የቅድስት ምንባብ 3(ሐዋ.10÷17-30 )

ጴጥሮስም ስለ አየው ራእይ ምን እንደሆነ ሲያወጣና ሲያወርድ ከቆርኔሌዎስ ተልከው የመጡ ሰዎች የስምዖንን ቤት እየጠየቁ በደጅ ቁመው ነበር፡፡

ተጣርተውም፡- ጴጥሮስ የተባለ ስምዖን በእንግድነት በዚያ ይኖር እንደሆነ ጠየቁ፡፡ ጴጥሮስም ስለ ታየው ራእይ ሲያወጣ ሲያወርድ መንፈስ ቅዱስ እንዲህ አለው÷ “እነሆ÷ ሦስት ሰዎች ይፈልጉሃል፡፡ ተነሥና ውረድ፤ ምንም ሳትጠራጠር ከእነርሱ ጋር ሂድ፤ እኔ ልኬአቸዋለሁና፡፡” ጴጥሮስም ወደ እነዚያ ሰዎች ወረደና÷ “እነሆ÷ የምትፈልጉኝ እኔ ነኝ፤ ለምን መጥታችኋል?” አላቸው፡፡ እነርሱም÷ “የመቶ አለቃ ቆርኔሌዎስ እግዚአብሔርን የሚፈራ ጻድቅ ሰው ነው፤ ቅዱስ መልአክ ተገልጦ አንተን ወደ ቤቱ እንዲጠራህ የምታስተምረውንም እንዲሰማ አዝዞታል፤” አሉት፡፡ እርሱም ተቀብሎ አሳደራቸው፤ በማግሥቱም ተነሥቶ አብሮአቸው ሄደ፤ በኢዮጴ ከተማ ከሚኖሩት ወንድሞችም አብረውት የሄዱ ነበሩ፡፡ በማግሥቱም ወደ ቂሳርያ ከተማ ገባ፤ ቆርኔሌዎስም ዘመዶቹንና የቅርብ ወዳጆቹን ጠርቶ ይጠብቃቸው ነበር፡፡ ጴጥሮስም በገባ ጊዜ ቆርኔሌዎስ ተቀበለው፤ ከእግሩ በታችም ወድቆ ሰገደለት፡፡ ጴጥሮስም÷ “ተነሥ እኔም እንደ አንተው ሰው ነኝ” ብሎ አነሣው፡፡ ከእርሱም ጋር እየተነጋገረ ገባ፤ ወደ እርሱም የመጡ ብዙ ሰዎችን አገኘ፡፡ ጴጥሮስም እንዲህ አላቸው÷”ለአይሁዳዊ ሰው ሄዶ ከባዕድ ወገን ጋር መቀላቀል እንደማይገባው ታውቃላችሁ፤ ለእኔ ግን ከሰው ማንንም ቢሆን እንዳልጸየፍና ርኩስ ነው እንዳልል እግዚአብሔር አሳየኝ፡፡ አሁንም ስለ ላካችሁብኝ ሳልጠራጠር ወደ እናንተ መጣሁ፤ በምን ምክንያት እንደ ጠራችሁኝ እጠይቃችኋለሁ፡፡”

የቅድስት ምንባብ 2(1ኛጴጥ.1÷13-ፍጻ. )

ስለዚህ የልቡናችሁን ወገብ ታጥቃችሁና ነቅታችሁ ኑሩ፤ ኢየሱስ ክርስቶስም ሲገለጥ የምታገኙትን ጸጋ ፈጽማችሁ ተስፋ አድርጉ፡፡

እንደሚታዘዙ ልጆች ባለማወቃችሁ አስቀድሞ የኖራችሁበትን ክፉ ምኞት አትከተሉ፡፡ ነገር ግን የጠራችሁ ቅዱስ እንደ ሆነ እንዲሁ እናንተም በአካሄዳችሁ ሁሉ ቅዱሳን ሁኑ፡፡ “እኔ ቅዱስ ነኝና ቅዱሳን ሁኑ” የሚል ተጽፎአልና፡፡ ለሰው ፊትም ሳያዳላ በእያንዳንዱ ላይ እንደ ሥራው የሚፈርድ አብን የምትጠሩት ከሆነ በሕይወታችሁ ዘመን ሁሉ በፍርሀት ኑሩ፡፡

ከአባቶቻችሁ ከወረሳችሁት ከማይረባና ከማይጠቅም ሥራችሁ የተቤዣችሁ በሚጠፋ በወርቅ ወይም በብር እንዳይደለ ታውቃላችሁ፡፡ ነውርና እድፍ እንደ ሌለው እንደ በግ ደም በክርስቶስ ክቡር ደም ነው እንጂ፡፡ ዓለም ሳይፈጠር የታወቀ÷ በኋላ ዘመን ስለ እናንተ የተገለጠ፡፡ ከሙታን ለይቶ በአስነሣው÷ ክብርንም በሰጠው በእግዚአብሔር በእርሱ ቃል ያመናችሁ÷ አሁንም እምነታችሁና ተስፋችሁ በእግዚአብሔር ይሁን፡፡

ሳትጠራጠሩ በፍጹም ልቡናችሁ ወንድሞቻችሁን ትወድዱ ዘንድ÷ ለእውነት በመታዘዝ ሰውነታችሁን አንጹ፤ እርስ በእርሳችሁም ተፋቀሩ፡፡ ዳግመኛ የተወለዳችሁት ከሚጠፋ ዘር አይደለም፤ በሕያውና ለዘለዓለም በሚኖር በእግዚአብሔር ቃል ከማይጠፋ ዘር ነው እንጂ፡፡

የቅድስት ምንባብ1(1ኛ ተሰ.4÷1-13)

አሁንም ወንድሞቻችን ሆይ÷ በእኛ ዘንድ እንደ ታዘዛችሁ በሚገባ ትሄዱ ዘንድ÷ እግዚአብሔርንም ደስ ታሰኙ ዘንድ÷ ደግሞ እንደ ሄዳችሁ ከፊት ይልቅ በዚሁ ታበዙና ትጨምሩ ዘንድ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ እንነግራችኋለን፤ እንማልዳችኋለንም፡፡ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስም ያዘዝናችሁን ትእዛዝ ታውቃላችሁ፡፡ የእግዚአብሔር ፈቃድ ይህ ነውና፤ እርሱም ከዝሙት ትርቁ ዘንድ መቀደሳችሁ ነው፡፡ ሁሉም እያንዳንዱ ገንዘቡን ይወቅ፤ በንጽሕናና በክብርም ይጠብቀው፡፡ እግዚአብሔርን እንደማያውቁት እንደ አረማውያንም በፍትወት ድል አትነሡ፡፡ ይህንም ለማድረግ አትደፋፈሩ፤ በሁሉም ወንድሞቻችሁን አትበድሉ፤ አስቀድሜ እንደ ነገርኋችሁና እንደ አዳኘሁባችሁ÷ በዚህ ሁሉ እግዚአብሔር የሚበቀል ነውና፡፡ እግዚአብሔር ለቅድስና እንጂ ለርኲሰት አልጠራንምና፡፡ አሁንም የሚክድ÷ መንፈስ ቅዱስን የሰጣችሁን እግዚአብሔርን እንጂ ሰውን የካደ አይደለም፡፡

ባልንጀሮቻችሁን ስለ መውደድ ግን ልንጽፍላችሁ አያስፈልጋችሁም፤ እርስ በርሳችሁ እንድትዋደዱ ራሳችሁ በእግዚአብሔር የተማራችሁ ናችሁና፡፡ በመቄዶንያ ሁሉ ካሉት ወንድሞቻችን ሁሉ ጋር እንዲሁ ታደርጋላችሁ፤ ነገር ግን ወንድሞቻችን ሆይ÷ ትበዙና ትጨምሩ ዘንድ÷ ሥራችሁንም ታከናውኑ ዘንድ እንደ አዘዝናችሁም በእጃችሁ ትሠሩ ዘንድ÷ በውጭ ባሉት ሰዎችንም ዘንድ ከማንም አንዳች ሳትሹ በሚገባ ትመላለሱ ዘንድ እንለምናችኋለን፡፡

7ኛው ሀገር አቀፍ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት /ግቢ ጉባኤያት/ ሴሚናር ነገ ይጀመራል፡፡

(ሐሙስ የካቲት 24  2003 ዓ.ም. ) 
በእንዳለ ደጀኔ
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በሰ/ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ማኅበረ ቅዱሳን 7ኛውን የግቢ ጉባኤያት ተወካዮች ሴሚናር ከየካቲት 25-27 ቀን 2003 ዓ.ም አዲስ አበባ ላይ እንደሚያካሄድ አስታወቀ፡፡

የግቢ ጉባኤያት ማደራጃና ማስተባበሪያ ክፍል ሓላፊ ዲ/ን ተ/ብርሃን ገ/ሚካኤል እንደገለጹት በሴሚናሩ 310 የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት /የግቢ ጉባኤያት/  ተወካዮች የ41 ማእከላትና ወረዳ ማእከላት የግቢ ጉባኤያት ማደራጃና ማስተባበሪያ ክፍል ሓላፊዎች ይገኛሉ፡፡

ሴሚናሩም ማኅበሩ በ1984 ዓ.ም በቅዱስ ሲኖዶስ ጸድቆ በተሰጠው መተዳደሪያ ደንብ መሠረት በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት /ግቢ ጉባኤያት/ የሚገኙ የቤተ ክርስቲያን ልጆች በማስተማርና ለቤተ ክርስቲያን ተተኪ ትውልድ እንዲሆኑ ለማብቃት እየሠራ መሆኑን የሚያሳይ ነው፡፡

ሴሚናሩ በሚካሄድባቸው 3 ቀናት በሀገሪቱ ካሉ የከፍተኛ ተቋማት የግቢ ጉባኤያት ተወካዮች ሴሚናር ላይ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የልምድ ተሞክሮ፣ የአገልግሎት ስልትና መንፈሳዊ ሕይወት እንዲሁም በምግባረ ሰናይ ያላቸውን ተሳትፎ አጠናክረው የሚሔዱበትን አቅጣጫ መንደፍ የሚያስችል ውይይት እንዲደረግ ይጠበቃል፡፡

የግቢ ጉባኤያት ሴሚናር፣ ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተመርቀው የሚወጡ ተማሪዎች ቤተ ክርስቲያናቸውንና ሀገራቸውን በጥሩ ሥነ-ምግባርና በታማኝነት በተማሩበት ሙያ ለማገልገል የሚያስችል የተለያዩ የአገልግሎት ስልቶችን የሚረዱበት፣ ራዕይ ያላቸው፤ በገንዘባቸው፣ በዕውቀታቸውና በጉልበታቸው አስተዋጽኦ ሊያበረክቱ የሚችሉበትን አቅጣጫ የሚያውቁበት ሲሆን፣ ከተቋማቸው ማኅበረሰብ፣ ከአጥቢያ ሰ/ት/ቤቶችና ሰ/ጉባኤያት ጋር በመሆን የቤተ ክርስቲያንን ሁለንተናዊ አገልግሎት ለመፈፀም የሚዘጋጁበት እንደሚሆን ሓላፊው ገልፀዋል፡፡

ማኅበሩ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሥር ከተቋቋመበት ከ1984 ዓ.ም ጀምሮ፣ ዓለም አቀፍ መንፈሳዊና ማኅበራዊ አገልግሎት በመስጠት ላይ የሚገኝ ሲሆን በአሁኑ ወቅት በሥሩ የሚገኙ ከ120.000 በላይ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎችን የቤተ ክርስቲያንን ትምህርት እያስተማረ ይገኛል፡፡

ለ7ኛ ጊዜ በተዘጋጀው በዚሁ የግቢ ጉባኤ ተወካዮች ሴሚናር ቅዱስ ፓትሪያሪኩን ጨምሮ ሊቃነ ጳጳሳት፣ የጠቅላይ ቤተክህነት የመምሪያ ሓላፊዎች፣ የአዲስ አበባ ሃ/ስብከት የመምሪያ ሓላፊዎችና ጥሪ የተደረገላቸው የክብር እንግዶች ይገኛሉ፡፡

ለእግዚአብሔር በፍርሃት ተገዙ /መዝ 2፡11-12/

በዲ/ን አሉላ መብራቱ

 

የዐቢይ ጾም የመጀመሪያ ሳምንት (ዘወረደ) ለአጠቃላይ ጾሙ መግቢያ የሚሆኑ ሦስት መሠረታዊ ጉዳዮች ላይ ያተኮሩ ትምህርቶች(መልዕክቶች) ይተላለፉበታል። እነዚህን ቀጥለን እንመለከታለን።

1.    ስለ ጾም

ዘወረደ የታላቁ ጾም የመጀመሪያ ሳምንት ስለሆነ ቤተ ክርስቲያን የጾም አዋጅ ታውጅበታለች፤ ስለ ጾም ጥቅምና እንዴት መጾም እንዳለብን ታስተምረናለች፡፡ጾመ ድጓው “አከለክሙ መዋእል ዘኃለፈ ዘተቀነይክሙ ለግእዘ ሥጋክሙ፤ ለሥጋቸሁ ፈቃድ የተገዛችሁበት ያለፈው ዘመን ይበቃችኋል፤ ከአሁን በኋላ ግን ጹሙ፣ ጸልዩ ለእግዚአብሔር ተገዙ” እያለ የጾም አዋጅ ያውጃል።

ጾም ፈቃደ ስጋን ለፈቃደ ነፍስ፣ ፈቃደ ነፍስን ለፈቃደ እግዚአብሔር/ለመንፈስ ቅዱስ/ የምናስገዛበት መንፈሳዊ መሳሪያ ነው፡፡ጾሙ ይህ የሚደረግበት መሆኑን ቤተክርስቲያን ሳምንቱ በሚጀመርበት ሰንበት በሚሰበከው ምስባክ እንዲህ ብላ ታሳስባለች፤ “ለእግዚአብሔር በፍርሃት ተገዙ፣በረዓድም ደስ ይበላችሁ” /መዝ 2፡11-12/ ጾም ከምግብና ከመጠጥ እንዲሁም ከሌሎች ምቾቶችና ደስታዎች ከመከልከል ያለፈ ጥልቅ ትርጉም ያለው ተግባር ነው። ጾም ውጤታማ እንዲሆን እነዚህ መከልከሎች ከጸሎት ፣ ከፍቅርና ራስን ከማዋረድ ጋር መተባበር አለባቸውና በዚህ ሳምንት ቤተ ክርስቲያን እንዲህ እያለች ታስተምራለች፦“ንጹም ጾመ ወናፍቅር ቢጸነ ከመ ያብርህ ብርሃነ ስብሃቲሁ በላዕሌነ፤ (የእግዚአብሔር) የክብሩ ብርሃን በላያችን ላይ ያበራ ዘንድ ጾምን እንጹም ፤ወንድማችንንም እንውደድ”

(ጾመ ድጓ)።በዘወረደ እሁድ የሚነበቡት ምንባባትም ይህንን መልዕክት የያዙ ናቸው።“ነገር ግን ፈጣሪያችን የምትበልጠውን ጸጋ ይሰጣል፤ ስለዚህም “እግዚአብሔር ትዕቢተኞችን ይቃወማል፤ ለትሑታን ግን ጸጋን ይሰጣል” ይላል፡፡ እንግዲህ እግዚአብሔርን እሺ በሉት፤ ሰይጣንን ግን እንቢ በሉት፤ ከእናንተም ይሸሻል፡፡ እግዚአብሔርን ቅረቡት፤ ይቀርባችሁማል፤ እናንተ ኃጥኣን እጆቻችሁን አንጹ፤ ሁለት ዐሳብም ያላችሁ እናንተ ልባችሁን አጥሩ፡፡ እዘኑና አልቅሱ፤ ሳቃችሁን ወደ ልቅሶ÷ ደስታችሁንም ወደ ኀዘን መልሱ፡፡ በእግዚአብሔር ፊት ራሳችሁን ዝቅ አድርጉ፤ እርሱም ከፍ ከፍ ያደርጋችኋል፡፡” /ያዕ 4÷6-10/

 “ በውኑ እንግዲህ በስሙ እናምን ዘንድ የከንፈሮቻችን ፍሬ የሚሆን የምስጋና መሥዋዕትን በየጊዜው ለእግዚአብሔር ልናቀርብ አይገባንምን? ነገር ግን ለድሆች መራራትን÷ከእነርሱም ጋር መተባበርን አትርሱ፤ እንዲህ ያለው መሥዋዕት እግዚአብሔርን ደስ ያሰኘዋልና፡፡” /ዕብ 13÷15-16/

“ ልባችሁ በመብል ያይደለ በጸጋ ቢጸና ይበልጣልና፤ በዚያ ይሄዱ የነበሩ እነዚያ አልተጠቀሙምና ። ” /ዕብ. 13፥9/በጾም የተጠቀሙ ቅዱሳንን እያሰብን ለጾም እንድንተጋም ወደ እነርሱ እንድንመለከት ቤተክርስቲያን ትጠቁማለች፡፡ ሳምንቱ በሚጀምርበት ሳምንት የሚነበበው የቅዱስ ጳውሎስ መልዕክትእንዲህ ይላል፡፡

“የእግዚአብሔርን ቃል የነገሩአችሁን ዋኖቻችሁን አስቡ፥ የኑሮአቸውንም ፍሬ እየተመለከታችሁ በእምነት ምሰሉአቸው።” /ዕብ. 13፥7/ጾመ ድጓው ከእነዚህ መካከል ጥቂቶቹን እንዲህ እያለ ያስታውሰናል፤“የእግዚአብሔር የክብሩ ብርሃን በላያችን ላይ ያበራ ዘንድ ጾምን እንጹም፤ ወንድሞቻችንም እንውደድ፤ ኤልያስ በጾም ወደ ሰማይ አርጓልና፤ዳንኤልም ከአናብስት አፍ ድኗልና፡፡”

2.    ስለ እግዚአብሔር ወልድ መውረድ (ሥጋዌ)

ከዐቢይ ጾም ጀምሮ እስከ ጰራቅሊጦስ ድረስ ያሉት ዕለታት ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የሰውን ልጆች ለማዳን ያደረጋቸው ነገሮች (ማስተማሩ፣ ተአምራት ማድረጉ፣ በፈቃዱ ተላልፎ መሰጠቱ፣ ሞቱ፣ ትንሣኤው፣ ዕርገቱ፣ መንፈስ ቅዱስን መላኩ…) በስፋት የሚነገርባቸው ናቸው።

የእነዚህ ሁሉ ነገሮች መሠረትና ያገኘናቸው ጸጋዎች ሁሉ ምንጭ የእግዚአብሔር ወልድ መውረድ (ሰው መሆን) ነው።ይህ ሣምንት የዐቢይ ጾም የመጀመሪያ ሣምንት እንደመሆኑ ቀጥለው ለሚነገሩት ነገሮች መሠረት የሆነው ይህ የእግዚአብሔር መውረድ ይነገርበታል። ዘወረደ (የወረደው) የሚል ስያሜ የተሰጠውም ከዚህ በመነሳት ነው።

ሣምንቱ በሚጀመርበት ሰንበት የሚነበበው ወንጌል ይህን መልእክት የሚያስተላልፍ ነው።“እውነት እውነት እልሃለሁ፥ የምናውቀውን እንናገራለን ያየነውንም እንመሰክራለን፥ ነገር ግን ምስክርነታችንንም አትቀበሉትም። በምድር ያለውን ስነግራችሁ ካላመናችሁኝ፥ በሰማይ  ያለውን ብነግራችሁ እንዴት ታምኑኛላችሁ? ከሰማይ ከወረደው የሰው ልጅ  በቀር ወደ ሰማይ የወጣ የለም፥ እርሱም በሰማይ የሚኖረው ነው። ሙሴ በምድረ በዳ እባቡን እንደ ሰቀለው የሰው ልጅ እንዲሁ ይሰቀል ዘንድ አለው፡፡ያመነበት ሁሉ ለዘለዓለም ሕያው ሆኖ እንዲኖር እንጂ እንዳይጠፋ።በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘለዓለም ሕይወትን እንዲያገኝ እንጂ እንዳይጠፋ እግዚአብሔር አንድያ ልጁን ቤዛ አድርጎ እስኪሰጥ ድረስ ዓለሙን እንዲሁ ወዶታልና።” /ዮሐ. 3፥11-16/ጾመ ድጓው የሚጀምረውም እንዲህ በማለት ነው፣ “ዘወረደ እምላዕሉ፣ አይሁድ ሰቀሉ…. እግዚአ ኩሉ ዘየሀዩ በቃሉ፤ ….በቃሉ የሚያድነውን ከላይ የወረደውን የሁሉን ጌታ አይሁድ ሰቀሉት… ”

3. ስለ ትምህርት

 ዐቢይ ጾም የትምህርት ዘመን ነው። በጥንት ቤተ ክርስቲያን አዳዲስ አማንያን /ንዑሰ ክርስቲያን/ የሚጠመቁት በትንሣኤ በዓል ስለነበር በዐቢይ ጾም ሰፊ ትምህርት ይሰጣቸው ነበር።ዛሬም ዐቢይ ጾም ጌታችን በዚህ ምድር በእግረ ሥጋ በተመላለሰባቸው ዘመናት ያደረጋቸው  ነገሮች (ትምህርቱ፣ ተአምራቱ፣ ሞቱ፣ ትንሣኤው … ) በሣምንታት ተከፋፍለውና ተደራጅተው የምንማርበት የትምህርት ዘመን ነው። በአብነት ትምህርት ቤቶቻችንም ዐቢይ ጾም ዋነኛ የትምህርት ዘመን መሆኑ ይታወቃል።

ስለዚህም ቤተ ክርስቲያን የትምህርት ዘመን በሆነው ዐቢይ ጾም መግቢያ ላይ ስለ ትምህርትና ስለ መምህራን እንዲህ እያለች ትሰብካለች፤

“የእግዚአብሔርን ቃል የነገሩአችሁን ዋኖቻችሁን አስቡ፥ የኑሮአቸውንም ፍሬ እየተመለከታችሁ በእምነት ምሰሉአቸው። ኢየሱስ ክርስቶስ ትናንትና ዛሬ እስከ ለዘላለምም የሚኖር እርሱ ነውና። ሌላ ልዩ ትምህርት አታምጡ።” /ዕብ. 13፥7-9/

“ለመምህሮቻችሁ ታዘዙ፤ ተገዙላቸውም፤ስለ እናንተ በእግዚአብሔር ፊት ምላሽ የሚሰጡ እንደመሆናቸው፣ ይህን ሳያዝኑ ደስ ብሎአቸው ያደርጉት ዘንድ ስለ ነፍሳችሁ ይተጋሉና፡፡” /ዕብ. 13፥17/

አምላካችን እግዚአብሔር ሆይ መዋዕለ ጾሙን በሠላም አሳልፈህ የትንሣኤህን ብርሃን ለማየት እንድታበቃን እንለምንሃለን። አሜን።

2011-1.jpg

መጋቢት 11 ሲምፖዚየም

2011-1.jpg

ልጆች በቤተክርስቲያን

       በአዜብ ገብሩ

“ልጆቼ ኑ ስሙኝ እግዚአብሔርን መፍራት አስትምራችኋለሁ፡፡” መዝ 34÷11

ልጆች እንደምን ሰነበታችሁ? ዛሬ ቤተክርስቲያን ውስጥ ስንሆን ምን ማድረግ ምን ደግሞ አለማድረግ እንደሚገባን የሚያሳየን ታሪክ ይዘን ቀርበናል፡፡ በደንብ ተከታተሉን፡፡

በድሮ ዘመን ደብረ ቀልሞን በምትባል አካባቢ የሚገኙ ሕፃናት ቅዳሴ ሊያስቀድሱ ወደ ቤተክርስቲያን ሄዱ፡፡ በቅደሴ ጊዜም ወዲያና ወዲህ እያሉ ቅደሴ ሲረብሹ እግዚአብሔር በጣም አዘነባቸው፡፡ ከዚያም እነዚህ ያጠፋት ልጆችን እንዲቀጡ መላእክትን ከሰማይ ላከ፡፡ የተላኩትም መላእክት በታዘዙት መሠረት ያጠፉትን ልጆች እንዲቀጡ መላእክትን ከሰማይ ላከ፡፡ የተላኩትም መላእክት በታዘዙት መሠረት ያጠፉትን ልጆች ቀጥተው ሲመለሱ ከተላኩት መላእክት አንዱ ግን ልጆቹን በሚቀጣበት ሰዓት አንድ የሚያምር ልጅ አጋጠመውና አዘነለት፡፡ “ይህንንስ የፈጠረው ይቅጣው” ብሎ ተወው፡፡ ይህን በማድረጉና የእግዚአብሔርን ትዕዛዝ በመተላላፉ መልአኩ እንደሌሎች መላእክት ወደ ሰማይ ለማረግ አልቻለም፡፡ በዚያ ወድቆ ሳለ አንድ ዲያቆን ለአገልግሎት ወደ ቤተክርስቲያን ሲገባ አገኘው፡፡ ተጠግቶም “አንተ ምድራዊ ነህ ወይስ ሰማያዊ” ብሎ ጠየቀው፡፡ መልአኩም “ሥራዬ ምድራዊ አደረገኝ እንጂ ተፈጥሮዬስ ሰማያዊ ነው፡፡ ሄደህ ለካህኑ ንገርልኝና ይደልይልኝ፡፡” አለው፡፡ ዲያቆኑም ሄዶ ለካህኑ ነገረው፡፡ ካህኑም ከሥዕለ ማርያም ሥር ተደፈቶ እመቤታችንን እየተማፀነ ጸለየለት እመቤታችንም ከሥዕሏ ላይ ተገልጻ “በቀኝ እጅህ ቀኝ ክንፉን በግራ እጅህ ግራ ክንፉን ይዘህ በፈጣሪ በእግዚአብሔር ስም ተነሥ በለው” አለችው፡፡ ካህኑም እንደታዘዘው አደረገ፡፡ መልአኩም ኃይሉ ተመለሰለትና ወደ ሰማይ ዓረገ፡፡

አያችሁ ልጆች በቤተክርስቲያን ውስጥ ወዲህ ወዲያ ማለት፣ መረበሽ ማውራት ቅጣት ያስከትላል፡፡ እንደውም ልጆቹ ባጠፉት ጥፋት ቅጣቱ ለመልአኩም ተርፎት ነበር፡፡ እመቤታችን ከፈጣሪ አማልዳ መልአካዊ ኃይሉን ባታስመልስለት ኑሮ በጣም አሳዛኝ ሁኔታ ላይ ወድቆ ነበር፡፡ ስለዚህ ልጆች ወደ ቤተክርስቲያን ስትሄዱ ጥንቃቄ አይለያችሁ እሺ ገላችሁን ታጥጣችሁ፣ የታጠበ ንጹሕ ልብስ ለብሳችሁ፣ ነጠላችሁን መስቀለኛ ለብሳችሁ፣ ቅዳሴ ከመጀመሩ በፊት በቤተክርስቲያን ተገኝታችሁ፣ ወደቁርባን ስትቀርቡ በሥርዓቱ ሳትጋፉ ተራ ጠብቃችሁ መቁረብ ይገባል፡፡ አንግዲህ ልጆች ከዚህ ታሪክ ትምህርት በማግኘት እናንተ ሥርዓት አክባሪና ጨዋ ልጆች ሆናችሁ ለሌሎች ልጆች እንደምትመክሩና እንደምታስተምሩ ተስፋ እናደርጋለን፡፡ በሉ ደህና ሁኑ ልጆች፡፡