የሆሣዕና ምንባብ14(ዕብ. 9÷11-ፍጻ.)
ክርስቶስ ግን ለምትመጣይቱ መልካም ነገር ሊቀ ካህናት ሆኖ÷ የሰው እጅ ወደ አልሠራት÷ በዚህ ዓለም ወደ አልሆነችው÷ ከፍተኛዪቱ ወደምትበልጠውና ወደምትሻለው ድንኳን÷ የዘለዓለም መድኀኒትን ገንዘብ አድርጎ÷ በገዛ ደሙ አንድ ጊዜ ወደ መቅደስ ገባ እንጂ በላምና በፍየል ደም አይደለም፡፡ የላምና የፍየል ደም÷ በረከሱትም ላይ የሚረጭ የጊደር አመድ÷ የሚያነጻና የረከሱትንም ሥጋቸውን የሚቀድሳቸው ከሆነ÷ ነውር የሌለው ሆኖ÷ በዘለዓለም መንፈስ ራሱን ለእግዚአብሔር ያቀረበ የክርስቶስ ደም ሕያው እግዚአብሔርም እናመልከው ዘንድ ሕሊናችንን ከሞት ሥራ እንዴት ይልቅ ያነጻ ይሆን?
ስለዚህ ኢየሱስ ሞትን ተቀብሎ÷ በቀደመው ሥርዐት ስተው የነበሩትን ያድናቸው ዘንድ ወደ ዘለዓለም ርስቱም የጠራቸው ተስፋውን ያገኙ ዘንድ÷ ለአዲሲቱ ኪዳን መካከለኛ ሆነ፡፡ ኑዛዜ ያለ እንደሆነ የተናዛዡ ሰሙ ሞት ይመጣ ዘንድ ግድ ነው፡፡ የሙአች ሰው ኑዛዜ የጸናች ናት፤ ተናዛዡ በሕይወት ባለበት ጊዜ አትጠቅምምና፡፡ ስለዚህም ፊተኛው ኪዳን እንኳ ያለ ደም አልከበረም፡፡ ሙሴ የኦሪትን ትእዛዝ ሁሉ ለመላው ሕዝብ ከነገረ በኋላ÷ የላምና የፍየል ደም ከውኃ ጋር ቀላቅሎ÷ ቀይ የበግ ጠጒርና የስሚዛ ቅጠል ነክሮ መጽሐፈ ኦሪቱንና ሕዝቡን ሁሉ ይረጭ ነበር፡፡ “እግዚአብሔር ያዘዛችሁ የኪዳኑ ደም ይህ ነው” ይላቸው ነበር፡፡ ድንኳኑንና የመገልገያው ዕቃ ሁሉ በደሙ ይረጭ ነበር፡፡ ደግሞም በቀረበው ሁሉ እንዲህ ያደርግ ነበር÷ በኦሪት ሕግ ሁሉ በደም ይነጻ ነበር፤ ደም ሳይረጭ ግን አይሰረይም ነበር፡፡
በሰማይ ባለው አምሳል የተሠራው ይህ ሥራ÷ በዚህ ደም የሚነጻ ከሆነ÷ ይህ ሰማያዊ መሥዋዕትስ ከዚህ ይበልጣል፡፡ ክርስቶስ በእጅ ወደ ተሠራች የእውነተኛይቱ ምሳሌ ወደ ምትሆን ቅድስት አልገባምና÷ ነገር ግን በእግዚአብሔር ፊት ስለ እኛ አሁን ይታይ ዘንድ÷ ወደ እርስዋ ወደ ሰማይ ገባ፡፡ ሊቀ ካህናቱ ያደረገው እንደ ነበረ÷ በያመቱም ደም ይዞ ወደ ቅድስት ይገባ እንደ ነበረ ዘወትር ራሱን የሚሠዋ አይደለም፡፡ ይህስ ባይሆን ዓለም ከተፈጠረ ጀምሮ ብዙ ጊዜ በሞተ ነበር፤ አሁን ግን በዓለም ፍጻሜ÷ ራሱን በመሠዋት ኀጢአትን ይሽራት ዘንድ አንድ ጊዜ ተገለጠ፡፡ ለሰው አንድ ጊዜ ሞት÷ ከዚያም በኋላ ፍርድ እንደ ሚጠብቀው÷ እንዲሁ ክርስቶስም የብዙዎችን ኀጢአት ያስተሰርይ ዘንድ ራሱን አንድ ጊዜ ሠዋ፤ በኋላ ግን ያድናቸው ዘንድ ተስፋ ለሚያደርጉት ያለ ኀጢአት ይገለጥላቸዋል፡፡