ለገዳሙ ካህናትና ዲያቆናት መሠረታዊ የኮምፒውተር አጠቃቀም ሥልጠና ተሰጣቸው

በይበረሁ ይጥና
በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የምስካየ ኅዙናን መድኃኔዓለም ገዳም የተምሮ ማስተማር ሰንበት ትምህርት ቤት ለስምንት ወራት በመሠረታዊ የኮምፒውተር ትምህርት ያሠለጠናቸውን አሥራ አምስት ካህናትና ዲያቆናት ጥር 30 ቀን 2002 ዓ. ም. አስመረቀ፡፡

የገዳሙ አስተዳዳሪ ቆሞስ መልአከ ፀሐይ አባ ገብረ ሥላሴ  በምረቃው መርሐ ግብር እንደተናገሩት፤ የቤተ ክርስቲያን አገልጋዮችን በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የታገዘ ትምህርት ማስተማር ዘመኑን የዋጀ አገልግሎት ለመስጠት ያስችላል፡፡ ትምህርቱን ያገኙት አባቶችም ሆኑ ዲያቆናት በኮምፒውተር ትምህርት መሠልጠናቸው የመረጃ ሥርዓትና ተዛማጅ ሥራዎች በዘመናዊ መልክ ለማከናወን እንደሚያግዛቸውም ተናግረዋል፡፡ ሰንበት ትምህርት ቤቱ ሥልጠናውን አዘጋጅቶ አባቶች፣ ዲያቆናትና የሰንበት ትምህርት ቤቱ ወጣቶች በአንድነት እንዲሠለጥኑ ማድረጉ ቤተ ክርስቲያንን በልማት ለማሳደግ ያለውን ርእይ እንደሚያሳይ ጠቁመው፤ ወደፊትም ከሰንበት ትምህርት ቤት ወጣቶች ቤተ ክርስቲያን ብዙ እንደምትጠብቅ ተናግረዋል፡፡

የሰንበት ትምህርት ቤቱ ምክትል ሰብሳቢ ዲያቆን ደረጀ ነጋሽ በበኩሉ፤ የመጀመሪያውን ዙር መሠረታዊ የኮምፒዩተር ሥልጠና ሠልጥነው ያጠናቀቁት፤ አንድ መነኩሴ፣ አሥራ ሦስት ዲያቆናትና አንዲት የሰንበት ትምህርት ቤት አባል ወጣት እንደሆኑ አስረድቷል፡፡ በሥልጠናው ወቅት ያገኙትም የትምህርት ዓይነት ኤም ኤስ ዊንዶ፣ ወርድ፣ ኤክሴል፣ አክሰስና የኢንተርኔት አጠቃቀም የተመለከቱ መሆናቸውን ሰብሳቢው ጠቁሞ፣ ሥልጠናው አገልግሎታቸውን ለማቀላጠፍ እንደሚረዳ አስታውቋል፡፡

ሥልጠናውን ለስምንት ወራት የሰጡት ቀደም ሲል በሰንበት ትምህርት ቤቱ ተኮትኩተው ያደጉ ወጣቶች ሲሆኑ፤ አሠልጣኞች በአሁኑ ጊዜ በኮምፒዩተር ሳይንስ ሙያ በተለያዩ ተቋማት የሚያስተምሩ አባላት እንደሆኑ ምክትል ሰብሳቢው አስረድቷል፡፡ ለወደፊትም ሥልጠናውን ከገዳሙም በተጨማሪ ወደ ሌሎችም አጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት በመሔድ ለአገልግሎትና ለሰንበት ትምህርት ቤት ወጣቶች ለመስጠት እቅድ መያዙን ተናግሯል፡፡

በምረቃ ሥነ ሥርዓቱ ላይ ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች የተገኙ ሲሆን በተለይ ቀደም ብሎ የሰንበት ትምህርት ቤቱ አባል የነበሩ አባቶች በሰጡት አስተያየት አባትና ልጅ በአንድ ሆነው መማራቸው በሰንበት ትምህርት ቤቱና በገዳሙ አባቶች መካከል ያለውን ፍቅርና አንድነት እንደሚያሳይ ገልጸዋል፡፡ሥራውም ለሌሎች ሰንበት ት/ቤት አርአያ እንደሚሆንም ተናግረዋል፡፡ ሰንበት ት/ቤቱ ከ1950 ዓ. ም. ጀምሮ እስከ 1993 ዓ. ም. ድረስ «ተምሮ ማስተማር ማኅበር» የሚል ስያሜን ይዞ ቤተ ክርስቲያንን እያገለገለ ነበር፡፡ ከ1993 ዓ. ም. ወዲህ «የተምሮ ማስተማር ሰንበት ት/ቤት» በሚል ስያሜ አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል፡፡

ለሕንፃ ቤተ ክርስቲያን ሥራ ድጋፍ ተጠየቀ

ደረጀ ትዕዛዙ

በሲዳማ ጌዴኦ አማሮና ቡርጁ ዞኖችና ልዩ ወረዳዎች ሀገረ ስብከት የሚገኘው የተፈሪ ኬላ ደብረ ስብሐት ቅዱስ በዓለ ወልድ ቤተ ክርስቲያን በእርጅና ምክንያት ከፍተኛ ጉዳት ላይ በመሆኑ አዲስ ሕንፃ ቤተ ክርስቲያን ለማነፅ ለተጀመረው ጥረት የድጋፍ ጥሪ ቀረበ፡፡

ባለፈው የጌታችን መድኃታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ልደት በተከበረበት ዕለት በቤተ ክርስቲያኑ በተከናወኑ ጉባኤ ላይ የሕንፃ አሠሪ ኮሚቴው ሰብሳቢ አቶ ሰብስቤ ካብት ይመር እንደገለፁት፤ ከአርባ ዓመት በላይ የሆነው ይህ ቤተ ክርስቲያን ያለ መሠረት የታነፀ ከመሆኑ በላይ በምስጥ እየተቦረቦረ ለመፍረስ እየተቃረበ ነው፡፡ በመሆኑም አዲስ ሕንፃ ቤተ ክርስቲያን ለማነፅ ባለፈው ዓመት የሕንፃ አሠሪ ኮሚቴ ተዋቅሮ ገንዘብ የማሰባሰቡ ሥራ እየተካኼደ መሆኑን የገለፁት ሰብሳቢው፤ እስካሁን ሰማንያ ሺሕ ብር ከምእመናን ማሰባሰብ መቻሉን ተናግረዋል፡፡

የአዲሱን ሕንፃ ቤተ ክርስቲያን ዲዛይን ማኅበረ ቅዱሳን ሠርቶ ለኮሚቴው ያስረከበ መሆኑን የጠቀሱት ሰብሳቢው፤ ሥራውን ለመጀመር በሚደረገው ጥረት በሀገር ውስጥና ውጪ ያሉ ምእመናን እንዲሁም በጎ አድራጊ ድርጅቶችና ማኅበራት ድጋፍ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል፡፡ በባንክ መላክ የሚፈልጉም በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ዲላ ቅርንጫፍ የባንክ ሒሳብ ቁጥር 15664   እንዲጠቀሙም ገልፀዋል፡፡

የቤተ ክርስቲያኑ አስተዳዳሪ መልአከ ገነት ተሾመ ወሰን በበኩላቸው፤ ሰበካ ጉባኤው፣ ሕንፃ አሠሪ ኮሚቴውና የወረዳው ቤተ ክህነት ከሕዝቡ ጋር በመተባበር ሕንፃ ቤተ ክርስቲያን ለማሠራት በብርቱ እንቅስቀሴ ላይ ናቸው፡፡ ሕንፃ ቤተ ክርስቲያን ለማሠራት የአካባቢው ሕዝብ አቅም ባይኖረውም ተሠርቶ የማየት ከፍተኛ ጉጉት እንዳለው አስተዳዳሪው ጠቅሰው በእስካሁኑ ሂደት ጥሩ ትብብር እያደረገ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በዚሁ በዓለ ንግሥ ዕለት ምእመናኑ ሃያ ሰባት ሺሕ ብር ድጋፍ ማድረጉ ታውቋል፡፡

ማኅበሩ የንብ እርባታ ፕሮጀክቱን አስረከበ

መቀሌ ማዕከል

ማኅበረ ቅዱሳን በማዕከላዊ ዞን አክሱም ሀገረ ስብከት ቆላተንቤን ወረዳ ለሚገኘው የእንደ እጨጌ ኪዳነ ምሕረት ገዳም ከሠላሳ ስድስት ሺሕ ብር በላይ ወጪ ያሠራው የንብ እርባታ ፕሮጀክት ተጠናቆ ርክክብ ተፈጸመ፡፡

በማኅበሩ የመቀሌ ማእከል ጸሐፊ የማን ኃይሉ በዚሁ የርክክብ ሥነ ሥርዓት ላይ እንዳሉት፤  የገዳሙ መነኮሳትን ችግር ለማቃለል ማኅበረ ቅዱሳን ከ2000 ዓ.ም ጀምሮ የፕሮጀክት ጥናት በማካሄደ በ36ሺ 450 ብር ወጪ የንብ እርባታ አጠናቆ ለገዳሙ ማስረከብ ችሏል፡፡

ከቅዱስ ሲኖዶስ ከተሰጠው ሓላፊነቶች አንዱ ገዳማት አድባራትና የአብነት ት/ቤቶች በገቢ እራሳቸውን እንዲችሉ ማገዝ መሆኑን የጠቆሙት ጸሐፊው ወደፊትም ይህን ተግባሩን አጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል፡፡

ግብርናና ገጠር ልማት ጽ/ቤት ተወካይ አቶ ግደይ መለስ በዚሁ ወቅት ባስተላለፉት መልእክት፤ የገዳሙን ቅርስና ሀብት ለቀጣዩ ትውልድ ለማስተላለፍ በሚደረገው ጥረት ለገዳማውያኑ ጥሬ ገንዘብ እየሰጡ ተመፅዋች ከማድረግ ይልቅ እንደ ማኅበረ ቅዱሳን እራስን የሚያስችል ፕሮጀክት ማከናወን ውጤታማ ያደርጋል ብለዋል፡፡ ለፕሮጀክቱ ውጤታማነት ጽ/ቤቱ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግም ቃል ገብተዋል፡፡

አበእምኔት መ/ር አባ ገ/ማሪያም ግደይ በበኩላቸው፤ «ገዳሙ ተዳክሞ መነኮሳቱም በችግር ምክንያት ፈልሰው ወደ መዘጋት በተቃረበበት ወቅት ማኅበሩ ደርሶ ለገዳሙ ፀሐይ አወጣለት» ሲሉ በገዳማውያኑ ስም ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡

በቀጣይ ሊገጥመው የሚችለውን ችግሮች እየተከታተለ ይፈታ ዘንድ የተማፅንኦ ቃል ያሰሙት አበ ምኔቱ ለፕሮጀክቱ ውጤታማነት መነኮሳቱ ተግተው እንደሚሠሩም ተናግረዋል፡፡
በርክክቡ ወቅት የተገኙት የቆላ ተንቤን ወረዳ ቤተ ክህነት ሥራ አስኪያጅ መ/ር አባ እዝራ ሃይሉ ማኅበሩ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ሆኖ እያከናወነ ያለው ዘርፈ ብዙ አገልግሎት የሚያስመሰግነው መሆኑን ጠቅሰው መንገዱ እጅግ አድካሚና አስቸጋሪ በሆነ ቦታ መጥቶ ከጥናት ጀምሮ እስከ ትግበራ ያከናወነው ፕሮጀክት ለሌሎች አርአያ ለመሆን የሚያስችለው ነው፡፡

ማኅበሩ የሠራውን ፕሮጀክት ተንከባክበው ውጤታማ በማድረግ ሥርዓተ ገዳማቸውን እንዲያፀኑ አሳስበዋል፡፡ በሠራው የተባበሩትን ሁሉ አመስግነዋል፡፡
ጥር 4 ቀን 2002 ዓ. ም ማኅበሩ ፕሮጀክቱን ለገዳሙ ባስረከበበት ወቅት እንደተገለፀው በሀገራችን ካሉት ቀደምት ገዳማት አንዱ መሆኑ የሚነገርለት ይኸው ገዳም በጣሊያን ወረራ ወቅት ከፍተኛ ጉዳት የደረሰበት ከመሆኑ በተ ጨማሪ ከ1966 ዓ.ም. ለውጥ በኋላ የገዳሙ ይዞታ ሙሉ በሙሉ በመወረሱ ገዳሙ ከፍተኛ ችግር ውስጥ ነበር፡፡

ፕሮጀክት ድጋፍ እንዲውል የማኅበረ ረድኤት ትግራይ ከሃያ ስድስት ሺሕ ብር በላይ ግምት ያለው የማር ማጣሪያ ዘመናዊ ማሽን እና ተያያዥ ቁሳቁሶችን በእርዳታ መለገሱ በፕሮጀክቱ ርክክብ ወቅት ተገልጿል፡፡

ደራሲዋ መጽሐፋቸውን ለሕንፃ ግንባታ ሥራ አበረከቱ

 

 በደረጀ ትዕዛዙ

 
በማኅበረ ቅዱሳን የሕንፃ ግንባታ ጽ/ቤት አሳታሚነት ለኅትመት የበቃው «እመ ምኔት» የተሰኘው የደራሲ ፀሐይ መላኩ አዲስ ረጅም ልብወለድ መጽሐፍ ተመረቀ፡፡  ጥር 9 ቀን 2002 ዓ.ም አንጋፋና ወጣት ደራሲያን፣ የሃይማኖት አባቶች እንዲሁም ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በተገኙበት በሩስያ ባህል ማዕከል /ፑሽኪን አዳራሽ/ የተመረቀው መጽሐፍ፤ በገዳማውያን ሕይወትና በውስብስብ ወንጀል ታሪክ ላይ ያተኮረ ሲሆን ደራሲዋ የመጽሐፉን ሸያጭ ገቢ ለማኅበሩ ጽ/ቤት ሕንፃ ግንባታ እንዲውል አበርክተዋል፡፡
የማኅበረ ቅዱሳን ምክትል ዋና ጸሐፊ እና የሕንፃ አሠሪ ኮሚቴው ተወካይ ዲያቆን ዋስይሁን በላይ በዚሁ ምረቃ ወቅት ባስተላለፉት መልእክት፤ ማኅበረ ቅዱሳን በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሰንበት ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ሥር ሆኖ ለበርካታ ዓመታት መንፈሳዊና ማኅበራዊ አገልግሎት ሲያበረክት መቆየቱን ጠቅሰው ይህንኑ አገልግሎት     በተጠናከረ ሁኔታ ለማከናወን የጽ/ቤት ሕንፃ ግንባታ እያካሄደ ነው፡፡
በሕንፃ ግንባታው ሂደት በርካታ ባለሙያዎች አስተዋጽኦ ማበርከታቸውን፣ ከአሁን ቀደምም በሦስት ደራስያን ሦስት መጻሕፍት ለሕንፃ ግንባታው ሥራ በድጋፍ መልክ መለገሳቸውን የገለጹት ዲያቆን ዋስይሁን፤ ደራሲ ፀሐይ መላኩ ለዚሁ ዓላማ ያደረጉት ድጋፍ የሚያስመሰግናቸው መሆኑን ተናግረዋል፡፡ እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ በቀጣዮቹ ሁለት ዓመታት ግንባታውን ሙሉ ለሙሉ ለማጠናቀቅ ለታቀደው ለዚሁ ሕንፃ ሥራ በጎ አድራጊዎች ድጋፍ እንዲያደርጉ በማሳሰብ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡
በመጽሐፉ ዙሪያ አጭር የዳሰሳ ጥናት ያቀረቡት የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የሥነ ጽሑፍ መምህር ተባባሪ ፕሮፌሰር ዘሪሁን አስፋው እንዳሉት፤ ከውስብስብስ የወንጀል ታሪክ እና ከዘመናዊ ረጅም ልቦለድ ባሕርያት አንጻር ድርሰቱ የተዋጣ ነው፡፡
«ከመጽሐፉ ውስጥ በገሀዱ ዓለም የሚታዩ እንደ ፍቅር፣ ጥላቻ፣ ቅናት፣ በቀል፣ ምቀኝነት፣ ታማኝነት፣ ጽናት፣ ወንጀል፣ ተንኮል፣ ትሕትና፣ ደግነት ይንጸባረቁበታል» ያሉት ፕሮፌሰሩ፤ «ደራሲዋ ይህንን መጽሐፍ ለሥነ ጽሑፍ ተማሪዎችና ለአጥኚዎች በማበርከታቸው ሊመሰገኑ ይገባቸዋል» ብለዋል፡፡
የደራስያን ማኅበር ፕሬዝዳንት አቶ ጌታቸው በለጠ በበኩላቸው፤ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ለሀገራችን ሥልጣኔና እውቀት ቀዳሚ መሆኗን ጠቅሰው፤ «ማኅበሩ ለቤተ ክርስቲያን ታላቅ ክብር አለው» ብለዋል፡፡ «ማኅበረ ቅዱሳን ለቤተ ክርስቲያን አገልግሎት ምን ያህል ታላቅ ሥራ እንደሚሠራ ማኅበሩ ይገነዘባል፡፡» ያሉት ፕሬዝዳንቱ፤ ለሚያከናውናቸው ሥራዎች የደራስያን ማኅበር ከጎኑ እንደሚቆም ተናግረዋል፡፡ ደራሲ ፀሐይ መላኩ ያበረከቱት አስተዋጽኦም የሚያስመሰግናቸው መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የዕለቱ የክብር እንግዳ መልአከ ምክር ቀሲስ ከፍያለው መራሒ በበኩላ ቸው፤ በመጽሐፉ ውስጥ ያለው ታሪክ ከሀገራችን የረጅም ታሪክና የበለጸገው ባህላችን የተነቀሰ የጥበብ ሀብት መሆኑን   ጠቅሰው፤ «ይህንኑ ከትውልድ ወደ ትውልድ እየተንከባለለ የመጣውን ሀብት የእግዚአብሔር ፈቃድ በመሆኑ ደራሲዋ ገልጸውታል» ብለዋል፡፡
ደራሲ ኃይለ መለኮት መዋዕልም፤ ደራሲዋ ከአሁን ቀደም ለአንባብያን ያበረከቷቸው መጻሕፍት የሚደነቁ መሆናቸውን ጠቅሰው፤ «ይህን አዲስ መጽሐፋቸውን ለማኅበሩ በጎ ሥራ ማበርከታቸው የሚያስመሰግናቸው ነው» ብለዋል፡፡
የመጽሐፉ ደራሲ ፀሐይ መላኩ በዚሁ ወቅት እንደገለጹት፤ የማኅበረ ቅዱሳን አባላት ለቤተ ክርስቲያኒቱ የሚያደርጉትን እንቅስቃሴ ሲመለከቱ መንፈሳዊ ቅናት ያድርባቸው እንደነበረ    ጠቅሰው፤ እርሳቸውም የበኩላቸውን ድርሻ ለማበርከት መጽሐፋቸውን ሲለግሱ ከፍተኛ ደስታ እየተሰማቸው መሆኑን ተናግረዋል፡፡
«በማኅበሩ ኤዲቶሪያል ቦርድ ተገምግሞ መጽሐፉ ለኅትመት እንደሚበቃ ሲነገረኝ በደስታ አለቀስኩ» ያሉት ደራሲዋ «የሕንፃ አሠሪ ኮሚቴው ጥያቄያቸውን በመቀበል ለኅትመት ማብቃቱ ሊያስመሰግነው ይገባዋልም» ብለዋል፡፡
ደራሲዋ እንዳሉት በንስሐ አባቶች፣ በመነኮሳትና ካህናት ላይ የሚሰነዘሩ ገንቢ ያልሆኑ ትችቶች ሲያናድዳቸው ለዚህ ምላሽ ይሆን ዘንድ በመልካም ጎኑ ይህንን መጽሐፍ ለመጻፍ ተነሣስተዋል፡፡
መጽሐፍ ከመጻፋቸው በፊት ሐይቅ እስጢፋኖስ አንድ ሱባኤ ከመቀመጣቸው በተጨማሪ ዝቋላ፣ አሰቦት፣ ራማ ኪዳነ ምሕረት፣ ዋሸራ እና ሌሎች ገዳማትን በመጎብኘት በመነኮሳት አኗኗር ላይ ጥናት በማድረግ አሥር ዓመታት ያህል እንደፈጀባቸው ተናግረዋል፡፡ ወደፊት በማንኛውም መልኩ የማኅበረ ቅዱሳንን እንቅስቃሴ ለማገዝ አንደሚጥሩም ገልጸዋል፡፡
በአሥራ አምስት ምዕራፍ የተከፈለው ይኸው «እመ ምኔት» መጽሐፍ 2002 ገጽ ያለው ሲሆን ለመጀመሪያ ጊዜ አምስት ሺሕ ኮፒ ታትሟል፡፡ መጽሐፉ በአሁኑ ወቅት በማኅበሩ ማእከላት፣ በሰንበት ት/ቤቶች እና በግቢ ጉባኤያት አማካኝነት እየተሸጠ መሆኑ ታውቋል፡፡ ደራሲዋን ለማበረታታም ከመጀመሪያው እትም ትርፍ አሥራ አምስት በመቶ ፐርሰንት እንደሚከፈላቸውም ተገልጿል፡፡
የሥነ ሥዕል፣ የሥነ ግጥም እና የእደ ጥበብ ሞያተኛ መሆናቸው የሚነገርላቸው ደራሲ ፀሐይ መላኩ ከአሁን ቀደም «አንጉዝ»፣ «ቋሳ» እና «ቢስራሔል» የተሰኙ ረጅም ወጥ ልቦለድ መጽሐፎችን ለንባብ አብቅተዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት በጡረታ ላይ የሚገኙት ደራሲ ፀሐይ በኢትዮጵያ ደራሲያን ማኅበር ሥራ አስፈጻሚ እንዲሁም የዜማ ብዕር ኢትዮጵያ ሴቶች የሥነ ጽሑፍ ማኅበር የቦርድ አባል ናቸው፡፡
በምረቃው ወቅት የማኅበረ ቅዱሳን መዘምራን መዝሙር ያቀረቡ ሲሆን፣ መነባንብ እና የደራሲዋ የተለያዩ ግጥሞች በሌሎች አንባብያን ለታዳሚዎቹ ቀርበዋል፡፡ የምረቃውን ሥርዓት ያዘጋጁት የዜማ ብዕር ኢትዮጵያ ሴቶች የሥነ ጽሑፍ ማኅበር ከማኅበረ ቅዱሳን ሕንፃ አሠሪ ኮሚቴ ጋር በመተባበር መሆኑ ታውቋል፡፡
Abune Timotiwos.JPG

የቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ የርቀት ትምህርት መርሐግብር ጀመረ

 በመንግስተአብ አበጋዝ

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ በሰርተፊኬት መርሐግብር የርቀት ትምህርት መስጠት መጀመሩን የኮሌጁ ዲን ዶክተር ብፁዕ አቡነ ጢሞቴዎስ አስታወቁ፡

Abune Timotiwos.JPG

የኮሌጁ ዲን ብፁዕ አቡነ ጢሞቴዎስ/ዶክተር/

የርቀት ትምህርት መርሐግብሩን አስመልክቶ ብፁዕ አቡነ ጢሞቴዎስ ለስምዐ ጽድቅ ጋዜጣ በሰጡት መግለጫ፤ የትምህርት መርሐግብሩ በርካታ ሊቃውንት የደከሙበት ረዥም ጊዜ የወሰደ ዝግጅት እንደተደረገበት ገልጸዋል፡፡ የኮሌጁ ዲን አያይዘውም፤ «ኮሌጁ ወደፊት የርቀት ትምህርቱን መርሐግብር ወደ ዲፕሎማና ዲግሪ ደረጃ አሳድጎ ለመቀጠል ዛሬ መሠረቱን ጥለንለታል፡፡ ምእመናንም ካለፈው ይልቅ በቅርበት ቤተክርስቲያናቸውን የሚያውቁበትን፣ ለአገልጋዮችም የተሻለ አገልግሎት ሊፈጽሙ የሚችሉበትን ዕድል ፈጥረንላቸዋል፡፡» በማለት የትምህርት መርሐግብሩ መጀመር ኮሌጁ ለቤተክርስቲያኒቱ መንፈሳዊና ማኅበራዊ አገልግሎት ዕድገት የሚያደርገውን አስተዋጽኦ ለማሳደግ እንደሚያግዘው ብፁዕነታቸው ጨምረው ገልጸዋል፡፡

የኮሌጁ አካዳሚክ ምክትል ዲን መምህር ፍስሐጽዮን ደሞዝ እንደገለጹት፤ ኮሌጁ የማስፋፊያ መርሐግብሮችን ቀይሶ መንቀሳቀስ ከጀመረባቸው ሥራዎች የርቀት ትምህርት መርሐግብር የመጀመሪያው እንደነበር ተናግረዋል፡፡ አያይዘውም የትምህርት መርጃ መጽሐፎቹ /ሞጁል/ የተዘጋጁበትን ቋንቋ ማንበብና መረዳት የሚችሉ በውጪና በሀገር ውስጥ የሚገኙ ምእመናን ሁሉ ሊሳተፉበት የሚችሉበትን ቅድመ ዝግጅት ከየአህጉረ ስብከት ሓላፊዎች ጋር የተደረገ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ የርቀት ትምህርቱን መከታተል የሚሹ ሁሉ በአቅራቢያው ወደሚገኙ የአህጉረ ስብከት ጽ/ቤት የርቀት ትምህርት ማእከል በመቅረብ ሊመዘግቡና ሊከታተሉ የሚችሉ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

በትምህርት ዝግጅቱ ወቅት ልዩ ልዩ እገዛዎችን ያደረጉና በማድረግ ላይ የሚገኙ ዩኒቨርስቲዎች ኮሌጆችና የኮሌጁ ማኅበረሰብ አባላትን በማመስገን የሚጀምሩት መምህር ቸሬ አበበ በቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ መምህርና የርቀት ትምህርት መርሐ ግብር ጸሐፊ ናቸው፡፡ እንደ መምህር ቸሬ ገለጻ፤ እስከ አሁን ሙሉ ለሙሉ ሥራቸው ተጠናቅቆ የታተሙ የትምህርት መርጃ መጻሕፍት /ሞጁልስ/ የቤተ ክርስቲያን ታሪክ፣ ሥራ አመራር፣ ሥነ-ምግባር፣ ትምህርተ አበው፣ ትምህርተ ሃይማኖት መግቢያ፣ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት መግቢያ ሲሆኑ የሌሎች ትምህርቶችም ዝግጅት የቀጠለ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የትምህርቱን መጀመር ከሩቅም ከቅርብም የሰሙ የቤተክርስቲያን ልጆች መመዝገብ መጀመራቸው ታውቋል፡፡ የኮሌጁ ዲን ዶክተር ብፁዕ አቡነ ጢሞቴዎስ ዕድሉ ለመላው ምእመናን የተሰጠ በመሆኑ በተለይ የቤተክርስቲያን አገልጋይ ካህናትና ዲያቆናት ተጠቃሚዎች እንዲሆኑ ጥሪያቸውን አስተላለፈዋል፡፡

 

ወስብሐት ለእግዚአብሔ
Asosa.JPG

በአሶሳ ከማሽ ከአራት ሺሕ በላይ የአካባቢው ተወላጆች ተጠመቁ

በሻምበል ጥላሁን

 
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የነገረ መለኮት ምሩቃን ማኅበር ከአሶሳ ሀገረ ስብከት ጋር በመተባበር ባደረገው ሐዋርያዊ ጉዞ ከአራት ሺሕ በላይ ሰዎች የክርስትና ጥምቀት እንዲጠመቁ ማስቻሉን አስታወቀ፡፡

የነገረ መለኮት ምሩቃን ማኅበር ለስምዐ ጽድቅ ጋዜጣ ዝግጅት ክፍል በላከው መረጃ እንዳስታወቀው፤ ሐዋርያዊ ጉዞና ጥምቀቱ የተከናወነው ከታኅሣሥ 16 እስከ 25 ቀን 2002 ዓ. ም የሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ሄኖክ፣ ሥራ አስኪያጁ ሊቀ መዘምራን ሐረገወይን ጫኔ፣ የከማሽ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት ሥራ አስኪያጅ መልአከሰላም ተገኝ ጋሻው በተገኙበት ነው፡፡

Asosa.JPG

የጉሙዝ ተወላጆች የክርስትና ጥምቀት ሲጠመቁ

በአሶሳ ሀገረ ስብከት ከማሽ ለአሥር ቀናት በቆየው ሐዋርያዊ ጉዞ ከአራት ሺሕ በላይ የጉሙዝ ተወላጆች መጠመቃቸውን መረጃው አመልክቷል፡፡

የክርስትና ጥምቀት ያገኙት እነዚህ የአካባቢው ተወላጆች የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን እምነት ተከታይ በመሆናቸው መደሰታቸውን የጠቆመው መረጃው፤ ሌሎችም   ለመጠመቅ ቤተ ክርስቲያኒቱን እየተጠባበቁ መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡

የልዑካን ቡድኑ ምእመናኑን ለማጥመቅ ከአምስትና ስድስት ሰዓታት በላይ በእግር እንደተጓዘ መረጃው አመልክቶ፤ በዞኑ በሚገኙ አሥራ ሰባት የተለያዩ ቦታዎች ምእመናኑን ለማጥመቅ ለተደረገው እንቅስቃሴ የሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ፣ የሀገረ ስብከቱ ሥራ አስኪያጅ የከማሼ ቤተክህነት ሥራ አስኪያጅ እና የሰበካ ጉባኤ አባላት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እና ጥረት ማድረጋቸውን ገልጿል፡፡

ምእመናኑ ለጥምቀት የበቁት ከአካባቢው ማኅበረሰብ በተለያዩ ጊዜ በማኅበረ ቅዱሳንና በጽርሐጽዮን የአንድነት ማኅበር አማካኝነት፤ የስብከተ ወንጌል ሥልጠና በተሰጣቸው የአካባቢው ተወላጆች ተተኪ መምህራን ባደረጉት ጥረት፤ እንዲሁም የከማሼ ቤተክህነት በተለያየ ጊዜ ባዘጋጀው የስብከተ ወንጌል ጉባኤ ባገኙት ትምህርት እንደሆነም መግለጫው አመልክቷል፡፡

ይሁን እንጂ ጥምቀቱን ያገኙ በከማሽ ዞን በተለያዩ ወረዳዎች የሚገኙ ምእመናን፤ እምነታቸውን የሚያጸኑበትና ሥጋና ደሙን የሚቀበሉበት፣ ልጆቻቸውን የሚያስጠምቁበት ቤተ ክርስቲያን በአቅራቢያቸው ስለሌለ በሌሎች የእምነት ድርጅቶች እንዳይወሰዱ ሥጋት እንዳለው የነገረ መለኮት ምሩቃን ማኅበሩ አስታውቋል፡፡

በመሆኑም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን በሕገ ልቡና በማመን በናፍቆት እየተጠባበቁ የሚገኙትን የዋሐን ምእመናን ወደ እናት ቤተ ክርስቲያናቸው ለመመለስና አገልግሎት የሚያገኙበትን ቤተ ክርስቲያን ለማነጽ የቤተ ክርስቲያን ልጆች ሁሉ በጋራ ሊሠሩ እንደሚገባም ማኅበሩ አስታውቋል፡፡

ማኅበሩ ወደፊት በራሳቸው ቋንቋ አገልግሎት የሚሰጡ ሃያ ስምንት የአካባቢውን ወጣቶች በመምረጥ በችግሻቅ ገብርኤልና በኮቢ ኪዳነ ምሕረት ቤተ ክርስቲያን ግብረ ዲቁና እንዲማሩ መምህር መቅጠሩን መረጃው ጠቁሞ፤ በርካታ ተጠማቂዎች በሚገኙበት አካባቢ የቅድሰት ሥላሴ ቤተ ክርስቲያን እንዲታነጽ የገንዘብ ድጋፍ ማድረጉንም አመልክቷል፡፡

ማኅበሩ በቀጣይም በጊዜ እጥረትና በቦታ ርቀት ምክንያት ያልተጠመቁትን ሌሎችም ለመጠመቅ የሚፈልጉትን ለማጥመቅ እንዲቻል ለሁለተኛ ጊዜ ሐዋርያዊ ጉዞ ለማድረግ ዕቅድ መያዙንም ገልጿል፡፡

ለምእመናኑ ጥምቀት መሳካት የሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስና ሥራ አስኪያጅ ያደረጉትን ከፍተኛ ጥረት አመስግኖ፤ በተለይ የክርስትና ጥምቀቱ የተከናወነበት የከማሽ ዞን ቤተ ክህነት ሥራ አስኪያጅ መልአከ ሰላም ተገኝ ጋሻውና ሰበካ ጉባኤው ከአሥር ሰዓት በላይ በእግር በመጓዝ ተጠማቂዎችን በማዘጋጀት ያከናወኑት ሥራ ላቅ ያለ መሆኑን አስታውሷል፡፡

ማኅበሩ ለተጠማቂዎቹ ከስምንት ሺሕ በላይ የአንገት ማተብ /ማኅተም/ እና ከአምስት ሺሕ በላይ አልባሳት፣ ለቁርባንና ለጥምቀት የሚያስፈልጉ ንዋያተ ቅድሳት አዘጋጅቶ ወደ ቦታው መጓዙንም መረጃው አመልክቷል፡፡

 

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

«ርትዕት ይእቲ ሃይማኖቶሙ ለቅዱሳን አበዊነ ( የአባቶቻችን ሃይማኖት የቀናች ናት)»፡፡

የንግግርና ሥነ ጽሕፈት ሙያን የተካኑ ምሁራን በትምህርት ጌጣቸው እንደሚሉት «ውሃን ከጥሩው ሲቀዱት፣ ነገርን ከሥሩ ሲያመጡት» ውሃው ጠጭውን፣ ነገሩም ሰሚውን ያረካዋል፡፡ በዚህ እውነተኛ ሃይማኖትን ከጊዜው ስመ መሳይ ኑፋቄና የለየለት ክሕደት ለይቶ በሚያሳይ ትምህርታችን «አበዊነ = አባቶቻችን» ያልናቸው እነማን እንደሆኑ በጥቅል ማመልከት እንወዳለን፡፡ የቃሉን ዐይነ ምስጢር ቁልጭ አድርጎ ለመግለጽ ያህል አባትነት መልክና ይዘቱ፣ ግብርና ዐይነቱ በጣሙን ብዙ ነው፡፡ ይሁንና እዚህ ላይ «የቀናች፣ የጸናች ሃይማኖት» ባለቤቶች ብለን በትምህርታችን ርእስ በመሪነት ያነሣናቸው፡፡

– ከአዳም ጀምሮ እስከ ኖኅ በደብር ቅዱስ የነበሩ አርእስተ አበውን፣
– ከአብርሃም ጀምሮ እስከ ሊቀ ነቢያት ሙሴ የነበሩትን የእግዚአብሔር ሰዎች፣
– አዕይንተ አርጋብ ዐበይት ደቂቅ ነቢያትን፣

ይልቁንም «አንተ ውእቱ ክርስቶስ ወልደ እግዚአብሔር ሕያው = አንተ የሕያው እግዚአብሔር ልጅ ክርስቶስ ነህ» ከማለታቸው አስከትለው «እግዚኦ ኀበ መኑ ነሐውር እንዘ ቃለ ሕይወት ዘለዓለም ብከ፣ ወንሕነሰ አመነ፣ ወአእመርነ፣ ከመ አንተ ውእቱ ክርስቶስ ወልዱ ለእግዚአብሔር ሕያው = አቤቱ! የዘለዓለም ደኅንነት የሚገኝበት ትምህርት ከአንተ ዘንድ እያለ ወደማን እንሔዳለን? እኛስ የሕያው እግዚአብሔር ልጁ ክርስቶስ እንደሆንህ ዐውቀን አምነናል» ማቴ.16-16፣ ዮሐ. 6-68-70 ብለው መስክረው ሲያበቁ ሃይማኖትን አብርተው ያረጋገጡ፣ ሁለንተናቸው በደመ እግዚእነ ኢየሱስ ክርሰቶስ ተኮልቶ የበራ፣ የጠራ ጽሩያነ አዕንይት የትምህርት፣ የሃይማኖት፣ የክህነት አባቶቻችን የሆኑ፣ በመንፈስ ቅዱስ ተቃኝተው የተሟሟቁ ቅዱሳን ሐዋርያትን ነው፡፡

ደግሞም የእነርሱን ዓላማና ግብር የተከተሉ ሰብአ አርድዕትና ምሉአነ አእምሮ ሠለስቱ ምእት ሊቃውንትን፣ ተጋዳልያን ሰማዕታትና ጻድቃን፣ ቅዱሳን ማለታችን ነው፣ እንጂ የመጀመሪያው የወንድሙ ነፍሰ ገዳይ የቃኤል ልጆችን ሁሉ አደባልቀን፣ ነገርን ከነገር አጣልፈን፤ ምስጢሩንም ደብቀን፣ ከሐድያን፣ ጣዖት አምላኪዎች መስሕታንን ቀደምት አበው ከሆኑ ብለን ሳናስተውል በጅምላው አይደልም፡፡ ስለይህ የእነዚህን ቅዱሳን = የተለዩ አበው የቀናች፣ የጸናች ሃይማኖት የሆነችው «ርትዕት ይእቲ ሃይማኖቶሙ ለቅዱሳን አበዊነ = የአባቶቻችን ሃይማኖት የቀናች የጸናች ናት፡፡» በዚች መሠረትነት ለሁለት ሺኽ ዘመናት እምነቷ፣ ሥርዐቷ፣ ባህሏ ተጠብቆ ለሕዝበ ክርስቲያን የሚገባውን መንፈሳዊና ሐዋርያዊ፣ ማኅበራዊም አገልግሎት ስታቀርብ የኖረች ጥንታዊት፣ ሐዋርያዊትና ብሔራዊት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በየዘመናቱ የገጠሙአትን ችግሮች፣ ፈተናዎች በታላቅ ትዕግሥት፣ በጾምና በጸሎት፤ በመንፈሳዊ ጥበብ የማለፍ ልምድና ዕውቀቷ በዓለም የተመሰከረ ነው፡፡ ይሁን እንጂ በአለንበት ጊዜ እምነቷን፣ ሕጓንና ሥርዐቷን ለማፋለስ በግልና በቡድን የተነሣሡ የእምነት ተቀናቃኞች በየአቅጣጫው በመዝመት ላይ መሆናቸው ለሕዝበ ክርስቲያን ግልጽ እየሆነ መጥቷል፤ አሁንም የበለጠ ሊታወቅ ይገባል፡፡

የመናፍቃንና የሃይማኖት ለዋጮች እንቅስቃሴ በቤተ ክርስቲያን ታሪክ ያልተለመደና እንግዳ ነገር አይደለም፡፡ ቀድሞ የነበረ፣ ያለና ወደፊትም የሚኖር ነው፡፡ ምክንያቱም አዝማቹ ጠላት በሞተ ሥጋ የማያርፍ ዲያብሎስ እንደሆነ በብሩህ ልቡና ይታወቃል፡፡ በመልካም እርሻ /ማሳ/ የተዘራው ንጹሕ ስንዴና ጠላት ጨለማ ለብሶ በስንዴው ማሳ ላይ የበተነው እንክርዳድ እስከ መኸር ጊዜ ዐብረው እንደሚኖሩ ጌታችን ራሱ ባለቤቱ በቅዱስ ወንጌል አስተምሮናል ማቴ. 13-24 – 31 ይህ የማይሻር ቃል ስለሆነ ሌላ ምን ይባላል? ዐይነ ኅሊናችንን ወደ ቀደመው ታሪክ ስናቀና በአበው ሐዋርያት ዘመንም በመልካም እርሻ ላይ በብርሃን የተዘራውን ጥሩ ዘር፣ ለማበላሸት የጥፋት ዘር በጨለማ የሚበትኑ ቢጽ ሐሳውያንና መናፍቃን ቤተ ክርስቲያንን ሲያውኩና ሲያምሱ ኖረዋል፡፡

በቀና ሃይማኖት ስምና ጥላ ተሸፍነው ትክክለኛውን እምነትና መሠረት ለማፋለስ ከማሴርም ዐልፈው ራሳቸውን በአማልክት ደረጃ በማስቀመጥ ሰዎችን ወደ ጥፋት በሚያደርስ መንገድ ለመምራት የቃጣቸው ብዙዎች ነበሩ፡፡ ዳሩ ግን ሁሉም እንደገለባ እሳት ብልጭ እያሉ ጠፍተዋል፡፡ በዓለም ላይ የበተኑት የጥፋት ዘር ግን ክሕደት የሚያብብበት ካፊያ ባካፋ ቁጥር በምንጭ ላይ እንደወደቀ ዘር በፍጥነት ይበቅላል፡፡ የእውነት ፀሐይ ስትወጣ ደግሞ መልሶ ይጠወልጋል፡፡ እንደነ ይሁዳ ዘገሊላ፣ እንደነ ቴዎዳስ ዘግብጽ የመሳሰሉት ከብዙዎች በምሳሌነት ሊጠቀሱ ይችላሉ፡፡ «ቴዎዳስ ዘግብጽ» አምላክ ነኝ ብሎ ተነሥቶ እሰከ አራት መቶ የሚደርሱ ተከታዮች አፍርቶ ነበር፡፡ ይሁን እንጂ ብዙ አልተጓዙም እርሱም፣ ተከታዮችም ፀሐየ ጽድቅ ሲወጣ እንደሚጠወልገው ሣር ፈጥነው ጠፍተዋል፡፡ ይሁዳ ዘገሊላም እንደዚሁ ነው፡፡ አልቆየም፤ ጠፍቷል፡፡ /ግ.ሐ. 5-37/

ጥንታዊት ሐዋርያዊት ብሔራዊት ቤተ ክርስቲያናችንን ለመበታተን የሚጥሩት ሁሉ መሠረቷ በክርስቶስ ደም የጸናውንና በቅዱሳን አባቶቻችን ዐፅም የታጠረችውን ቤተ ክርስቲያን ሲገፏትና ሲነቀንቋት ፈተናውን በትዕግሥት በማስተዋልና በትምህርት በመከላከል ትቋቋመዋለች፡፡ ይህ የብዙ ዘመን ልማዷ ነው፡፡ መቼውንም ቢሆን ግራ አያጋባትም፡፡

አባቶቻችን ያቆዩን የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሃይማኖት ጥንታዊት የቀናች፣ የጠራች፣ ስለሆነች ተካታዮቿን የምታኮራ እንጂ የምታሳፍር አይደለችም፡፡… በሰዎች የግል ድካም እንጻርም አትመዘንም፡፡ ለመከራም አትበገርም፡፡ ቤተ ክርስቲያናችን እስከ ዛሬ ድረስ በእምነቷ፣ በጾሟና በጸሎቷ የማያቋርጥ የገቢረ ተአምራት ወመንክራት፣ ኀይላትም ሥራ ስትሠራ የምትገኝ ለተከታዮቿ ተስፋ ሆና የምትኖር እውነተኛ ቤተ ክርስቲያን ናት፡፡ ርግጥ ነው፤ በቅን ልቡናና በትሑት ሰብእና ለተቀበለው ሸክሟ ቀላል ቀንበሯ ልዝብ ነው፡፡ ዳሩ ግን በገድል የተቀመመ ሕጓ፣ ባህሏና ሥርዐቷ ጥብቅ ስለሆነ የሕግና የሥርዐት ቀንበር ላለመደ ስስ ጫንቃ አይመችም፡፡ መንገዱ ቀጭን፣ በሯ ጠባብ ነው፡፡ የእግዚአብሔርም መንግሥት የምትወርሰው በመከራ መስቀልና ብዙ ትዕግሥት፣ በዚሁ ቀጭን መንገድ ተጉዞና በጠባቡ በር ዐልፎ ስለሆነ በቀና ሃይማኖት ጸንቶ፣ በጾም በጸሎት ተወስኖ ሕይወቱን = አኗኗሩን በሥነ ምግባር፣ ገዝቶ በአበው፣ መንፈሳዊ መንገድ መጓዝ ለክርስቲያን አምላካዊ ትእዛዝ ነው፡፡ ማቴ. 7-13-05 የሐዋ.14-22 ይህ ጠባብ በርና ቀጭን መንገድ የሃሪካችን መዛባት የለበትም፡፡ ተቆርቋሪዎች እንሁን፡፡ የወይራ ዛፍ ተቀጥላው ብሳና ቢሆን እጅግ ያሳፍራልና፡፡ በነገረ ጠቢባን «ሳይረቱ አይበረቱ» ተብሏልና፡፡

ለመሆኑስ አባቶቻችን ታቦት ተሸክመው እየዘመቱ ከጾም ጸሎታቸው ጋር በተጋድሎ አጥንታቸውን ከስክሰው፣ ደማቸውን አፍስሰው በአቆዩአት ኢትዮጵያ ሀገራችን ነጻነታችንን ማን ይነካብናል ብለን እንሰጋለን? ሕግ አክባሪነትና ወሰን የሌለው ትዕግሥታችን ካልሆነ በስተቀር ለመሥዋትነቱ ከቶ የእነማን ልጆች እንደሆን ሊዘነጋ አይገባምና በአካልም በመንፈስም ስለ ሃይማኖታችን እንበርታ፡፡ የእውነተኛ ሃይማኖት ዐላማው፣ ውጤቱ እስከ ሞት ድረስ እንኳ ትንሽም አለመፍራት መሆኑን ማስታወስ አለብን፡፡ ት.ዳ.3-13-ፍጻ፡፡ አሁንም እንደ ቀድሞው መንፈሰ ኀይልን ታጥቀን እንነሣ፤ አምላካችን እንደ አባቶቻችን የኀይልና የጥበብ መንፈስን እንጂ የፍርሀትና የመደንገጥ ሀብትን አልሰጠንምና በሃይማኖታችን ማንንም አንፍራ፤ አንሸበር፡፡ የዜግነት ግዴታችንን እየተወጣን መብታችንን ጠብቀን ለማስጠበቅ እንታገል፡፡ 2ጢሞ.1-7፡፡

በሰፊዋ ሀገራችን እንኳን ተወልደው ያሉ ዜጎቿ ቀርቶ ከተለያዩ ሀገሮች የሚመጡ ባዕዳን ሁሉ በተለያየ እምነታቸው ተከራይተውና ተጎራብተው እንዲኖሩ ቤተ ክርስቲያናችን አልተቃወመችም፡፡ ከማንኛውም የእምነት መሳይ ተቋም ደልላ የእንጀራ ልጆች ለማፍራትም አትፈልግም፡፡ ከጅሏትም አያውቅ፡፡ ይህን የሚያደርጉ ግን ሌሎች ናቸው፤ እዚህ ላይ ስማቸው ባይጠራም በዚሁ የሃይማኖት መሳይ ኑፋቄ የደላላነት ግብራቸው ይታወቃሉ፡፡ ማቴ. 7-15

«የሁሉ ሰው መብትና ነጻነት ሰብአዊ ፍላጎትም ተጠብቆ በእኩልነት እንኑር» የሚለውን የአስተዳደር መርሕ እንቀበላለን፡፡ አምላካዊ ሕግም ነው፡፡ በሃይማኖት ከማይመስሉን ጋር ግን በእምነት ጉዳይ መቼም ቢሆን አንድነት የለንም አይስማማንም፡፡ ከይዞታችንና መብታችን ሌሎች እንዲገቡብንም አንፈልግም፡፡ እኛም ከነሱ የምንሻው ምንም ነገር የለም፡፡ አይጠቅመንምና፡፡ ይህ ምርጫችን ነው፡፡ ግድ የሚለን የለም፡፡ «ሲኖሩ ልጥቅ፣ ሲሔዱ ምንጥቅ» የሚለው የአበው ምሳሌያዊ ቃለ ኀይል ሥጋችንን ዐልፎ ዐጥንታችንን በማስተዋል አለምልሞታልና፡፡ ይልቁንም «ብርሃንን ከጨለማ ጋር የሚቀላቅለው ማነው?» የሚለው ቃለ ቅዱስ መጽሐፍ ጠፈር፣ ደፈር ሆኖ ይከለክለናል፡፡ክርስትናችንን ይበርዝብናል ክልክል ነው፡፡ 2ኛቆሮ.6-14-ፍጻ፡፡ ይህን በጥሞና እንገንዘበው፡፡ እኛ ሃይማኖት መጽደቂያ፣ ምግባረ ሃይማኖት ማጽደቂያ እንጂ የሥጋ መተዳደሪያ እንዳልሆነ በውል ስለምናውቅ የሃይማኖትን ጉዳይ ከማናቸውም ሥጋዊና ጊዜያዊ ደስታ ጥቅም ጋር አናያይዘውም፡፡. . . ለዚህም ብለን ሃይማኖትና ሥርዐታችንን አንሸጥም፤ አንለዋውጥም፡፡ ይህ የቅዱሳን አበው ትውፊታችን ነው፡፡ ከደማችን የተዋሐደ ክርስቲያናዊ ጠባያችንም ይኸው ነው፡፡ ሮሜ12-18 ነገር ግን ይህ አቋምና ጠባያችን ከሞኝነት ተቆጥሮ ያላችሁን ሁሉ እንቀማችሁ እንቀስጣችሁ የሚሉንን አምረን እንቃወማለን፡፡ ይገባናልም፡፡ ብዙዎች የእምነት ተቋሞች ሳይሆኑ ነን ባዮች የታሪክና የሃይማኖት መሠረታቸውን እየለቀቁ፣ የነበራቸውን ትውፊት በቁሳቁስና በኃላፊ ጥቅም እየለወጡ ባዶ እጃቸውን ስለቀሩ እኛ ከቅዱሳን አበው ወርሰን ጠብቀንና አጥብቀን የያዝነውን ነፍስ እንዳላወቀ ሕፃን «ካክሽ» እያሉ በማስጣል እኛነታችንን ሊአስረሱን ይፈልጋሉ፤ አልፈው ተርፈውም ወቅትንና አጋጣሚን ዐይነተኛ ተገን /መሣሪያ/ በማድረግ፣ ነገሮችንም ከፖለቲካና ከግዚያዊ ችግር ጋር በማስተሳሰር የሕዝብን አስተያየት ለማዘናጋትና የመብታችን ተካፋዮች ለመሆን መስለው ይቀርባሉ፡፡ ከሃይማኖት መሳይ ቤተሰባቸው ለጊዜያዊ ችግር የሚገኘውን ጥቂት ርዳታ የሃይማኖት፣ የታሪክና የቅርስ መለወጫ ሊአደርጉትም በእጅጉ ይሻሉ፡፡

እውነተኛው የኢትዮጵያ ሕዝብ ግን «ኩራት እራቱ» ስለሆነ እንደኤሳው ብኩርናውን በጊዜያዊ ጥቅም /ነገር/ አይለውጥም፡፡ «ነብር ዥንጉርጉርነቱን» እንደማይለውጥ የኢትዮጵያ ሕዝብም፣ ለሃይማኖቱ፣ ለክብሩ፣ ለታሪኩና፣ ለነጻነቱ መሞት እንኳ የተለየ መታወቂያው፣ የማይለወጥ ጠባዩ ነው፡፡ ኤር. 13-23፡፡

በዐያሌው ከልብ የተወደዳችሁ፣ እውነቱ ያልተሰወራችሁ የቤተ ክርስቲያን አባላት ሆይ!

የእምነታችሁና ሥርዐታችሁ ጠባቂዎች፣ የቤተ ክርስቲያናችን ሕይወቷ ደስታዋና ክብሯ ተከታዮቿ እናንት ምእመናን ስለሆናችሁ ልጆቻችሁና ወዳጆቻችሁ በዐዲስ የሃይማኖት ትምህርት መሰል ክሕደት እንዳይወስዱ ጊዜና ቦታ በማይገድባቸው ወደ ጥፋት በሚወስዱ ሰፋፊ መንገዶች ከሚመሩ አዘናጊዎች መናፍቃንና ቢጽ ሐሳውያን መምህራን እንድትጠበቁ፣ «ዐደራ»! ትላችኋለች እናታችሁ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን፡፡ ደግሞም በቅዱሳን አበው ሃይማኖታችሁ እንድትጸኑ ታሪካችሁን፣ ሀገራችሁን ባህላቸሁን፣ ፍቅራችሁን፣ አንድነታችሁን ጠብቃችሁ በጥንቃቄና በሥርዐት እንድትኖሩ፣ እኛም እጅግ ጥብቅ የሆነ መንፈሳዊ ፍቅር የተመላ መልእክታችንን በእናት ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ሕያው ስም ከቅን ልቡና በመነጨ ሐሳብ አናስተላልፋልን፡፡ 1ቆሮ.14-15

መድኀኒታችን እንዳስጠነቀቀው ከሐሰተኞች መምህራን ተጠበቁ፤ የዘመኑን ምትሐታዊ ሒደትና ይዘት ዕወቁ፤ በመንፈሳዊ ሕይወት ጽኑ፡፡ በተለያዩ የተፈጥሮና ሰው ሠራሽ ችግሮች ምክንያት ከዓለም ኅብረተሰብ የምናገኘው ጊዜያዊ ርዳታ በሰብአዊና ማኅበራዊ ግዴታ ላይ የተመሠረተ እንጂ የሃይማኖትና የታሪክ ለውጥ መዋዋያ አይደለም፡፡ የመልካም ጠባይና ማንነት መለወጫም አይደለም፡፡ ድኽነትን ከየቤታችን ለማጥፋት ሥራን እንውደድ፡፡ እርስ በርስ እንረዳዳ፡፡ ችግረኛውን ተባብረን ነፃ እናውጣው፡፡ እንደቀሞው ባህላችን ያለንን ተካፍለን ዐብረን እንብላ እንጂ መነፋፈግን አንልመድ፡፡ በዚህ ጊዜ የበረከት አምላክ ረድኤት በረከቱን ይሰጠናል፡፡ ወገንና መጠናችንንም ለይተን ዕንወቅ እንጂ የቅዱሳን አበው ልጆች እዚህ ላይ አትኩረን ልብ እንበል፡፡ በምንም ሰበብ እንደ ገደል ውሃ ክንብል አንበል፡፡ ይህን ከመሰለው ደካማ ሐሳብም ልጆቻችሁን በብዙ ዘዴ ጠብቁ፡፡ የሃይማኖት ፍቅር ቁም ነገሩም ከቤተሰብ በላይ ስለሆነም ይህን አትርሱ፡፡ ምንም ቢሆን ክፉን ማስወጣት ያቃተው ስንኳ ቢኖር መውጣት አያቅተውም፡፡ ማቴ. 10-36-40

በቤተሰብ አባላት በወዳጅ ዘመድና በጎረቤት መስለው የሚመጡ የበግ ለምድ ለባሾችን ዕወቁባቸው፡፡ ፊልጵ. 3-2 ዋናው ዘዴ ከእነርሱ ጋር ዐብሮ አለመራመድ፣ ዐብሮ አለመገኘት ነው፡፡ ከደጃቸውም አለመቆም ነው፡፡ የእነርሱ የሆነንም ሁሉ አለመከጀል፣ ፈጽሞ አለመንካት ነው፡፡ የጠላት ገንዘብ ምግብ፣ ልብስና ቁሳቁስ በሙሉ የተወገዘ፣ እርኩስ ነው፡፡ ሕርም ነው፣ መርዝ ነው፡፡ ደዌ ክሕደትን ያመጣል እንጂ ጤና ሕይወት አይሆንም፡፡ እንወቅ፡፡ በሌላ በኩል በእውነቱ ከሆነ አንድ ልጅ እናቱ መልካም ፍትፍት ምግብ አዘገጅታ ባትሰጠው እንኳ ከጎረቤት ሔዶ በመርዝ የተቀመመ ምግብ መብላትና መታመም፣ ዐልፎም መሞት የለበትም፡፡ እንደዚሁም ታዲያ በሥራዋና በመልካም አቋሟ ሁሉ እንደ መማር፣ ባይሆንም እንደ መጠየቅ «እናቴ ቤተ ክርስቲያን ጮኻ ባታስተምረኝ ነው» እያሉ ከክሕደትና ኑፋቄ ማኅበር እንደ እሳት ራት ዘሎ መግባት አግባብ አይደለም፤ የሰውነት መመዘኛም አይሆንም፡፡ እንግዲያውስ ተጠበቁ፡፡ ተጠንቀቁ፤ ሌላ የሚያዋጣ ነገር ፊጽሞ አይገኝም፤ ዐጉል መዋተት ብቻ ይሆናል፡፡ በዚህ ዐዲስ ዘመን ዐዳዲስ የሃይማኖት መሳይ ድርጅት የቀናች አንዲት እውነተኛ የአበው ሃይማኖትን ሊተካት ቀርቶ ሊመስላት አይችልም፡፡ ይህን የመሰለው ሐሳብ የዘባቾች ከንቱ ዘበት ነው፡፡

ሰው ሆኖ በተዋሕዶ ተገልጾ በባሕርይ ክብሩ ያለ መድኀኒታችን የባሕርይ አምላክ ኢየሱስ ክርስቶስንም ከባለቤቱ እንደባዘነ የቤት እንስሳ በዚህ ዘመን በየሜዳውና በየግል አጋጣሚ «አገኘሁት» አይባልም፡፡ ድፍን ያለ ሐሰት ነው፡፡ እናስተውል፡፡ ወይም እራሳቸውን እንኳ በማያውቁ ልሙጥ ማይማን ዘባቾች «ተቀበሉት» የሚባልለት ቁስ አካል፣ አልያም ማደሪያ የሌለው ባይተዋር አይደለም፡፡ ዓለምን በእጁ የያዘ እርሱ በእኛ የሚወሰን ይመስል የተለያየ ችግር ባለባቸው፣ ተግባር ሥጋዊን በጠሉ፣ የዕለት ምግብ ፈላጊዎች ልንጎተትና በእነርሱ ዐቅም ተታለን በየዛኒጋባው ልንመሰግ የሚገባን ሰብአዊ ግብር አይደለንም፡፡ አሁንም በሃይማኖት ቁሙ፣ ጠንክሩ፣ ንቁም በተማራችሁትና በያዛችሁት እውነተኛ ሃይማኖታችሁ ጽኑ፡፡ ባይረዳችሁ እንኳ ከእናታችሁ ቅድስት ቤተክርስቲያን ተግታችሁ ተማሩ፤ ጠይቁ፡፡ «ርትዕት ይእቲ ሃይማኖቶሙ ለቅዱሳን አበዊነ = የቅዱሳን አባቶቻችን ሃይማኖት የቀናች፣ የጸናች እውነተኛም ናት» አማራጭ ተለዋጭ ፈጽሞ የላትም፤ ዘለዓለማዊት ናት፡፡ በባዕድ ዘመን አመጣሽ ትምህርት እንዳትወሰዱ አሁንም፣ ምን ጊዜም ተጠበቁ፤ ዕወቁ፤ ተጠንቀቁ፡፡ በቃለ አበው ሐዋርያት ተገዝታችኋል፡፡ ስለእውነተኛዋ ሃይማኖታችሁ በየትና በማን እንደምትማሩ ለይታችሁ አስተውሉ፡፡ ተረዱም፡፡ በቀናች ሃይማኖታችሁ ጸንታችሁ በሰላም በብርታት እንድትኖሩም፣ ለጸሎትና ምህላ ትጉ በሥራችሁ ሁሉ እንዳትሰናከሉም፣ እንቅፋታችሁን «ወአምላከ ሰላም ለይቀጥቅጦ ለሰይጣን በታሕተ እገሪክሙ ፍጡነ = የሰላም አምላክ ፈጥሮ ሰይጣንን ከእግራችሁ በታች ይቀጥቅጠው!!!» ኀያሉ አምላክ ኀይል፣ ከለላ፣ ይሁነን፡፡ የእመቤታችን ቅድስት፣ ድንግል ማርያም አማላጅነት፣ የቅዱሳን ጸሎት ግርማ ሞገስ ይሁነን፡፡ ሮሜ 16-20፣ 1ኛቆሮ.16-13፣ ገላ.1-8፣ ቆላ.2-6-11

ምንጊዜም «ክፉ አይልከፋችሁ፣ ደግ አይለፋችሁ»

 

ከሊቀ ትጉሃን ኀ/ጊዮርጊስ ዳኘ
በጠ/ቤተ ክህነት የዕቅድና ልማት መምሪያ ም/ሓላፊ
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
አምላከ ሰማያት ወምድር