መጋቢት 18/2004 ዓ.ም.
ጸሎት ጸለየ፡- ለመነ፣ ጠየቀ አማለደ፣ ማለደ ካለው የግዕዝ ቃል የወጣ ቃል ነው፡፡ ጸሎት ማለት ጠቅለል አድርገን ስንመለከተው ከእግዚአብሔር ጋር መነጋገር እግዚአብሔርን ማመስገን መለመን፣ መጠየቅ፣ መማለድ፣ መማፀን ነው፡፡ “ጸሎት ብሂል ተናግሮ ምስለ እግዚአብሔር፡፡” አባታችን አዳምም ከመላእክት ተምሮ በየሰዓቱ ይጸልይ ያመሰግን ነበር፡፡ ዲያብሎስ በእባብ አድሮ ወደ አዳም በመጣ ጊዜ ጸሎት እያደረገ ስለነበር ዲያብሎስን ድል ነሥቶታል ሔዋንን ግን ሥራ ፈትታ እግሯን ዘርግታ ስለአገኛት ድል ነስቷታል፡፡
ጸሎት ሰማእታት ከነደደ እሳት፣ ከተሳለ ስለት፣ ከአላውያን መኳንንት፣ ከአሕዛብ ነገሥታት ከዲያብሎስ ተንኮል እና ሽንገላ ዲያብሎስ በእነርሱ ላይ ከአጠመደው አሽከላ የዳኑበት ጋሻ ነው፡፡ ኤፌ.6፥10 21 ጸሎት፣ ሰው አሳቡን ለእግዚአብሔር የሚገልጥበት እግዚአብሔርም የሰውን ልመና ተቀብሎ ፈቃዱን የሚፈጽምበት ረቂቅ ምስጢር ነው፡፡
የጸሎት መሠረቱ “ዕሹ ታገኛላችሁ ለምኑ ይሰጣችኋል ደጁ ምቱ ይከፈትላችኋል” የሚለው የጌታችን ትምህርት ነው ማቴ.7፥7
ጸሎት፡- በሦስት ክፍል ይከፈላል
-
ጸሎተ አኰቴት
-
ጸሎተ ምህላ
-
ጸሎተ አስተብቊዖት
-
ጸሎተ አኰቴት፡- ማለት እግዚአብሔርን ከሁሉም አስቀድሞ ስለተደረገልን ነገር በማመስገን የሚጀመር ጸሎት ነው ይህም ዓይነት ጸሎት የቅዱስ ባስልዮስን የምስጋና ጸሎት የመሰለ ነው፡፡
“ነአኲቶ ለገባሬ ሠናያት ላዕሌነ እግዚአብሔር መሐሪ”
“ለእኛ በጎ ነገርን ያደረገ ይቅርባይ እግዚአብሔር አምላካችንን እናመሰግነዋለን” ይልና ምክንኀያቱን ሲገልጥ ጠብቆናልና፥ አቅርቦናልና፥ ወደ እርሱም ተቀብሎናልና፥ እስከዚችም ሰዓት አድርሶናልና” ይላል፡፡ /ሥርዐተ ቅዳሴ/ ይህ ጸሎት የምስጋና ጸሎት /ጸሎተ አኰቴት/ ይባላል፡፡ ቅዱስ ጳውሎስም ይህንን የምስጋና ጸሎት ለፊልጵስዮስ ክርስቲያኖች ሲጽፍላቸው “ነገር ግን በሁሉ ነገር ጸልዩ ማልዱም እያመሰገናችሁም ልመናችሁን ለእግዚአብሔር ግለጡ” ይላል፡፡ ፊል.4፥6 ዳግመኛም “ስለእናንተ በኢየሱስ ክርስቶስ ከእግዚአብሔር ዘንድ ለእናንተ ስለተሰጣችሁ ጸጋ ዘወትር እግዚአብሔርን አመስግነዋለሁ” 1ቆሮ.1፥4 ብሎ ከመለመን አስቀድሞ እግዚአብሔርን ማመስገን አስፈላጊ መሆኑን አስተምሯል፡፡ በዚህ መሠረት ሰው የተደረገለትን በጎ ነገር ሁሉ በማሰብ ፈጣሪውን ማመስገን ከማመስገንም ቀጥሎ የሚያስፈልገውን ከፈጣሪው መለመን አስፈላጊ ነው፡፡
ከቅዱስ ጳውሎስ የምንማረው ለእኛ ስለተደረገልን ብቻ ማመስገንን አይደለም፤ ሌሎች ስለተደረገላቸውም ማመስገን ተገቢ መሆኑን እንጂ፡፡ “ለእናንተ ስለተሰጣችሁ ጸጋ ዘወትር እግዚአብሔርን አመሰግናለሁ” ሲል ለወገኖቹ ስለተደረገላቸው በጎ ነገር በደስታ ማመስገኑ ነው፡፡ ክርስትና ማለት ለእኔ ብቻ ማለት ሳይሆን ለሌሎችም መኖር፣ ለሌሎች በተደረገው የእግዚአብሔር ስጦታም ደስ መሰኘት ነው፡፡ ይህን የምስጋና ጸሎት /ጸሎተ አኮቴት/ ብዙ አባቶች፣ እናቶች ተጠቅመውበታል፡፡ ለምሳሌም ያህል ዘካርያስንና ኤልሳቤጥን መመልከት እንችላለን፡፡ ቅድስት ኤልሳቤጥ እግዚአብሔር ያደረገላትን በጎ ነገር ስትመሰክር “እግዚአብሔር በዚህ ወራት ከሰው ስድቤን ያርቅ ዘንድ በጎበኘን ጊዜ እንዲህ አደረገልኝ” ብላለች፡፡ ሉቃ.1፥25 እግዚአብሔር ጎበኘኝ ብላ ቸርነቱን አደረገለኝም በማለት የተደረገላትን መልካም ስጦታ ዮሐንስን መጽነሷን ገልጣ አመስግናለች፡፡ ዘካርያስም እንዲሁ አመስግኗል፡፡ “ያን ጊዜም አፉ ተከፈተ አንደበቱም ተናገረ እግዚአብሔርንም አመሰገነ” ሉቃ.1፥65 “ከዚህ ጊዜ ያደረስከኝ፥ ከደዌ የፈወስከኝ፥ ዮሐንስን የሰጠኸኝ ብሎ ፈጣሪውን አመስግኗል በመቀጠልም ይቅር ያለን ለወገኖቹም ድኅነትን ያደረገ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ይመስገን ከባሪያው ከዳዊት ቤት የምንድንበትን ቀንድ አስነሣልን፡፡” ሉቃ.1፥68 በዘካርያስ ጸሎት ውስጥ ምስጋናውን አስቀድሞ ትንቢቱን አስከትሎ እናገኘዋለን፡፡ በዚህ ምስጋናውና ትንቢቱ አምላክ ለእኛ ያደረገው የቤዛነቱን ሥራ በመግለጥ ሲያመሰግን እንመለከታለን፡፡
2. ጸሎተ ምህላ፡- ጸሎተ ምህላ ስለፈውሰ ሕሙማን …… ስለ ሀገርና ስለነገሥታት ስለ ጳጳሳት፣ ካህናት ዲያቆናት፣ ምዕመናን ሕይወት ቸነፈር፣ ጦርነት፣ ረሀብ፣ ድርቅ ወይም ሌላ አስጊ ነገር በሆነ ጊዜ በብዛት፣ በማኅበር የሚጸለይ ጸሎት ነው፡፡ የምህላ ጸሎት ሲጸለይ በእስራኤል ላይ ቸነፈር በተነሣ ጊዜ አሮን በሽተኞን ባንድ ወገን ጤነኞችን ባንድ ወገን አድርጎ የክህነት ልብሱን ለብሶ ማዕጠንተ ወርቁን ይዞ በራስህ የማልክላቸውን አብርሃምን፣ ይስሐቅን፣ ያዕቆብን አስበህ የወገኖችህን ኀጢአት ይቅር በል” እንደጸለየላቸው ነው፡፡ ዘኁ.16፥46-50
ዛሬም ካህናት ከጠቀስናቸው አስጊ ነገሮች ማንኛውም በሀገር ላይ ቢመጣ ወደ ሀገር እንዳይገባ ገብቶ ቢሆን ከፍ ያለ ጉዳት እንዳያመጣ የክህነት ልብስ ለብሰው ማዕጠንቱ ይዘው ሥዕለ ማርያም፣ መስቀል አቅርበው ማኅበረ ክርስቲያንን ሰብስበው፣ ኢየሱስ ክርስቶስን “ስለእኛ ከድንግል ማርያም መወለድህን ስለእኛ መሠቀል መሞትህን አስበህ የህዝብን ኀጢአት ይቅር በል ከመዓት ወደ ምሕረት ተመለሰ” እያሉ በምህላ ይጸልያሉ፡፡
የምህላ ጸሎት መአትን መቅሰፍትን ይመልሳል ጦርን፣ ቸነፈርን ያስታግሳል መሠረቱም፡፡
“ጾም ለዩ ምህላ ስበኩ” ያለው ቃል ነው፡፡ ይህ ጸሎት በሰላም ጊዜ ሰላሙ ዘላቂ እንዲሆን በጦርነት ጊዜ ለመከላከያነት ዋና መሣሪያ ነው፡፡ ስለዚህ አጥብቀን ልንከተለው ይገባል፡፡
የምህላ ጸሎት ነገሠታት ከዙፋናቸው ወርደው ወንድ ሙሽራ ሴት ሙሽራ ከጫጉላቸው፣ ከመጋረጃቸው ለምግብ የደረሱ ልጆች ከምግብ ለምግብ ያልደረሱ ከጡት ተከልክለው ሕዝብ ሁሉ ምንጣፍ ለብሰው አመድ ነስንሰው የሚጸልዩት ከፍተኛ ጸሎት ነው ኢዩ.2፥12-18፣ ዮና.3፥5
3. ጸሎተ አስብቊዖት
ይህ ጸሎት አንድ ሰው ስለሚፈልገው ነገር ቦታ ለይቶ ሱባኤ ገብቶ የሚጸልየው ጸሎት ነው፡፡ ይህ ጸሎት በተለይ ጣዕመ ጸጋን በቀመሱ በተባሕትዎ፣ በምናኔ በገዳም በሚኖሩ አበው ዘንድ የተለመደና የሚደረግ ጸሎት ነው፡፡ ወጣንያን እግዚአብሔርን ጠይቀው አድርግ አታድርግ የሚል መልስን አይጠብቁም፡፡ ፍጹማን አባቶች ግን እግዚአብሔር ጠይቀው አድርግ ወይም አታድርግ የሚል ፈቃደ እግዚአብሔርን ሳይቀበሉ የሚያደርጉት ነገር የለምና ቦታ፣ ጊዜ ወስነው ፈቃደ እግዚአብሔር ይጠይቃሉ፡፡ ይህ ጸሎተ አስተብቊዖት ይባላል፡፡ ይህም ማለት መላልሶ ደጋግሞ ያለ ዕረፍት ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይሉ የሚደረግ ጸሎት ነው፡፡ ለምሳሌ ትልቁ መቃርስ ዓለምን ዞሮ ለመጎብኘት ለተከታታይ አምስት ዓመታት እግዚአብሔርን ከለመነ በኋላ እየዞረ መካነ ቅዱሳንን እንዲጎበኝ ከእግዚአብሔር ፈቃድ አግኝቷል በዚህም ከእርሱ ከገድል በትሩፋት የሚበልጡ መናንያን በማግኘቱ መነኮሳትማ እነርሱ እንጂ እኔ ምንድን ነኝ? እያለ ራሱን እየወቀሰ እንደተመለሰ በመጽሐፈ መነኮሳት ተጽፎ እናገኛለን፡፡ በቤተ ክርስቲያናችን “መስተበቊዕ” የሚባል የጸሎት ክፍል፡፡ አለ ይህ ጸሎት በካህናት አባቶቻችን ስለሙታን፣ ስለሕያዋን፣ ስለነገሠታት፣ ስለ ጳጳሳት ስለ ንዑሰ ክርስቲያን፣ ስለ ምእመናን መባዕ ስለሚያቀርቡ ስለነጋድያን፣ ስለዝናም ስለ ወንዞች የሚጸለይ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው የጸሎት ክፍል ነው፡፡
ጠቅላላውን በቤተ ክርስቲያን የሚጸልዩ ጸሎታት ጸሎተ ፍትሐት፣ ጸሎተ ተክሊል፣ ጸሎተ ህሙማን፣ ጸሎተ ቅዳሴ፣ ጸሎተ ሰዓታት፣ የግል ጸሎት፣ የማኅበር ጸሎት እነዚህ ሁሉ ከላይ ከዘረዘርዓቸው ሦስቱ የጸሎት ክፍሎች አይወጡም፡፡ ከጸሎተ አኰቴት ከጸሎተ ምህላ፣ ከጸሎተ አስተበቊዖት ይመደባሉ፡፡ እነዚህን ጸሎታት በሰቂለ ኅሊና በአንቃዕድዎ /ዐይንን ወደ እግዚአብሔር በማንሳት/ መጸለይ ታላቅ ዋጋ የሚያሰጥ ከሰይጣን ወጥመድ የሚታደግ ሕይወትን የሚስተካከል ከእግዚአብሔር ጋር የሚያስታርቅ አጋንንትን የሚያርቅ ኀይለ እግዚአብሔርን ለሚጸልየው የሚያስታጥቅ መላእክትን የሚያስመስል ነው፡፡
እኛም ሰውነታችን ከበደል ልቡናችን ከቂም ከበቀል እንዲሁም ከተንኮል ንጹሕ አድርገን ብንጸልይ እንጠቀማለን ጸሎታችን ተሰሚ ልመናችንና ጩኸታችን ግዳጅ ፈጻሚ ይሆናል፡፡ የአባቶቻችን ጸሎት የተቀበለ እግዚአብሔር አምላካችን ጸሎታችንን ይቀበለናል፡፡
ይቆየን