ለ፲፰ ቀናት የቆየው የ፳፻፲፩ ዓ.ም የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ማኅበራዊና መንፈሳዊ ጉዳዮችን ለማስፈጸም ውሳኔዎችን አሳለፈ
በሕይወት ሳልለው
ከግንቦት ፲፬ እስከ ሰኔ ፫ ፳፻፲፩ ዓ.ም ድረስ የተካሄደው የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ የ፳፻፲ እና ፳፻፲፩ ማኅበራዊና መንፈሳዊ ጉዳዮች ላይ ውሳኔ ማሳላፉን ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት በመግለጫቸው አስታወቁ፡፡
በአሁኑ ጊዜ በአብያተ ክርስቲያናት ላይ እየደረሰ ያለውን ጥቃት በመንቀፍ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ኃላፊነቷን ለመወጣት የሚያስችል ውሳኔ መወሰኑን ይፋ አድርገዋል፡፡ ለተቃጠሉት አብያተ ክርስቲያናት መልሶ ግንባታ የሚሆን ገንዘብ ማሰባሰቡን ፤ ምእመናን ላይ እየደረሰ ያለውን ጥቃትና በሀገር ደረጃ ሰላም፤ፍቅርና አንድነት እንዳይኖር የሚያግዱ ችግሮችን ማውገዙንና ሃይማኖታዊ ሥርዓትን ለማስጠበቅ የሚያስችሉ ውሳኔዎችን ማሳለፋቸውን ቅዱስ ፓትርያርኩ ገልጸዋል፡፡ «በውጭ ሀገር የሚገኙ አህጉረ ስብከቶችን የቤተ ክርስቲያንን በማጠናከር መንፈሳዊና ማኅበራዊ አገልግሎት ማስፋፋት እንዲቻል ቃለ ዓዋዲው ከየሀገራቱ መንግሥታት ሕግ ጋር የተጣጣመ ደንብ ሆኖ እንዲዘጋጅና ለጥቅምት ፳፻፲፪ ዓ.ም. የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ እንዲቀርብ ተወስኗል» ብለዋል፡፡
በተለይም ከቀናት በፊት ቅዱስ ሲኖዶሱ ስላወገዘው የግብረ ሰዶማውያን እንቅስቃሴም ቅዱስ ፓትርያርኩ አሳስበዋል፡፡ «የሀገራችንን የቱሪስት መስሕብነት ምክንያት በማድረግ ዜጎች በቅድስናና በፈሪሀ እግዚአብሔር ተከብረው የሚታወቁባትን የሀገራችንን ታሪክ የሚቀይር፤ የዜጎችን መልካም ሥነ ምግባር የሚለውጥ፤ ሕገ ተፈጥሮንና የተቀደሰውን ሥርዓተ ጋብቻን የሚያበላሽ፤ በቅዱሳት መጻሕፍት ሁሉ የተወገዘ ግብረ-ሰዶምን በሀገራችን ለማስፋፋት፤ በዚህም የቅድስት ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን ቅድስና የሚጎዳ ሕገ-ወጥ ተግባር ለመፈጸም መቀመጫውን በአሜሪካን ሀገር ያደረገው የግብረ-ሰዶማዊያን አስጎብኚ ድርጅትን በመቃወም ወደ ቅድስት ሀገራችን ኢትዮጵያ እንዳይገባ፤ቅዱሳት መካናትንም እንዳይጎበኝ የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤው አውግዟል»
እነዚህንና ሌሎች ችግሮችን ለመፍታት ምልአተ ጉባኤው በውይይቱ ላይ ፲፭ ዋና ዋና ጉዳዮች ያነሳ ሲሆን በእያንዳንዳቸው ላይ ጥናት በማካሄድና ችግሮቹን በመለየት ዘላቂ መፍትሔ ለማምጣት በሚል ባለሞያዎችንም እንደመደበ አስታውቋል፡፡ በተጨማሪም በቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ በየሦስት ዓመቱ የሚመረጡ የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊን የጠቅላይ ቤ ክርስቲያን ዋና ሥራ አስኪያጅ ብፁዕ አቡነ ዮሴፍ የምሥራቅ ጎጃም ሀገረ ስብከት፤ ሊቀጳጳስ፤ የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሓፊ እና ብፁዕ አቡነ ያሬድ የሰበካ ጉባኤ ማደራጃ መምሪያና የአርሲ ሀገረ ስብከት ሊቀጳጳስ፤ የጠቅላይ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ አድርጎ መሰየሙን አሳውቋል፡፡
በመጨረሻም ከ፳፬ ዓመት በኋላ የቤተ ክርስቲያኗ ታላላቅና ሁለት መለስተኛ ሕንጻዎች በአቤቱታ መመለሳቸውን የሚያረጋግጥ ደብዳቤ ግንቦት ፳፱ ቀን መቀበላቸውን ሊቀ ካህናት ኀይለ ስላሴ ዘማርያም ገልጸው ሰኔ ፫ ቀን ርክክቡ በፊርማ ጸድቋል፡፡