲስ አበባ ማእከል የመዝሙር ክፍል አባላት፤ እንዲሁም ተመራቂ ተማሪዎች ያሬዳዊ ወረብና ዝማሬ አቅርበዋል፡፡ በመጨረሻም በዩኒቨርስቲ ቆይታቸው ከፍተኛ ውጤት ላመጡ ተመራቂዎች በማኅበሩ የተዘጋጀላቸውን የምስክር ወረቀት ተቀብለዋል፡፡

    
     
            

ሰዋሰወ ግእዝ ክፍል ሦስት

ሰኔ 26 ቀን 2005 ዓ.ም.

በመ/ት ኑኀሚን ዋቅጅራ

ባለፈው ሳምንት አምዳችን ከ፳፮ (26)ቱ የግእዝ ፊደላት መካከል የ፲፫(13)ቱን የግእዝ ፊደላት ቅርጽ ከነትርጒማቸው መግለጻችን ይታወቃል፡፡

ዛሬ ደግሞ ተከታዮቹን አሥራ ሦስት (፲፫) ፊደላት እንመልከት

፲፬. ከ ብሂል- ከሃሊ እግዚአብሔር፡፡
      ከማለት – እግዚአብሔር ሁሉን ቻይ ነው፡፡

፲፭. ወብሂል – ወረደ እም ሰማይ እግዚእነ
      ወ ማለት -ጌታችን ከሰማይ ወረደ፡፡

፲፮. ዐ ብሂል – ዐርገ ሰማያተ እግዚእነ፡፡
      ዐ ማለት – ጌታችን ወደሰማይ ወጣ /ዐረገ/፡፡

፲፯. ዘ ብሂል – ዘኲሎ ይእኅዝ እግዚአብሔር፡፡
      ዘ ማለት -እግዚአብሔር ይይዛል /ሁሉን የሚይዝ ነው/፡፡

፲፰. የ ብሂል – የማነ እግዚአብሔር ገብረት ኀይለ፡፡
      የ ማለት – የእግዚአብሔር ቀኝ ኀይልን አደረገች፡፡

፲፱. ደ ብሂል – ደመረ ሥጋነ ምስለ መለኮቱ፡፡
      ደ ማለት – ሥጋችንን ከመለኮት ጋር አንድ አደረገልን፡፡

፳. ገ ብሂል – ገብረ ሰማያተ በጥበቡ፡፡
     ገ ማለት – ሰማያትን በጥበቡ ሠራ፡፡

፳፩. ጠ ብሂል – ጠዐሙ ወታእምሩ ከመ ኄር እግዚአብሔር፡፡
      ጠ ማለት – የእግዚአብሔርን ቸርነት ታውቁ ዘንድ ቅመሱ፡፡

፳፪. ጰ ብሂል – ጰራቅሊጦስ መንፈሰ ጽድቅ፡፡
      ጰ ማለት – ጰራቅሊጦስ የእውነት መንፈስ ነው፡፡

፳፫. ፀ ብሂል – ፀሐይ ጸልመ በጊዜ ስቅለቱ ለእግዚእነ፡፡
      ፀ ማለት – ጌታ በተሰቀለ ጊዜ ፀሐይ ጨለመ፡፡

፳፬. ጸ ብሂል – ጸጋ ወክብር ተውህበ ለነ፡፡
      ጸ ማለት – ጸጋ እና ክብር ለእኛ ተሰጠን፡፡

፳፭. ፈ ብሂል – ፈጠረ ሰማየ ወምድረ፡፡
      ፈ ማለት እግዚአብሔር ሰማይና ምድርን ፈጠረ፡፡

፳፮. ፐ ብሂል – ፓፓኤል ሥሙ ለአምላክ፡፡
      ፐ ማለት – ፓፓኤል የአምላክ ስም ነው፡፡ 

ከዚህ በመቀጠል ዝርዋን የግእዝ ፊደላትን /የግእዝ ፊደል ዲቃሎች/ ተብለው የሚጠሩትን ፈደላትና በፊደል ገበታ ላይ በስተመጨረሻ ተጽፈው የምናገኛቸውን ፊደላት እንመለከታለን፡፡

  • በፊደል ገበታ ላይ በስተመጨረሻ ተጽፈው የምናገኛቸው ከዋናው የፊደል የአጻጻፍ ቅርጽ ወጣ ያሉ ሁለት ዓይነት ፊደላትን እናገኛለን፡፡

  • ፩ ዲቃሎች /ዝርዋን/ የግእዝ ፊደላት ፪ ዲቃሎች /ዝርዋን/ የአማርኛ ፊደላት በመባል ይታወቃሉ፡፡

ከግእዝ ፊደላት ዝርዝር ጋር የሚሄዱትን የግእዝ ዝርዋን /ዲቃሎች/ ፊደላትን እንመለከታን፡፡

  • ዝርው ማለት ብትን /ቅደም ተከተልን ያልጠበቀ/ ማለት ነው፡፡

  • ዝርዋን የግእዝ ፊደላት ዝርዋን የሚል ስም የተሰጣቸው ከዋናዎቹ የግእዝ ፊደላት ላይ የተወሰነ ቅጥያ እየተጨመረ የተመሠረቱ ፊደላት በመሆናቸው ነው፡፡

  • ዝርዋን መባላቸው እንደ ዋንኞቹ የግእዝ ፊደላት ቅደም ተከተላቸውን ጠብቀው በሰባቱ የፊደላት ዝርዝር ባለመዘርዘራቸውና አብዛኛውን ጊዜ በግእዝ ፊደል በተጻፉ ጽሑፎች ላይ ብቻ መገኘታቸው ነው፡፡ እነዚህ ፊደላት የተመሠረቱት በዋንኞቹ የግእዝ ፊደላት ላይ የተወሰነ ቅጥያ በማድረግ ነው፡፡

  • ዋንኞቹ የግእዝ ፊደላት የአዘራዘር ሥልት በግእዝ ጀምረው በሳብዕ ቅደም ተከተላቸውን ጠብቀው ይዘረዘራሉ፡፡

ምሳሌ፡- ግእዝ      ካዕብ      ሣልስ         ራብዕ      ኀምስ    ሳድስ      ሳብዕ
       ሀ           ሁ          ሂ          ሃ          ሄ           ህ       ሆ    
       ለ           ሉ          ሊ         ላ          ሌ          ል       ሎ

 

የዝርዋን የግእዝ ፊደላት የአዘራዘር ሥልት ግን ከእነዚህ ይለያል

መነሻ ፊደላት

ግእዝ

ሳድስ

ሣልስ

ራብዕ

ኀምስ

 

የዛሬ አምዳችንን በዚህ እናጠናቅቃለን ሳምንት በአማርኛ ፊደላትና ዝርዋን የአማርኛ ፊደላትን የአጻጻፍና የአዘራዘር ሥልት ይዘንላችሁ እስከምንገናኝ ቸር ይግጠመን፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር