‹‹ነገን ዛሬ እንሥራ!››

ክፍል አንድ

ዲያቆን ይትባረክ መለሰ

መጋቢት ፪፤፳፻፲፮ ዓመተ ምሕረት

ቤተ ክርስቲያን ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በደሙ ዋጅቶ የመሠረታት፣ በክርስቶስ ክርስቲያን ለተባልን በሙሉ መሰብሰቢያችን የተቀደሰች ቤታችን ናት፡፡ ቤተ ክርስቲያን ስንልም ሕንጻ ቤተ ክርስቲያን፣ የክርስቲያን ወገን፣ የምእመናን አንድነት ወይንም ማኅበረ ምእመናን  እያንዳንዱን ማለታችን ነው፡፡ (የቤተ ክርስቲያን ታሪክ ቁጥር ፩)

ውድ አንባብያን! የዚህ ጽሑፍ ዓላማ ስለ ቤተ ክርስቲያን ምንነት፣ ታሪክ ወዘተ መተንተን አይደለም፡፡ የነገዋ ቤተ ክርስቲያን ምን መምሰል አለባት? እንዴትስ ለትውልዱ እስከ ክብሯና ግርማ ሞገሷ ትሻገር? የሚለውን አሳሳቢ ጉዳዮችን መዳሰስ ነው እንጂ፡፡

ትውልድ ጅረት ነው፡፡ አንድ ትውልድ አልፎ ሌላ ትውልድ ይተካል፡፡ አንዱ አልፎ ሌላው ሲተካ ግን ተተኪው ትውልድ በቅብብሎሽ የሚተላለፉ ነገሮችን እየተቀበለና እየጨመረባቸው እንደ ዘመኑና እንደ ወቅቱ እያሳደጋቸው፣ እርሱም በተራው ለሌላው ትውልድ እያወረሳቸው ይተላለፋሉ፡፡

ቤተ ክርስቲያን ከትውልድ ወደ ትውልድ በበርካታ ትውልዶች ቅብብሎሽ ከዛሬው ትውልድ ከደረሱ ሀብቶች ዋናዋ ናት፡፡ ሀብት ብዙ ወገን ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያን ሀብተ ሥጋና ሀብተ ነፍስን የምታሰጥ ናት፡፡ በተጋድሎ በጠንካራ ሥራ፣ በብዙ ውጣ ውረድ ደምና ላብ ፈስሶበት የተገነባን ሀብት የተቀበለ ትውልድ ብቻውን ተጠቅሞ ጨርሶ ለተተኪው ትውልድ በተለይ መንፈሳዊ ውርስ ሳያተርፉ መሄድ ዕዳና በደል ነው፡፡ ይህ ሀብት የምንጠቀመው ብቻ ሳይሆን የምናስተላልፈው አደራ ጭምር ነው፡፡

አባቶቻችን ይህን አደራ አላፋለሱም፡፡ ቤተ ክርስቲያንን ከተቀበሉት አብልጠው፣ ከተጠቀሙት አትርፈው ከጥፋትና ከብክነት ጠብቀው ከእኛ ዘመን ያደረሱልን መተኪያ የሌላት መንፈሳዊ ሀብታችን ናት፡፡

ቁም ነገሩ የዛሬዋ ቤተ ክርስቲያን ለነገው ትውልድ በምን ሁኔታ ነው የምትተላለፈው? ትውልዱስ እንዴት ነው የሚቀበላት? እኛ የዛሬዎቹ ትውልዶችስ እንዴት ለማስተላለፍ ለማውረስ አስበናል? አባቶቻችን ካወረሱን አጉድለን ወይስ አትርፈን ነው የምናስተላልፋት? የሚሉ ጥያቄዎች መጠየቅ ያለባቸው ናቸው፡፡

ከላይ እንደጠቀስነው ቤተ ክርስቲያን (ምእመኑን፣ ጉባኤውን ወይም አንድነቱን እና ሕንጻ ቤተ ክርስቲያኑን እስከ ሥርዓትና ትውፊቱ) በጥቅል ቤተ ክርስቲያን ብለን ወስደን እንዴት ተቀበልናት እንዴትስ እናስተላልፋት የሚለውን ሐሳብ ማንሳት አስፈላጊ ነው፡፡

ቤተ ክርስቲያንን እንዴት ተቀበልናት?

አባቶቻችን ቤተ ክርስቲያን እንድትሰፋ፣ ዶግማና ቀኖናዋ እንዲጠበቅ፣ ምእመናን ወንጌል ሰምተው፣ ሃይማኖትን ጠብቀው፣ ምግባር ትሩፋት ሠርተው፣ በንስሓ በሥጋ ወደሙ ተጠብቀው መንግሥቱን ርስቱን እንዲወርሱ፣ ጉባኤው ሰፍቶ፣ አንድነቱ ጸንቶ አንዲኖር፣ ሕንጻ ቤተ ክርስቲያንም በዓለም እንድትታነጽ፣ ጉባኤም እንዲ ሠራባት፣ ምእመናንም እንዲገለገሉባት ለማድረግ አገልግሉኝ ሳይሉ አገልግለው፣ ለራሳቸው ክብር ሳይሆን ለቤተ ክርስቲያን ክብር፣ ለራሳቸው ምቾት ሳይሆን ለምእመናን ምቾት፣ ለራሳቸው ሥጋዊ ጥቅም ሳይሆን ለቤተ ክርስቲያን ሁለንተናዊ ጥቅም በትጋት ሠርተው አልፈዋል፡፡

‹‹ስለዚህም አንታክትም፤ ነገር ግን የውጭው ሰውነታችን ቢጠፋ እንኳን የውስጡ ሰውነታችን ዕለት ዕለት ይታደሳል›› እንዳለ ቅዱስ ጳውሎስ ስለ ቤተ ክርስቲያን ስለ ወንጌል የማይታክቱ፣ አደራ ጠባቂ አደራ አስጠባቂ አባቶች ቤተ ክርስቲያንን እስከ ክብሯ ከትውልድ ትውልድ እያሸጋገሩ ከዚህ ትውልድ አድርሰዋታል፡፡ (፪ ቆሮ. ፬፥፲፮፡) ሃይማኖት ለማጽናት፣ ምግባር ለማቅናት፣ ቤተ ክርስቲያንን ለማስፋት፣ ምእመናንን ለማብዛት፣ መናፍቃንን /ከሐድያንን ለመለየት፣ ሕግና ሥርዓት ለማውጣትና ለማስፈጸም በአጠቃላይ የቤተ ክርስቲያንን ሁለንተናዊ ጥቅም ለማስጠበቅ መብቷን ለማስከበር አስተምህሮዋን ለማስፋት እና ለማስቀጠል የጥረት የሚያደርጉ አባቶች በየዘመኑ ስለነበሯት ነው፡፡ በደሙ ለዋጃት ቤተ ክርስቲያን፣ በደሙ ለዋጃቸው ምእመናን /ለመንጋው/ እንዲሁም ለራሳቸው እንዲጠነቀቁ አደራ የተሰጣቸው ባላደራ ናቸውና የአደራቸውን አላጓደሉም፡፡ (ሐዋ.ሥራ ፳÷፳፰)

አባቶቻችን ቤተ ክርስቲያንን ከእኛ ለማድረስ ብዙ መከራን ተቀብለዋል፡፡ መከራው የጀመረው ገና ከሐዋርያት ዘመን ነው፡፡ ገና ከጅምሩም ነው፡፡ ‹‹በኢየሩሳሌም ባለችው ቤተ ክርስቲያን ላይ ታላቅ ስደት ሆነ›› ብሎ መጽሐፍ እንደነገረን (የሐዋ.ሥራ ፰፥፩)፡፡ ይህም የቅዱስ እስጢፋኖስን በድንጋይ ተወግሮ መሞት የጉባኤውን መበተን፣ በቤተ ክርስቲያን ላይ የደረሰውን ስደትና ሥቃይ የሚያስታውስ ቃል ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያን በትውልድ ቅብብሎሽ ስትመጣ እንዲሁ አይደለም የሚባለውም ለዚህ ነው፡፡ ብዙዎች በድንጋይ ተወግረው፣ በእሳት ተቃጥለው፣ በምሳር ተወግተው፣ በሰይፍ ተቀልተው፣ በገደል ተወርውረው በእስራት፣ በእርዛት፣ በረኃብ በጽም ተፈትነው ያቆዩን ናት ለማለት ነው፡፡ (ገድለ ሐዋርያት)

ከሐዋርያት ዘመንም በኋላ በሐዋርያት አበውም በሊቃውንትም ዘመን የቤተ ክርስቲያን ጉዞ አልጋ በአልጋ እንዳልነበር የቤተ ክርስቲያን ታሪክ ምስክር ነው፡፡ ጥርሱ እንደወለቀው፣ ጺሙ እንደተነጨው፣ ፊቱ እንደተጸፋው እንደ ዲዮስቆሮስ፣ በፓትርያሪክነት ዘመኑ አምስት ጊዜ  እንደተጋዘው አትናቴዎስ፣ ንግሥቲቱን በመዝለፉ፣ ሥርዓት አልበኛ ካህናትና ጳጳሳትን ከሹመታቸው በመሻሩ በስደትና በመከራ ሕይወቱ እንዳለፈው እንደ ዮሐንስ አፈወርቅ ያሉ አባቶችን ስናስብ ቤተ ክርስቲያንን ወደ እኛ ለማሸጋገር የተከፈለው ዋጋ ይገባናል፡፡ (የሃይማኖተ አበው ትርጓሜ መቅድም/የቤ ክርስቲያን ታሪክ)

በቤተ ክርስቲያን ታሪክ ቅዱስ ዲዮስቆሮስ ከመርቅያን ንጉሥና ከብርክልያ ንግሥት፣ መከራን ተቀብሏል፡፡ በጉባኤ ኬልቄዶን የተነሣውን ምንፍቅና በመቃወሙ፣ የሊቀ ጳጳሱን ደብዳቤ ባለ መቀበሉ፣ ንግሥቲቱና ደንገጡሮቿ ፊቱን ጸፍተው ጺሙን ነጭተው ጥርሱን ሰብረው ወደ ግዞት እንደላኩት የቤተ ክርስቲያን ታሪክ ያስረዳል፡፡

ቅዱስ ዮሐንስ አፈ ወርቅም ሰነፍና ሥርዓት አልበኛ ካህናትንና ጳጳሳትን በመሻሩ፣ ከተማ ለከተማ የሚዞሩ መነኮሳትን በመገሠፁ፣ በሚሠሩት ግፍ ንግሥቲቱንና ባለ ሥልጣናቱን በድፍረት በመገሠፁ መከራ ደርሶበታል፤ በግፍም በግዞት ሞቷል፡፡ (የቤተ ክርስቲያን ታሪክ/ግንቦት ፲፪ ስንክሳር፣ ሰማዕትነት አያምልጣችሁ) ይህም ለራስ ክብር ሳይሆን ለቤተ ክርስቲያን የተደረገ ነው፡፡

ቤተ ክርስቲያን በዘመነ ሰማዕታት፣ ከዚያ በኋላም ሆነ በፊት እስከ ዛሬዋ ዕለት ቤተ ክርስቲያን እንድትቀጥል፣ ዘመናትን ተሻግራ ሙሽራዋ ክርስቶስ እስኪመጣ ተከብራ ትጠብቀው ዘንድ፣  ትውልዱ በየዘመኑ የበረከት ፍሬዋን ይመገብ ዘንድ፣ የጸጋ ግምጃዋን ይለብስ ዘንድ፣ የአጋንንትና ክፉ ሰዎችን ውጊያ የተዋጉላት ለክብሯና ለህልውናዋ ራሳቸውን አሳልፈው የሰጡላት፣ ብርቱ የማይታክቱ አገልጋዮች፣ መሪዎች፣ አማኞች ስለ ነበሯት መሆኑን እንረዳለን፡፡ (፪ ቆሮ. ፬፥፩)

ጠፍር ታጥቀው፣ ጥሬ ቆርጥመው፣ ውኃ ጠጥተው፣ ሰሌን አንጥፈው፣ ማቅ ለብሰው ቤተ ክርስቲያንን የጠበቋት ክፉ ቀንን ያሳለፏት፣ የዚህ ዓለም ሀብት፣ ሹመት ሽልማት፣ ሥጋዊ ደማዊ ጥቅም ያላበላሻቸው አባቶቻችንና እናቶቻችን ብዙ የብዙ ብዙ ነበሩ፡፡ ‹‹የቀረውንም  ነገር ሳልቆጥር ዕለት ዕለት የሚከብድብኝ የአብያተ ክርስቲያናት ሁሉ ዐሳብ  ነው›› እንዳለ ቅዱስ ጳውሎስ የወንጌል አለመሰበክ፣ የምእመናን አለ መብዛት፣ የቤተ ክርስቲያን አለ መስፋት፣ የዕለት ዕለት ዐሳብ ሸክም የሆነባቸው፣ እየሠሩ የማይደክሙ፣ ትጉሃን ጽኑዓን አባቶቻችንና እናቶቻችን ለእኛ አደረሱልን፡፡ (፪ቆሮ.፲፩፥፳፰)

በዚህም የተነሣ ዳር ደንበሯ ሰፍቶ፣ ምእመኖቿ በዝተው፣ አጥር ቅጥሯ ተከብሮ፣ ጉባኤዋ ሰፍቶ፣ መንፈሳዊ ሀብት ንብረቷ ፋፍቶ ደርጅቶ፣ ክብሯ ገናንነቷ ዓለምን ናኝቶ፣ ለወዳጅ ትምክሕት፣ ለጠላት ኀፍረት ቁጭት ፈጥሮ፣ በየአህጉሩ ያለች ገናና ቤተ ክርስቲያንን አስረከቡን፤ እኛም ተረከብን፡፡

ውድ የዚህ ጽሑፍ ተከታታዮች! አምላካችን ቢፈቅድ በሕይወትም ብንኖር ክፍል ሁለትን ይዘንላችሁ እንቀርባለን፤ ቸር እንሰንብት!