የእግዚአብሔርን ቅንነት የተረዳ ቅዱስ አባት

ሐምሌ 82003 ዓ.
ቅዱስ ኪሮስ ወደ አባ በብኑዳ በደረሰ ጊዜ ዐፅሙ በየቦታው ተበትኖ አንበሳ ሲበላው አገኘ በዚህም ሠዓት በጣም አምርሮ እያለቀሰ “ጌታ ሆይ፥ ለምን እንዲህ ታደርጋለህ ፍርድህ መልካም አይደለም፤ በመንግሥት፥ በመብልና በመጠጥ በደስታ የኖሩትን በክብር እንዲቀበሩ ታደርጋለህ፥ ስለ አንተ ሲሉ አባትና እናትን ሚስትን ልጆችን ደስታን ሁሉ ትተው በተራራና በዋሻ በጾምና በጸሎት የኖሩትን ደግሞ ሥጋቸውን ለዱር አራዊት ትሰጣለህ፥ “የአንተን ፍርድ ነገር ላልሰማ እንዳልነሣ ሕያው ስምህን” ብሎ መሬት ላይ ተኛ፡፡

ቅዱስ ኪሮስ የሮም ንጉሥ የነበረው የአብያና የሚስቱ ሜናሴር ሁለተኛ ልጅ ነው። ስሙንም ዲላሶር አሉት። ንጉሥ አብያ ካረፈ በኋላ ታላቁ ቴዎዶስዮስ ነገሠ፡፡ ዲላሶርም በከተማ ውስጥ የሚሠራውን ዓመፅ በዐየ ጊዜ በሌሊት ተነሥቶ፥ ከሀገር ወጥቶ፥ ትንሽ በዓት አግኝቶ ዐሥር ቀን በዚያች ቆየ፡፡ መንፈስ ቅዱስ ኪሮስ ብሎ ጠራውና “ለብዙዎች አባት ትሆናለህ፥ በቃልህም ክርዳድ ይነቀላል፥ የአንድ ቀን መንገድ ሒድና ገዳማዊ መነኰስ ታገኛለህ፥ ከእርሱም ልብሰ ምንኲስና ትለብሳለህ” አለው፡፡ እንደ ታዘዘው በሔደ ጊዜ ከአንዲት በዓት የራስ ፀጉሩ እስከ እግሩ የሚደርስ፣ ግርማው የሚያስፈራ ገዳማዊ ወጥቶ “ኪሮስ መነኲሴ ለመሆን ወደዚህ መጣህን አለው፡፡ ኪሮስም ግርማውን እያደነቀ ቀርቦ ተባረከና ሦስት ቀን ከቆየ በኋላ “ኪሮስ ሆይ፥ እንደ እኔ መሆን ትፈልጋለህን” አለው፡፡ እርሱም “አዎ፥ በጣም እፈልጋለሁ” ባለው ጊዜ አባ በብኑዳ ትንሽ ደመናን ጠርቶ በዚያ ላይ በመሆን ከአስቄጥስ ገዳም በመሄድ የምንኲስናን ልብስ ተቀብሎ በዚያችው ደመና ኪሮስ ካለበት ቦታ ተመለሰ፡፡ ያመጣውን አልባሰ ምንኲስናም ለኪሮስ አለበሰው፡፡
ለአባ በብኑዳ ሁልጊዜ በሠርክ ሰማያዊ ኅብስትና ጽዋዐ ወይን ቅዱስ ሚካኤል ያመጣለት ነበር፡፡ አባ ኪሮስ በዚያ ለአባ በብኑዳ እየታዘዘ ሲኖር አንድ ገዳማዊ ሰው ወደ አባ በብኑዳ መጥቶ ሳለ ምንም ነገር እንደ ሌለው ዐይቶ “ምን ትበላለህ” ቢለው “አምላካችን ይሰጠናል” አለው፡፡ ያ እንግዳ መነኲሴም በልቡ “እንደ እኛ ሰው አይደለምን” እያለ ሲያስብ አባ በብኑዳ በመንፈስ ዐውቆ “ለምን እንዲህ ታስባለህ” “እኔም እንዳንተ በደለኛና ኀጥእ የሆንኩ መነኲሴ ነኝ” አለው፡፡ ይህን እየተነጋገሩ ሳለ የሠርክ ጸሎት ደርሶ በኅብረት ሲጸልዩ ፈጽሞ ደስ የሚል መዓዛ መጣ፥ ወዲያውም የተዘጋጀ ኅብስትና ጽዋዐ ወይን ይዞ ቅዱስ ሚካኤልን ሲመጣ ዐየውና ተቀበለው፥ ያ እንግዳ መነኲሴ ግን አላየውም፥ አሁንም “አስቀድሞ ያልነበረ ይህን ጽዋና ኅብስት ከየት አገኘው ይህ ባሕታዊ መሠሪ ነው” እያለ አሰበ፥ አባ በብኑዳም “ለምን እንዲህ ክፉ ታስባለህ?” አለው፥ መነኲሴውም አድንቆ ተቀምጠው መመገብ ጀመሩ፡፡
ያ እንግዳ መነኲሴ ግን ከዚያ ኅብስተ ሰማይ ቆርሶ በልብሱ ደብቆ ወደ አስቄጥስ ገዳም ሔደ፡፡ በዚያ ያሉ መነኰሳትንም ሰብስቦ ያን በረድ የሚመስል ኅብስተ ሰማይ አሳያቸው፡፡ “የት አገኘኸው” ቢሉት፥ “በዮርዳኖስ ገዳም ውስጥ በብኑዳ የሚባል መሠሪ ሰው አለ፥ ኑ ተከተሉኝና ታመጡት ዘንድ ወደዚያ ልውሰዳችሁ” አላቸው፡፡ ይህን ሲነጋገሩ ቅዱስ ሚካኤል መጥቶ ያችን የኅብስት ቁራሽ ወደ ሰማይ ወሰዳትና በልዑል ፊት ሰገደ፥ እግዚአብሔርም “መልካም አገልጋዬ ሆይ፥ የተቀደሰውን ለውሻ የሰጠ በብኑዳ ክፉ አደረገ፥ ስለዚህም በአንበሳ ተሰብሮ እንዲሞት አደረግኹ፥ ይህም በረከት ይከለከላል፥ ይህንንም ኅብስት በበረሃ ላለ ፊልሞና ለሚባል መነኲሴ እስከ ዕለተ ሞቱ ሲሳይ እንዲሆነው ስጠው” አለው፡፡ ቅዱስ ሚካኤልም እንደ ታዘዘው አደረገ፡፡ የአስቄጥስ ገዳም ቅዱሳንም ያን መነኲሴ “እኛን ማን መምህርና ፈራጅ አድርጐ ሾመን” አሉት፥ በዚህ ጊዜ አዘነና ወደ ማደርያው ሔዶ ታንቆ ሞተ፡፡
አባ በብኑዳም ይመጣለት የነበረው መና ተከለከለ፥ ሦስት ቀን ምንም ሳይቀምስ ከቆየ በኋላ እያለቀሰ አባ ኪሮስን “ልጄ ሆይ፥ ሰይጣን ወደ ማደርያችን ገብቶአል፥ ያገኘን ይህ ነገር ምንድ ነው” አለው፡፡ አባ ኪሮስም “ያ መነኲሴ መጥቶ ከሄደ በኋላ እግዚአብሔር ተቆጥቷል” አለው፡፡  አባ በብኑዳም “የእግዚአብሔር ፈቃድ ይሁን” አለ፡፡ ከዚያም አባ ኪሮስ ፍሬን እየሰበሰበ ይመለስ ነበር፥ አባ በብኑዳ ግን በቀንም ሆነ በማታ ከበኣቱ ሳይወጣ ይጸልይ እንደ መንኰራኲርም ይሰግድ ነበር፡፡
አባ ኪሮስም እንዲህ እያለ ሲኖር፥ አንድ ቀን የዕለት ሲሳይ ፍለጋ ወደ አንድ ሀገር ሄዶ ሳለ የኬልቄዶን ንጉሥ ሞቶ፥ ሕዝቡ ሁሉ እየጮኹና እያለቀሱ፥ ምድር እየረገጡ፥ ብዙ የፈረሰኛ ሰልፍ ተሰልፎ፥ በአስከሬኑ ላይ ድባብ እየዘረጉ ካህናት በማዕጠንት በፊቱና በኋላው እየዘመሩ ባየ ጊዜ አንዱን ሰው “ይህ የማየው ምንድን ነው?” ብሎ ቢጠይቀው “የኬልቄዶን ንጉሥ ስለ ሞተ ነው” አለው፡፡ አባ ኪሮስም “ለሞተ ሰው ይህን ያህል ይደረጋልን እኔስ ንጉሥ ለልጁ ሰርግ ያደረገ መስሎኝ ነበር” አለ፡፡ ይህን ብሎ አልፎ ፍሬ ሰብስቦ ወደ ማደርያው ወደ አባ በብኑዳ በደረሰ ጊዜ ዐፅሙ በየቦታው ተበታትኖ አንበሳ ሲበላው ባገኘ ጊዜ በጣም አምርሮ እያለቀሰ “ጌታ ሆይ፥ ለምን እንዲህ ታደርጋለህ ፍርድህ መልካም አይደለም፤ በመንግሥት፥ በመብልና በመጠጥ በደስታ የኖሩትን በክብር እንዱቀበሩ ታደርጋለህ፥ ስለ አንተ ሲሉ አባትና እናትን ሚስትን ልጆችን ደስታን ሁሉ ትተው በተራራና በዋሻ በጾምና በጸሎት የኖሩትን ደግሞ ሥጋቸውን ለዱር አራዊት ትሰጣለህ፥ የአንተን ፍርድ ነገር ላልሰማ እንዳልነሣ ሕያው ስምህን ብሎ መሬት ላይ ተኛ፡፡ አርባ ዓመት ሲሆነው ግማሽ ሥጋው አለቀ፤ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመልአክ አምሳል ተገጾ “ተጋዳይ የሆንክ አርበኛ ኪሮስ ሆይ፥ ሰላም ላንተ ይሁን፥ ተነሥ” አለው፡፡
ኪሮስም “አንተ ማነህ መልአከ እግዚአብሔር ከሆንክ በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ በል” አለው፡፡ ጌታችንም “በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ” አለ፡፡ ኪሮስ መነሣት ባቃተው ጊዜ ምድርን “ሥጋውን አትያዥ” ባላት ጊዜ ፈጥኖ ተነሣ፥ ኪሮስም ጌታችን እንደ ሆነ ዐወቀው፤ መላ ሰውነቱን ዳበሰው፤ ሰውነቱ እንደ ሕፃን ሆነ፤ በምድር ላይ ሰግዶ ጌታችን እንደ መብረቅ ሲለወጥና እልፍ አእላፋት መላእክት ሲያመሰግኑት አያቸው፡፡ ጌታችንም “ኪሮስ ሆይ፥ አንተ ሚስትህን፣ ልጆችህን፣  መንግሥትህን የተውህልኝ የማርያም ልጅ ኢየሱስ ነኝ፥ ስለ ሁሉ ብዙ የብዙ ብዙ ታገኛለህ፥ በምድር ላይ እንዳንተ ትዕግሥትን የለበሰ አላገኘሁም፥ ለዚያ እንግዳ መነኲሴ ቅድሳቴን ለምን ሰጣችሁት ስለዚህ ነው የበብኑዳን ሥጋ ለአራዊት የሰጠሁት፤ በዚህ ምክንያት በፊቴ እንዳይወቀስ ነው፡፡ ለሁሉ ሥራ ፍዳ አለውና፥ አምላኩ በምድር ላይ የገሠጸው ሰው ብፁዕ ነው፥ ያለውን አልሰማህምን” ኪሮስም “ጌታዬ ሆይ፥ ፍርድህ ቅን ነው” አለ፡፡ ጌታችንም “ከዚህ በኋላ የነፍስን ከሥጋ መለየት ታይ ዘንድ በገዳማት ሒድ፥ ከዚያም ወደ ማደሪያህ ተመለስ” ብሎት ተሠወረ፡፡
አባ ኪሮስ በጌታችን ታዝዞ ደብረ ባሳት በደረሰ ጊዜ ቤተ ክርስቲያንን ተሳልሞ፥ የእመቤታችንን ሥዕል ዐይቶ ከዐይኖቹ እንባ እያፈሰሰ “እመቤቴ ሆይ፥ አስቢኝ” አላት፡፡ ሥዕሊቱም “ኪሮስ ሆይ፥ መምጣትህ መልካም ነው፤ የአባትህን ዐፅም ትጠብቅ ዘንድ ወደ ማደርያህ ተመለስ” አለችው፡፡ ይህን ሰምቶ ከሥዕሏ ፊት ሰባት መቶ ስግደት ሰገደ፤ በዕብራይስጥ ቋንቋም “እንግዳ ነህና በቃህ፥ በምሕረት መዝገብም ተመዝግቦልሃል” የሚለውን ቃል ሰማ፡፡ ከዚያም መስፈርስ የሚባል ሕማም ለብዙ ጊዜ የታመመና በምድር ላይ የወደቀ ሰውን አገኘ፡፡ በራስጌው ቅዱስ ሚካኤልን፥ በግርጌው ገብርኤልን በቀኙም ሩፋኤልን በግራውም ሰዳክኤልን በክንፋቸው ጋርደውት ዐየ፡፡ እነርሱም “በገዳዮች ፊት ሞትን የማይፈራ ሆይ፥ እንዴት ነህ” ብለው ሰላምታ ሰጡት፡፡ እርሱም አድንቆ “በልዕልና ነዋሪዎች ሆይ፥ በዚህ ለምን ተቀመጣችሁ” አላቸው፡፡ እነርሱም “ይህን ድሀ እንድንጠብቀው ከእግዚአብሔር ታዝዘናል” አሉት፡፡ “እስከ መቼ” ቢላቸው “አምላካችን እስከሚያሳርፈው ድረስ” ብለውታል፡፡
ከዚህም በኋላ ወደ ታመመው ተመልሶ “በዚህ ቦታ ከኖርህና ከታመምህ ምን ያህል ዘመን ነው” ብሎ ጠየቀው፡፡ በሽተኛውም “በዚህ ቦታ ስኖር 65 ዓመት ነው፤ ከታመምኩ ሃያ ዓመት ነው” አለው፡፡ መልሶም “አበ ምኔቱና የገዳሙ መነኰሳት ይጐበኙሃል” አለው፡፡ በሽተኛውም “አባቴ ሆይ፥ የለም፥ ፊታቸውን ከዐየሁ ዐሥራ አምስት ዓመት ነው” አለው፡፡ አባ ኪሮስም “አባትህ ማነው እናትህስ ማናት” ብሎ በጠየቀው ጊዜ “አባቴ የኬልቄዶን ንጉሥ ነው፥ እናቴም ንግሥት ናት፥ በአባቴ ቤት ያሉ ሰዎች ወርቁንና ብሩን ቀጭኑንም ልብስ ከብዛቱ የተነሣ በእግሮቻቸው ይረግጡታል” አለው፡፡ ጥያቄውን በመቀጠል “ወደዚያች ገዳም ማን አደረሰህ?” ብሎ ጠየቀው፡፡ እርሱም “እንደ አንተ ያሉ ሁለት ሰዎች ወደ አባቴ ቤት መጥተው ከዚያ አደሩ፡፡ እኩለ ሌሊትም ሲሆን ፊቱ ብሩህ የሆነ ሰው ወደ እኔ መጥቶ ሚሳኤል ብሎ ጠርቶ ሲነጋ ተነሥተህ ከእነዚህ ቅዱሳን ጋር ሒድ አለኝ፡፡ እኔም ወጥቼ ወደዚህ ገዳም ደረስኩ” አለው፡፡ አባ ኪሮስም የአባቱን የበብኑዳንና የሌሎችንም ቤተ መንግሥትን እየተዉ የመነኑ ቅዱሳንን ሁኔታ እያነሣ አጽናናው፡፡ “እግዚአብሔርም የሚወደውን ይገሥጻልና አታድንቅ” አለው፡፡ ያ በሽተኛ /ሚሳኤልም/ “እውነት ነው ለእኔ ይገባኛል። ስለ ኃጢአቴም ይህን ተቀበልኩ” ብሎ መለሶ ዝም አለ፡፡
ያን ጊዜ በሞት ያሰናብተው ዘንድ አባ ኪሮስ ወደ እግዚአብሔር ጸለየ፡፡ ጌታችንም በክብር መጣ፡፡ ጌታችንም አባ ኪሮስን “ምን ያህል እንደምወድህ የመላእክት ሠራዊት ያዩና ያውቁ ዘንድ ይህችን የገነት ተክል አበባ ከእጄ ወስደህ በፊቱ ላይ ጣል” አለው፡፡ ኪሮስም እንዲሁ አደረገ፡፡ ያን ጊዜ የበሽተኛው የሚሳኤል ነፍስ ያለ ጻዕር በፍጥነት ወጣች፡፡ መድኃኒታችንም ተቀብሎ ሳማት፡፡ ከእርሱ ጋርም በብርሃን ሠረገላ ውስጥ አስቀመጣት፥ አውጥቶም በሰማያዊ ክብር አኖራት፥ አባ ኪሮስም አለቀሰ፡፡ አባ ኪሮስም የገዳሙን መነኰሳት “ያን በሽተኛ ቅበሩት” ሲላቸው ፈቃደኞች ባለመሆን እያንጐራጐሩ ነበር፡፡ አራቱ የመላእክት አለቆች ሥጋውን በከርቤና በሚዓ አጠኑ፡፡ የገዳሙ መነኰሳትም “የሚሸተን ምንድን ነው ይህ መነኰስ ሥራይን ያውቅ ይሆንን” ተባባሉ፡፡ ሥጋውንም በገዳሙ በእንግዳ መቃብር ቀበሩት፥ ከመቃብሩም ጥሩ ውኃ ፈለቀ፥ ለበሽተኖችም ፈውስ ሆነ፡፡ አባ ኪሮስም እነዚያን መነኰሳት በክፉ ሥራቸው ገሠጻቸው፥ መከራም ይመጣባችኋል አላቸው፡፡ ሊወግሩትም ድንጋይ በአነሡ ጊዜ ሠረገላ መጥቶ ወደ ማደርያው አደረሰው፡፡ በማግሥቱም ሽፍቶች መጥተው የዚያን ገዳም መነኰሳት በሙሉ ፈጁአቸው፥ ገዳሙንም አቃጠሉት፡፡
አባ ኪሮስ በበአቱ ሆኖ ሠራዊተ ጽልመት የእነዚህን ክፉዎች መነኰሳት ነፍሳት እያቻኰሉ ወደ ሲኦል ሲወስዷቸው ዐይቶ ይገባቸዋል አለ፡፡ በኋላ ግን እኒህ ስሑታን አሳቱኝ ብሎ እግዚአብሔር ይምራቸው ዘንድ 40 ቀንና ሌሊት ጾመ፡፡ “አልምራቸውምና አትድከም” የሚል ቃልን ሰማ፡፡ ከዚያም ከጋለ ድንጋይ ላይ ተኝቶ ሥጋው በእሳት እንደ ተጠበሰ እስኪሆን ቆየ፤ ቃልም “አልምራቸውምና አትድከም” አለው፡፡ እንደ ገና በሆዱ ተኝቶ ዐይኑ ወልቆ ታወረ፡፡ ሰይጣንም ከሩቅ ሆኖ “ብዙዎችን በኪዳንህ ያሳትክና ገንዘቤን ልትወስድ የተነሣህ ኪሮስ አንተ ነህን አሁን ዐይንህ ጠፋ ማን ይረዳሃል ማንስ ይመራሃል አለው፡፡ ይህን ሲሰማ አባ ኪሮስ ወደ ጌታችን ፈጽሞ እያለቀሰ ጸለየ፥ ጌታችንም ወደርሱ መጥቶ “ኪሮስ ሆይ፥ ሰላም ላንተ ይሁን፥ በእውነት አንተ ሰውን ወዳጅ ነህ፥ ድካምህ ሁሉ በኢየሩሳሌም ሰማያዊት ተመዝግቦአል፡፡ ልጁን በስምህ ለሚጠራ፥ በእምነት ሆኖ የገድልህን መጽሐፍ ያጻፈ፥ ያነበበ፥ መባዕና ዕጣን ለቤተ ክርስቲያንህ የሰጠውን ላንተ ዓሥራት ይሆን ዘንድ ሰጠሁህ፤ ካንተም ጋራ ባሕረ እሳትን ይለፍ፥ ደስም ይሰኝ” አለው፡፡ ይህንኑ ብሎ ራሱን በእጆቹ ይዞ ፈወሰው፡፡ ቅዱስ ኪሮስም “በፊትህ ሞገስ ካገኘሁ እነዚያን መነኲሳት ማርልኝ” አለው፡፡ ጌታችንም ያመጧቸው ዘንድ አዘዘ፥ ነፍሳቸውንም ከሥጋቸው ጋር አዋሕዶ አሥነሳቸው፥ አባ ኪሮስንም በዐዩ ጊዜ አፈሩ፡፡ በአባ ኪሮስ ልመና አልባሰ ምንኲስና ለበሱ፥ ወደ ገዳማቸው የሚወስድ መንገድንም አሳይቶአቸው እንዲሔዱ አዘዛቸው፡፡ ከገዳማቸውም ደርሰው ቤተ ክርስትየን ሠርተው በጾም በጸሎትና እንግዳ በመቀበል ኖሩ፡፡
ከብዙ ጊዜ በኋላ ቅዱስ ኪሮስ፥ የእነዚያን መነኰሳት ሕይወታቸውን ያይ ዘንድ መልአኩን ላክ ብሎ በጸለየ ጊዜ፥ ጌታችን፡- “አንተው ሔደህ ጐብኛቸው” ብሎ ደመናን ጠርቶ፥ በዚያች ላይ አውጥቶ፥ በሰላም ሒድ ብሎ አሰናበተው፡፡ ኪሮስም ወዲያው ደርሶ ወደ ሚሳኤል መቃብር ሔደ፥ መነኰሳትም ባዩት ጊዜ ከአበምኔቱ ጋር ሮጠው ሔደው አቅፈው እየሳሙት “ደኅና ነህን” አሉት። እርሱም “ውሻና ነዳይ ለምሆን ለእኔ ይህ ክብር ለምኔ ነው” አላቸው፡፡ እነርሱም ባለማወቃችን ያሳዘንህን ይቅር በለን ባሉት ጊዜ “እግዚአብሔር ይቅር ይበላችሁ፥ ነገር ግን ሁላችሁም የእግዚአብሔር አገልጋይ ሚሳኤል ሆይ፥ ይቅር በለን በሉ” አላቸው፡፡ እነርሱም “የእግዚአብሔር አገልጋይ ሚሳኤል ሆይ፥ ይቅር በለን” አሉ፡፡ በዚህን ጊዜ “እግዚአብሔር ይቅር ይበላችሁ፥ በእናንተ ምክንያት ወደ መንግሥተ ሰማያት ገብቻለሁና” የሚል ቃል ሰሙ፡፡
እነርሱም “ይህ የናቅነውና የጣልነው ሚሳኤል አይደለምን” ብለው እያደነቁ ዐፅሙን ወደ ቤተ ክርስቲየን ውስጥ ሊያስገቡት በፈለጉ ጊዜ “ባለበት ተዉት ነገር ግን በጸሎቱ ትጠቀሙ ዘንድ ተዝካሩን አድርጉ” አላቸው፡፡ እርሱም እየመከራቸው ወደ ቤተ ክርስቲያን ደረሱ፡፡ አባ ኪሮስም “የክርስቶስ ማደረያው ሆይ፥ ሰላም” ብሎ በተሳለመ ጊዜ “በሐከ ፈላሲ ክቡር፥ ክቡር መጻተኛ ሆይ ሰላም” ስላለው አደነቀ፡፡ አበ ምኔቱ በቤቴ እደር ቢለውም አይሆንም ብሎ በሚሳኤል ማደርያ በነበረው አንጻር ሔዶ አደረ፡፡ በማግሥቱም “ከእንግዲህ ወዲህ በመንግሥተ ሰማያት እንጂ በዚህ ምድር አንተያይምና በጸሎታችሁ አስቡኝ” ብሎ ተሰናብቷቸው ወደ ማደሪያው ተመልሶ አጋንንትን ኑ ሲላቸው እየመጡ፥ ሒዱ ሲላቸው እየሔዱ ሲገዛቸው ኖረ፡፡ ከዚያም በኋላ ቅዱስ ኪሮስ በገድልና በትሩፋት እየተቀጠቀጠ ለብዙ ዘመናት ከኖረ በኋላ ሐምሌ 8 ቀን ቅዱስ ዳዊት እየዘመረለት እልፍ አእላፋት ቅዱሳን መላእክት በተገኙበት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነፍሱን ከሥጋው ለይቶ አሳርጓታል፡፡ ጌታችንም የአስቄጥስ ገዳም አባ ባውማ ሥጋውን ገንዞ እንዲቀብረው አደረገ። እርሱም የንጉሥ ዘይኑን ልጅ ቅድስት ኢላርያን ሥጋዋን የገነዘ ነው። ደግሞም አባ ባውማ ጌታችን እንዳዘዘው በመንፈስ ቅዱስ የቅዱስ ኪሮስን ገድሉን የጻፈ ነው። “እኔ አባ ባውማም የቅዱስ ኪሮስን ገድሉን ጽፌ ለሚያነበውና ለሚሰማው ሁሉ መጽናኛ ይሆን ዘንድ ወደ አብያተ ክርስቲያናት ሁሉና ወደ ገዳማትም ላክሁ።” እንዳለ ስንክሳር ዘወርኀ ሐምሌ
ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም በጻድቁ አቡነ ኪሮስ ጸሎት ይማረን በረከቱም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን፡፡
ሰላም ለኪሮስ ዘሰዓሞ ነደ ከናፍር፡፡ ወበዘባኑ ተጽዕነ ለእግዚአብሔር፡፡ ወከመ ትጻእ ነፍሱ ዘእንበለ ጻዕር፡፡ ኀለየ እንዘ ይብል በመሰንቆ ሐዋዝ መዝሙር፡፡ ለጻድቅ ብእሲ ሞቱ ክቡር፡፡
 
ምንጭ፡- ያረጋል አበጋዝ (ዲ/ን) ና አሉላ ጥላሁን ፣ 1997። ነገረ ቅዱሳን 3። ማኅበረ ቅዱሳን፣ አ.አ።
        ስንክሳር በግዕዝና በአማርኛ ከመጋቢት እስከ ጳጒሜን፣ 1993
ትንሣኤ ዘጉባኤ ማተሚያ ቤት፣ አ.አ።

“የሚያየኝን አየሁት”

በትዕግሥት ታፈረ ሞላ

 04/11/2003

የክረምት ብርድ በተለያየ ምክንያት ከቤቱ የወጣውን መንገደኛ ፊት አጨፍግጎታል፡፡ ሰጥ አርጋቸው ደርጉም ከቡድኖቹ ጋር የዕለት እንጀራውን ለመጋገር ታክሲ ውስጥ ገብቷል፡፡ እሱም ሆነ ጓደኞቹ የማውራት ፍላጎት የላቸውም፡፡ ሌሊት በእርሱ አጠራር “ግዳጅ” የሚሉት የተደራጀ የሌብነት ሥራ ሲሠሩ ስላደሩ እንቅልፍ በማጣት ዐይኖቻቸው ቀልተው አብጠዋል፡፡ የወረዛው የታክሲው መስታወት ላይ የእነሱ ትንፋሽ ተጨምሮበት በጉም ውስጥ የሚሔዱ አስመሰላቸው፡፡

“ወራጅ” አለ፤ ሰጥ አርጋቸው፤ መስታወቱን በእጁ ጠረግ ጠረግ አድርጎ ወደ ውጭ እየተመለከተ፡፡ እጁ ላይ ውፍረቱ እጅግ የሚደንቅ የወርቅ ካቴና አድርጓል፡፡ ባለታክሲው ቅዱስ ጴጥሮስ ወጳውሎስ ቤተ ክርስቲያን የተሰበሰበው ሕዝብ ግርግር ስለፈጠረበት አለፍ አድርጎ አወረዳቸው፡፡ ስድስት ወንዶችና ሁለት ነጠላ መስቀለኛ ያጣፉ ሴቶች እንደኮማንደር በየተራ ዱብ ዱብ አሉና ሰጥ አርጋቸውን ከበቡት፡፡ 

“ሄይ! ጊዜ አናጥፋ፤ ባለፈው ዓመት እንዳደረግነው ቶሎ ቶሎ ሒሳባችንን ዘግተን ውልቅ፡፡” ሲል፤ አንደኛዋ ሴት “አዎ በእናታችሁ መታ መታ እናድርግና ከዚህ እንጥፋ፤ ዛሬ የምንቅመው ጫት መቼም…” ስትል የቡድኑ መሪ አቋረጣትና “ዲሞትፈርሽን ይዘሻል?” አላት፡፡ በነጠላዋ ደብቃ ስለቷ የበዛ ትንሽ ምላጭ በኩራት አሳየችው፡፡ “በቃ እኔ አምና ከቆምኩበት ከመቃብር ቤቱ ጎን እቆማለሁ፡፡ ዕቃ ከበዛባችሁ እያመጣችሁ አስቀምጡ፡፡ የቡድናችንን ሕግ በየትኛውም ደቂቃ እንዳትረሱ፡፡” አላቸው፡፡ ሕጉ ከመካከላቸው አንድ ሰው ቀን ጥሎት ቢያዝ፤ ብቻውን ይወጣዋል፡፡ ስለቡድኑ መረጃ ከመስጠት ይልቅ አንገቱን ለሰይፍ ቢሰጥ ይመርጣል፡፡ 

ሰጥ አርጋቸው ረጋ ባለ ድምፅ “ዳይ… ዳይ እግዚአብሔር ይርዳን” ሲላቸው ሁሉም ወደ ቤተ ክርስቲያኑ እግራቸውን አፈጠኑ፡፡ እሱም ከኋላቸው የጨዋ መልክ ተላብሶ ተከተላቸው፡፡ የእጁን ካቴና፣ የአንገቱን ገመድ መሳይ ሀብል ያየ ሁሉ ለእሱ በመስጋት ያዩታል፡፡ ሐሳባቸውን ቢረዳ “ሌባን ሌባ ቢሰርቀው ምን ይደንቀው” የሚለውን ተረት ይተርትባቸው ነበር፡፡ 

ቅዳሴው አልቶ ታቦት እየወጣ ነው፡፡ እልልታው ይቀልጣል፡፡ ወንዶች ፊታቸውን አብርተው ወደ መድረኩ ቁመታቸው በፈቀደላቸው መጠን እያዩ እጃቸው እስኪቃጠል ያጨበጭባሉ፡፡

ሰጥአርጋቸው እግረ መንገዱን አንድ ዘመናዊ ሞባይል በተመስጦ በሚያጨበጭብ ወጣት ኪስ ውስጥ ሲያይ በተለመደው ፍጥነቱ ወስዶ ጓደኞቹን ወደ ቀጠረበት ቦታ ለመድረስ በሰው መሐል ይሹለከለካል፡፡

አሁን እልልታውና ጭብጨባው ጋብ ብሎ ለዕለቱ የሚስማማ ስብከተ ወንጌል እንዲያቀርቡ የተመደቡት ሊቀ ጠበብት መድረኩን ይዘውታል፡፡ 

    “…. ዛሬ እንደሚታወቀው የሁለቱ ዐበይት ሐዋርያት ክብረ በዓል ነው፡፡ ትምህርታችን ግልጥ እንዲሆንልን በወንጌል እጅግ ብዙ ፍሬ ከማፍራታቸው በፊት ስለነበራ    ቸው ሕይወት እናንሣ፡፡ ቅዱስ ጴጥሮስ ከጌታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር በተቀመጠ ጊዜ “ጌታ ሆይ ሁሉም ቢክዱ እንኳን፤ እኔ ግን እስከመጨረሻው እከተልሃለሁ” ሲለው በራሱ እጅግ ተመክቶ ነበር፡፡ ነገር ግን መድኃኒታችን ኢየስስ ክርስቶስ “እውነት እውነት እልሃለሁ ዶሮ ሳይጮኸ ሦስት ጊዜ ትክደኛለህ፡፡” አለው፡፡ ጴጥሮስ ተሟገተ፡፡ 

    “ነገር ግን ክርስቲያኖች ታሪኩን እንደምታውቁት የመጀመሪያውን አንዲት ሴትን ፈርቶ ካደ፡፡ እየቀጠለ ሦስት ጊዜ ሲክድ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በአይሁድ የመከራ እጅ እንዳለ ዘወር ብሎ ጴጥሮስን አየው፡፡ቅዱስ ጴጥሮስ የክርስቶስ እይታ እንደ መርፌ ወጋው፡፡ ባዶ ትምክህቱ ተገለጸለት፡፡ ከዛ ዘወር አለና አንጀቱ፣ ሆድ ዕቃው እሰኪናወጽ ይንሰቀሰቅ ገባ፡፡ ጌታ እንዳየው ጴጥሮስ ራሱን በራሱ ከሰሰ፡፡ እንባዎቹ እሳት ሆነው በጉንጮቹ ላይ ይጎርፉ ጀመር…” 

የሰጥ አርጋቸው ቡድን አባላት እየቀናቸው ነው፡፡ የአንገት ሀብል፣ የተቀንቀሳቃሽ ስልክ ቀፎ፣ የገንዘብ ቦርሳዎች ሰብስበው ለዳግም ሙከራ ተሰማርተዋል፡፡ 

መምህሩ በተመስጦ ትምህርታቸውን እንደቀጠሉ ነው፡፡ “….ወዳጆቼ እኛንም እኮ በተለያየ ኃጢአት ውስጥ ስንመላለስ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እኛንና ምድርን የፈጠረ አባት የማያየን ይመስለን ይሆን? አንዳንዶቻችን  ፈጣሪ ሰባተኛው ሰማይ ላይ ስለሚኖር፤ ይኼ የምናየው ሰማይ እግዚአብሔርን እንደመጋረጃ የሚጋርደው መሰለን እንዴ?…” እያሉ በሚስብ አንደበታቸው በተመስጦ ይናገራሉ፡፡ 

የሰጥአርጋቸው ጓደኞች እየተመላለሱ የሚያሲዙትን ዕቃ በትልቅ ጥቁር ፌስታል አቅፎ ቁጭ ባለበት ጆሮው የዐውደ ምሕረቱን ትምህርት እያመጣ ያቀብለዋል፡፡ ጆሮ ክዳን የለው፡፡ 

“…. ቅዱስ ጴጥሮስ ግን…..” ቀጥለዋል አባ፤

    “…. በፀፀት እንባው ኃጢአቱን ሁሉ አጠበ፡፡ ትርጉሙ “ሸንበቆ” የነበረ “ስምዖን” የተባለ ስሙን ጌታችን ኢየሱሱ ክርስቶስ ለውጦ ጴጥሮስ አለው፡፡ ጴጥሮስ ማለት “ዐለት” ማለት ነው፡፡እንደገናም ጌታችን ጴጥሮስን ሦስት ጊዜ ደጋግሞ አንድ ጥያቄ ጠየቀው “ጴጥሮስ ትወደኛለህን?” “አዎን ጌታ ሆይ” አለ፤ “ጴጥሮስ ትወደኛለህን” “አዎን ጌታ ሆይ” “ጴጥሮስ ትወደኛለህን” ሲለው ለሦስተኛ ጊዜ ጴጥሮስ አንዲት ኃይለ ቃል ተናገረ “እንድወድህ አንተ ታውቃለህ፡፡” አለው፡፡ በንስሐው ጊዜ ራስን ዝቅ ማድረግን ተምሯልና፡፡ እንደቀደመው ጊዜ በራሱ ትምክህት “እንዲህ አደርጋለሁ፤ እንዲህ እፈጥራለሁ” አላለም፡፡ በኋላም በሕይወቱ ዘመን ሁሉ ባደረገው ክርስቲያናዊ ተግባር ለኢየሱስ ክርስቶስ ያለውን ፍቅር አሳየ የክርስቲያን ጠላቶች ሰቅለው ሊገድሉት በያዙት ጊዜም “እኔ እንደጌታዬ እንዴት እሰቀላለሁ? ራሴን ወደ ምድር ዘቅዝቃችሁ ስቀሉኝ፡፡ በማለት እንደ ዐለት የጠነከረ እምነቱን ገለጸ፡፡ 

የሰባኪ ወንጌሉ ድምፅ ለአፍታ ተገታና መርሐ ግብር መሪው በእልህ መናገር ጀመረ፡፡ “….ምእመናን እባካችሁ ከሌቦች ራሳችሁን ጠብቁ በጣም ብዙ አቤቱታ እየደረሰን ነው፡፡ ሞባይል ስልኮች በሴቶች በኩል ቦርሳቸው በምላጭ እየተቀደደ እየተወሰደ ነው፡፡ ወንዶችም ኪሶቻችሁን ጠብቁ፡፡ በረት የገባው ሁሉ በግ አይደለም!” አለና ይቅርታ ጠይቆ ድምፅ ማጉያውን ለሊቀ ጠበብት ሰጣቸው፡፡ 

ሰጥ አርጋቸው የፕሮግራም መሪውን የእልህ ንግግር እየሰማ ፈገግ ለማለት ሞከረና አንዳች ነገር ሽምቅቅ አደረገው፡፡ ቀና ብሎ ወደ ሰማይ ተመለከተ፡፡ ሰማዩ እንደ ድሮው ነው፡፡ 

ሊቀ ጠበብት የቅዱስ ጳውሎስን ታሪክ ማስተማር ቀጥለዋል፡፡ 

    “ሰማዕቱ ቅዱስ እሰጢፋኖስ ሲወገር ልብሳቸውን ከወጋሪዎቹ ጋር ተስማምቶ ይጠብቅ ነበር፡፡ ሴት ወንዱን እያስያዘ እስር ቤቶችን ሁሉ ሞላ፡፡ በኋላም የጠለቀ ክርስቲያኖችን ለመያዝ እንዲያመቸው የድጋፍ ደብዳቤ ለማምጣት ወደ ደማስቆ ሲሔድ በመንገድ ዳመና ጋረደውና “ሳ..ውል…ሳውል ስለምን ታሳድደኛለህ?” አለው፡፡ በአምላካዊ ድምፅ ጌታ እኮ ሳውልን ማጥፋት ወይም መቅጣት አቅቶት አይደለም፡፡ ምስክር ሲሆነው ምርጥ ዕቃው አድርጎ መርጦታልና፡፡ 

    “ጌታ ሆይ አንተ ማን ነህ?” አለ ቅዱስ ጳዉሎስ ግራ ገብቶት 

    “እኔ አንተ የምታሳድደኝ ኢየሱስ ነኝ አለው፡፡” “ተመልከቱ እንግዲህ” አሉ አባ እጅግ ተመስጠው፡፡ 

አንዳንድ እናቶች ከንፈራቸውን በተመስጦና በሐዘን ሲመጡ ከሚያሰሙት ድምፅ ሌላ ሁሉም በያለበት ቆሞ ጆሮውንና ልቡን ሰጥቷቸዋል፡፡ ሥራ ላይ ከተሰማሩት የሰጥአርጋቸው ቡድኖች በቀር፤ “…. ቅዱስ ጳዉሎስ ኢየሱስ ክርስቶስን እኮ በአካል አላገኘውም፡፡ ታዲያ እንዴት ለምን ታሳድደኛለህ አለው? ክርስቲያን ማለት በክርስቶስ ያመነ ማለት አይደለም ወገኖቼ? አይደለም ወይ?” ሲሉ ከፊት ያሉ ሕፃናት ድምፃቸውን ከሌሎች አጉልተው “ነው!” ብለው መለሱ፡፡ 

    “ሳውልም ያሳድድ የነበረው ክርስቲያኖችን ነበርና ነው፡፡ ዛሬ እኛም ስንቶችን አሳደድን ወገኖቼ! አሁን መርሐ ግብር መሪው የተናገረውን ሰምታችኋል አይደል? እዚህ መድረክ ላይ ብዙ ምእመናን ንብረታቸውን ተገፈው እያለቀሱ ነው፡፡ ማን ነው ከዚህ መሐል በክርስቲያኖች ላይ እጁን የዘረጋው? ዛሬም መድኃኔዓለም “ሳውል ሳውል ስለምን ታሳድደኛለህ? ቅዱስ ጳዉሎስስ የኦሪት ሊቅ ነበርና ማሳደዱ ስለ አምልኮቱ ቀንቶ እንጂ ስለ ሆዱ አልነበረም፡፡ እሱን ሦስት ቀን የዐይኖቹን ብርሃን በመጋረድ የቀጣ አምላክ እኛንማ እንዴት ባለ ጨለማ ይቀጣን ይሆን? እሱን አምነው በተሰበሰቡ ክርስቲያኖች ላይ ደክመው ያፈሩትን በመስረቅ በማታለል ልጆቹን እያሳደድን ነው፡፡ ይኽን ያደረክ ወንድሜ! ይኽን ያረግሽ እኅቴ ሆይ መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ “ለምን ታሳድጅኛለሽ? ይልሻል፣ ይልሃል፡፡…” 

ሲሉ ሰባኪው፤ ሰጥአርጋቸው እጆቹ መንቀጥቀጥ ጀምረዋል፡፡ ሊቀ ጠበብት በሰውኛ ባህርያቸው ሁሉንም እያዩ ያስተምራሉ፡፡ በእሳቸው አካል ላይ ግን ለሰጥአርጋቸው የጌታችንና የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ዐይኖች ታዩት፡፡ የተጨነቁ ዐይኖቹን ወደ ሰማይ ላካቸው፡፡ በዚያም የክርስቶስ ዐይን ነበር፡፡ ወደ መሬት አቀረቀረ በዚያም የክርስቶስ ዐይን ነበር፡፡ “ለካ እስከ ዛሬ ክርስቶስ ያየኝ ነበር፤ ያላየሁት እኔ ነኝ” አለ በልቡ፡፡ 

ሊቀጠበብት እንደቀጠሉ ነው “ወገኖቼ የእኛ አምላክ የቀደመውን በደላችንን ሳይሆን የኋላውን ብርታታችንን የሚመለከት ነውና፤ ቅዱስ ጳዉሎስ ጨርቁ እንኳን ድውያንን ይፈውስ ዘንድ እጅግ ብዙ ጸጋ በዛለት፡፡ ሐዋረያው ጳዉሎስም እውነት ለሆነው በፍፁም ፍቅር ሊጠራው ለእኛም ሳይገባው ቁስላችንን ለቆሰለልን፣ እሱ ታሞ ለፈወሰን፣ ተጠምቶ ላረካን፣ ተርቦ ላበላን ለጌታችን ለኢየሱስ ክርስቶስ ሲመሰክር አንገቱን በሰይፍ ተቆረጠ፡፡ ሰማዕትነትን በዚህች ቀን ተቀበለ፡፡ ዛሬ ሐምሌ አምስት ቀን የምናከብረው ቅዱስ ጴጥሮስና ቅዱስ ጳዉሎስ ሰማዕትነትን የተቀበሉበት ቀን በመሆኑ ነው፡፡ ወገኖቼ እኛስ አንገታችንን የምንሰጠው ለማን ነው? ለዘላለም ሕይወት ለሚሰጠን ለአምላካችን ነው ወይስ በተንኮል ለሚተባበረን ባልንጀራችን? …” 

ሰጥአርጋቸው ጥቁሩን ፌስታል እንደያዘ ድንገት ብድግ አለና በሰዎች መሐል ወደ ፊት ይገሰግስ ጀመር፡፡ አንዱ ባልንጀራው ያገኘውን ይዞ ወደ እሱ ሲመጣ በሰው መሐል ሲሹለከለከ ያየውና “ለእኔ በጠቆመኝ ይሻል ነበር፡፡” እያለ በዐይኑ ይከተለዋል፡፡ የቡድናቸው መሪ ግን ግቡ ቅርብ አይመስልም፡፡ አሁንም በሰዎች መሐል ወደፊት እየተሹለከለከ ነው፡፡ 

ሊቀጠበብት እንደቀጠሉ ነው፡፡ “ቅዱስ ጳዉሎስ አሳዳጅ የነበረ ቢሆንም፤ በኋላ ግን የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱሱ ክርስቶስ ፍቅር በዝቶለት ልሔድ ከእርሱ ጋር ልኖር እናፍቃለሁ..” እያለ በሙሉ ልቡ ይናገር የነበረው ስለ ስሙ ታስሮ ተገርፎ ተሰቃይቶ…” እያሉ ሲናገሩ አንድ ሰውነቱ ሞላ ያለ ወጣት እግራቸው ሥር ተንበርክኮ ከፌስታል ውስጥ ብዙ ቦርሳዎች፣ ተንቀሳቃሽ ስልኮችና ወርቆች ዘረገፈ፡፡ 

ሊቀ ጠበብት ግራ ተጋብተው ወደ ልጁ ተጠጉና “ልጄ ሆይ! ምንድን ነው?” አሉት፡፡

ሰጥአርጋቸው አንገቱ ላይ ያለውን ወርቅ እየፈታ ቀና ብሎ አያቸው፡፡ እሳቸው ዐይን ውስጥ የኢየሱሱ ክርስቶስን ዐይን አየ፡፡ ዐይኖቹ በእንባ ተሞሉና በለሆሳስ “የሚያየኝን አየሁት” አላቸውና እግራቸው ሥር ተደፋ፡፡ 

ሊቀ ጠበብት በርከክ አሉና በፍቅር አቀፉት “ልጄ ስምህ ማነው?” ብለው ጠየቁት፡፡ 

“ሰጥአርጋቸው” አለ አንገታቸው ውስጥ እንደተሸጎጠ፡፡ ሕዝቡ ገና ግራ በመጋባት ማጉረምረም ጀምሯል፡፡ ሊቀ ጠበብት በፍፁም ፍቅር ግንባሩን ሳሙና “እኔስ “ምሕረት” ብዬሀለሁ” አሉት፤ የእጁን የወርቅ ካቴና ሊያወልቅ ሲታገል እያገዙት እግዚአብሔር ይፍታህ ልጄ እግዚአብሔር ይፍታህ ይላሉ፤ ደጋግመው፡፡ 

/ምንጭ፦ ሐመር 17ኛ ዓመት ቁጥር 6/ 

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

መምሪያው ለቤተክርስቲያን ወጣቶች ተፈጠረ እንጂ ወጣቶች ለመምሪያው አልተፈጠሩም

/ምንጭ፦ሐመር መጽሔት 19ኛ ዓመት ቁጥር 2 ሰኔ 2003ዓ.ም/

ለመንጋው ምሳሌ ሁኑ እንጂ ማኅበሮቻችሁን በኃይል አትግዙ 1ጴጥ. 5፣ 3

ቤተክርስቲያናችን በዚህ ዘመን ትኩረት ሰጥታ ልትፈጽማቸው ከሚገባት ተግባራት አንዱ፤ ወጣቶች በቤተክርስቲያን ውስጥ ያላቸውን አገልግሎት ከመቼውም ጊዜ በላይ ማሳደግና ቤተ ክርስቲያን የምትሰጠውን መንፈሳዊ አገልግሎት ተጠቃሚ እንዲሆኑ ማድረግ ነው፡፡ ይህ ጉዳይ ትኩረት እንዲሰጠው የሚያደርጉ በርካታ ነገሮች አሉ፡፡ በዋናነት ግን ሥጋዊው ዓለም በቤተክርስቲያን ወጣቶች ሃይማኖታዊ ሕይወትና  መንፈሳዊ አኗኗር ላይ እያሳደረ ያለው ጫና ነው፡፡ ከመረጃ ቴክኖሎጂ ማደግና እርሱን ተከትሎ እየሰፋና እያደገ የመጣው የሉላዊነትና ዘመናዊነት አሉታዊ ገጽታ ባመጣው ግፊት፤ ወጣቶች ባሏቸው ክርስቲያናዊ ኑሮና እሴቶች ላይ ፈተና ደቅኖባቸዋል፡፡

በርካቶች የዚህ ጫና ሰለባ በመሆን ለብ ወዳለ አኗኗር ራሳቸውን እየለወጡ ነው፡፡ ሌሎች ደግሞ ዓለሙን መስለው፣ የክርስትናን አስተምህሮ ሸርሽረው፣ ሕግና ትእዛዛቱን አሽቀንጥረው ጥለው ለሥጋ ፍላጎታቸው በሚመች መንገድ በራሳቸው ማስተዋል ባቋቋሟቸው ቤተ እምነቶች ወስጥ ታቅፈዋል፡፡ ይህም ሆኖ እንኳን ትክክለኛ ሃይማኖታቸውን ከልብ የተረዱና የዘመኑ የክህደት ማዕበል የተረዳቸው በርካታ ወጣቶች ያንን በመቋቋም የራሳቸውን ሕይወት ለመጠበቅና የቤተክርስቲያንን አስተምህሮ፣ ትውፊትና ሥርዐት እንደተከበረ ለቀጣይ ትውልድ ለማሸጋገር እየተጉ ነው፡፡ ለዚህም በየአጥቢያው ባሉ ሰንበት ትምህርት ቤቶችና ማኅበራት ገብተው ሕግና ሥርዐት በሚፈቅደው መንገድ አገልግሎት እየሰጡና እየተቀበሉ ይገኛሉ፡፡ ይሁንና ጊዜው ከሚጠይቀው ምላሽና ጥረት አንጻር እየተጫወቱ ያሉት ሚና በቂ አይደለም፡፡ ይሄ ውስንነት የተፈጠረው ግን በወጣቶቹ የተሳትፎ ፍላጎት ማጣት ሳይሆን፡፡ የወጣቶቹን ዘርፈ ብዙ የአገልግሎት ፍላጎት በቅልጥፍናና በበቂ ሁኔታ እምነትም በሚጣልበት አመራር ማስኬድ አለመቻሉ ነው፡፡

እንደሚታወቀው ቤተክርስቲያን የአጠቃላዩን የወጣቶች አገልግሎት አሰጣጥና አቀባበል፣ ውጤታማ ለማድረግ እንዲቻል የሰንበት ትምህርት ቤቶች ማደራጃ መምሪያ አቋቁማ ለዓመታት እየሠራች ቆይታለች፡፡ መምሪያው በተለያዩ ጊዜያት የተለያዩ ተግባራትን እያከናወነ ቢቆይም አሁን እያደገ ላለው የወጣቶች ተሳትፎ በሚመጥን ደረጃ ግን ራሱን ለውጧል ማለት አይቻልም፡፡ የዚህ ችግር መሠረታዊ ምክንያት ደግሞ የቤተክርስቲያን ወጣቶችን የጊዜውን በጎ ፍላጎት ከግምት ያስገባ፣ ወጣቶች ያሉባቸውን ችግሮች ተደራሽ ያደረገ፣ ርእይና ተልእኮውን በውል ያስቀመጠ፣ መነሻና መድረሻው የሚታወቅ ስልታዊ ዕቅድ ያለው፣ ወጣቶች ለሀገርም ለቤተ ክርስቲያንም ዕድገት አዎንታዊ ሚና እንዲጫወቱ ለማድረግ የሚያስችል አቅም የያዘ አለመሆኑ ነው፡፡ መምሪ ያው አፈጻጸሙ እንዲዳከምና የሚፈለ ገውን አስተዋጽኦ እንዳያበረክት ያደረ ገው የመምሪያው ሓላፊ በራሳቸው አቅምና ፍላጎት ብቻ አሠራሩን ለመገደብ ስለሚጥሩ ነው፡፡

በዚህም ምክንያት አሁን ባለው በራሱ በማደራጃው አቅም ልክ ብቻ የወጣቶች ተሳትፎ እንዲወሰን ሲጥር እንጂ ከእርሱ እየቀደመ ስላለው የሰን በት ትምህርት ቤቶችና የማኅበራት እንቅስቃሴ በሚመጥን ሁኔታ የራሱን አቅምና የአገልግሎት አሰጣጥ ሲያሳ ድግ አይታይም፡፡ እንደውም እንዲቀጭጭ የሚፈልግ አካል በውስጡ መኖሩ ጉዳዩን የበለጠ አሳሳቢ አድርጎ ታል፡፡ ይህም ሁኔታ ማኅበረ ቅዱሳን እያደረገ ባለው ዘርፈ ብዙ እንቅስቃሴ ላይ እየፈጠረ ያለው መሰናክል ለዚህ እንደ ማስረጃ የሚጠቀስ ነው፡፡

ማኅበረ ቅዱሳን በመላው ሀገሪቱ ያለውን የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የመስፋፋት ዕድል ተጠቅሞ በየተቋማቱ ያሉትን የቤተክርስቲያን ወጣቶች በሃይማኖታዊ ሕይወታቸው ጸንተው እንዲቀጥሉና አስቀድመን የጠቀስናቸውን የዓለምን ወጣቶች እየተፈታተኑ ካሉ ዘመን አመጣሽ ጾሮች እንዲድኑ ለማ ድረግ እየሠራ ነው፡፡ ለዚህም የቤተ ክርስቲያናችንን ትምህርት አሰጣጥ መሠረት ያደረገ ሥርዐተ ትምህርት ቀርጾ መዋቅሩንም አጠናክሮ እየተራመደ ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪ በአጥቢ ያዎችና በሰንበት ትምህርት ቤቶች ባለው ተሳትፎ አባላቱ ጉልህ ሚና እን ዲጫወቱ እያደረገም ነው፡፡ ስብከተ ወንጌል እንዳይዳከም ገዳማትና አድባ ራት እንዳይዘጉ፣ የአብነት ትምህርት ቤቶች እንዳይበተኑ፣ የቤተክርስቲያን ክብሯ፣ ታሪኳ እንዳይደፈር ለማድረግ በስፋት እየተንቀሳቀሰ ነው፡፡ ሌሎችም ሰንበት ትምህርት ቤቶችና ማኅበራት በዚህ ደረጃ አገልግሎት መስጠት በሚ ያስችል ደረጃ ላይ ደርሰው ቤተክርስቲያናችን ከጌታዋ የተሰጣትን መንፈሳዊ አደራ በብቃት እንድትወጣ ጠንክሮ እየሠራ ነው፡፡

ይህ በእንዲህ እያለ ነው በተደጋጋሚ እየተሰማ እንዳለው የማደራጃ መመሪያው ሓላፊ በተለያዩ ሚዲያዎች ተገቢ ያልሆነና አንድ መምሪያ አገልግሎት በሚሰጣቸው አካላት ላይ ሊፈጽመው የማይገባ ስም ማጥፋት እየፈጸሙ የሚገኙት፡፡ ነገሩን የበለጠ አስገራሚ የሚያደርገው ደግሞ አገልግሎት እንዲሰጣቸው ታስቦ በሥሩ እየተንቀሳቀሱ በመላው ሀገሪቱ ላሉ ሰንበት ትምህርት ቤቶች ይህ ነው የሚባል ተጨባጭ ለውጥ የሚያመጣ ሥራ አለመሠራቱ እየተነገረ ባለበት ሁኔታ ውስጥ መሆኑ ነው፡፡ በቤተክርስቲያኒቱ ውስጥ አገልግሎት የሚሰጡና የሚቀበሉ ወጣቶች ለሀገርም ለቤተክርስቲያንም ፍሬ ያለው ተግባር እንዲፈጽሙ ለማበረታታት ፈቃደኝነት የማይታይበት መምሪያ የአገልግሎት ፍጥነት እየተጠየቀ ባለበት በዚህ ዘመን የማኅበረ ቅዱሳንን አገልግሎት ለማዘግየት መነሣቱ ከላይ ለጠቀስነው ለመምሪያው የመምራት ብቃት ማነስ ዐቢይ ምስክር ነው፡፡

የዚህም መነሻ ጌታችን ሰንበት ለሰው ተፈጠረ እንጂ ሰው ለሰንበት አልተፈጠረም እንዳለው ሥርዐት፣ መዋቅር፣ ሕግ፣ ደንብ፣ መመሪያ ለክርስቲያኖች ሰላም ለሰውም በጎ ፈቃድ የሚዘጋጅ መሆኑን በውል ያለማጤን ችግር ነው፡፡ በተለይ የመምሪያው ሓላፊ ችግር ሰንበት ትምህርት ቤቶችና ማኅበራት ለመምሪያው የተፈጠሩ እንጂ መምሪያው ለእነርሱ የተፈጠረ አድርጎ ያለማሰብ እንደሆነም እናስባለን፡፡ ይህ ደግሞ ሰንበት ትምህርት ቤቶችንና ማኅበራትን የማገልገል ሳይሆን የመግዛት፤ በግለሰቦች ፈቃድም ላይ ተደግፈው እንዲሔዱ የማስገደድ ዝንባሌን አስከትሏል፡፡ ይህ እየተባባሰ ከመጣ ደግሞ ወጣቶች ዓለሙ እያስከተለባቸው ባለው ጫና ላይ የታከለ የውስጥ ፈተና ስለሚሆን ጥያቄ ማስከተሉ አይቀርም፡፡ ስለዚህ በሰንበት ትምህርት ቤቶችና በማኅበራት ታቅፈው የጊዜያቸውን ፈተና ለመቋቋም ለተሰለፉ፣ የሚሰጣቸውን ሃይማኖታዊ አገልግሎት በጉጉት ለሚጠባበቁ ወጣቶች ቤተክርስቲያን የአገልግሎት አሰጣጧን በመፈተሽ ማስተካከያ ማድረግ አለባት እንላለን፡፡ ለዚህ ስምረት ደግሞ የአጥቢያ አብያተ ክርስቲያናትን ተሞክሮ ማየቱ ጠቃሚ ይሆናል፡፡

ለዚህም ችግሮችን ከመቅረፍና ዘመኑን የዋጀ ተአማኒነት ያለው አሠራር ከመዘርጋት አንጻር የሚመለከታቸው የቤተ ክህነቱ አካላት ገንቢ የሆነ ሚና ሊጫወቱ ይገባል፡፡ በተለይ የሰንበት ትምህርት ቤት ወጣቶችና ማኅበራት የልባቸውን የሚያደርስ፣ ቤተክርስቲያንን የሚፈለገው ስኬታማ ደረጃ ላይ ለማድረስ የምናደርገውን እልህ አስጨራሽ እንቅስቃሴ የሚያፋጥን አመራር ማደራጃ መምሪያችን እንዲሰጥ ግፊት ማድረግ አለብን፡፡

ከምንም በላይ ሰንበት ትምህርት ቤቶችና ማኅበራት የማደራጃ መምሪያው አገልግሎት ተቀባዮች በመሆናቸው አገልግሎት የሚሰጣቸውን መምሪያ በሚያቅደው ዕቅድ ላይ የመወያየት፣ በአጠቃላይ የአፈጻጸም ሪፖርቱን የመገምገም፣ በየጊዜው ያለበትን አቅም እየፈተሹ በደካማ አሠራሩ የማሻሻያ አስተያየት የመስጠት ወዘተ ሓላፊነትና ክርስቲያናዊ ግዴታችንን መወጣት ይኖርባቸዋል፡፡ ቃለዐዋዲው ባስቀመጠው መሠረት የተሰጠውን ሓላፊነት ለመወጣት በየደረጃው ላሉ የማደራጃ መምሪያው ተወካዮች በቂ ድጋፍ እየሰጠ ተግባሩን ለማከናወን የሔደበትን ርቀት መለካት ይገባናል፡፡ ተጠሪ ለሆነለት አካል ብቻ ሳይሆን አገልግሎት ሊሰጣቸው ቃልኪዳን ለተቀበለባቸው ሰንበት ትምህርት ቤቶችና ማኅበራትም ሪፖርት እያቀረበ የሚመዘንበትን አሠራር ለማስፈን መጣር ይኖርብናል፡፡

በዋናነትም ቅዱስ ሲኖዶስ ለማደራጃ መምሪያው ሊቀ ጳጳስ በመመደብ የጀመረውን ትኩረት የመስጠት እንቅስቃሴ፤ በቀጣይም የአገልግሎት ተቀባዮቹን የማኅበራትና የሰንበት ትምህርት ቤቶች አስተያየትና በጎ ፍላጎት ተቀብሎ እየመከረ ማስተካከያ በመስጠት ሊያጠናክረው እንደሚገባ ማሳሰብ ይጠበቅብናል፡፡ ቤተክርስቲያን ይህን ታላቅ ሓላፊነት የጣለችበትን መምሪያ በብቁ የሰው ኃይል፣ የበጀትና የማቴሪያል አቅምም እንዲኖረው ትኩረት ሊሰጠው ይገባል እንላለን፡፡ ቤተ ክርስቲያናችን ከእነዚህ ማኅበራትና ሰንበት ትምህርት ቤቶች ተነጥላ የምትሰጠው አገልግሎት፤ ለአገልግሎቱ የምታስተባብረው ቅድሚያ የሚሰጠው አካል አለ ብለን እናምንም፡፡ ወጣቶች የዛሬዋ ቤተክርስቲያን ብርቱ አገልጋዮች ለነገው ትውልድ ከማስረከብ አንጻርም የቤተክርስቲያን ማኅበረሰቡ እምብርት ናቸው፡፡

ስለዚህ ማኅበራትና ሰንበት ትምህርት ቤቶች የሚኖረንን ድርሻ ከማስጠበቅ አንጻር በየደረጃው ካለው የቤተክርስቲያን አስተዳደር አካላት ጋር በመምከር በዚሁ ረገድ ያለንን የጸና አቋም ለብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት ባገኘነው አጋጣሚ ሁሉ በመግለጽ አገልግሎታችንን የሚያስተባብረው መምሪያ የአገልግሎት ተቀባዮችን በጎ ፍላጎት መሠረት ያደረገ ያአሠራር ማሻሻያ እንዲደረግበት፡፡

ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት የቤተክርስቲያኒቱ የተለያዩ መምሪያ ሓላፊዎችና ሠራተኞች በየደረጃው ባሉ መዋቅሮች ያሉ የቤተክርስቲያኒቱ አስተዳደር አካላት ሰንበት ትምህርት ቤት ማደራጃ መመሪያ እንቅስቃሴ አሁን እያደገ የመጣውን የቤተክርስቲያኒቱ ወጣቶች የአገልግሎት ተሳትፎን የሚመጥን አለመሆኑንና ከዚህም አልፎ በመምሪያው በሓላፊነት ያሉ አንዳንድ ግለሰቦች አፍራሽ በሆነ እንቅስቃሴዎች ውስጥ በመግባታቸው ያለውን አሠራር መሸከም የማይቻልበት ደራጃ ላይ እየተደረሰ መሆኑን እንዲረዱን ይፈለጋል፡፡

ብዙ ማኅበራትና ሰንበት ትምህርት ቤቶችንም እያደራጀ ውጤታማ ሥራ ከመሥራት ይልቅ፤ የተደራጁትም እንዲፈርሱ፣ ለግለሰቦች ግልጽና ስውር ፍላጎት እንዲንበረከኩ፣ ከእግዚአብሔር ይልቅ ለሰው እንዲታዘዙ ለማድረግ ጥረት እየተ ደረገ ነው፡፡ በዚሁ ሁሉ ምክንያት ወጣቶች ጊዜው ካስከተለባቸው ፈተና በላይ በአሠራርና በቢሮክራሲ ስም ከፈተናው ለማምለጥ ከተሰበሰቡበት መርከብ ለማስወጣት የሚደረገው ጥረት አሳሳቢ ሆኖ ይገኛል፡፡ ስለዚህ አስቀድመን የጠቀስናቸው የቤተ ክርስቲያኒቱ አስተዳደር አካላት በማደራጃ መምሪያው ስም የሚንቀሳቀሱ አንዳንድ ግለሰቦችን ሩጫ በመግታት ረገድ ከፍተኛ ሚና ሊጫወቱ ይገባል፡፡ የቤተክህነት ወገኖች የሚያከብሯቸውን፣ ተከብረውም እንዲኖሩ የሚፈልጉ ወጣት የሰንበት ትምህርት ቤትና ማኅበራት አባላትን ጥያቄዎችና ስሜቶች በአግባቡ እያጤኑ መሔድ የቤተክህነቱ ወገኖች ሁሉ ሓላፊነት ነው፡፡ ይህም በዘላቂነት ከምእመናን ጋር ቤተክህነቱ ለሚያደርገው ግንኙነትና አጠቃላይ አገልግሎት አሰጣጥ ስኬት ወሳኝ መሆኑን ተረድተው የመምሪያው አሠራሮች እንዲስተካከሉ መምከር አለባቸው እንላለን፡፡ ቤተክርስቲያንን ለትውልድ ለማስረከብ ተረካቢውን ትውልድ ትኩረት ሰጥቶ በአግባቡ  መቅረጽና ማደራጀት ተገቢ ነውና፡፡

ማኅበረ ቅዱሳን አባላቱ በጋራም፣ በተናጠልም በየአጥቢያ ሰንበት ትምህርት ቤቱና በመዋቅራቸው የሚያደርጓቸውን አገልግሎቶች በስፋት የማስቀጠሉን ጥረት አጠናክረው እንደሚሔዱ እየገለጸ ለአጠቃላዩ የወጣቶች የአገልግሎት ተሳትፎ ማደግና ችግሮችን ለመቅረፍ በሚደረገው ጥረት ከመቼውም ጊዜ በላይ አሁን በትጋት እየተንቀሳሱ መሆኑን መግለጽ ይፈልጋል፡፡

የመዝሙር ዐውደ ርዕይ ተከፈተ

  በዲ/ን ቴዎድሮስ ኃይሉ 
ሰኔ 29፣ 2003 ዓ.ም
 
ማኅበረ ቅዱሳን የአዲስ አበባ ማዕከል ትምህርትና ሐዋርያዊ አገልግሎት የመዝሙር ንዑስ ክፍል የተዘጋጀ የመዝሙር ዐውደ ርዕይ ሰኔ 28/2003 ዓ.ም በሊቀ ትጉኃን ቀሲስ ዶክተር ሙሉጌታ ስዩም እና በመዝገበ ጥበባት ጌትነት በማኅበረ ቅዱሳን ሕንጻ ላይ ተከፈተ፡፡  
 
የመዝሙሩ ዐውደ ርዕይ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ጸዋትወ ዜማ፤ የዜማ ይትበሃል፤ የዜማ (የመዝሙር) መሣሪያዎችና ምሥጢራዊ ምሳሌነታቸውን፤ የአማርኛ መዝሙራት እንዲሁም ማኅበረ ቅዱሳን በመዝሙር ዙርያ ያከናወናቸው ተግባራትን ያስቃኛል፡፡
በመጀመሪያው ትዕይንት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ጸዋትወ ዜማ በሚል÷ በውስጡ የቅዱስ ያሬድን የዜማ ስልት(ዓይነት)፤ የቅዱስ ያሬድን የዜማ ድርስቶች እና የዜማ ምልክቶች እንዲሁም ቅዱስ ያሬድ ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ያደረገው አስተዋጽኦ የቀረበበት ነው፡፡ ሁለተኛው ትዕይንት በውስጡ ስለ የዜማ ይትበሃል፣ ምንነትና ታሪካዊ አመጣጥ ያስቃኛል፡፡ የሦስተኛው ትዕይንት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን የዜማ (የመዝሙር) መሣሪያዎችና ምስጢራዊ ምሳሌነታቸውን የሚቀርብበት ነው፡፡ አራተኛው ትዕይንት ስለ አማርኛ መዝሙር ምንነትን ፣ የመዝሙር ጥቅምን ፣ የአማርኛ መዝሙር አጀማመርና መስፈርቶች ፣ አሁን ያለበት ሁኔታ እና መዝሙርን ሁሉ እንዳገኘን ብንዘምር ምን ችግር ያስከትላል የሚሉ ንዑሳን ርዕሶች ተካተዋል፡፡ የመጨረሻው ትዕይንት ማኅበረ ቅዱሳን በመዝሙር ዙርያ ያከናወናቸውን ተግባራት ያስቃኛል፡፡

ዐውደ ርዕዩ አባቶቻችን ያቆዩልንን የቤተ ክርስቲያን አሻራ የሆነውን ዜማችንን የሚያሳውቅ፣ የሰንበት ት/ቤቶች መዝሙር አሁን ያለበትን ደረጃ የሚያሳይ እንዲሁም በመዝሙር ዙሪያ ላሉ ችግሮች የመፍትሔ ሐሳብ የሚወሰድበት ነው፡፡

በዕለቱ አንዳንድ እንግዶች አስተያየት የሰጡ ሲሆን ከነዚህ መሀል መዝገበ ጥበባት ጌትነት እንዳሉት ‹‹ያየሁት ለሰሚ ድንቅ ነው፡፡ ብዙዎች ቢያዩት መልካም ነው›› ሲሉ ሊቀ መዘምራን ኪነጥበብ ወልደ ቂርቆስ በበኩላቸው ‹‹ያለው የነበረው የቀረበበት›› ዐውደ ርዕይ ነው ብለዋል፡፡

 
ከዝግጅቱ አስተባባሪ ወ/ት ገነት አባተ እንደተረዳነው ዝግጅቱ ከሰኔ 29/2003 ዓ.ም እስከ ሐምሌ 3/2003 ዓ.ም ከጠዋቱ 2፡30 እስከ ምሽቱ 2፡30 ለምዕመናን ክፍት ሆኖ የሚቆይ ሲሆን÷ በመዝጊያው ዕለት ሐምሌ 3/2003 ዓ.ም ከ7፡30 እስከ 11፡30 ለየት ያለ ዝግጅት እንደሚኖር ነግረውናል ፡፡

ማኅበረ ቅዱሳን በመዝሙር ዙሪያ ዐውደ ርዕይ ሲያዘጋጅ ይህ የመጀመሪያው ነው፡፡
                                                           

የወልደ ነጎድጓድ ልጆች እንቅስቃሴ

በፈትለወርቅ ደስታ
 ሰኔ 28ቀን 2003ዓ.ም

 

ጊዜው ትውልዱ በሶሻሊዝም ፍልስፍና እየተሳበ የነበረበት ነበር፡፡ 1960ዓ.ም ማለትም የዛሬ 43 ዓመት ሆነ፡፡ የቤተ ክርስቲያኗ አስተዳደር የነበሩት መምህር መዘምርና መምህር ዘውዴ የቅዱስ ዮሐንስ ወልደ ነጎድጓድ ሰንበት ትምህርት ቤትን እንደመሠረቱት የሚነገረው በዚህ ጊዜ ነው፡፡ ሕፃናትንና ወጣቶችን በመሰብሰብ ምሥረታው አሐዱ የተባለው ሰንበት ትምህርት ቤት አሁን በሕይወት የሌሉት ብፁዕ አቡነ ያዕቆብ የቅርብ ክትትል ይደረግለት ነበር፡፡ ብፁዕነታቸው የደብሩ አስተዳዳሪ በነበሩበት ወቅት አባላትን እንደልጅ እየኮተኮቱና እየተንከባከቡ ያሳድጓቸው ነበር፡፡ ቅዳሜና እሑድ የሚሰጠውን የትምህርት መርሐ ግብር የሚመጡትንም /የሚመደቡትን/ መምህራንና የሚያስተምሩትን ትምህርት በመቆጣጠርና በማረም ሰንበት ትምህርት ቤቱን ጥሩ ደረጃ ላይ አድርሰውታል፡፡

የትምህርት መርሐ ግብር

ሥርዓተ ትምህርት በመቅረጽ ለምዕመናን ጥሪ በማድረግ የሚያስተምረው ሰንበት ትምህርት ቤቱ በዓመት ሁለት መርሐ ግብሮች አሉት፣ በበጋና በክረምት የሚከናወኑ፡፡ ከሰኞ እስከ አርብ በማታው መርሐ ግብር እንዲሁም ቅዳሜና እሑድ ደግሞ በቀን መርሐ ግብር ለምእመናን የቤተ ክርስቲያን ትምህርት ያስተምራል፡፡ የተማሪዎችንም የክረምት እረፍት ተከትሎ ተጠናክሮ ይካሄዳል፡፡

በእድሜ ክልል በመክፈል ቀዳማይ፣ ካልዓይና ሣልሳይ በማለት የአንድ ዓመት ኮርሶችን ያስተምራል፡፡ ትምህርተ ሃይማኖት፣ ክርቲያናዊ ሥነ ምግባር፣ ታሪክ በመጽሐፍ ቅዱስ፣ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት፣ የቤተ ክርስቲያን ታሪክ ለዓለም መድረክና በኢትዮጵያ፣ ምሥጢራተ ቤተ ክርስቲያን እንዲሁም የዮሐንስ ወንጌል አንድምታ ከሚሰጡት ውስጥ ይጠቀሳሉ፡፡

ከጥሩ ተሞክሮዎቹ

ይህን ያህል የገነነ ተሞክሮ የለንም በማለት በትሕትና የሚገልጡት የሰንበት ትምህርት ቤቱ ሰብሳቢ አቶ አበበ ሥዩም ጥቂቶቹን ይገልጻሉ፡፡

ከአዲስ አበባ ወጣ ካሉ ሰንበት ትምህርት ቤት ጋር ጥሩ ግንኙነት እንደመሠረቱ የሚገልጡት አቶ አበበ ኪናዊ የሆነ ሥራዎችን በማዋስ፣ ልምድ ለማካፈል እንደሚያግዟቸው ይናገራሉ፡፡

በነሐሴ 16 እና የካቲት 16 ዓመታዊ የኪዳነ ምሕረት በዓላት ወደ ፍቼ ኪዳነ ምሕረት በመጓዝ ሙሉ መርሐ ግብር በመሸፈን አገልግሎት ይሰጣል፡፡ ነገር ግን አሁን አሁን ቀዝቀዝ በማለቱ ለማጠናከር ጥረት እየተደረገ ነው ይላሉ ሰብሳቢው፡፡

በቤተ ክርስቲያንና በሰንበት ትምህርት ቤቱ ላይ ፈተና ሲመጣ መባ ይዞ በመሄድ ወይም በመላክ በጸሎት እንዲያስቡ ያደርጋሉ ሰንበት ትምህርት ቤቱ በራሱም የጸሎትና የጉባኤ መርሐ ግብር በማዘጋጀት በቂ ግንዛቤ ያስጨብጣል፡፡ አብዛኛው ምእመን ሱባኤ በመያዝ በየገዳማቱና የገጠር አብያተ ክርስቲያናት በሚያሳልፍበት በጳጉሜን ወር ትምህርት ጸሎትና ምክረ አበው በማዘጋጀት እንዲያሳልፍ ያደርጋል፡፡ ይሄም የሚናፈቅ እንደሆነ የሰንበት ትምህርት ቤቱ አባላት ይገልጻሉ፡፡

የአብነት ትምህርትን በማስተማር በኩል ሊጠቀስ የሚችል ሥራ ሠርቷል፣ ሰንበት ትምህርት ቤቱ እንደ ዲያቆን ወሳኙ ገለጻ ሰንበት ትምህርት ቤቱ የአብነት ትምህርት ማስተማር ከጀመረ ወደ ሰባት ዓመት አስቶጥሯል፡፡ በእነዚህ ጊዜያት ወደ 20 የሚጠጉ ዲያቆናት አፍርቷል፡፡ በአሁኑ ጊዜ በደብሩም ውስጥ የሚያገለግሉ አሉ፡፡ ቢሆንም የሚጠበቅበትን ያህል እየሄደ እንዳልሆነ የሚገልጹት ዲያቆን ወሳኙ ከዚህ በፊት የነበሩት አንድ መምህር ብቻ መሆናቸውና እርሳቸውም ደጅ ጠኚ ሆነው በትራንስፖርት /በመጓጓዣ/ አበል ብቻ ያስተምሩ እንደነበር ነው፡፡ ትምህርቱም ሥርዓተ ትምህርት ተቀርጾለት አለመሰጠቱ ሌላው ችግር ነው፡፡ ይህም የተፈለገውን ያህል ለማስፋፋት እንዳላስቻለ ይገልጻሉ ዲ/ን ወሳኙ፡፡

ሰንበት ትምህርት ቤቱ ለአብነት ትምህርቱ ምእመናን እንዲሳተፉ ቅስቀሳ የሚካሄደው የደብረ ታቦር ዕለት ነው፡፡ የቆሎ ትምህርት ቤትን ገጽታ የሚያሳይ ኪናዊ ሥራ በማሳየት አውደ ምሕረት ላይ ቅስቀሳ ይደረጋል፡፡ ምንም እንኳን በርካታ ወጣቶች ቢመዘገቡም፤ ጥቂቶች ብቻ ለውጤት እንደሚበቁ ይገልጻሉ ዲ/ን ወሳኙ፡፡ አሁን ግን ቤተ ክርስቲያኗ የአብነት መምህር በመቅጠሯ የተሻለ የመማር እድል አለ፡፡

የወደፊት እቅድ

በጅምር ላይ ያለው የሰንበት ትምህርት ቤቱ አዳራሽ ሲያልቅ በውስጡ የእደ ጥበብ ሥራዎችን በማምረት ያከፋፍላል፣ ይሸጣል፣ ከሌሎች ሰንበት ትምህርት ቤቶችና ማኅበራት ጋር በመቀናጀት ሙያዊ ሥልጠናዎችን፣ ተሞክሮዎችንና ድጋፍ ካገኘ በኋላ የልማት ሥራዎችን ይሠራል፡፡

በመጪዎቹ አሥር ዓመታት ውስጥ የአብነት ትምህርት ቤቱን በማጠናከር አብነት መር የሆነ ሰንበት ትምህርት ቤት ለመፍጠር እቅድ አለ፡፡ ይህንንም ለመፈጸም ጥናቱን አጠናቆ ተግባራዊ ይደረጋል ብለዋል ዲ/ን ወሳኙ፡፡

ሁሉም ሰንበት ትምህርት ቤቶች እጅ ለእጅ ተያይዘን አንዲት ቤተ ክርስቲያንን ለማገልገል ቆርጠን መነሣት አለብን በማለት የሚያሳስቡት የሰንበት ትምህርት ቤቱ አቶ አበበ ስዩም በአሁኑ ጊዜ ቤተ ክርስቲያን የገጠማትን ከበድ ያለ ወቅታዊ ፈተና ያነሣሉ፡፡

“ቤተ ክርስቲያን እውነት በመያዟ ልትፈተን የግድ ነው፡፡ ነገር ግን የተፈጠረባትን ፈተና እንዲጋፈጡ ለተወሰኑ ሊቃነ ጳጳሳት፣ መምህራንና ማኅበራትና ሰንበት ትምህርት ቤቶች የመተው ሁኔታ አለ፡፡ ይሄ ደግሞ ፈተናውን የከፋ እንዲሆን ያደርገዋል፡፡” በማለት ዲ/ን ወሳኙ ያክላሉ፡፡ ቤተ ክርስቲያንን እኛ የምንታደጋት የሚቀርባት ስላለ ሳይሆን እኛ የሚቀርብን ስላለ ነው፡፡ የድርሻችንን አውቀን መወጣት እንጂ የእነ እገሌ ብሎ ለሌላ መስጠት ተገቢ አይደለም በማለት ያሳስባሉ፡፡

በቅዱስ ዮሐንስ ቤተ ክርስቲያን ምድር ቤት ፊት ለፊት ደረጃው ሥር ባሉ ክፍሎች በመሰባሰብ የተጀመረው ሰንበት ትምህርት ቤቱ፣ ቀጥሎም በክርስትና ቤት፤ የአባላት ቁጥር ሲጨምርም ትልቅ የቆርቆሮ ቤት በመሥራት እንዲቀጥል ሆኗል፡፡ በእግዚአብሔር ፈቃድ የያኔው ተክል እያበበ እያፈራ 43 ዓመቱን ያከበረው ባለፈው ከግንቦት 19 እስከ 21 ቀን 2003 ዓ.ም ለሦስት ቀናት በተዘጋጀ መርሐ ግብር ነበር፡፡ የሰንበት ትምህርት ቤቱ የኪነ ጥበብ ክፍል ከላሊበላ አርቲስቶች ጋር በመተባበር “ተዋሕዶ” በሚል ርዕስ ያዘጋጁትን ድራማ ለምእመናን አቅርበዋል፡፡ በሦስቱ ቀን መርሐ ግብር የልማትና የጸሎት ክፍል የጸሎት መርሐ ግብር አዘጋጅቶ ነበር፡፡ የቤተ ክርስቲያንን ወቅታዊ ጉዳይና አጽራረ ቤተ ክርስቲያንን በተመለከተም በጉባኤው ላይ ለታደሙት ምእመናንና ተጋባዥ እንግዶች መረጃ እንደደረሰ ዲ/ን ወሳኙ ዘውዴና አቶ አበበ ስዩም ገልጸዋል፡፡

ትምህርተ ጦም በሊቃውንት

ሰኔ 24/2003 ዓ.ም.

 በዲ/ን ሽመልስ መርጊያ
 
በዚህ ጽሑፍ ጦምን አስመልክቶ የቅዱሳን አባቶችን አስተምህሮ እንመለከታለን
 
አንድ የገዳም አበምኔት  አንድ ወቅት አባ ጳይመን የሚባሉትን አባት “እግዚአብሔርን መፍራት እንዴት ገንዘቤ ማድረግ ይቻለኛል” ብለው  ይጠይቋቸዋል፡፡ እሳቸውም ሲመልሱ “እንዴት ሰው በላመና በጣፈጠ መብልና መጠጥ ሆዱን እየሞላ እግዚአብሔርን መፍራት ገንዘቡ ሊያደርግ ይችላል? ስለዚህም ጦም እግዚአብሔርን ወደመፍራት ይመራል፡፡ የጦም የመጨረሻ ግቡ እግዚአብሔርን ወደመፍራት ማምጣት  ነው”  ብለው ይመልሱላቸዋል፡፡
 
አንድ ወቅት አንድ ጠዋሚ በጦም ወቅት ማልዶ ይርበዋል፡፡ እናም ከሦስት ሰዓት በፊት ላለመመገብ ከፍላጎቱ ጋር ይሟገታል፡፡ ሦስት ሰዓትም ሲሆን እንደምንም ብሎ እስከ ስድስት ሰዓት ሊቆይ ይወስናል፡፡ ስድስት ሰዓት ደርሶ ሊመገብ ማዕዱን በቆረሰ ጊዜ እንደገና ለራሱ እስከ ዘጠኝ ሰዓት ልቆይ ብሎ በመናገር ምግቡን ከመመገብ ይከለከላል፡፡ ዘጠኝ ሰዓት ላይ ጸሎቱን አድርሶ ሊመገብ ሲል ሰይጣን ልክ እንደጭስ ከሰውነቱ ሲወጣ ታየው ወዲያው ረሃቡ ጠፋ፡፡
 

እየጦምክ ነውን? ለተራበ አብላ ፣ለተጠማም አጠጣ፣ ሕመምተኞችን ጎብኝ፣ የታሰሩትን ጠይቅ፣ በመከራ ላሉት እራራላቸው፣ በጭንቀት ወድቀው የሚያለቅሱትን አጽናናቸው፣ ርኅሩኅ፣ ትሑት፣የዋህ፣ ሰላማዊ፣ አዛኝ፣ይቅር ባይ፣ እውነተኛ እና ታማኝ ሁን፡፡ እንዲህ ከሆንክ እግዚአብሔር ጦምህን ይቀበልልሃል፡፡ ስለንስሐም ብዙ የንስሐ ፍሬን ይሰጥሃል፡፡ ጦም ለነፍስ ምግብ ነው፡፡

 ቁጣ መቼም ቢሆን የሚመከር አይደለም፤በተለይ በጦም ሰዓት ከቁጣ መራቅ ተገቢ ነው፡፡ ትሕትናንና ፣የዋሃትን ገንዘብህ አድርግ፤ክፉ ፈቃዶችንና አሳቦችን ተቃወማቸው፤ ራስህን መርምር በየእለቱ ወይም በሳምንት ውስጥ ምን መልካም እንደሠራህ አእምሮህን ጠይቀው፡፡ እንዲሁም ምን ስሕተትን ፈጽመህ እንደነበርና ስሕተትሕን ደግመህ እንዳትፈጽም የመፍትሔህ እርምጃዎች ምን ሊሆኑ እንዲገባቸው አሰላስል፡፡ ጦምህ እንዲህ ሊሆን ይገባዋልና፡፡

ምግብ ሰውነትን እንደሚያሰባ እንዲሁ ጦም ነፍስን ከሥጋ አስተሳሰብ ተላቃ ወደ ላይ በመነጠቅ ሰማያዊ ነገሮችን ለመመርመርና ከምድራዊ ደስታ ይልቅ እጅግ ግሩም የሆነ ደስታን ለማግኘት ጥንካሬን ይሰጣታል፡፡

 አርባ ቀን ሙሉ ከምግብ ተከልክዬ ጦምኩ አትበለኝ፡፡ ይህንና ያንን አልበላሁም ወይንም ከአፌ አልገባም አትበለኝ፡፡ እኔ ይህንን ካንተ አልሻም፣ ነገር ግን ከቁጣ ርቀህ ታጋሽ መሆንህን አሳየኝ፤ ከጭካኔህ ተመልሰህ አዛኝ ወደመሆን እንደመጣህ አሳየኝ፡፡ ነገር ግን ቁጣ የሞላብህ ከሆነ ስለምን ሥጋህን በጦም በከንቱ ትጎስማታለህ ? ሰዎችን ሁሉ የምትጠላና ስስታም ከሆንክ ለአንተ ከምግብ ተከልክለህ ውሃ ብቻ መጠጣትህ ምን ትርፍ ያመጣልሃል?

ጦም እጅግ ግሩም የሆነ ነገር ነው፡፡ ኃጢአታችንን እንደማይጠቅም አረም ከውስጣችን ይነቅለዋል፡፡  እውነተኛው የጽድቅ ተክልም  በውስጣችን ልክ እንደ አበባ እንዲያብብ ይረዳዋል፡፡ (ቅዱስ ባሲልዮስ)

ጸሎት፣ ጦም ፣ትጋህ ሌሊት እና ሌሎችም አንድ ክርስቲያን የሚተገብራቸው ክርስቲያናዊ ተግባራት ምንም መልካሞች ቢሆኑ የክርስቲያናዊ ሕይወት ግቦች ግን አይደሉም፡፡ ነገር ግን ወደ ትክክለኛው ክርስቲያናዊ ሕይወት ለመድረስ የሚያገለግሉን መንፈሳዊ ትጥቆች ናቸው፡፡ትክክለኛው የክርስቲያን ግብ መንፈስ ቅዱስ በእርሱ ሰውነት ውስጥ ሥራ እንዲሠራ በመፍቀድ የመንፈስ ቅዱስ ፍሬዎችን አፍርቶ መገኘት ነው፡፡በዚህ ምድር የመንፈስ ቅዱስ ፍሬዎች ማፍራት እስካልቻልን ድረስ የእግዚአብሔርን መንግሥት መውረስ አይቻለንም፡፡ (ቅዱስ ሱራፊ)

የአዋጅ ጦም ሲገባ መንፈሳዊ የበጋ ወራቱ እንደገባ ልብ እንበል፡፡ ስለዚህም የጦር መሳሪያችንን እንወለውለው  ከእርሻቸው አዝመራውን የሚሰበሰቡትም ገበሬዎች ማጭዳቸውን ይሳሉ፤ ነጋዴዎችም በከንቱ ገንዘባቸውን ከማባከን ይከልከሉ፣ መንገደኞችም ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ለመግባት መንገዳቸውን ያቅኑ፡፡ ወደ እግዚአብሔር መንግሥት የምትወስደው ጎዳና ቀጭንና ጠባብ ናትና በጥንቃቄ እያስተዋላችሁ ተጓዙ፡፡

እንዲያው በልማድ ሰዎች እንደሚፈጽሙት ዓይነት ጦም ትጦሙ ዘንድ አልመክራችሁም፡፡ ነገር ግን ከምግብ ስለምንከለከልባት ጦም ብቻ ሳይሆን ከኃጢአት ስለምንከለከልባት  እውነተኛይቱ ስለሆነችው ጦም እጽፍላችኋለሁ፡፡ ጦም በባሕርይዋ በሕግ ካልተመራች  ለሚተገበሩዋት ሰዎች ዋጋን አታሰጥም፡፡ ስለዚህም ጦምን ለመጦም ስንዘጋጅ የጦም ዘውድ የሆነውን ነገር መዘንጋት የለብንም፡፡ ስለዚህ ስለምን ያ በእግዚአብሔር ቤተመቅደስ ደጅ ሆኖ ጸሎቱን ያደረሰው ፈሪሳዊ ከእግዚአብሔር ዘንድ ስለጦሙ አንዳች ዋጋ ሳያገኝ በባዶው እጁ እንደተመለሰ መረዳት ተቀዳሚ ተግባራችን ሊሆን ይገባዋል (ሉቃ. ፲፰፥፱-፲፬(18፡9-14))፡፡ ቀራጩ አልጦመም ነገር ግን ጸሎቱ ተሰምቶለታል፡፡ ጦም ሌሎች አባሪ የሚሆኑ መልካም ሥራዎች ካልታከሉበት በቀር ልክ እንደዚኛው ፈሪሳዊ ዋጋ አያሰጠንም፡፡

ጦም ማለት መድኃኒት ማለት ናት፡፡ እንደ ሌሎቹ መድኃኒቶች ሁሉ ጦምን እንዴት እንደሚጠቀምበት የሚያውቅ ሰው ዋጋ ያገኝበታል፡፡ በጥበብ ላልተጠቀመበት ሰው ግን የማይረባና የማይጠቅም ይሆንበታል፡፡ ከጦም የሚገኘው ክብር ከምግብ በመከልከላችን ምክንያት የምናገኘው ብቻ አይደለም፡፡ ከኃጢአት ሥራዎችም ፈጽመን በመከልከላችን ምክንያት የምናገኘው ክብር ጭምር ነው ፡፡ ጦም ሰይጣን ወደ እኛ እንዳይቀርብ እንደጋሻ የሚያገልግለን መሣሪያ ነው፡፡ ነገር ግን በጦም ሰዓት ኃጢአትን ፈቅደን የምንሠራት ከሆነ ሰይጣን አጥሩን ጥሶ እንዲገባና በእኛ ላይ እንዲሠለጥን ምክንያት እየሆንነው ነው፡፡ ጦማችን ከምግብ በመከልከል ብቻ የተወሰነ ከሆነ ጦምን እናስነቅፋታለን፡፡

እየጦምክ ነውን ? መጦምህን በሥራህ ገልጠህ አሳየኝ፡፡ ድሃው እርዳታህን ፈልጎ እንደሆነ ቸርነትን አድርግለት፡፡ ጠላት ያደረግኸውን ካየኸው ከእርሱ ጋር ፈጥነህ ታረቅ፡፡ ጓደኛህ ተሳክቶለት ካየኸው በእርሱ ላይ ቅናት አይደርብህ፡፡ አፍህ ብቻ አይጡም ዐይንህም ጆሮህም እግርህም እጅህም የሰውነትህ ሕዋሳቶች ሁሉ ክፉ ከማድረግ ይጡሙ፡፡

እጆችህ ከዝርፊያና ከሕግ ውጪ ለመክበር ሲባል ትርፍን ከማጋበስ ይጡሙ፡፡ እግሮችህ የኃጢአት ሥራን ለመፈፀም ከመፋጠን ይጡሙ፡፡ ዐይኖችህም ውጫዊ በሆነ ውበት ምክንያት ከመቅበዝበዝ ይጡሙ፡፡ የሚታዩ ነገሮች ለዐይን ምግቦች ናቸው፡፡ ነገር ግን ከእግዚአብሔር ሕግ ጋር የሚጣረሱ ምልከታዎች ጦምን ያፈርሳሉ፡፡ነፍስንም እንድትነዋወጥ ያደርጉአታል፡፡ የምናያቸውን ነገሮች ከእግዚአብሔር ሕግ ጋር የሚስማሙ ከሆኑ ጦማችንን ያስጌጡዋታል፡፡ በጦም ምክንያት በጦም ሰዓት መመገብ የተከለከሉትን ምግቦች መመገብ የሚያስነቅፍ ከሆነ ፤ እንዴት ታዲያ በዐይናችን እንድንመለከተው በሕግ የተከለከልነውን ነገር መመልከታችን ይበልጥ አያስነቅፈን ? ምግብን ከመብላት ተከልክለሃልን? እንዲሁ ለሰውነትህ ጎጂ የሆኑ ነገሮችን በዐይንህም በጆሮህም ከመመገብ ተከልከል፡፡ ጆሮ የምትጦመው ለኃጢአት ከሚጋብዙ ክፉ ወሬዎችና ሐሜትን ከመስማት ነው፡፡ “ሐሰተኛ ወሬን አትቀበል ሐሰተኛ ምስክርም ትሆን ዘንድ ከኃጢአተኛ ጋር እጅህን አታንሣ፡፡”እንዲል(ዘጸአ.፳፫፥፩(23፡1))

አፍህም ከከንቱ ንግግር ይጡም ፡፡ ከአሣና በጦም ሰዓት መመገብ ከተከለከልናቸው የፍስክ ምግቦች ተከልክለን ወንድሞቻችንንና እኅቶቻችንን በክፉ ቃላችን ሕሊናቸውን የምናቆስልና በሐሜት ሥጋቸውን የምንበላ ከሆነ ከጦማችን ምን ዋጋን እናገኛለን? ክፉ ተናጋሪ የወንድሙን አካል ያቆስላል ሥጋውንም ይበላል፡፡ ስለዚህም ቅዱስ ጳውሎስ ይህን አስመልክቶ  እጅግ የሚያስደነግጥ ንግግርን ተናገረ “ሕግ ሁሉ በአንድ ቃል ይፈጸማልና እርሱም፡- ባልንጀራህም እንደ ራስህ ውደድ  የሚል ነው፡፡ ነገር ግን እርስ በእርሳችሁ ብትነካከሱና ብትበላሉ እርስ በእርሳችሁ እንዳትጠፋፉ ተጠንቀቁ፡፡(ገላ.፭፥፲፭(5፡15))ብሎ አስጠነቀቀን፡፡

ስለታሙ የሐሜት ጥርስህ የሚያርፈው በወንድምህ ሥጋ ላይ ሳይሆን ነፍስ ላይ ነው፡፡ በዚህም ጥርስህ ወንድምህን በእጅጉ ትጎዳዋለህ፡፡ እንዲህ በማድረግህ አንተም እርሱንም ሌሎችንም ብዙ ሺህ ጊዜ ትጎዳቸዋለህ፡፡ በሐሜትህ አንተን የሚሰማህ ባልንጀራህ የሐሜት ተባባሪ ይሆናል፡፡ በዚህም ምክንያት እርሱንም በደለኛ ታደርገዋለህ፡፡ እርሱም በእርሱ ላይ ከነገሠበት ኃጢአት የተነሣ ለሌላ ለወዳጁ ምን መርጦ ማውራት እንዳለበት ሳያውቅ ከሐሜተኞች ጎራ ይቀላቀላል፡፡እንዲህ ዓይነት ሰው ጻድቅ ልንለው እንችላለንን? እንዲህ ዓይነት ሰው  በመጦሙ ትልቅ የጽድቅ ሥራን እንደፈጸመ ቆጥሮ ይኩራራል፡፡ ሰዎችን ወደ ኃጢአት እየመራ ትልቅ ሥራን እንደሠራ ሰው ራሱን በከንቱ ያስኮፍሳል፡፡ ከዚህ ጎን ለጎን ሊታይ የሚገባው ትልቁ ቁም ነገር ስለቤተክርስቲያን ጥቅም ሲባል የእንዲህ ዓይነቱን ሰው ንግግር ከመስማት መከልከል እንደሚገባ ነው፡፡ ምክንያቱም የዚህ ሐሜተኛ ወሬ እርሱን ብቻ ኃጢአተኛ የሚያሰኝ ጉዳይ ሳይሆን ቤተክርስቲያንንም ጭምር የሚያሰድብ ነውና፡፡

ስለዚህ በጦም ሰዓታችሁ ጊዜም ይሁን አይሁን  ሦስት ነገሮችን በሕሊናችሁ ትይዙ ዘንድ እመክራችኋለሁ፡፡ እነርሱም ክፉ ከመናገር መከልከልን፣ ማንንም ሰው እንደጠላት ከማየት መቆጠብንና እንደልምድ አድርጋችሁ ከያዛችሁት መሐላ ትርቁ ዘንድ እመክራቸኋለሁ፡፡

በአጨዳ ላይ ያለ ገበሬ እህሉን ከእርሻው ላይ በአንዴ እንዳይሰበስብ ነገር ግን ጥቂት በጥቂት እንዲሰበስብ እኛም እነዚህን ምክሮች ተግባራዊ በማድረግ በዚህ የጦም  ወቅት ልንለማመዳቸው እና መልካም ልምዶቻችን ልናደርጋቸው ይገባናል፡፡ እንዲህም በማድረጋችን በቀላሉ መንፈሳዊ ጥበብን ገንዘባችን ማድረግ ይቻለናል፡፡ በዚህም ዓለም ሳለን መልካም ተስፋ ያለውን አዝመራ እናፈራለን፡፡በሚመጣውም ዓለም በክርስቶስ ፊት ያለፍርሃት በደስታ ተሞልተን እንድንቆም ይረዱናል፡፡ ለእግዚአብሔር መንግሥት የሚያበቃንን ጸጋ አግኝተን የክብሩ ወራሾች ያድርገን፤ ለአብ ለወልድ ለመንፈስ ቅዱስ ክብር ምስጋና ይሁን ዛሬም ዘወትርም እስከዘላለሙ አሜን፡፡

 ጦም የጤንነት እናት፣ የፍቅር እኅት፣ የትሕትና ወዳጅ ናት፡፡ ሕመሞች አብዛኛውን ጊዜ ያለቅጥ ከመመገብ የሚመነጩ ናቸው፡፡ (ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ)

ከምግባራት ሁሉ ታላቁ ጸሎት ነው ነገር ግን የእርሱ መሠረቱ ጦም ነው፡፡የምንጦምበት ምክንያት ርኩስ የሆነውን የሰይጣንን መንፈስ በነፍሳችን ውስጥ እንዳያድር ለመጠበቅ ነው፡፡ ሥጋችንን ለጦም ባስገዛነው ጊዜ ነፍሳችን ነፃነትን፤ ጥንካሬን ሰላምን ፣ንጽሕናን እንዲሁም እውቀትን ለመለየት እንድትበቃ ትሆናለች፡፡ (ጻድቁ ዮሐንስ ዘክሮስታንድ)

እውነተኛ ጦዋሚ ራሱን ከክፉ ምግባራት የከለከለ፤ ከንቱ የሆኑ ንግግሮችን ከመናገር የተቆጠበ፣ ሐሰትን የማይናገር፣ ሐሜተኛ ያልሆነ፣ በማንም ላይ የማይፈርድ፣ሽንገላን የማይወድና እኒህንም ከመሰሉ ነገሮች ራሱን የተጠበቀ ፣የማይቆጣ፣ የማይበሳጭ ፣ተንኮለኛ ያልሆነ ፣ ቂመኛ ያልሆነና፣ እነዚህን ከመሳሰሉ ክፋቶች ሁሉ የራቀ ሰው ነው፡፡

ሕሊናህ ኃጢአትን  ከማሰብ ይጡም፡ አእምሮህም ኃጢአትን ከማስታወስ ይከልከል፡፡ ክፉን ከመመኘት ሁሉ ጡም፡፡ ዐይኖችህ ከንቱ የሆኑ ነገሮችን ከመመልከት፣ ጆሮህም ከንቱ ከሆኑ ዘፈኖችና ከሐሜተኞች ሹክሹክታዎች ጠብቅ፡፡ አንደበትህ ከሐሜት፣ በሌላው ላይ ከመፍረድ ፣ከስድብ፣ ከውሸት ፣ከማታለል፣ከሽንገላ ንግግሮች እንዲሁም ከማይጠቅሙና አጸያፊ ከሆኑ  ቃላት ይጡሙ፡፡ እጆችህም ሰውን ከመግደልና የሌላውን ንብረት ከመዝረፍ ይጡሙ፡፡ እግሮችህም ኃጢአትን ለመፈጸም ከመሄድ ይጡሙ፡፡ ከክፉ ተመለስ መልካምንም ፈጽም፡፡ (ቅዱስ ኤፍሬም)

 ጦም ምን እንደሚያደርግ ትመለከታለህን? ሕመምን ይፈውሳል ፣አጋንንትን ያስወጣል፣ ክፉ አሳቦችን ከአእምሮ ያስወግዳቸዋል፣ ልብንም ንጹሕ ያደርጋታል፡፡ አንድ ሰው በክፉ መንፈስ የተያዘ ቢሆን  እንዲህ ዐይነት መንፈስ በጦምና በጸሎት እንደሚወጣ ያስተውል፡፡ ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ “ይህ ዓይነት ግን ከጸሎትና ከጦም በቀር አይወጣም” እንዳለው (ማቴ. ፲፯፥፳፩(17፡21)) (ቅዱስ ቲክሆን)

የአርባ ቀን ጦም የሥጋ ፍትወታትን ይገድላቸዋል፣ቁጣንና ብስጭትን ከሰውነታችን ያስወግዳቸዋል፣  ከሆዳምነት ከሚመነጩ የትኞቹም ነገሮች ሁሉ ነፃ ያወጣናል፡፡ በበጋ ወራት ፀሐይ ከነሙሉ ኃይሉዋ እንድትወጣና ምድርንም በሙቀቱዋ እንደምታግል በላዩዋም የበቀሉ አትክልቶችን እንደምታደርቅ፤ ከሰሜን የሚነፍሰውም ነፋስ የደረቁትን ሳሮች እንደሚጠርጋቸው፤  እንዲሁ በጦም ወቅትም አብዝቶ በመመገብ የበቀሉትን የሥጋ ፍትወታት ይወገዳሉ፡፡ (ቅዱስ አትናቴዎስ)

ቅዱሳን ጠዋሚዎች ጽኑ ወደሆነው የጦም ሥርዓት የገቡት ወዲያው አይደለም፡፡  በጥቂት ምግብ ወደ መጥገብ የመጡት ቀስ በቀስ ነው፡፡ እነዚህ ቅዱሳን ኃጢአትን ፈጽመው አያውቋትም፡፡ ሁልጊዜ ለመልካም ሥራ እንደተፋጠኑ ነው፡፡ በእነርሱ ዘንድ ሕመም አይታወቅም እድሜአቸውም  ከሰው ሁሉ በተለየ የረዘመ ነው፡፡ (ቅዱስ አግናጢዎስ)

ጦም  የሰውን እድሜ አያሳጥርም ፣ ቅዱስ ቄርሎስ ዘአንኮራይት በ108 እድሜው አረፈ፡፡ ቅዱስ እንጦስም 105 ዓመት ሙሉ ኖሮአል፡፡ ቅዱስ መቃርስ ዘእስክንድሪያ የኖረበት እድሜ 100 ዓመት ነበር ፡፡ (ቅዱስ አውግስጢኖስ)

አርባውን ቀን መጦምን ቸል አትበሉ፡፡ ምክንያቱም ክርስቶስን የምንመስልበት ሕይወት ከዚህ ጦም እናገኛለንና፡፡ (ቅዱስ እንጦስ)

ወስብሐት ለእግዚአብሔር