“ጾማችን በእግዚአብሔር ዘንድ ተቀባይነት የሚኖረው የተፈናቀሉት ወገኖቻችን ወደ ቀያቸው ተመልሰው ሰላማዊ ኑሮ መኖር ሲችሉ፣ የተራቡት ሲደገፉ፣ ፍትሕ ያጡት ፍትሕ ሲያገኙ ነው፡፡“
ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ
ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአኵስም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት የ፳፻፲፮ ዓ.ም ዐቢይ ጾምን አስመልክተው መልእክት አስተላልፈዋል።
ቅዱስነታቸው ያስተላለፉት ሙሉ መልእክት እንደሚከተለው ቀርቧል።
መልእክተ ቅዱስ ፓትርያርክ
በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!!!
በሀገር ውስጥና በዓለም ዙሪያ ሁሉ የምትገኙ ምእመናንና ምእመናት ልጆቻችን በሙሉ!
እንኳን ለሁለት ሺህ ዐሥራ ስድስት ዓመተ ምሕረት የጾመ ኢየሱስ ሱባኤ በሰላም አደረሰን አደረሳችሁ!
“ወእምዝ ኃደጎ ዲያብሎስ ወናሁ መጽኡ መላእክት ይትለአክዎ፡- ከዚህ በኋላ ዲያብሎስ ትቶት ሄደ፤ እነሆም ያገለግሉት ዘንድ መላእክት መጡ›› (ማቴ ፬፲፩)፡፡
በቀጣዮቹ ሁለት ወራት በከፍተኛ ሃይማኖታዊ ተመሥጦ የምንጾመው ጾም፣ ጾመ ኢየሱስ ተብሎ የሚታወቀው ነው፡፡ ይህ ጾም በጥንት ጊዜ ሰው በኃጢአት የወደቀበትን ምክንያት፣ እንደዚሁም ሰው ኃጢአትንና ዲያብሎስን እንዴት እንደሚያሸንፍ ጌታችን እኛን ያስተማረበት ጾም ነው፡፡
ቅድስት ቤተ ክርስቲያን በቅዱስ መጽሐፏ እንደምታስተምረን፣ ኃጢአትና ዲያብሎስ የአንድ ሳንቲም _ ሁለት ገጽታዎች ናቸው፤ ይህም ማለት ዲያብሎስ ባለበት ኃጢአት አለ ፤ ኃጢአት ባለበትም ዲያብሎስ አለ ማለት ነው፤ እነዚህ ሁለቱ የሚለያዩ አይደሉም፤ የመጨረሻ ግባቸው ደግሞ ሰውን መጣል ነው፡፡ዲያብሎስ የሰውን ደካማ ዝንባሌ ወይም በሆነ ነገር መጐምጀትን በሰው ሲመለከት ያንኑ የጐመጀበትን ክፉ ምኞት እንዲፈጽም፣ በረቂቅ የሰው ኅሊና ውስጥ ገብቶ በከፍተኛ ደረጃ ይገፋፋል፤ ሰውም በራሱ የመጐምጀት ዝንባሌና በዲያብሎስ ግፊት ለመንፈሳዊ ሕይወቱ ጐጂ የሆነውን ድርጊት ይፈጽማል ፤ ቀጥሎም ድርጊቱ በእግዚአብሔር ፊት በደል ይሆንና ከእግዚአብሔር ይለየዋል፡፡ ሰው ከእግዚአብሔር ከተለየ ደግሞ ዘለዓለማዊ ሕይወትንና ክብርን ጨምሮ ብዙ መልካም ነገርን ያጣል፤ ኃጢአት የሚባለውም ይህ ነው፤ በቀደሙት አባትና እናት ማለትም በአዳምና ሔዋን የተከሠተው ነገርም ይኸው ነው፡፡
የተወደዳችሁ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻችን ምእመናንና ምእመናት!
ኃጢአትን በጽድቅ፣ ዲያብሎስን በጾም በማሸነፍ የአሸናፊነትን መንገድ ሊያሳየን የመጣው አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ በአዳምና በሔዋን የተፈጸመው ውድቀት እንዴት እንደሚቀለበስ በዚህ ጾም አስተምሮናል፡፡ ጌታችን ዐርባ ቀንና ዐርባ ሌሊት ከጾመ በኋላ ተራበ፤ ዲያብሎስም መራቡን አይቶ ይጐመጅልኛል ብሎ በምግብ ፈተነው፡፡ የጌታችን መልስ ግን ሰው በእንጀራ ብቻ አይኖርም ከእግዚአብሔር አፍ በሚወጣ ቃል ሁሉ እንጂ የሚል ነበረ፣ በተመሳሳይም በፍቅረ ንዋይና በአምልኮ ባዕድ ፈተነው የጌታ መልስ ግን በተቃራኒው ነበረ፡፡
ዲያብሎስ በሦስቱም የማስጐምጃ ፈተናዎች ጌታ ሊሸነፍለት ካለመቻሉም በላይ “አንተ ሰይጣን ከኋላዬ ሂድ” ብሎ ሲገሥጸው ተሸንፎ ትቶት ሂዶአል፡ በአሸናፊነቱ የተደሰቱ መላእክትም ወዲያውኑ መጥተው በክብረ አምልኮ አገለገሉት፤ በዚህ ድርጊት የምንመለከተው እውነታ ቀዳማይ አዳምን ባሸነፈበት ስልት ዳግማይ አዳም ክርስቶስን ለመጣል ዲያብሎስ የሄደበትን ርቀት በአንድ በኩል ስናይ፣ በሌላ በኩል ደግሞ ዳግማይ አዳም ክርስቶስ የቀዳማይ አዳም ተሸናፊነትና ውድቀት ለመቀልበስ ያሳየውን ጥብዓት እናያለን፡፡
በዚህም የቀደመው ውድቀት በኋለኛው አሸናፊነት ሙሉ በሙሉ ተቀልብሶ፣ ዲያብሎስ ጓዙን ጠቅልሎና ተስፋ ተስፋ ቆርጦ መሄዱን እናስተውላለን።
የተወደዳችሁ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻችን ምእመናንና ምእመናት!
ጌታችን የአሸናፊነትን መንገድ በቃልና በተግባር አስተምሮናል፤ አሳይቶናልም፤ ይህንም ያደረገው እሱ አሸንፎልናል እያልን ለመኵራራት ሳይሆን፣ በእሱ ኃይል እየታገዝንና እሱ ባሸነፈበት ስልት እየተጠቀምን እንድናሸንፈው ነው፡፡ ሰይጣን የሚሸነፍበት ስልት በሌላ ሳይሆን፤ ሥጋዊ መጐምጀትን ከአእምሮአችን አውጥተን በመወርወር ነው፡፡
ሥጋችን በፍቅረ ንዋይ፣ በሥልጣን፣ በዝሙት እንደዚሁም በተለያዩ ሥጋዊ ምኞቶች ሊጐመጅ ይችላል፤ ያን ጊዜ ሰይጣን እነሱን እንድንፈጽም ሊገፋፋን ከበኋላችን እንደቆመ እናስብና “አንተ ሰይጣን ከኋላዬ ሃድ” እንበለው፡፡ በቃል ብቻ ሳይሆን በተግባር ያስጐመጁን ነገሮችን ከኅሊናችን አውጥተን በመጣል እሱን ማሸነፍ አለብን፤ በዚህ ጊዜ ሰይጣን ይሸሻል፤ መላእክትም ወደኛ መጥተው ይረዱናል፣ ይጠብቁናል፤ ያግዙናል፣ ያድኑናል፡፡ ዲያብሎስ የሰዎችን የመጐምጀት ዝንባሌን ተከትሎ በመገፋፋት ዛሬም ዓለማችንን ለከፋ ውድቀት እየዳረጋት ነው፣ ሀገራችንን ጨምሮ በየአካባቢው የሚቀሰቀሱት አለመግባባቶችና ግጭቶች መንሥኤያቸው ከመጐምጀት ውጭ ሊሆን አይችልም፡፡ ግማሹ በሥልጣን፣ ግማሹ በሀብት፥ ግማሹ በራስ ወዳድነት፣ ግማሹ ደግሞ የበላይ ለመሆን በሚል እሳቤ የሰው ኅሊና በክፉ ምኞት ይጐመጅና በዲያብሎስ ገፋፊነት ወደ ተግባራዊ ጥፋት ይገባል፡ በውጤቱም ሰው ይጎዳል፡፡
የተወደዳችሁ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻችን ምእመናንና ምእመናት!
ጾም ማለት እህልንና የእንስሳት ውጤቶችን ከመመገብ መከልከል ብቻ አይደለም፣ የእንስሳት ውጤት የሆኑትን ላለመመገብ ከምንወስነው በላይ እኩያት ፍትወታትንና ኃጣውእን ላለማስተናገድ በቁርጥ መወሰን ይጠበቅብናል፡፡ ስንጾም መገዳደልን፤ መጣላትን መለያየትን፤ መገፋፋትን በሆነ ነገር መጐምጀትን እርም ብለን በመተው ዲያብሎስን የምናሸንፍበት የአሸናፊነት ኅሊና መላበስ አለብን፣ ከክፉ ኅሊና እና ተግባር የተለየን ያህል በአንጻሩ ደግሞ በጎ ነገርን ለመስራት በእጅጉ መበርታት ይጠበቅብናል፡፡
ዲያብሎስ ተስፋ ቆርጦ የሚሸሸው ይቅር ይቅር ስንባባል፤ ለሰላምና ለአንድነት፣ ለፍቅርና ለስምምነት ስንቆም ነው! ከዚህም ጋር በእግዚአብሔር ፊት እጅግ ጸያፍ የሆነው ግብረ ኃጢአት በዚህች ምድር እንዳይፈጸም ማኅበረ ሰባችን በተጠንቀቅ ሲቆም ነው፤ እንደዚሁም ደም መፋሰስ፣ አለመተማመንና በሴት ልጆቻችን የሚደርስው አካላዊ፣ መንፈሳዊና ሞራላዊ ጥቃት ሲቆም ነው፡፡ ጾማችን በእግዚአብሔር ዘንድ ተቀባይነት የሚኖረው የተፈናቀሉት ወገኖቻችን ወደ ቀያቸው ተመልሰው ሰላማዊ ኑሮ መኖር ሲችሉ፣ የተራቡት ሲደገፉ፣ ፍትሕ ያጡት ፍትሕ ሲያገኙ ነው፡፡
ይህ ዓይነት መልካም ሥነ ምግባር በእያንዳንዱ የማኅበረሰብ አእምሮ ቦታ አግኝቶ ሲተገበር ትክክለኛውን ጾም ጾምን ማለት እንችላለን፣ ዲያብሎስም በእርግጠኝነት በዚህ ይሸነፋል፤ የሰው ጣዕመ ሕይወትም በዚህ ይለመልማል! ምድሪቱም በእግዚአብሔር በረከት ትሞላለች፡፡ ይህን ቅዱስ ተግባር በወርኃ ጾሙ በደንብ እንድንተገብረው ለመላው ኢትዮጵያውያን በተለይም ለኦርቶዶክሳዊው ማኅበረሰብ መንፈሳዊና አባታዊ ጥሪያችንን እናቀርባለን፡፡
በመጨረሻም
በሀገራችን ረኃብ የሚያጠቃቸው ወገኖች በበዙበት በአሁኑ ወቅት፤ ሳንመጸውት ጾምን ጾምን ማለት ማጣፈጫ ወጥ የሌለው ምግብ መመገብ ማለት ስለሆነ፣ ሁሉም ኢትዮጵያዊ የቁርስ በጀቱን ለተራቡ ወገኖች በመለገስ ወገኖቹን በረኃብ ከመሞት እንዲታደግ ወቅታዊ ጥሪያችንን በእግዚአብሔር ስም እናስተላልፋለን፡፡
መልካም የጾም ወቅት ያድርግልን! እግዚአብሔር አምላክ ኢትዮጵያንና ሕዝቦቿን ይባርክ!
ወስብሐት ለእግዚአብሔር!!! አሜን!!!
አባ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ
ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ
ሊቀ ጳጳስ ዘአኵስም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት
መጋቢት ፩ ቀን ፳፻፲፮ ዓ.ም.
አዲስ አበባ – ኢትዮጵያ