ፈረሰኛው ቅዱስ ጊዮርጊስ
በአስናቀች ታመነ
እንደምን ሰነበታችሁ ልጆች? ደህና ናችው? እግዚያብሔር ይመስገን እንዳላችሁ ተስፋ እናደርጋለን፡፡ ልጆች! ትምህርት እንዴት ነው? ከዓለማዊው ትምህርታችሁ ጎን ለጎን እናንተን ያስተምራል እንዲሁም በምግባር ያንጻል ብለን ያሰበነውን ታሪክ ይዘንላችሁ ቀርበናል፡፡ ልጆች በዚህ ዕትማችን ይዘንላችሁ የቀርብነው የሰማዕቱ ቅዱስ ጊዮርጊስን ታሪክ ነው፡፡ ከታሪኩ ብዙ እንደምትማሩ ተስፋ እናደርጋለን፤ በጽሞና እንድታነቡም ተጋብዛችኋል፤ መልካም ንባብ ይሁንላችው፡፡
ልጆች! ልዳ በምትባል ሀገር የሚኖሩ ዞሮንቶስና ቴዎብስታ የሚባሉ ባልና ሚስቶች ነበሩ፡፡ ታዲያ እነዚህ ሰዎች አንድ ወንድ ልጅና ሁለት ሴቶች ልጆች ነበሯቸው፣ ሴቶቹ አንደኛዋ ማርታ ሁለተኛዋ ድስያ ወንድማቸው ደግሞ ጊዮርጊስ ይባላሉ፡፡ ታዲያ እነዚህ ቤተሰቦች በጣም ይዋደዱና ይከባበሩ ነበር፡፡ ሲኖሩ… ሲኖሩ… ሲኖሩ አንድ ቀን በድንገት አሣዛኝ ነገር ተከሠተ፡፡ ይኽውም የእነ ጊዮርጊስ አባት ዞሮንቶስ ታመመና ሞተ፡፡ አባታቸው ሲሞት ጊዮርጊስ ፲ ዓመቱ ነበር፡፡ ከዚያም ትንሽ ጊዜ እንደቆዩ ጊዮርጊስን ሌላ መስፍን መጣና በእምነትና በምግባር ሊያሳድገው ቃል ገብቶ ከእናቱ ዘንድ ወሰደው፡፡ ልጆች! እናንተም ጓደኞቻችሁን እና ቤተሰባችሁን እንደራሳችሁ አደርጋችሁ መውደድና ማክበር አለባችሁ፡፡ ወደ ታሪኩ እንመለስና ይህ መስፍን ታዲያ የእግዚአብሔርን ቃል እያስተማረው ሲሔድ ጊዮርጊስ ጠንካራ፣ ለእምነቱ ሟችና ተሟጋች ሆነ፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ፈረስ መጋለብና ቀስት መወርወርን ተማረ፡፡ ታዲያ ልጆች ጊዮርጊስ የወረወረው ቀስት ካሰበበት ቦታ ነበር የሚያርፈው፡፡
ታዲያ በቡድን በቡድን ሆነው ሲፎካከሩ ጊዮርጊስ ያለበት ቡድን ያሸንፋቸው ስለበር በጣም ይበሳጫሉ፡፡ ‹‹ያንን ባለነጭ ፈረስ አስወጡልን… አስወጡልን ብለው›› ተንጫጩ፡፡ ‹‹እኔ የክርስቶስ ወታደር መጣሁላቸሁ!›› እያለ ሁሉንም ድል ያደርጋቸዋል፡፡ ጊዮርጊስ ያለበት ጦርነት ሁሉ አንድ ቀን ተሸንፎ አያውቅም፡፡ የማይሸነፍበት ምክንያት ደግሞ ልክ ውድድሩ ከመጀመሩ በፊት እግዚዘብሔር አምላኩን በጸሎት ይጠይቅ ስለነበር ነው፡፡ የጊዮርጊስ መስፍን በእርሱ ጥንካሬና እምነት በጣም ይደሰት ነበርና አንዳንዴ እቅፍ አድርጎ ይስመዋል፤ አንዳንዴ ደግሞ ይሸልመዋል፡፡ በጣም ይኮራበታል፤ በጣምም ይወድደዋል፡፡ አያችሁ ልጆች! እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ከሆነ ሁልጊዜም አሸናፊዎች እኛው ነን፡፡ ኃይለ እግዚአብሔርና ፍቅረ እግዚአብሔር በልባችን ውስጥ ካለ ሁልጊዜም ጠላቶቻችንን ድል የምንነሳው እኛ ነን፡፡
ጊዮርጊስም ፳፩ ዓመት ሆነው፤ ከዚያም የጊዮርጊስ መስፍኑ ምን አሰበ መሰላችሁ ልጆች ‹‹እኔ አርጅቻለሁ፤ ሳልሞት ለጊዮርጊስ ልጄን መዳር አለብኝ፤ እናም ሀብቴንም መውረስ አለበት፤›› አለ፡፡ ከዚያም ከዕለታት በአንድ ቀን ድግስ ተደገሰና ትልቅ ዳስ ተጣለ፡፡ ነገር ግን በአጋጣሚ መስፍኑ የድግሡ ቀን ሳይታሰብ አረፉ፤ ሰርጉም ቀረ፡፡ ልጆች! ከድንገተኛ ሞትና ወጥቶ ከመቅርት እግዚአብሔር ይሰውረን፡፡
ጊዮርጊስም ባሳደገው በመስፍኑ ሞት በጣም አዘነ፡፡ ኀዘኑንም ሲጨርስ ቤሩት ወደምትባል ሀገር ተነሥቶ ሔደ፡፡ ቤሩት በኢያሪኮ ዳርቻ የምትገኝ ሀገር ስትሆን በጣም ሰፊና ኃያል የምትባል ሀገር ናት፡፡ ቢሆንም ግን በውስጡ የሚኖሩት ሰዎች እግዚአብሔር አምላክን የማያውቁና ደራጎን የሚባለውን አውሬ አምላካችን ብለው የሚያመሊኩ ሰዎች ነበሩ፡፡ ደራጎን እንደንሥር ሁለት ክንፍ፣ እንደፍየል ፂም ያለው፣ እንደ አንበሳ ፈርጣማ ክንድ፣ እግሩ እንደ ዘንዶ ጅራት ያለው፣ ከአንገቱ እንደ ሰጐን የሰገገ፣ ጥርሶቹ እንደ አዞ የረዘሙ አስፈሪ ፍጥርት ነው፡፡
የቤሩት ሰዎች ታዲያ አምላካችን ድራጎን ነው እያሉ ቆንጆ ሴት ልጆቻቸውን ለደራጎን መሥዋዕት ያቀርቡልታል፡፡ ታዲያ ሕዝቡ ሁሉ ሴት ልጆቻቸውን ለደራጎን አሥበልተው የቤሩቱ ንጉሥ ሴት ልጅ ብቻ ቀረች፡፡ ሕዝቡም ተሰብስቦ ማጉረምረም ጀመረ፡ ‹‹የንጉሡ ሴት ልጅ ለምን ለደራጐን አትሰጥም፤ ካለበለዚያ ደራጎኑ ሁላችንንም ይበላናል›› ብለው ተማከሩና የንጉሡን ቤት ከበቡት፡፡ ‹‹እኛ ልጆቻችንን ለደራጎን ሰጥተናል፤ ለደራጎን መሥዋዕት ማቅረቢያ ጊዜም ተቃርቧል አሉ፡፡ ስለዚህ ደራጎን ተቆጥቶ ሁላችንንም ሳይበላን የሆነ መላ መፈጠር አለበት እያሉ ጮሁ፡፡ ወይ ደግሞ እኛ ሀገራችንን ቤሩትን ለቀን እንወጣለን አሉ፡፡›› ንጉሡም ሰምቷቸው ነበርና ወጥቶ እንዲህ አላቸው ‹‹ተረጋጉ… ተረጋጉ አትረብሹ፤ እናንተ ሀገራችሁን ለቃችሁ አትወጡም፤ የእኔ ልጅ ለደራጎን ትሰጣለች›› አላቸው፡፡ ይህንን ሲላቸው ደስ እያላቸው ወደየቤታቸው ተመለሱ፡፡
ለደራጎን መሥዋዕት የሚቀርብበትም ጊዜው ደረሰና የንጉሡ አሽከሮች የንጉሡን ልጅ ዛፍ ላይ አስረው ጥላዋት ተመለሱ፡፡ እርስዋም ማልቀስ ጀመረች፡፡ ‹‹እረ ደራጎን ሊበላኝ ነው፤ ማነው የሚያድነኝ›› እያለች ታለቅሣለች፡፡ ቅዱስ ጊዮርጊስም በፈረሱ ላይ ተቀምጦ በአጠገቧ ሲያለፍ ለቅሶዋን ሰማ ያንጊዜ ወደ እርሷ ቀረብ ብሎ ‹‹ምን ሆነሽ ነው አላት?›› እርሷም ‹‹ለደራጎን ለአምላካችን ተሰጥቼ ነው›› አለችው፤ እንባዋን እያነባች፤ ‹‹ሒድ! ከመጣ አንተንም ይበላሃል፤›› ስትልም ለመነችው፡፡ እርሱም ‹‹አልሔድም፤ ነይ ገመዱን ልፍታልሽ ብሎ ገመዱን ፈታላት፡፡›› ‹‹ለምን? ከመጣ እኮ ሁለታችንንም ይበላናል፤ እንደዛ ከሚሆን እኔ ልቆይ›› አለችው፡፡ ጊዮርጊስም በዚህ ጊዜ ‹‹ስሚ! የፈጠረሽ እግዚአብሔር ነው፤ የእኔ አምላክ ከዚህ ከክፉ አውሬ ያድናል፤ አንቺም እኔም ምንም አንሆንም፤ አትፍሪ›› ብሎ አጽናናት፡፡ ከዚያም አስፈሪው አውሬ ከተፍ አለ፤ ወደ እነርሱም እየተጠጋ መጣ፤ ቅዱስ ጊዮርጊስን በቀረበው ጊዜ በእጁ መስቀለኛ ሠርቶ ‹‹በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን›› ብሎ ሲያማትብ ያ አስፈሪ አውሬ ኃይሉ ደከመና ዝልፍልፍ ብሎ ወደቀ፡፡ ከዚያም ቤሩታዊቷ ሴት በታሠረችበት ገመድ አስሮ እርሷ እየጎተተችው፤ እርሱ ደግሞ በፈረሱ ላይ ተቀምጦ ከተማውን እየዞረ ‹‹እኔ ክርስቲያን ነኝ፤›› እያለ ደራጎንን በማዞር ለሕዝቡ ሁሉ አሳያቸው፡፡
አያችሁ ልጆች! በእግዚአብሔር ከታመንን የማያንቀላፋው አምላካችን ከክፉ ሁሉ ይጠበቀናል፡፡
እኔ ክርስቲያን ነኝ! እኔ ክርስቲያን ነኝ! እናንተም በእኔ አምላክ እመኑ ሲላቸው ‹‹የከተማው ሕዝብ በፍራቻ ‹‹ኧረ ታስፈጀናለህ ለምን አሠርክብን›› ብለው በማመስገን ፋንታ አጉረመረሙ መሸሽ ጀመሩ፡፡ ‹‹እርሱ ራሱን ማዳን የማይችል የእግዚአብሔር ፍጡር የሆነ እንስሳ እንዴት አምላካችን ትላላችሁ አላቸው›› ብሎ ገሰጻቸው፤ ሕዝቡም መልሰው ‹‹ከገደልከው እኛ ያንተን አምላክ እናመልካለን›› አሉት፡፡ ቅዱስ ጊዮርጊስም ከከተማ አውጥቶ በጦር ወግቶ ገደለው፤ እነርሱም ይህን አይተው በእግዚአብሔር አመኑ፤ ተጠምቀውም ክርስቲያን ሆኑ፡፡
ልጆች! እንደ ቅዱስ ጊዮርጊስ ጠንካራ ለመሆን እግዚአብሔርን በጸሎት መጠየቅ፣ በፍጹም ልባችሁ ማመን ያስፈልጋል፡፡ በእግዚአብሔር ያመነና የታመነ ሁሉን ማድረግ ይችላል፡፡ የቅዱስ ጊዮርጊስ በረከትም በሁላችን ይደር፡፡ ታሪኩ ጥሩ ነው አይደል? መቸም ጥሩ ትምህርት እንደተማራችሁበት ተስፋ እናድርጋለን፡፡ በሉ ሌላ አስተማሪ ታሪክ በሌላ ጊዜ ይዘንላችሁ እስከንቀርበ ድረስ ደኅና ሁኑ፡ እግዚአብሔር አምላክ ከእናንት ጋር ይሁን፡፡
ምንጭ፤ መዝገበ ታሪክ